የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • nwt ሶፎንያስ 1:1-3:20
  • ሶፎንያስ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሶፎንያስ
  • አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
ሶፎንያስ

ሶፎንያስ

1 በይሁዳ ንጉሥ በአምዖን+ ልጅ በኢዮስያስ+ ዘመን ወደ ሕዝቅያስ ልጅ፣ ወደ አማርያህ ልጅ፣ ወደ ጎዶልያስ ልጅ፣ ወደ ኩሺ ልጅ፣ ወደ ሶፎንያስ* የመጣው የይሖዋ ቃል ይህ ነው፦

 2 “ማንኛውንም ነገር ሙሉ በሙሉ ከምድር ገጽ ጠራርጌ አጠፋለሁ” ይላል ይሖዋ።+

 3 “ሰውንና እንስሳን ጠራርጌ አጠፋለሁ።

የሰማይ ወፎችንና የባሕር ዓሣን

እንዲሁም ማሰናከያዎቹንና*+ ክፉ ሰዎችን ጠራርጌ አጠፋለሁ፤+

ደግሞም የሰውን ዘር ከምድር ገጽ አስወግዳለሁ” ይላል ይሖዋ።

 4 “በይሁዳና በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ሁሉ ላይ

እጄን እዘረጋለሁ፤

የባአልን ቀሪዎች* ሁሉና የባዕድ አምላክ ካህናትን ስም

ከሌሎቹ ካህናት ጋር ከዚህ ስፍራ ፈጽሜ አስወግዳለሁ፤+

 5 በቤት ጣሪያዎች ላይ ሆነው ለሰማያት ሠራዊት የሚሰግዱትን+

እንዲሁም በአንድ በኩል ለይሖዋ እየሰገዱና ታማኝ እንደሚሆኑ ቃል እየገቡ+

በሌላ በኩል ግን ለማልካም ታማኝ እንደሚሆኑ ቃል የሚገቡትን አጠፋለሁ፤+

 6 ደግሞም ይሖዋን ከመከተል ወደኋላ የሚሉትን፣+

ይሖዋን የማይፈልጉትን ወይም እሱን የማይጠይቁትን አጠፋለሁ።”+

 7 በሉዓላዊው ጌታ በይሖዋ ፊት ዝም በሉ፤ የይሖዋ ቀን ቀርቧልና።+

ይሖዋ መሥዋዕት አዘጋጅቷል፤ የጠራቸውን ቀድሷል።

 8 “በይሖዋ የመሥዋዕት ቀን መኳንንቱን፣

የንጉሡን ወንዶች ልጆችና+ የባዕዳንን ልብስ የሚለብሱትን ሁሉ እቀጣለሁ።

 9 በዚያም ቀን መድረኩ* ላይ የሚወጡትን ሁሉ፣

የጌቶቻቸውንም ቤት በዓመፅና በማታለል የሚሞሉትን እቀጣለሁ።

10 በዚያም ቀን” ይላል ይሖዋ፣

“ከዓሣ በር+ የጩኸት ድምፅ፣

ከከተማዋም ሁለተኛ ክፍል+ ዋይታ፣

ከኮረብቶቹም ታላቅ ሁከት ይሰማል።

11 እናንተ የማክተሽ* ነዋሪዎች፣ ዋይ በሉ፤

ነጋዴዎቹ ሁሉ እንዳልነበሩ ሆነዋልና፤*

ብር የሚመዝኑትም ሁሉ ጠፍተዋል።

12 በዚያ ጊዜ ኢየሩሳሌምን በመብራት እፈትሻለሁ፤

ደግሞም ቸልተኛ የሆኑትንና*

በልባቸው ‘ይሖዋ መልካምም ሆነ ክፉ ነገር አያደርግም’ የሚሉትን ሰዎች እቀጣለሁ።+

13 ሀብታቸው ይዘረፋል፤ ቤቶቻቸውም ይወድማሉ።+

ቤቶችን ይሠራሉ፤ ሆኖም አይኖሩባቸውም፤

ወይንም ይተክላሉ፤ ሆኖም የወይን ጠጁን አይጠጡም።+

14 ታላቁ የይሖዋ ቀን ቅርብ ነው!+

ቅርብ ነው፤ ደግሞም በፍጥነት እየቀረበ ነው!*+

የይሖዋ ቀን ድምፅ አስፈሪ* ነው።+

በዚያ ተዋጊው ይጮኻል።+

15 ያ ቀን የታላቅ ቁጣ ቀን፣+

የጭንቀትና የሥቃይ ቀን፣+

የአውሎ ነፋስና የጥፋት ቀን፣

የጨለማና የጭጋግ ቀን፣+

የደመናና የድቅድቅ ጨለማ ቀን ይሆናል፤+

16 በተመሸጉ ከተሞችና በቅጥር ማዕዘኖች ላይ ባሉ ረጃጅም ማማዎች ላይ+

የቀንደ መለከትና የጦርነት ሁካታ ድምፅ የሚሰማበት ቀን ይሆናል።+

17 በሰዎች ላይ ጭንቀት አመጣለሁ፤

እነሱም እንደ ዕውር ይሄዳሉ፤+

ምክንያቱም በይሖዋ ላይ ኃጢአት ሠርተዋል።+

ደማቸው እንደ አቧራ፣

አንጀታቸውም እንደ ፋንድያ ይፈስሳል።+

18 በይሖዋ ታላቅ ቁጣ ቀን ብራቸውም ሆነ ወርቃቸው ሊያድናቸው አይችልም፤+

መላዋ ምድር በቅንዓቱ እሳት ትበላለች፤+

ምክንያቱም በምድር ላይ የሚኖሩትን ሁሉ በአሰቃቂ ሁኔታ ያጠፋቸዋል።”+

2 እናንተ ኀፍረት የማይሰማችሁ ሕዝቦች ሆይ፣+

በአንድነት ተሰብሰቡ፤ አዎ ተሰብሰቡ።+

 2 የተላለፈው ውሳኔ ከመፈጸሙ በፊት፣

ቀኑ እንደ ገለባ ከማለፉ በፊት፣

የሚነደው የይሖዋ ቁጣ ሳይመጣባችሁ፣+

የይሖዋ የቁጣ ቀን ሳይደርስባችሁ፣

 3 እናንተ የጽድቅ ድንጋጌዎቹን* የምታከብሩ፣

በምድር ላይ የምትኖሩ የዋሆች* ሁሉ ይሖዋን ፈልጉ።+

ጽድቅን ፈልጉ፤ የዋህነትን* ፈልጉ።

ምናልባት በይሖዋ የቁጣ ቀን ትሰወሩ ይሆናል።+

 4 ጋዛ የተተወች ከተማ ትሆናለችና፤

አስቀሎንም ባድማ ትሆናለች።+

አሽዶድ በጠራራ ፀሐይ* ትባረራለች፤

ኤቅሮንም ከሥሯ ትመነገላለች።+

 5 “በባሕሩ ዳርቻ ለሚኖረው ሕዝብ ይኸውም ለከሪታውያን ብሔር ወዮለት!+

የይሖዋ ቃል በአንተ ላይ ነው።

የፍልስጤማውያን ምድር የሆንሽው ከነአን ሆይ፣ አጠፋሻለሁ፤

አንድም ነዋሪ አይተርፍም።

 6 የባሕሩ ዳርቻም መሰማሪያ ይሆናል፤

ለእረኞች የውኃ ጉድጓድና ለበጎች ከድንጋይ የተሠራ ጉረኖ ይኖረዋል።

 7 ከይሁዳ ቤት ለቀሩት ሰዎች መኖሪያ ስፍራ ይሆናል፤+

በዚያም የግጦሽ ቦታ ያገኛሉ።

በምሽት በአስቀሎን ቤቶች ውስጥ ይተኛሉ።

አምላካቸው ይሖዋ ትኩረቱን በእነሱ ላይ ያደርጋልና፤*

የተማረኩባቸውንም ሰዎች መልሶ ይሰበስባል።”+

 8 “ሞዓብ የሰነዘረችውን ነቀፋና+ የአሞናውያንን ስድብ ሰምቻለሁ፤+

እነሱ በሕዝቤ ላይ ተሳልቀዋል፤ ግዛታቸውንም ለመውሰድ በእብሪት ዝተዋል።+

 9 ስለዚህ በሕያውነቴ እምላለሁ” ይላል የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ፣

“ሞዓብ እንደ ሰዶም፣+

አሞናውያንም እንደ ገሞራ ይሆናሉ፤+

ሳማ የወረሰው ምድርና የጨው ጉድጓድ ይሆናሉ፤ ለዘለቄታውም ባድማ ሆነው ይቀራሉ።+

የሕዝቤ ቀሪዎች ይዘርፏቸዋል፤

ከገዛ ብሔሬ የቀሩት ሰዎችም ይወርሷቸዋል።

10 ከኩራታቸው የተነሳ ይህ ይደርስባቸዋል፤+

ምክንያቱም በሠራዊት ጌታ በይሖዋ ሕዝብ ላይ ተሳልቀዋል፤ ራሳቸውንም ከፍ ከፍ አድርገዋል።

11 ይሖዋ በእነሱ ዘንድ የተፈራ* ይሆናል፤

በምድር ላይ ያሉትን አማልክት ሁሉ እንዳልነበሩ ያደርጋቸዋልና፤*

የብሔራት ደሴቶች ሁሉ በያሉበት ሆነው

ለእሱ ይሰግዳሉ።*+

12 እናንተም ኢትዮጵያውያን በሰይፌ ትገደላላችሁ።+

13 እሱ እጁን ወደ ሰሜን ይዘረጋል፤ አሦርንም ያጠፋል፤

ነነዌንም ባድማና እንደ በረሃ ደረቅ ያደርጋታል።+

14 መንጎች ይኸውም ሁሉም ዓይነት የዱር እንስሳት* በውስጧ ይተኛሉ።

ሻላ* እና ጃርት በፈራረሱት ዓምዶቿ መካከል ያድራሉ።

የዝማሬ ድምፅ በመስኮት ይሰማል።

ደጃፍ ላይ ፍርስራሽ ይኖራል፤

የአርዘ ሊባኖስ እንጨቶቹ እንዲጋለጡ ያደርጋልና።

15 በልቧ ‘እኔ ብቻ ነኝ፤ ከእኔም በቀር ሌላ የለም’ ስትል የነበረችው

ያለስጋት የተቀመጠችው ኩሩዋ ከተማ ይህች ናት።

ምንኛ አስፈሪ ቦታ ሆነች!

የዱር እንስሳት የሚተኙባት ስፍራ ሆናለች።

በእሷ በኩል የሚያልፍ ሁሉ ያፏጫል፤ ራሱንም ይነቀንቃል።”+

3 ዓመፀኛ ለሆነችው፣ ለረከሰችውና ለጨቋኟ ከተማ ወዮላት!+

 2 ማንንም ለመታዘዝ ፈቃደኛ አልሆነችም፤+ ምንም ዓይነት ተግሣጽ አልተቀበለችም።+

በይሖዋ አልታመነችም፤+ ወደ አምላኳም አልቀረበችም።+

 3 በውስጧ ያሉት መኳንንቷ የሚያገሱ አንበሶች ናቸው።+

ፈራጆቿ የሌሊት ተኩላዎች ናቸው፤

ለጠዋት ምንም ሳያስቀሩ አጥንቱን ሁሉ ይግጣሉ።

 4 ነቢያቷ እብሪተኞችና አታላዮች ናቸው።+

ካህናቷ ቅዱስ የሆነውን ነገር ያረክሳሉ፤+

በሕጉ ላይ ያምፃሉ።+

 5 በመካከሏ ያለው ይሖዋ ጻድቅ ነው፤+ እሱ ምንም ዓይነት ስህተት አይፈጽምም።

ፍርዱን እንደማይነጥፍ የንጋት ብርሃን፣

በየማለዳው ያሳውቃል።+

ክፉ ሰው ግን ኀፍረት የሚባል ነገር አያውቅም።+

 6 “ብሔራትን አጥፍቻለሁ፤ በቅጥር ማዕዘኖች ላይ ያሉ ማማዎቻቸው ወድመዋል።

ማንም ሰው እንዳያልፍባቸው መንገዶቻቸውን አፍርሻለሁ።

ከተሞቻቸው ፈራርሰዋል፤ በዚያ አንድም ሰው የለም፤ ነዋሪም አይገኝባቸውም።+

 7 እኔም ‘በእርግጥ ትፈሪኛለሽ፤ ተግሣጽም* ትቀበያለሽ’ አልኩ፤+

ይህም መኖሪያዋ እንዳይጠፋ ነው፤+

ለሠራችው ኃጢአት ሁሉ ተጠያቂ አደርጋታለሁ።*

እነሱ ግን ብልሹ ነገር ለመፈጸም ይበልጥ ጓጉ።+

 8 ‘ስለዚህ ለመበዝበዝ እስከምነሳበት ቀን* ድረስ

እኔን በተስፋ ተጠባበቁ’*+ ይላል ይሖዋ፤

‘ብሔራትን ለመሰብሰብ፣ መንግሥታትን ለማከማቸት፣

በእነሱም ላይ መዓቴንና የሚነደውን ቁጣዬን ሁሉ ለማውረድ የፍርድ ውሳኔ አስተላልፌአለሁና፤+

መላዋ ምድር በቅንዓቴ እሳት ትበላለች።+

 9 በዚያን ጊዜ ሰዎች ሁሉ የይሖዋን ስም እንዲጠሩና

እጅ ለእጅ ተያይዘው እንዲያገለግሉት*

ቋንቋቸውን ለውጬ ንጹሕ ቋንቋ እሰጣቸዋለሁ።’+

10 የሚለምኑኝ ሰዎች ይኸውም የተበተኑት ሕዝቦቼ

የኢትዮጵያ ወንዞች ከሚገኙበት ስፍራ ስጦታ ያመጡልኛል።+

11 በዚያን ቀን በእኔ ላይ በማመፅ በፈጸምሻቸው ሥራዎች ሁሉ

ለኀፍረት አትዳረጊም፤+

በዚያን ጊዜ በትዕቢት ጉራ የሚነዙትን ከመካከልሽ አስወግዳለሁና፤

አንቺም ከእንግዲህ በተቀደሰው ተራራዬ ላይ ፈጽሞ አትታበዪም።+

12 እኔም ትሑት የሆነና ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ሕዝብ በመካከላችሁ እንዲቀር አደርጋለሁ፤+

እነሱም የይሖዋን ስም መጠጊያቸው ያደርጉታል።

13 የእስራኤል ቀሪዎች+ ምንም ዓይነት ክፋት አይሠሩም፤+

ውሸት አይናገሩም፤ በአፋቸውም ውስጥ አታላይ ምላስ አይገኝም፤

ይልቁንም ይመገባሉ፤* ይተኛሉ፤ የሚያስፈራቸውም አይኖርም።”+

14 የጽዮን ሴት ልጅ ሆይ፣ እልል በይ!

እስራኤል ሆይ፣ በድል አድራጊነት ጩኺ!+

የኢየሩሳሌም ሴት ልጅ ሆይ፣ በሙሉ ልብሽ ደስ ይበልሽ፤ ሐሴትም አድርጊ!+

15 ይሖዋ በአንቺ ላይ የተላለፈውን ፍርድ ሽሯል።+

ጠላትሽን ከአንቺ መልሷል።+

የእስራኤል ንጉሥ ይሖዋ በመካከልሽ ነው።+

ከእንግዲህ ወዲህ ጥፋት አያስፈራሽም።+

16 በዚያን ቀን ለኢየሩሳሌም እንዲህ ይባላል፦

“ጽዮን ሆይ፣ አትፍሪ።+

እጆችሽ አይዛሉ።

17 አምላክሽ ይሖዋ በመካከልሽ ነው።+

እንደ ኃያል ተዋጊ ያድናል።

በታላቅ ደስታ በአንቺ ሐሴት ያደርጋል።+

ለአንቺ ፍቅር በማሳየቱ ረክቶ ዝም ይላል።*

በእልልታ በአንቺ ሐሴት ያደርጋል።

18 በበዓላትሽ ላይ ባለመገኘታቸው ያዘኑትን ሰዎች እሰበስባለሁ፤+

ለእሷ ሲሉ በደረሰባቸው ነቀፋ የተነሳ ወደ አንቺ አልመጡም።+

19 እነሆ፣ በዚያን ጊዜ በሚጨቁኑሽ ሁሉ ላይ እርምጃ እወስዳለሁ፤+

የምታነክሰውንም አድናታለሁ፤+

የተበተነችውንም እሰበስባለሁ።+

ኀፍረት በተከናነቡበት ምድር ሁሉ

እንዲወደሱና ዝና* እንዲያተርፉ አደርጋቸዋለሁ።

20 በዚያን ጊዜ መልሼ አመጣችኋለሁ፤

አዎ፣ በዚያን ጊዜ እሰበስባችኋለሁ።

ተማርከው የተወሰዱባችሁን ሰዎች በፊታችሁ መልሼ በምሰበስብበት ጊዜ+

በምድር ሕዝቦች ሁሉ መካከል ዝና* እንድታተርፉና እንድትወደሱ አደርጋለሁና”+ ይላል ይሖዋ።

“ይሖዋ ሸሸገ (ተንከባከበ)” የሚል ትርጉም አለው።

ከጣዖት አምልኮ ጋር ንክኪ ያላቸውን ቁሳቁሶች ወይም ተግባሮች የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም።

ወይም “ርዝራዦች።”

ወይም “ደፉ።” የንጉሡን ዙፋን መድረክ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።

በዓሣ በር አቅራቢያ የሚገኝ ኢየሩሳሌም ውስጥ ያለ ቦታ ሳይሆን አይቀርም።

ቃል በቃል “ጸጥ ተደርገዋልና።”

ቃል በቃል “በአተላቸው ላይ የረጉትንና።” በወይን መጭመቂያ ውስጥ እንደሚሆነው ማለት ነው።

ወይም “እጅግ እየተቻኮለ ነው!”

ቃል በቃል “መራራ።”

ቃል በቃል “ፍርዶቹን።”

ወይም “ትሑታን።”

ወይም “ትሕትናን።”

ወይም “በቀትር።”

ወይም “እንክብካቤ ያደርግላቸዋልና።”

ወይም “የሚያሸብር።”

ወይም “ያመነምናቸዋልና።”

ወይም “እሱን ያመልኩታል።”

ቃል በቃል “አንድ ብሔር ያለው እንስሳ ሁሉ።”

ወይም “ገርጌሶ።” ጠፍጠፍ ያለ ረጅም መንቆር ያለው ትልቅ አሞራ።

ወይም “እርማትም።”

ወይም “እቀጣታለሁ።”

“ምሥክር ሆኜ እስከምነሳበት ቀን” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “እኔን በትዕግሥት ጠብቁ።”

ወይም “በአንድነት እንዲያመ​ልኩት።”

ወይም “ይግጣሉ።”

ወይም “ጸጥ ይላል፤ ያርፋል፤ ስሜቱ ይረ​ጋጋል።”

ቃል በቃል “ስም።”

ቃል በቃል “ስም።”

    የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ ጽሑፎች (2011-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ