ለዘላለም መኖር እና የአምልኮ አንድነት የተባሉትን መጽሐፎች አስጠና
1 ፍላጎት ላላቸው ሰዎች የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር በትራክቶች፣ በብሮሹሮች፣ በመጽሔቶችና በመጽሐፎች መጠቀም ይቻላል። በስፋት በመሰራጨቱና ማራኪ በመሆኑ ምክንያት እስከ ዛሬ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው የተባለውን መጽሐፍ ጥናት ለማስጀመር እየተጠቀምንበት ነው። በእውነቱ ሁሉም ሰው መጽሐፉን እንዲያነበውና እንዲያጠናው ማበረታቻ ሊሰጠው ይገባል።
2 ይሁን እንጂ አዲሶች ሊያጠኗቸው የሚገቧቸው ሁለት መጽሐፎች አሉ። እነዚህ መጽሐፎች ዋና ዋናዎቹን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረተ ትምህርቶች እና የክርስትናን የአኗኗር ደረጃዎች እንዲያውቁ ይረዷቸዋል። እነርሱም:- በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ እና እውነተኛው አንድ አምላክ ያስገኘው የአምልኮ አንድነት የተባሉት መጽሐፎች ናቸው። በሌሎች ጽሑፎች አማካኝነት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚመሩ አስፋፊዎች በተቻለ መጠን ቶሎ ብለው የሚያስጠኑበትን ጽሑፍ ከነዚህ መጽሐፎች በአንዱ ቢቀይሩት ጥሩ ነው። ጥናቱን የምትመራው ታላቁ ሰው በተባለው መጽሐፍ ከነበረ ተማሪው መጽሐፉን በግሉ ማንበቡን እንዲቀጥል አበረታታው። ተማሪው ሁለተኛውን መጽሐፍ አጥንቶ ሳይጨርስ ሊጠመቅ ቢችልም ለዘላለም መኖር እና የአምልኮ አንድነት የተባሉትን መጻሕፍት አጥንቶ እስኪጨርስ ድረስ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ መቀጠል አለበት። ይህም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪው ይበልጥ ጥልቀት ያለው አስተሳሰብና ጽኑ መንፈሳዊ አቋም እንዲኖረው ያስችለዋል።