በመጀመሪያው ቀን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዴት እንደሚካሄድ ለሰዎች አሳይታችሁ ታውቃላችሁ?
ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠኑ ግብዣ ስታቀርቡ የቤቱ ባለቤት ፍላጎት እንደሌለው ወይም በቤተ ክርስቲያኑ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚማር ሊነግራችሁ ይችላል። እኛ መጽሐፍ ቅዱስን የምናስጠናበት መንገድ ከሌሎች ሃይማኖቶች የተለየ እንደሆነ ላያውቁ ስለሚችሉ ከእኛ ጋር ማጥናታቸው ምን ያህል መንፈሳዊ እውቀት እንደሚያስገኝላቸውና አስደሳች እንደሆነ ላይገባቸው ይችላል። ስለሆነም በመጀመሪያው ቀን አንድን ሰው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠና መጋበዝ ብቻ ሳይሆን ጥቂት ደቂቃ ወስዳችሁ እንዴት እንደሚጠና ማሳየትም ትችላላችሁ። በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ ጥሩ አድርጋችሁ ምግብ መሥራት እንደምትችሉና ምግቡን በሌላ ጊዜ ይዛችሁለት እንደምትመጡ ከመናገር ይልቅ ወዲያውኑ ምግቡን እንዲቀምስ አድርጉ። የጥር 2006 የመንግሥት አገልግሎታችን ገጽ 6 ላይ ይህንን በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ እንዴት ማድረግ እንደምትችሉ የሚናገር ሐሳብ ይዟል፦
“በዚህ ጥቅስ ላይ የሚገኘው ትንቢት ይፈጸማል ብለው አስበው ያውቃሉ? [ኢሳይያስ 33:24ን አንብብ፤ ከዚያም ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው።] ይህን ጉዳይ በተመለከተ አንድ ግሩም ሐሳብ ላሳይዎት።” ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ ለቤቱ ባለቤት ስጡትና በገጽ 36 አንቀጽ 22 ላይ ያለውን ሐሳብ አሳዩት። በመጽሐፉ ግርጌ ያለውን ጥያቄ ካነበባችሁ በኋላ የቤቱ ባለቤት አንቀጹን ስታነቡ የጥያቄውን መልስ እንዲፈልግ ንገሩት። ከዚያም ጥያቄውን እንደገና ከጠየቃችሁት በኋላ የቤቱ ባለቤት የሚሰጠውን መልስ አዳምጡ። ሌሎቹን ጥቅሶች አንድ ላይ አንብቧቸው። በሚቀጥለው ጊዜ መልስ የሚያገኝ አንድ ጥያቄ አንሱና የምትመለሱበትን ቀንና ሰዓት በተመለከተ ቁርጥ ያለ ቀጠሮ ያዙ። እንዲህ አደረጋችሁ ማለት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመራችሁ ማለት ነው!