ለቆላስይስ ሰዎች የተጻፈ ደብዳቤ
1 በአምላክ ፈቃድ የክርስቶስ ኢየሱስ ሐዋርያ ከሆነው ከጳውሎስና ከወንድማችን ከጢሞቴዎስ፣+ 2 በቆላስይስ ለሚገኙ ከክርስቶስ ጋር አንድነት ላላቸው ታማኝ የሆኑ ቅዱሳን ወንድሞች፦
አባታችን ከሆነው አምላክ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።
3 ስለ እናንተ ስንጸልይ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አባት የሆነውን አምላክ ሁልጊዜ እናመሰግናለን፤ 4 ምክንያቱም በክርስቶስ ኢየሱስ ላይ ስላላችሁ እምነትና ለቅዱሳን ሁሉ ስለምታሳዩት ፍቅር ሰምተናል፤ 5 ይህም የሆነው በሰማይ ከሚጠብቃችሁ ተስፋ የተነሳ ነው።+ ይህን ተስፋ በተመለከተ ቀደም ሲል የሰማችሁት፣ በተነገራችሁ የእውነት መልእክት ይኸውም በምሥራቹ አማካኝነት ሲሆን 6 ይህም ምሥራች ወደ እናንተ ደርሷል። ምሥራቹ በመላው ዓለም እየተስፋፋና ፍሬ እያፈራ+ እንደሆነ ሁሉ የአምላክን ጸጋ እውነት ከሰማችሁበትና በትክክል ካወቃችሁበት ቀን አንስቶ በእናንተም መካከል እያደገና ፍሬ እያፈራ ነው። 7 የክርስቶስ ታማኝ አገልጋይ ሆኖ በእኛ ምትክ ከሚሠራውና አብሮን ባሪያ ከሆነው ከተወዳጁ ኤጳፍራ+ የተማራችሁት ይህን ነው። 8 ደግሞም ስለ መንፈሳዊ ፍቅራችሁ ነግሮናል።
9 ከዚህም የተነሳ ይህን ከሰማንበት ቀን አንስቶ ከጥበብና ከመንፈሳዊ ግንዛቤ+ ሁሉ ጋር በፈቃዱ ትክክለኛ እውቀት+ ትሞሉ ዘንድ ስለ እናንተ መጸለያችንንና መለመናችንን አላቋረጥንም፤+ 10 ይህም በመልካም ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁና ስለ አምላክ ትክክለኛ እውቀት በመቅሰም+ እያደጋችሁ ስትሄዱ ለይሖዋ* በሚገባ ሁኔታ እንድትመላለሱና እሱን ሙሉ በሙሉ እንድታስደስቱ ነው፤ 11 በትዕግሥትና በደስታ ሁሉንም ነገር በጽናት እንድትቋቋሙ የአምላክ ታላቅ ኃይል የሚያስፈልጋችሁን ብርታት ሁሉ ይስጣችሁ፤+ 12 ደግሞም በብርሃን ውስጥ ያሉት ቅዱሳን ከሚያገኙት ውርሻ+ ለመካፈል ያበቃችሁን አባት አመስግኑ።
13 እሱ ከጨለማው ሥልጣን ታድጎን+ ወደሚወደው ልጁ መንግሥት አሻግሮናል፤ 14 ልጁም ቤዛውን በመክፈል ነፃ እንድንወጣ ይኸውም የኃጢአት ይቅርታ እንድናገኝ አድርጎናል።+ 15 እሱ የማይታየው አምላክ አምሳልና+ የፍጥረት ሁሉ በኩር ነው፤+ 16 ምክንያቱም በሰማያትና በምድር ያሉ ሌሎች ነገሮች በሙሉ፣ የሚታዩትና የማይታዩት ነገሮች፣ ዙፋኖችም ሆኑ ጌትነት፣ መንግሥታትም ሆኑ ሥልጣናት የተፈጠሩት በእሱ አማካኝነት ነው።+ ሌሎች ነገሮች በሙሉ የተፈጠሩት በእሱ በኩልና+ ለእሱ ነው። 17 በተጨማሪም እሱ ከሌሎች ነገሮች ሁሉ በፊት ነው፤+ ሌሎች ነገሮች ሁሉ ወደ ሕልውና የመጡትም በእሱ አማካኝነት ነው፤ 18 እሱ የአካሉ ማለትም የጉባኤው ራስ ነው።+ በሁሉም ነገር ቀዳሚ መሆን እንዲችልም እሱ የመጀመሪያ፣ ከሙታን መካከልም በኩር ነው፤+ 19 ይህም የሆነው እሱ በሁሉም ነገር ሙሉ እንዲሆን አምላክ ስለፈለገ ነው፤+ 20 እንዲሁም በመከራው እንጨት* ላይ ባፈሰሰው ደም+ አማካኝነት ሰላም በመፍጠር ሌሎቹን ነገሮች ሁሉ ይኸውም በምድርም ሆነ በሰማያት ያሉትን ነገሮች ሁሉ በእሱ በኩል ከራሱ ጋር ለማስታረቅ ስለወደደ ነው።+
21 በእርግጥ እናንተ በአንድ ወቅት አእምሯችሁ በክፉ ሥራዎች ላይ ያተኮረ ስለነበር ከአምላክ የራቃችሁና ጠላቶች ነበራችሁ፤ 22 አሁን ግን እሱ ቅዱሳንና እንከን የሌለባችሁ እንዲሁም ከማንኛውም ክስ ነፃ የሆናችሁ አድርጎ በፊቱ ሊያቀርባችሁ ስለፈለገ+ ራሱን ለሞት አሳልፎ በሰጠው ሰው ሥጋዊ አካል አማካኝነት ከራሱ ጋር አስታርቋችኋል፤ 23 በእርግጥ ይህ የሚሆነው በእምነት መሠረት ላይ ታንጻችሁና+ ተደላድላችሁ በመቆም፣+ የሰማችሁት ምሥራች ካስገኘላችሁ ተስፋ ሳትወሰዱ በእምነት ጸንታችሁ ስትኖሩ ነው፤+ ይህም ምሥራች ከሰማይ በታች ላለ ፍጥረት ሁሉ* ተሰብኳል።+ እኔም ጳውሎስ የዚህ ምሥራች አገልጋይ ሆኛለሁ።+
24 ለእናንተ ስል በተቀበልኩት መከራ+ አሁን እየተደሰትኩ ነው፤ በክርስቶስ የተነሳ በአካሌ ላይ የሚደርሰው መከራ በዚህ ብቻ አያበቃም። ይህ መከራ እየደረሰብኝ ያለው ለአካሉ+ ይኸውም ለጉባኤው+ ስል ነው። 25 የአምላክን ቃል በተሟላ ሁኔታ እሰብክ ዘንድ ለእናንተ ጥቅም ሲባል ከአምላክ ከተሰጠኝ የመጋቢነት ሥራ+ ጋር በሚስማማ መንገድ የዚህ ጉባኤ አገልጋይ ሆኛለሁ፤ 26 ይህም ቃል ካለፉት ሥርዓቶችና* ካለፉት ትውልዶች አንስቶ ተሰውሮ+ የቆየው ቅዱስ ሚስጥር+ ነው። አሁን ግን ለቅዱሳኑ ተገልጧል።+ 27 በተጨማሪም አምላክ በአሕዛብ መካከል የዚህን ቅዱስ ሚስጥር ታላቅ ብልጽግና ለቅዱሳኑ ያሳውቅ ዘንድ ወዷል፤+ ይህ ቅዱስ ሚስጥር የክብሩ ተስፋ+ የሆነውና ከእናንተ ጋር አንድነት ያለው ክርስቶስ ነው። 28 እያንዳንዱን ሰው የጎለመሰ* የክርስቶስ ደቀ መዝሙር አድርገን ለአምላክ ማቅረብ እንድንችል ሰውን ሁሉ እያሳሰብንና በጥበብ ሁሉ እያስተማርን የምናውጀው ስለ እሱ ነው።+ 29 ይህን ዳር ለማድረስ፣ በውስጤ እየሠራ ባለው በእሱ ብርቱ ኃይል አማካኝነት አቅሜ በሚፈቅደው ሁሉ በትጋት እየሠራሁ ነው።+
2 ለእናንተና በሎዶቅያ+ ላሉት እንዲሁም በአካል አይተውኝ ለማያውቁ* ሁሉ ስል ምን ያህል ብርቱ ትግል እያደረግኩ እንዳለሁ እንድትገነዘቡ እፈልጋለሁ። 2 ይህም ልባቸው እንዲጽናና+ እንዲሁም ስምም ሆነው በፍቅር እርስ በርስ እንዲተሳሰሩ ነው።+ በዚህ መንገድ ታላቅ የሆነውን ብልጽግና ይኸውም ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ የሆኑበትን የእውነት ግንዛቤ ማግኘት ብሎም የአምላክ ቅዱስ ሚስጥር ስለሆነው ስለ ክርስቶስ+ ትክክለኛ እውቀት መቅሰም ይችላሉ። 3 የጥበብና የእውቀት ውድ ሀብት ሁሉ በሚገባ ተሰውሮ የሚገኘው በክርስቶስ ውስጥ ነው።+ 4 ይህን የምለው ማንም ሰው አግባብቶ እንዳያታልላችሁ ነው። 5 በአካል ከእናንተ ጋር ባልሆንም በመንፈስ ግን ከእናንተ ጋር ስለሆንኩ ሥርዓት ያለውን አኗኗራችሁንና+ በክርስቶስ ላይ ያላችሁን ጽኑ እምነት+ በማየት እየተደሰትኩ ነው።
6 ስለዚህ ጌታ ክርስቶስ ኢየሱስን እንደተቀበላችሁት ሁሉ ከእሱ ጋር በአንድነት መመላለሳችሁን ቀጥሉ፤ 7 በተማራችሁት መሠረት በእሱ ላይ ሥር ሰዳችሁና ታንጻችሁ ኑሩ፤+ እንዲሁም በእምነት ጸንታችሁ መኖራችሁን ቀጥሉ፤+ ብዙ ምስጋናም አቅርቡ።+
8 በክርስቶስ ላይ ሳይሆን በዓለም መሠረታዊ ነገሮች እንዲሁም በሰው ወግ ላይ በተመሠረተ ፍልስፍናና ከንቱ ማታለያ+ ማንም ማርኮ* እንዳይወስዳችሁ ተጠንቀቁ፤ 9 ምክንያቱም መለኮታዊው ባሕርይ በተሟላ ሁኔታ በአካል የሚኖረው በእሱ ውስጥ ነው።+ 10 በመሆኑም የገዢነትና የሥልጣን ሁሉ ራስ+ በሆነው በእሱ አማካኝነት ሁሉንም ነገር አግኝታችኋል። 11 ከእሱ ጋር ባላችሁ ዝምድና የተነሳ በእጅ ባልተከናወነ ግርዘት ተገርዛችኋል፤ ይህም ኃጢአተኛውን ሥጋዊ አካል በማስወገድ+ የሚከናወን የክርስቶስ አገልጋዮች ግርዘት ነው።+ 12 የእሱን ዓይነት ጥምቀት በመጠመቅ ከእሱ ጋር ተቀብራችሁ ነበርና፤+ ከእሱ ጋር ባላችሁ ዝምድና የተነሳም አብራችሁ ተነስታችኋል፤+ ይህም የሆነው እሱን ከሞት ያስነሳው+ አምላክ ባከናወነው ታላቅ ሥራ ላይ ባላችሁ እምነት አማካኝነት ነው።
13 በተጨማሪም በበደላችሁና በሥጋችሁ አለመገረዝ የተነሳ ሙታን የነበራችሁ ቢሆንም አምላክ ከእሱ ጋር ሕያዋን አድርጓችኋል።+ በደላችንን ሁሉ በደግነት ይቅር ብሎናል፤+ 14 ድንጋጌዎችን የያዘውንና+ ይቃወመን የነበረውን+ በእጅ የተጻፈ ሰነድም ደመሰሰው።+ በመከራው እንጨት* ላይ ቸንክሮም ከመንገድ አስወገደው።+ 15 በመከራው እንጨት* አማካኝነት መንግሥታትንና ባለሥልጣናትን ገፎ በድል ሰልፍ እየመራ እንደ ምርኮኛ በአደባባይ እንዲታዩ አድርጓቸዋል።+
16 ስለዚህ በምትበሉትም ሆነ በምትጠጡት ወይም በዓልን፣ የወር መባቻንና*+ ሰንበትን በማክበር+ ረገድ ማንም ሰው አይፍረድባችሁ።+ 17 እነዚህ ለሚመጡት ነገሮች ጥላ ናቸው፤+ እውነተኛው ነገር* ግን የክርስቶስ ነው።+ 18 በውሸት ትሕትናና በመላእክት አምልኮ* የሚደሰት ማንኛውም ሰው ሽልማቱን እንዲያሳጣችሁ አትፍቀዱ።+ እንዲህ ያለ ሰው ባያቸው ነገሮች ላይ ተመሥርቶ “ጥብቅ አቋም የሚይዝ”* ከመሆኑም በላይ ሥጋዊ አስተሳሰቡ በከንቱ እንዲታበይ ያደርገዋል። 19 እነዚህ ሰዎች ራስ+ ከሆነው ጋር በጥብቅ የተቆራኙ አይደሉም፤ መላው አካል በመገጣጠሚያዎችና በጅማቶች አማካኝነት የሚያስፈልገውን ነገር የሚያገኘውና እርስ በርስ ስምም ሆኖ የተያያዘው እንዲሁም የሚያድገው ራስ በሆነው አማካኝነት ነው። ይህም እድገት የሚገኘው ከአምላክ ነው።+
20 የዚህን ዓለም መሠረታዊ ነገሮች በመተው ከክርስቶስ ጋር ከሞታችሁ+ ለድንጋጌዎቹ+ ራሳችሁን በማስገዛት አሁንም የዓለም ክፍል የሆናችሁ በሚመስል ሁኔታ ለምን ትኖራላችሁ? 21 ድንጋጌዎቹም “አትውሰድ፣ አትቅመስ፣ አትንካ” የሚሉ ናቸው። 22 እነዚህ ሁሉ የሰው ትእዛዛትና ትምህርቶች ስለሆኑ ሁሉም ጥቅም ላይ ውለው እንዲጠፉ የተወሰነባቸው ናቸው።+ 23 እነዚህ ነገሮች በገዛ ፈቃድ በሚቀርብ አምልኮና በውሸት ትሕትና፣ ሰውነትን በማሠቃየት+ የሚገለጹ ጥበብ ያለባቸው ነገሮች ቢመስሉም የሥጋን ፍላጎት በማሸነፍ ረገድ አንዳች ፋይዳ የላቸውም።
3 ይሁን እንጂ ከክርስቶስ ጋር አብራችሁ ከተነሳችሁ+ ክርስቶስ በአምላክ ቀኝ+ በተቀመጠበት በላይ ያሉትን ነገሮች ፈልጉ። 2 አእምሯችሁ በምድር ባሉት ነገሮች ላይ ሳይሆን+ ምንጊዜም በላይ ባሉት ነገሮች ላይ እንዲያተኩር አድርጉ።+ 3 እናንተ ሞታችኋልና፤ ሕይወታችሁም ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ ሁኔታ ከክርስቶስ ጋር ተሰውሯል። 4 ሕይወታችን የሆነው ክርስቶስ+ በሚገለጥበት ጊዜ እናንተም ከእሱ ጋር በክብር ትገለጣላችሁ።+
5 ስለዚህ በምድር ያሉትን የአካል ክፍሎቻችሁን ግደሉ፤+ እነሱም የፆታ ብልግና፣* ርኩሰት፣ ልቅ የሆነ የፍትወት ስሜት፣+ መጥፎ ፍላጎትና ጣዖት አምልኮ የሆነው ስግብግብነት ናቸው። 6 በእነዚህ ነገሮች ምክንያት የአምላክ ቁጣ ይመጣል። 7 እናንተም በቀድሞ ሕይወታችሁ በዚህ መንገድ ትኖሩ ነበር።+ 8 አሁን ግን ቁጣን፣ ንዴትን፣ ክፋትንና+ ስድብን+ ሁሉ ከእናንተ አስወግዱ፤ ጸያፍ ንግግርም+ ከአፋችሁ አይውጣ። 9 አንዳችሁ ሌላውን አትዋሹ።+ አሮጌውን ስብዕና* ከነልማዶቹ ገፋችሁ ጣሉ፤+ 10 እንዲሁም ከፈጣሪው አምሳል ጋር በሚስማማ ሁኔታ+ በትክክለኛ እውቀት አማካኝነት እየታደሰ የሚሄደውን አዲሱን ስብዕና ልበሱ፤+ 11 በዚህ ሁኔታ ግሪካዊ ወይም አይሁዳዊ፣ የተገረዘ ወይም ያልተገረዘ፣ የባዕድ አገር ሰው፣ እስኩቴስ፣* ባሪያ ወይም ነፃ ሰው ብሎ ልዩነት የለም፤ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉም ነገር ነው፤ እንዲሁም በሁሉም ነው።+
12 እንግዲህ የአምላክ ምርጦች፣+ ቅዱሳንና የተወደዳችሁ እንደመሆናችሁ መጠን ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄን፣+ ደግነትን፣ ትሕትናን፣+ ገርነትንና+ ትዕግሥትን+ ልበሱ። 13 አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖረው+ እንኳ እርስ በርስ መቻቻላችሁንና በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ።+ ይሖዋ* በነፃ ይቅር እንዳላችሁ ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉ።+ 14 ይሁንና በእነዚህ ነገሮች ሁሉ ላይ ፍቅርን ልበሱ፤+ ፍቅር ፍጹም የሆነ የአንድነት ማሰሪያ ነውና።+
15 በተጨማሪም አምላክ የጠራችሁ አንድ አካል እንድትሆኑና በሰላም እንድትኖሩ ስለሆነ የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይግዛ።*+ እንዲሁም አመስጋኝ መሆናችሁን አሳዩ። 16 የክርስቶስ ቃል ከጥበብ ሁሉ ጋር በተትረፈረፈ ሁኔታ በውስጣችሁ ይኑር። በመዝሙራት፣ ለአምላክ በሚቀርብ ውዳሴና በአመስጋኝነት መንፈስ* በሚዘመሩ መንፈሳዊ ዝማሬዎች ትምህርትና ማበረታቻ* መስጠታችሁን ቀጥሉ፤+ በልባችሁም ለይሖዋ* ዘምሩ።+ 17 በቃልም ሆነ በተግባር የምታደርጉት ነገር ምንም ሆነ ምን አባት የሆነውን አምላክ በኢየሱስ በኩል እያመሰገናችሁ ሁሉንም ነገር በጌታ ኢየሱስ ስም አድርጉት።+
18 ሚስቶች ሆይ፣ የክርስቶስ ተከታዮች ሊያደርጉት የሚገባ ስለሆነ ለባሎቻችሁ ተገዙ።+ 19 ባሎች ሆይ፣ ሚስቶቻችሁን መውደዳችሁን ቀጥሉ፤+ መራራ ቁጣም አትቆጧቸው።*+ 20 ልጆች ሆይ፣ በሁሉም ነገር ለወላጆቻችሁ ታዘዙ፤+ እንዲህ ማድረጋችሁ ጌታን ያስደስተዋልና። 21 አባቶች ሆይ፣ ቅስማቸው እንዳይሰበር* ልጆቻችሁን አታበሳጯቸው።+ 22 ባሪያዎች ሆይ፣ ሰውን ለማስደሰት ብላችሁ ሰብዓዊ ጌቶቻችሁ በሚያዩአችሁ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በቅን ልብ ተነሳስታችሁ ይሖዋን* በመፍራት ጌቶቻችሁ ለሆኑት በሁሉም ነገር ታዛዥ ሁኑ።+ 23 የምታደርጉትን ሁሉ ለሰው ሳይሆን ለይሖዋ* እንደምታደርጉት በማሰብ በሙሉ ነፍሳችሁ* አድርጉት፤+ 24 ከይሖዋ* ዘንድ እንደ ሽልማት የምትቀበሉት ውርሻ እንዳለ ታውቃላችሁና።+ ጌታችንን ክርስቶስን እንደ ባሪያ አገልግሉ። 25 መጥፎ ነገር የሚሠራ የእጁን እንደሚያገኝ የተረጋገጠ ነው፤+ ደግሞም አድልዎ የለም።+
4 ጌቶች ሆይ፣ እናንተም በሰማይ ጌታ እንዳላችሁ በመገንዘብ ባሪያዎቻችሁን በጽድቅና በፍትሕ አስተዳድሯቸው።+
2 በጸሎት ረገድ ዘወትር ንቁ በመሆንና ምስጋና በማቅረብ+ በጽናት ጸልዩ።+ 3 ደግሞም ለእኔ መታሰር ምክንያት የሆነውን ስለ ክርስቶስ የሚገልጸውን ቅዱስ ሚስጥር ማወጅ እንድንችል+ አምላክ የቃሉን በር እንዲከፍትልን ለእኛም ጸልዩልን፤+ 4 ቅዱሱን ሚስጥር የሚገባኝን ያህል በግልጽ እንዳውጅም ጸልዩልኝ።
5 ጊዜያችሁን በተሻለ መንገድ በመጠቀም* በውጭ ካሉት ጋር* ባላችሁ ግንኙነት በጥበብ መመላለሳችሁን ቀጥሉ።+ 6 ለእያንዳንዱ ሰው እንዴት መልስ መስጠት እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ምንጊዜም በጨው+ የተቀመመ ያህል ለዛ ያለው ይሁን።+
7 በጌታ ታማኝ አገልጋይና አብሮኝ ባሪያ የሆነው የተወደደው ወንድሜ ቲኪቆስ+ ስለ እኔ ሁሉንም ነገር ይነግራችኋል። 8 እሱን ወደ እናንተ የምልከው ስላለንበት ሁኔታ እንድታውቁና ልባችሁን እንዲያጽናና ነው። 9 እናንተ ጋ ከነበረው ከታማኙና ከተወደደው ወንድሜ ከአናሲሞስ+ ጋር ይመጣል፤ እነሱም እዚህ እየተከናወነ ስላለው ነገር ሁሉ ያሳውቋችኋል።
10 አብሮኝ የታሰረው አርስጥሮኮስ+ ሰላምታ ያቀርብላችኋል፤ የበርናባስ ዘመድ* የሆነው ማርቆስም+ ሰላም ብሏችኋል (እሱን በተመለከተ ወደ እናንተ ከመጣ እንድትቀበሉት+ መመሪያ ደርሷችኋል)፤ 11 ኢዮስጦስ ተብሎ የሚጠራው ኢየሱስም ሰላምታ ያቀርብላችኋል፤ እነዚህ ከተገረዙት ወገን ናቸው። ለአምላክ መንግሥት አብረውኝ የሚሠሩት እነዚህ ብቻ ናቸው፤ እነሱም የብርታት ምንጭ ሆነውልኛል።* 12 ከእናንተ ጋር የነበረው የክርስቶስ ኢየሱስ ባሪያ የሆነው ኤጳፍራ+ ሰላምታ ልኮላችኋል። በአምላክ ፈቃድ ሁሉ ፍጹምና* ጽኑ እምነት ያላችሁ ሆናችሁ እስከ መጨረሻው እንድትቆሙ ዘወትር በጸሎቱ ስለ እናንተ እየተጋደለ ነው። 13 ስለ እናንተ እንዲሁም በሎዶቅያና በሂራጶሊስ ስላሉት ብዙ እንደሚደክም እኔ ራሴ እመሠክርለታለሁ።
14 የተወደደው ሐኪም ሉቃስ+ ሰላምታ ያቀርብላችኋል፤ ዴማስም+ ሰላም ብሏችኋል። 15 በሎዶቅያ ላሉት ወንድሞችና ለንምፉን እንዲሁም በቤቷ ላለው ጉባኤ+ ሰላምታዬን አቅርቡልኝ። 16 እንዲሁም ይህ ደብዳቤ እናንተ ጋ ከተነበበ በኋላ በሎዶቅያውያን ጉባኤ እንዲነበብና ከሎዶቅያ የሚደርሳችሁ ደብዳቤ ደግሞ እናንተ ጋ እንዲነበብ ዝግጅት አድርጉ።+ 17 በተጨማሪም አርክጳን+ “በጌታ የተቀበልከውን አገልግሎት ከፍጻሜ እንድታደርስ ለአገልግሎቱ ትኩረት ስጥ” በሉት።
18 እኔ ጳውሎስ በገዛ እጄ የጻፍኩላችሁ ሰላምታ ይድረሳችሁ።+ በሰንሰለት ታስሬ+ እንዳለሁ አስታውሱ። የአምላክ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ከሰማይ በታች ባለ ፍጥረት ሁሉ መካከል።”
ወይም “ካለፉት ዘመናትና።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ፍጹም።”
ቃል በቃል “በሥጋ ፊቴን አይተው ለማያውቁ።”
ወይም “አጥምዶ።”
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
“በእሱ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “አዲስ ጨረቃንና።”
ቃል በቃል “አካሉ።”
ወይም “መላእክት በሚያቀርቡት ዓይነት አምልኮ።”
ወይም “ወዳየው ነገር የሚገባ።” አንድ ሰው በአረማውያን አምልኮ ሲታቀፍ ከሚከናወነው ሚስጥራዊ ሥነ ሥርዓት የተወሰደ አባባል ነው።
ግሪክኛ፣ ፖርኒያ። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ቃል በቃል “ሰው።”
“እስኩቴስ” የሚለው ቃል ያልሠለጠነ ሕዝብን ያመለክታል።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “ልባችሁን ይቆጣጠር።”
ወይም “በጸጋ።”
ወይም “ምክር።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “ኃይለኛም አትሁኑባቸው።”
ወይም “ተስፋ እንዳይቆርጡ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
የቃላት መፍቻው ላይ “ነፍስ” የሚለውን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “አመቺ የሆነውን ጊዜ በመግዛት።”
ወይም “የክርስቲያን ጉባኤ አባል ካልሆኑ ሰዎች ጋር።”
የበርናባስ የአጎቱ ወይም የአክስቱ ልጅ ሊሆን ይችላል።
ወይም “በእጅጉ አጽናንተውኛል።”
ወይም “ጎልማሳና።”