በአገልግሎት ረገድ ክህሎታችንን ማዳበር—ውይይት የሚያስቆሙ ሐሳቦች ሲሰነዘሩ መልስ መስጠት
አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? አንድ የተፈጥሮ አደጋ በአካባቢህ ሊደርስ እንደሆነ አወቅህ እንበል። ሰዎች ከዚያ አካባቢ ሸሽተው ካላመለጡ ሕይወታቸው አደጋ ላይ ነው። በመሆኑም ጎረቤትህን ልታስጠነቅቀው ወደ ቤቱ ሄድክ፤ ይሁን እንጂ ጉዳዩን እየነገርከው እያለ ጎረቤትህ ያቋርጥህና አሁን ሥራ እንደሚበዛበት ነገረህ። ታዲያ እሱን ለመርዳት የምታደርገውን ጥረት ወዲያውኑ ታቆማለህ? እንዲህ እንደማታደርግ የታወቀ ነው! በተመሳሳይም በክልላችን የሚገኙ ብዙ ሰዎች መልእክታችን ሕይወት አድን መሆኑን ስለማያውቁ ውይይቱን ለማስቆም የተለያዩ ሐሳቦችን ይሰነዝራሉ። ምናልባትም ቤታቸው በሄድንበት ወቅት በሥራ ተወጥረው ይሆናል። (ማቴ. 24:37-39) ወይም ደግሞ የሰሙት የውሸት ወሬ በእኛ ላይ ጥላቻ አሳድሮባቸው ሊሆን ይችላል። (ማቴ. 11:18, 19) በመሆኑም እኛም መጥፎ ፍሬ ከሚያፈሩት ሌሎች ሃይማኖቶች እንደማንለይ ያስቡ ይሆናል። (2 ጴጥ. 2:1, 2) እንግዲያው ያነጋገርነው ሰው መጀመሪያ ላይ ለመልእክታችን ፍላጎት ባያሳይ ቶሎ ተስፋ መቁረጥ አይኖርብንም።
በዚህ ወር እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦
በአገልግሎት ላይ የምታገኙት አንድ ሰው ውይይት የሚያስቆም ሐሳብ ከሰነዘረ ከግለሰቡ ጋር ከተለያያችሁ በኋላ እንዴት አድርጋችሁ መልስ ብትሰጡ ኖሮ የተሻለ ይሆን እንደነበር ከአገልግሎት ጓደኛችሁ ጋር ተወያዩ።