ለጢሞቴዎስ የተጻፈ ሁለተኛው ደብዳቤ
1 በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት የሚገኘውን ሕይወት+ በተመለከተ ከተገባው ቃል ጋር በሚስማማ ሁኔታ በአምላክ ፈቃድ የክርስቶስ ኢየሱስ ሐዋርያ ከሆነው ከጳውሎስ፣ 2 ለተወዳጁ ልጄ ለጢሞቴዎስ፦+
አባት ከሆነው አምላክና ከጌታችን ከክርስቶስ ኢየሱስ ጸጋ፣ ምሕረትና ሰላም ለአንተ ይሁን።
3 የቀድሞ አባቶቼ እንዳደረጉት ቅዱስ አገልግሎት የማቀርብለትንና በንጹሕ ሕሊና የማገለግለውን አምላክ አመሰግናለሁ፤ ደግሞም ሌት ተቀን አንተን ዘወትር በምልጃዬ አስታውሳለሁ። 4 እንባህን ሳስታውስ፣ በደስታ እሞላ ዘንድ ላይህ እናፍቃለሁ። 5 በአንተ ውስጥ ያለውን ግብዝነት የሌለበት እምነት+ አስታውሳለሁና፤ ይህ እምነት በመጀመሪያ በአያትህ በሎይድ እንዲሁም በእናትህ በኤውንቄ ዘንድ ነበር፤ ይሁንና በአንተም ውስጥ እንዳለ እርግጠኛ ነኝ።
6 ስለዚህ በአንተ ላይ እጄን በጫንኩበት+ ጊዜ የተቀበልከውን የአምላክ ስጦታ በቅንዓት እንድትጠቀምበት* አሳስብሃለሁ። 7 አምላክ የኃይል፣+ የፍቅርና የጤናማ አእምሮ መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና።+ 8 ስለሆነም ስለ ጌታችን መመሥከር አያሳፍርህ፤+ ደግሞም ለእሱ ስል እስረኛ በሆንኩት በእኔ አትፈር፤ ከዚህ ይልቅ በአምላክ ኃይል በመታመን+ አንተም ለምሥራቹ የበኩልህን መከራ ተቀበል።+ 9 እሱ በእኛ ሥራ ሳይሆን በራሱ ዓላማና ጸጋ የተነሳ አዳነን፤+ እንዲሁም ቅዱስ በሆነ ጥሪ ጠራን።+ ይህን ጸጋ ከረጅም ዘመናት በፊት በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ሰጠን፤ 10 አሁን ግን ይህ ጸጋ አዳኛችን የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ በመገለጡ ግልጽ ሆኖ ታይቷል፤+ እሱ ሞትን አስወግዶ+ በምሥራቹ አማካኝነት+ ሕይወትንና አለመበስበስን+ በተመለከተ ብርሃን ፈንጥቋል፤+ 11 እኔም ለዚህ ምሥራች ሰባኪ፣ ሐዋርያና አስተማሪ ሆኜ ተሹሜአለሁ።+
12 አሁን መከራ እየተቀበልኩ ያለሁትም ለዚሁ ነው፤+ ሆኖም አላፍርበትም።+ ያመንኩበትን እሱን አውቀዋለሁና፤ በአደራ የሰጠሁትንም እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ጠብቆ ማቆየት እንደሚችል እተማመናለሁ።+ 13 ከእኔ የሰማኸውን የትክክለኛ* ትምህርት+ መሥፈርት* ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር ባለህ አንድነት ካገኘኸው እምነትና ፍቅር ጋር አጥብቀህ ያዝ። 14 ይህን መልካም አደራ በእኛ ውስጥ በሚኖረው መንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ጠብቅ።+
15 ፊጌሎስንና ሄርሞጌኔስን ጨምሮ በእስያ አውራጃ+ ያሉት ሁሉ ትተውኝ እንደሄዱ ታውቃለህ። 16 ጌታ ለኦኔሲፎሮስ+ ቤተሰብ ምሕረትን ይስጥ፤ እሱ ብዙ ጊዜ መንፈሴን አድሶልኛልና፤ በታሰርኩበት ሰንሰለትም አላፈረም። 17 እንዲያውም ሮም በነበረ ጊዜ አፈላልጎ አገኘኝ። 18 ጌታ ይሖዋ* በዚያ ቀን ምሕረቱን ይስጠው። ደግሞም በኤፌሶን ያከናወነውን አገልግሎት ሁሉ በሚገባ ታውቃለህ።
2 እንግዲህ ልጄ+ ሆይ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ በሚገኘው ጸጋ አማካኝነት በርታ፤* 2 ከእኔ የሰማኸውንና ብዙዎች የመሠከሩለትን ነገር፣+ ታማኝ ለሆኑ ሰዎች አደራ ስጥ፤ እነሱም በበኩላቸው ሌሎችን ለማስተማር ብቃቱን ያሟላሉ። 3 የክርስቶስ ኢየሱስ ምርጥ ወታደር+ እንደመሆንህ መጠን አንተም በበኩልህ መከራ ተቀበል።+ 4 ወታደር ሆኖ የሚያገለግል ማንኛውም ሰው ለውትድርና የመለመለውን ሰው ደስ ማሰኘት ስለሚፈልግ ራሱን በንግድ ሥራ* አያጠላልፍም። 5 በውድድር የሚሳተፍ ማንኛውም ሰው የውድድሩን ደንብ ጠብቆ ካልተወዳደረ የድሉን አክሊል አይሸለምም።+ 6 ጠንክሮ የሚሠራ ገበሬ ከፍሬው የመጀመሪያው ተቋዳሽ መሆን አለበት። 7 ለምናገረው ነገር ምንጊዜም ትኩረት ስጥ፤ ጌታም በሁሉም ነገር ማስተዋል ይሰጥሃል።
8 ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት እንደተነሳ+ እንዲሁም የዳዊት ዘር+ እንደሆነ አስታውስ፤ እኔም የምሰብከው ምሥራች ይህ ነው፤+ 9 ከዚህም የተነሳ እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሬ መከራ እየተቀበልኩ ነው፤ ደግሞም ታስሬአለሁ።+ ሆኖም የአምላክ ቃል አልታሰረም።+ 10 ከዚህም የተነሳ የተመረጡትም በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት የሚገኘውን መዳን ከዘላለማዊ ክብር ጋር ያገኙ ዘንድ ለእነሱ ስል ሁሉንም ነገር በጽናት ተቋቁሜ እኖራለሁ።+ 11 የሚከተለው ቃል እምነት የሚጣልበት ነው፦ አብረን ከሞትን አብረን ደግሞ በሕይወት እንደምንኖር የተረጋገጠ ነው፤+ 12 ጸንተን ከኖርን አብረን ደግሞ እንነግሣለን፤+ ብንክደው እሱም ይክደናል፤+ 13 ታማኞች ሆነን ባንገኝ እሱ ምንጊዜም ታማኝ ሆኖ ይኖራል፤ እሱ ራሱን ሊክድ አይችልምና።
14 ስለ ቃላት እንዳይነታረኩ በአምላክ ፊት እየመከርክ* እነዚህን ነገሮች ዘወትር አሳስባቸው፤ እንዲህ ያለው ነገር በሚሰሙት ሰዎች ላይ ጉዳት ከማስከተል* በስተቀር ምንም ጥቅም የለውም። 15 የእውነትን ቃል በአግባቡ በመጠቀም፣ ተቀባይነት ሊያገኝ እንደሚገባውና ምንም የሚያፍርበት ነገር እንደሌለው ሠራተኛ አድርገህ ራስህን በአምላክ ፊት ለማቅረብ የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ።+ 16 ሆኖም ቅዱስ የሆነውን ነገር ከሚጻረሩ ከንቱ ንግግሮች ራቅ፤+ እንዲህ ያሉ ንግግሮች* ሰዎች ይበልጥ ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው እየሆኑ እንዲሄዱ ያደርጋሉና፤ 17 እንዲህ ያሉ ንግግሮችን የሚናገሩ ሰዎች ቃላቸው እንደተመረዘ ቁስል ይሰራጫል። ከእነሱም መካከል ሄሜኔዎስና ፊሊጦስ ይገኙበታል።+ 18 እነዚህ ሰዎች ‘ትንሣኤ ቀደም ብሎ ተከናውኗል’ ብለው በመናገር ከእውነት ርቀዋል፤+ ደግሞም የአንዳንዶችን እምነት እያፈረሱ ነው። 19 ይሁን እንጂ “ይሖዋ* የእሱ የሆኑትን ያውቃል”+ እንዲሁም “የይሖዋን* ስም የሚጠራ ሁሉ+ ከክፋት ይራቅ” የሚል ማኅተም ያለበት ጠንካራው የአምላክ መሠረት ጸንቶ ይኖራል።
20 በአንድ ትልቅ ቤት ውስጥ የወርቅና የብር ዕቃ ብቻ ሳይሆን የእንጨትና የሸክላ ዕቃም ይኖራል፤ አንዳንዱ ክብር ላለው ዓላማ የሚያገለግል ሲሆን ሌላው ግን ክብር ለሌለው ዓላማ ያገለግላል። 21 እንግዲህ ማንም ከእነዚህ ከኋለኞቹ ነገሮች ቢርቅ ክብር ላለው ዓላማ የሚያገለግል፣ የተቀደሰ፣ ለባለቤቱ የሚጠቅምና ለመልካም ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ መሣሪያ* ይሆናል። 22 ስለዚህ ከወጣትነት ምኞቶች ሽሽ፤ ከዚህ ይልቅ በንጹሕ ልብ ጌታን ከሚጠሩት ጋር ጽድቅን፣ እምነትን፣ ፍቅርንና ሰላምን ለማግኘት ተጣጣር።
23 በተጨማሪም ጠብ ሊያስከትል እንደሚችል በመገንዘብ ሞኝነትና አላዋቂነት ከሚንጸባረቅበት ክርክር ራቅ።+ 24 የጌታ ባሪያ ሊጣላ አይገባውምና፤ ከዚህ ይልቅ ለሰው ሁሉ ገር፣*+ ለማስተማር ብቁ የሆነና በደል ሲደርስበት ራሱን የሚገዛ፣+ 25 እንዲሁም ቀና አመለካከት የሌላቸውን በገርነት* የሚያርም ሊሆን ይገባዋል።+ ምናልባትም አምላክ ትክክለኛ የእውነት እውቀት ያገኙ ዘንድ+ ለንስሐ* ያበቃቸው ይሆናል፤ 26 እነሱም ዲያብሎስ ፈቃዱን ያደርጉ ዘንድ በሕይወት እንዳሉ አጥምዶ እንደያዛቸው+ በመረዳት ወደ ልቦናቸው ተመልሰው ከእሱ ወጥመድ ሊወጡ ይችላሉ።
3 ነገር ግን በመጨረሻዎቹ ቀናት+ ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን እንደሚመጣ ይህን እወቅ። 2 ምክንያቱም ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብ የሚወዱ፣ ጉረኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ታማኝ ያልሆኑ፣ 3 ተፈጥሯዊ ፍቅር የሌላቸው፣* ለመስማማት ፈቃደኞች ያልሆኑ፣ ስም አጥፊዎች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ ጥሩ ነገር የማይወዱ፣ 4 ከዳተኞች፣ ግትሮች፣ በኩራት የተወጠሩ፣ ከአምላክ ይልቅ ሥጋዊ ደስታን የሚወዱ ይሆናሉ፤ 5 ለአምላክ ያደሩ መስለው ይታያሉ፤ በሥራቸው ግን ኃይሉን ይክዳሉ፤+ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ። 6 በየቤቱ ሾልከው የሚገቡ ሰዎች የሚነሱት ከእነዚህ መካከል ነው፤ እነዚህ ሰዎች በተለያዩ ምኞቶች የሚነዱትን፣ በኃጢአት የተተበተቡትን ደካማ ሴቶች ይማርካሉ፤ 7 እንደነዚህ ያሉት ሴቶች ሁልጊዜ ይማራሉ፤ ሆኖም ትክክለኛውን የእውነት እውቀት መረዳት አይችሉም።
8 እንግዲህ ኢያኔስና ኢያንበሬስ ሙሴን እንደተቃወሙት ሁሉ እነዚህም እውነትን ይቃወማሉ። እንዲህ ያሉ ሰዎች አእምሯቸው ሙሉ በሙሉ የተበላሸ ከመሆኑም ሌላ በእምነት ጎዳና ስለማይመላለሱ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አጥተዋል። 9 ይሁንና የእነዚያ ሁለት ሰዎች ሞኝነት ለሰው ሁሉ በጣም ግልጽ እንደነበረ ሁሉ የእነዚህ ሰዎች ሞኝነትም ግልጽ ስለሚሆን በአካሄዳቸው ብዙም ሊገፉበት አይችሉም።+ 10 አንተ ግን ትምህርቴን፣ አኗኗሬን፣+ ዓላማዬን፣ እምነቴን፣ ትዕግሥቴን፣ ፍቅሬንና ጽናቴን በጥብቅ ተከትለሃል፤ 11 እንደ አንጾኪያ፣+ ኢቆንዮንና+ ልስጥራ+ ባሉ ቦታዎች የደረሰብኝን ስደትና መከራ ታውቃለህ። ይህን ሁሉ ስደት በጽናት አሳልፌአለሁ፤ ጌታም ከዚህ ሁሉ ታደገኝ።+ 12 በእርግጥም የክርስቶስ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በመሆን ለአምላክ ያደሩ ሆነው መኖር የሚፈልጉ ሁሉ ስደት ይደርስባቸዋል።+ 13 ሆኖም ክፉ ሰዎችና አስመሳዮች እያሳሳቱና እየተሳሳቱ በክፋት ላይ ክፋት እየጨመሩ ይሄዳሉ።+
14 አንተ ግን በተማርካቸውና አምነህ በተቀበልካቸው ነገሮች ጸንተህ ኑር፤+ ምክንያቱም እነዚህን ነገሮች እነማን እንዳስተማሩህ ታውቃለህ፤ 15 እንዲሁም በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን ለመዳን የሚያበቃ ጥበብ እንድታገኝ የሚያስችሉህን ቅዱሳን መጻሕፍት+ ከጨቅላነትህ+ ጀምሮ አውቀሃል።+ 16 ቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉ ናቸው፤+ እንዲሁም ለማስተማር፣+ ለመውቀስ፣ ነገሮችን ለማቅናትና* በጽድቅ ለመገሠጽ ይጠቅማሉ፤+ 17 ይኸውም የአምላክ ሰው ለማንኛውም መልካም ሥራ በሚገባ በመታጠቅ ሙሉ በሙሉ ብቁ ሆኖ እንዲገኝ ነው።
4 በአምላክ ፊት እንዲሁም በሕያዋንና በሙታን+ ላይ በሚፈርደው+ በክርስቶስ ኢየሱስ ፊት አጥብቄ አሳስብሃለሁ፤ ደግሞም በእሱ መገለጥና+ በመንግሥቱ+ አማካኝነት አዝሃለሁ፦ 2 ቃሉን ስበክ፤+ አመቺ በሆነ ጊዜም ሆነ በአስቸጋሪ ጊዜ በጥድፊያ ስሜት አገልግል፤ በብዙ ትዕግሥትና በማስተማር ጥበብ ውቀስ፣+ ገሥጽ እንዲሁም አጥብቀህ ምከር።+ 3 ትክክለኛውን ትምህርት* የማይታገሡበት ጊዜ ይመጣልና፤+ ከዚህ ይልቅ ከራሳቸው ፍላጎት ጋር በሚስማማ ሁኔታ ጆሯቸውን እንዲኮረኩሩላቸው* በዙሪያቸው አስተማሪዎችን ይሰበስባሉ።+ 4 እውነትን ከመስማት ጆሯቸውን ይመልሳሉ፤ ለተረትም ጆሮ ይሰጣሉ። 5 አንተ ግን በሁሉም ነገር የማስተዋል ስሜትህን ጠብቅ፣ መከራን በጽናት ተቋቋም፣+ የወንጌላዊነትን ሥራ አከናውን* እንዲሁም አገልግሎትህን በተሟላ ሁኔታ ፈጽም።+
6 እኔ እንደ መጠጥ መባ እየፈሰስኩ ነውና፤*+ ደግሞም ነፃ የምለቀቅበት ጊዜ+ በጣም ቀርቧል። 7 መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፤+ ሩጫውን ጨርሻለሁ፤+ እምነትን ጠብቄአለሁ። 8 ከዚህ በኋላ የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶ ይጠብቀኛል፤+ ጻድቅ ፈራጅ+ የሆነው ጌታ በፍርድ ቀን ይህን እንደ ሽልማት አድርጎ ይሰጠኛል፤+ ይሁንና ለእኔ ብቻ ሳይሆን የእሱን መገለጥ ለሚናፍቁ ሁሉ ነው።
9 ወደ እኔ ቶሎ ለመምጣት የተቻለህን ሁሉ አድርግ። 10 ዴማስ+ በአሁኑ ጊዜ ያለውን ሥርዓት* ወዶ፣ ትቶኝ ወደ ተሰሎንቄ ሄዷልና፤ ቄርቂስ ወደ ገላትያ፣ ቲቶ ደግሞ ወደ ድልማጥያ ሄደዋል። 11 አብሮኝ ያለው ሉቃስ ብቻ ነው። ማርቆስ በአገልግሎት ስለሚረዳኝ ከአንተ ጋር ይዘኸው ና። 12 ቲኪቆስን+ ግን ወደ ኤፌሶን ልኬዋለሁ። 13 ስትመጣ በጥሮአስ፣ ካርጶስ ጋ የተውኩትን ካባ እንዲሁም የመጽሐፍ ጥቅልሎቹን በተለይም ብራናዎቹን* አምጣልኝ።
14 የመዳብ አንጥረኛው እስክንድር ብዙ ጉዳት አድርሶብኛል። ይሖዋ* እንደ ሥራው ይከፍለዋል።+ 15 አንተም ከእሱ ተጠንቀቅ፤ መልእክታችንን ክፉኛ ተቃውሟልና።
16 የመጀመሪያ መከላከያዬን ባቀረብኩበት ወቅት ሁሉም ትተውኝ ሄዱ እንጂ ከእኔ ጎን የቆመ ማንም አልነበረም፤ አምላክ ይህን አይቁጠርባቸው። 17 ሆኖም የስብከቱ ሥራ በእኔ አማካኝነት ሙሉ በሙሉ እንዲፈጸምና ብሔራት ሁሉ እንዲሰሙት ጌታ አጠገቤ ቆሞ ኃይል ሰጠኝ፤+ ከአንበሳ አፍም ዳንኩ።+ 18 ጌታ ከክፉ ሥራ ሁሉ ይታደገኛል፤ እንዲሁም አድኖኝ ለሰማያዊ መንግሥቱ ያበቃኛል።+ ለእሱ ለዘላለም ክብር ይሁን። አሜን።
19 ለጵርስቅላና ለአቂላ+ እንዲሁም ለኦኔሲፎሮስ+ ቤተሰብ ሰላምታ አቅርብልኝ።
20 ኤርስጦስ+ በቆሮንቶስ ቀርቷል፤ ጢሮፊሞስ+ ግን ስለታመመ በሚሊጢን ትቼዋለሁ። 21 ክረምቱ ከመግባቱ በፊት ለመምጣት የተቻለህን ሁሉ አድርግ።
ኤውቡሉስ ሰላም ብሎሃል፤ እንዲሁም ጱዴስ፣ ሊኖስ፣ ቅላውዲያና ወንድሞች ሁሉ ሰላምታቸውን ልከውልሃል።
22 ጌታ ከምታሳየው መንፈስ ጋር ይሁን። ጸጋው ከእናንተ ጋር ይሁን።
ወይም “እንደ እሳት እንድታቀጣጥል።”
ወይም “የጤናማ፤ ጠቃሚ የሆነ።”
ወይም “ንድፍ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “ኃይል ማግኘትህን ቀጥል።”
“በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “የተሟላ ምሥክርነት እየሰጠህ።”
ወይም “የሚሰሙትን ሰዎች ከማጥፋት፤ ከማፍረስ።”
እንዲህ ያሉ ንግግሮችን የሚናገሩ ሰዎችንም ሊያመለክት ይችላል።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “ዕቃ።”
ወይም “ከሰው ጋር ባለው ግንኙነት ዘዴኛ።”
“ልዝብ፤ ለስላሳ፤ ሸካራ ያልሆነ” የሚል ትርጉም አለው።
የአስተሳሰብ ለውጥ ማድረግን ያመለክታል።
ወይም “ለሰው ፍቅር የሌላቸው።”
ወይም “ለማረምና።”
ወይም “ጤናማውን ትምህርት፤ ጠቃሚውን ትምህርት።”
ወይም “መስማት የሚፈልጉትን እንዲነግሯቸው።”
ወይም “ምሥራቹን መስበክህን ቀጥል።”
ፊልጵ 2:17 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።
ወይም “የአሁኑን ዘመን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ከቆዳ የተዘጋጁትን ጥቅልሎች ያመለክታል።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።