“በተደጋጋሚ ቤቱ ብሄድም ላገኘው አልቻልኩም!”
መጀመሪያ ባነጋገራችሁት ወቅት ፍላጎት ስላሳየ ሰው እንዲህ ብላችሁ ታውቃላችሁ? ለግለሰቡ ተመላልሶ መጠይቅ ለማድረግ በተደጋጋሚ ብትሄዱም እንኳ የዘራችሁትን የእውነት ዘር ውኃ ማጠጣት አልቻላችሁ ይሆናል። (1 ቆሮ. 3:6) ተሞክሮ ያላቸው አንዳንድ አስፋፊዎች ያነጋገሩትን ግለሰብ ቤቱ ማግኘት ካልቻሉ ደብዳቤ ይጽፉለታል፤ ወይም ማስታወሻ ጽፈው በሩ ላይ ያስቀምጡለታል። ሌሎች አስፋፊዎች ደግሞ ያነጋገሩትን ግለሰብ እንደገና ማግኘት አስቸጋሪ እንደሚሆን ከተሰማቸው መጀመሪያ ባነጋገሩት ዕለት ስልክ ቁጥሩን ይጠይቁታል፤ ለምሳሌ “በሞባይልዎ መልእክት ልልክልዎት እችላለሁ?” ብለው በዘዴ ይጠይቃሉ። ለግለሰቡ ምሥክርነት ለመስጠት በማሰብ ደብዳቤ፣ ኢ-ሜይል ወይም የሞባይል መልእክት ከጻፍን አሊያም በሩ ላይ ማስታወሻ ትተን ከሄድን ወይም ስልክ ከደወልንለት ተመላልሶ መጠይቅ ብለን መመዝገብ እንችላለን። ግለሰቡ ብዙውን ጊዜ ቤቱ ባይገኝም እንኳ በዚህ መንገድ ፍላጎቱን ማሳደግ እንችላለን።