አስቴር
1 ከሕንድ አንስቶ እስከ ኢትዮጵያ* ድረስ ባሉ 127 አውራጃዎች+ ይገዛ በነበረው በአሐሽዌሮስ* ዘመን 2 ይኸውም ንጉሥ አሐሽዌሮስ በሹሻን*+ ግንብ* በሚገኘው ንጉሣዊ ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ይገዛ በነበረበት ጊዜ፣ 3 በግዛት ዘመኑ ሦስተኛ ዓመት ላይ ለመኳንንቱና ለአገልጋዮቹ በሙሉ ግብዣ አደረገ። የፋርስና+ የሜዶን+ ሠራዊት፣ ታላላቆቹ ሰዎችና የየአውራጃዎቹ መኳንንት በፊቱ ነበሩ፤ 4 እሱም የክብራማ መንግሥቱን ብልጽግና እንዲሁም የግርማውን ታላቅነትና ውበት ለብዙ ቀናት ይኸውም ለ180 ቀናት ሲያሳያቸው ቆየ። 5 እነዚህ ቀናት ሲያበቁ ንጉሡ ትልቅ ትንሽ ሳይባል በሹሻን* ግንብ* ለተገኘው ሕዝብ ሁሉ በንጉሡ ቤተ መንግሥት የአትክልት ስፍራ ባለው ግቢ ለሰባት ቀን ታላቅ ግብዣ አደረገ። 6 በዚያም ከበፍታ፣ ከጥሩ ጥጥና ከሰማያዊ ጨርቅ የተሠሩ መጋረጃዎች፣ ከፍተኛ ጥራት ካለው ክርና ከሐምራዊ ሱፍ በተሠሩ ገመዶች፣ በእብነ በረድ ዓምዶቹ ላይ በነበሩት የብር ቀለበቶች ላይ ታስረው ነበር፤ ነጭ ነጠብጣብ ያለው ቀይ ድንጋይ፣ ነጭ እብነ በረድ፣ ዕንቁና ጥቁር እብነ በረድ በተነጠፈበት መሬት ላይ ደግሞ ከወርቅና ከብር የተሠሩ ድንክ አልጋዎች ነበሩ።
7 የወይን ጠጅ በወርቅ ጽዋዎች* ቀርቦ ነበር፤ ጽዋዎቹም አንዳቸው ከሌላው የተለዩ ናቸው፤ ከንጉሡም ብልጽግና የተነሳ የቤተ መንግሥቱ የወይን ጠጅ በገፍ ቀርቦ ነበር። 8 የመጠጡ ዝግጅት የተደረገው ማንም ጫና* እንዳይደረግበት ከሚያዘው ደንብ ጋር በሚስማማ ሁኔታ ነበር፤ ንጉሡ እያንዳንዱ ሰው ደስ ያሰኘውን ማድረግ እንዲችል ለቤተ መንግሥቱ ባለሥልጣናት መመሪያ አስተላልፎ ነበርና።
9 ንግሥት አስጢንም+ በንጉሥ አሐሽዌሮስ ንጉሣዊ ቤት* ውስጥ ለሴቶቹ ታላቅ ግብዣ አድርጋ ነበር።
10 በሰባተኛው ቀን ንጉሥ አሐሽዌሮስ የወይን ጠጅ ጠጥቶ ደስ በተሰኘ ጊዜ የቅርብ አገልጋዮቹ ለነበሩት ሰባት የቤተ መንግሥት ባለሥልጣናት ማለትም ለሜሁማን፣ ለቢዝታ፣ ለሃርቦና፣+ ለቢግታ፣ ለአባግታ፣ ለዜታር እና ለካርካስ 11 ንግሥት አስጢንን የንግሥትነት አክሊሏን* እንዳደረገች ወደ ንጉሡ ፊት እንዲያመጧት ነገራቸው፤ ይህን ያደረገው በጣም ቆንጆ ስለነበረች ሕዝቡና መኳንንቱ ውበቷን እንዲያዩ ነበር። 12 ንግሥት አስጢን ግን ንጉሡ በቤተ መንግሥት ባለሥልጣናቱ በኩል ያስተላለፈውን ትእዛዝ ባለመቀበል ፈጽሞ ለመምጣት ፈቃደኛ ሳትሆን ቀረች። በዚህ ጊዜ ንጉሡ በኃይል ተቆጣ፤ በጣም ተናደደ።
13 ከዚያም ንጉሡ ስለ ቀድሞው ዘመን* ጥልቅ ማስተዋል ያላቸውን ጥበበኛ ሰዎች አማከረ (ንጉሡ የሚያጋጥሙት ነገሮች ሕግንና የፍርድ ጉዳዮችን ጠንቅቀው በሚያውቁ ሰዎች ሁሉ ፊት የሚቀርቡት በዚህ መንገድ ነበርና፤ 14 የቅርብ ሰዎቹም ካርሼና፣ ሼታር፣ አድማታ፣ ተርሴስ፣ ሜሬስ፣ ማርሴና እና ሜሙካን ነበሩ፤ እነዚህ ንጉሡ ፊት መቅረብ የሚችሉና በመንግሥቱ ውስጥ ከፍተኛውን ቦታ የያዙ ሰባቱ የፋርስና የሜዶን መኳንንት+ ናቸው)። 15 ንጉሡም እንዲህ ሲል ጠየቀ፦ “ንጉሥ አሐሽዌሮስ በቤተ መንግሥት ባለሥልጣናቱ በኩል ያስተላለፈውን ትእዛዝ ባለማክበሯ በሕጉ መሠረት በንግሥት አስጢን ላይ ምን ቢደረግ ይሻላል?”
16 በዚህ ጊዜ ሜሙካን በንጉሡና በመኳንንቱ ፊት እንዲህ አለ፦ “ንግሥት አስጢን የበደለችው ንጉሡን ብቻ አይደለም፤+ ከዚህ ይልቅ መኳንንቱን ሁሉና በመላው የንጉሥ አሐሽዌሮስ አውራጃዎች የሚኖሩትን ሕዝቦች ሁሉ ነው። 17 ሌሎች ሚስቶች ሁሉ ንግሥቲቱ ያደረገችውን ነገር ማወቃቸው ስለማይቀር ባሎቻቸውን ይንቃሉ፤ ደግሞም ‘ንጉሥ አሐሽዌሮስ ንግሥት አስጢንን በፊቱ እንዲያቀርቧት አዝዞ ነበር፤ እሷ ግን አልቀረበችም’ ይላሉ። 18 በዚህ ቀን ንግሥቲቱ ያደረገችውን ነገር የሰሙ የፋርስና የሜዶን ልዕልቶች ለንጉሡ መኳንንት ሁሉ ተመሳሳይ መልስ ሊሰጡ ነው፤ ይህም ከፍተኛ ንቀትና ቁጣ ያስከትላል። 19 በመሆኑም ንጉሡ መልካም መስሎ ከታየው አስጢን፣ ንጉሥ አሐሽዌሮስ ፊት ዳግመኛ እንዳትቀርብ የሚያዝዝ ንጉሣዊ አዋጅ ያውጣ፤ ይህም የማይሻር ሆኖ+ በፋርስና በሜዶን ሕጎች ውስጥ ይካተት፤ ንጉሡም የእቴጌነት ክብሯን ከእሷ ለተሻለች ሴት ይስጥ። 20 ንጉሡም የሚያወጣው አዋጅ ሰፊ በሆነው ግዛቱ ሁሉ ሲነገር ትልቅ ትንሽ ሳይል ሁሉም ሚስቶች ባሎቻቸውን ያከብራሉ።”
21 ይህ ሐሳብ ንጉሡንና መኳንንቱን ደስ አሰኛቸው፤ ንጉሡም ሜሙካን እንዳለው አደረገ። 22 በመሆኑም እያንዳንዱ ባል በቤቱ ውስጥ ጌታ እንዲሆንና* በራሱ ሕዝብ ቋንቋ እንዲናገር የሚያዝዝ ደብዳቤ ለመላው የንጉሡ አውራጃዎች+ ላከ፤ ደብዳቤውም ለእያንዳንዱ አውራጃ በየራሱ ጽሑፍ፣* ለእያንዳንዱም ሕዝብ በገዛ ቋንቋው የተዘጋጀ ነበር።
2 ከዚህ በኋላ ንጉሥ አሐሽዌሮስ+ ቁጣው ሲበርድለት አስጢን ያደረገችውን ነገርና+ በእሷ ላይ የተላለፈውን ውሳኔ+ አስታወሰ። 2 ከዚያም የንጉሡ የቅርብ አገልጋዮች እንዲህ አሉ፦ “ለንጉሡ ቆንጆ የሆኑ ወጣት ደናግል ይፈለጉለት። 3 ንጉሡም ቆንጆ የሆኑትን ወጣት ደናግል ሁሉ ሰብስበው በሹሻን* ግንብ* ወደሚገኘው፣ ሴቶች ወደሚኖሩበት ቤት* እንዲያመጧቸው በግዛቱ ውስጥ በሚገኙት አውራጃዎች ሁሉ+ ሰዎችን ይሹም። እነሱም የንጉሡ ጃንደረባና የሴቶቹ ጠባቂ በሆነው በሄጌ+ ኃላፊነት ሥር ይሁኑ፤ የውበት እንክብካቤም ይደረግላቸው።* 4 ንጉሡ እጅግ ደስ የተሰኘባት ወጣትም በአስጢን ምትክ ንግሥት ትሆናለች።”+ ንጉሡም በሐሳቡ ደስ ተሰኘ፤ እንደተባለውም አደረገ።
5 በዚህ ጊዜ መርዶክዮስ+ የተባለ አንድ አይሁዳዊ በሹሻን*+ ግንብ* ይኖር ነበር፤ እሱም የቢንያማዊው+ የቂስ ልጅ፣ የሺምአይ ልጅ የሆነው የያኢር ልጅ ነው፤ 6 ይህ ሰው የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር በግዞት ከወሰደው ከይሁዳ ንጉሥ ከኢኮንያን*+ ጋር ከኢየሩሳሌም በግዞት ከተወሰዱት ሰዎች አንዱ ነበር። 7 እሱም የአባቱ ወንድም ልጅ የሆነችው የሃዳሳ* ማለትም የአስቴር አሳዳጊ* ነበር፤+ አስቴር አባትም ሆነ እናት አልነበራትም። ወጣቷ ቁመናዋ ያማረ፣ መልኳም ቆንጆ ነበር፤ መርዶክዮስም አባትና እናቷ ሲሞቱ እንደ ራሱ ልጅ አድርጎ ወሰዳት። 8 የንጉሡ ቃልና ያወጣው ሕግ ታውጆ በርካታ ወጣት ሴቶች በሄጌ+ ኃላፊነት ሥር እንዲሆኑ በሹሻን* ግንብ* ሲሰበሰቡ አስቴርም ወደ ንጉሡ ቤት* ተወስዳ የሴቶች ጠባቂ በሆነው በሄጌ ኃላፊነት ሥር እንድትሆን ተደረገ።
9 እሱም በወጣቷ ደስ ተሰኘባት፤ እንዲሁም በእሱ ዘንድ ሞገስ አገኘች፤* በመሆኑም የውበት እንክብካቤ እንዲደረግላትና*+ የተለየ ምግብ እንዲሰጣት ወዲያውኑ ዝግጅት አደረገ፤ ከንጉሡም ቤት የተመረጡ ሰባት ወጣት ሴቶች መደበላት። በተጨማሪም እሷንና የተመደቡላትን ሴቶች በሴቶቹ ቤት* ውስጥ ወደሚገኘው ምርጥ ወደሆነው ቦታ አዛወራቸው። 10 መርዶክዮስ+ ለማንም እንዳትናገር አዟት ስለነበር+ አስቴር ስለ ሕዝቦቿም+ ሆነ ስለ ዘመዶቿ ምንም አልተናገረችም። 11 መርዶክዮስ ስለ አስቴር ደህንነትና ስላለችበት ሁኔታ ለማወቅ በሴቶቹ ቤት* ግቢ ፊት ለፊት በየዕለቱ ይመላለስ ነበር።
12 እያንዳንዷ ወጣት ለሴቶቹ በታዘዘው መሠረት 12 ወር የሚፈጅ እንክብካቤ ከተደረገላት በኋላ ተራዋ ደርሶ ወደ ንጉሥ አሐሽዌሮስ ትገባ ነበር፤ የውበት እንክብካቤው* በተሟላ ሁኔታ የሚከናወንላቸው በዚህ መንገድ ነበርና፤ ስድስት ወር በከርቤ+ ዘይት፣ ስድስት ወር ደግሞ በበለሳን ዘይት+ እንዲሁም በተለያዩ ቅባቶች የውበት እንክብካቤ ይደረግላቸው ነበር።* 13 ከዚያም ወጣቷ ወደ ንጉሡ ለመግባት ዝግጁ ትሆናለች፤ ከሴቶቹ ቤት* ወደ ንጉሡ ቤት በምትሄድበት ጊዜም የምትጠይቀው ነገር ሁሉ ይሰጣት ነበር። 14 ምሽት ላይ ትገባለች፤ ጠዋት ላይ ደግሞ የቁባቶች ጠባቂ በሆነው በንጉሡ ጃንደረባ+ በሻአሽጋዝ ኃላፊነት ሥር ወዳለው ወደ ሁለተኛው የሴቶች ቤት* ትመለሳለች። ንጉሡ በጣም ካልተደሰተባትና በስም ጠቅሶ ካላስጠራት በስተቀር ዳግመኛ ወደ ንጉሡ አትገባም።+
15 መርዶክዮስ እንደ ልጁ አድርጎ የወሰዳት+ የአጎቱ የአቢሃይል ልጅ አስቴር ወደ ንጉሡ የምትገባበት ተራ ሲደርስ የሴቶች ጠባቂ የሆነው የንጉሡ ጃንደረባ ሄጌ እንድትጠይቅ ከነገራት ነገር በስተቀር ምንም አልጠየቀችም። (በዚህ ሁሉ ጊዜ አስቴር ባዩአት ሁሉ ዘንድ ሞገስ አግኝታ ነበር።) 16 አስቴር ንጉሥ አሐሽዌሮስ በነገሠ በሰባተኛው ዓመት+ ቴቤት* ተብሎ በሚጠራው አሥረኛ ወር ወደ ንጉሡ ቤት ተወሰደች። 17 ንጉሡም ከሌሎቹ ሴቶች ሁሉ ይበልጥ አስቴርን ወደዳት፤ ከሌሎቹም ደናግል ሁሉ ይበልጥ በእሱ ዘንድ ሞገስና ተቀባይነት አገኘች።* በመሆኑም በራሷ ላይ የንግሥትነት አክሊል* አደረገላት፤ በአስጢንም+ ፋንታ ንግሥት አደረጋት።+ 18 ንጉሡም ለመኳንንቱ ሁሉና ለአገልጋዮቹ በሙሉ እጅግ ታላቅ ግብዣ አዘጋጀ፤ ይህን ታላቅ ግብዣ ያዘጋጀው ለአስቴር ክብር ሲል ነው። ከዚያም በአውራጃዎቹ ውስጥ ለሚኖሩ ምሕረት አደረገ፤ ንጉሡም ካለው ብልጽግና የተነሳ ስጦታዎችን ይሰጥ ነበር።
19 ደናግሉ*+ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሰበሰቡ መርዶክዮስ በንጉሡ በር ተቀምጦ ነበር። 20 መርዶክዮስ ባዘዛት መሠረት አስቴር ስለ ዘመዶቿም ሆነ ስለ ሕዝቦቿ ምንም አልተናገረችም፤+ አስቴር ከመርዶክዮስ ጋር በነበረችበት ጊዜ ታደርግ እንደነበረው ሁሉ አሁንም እሱ የሚለውን ትታዘዝ ነበር።+
21 በዚያን ጊዜ መርዶክዮስ በንጉሡ በር ተቀምጦ ሳለ በር ጠባቂዎች የሆኑት ቢግታን እና ቴሬሽ የተባሉ የንጉሡ ሁለት የቤተ መንግሥት ባለሥልጣናት ተቆጡ፤ ንጉሥ አሐሽዌሮስንም ለመግደል* አሴሩ። 22 ሆኖም መርዶክዮስ ይህን ጉዳይ አወቀ፤ ወዲያውኑም ለንግሥት አስቴር ነገራት። ከዚያም አስቴር ጉዳዩን በመርዶክዮስ ስም* ለንጉሡ ነገረችው። 23 በመሆኑም ሁኔታው ሲጣራ እውነት ሆኖ ተገኘ፤ ከዚያም ሁለቱ ሰዎች እንጨት ላይ ተሰቀሉ፤ ይህ ሁኔታም በዘመኑ በነበረው የታሪክ መጽሐፍ ላይ በንጉሡ ፊት ተጻፈ።+
3 ከዚህ በኋላ ንጉሥ አሐሽዌሮስ የአጋጋዊውን+ የሃመዳታን ልጅ የሃማን+ ዙፋን አብረውት ካሉት ከሌሎቹ መኳንንት ሁሉ በላይ በማድረግ ላቅ ያለ ሹመት ሰጠው፤ ደግሞም ከፍ ከፍ አደረገው።+ 2 በንጉሡ በር የነበሩት የንጉሡ አገልጋዮች በሙሉ ሃማን እጅ ይነሱትና ለእሱ ይሰግዱለት ነበር፤ ንጉሡ እንዲህ እንዲደረግለት አዝዞ ነበርና። መርዶክዮስ ግን እጅ ለመንሳትም ሆነ ለመስገድ ፈቃደኛ አልሆነም። 3 በመሆኑም በንጉሡ በር የነበሩት የንጉሡ አገልጋዮች መርዶክዮስን “የንጉሡን ትእዛዝ የማታከብረው ለምንድን ነው?” አሉት። 4 በየቀኑ ይህን ጉዳይ ቢያነሱበትም እሱ ግን ሊሰማቸው ፈቃደኛ አልሆነም። ከዚያም የመርዶክዮስ አድራጎት በቸልታ የሚታለፍ እንደሆነና+ እንዳልሆነ ለማየት ጉዳዩን ለሃማ ነገሩት፤ መርዶክዮስ አይሁዳዊ መሆኑን ነግሯቸው ነበርና።+
5 ሃማም መርዶክዮስ እሱን እጅ ለመንሳትና ለእሱ ለመስገድ ፈቃደኛ አለመሆኑን ባስተዋለ ጊዜ እጅግ ተቆጣ።+ 6 ሆኖም ስለ መርዶክዮስ ወገኖች ነግረውት ስለነበር መርዶክዮስን ብቻ ማስገደሉ* ተራ ነገር እንደሆነ ተሰማው። ስለዚህ ሃማ በመላው የአሐሽዌሮስ ግዛት የሚገኙትን አይሁዳውያን በሙሉ ማለትም የመርዶክዮስን ወገኖች በአጠቃላይ ለማጥፋት ዘዴ ይፈልግ ጀመር።
7 ንጉሥ አሐሽዌሮስ በነገሠ በ12ኛው ዓመት+ ኒሳን* በተባለው የመጀመሪያ ወር ላይ፣ ቀኑንና ወሩን ለመወሰን በሃማ ፊት ፑር+ (ዕጣ ማለት ነው) ጣሉ፤ ዕጣውም በ12ኛው ወር ማለትም በአዳር*+ ወር ላይ ወደቀ። 8 ከዚያም ሃማ ንጉሥ አሐሽዌሮስን እንዲህ አለው፦ “በግዛትህ ውስጥ ባሉት አውራጃዎች ሁሉ+ ተበታትኖና ተሰራጭቶ የሚገኝ፣+ የሚመራበትም ሕግ ከሌሎቹ ሕዝቦች ሁሉ የተለየ አንድ ሕዝብ አለ፤ የንጉሡንም ሕጎች አያከብርም፤ ንጉሡም ይህን ሕዝብ ዝም ብሎ መመልከቱ ይጎዳዋል። 9 ለንጉሡ መልካም መስሎ ከታየው እነዚህ ሰዎች እንዲጠፉ የሚያዝዝ ድንጋጌ በጽሑፍ ይውጣ። እኔም ወደ ንጉሡ ግምጃ ቤት እንዲያስገቡ ለባለሥልጣናቱ 10,000 የብር ታላንት* እከፍላለሁ።”*
10 በዚህ ጊዜ ንጉሡ የማኅተም ቀለበቱን ከእጁ አውልቆ+ የአይሁዳውያን ጠላት ለነበረው ለአጋጋዊው+ ለሃመዳታ ልጅ ለሃማ ሰጠው።+ 11 ንጉሡም ሃማን “ተገቢ መስሎ የታየህን እንድታደርግበት ብሩም ሆነ ሕዝቡ ለአንተ ተሰጥቷል” አለው። 12 ከዚያም በመጀመሪያው ወር 13ኛ ቀን የንጉሡ ጸሐፊዎች+ ተጠሩ። የሃማን ትእዛዝ ሁሉ በተለያዩ አውራጃዎች ላይ ለተሾሙት የንጉሡ አስተዳዳሪዎችና ገዢዎች እንዲሁም ለተለያዩ ሕዝቦች መኳንንት ጻፉ፤+ ለእያንዳንዱ አውራጃ በራሱ ጽሑፍ፣* ለእያንዳንዱም ሕዝብ በራሱ ቋንቋ ተጻፈ። ደብዳቤው የተጻፈው በንጉሥ አሐሽዌሮስ ስም ሲሆን በንጉሡ የማኅተም ቀለበትም ታተመ።+
13 ወጣት ሽማግሌ፣ ሕፃንም ሆነ ሴት ሳይባል አይሁዳውያን በጠቅላላ በአንድ ቀን ይኸውም አዳር+ በተባለው በ12ኛው ወር 13ኛ ቀን ላይ እንዲጠፉ፣ እንዲገደሉ፣ እንዲደመሰሱና ንብረታቸው እንዲወረስ+ የሚያዝዙ ደብዳቤዎች በመልእክተኞች አማካኝነት ወደ ንጉሡ አውራጃዎች ሁሉ ተላኩ። 14 ሕዝቡም ሁሉ ለዚያ ቀን ዝግጁ እንዲሆን ሲባል በደብዳቤዎቹ ላይ የሰፈረው ሐሳብ በሁሉም አውራጃዎች ውስጥ ሕግ ሆኖ እንዲደነገግና ለሕዝቡ ሁሉ እንዲታወጅ መመሪያ ተላለፈ። 15 መልእክተኞቹም ከንጉሡ ትእዛዝ የተነሳ ተጣድፈው ወጡ፤+ ሕጉም በሹሻን* ግንብ*+ ታወጀ። ከዚያም ንጉሡና ሃማ ሊጠጡ ተቀመጡ፤ የሹሻን* ከተማ ግን ግራ ተጋባች።
4 መርዶክዮስ+ የተደረገውን ነገር ሁሉ ባወቀ ጊዜ+ ልብሱን ቀደደ፤ ማቅም ለበሰ፤ በራሱም ላይ አመድ ነሰነሰ። ከዚያም ድምፁን ከፍ አድርጎ እየጮኸና ምርር ብሎ እያለቀሰ ወደ ከተማዋ መሃል ወጣ። 2 ማንም ሰው ማቅ ለብሶ በንጉሡ በር እንዲገባ ስለማይፈቀድለት እስከ ንጉሡ በር ድረስ መጣ። 3 የንጉሡ ቃልና ድንጋጌ በተሰማባቸው አውራጃዎች በሙሉ+ በሚገኙ አይሁዳውያን መካከል ታላቅ ሐዘን ሆነ፤ እነሱም ጾሙ፤+ አለቀሱ፤ እንዲሁም ዋይታ አሰሙ። ብዙዎቹ ማቅ አንጥፈው፣ አመድ ነስንሰው ተኙ።+ 4 የአስቴር ሴት አገልጋዮችና ጃንደረቦችም ወደ እሷ ገብተው በነገሯት ጊዜ ንግሥቲቱ እጅግ ተጨነቀች። ከዚያም መርዶክዮስ ማቁን አውልቆ የሚለብሰው ልብስ ላከችለት፤ እሱ ግን አልተቀበለም። 5 በዚህ ጊዜ አስቴር ከንጉሡ ጃንደረቦች አንዱ የሆነውንና ንጉሡ እሷን እንዲያገለግል የመደበውን ሃታክን ጠርታ ወደ መርዶክዮስ ሄዶ ምን ችግር እንደተፈጠረና ምን እንደተከሰተ እንዲያጣራ አዘዘችው።
6 ስለዚህ ሃታክ በንጉሡ በር ፊት ለፊት ባለው የከተማዋ አደባባይ ወደሚገኘው ወደ መርዶክዮስ ወጣ። 7 መርዶክዮስም ያጋጠመውን ነገር ሁሉ ነገረው፤ እንዲሁም ሃማ አይሁዳውያንን ለማጥፋት+ ወደ ንጉሡ ግምጃ ቤት ለማስገባት ቃል ስለገባው ገንዘብ መጠን ነገረው።+ 8 በተጨማሪም እነሱን ለማጥፋት በሹሻን*+ በጽሑፍ የወጣውን ድንጋጌ ቅጂ ሰጠው። ቅጂውን ለአስቴር እንዲያሳያትና እንዲያስረዳት እንዲሁም ወደ ንጉሡ ገብታ ሞገስ እንዲያሳያት እንድትለምነውና ስለ ሕዝቧ በግንባር ቀርባ እንድትማጸነው ይነግራት ዘንድ+ አሳሰበው።
9 ሃታክ ተመልሶ መርዶክዮስ ያለውን ለአስቴር ነገራት። 10 አስቴርም ለመርዶክዮስ+ እንዲህ ብሎ እንዲነግረው ሃታክን አዘዘችው፦ 11 “የንጉሡ አገልጋዮች ሁሉና በንጉሡ አውራጃዎች ውስጥ የሚኖሩት ሕዝቦች፣ ሳይጠራ ወደ ንጉሡ ውስጠኛ ግቢ+ የሚገባን ማንኛውንም ወንድ ወይም ሴት በተመለከተ ንጉሡ አንድ ሕግ እንዳለው ያውቃሉ፦ እንዲህ ያደረገ ሰው ይገደላል፤ ሰውየው በሕይወት ሊተርፍ የሚችለው ንጉሡ የወርቅ በትረ መንግሥቱን ከዘረጋለት ብቻ ነው።+ እኔ ደግሞ ላለፉት 30 ቀናት ወደ ንጉሡ እንድገባ አልተጠራሁም።”
12 መርዶክዮስ፣ የአስቴር ቃል በተነገረው ጊዜ 13 ለአስቴር ይህን መልስ ላከ፦ “በንጉሡ ቤት ስላለሽ ብቻ ከሌሎቹ አይሁዳውያን ተለይቼ እኔ እተርፋለሁ ብለሽ እንዳታስቢ። 14 በዚህ ጊዜ አንቺ ዝም ብትዪ አይሁዳውያን እፎይታና መዳን ከሌላ ቦታ ያገኛሉ፤+ አንቺና የአባትሽ ቤት ግን ትጠፋላችሁ። ደግሞስ ንግሥት ለመሆን የበቃሽው እንዲህ ላለው ጊዜ እንደሆነ ማን ያውቃል?”+
15 ከዚያም አስቴር በምላሹ እንዲህ የሚል መልእክት ወደ መርዶክዮስ ላከች፦ 16 “ሂድ፤ በሹሻን* ያሉትን አይሁዳውያን ሁሉ ሰብስብ፤ ስለ እኔም ጹሙ።+ ቀንም ሆነ ሌሊት ለሦስት ቀን እንዳትበሉ እንዲሁም እንዳትጠጡ።+ እኔም ከሴት አገልጋዮቼ ጋር እጾማለሁ። ከዚያም ሕጉ ባይፈቅድም እንኳ ወደ ንጉሡ እገባለሁ፤ ከጠፋሁም ልጥፋ።” 17 በመሆኑም መርዶክዮስ ሄደ፤ አስቴር ያዘዘችውንም ነገር ሁሉ አደረገ።
5 በሦስተኛው ቀን+ አስቴር ልብሰ መንግሥቷን ለብሳ ከንጉሡ ቤት ፊት ለፊት በሚገኘው በንጉሡ ቤት* ውስጠኛ ግቢ ቆመች፤ ንጉሡም በመግቢያው ፊት ለፊት በሚገኘው በንጉሡ ቤት ውስጥ በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ነበር። 2 ንጉሡ፣ ንግሥት አስቴርን ግቢ ውስጥ ቆማ ሲያያት በፊቱ ሞገስ አገኘች፤ ንጉሡም እጁ ላይ የነበረውን የወርቅ በትረ መንግሥት ለአስቴር ዘረጋላት።+ በዚህ ጊዜ አስቴር ቀርባ የበትሩን ጫፍ ነካች።
3 ንጉሡም “ንግሥት አስቴር ሆይ፣ ምን ችግር አጋጠመሽ? የምትፈልጊው ምንድን ነው? እስከ መንግሥቴ እኩሌታ እንኳ ብትጠይቂ ይሰጥሻል!” አላት። 4 አስቴርም መልሳ “ንጉሡን ደስ የሚያሰኘው ከሆነ ንጉሡ ለእሱ ባዘጋጀሁት ግብዣ ላይ ዛሬ ከሃማ+ ጋር ይገኝልኝ” አለች። 5 በመሆኑም ንጉሡ አገልጋዮቹን “አስቴር ባቀረበችው ጥያቄ መሠረት በአስቸኳይ እንዲመጣ ለሃማ ንገሩት” አለ። ስለዚህ ንጉሡና ሃማ አስቴር ወዳዘጋጀችው ግብዣ መጡ።
6 በወይን ጠጅ ግብዣው ላይ ንጉሡ አስቴርን እንዲህ አላት፦ “የምትጠይቂው ምንድን ነው? የጠየቅሽው ይሰጥሻል! የምትፈልጊውስ ምንድን ነው? እስከ መንግሥቴ እኩሌታ እንኳ ብትጠይቂ ይሰጥሻል!”+ 7 አስቴርም እንዲህ ስትል መለሰች፦ “የምጠይቀውም ሆነ የምፈልገው ነገር ይህ ነው፦ 8 በንጉሡ ዘንድ ሞገስ ካገኘሁ እንዲሁም ንጉሡ የምጠይቀውን ነገር መስጠትና የምፈልገውን መፈጸም ደስ ካሰኘው ነገ ንጉሡና ሃማ ለእነሱ በማዘጋጅላቸው ግብዣ ላይ ይገኙ፤ እኔም በነገው ዕለት ንጉሡ ያለውን አደርጋለሁ።”
9 በዚያ ቀን ሃማ ተደስቶ ልቡም ሐሴት አድርጎ ወጣ። ሆኖም ሃማ፣ መርዶክዮስን በንጉሡ በር ላይ ሲያየው እንዲሁም እንዳልተነሳለትና በፊቱ እንዳልተንቀጠቀጠ ሲመለከት በመርዶክዮስ ላይ ቁጣው ነደደ።+ 10 ይሁንና ሃማ ራሱን ተቆጣጥሮ ወደ ቤቱ ሄደ። ከዚያም ጓደኞቹንና ሚስቱን ዜሬሽን+ አስጠራቸው። 11 ሃማም ስለ ሀብቱ ታላቅነትና ስለ ወንዶች ልጆቹ ብዛት+ እንዲሁም ንጉሡ ላቅ ያለ ሹመት እንደሰጠውና ከመኳንንቱም ሆነ ከንጉሡ አገልጋዮች በላይ ከፍ ከፍ እንዳደረገው+ በጉራ ይነግራቸው ጀመር።
12 ሃማ በመቀጠል እንዲህ አለ፦ “ምን ይሄ ብቻ፣ ንግሥት አስቴር አዘጋጅታ በነበረው ግብዣ+ ላይ ከንጉሡ ጋር እንድገኝ የጋበዘችው እኔን ብቻ ነው። በተጨማሪም ነገ ከንጉሡና ከእሷ ጋር እንድገኝ ጋብዛኛለች።+ 13 ይሁን እንጂ አይሁዳዊውን መርዶክዮስን በንጉሡ በር ላይ ተቀምጦ የማየው ከሆነ ይህ ሁሉ ምንም አያስደስተኝም።” 14 በዚህ ጊዜ ሚስቱ ዜሬሽና ጓደኞቹ በሙሉ እንዲህ አሉት፦ “ቁመቱ 50 ክንድ* የሆነ እንጨት አስተክል። ከዚያም ነገ ጠዋት በላዩ ላይ መርዶክዮስ እንዲሰቀል ለንጉሡ ንገረው።+ አንተም ከንጉሡ ጋር በግብዣው ላይ ተገኝተህ ሐሴት አድርግ።” ይህ ሐሳብ ሃማን አስደሰተው፤ እንጨቱንም አስተከለ።
6 በዚያ ሌሊት ንጉሡ እንቅልፍ እንቢ አለው።* በመሆኑም በዘመኑ የነበረውን የታሪክ መጽሐፍ+ እንዲያመጡለት አዘዘ። መጽሐፉም በንጉሡ ፊት ተነበበ። 2 በዚህ ጊዜ ንጉሥ አሐሽዌሮስን ለመግደል* አሲረው የነበሩትን የንጉሡን ሁለት የቤተ መንግሥት ባለሥልጣናት ማለትም በር ጠባቂዎቹን ቢግታናን እና ቴሬሽን አስመልክቶ መርዶክዮስ የተናገረው ነገር ተጽፎ ተገኘ።+ 3 ንጉሡም “ታዲያ መርዶክዮስ ይህን በማድረጉ ምን ክብርና እውቅና አገኘ?” ሲል ጠየቀ። በዚህ ጊዜ የንጉሡ የቅርብ አገልጋዮች “ምንም አልተደረገለትም” አሉ።
4 ንጉሡም “በግቢው ውስጥ ያለው ማን ነው?” አለ። ሃማም ባዘጋጀው እንጨት ላይ መርዶክዮስ እንዲሰቀል ለንጉሡ ለመናገር+ ወደ ንጉሡ ቤት* ውጨኛ ግቢ+ ገብቶ ነበር። 5 የንጉሡ አገልጋዮችም “ሃማ+ ግቢው ውስጥ ቆሟል” አሉት። ንጉሡም “ግባ በሉት” አለ።
6 ንጉሡም ሃማ በገባ ጊዜ “ንጉሡ ሊያከብረው ለወደደው ሰው ምን ሊደረግለት ይገባል?” አለው። ሃማም በልቡ “ንጉሡ ከእኔ በላይ ሊያከብረው የሚወደው ሰው ማን አለ?” ሲል አሰበ።+ 7 በመሆኑም ሃማ ንጉሡን እንዲህ አለው፦ “ንጉሡ ሊያከብረው ለወደደው ሰው፣ 8 ንጉሡ የሚጎናጸፈውን ልብሰ መንግሥት+ እንዲሁም ንጉሡ የሚቀመጥበትንና በራሱ ላይ አክሊል የተደረገለትን ፈረስ ያምጡለት። 9 ከዚያም ልብሱና ፈረሱ ከንጉሡ ታላላቅ መኳንንት መካከል ለአንዱ በኃላፊነት ይሰጥ፤ እነሱም ንጉሡ ሊያከብረው የወደደውን ሰው ያልብሱት፤ እንዲሁም በፈረሱ ላይ አስቀምጠው በከተማው አደባባይ እንዲያልፍ ያድርጉ። በፊቱም ‘ንጉሡ ሊያከብረው ለወደደው ሰው እንዲህ ይደረግለታል!’ ይበሉ።”+ 10 ንጉሡም ወዲያውኑ ሃማን እንዲህ አለው፦ “ፈጠን በል! ልብሱንና ፈረሱን ውሰድ፤ በንጉሡ በር ላይ ለሚቀመጠው ለአይሁዳዊው ለመርዶክዮስም ልክ እንዳልከው አድርግለት። ከተናገርከው ውስጥ አንዱም ሳይፈጸም እንዳይቀር።”
11 ስለዚህ ሃማ ልብሱንና ፈረሱን ወሰደ፤ መርዶክዮስንም+ አለበሰው፤ በፈረሱም ላይ አስቀምጦ በከተማው አደባባይ እንዲያልፍ አደረገ፤ “ንጉሡ ሊያከብረው ለወደደው ሰው እንዲህ ይደረግለታል!” እያለ በፊቱ ያውጅ ነበር። 12 ከዚያም መርዶክዮስ ወደ ንጉሡ በር ተመለሰ፤ ሃማ ግን ራሱን ተከናንቦ እያዘነ በጥድፊያ ወደ ቤቱ ሄደ። 13 ሃማ ያጋጠመውን ነገር ሁሉ ለሚስቱ ለዜሬሽና+ ለጓደኞቹ በሙሉ ሲነግራቸው ጥበበኛ አማካሪዎቹና ሚስቱ ዜሬሽ “በፊቱ መውደቅ የጀመርክለት መርዶክዮስ የአይሁዳውያን ዘር ከሆነ ልታሸንፈው አትችልም፤ ያለምንም ጥርጥር በፊቱ ትወድቃለህ” አሉት።
14 እነሱም ገና ከእሱ ጋር እየተነጋገሩ ሳሉ የንጉሡ የቤተ መንግሥት ባለሥልጣናት ደርሰው ሃማን አስቴር ወዳዘጋጀችው ግብዣ እያጣደፉ ወሰዱት።+
7 ንጉሡና ሃማም+ ንግሥት አስቴር ወዳዘጋጀችው ግብዣ መጡ። 2 በሁለተኛው ቀን በወይን ጠጅ ግብዣው ላይ ንጉሡ አስቴርን በድጋሚ እንዲህ አላት፦ “ንግሥት አስቴር ሆይ፣ የምትጠይቂው ምንድን ነው? የጠየቅሽው ይሰጥሻል። የምትፈልጊውስ ምንድን ነው? እስከ መንግሥቴ እኩሌታ እንኳ ብትጠይቂ ይሰጥሻል!”+ 3 ንግሥት አስቴርም እንዲህ ስትል መለሰች፦ “ንጉሥ ሆይ፣ በፊትህ ሞገስ ካገኘሁና ንጉሡን የሚያስደስተው ከሆነ ሕይወቴን* እንድትታደግልኝ እማጸንሃለሁ፤ ሕዝቤንም+ እንድታድንልኝ እጠይቅሃለሁ። 4 እኔና ሕዝቤ ለጥፋት፣ ለመገደልና ለመደምሰስ+ ተሸጠናልና።+ የተሸጥነው ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎች እንድንሆን ብቻ ቢሆን ኖሮ ዝም ባልኩ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ጥፋት በንጉሡም ላይ ጉዳት ስለሚያስከትል በቸልታ መታለፍ የለበትም።”
5 ንጉሥ አሐሽዌሮስም ንግሥት አስቴርን “ለመሆኑ ይህ ሰው ማን ነው? እንዲህ ያለውን ነገር ለማድረግ የደፈረውስ ሰው የታለ?” አላት። 6 አስቴርም “ባላጋራና ጠላት የሆነው ሰው ይህ ክፉው ሃማ ነው” አለች።
ሃማም በንጉሡና በንግሥቲቱ ፊት በፍርሃት ተንቀጠቀጠ። 7 ንጉሡም ከወይን ጠጅ ግብዣው ላይ ተቆጥቶ ተነሳ፤ ወደ ቤተ መንግሥቱም የአትክልት ስፍራ ሄደ፤ ይሁንና ሃማ ንጉሡ ሊቀጣው ቆርጦ እንደተነሳ ስለተገነዘበ ንግሥት አስቴር ሕይወቱን* እንድታድንለት ለመማጸን ቆመ። 8 ንጉሡ ከቤተ መንግሥቱ የአትክልት ስፍራ ወደ ወይን ጠጅ ግብዣው ተመልሶ ሲመጣ ሃማ አስቴር ባለችበት ድንክ አልጋ ላይ ተደፍቶ ተመለከተ። ንጉሡም “ብሎ ብሎ በገዛ ቤቴ ንግሥቲቱን ሊደፍራት ያስባል?” ብሎ ጮኸ። ይህ ቃል ከንጉሡ አፍ እንደወጣ የሃማን ፊት ሸፈኑት። 9 ከንጉሡ የቤተ መንግሥት ባለሥልጣናት አንዱ የሆነው ሃርቦና+ እንዲህ አለ፦ “ሃማ፣ የንጉሡ ሕይወት እንዲተርፍ ሴራውን ላጋለጠው+ ለመርዶክዮስ የመሰቀያ እንጨትም አዘጋጅቷል።+ እንጨቱ 50 ክንድ* ቁመት ያለው ሲሆን በሃማ ቤት ቆሟል።” በዚህ ጊዜ ንጉሡ “በዚያው እንጨት ላይ ስቀሉት” አለ። 10 በመሆኑም ሃማን ለመርዶክዮስ ባዘጋጀው እንጨት ላይ ሰቀሉት፤ የንጉሡም ቁጣ በረደ።
8 በዚያው ቀን ንጉሥ አሐሽዌሮስ የአይሁዳውያን ጠላት+ የነበረውን የሃማን ቤት ለንግሥት አስቴር ሰጣት፤+ አስቴር ከመርዶክዮስ ጋር ምን ዝምድና እንዳላቸው+ ለንጉሡ ነግራው ስለነበር መርዶክዮስ ንጉሡ ፊት ቀረበ። 2 ከዚያም ንጉሡ ከሃማ ላይ የወሰደውን የማኅተም ቀለበቱን አውልቆ+ ለመርዶክዮስ ሰጠው። አስቴርም መርዶክዮስን በሃማ ቤት ላይ ሾመችው።+
3 በተጨማሪም አስቴር ንጉሡን እንደገና አናገረችው። እግሩ ላይ ወድቃ እያለቀሰች አጋጋዊው ሃማ ያደረሰውን ጉዳትና በአይሁዳውያን ላይ የጠነሰሰውን ሴራ እንዲያስወግድ ለመነችው።+ 4 ንጉሡም የወርቅ በትረ መንግሥቱን ለአስቴር ዘረጋላት፤+ አስቴርም ተነስታ በንጉሡ ፊት ቆመች። 5 እሷም እንዲህ አለች፦ “ንጉሡን ደስ የሚያሰኘው ከሆነና እኔም በፊቱ ሞገስ ካገኘሁ፣ ነገሩም በንጉሡ ፊት ተገቢ ሆኖ ከተገኘና በእኔ ደስ ከተሰኘ፣ ያ ሴረኛ አጋጋዊው+ የሃመዳታ ልጅ ሃማ+ በመላው የንጉሡ አውራጃዎች የሚገኙትን አይሁዳውያን ለማጥፋት ያዘጋጀውን ሰነድ የሚሽር ትእዛዝ ይጻፍ። 6 በሕዝቤ ላይ መዓት ሲወርድ ዓይኔ እያየ እንዴት አስችሎኝ ዝም እላለሁ? ዘመዶቼ ሲጠፉስ እያየሁ እንዴት አስችሎኝ ዝም እላለሁ?”
7 በመሆኑም ንጉሥ አሐሽዌሮስ ንግሥት አስቴርንና አይሁዳዊውን መርዶክዮስን እንዲህ አላቸው፦ “የሃማን ቤት ለአስቴር ሰጥቻለሁ፤+ አይሁዳውያንን ለማጥቃት በጠነሰሰው ሴራ የተነሳም* በእንጨት ላይ እንዲሰቀል አድርጌአለሁ።+ 8 በንጉሡ ስም የተጻፈንና በንጉሡ የማኅተም ቀለበት የታተመን ድንጋጌ መሻር ስለማይቻል አይሁዳውያንን በተመለከተ ተገቢ መስሎ የታያችሁን ማንኛውንም ነገር በንጉሡ ስም ጻፉ፤ በንጉሡም የማኅተም ቀለበት አትሙት።”+
9 ስለሆነም ሲዋን* በተባለው በሦስተኛው ወር፣ በ23ኛው ቀን የንጉሡ ጸሐፊዎች ተጠሩ፤ እነሱም መርዶክዮስ ያዘዘውን ሁሉ ለአይሁዳውያኑ፣ ለአስተዳዳሪዎቹ፣+ ለገዢዎቹና ከሕንድ አንስቶ እስከ ኢትዮጵያ ላሉት 127 አውራጃዎች መኳንንት+ ጻፉ፤ ለእያንዳንዱ አውራጃ በራሱ ጽሑፍ፣* ለእያንዳንዱም ሕዝብ በራሱ ቋንቋ ተጻፈለት፤ ለአይሁዳውያኑም በራሳቸው ጽሑፍና በራሳቸው ቋንቋ ተጻፈላቸው።
10 እሱም ደብዳቤውን በንጉሥ አሐሽዌሮስ ስም ጽፎ በንጉሡ የማኅተም ቀለበት+ አተመው፤ ደብዳቤውንም ፈረስ በሚጋልቡ መልእክተኞች እጅ ላከው፤ እነዚህ መልእክተኞች ለንጉሡ አገልግሎት የሚያሳድጓቸውን፣ ደብዳቤ ለማድረስ የሚያገለግሉ ፈጣን ፈረሶች የሚጋልቡ ነበሩ። 11 በእነዚህም ደብዳቤዎች ላይ በተለያዩ ከተሞች የሚገኙ አይሁዳውያን በሙሉ ተሰብስበው ሕይወታቸውን* ከጥቃት እንዲከላከሉ እንዲሁም ሴቶችንና ልጆችን ጨምሮ በእነሱ ላይ ጥቃት የሚሰነዝሩትን የየትኛውም ሕዝብ ወይም አውራጃ ኃይሎች በሙሉ እንዲያጠፉ፣ እንዲገድሉና እንዲደመስሱ ብሎም ንብረታቸውን እንዲዘርፉ ንጉሡ መፍቀዱን የሚገልጽ ሐሳብ ሰፍሮ ነበር።+ 12 ይህም በመላው የንጉሥ አሐሽዌሮስ አውራጃዎች በተመሳሳይ ቀን ይኸውም አዳር* በተባለው በ12ኛው ወር 13ኛ ቀን ላይ እንዲፈጸም ተወሰነ።+ 13 በደብዳቤው ላይ የሰፈረው ጽሑፍ* በሁሉም አውራጃዎች ውስጥ ሕግ ሆኖ እንዲወጣ ተወስኖ ነበር። በተጨማሪም አይሁዳውያኑ በዚያ ቀን ጠላቶቻቸውን ለመበቀል ዝግጁ እንዲሆኑ ለማድረግ ሲባል ለሕዝቦቹ ሁሉ እንዲታወጅ ተደንግጎ ነበር።+ 14 ለንጉሡ አገልግሎት የተመደቡትን ደብዳቤ ለማድረስ የሚያገለግሉ ፈረሶች የሚጋልቡት መልእክተኞች በንጉሡ ትእዛዝ መሠረት እየተቻኮሉና እየተጣደፉ ወጡ። ሕጉ በሹሻን* ግንብም *+ ታውጆ ነበር።
15 መርዶክዮስም ሰማያዊና ነጭ ልብሰ መንግሥት ለብሶ፣ ትልቅ የወርቅ አክሊል ደፍቶ እንዲሁም ከፍተኛ ጥራት ካለው ክርና ከሐምራዊ ሱፍ የተሠራ መጎናጸፊያ ደርቦ ከንጉሡ ፊት ወጣ።+ የሹሻን* ከተማም እልል አለች። 16 ለአይሁዳውያኑም እፎይታ፣* ደስታ፣ ሐሴትና ክብር ሆነላቸው። 17 የንጉሡ ድንጋጌና ሕግ በተሰማባቸው በሁሉም አውራጃዎችና ከተሞች የሚኖሩ አይሁዳውያን ተደሰቱ፤ ሐሴትም አደረጉ፤ የግብዣና የፈንጠዝያ ቀን ሆነ። ብዙዎቹ የምድሪቱ ነዋሪዎች አይሁዳውያንን ከመፍራታቸው የተነሳ አይሁዳዊ ሆኑ።+
9 አዳር* በተባለው በ12ኛው ወር፣ 13ኛ ቀን፣+ የንጉሡ ቃልና ሕግ በሚፈጸምበት+ እንዲሁም የአይሁዳውያን ጠላቶች በአይሁዳውያን ላይ ድል እንደሚቀዳጁ ተስፋ አድርገው በነበረበት ቀን ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆነ፤ አይሁዳውያኑ የሚጠሏቸውን ሰዎች ድል አደረጉ።+ 2 አይሁዳውያኑ እነሱን ለመጉዳት በሚሹ ሰዎች ላይ እጃቸውን ለማንሳት በንጉሥ አሐሽዌሮስ+ አውራጃዎች በሙሉ በሚገኙ ከተሞቻቸው ውስጥ ተሰባሰቡ፤ ሕዝቡም ሁሉ ፈርቷቸው ስለነበር ሊቃወማቸው የቻለ አንድም ሰው አልነበረም።+ 3 የአውራጃዎቹ መኳንንት በሙሉ፣ አስተዳዳሪዎቹ፣+ ገዢዎቹና የንጉሡን ጉዳይ የሚያስፈጽሙ ሰዎችም መርዶክዮስን ፈርተውት ስለነበር አይሁዳውያኑን ይረዷቸው ነበር። 4 መርዶክዮስ በንጉሡ ቤት* ውስጥ ገናና ሆኖ ነበር፤+ ገናናነቱም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ስለመጣ ዝናው በየአውራጃው ተዳረሰ።
5 አይሁዳውያኑ ጠላቶቻቸውን በሙሉ በሰይፍ ጨፈጨፏቸው፤ ገደሏቸው፤ እንዲሁም ደመሰሷቸው፤ በሚጠሏቸውም ሰዎች ላይ የፈለጉትን አደረጉባቸው።+ 6 አይሁዳውያኑ በሹሻን* ግንብ*+ 500 ሰዎችን ገደሉ፤ ደግሞም አጠፉ። 7 በተጨማሪም ፓርሻንዳታ፣ ዳልፎን፣ አስፋታ፣ 8 ፖራታ፣ አዳሊያ፣ አሪዳታ፣ 9 ፓርማሽታ፣ አሪሳይ፣ አሪዳይ እና ዋይዛታ የተባሉትን፣ 10 የአይሁዳውያን ጠላት+ የነበረውን የሃመዳታን ልጅ የሃማን አሥር ወንዶች ልጆች ገደሉ። ከገደሏቸው በኋላ ግን አንድም ምርኮ አልወሰዱም።+
11 በዚያ ቀን በሹሻን* ግንብ* የተገደሉት ሰዎች ብዛት ለንጉሡ ተነገረው።
12 ንጉሡ ንግሥት አስቴርን እንዲህ አላት፦ “አይሁዳውያኑ በሹሻን* ግንብ* 500 ሰዎችንና አሥሩን የሃማ ወንዶች ልጆች ገድለዋል፤ ደግሞም አጥፍተዋል። በቀሩት የንጉሡ አውራጃዎችስ+ ምን አድርገው ይሆን? አሁንስ የምትጠይቂው ምንድን ነው? የጠየቅሽው ይሰጥሻል። ሌላስ የምትፈልጊው ነገር አለ? ይደረግልሻል።” 13 አስቴርም እንዲህ ስትል መለሰች፦ “ንጉሡን ደስ የሚያሰኘው ከሆነ+ በሹሻን* የሚኖሩት አይሁዳውያን ዛሬ ተግባራዊ ያደረጉትን ሕግ+ ነገም እንዲደግሙት ይፈቀድላቸው፤ አሥሩ የሃማ ልጆችም በእንጨት ላይ ይሰቀሉ።”+ 14 ንጉሡም እንዲሁ እንዲደረግ አዘዘ። ከዚያም በሹሻን* ሕግ ወጣ፤ አሥሩ የሃማ ልጆችም ተሰቀሉ።
15 በሹሻን* የሚኖሩት አይሁዳውያን አዳር+ በተባለው ወር 14ኛ ቀን ላይ በድጋሚ ተሰበሰቡ፤ በሹሻንም* 300 ሰዎችን ገደሉ፤ ይሁንና አንድም ምርኮ አልወሰዱም።
16 በንጉሡ አውራጃዎች የሚኖሩት የቀሩት አይሁዳውያንም ተሰብስበው ሕይወታቸውን ከጥቃት ተከላከሉ።*+ እነሱን ይጠሏቸው ከነበሩት ሰዎች መካከል 75,000 ሰዎችን በመግደል ጠላቶቻቸውን አጠፉ፤+ ይሁንና አንድም ምርኮ አልወሰዱም። 17 ይህ የሆነው አዳር በተባለው ወር 13ኛ ቀን ላይ ነበር፤ እነሱም በ14ኛው ቀን አረፉ፤ ዕለቱንም የግብዣና የሐሴት ቀን አደረጉት።
18 በሹሻን* የነበሩት አይሁዳውያን በ13ኛው ቀንና+ በ14ኛው ቀን+ ላይ ተሰበሰቡ፤ በ15ኛው ቀን ደግሞ አረፉ፤ ቀኑንም የግብዣና የሐሴት ቀን አደረጉት። 19 ከዋና ከተማዋ ውጭ በሚገኙ የገጠር ከተሞች የሚኖሩት አይሁዳውያን አዳር የተባለውን ወር 14ኛ ቀን የሐሴትና የግብዣ ቀን፣ የፈንጠዝያ ቀንና+ አንዳቸው ለሌላው ምግብ የሚልኩበት ጊዜ+ እንዲሆን ያደረጉት በዚህ የተነሳ ነው።
20 መርዶክዮስ+ እነዚህን ክንውኖች ከመዘገበ በኋላ በቅርብም ይሁን በሩቅ ስፍራ ላሉ፣ በመላው የንጉሥ አሐሽዌሮስ አውራጃዎች ለሚኖሩ አይሁዳውያን በሙሉ ሕጋዊ እውቅና ያላቸው ደብዳቤዎች ላከ። 21 በየዓመቱ የአዳርን ወር 14ኛና 15ኛ ቀን እንዲያከብሩ አዘዛቸው፤ 22 ምክንያቱም እነዚህ ቀናት አይሁዳውያኑ ከጠላቶቻቸው ያረፉባቸውና ሐዘናቸው ወደ ሐሴት፣ ለቅሷቸውም ወደ ፈንጠዝያ የተለወጠባቸው ቀናት ናቸው።+ እነዚህን ቀናት የግብዣና የደስታ እንዲሁም አንዳቸው ለሌላው ምግብ የሚልኩባቸውና ለድሆች ምጽዋት የሚሰጡባቸው ቀናት አድርገው እንዲያከብሩ ታዘው ነበር።
23 አይሁዳውያንም ማክበር የጀመሩትን ይህን በዓል ማክበራቸውን ለመቀጠልና መርዶክዮስ የጻፈላቸውን ነገር ለመፈጸም ተስማሙ። 24 የአይሁዳውያን ሁሉ ጠላት የነበረው የአጋጋዊው+ የሃመዳታ ልጅ ሃማ+ አይሁዳውያንን ለማጥፋት ሴራ ሸርቦ ነበርና፤+ እንዲሁም እነሱን ለማሸበርና ለመደምሰስ ፑር+ ወይም ዕጣ ጥሎ ነበር። 25 ሆኖም አስቴር ወደ ንጉሡ በገባች ጊዜ ንጉሡ “በአይሁዳውያን ላይ የሸረበው መጥፎ ሴራ+ በራሱ ላይ ይድረስበት” የሚል የጽሑፍ ትእዛዝ አስተላለፈ፤+ እነሱም እሱንና ልጆቹን በእንጨት ላይ ሰቀሏቸው።+ 26 በዚህም የተነሳ እነዚህን ቀናት ፑሪም አሏቸው፤ ይህ ስም የተወሰደው ፑር*+ ከተባለው ቃል ነው። በመሆኑም በዚህ ደብዳቤ ላይ ከሰፈረው ሐሳብ እንዲሁም ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ካዩአቸውና ካጋጠሟቸው ነገሮች የተነሳ 27 አይሁዳውያኑ ራሳቸውም ሆኑ ዘሮቻቸው እንዲሁም ከእነሱ ጋር የተባበሩ ሁሉ+ በየዓመቱ እነዚህን ሁለት ቀናት በተወሰነላቸው ጊዜ ላይ ለማክበርና እነዚህን ቀናት አስመልክቶ የተሰጣቸውን ትእዛዝ ለመፈጸም ቁርጥ ውሳኔ አደረጉ። 28 እያንዳንዱ ትውልድ፣ እያንዳንዱ ቤተሰብ፣ እያንዳንዱ አውራጃና እያንዳንዱ ከተማ እነዚህን ቀናት ማሰብና ማክበር ይጠበቅበት ነበር፤ እነዚህን የፑሪም ቀናት አይሁዳውያኑ ማክበራቸውን መተው የለባቸውም፤ መታሰቢያቸውም ከዘሮቻቸው መካከል መጥፋት የለበትም።
29 ከዚያም የአቢሃይል ልጅ ንግሥት አስቴርና አይሁዳዊው መርዶክዮስ ፑሪምን በተመለከተ የተጻፈውን ሁለተኛ ደብዳቤ በሙሉ ሥልጣናቸው አጸኑት። 30 እሱም የሰላምና የእውነት ቃል የያዙ ሕጋዊ እውቅና ያላቸው ደብዳቤዎችን በአሐሽዌሮስ+ ግዛት ውስጥ በሚገኙት 127 አውራጃዎች+ ለሚኖሩት አይሁዳውያን በሙሉ ላከ፤ 31 ይህም አይሁዳዊው መርዶክዮስና ንግሥት አስቴር ባዘዟቸው መሠረት+ እንዲሁም እነሱ ራሳቸው መጾምንና+ ምልጃ+ ማቅረብን ጨምሮ የሚጠበቅባቸውን ነገር ለመፈጸም ራሳቸውንና* ዘሮቻቸውን ግዴታ ውስጥ ባስገቡት መሠረት+ የፑሪምን ቀናት በተወሰነው ጊዜ እንዲያከብሩ ለማድረግ ነው። 32 አስቴር ያስተላለፈችውም ትእዛዝ ከፑሪም+ ጋር የተያያዙትን እነዚህን ነገሮች አጸና፤ ደግሞም መጽሐፍ ላይ ሰፈረ።
10 ንጉሥ አሐሽዌሮስ በምድሪቱና በባሕር ደሴቶች ላይ የሚኖሩ ሰዎች የግዳጅ ሥራ እንዲሠሩ አደረገ።
2 ንጉሡ ያከናወናቸው ታላላቅና አስደናቂ ሥራዎች በሙሉ እንዲሁም መርዶክዮስን+ ከፍ ከፍ እንዲያደርገው+ ስላነሳሳው ስለ መርዶክዮስ ታላቅነት የሚገልጸው ዘገባ በሜዶንና በፋርስ ነገሥታት+ ዘመን ስለተከናወኑ ነገሮች በሚተርከው መጽሐፍ+ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም? 3 አይሁዳዊው መርዶክዮስ ከንጉሥ አሐሽዌሮስ ቀጥሎ ያለ ሁለተኛ ሰው ነበር። በአይሁዳውያን መካከል ትልቅ ቦታ የነበረው፣* በብዙ ወንድሞቹ ዘንድ የተከበረ፣ ለወገኖቹ ጥቅም የቆመ እንዲሁም ለዘሮቻቸው ሁሉ ደህንነት የሚቆረቆር* ሰው ነበር።
ወይም “ኩሽ።”
የታላቁ ዳርዮስ (ዳርዮስ ሂስታስፒስ) ልጅ የሆነው ቀዳማዊ ጠረክሲስ እንደሆነ ይታመናል።
ወይም “በሱሳ።”
ወይም “ቤተ መንግሥት፤ ምሽግ።”
ወይም “በሱሳ።”
ወይም “ቤተ መንግሥት፤ ምሽግ።”
ወይም “ዕቃዎች፤ ዋንጫዎች።”
ወይም “ገደብ።”
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
ወይም “የንግሥትነት ጥምጥሟን።”
ወይም “አሠራር።” ቃል በቃል “ጊዜያት።”
ወይም “አለቃ እንዲሆንና።”
ወይም “የአጻጻፍ ስልት።”
ወይም “በሱሳ።”
ወይም “ቤተ መንግሥት፤ ምሽግ።”
ወይም “የሴቶች ክፍል።”
ወይም “ሰውነታቸው ይታሽ።”
ወይም “በሱሳ።”
ወይም “ቤተ መንግሥት፤ ምሽግ።”
በ2ነገ 24:8 ላይ ዮአኪን ተብሎም ተጠርቷል።
“አደስ” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “ተንከባካቢ።”
ወይም “በሱሳ።”
ወይም “ቤተ መንግሥት፤ ምሽግ።”
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
ወይም “እንዲሁም ታማኝ ፍቅር አሳያት።”
ወይም “ሰውነቷ እንዲታሽና።”
ወይም “በሴቶቹ ክፍል።”
ወይም “በሴቶቹ ክፍል።”
ወይም “እሽቱ።”
ወይም “ሰውነታቸው ይታሽ ነበር።”
ወይም “ከሴቶቹ ክፍል።”
ወይም “የሴቶች ክፍል።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።
ወይም “ታማኝ ፍቅር አተረፈች።”
ወይም “ጥምጥም።”
ወይም “ወጣቶቹ ሴቶች።”
ቃል በቃል “በንጉሥ አሐሽዌሮስ ላይ እጃቸውን ለማሳረፍ።”
ወይም “መርዶክዮስን ወክላ።”
ቃል በቃል “በመርዶክዮስ ላይ ብቻ እጁን ማሳረፉ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።
አንድ ታላንት 34.2 ኪሎ ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
“ወደ ንጉሡ ግምጃ ቤት እንዲያስገቡ ሥራውን ለሚያስፈጽሙት ሰዎች 10,000 ታላንት እከፍላለሁ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “የአጻጻፍ ስልት።”
ወይም “በሱሳ።”
ወይም “ቤተ መንግሥት፤ ምሽግ።”
ወይም “የሱሳ።”
ወይም “በሱሳ።”
ወይም “በሱሳ።”
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
ወደ 22.3 ሜትር ገደማ ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ቃል በቃል “የንጉሡ እንቅልፍ ሸሸ።”
ቃል በቃል “በንጉሥ አሐሽዌሮስ ላይ እጃቸውን ለማሳረፍ።”
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
ወይም “ነፍሴን።”
ወይም “ነፍሱን።”
ወደ 22.3 ሜትር ገደማ ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ቃል በቃል “በአይሁዳውያን ላይ እጁን በመዘርጋቱም።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።
ወይም “የአጻጻፍ ስልት።”
ወይም “ነፍሳቸውን።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።
ወይም “የደብዳቤው ቅጂ።”
ወይም “በሱሳ።”
ወይም “ቤተ መንግሥትም፤ ምሽግም።”
ወይም “የሱሳ።”
ቃል በቃል “ብርሃን።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
ወይም “በሱሳ።”
ወይም “ቤተ መንግሥት፤ ምሽግ።”
ወይም “በሱሳ።”
ወይም “ቤተ መንግሥት፤ ምሽግ።”
ወይም “በሱሳ።”
ወይም “ቤተ መንግሥት፤ ምሽግ።”
ወይም “በሱሳ።”
ወይም “በሱሳ።”
ወይም “በሱሳ።”
ወይም “በሱሳም።”
ወይም “ለነፍሳቸው ቆሙ።”
ወይም “በሱሳ።”
“ፑር” የሚለው ቃል “ዕጣ” የሚል ትርጉም አለው። ብዙ ቁጥርን ለማመልከት የሚሠራበት “ፑሪም” የሚለው ቃል በቅዱሱ የቀን መቁጠሪያ በ12ኛው ወር የሚከበረው የአይሁዳውያን በዓል መጠሪያ ሆኗል። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።
ወይም “ነፍሳቸውንና።”
ወይም “ከፍ ተደርጎ ይታይ የነበረ።”
ቃል በቃል “ሰላም የሚናገር።”