ድንገት ሊያጋጥም ለሚችል የጤና ችግር ተዘጋጅተሃል?
ማናችንም ብንሆን ሕክምና የሚያሻው ድንገተኛ የጤና ችግር ሊያጋጥመን ይችላል። (ያዕ. 4:14) በመሆኑም አስተዋይ የሆነ ሰው አስቀድሞ ዝግጅት ያደርጋል። (ምሳሌ 22:3) ታዲያ ምን ዓይነት ሕክምና እንደምትፈልግ አስቀድመህ ወስነሃል? ውሳኔህንስ በጽሑፍ አስፍረሃል? በዚህ ረገድ አንተን ለመርዳት ትራንስፊውዥን ኦልተርኔቲቭስ የተባለ ጥናታዊ ፊልሞችን የያዘ ዲቪዲ ተዘጋጅቷል፤ በዚህ ዲቪዲ ላይ ከሚገኙት ፊልሞች መካከል ሁለተኛው በደም ምትክ የሚሰጥ ሕክምና—የሕሙማንን መብትና ፍላጎት ማክበር (ትራንስፊውዥን-ኦልተርኔቲቭስ ሄልዝ ኬር—ሚቲንግ ፔሸንት ኒድስ ኤንድ ራይትስ) የሚል ነው። ይህን ቪዲዮ ስትመለከት ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ሞክር። ቪዲዮው ቀዶ ሕክምና ሲደረግ የሚያሳዩ ክፍሎች ስላሉት ወላጆች ከትናንሽ ልጆቻቸው ጋር ፊልሙን ሊያዩት ይገባ እንደሆነና እንዳልሆነ አመዛዝነው መወሰን ይኖርባቸዋል።
(1) በሕክምናው መስክ የተሰማሩ አንዳንድ ባለሙያዎች ደም በመስጠት የሚደረግ ሕክምናን እንደገና ማጤን የጀመሩት ለምንድን ነው? (2) ያለ ደም ከተከናወኑ ከባድ ቀዶ ሕክምናዎች ውስጥ ሦስት ምሳሌዎች ጥቀስ። (3) በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሺህ የሚቆጠሩ ሐኪሞችና የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች ሕሙማንን ያለ ደም ለማከም ፈቃደኛ የሆኑት ለምንድን ነው? (4) በቅርቡ በሆስፒታሎች ውስጥ በተካሄዱ ጥናቶች መሠረት ደም መውሰድን በተመለከተ ምን ነገር ሊታወቅ ችሏል? (5) ደም ከመውሰድ ጋር በተያያዘ ምን ዓይነት የጤና እክሎች ሊያጋጥሙ ይችላሉ? (6) በርካታ ባለሙያዎች በደም ምትክ የሚሰጡ የሕክምና አማራጮች የሚያስገኟቸውን ጥቅሞች በተመለከተ ምን መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል? (7) ደም ማነስ ከምን ይመጣል? ደም ማነስን ለማስተካከልስ ምን ማድረግ ይቻላል? (8) የአንድ ሕመምተኛ ሰውነት ተጨማሪ ቀይ የደም ሕዋስ እንዲያመርት ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? (9) ሐኪሞች በቀዶ ሕክምና ወቅት የሚፈስሰውን ደም ለመቀነስ በየትኞቹ መንገዶች ይጠቀማሉ? (10) በደም ምትክ የሚሰጡ ሕክምናዎች ለትናንሽ ልጆች ወይም ለሕይወት የሚያሰጋ ድንገተኛ አደጋ ላጋጠማቸው ሰዎች ውጤታማ ሊሆኑ ይችላሉ? (11) ከጥሩ ሕክምና ተቀዳሚ የሥነ ምግባር መመሪያዎች አንዱ ምንድን ነው?
በዚህ ቪዲዮ ላይ የቀረቡትን የሕክምና አማራጮች መቀበል ወይም አለመቀበል ለሕሊና የተተወ ጉዳይ ስለሆነ የምትፈልገውን የሕክምና ዓይነት ለመወሰን አደጋ እስኪደርስ ድረስ አትጠብቅ። ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’ በተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 7 እና በምዕራፉ ውስጥ በተጠቀሱት ተጨማሪ ጽሑፎች እንዲሁም በኅዳር 2006 የመንግሥት አገልግሎታችን አባሪ ላይ የሚገኙትን ሐሳቦች መመርመርህ በእውቀት ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ለማድረግ ያስችልሃል። ከዚያም የተጠመቅህ ክርስቲያን ከሆንክ ምርጫህን በሕክምና ሰነድ ላይ በትክክል አስፍር፤ እንዲሁም ይህ ሰነድ ምንጊዜም አይለይህ።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ምን ዓይነት ሕክምና እንደምትፈልግ አስቀድመህ ወስነሃል? ውሳኔህንስ በጽሑፍ አስፍረሃል?