የአቀራረብ ናሙናዎች
በወሩ የመጀመሪያ ቅዳሜ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር የሚረዳ አቀራረብ
“የምናነጋግራቸው ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የተለያየ አመለካከት አላቸው። አንዳንዶች የአምላክ ቃል እንደሆነ ሲያምኑ ሌሎች ደግሞ እንደማንኛውም ተራ መጽሐፍ አድርገው ይመለከቱታል። እርስዎስ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ምን አመለካከት አለዎት?” ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው። የየካቲት 1ን መጠበቂያ ግንብ ስጠውና በመጨረሻ ገጽ ላይ ያለውን ዓምድ አሳየው፤ ከዚያም በመጀመሪያው ጥያቄ ሥር ባለው ሐሳብ እና በዚያ ውስጥ ከተጠቀሱት ጥቅሶች መካከል ቢያንስ በአንዱ ላይ ተወያዩ። መጽሔቶቹን ካበረከትክለት በኋላ በሚቀጥለው ጥያቄ ላይ ለመወያየት ቀጠሮ ያዝ።
መጠበቂያ ግንብ የካቲት 1
“ብዙ ሰዎች ጦርነት የማይኖርበትን ጊዜ ለማየት ይናፍቃሉ። በመላው ዓለም ላይ ሰላም የሚሰፍንበት ጊዜ ይመጣል ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ እንደሆነ ይሰማዎታል? [ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው።] መጽሐፍ ቅዱስ ይህን አስመልክቶ ምን ተስፋ እንደሚሰጥ እስቲ ይመልከቱ። [መዝሙር 46:9ን አንብብ።] በአንደኛው የዓለም ጦርነትና ከዚያ በኋላ ባሉት ጊዜያት የተፈጸሙት ክንውኖች በቅርቡ አምላክ ይህ ትንቢት እንዲፈጸም እንደሚያደርግ እርግጠኞች እንድንሆን ያስችለናል። ይህ መጽሔት ስለዚህ ጉዳይ ተጨማሪ ማብራሪያ ይዟል።”
ንቁ! የካቲት
“ዛሬ ቤትዎ የመጣነው ሁላችንንም ስለሚያሳስበን አንድ ጉዳይ በአጭሩ ለመወያየት ነው። ብዙዎቻችን ያሰብነውን ነገር ለማከናወን የሚያስችል በቂ ጊዜ ማግኘት አስቸጋሪ እየሆነብን ሄዷል። ታዲያ ምን ይመስልዎታል? እንዲህ ጊዜ የሚያጥረን ሥራ ስለሚበዛብን ነው ወይስ ጊዜያችንን በከንቱ ስለምናባክን? [ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው።] ብዙዎች መጽሐፍ ቅዱስ ጊዜያችንን በአግባቡ ለመጠቀም እንድንችል የሚረዳ ጠቃሚ ምክር እንደያዘ አይገነዘቡም። እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት። [ፊልጵስዩስ 1:10ሀን አንብብ።] ይህ መጽሔት ብዙዎች ጊዜያቸውን በጥበብ እንዲጠቀሙ የረዷቸውን አራት ዘዴዎች ያብራራል።”