ዘኁልቁ
2 ይሖዋ ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦ 2 “እስራኤላውያን ሦስት ነገዶችን ላቀፈው ምድባቸው+ በተሰጠው ቦታ ይስፈሩ፤ እያንዳንዱም ሰው ለአባቶቹ ቤት በቆመው ዓርማ* አጠገብ ይስፈር። ፊታቸውን ወደ መገናኛ ድንኳኑ አድርገው ዙሪያውን ይስፈሩ።
3 “በስተ ምሥራቅ ፀሐይ በምትወጣበት አቅጣጫ በየምድቡ* የሚሰፍረው ሦስት ነገዶችን ያቀፈው የይሁዳ ምድብ ይሆናል፤ የይሁዳ ልጆች አለቃ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን+ ነው። 4 በሠራዊቱ ውስጥ የተመዘገቡትም 74,600 ናቸው።+ 5 ከእሱም ቀጥሎ የሚሰፍረው የይሳኮር ነገድ ይሆናል፤ የይሳኮር ልጆች አለቃ የጹአር ልጅ ናትናኤል+ ነው። 6 በሠራዊቱ ውስጥ የተመዘገቡትም 54,400 ናቸው።+ 7 ከዚያ ቀጥሎ የዛብሎን ነገድ ይስፈር፤ የዛብሎን ልጆች አለቃ የሄሎን ልጅ ኤልያብ+ ነው። 8 በሠራዊቱ ውስጥ የተመዘገቡትም 57,400 ናቸው።+
9 “በይሁዳ ምድብ በሠራዊቱ ውስጥ የተመዘገቡት በአጠቃላይ 186,400 ናቸው። መጀመሪያ ድንኳናቸውን ነቅለው የሚነሱት እነሱ ይሆናሉ።+
10 “ሦስት ነገዶችን ያቀፈው የሮቤል+ ምድብ በየምድቡ* በመሆን በስተ ደቡብ አቅጣጫ ይስፈር፤ የሮቤል ልጆች አለቃ የሸደኡር ልጅ ኤሊጹር+ ነው። 11 በሠራዊቱ ውስጥ የተመዘገቡትም 46,500 ናቸው።+ 12 ከእሱ ቀጥሎ የሚሰፍረው የስምዖን ነገድ ይሆናል፤ የስምዖን ልጆች አለቃ የጹሪሻዳይ ልጅ ሸሉሚኤል+ ነው። 13 በሠራዊቱ ውስጥ የተመዘገቡትም 59,300 ናቸው።+ 14 ከዚያ ቀጥሎ የጋድ ነገድ ይስፈር፤ የጋድ ልጆች አለቃ የረኡዔል ልጅ ኤሊያሳፍ+ ነው። 15 በሠራዊቱ ውስጥ የተመዘገቡትም 45,650 ናቸው።+
16 “በሮቤል ምድብ በሠራዊቱ ውስጥ የተመዘገቡት በአጠቃላይ 151,450 ናቸው፤ በሁለተኛ ደረጃ ድንኳናቸውን ነቅለው የሚነሱት እነሱ ናቸው።+
17 “የመገናኛ ድንኳኑ ከቦታ ወደ ቦታ በሚንቀሳቀስበት ጊዜ+ የሌዋውያኑ ሰፈር በሌሎቹ ሰፈሮች መሃል መሆን ይኖርበታል።
“እነሱም ልክ በሰፈሩበት ሁኔታ እያንዳንዳቸው ቦታቸውን ጠብቀው+ ሦስት ነገድ ባቀፈው ምድባቸው መሠረት መጓዝ ይኖርባቸዋል።
18 “ሦስት ነገዶችን ያቀፈው የኤፍሬም ምድብ በየምድቡ* በመሆን በስተ ምዕራብ አቅጣጫ ይስፈር፤ የኤፍሬም ልጆች አለቃ የአሚሁድ ልጅ ኤሊሻማ+ ነው። 19 በሠራዊቱ ውስጥ የተመዘገቡትም 40,500 ናቸው።+ 20 ከእሱም ቀጥሎ የምናሴ+ ነገድ ይስፈር፤ የምናሴ ልጆች አለቃ የፐዳጹር ልጅ ገማልያል+ ነው። 21 በሠራዊቱ ውስጥ የተመዘገቡትም 32,200 ናቸው።+ 22 ከዚያ ቀጥሎ የቢንያም ነገድ ይስፈር፤ የቢንያም ልጆች አለቃ የጊድኦኒ ልጅ አቢዳን+ ነው። 23 በሠራዊቱ ውስጥ የተመዘገቡትም 35,400 ናቸው።+
24 “በኤፍሬም ምድብ በሠራዊቱ ውስጥ የተመዘገቡት በአጠቃላይ 108,100 ናቸው፤ በሦስተኛ ደረጃ ድንኳናቸውን ነቅለው የሚነሱት እነሱ ናቸው።+
25 “ሦስት ነገዶችን ያቀፈው የዳን ምድብ በየምድቡ* በመሆን በስተ ሰሜን አቅጣጫ ይስፈር፤ የዳን ልጆች አለቃ የአሚሻዳይ ልጅ አሂዔዜር+ ነው። 26 በሠራዊቱ ውስጥ የተመዘገቡትም 62,700 ናቸው።+ 27 ከእሱም ቀጥሎ የሚሰፍረው የአሴር ነገድ ይሆናል፤ የአሴር ልጆች አለቃ የኦክራን ልጅ ፓጊኤል+ ነው። 28 በሠራዊቱ ውስጥ የተመዘገቡትም 41,500 ናቸው።+ 29 ከዚያ ቀጥሎ የንፍታሌም ነገድ ይስፈር፤ የንፍታሌም ልጆች አለቃ የኤናን ልጅ አሂራ+ ነው። 30 በሠራዊቱ ውስጥ የተመዘገቡትም 53,400 ናቸው።+
31 “በዳን ምድብ የተመዘገቡት በአጠቃላይ 157,600 ናቸው። ሦስት ነገዶችን ባቀፈው ምድባቸው መሠረት መጨረሻ ላይ ድንኳናቸውን ነቅለው የሚነሱት እነሱ ናቸው።”+
32 በአባቶቻቸው ቤት መሠረት የተመዘገቡት እስራኤላውያን እነዚህ ነበሩ፤ ወደ ሠራዊቱ ለመቀላቀል በሰፈሩ ውስጥ የተመዘገቡት በአጠቃላይ 603,550 ነበሩ።+ 33 ሌዋውያኑ ግን ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት ከሌሎቹ እስራኤላውያን ጋር+ አልተመዘገቡም።+ 34 እስራኤላውያንም ይሖዋ ሙሴን ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ። እያንዳንዳቸው በየቤተሰባቸውና በየአባቶቻቸው ቤት በመሆን ሦስት ነገዶችን ባቀፈው ምድባቸው+ መሠረት የሰፈሩትም ሆነ ድንኳናቸውን ነቅለው የተነሱት በዚህ መንገድ ነው።+