መጽሐፍ ቅዱስ—በአንተ ሕይወት ውስጥ ያለው ኃይል
መጽሐፍ ቅዱስ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ በጎ ለውጥ እንዲያደርጉ ረድቷል። በሕይወታችን ተግባራዊ ብናደርጋቸው በጊዜያችን የሚያጋጥሙንን ችግሮች ለመቋቋም የሚረዱን አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የትኞቹ ናቸው? መጽሐፍ ቅዱስ—የእውነትና የትንቢት መጽሐፍ የተባለው ዲቪዲ ከያዛቸው ሦስት ፊልሞች መካከል መጽሐፍ ቅዱስ—በአንተ ሕይወት ውስጥ ያለው ኃይል የሚለውን ሁለተኛ ክፍል በመመልከት የዚህን ጥያቄ መልስ እንደምታገኙ ማወቃችሁ እንደሚያስደስታችሁ ምንም ጥርጥር የለውም። ፊልሙን ከተመለከታችሁ በኋላ ቀጥሎ ለቀረቡት ጥያቄዎች መልስ ስጡ።
(1) መጽሐፍ ቅዱስ ድንቅ የሥነ ጽሑፍ ሥራ ብቻ አይደለም የምንለው ለምንድን ነው? (ዕብ. 4:12) (2) መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎች ሕይወት እንዲሻሻል የሚረዳ ከሆነ የሰው ልጆች ሕይወት በተለያዩ ችግሮች የተሞላው ለምንድን ነው? (3) የመጽሐፍ ቅዱስ ዋና ጭብጥ ምንድን ነው? (4) ባለ ትዳሮች (ሀ) እርስ በርስ የሚያደርጉትን የሐሳብ ልውውጥ እንዲያሻሽሉ (ለ) ቁጣቸውን እንዲቆጣጠሩ የሚረዷቸው የትኞቹ ጥቅሶች ናቸው? (5) ስለ ትዳር ክርስቲያናዊ አመለካከት ማዳበር የቤተሰብን ሕይወት የሚያሻሽለው እንዴት ነው? (ኤፌ. 5:28, 29) (6) ይሖዋ ለወላጆች ፍጹም ምሳሌ የሚሆነው እንዴት ነው? (ማር. 1:9-11) (7) ወላጆች የቤተሰብ ጥናትን አስደሳች ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? (8) ወላጆች ልጆቻቸውን መጽሐፍ ቅዱስ ከማስጠናት በተጨማሪ ለልጆቻቸው ምን እንዲያደርጉ የአምላክ ቃል ያበረታታቸዋል? (9) መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ምክር ቤተሰቦች የሚያጋጥማቸውን የኢኮኖሚ ችግር እንዲቋቋሙ የሚረዳቸው እንዴት ነው? (10) ንጽሕናን፣ ዕፅ መውሰድን፣ የአልኮል መጠጥ ከመጠን በላይ መጠጣትን እንዲሁም ጭንቀትን በተመለከተ የተሰጡና ተግባራዊ ከተደረጉ የጤና ችግሮችን ለመቀነስ የሚረዱ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች የትኞቹ ናቸው? (11) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት የትኞቹ ተስፋዎች ያጽናኑናል? (ኢዮብ 33:25፤ መዝ. 145:16) (12) በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙት ትምህርቶች ሕይወትህን እንድታሻሽል የረዱህ እንዴት ነው? (13) ይህንን ቪዲዮ ሌሎች ሰዎችን ለመርዳት እንዴት ልትጠቀምበት ትችላለህ?