የመታሰቢያውን በዓል የምናስተዋውቅበት ዘመቻ መጋቢት 17 ይጀምራል
1. መጋቢት 17 የሚጀምረው ዘመቻ ምንድን ነው?
1 በየዓመቱ የሚከበረው የመታሰቢያ በዓል ስለ ኢየሱስ ሞት ለማወጅ ይረዳናል። (1 ቆሮ. 11:26) በመሆኑም ሌሎች ሰዎች በበዓሉ ላይ ተገኝተው፣ ይሖዋ ቤዛውን በመስጠት ስላደረገው ፍቅራዊ ዝግጅት እንዲያውቁ እንፈልጋለን። (ዮሐ. 3:16) በዚህ ዓመት፣ ሰዎች በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኙ ለመጋበዝ የምናደርገው ዘመቻ ቅዳሜ፣ መጋቢት 17 ይጀምራል። በዚህ ዘመቻ የተሟላ ተሳትፎ ለማድረግ ዝግጁ ናችሁ?
2. የመጋበዣ ወረቀቱን ለሰዎች ስንሰጥ ምን ማለት እንችላለን?
2 ምን ማለት እንችላለን? አቀራረባችን አጭር መሆኑ ጠቃሚ ነው። እንደሚከተለው ማለት እንችላለን፦ “ጤና ይስጥልኝ። ዛሬ የመጣነው ሐሙስ፣ መጋቢት 27, 2004 (እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ሚያዝያ 5, 2012) በዓለም ዙሪያ በሚከበር ዓመታዊ የመታሰቢያ በዓል ላይ ከቤተሰብዎ ጋር እንዲገኙ የመጋበዣ ወረቀት ልንሰጥዎት ነው። የኢየሱስ ሞት ምን እንዳስገኘና በአሁኑ ወቅት ኢየሱስ ምን እያከናወነ እንደሆነ የሚያብራራ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ንግግር ይቀርባል። ይህ የመጋበዣ ወረቀት ስብሰባው በአካባቢያችን የሚደረግበትን ቦታና ሰዓት ይገልጻል።” ቅዳሜና እሁድ የመጋበዣ ወረቀቱን ስናሰራጭ ሁኔታው የሚፈቅድ ከሆነ መጽሔቶችን አያይዘን ማበርከት እንችላለን።
3. በተቻለን መጠን ብዙ ሰዎችን መጋበዝ የምንችለው እንዴት ነው?
3 በተቻላችሁ መጠን ብዙ ሰዎችን ጋብዙ፦ ግባችን በተቻለን መጠን ብዙ ሰዎችን መጋበዝ ነው። በመሆኑም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችሁን፣ ተመላልሶ መጠይቅ የምታደርጉላቸውን ሰዎች፣ ዘመዶቻችሁን፣ የሥራ ባልደረቦቻችሁን፣ አብረዋችሁ የሚማሩትን፣ ጎረቤቶቻችሁንና ሌሎች የምታውቋቸውን ሰዎች መጋበዝ እንዳለባችሁ አትርሱ። የጉባኤያችሁ ሽማግሌዎች የአገልግሎት ክልላችሁን መሸፈን ስለምትችሉበት መንገድ መመሪያ ይሰጧችኋል። ሰዎች በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኙ ለመጋበዝ የምናደርገው ዓመታዊ ዘመቻ ውጤት እያስገኘ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ባለፈው ዓመት አንዲት ሴት በመታሰቢያው በዓል ላይ ተገኝታ ነበር፤ ወደ አዳራሹ ስትገባ አስተናጋጁ ከጋበዛት ሰው ጋር ሊያገናኛት እንደሚችል ነገራት። ሆኖም ሴትየዋ፣ በዚያ ዕለት አንድ ሰው ቤቷ መጥቶ የመጋበዣ ወረቀቱን እንደሰጣትና በአዳራሹ ውስጥ ካሉት መካከል ማንንም እንደማታውቅ ነገረችው።
4. በዘመቻው ላይ በቅንዓት የምንካፈለው ለምንድን ነው?
4 በመታሰቢያ በዓል ላይ ከተገኙት ሰዎች መካከል አንዱ ምናልባት እናንተ የመጋበዣ ወረቀት የሰጣችሁት ሰው ሊሆን ይችላል። ሆኖም አንድ ሰው የመጋበዣ ወረቀቱን ተቀበለም አልተቀበለ የምታደርጉት ትጋት የተሞላበት ጥረት ምሥክርነት መስጠቱ አይቀርም። የምታሰራጯቸው የመጋበዣ ወረቀቶች ኢየሱስ በአሁኑ ወቅት ኃያል ንጉሥ እንደሆነ ያውጃሉ። በዚህ ሥራ በቅንዓት የምታደርጉት ተሳትፎ ሰዎች ሁሉ ይኸውም በክልላችሁ የሚገኙ ሰዎችና ሌሎች አስፋፊዎች ከሁሉ በላይ ደግሞ ይሖዋ ለቤዛው ዝግጅት ያላችሁን ጥልቅ አድናቆት እንዲመለከቱ ያስችላል።—ቆላ. 3:15