የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • nwt 1 ዮሐንስ 1:1-5:21
  • 1 ዮሐንስ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • 1 ዮሐንስ
  • አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
1 ዮሐንስ

የዮሐንስ የመጀመሪያው ደብዳቤ

1 ከመጀመሪያ የነበረውን፣ የሰማነውን፣ በዓይናችን ያየነውን፣ በትኩረት የተመለከትነውንና በእጃችን የዳሰስነውን የሕይወትን ቃል በተመለከተ እንጽፍላችኋለን፤+ 2 (አዎ፣ ይህ ሕይወት ተገልጧል፤ እኛም አይተናል፤ ደግሞም እየመሠከርን ነው፤+ እንዲሁም በአብ ዘንድ የነበረውንና ለእኛ የተገለጠውን የዘላለም ሕይወት+ ለእናንተ እየነገርናችሁ ነው፤) 3 እናንተም ከእኛ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ* ያየነውንና የሰማነውን ለእናንተም እየነገርናችሁ ነው።+ ደግሞም ይህ ኅብረታችን ከአብና ከልጁ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው።+ 4 እነዚህን ነገሮች የምንጽፍላችሁ ደስታችን የተሟላ እንዲሆን ነው።

5 ከእሱ የሰማነውና ለእናንተ የምናሳውቀው መልእክት ይህ ነው፦ አምላክ ብርሃን ነው፤+ በእሱም ዘንድ* ጨለማ ፈጽሞ የለም። 6 “ከእሱ ጋር ኅብረት አለን” ብለን እየተናገርን በጨለማ የምንመላለስ ከሆነ እየዋሸን ነው፤ እውነትንም ሥራ ላይ እያዋልን አይደለም።+ 7 ይሁን እንጂ እሱ ራሱ በብርሃን እንዳለ ሁሉ እኛም በብርሃን የምንመላለስ ከሆነ እርስ በርሳችን ኅብረት ይኖረናል፤ እንዲሁም የልጁ የኢየሱስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል።+

8 “ኃጢአት የለብንም” ብለን የምንናገር ከሆነ ራሳችንን እያታለልን ነው፤+ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም። 9 ኃጢአታችንን የምንናዘዝ ከሆነ እሱ ታማኝና ጻድቅ ስለሆነ ኃጢአታችንን ይቅር ይለናል፤ እንዲሁም ከክፋት ሁሉ ያነጻናል።+ 10 “ኃጢአት አልሠራንም” ብለን የምንናገር ከሆነ እሱን ውሸታም እያደረግነው ነው፤ ቃሉም በውስጣችን የለም።

2 የተወደዳችሁ ልጆቼ፣ እነዚህን ነገሮች የምጽፍላችሁ ኃጢአት* እንዳትሠሩ ነው። ማንም ኃጢአት ቢሠራ ግን በአብ ዘንድ ረዳት* አለን፤ እሱም ጻድቅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።+ 2 እሱ ለእኛ ኃጢአት+ የቀረበ የማስተሰረያ* መሥዋዕት ነው፤+ ሆኖም ለእኛ ኃጢአት ብቻ ሳይሆን ለዓለም ሁሉ ኃጢአት ጭምር ነው።+ 3 ደግሞም ትእዛዛቱን መፈጸማችንን ከቀጠልን እሱን የምናውቅ መሆናችንን በዚህ እንረዳለን። 4 “እሱን አውቀዋለሁ” እያለ ትእዛዛቱን የማይፈጽም ሰው ቢኖር ውሸታም ነው፤ እውነትም በዚህ ሰው ውስጥ የለም። 5 ሆኖም የእሱን ቃል የሚጠብቅ ማንም ቢኖር የአምላክ ፍቅር በእርግጥ በዚህ ሰው ላይ ፍጹም በሆነ መንገድ ይታያል።+ ከእሱ ጋር አንድነት እንዳለንም በዚህ እናውቃለን።+ 6 ከእሱ ጋር ያለኝን አንድነት ጠብቄ እኖራለሁ የሚል፣ እሱ በተመላለሰበት መንገድ የመመላለስ ግዴታ አለበት።+

7 የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ የምጽፍላችሁ ከመጀመሪያ ጀምሮ የነበራችሁን የቆየውን ትእዛዝ እንጂ አዲስ ትእዛዝ አይደለም።+ ይህ የቆየው ትእዛዝ የሰማችሁት ቃል ነው። 8 ይሁንና በእሱም ሆነ በእናንተ ዘንድ እውነት የሆነውን አዲስ ትእዛዝ እጽፍላችኋለሁ፤ ምክንያቱም ጨለማው እያለፈና እውነተኛው ብርሃን አሁንም እንኳ እያበራ ነው።+

9 በብርሃን ውስጥ እንዳለ እየተናገረ ወንድሙን የሚጠላ+ አሁንም በጨለማ ውስጥ ነው።+ 10 ወንድሙን የሚወድ በብርሃን ውስጥ ይኖራል፤+ በእሱም ዘንድ ምንም የሚያሰናክል ነገር የለም። 11 ወንድሙን የሚጠላ ግን በጨለማ ውስጥ ነው፤ በጨለማም ይመላለሳል፤+ ደግሞም ጨለማው ዓይኑን ስላሳወረው ወዴት እንደሚሄድ አያውቅም።+

12 ልጆቼ ሆይ፣ የምጽፍላችሁ ለእሱ ስም ሲባል ኃጢአታችሁ ይቅር ስለተባለላችሁ ነው።+ 13 አባቶች ሆይ፣ የምጽፍላችሁ ከመጀመሪያ ያለውን እሱን ስላወቃችሁት ነው። እናንተ ወጣት ወንዶች፣ የምጽፍላችሁ ክፉውን ስላሸነፋችሁት ነው።+ ልጆች ሆይ፣ የምጽፍላችሁ አብን ስላወቃችሁት ነው።+ 14 አባቶች ሆይ፣ የምጽፍላችሁ ከመጀመሪያ ያለውን እሱን ስላወቃችሁት ነው። እናንተ ወጣት ወንዶች፣ የምጽፍላችሁ ጠንካሮች ስለሆናችሁ፣+ የአምላክ ቃል በልባችሁ ስለሚኖርና+ ክፉውን ስላሸነፋችሁት ነው።+

15 ዓለምንም ሆነ በዓለም ውስጥ ያሉትን ነገሮች አትውደዱ።+ ማንም ዓለምን የሚወድ ከሆነ የአብ ፍቅር በውስጡ የለም፤+ 16 ምክንያቱም በዓለም ያለው ነገር ሁሉ ይኸውም የሥጋ ምኞት፣+ የዓይን አምሮትና+ ኑሮዬ ይታይልኝ ማለት* ከዓለም እንጂ ከአብ የሚመነጭ አይደለም። 17 ከዚህም በተጨማሪ ዓለምም ሆነ ምኞቱ ያልፋሉ፤+ የአምላክን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።+

18 ልጆቼ ሆይ፣ ይህ የመጨረሻው ሰዓት ነው፤ እንደሰማችሁትም ፀረ ክርስቶስ እየመጣ ነው፤+ አሁንም እንኳ ብዙ ፀረ ክርስቶሶች መጥተዋል፤+ ከዚህም በመነሳት ይህ የመጨረሻው ሰዓት መሆኑን እናውቃለን። 19 በእኛ መካከል ነበሩ፤ ሆኖም ከእኛ ወገን ስላልነበሩ ትተውን ሄደዋል።+ ከእኛ ወገን ቢሆኑማ ኖሮ ከእኛ ጋር ጸንተው በኖሩ ነበር። ሆኖም ከእኛ ወገን የሆኑት ሁሉም አለመሆናቸው በግልጽ ይታይ ዘንድ ከእኛ ተለይተው ወጡ።+ 20 እናንተ ግን ቅዱስ ከሆነው ከእሱ የመንፈስ ቅብዓት አግኝታችኋል፤+ ደግሞም ሁላችሁም እውቀት አላችሁ። 21 የምጽፍላችሁ እውነትን+ ስለማታውቁ ሳይሆን እውነትን ስለምታውቁና ከእውነት ምንም ዓይነት ውሸት ስለማይወጣ ነው።+

22 ኢየሱስን፣ ክርስቶስ አይደለም ብሎ ከሚክድ በቀር ውሸታም ማን ነው?+ ይህ አብንና ወልድን የሚክደው ፀረ ክርስቶስ ነው።+ 23 ወልድን የሚክድ ሁሉ በአብ ዘንድም ተቀባይነት የለውም።+ ወልድን አምኖ የሚቀበል ሁሉ+ ግን በአብም ዘንድ ተቀባይነት አለው።+ 24 በእናንተ በኩል ግን ከመጀመሪያ የሰማችሁት በልባችሁ ይኑር።+ ከመጀመሪያ የሰማችሁት በልባችሁ የሚኖር ከሆነ እናንተም ከወልድና ከአብ ጋር ያላችሁን አንድነት ጠብቃችሁ ትኖራላችሁ። 25 ከዚህም በተጨማሪ እሱ ራሱ የገባልን የተስፋ ቃል የዘላለም ሕይወት ነው።+

26 እነዚህን ነገሮች የምጽፍላችሁ ሊያሳስቷችሁ ከሚሞክሩት ሰዎች የተነሳ ነው። 27 እናንተ ግን ከእሱ የተቀበላችሁት የመንፈስ ቅብዓት+ በውስጣችሁ ይኖራል፤ በመሆኑም ማንም እንዲያስተምራችሁ አያስፈልግም፤ ከዚህ ይልቅ ከእሱ ያገኛችሁት ይህ ቅብዓት ስለ ሁሉም ነገር እያስተማራችሁ ነው፤+ ደግሞም እውነት እንጂ ውሸት አይደለም። ይህ ቅብዓት ባስተማራችሁ መሠረት ከእሱ ጋር ያላችሁን አንድነት ጠብቃችሁ ኑሩ።+ 28 እንግዲህ ልጆቼ፣ እሱ በሚገለጥበት ጊዜ የመናገር ነፃነት+ እንዲኖረንና እሱ በሚገኝበት ወቅት ለኀፍረት ተዳርገን ከእሱ እንዳንርቅ ከእሱ ጋር ያላችሁን አንድነት ጠብቃችሁ ኑሩ። 29 እሱ ጻድቅ መሆኑን ካወቃችሁ ጽድቅን የሚያደርግ ሁሉ ከእሱ የተወለደ መሆኑን ታውቃላችሁ።+

3 የአምላክ ልጆች ተብለን እንድንጠራ+ አብ ምን ያህል ታላቅ ፍቅር እንዳሳየን ተመልከቱ!+ ደግሞም ልጆቹ ነን። ዓለም እኛን የማያውቀን ለዚህ ነው፤+ ምክንያቱም ዓለም እሱን አላወቀውም።+ 2 የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ እኛ አሁን የአምላክ ልጆች ነን፤+ ሆኖም ወደፊት ምን እንደምንሆን ገና አልተገለጠም።+ እሱ በሚገለጥበት ጊዜ እንደ እሱ እንደምንሆን እናውቃለን፤ ምክንያቱም እሱን በእርግጥ እናየዋለን። 3 በእሱ ላይ እንዲህ ያለ ተስፋ ያላቸው ሁሉ እሱ ንጹሕ እንደሆነ እነሱም ራሳቸውን ያነጻሉ።+

4 በኃጢአት ጎዳና የሚመላለስ ሁሉ ዓመፀኛ ነው፤ ኃጢአትም ዓመፅ ነው። 5 በተጨማሪም እሱ እንዲገለጥ የተደረገው ኃጢአታችንን እንዲያስወግድ መሆኑን ታውቃላችሁ፤+ እሱ ደግሞ ኃጢአት የለበትም። 6 ከእሱ ጋር ያለውን አንድነት ጠብቆ የሚኖር ሁሉ በኃጢአት ጎዳና አይመላለስም፤+ በኃጢአት ጎዳና የሚመላለስ ሁሉ እሱን አላየውም ደግሞም አላወቀውም። 7 ልጆቼ ሆይ፣ ማንም አያሳስታችሁ፤ እሱ ጻድቅ እንደሆነ ሁሉ በጽድቅ ጎዳና የሚመላለስ ሰውም ጻድቅ ነው። 8 በኃጢአት ጎዳና የሚመላለስ የዲያብሎስ ወገን ነው፤ ምክንያቱም ዲያብሎስ ከመጀመሪያው አንስቶ* ኃጢአት ሲሠራ ቆይቷል።+ የአምላክ ልጅ የተገለጠው የዲያብሎስን ሥራ ለማፍረስ* ነው።+

9 ከአምላክ የተወለደ ሁሉ በኃጢአት ጎዳና አይመላለስም፤+ የአምላክ ዘር* እንዲህ ባለው ሰው ውስጥ ይኖራልና፤ በኃጢአት ጎዳናም ሊመላለስ አይችልም፤ ይህ ሰው ከአምላክ የተወለደ ነውና።+ 10 የአምላክ ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች በዚህ በግልጽ ይታወቃሉ፦ በጽድቅ ጎዳና የማይመላለስ ሁሉ የአምላክ ወገን አይደለም፤ ወንድሙን የማይወድም የአምላክ ወገን አይደለም።+ 11 ከመጀመሪያ የሰማችሁት መልእክት እርስ በርሳችን መዋደድ አለብን የሚል ነውና፤+ 12 ከክፉው* ወገን እንደሆነውና ወንድሙን በጭካኔ እንደገደለው እንደ ቃየን መሆን የለብንም።+ ቃየን ወንድሙን በጭካኔ የገደለው በምን ምክንያት ነበር? የእሱ ሥራ ክፉ፣+ የወንድሙ ሥራ ግን ጽድቅ ስለነበረ ነው።+

13 ወንድሞች፣ ዓለም ቢጠላችሁ አትደነቁ።+ 14 እኛ ወንድሞችን ስለምንወድ+ ከሞት ወደ ሕይወት እንደተሻገርን እናውቃለን።+ ወንድሙን የማይወድ በሞት ውስጥ ይኖራል።+ 15 ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፤+ ነፍሰ ገዳይ የሆነ ሁሉ ደግሞ የዘላለም ሕይወት እንደሌለው ታውቃላችሁ።+ 16 እሱ ሕይወቱን* ለእኛ አሳልፎ ስለሰጠ በዚህ ፍቅርን አውቀናል፤+ እኛም ሕይወታችንን* ለወንድሞቻችን አሳልፈን የመስጠት ግዴታ አለብን።+ 17 ይሁን እንጂ የዚህ ዓለም ቁሳዊ ንብረት ያለው ሰው ወንድሙ ሲቸገር ተመልክቶ ሳይራራለት ቢቀር ‘የአምላክ ፍቅር በእሱ ውስጥ አለ’ እንዴት ሊባል ይችላል?+ 18 ልጆቼ ሆይ፣ በተግባርና+ በእውነት+ እንጂ በቃልና በአንደበት ብቻ አንዋደድ።+

19 ከእውነት ወገን መሆናችንን በዚህ እናውቃለን፤ ልባችንም በፊቱ እንዲረጋጋ* እናደርጋለን፤ 20 ይህን የምናደርገው ልባችን እኛን በሚኮንንበት ነገር ሁሉ ነው፤ ምክንያቱም አምላክ ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነው፤ ደግሞም ሁሉንም ነገር ያውቃል።+ 21 የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ ልባችን የማይኮንነን ከሆነ ከአምላክ ጋር በነፃነት መነጋገር እንችላለን፤+ 22 እንዲሁም ትእዛዛቱን ስለምንጠብቅና በፊቱ ደስ የሚያሰኙትን ነገሮች ስለምናደርግ የምንጠይቀውን ሁሉ ከእሱ እንቀበላለን።+ 23 በእርግጥም ትእዛዙ ይህ ነው፦ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንድናምንና+ እሱ ባዘዘን መሠረት እርስ በርሳችን እንድንዋደድ ነው።+ 24 በተጨማሪም ትእዛዛቱን የሚጠብቅ ሰው ከእሱ ጋር ያለውን አንድነት ጠብቆ ይኖራል፤ እሱም እንዲህ ካለው ሰው ጋር አንድነት ይኖረዋል።+ እሱ ከእኛ ጋር ያለውን አንድነት ጠብቆ እንደሚኖር በሰጠን መንፈስ አማካኝነት እናውቃለን።+

4 የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ በመንፈስ የተነገረን ቃል* ሁሉ አትመኑ፤+ ከዚህ ይልቅ በመንፈስ የተነገሩት ቃላት* ከአምላክ የመነጩ መሆን አለመሆናቸውን መርምሩ፤+ ብዙ ሐሰተኛ ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና።+

2 በመንፈስ የተነገረው ቃል ከአምላክ የመነጨ መሆኑን በዚህ ማወቅ ትችላላችሁ፦ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደመጣ የሚመሠክር በመንፈስ የተነገረ ቃል ሁሉ ከአምላክ የመነጨ ነው።+ 3 ሆኖም ስለ ኢየሱስ የማይመሠክር በመንፈስ የተነገረ ቃል ሁሉ ከአምላክ የሚመነጭ አይደለም።+ ይህ በመንፈስ የተነገረ ቃል ከፀረ ክርስቶስ የሚመነጭ ነው፤ ፀረ ክርስቶስ እንዲህ ያሉ ነገሮችን እንደሚናገር ሰምታችኋል፤+ አሁንም እንኳ ይህ ቃል በዓለም ላይ እየተነገረ ነው።+

4 ልጆቼ ሆይ፣ እናንተ ከአምላክ ወገን ናችሁ፤ እነሱንም* አሸንፋችኋል፤+ ምክንያቱም ከእናንተ ጎን ያለው፣+ ከዓለም ጎን ካለው ይበልጣል።+ 5 እነሱ የዓለም ወገን ናቸው፤+ ከዓለም የሚመነጨውን ነገር የሚናገሩትና ዓለምም የሚሰማቸው ለዚህ ነው።+ 6 እኛ ከአምላክ ወገን ነን። አምላክን የሚያውቅ ሁሉ ይሰማናል፤+ ከአምላክ ወገን ያልሆነ ሁሉ አይሰማንም።+ በመንፈስ የተነገረውን የእውነት ቃልና በመንፈስ የተነገረውን የስህተት ቃል ለይተን የምናውቀው በዚህ መንገድ ነው።+

7 የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ እርስ በርስ መዋደዳችንን እንቀጥል፤+ ምክንያቱም ፍቅር ከአምላክ ነው፤ ፍቅር የሚያሳይ ሁሉ ከአምላክ የተወለደ ሲሆን አምላክን ያውቃል።+ 8 ፍቅር የማያሳይ አምላክን አያውቅም፤ ምክንያቱም አምላክ ፍቅር ነው።+ 9 የአምላክ ፍቅር ከእኛ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በዚህ መንገድ ተገልጧል፤ እኛ በእሱ አማካኝነት ሕይወት ማግኘት እንድንችል+ አምላክ አንድያ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታል።+ 10 ይህ ፍቅር የተገለጠው በዚህ መንገድ ነው፦ እኛ አምላክን ስለወደድነው ሳይሆን እሱ ስለወደደንና ለኃጢአታችን የማስተሰረያ መሥዋዕት* እንዲሆን+ ልጁን ስለላከ ነው።+

11 የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ አምላክ የወደደን በዚህ መንገድ ከሆነ እኛም እርስ በርሳችን የመዋደድ ግዴታ አለብን።+ 12 መቼም ቢሆን አምላክን ያየው ማንም የለም።+ እርስ በርስ መዋደዳችንን ከቀጠልን አምላክ ከእኛ ጋር ይሆናል፤ ፍቅሩም በመካከላችን ፍጹም ይሆናል።+ 13 እሱ መንፈሱን ስለሰጠን እኛ ከእሱ ጋር አንድነት እንዳለንና እሱም ከእኛ ጋር አንድነት እንዳለው እናውቃለን። 14 ከዚህ በተጨማሪ አብ ልጁን የዓለም አዳኝ አድርጎ እንደላከው እኛ ራሳችን አይተናል፤ ደግሞም እየመሠከርን ነው።+ 15 ማንም ሰው ኢየሱስ የአምላክ ልጅ መሆኑን የሚመሠክር+ ከሆነ አምላክ እንዲህ ካለው ሰው ጋር አንድነት ይኖረዋል፤ እሱም ከአምላክ ጋር አንድነት ይኖረዋል።+ 16 ደግሞም አምላክ ለእኛ ያለውን ፍቅር አውቀናል፤ እንዲሁም አምነናል።+

አምላክ ፍቅር ነው፤+ በፍቅር የሚኖር ከአምላክ ጋር ያለውን አንድነት ጠብቆ ይኖራል፤ አምላክም ከእሱ ጋር አንድነት ይኖረዋል።+ 17 በመሆኑም በፍርድ ቀን የመናገር ነፃነት* ይኖረን ዘንድ+ ፍቅር በእኛ መካከል ፍጹም የሆነው በዚህ መንገድ ነው፤ ምክንያቱም በዚህ ዓለም ውስጥ እኛ ራሳችን እንደ እሱ* ነን። 18 በፍቅር ፍርሃት የለም፤+ እንዲያውም ፍጹም ፍቅር ፍርሃትን አውጥቶ ይጥላል፤* ምክንያቱም ፍርሃት ወደኋላ እንድንል ያደርገናል። ደግሞም የሚፈራ ሰው ፍጹም የሆነ ፍቅር የለውም።+ 19 እሱ አስቀድሞ ስለወደደን እኛም ፍቅር እናሳያለን።+

20 ማንም “አምላክን እወደዋለሁ” እያለ ወንድሙን የሚጠላ ከሆነ ይህ ሰው ውሸታም ነው።+ ያየውን ወንድሙን የማይወድ+ ያላየውን አምላክ ሊወድ አይችልምና።+ 21 እሱም “አምላክን የሚወድ ሁሉ ወንድሙንም መውደድ ይገባዋል” የሚለውን ይህን ትእዛዝ ሰጥቶናል።+

5 ኢየሱስ በእርግጥ ክርስቶስ እንደሆነ የሚያምን ሁሉ ከአምላክ ተወልዷል፤+ አባቱን የሚወድ ሁሉ ደግሞ ከእሱ የተወለደውንም ይወዳል። 2 አምላክን ስንወድና ትእዛዛቱን ስንፈጽም የአምላክን ልጆች+ እንደምንወድ በዚህ እናውቃለን። 3 አምላክን መውደድ ማለት ትእዛዛቱን መጠበቅ ማለት ነውና፤+ ትእዛዛቱ ደግሞ ከባድ አይደሉም፤+ 4 ምክንያቱም ከአምላክ የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋል።+ ዓለምን ድል እንድናደርግ ያስቻለን እምነታችን ነው።+

5 ዓለምን ሊያሸንፍ የሚችል ማን ነው?+ ኢየሱስ የአምላክ ልጅ እንደሆነ የሚያምን ሰው አይደለም?+ 6 በውኃና በደም አማካኝነት የመጣው፣ እሱ ይኸውም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ የመጣውም ከውኃ ጋር ብቻ ሳይሆን+ ከውኃና ከደም ጋር ነው።+ ምሥክርነት የሚሰጠውም መንፈስ ነው፤+ ምክንያቱም መንፈስ እውነት ነው። 7 ምሥክርነት የሚሰጡ ሦስት ነገሮች አሉ፦ 8 እነሱም መንፈሱ፣+ ውኃውና+ ደሙ+ ናቸው፤ እነዚህ ሦስቱ ደግሞ ይስማማሉ።

9 ሰዎች የሚሰጡትን ምሥክርነት ከተቀበልን አምላክ የሚሰጠው ምሥክርነት ደግሞ ከዚያ የላቀ ነው። ምክንያቱም አምላክ የሰጠው ምሥክርነት ስለ ልጁ የሰጠው የምሥክርነት ቃል ነው። 10 በአምላክ ልጅ የሚያምን የምሥክርነቱ ቃል በልቡ አለው። በአምላክ የማያምን ግን አምላክ ስለ ልጁ የሰጠውን ምሥክርነት ስላላመነ እሱን ውሸታም አድርጎታል።+ 11 ምሥክርነቱም ይህ ነው፤ አምላክ የዘላለም ሕይወት ሰጠን፤+ ይህም ሕይወት የተገኘው በልጁ ነው።+ 12 ልጁ ያለው ይህ ሕይወት አለው፤ የአምላክ ልጅ የሌለው ይህ ሕይወት የለውም።+

13 እነዚህን ነገሮች የምጽፍላችሁ በአምላክ ልጅ ስም የምታምኑት+ እናንተ የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ እንድታውቁ ነው።+ 14 በእሱ ላይ ያለን ትምክህት* ይህ ነው፤+ የምንጠይቀው ነገር ምንም ይሁን ምን ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ ሁኔታ እስከለመንን ድረስ ይሰማናል።+ 15 የምንጠይቀውንም ነገር ሁሉ እንደሚሰማን ስለምናውቅ የምንጠይቀውን ነገር እንደምናገኝ እርግጠኞች ነን።+

16 ማንም ሰው ወንድሙ ለሞት የማያበቃ ኃጢአት ሲሠራ ቢያየው ስለ እሱ ይለምናል፤ አምላክም ሕይወት ይሰጠዋል።+ ይህ የሚሆነው ለሞት የሚያበቃ ኃጢአት ላልሠሩ ሰዎች ነው። ይሁን እንጂ ለሞት የሚያበቃ ኃጢአት አለ።+ እንዲህ ዓይነት ኃጢአት ለሠራ ግለሰብ ማንም ሰው ይጸልይ አልልም። 17 ጽድቅ ያልሆነ ነገር ሁሉ ኃጢአት ነው፤+ ይሁንና ለሞት የማያበቃ ኃጢአት አለ።

18 ከአምላክ የተወለደ ሁሉ በኃጢአት ጎዳና እንደማይመላለስ እናውቃለን፤ ይልቁንም ከአምላክ የተወለደው* ይጠብቀዋል፤ ክፉውም* ምንም ሊያደርገው አይችልም።+ 19 እኛ ከአምላክ ወገን መሆናችንን እናውቃለን፤ መላው ዓለም ግን በክፉው ቁጥጥር ሥር ነው።+ 20 ይሁንና የአምላክ ልጅ እንደመጣ እናውቃለን፤+ እሱም ስለ እውነተኛው አምላክ እውቀት ማግኘት እንድንችል ማስተዋል* ሰጥቶናል። እኛም በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ከእሱ ጋር አንድነት አለን።+ አዎ፣ እሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው።+ 21 ልጆቼ ሆይ፣ ከጣዖቶች ራቁ።+

ወይም “ተካፋይ እንድትሆኑ።”

ወይም “ከእሱም ጋር በተያያዘ።”

እዚህ ላይ የገባው ግሪክኛ ቃል በሆነ ጊዜ ላይ ለአፍታ የተፈጸመን ድርጊት የሚያመለክት ነው።

ወይም “ጠበቃ።”

ወይም “የእርቅ።”

ወይም “በሀብት ጉራ መንዛት።”

ወይም “ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ።”

ወይም “ለማጥፋት።”

ዘር የሚተካን ወይም ፍሬ የሚያፈራን ዘር ያመለክታል።

ሰይጣንን ያመለክታል።

ወይም “ነፍሱን።”

ወይም “ነፍሳችንን።”

ወይም “ሙሉ እምነት እንዲያድርበት።”

ቃል በቃል “መንፈስን።”

ቃል በቃል “መናፍስት።”

ይህ ቃል ሐሰተኛ ነቢያትን ያመለክታል።

ወይም “የእርቅ መሥዋዕት።”

ወይም “የመተማመን ስሜት።”

ኢየሱስ ክርስቶስን ያመለክታል።

ወይም “ያስወግዳል።”

ወይም “የመናገር ነፃነት።”

የአምላክ ልጅ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ያመለክታል።

ሰይጣንን ያመለክታል።

ቃል በቃል “የአእምሮ ግንዛቤ፤ የማሰብ ችሎታ።”

    የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ ጽሑፎች (2011-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ