ሩት
1 መሳፍንት+ ፍትሕን ያስፈጽሙ* በነበረበት ዘመን በምድሪቱ ላይ ረሃብ ተከሰተ፤ አንድ ሰው ከሚስቱና ከሁለት ወንዶች ልጆቹ ጋር የባዕድ አገር ሰው ሆኖ ለመኖር በይሁዳ ከምትገኘው ከቤተልሔም+ ተነስቶ ወደ ሞዓብ+ ምድር አቀና። 2 የሰውየው ስም ኤሊሜሌክ፣* የሚስቱ ስም ናኦሚ፣* የሁለቱ ወንዶች ልጆቹ ስም ደግሞ ማህሎን* እና ኪሊዮን* ነበር። እነሱም በይሁዳ በምትገኘው በቤተልሔም የሚኖሩ ኤፍራታውያን ነበሩ። ወደ ሞዓብም መጥተው በዚያ መኖር ጀመሩ።
3 ከጊዜ በኋላም የናኦሚ ባል ኤሊሜሌክ ሞተ፤ ስለሆነም ናኦሚ ከሁለት ልጆቿ ጋር ቀረች። 4 በኋላም ልጆቿ ሞዓባውያን ሴቶችን አገቡ፤ የአንደኛዋ ስም ዖርፋ፣ የሌላኛዋ ደግሞ ሩት+ ነበር። በዚያም ለአሥር ዓመት ያህል ኖሩ። 5 ከዚያም ሁለቱ ወንዶች ልጆቿ ማህሎንና ኪሊዮን ሞቱ፤ ናኦሚም ሁለት ልጆቿንና ባሏን አጥታ ብቻዋን ቀረች። 6 እሷም በሞዓብ ምድር ሳለች ይሖዋ ለሕዝቡ እህል በመስጠት ፊቱን ወደ እነሱ እንደመለሰ ስለሰማች ከምራቶቿ ጋር ወደ አገሯ ለመመለስ ከሞዓብ ተነሳች።
7 ከሁለቱ ምራቶቿም ጋር ትኖርበት የነበረውን ቦታ ትታ ሄደች። ወደ ይሁዳ ምድር ለመመለስ ወደዚያ የሚወስደውን መንገድ ይዘው እየሄዱ ሳሉም 8 ናኦሚ ሁለቱን ምራቶቿን እንዲህ አለቻቸው፦ “ሂዱ፣ ሁለታችሁም ወደ እናቶቻችሁ ቤት ተመለሱ። ለሞቱት ባሎቻችሁና ለእኔ ታማኝ ፍቅር+ እንዳሳያችሁ ሁሉ ይሖዋም ለእናንተ ታማኝ ፍቅር ያሳያችሁ። 9 ይሖዋ በየባላችሁ ቤት+ ያለስጋት እንድትኖሩ ያድርጋችሁ።”* ከዚያም ሳመቻቸው፤ እነሱም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ማልቀስ ጀመሩ። 10 እንዲህም አሏት፦ “በፍጹም! ከአንቺ ጋር ወደ ወገኖችሽ እንሄዳለን።” 11 ናኦሚ ግን እንዲህ አለቻቸው፦ “ልጆቼ፣ ተመለሱ። ለምን ከእኔ ጋር ትሄዳላችሁ? ለእናንተ ባሎች ሊሆኑ የሚችሉ ወንዶች ልጆች አሁንም ልወልድ የምችል ይመስላችኋል?+ 12 ልጆቼ፣ ተመለሱ። እኔ እንደሆነ በጣም ስላረጀሁ ከእንግዲህ ባል ላገባ አልችልም፤ ስለዚህ ሂዱ። ዛሬ ማታ ባል የማግኘትና ልጆች የመውለድ ተስፋ ቢኖረኝ እንኳ 13 እስኪያድጉ ድረስ ትጠብቃላችሁ? እነሱን በመጠበቅስ ባል ሳታገቡ ትቆያላችሁ? ልጆቼ፣ ይሄማ አይሆንም፤ የይሖዋ እጅ በእኔ ላይ ስለተነሳ የእናንተን ሁኔታ ሳስብ ሕይወቴ መራራ ይሆንብኛል።”+
14 እነሱም እንደገና ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ፤ ከዚያም ዖርፋ አማቷን ስማ ተሰናበተቻት። ሩት ግን ከእሷ ላለመለየት የሙጥኝ አለች። 15 ናኦሚም “ተመልከች፣ መበለት የሆነችው የባልሽ ወንድም ሚስት ወደ ወገኖቿና ወደ አማልክቷ ተመልሳለች። አብረሻት ተመለሽ” አለቻት።
16 ሩት ግን እንዲህ አለቻት፦ “ከአንቺ እንድለይና ትቼሽ እንድመለስ አትማጸኚኝ፤ እኔ እንደሆነ ወደምትሄጂበት እሄዳለሁ፤ በምታድሪበት አድራለሁ። ሕዝብሽ ሕዝቤ፣ አምላክሽም አምላኬ ይሆናል።+ 17 በምትሞቺበት እሞታለሁ፤ በዚያም እቀበራለሁ። ከሞት በቀር ከአንቺ የሚለየኝ ቢኖር ይሖዋ አንዳች ነገር ያምጣብኝ፤ ከዚያም የከፋ ያድርግብኝ።”
18 ናኦሚ፣ ሩት ከእሷ ጋር ለመሄድ እንደቆረጠች ስታውቅ መወትወቷን አቆመች። 19 ከዚያም ወደ ቤተልሔም ጉዟቸውን ቀጠሉ።+ ቤተልሔም እንደደረሱም በእነሱ ምክንያት መላ ከተማዋ ታመሰች፤ ሴቶቹም “ይህች ናኦሚ አይደለችም እንዴ?” ይሉ ነበር። 20 እሷም እንዲህ ትላቸው ነበር፦ “ናኦሚ* ብላችሁ አትጥሩኝ። ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ሕይወቴን መራራ አድርጎታልና ማራ* ብላችሁ ጥሩኝ።+ 21 ከዚህ ስወጣ ሙሉ ነበርኩ፤ ይሖዋ ግን ባዶ እጄን እንድመለስ አደረገኝ። ይሖዋ ተቃውሞኝና ሁሉን የሚችለው አምላክ መከራ አምጥቶብኝ ሳለ ለምን ናኦሚ ብላችሁ ትጠሩኛላችሁ?”+
22 እንግዲህ ናኦሚ ምራቷ ከሆነችው ከሞዓባዊቷ ሩት ጋር ከሞዓብ ምድር+ የተመለሰችው በዚህ ሁኔታ ነበር። ቤተልሔም የደረሱትም የገብስ አዝመራ መሰብሰብ በጀመረበት ወቅት ነበር።+
2 ናኦሚ በባሏ በኩል ሀብታም የሆነ የቅርብ ዘመድ ነበራት፤ ይህ ሰው ቦዔዝ+ የሚባል ሲሆን የኤሊሜሌክ ቤተሰብ ነበር።
2 ሞዓባዊቷም ሩት ናኦሚን “እባክሽ ወደ እርሻ ቦታዎቹ ልሂድና ሞገስ የሚያሳየኝ ሰው ካገኘሁ እህል ልቃርም”+ አለቻት። ናኦሚም “ልጄ ሆይ፣ ሂጂ” አለቻት። 3 ሩትም ሄደች፤ በማሳውም ውስጥ ከአጫጆቹ ኋላ እየተከተለች መቃረም ጀመረች። እንደ አጋጣሚ ሆኖ የገባችው የኤሊሜሌክ ቤተሰብ+ ወደሆነው ወደ ቦዔዝ+ እርሻ ነበር። 4 በዚህ ጊዜ ቦዔዝ ከቤተልሔም መጣ፤ አጫጆቹንም “ይሖዋ ከእናንተ ጋር ይሁን” አላቸው። እነሱም “ይሖዋ ይባርክህ” ብለው መለሱለት።
5 ከዚያም ቦዔዝ የአጫጆቹ አለቃ የሆነውን ወጣት “ይህች ወጣት የማን ነች?” ሲል ጠየቀው። 6 የአጫጆቹ አለቃ የሆነው ወጣትም እንዲህ በማለት መለሰ፦ “ወጣቷ፣ ናኦሚ ከሞዓብ ምድር+ ስትመለስ አብራት የመጣች ሞዓባዊት+ ነች። 7 እሷም ‘እባክህ፣ ከአጫጆቹ ኋላ እየተከተልኩ የወደቁትን ዛላዎች* መቃረም+ እችላለሁ?’ አለችኝ። ይኸው ወደዚህ ከመጣችበት ከጠዋት አንስቶ ወደ ዳሱ ገብታ ጥቂት አረፍ እስካለችበት እስካሁን ድረስ አንዴም እንኳ ቁጭ አላለችም።”
8 ከዚያም ቦዔዝ ሩትን እንዲህ አላት፦ “ልጄ ሆይ፣ ስሚኝ። ለመቃረም ወደ ሌላ እርሻ አትሂጂ፤ የትም አትሂጂ፤ ከወጣት ሴት ሠራተኞቼም አትራቂ።+ 9 የሚያጭዱበትን ማሳ እያየሽ አብረሻቸው ሂጂ። ወጣቶቹም ወንዶች እንዳይነኩሽ* አዝዣቸዋለሁ። ውኃ ሲጠማሽ ወደ እንስራዎቹ ሄደሽ ወጣቶቹ ቀድተው ካስቀመጡት ጠጪ።”
10 እሷም መሬት ላይ በግንባሯ ተደፍታ በመስገድ “እኔ የባዕድ አገር ሰው ሆኜ+ ሳለሁ በፊትህ ሞገስ ላገኝ የበቃሁትና ትኩረት ልትሰጠኝ የቻልከው እንዴት ነው?” አለችው። 11 ቦዔዝም እንዲህ ሲል መለሰላት፦ “ባልሽ ከሞተ በኋላ ለአማትሽ ያደረግሽላትን ሁሉ እንዲሁም አባትሽን፣ እናትሽንና ዘመዶችሽ የሚኖሩበትን አገር ትተሽ ቀድሞ ወደማታውቂው ሕዝብ እንዴት እንደመጣሽ በሚገባ ሰምቻለሁ።+ 12 ላደረግሽው ሁሉ ይሖዋ ብድራትሽን ይመልስልሽ፤+ በክንፎቹ ሥር ለመጠለል+ ብለሽ ወደ እሱ የመጣሽበት የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ሙሉ ዋጋሽን* ይክፈልሽ።” 13 እሷም መልሳ “ጌታዬ ሆይ፣ እኔ ከሴት አገልጋዮችህ አንዷ ባልሆንም እንኳ ስላጽናናኸኝና እኔን አገልጋይህን በሚያበረታታ መንገድ ስላነጋገርከኝ* ምንጊዜም በፊትህ ሞገስ ላግኝ” አለችው።
14 የምግብ ሰዓትም ሲደርስ ቦዔዝ “ወደዚህ ቀረብ በይ፤ ዳቦ ወስደሽ ብዪ፤ የቆረስሽውንም ሆምጣጤ ውስጥ አጥቅሺ” አላት። በመሆኑም ከአጫጆቹ ጋር ተቀመጠች። እሱም ቆሎ ዘግኖ ሰጣት፤ እሷም እስክትጠግብ ድረስ በላች፤ የተወሰነም ተረፋት። 15 ለመቃረም+ በተነሳች ጊዜም ቦዔዝ ወጣቶቹን ወንዶች እንዲህ ሲል አዘዛቸው፦ “ከታጨዱት ዛላዎች* ላይ እንኳ ሳይቀር ትቃርም፤ ምንም እንዳትበድሏት።+ 16 ከታሰረው ነዶ ላይም የተወሰኑ ዛላዎችን እየመዘዛችሁ ጣሉላትና ትቃርም፤ ማንም እንዳይከለክላት።”
17 እሷም እስከ ማታ ድረስ ስትቃርም ቆየች።+ የቃረመችውንም ገብስ በወቃችው ጊዜ አንድ የኢፍ* መስፈሪያ ያህል ሆነ። 18 እህሉንም ይዛ ወደ ከተማ ሄደች፤ አማቷም ምን ያህል እንደቃረመች አየች። በተጨማሪም ሩት በልታ ከጠገበች በኋላ አስተርፋ ያመጣችውን ምግብ+ አውጥታ ለአማቷ ሰጠቻት።
19 በዚህ ጊዜ አማቷ “ዛሬ የቃረምሽው የት ነው? የትስ ስትሠሪ ዋልሽ? ትኩረት የሰጠሽ ሰው የተባረከ ይሁን” አለቻት።+ እሷም “ዛሬ ስሠራ የዋልኩት ቦዔዝ በተባለ ሰው እርሻ ውስጥ ነው” በማለት ከማን ጋር ስትሠራ እንደዋለች ለአማቷ ነገረቻት። 20 ናኦሚም ምራቷን “ለሕያዋንም ሆነ ለሙታን ታማኝ ፍቅሩን ከማሳየት ወደኋላ የማይለው ይሖዋ ይባርከው” አለቻት።+ አክላም “ሰውየው ዘመዳችን ነው።+ ከሚቤዡን ሰዎች አንዱ ነው”* አለች።+ 21 ከዚያም ሞዓባዊቷ ሩት “ደግሞም ‘ወጣቶቹ ሠራተኞቼ አዝመራዬን በሙሉ ሰብስበው እስኪጨርሱ ድረስ ከእነሱ አትራቂ’ ብሎኛል” አለቻት።+ 22 ናኦሚም ምራቷን ሩትን “ልጄ ሆይ፣ ወደ ሌላ እርሻ ብትሄጂ ሊተናኮሉሽ ስለሚችሉ ከእሱ ሴት ሠራተኞች ጋር አብረሽ መሆን ይሻልሻል” አለቻት።
23 ስለዚህ ሩት የገብሱ አዝመራና+ የስንዴው አዝመራ ተሰብስቦ እስኪያልቅ ድረስ ከቦዔዝ ሴት ሠራተኞች ሳትርቅ ስትቃርም ቆየች። ከአማቷም ጋር መኖሯን ቀጠለች።+
3 ከዚያም አማቷ ናኦሚ እንዲህ አለቻት፦ “ልጄ ሆይ፣ መልካም ይሆንልሽ ዘንድ ቤት* ልፈልግልሽ አይገባም?+ 2 ቦዔዝ ዘመዳችን አይደለም?+ አብረሻቸው የነበርሽው ወጣት ሴቶች የእሱ ናቸው። ዛሬ ማታ በአውድማው ላይ ገብስ ያዘራል። 3 ስለዚህ ተነስተሽ ተጣጠቢና ሰውነትሽን ጥሩ መዓዛ ያለው ዘይት ተቀቢ፤ ከዚያም ልብስሽን ለባብሰሽ* ወደ አውድማው ውረጂ። ሰውየው በልቶና ጠጥቶ እስኪጨርስ ድረስ እዚያ መኖርሽን እንዲያውቅ ማድረግ የለብሽም። 4 ሲተኛም የሚተኛበትን ቦታ ልብ ብለሽ እዪ፤ ከዚያም ሄደሽ እግሩን ገልጠሽ ተኚ። እሱም ምን ማድረግ እንዳለብሽ ይነግርሻል።”
5 እሷም “ያልሽኝን ሁሉ አደርጋለሁ” አለቻት። 6 ስለዚህ ሩት ወደ አውድማው በመውረድ ሁሉንም ነገር ልክ አማቷ እንዳዘዘቻት አደረገች። 7 ቦዔዝም ከበላና ከጠጣ በኋላ ልቡ በደስታ ተሞላ። ከዚያም ሄዶ የተቆለለው እህል አጠገብ ተኛ። ሩትም በቀስታ መጥታ እግሩን ገልጣ ተኛች። 8 እኩለ ሌሊትም ሲሆን ቦዔዝ እየተንቀጠቀጠ ከእንቅልፉ ባነነ፤ ቀና ሲልም አንዲት ሴት እግሩ ሥር ተኝታ ተመለከተ። 9 እሱም “ለመሆኑ አንቺ ማን ነሽ?” አላት። እሷም መልሳ “እኔ አገልጋይህ ሩት ነኝ። መቤዠት+ የሚገባህ አንተ ስለሆንክ መጎናጸፊያህን በአገልጋይህ ላይ ጣል” አለችው። 10 በዚህ ጊዜ እንዲህ አላት፦ “ልጄ ሆይ፣ ይሖዋ ይባርክሽ። ሀብታምም ሆኑ ድሃ፣ ወጣት ወንዶችን ተከትለሽ ባለመሄድሽ ከበፊቱ ይልቅ+ አሁን ያሳየሽው ታማኝ ፍቅር በለጠ። 11 ስለዚህ የእኔ ልጅ፣ አትፍሪ። አንቺ ምግባረ መልካም ሴት መሆንሽን የከተማው* ሰው ሁሉ ስለሚያውቅ ያልሽውን ሁሉ አደርግልሻለሁ።+ 12 እኔ መቤዠት+ እንዳለብኝ የማይካድ ቢሆንም ከእኔ ይልቅ የቅርብ ዘመድ የሆነ መቤዠት የሚችል ሰው አለ።+ 13 ዛሬ እዚሁ እደሪ፤ ሲነጋም ሰውዬው የሚቤዥሽ ከሆነ፣ መልካም! እሱ ይቤዥሽ።+ ሊቤዥሽ የማይፈልግ ከሆነ ግን ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ እኔው ራሴ እቤዥሻለሁ። እስከ ማለዳ ድረስ ግን እዚሁ ተኚ።”
14 በመሆኑም እስኪነጋ ድረስ እግሩ ሥር ተኛች፤ ከዚያም ጎህ ቀዶ ሰውን በውል መለየት የሚያስችል ብርሃን ከመውጣቱ በፊት ተነሳች። እሱም “አንዲት ሴት ወደ አውድማው መጥታ እንደነበር ማንም አይወቅ” አለ። 15 በተጨማሪም “የለበስሽውን ኩታ ዘርግተሽ ያዢው” አላት። ስትዘረጋለትም ስድስት መስፈሪያ* ገብስ ሰፈረላትና አሸከማት፤ በኋላም ወደ ከተማ ሄደ።
16 እሷም ወደ አማቷ ሄደች፤ አማቷም “ልጄ ሆይ፣ እንዴት ሆነልሽ?”* አለቻት። ሩትም ሰውየው ያደረገላትን ሁሉ አንድ በአንድ ነገረቻት። 17 እንዲሁም “‘ወደ አማትሽ ባዶ እጅሽን አትሂጂ’ ብሎ ይህን ስድስት መስፈሪያ ገብስ ሰጠኝ” አለቻት። 18 በዚህ ጊዜ ናኦሚ እንዲህ አለቻት፦ “ልጄ ሆይ፣ ከዚህ በኋላ ቁርጡ እስኪታወቅ ድረስ ዝም ብለሽ ተቀመጪ፤ ምክንያቱም ሰውየው ዛሬውኑ ለጉዳዩ እልባት ሳያበጅ ዝም ብሎ አይቀመጥም።”
4 ከዚያም ቦዔዝ ወደ ከተማዋ በር+ ሄዶ በዚያ ተቀመጠ። በዚህ ጊዜ ቦዔዝ ቀደም ሲል ጠቅሶት የነበረው የሚቤዠው ሰው+ በዚያ ሲያልፍ ተመለከተ። ቦዔዝም “እገሌ፣ አንዴ ወደዚህ ና፤ እዚህ ተቀመጥ” አለው። ሰውየውም መጥቶ ተቀመጠ። 2 ከዚያም ቦዔዝ ከከተማዋ ሽማግሌዎች+ መካከል አሥር ሰዎች አምጥቶ “እዚህ ተቀመጡ” አላቸው። እነሱም ተቀመጡ።
3 ቦዔዝም የሚቤዠውን+ ሰው እንዲህ አለው፦ “ከሞዓብ ምድር+ የተመለሰችው ናኦሚ የወንድማችንን የኤሊሜሌክን+ የእርሻ ቦታ ልትሸጠው ነው። 4 ስለዚህ ጉዳዩን ለአንተ ላሳውቅህና እንዲህ ልልህ አሰብኩ፦ ‘እዚህ በተሰበሰቡት ነዋሪዎችና በአገሬ ሽማግሌዎች ፊት ግዛው።+ ልትቤዠው የምትፈልግ ከሆነ ተቤዠው። ልትቤዠው የማትፈልግ ከሆነ ግን ንገረኝና ልወቀው፤ ምክንያቱም በቅድሚያ የመቤዠት መብት ያለህ አንተ ነህ፤ እኔ ደግሞ ከአንተ ቀጥሎ ነኝ።’” ሰውየውም “ልቤዠው ፈቃደኛ ነኝ” አለ።+ 5 ከዚያም ቦዔዝ “መሬቱን ከናኦሚ በምትገዛበት ቀን ውርሱ በሟቹ ስም እንዲጠራ ለማድረግ የሟቹ ሚስት ከሆነችው ከሞዓባዊቷ ሩት ላይም መግዛት እንዳለብህ እወቅ” አለው።+ 6 የሚቤዠውም ሰው “የገዛ ርስቴን አደጋ ላይ ልጥል ስለምችል ልቤዠው አልችልም። እኔ ልቤዠው ስለማልችል በእኔ የመቤዠት መብት ተጠቅመህ አንተ ለራስህ ተቤዠው” አለው።
7 በጥንት ዘመን በእስራኤል ውስጥ በነበረው ልማድ መሠረት ከመቤዠት መብትም ሆነ ይህን መብት ለሌላ ሰው ከማስተላለፍ ጋር በተያያዘ ማንኛውም ዓይነት ስምምነት የሚጸድቀው አንድ ሰው ጫማውን አውልቆ+ ለሌላው ወገን ሲሰጥ ነበር፤ በእስራኤል ውስጥ አንድ ውል* የሚጸናው በዚህ መንገድ ሲከናወን ነበር። 8 በመሆኑም የሚቤዠው ሰው ቦዔዝን “አንተ ለራስህ ግዛው” በማለት ጫማውን አወለቀ። 9 ከዚያም ቦዔዝ ለሽማግሌዎቹና ለሕዝቡ ሁሉ እንዲህ አለ፦ “የኤሊሜሌክ የሆነውን ሁሉ እንዲሁም የኪሊዮንና የማህሎን የሆነውን ሁሉ ከናኦሚ ለመግዛቴ ዛሬ እናንተ ምሥክሮች ናችሁ።+ 10 በተጨማሪም የሟቹ ስም ከወንድሞቹ መካከል እንዲሁም ከሚኖርባት ከተማ በር እንዳይጠፋ የሟቹን ስም ዳግም በርስቱ ለማስጠራት+ የማህሎን ሚስት የሆነችውን ሞዓባዊቷን ሩትን ሚስት አድርጌ ወስጃታለሁ። ለዚህም እናንተ ዛሬ ምሥክሮች ናችሁ።”+
11 በዚህ ጊዜ በከተማዋ በር ላይ የነበሩት ሰዎች ሁሉና ሽማግሌዎቹ እንዲህ አሉ፦ “እኛ ምሥክሮች ነን! ይሖዋ ወደ ቤትህ የምትገባውን ሚስት የእስራኤልን ቤት እንደገነቡት እንደ ራሔልና እንደ ሊያ ያድርጋት።+ አንተም በኤፍራታ+ የበለጸግክ ሁን፤ በቤተልሔምም+ መልካም ስም አትርፍ።* 12 እንዲሁም ይሖዋ ከዚህች ወጣት ሴት በሚሰጥህ ዘር አማካኝነት ቤትህ ትዕማር ለይሁዳ እንደወለደችለት እንደ ፋሬስ+ ቤት ይሁን።”+
13 በመሆኑም ቦዔዝ ሩትን ወሰዳት፤ ሚስቱም ሆነች። ከእሷም ጋር ግንኙነት ፈጸመ፤ ይሖዋም እንድትፀንስ አደረጋት፤ ወንድ ልጅም ወለደች። 14 ሴቶቹም ናኦሚን እንዲህ አሏት፦ “ዛሬ የሚቤዥ ሰው ያላሳጣሽ ይሖዋ ይወደስ። ስሙም በእስራኤል ይታወጅ! 15 የምትወድሽና+ ከሰባት ወንዶች ልጆች የምትበልጥብሽ ምራትሽ የወለደችው ስለሆነ እሱ* ሕይወትሽን* የሚያድስ ይሆናል፤ በእርጅናሽም ዘመን ይጦርሻል።” 16 ናኦሚም ልጁን ወስዳ አቀፈችው፤ ትንከባከበውም ጀመር።* 17 ከዚያም ጎረቤቶቿ የሆኑ ሴቶች ስም አወጡለት። እንዲሁም “ለናኦሚ ወንድ ልጅ ተወለደላት” አሉ፤ ስሙንም ኢዮቤድ+ አሉት። እሱም የዳዊት አባት የሆነው የእሴይ+ አባት ነው።
18 እንግዲህ የፋሬስ+ የትውልድ ሐረግ ይህ ነው፦ ፋሬስ ኤስሮንን+ ወለደ፤ 19 ኤስሮንም ራምን ወለደ፤ ራምም አሚናዳብን ወለደ፤+ 20 አሚናዳብም+ ነአሶንን ወለደ፤ ነአሶንም ሰልሞንን ወለደ፤ 21 ሰልሞንም ቦዔዝን ወለደ፤ ቦዔዝም ኢዮቤድን ወለደ፤ 22 ኢዮቤድም እሴይን ወለደ፤+ እሴይም ዳዊትን+ ወለደ።
ቃል በቃል “ይፈርዱ።”
“አምላኬ ንጉሥ ነው” የሚል ትርጉም አለው።
“ደስታዬ” የሚል ትርጉም አለው።
“ደካማ፤ በሽተኛ” የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ ቃል የተገኘ ሳይሆን አይቀርም።
“የሚወድቅ፤ ያበቃለት” የሚል ትርጉም አለው።
ቃል በቃል “ማረፊያ ስፍራ ይስጣችሁ።”
ይህ ስም “ደስታዬ” የሚል ትርጉም አለው።
“መራራ” የሚል ትርጉም አለው።
“ነዶዎች” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “እንዳይተናኮሉሽ።”
ወይም “ሙሉ ወሮታሽን።”
ቃል በቃል “ለእኔ ለአገልጋይህ ልብ ስለተናገርክ።”
“ነዶዎች” ማለትም ሊሆን ይችላል።
አንድ ኢፍ 22 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “የመቤዠት (የመዋጀት) መብት ካላቸው ዘመዶቻችን አንዱ ነው።”
ቃል በቃል “ማረፊያ ስፍራ።”
ወይም “መደረቢያሽን ለብሰሽ።”
ቃል በቃል “የሕዝቤ በር ሁሉ።”
ስድስት የሲህ መስፈሪያ ወይም 44 ሊትር ገደማ ሊሆን ይችላል። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ቃል በቃል “አንቺ ማነሽ?”
ወይም “የምሥክርነት ቃል።”
ቃል በቃል “ስምህ ይግነን።”
የናኦሚን የልጅ ልጅ ያመለክታል።
ወይም “ነፍስሽን።”
ወይም “ሞግዚትም ሆነችው።”