የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • nwt ፊልጵስዩስ 1:1-4:23
  • ፊልጵስዩስ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ፊልጵስዩስ
  • አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
ፊልጵስዩስ

ለፊልጵስዩስ ሰዎች የተጻፈ ደብዳቤ

1 የክርስቶስ ኢየሱስ ባሪያዎች ከሆኑት ከጳውሎስና ከጢሞቴዎስ፣ ሽማግሌዎችንና የጉባኤ አገልጋዮችን+ ጨምሮ በፊልጵስዩስ+ ለሚገኙ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድነት ላላቸው ቅዱሳን ሁሉ፦

2 አባታችን ከሆነው አምላክና ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።

3 እናንተን ባስታወስኩ ቁጥር ሁልጊዜ አምላኬን አመሰግናለሁ፤ 4 ይህን የማደርገው ስለ እያንዳንዳችሁ ምልጃ ባቀረብኩ ጊዜ ሁሉ ነው። ደግሞም ምንጊዜም ምልጃ የማቀርበው በደስታ ነው፤+ 5 ምክንያቱም ምሥራቹን ከሰማችሁበት ከመጀመሪያው ቀን አንስቶ እስከዚህ ጊዜ ድረስ ለምሥራቹ አስተዋጽኦ* ስታደርጉ ቆይታችኋል። 6 በእናንተ መካከል መልካም ሥራ የጀመረው አምላክ፣ ሥራውን እስከ ክርስቶስ ኢየሱስ ቀን+ ድረስ ወደ ፍጻሜ እንደሚያመጣው እርግጠኛ ነኝ።+ 7 ስለ እናንተ ስለ ሁላችሁ እንዲህ ብዬ ማሰቤ ትክክል ነው፤ ምክንያቱም በእስራቴም+ ሆነ ለምሥራቹ ስሟገትና በሕግ የጸና እንዲሆን ለማድረግ ስጥር+ ከእኔ ጋር የጸጋው ተካፋዮች የሆናችሁት እናንተ በልቤ ውስጥ ናችሁ።

8 ክርስቶስ ኢየሱስ ባለው ዓይነት ጥልቅ ፍቅር እናንተ ሁላችሁም በጣም እንደምትናፍቁኝ አምላክ ምሥክሬ ነው። 9 ፍቅራችሁ ከአምላክ ፈቃድ ትክክለኛ እውቀትና+ ጥልቅ ግንዛቤ+ ጋር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንዲሄድ መጸለዬን እቀጥላለሁ፤+ 10 ደግሞም ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ በማወቅ+ እስከ ክርስቶስ ቀን ድረስ እንከን የማይገኝባችሁ እንድትሆኑና ሌሎችን እንዳታሰናክሉ+ 11 እንዲሁም ለአምላክ ክብርና ምስጋና በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የተትረፈረፈ የጽድቅ ፍሬ እንድታፈሩ እጸልያለሁ።+

12 እንግዲህ ወንድሞች፣ እኔ ያጋጠመኝ ሁኔታ ምሥራቹ ይበልጥ እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ እንዳደረገ እንድታውቁ እወዳለሁ፤ 13 የታሰርኩት+ የክርስቶስ አገልጋይ በመሆኔ የተነሳ እንደሆነ በንጉሠ ነገሥቱ የክብር ዘብ ሁሉና በሌሎች ሰዎች ሁሉ ዘንድ በይፋ ታውቋል።+ 14 ጌታን የሚያገለግሉ አብዛኞቹ ወንድሞች በእኔ መታሰር ምክንያት የልበ ሙሉነት ስሜት አድሮባቸው የአምላክን ቃል ያለፍርሃት ለመናገር ከቀድሞው የበለጠ ድፍረት እያሳዩ ነው።

15 እርግጥ፣ አንዳንዶች ክርስቶስን እየሰበኩ ያሉት በቅናትና በፉክክር መንፈስ ነው፤ ይሁንና ሌሎች ይህን እያደረጉ ያሉት በጥሩ ዓላማ ነው። 16 እነዚህ፣ እኔ ለምሥራቹ ለመሟገት+ እንደተሾምኩ ስለሚያውቁ ስለ ክርስቶስ የሚያውጁት ከፍቅር ተነሳስተው ነው፤ 17 እነዚያ ግን በእስራቴ ላይ ችግር ሊፈጥሩብኝ ስላሰቡ ይህን የሚያደርጉት በቅን ልቦና ሳይሆን በጥላቻ ተነሳስተው ነው። 18 ታዲያ ይህ ምን አስከተለ? በማስመሰልም ሆነ በእውነት፣ በሁሉም መንገድ ክርስቶስ እንዲሰበክ አስችሏል፤ በዚህ ደግሞ ደስተኛ ነኝ። ወደፊትም ቢሆን መደሰቴን እቀጥላለሁ፤ 19 ይህ በእናንተ ምልጃ+ እንዲሁም የኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ በሚሰጠኝ ድጋፍ+ መዳን እንደሚያስገኝልኝ አውቃለሁና። 20 ይህም በጉጉት ከምጠባበቀው ነገርና ከተስፋዬ ጋር በሚስማማ ሁኔታ በማንኛውም መንገድ እንዳላፍር ነው፤ ከዚህ ይልቅ በነፃነት በመናገር በሕይወትም ሆነ በሞት እንደ ወትሮው ሁሉ አሁንም ክርስቶስን በሰውነቴ አማካኝነት ከፍ ከፍ አደርገው ዘንድ ነው።+

21 እኔ ብኖር የምኖረው ለክርስቶስ ነውና፤+ ብሞት ደግሞ እጠቀማለሁ።+ 22 በሥጋ መኖሬን የምቀጥል ከሆነ በማከናውነው ሥራ አማካኝነት ብዙ ፍሬ ማፍራት እችላለሁ፤ ይሁንና የትኛውን እንደምመርጥ አላሳውቅም። 23 በእነዚህ ሁለት ነገሮች አጣብቂኝ ውስጥ ገብቻለሁ፤ ምኞቴ ነፃ መለቀቅና ከክርስቶስ ጋር መሆን ነውና፤+ እርግጡን ለመናገር ይህ እጅግ የተሻለ ነው።+ 24 ይሁን እንጂ ለእናንተ ሲባል በሥጋ መኖሬ ይበልጥ አስፈላጊ ነው። 25 በመሆኑም በዚህ ጉዳይ እርግጠኛ ስለሆንኩ እድገት እንድታደርጉና በእምነት ደስታ እንድታገኙ ስል በሥጋ እንደምቆይና ከሁላችሁም ጋር መኖሬን እንደምቀጥል አውቃለሁ፤ 26 ይህም ዳግመኛ በእናንተ መካከል ስገኝ በእኔ ምክንያት ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር በተያያዘ ደስታችሁ ይትረፈረፍ ዘንድ ነው።

27 ብቻ አኗኗራችሁ ስለ ክርስቶስ ከሚገልጸው ምሥራች ጋር የሚስማማ ይሁን፤*+ ይህም መጥቼ ባያችሁም ሆነ ከእናንተ ብርቅ አንድ ላይ ሆናችሁ በምሥራቹ ላይ ያላችሁን እምነት ጠብቃችሁ ለመኖር በአንድ ነፍስ* በመጋደል በአንድ መንፈስ ጸንታችሁ መቆማችሁን+ 28 እንዲሁም በምንም መንገድ በጠላቶቻችሁ አለመሸበራችሁን እሰማና አውቅ ዘንድ ነው። ይህ ነገር እነሱ እንደሚጠፉ+ እናንተ ግን እንደምትድኑ የሚያሳይ+ ማስረጃ ነው፤ ይህም ከአምላክ የተሰጠ ነው። 29 እናንተ በክርስቶስ እንድታምኑ ብቻ ሳይሆን ለእሱ ስትሉ መከራ እንድትቀበሉም መብት ተሰጥቷችኋል።+ 30 እኔ ስጋፈጥ ያያችሁትንና+ አሁንም እየተጋፈጥኩት እንዳለሁ የሰማችሁትን ያንኑ ትግል እናንተም እየተጋፈጣችሁ ነውና።

2 እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ባላችሁ አንድነት በመካከላችሁ ማንኛውም ዓይነት ማበረታቻ፣ ማንኛውም ዓይነት ፍቅራዊ ማጽናኛ፣ ማንኛውም ዓይነት መንፈሳዊ ኅብረት፣ ማንኛውም ዓይነት ጥልቅ ፍቅርና ርኅራኄ ካለ፣ 2 ፍጹም አንድነት ኖሯችሁና* አንድ ዓይነት አስተሳሰብ ይዛችሁ በአንድ ሐሳብና በአንድ ፍቅር በመኖር ደስታዬን የተሟላ አድርጉልኝ።+ 3 ሌሎች ከእናንተ እንደሚበልጡ በትሕትና አስቡ+ እንጂ በጠበኝነት መንፈስ+ ወይም በትምክህተኝነት+ ምንም ነገር አታድርጉ፤ 4 ስለ ራሳችሁ ፍላጎት ብቻ ከማሰብ ይልቅ+ እያንዳንዳችሁ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎትም ትኩረት ስጡ።+

5 ክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ይህ አስተሳሰብ በእናንተም ዘንድ ይኑር፤+ 6 እሱ በአምላክ መልክ ይኖር የነበረ ቢሆንም+ ከአምላክ ጋር እኩል ለመሆን የመሞከር ሐሳብም እንኳ ወደ አእምሮው አልመጣም።+ 7 ከዚህ ይልቅ ራሱን ባዶ በማድረግ የባሪያን መልክ ያዘ፤+ ደግሞም ሰው ሆነ።*+ 8 ከዚህም በላይ ሰው ሆኖ በመጣ ጊዜ* ራሱን ዝቅ በማድረግ እስከ ሞት ድረስ ያውም በመከራ እንጨት*+ ላይ እስከ መሞት ድረስ ታዛዥ ሆኗል።+ 9 በዚህም ምክንያት አምላክ የላቀ ቦታ በመስጠት ከፍ ከፍ አደረገው፤+ እንዲሁም ከሌላ ከማንኛውም ስም በላይ የሆነ ስም በደግነት ሰጠው፤+ 10 ይህም በሰማይና በምድር እንዲሁም ከምድር በታች ያሉ ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ ነው፤+ 11 ምላስም ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደሆነ በመመሥከር+ አባት ለሆነው አምላክ ክብር ያመጣ ዘንድ ነው።

12 ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ እኔ አብሬያችሁ ስሆን ብቻ ሳይሆን ይልቁንም አሁን አብሬያችሁ በሌለሁበት ወቅት ሁልጊዜ ታዛዥ እንደሆናችሁ ሁሉ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ከፍጻሜ ለማድረስ ተግታችሁ ሥሩ። 13 ለተግባር የሚያነሳሳ ፍላጎት እንዲያድርባችሁም ሆነ ኃይል እንድታገኙ በማድረግ እሱ ደስ ለሚሰኝበት ነገር ብርታት የሚሰጣችሁ አምላክ ነውና። 14 ምንጊዜም ማንኛውንም ነገር ሳታጉረመርሙና+ ሳትከራከሩ አድርጉ፤+ 15 ይህም በጠማማና በወልጋዳ ትውልድ+ መካከል እንከንና እድፍ የሌለባችሁ ንጹሐን የአምላክ ልጆች እንድትሆኑ ነው።+ በዚህ ዓለም ውስጥ እንደ ብርሃን አብሪዎች ታበራላችሁ፤+ 16 ይህን የምታደርጉትም የሕይወትን ቃል አጥብቃችሁ በመያዝ ነው።+ ያን ጊዜ ሩጫዬም ሆነ ድካሜ ከንቱ ሆኖ እንዳልቀረ ስለምገነዘብ በክርስቶስ ቀን ሐሴት የማደርግበት ነገር ይኖረኛል። 17 ይሁንና በእምነት ተነሳስታችሁ በምታቀርቡት መሥዋዕትና+ ቅዱስ አገልግሎት* ላይ እንደ መጠጥ መባ ብፈስ+ እንኳ ደስ ይለኛል፤* እንዲሁም ከሁላችሁም ጋር ሐሴት አደርጋለሁ። 18 እናንተም ልክ እንደዚሁ ተደሰቱ፤ ከእኔም ጋር ሐሴት አድርጉ።

19 ስለ እናንተ በምሰማበት ጊዜ እንድበረታታ፣ ጌታ ኢየሱስ ቢፈቅድ ጢሞቴዎስን+ በቅርቡ ወደ እናንተ እንደምልከው ተስፋ አደርጋለሁ። 20 ስለ እናንተ ጉዳይ ከልብ የሚጨነቅ እንደ እሱ ያለ በጎ አመለካከት ያለው ሌላ ማንም የለኝምና። 21 ሌሎቹ ሁሉ የኢየሱስ ክርስቶስን ሳይሆን የራሳቸውን ፍላጎት ለማሟላት ይሯሯጣሉ። 22 እሱ ግን ከአባቱ ጋር እንደሚሠራ ልጅ+ ምሥራቹን በማስፋፋቱ ሥራ ከእኔ ጋር እንደ ባሪያ በማገልገል ማንነቱን እንዴት እንዳስመሠከረ ታውቃላችሁ። 23 በመሆኑም የእኔ ጉዳይ ምን ላይ እንደደረሰ ሳውቅ ወዲያውኑ ወደ እናንተ ልልከው ያሰብኩት እሱን ነው። 24 እንዲያውም የጌታ ፈቃድ ከሆነ እኔ ራሴም በቅርቡ እንደምመጣ እርግጠኛ ነኝ።+

25 ለአሁኑ ግን በሚያስፈልገኝ ሁሉ በግል እንዲያገለግለኝ የላካችሁትን ወንድሜን፣ የሥራ ባልደረባዬንና አብሮኝ ወታደር የሆነውን አፍሮዲጡን ወደ እናንተ መላኩን አስፈላጊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፤+ 26 ምክንያቱም ሁላችሁንም ለማየት ናፍቋል፤ በተጨማሪም እንደታመመ መስማታችሁን ስላወቀ ተጨንቋል። 27 በእርግጥም በጠና ታሞ ሞት አፋፍ ደርሶ ነበር፤ ሆኖም አምላክ ምሕረት አደረገለት፤ ደግሞም ምሕረት ያደረገው ለእሱ ብቻ ሳይሆን በሐዘን ላይ ሐዘን እንዳይደራረብብኝ ለእኔም ጭምር ነው። 28 ስለዚህ ስታዩት ዳግመኛ እንድትደሰቱና የእኔም ጭንቀት እንዲቀል እሱን በተቻለ ፍጥነት ወደ እናንተ እልከዋለሁ። 29 ስለዚህ የጌታን ተከታዮች ወትሮ በምትቀበሉበት መንገድ በታላቅ ደስታ ተቀበሉት፤ እንዲሁም እንደ እሱ ያሉትን ሰዎች በአክብሮት ያዟቸው፤+ 30 ምክንያቱም እሱ፣ እናንተ እዚህ ሆናችሁ በግል ልትሰጡኝ ያልቻላችሁትን አገልግሎት በሚገባ ለማሟላት ሲል ከክርስቶስ ሥራ* የተነሳ ሕይወቱን* ለአደጋ በማጋለጥ ለሞት ተቃርቦ ነበር።+

3 በመጨረሻም ወንድሞቼ፣ ምንጊዜም በጌታ ደስ ይበላችሁ።+ ያንኑ ነገር ደግሜ ብጽፍላችሁ እኔን አይታክተኝም፤ ይህ ደግሞ ለእናንተ ጠቃሚ ነው።

2 ከውሾች ተጠንቀቁ፤ ጎጂ ነገር ከሚያደርጉ ሰዎች ተጠንቀቁ፤ ሥጋን ከሚቆርጡ* ሰዎች ተጠንቀቁ።+ 3 እውነተኛውን ግርዘት የተገረዝነው እኛ ነንና፤+ እኛ በአምላክ መንፈስ፣ ቅዱስ አገልግሎት እናቀርባለን፤ በክርስቶስ ኢየሱስ እንኩራራለን፤+ ደግሞም በሥጋ አንመካም፤ 4 ይሁንና በሥጋ የምመካበት ነገር አለኝ የሚል ማንም ቢኖር ያ ሰው እኔ ነኝ።

በሥጋ የሚመካበት ነገር እንዳለው አድርጎ የሚያስብ ሌላ ማንም ሰው ቢኖር እኔ እበልጣለሁ፦ 5 በስምንተኛው ቀን የተገረዝኩና+ ከእስራኤል ብሔር፣ ከቢንያም ነገድ የተገኘሁ ስሆን ከዕብራውያን የተወለድኩ ዕብራዊ ነኝ፤+ ስለ ሕግ ከተነሳ ፈሪሳዊ ነበርኩ፤+ 6 ስለ ቅንዓት ከተነሳ በጉባኤው ላይ ስደት አደርስ ነበር፤+ ሕጉን በመታዘዝ ስለሚገኘው ጽድቅ ከተነሳ ደግሞ እንከን የማይገኝብኝ መሆኔን አስመሥክሬአለሁ። 7 ሆኖም ለእኔ ትርፍ የነበረውን ነገር ሁሉ ለክርስቶስ ስል እንደ ኪሳራ ቆጥሬዋለሁ።*+ 8 ከዚህም በላይ ስለ ጌታዬ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ከሚገልጸው የላቀ ዋጋ ያለው እውቀት አንጻር ሁሉንም ነገር እንደ ኪሳራ እቆጥረዋለሁ። ለእሱ ስል ሁሉንም ነገር አጥቻለሁ፤ ያጣሁትንም ነገር ሁሉ እንደ ጉድፍ* እቆጥረዋለሁ፤ ይህም ክርስቶስን አገኝ ዘንድ ነው። 9 እንዲሁም ሕግ በመጠበቅ ባገኘሁት በራሴ ጽድቅ ሳይሆን በክርስቶስ በማመን+ በሚገኘው ጽድቅ+ ይኸውም በእምነት ላይ በተመሠረተው ከአምላክ በሚገኘው ጽድቅ+ ከክርስቶስ ጋር አንድ ለመሆን ነው። 10 ፍላጎቴ እሱንና የትንሣኤውን ኃይል+ ማወቅ እንዲሁም እሱ ለሞተው ዓይነት ሞት ራሴን አሳልፌ በመስጠት+ የሥቃዩ ተካፋይ+ መሆን ነው፤ 11 ደግሞም በተቻለ መጠን መጀመሪያ ላይ ትንሣኤ ከሚያገኙት መካከል መሆን ነው።+

12 አሁን ሽልማቱን አግኝቻለሁ ወይም አሁን ወደ ፍጽምና ደርሻለሁ ማለት አይደለም፤ ነገር ግን ክርስቶስ ኢየሱስ እኔን የመረጠበትን ያን ነገር የራሴ ማድረግ እችል እንደሆነ ለማየት ጥረት እያደረግኩ ነው።+ 13 ወንድሞች፣ እኔ እንዳገኘሁት አድርጌ አላስብም፤ ነገር ግን ስለ አንድ ነገር እርግጠኛ ነኝ፦ ከኋላዬ ያሉትን ነገሮች እየረሳሁ+ ከፊቴ ወዳሉት ነገሮች እንጠራራለሁ፤+ 14 አምላክ በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል የሚሰጠውን የሰማያዊውን ሕይወት+ ሽልማት አገኝ ዘንድ ግቡ ላይ ለመድረስ እየተጣጣርኩ ነው።+ 15 እንግዲህ ጎልማሳ+ የሆንነው እኛ ይህ አስተሳሰብ ይኑረን፤ በማንኛውም ረገድ ከዚህ የተለየ ሐሳብ ቢኖራችሁ አምላክ ትክክለኛውን አስተሳሰብ ይገልጥላችኋል። 16 ያም ሆነ ይህ ምንም ያህል እድገት ያደረግን ብንሆን በዚሁ መንገድ በአግባቡ ወደፊት መጓዛችንን እንቀጥል።

17 ወንድሞች፣ ሁላችሁም የእኔን ምሳሌ ተከተሉ፤+ እንዲሁም እኛ ከተውንላችሁ ምሳሌ ጋር በሚስማማ መንገድ የሚመላለሱትን ሁሉ ልብ ብላችሁ ተመልከቱ። 18 የክርስቶስ የመከራ እንጨት* ጠላቶች ሆነው የሚመላለሱ ብዙዎች አሉና፤ ከዚህ በፊት ደጋግሜ እጠቅሳቸው ነበር፤ ሆኖም አሁን በእንባ ጭምር እጠቅሳቸዋለሁ። 19 መጨረሻቸው ጥፋት ነው፤ ሆዳቸው* አምላካቸው ነው፤ ሊያፍሩበት በሚገባው ነገር ይኩራራሉ፤ አእምሯቸው ደግሞ ያተኮረው በምድራዊ ነገሮች ላይ ነው።+ 20 እኛ ግን የሰማይ+ ዜጎች ነን፤+ ከዚያ የሚመጣውንም አዳኝ ይኸውም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በጉጉት እንጠባበቃለን፤+ 21 እሱም ክብር የተላበሰውን አካሉን እንዲመስል፣* ታላቅ ኃይሉን ተጠቅሞ ደካማውን አካላችንን ይለውጠዋል፤+ እንዲሁም ሁሉንም ነገር ለራሱ ያስገዛል።+

4 ስለዚህ የምወዳችሁና የምናፍቃችሁ እንዲሁም ደስታዬና አክሊሌ+ የሆናችሁ ወንድሞቼና ወዳጆቼ፣ አሁን በገለጽኩላችሁ መሠረት ከጌታ ጋር ባላችሁ አንድነት ጸንታችሁ ቁሙ።+

2 በጌታ አንድ ዓይነት አስተሳሰብ እንዲኖራቸው+ ኤዎድያንን እመክራለሁ፤ ሲንጤኪንም እመክራለሁ። 3 አዎ፣ እውነተኛ የሥራ አጋሬ የሆንከው አንተም፣ ከቀሌምንጦስና ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ከሰፈረው+ ከቀሩት የሥራ ባልደረቦቼ ጋር ለምሥራቹ ሲሉ ከጎኔ ተሰልፈው ብዙ የደከሙትን* እነዚህን ሴቶች መርዳትህን እንድትቀጥል አደራ እልሃለሁ።

4 ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ። ደግሜ እላለሁ ደስ ይበላችሁ!+ 5 ምክንያታዊነታችሁ*+ በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን። ጌታ ቅርብ ነው። 6 ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ፤+ ከዚህ ይልቅ ስለ ሁሉም ነገር በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ፤+ 7 ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም+ በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ልባችሁንና+ አእምሯችሁን* ይጠብቃል።

8 በመጨረሻም ወንድሞች፣ እውነት የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ቁም ነገር ያለበትን ነገር ሁሉ፣ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ተወዳጅ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ በመልካም የሚነሳውን ነገር ሁሉ፣ በጎ የሆነውን ሁሉና ምስጋና የሚገባውን ነገር ሁሉ ማሰባችሁን* አታቋርጡ።+ 9 ከእኔ የተማራችሁትንም ሆነ የተቀበላችሁትን እንዲሁም የሰማችሁትንና ያያችሁትን ነገር ሁሉ ሥራ ላይ አውሉ፤+ የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል።

10 አሁን ለእኔ እንደገና ማሰብ በመጀመራችሁ በጌታ እጅግ ደስ ይለኛል።+ ስለ እኔ ደህንነት ታስቡ የነበረ ቢሆንም ይህን በተግባር ለማሳየት የሚያስችል አጋጣሚ አላገኛችሁም። 11 ይህን ስል እንደተቸገርኩ መናገሬ አይደለም፤ ምክንያቱም በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ብሆን ባለኝ ረክቼ መኖርን ተምሬአለሁ።+ 12 በትንሽ ነገር እንዴት መኖር እንደሚቻልም+ ሆነ ብዙ አግኝቶ እንዴት መኖር እንደሚቻል አውቃለሁ። በማንኛውም ነገርና በሁሉም ሁኔታ ጠግቦም ሆነ ተርቦ፣ ብዙ አግኝቶም ሆነ አጥቶ መኖር የሚቻልበትን ሚስጥር ተምሬአለሁ። 13 ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ አማካኝነት ለሁሉም ነገር የሚሆን ብርታት አለኝ።+

14 የሆነ ሆኖ የመከራዬ ተካፋዮች በመሆናችሁ መልካም አድርጋችኋል። 15 እንዲያውም እናንተ የፊልጵስዩስ ወንድሞች፣ ምሥራቹን መጀመሪያ ከሰማችሁ በኋላ ከመቄዶንያ ስወጣ በመስጠትም ሆነ በመቀበል ረገድ ከእናንተ በስተቀር ከእኔ ጋር የተባበረ አንድም ጉባኤ እንዳልነበረ ታውቃላችሁ፤+ 16 በተሰሎንቄ በነበርኩበት ጊዜ የሚያስፈልገኝን ነገር ከአንዴም ሁለቴ ልካችሁልኛልና። 17 ይህን ስል ስጦታ ለማግኘት በመፈለግ ሳይሆን እናንተ የምታገኙት ጥቅም እንዲጨምር የሚያደርገውን ፍሬ ለማየት በመፈለግ ነው። 18 ይሁን እንጂ የሚያስፈልገኝ ነገር ሁሉ፣ እንዲያውም ከሚያስፈልገኝ በላይ አለኝ። የላካችሁልኝን ከአፍሮዲጡ+ ስለተቀበልኩ ሞልቶ ተትረፍርፎልኛል፤ ይህም ጥሩ መዓዛ ያለው ሽታ፣+ ተቀባይነት ያለው መሥዋዕትና አምላክ ደስ የሚሰኝበት ነገር ነው። 19 በአጸፋው ደግሞ አምላኬ እንደ ታላቅ ብልጽግናው መጠን በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ አሟልቶ ይሰጣችኋል።+ 20 እንግዲህ ለአምላካችንና ለአባታችን ለዘላለም ክብር ይሁን። አሜን።

21 ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድነት ላላቸው ቅዱሳን ሁሉ ሰላምታዬን አድርሱልኝ። ከእኔ ጋር ያሉ ወንድሞች ሰላምታ ልከውላችኋል። 22 ቅዱሳን ሁሉ በተለይ ደግሞ ከቄሳር ቤተሰብ+ የሆኑት ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።

23 የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከምታሳዩት መንፈስ ጋር ይሁን።

ወይም “ምሥራቹን በማስፋፋቱ ሥራ ተሳትፎ።”

ወይም “ዜጎች እንደመሆናችሁ መጠን ስለ ክርስቶስ ከሚገልጸው ምሥራች ጋር በሚስማማ መንገድ ኑሩ።”

ወይም “በአንድነት።”

ወይም “በአንድ ነፍስ ተሳስራችሁና።”

ቃል በቃል “በሰዎች አምሳል ተገኘ።”

ቃል በቃል “በሰው መልክ በተገኘ ጊዜ።”

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “ሕዝባዊ አገልግሎት።”

እዚህ ላይ ጳውሎስ የመጠጥ መባን ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ የተጠቀመ ሲሆን ክርስቲያን ባልንጀሮቹን ለመጥቀም ሲል ራሱን ሳይቆጥብ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆኑን ያሳያል።

“ከጌታ ሥራ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “ነፍሱን።”

የግርዘት ልማድን የሚደግፉ ሰዎችን ያመለክታል።

“በፈቃደኝነት ትቼዋለሁ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “ቆሻሻ፤ ትርኪ ምርኪ።”

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “ሥጋዊ ፍላጎታቸው።”

ቃል በቃል “(ከክቡር አካሉ ጋር) እንዲስማማ።”

ወይም “የተጋደሉትን።”

ቃል በቃል “ገርነታችሁ፤ እሺ ባይነታችሁ።”

ወይም “ሐሳባችሁን።”

ወይም “ማውጠንጠናችሁን፤ ማሰላሰላችሁን።”

    የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ ጽሑፎች (2011-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ