አዲስ የወረዳ ስብሰባ ፕሮግራም
እውነተኛውን አምልኮ ክፉኛ የሚቃወሙትን በጽናት መቋቋም የሚቻለው እንዴት ነው? እኛን ፈሪሃ አምላክ ወደሌለው ዓለም መልሰው ለመክተት የማያቋርጥ ጥረት የሚያደርጉትን ኃይሎች ማሸነፍ የምንችለው እንዴት ነው? የ2009 የአገልግሎት ዓመት የወረዳ ስብሰባ ለእነዚህ ወሳኝ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ይሰጣል። የወረዳ ስብሰባው ጭብጥ ‘ክፉን በመልካም አሸንፉ’ የሚል ነው። (ሮም 12:21) የስብሰባው ይዘት ምን እንደሚመስል እስቲ እንመልከት።
የአውራጃ የበላይ ተመልካቹ “ክፉን በመልካም ለማሸነፍ ራሳችንን ማጠናከር፣” “ከልክ በላይ በራስ የመመካት መንፈስ ወጥመድ እንዳይሆንባችሁ ተጠንቀቁ!፣” “ክፋት በሙሉ በቅርቡ ይወገዳል!” እና “ዓለምን ለማሸነፍ እምነታችንን ማጠናከር” የሚል ርዕስ ያላቸውን ንግግሮች ያቀርባል። የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ደግሞ በሮም 13:11-13 ላይ የተመሠረተውን “ንቁ ሆነን የምንጠብቅበት ጊዜ አሁን ነው!” የሚል ጭብጥ ያለውንና በምሳሌ 24:10 [NW] ላይ የተመሠረተውን “በመከራ ቀን ተስፋ አትቁረጡ” የሚል ጭብጥ ያለውን ንግግር ያቀርብልናል። “ወረዳው ለሚያስፈልጉት ነገሮች ትኩረት መስጠት” የሚለውን የወረዳ የበላይ ተመልካቹን ንግግርም በጉጉት እንጠብቃለን። “አቅኚ በመሆን ‘አገልግሎቱን’ ማከናወን ትችላላችሁ?” የሚል ርዕስ ያለው የሚያበረታታ ንግግርም ይቀርባል። ከሚቀርቡት ሁለት ሲምፖዚየሞች የመጀመሪያው “የዲያብሎስን መሠሪ ዘዴዎች በጽናት ተቋቋሙ” የሚል ርዕስ ያለው ነው። ይህ ሲምፖዚየም ዲያብሎስ በዘመናዊው ቴክኖሎጂ፣ በመዝናኛው እንዲሁም በትምህርቱ መስክ ምን መሠሪ ዘዴዎችን እንደሚጠቀምና ከእነዚህ መሠሪ ዘዴዎች መራቅ የምንችልበትን መንገድ እንድናውቅ ይረዳናል። “በዚህ ክፉ ዘመን ሰይጣንን የምንቋቋምበት ኃይል ማግኘት” በሚል ርዕስ የሚቀርበው ሲምፖዚየም በኤፌሶን 6:10-18 ላይ ያለውን በመንፈስ መሪነት የተጻፈውን ምክር እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደምንችል ያስገነዝበናል።
የክፉትን ምንጭ ድል በማድረግና የመንግሥቱን መልእክት በመስበክ መካከል ቀጥተኛ ግንኙነት አለ። (ራእይ 12:17) ሰይጣን በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ያለማቋረጥ ጥቃት መሰንዘሩ የሚያስገርም አይደለም! (ኢሳ. 43:10, 12) እኛ ‘ክፉን በመልካም ለማሸነፍ’ ቆርጠን ስለተነሳን ሰይጣን አይሳካለትም። በዚህ የወረዳ ስብሰባ ላይ በሁለቱም ቀን ከሚቀርበው ትምህርት በሚገባ ለመጠቀም ከወዲሁ ዝግጅት አድርጉ።