የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • nwt 1 ጴጥሮስ 1:1-5:14
  • 1 ጴጥሮስ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • 1 ጴጥሮስ
  • አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
1 ጴጥሮስ

የጴጥሮስ የመጀመሪያው ደብዳቤ

1 የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ከሆነው ከጴጥሮስ፤+ በጳንጦስ፣ በገላትያ፣ በቀጰዶቅያ፣+ በእስያና በቢቲኒያ ተበትነው ለሚገኙ፣ ጊዜያዊ ነዋሪዎች ለሆኑ የአምላክ ምርጦች፣ 2 ይኸውም አባት የሆነው አምላክ አስቀድሞ ባወቀው መሠረት ለተመረጡት+ ደግሞም ታዛዥ እንዲሆኑና በኢየሱስ ክርስቶስ ደም እንዲረጩ+ በመንፈስ ለተቀደሱት፦+

ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ።

3 የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይወደስ፤ እሱ በታላቅ ምሕረቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ+ አማካኝነት ለሕያው ተስፋ+ እንደ አዲስ ወልዶናልና፤+ 4 እንዲሁም ለማይበሰብስ፣ ለማይረክስና ለማይጠፋ ርስት ወልዶናል።+ ይህም በሰማይ ለእናንተ ተጠብቆላችኋል፤+ 5 እናንተንም አምላክ በዘመኑ መጨረሻ ለሚገለጠው መዳን በእምነት አማካኝነት በኃይሉ እየጠበቃችሁ ነው። 6 አሁን ለአጭር ጊዜ በልዩ ልዩ ፈተናዎች መጨነቃችሁ የግድ ቢሆንም በእነዚህ ሁሉ ነገሮች የተነሳ እጅግ እየተደሰታችሁ ነው፤+ 7 እነዚህ ፈተናዎች የሚደርሱባችሁ፣ በእሳት የተፈተነ ቢሆንም እንኳ ሊጠፋ ከሚችለው ወርቅ እጅግ የላቀ ዋጋ ያለውና ተፈትኖ* የተረጋገጠው እምነታችሁ+ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ ምስጋናን፣ ግርማንና ክብርን ያስገኝ ዘንድ ነው።+ 8 እሱን አይታችሁት ባታውቁም ትወዱታላችሁ። አሁን ባታዩትም እንኳ በእሱ ላይ እምነት እያሳያችሁና በቃላት ሊገለጽ በማይችል ታላቅ ደስታ እጅግ ሐሴት እያደረጋችሁ ነው፤ 9 ምክንያቱም የእምነታችሁ ግብ ላይ እንደምትደርሱ ይኸውም ራሳችሁን* እንደምታድኑ ታውቃላችሁ።+

10 ለእናንተ ስለሚሰጠው ጸጋ የተነበዩት ነቢያት ይህን መዳን በተመለከተ ትጋት የተሞላበት ምርምርና ጥልቅ ጥናት አካሂደዋል።+ 11 በውስጣቸው ያለው መንፈስ በክርስቶስ ላይ ስለሚደርሱት መከራዎችና+ ከዚያ በኋላ ስለሚመጣው ክብር አስቀድሞ ሲመሠክር ከክርስቶስ ጋር በተያያዘ ስለ የትኛው ጊዜ ወይም ወቅት እያመለከተ እንዳለ ይመረምሩ ነበር።+ 12 እነሱ ራሳቸውን እያገለገሉ እንዳልሆነ ተገልጦላቸው ነበር። ከዚህ ይልቅ ከሰማይ በተላከ መንፈስ ቅዱስ+ ምሥራቹን ባበሰሩላችሁ ሰዎች አማካኝነት ከተነገሯችሁ ነገሮች ጋር በተያያዘ እናንተን እያገለገሉ ነበር። መላእክትም እነዚህን ነገሮች ለማየት ይጓጓሉ።

13 በመሆኑም አእምሯችሁን ዝግጁ በማድረግ ለሥራ ታጠቁ፤+ የማስተዋል ስሜታችሁን በሚገባ ጠብቁ፤+ ተስፋችሁን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ በምታገኙት ጸጋ ላይ አድርጉ። 14 ታዛዥ ልጆች እንደመሆናችሁ መጠን ቀድሞ እውቀት ባልነበራችሁ ጊዜ ትከተሉት በነበረው ምኞት መሠረት መቀረጻችሁን አቁሙ፤ 15 ከዚህ ይልቅ የጠራችሁ ቅዱስ አምላክ፣ ቅዱስ እንደሆነ ሁሉ እናንተም በምግባራችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፤+ 16 “እኔ ቅዱስ ስለሆንኩ እናንተም ቅዱሳን ልትሆኑ ይገባል” ተብሎ ተጽፏልና።+

17 ደግሞም ምንም ሳያዳላ+ በእያንዳንዱ ላይ እንደ ሥራው የሚፈርደውን አባት የምትለምኑ ከሆነ ጊዜያዊ ነዋሪዎች ሆናችሁ በምትኖሩበት ዘመን ሁሉ አምላክን በመፍራት ኑሩ።+ 18 እናንተ ከቀድሞ አባቶቻችሁ ከወረሳችሁት* ከንቱ አኗኗር ነፃ የወጣችሁት*+ ሊበላሹ በሚችሉ ነገሮች ይኸውም በብር ወይም በወርቅ እንዳልሆነ ታውቃላችሁና። 19 ከዚህ ይልቅ ነፃ የወጣችሁት ነውርና እንከን እንደሌለበት በግ+ ደም ባለ ውድ ደም+ ይኸውም በክርስቶስ ደም ነው።+ 20 እርግጥ እሱ አስቀድሞ የታወቀው፣ ዓለም ከመመሥረቱ* በፊት+ ነው፤ ሆኖም ለእናንተ ሲባል በዘመናት መጨረሻ ላይ እንዲገለጥ ተደረገ።+ 21 እናንተም እምነታችሁና ተስፋችሁ በአምላክ ላይ ይሆን ዘንድ እሱን ከሞት ባስነሳውና+ ክብር ባጎናጸፈው+ አምላክ ያመናችሁት በእሱ አማካኝነት ነው።+

22 እንግዲህ ለእውነት በመታዘዝ ራሳችሁን* ስላነጻችሁ ግብዝነት የሌለበት የወንድማማች መዋደድ አላችሁ፤+ በመሆኑም እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ከልብ ተዋደዱ።+ 23 ሕያው በሆነውና ጸንቶ በሚኖረው አምላክ ቃል አማካኝነት እንደ አዲስ የተወለዳችሁት+ በሚበሰብስ ሳይሆን በማይበሰብስ ዘር*+ ነው።+ 24 “ሥጋ ሁሉ* እንደ ሣር ነውና፤ ክብሩም ሁሉ እንደ ሜዳ አበባ ነው፤ ሣሩ ይጠወልጋል፤ አበባውም ይረግፋል፤ 25 የይሖዋ* ቃል ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።”+ ለእናንተም የተሰበከላችሁ ምሥራች ይህ “ቃል” ነው።+

2 እንግዲህ ክፋትን ሁሉ፣ ማታለልን፣ ግብዝነትን፣ ቅናትንና ሐሜትን ሁሉ አስወግዱ።+ 2 ገና እንደተወለዱ ሕፃናት+ በአምላክ ቃል ውስጥ ለሚገኘው ያልተበረዘ* ወተት ጉጉት አዳብሩ፤ ይህም በእሱ አማካኝነት ወደ መዳን ማደግ እንድትችሉ ነው፤+ 3 ጌታ ደግ መሆኑን ቀምሳችኋልና።*

4 በሰዎች ወደተናቀው+ በአምላክ ግን ወደተመረጠውና በፊቱ ክቡር ወደሆነው ወደ እሱ ይኸውም ሕያው ወደሆነው ድንጋይ+ በመምጣት 5 እናንተ ራሳችሁ ቅዱሳን ካህናት ለመሆን እንደ ሕያዋን ድንጋዮች መንፈሳዊ ቤት ለመሆን እየተገነባችሁ ነው፤+ ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መንፈሳዊ መሥዋዕት ማቅረብ ትችሉ ዘንድ ነው።+ 6 ምክንያቱም ቅዱስ መጽሐፉ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፣ በጽዮን የተመረጠ ድንጋይ ይኸውም ክቡር የሆነ የማዕዘን የመሠረት ድንጋይ አኖራለሁ፤ ደግሞም በእሱ የሚያምን ሁሉ ፈጽሞ አያፍርም።”+

7 በመሆኑም እናንተ አማኞች ስለሆናችሁ እሱ ለእናንተ ክቡር ነው፤ የማያምኑትን በተመለከተ ግን እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፦ “ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣+ እሱ የማዕዘን ራስ ድንጋይ* ሆነ”፤+ 8 እንዲሁም “የሚያደናቅፍ ድንጋይና የሚያሰናክል ዓለት ሆነ።”+ እነሱ የሚሰናከሉት ለቃሉ ስለማይታዘዙ ነው። እነዚህ ሰዎች የሚጠብቃቸው ነገር ይኸው ነው። 9 እናንተ ግን ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃኑ የጠራችሁን+ የእሱን “ድንቅ ባሕርያት* በየቦታው እንድታውጁ+ የተመረጠ ዘር፣ ንጉሣዊ ካህናት፣ ቅዱስ ብሔር፣+ ልዩ ንብረት እንዲሆን የተለየ ሕዝብ”+ ናችሁ። 10 እናንተ በአንድ ወቅት የአምላክ ሕዝብ አልነበራችሁም፤ አሁን ግን የአምላክ ሕዝብ ናችሁ፤+ ቀደም ሲል ምሕረት አልተደረገላችሁም ነበር፤ አሁን ግን ምሕረት አግኝታችኋል።+

11 የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ የባዕድ አገር ሰዎችና ጊዜያዊ ነዋሪዎች+ እንደመሆናችሁ መጠን እናንተን ከሚዋጉት* ሥጋዊ ፍላጎቶች+ ምንጊዜም እንድትርቁ አሳስባችኋለሁ።+ 12 ክፉ አድራጊዎች እንደሆናችሁ አድርገው ሲከሷችሁ መልካም ሥራችሁን በዓይናቸው ማየት እንዲችሉ+ ብሎም አምላክ ለመመርመር በሚመጣበት ቀን እሱን እንዲያከብሩ በዓለም ባሉ ሰዎች መካከል መልካም ምግባር ይኑራችሁ።+

13 ለጌታ ብላችሁ ለሰብዓዊ ሥልጣን* ሁሉ ተገዙ፦+ የበላይ ስለሆነ ለንጉሥ ተገዙ፤+ 14 ደግሞም ክፉ አድራጊዎችን ለመቅጣት፣ መልካም የሚያደርጉትን ግን ለማመስገን በእሱ የተላኩ ስለሆኑ ለገዢዎች ተገዙ።+ 15 የአምላክ ፈቃድ፣ መልካም ነገር በማድረግ ከንቱ ንግግር የሚናገሩትን ምክንያታዊ ያልሆኑ ሰዎች አፍ ዝም እንድታሰኙ* ነውና።+ 16 እንደ ነፃ ሰዎች ኑሩ፤+ ነፃነታችሁን እንደ አምላክ ባሪያዎች+ ሆናችሁ ተጠቀሙበት እንጂ ለክፋት መሸፈኛ* አታድርጉት።+ 17 ሁሉንም ዓይነት ሰው አክብሩ፤+ ለመላው የወንድማማች ማኅበር ፍቅር ይኑራችሁ፤+ አምላክን ፍሩ፤+ ንጉሥን አክብሩ።+

18 አገልጋዮች ጥሩና ምክንያታዊ ለሆኑት ብቻ ሳይሆን በቀላሉ ለማይደሰቱ ጌቶቻቸውም እንኳ ተገቢ ፍርሃት በማሳየት ይገዙ።+ 19 አንድ ሰው በአምላክ ፊት ንጹሕ ሕሊና እንዲኖረው ሲል መከራን* ችሎ ቢያሳልፍና ግፍ ቢደርስበት ይህ ደስ የሚያሰኝ ነውና።+ 20 ኃጢአት በመሥራታችሁ የሚደርስባችሁን ዱላ ብትቋቋሙ ምን ጥቅም አለው?+ መልካም ነገር በማድረጋችሁ መከራ ሲደርስባችሁ ችላችሁ ብታሳልፉ ግን ይህ አምላክ ደስ የሚሰኝበት ነገር ነው።+

21 ደግሞም የተጠራችሁት በዚህ ጎዳና እንድትሄዱ ነው፤ ምክንያቱም ክርስቶስም እንኳ የእሱን ፈለግ በጥብቅ እንድትከተሉ አርዓያ ትቶላችሁ+ ስለ እናንተ መከራ ተቀብሏል።+ 22 እሱ ምንም ኃጢአት አልሠራም፤+ በአንደበቱም የማታለያ ቃል አልተገኘም።+ 23 ሲሰድቡት+ መልሶ አልተሳደበም።+ መከራ ሲደርስበት+ አልዛተም፤ ከዚህ ይልቅ በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን በአደራ ሰጠ።+ 24 ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር እሱ ራሱ በገዛ አካሉ ኃጢአታችንን በእንጨት* ላይ+ ተሸከመ።+ ደግሞም “በእሱ ቁስል እናንተ ተፈወሳችሁ።”+ 25 እናንተ እንደባዘኑ በጎች ነበራችሁና፤+ አሁን ግን ወደ ነፍሳችሁ* እረኛና+ ጠባቂ* ተመልሳችኋል።

3 በተመሳሳይም እናንተ ሚስቶች፣ ለቃሉ የማይታዘዙ ባሎች ካሉ ያለቃል በሚስቶቻቸው ምግባር እንዲማረኩ+ ለባሎቻችሁ ተገዙ፤+ 2 ሊማረኩ የሚችሉትም ንጹሕ ምግባራችሁንና+ የምታሳዩትን ጥልቅ አክብሮት ሲመለከቱ ነው። 3 ውበታችሁ በውጫዊ ነገሮች በማጌጥ ይኸውም ሹሩባ በመሠራት፣ የወርቅ ጌጣጌጦች በማድረግ+ ወይም ያማረ ልብስ በመልበስ አይሁን፤ 4 ከዚህ ይልቅ ውበታችሁ የማይጠፋውን ጌጥ ይኸውም በአምላክ ፊት ከፍተኛ ግምት የሚሰጠውን የሰከነና ገር መንፈስ የተላበሰ+ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁን። 5 ተስፋቸውን በአምላክ ላይ የጣሉ በቀድሞ ጊዜ የነበሩ ቅዱሳን ሴቶች ራሳቸውን ለባሎቻቸው በማስገዛት በዚህ ዓይነት ሁኔታ ራሳቸውን ያስውቡ ነበርና፤ 6 ሣራም አብርሃምን ጌታዬ እያለች በመጥራት ትታዘዘው ነበር።+ እናንተም መልካም ማድረጋችሁን ከቀጠላችሁና በፍርሃት ካልተሸነፋችሁ+ ልጆቿ ናችሁ።

7 በተመሳሳይም እናንተ ባሎች ከእነሱ ጋር በእውቀት* አብራችሁ ኑሩ። እነሱም ከእናንተ ጋር የሕይወትን ጸጋ አብረው ስለሚወርሱ+ ጸሎታችሁ እንዳይታገድ ከእናንተ ይበልጥ እንደ ተሰባሪ ዕቃ የሆኑትን ሴቶችን አክብሯቸው።+

8 በመጨረሻም ሁላችሁም የአስተሳሰብ አንድነት* ይኑራችሁ፤+ የሌላውን ስሜት የምትረዱ ሁኑ፤ የወንድማማች መዋደድ ይኑራችሁ፤ ከአንጀት የምትራሩ ሁኑ፤+ ትሑታን ሁኑ።+ 9 ክፉን በክፉ+ ወይም ስድብን በስድብ አትመልሱ።+ ከዚህ ይልቅ ባርኩ፤+ የተጠራችሁት ይህን ጎዳና በመከተል በረከትን እንድትወርሱ ነውና።

10 ስለዚህ “ሕይወትን የሚወድና መልካም ቀኖችን ማየት የሚፈልግ ሰው በምላሱ ክፉ ነገር ከመናገር፣+ በከንፈሩም ከማታለል ይቆጠብ። 11 ክፉ ከሆነ ነገር ይራቅ፤+ መልካም የሆነውንም ያድርግ፤+ ሰላምን ይፈልግ፤ ይከተለውም።+ 12 የይሖዋ* ዓይኖች ጻድቃንን ይመለከታሉና፤ ጆሮዎቹም ምልጃቸውን ይሰማሉ፤+ የይሖዋ* ፊት ግን ክፉ ነገሮችን በሚያደርጉ ላይ ነው።”+

13 መልካም ነገር ለማድረግ ቀናተኞች ብትሆኑ ጉዳት የሚያደርስባችሁ ማን ነው?+ 14 ሆኖም ለጽድቅ ስትሉ መከራ ብትቀበሉ ደስተኞች ናችሁ።+ ይሁን እንጂ እነሱ የሚፈሩትን እናንተ አትፍሩ፤* ደግሞም አትሸበሩ።+ 15 ነገር ግን ክርስቶስን እንደ ጌታ አድርጋችሁ በልባችሁ ቀድሱት። እናንተ ስላላችሁ ተስፋ፣ ምክንያት እንድታቀርቡ ለሚጠይቃችሁ ሰው ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር ዝግጁ ሁኑ፤ ይህን ስታደርጉ ግን በገርነት* መንፈስና+ በጥልቅ አክብሮት ይሁን።+

16 ስለ እናንተ መጥፎ ነገር የሚናገሩ ሰዎች፣ የክርስቶስ ተከታዮች እንደመሆናችሁ መጠን በምታሳዩት መልካም ምግባር+ የተነሳ ስለ እናንተ በሚናገሩት በማንኛውም መጥፎ ነገር እንዲያፍሩ+ ጥሩ ሕሊና ይኑራችሁ።+ 17 ክፉ ነገር ሠርታችሁ መከራ ከምትቀበሉ+ ይልቅ የአምላክ ፈቃድ ከሆነ፣ መልካም ነገር ሠርታችሁ መከራ ብትቀበሉ ይሻላልና።+ 18 ጻድቅ የሆነው ክርስቶስ እንኳ ለዓመፀኞች+ ሲል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በመሞት+ ከኃጢአት ነፃ አውጥቷቸዋልና። ይህን ያደረገው እናንተን ወደ አምላክ ለመምራት ነው።+ ሥጋ ሆኖ ተገደለ፤+ ሆኖም መንፈስ ሆኖ ሕያው ሆነ።+ 19 በዚህ ሁኔታ እያለም ሄዶ በእስር ላሉት መናፍስት ሰበከላቸው፤*+ 20 እነዚህ መናፍስት ቀደም ሲል ማለትም በኖኅ ዘመን ጥቂት ሰዎች ይኸውም ስምንት ነፍሳት* በውኃው መካከል አልፈው የዳኑበት+ መርከብ እየተሠራ በነበረበት ጊዜ፣+ አምላክ በትዕግሥት እየጠበቀ ሳለ* ሳይታዘዙ የቀሩ ናቸው።+

21 አሁንም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነው ጥምቀት በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ አማካኝነት እናንተን እያዳናችሁ ነው። ጥምቀት የሰውነትን እድፍ የሚያስወግድ ሳይሆን ጥሩ ሕሊና ለማግኘት ለአምላክ የሚቀርብ ልመና ነው።+ 22 ኢየሱስ ወደ ሰማይ የሄደ ሲሆን አሁን በአምላክ ቀኝ ይገኛል፤+ እንዲሁም መላእክት፣ ሥልጣናትና ኃይላት እንዲገዙለት ተደርጓል።+

4 ክርስቶስ በሥጋ መከራ ስለተቀበለ+ እናንተም ይህንኑ አስተሳሰብ* ለማንጸባረቅ ዝግጁ ሁኑ፤ ምክንያቱም በሥጋ መከራ የተቀበለ ሰው ኃጢአት መሥራት አቁሟል፤+ 2 ይኸውም ከእንግዲህ ወዲህ በሥጋ በሚኖርበት ቀሪ ሕይወቱ ለሰው ፍላጎት ሳይሆን+ ለአምላክ ፈቃድ መኖር ይችል ዘንድ ነው።+ 3 ማንአለብኝነት የሚንጸባረቅባቸው ድርጊቶች በመፈጸም፣* ልቅ በሆነ የሥጋ ፍላጎት፣ ከልክ በላይ በመጠጣት፣ መረን በለቀቀ ድግስ፣ በመጠጥ ግብዣዎችና በአስጸያፊ የጣዖት አምልኮ በመካፈል የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት+ ያለፈው ጊዜ ይበቃል።+ 4 ይህን በመሰለው ያዘቀጠ ወራዳ ሕይወት ከእነሱ ጋር መሮጣችሁን ስለማትቀጥሉ ግራ ይጋባሉ፤ በመሆኑም ይሰድቧችኋል።+ 5 ይሁንና እነዚህ ሰዎች በሕያዋንና በሙታን ላይ ሊፈርድ ለተዘጋጀው መልስ ይሰጣሉ።+ 6 እንዲያውም ምሥራቹ ለሙታንም* የተሰበከው በዚህ ምክንያት ነው፤+ በመሆኑም ከሰው አመለካከት አንጻር በሥጋ የሚፈረድባቸው ቢሆንም ከአምላክ አመለካከት አንጻር ከመንፈስ ጋር በሚስማማ ሁኔታ መኖር ይችላሉ።

7 ሆኖም የሁሉም ነገር መጨረሻ ቀርቧል። ስለዚህ ጤናማ አስተሳሰብ ይኑራችሁ፤+ እንዲሁም በጸሎት ረገድ ንቁዎች ሁኑ።+ 8 ከሁሉም በላይ አንዳችሁ ለሌላው የጠለቀ ፍቅር ይኑራችሁ፤+ ምክንያቱም ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናል።+ 9 ሳታጉረመርሙ አንዳችሁ ለሌላው የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ አሳዩ።+ 10 በልዩ ልዩ መንገዶች የተገለጸው የአምላክ ጸጋ መልካም መጋቢዎች እንደመሆናችሁ መጠን፣ እያንዳንዳችሁ በተቀበላችሁት ስጦታ መሠረት የተሰጣችሁን ስጦታ አንዳችሁ ሌላውን ለማገልገል ተጠቀሙበት።+ 11 የሚናገር ማንም ቢኖር ከአምላክ የተቀበለውን ቃል እየተናገረ እንዳለ ሆኖ ይናገር፤ የሚያገለግል ማንም ቢኖር አምላክ በሚሰጠው ኃይል ተማምኖ ያገልግል፤+ ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት አምላክ በሁሉም ነገር እንዲከበር ነው።+ ክብርና ኃይል ለዘላለም የእሱ ነው። አሜን።

12 የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ እንደ እሳት ባሉ ከባድ ፈተናዎች ስትፈተኑ እንግዳ የሆነ ነገር እየደረሰባችሁ እንዳለ አድርጋችሁ በማሰብ አትደነቁ።+ 13 ከዚህ ይልቅ ክርስቶስ በክብሩ በሚገለጥበት ወቅት+ እናንተም እንድትደሰቱና እጅግ ሐሴት እንድታደርጉ እሱ የተቀበለው መከራ ተካፋዮች+ በመሆናችሁ ምንጊዜም ደስ ይበላችሁ።+ 14 ለክርስቶስ ስም ስትሉ ብትነቀፉ* ደስተኞች ናችሁ፤+ ምክንያቱም የክብር መንፈስ ይኸውም የአምላክ መንፈስ በእናንተ ላይ ያርፋል።

15 ይሁን እንጂ ከእናንተ መካከል ማንም ነፍሰ ገዳይ ወይም ሌባ ወይም ክፉ አድራጊ ወይም በሌሎች ሰዎች ጉዳይ ጣልቃ የሚገባ ሆኖ መከራ አይቀበል።+ 16 ይሁንና ማንም ሰው ክርስቲያን በመሆኑ መከራ ቢደርስበት ምንም ኀፍረት አይሰማው፤+ ይልቁንም ይህን ስም ተሸክሞ አምላክን ያክብር። 17 ፍርድ ከአምላክ ቤት+ የሚጀምርበት አስቀድሞ የተወሰነው ጊዜ ይህ ነውና። እንግዲህ ፍርድ በእኛ የሚጀምር ከሆነ+ ለአምላክ ምሥራች ታዛዥ ያልሆኑ ሰዎች መጨረሻ ምን ይሆን?+ 18 “እንግዲህ ጻድቅ በጭንቅ የሚድን ከሆነ ኃጢአተኛውና ፈሪሃ አምላክ የሌለው ሰውማ ምን ይውጠው ይሆን?”+ 19 ስለዚህ የአምላክን ፈቃድ በማድረጋቸው መከራ የሚደርስባቸው ሰዎች መልካም እያደረጉ ራሳቸውን* ታማኝ ለሆነው ፈጣሪ አደራ ይስጡ።+

5 ስለዚህ እኔም እንደ እነሱ ሽማግሌ እንዲሁም የክርስቶስ መከራ ምሥክርና ወደፊት የሚገለጠው ክብር ተካፋይ እንደመሆኔ መጠን+ በመካከላችሁ ያሉትን ሽማግሌዎች እንዲህ በማለት አጥብቄ እለምናለሁ፦* 2 የበላይ ተመልካቾች ሆናችሁ በማገልገል* በአደራ የተሰጣችሁን የአምላክን መንጋ እንደ እረኞች ሆናችሁ ተንከባከቡ፤+ ሥራችሁን በግዴታ ሳይሆን በአምላክ ፊት በፈቃደኝነት ተወጡ፤+ አግባብ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት በመመኘት ሳይሆን+ ለማገልገል በመጓጓት፣ 3 የአምላክ ንብረት በሆኑት ላይ ሥልጣናችሁን በማሳየት ሳይሆን+ ለመንጋው ምሳሌ በመሆን ጠብቁ።+ 4 የእረኞች አለቃ+ በሚገለጥበት ጊዜ የማይጠፋ የክብር አክሊል ትቀበላላችሁ።+

5 በተመሳሳይም እናንተ ወጣቶች፣ ለሽማግሌዎች ተገዙ።+ ይሁንና እርስ በርስ ባላችሁ ግንኙነት ሁላችሁም ትሕትናን ልበሱ፤* ምክንያቱም አምላክ ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።+

6 ስለዚህ በተገቢው ጊዜ ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው የአምላክ እጅ በታች ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤+ 7 የሚያስጨንቃችሁንም* ነገር ሁሉ በእሱ ላይ ጣሉ፤+ ምክንያቱም እሱ ስለ እናንተ ያስባል።+ 8 የማስተዋል ስሜታችሁን ጠብቁ፤ ንቁ ሆናችሁ ኑሩ!+ ጠላታችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ ይንጎራደዳል።+ 9 ሆኖም በዓለም ዙሪያ በመላው የወንድማማች ማኅበር ውስጥ ያሉት ወንድሞቻችሁ ተመሳሳይ መከራ እየደረሰባቸው እንዳለ ተገንዝባችሁ+ በእምነት ጸንታችሁ በመቆም ተቃወሙት።+ 10 ከክርስቶስ ጋር ባላችሁ አንድነት ወደ ዘላለማዊ ክብሩ የጠራችሁ+ የጸጋ ሁሉ አምላክ ለጥቂት ጊዜ መከራ ከተቀበላችሁ በኋላ እሱ ራሱ ሥልጠናችሁ እንዲጠናቀቅ ያደርጋል። ጽኑ እንድትሆኑ ያደርጋችኋል፤+ ደግሞም ያጠነክራችኋል፤+ አጽንቶም ያቆማችኋል። 11 ኃይል ለዘላለም የእሱ ይሁን። አሜን።

12 እኔ ታማኝ ወንድም አድርጌ በምቆጥረው በስልዋኖስ*+ አማካኝነት ይህን በአጭሩ ጽፌላችኋለሁ፤ የጻፍኩላችሁም እናንተን ለማበረታታትና ይህ የአምላክ እውነተኛ ጸጋ እንደሆነ አጥብቄ ለመመሥከር ነው። ይህን ጸጋ አጥብቃችሁ ያዙ። 13 እንደ እናንተ የተመረጠችው በባቢሎን የምትገኘው ሰላምታ ታቀርብላችኋለች፤ ልጄ ማርቆስም+ ሰላምታ ያቀርብላችኋል። 14 በፍቅር እርስ በርስ በመሳሳም ሰላምታ ተለዋወጡ።

ከክርስቶስ ጋር አንድነት ያላችሁ ሁሉ፣ ሰላም ለእናንተ ይሁን።

ወይም “ተጣርቶ።”

ወይም “ነፍሳችሁን።”

ወይም “በወግ ከወረሳችሁት።”

ቃል በቃል “የተዋጃችሁት።”

ይህ አባባል የአዳምንና የሔዋንን ዘሮች ያመለክታል።

ወይም “ነፍሳችሁን።”

ዘር የሚተካን ወይም ፍሬ የሚያፈራን ዘር ያመለክታል።

ወይም “ሰው ሁሉ።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “ንጹሕ።”

ወይም “አይታችኋልና።”

ቃል በቃል “የማዕዘኑ ራስ።” ማቴ 21:42 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።

ቃል በቃል “በጎነት።” የእሱን የሚደነቁ ባሕርያትና ተግባራት ያመለክታል።

ወይም “ነፍስን ከሚዋጉት።”

ወይም “ተቋም።”

ቃል በቃል “እንድትለጉሙ።”

ወይም “ሰበብ።”

ወይም “ሐዘንን፤ ሥቃይን።”

ወይም “በዛፍ።”

ወይም “ሕይወታችሁ።”

ቃል በቃል “የበላይ ተመልካች።”

ወይም “ለእነሱ አሳቢነት በማሳየት፤ ሁኔታቸውን በመረዳት።”

ወይም “የሐሳብ ስምምነት።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

“ዛቻቸውን አትፍሩ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

“ልዝብ፤ ለስላሳ፤ ሻካራ ያልሆነ” የሚል ትርጉም አለው።

ወይም “የፍርድ መልእክት አወጀ።”

ወይም “ሰዎች።”

ቃል በቃል “የአምላክ ትዕግሥት እየጠበቀ ሳለ።”

ወይም “ቆራጥ አቋም፤ ቁርጥ ውሳኔ።”

ወይም “እፍረተ ቢስነት በሚንጸባረቅበት ምግባር።” እዚህ ላይ የገባው አሴልጊያ የሚለው ግሪክኛ ቃል ብዙ ቁጥር ነው። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ይህ በመንፈሳዊ ሁኔታ ሙታን የሆኑትን ያመለክታል። ኤፌ 2:1ን ተመልከት።

ወይም “ብትሰደቡ።”

ወይም “ነፍሳቸውን።”

ወይም “እመክራለሁ።”

ወይም “መንጋውን በጥንቃቄ በመከታተል።”

ወይም “ታጠቁ።”

ወይም “የሚያሳስባችሁንም።”

ሲላስ ተብሎም ይጠራል።

    የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ ጽሑፎች (2011-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ