-
ማርቆስ 2:3-12አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
-
-
3 ሰዎችም አንድ ሽባ በአራት ሰዎች አሸክመው ወደ እሱ አመጡ።+ 4 ሆኖም ከሕዝቡ ብዛት የተነሳ ሽባውን ወደ ኢየሱስ ማቅረብ ስላልቻሉ ከኢየሱስ በላይ ያለውን ጣሪያ ከነደሉ በኋላ ሽባው የተኛበትን ቃሬዛ ወደ ታች አወረዱት። 5 ኢየሱስም እምነታቸውን በማየት+ ሽባውን “ልጄ ሆይ፣ ኃጢአትህ ይቅር ተብሎልሃል” አለው።+ 6 በዚያ ተቀምጠው የነበሩ አንዳንድ ጸሐፍት ግን እንዲህ ሲሉ በልባቸው አሰቡ፦+ 7 “ይህ ሰው እንዲህ ብሎ የሚናገረው ለምንድን ነው? አምላክን እየተዳፈረ እኮ ነው። ከአንዱ ከአምላክ በቀር ኃጢአትን ማን ይቅር ሊል ይችላል?”+ 8 ሆኖም ኢየሱስ በልባቸው ይህን እያሰቡ እንዳሉ ወዲያው በመንፈሱ ተረድቶ “በልባችሁ እንዲህ እያላችሁ የምታስቡት ለምንድን ነው?+ 9 ሽባውን ‘ኃጢአትህ ይቅር ተብሏል’ ከማለትና ‘ተነሳና ቃሬዛህን ተሸክመህ ሂድ’ ከማለት የቱ ይቀላል? 10 ይሁንና የሰው ልጅ+ በምድር ላይ ኃጢአትን ይቅር የማለት ሥልጣን እንዳለው ታውቁ ዘንድ . . .”+ ካለ በኋላ ሽባውን እንዲህ አለው፦ 11 “ተነስ፣ ቃሬዛህን ተሸክመህ ወደ ቤትህ ሂድ።” 12 በዚህ ጊዜ ሽባው ብድግ ብሎ ወዲያው ቃሬዛውን በማንሳት በሁሉ ፊት እየተራመደ ወጣ። ይህን ሲያዩ ሁሉም እጅግ ተደነቁ፤ ደግሞም “እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ አይተን አናውቅም”+ በማለት አምላክን አከበሩ።
-
-
ሉቃስ 5:18-26አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
-
-
18 በዚያን ጊዜም አንድ ሽባ ሰው በቃሬዛ የተሸከሙ ሰዎች መጡ፤ ሽባውን ወደ ውስጥ ለማስገባትና ኢየሱስ ፊት ለማስቀመጥ ጥረት አደረጉ።+ 19 ከሕዝቡም ብዛት የተነሳ መግቢያ ስላላገኙ ጣራው ላይ ወጥተው ጡቡን ካነሱ በኋላ የተኛበትን ቃሬዛ አሾልከው፣ ሽባውን ኢየሱስ ፊት በነበሩት ሰዎች መካከል አወረዱት። 20 ኢየሱስም እምነታቸውን በማየት “አንተ ሰው፣ ኃጢአትህ ይቅር ተብሎልሃል” አለው።+ 21 በዚህ ጊዜ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን “አምላክን የሚዳፈረው ይሄ ማን ነው? ከአምላክ በቀር ኃጢአትን ማን ይቅር ሊል ይችላል?” ይባባሉ ጀመር።+ 22 ኢየሱስ ግን ሐሳባቸውን ተረድቶ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “በልባችሁ የምታስቡት ምንድን ነው? 23 ‘ኃጢአትህ ይቅር ተብሏል’ ከማለትና ‘ተነስተህ ሂድ’ ከማለት የቱ ይቀላል? 24 ይሁንና የሰው ልጅ በምድር ላይ ኃጢአትን ይቅር የማለት ሥልጣን እንዳለው ታውቁ ዘንድ . . .” አላቸውና ሽባውን “ተነስ፣ ቃሬዛህን ተሸከምና ወደ ቤትህ ሂድ” አለው።+ 25 በዚህ ጊዜ ሰውየው በፊታቸው ተነስቶ ተኝቶበት የነበረውን ቃሬዛ ተሸከመና አምላክን እያመሰገነ ወደ ቤቱ ሄደ። 26 ይህን ሲያዩ ሁሉም በአድናቆት ተውጠው አምላክን ማመስገን ጀመሩ፤ ታላቅ ፍርሃትም አድሮባቸው “ዛሬ የሚያስደንቅ ነገር አየን!” አሉ።
-