የአምላክ ቃል መመሪያ ይሰጣል
1 “የምንኖረው መከራ በሞላበትና መፍትሄ በታጣበት ዓለም ውስጥ ነው። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይራባሉ። ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄድ ሰዎች በአደንዛዥ ዕፅ ሱስ ተጠምደዋል። ብዙ ቤተሰቦች እየፈራረሱ ነው። የቅርብ ዘመድን ማስነወርና በአንድ የቤተሰብ አባል ላይ የሚፈጸም የኃይል ድርጊት ዘወትር በዜና ማሰራጫዎች ይሰማሉ። የምንተነፍሰው አየርና የምንጠጣው ውኃ ቀስ በቀስ እየተመረዘ በመሄድ ላይ ነው። በተጨማሪም ብዙዎቻችን የወንጀል ጥቃት ዒላማ ሆነናል።”
2 መጽሐፍ ቅዱስ—የአምላክ ቃል ነው ወይም የሰው? የተሰኘው መጽሐፍ ከላይ እንደተገለጸው በማለት ይጀምራል። መግቢያው ላይ የሰፈሩት ሐሳቦች መጽሐፉ ከሰባት ዓመት በፊት በታተመበት ጊዜ ከነበረው ይልቅ በአሁኑ ጊዜ የበለጠ ተፈጻሚነት አላቸው። ሰዎች የአምላክ ቃል መመሪያ እንደሚሰጥና እንደ ወረርሽኝ ለተዛመቱት ችግሮቻቸው መፍትሄ የሚሆኑ ሐሳቦች እንደሚያቀርብ ማወቅ ይኖርባቸዋል። በታኅሣሥ የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም፣ መጽሐፍ ቅዱስ—የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? እና የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ የተሰኙትን መጻሕፍት በማበርከት ሰዎችን ለመርዳት እንጣጣራለን። እርግጥ ጽሑፎችን ለአንድ ሰው ማበርከት ብቻውን ሰውዬው የአምላክን መመሪያ እንዲቀበል ዋስትና አይሆነውም። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የማስጀመር ግብ ይዘን ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ አለብን። እንዲህ ያለ ጥረት የምናደርግ ከሆነ እርዳታ እንደምናገኝ ማረጋገጫ ተሰጥቶናል። (ማቴ. 28:19, 20) ከዚህ ቀጥሎ አንዳንድ አቀራረቦች ተገልጸዋል:-
3 አረጋዊ የሆነ ሰው ካገኘህ ይህንን አቀራረብ ልትጠቀም ትችላለህ:-
◼ “ጥያቄ ብጠይቆት:- ወጣት በነበሩበት ጊዜ በአካባቢዎ የሚኖሩ ሰዎች እርስ በርሳቸው የነበራቸው ግንኙነት ምን ይመስል ነበር? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] በአሁኑ ጊዜ ነገሮች ሁሉ በጣም ተለውጠዋል። አይደለም እንዴ? እንዲህ ያለውን ለውጥ ያስከተለው ምን ይመስሎታል? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] በእርግጥም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈሩትን ትንቢቶች ፍጻሜ እየተመለከትን ነው። [2 ጢሞቴዎስ 3:1-5ን አንብብ።] መጽሐፍ ቅዱስ በአሁኑ ጊዜ ያለውን የዓለም ሁኔታ በትክክል ከመግለጹም በላይ በቅርብ ጊዜ የተሻለ ዓለም እንደሚመጣ ተስፋ ይሰጣል። በዚህም ምክንያት ሁሉም ሰው መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያነብ እናበረታታለን። ቀደም ሲል ጥቅሱን ያነበብኩበት የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የተባለው መጽሐፍ ቅዱስ ግልጽ በሆነ ቋንቋ እንደተጻፈ አስተውለዋል?” መጽሐፍ ቅዱስን በቀላሉ ለመረዳት እንዲቻል በዘመናዊ የእንግሊዝኛ ቋንቋ የተጻፈ መሆኑን ግለጽ። መጽሐፍ ቅዱስ—የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? የተሰኘውን መጽሐፍ ካሳየኸው በኋላ በአሁኑ ጊዜ ሲፈጸም የምናየውን ሌላ ትንቢት የሚያብራራውን ምዕራፍ 10ን አውጥተህ አሳየው። ከዚያም መጽሐፍ ቅዱሱንና መጽሐፉን አበርክት።
4 መጽሐፍ ቅዱስና መጽሐፉን ወደ አበረከትክለት አረጋዊ ሰው ተመልሰህ በምትሄድበት ጊዜ እንዲህ ልትል ትችላለህ:-
◼ “ባለፈው ጊዜ ስንነጋገር ዘመናዊውን ኅብረተሰብ ከጥቂት ዓመታት በፊት ከነበረው ሕይወት ጋር ስናወዳድረው ከበፊቱ በባሰ ሁኔታ መጥፎ እየሆነ መጥቷል በሚለው ሐሳብ ተስማምተን ነበር። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ወደፊት በጣም የተሻለ ዓለም እንደሚመጣ የሚሰጠውን ተስፋ ላሳይዎት ተመልሼ መጥቻለሁ። [ራእይ 21:3, 4ን አንብብ።] ይህ አምላክ የተናገረው ቃል መሆኑን ማወቃችን መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገራቸውን ሌሎች ነገሮችንም በትኩረት እንድንከታተል ያበረታታናል።” የአምላክ ቃል የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 14ን አውጣና አንቀጽ 3ና 4ን አንብብ። ነፃ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀምር ጋብዘው።
5 ከወጣት ልጅ ጋር ውይይት የምታደርግ ከሆነ ደግሞ የሚከተለውን ልትል ትችላለህ:-
◼ “አንድ ጥያቄ ብጠይቅህ ደስ ይለኛል:- ወጣት እንደመሆንህ መጠን የወደፊቱ ጊዜ የተሻለ ይሆናል ብለህ እንድታምን የሚያደርጉ ምክንያቶች አሉህ? የወደፊቱን ጊዜ የምትመለከተው እንዴት ነው? [መልስ አንዲሰጥ ፍቀድለት።] ደስ የሚለው የወደፊቱን ጊዜ ብሩህ በሆነ ተስፋ የምንመለከትበት በቂ ምክንያት አለን። [መዝሙር 37:10, 11ን አንብብ።] ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስና በውስጡ ለሰፈሩት ሐሳቦች የተለያየ አመለካከት ስላላቸው መጽሐፍ ቅዱስ—የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው የተባለውን ይህን መጽሐፍ አሳትመናል። ይህ መጽሐፍ መጽሐፍ ቅዱስን እንድናነብ የሚሰጠውን ምክንያቶች ልብ በል። [በገጽ 10ና 11 ላይ የሚገኙትን አንቀጽ 16ና 17ን አንብብ።] መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ነገር ትክክል መሆኑን አንዴ ካመንበት ለወደፊቱ ጊዜ የተረጋገጠ ተስፋ ይኖረናል ማለት ነው። ይህን መጽሐፍ ማንበብ የምትፈልግ ከሆነ አንድ ቅጂ ብተውልህ ደስ ይለኛል።”
6 “የአምላክ ቃል” የተሰኘውን መጽሐፍ ላበረከትክለት ሰው ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ በምትሄድበት ጊዜ እንዲህ ብለህ በመናገር ውይይትህን መጀመር ትችላለህ:-
◼ “ስለ ወደፊቱ ጊዜ እንደምታስብ በማወቄ ተደስቻለሁ። አስደሳችና ሰላም የሰፈነበት ጊዜ ወደፊት እንደሚመጣ ተስፋ የሚሰጠንን ባለፈው ጊዜ ያሳየሁህን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ታስታውሳለህ። አሁን ደግሞ ሌላ ጥቅስ አነብልሃለሁ። [ራእይ 21:3, 4 አንብብ።] ባለፈው ጊዜ ትቼልህ የሄድኩት መጽሐፍ መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ሳይሆን የአምላክ ቃል እንደሆነ አሳማኝ ማስረጃ ያቀርባል። ይህ እውነታ የሚጠቁማቸው ነገሮች አሉ። እነርሱም ምን እንደሆኑ ልብ በል። [ገጽ 184-5 ላይ ያሉትን አንቀጽ 1ና 2ን አንብብ።] የምትፈልግ ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ አብረን ብናጠና ደስ ይለኛል።” ለማጥናት ከተስማማ ወጣቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ እንዳለው ጠይቅ። ከሌለው የአዲሲቱ ዓለም ትርጉምን አበርክትለት።
7 ወላጆች ለሚከተለው አቀራረብ ጥሩ ምላሽ ሊሰጡ ይችላሉ:-
◼ “ልጆች ለአምላክ ፍቅርና አክብሮት እንዲኖራቸው ማስተማር አስቸጋሪ በሆነበት ጊዜ ውስጥ እንኖራለን። እውነት አይደለም? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] አምላክ ስላደረገልን ነገሮች፣ ወደፊት ምን እንደሚያደርግልንና ጥሩ ሰዎችን እንዴት እንደባረካቸው እንዲሁም ታዛዥ ያልሆኑ ሰዎችን ደግሞ እንዴት እንደቀጣቸው ሁሉም ወላጆች ለልጆቻቸው ለማስተማር ዝግጅት ቢያደርጉ ምንኛ የተሻለ ይሆን ነበር! ይህም ጥቅስ የሚናገረው ይህንኑ ሐሳብ ነው። [ሮሜ 15:4ን ወይም ምሳሌ 22:6ን አንብብ።] ልጆቻቸውን ወይም ወጣት ዘመዶቻቸውን ለመርዳት ለሚፈልጉ አዋቂዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን መማሪያ መጽሐፌ የተባለ ርዕስ ያለው ግሩም የሆነ መሣሪያ አለ። እርግጥ ነው ብዙ ትልልቅ ሰዎችም ይህን መጽሐፍ በማንበባቸው ተደስተዋል!” ጥቂት ርዕሶችንና ሥዕሎችን አሳይና መጽሐፉን አበርክት።
8 ተመላልሶ መጠየቅ ስታደርግ እንዲህ ማለት ትችላለህ:-
◼ “ባለፈው ጊዜ ከተነጋገርን ጀምሮ ትቼልዎት የሄድኩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን የያዘውን መጽሐፍ እርስዎና ትንንሽ ልጆችዎ እንዴት እንዳነበባችሁትና እንደተወያያችሁበት ለማወቅ ስጓጓ ነበር። [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] ብዙ አዋቂ ሰዎች እነርሱ ራሳቸው የማያውቋቸው ነገሮች በመጽሐፉ ውስጥ እንዳለ ተገንዝበዋል። ለምሳሌ እዚህ ታሪክ 98 ላይ ኢየሱስ ስለ ራሱ ዳግም መምጣት የተናገረውን ትንቢት እናነባለን። [በመጨረሻዎቹ ሦስት አንቀጾች ላይ ተወያዩ።] ይህ የሚያስደስት አይደለም? ይህንን ጉዳይ የሚያብራሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በገጹ መጨረሻ ላይ ሰፍረዋል። ስለዚህ ጉዳይ ተጨማሪ እውቀት ለማግኘት ይፈልጋሉ? [እውቀት በተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 1 ላይ እንድትወያዩ ሐሳብ አቅርብ።]” ሌላው አማራጭ ደግሞ በታሪክ 114 ወይም 115 ላይ ውይይት ማድረግ ነው።
9 ትልልቅ ሰዎችም ሆኑ ወጣቶች የመጽሐፍ ቅዱስን ጠቃሚነትና በሕይወታችን ውስጥ የሚሰጠውን መመሪያ እንዲያደንቁ ለመርዳት የምናደርገውን ጥረት ይሖዋ ይባርከዋል።— መዝ. 119:105