ይሖዋ ላሳየን ፍቅር አመስጋኝ መሆን የሚያስገኛቸው በረከቶች —ክፍል 1
1 ሐዋርያው ዮሐንስ “እርሱ [ይሖዋ] አስቀድሞ ወዶናልና እኛ እንወደዋለን” በማለት ጽፏል። (1 ዮሐ. 4:19) ይሖዋ ስላደረገልን ነገር ስናስብ በምላሹ ከልብ እንድናመሰግነው እንገፋፋለን። ኢየሱስ ስለ አምላክ ስም እና መንግሥት በታዛዥነት በመመስከር ይህን ዓይነቱን አመስጋኝነት በማሳየት ረገድ ምሳሌ ትቷል። (ዮሐ. 14:31) ይሖዋ ላሳየን ፍቅር አመስጋኝነታችንን መግለጽ የምንችልባቸውን አንዳንድ መንገዶችና በውጤቱም የምናገኘውን በረከት መመርመራችን ጠቃሚ ነው።
2 ከቤት ወደ ቤት መሄድ:- ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን የመንግሥቱን ስብከት ሥራ እንዴት እንደሚያከናውኑ አስተምሯቸው ነበር። የሰጣቸው መመሪያ ከቤት ወደ ቤት በመሄድ ምሥራቹን ማሰራጨት እንዳለባቸው በግልጽ የሚጠቁም ነበር። (ሉቃስ 9:1-6፤ 10:1-7) የሰዎች ግዴለሽነትና ተቃውሞ እያለም ከቤት ወደ ቤት መሄዳችንን መቀጠል ለአምላክና ለሰዎች ፍቅር ማዳበርን ይጠይቃል። እምነታችንን ስለሚያጠናክረውና ተስፋችንን ይበልጥ ብሩህ ስለሚያደርግልን ከቤት ወደ ቤት በመሄዳችን እኛም በግል እንጠቀማለን።
3 በሥራችን መላእክት ስለሚመሩን ለእውነት የተራቡና የተጠሙ ብዙ ሰዎችን እናገኛለን። (ራእይ 14:6) የይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት ሲሄዱ ያገኟቸው አንዳንድ ሰዎች በራቸው በተንኳኳበት ወቅት እርዳታ ለማግኘት እየጸለዩ እንደነበር ተናግረዋል። በአንዲት የካሪቢያን ደሴት ሁለት ምሥክሮችና አንድ ትንሽ ልጅ ከቤት ወደ ቤት ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ ሁለቱ እህቶች የዕለቱን አገልግሎታቸውን ለማብቃት ሲወስኑ ልጁ ግን ብቻውን ሄዶ የሚቀጥለውን በር አንኳኳ። አንዲት ወጣት ሴት በሩን ከፈተች። ይህን ሲመለከቱ ሁለቱ እህቶች ሄደው አነጋገሯት። ወጣቷ ሴት ወደ ቤት እንዲገቡ ጋበዘቻቸውና በሩ በተንኳኳበት ወቅት መጽሐፍ ቅዱስን ያስተምሯት ዘንድ ምሥክሮቹን እንዲልክላት ወደ አምላክ እየጸለየች እንደነበር ነገረቻቸው!
4 በመንገድ ላይ በመመስከር:- በአንዳንድ አካባቢዎች ሰዎችን በቤታቸው ማግኘት አስቸጋሪ ስለሆነ በመንገድ ላይ መመስከር ለሰዎች ምስክርነቱን ለመስጠት የሚያስችል ውጤታማ መንገድ ነው። ከዚህም በላይ ከቤት ወደ ቤት መሄድ በማይቻልባቸው የታጠሩ ሰፈሮች ወይም ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግባቸው ሕንጻዎች ውስጥ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች አሉ። ይሁን እንጂ ይሖዋ ላሳየን ፍቅር ያለን አመስጋኝነት የመንግሥቱን መልእክት ለሰዎች ለማዳረስ በመንገድ ላይ መመስከርን ጨምሮ የተገኘውን አጋጣሚ ሁሉ እንድንጠቀም ይገፋፋናል።—ምሳሌ 1:20, 21
5 ተመላልሶ መጠይቅ ማድረግ:- “ለመንፈሳዊ ፍላጎታቸው ንቁ የሆኑ” ሰዎችን እየፈለግን ስለሆነ ይህን ፍላጎታቸውን ለማርካት የሚቻለንን ሁሉ እናደርጋለን። (ማቴ. 5:3) ይህም የተከልነውን የእውነት ዘር ውኃ ለማጠጣት ተመልሰን መሄድ ይጠይቅብናል። (1 ቆሮ. 3:6-8) በአውስትራሊያ የምትገኝ አንዲት እህት እምብዛም ፍላጎት ላላሳየች አንዲት ሴት ትራክት አበረከተችላት። ሴትየዋ ፍላጎት ባታሳይም እህት በድጋሚ ለማነጋገር ጥረት ማድረጓን ቀጠለች። በመጨረሻ ስታገኛት ከመጀመሪያ ውይይታቸው በኋላ ሴትየዋ ውድ ዋጋ ያለው መጽሐፍ ቅዱስ እንደ ገዛች ተረዳች። እህት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመረችላት!
6 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን መምራት:- ይህ ከሁሉም የአገልግሎት ዘርፎች የበለጠ አስደሳችና አርኪ ሊሆን ይችላል። ሰዎችን ስለ ይሖዋ እንዲማሩ መርዳት፣ እርሱን ለማስደሰት በሕይወታቸው ላይ ለውጥ ሲያደርጉና ራሳቸውን ለአምላክ መወሰናቸውን ለማሳየት ሲጠመቁ መመልከት እንዴት ያለ በረከት ነው!—1 ተሰ. 2:20፤ 3 ዮሐ. 4
7 በሚቀጥለው እትም ይሖዋ ላሳየን ፍቅር አመስጋኝ በመሆን የምንባረክባቸውን ሌሎች ተጨማሪ መንገዶች እንመለከታለን።