ምሥራቹን ለማዳረስ በትራክቶች ተጠቀሙ
1. የአምላክ ሕዝቦች ትራክቶችን የተጠቀሙት እንዴት ነው?
1 የይሖዋ ሕዝቦች ምሥራቹን ለማዳረስ በትራክቶች መጠቀም ከጀመሩ ቆይተዋል። በ1880 ወንድም ራስልና ባልደረቦቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ትራክት (እንግሊዝኛ) የተባሉትን በራሪ ወረቀቶች ማዘጋጀት የጀመሩ ሲሆን የመጠበቂያ ግንብ አንባቢያን እነዚህን ትራክቶች ለሕዝብ ያሰራጩ ነበር። በ1884 ወንድም ራስል ከአምላክ መንግሥት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለማራመድ የሚጠቀሙበትን አትራፊ ያልሆነ ሕጋዊ ማኅበር ሲያስመዘግብ “ትራክት” የሚለው ቃል ድርጅቱ በሚጠራበት ስም ውስጥ እንዲካተት ማድረጉ ትራክቶች በጣም ጠቃሚ መሣሪያ እንደነበሩ ያሳያል፤ በወቅቱ ዛየንስ ዎች ታወር ትራክት ሶሳይቲ ይባል የነበረው ይህ ድርጅት በአሁኑ ጊዜ ዎች ታወር ባይብል ኤንድ ትራክት ሶሳይቲ ኦቭ ፔንስልቬንያ በመባል ይታወቃል። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ እስከ 1918 ድረስ ከ300 ሚሊዮን የሚበልጡ ትራክቶችን አሰራጭተዋል። ዛሬም ቢሆን የምሥክርነቱን ሥራ ለማካሄድ ትራክቶችን መጠቀም ውጤታማ ሆኖ ተገኝቷል።
2. ትራክቶች ውጤታማ መሣሪያ የሆኑት ለምንድን ነው?
2 ውጤታማ የሆኑት ለምንድን ነው? ትራክቶች በርካታ ቀለሞች ያላቸው ከመሆኑም ሌላ የሚስቡ ናቸው። በውስጣቸው የያዙት እጥር ምጥን ያለ መረጃ የሚመስጥ ከመሆኑም በላይ ግንዛቤ ያሰፋል። መጽሔቶችን ወይም መጻሕፍትን መውሰድ የሚፈሩ ሰዎች እንኳ ትራክት ሊቀበሉ ይችላሉ። አዳዲስ አስፋፊዎችና ልጆችም ጭምር ትራክቶችን በቀላሉ ማበርከት ይችላሉ። በተጨማሪም ትራክቶች አነስተኛ መጠን ስላላቸው ለመያዝ ቀላል ናቸው።
3. የትራክቶችን ጥቅም ጎላ አድርጎ የሚገልጽ፣ የራስህን ወይም ጽሑፍ ላይ ያነበብከውን ተሞክሮ ተናገር።
3 ብዙ ሰዎች እውነትን የሰሙት በትራክቶች አማካኝነት ነው። ለምሳሌ በሄይቲ የምትኖር አንዲት ሴት ከትራክቶቻችን መካከል አንዱን መንገድ ላይ ወድቆ አየች። አንስታ ካነበበችው በኋላ “እውነትን አገኘሁ!” በማለት በአድናቆት ተናግራለች። ይህች ሴት ከጊዜ በኋላ ወደ መንግሥት አዳራሽ የሄደች ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስን አጥንታ ተጠምቃለች፤ ይህ ውጤት ሊገኝ የቻለው ትራክቱ ውስጥ የሚገኘው የአምላክ ቃል ባለው ኃይል ነው።
4. ትራክቶች በወሩ ውስጥ የሚበረከቱ ጽሑፎች በሚሆኑበት ጊዜ ምን ጥረት እናደርጋለን?
4 ከቤት ወደ ቤት፦ ትራክቶች የምሥክርነቱን ሥራ ለማካሄድ ውጤታማ መሣሪያዎች በመሆናቸው ከኅዳር ወር ጀምሮ አልፎ አልፎ በወሩ ውስጥ የሚበረከቱ ጽሑፎች ይሆናሉ። በዚህ ጊዜ ጥረት የምናደርገው ትራክቶችን ለማበርከት ብቻ ሳይሆን በትራክቶች ተጠቅመን ውይይት ለመጀመርም ነው። ግለሰቡን ለመጀመሪያ ጊዜ ስናነጋግረውም ሆነ ተመላልሶ መጠየቅ ስናደርግለት ፍላጎት ካሳየ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ አሊያም ሌላ የማስጠኛ ጽሑፍ በመጠቀም ጥናት ልናስጀምረው እንችላለን። ታዲያ ትራክቶችን ከቤት ወደ ቤት ለማበረከት ምን ማለት እንችላለን? ትራክቶቻችን የተለያየ ይዘት ያላቸው በመሆኑ ከእያንዳንዱ ትራክት ጋር በደንብ መተዋወቅ አለብን።
5. ትራክቶችን ከቤት ወደ ቤት ማበርከት የሚቻለው እንዴት ነው?
5 ትራክት ስናበረክት፣ መግቢያችን እንደ ክልሉና እንደ ትራክቱ ዓይነት የተለያየ እንደሚሆን የታወቀ ነው። ውይይት ለመጀመር ትራክቱን ለቤቱ ባለቤት መስጠት እንችላለን። የትራክቱ የሚስብ ሽፋን የግለሰቡን ፍላጎት ሊቀሰቅስ ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ የተለያዩ ትራክቶችን ለቤቱ ባለቤት በማሳየት የሚፈልገውን እንዲመርጥ ልንጋብዘው እንችላለን። በምናገለግልበት ክልል ሰዎች በራቸውን ለመክፈት ፈቃደኛ ካልሆኑ ትራክቱን የቤቱ ባለቤት እንዲያየው አድርገን መያዝ ይቻላል፤ ወይም ስለ አንድ ጉዳይ የእሱን አመለካከት መስማት እንደምንፈልግ በመግለጽ ትራክቱን በበሩ ሥር ብንከትለት ፈቃደኛ መሆኑን ልንጠይቀው እንችላለን። የትራክቱ ርዕስ በጥያቄ መልክ የቀረበ ከሆነ ግለሰቡ ስለ ጉዳዩ ያለውን አመለካከት እንዲነግረን ርዕሱን መጠየቅ ይቻላል። አሊያም የሰውየው ፍላጎት እንዲቀሰቀስና ውይይት እንዲጀምር የሚያደርገው ሌላ ጥያቄ ማንሳት ይቻል ይሆናል። ከዚያም ከትራክቱ ላይ የተወሰነውን ክፍል ልናነብለት እንችላለን፤ በትራክቱ ላይ ያሉትን ጥያቄዎች ስናነብ ቆም እያልን የቤቱ ባለቤት ሐሳቡን እንዲገልጽ ማድረግ ይቻላል። እንዲሁም ቁልፍ የሆኑትን ጥቅሶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ማንበብ እንችላለን። በትራክቱ የተወሰነ ክፍል ላይ ከተወያየን በኋላ በሌላ ጊዜ ለመመለስ ቁርጥ ያለ ቀጠሮ በመያዝ ውይይቱን መደምደም ይቻላል። ጉባኤው ቤታቸው ላልተገኙ ሰዎች ጽሑፎችን አስቀምጦ የመሄድ ልማድ ካለው ትራክቶችን አላፊ አግዳሚው በማያይበት ቦታ ላይ አስቀምጦ መሄዱ የተሻለ ነው።
6. በመንገድ ላይ ስንመሠክር ትራክቶችን መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?
6 በመንገድ ላይ ምሥክርነት፦ በመንገድ ላይ ስትመሠክር ትራክቶችን ተጠቅመህ ታውቃለህ? አንዳንድ ሰዎች ስለሚቸኩሉ ከእኛ ጋር ቆመው መወያየት አይችሉ ይሆናል። እነዚህ ሰዎች ፍላጎት ያላቸው መሆን አለመሆኑን ማወቅ ሊከብደን ይችላል። በዚህ ወቅት ያነቡት እንደሆነ ሳናውቅ በቅርብ የወጡ መጽሔቶችን ከማበርከት ይልቅ ትራክቶችን መስጠት እንችላለን። ሽፋኑ የሚስብና መልእክቱም እጥር ምጥን ያለ በመሆኑ ጥቂት ደቂቃዎችን ሲያገኙ ትራክቱን ለማንበብ ጉጉት ሊያድርባቸው ይችላል። እርግጥ ነው፣ የማይቸኩሉ ከሆነ ከትራክቱ ላይ ጥቂት ሐሳቦችን ማወያየቱ የተሻለ ነው።
7. መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለመመሥከር ትራክቶችን እንዴት መጠቀም እንደሚቻል የሚያሳዩ ተሞክሮዎችን ተናገር።
7 መደበኛ ባልሆነ ምሥክርነት፦ በትራክቶች ተጠቅሞ መደበኛ ባልሆነ መንገድ መመሥከር ቀላል ነው። አንድ ወንድም ሁልጊዜ ከቤት ከመውጣቱ በፊት በኪሱ ትራክቶችን ይይዛል። ይህ ወንድም፣ አንድ ሰው ሲያገኝ ለምሳሌ የሱቅ ባለቤት ሊሆን ይችላል የሚያነበው ነገር ቢሰጠው ፈቃደኛ እንደሆነ በመጠየቅ ብቻ ትራክት ያበረክታል። አንድ ባልና ሚስት ወደ ኒው ዮርክ ሲቲ ለጉብኝት ሲሄዱ በዚያ ከተማ ከተለያዩ አገሮች የመጡ ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ተገነዘቡ። በመሆኑም ለሰዎች ሁሉ (እንግሊዝኛ) የተባለውን ቡክሌትና በተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጁ ትራክቶችን ይዘው ሄዱ። ከዚያም በመንገድ ላይም ሆነ በመናፈሻ አሊያም በምግብ ቤት አንድ ሰው የውጭ አገር ቋንቋ ሲናገር ሲሰሙ ለግለሰቡ በቋንቋው የተዘጋጀ ትራክት ያበረክቱለት ነበር።
8. ትራክቶች ከዘር ጋር የሚመሳሰሉት እንዴት ነው?
8 ዘርህን ዝራ፦ ትራክቶች ከዘር ጋር ሊመሳሰሉ ይችላሉ። አንድ ገበሬ የትኛው ዘር እንደሚያፈራ ስለማያውቅ ዘሩን እየዘገነ ይበትነዋል። መክብብ 11:6 እንዲህ ይላል፦ “ጠዋት ላይ ዘርህን ዝራ፤ ማታም ላይ እጅህ ሥራ አይፍታ፤ ይህ ወይም ያ፣ ወይም ሁለቱ መልካም ይሁኑ፣ የቱ እንደሚያፈራ አታውቅምና።” በመሆኑም ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመመሥከር በሚያስችለው በዚህ መሣሪያ አማካኝነት ‘እውቀትን እንዝራ።’—ምሳሌ 15:7 የ1954 ትርጉም
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ትራክቶች የምሥክርነቱን ሥራ ለማካሄድ ውጤታማ መሣሪያዎች በመሆናቸው ከኅዳር ወር ጀምሮ አልፎ አልፎ በወሩ ውስጥ የሚበረከቱ ጽሑፎች ይሆናሉ