የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • nwt 2 ጴጥሮስ 1:1-3:18
  • 2 ጴጥሮስ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • 2 ጴጥሮስ
  • አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
2 ጴጥሮስ

የጴጥሮስ ሁለተኛው ደብዳቤ

1 የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያና ሐዋርያ ከሆነው ከስምዖን ጴጥሮስ፣ በአምላካችን ጽድቅ እንዲሁም በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጽድቅ አማካኝነት እኛ ያገኘነውን ዓይነት ክቡር እምነት ለተቀበሉ፦

2 ስለ አምላክና ስለ ጌታችን ኢየሱስ በምትቀስሙት ትክክለኛ እውቀት+ አማካኝነት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ። 3 መለኮታዊ ኃይሉ፣ በገዛ ክብሩና በጎነቱ ስለጠራን አምላክ ባገኘነው ትክክለኛ እውቀት+ ለአምላክ ያደርን ሆነን ለመኖር የሚረዱንን ነገሮች ሁሉ ሰጥቶናል።* 4 በእነዚህ ነገሮች አማካኝነት ክቡርና እጅግ ታላቅ የሆነ ተስፋ ሰጥቶናል፤*+ ይህን ያደረገውም የመጥፎ ምኞት* ውጤት ከሆነው ከዓለም ብልሹ ምግባር አምልጣችሁ፣ በዚህ ተስፋ አማካኝነት ከመለኮታዊ ባሕርይ ተካፋዮች እንድትሆኑ ነው።+

5 በመሆኑም ልባዊ ጥረት በማድረግ+ በእምነታችሁ ላይ በጎነትን ጨምሩ፤+ በበጎነት ላይ እውቀትን፣+ 6 በእውቀት ላይ ራስን መግዛትን፣+ ራስን በመግዛት ላይ ጽናትን፣ በጽናት ላይ ለአምላክ ማደርን፣+ 7 ለአምላክ በማደር ላይ ወንድማዊ መዋደድን፣ በወንድማዊ መዋደድ ላይ ፍቅርን ጨምሩ።+ 8 እነዚህ ነገሮች በውስጣችሁ ቢኖሩና ቢትረፈረፉ፣ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያላችሁን ትክክለኛ እውቀት ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች እንዳትሆኑ ይጠብቋችኋል።+

9 እነዚህ ነገሮች የሚጎድሉት ማንኛውም ሰው ብርሃን ላለማየት ዓይኑን የጨፈነ ዕውር ሰው* ነው፤+ ደግሞም ከቀድሞ ኃጢአቱ መንጻቱን ረስቷል።+ 10 በመሆኑም ወንድሞች፣ መጠራታችሁንና+ መመረጣችሁን አስተማማኝ ለማድረግ ከበፊቱ ይበልጥ ትጉ፤ እነዚህን ነገሮች የምታደርጉ ከሆነ ፈጽሞ አትወድቁምና።+ 11 እንዲያውም በእጅጉ ትባረካላችሁ፤ ጌታችንና አዳኛችን ወደሆነው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘላለማዊ መንግሥትም+ ትገባላችሁ።+

12 ስለዚህ ምንም እንኳ እነዚህን ነገሮች የምታውቁና በተማራችሁት እውነት ጸንታችሁ የቆማችሁ ብትሆኑም፣ ስለ እነዚህ ነገሮች ሁልጊዜ እናንተን ከማሳሰብ ወደኋላ አልልም። 13 በዚህ ድንኳን*+ እስካለሁ ድረስ እናንተን በማሳሰብ ማነቃቃት ተገቢ ይመስለኛል፤+ 14 ምክንያቱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በግልጽ እንዳሳወቀኝ ይህ ድንኳን የሚወገድበት ጊዜ እንደቀረበ አውቃለሁ።+ 15 እኔ ከሄድኩ በኋላ እነዚህን ነገሮች ማስታወስ* እንድትችሉ ሁልጊዜ አቅሜ የፈቀደውን ሁሉ አደርጋለሁ።

16 የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ኃይልና መገኘት ያሳወቅናችሁ በብልሃት የተፈጠረ ተረት ተከትለን ሳይሆን ግርማውን በገዛ ዓይናችን አይተን ነው።+ 17 ከግርማዊው ክብር “እኔ ራሴ በጣም የምደሰትበት፣ የምወደው ልጄ ይህ ነው”+ የሚል ቃል* ለእሱ በተነገረ ጊዜ ከአባታችንና ከአምላካችን ክብርና ሞገስ ተቀብሏል። 18 ከእሱ ጋር በቅዱሱ ተራራ በነበርንበት ጊዜ ይህ ቃል ከሰማይ ሲመጣ ሰምተናል።

19 በመሆኑም ትንቢታዊው ቃል ይበልጥ ተረጋግጦልናል፤ ጎህ እስኪቀድና የንጋት ኮከብ+ እስኪወጣ ድረስ በጨለማ ቦታ፣ በልባችሁ ውስጥ ለሚበራ መብራት+ የምትጠነቀቁትን ያህል ለትንቢታዊው ቃል ትኩረት መስጠታችሁ መልካም ነው። 20 በመጀመሪያ ደረጃ፣ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ያለው ትንቢት ሁሉ በሰው ሐሳብ ላይ የተመሠረተ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ። 21 መቼም ቢሆን ትንቢት በሰው ፈቃድ አልመጣምና፤+ ከዚህ ይልቅ ሰዎች ከአምላክ የተቀበሉትን ትንቢት በመንፈስ ቅዱስ ተገፋፍተው* ተናገሩ።+

2 ይሁን እንጂ በሕዝቡ መካከል ሐሰተኛ ነቢያት እንደነበሩ ሁሉ በእናንተም መካከል ሐሰተኛ አስተማሪዎች ይነሳሉ።+ እነዚህ ሰዎች ጥፋት የሚያስከትል ኑፋቄ በስውር ያስገባሉ፤ የዋጃቸውን+ ጌታ እንኳ ሳይቀር ክደው በራሳቸው ላይ ፈጣን ጥፋት ያመጣሉ። 2 በተጨማሪም ብዙዎች እነሱ በማንአለብኝነት የሚፈጽሙትን ድርጊት* ይፈጽማሉ፤+ በዚህም ምክንያት የእውነት መንገድ ይሰደባል።+ 3 እነዚህ ሐሰተኛ አስተማሪዎች አስመሳይ ቃላት በመናገር እናንተን በስግብግብነት ይበዘብዟችኋል። ሆኖም ከብዙ ዘመን በፊት የተበየነባቸው ፍርድ+ አይዘገይም፤ ጥፋት እንደሚደርስባቸውም ጥርጥር የለውም።*+

4 ደግሞም አምላክ ኃጢአት የሠሩትን መላእክት ከመቅጣት ወደኋላ አላለም፤+ ይልቁንም በድቅድቅ ጨለማ አስሮ* በማስቀመጥ ፍርዳቸውን እንዲጠባበቁ+ ወደ እንጦሮጦስ* ጣላቸው።+ 5 እንዲሁም የጽድቅ ሰባኪ የነበረውን ኖኅን+ ከሌሎች ሰባት ሰዎች ጋር አድኖ+ ፈሪሃ አምላክ ባልነበራቸው ሰዎች በተሞላው ዓለም ላይ የጥፋት ውኃ ባመጣ ጊዜ+ የጥንቱን ዓለም ከመቅጣት ወደኋላ አላለም።+ 6 ደግሞም ፈሪሃ አምላክ ለሌላቸው ሰዎች ለወደፊቱ ምሳሌ እንዲሆኑ+ የሰዶምና የገሞራ ከተሞችን አመድ በማድረግ ፈርዶባቸዋል።+ 7 ሆኖም ለሕግ የማይገዙ ሰዎች በማንአለብኝነት በሚፈጽሙት ድርጊት* እጅግ እየተሳቀቀ ይኖር የነበረውን ጻድቁን ሎጥን አድኖታል።+ 8 ይህ ጻድቅ ሰው ዕለት ተዕለት በመካከላቸው ሲኖር በሚያየውና በሚሰማው መረን የለቀቀ ድርጊታቸው ጻድቅ ነፍሱን* ያስጨንቅ ነበር። 9 በመሆኑም ይሖዋ፣* ለአምላክ ያደሩ ሰዎችን ከፈተና እንዴት እንደሚያድንና+ ዓመፀኞችን ደግሞ በፍርድ ቀን ለሚደርስባቸው ጥፋት እንዴት ጠብቆ እንደሚያቆይ ያውቃል።+ 10 በተለይ ደግሞ ሰዎችን ለማርከስ+ ሲሉ ከእነሱ ጋር የፆታ ብልግና ለመፈጸም የሚመኙትንና ሥልጣን ያላቸውን የሚንቁትን*+ ለፍርድ ጠብቆ ያቆያቸዋል።

ደፋሮችና በራሳቸው የሚመሩ ከመሆናቸውም በላይ የተከበሩትን ሲሳደቡ አይፈሩም። 11 ይሁንና መላእክት፣ ከእነሱ የላቀ ብርታትና ኃይል ያላቸው ቢሆንም ለይሖዋ* ካላቸው አክብሮት የተነሳ* ሐሰተኛ አስተማሪዎቹን በመስደብ አልነቀፏቸውም።+ 12 እነዚህ ሰዎች ግን ተይዘው ለመገደል እንደተወለዱ፣ በደመ ነፍስ እንደሚንቀሳቀሱ አእምሮ የሌላቸው እንስሳት ናቸው፤ በማያውቁት ነገር እየገቡ ይሳደባሉ።+ በሚከተሉት የጥፋት ጎዳና የተነሳ ለጥፋት ይዳረጋሉ። 13 በሠሩት ክፉ ድርጊት የተነሳ በራሳቸው ላይ ክፉ ነገር በማምጣት ብድራታቸውን ይቀበላሉ።

በጠራራ ፀሐይ የሥጋ ፍላጎታቸውን ማርካትን እንደ ደስታ ይቆጥሩታል።+ እነዚህ ሰዎች እንደ ቆሻሻና እድፍ ናቸው፤ ከእናንተ ጋር በግብዣ ላይ ሲገኙ አታላይ በሆኑ ትምህርቶቻቸው ሌሎችን በማሳት እጅግ ይደሰታሉ።+ 14 አመንዝራ ዓይን+ ያላቸው በመሆኑ ኃጢአት ከመሥራት መታቀብ አይችሉም፤ ጸንተው ያልቆሙትንም* ያማልላሉ። መስገብገብ የለመደ ልብ አላቸው። የተረገሙ ልጆች ናቸው። 15 ቀናውን መንገድ ትተው በተሳሳተ ጎዳና ሄደዋል። ለጥቅም ሲል ክፉ ድርጊት መፈጸም የመረጠውን የቢዖርን ልጅ የበለዓምን መንገድ ተከትለዋል።+ 16 በለዓም ግን ትክክለኛውን መመሪያ በመጣሱ ተወቅሷል።+ መናገር የማትችል አህያ እንደ ሰው ተናግራ የነቢዩን የእብደት አካሄድ ለመግታት ሞከረች።+

17 እነዚህ ሰዎች የደረቁ ምንጮችና በአውሎ ነፋስ የሚነዱ ደመናዎች ናቸው፤ ድቅድቅ ጨለማም ይጠብቃቸዋል።+ 18 በከንቱ ጉራ ይነዛሉ። በተሳሳተ ጎዳና ከሚመላለሱት መካከል በቅርቡ ያመለጡትን ሰዎች የሥጋ ምኞቶቻቸውን በመቀስቀስና+ ማንአለብኝነት የሚንጸባረቅበት ድርጊት በመፈጸም* ያማልሏቸዋል።+ 19 እነሱ ራሳቸው የመጥፎ ሥነ ምግባር ባሪያዎች ሆነው ሳሉ ነፃ ትወጣላችሁ እያሉ ተስፋ ይሰጧቸዋል፤+ ማንም ሰው በሌላ ሰው ከተሸነፈ የዚያ ሰው ባሪያ ይሆናልና።*+ 20 ስለ ጌታችንና አዳኛችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ባገኙት ትክክለኛ እውቀት አማካኝነት ከዓለም ርኩሰት ካመለጡ በኋላ+ ተመልሰው በዚሁ ነገር ከተጠመዱና ከተሸነፉ ከመጀመሪያው ይልቅ የኋለኛው ሁኔታቸው የከፋ እንደሚሆንባቸው ምንም ጥርጥር የለውም።+ 21 የጽድቅን መንገድ በትክክል ካወቁ በኋላ ከተሰጣቸው ቅዱስ ትእዛዝ ወደኋላ ከሚሉ ቀድሞውኑ ባያውቁት ይሻላቸው ነበር።+ 22 “ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል፤ የታጠበች አሳማም ተመልሳ ጭቃ ላይ ትንከባለላለች”+ የሚለው እውነተኛ ምሳሌ በእነሱ ላይ ተፈጽሟል።

3 የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ ይህ አሁን የምጽፍላችሁ ሁለተኛ ደብዳቤ ነው። በመጀመሪያው ደብዳቤዬ እንዳደረግሁት አሁንም ልጽፍላችሁ የተነሳሁት ማሳሰቢያ በመስጠት በትክክል ማሰብ እንድትችሉ ለማነቃቃት ሲሆን+ 2 ይህም ቀደም ሲል ቅዱሳን ነቢያት የተናገሩትን ቃል* እንዲሁም ጌታችንና አዳኛችን በሐዋርያት* አማካኝነት የሰጠውን ትእዛዝ እንድታስታውሱ ለመርዳት ነው። 3 ከሁሉ አስቀድሞ ይህን እወቁ፦ በመጨረሻዎቹ ቀናት የራሳቸውን ምኞት እየተከተሉ የሚያፌዙ ፌዘኞች ይመጣሉ።+ 4 እነዚህ ፌዘኞች “‘እገኛለሁ’ ያለው ታዲያ የት አለ?+ አባቶች በሞት ካንቀላፉበት ጊዜ ጀምሮ ሁሉም ነገር ከፍጥረት መጀመሪያ አንስቶ እንዳለ ይቀጥላል” ይላሉ።+

5 በጥንት ዘመን ሰማያት እንደነበሩ እንዲሁም ደረቁ ምድር በአምላክ ቃል ከውኃ በላይ ጸንቶ እንደቆመና በውኃ መካከል እንደነበረ የሚያረጋግጠውን ሐቅ ሆን ብለው ችላ ይላሉ።+ 6 በዚያ ጊዜ የነበረው ዓለም በእነዚህ ነገሮች ጠፍቷል። ይህም የሆነው መላዋ ምድር በውኃ በተጥለቀለቀች ጊዜ ነው።+ 7 ሆኖም በዚያው ቃል አሁን ያሉት ሰማያትም ሆኑ ምድር ለእሳትና ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች ለሚጠፉበት የፍርድ ቀን ተጠብቀው ይቆያሉ።+

8 የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ እናንተ ግን በይሖዋ* ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት፣ ሺህ ዓመት ደግሞ እንደ አንድ ቀን መሆኑን ልትዘነጉ አይገባም።+ 9 አንዳንድ ሰዎች እንደሚያስቡት ይሖዋ* የገባውን ቃል ለመፈጸም አይዘገይም፤+ ከዚህ ይልቅ እናንተን የታገሠው፣ ሁሉ ለንስሐ እንዲበቃ እንጂ ማንም እንዲጠፋ ስለማይፈልግ ነው።+ 10 ይሁንና የይሖዋ* ቀን+ እንደ ሌባ ይመጣል፤+ በዚያም ቀን ሰማያት በነጎድጓድ ድምፅ* ያልፋሉ፤+ ንጥረ ነገሮቹም በኃይለኛ ሙቀት ይቀልጣሉ፤ ምድርና በላይዋ የተሠሩ ነገሮችም ይጋለጣሉ።+

11 እነዚህ ሁሉ ነገሮች በዚህ ሁኔታ የሚቀልጡ ከሆነ ቅዱስ ሥነ ምግባር በመከተልና ለአምላክ ያደራችሁ መሆናችሁን የሚያሳዩ ተግባሮች በመፈጸም ምን ዓይነት ሰዎች መሆን እንዳለባችሁ ልታስቡበት ይገባል! 12 ሰማያት በእሳት ተቃጥለው የሚጠፉበትንና+ ንጥረ ነገሮቹም በኃይለኛ ሙቀት የሚቀልጡበትን የይሖዋን* ቀን መምጣት* እየጠበቃችሁና በአእምሯችሁ አቅርባችሁ እየተመለከታችሁ* ልትኖሩ ይገባል!+ 13 በሌላ በኩል ግን አምላክ በገባው ቃል መሠረት አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር እንጠባበቃለን፤+ በእነዚህም ውስጥ ጽድቅ ይሰፍናል።+

14 ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ እነዚህን ነገሮች እየተጠባበቃችሁ ስለሆነ በመጨረሻ በእሱ ፊት ቆሻሻና እድፍ ሳይኖርባችሁ በሰላም እንድትገኙ የተቻላችሁን ጥረት አድርጉ።+ 15 በተጨማሪም የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስ በተሰጠው ጥበብ እንደጻፈላችሁ የጌታችንን ትዕግሥት እንደ መዳን ቁጠሩት፤+ 16 እንዲያውም በሁሉም ደብዳቤዎቹ ላይ ስለ እነዚህ ነገሮች ጽፏል። ይሁንና በደብዳቤዎቹ ውስጥ ለመረዳት የሚከብዱ አንዳንድ ነገሮች አሉ፤ እውቀት የጎደላቸውና* የሚወላውሉ ሰዎች ሌሎቹን ቅዱሳን መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ ሁሉ እነዚህንም ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ።

17 ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ ይህን አስቀድማችሁ ስላወቃችሁ ሕግ የሚተላለፉ ሰዎች በሚፈጽሙት ስህተት ከእነሱ ጋር ተታልላችሁ እንዳትወሰዱና ጽኑ አቋማችሁ እንዳይናጋ ተጠንቀቁ።+ 18 ከዚህ ይልቅ በጌታችንና በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና እውቀት እድገት አድርጉ። አሁንም ሆነ ለዘላለም ለእሱ ክብር ይሁን። አሜን።

ወይም “በነፃ ሰጥቶናል።”

ወይም “በነፃ ሰጥቶናል።”

ወይም “የፍትወት።”

“በቅርብ ያለውን ብቻ የሚያይ፣ ዕውር ሰው” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ሥጋዊ አካሉን ያመለክታል።

ወይም “መጥቀስ።”

ቃል በቃል “ድምፅ።”

ቃል በቃል “ተነድተው።”

ወይም “የሚፈጽሙትን እፍረተ ቢስነት የሚንጸባረቅበት ምግባር።” እዚህ ላይ የገባው አሴልጊያ የሚለው ግሪክኛ ቃል ብዙ ቁጥር ነው። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ቃል በቃል “ጥፋታቸውም አያንቀላፋም።”

“ጉድጓድ ውስጥ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “እፍረተ ቢስነት የሚንጸባረቅበት ምግባር።” ግሪክኛ፣ አሴልጊያ። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “ጌትነትን የሚንቁትን።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “በይሖዋ ፊት።”

ወይም “ጸንተው ያልቆሙትን ነፍሳትም።”

ወይም “እፍረተ ቢስነት በሚንጸባረቅበት ድርጊት።” እዚህ ላይ የገባው አሴልጊያ የሚለው ግሪክኛ ቃል ብዙ ቁጥር ነው። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “ለተሸነፈለት ነገር ሁሉ ባሪያ ነውና።”

ወይም “የተነበዩአቸውን ነገሮች።”

ቃል በቃል “በሐዋርያዎቻችሁ።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “በፈጣን ድምፅ።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ቃል በቃል “መገኘት።”

ወይም “እየናፈቃችሁ።” ቃል በቃል “እያፋጠናችሁ።”

ወይም “ያልተማሩና።”

    የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ ጽሑፎች (2011-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ