አዲስ የልዩ ስብሰባ ቀን ፕሮግራም
ከመስከረም 1999 ጀምሮ የሚካሄደው የልዩ ስብሰባ ቀን ፕሮግራም “የአምላክን ጥልቅ ነገሮች መመርመር” የሚል ጭብጥ ይኖረዋል። (1 ቆሮ. 2:10) ምን ጠቃሚ ነገሮች እንማራለን?
ብዙ ሰዎች እውቀት ለማግኘት በሚያደርጉት ፍለጋ የሚያረካ መልስ ሳያገኙ ይቀራሉ። የወረዳ የበላይ ተመልካቹ “የአምላክን ቃል መመርመር እርካታ ያስገኛል” በሚል ርዕስ በሚያቀርበው ክፍል ላይ እንደሚገለጸው መጽሐፍ ቅዱስ ብርታት ይሰጠናል። ጎብኚ ተናጋሪው “የመንግሥቱን የስብከት ሥራ እንዴት ትመለከቱታላችሁ?” የሚለውን ጥያቄ ሲያብራራ የአምላክን ጥልቅ ነገሮች በመመርመርና ምሥራቹን በመስበክ መካከል ያለውን ግንኙነት ይገልጻል።
ወላጆች ልጆቻቸው የአምላክን ቃል በጥልቅ እንዲቆፍሩ እንዴት ሊረዷቸው ይችላሉ? “በልጆቻችሁ ልብ ውስጥ የአምላክን ቃል ቅረጹ” በሚለው ክፍል ላይ ተግባራዊ የሆኑ ሐሳቦች ይቀርባሉ። ክርስቲያን ወጣቶች ጉባኤ ውስጥ ካሉ በመንፈሳዊ የጎለመሱ ወንድሞች ጋር መቀራረባቸው በእነርሱ ላይ በጎ ተጽዕኖ ይኖረዋል። “በዕድሜ ከበሰሉት የሚማሩ ወጣቶች” በሚለው ክፍል ላይ ወጣቶች እንዴት በጎ ተጽእኖ እንዳደረባቸው የሚያሳዩ ምሳሌዎች ይጎላሉ።
ይሖዋ ምሥጢር ገላጭ አምላክ ነው። በዚህ ጊዜ፣ ተሰውሮ ያለውን መንፈሳዊ ሃብት ለማግኘት በትጋት መፈለግ ያለብን ለምንድን ነው? “ይሖዋ ጥልቅ ነገሮችን ደረጃ በደረጃ ይገልጣል” በሚለው ንግግሩ ላይ ጎብኚ ተናጋሪው፣ ይሖዋ ጥንትም ሆነ ዛሬ ምን ነገሮችን እንደገለጸ ያብራራል። ይህም ‘የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገሮች መመርመራችንን’ ለመቀጠል ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ያጠናክርልናል።
ስብሰባው ላይ ለመገኘት ከአሁኑ እቅድ አውጡ። ራሳቸውን ለይሖዋ መወሰናቸውን በጥምቀት ማሳየት የሚፈልጉ ሁሉ ሳይዘገዩ ለሰብሳቢ የበላይ ተመልካቹ ማሳወቅ አለባቸው። የአምላክን ቃል በጥልቅ ለመረዳት ያለን ልባዊ ምኞት ስብሰባው ላይ በምንሰማው ነገር ይጠናከራል። በመሆኑም መንፈሳዊ ትምህርት የምታገኙበት ይህ ልዩ ቀን አያምልጣችሁ!