ጽሑፎቻችንን ጥሩ አድርጋችሁ ተጠቀሙባቸው
1. ለይሖዋ ዝግጅቶች አድናቆት በማሳየት ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?
1 ኢየሱስ ብዙ ቁጥር ያለውን ሕዝብ በተአምር ከመገበ በኋላ የተረፈው ቁርስራሽ እንዲሰበሰብ ዝግጅት አድርጎ ነበር። (ማቴ. 14:19-21) ኢየሱስ በዚህ መንገድ ለይሖዋ ዝግጅቶች አድናቆት ማሳየቱ እኛም ይሖዋ ‘በታማኙ መጋቢ’ በኩል የሚያደርግልንን ዝግጅት ጥሩ አድርገን በመጠቀም ‘አመስጋኝ መሆናችንን እንድናሳይ’ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል።—ቆላ. 3:15፤ ሉቃስ 12:42፤ ማቴ. 24:45-47
2. መጽሔቶች እንዳይከማቹብን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
2 መጽሔቶች፦ መጽሔቶችን ከሥር ከሥሩ ካላበረከትናቸው በቀላሉ ሊከማቹብን ይችላሉ። ለማበርከት ከምንወስዳቸው መጽሔቶች መካከል የተወሰነው የሚተርፍ ከሆነ ትእዛዛችንን መቀነስ ይገባናል። ስለ ቆዩ መጽሔቶችስ ምን ማለት ይቻላል? እነዚህ መጽሔቶች የቆዩ ስለሆኑ ብቻ ጊዜ የሚያልፍባቸው አይደሉም። የቆዩ መጽሔቶች በብዛት ካሉን ምናልባት የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ ወይም ሌላ ሽማግሌ መጽሔቶቹን እንዴት ውጤታማ በሆነ መንገድ ማበርከት እንደምንችል ሊረዳን ይችላል።
3, 4. ከጉባኤ ጽሑፎችን ስንወስድ የትኞቹን ነጥቦች ማስታወስ ይኖርብናል?
3 ሌሎች ጽሑፎች፦ ወሩ አልፎ የሚበረከተው ጽሑፍ ሲቀየር ተጨማሪ ጽሑፎችን ከጉባኤ ከመውሰድህ በፊት ያ ጽሑፍ እቤትህ ይገኝ እንደሆነና እንዳልሆነ አረጋግጥ። በሳምንቱ ውስጥ ለማበርከት የሚያስፈልግህን ያህል ብቻ ውሰድ፤ የወሰድከውን ካበረከትክ በኋላ ተጨማሪ መውሰድ ትችላለህ።
4 ለግል የምትጠቀምባቸውን ጽሑፎች በተመለከተ ደግሞ የሚያስፈልጉህን ብቻ እዘዝ። በጽሑፎቹ ላይ ስም ለመጻፍ በተዘጋጀው ቦታ ላይ ስምህን ጻፍ። እንዲህ ማድረግህ ጽሑፉ ቢጠፋብህ እንኳ መልሰህ እንድታገኘው ይረዳሃል። በሲዲ የተዘጋጀውን ዎችታወር ላይብረሪ የምትጠቀም እንዲሁም የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔት የግል ቅጂዎችህን በደንብ የምታስቀምጥ ከሆነ የእነዚህን መጽሔቶች ጥራዝ ማዘዝ ላያስፈልግህ ይችላል።
5. ጽሑፎቻችንን ስናበረክት ምን ነገሮችን በአእምሯችን መያዝ ይኖርብናል?
5 ጽሑፎችን ስናበረክት፦ ጽሑፎቻችንን እውነተኛ ፍላጎት ላላቸው ሰዎች ብቻ ለማበርከት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። በመስክ አገልግሎት ላይ የምናበረክታቸውን የእነዚህን ጠቃሚ መሣሪያዎች ወጪ የመሸፈን ኃላፊነት በዋነኝነት የተጣለው በእኛ ላይ መሆኑን መዘንጋት አይኖርብንም። ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች ጽሑፎችን ስታበረክት ዓለም አቀፉን ሥራ በገንዘብ የመደገፍ መብት እንዳላቸው ከመግለጽ ወደኋላ አትበል።
6. ጽሑፎቻችንን ከፍ አድርገን የምንመለከታቸው ለምንድን ነው? ይህስ ምን እንዳናደርጋቸው ያነሳሳናል?
6 ኢየሱስ በተአምር ሰዎችን መግቧል፤ ሆኖም ብዙውን ጊዜ ሰዎችን የመገበው በመንፈሳዊ ነበር። ኢየሱስ “ሰው ከይሖዋ አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በምግብ ብቻ ሊኖር አይችልም” ብሎ ነበር። (ማቴ. 4:4) ጽሑፎቻችን የዘላለም ሕይወት ለማግኘት በጣም አስፈላጊ የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ያስተምሩናል። (ዮሐ. 17:3) እነዚህ ጽሑፎች በጣም ዋጋ ያላቸው በመሆናቸው ልናባክናቸው አይገባም!