ያገኘሃቸውን ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች አትርሳቸው
1 መጽሔቶቻችንንና ሌሎች ቲኦክራሲያዊ ጽሑፎችን በምናሰራጭበት ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስ የገለጸውን መልእክት ማሰራጨታችን ነው። ስለዚህ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ሁሉ ተመልሰን ሄደን ለማነጋገር የተለየ ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል።
2 በንቁ! መጽሔት ውስጥ ሰውየው ፍላጎት ባሳየበት አንድ ርዕስ ላይ ተወያይታችሁ ከነበረ ተመልሰህ መጥተህ በምታነጋግረው ጊዜ ውይይታችሁ በአንድ ቁልፍ የሆነ ጥቅስና ምናልባትም በአንድ ወይም በሁለት አንቀጾች ላይ የተመረኮዘ እንዲሆን በማድረግ በዚያው ርዕስ ላይ ተጨማሪ ነጥቦችን አክለህ አዳብረው። ሰውየው አሁንም ፍላጎት እንዳሳየ ከሆነ የንቁ! መጽሔት ቤተሰቡን በሙሉ እንደሚጠቅም ግለጽለት። እያንዳንዱ እትም ስለ አካባቢ ሁኔታ፣ ራስን ስለማሻሻል፣ በዛሬው ጊዜ ያሉትን ችግሮች እንዴት ለመወጣት እንደሚቻል እንዲሁም ወጣቶችን የሚያሳስቧቸውን ጥያቄዎች እና የመሳሰሉትን የሚዳስሱ የተለያዩ ርዕሶች ይዞ ይወጣል። ሰውየው የንቁ! መጽሔት ኮንትራት መግባት እንደሚቻልና የተለመደውን መዋጮ በመክፈል በአንድ ዓመት ውስጥ 24 ቅጂዎችን አለዚያም በስድስት ወር ውስጥ 12 ቅጂዎች ማግኘት እንደሚችል ንገረው።
3 ሰውየው በቅርብ ከወጣው የንቁ! መጽሔት ርዕሶች ውስጥ አንዳቸውም ባይስቡትስ? ውይይቱን ከማቆም ይልቅ ይህንን አጋጣሚ ምክንያቱን ማስረዳት በተባለው መጽሐፍ ገጽ 206 ላይ ባለው ሐሳብ መሠረት የይሖዋ ምስክሮችን ሥራ በተመለከተ ሰውየውን ለማስተማር ልትጠቀምበት ትችላለህ።
4 ቀደም ሲል 2 ጢሞቴዎስ 3:1–5ን በመጠቀም እንዲሁም በመጽሔቱ ገጽ 2 ላይ የተገለጸውን ሐሳብ በማጉላት “መጠበቂያ ግንብ” አበርክተህለት ከነበረ ተመልሰህ በምትሄድበት ጊዜ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ነገር ልትናገር ትችል ይሆናል፦
◼ “ባለፈው ውይይታችን በዛሬው ጊዜ በዓለም ዙሪያ እየተፈጸሙ ያሉት ነገሮች ምን ትርጉም እንዳላቸው ተወያይተን ነበር። ብዙ ሰዎች ለአምላክና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለሚገኙት እርሱ ላወጣቸው የአኗኗር ሥርዓቶች ግድ የሌላቸው ይመስላሉ። ይህም በ2 ጢሞቴዎስ 3:1–5 ላይ በሚገኘው ጥቅስ ውስጥ እንደተገለጸው ሰዎች እርስ በርሳቸው ባላቸው አመለካከት ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ተፅዕኖ አሳድሯል። ወደፊት የተሻሻሉ ሁኔታዎች ይመጣሉ ብሎ ለመጠበቅ የሚያሳምን ምክንያት ያለ ይመስልዎታል?” ሐሳብ እንዲሰጥ ጊዜ ከሰጠኸው በኋላ በ2 ጴጥሮስ 3:13 ላይ እንዲያተኩር ልታደርገው ትችላለህ። ከዚያም ምክንያቱን ማስረዳት በተባለው መጽሐፍ ገጽ 227–233 በመሄድ መንግሥቲቱ ለሰው ልጆች ምን እንደምታደርግላቸው ጎላ አድርገህ ግለጽ።
5 ተመላልሶ መጠየቅ በምታደርግለት ጊዜ ሰውየው ሃይማኖት የግል ጉዳይ እንደሆነ ተሰምቶት ሃይማኖቱን በሚመለከት ለመወያየት ፈቃደኛ እንዳልሆነ ታስተውል ይሆናል። ቀጥሎ ካለው ጋር ተመሳሳይ የሆነ ነገር ልትናገር ትችላለህ፦
◼ “ምንም እንኳን በጣም ብዙ ሃይማኖቶች ቢኖሩም ፈጣን በሆኑ የመጓጓዣ ዘዴዎችና የመገናኛ መሥመሮች አማካኝነት በጣም በተቀራረበችው ዓለም ላይ ያሉ የተለያዩ እምነቶች የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ወደድንም ጠላን በዓለም ዙሪያ የታወቀ ሆኗል። ስለዚህ የተለያዩ እምነቶች ያሏቸው ሰዎች ሐሳብ ለሐሳብ መለዋወጣቸው ይበልጥ ጥሩ ወደሆነ ግንኙነት ይመራል። ይህም በሃይማኖታዊ እምነቶች የተነሳ የተፈጠሩትን አንዳንድ ጥላቻዎች ሊያጠፋ ይችላል። አይመስልዎትም?” ሐሳብ እንዲሰጥ ጊዜ ከሰጠኸው በኋላ ሰውየው የሰው ልጅ አምላክን ለማግኘት ያደረገው ፍለጋ በተባለው መጽሐፍ ማውጫ ላይ እንዲያተኩር አድርግ።
6 ለእውነት ፍላጎት ያሳዩትን ሰዎች ሁሉ ተመልሰን ሄደን በማነጋገር ወደ ዘላለም ሕይወት በሚመራው ጎዳና ላይ እንዲጓዙ ለመርዳት የምንችለውን ጥረት ሁሉ እናድርግ። — ዮሐ. 4:23, 24