የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • nwt ኤፌሶን 1:1-6:24
  • ኤፌሶን

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ኤፌሶን
  • አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
ኤፌሶን

ለኤፌሶን ሰዎች የተጻፈ ደብዳቤ

1 በአምላክ ፈቃድ የክርስቶስ ኢየሱስ ሐዋርያ ከሆነው ከጳውሎስ፣ በኤፌሶን+ ላሉ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድነት ላላቸው ታማኝ የሆኑ ቅዱሳን፦

2 አባታችን ከሆነው አምላክና ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።

3 ከክርስቶስ ጋር ባለን አንድነት በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት* ሁሉ ስለባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይወደስ፤+ 4 በእሱ ፊት ፍቅር እንድናሳይ እንዲሁም ቅዱሳንና እንከን የለሽ ሆነን እንድንገኝ+ ዓለም ከመመሥረቱ* በፊት ከክርስቶስ ጋር አንድ እንድንሆን መርጦናልና። 5 ደግሞም እሱ እንደወደደና እንደ በጎ ፈቃዱ+ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት የገዛ ራሱ ልጆች አድርጎ ሊወስደን+ አስቀድሞ ወስኗል፤+ 6 ይኸውም በተወደደው ልጁ+ አማካኝነት በደግነት ለእኛ በሰጠው ክቡር በሆነው ጸጋው+ የተነሳ እንዲወደስ ነው። 7 በተትረፈረፈ ጸጋው መሠረት በልጁ ደም አማካኝነት ቤዛውን በመክፈሉ ነፃ ወጥተናል፤+ አዎ፣ ለበደላችን ይቅርታ አግኝተናል።+

8 ጸጋውንም ከጥበብና ከማስተዋል ሁሉ ጋር አትረፍርፎ ሰጥቶናል፤ 9 ይህን ያደረገው የፈቃዱን ቅዱስ ሚስጥር ለእኛ በማሳወቅ ነው።+ ይህ ሚስጥር ደግሞ እሱ ራሱ ካሰበው ዓላማው ጋር የሚስማማ ነው፤ 10 ዓላማውም በተወሰኑት ዘመናት ማብቂያ ላይ አንድ አስተዳደር ለማቋቋም ይኸውም ሁሉንም ነገሮች ማለትም በሰማያት የሚሆኑ ነገሮችንና በምድር የሚሆኑ ነገሮችን በክርስቶስ አንድ ላይ ለመሰብሰብ ነው።+ አዎ፣ በእሱ አማካኝነት ሁሉም ነገሮች ይሰበሰባሉ፤ 11 እኛም ከእሱ ጋር አንድነት ያለን ሲሆን ወራሾች እንድንሆንም ተመርጠናል፤+ ምክንያቱም ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ ሁኔታ ሁሉንም ነገር በወሰነው መንገድ የሚያከናውነው እሱ ከዓላማው ጋር በሚስማማ ሁኔታ አስቀድሞ መርጦናል፤ 12 ይህም የሆነው በክርስቶስ ተስፋ በማድረግ የመጀመሪያ የሆንነው እኛ አምላክን ከፍ ከፍ እንድናደርግና እንድናወድስ ነው። 13 ይሁንና እናንተም የእውነትን ቃል ማለትም ስለ መዳናችሁ የሚገልጸውን ምሥራች ከሰማችሁ በኋላ በእሱ ተስፋ አድርጋችኋል። ካመናችሁ በኋላ በእሱ አማካኝነት፣ ቃል በተገባው መንፈስ ቅዱስ ታትማችኋል፤+ 14 ይህም ለአምላክ ታላቅ ምስጋና ያስገኝ ዘንድ የራሱ ንብረት+ የሆኑትን በቤዛ+ አማካኝነት ነፃ ለማውጣት ለውርሻችን አስቀድሞ የተሰጠ ማረጋገጫ* ነው።+

15 ስለዚህ በጌታ ኢየሱስ ላይ ስላላችሁ እምነት እንዲሁም ለቅዱሳን ሁሉ ስለምታሳዩት ፍቅር ከሰማሁበት ጊዜ አንስቶ 16 ስለ እናንተ ምስጋና ማቅረቤን አላቋረጥኩም። ወደፊትም ስለ እናንተ መጸለዬን እቀጥላለሁ፤ 17 የክብር አባት የሆነው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ስለ እሱ ትክክለኛ እውቀት ስትቀስሙ የጥበብ መንፈስ እንዲሰጣችሁና እሱ የሚገልጣቸውን ነገሮች መረዳት እንድትችሉ እጸልያለሁ።+ 18 የልባችሁ ዓይኖች እንዲበሩ አድርጓል፤ ይህን ያደረገው ለምን ዓይነት ተስፋ እንደጠራችሁ እንድታውቁ፣ ለቅዱሳን ውርሻ አድርጎ የሚሰጠው ታላቅ ብልጽግና ምን እንደሆነ እንድትረዱ+ 19 እንዲሁም ታላቅ ኃይሉ ለእኛ ለምናምነው ምን ያህል የላቀ እንደሆነ እንድታውቁ ነው።+ የዚህ ኃይል ታላቅነት፣ እጅግ ከፍተኛ የሆነው ብርታቱ በሚያከናውነው ሥራ ታይቷል፤ 20 ክርስቶስን ከሞት ባስነሳውና በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ባስቀመጠው+ ጊዜ ይህን ኃይሉን ተጠቅሟል፤ 21 በዚህ ሥርዓት* ብቻ ሳይሆን በሚመጣውም ጭምር ከየትኛውም መስተዳድር፣ ሥልጣን፣ ኃይልና ጌትነት እንዲሁም ከተሰየመው ከየትኛውም ስም በላይ እጅግ የላቀ ቦታ ሰጥቶታል።+ 22 በተጨማሪም ሁሉንም ነገር ከእግሩ በታች አስገዛለት፤+ ከጉባኤው ጋር በተያያዘም በሁሉ ነገር ላይ ራስ አደረገው፤+ 23 ጉባኤው የእሱ አካል+ ከመሆኑም በላይ በእሱ የተሞላ ነው፤ እሱ ደግሞ ሁሉንም ነገር በሁሉ የሚሞላ ነው።

2 በተጨማሪም፣ እናንተ በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ምክንያት ሙታን የነበራችሁ ቢሆንም አምላክ ሕያው አድርጓችኋል፤+ 2 በዚያን ጊዜ የዚህን ዓለም ሥርዓት* ተከትላችሁ፣+ የአየሩ ሥልጣን ገዢ+ በሚፈልገው መንገድ ትመላለሱ ነበር፤ ይህም አየር በማይታዘዙት ልጆች ላይ አሁን ተጽዕኖ እያሳደረ ያለ መንፈስ ነው።+ 3 አዎ፣ እኛ ሁላችን በአንድ ወቅት የሥጋችንንና የሐሳባችንን ፈቃድ እየፈጸምን+ ከሥጋችን ፍላጎት ጋር ተስማምተን በመካከላቸው እንኖር ነበር፤+ እንደ ሌሎቹ ሁሉ እኛም በተፈጥሯችን የቁጣ ልጆች ነበርን።+ 4 ሆኖም አምላክ ምሕረቱ ብዙ ነው፤+ እኛን ከወደደበት ታላቅ ፍቅሩ የተነሳ+ 5 በበደላችን ሙታን በነበርንበት ጊዜም እንኳ ሕያዋን አድርጎ ከክርስቶስ ጋር አንድ አደረገን፤+ እንደ እውነቱ ከሆነ የዳናችሁት በጸጋ ነው። 6 ደግሞም ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድነት ስላለን ከእሱ ጋር አስነሳን፤ እንዲሁም ከእሱ ጋር በሰማያዊ ስፍራ አስቀመጠን፤+ 7 ይህን ያደረገው ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድነት ላለን ለእኛ በቸርነቱ* የገለጠውን ወደር የሌለውን የጸጋውን ብልጽግና በመጪዎቹ ሥርዓቶች* ያሳይ ዘንድ ነው።

8 እናንተ የዳናችሁት በእምነት አማካኝነት በዚህ ጸጋ ነው፤+ ይህም እናንተ በራሳችሁ ያገኛችሁት አይደለም፤ ይልቁንም የአምላክ ስጦታ ነው። 9 ማንም ሰው የሚኩራራበት ምክንያት እንዳይኖር ይህ በሥራ የሚገኝ አይደለም።+ 10 እኛ የአምላክ የእጁ ሥራዎች ነን፤ ደግሞም አምላክ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር ባለን አንድነት+ የፈጠረን፣+ እኛ እንድንሠራቸው አስቀድሞ ያዘጋጀልንን መልካም ሥራዎች እንድንሠራ ነው።

11 ስለዚህ በሰው እጅ በሥጋ “የተገረዙት፣” በአንድ ወቅት በትውልድ አሕዛብ የነበራችሁትን እናንተን “ያልተገረዙ” ይሏችሁ እንደነበር አስታውሱ። 12 በዚያን ጊዜ ከእስራኤል ብሔር ተገልላችሁና ለተስፋው ቃል ኪዳኖች+ ባዕዳን ሆናችሁ በዓለም ውስጥ ያለተስፋና ያለአምላክ እንዲሁም ያለክርስቶስ ትኖሩ እንደነበረ አስታውሱ።+ 13 ሆኖም እናንተ በአንድ ወቅት ርቃችሁ የነበራችሁ አሁን ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድነት ያላችሁ ሆናችኋል፤ እንዲሁም በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል። 14 ሁለቱን ወገኖች አንድ ያደረገውና+ ይለያያቸው የነበረውን በመካከል ያለ ግድግዳ ያፈረሰው+ እሱ ሰላም አምጥቶልናልና።+ 15 ሁለቱን ወገኖች ከራሱ ጋር አንድነት እንዲኖራቸው በማድረግ አንድ አዲስ ሰው መፍጠርና+ ሰላም ማስፈን ይችል ዘንድ በሥጋው አማካኝነት ጠላትነትን ይኸውም ትእዛዛትንና ድንጋጌዎችን የያዘውን ሕግ አስወገደ፤ 16 እንዲሁም ይህን ያደረገው በመከራው እንጨት*+ ሁለቱን ወገኖች አንድ አካል አድርጎ ከአምላክ ጋር ሙሉ በሙሉ ለማስታረቅ ነው፤ ምክንያቱም በገዛ አካሉ ጠላትነትን አስወግዷል።+ 17 እሱም መጥቶ ከአምላክ ርቃችሁ ለነበራችሁት ለእናንተም ሆነ ወደ እሱ ቀርበው ለነበሩት የሰላምን ምሥራች አወጀ፤ 18 ምክንያቱም እኛ፣ የሁለቱም ወገን ሕዝቦች በእሱ አማካኝነት በአንድ መንፈስ ወደ አብ በነፃነት መቅረብ እንችላለን።

19 ስለዚህ እናንተ ከዚህ በኋላ እንግዶችና ባዕዳን አይደላችሁም፤+ ከዚህ ይልቅ ከቅዱሳን ጋር የአንድ አገር ዜጎችና+ የአምላክ ቤተሰብ አባላት ናችሁ፤+ 20 እንዲሁም በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ተገንብታችኋል፤+ ዋናው የመሠረት ድንጋይ* ክርስቶስ ኢየሱስ ራሱ ነው።+ 21 ሕንጻው በሙሉ ከክርስቶስ ጋር አንድ ላይ በመሆን ልዩ ልዩ ክፍሎቹ ስምም ሆነው እየተገጣጠሙ+ የይሖዋ* ቅዱስ ቤተ መቅደስ ለመሆን በማደግ ላይ ነው።+ 22 እናንተም ከእሱ ጋር ባላችሁ አንድነት አምላክ በመንፈስ የሚኖርበት ቦታ ለመሆን አንድ ላይ እየተገነባችሁ ነው።+

3 በዚህ ምክንያት እኔ ጳውሎስ ከአሕዛብ ወገን ለሆናችሁት ለእናንተ ስል የክርስቶስ ኢየሱስ እስረኛ ሆኛለሁ።+ 2 ለእናንተ ጥቅም ሲባል ስለተሰጠኝ የአምላክ ጸጋ መጋቢነት+ በእርግጥ ሰምታችኋል፤ 3 ቀደም ሲል በአጭሩ እንደጻፍኩት ቅዱሱ ሚስጥር ተገልጦልኛል። 4 በመሆኑም ይህን ስታነቡ ስለ ክርስቶስ ቅዱስ ሚስጥር+ ያለኝን ግንዛቤ መረዳት ትችላላችሁ። 5 ይህ ሚስጥር አሁን ለቅዱሳን ሐዋርያትና ነቢያት በመንፈስ እንደተገለጠው ባለፉት ትውልዶች ለነበሩ የሰው ልጆች አልተገለጠም ነበር።+ 6 ሚስጥሩ ይህ ነው፦ ከአሕዛብ ወገን የሆኑ ሰዎች ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ በመሆን በምሥራቹ አማካኝነት አብረው ወራሾች፣ የአንድ አካል ክፍሎችና+ ከእኛ ጋር የተስፋው ተካፋዮች ይሆናሉ። 7 አምላክ የኃይሉ መግለጫ አድርጎ በሰጠኝ ነፃ ስጦታ ይኸውም በጸጋው አማካኝነት የዚህ ሚስጥር አገልጋይ ሆኛለሁ።+

8 ከቅዱሳን ሁሉ ለማንስ+ ለእኔ ይህ ጸጋ ተሰጠኝ፤+ ይህም ሊደረስበት ስለማይችለው የክርስቶስ ብልጽግና የሚገልጸውን ምሥራች ለአሕዛብ እንዳውጅ 9 እንዲሁም ሁሉን ነገር የፈጠረው አምላክ ለብዙ ዘመናት ሰውሮት የቆየው ቅዱሱ ሚስጥር ሥራ ላይ የዋለበትን መንገድ ሰዎች ሁሉ እንዲያስተውሉ እረዳቸው ዘንድ ነው።+ 10 ይህ የሆነው በርካታ ገጽታዎች ያሉት የአምላክ ጥበብ በሰማያዊ ስፍራ ላሉት መስተዳድሮችና ባለሥልጣናት አሁን በጉባኤው አማካኝነት ግልጽ ይሆን ዘንድ ነው።+ 11 ይህም አምላክ ከጌታችን ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር በተያያዘ ባዘጋጀው ዘላለማዊ ዓላማ መሠረት ነው፤+ 12 በእሱም አማካኝነት ይህ የመናገር ነፃነት አለን፤ በክርስቶስ ላይ ባለን እምነት አማካኝነትም በልበ ሙሉነት ወደ አምላክ በነፃነት መቅረብ እንችላለን።+ 13 ስለዚህ ለእናንተ ስል እየደረሰብኝ ባለው መከራ የተነሳ ተስፋ እንዳትቆርጡ አደራ እላችኋለሁ፤ ይህ ለእናንተ ክብር ነውና።+

14 በዚህም ምክንያት በአብ ፊት ለመጸለይ እንበረከካለሁ፤ 15 በሰማይና በምድር ያለ እያንዳንዱ ቤተሰብ ስያሜውን ያገኘው ከእሱ ነው። 16 እሱ ታላቅ ክብር ያለው እንደመሆኑ መጠን ውስጣዊውን ሰውነታችሁን የሚያጠነክር ኃይል+ በመንፈሱ አማካኝነት እንዲሰጣችሁ እጸልያለሁ፤ 17 ደግሞም በእምነታችሁ አማካኝነት ክርስቶስ ከፍቅር+ ጋር በልባችሁ ውስጥ እንዲያድር እጸልያለሁ። ሥር እንድትሰዱና+ በመሠረቱ ላይ እንድትታነጹ+ ያስችላችሁ ዘንድ እለምናለሁ፤ 18 ይህም ስፋቱ፣ ርዝመቱ፣ ከፍታውና ጥልቀቱ ምን ያህል እንደሆነ ከቅዱሳን ሁሉ ጋር በሚገባ መረዳት እንድትችሉ 19 እንዲሁም አምላክ በሚሰጠው ሙላት ሁሉ ትሞሉ ዘንድ ከእውቀት በላይ የሆነውን የክርስቶስ ፍቅር እንድታውቁ ነው።+

20 እንግዲህ በእኛ ውስጥ ከሚሠራው ኃይሉ ጋር በሚስማማ ሁኔታ፣+ ከምንጠይቀው ወይም ከምናስበው ሁሉ በላይ እጅግ አብልጦ ማድረግ ለሚችለው+ 21 ለእሱ በጉባኤው አማካኝነትና በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት በትውልዶች ሁሉ ለዘላለም ክብር ይሁን። አሜን።

4 እንግዲህ በጌታ እስረኛ የሆንኩ+ እኔ ከተጠራችሁበት ጥሪ ጋር በሚስማማ ሁኔታ ትመላለሱ ዘንድ እለምናችኋለሁ፤+ 2 በፍጹም ትሕትናና+ ገርነት፣ በትዕግሥት+ እንዲሁም እርስ በርሳችሁ በፍቅር በመቻቻል ኑሩ፤+ 3 አንድ ላይ በሚያስተሳስረው የሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ልባዊ ጥረት አድርጉ።+ 4 እናንተ የተጠራችሁበት አንድ ተስፋ+ እንዳለ ሁሉ አንድ አካልና+ አንድ መንፈስ+ አለ፤ 5 አንድ ጌታ፣+ አንድ እምነት፣ አንድ ጥምቀት አለ፤ 6 ደግሞም ከሁሉ በላይ የሆነ፣ በሁሉም አማካኝነት የሚሠራና በሁሉም ላይ የሚሠራ የሁሉም አባት የሆነ አንድ አምላክ አለ።

7 ደግሞም ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጥቶናል፤ ይህን የተቀበልነው ክርስቶስ ነፃ ስጦታውን ባከፋፈለን መሠረት ነው።+ 8 እንዲህ ይላልና፦ “ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮኞችን ወሰደ፤ ሰዎችንም ስጦታ አድርጎ ሰጠ።”+ 9 ታዲያ “ወደ ላይ ወጣ” የሚለው አነጋገር ምን ማለት ነው? ወደ ታች ይኸውም ወደ ምድርም ወርዷል ማለት ነው። 10 ሁሉንም ነገር ወደ ሙላት ያደርስ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ+ የወጣው+ ያው ወደ ታች የወረደው ራሱ ነው።

11 እንዲሁም አንዳንዶቹን ሐዋርያት፣+ አንዳንዶቹን ነቢያት፣+ አንዳንዶቹን ወንጌላውያን፣*+ አንዳንዶቹን ደግሞ እረኞችና አስተማሪዎች+ አድርጎ ሰጠ፤ 12 ይህን ያደረገው ቅዱሳንን እንዲያስተካክሉ፣* ሌሎችን እንዲያገለግሉና የክርስቶስን አካል* እንዲገነቡ ነው፤+ 13 ይህም ሁላችንም በእምነትና ስለ አምላክ ልጅ ትክክለኛ እውቀት በመቅሰም ወደሚገኘው አንድነት እንዲሁም ሙሉ ሰው ወደ መሆን*+ ይኸውም እንደ ክርስቶስ የተሟላ የጉልምስና ደረጃ ላይ እስክንደርስ ድረስ ነው። 14 በመሆኑም ከእንግዲህ ሕፃናት መሆን የለብንም፤ በማዕበል የምንነዳ ይመስል በማንኛውም የትምህርት ነፋስ፣+ በሰዎች የማታለያ ዘዴና በተንኮል በተወጠነ አሳሳች ሐሳብ የምንንገዋለልና ወዲያና ወዲህ የምንል መሆን የለብንም። 15 ከዚህ ይልቅ እውነትን በመናገር በሁሉም ነገር ወደ እሱ ይኸውም የአካሉ ራስ ወደሆነው ወደ ክርስቶስ+ በፍቅር እንደግ። 16 በእሱ አማካኝነት የአካል ክፍሎች ሁሉ+ አስፈላጊ የሆነውን ነገር በሚያሟላው በእያንዳንዱ መገጣጠሚያ አማካኝነት እርስ በርስ ተስማምተው ተገጣጥመዋል። እያንዳንዱ የአካል ክፍል በአግባቡ ሥራውን ማከናወኑ አካሉ ራሱን በፍቅር እያነጸ እንዲያድግ አስተዋጽኦ ያበረክታል።+

17 ስለዚህ አሕዛብ በአእምሯቸው ከንቱነት*+ እንደሚመላለሱ እናንተም ከእንግዲህ እንዳትመላለሱ በጌታ እናገራለሁ እንዲሁም እመሠክራለሁ።+ 18 እነሱ በውስጣቸው ካለው ድንቁርናና ከልባቸው መደንደን የተነሳ አእምሯቸው ጨልሟል፤ እንዲሁም ከአምላክ ከሚገኘው ሕይወት ርቀዋል። 19 የሥነ ምግባር ስሜታቸው ስለደነዘዘ በስግብግብነት ማንኛውንም ዓይነት ርኩሰት ለመፈጸም ራሳቸውን ማንአለብኝነት ለሚንጸባረቅበት ድርጊት*+ አሳልፈው ሰጥተዋል።

20 እናንተ ግን ክርስቶስ እንዲህ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ፤ 21 ይህ ሊሆን የሚችለው በእርግጥ ኢየሱስ ካስተማረው እውነት ጋር በሚስማማ መንገድ እሱን ከሰማችሁና ከእሱ ከተማራችሁ ነው። 22 ከቀድሞ አኗኗራችሁ ጋር የሚስማማውንና አታላይ በሆነው ምኞቱ እየተበላሸ የሚሄደውን+ አሮጌውን ስብዕናችሁን* አውልቃችሁ እንድትጥሉ+ ተምራችኋል። 23 ደግሞም አእምሯችሁን የሚያሠራው ኃይል* እየታደሰ ይሂድ፤+ 24 እንዲሁም እንደ አምላክ ፈቃድ የተፈጠረውንና ከእውነተኛ ጽድቅና ታማኝነት ጋር የሚስማማውን አዲሱን ስብዕና* መልበስ ይኖርባችኋል።+

25 ስለዚህ አሁን አታላይነትን ስላስወገዳችሁ እያንዳንዳችሁ ከባልንጀራችሁ* ጋር እውነትን ተነጋገሩ፤+ ምክንያቱም ሁላችንም የአንድ አካል ክፍሎች ነን።+ 26 ተቆጡ፤ ሆኖም ኃጢአት አትሥሩ፤+ ተቆጥታችሁ እያለ ፀሐይ አይጥለቅባችሁ፤+ 27 ዲያብሎስ አጋጣሚ እንዲያገኝ አታድርጉ።*+ 28 የሚሰርቅ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ፤ ከዚህ ይልቅ ለተቸገረ ሰው የሚያካፍለው ነገር እንዲኖረው በእጆቹ መልካም ተግባር እያከናወነ በትጋት ይሥራ።+ 29 እንደ አስፈላጊነቱ ሌሎችን የሚያንጽና ሰሚዎቹን ሊጠቅም የሚችል መልካም ቃል ብቻ+ እንጂ የበሰበሰ ቃል ከቶ ከአፋችሁ አይውጣ።+ 30 በተጨማሪም በቤዛው ነፃ ለምትወጡበት+ ቀን የታተማችሁበትን+ የአምላክን ቅዱስ መንፈስ አታሳዝኑ።+

31 የመረረ ጥላቻ፣+ ቁጣ፣ ንዴት፣ ጩኸትና ስድብ ሁሉ+ እንዲሁም ክፋት ሁሉ ከእናንተ መካከል ይወገድ።+ 32 ይልቁንም አንዳችሁ ለሌላው ደጎችና ከአንጀት የምትራሩ ሁኑ፤+ አምላክ በክርስቶስ አማካኝነት በነፃ ይቅር እንዳላችሁ ሁሉ እናንተም እርስ በርሳችሁ በነፃ ይቅር ተባባሉ።+

5 ስለዚህ የተወደዳችሁ ልጆቹ በመሆን አምላክን የምትመስሉ ሁኑ፤+ 2 ክርስቶስ እንደወደደንና*+ ጥሩ መዓዛ እንዳለው ሽታ ራሱን ስለ እኛ* መባና መሥዋዕት አድርጎ ለአምላክ እንደሰጠ+ ሁሉ እናንተም በፍቅር መመላለሳችሁን ቀጥሉ።+

3 ለቅዱሳን የማይገባ ስለሆነ የፆታ ብልግናና* ማንኛውም ዓይነት ርኩሰት ወይም ስግብግብነት በመካከላችሁ ከቶ አይነሳ፤+ 4 አሳፋሪ ምግባር፣ የማይረባ ንግግርም ሆነ ጸያፍ ቀልድ የማይገቡ ነገሮች ናቸው፤+ ከዚህ ይልቅ አምላክን የምታመሰግኑ ሁኑ።+ 5 እንደምታውቁትና በሚገባ እንደምትገነዘቡት ሴሰኛ*+ ወይም ርኩስ ወይም ስግብግብ+ ማለትም ጣዖት አምላኪ የሆነ ማንኛውም ሰው በክርስቶስና በአምላክ መንግሥት ምንም ውርሻ የለውም።+

6 በእነዚህ ነገሮች ምክንያት የአምላክ ቁጣ በማይታዘዙት ልጆች ላይ ስለሚመጣ ማንም በከንቱ ንግግር አያታላችሁ። 7 ስለዚህ ከእነዚህ ሰዎች ጋር አትተባበሩ፤ 8 እናንተ በአንድ ወቅት ጨለማ ውስጥ ነበራችሁና፤ አሁን ግን የጌታ በመሆናችሁ+ ብርሃን ውስጥ ናችሁ።+ የብርሃን ልጆች ሆናችሁ መመላለሳችሁን ቀጥሉ፤ 9 የብርሃን ፍሬ ሁሉንም ዓይነት ጥሩነት፣ ጽድቅና እውነት የያዘ ነውና።+ 10 በጌታ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ነገር ምን እንደሆነ ምንጊዜም መርምራችሁ አረጋግጡ፤+ 11 ፍሬ ቢስ በሆኑ የጨለማ ሥራዎች ከእነሱ ጋር መተባበራችሁን አቁሙ፤+ ይልቁንም አጋልጧቸው። 12 በድብቅ የሚፈጽሟቸው ነገሮች ለመናገር እንኳ የሚያሳፍሩ ናቸውና። 13 ደግሞም ተጋልጠው ይፋ የሚወጡት ነገሮች ሁሉ እንዲገለጡ የሚደረገው በብርሃን ነው፤ ስለዚህ የተጋለጡት ነገሮች በሙሉ ብርሃን ይሆናሉ። 14 በመሆኑም እንዲህ ተብሏል፦ “አንተ እንቅልፋም፣ ንቃ፤ ከሞትም ተነሳ፤+ ክርስቶስ በአንተ ላይ ያበራል።”+

15 ስለዚህ የምትመላለሱት ጥበብ እንደጎደላቸው ሳይሆን እንደ ጥበበኛ ሰዎች መሆኑን ምንጊዜም በጥንቃቄ አስተውሉ፤ 16 ቀኖቹ ክፉዎች ስለሆኑ ጊዜያችሁን በተሻለ መንገድ ተጠቀሙበት።*+ 17 ከዚህ የተነሳ የይሖዋ* ፈቃድ ምን እንደሆነ አስተውሉ እንጂ የማመዛዘን ችሎታ የጎደላችሁ አትሁኑ።+ 18 በተጨማሪም መረን ለለቀቀ ሕይወት* ስለሚዳርጋችሁ በወይን ጠጅ አትስከሩ፤+ ከዚህ ይልቅ በመንፈስ መሞላታችሁን ቀጥሉ። 19 በመዝሙርና በውዳሴ እንዲሁም በመንፈሳዊ ዝማሬ እርስ በርሳችሁ* ተነጋገሩ፤ በልባችሁም ለይሖዋ* የምስጋና መዝሙር ዘምሩ፤+ 20 በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም+ ስለ ሁሉም ነገር አምላካችንን እና አባታችንን ሁልጊዜ አመስግኑ።+

21 ክርስቶስን በመፍራት አንዳችሁ ለሌላው ተገዙ።+ 22 ሚስቶች ለጌታ እንደሚገዙ ሁሉ ለባሎቻቸው ይገዙ፤+ 23 ምክንያቱም ክርስቶስ አካሉ ለሆነውና አዳኙ ለሆነለት ጉባኤ ራስ እንደሆነ+ ሁሉ ባልም የሚስቱ ራስ ነው።+ 24 ደግሞም ጉባኤው ለክርስቶስ እንደሚገዛ ሁሉ ሚስቶችም በሁሉም ነገር ለባሎቻቸው ይገዙ። 25 ባሎች ሆይ፣ ክርስቶስ ጉባኤውን እንደወደደና ራሱን ለጉባኤው አሳልፎ እንደሰጠ+ ሁሉ እናንተም ሚስቶቻችሁን መውደዳችሁን ቀጥሉ፤+ 26 እሱ ይህን ያደረገው ጉባኤውን በቃሉ አማካኝነት በውኃ አጥቦ በማንጻት ይቀድሰው ዘንድ ነው፤+ 27 ይህም ጉባኤውን ጉድፍ ወይም የቆዳ መጨማደድ ወይም እንዲህ ያሉ ጉድለቶች የማይገኙበት+ ቅዱስና እንከን የለሽ አድርጎ ውበቱን እንደጠበቀ ለራሱ ለማቅረብ ነው።+

28 በተመሳሳይም ባሎች ሚስቶቻቸውን እንደ ገዛ አካላቸው አድርገው ሊወዷቸው ይገባል። ሚስቱን የሚወድ ሰው ራሱን ይወዳል፤ 29 የገዛ አካሉን* የሚጠላ ማንም ሰው የለምና፤ ከዚህ ይልቅ ይመግበዋል እንዲሁም ይሳሳለታል፤ ክርስቶስም ለጉባኤው ያደረገው እንደዚሁ ነው፤ 30 ምክንያቱም እኛ የእሱ አካል ክፍሎች ነን።+ 31 “ከዚህ የተነሳ ሰው ከአባቱና ከእናቱ ይለያል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣበቃል፤* ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።”+ 32 ይህ ቅዱስ ሚስጥር+ ታላቅ ነው። እኔም እየተናገርኩ ያለሁት ስለ ክርስቶስና ስለ ጉባኤው ነው።+ 33 ይሁንና ከእናንተ እያንዳንዱ ራሱን እንደሚወድ ሁሉ ሚስቱንም ይውደድ፤+ በሌላ በኩል ደግሞ ሚስት ባሏን በጥልቅ ታክብር።+

6 ልጆች ሆይ፣ ከጌታ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ ለወላጆቻችሁ ታዘዙ፤+ ይህ የጽድቅ ተግባር ነውና። 2 “አባትህንና እናትህን አክብር”+ የሚለው የመጀመሪያው ትእዛዝ እንዲህ የሚል የተስፋ ቃል ይዟል፦ 3 “ይህም መልካም እንዲሆንልህና* ዕድሜህ በምድር ላይ እንዲረዝም ነው።” 4 አባቶች ሆይ፣ ልጆቻችሁን አታስመርሯቸው፤+ ከዚህ ይልቅ በይሖዋ* ተግሣጽና+ ምክር* አሳድጓቸው።+

5 እናንተ ባሪያዎች ሆይ፣ ለክርስቶስ እንደምትታዘዙ ሁሉ ለሰብዓዊ ጌቶቻችሁ ከልብ በመነጨ ቅንነት፣ በአክብሮትና በፍርሃት ታዘዙ፤+ 6 ሰዎችን ለማስደሰት+ እንዲሁ ለታይታ ሳይሆን እንደ ክርስቶስ ባሪያዎች የአምላክን ፈቃድ በሙሉ ነፍስ*+ በመፈጸም ታዘዟቸው። 7 ሰዎችን ሳይሆን ይሖዋን* እንደምታገለግሉ አድርጋችሁ በማሰብ በፈቃደኝነት አገልግሉ፤+ 8 ባሪያም ሆነ ነፃ ሰው፣ እያንዳንዱ ለሚያደርገው ማንኛውም መልካም ነገር ከይሖዋ* ወሮታ እንደሚቀበል ታውቃላችሁና።+ 9 እናንተም ጌቶች ሆይ፣ ለእነሱ እንዲሁ ዓይነት አመለካከት ይኑራችሁ፤ የእነሱም ሆነ የእናንተ ጌታ በሰማያት እንዳለና+ እሱ ደግሞ እንደማያዳላ ስለምታውቁ አታስፈራሯቸው።

10 በተረፈ ከጌታና ከታላቅ ብርታቱ ኃይል+ ማግኘታችሁን እንድትቀጥሉ አሳስባችኋለሁ። 11 የዲያብሎስን መሠሪ ዘዴዎች* መቋቋም እንድትችሉ ከአምላክ የሚገኘውን ሙሉ የጦር ትጥቅ ልበሱ፤+ 12 ምክንያቱም የምንታገለው+ ከደምና ከሥጋ ጋር ሳይሆን ከመንግሥታት፣ ከሥልጣናት፣ ይህን ጨለማ ከሚቆጣጠሩ የዓለም ገዢዎች እንዲሁም በሰማያዊ ስፍራ ካሉ ከክፉ መንፈሳዊ ኃይሎች ጋር ነው።+ 13 ስለሆነም ክፉው ቀን በሚመጣበት ጊዜ መቋቋም እንድትችሉና ሁሉንም ነገር ከፈጸማችሁ በኋላ ጸንታችሁ መቆም እንድትችሉ ከአምላክ የሚገኘውን ሙሉ የጦር ትጥቅ አንሱ።+

14 እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ቀበቶ ታጥቃችሁና+ የጽድቅን ጥሩር ለብሳችሁ+ ጸንታችሁ ቁሙ፤ 15 እንዲሁም የሰላምን ምሥራች ለማወጅ ዝግጁ በመሆን እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ።*+ 16 ከዚህ ሁሉ በተጨማሪ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች* ሁሉ ማምከን የምትችሉበትን ትልቅ የእምነት ጋሻ አንሱ።+ 17 በተጨማሪም የመዳንን የራስ ቁር አድርጉ፤+ እንዲሁም የመንፈስን ሰይፍ ይኸውም የአምላክን ቃል ያዙ፤+ 18 ከዚህም በተጨማሪ በሁሉም ዓይነት ጸሎትና+ ምልጃ በማንኛውም ጊዜ በመንፈስ መጸለያችሁን ቀጥሉ።+ ለዚህም ሲባል ዘወትር ንቁ ሁኑ፤ እንዲሁም ስለ ቅዱሳን ሁሉ ምልጃ አቅርቡ። 19 የምሥራቹን ቅዱስ ሚስጥር በድፍረት ለሌሎች ማሳወቅ እንድችል አፌን በምከፍትበት ጊዜ የምናገረው ቃል እንዲሰጠኝ ለእኔም ጸልዩልኝ፤+ 20 በሰንሰለት የታሰረ አምባሳደር ሆኜ እያገለገልኩ+ ያለሁት ለዚሁ ምሥራች ነው፤ ስለ ምሥራቹ የሚገባኝን ያህል በድፍረት መናገር እንድችል ጸልዩልኝ።

21 እንግዲህ ስለ እኔ እንዲሁም እያከናወንኩ ስላለሁት ነገር እናንተም እንድታውቁ የተወደደ ወንድማችንና በጌታ ታማኝ አገልጋይ የሆነው ቲኪቆስ+ ሁሉንም ነገር ይነግራችኋል።+ 22 በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንዳለን እንድታውቁና ልባችሁን እንዲያጽናና ለዚሁ ዓላማ ስል ወደ እናንተ እልከዋለሁ።

23 አባታችን ከሆነው አምላክና ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምና ፍቅር ከእምነት ጋር ለወንድሞች ይድረስ። 24 ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የማይከስም ፍቅር ካላቸው ሁሉ ጋር የአምላክ ጸጋ ይሁን።

ወይም “አምላክ በመንፈስ ቅዱሱ አማካኝነት በሰጠን በረከት።”

ይህ አባባል የአዳምንና የሔዋንን ዘሮች ያመለክታል።

ወይም “ቀብድ፤ ወደፊት ለሚመጣው ነገር ዋስትና (መያዣ)።”

ወይም “በዚህ ዘመን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “አካሄድ።”

ወይም “ሞገስ በማሳየት።”

ወይም “በመጪዎቹ ዘመናት።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “የመሠረቱ የማዕዘን ድንጋይ።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “የምሥራቹ አዋጅ ነጋሪዎች።”

ወይም “እንዲያሠለጥኑ።”

የክርስቶስን ተከታዮች ጉባኤ ያመለክታል።

ወይም “ወደ ጉልምስና።”

ወይም “ባዶነት።”

ወይም “እፍረተ ቢስነት ለሚንጸባረቅበት ምግባር።” ግሪክኛ፣ አሴልጊያ። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ቃል በቃል “ሰው።”

ወይም “አስተሳሰባችሁ።” ቃል በቃል “የአእምሯችሁ መንፈስ።”

ቃል በቃል “ሰው።”

“ባልንጀራ” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል የአንድን ሰው የቅርብ ጓደኛ ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም ሰው ሊያመለክት ይችላል።

ወይም “ዲያብሎስ ስፍራ እንዲያገኝ አትፍቀዱለት።”

“እንደወደዳችሁና” ማለትም ሊሆን ይችላል።

“ስለ እናንተ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ግሪክኛ፣ ፖርኒያ። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

የቃላት መፍቻው ላይ “የፆታ ብልግና” የሚለውን ተመልከት።

ወይም “ጊዜ ግዙ።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “ለሥርዓት አልበኝነት።”

“ከራሳችሁ ጋር” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ቃል በቃል “ሥጋውን።”

ወይም “ይኖራል።”

ወይም “እንዲሳካልህና።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “ትምህርት፤ መመሪያ።” ቃል በቃል “(የይሖዋን) አስተሳሰብ በመክተት።”

የቃላት መፍቻው ላይ “ነፍስ” የሚለውን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “ሴራዎች።”

ወይም “የሰላምን ምሥራች ለማወጅ ዝግጁ ሆናችሁ ቁሙ።”

ወይም “ተወንጫፊ መሣሪያዎች።”

    የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ ጽሑፎች (2011-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ