በመጽሔቶች አማካኝነት ሌሎች እንዲጠቀሙ አድርግ
1 በቅርብ የወጡት የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔቶች ሲደርሱን እንዴት ደስ ይለናል? ከሚቀርብልን ትምህርት ጥቅም ለማግኘት እንችል ዘንድ መጽሔቶቹ እንደደረሱን ለማንበብ ያለንን አጋጣሚ በአድናቆት እንመለከታለን። መጽሔቶቹን ስናነብ እኛን በግላችን በሚጠቅመን ሐሳብ ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ መጽሔቱን ለሌሎች በምናበረክትበት ጊዜ ልንጠቀምባቸው በምንችላቸው ሐሳቦችም ላይ ትኩረት ብንሰጥ ጥሩ ነው። በጉባኤያችን ክልል ውስጥ ያሉትን ሰዎች ሊማርኩ በሚችሉ ክፍሎች ላይ ምልክት ልናደርግ ወይም በአካባቢያችን ላሉ ሰዎች የመነጋገሪያ ነጥቦቹንና ርዕሰ ትምህርቱን እንዴት አድርገን ለማስተዋወቅ እንደምንችል ለማስታወስ በግል ቅጂያችን ግርጌ ማስታወሻ ለመጻፍ እንፈልግ ይሆናል።
2 መጽሔቶቻችን ዘላቂ ጥቅም አላቸው። ምንም እንኳን በመጀመሪያ ትኩረት ሰጥተን የምናበረክተው በቅርብ የወጡትን መጽሔቶች ቢሆንም በቆዩት ጽሑፎች ውስጥ ያለው ሐሳብ ጊዜው ስለማያልፍበት ልንጥላቸው አይገባንም። በምትመሰክርበት ጊዜ ለማበርከት እንድትችል የበፊቶቹን እትሞች በአገልግሎት ቦርሳህ ውስጥ አስቀምጥ። በተለይ የቤቱ ባለቤት የሚያስፈልገው ነገር ምን እንደሆነ ካወቅህ እነዚህ መጽሔቶች ሊጠቅሙህ ይችሉ ይሆናል።