የአቀራረብ ናሙናዎች
በሐምሌ ወር የመጀመሪያ ቅዳሜ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር የሚረዳ አቀራረብ
“አምላክ ስለምናቀርበው ጸሎት ምን ይሰማዋል? ጸሎታችንን ከልቡ የሚያዳምጠን ይመስልዎታል? ወይስ ሰምቶ ዝም ይለናል?” ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው። ከዚያም በሐምሌ 1 መጠበቂያ ግንብ የመጨረሻ ገጽ ላይ ያለውን የመጀመሪያ ጥያቄ አሳየው፤ በጥያቄው ሥር ባለው ሐሳብ እና በአንቀጹ ላይ ካሉት ጥቅሶች መካከል ቢያንስ በአንዱ ላይ ተወያዩ። መጽሔቶቹን ካበረከትክለት በኋላ በሚቀጥለው ጥያቄ ላይ ለመወያየት ቀጠሮ ያዝ።
መጠበቂያ ግንብ ሐምሌ 1
“ፈጣሪ ምንም የሚሳነው ነገር የለም፤ ታዲያ በሰዎች ላይ ለሚደርሱት መጥፎ ነገሮች ተጠያቂ ነው?” [ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው። ከዚያም ያዕቆብ 1:13ን አንብብ።] ይህ መጽሔት መጥፎ ነገሮች በሰዎች ላይ የሚደርሱት ለምን እንደሆነ እንዲሁም አምላክ ክፋትንና መከራን ለማስወገድ ምን እንደሚያደርግ ያብራራል።”
ንቁ! ሐምሌ
“ሐዘን የሚያስከትል ነገር በማናችንም ላይ ሊደርስ ይችላል፤ ለምሳሌ የተፈጥሮ አደጋ ሊደርስብን ይችላል፤ ወይም ደግሞ ለሞት በሚዳርግ በሽታ ልንያዝ ወይም ቤተሰባችንን በሞት ልናጣ እንችላለን። እንዲህ ያለ ነገር ሲያጋጥመን ብሩህ አመለካከት መያዝ ጥቅም አለው ብለው ያስባሉ? [ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው።] ብዙ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለው ሐሳብ የደረሰባቸውን ሐዘን እንዲቋቋሙ እንደረዳቸው ይሰማቸዋል። [ሮም 15:4ን አንብብ።] ይህ መጽሔት አሳዛኝ ነገር ሲያጋጥመን መጽሐፍ ቅዱስ የሚረዳን እንዴት እንደሆነ ያብራራል።”