የሰዎችን አእምሮና ልብ ለመማረክ በብሮሹሮች ተጠቀሙ
1 የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የሰዎችን አእምሮና ልብ በሚማርክ መንገድ መቅረብ ይኖርበታል። ኢየሱስ እውነትን ለአድማጮቹ በሚያቀርብበት ጊዜ የሰዎቹን ትኩረት የሚስቡና ፍላጎታቸውን የሚቀሰቅሱ ርዕሰ ጉዳዮች ይመርጥ ነበር። (ሉቃስ 24:17, 27, 32, 45) የአገልግሎታችን ስኬታማነት በአብዛኛው የተመካው የምናነጋግራቸውን ሰዎች መንፈሳዊ ፍላጎቶች ለይተን ለማወቅ በምናደርገው ጥረት ላይ ነው።
2 ብሮሹሮች በአገልግሎት የምናገኛቸውን ሰዎች አእምሮና ልብ ለመንካት የሚያስችሉ ውጤታማ መሣሪያዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ለራሳችሁ ግብ አውጡ። በአንድ ጊዜ ከአንድ በላይ ብሮሹሮችን አስተዋውቁ። በነሐሴ ወር የሚበረከቱት ብሮሹሮች የያዟቸው መልእክቶች የእነማንን ፍላጎት ሊቀሰቅሱ እንደሚችሉ አስቀድማችሁ አስቡ።
—የሙታን መናፍስት፣ ሊጎዱህ ወይም ሊረዱህ ይችላሉን? ደግሞስ በእርግጥ አሉን? ይህ ብሮሹር ጥንቆላን፣ ድግምትን፣ ሟርትንና በመስካችን በስፋት የሚታመንባቸውን ሌሎች መናፍስታዊ ድርጊቶች በሚመለከት ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ ሊሰጥ ይችላል። በተጨማሪም የትንሣኤን ተስፋ ጎላ አድርጎ ይገልጻል።
—በምድር ላይ ለዘላለም በደስታ ኑር! ብሮሹሩ በውስጡ የያዛቸው በርካታ ሥዕሎችና ጥቅሶች ለልጆችና የንባብ ችሎታቸው ውስን በመሆኑ ምክንያት የአምላክን ዓላማ መረዳት ለሚያዳግታቸው ሰዎች የሚጠቅም ነው።
—የአምላክ መንግሥት ገነትን ታመጣለች። የአምላክ መንግሥት የሰው ልጆች ያሉባቸውን ችግሮች እንዴት እንደሚያስወግድ የሚገልጸውን ይህን መልእክት ለመስማት ማንኛውም ሰው ፈቃደኛ ሊሆን ይችላል።
—ለዘላለም ጸንቶ የሚኖረው መለኮታዊው ስም። ይህ ብሮሹር ሰዎች የአምላክ ስም ያለውን ትርጉምና በስሙ መጠቀሙ አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት እንዲረዱ ጥሩ አጋጣሚ ይሰጣቸዋል።
—በሥላሴ ማመን ይገባሃልን? የሕዝበ ክርስትናን ዋነኛ መሠረተ ትምህርት ለሚያጋልጠው ለዚህ አሳማኝ በሆነ መንገድ ለተብራራው እውነት አክራሪ ሃይማኖተኛ የሆነን ሰው ፍላጎት ሊቀሰቅስ ይችላል።
3 ቀደም ብላችሁ ከእያንዳንዱ ብሮሹር ይዘት ጋር በሚገባ ተዋወቁ፤ እንዲሁም በአገልግሎት ክልላችሁ እንዴት ውጤታማ በሆነ መንገድ ልትጠቀሙበት እንደምትችሉ አስቀድማችሁ ወስኑ። አቀራረብን በሚመለከት ሐሳቦችን ለማግኘት እንድትችሉ በሐምሌ 1998 የመንግሥት አገልግሎታችን እትም መጨረሻ ገጽ ላይ የወጣውን ክፍል ተመልከቱ። የሰዎችን አእምሮና ልብ ለመንካት የምታደርጉትን ጥረት ይሖዋ ይባርክላችሁ።—ማር. 6:34