የአቀራረብ ናሙናዎች
በወሩ የመጀመሪያ ቅዳሜ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር የሚረዳ አቀራረብ
“ሁሉም ሰው ረጅም ዕድሜና ደስተኛ ሕይወት ቢኖረው ደስ ይለዋል። እስቲ በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ ጥያቄ ልጠይቅዎት፤ ሳይንስና የሕክምናው መስክ አንድ ቀን ለዘላለም መኖር እንድንችል የሚያደርጉን ይመስልዎታል? [ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው።] እስቲ አንድ ጽሑፍ ላሳይዎት።” የሐምሌ 1ን መጠበቂያ ግንብ ስጠውና በመጨረሻ ገጽ ላይ ያለውን ዓምድ አሳየው። ከዚያም በመጀመሪያው ጥያቄ ሥር ባለው ሐሳብ ላይ እና በዚያ ውስጥ ከተጠቀሱት ጥቅሶች መካከል ቢያንስ በአንዱ ላይ ተወያዩ። መጽሔቶቹን ካበረከትክለት በኋላ በሚቀጥለው ጥያቄ ላይ ለመወያየት ቀጠሮ ያዝ።
ማሳሰቢያ፦ ይህ የመግቢያ ሐሳብ በወሩ የመጀመሪያ ቅዳሜ በሚደረገው የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ ላይ በሠርቶ ማሳያ መልክ መቅረብ ይኖርበታል።
መጠበቂያ ግንብ ሐምሌ 1
“ከጎረቤቶችዎ ጋር በብዙ ሃይማኖተኛ ሰዎች አእምሮ ውስጥ ስለሚመላለስ አንድ ጥያቄ ስንወያይ ነበር፤ ይኸውም ‘አምላክ የሚደርስብን ሥቃይና መከራ ያሳስበዋል?’ የሚለው ነው። ምክንያቶቹ ይለያዩ እንጂ ሁሉም ሰው መከራ ይደርስበታል፤ ለምሳሌ ከጤና፣ ከገንዘብ፣ ከስሜት ወይም ከሌላ ነገር ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል። እርስዎስ ምን ይሰማዎታል? አምላክ በሰው ልጆች ላይ የሚደርሰው ሥቃይና መከራ ያሳስበዋል? [ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው።] መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ በግዞት ላይ የነበሩት ሕዝቦቹ ስለሚደርስባቸው መከራ ምን እንደተሰማው ሲናገር በዘፀአት 3:7 ላይ እንዲህ ይላል። [ጥቅሱን አንብብ፤ እንዲሁም አምላክ የተሰማውን ነገር ጎላ አድርገህ ግለጽ።] ይህ መጽሔት ስለዚህ ጉዳይ ተጨማሪ ማብራሪያ የያዘ ነው።”
ንቁ! ሐምሌ
“እዚህ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎችን፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለሚገኝ አንድ አስፈላጊ ርዕሰ ጉዳይ ማለትም ስለ አምላክ መንግሥት እያነጋገርናቸው ነበር። ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት እንዲመጣ መጸለይ እንዳለብን ማስተማሩን ያስታውሱ ይሆናል። መንግሥቱ ሲመጣ ግን ምን የሚያደርግልን ይመስልዎታል? [ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው።] ዳንኤል 7:14 ላይ የሚገኘውን ጥቅስ ላንብብልዎት? [ጥቅሱን አንብበህ አብራራ።] ይህ መጽሔት የአምላክ መንግሥት የሚያመጣቸውን በረከቶች እንዲሁም አምላክ ወደፊት የተሻለ ሕይወት እንደሚያመጣ የሰጠውን እርግጠኛ የሆነ ተስፋ ያብራራል፤ መጽሔቱን ቢያነቡት ደስ ይለኛል።”
ከአምላክ የተላከ ምሥራች!
“በዚህ አካባቢ ለምናገኛቸው ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ያገኘነውን የሚያበረታታ ሐሳብ እያካፈልናቸው ነበር። አብዛኞቹ ያናገርናቸው ሰዎች አምላክ በዓለም ላይ ይህን ያህል ሥቃይና መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምን እንደሆነ ይጠይቃሉ። አምላክ ለምድር የነበረው የመጀመሪያ ዓላማ ይህ የነበረ ይመስልዎታል?” ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው። ከዚያም ትምህርት 5ን አውጥታችሁ በመጀመሪያዎቹ ሁለት አንቀጾችና በሰያፍ በተጻፉት ጥቅሶች ላይ ተወያዩ። ብሮሹሩን ካበረከትክለት በኋላ ደመቅ ተደርጎ በተጻፈው በሚቀጥለው ጥያቄ ላይ ለመወያየት ቀጠሮ ያዝ።