የአቀራረብ ናሙናዎች
በወሩ የመጀመሪያ ቅዳሜ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር የሚረዳ አቀራረብ
“ጎረቤቶቻችን መጽሐፍ ቅዱሳቸውን እንዲያነብቡ እያበረታታን ነው። ብዙ ሰዎች ግን መጽሐፍ ቅዱስን መረዳት ከባድ እንደሆነ ይሰማቸዋል። እርስዎስ እንደዚህ ይሰማዎታል? [ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው።] እስቲ ይህን ርዕስ ይመልከቱ።” የሚያዝያ 1ን መጠበቂያ ግንብ ስጠውና በመጨረሻ ገጽ ላይ ያለውን ዓምድ አሳየው። ከዚያም በመጀመሪያው ጥያቄ ሥር ባለው ሐሳብ ላይ እና በዚያ ውስጥ ከተጠቀሱት ጥቅሶች መካከል ቢያንስ በአንዱ ላይ ተወያዩ። መጽሔቶቹን ካበረከትክለት በኋላ በሚቀጥለው ጥያቄ ላይ ለመወያየት ቀጠሮ ያዝ።
መጠበቂያ ግንብ ሚያዝያ 1
“ሁሉም ሰው በሕይወቱ ውስጥ የተለያዩ ችግሮች ያጋጥሙታል። በዚህ ምክንያት ሰዎች ሕይወት ትርጉም ያለው መሆኑን ይጠራጠራሉ። በዛሬው ጊዜ ሰዎች ደስተኛ እንዳይሆኑ ከሁሉም በላይ እንቅፋት የሆነባቸው ነገር ምንድን ነው ይላሉ? [ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው።] በአሁኑ ጊዜ የሚያጋጥሙንን ችግሮች በሙሉ አምላክ በቅርቡ እንደሚያስወግድ የሰጠውን ተስፋ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። [ራእይ 21:4ን አንብብ።] ይህ መጽሔት ወደፊት ስለምናገኛቸው ተስፋዎች እንዲሁም በአሁኑ ጊዜም እንኳ ትርጉም ያለው ሕይወት መምራት ስለምንችልበት መንገድ ያብራራል።”
ንቁ! ሚያዝያ
“በትዳር ጓደኛ ላይ የሚሰነዘር ጥቃት በዓለም ዙሪያ የተለመደ ነገር እየሆነ መጥቷል። አንድ ሰው ይህን ድርጊት እንዲፈጽም ከሚያነሳሱት ነገሮች መካከል የአካባቢው ባሕል፣ ያደገበት ቤተሰብ እና ዓመፅ የሚታይበት መዝናኛ እንደሚገኙበት አንዳንድ ሰዎች ይናገራሉ። እርስዎስ ዋነኛው ምክንያት ምንድን ነው ይላሉ? [ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው።] መጽሐፍ ቅዱስ፣ አንድ ባልና ሚስት ምን ዓይነት ግንኙነት ሊኖራቸው እንደሚገባ ይነግረናል። [ኤፌሶን 5:33ን አንብብ።] ይህ መጽሔት፣ አንዳንድ ባለትዳሮች የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮችን ተግባራዊ በማድረግ ትዳራቸውን መታደግ የቻሉት እንዴት እንደሆነ ይገልጻል።”