የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • nwt ሚክያስ 1:1-7:20
  • ሚክያስ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሚክያስ
  • አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
ሚክያስ

ሚክያስ

1 በይሁዳ ነገሥታት+ በኢዮዓታም፣+ በአካዝና+ በሕዝቅያስ+ ዘመን ወደ ሞረሸታዊው ወደ ሚክያስ*+ የመጣው እንዲሁም ሚክያስ ስለ ሰማርያና ስለ ኢየሩሳሌም በራእይ ያየው የይሖዋ ቃል ይህ ነው።”+

 2 “እናንተ ሕዝቦች ሁላችሁም ስሙ!

ምድርና በውስጧ ያሉ ሁሉ፣ በትኩረት ያዳምጡ፤

ይሖዋ ቅዱስ በሆነው ቤተ መቅደሱ ነው።

ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ በእናንተ ላይ ይመሥክርባችሁ።+

 3 እነሆ፣ ይሖዋ ከስፍራው ይወጣል፤

ወደ ታች ወርዶ የምድርን ከፍ ያሉ ቦታዎች ይረግጣል።

 4 በእሳት ፊት እንዳለ ሰምና

በገደል ላይ እንደሚወርድ ውኃ

ተራሮቹ ከሥሩ ይቀልጣሉ፤+

ሸለቆዎቹም* ይሰነጠቃሉ።

 5 ይህ ሁሉ የሆነው በያዕቆብ ዓመፅ፣

በእስራኤልም ቤት ኃጢአት የተነሳ ነው።+

ለያዕቆብ ዓመፅ ተጠያቂው ማን ነው?

ሰማርያ አይደለችም?+

በይሁዳ ለሚገኙት ከፍ ያሉ የማምለኪያ ቦታዎችስ ተጠያቂው ማን ነው?+

ኢየሩሳሌም አይደለችም?

 6 ሰማርያን በሜዳ እንደሚገኝ የፍርስራሽ ክምር፣

ወይን እንደሚተከልበትም ስፍራ አደርጋታለሁ፤

ድንጋዮቿን ወደ ሸለቆ እወረውራለሁ፤*

መሠረቶቿንም አራቁታለሁ።

 7 የተቀረጹ ምስሎቿ በሙሉ ይደቅቃሉ፤+

ለዝሙት አዳሪነቷ የተሰጧት ስጦታዎች ሁሉ በእሳት ይቃጠላሉ።*+

ጣዖቶቿን ሁሉ እደመስሳለሁ።

እነዚህን ሁሉ ነገሮች የሰበሰበችው ለዝሙት አዳሪነቷ በተከፈላት ደሞዝ ነው፤

አሁን ደግሞ እነዚህ ነገሮች በሌላ ቦታ ላሉ ዝሙት አዳሪዎች ክፍያ እንዲሆኑ ይወሰዳሉ።”

 8 ከዚህ የተነሳ ዋይ ዋይ እላለሁ፤ ደግሞም አላዝናለሁ፤+

ባዶ እግሬንና ራቁቴን እሄዳለሁ።+

እንደ ቀበሮዎች አላዝናለሁ፤

እንደ ሰጎኖችም አለቅሳለሁ።

 9 ቁስሏ ሊፈወስ አይችልም፤+

እስከ ይሁዳ ድረስ ተሰራጭቷል።+

መቅሰፍቱ እስከ ሕዝቤ በር፣ እስከ ኢየሩሳሌም ድረስ ተዛምቷል።+

10 “በጌት አታውሩት፤

ከቶም አታልቅሱ።

በቤትአፍራ* በአፈር ላይ ተንከባለሉ።

11 የሻፊር ነዋሪዎች ሆይ፣ እርቃናችሁን ሆናችሁ በኀፍረት ተሻገሩ።

የጻናን ነዋሪዎች አልወጡም።

በቤትዔጼል ዋይታ ይኖራል፤ ለእናንተ ድጋፍ መስጠቱንም ያቆማል።

12 የማሮት ነዋሪዎች መልካም ነገርን ተጠባበቁ፤

ይሁንና ከይሖዋ ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም በር የወረደው ክፉ ነገር ነው።

13 የለኪሶ+ ነዋሪዎች ሆይ፣ ፈረሶቹን ከሠረገላው ጋር እሰሩ።

ለጽዮን ሴት ልጅ የኃጢአት መጀመሪያ ነበራችሁ፤

በእናንተ ውስጥ የእስራኤል ዓመፅ ተገኝቷልና።+

14 ስለዚህ ለሞረሸትጋት የመሰነባበቻ ስጦታ ትሰጫለሽ።

የአክዚብ ቤቶች ለእስራኤል ነገሥታት ማታለያ ነበሩ።

15 የማሬሻህ+ ነዋሪዎች ሆይ፣ ድል አድራጊውን* ገና አመጣባችኋለሁ።+

የእስራኤል ክብር እስከ አዱላም+ ድረስ ይመጣል።

16 ለምትወዷቸው ልጆቻችሁ ፀጉራችሁን ተቆረጡ፤ ራሳችሁንም ተላጩ።

እንደ ንስር ተመለጡ፤

ልጆቻችሁ በግዞት ተወስደውባችኋልና።”+

2 “መጥፎ ነገር ለሚሸርቡና

በአልጋቸው ላይ ሆነው ክፉ ነገር ለሚያውጠነጥኑ ወዮላቸው!

ጠዋት ሲነጋ ያሰቡትን ይፈጽማሉ፤

ምክንያቱም ይህን የሚያደርጉበት ኃይል በእጃቸው ነው።+

 2 እርሻን ይመኛሉ፤ ነጥቀውም ይይዙታል፤+

ቤቶችንም ይመኛሉ፤ ደግሞም ይወስዳሉ፤

የሰውን ቤት፣

የሰውንም ርስት አታለው ይወስዳሉ።+

 3 ስለዚህ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦

‘እነሆ፣ በዚህ ወገን ላይ ጥፋት ላመጣ አስቤአለሁ፤+ እናንተም ከዚህ ጥፋት አታመልጡም።*+

ከእንግዲህ ወዲህ በትዕቢት አትመላለሱም፤+ ይህ የጥፋት ጊዜ ነውና።+

 4 በዚያም ቀን ሰዎች እናንተን አስመልክተው ምሳሌ ይናገራሉ፤

በእናንተም የተነሳ አምርረው ያለቅሳሉ።+

እንዲህ ይላሉ፦ “እኛ ፈጽሞ ጠፍተናል!+

የሕዝቤን ድርሻ ለሌሎች ሰጥቷል፤ ከእኔም ወስዶታል!+

እርሻዎቻችንን ለከዳተኛው ይሰጣል።”

 5 ስለዚህ በይሖዋ ጉባኤ ውስጥ፣

ምድሪቷን ለማከፋፈል በገመድ የሚለካ ሰው አይኖርህም።

 6 “አትስበኩ!” ብለው ይሰብካሉ፤

“እነዚህን ነገሮች መስበክ አይገባቸውም፤

ውርደት አይደርስብንም!”

 7 የያዕቆብ ቤት ሆይ፣

“የይሖዋ መንፈስ አይታገሥም?

እነዚህንስ ነገሮች ያደረገው እሱ ነው?” ሲባል ሰምተሃል?

ቀና በሆነ መንገድ ለሚሄዱ የገዛ ቃሌ መልካም ነገር አያስገኝም?

 8 ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የገዛ ሕዝቤ ጠላት ሆኖ ተነስቷል።

ከጦርነት እንደሚመለሱ ሰዎች በልበ ሙሉነት ከሚያልፉት ላይ

የሚያምረውን ጌጥ ከልብሱ ጋር* በይፋ ገፈፋችሁ።

 9 የሕዝቤን ሴቶች ከሚያምረው ቤታቸው አፈናቀላችኋቸው፤

ክብሬን ከልጆቻቸው ለዘላለም ወሰዳችሁ።

10 ተነሱና ከዚህ ሂዱ፤ ይህ የማረፊያ ቦታ አይደለምና።

ከርኩሰት የተነሳ+ ጥፋት ይመጣል፤ ጥፋቱም ከባድ ነው።+

11 አንድ ሰው ነፋስንና ማታለያን ተከትሎ ቢሄድና

“ስለ ወይን ጠጅና ስለ መጠጥ እሰብክላችኋለሁ” ብሎ ውሸት ቢናገር

ይህ ሰው ለዚህ ሕዝብ ተቀባይነት ያለው ሰባኪ ይሆናል!+

12 ያዕቆብ ሆይ፣ ሁላችሁንም በእርግጥ እሰበስባለሁ፤

ከእስራኤል የቀሩትን ያላንዳች ጥርጥር አንድ ላይ እሰበስባለሁ።+

በጉረኖ ውስጥ እንዳለ በግ፣

በግጦሽ መስክ ላይ እንዳለም መንጋ በአንድነት አኖራቸዋለሁ፤+

ቦታውም በሕዝብ ሁካታ ይሞላል።’+

13 የሚሰብረውም ከፊታቸው ይሄዳል፤

እነሱም ሰብረው በበሩ በኩል ያልፋሉ፤ በዚያም ወጥተው ይሄዳሉ።+

ንጉሣቸው በፊታቸው ያልፋል፤

ይሖዋም ከፊታቸው ይሄዳል።”*+

3 እንዲህ አልኩ፦ “እናንተ የያዕቆብ መሪዎችና

የእስራኤል ቤት ገዢዎች፣ እባካችሁ ስሙ።+

ትክክል የሆነውን ነገር ማወቅ አይገባችሁም?

 2 ሆኖም እናንተ መልካም የሆነውን ትጠላላችሁ፤+ ክፉ የሆነውን ደግሞ ትወዳላችሁ፤+

የሕዝቤን ቆዳ ትገፍፋላችሁ፤ ሥጋቸውንም ከአጥንቶቻቸው ትለያላችሁ።+

 3 የሕዝቤንም ሥጋ ትበላላችሁ፤+

ቆዳቸውንም ትገፍፋላችሁ፤

አጥንቶቻቸውንም ትሰባብራላችሁ፤+

በድስት ውስጥ እንዳለ አጥንትና በአፍላል* ውስጥ እንዳለ ሥጋ ትቆራርጧቸዋላችሁ።

 4 በዚያን ጊዜ እርዳታ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ይጮኻሉ፤

እሱ ግን አይመልስላቸውም።

ክፉ ድርጊት በመፈጸማቸው፣+

በዚያን ጊዜ ፊቱን ይሰውርባቸዋል።+

 5 ሕዝቤ እንዲባዝን በሚያደርጉ፣+

በጥርሳቸው ሲነክሱ*+ ‘ሰላም!’ እያሉ በሚያውጁ፣+

አፋቸው ላይ የሚያደርጉት ነገር በማይሰጣቸው ሰው ሁሉ ላይ ግን ጦርነት በሚያውጁ* ነቢያት ላይ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦

 6 ‘ሌሊት ይመጣባችኋል፤+ ራእይም አታዩም፤+

ጨለማ ብቻ ይሆንባችኋል፤ ሟርትም አታሟርቱም።

ፀሐይ በነቢያቱ ላይ ትጠልቅባቸዋለች፤

ቀኑም ወደ ጨለማ ይለወጥባቸዋል።+

 7 ባለ ራእዮች ኀፍረት ይከናነባሉ፤+

ሟርተኞችም ይዋረዳሉ።

ከአምላክ ዘንድ መልስ ስለማይኖር

ሁሉም አፋቸውን* ይሸፍናሉ።’”

 8 እኔ በበኩሌ ለያዕቆብ ዓመፁን፣ ለእስራኤልም ኃጢአቱን እንድነግር

በይሖዋ መንፈስ ኃይልን፣

ፍትሕንና ብርታትን ተሞልቻለሁ።

 9 ፍትሕን የምትጸየፉና ቀና የሆነውን ነገር ሁሉ የምታጣምሙ፣+

እናንተ የያዕቆብ ቤት መሪዎች፣

የእስራኤልም ቤት ገዢዎች፣ እባካችሁ ይህን ስሙ፤+

10 ጽዮንን ደም በማፍሰስ፣ ኢየሩሳሌምንም በዓመፅ የምትገነቡ፣ ስሙ።+

11 መሪዎቿ* በጉቦ ይፈርዳሉ፤+

ካህናቷ በክፍያ ያስተምራሉ፤+

ነቢያቷም በገንዘብ* ያሟርታሉ።+

ያም ሆኖ “ይሖዋ ከእኛ ጋር አይደለም?+

ምንም ዓይነት ጥፋት አይደርስብንም”+

እያሉ በይሖዋ ይመካሉ።*

12 ስለዚህ በእናንተ የተነሳ

ጽዮን እንደ እርሻ ትታረሳለች፤

ኢየሩሳሌም የፍርስራሽ ክምር ትሆናለች፤+

የቤቱም* ተራራ፣ በጫካ እንዳሉ ከፍ ያሉ ቦታዎች* ይሆናል።+

4 በዘመኑ መጨረሻ*

የይሖዋ ቤት ተራራ+

ከተራሮች አናት በላይ ጸንቶ ይቆማል፤

ከኮረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፤

ሕዝቦችም ወደዚያ ይጎርፋሉ።+

 2 ብዙ ብሔራትም ሄደው እንዲህ ይላሉ፦

“ኑ፤ ወደ ይሖዋ ተራራና

ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ።+

እሱ ስለ መንገዶቹ ያስተምረናል፤

በጎዳናዎቹም እንሄዳለን።”

ሕግ* ከጽዮን፣

የይሖዋም ቃል ከኢየሩሳሌም ይወጣልና።

 3 እሱ በብዙ ሕዝቦች መካከል ይፈርዳል፤+

በሩቅ ካሉ ኃያላን ብሔራት ጋር በተያያዘም ሁሉንም ነገር ያቀናል።*

እነሱ ሰይፋቸውን ማረሻ፣

ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ።+

አንዱ ብሔር በሌላው ብሔር ላይ ሰይፍ አያነሳም፤

ከእንግዲህ ወዲህ ጦርነት አይማሩም።+

 4 እያንዳንዱም ከወይኑና ከበለስ ዛፉ ሥር ይቀመጣል፤*+

የሚያስፈራቸውም አይኖርም፤+

የሠራዊት ጌታ የይሖዋ አፍ ተናግሯልና።

 5 ሕዝቦች ሁሉ፣ እያንዳንዳቸው በአምላካቸው ስም ይሄዳሉ፤

እኛ ግን በአምላካችን በይሖዋ ስም ለዘላለም እንሄዳለን።+

 6 “በዚያ ቀን” ይላል ይሖዋ፣

“የሚያነክሰውን* እሰበስባለሁ፤

ደግሞም የተበተኑትንና

ያንገላታኋቸውን ሰዎች አንድ ላይ እሰበስባለሁ።+

 7 የሚያነክሰው የተወሰኑ ቀሪዎች እንዲኖሩት* አደርጋለሁ፤+

ወደ ሩቅ ስፍራ የተወሰደውንም ኃያል ብሔር አደርገዋለሁ፤+

ይሖዋም ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም

በጽዮን ተራራ በእነሱ ላይ ንጉሥ ሆኖ ይገዛል።

 8 አንተም የመንጋው ማማ፣

የጽዮን+ ሴት ልጅ ጉብታ ሆይ፣

አንተ ወዳለህበት ይመለሳል፤ አዎ፣ የመጀመሪያው* ግዛትህ፣

የኢየሩሳሌም ሴት ልጅ መንግሥት ይመለሳል።+

 9 አሁንስ ድምፅሽን ከፍ አድርገሽ የምትጮኺው ለምንድን ነው?

ንጉሥ የለሽም?

ወይስ አማካሪሽ ጠፍቷል?

ልትወልድ እንደተቃረበች ሴት የምትሠቃዪው ለዚህ ነው?+

10 የጽዮን ሴት ልጅ ሆይ፣ ልትወልድ እንደተቃረበች ሴት

ተንፈራገጪ፤ አቃስቺም፤

አሁን ከከተማ ወጥተሽ በሜዳ ትሰፍሪያለሽና።

እስከ ባቢሎን ድረስ ትሄጃለሽ፤+

በዚያም ይታደግሻል፤+

በዚያ ይሖዋ ከጠላቶችሽ እጅ ይዋጅሻል።+

11 አሁንም ብዙ ብሔራት በአንቺ ላይ ይሰበሰባሉ፤

እነሱም ‘የረከሰች ትሁን፤

ዓይኖቻችንም ይህ በጽዮን ላይ ሲደርስ ይመልከቱ’ ይላሉ።

12 ይሁንና የይሖዋን ሐሳብ አያውቁም፤

ዓላማውንም አይረዱም፤

እሱ ገና እንደታጨደ እህል ወደ አውድማ ይሰበስባቸዋልና።

13 የጽዮን ሴት ልጅ ሆይ፣ ተነስተሽ እህሉን ውቂ፤+

ቀንድሽን ወደ ብረት፣

ሰኮናሽንም ወደ መዳብ እለውጣለሁና፤

አንቺም ብዙ ሕዝቦችን ታደቂያለሽ።+

በማጭበርበር ያገኙት ትርፍ ለይሖዋ የተወሰነ እንዲሆን፣

ሀብታቸውም ለምድር ሁሉ ጌታ ብቻ እንዲውል ታደርጊያለሽ።”+

5 “አንቺ ጥቃት የተሰነዘረብሽ ሴት ልጅ ሆይ፣

አሁን ሰውነትሽን ትተለትያለሽ፤

ዙሪያችንን ተከበናል።+

የእስራኤልን ፈራጅ ጉንጩን በዱላ ይመቱታል።+

 2 ከይሁዳ አእላፋት* መካከል በጣም ትንሽ የሆንሽው

ቤተልሔም ኤፍራታ+ ሆይ፣

ምንጩ ከጥንት፣ ከረጅም ዘመን በፊት የሆነ፣

በእስራኤል ገዢ የሚሆን ከአንቺ ይወጣልኛል።+

 3 ስለዚህ ልትወልድ የተቃረበችው ሴት እስክትወልድ ድረስ

አሳልፎ ይሰጣቸዋል።

የቀሩት ወንድሞቹም ወደ እስራኤል ሕዝብ ይመለሳሉ።

 4 እሱ በይሖዋ ብርታትና በአምላኩ በይሖዋ ስም ታላቅነት ይነሳል፤

መንጋውንም እንደ እረኛ ይጠብቃል።+

እነሱም በዚያ ያለስጋት ይቀመጣሉ፤+

በዚያን ጊዜ ታላቅነቱ እስከ ምድር ዳርቻ ይደርሳልና።+

 5 እሱም ሰላም ያመጣል።+

አሦራዊው ምድራችንን ከወረረና የማይደፈሩ ማማዎቻችንን ከረገጠ+

በእሱ ላይ ሰባት እረኞችን፣ አዎ ከሰው ልጆች መካከል ስምንት አለቆችን* እናስነሳበታለን።

 6 እነሱ የአሦርን ምድር በሰይፍ ይቀጣሉ፤+

የናምሩድንም+ ምድር መግቢያዎች ይቆጣጠራሉ።

አሦራዊው ምድራችንን ሲወርና ክልላችንን ሲረግጥ

እሱ ይታደገናል።+

 7 የተረፉት የያዕቆብ ወገኖች በብዙ ሕዝቦች መካከል፣

ከይሖዋ ዘንድ እንደሚወርድና

ሰውን ተስፋ እንደማያደርግ

ወይም የሰው ልጆችን እንደማይጠባበቅ ጠል፣

በአትክልትም ላይ እንደሚወርድ ካፊያ ይሆናሉ።

 8 በዱር እንስሳት መካከል እንዳለ አንበሳ፣

በሚያልፍበት ጊዜ እየረጋገጠና እየሰባበረ እንደሚሄድ፣

በበግ መንጎች መካከል እንዳለ ደቦል አንበሳ፣

የተረፉት የያዕቆብ ወገኖችም በብሔራት፣

በብዙ ሕዝቦችም መካከል እንዲሁ ይሆናሉ፤

ሊያስጥል የሚችልም አይኖርም።

 9 እጅህ ከባላጋራዎችህ በላይ ከፍ ከፍ ትላለች፤

ጠላቶችህም ሁሉ ይወገዳሉ።”

10 “በዚያም ቀን” ይላል ይሖዋ፣

“ፈረሶችህን ከመካከልህ አስወግዳለሁ፤ ሠረገሎችህንም አጠፋለሁ።

11 በምድርህ ላይ የሚገኙትን ከተሞች እደመስሳለሁ፤

የተመሸጉ ስፍራዎችህንም ሁሉ አፈራርሳለሁ።

12 ጥንቆላህን አስወግዳለሁ፤*

ከእንግዲህም አስማተኛ በመካከልህ አይኖርም።+

13 የተቀረጹ ምስሎችህንና ዓምዶችህን ከመካከልህ አስወግዳለሁ፤

ከእንግዲህም ወዲህ ለእጆችህ ሥራ አትሰግድም።+

14 የማምለኪያ ግንዶችህንም* ከመካከልህ እነቅላለሁ፤+

ከተሞችህንም እደመስሳለሁ።

15 ታዛዥ ያልሆኑትን ብሔራት፣

በቁጣና በንዴት እበቀላለሁ።”

6 ይሖዋ የሚለውን እባካችሁ ስሙ።

ተነሱ፤ በተራሮች ፊት ሙግታችሁን አቅርቡ፤

ኮረብቶችም ቃላችሁን ይስሙ።+

 2 ተራሮች ሆይ፣ እናንተ ጽኑ የምድር መሠረቶች፣

የይሖዋን ሙግት ስሙ፤+

ይሖዋ ከሕዝቡ ጋር ሙግት አለውና፤

ከእስራኤልም ጋር ይከራከራል፦+

 3 “ሕዝቤ ሆይ፣ ምን ያደረግኩህ ነገር አለ?

ያደከምኩህስ ምን አድርጌ ነው?+

እስቲ መሥክርብኝ።

 4 ከግብፅ ምድር አወጣሁህ፤+

ከባርነትም ቤት ዋጀሁህ፤+

ሙሴን፣ አሮንንና ሚርያምን+ በፊትህ ላክሁ።

 5 ሕዝቤ ሆይ፣ የሞዓብ ንጉሥ ባላቅ ያሴረብህን ነገር፣+

የቢዖር ልጅ በለዓምም የሰጠውን መልስ+ እባክህ አስታውስ፤

የይሖዋን የጽድቅ ሥራ ታውቅ ዘንድ

ከሺቲም+ እስከ ጊልጋል+ ድረስ የሆነውን ነገር አስታውስ።”

 6 በይሖዋ ፊት ምን ይዤ ልቅረብ?

ከፍ ባለ ስፍራ በሚኖረው አምላክ ፊት ምን ይዤ ልስገድ?

ሙሉ በሙሉ የሚቃጠሉ መባዎችና

የአንድ ዓመት ጥጃዎች ይዤ ልቅረብ?+

 7 ይሖዋ በሺህ በሚቆጠሩ አውራ በጎች

ወይስ በእልፍ የዘይት ፈሳሾች ደስ ይለዋል?+

ለሠራሁት በደል የበኩር ወንድ ልጄን፣

ለሠራሁትም* ኃጢአት የሆዴን ፍሬ ላቅርብ?+

 8 ሰው ሆይ፣ መልካም የሆነውን ነግሮሃል።

ይሖዋ ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው?

ፍትሕን እንድታደርግ፣*+ ታማኝነትን እንድትወድና*+

ልክህን አውቀህ+ ከአምላክህ ጋር እንድትሄድ ብቻ ነው!+

 9 የይሖዋ ድምፅ ከተማዋን ይጣራል፤

ጥበበኞች* ስምህን ይፈራሉ።

የበትሩን ድምፅና ቅጣቱን የወሰነውን ስሙ።+

10 ክፉ በሆነ ሰው ቤት፣ በክፋት የተገኘ ሀብት

እንዲሁም አስጸያፊ የሆነ ጎዶሎ የኢፍ መስፈሪያ* አሁንም አለ?

11 አባይ ሚዛንና* የተዛቡ* የድንጋይ መለኪያዎች የያዘ ከረጢት+ እየተጠቀምኩ

ንጹሕ ሥነ ምግባር ሊኖረኝ ይችላል?*

12 ባለጸጎቿ በግፍ የተሞሉ ናቸው፤

ነዋሪዎቿም ውሸት ይናገራሉ፤+

ምላሳቸው በአፋቸው ውስጥ አታላይ ነው።+

13 “ስለዚህ መትቼ አቆስልሃለሁ፤+

ከኃጢአትህ የተነሳ አጠፋሃለሁ።

14 ትበላለህ፤ ግን አትጠግብም፤

ሆድህም ባዶ ይሆናል።+

የምትወስዳቸውን ነገሮች ጠብቀህ ማቆየት አትችልም፤

ጠብቀህ ያቆየኸውንም ነገር ሁሉ ለሰይፍ አሳልፌ እሰጠዋለሁ።

15 ዘር ትዘራለህ፤ ሆኖም የምታጭደው ነገር አይኖርም።

የወይራ ፍሬ ትጨምቃለህ፤ ሆኖም ዘይቱን አትጠቀምበትም፤

ደግሞም አዲስ የወይን ጠጅ ትጨምቃለህ፤ ሆኖም የወይን ጠጅ አትጠጣም።+

16 የኦምሪን ደንቦችና የአክዓብን ቤት ሥራ ሁሉ ትከተላላችሁና፤+

ምክራቸውንም ተከትላችሁ ትሄዳላችሁ።

ስለዚህ አንተን መቀጣጫ፣

ነዋሪዎቿንም ማፏጫ አደርጋለሁ፤+

የሰዎችንም ፌዝ ትሸከማላችሁ።”+

7 ወዮልኝ! የበጋ ፍሬ* ከተሰበሰበና

ወይን የሚሰበሰብበት ጊዜ አብቅቶ

ቃርሚያ ከተለቀመ በኋላ

የሚበላ የወይን ዘለላ እንደማያገኝ ሰው ሆኛለሁ፤

በጣም የምመኘውን፣* በመጀመሪያው ወቅት የሚደርሰውን በለስም አላገኘሁም።

 2 ታማኝ ሰው ከምድሪቱ ጠፍቷል፤*

ከሰው ልጆችም መካከል ቅን የሆነ የለም።+

ሁሉም ደም ለማፍሰስ ያደባሉ።+

እያንዳንዱም የገዛ ወንድሙን በመረብ ያጠምዳል።

 3 እጆቻቸው መጥፎ ነገር በማድረግ የተካኑ ናቸው፤+

ገዢው የሆነ ነገር እንዲደረግለት ይጠይቃል፤

ፈራጁ ክፍያ ይጠይቃል፤+

ታዋቂ የሆነው ሰው የራሱን ፍላጎት ይገልጻል፤*+

እነሱም አንድ ላይ ሆነው ያሴራሉ።*

 4 ከእነሱ መካከል የተሻለ የተባለው እንደ እሾህ ነው፤

እጅግ ቅን የተባለው ደግሞ ከእሾህ ቁጥቋጦ የከፋ ነው።

ጠባቂዎችህ የተናገሩለት፣ አንተ የምትጎበኝበት ቀን ይመጣል።+

እነሱ አሁን ይሸበራሉ።+

 5 ባልንጀራህን አትመን፤

ወይም በቅርብ ወዳጅህ አትታመን።+

በእቅፍህ ለምትተኛው ስለምትናገረው ነገር ተጠንቀቅ።

 6 ወንድ ልጅ አባቱን ይንቃልና፤

ሴት ልጅ በእናቷ ላይ ትነሳለች፤+

ምራት ደግሞ በአማቷ ላይ ትነሳለች፤+

የሰው ጠላቶቹ ቤተሰቦቹ ናቸው።+

 7 እኔ ግን ይሖዋን በጉጉት እጠባበቃለሁ።+

የሚያድነኝን አምላክ በትዕግሥት እጠብቃለሁ።*+

አምላኬ ይሰማኛል።+

 8 ጠላቴ ሆይ፣ በእኔ ላይ በደረሰው ነገር ሐሴት አታድርጊ።

ብወድቅም እንኳ እነሳለሁ፤

በጨለማ ውስጥ ብቀመጥም ይሖዋ ብርሃን ይሆንልኛል።

 9 በእሱ ላይ ኃጢአት ስለሠራሁ+

ለእኔ እስኪሟገትልኝና ፍትሕ እንዳገኝ እስከሚያደርግ ድረስ

የይሖዋን ቁጣ ችዬ እኖራለሁ።

እሱ ወደ ብርሃን ያወጣኛል፤

እኔም የእሱን ጽድቅ አያለሁ።

10 “አምላክህ ይሖዋ የት አለ?”

ስትለኝ የነበረችው ጠላቴም ታያለች፤

ኀፍረትም ትከናነባለች።+

ዓይኖቼም ያዩአታል።

በዚያን ጊዜ በጎዳና ላይ እንዳለ ጭቃ የምትረገጥ ቦታ ትሆናለች።

11 የድንጋይ ቅጥሮችሽ የሚገነቡበት ቀን ይሆናል፤

በዚያ ቀን ድንበሩ ይሰፋል።*

12 በዚያ ቀን ከአሦርና ከግብፅ ከተሞች፣

ከግብፅ አንስቶ እስከ ወንዙ* ድረስ፣

ከባሕር እስከ ባሕር፣ ከተራራም እስከ ተራራ ድረስ ያሉ ሰዎች

ወደ አንቺ ይመጣሉ።+

13 ምድሪቱም ከነዋሪዎቿና ከሠሩት ነገር* የተነሳ

ባድማ ትሆናለች።

14 ሕዝብህን ይኸውም በጫካ ውስጥ በፍራፍሬ እርሻ መካከል ብቻውን ያለውን፣

የርስትህን መንጋ እንደ እረኛ በበትር ጠብቅ።+

እንደ ድሮው ዘመን በባሳንና በጊልያድ ይሰማሩ።+

15 “ከግብፅ ምድር በወጣችሁበት ዘመን እንደነበረው

ድንቅ ሥራዎችን አሳያችኋለሁ።+

16 ብሔራትም ያያሉ፤ ታላቅ ኃይል ቢኖራቸውም ያፍራሉ።+

እጃቸውን በአፋቸው ላይ ይጭናሉ፤

ጆሯቸው ይደነቁራል።

17 እንደ እባብ አፈር ይልሳሉ፤+

በምድር ላይ እንደሚሳቡ እንስሳት እየተንቀጠቀጡ ከምሽጎቻቸው ይወጣሉ።

በፍርሃት ተውጠው ወደ አምላካችን ወደ ይሖዋ ይመጣሉ፤

አንተንም ይፈሩሃል።”+

18 የርስቱን ቀሪዎች+ ኃጢአት ይቅር የሚል፣ በደላቸውንም የሚያልፍ

እንደ አንተ ያለ አምላክ ማን ነው?+

እሱ ለዘላለም አይቆጣም፤

ታማኝ ፍቅር በማሳየት ደስ ይሰኛልና።+

19 ዳግመኛ ምሕረት ያሳየናል፤+ በደላችንን በቁጥጥሩ ሥር ያደርጋል።*

ኃጢአታቸውን ሁሉ ወደ ጥልቅ ባሕር ትጥላለህ።+

20 በጥንት ዘመን ለአባቶቻችን በማልክላቸው መሠረት

ለያዕቆብ ታማኝነትን፣

ለአብርሃም ደግሞ ታማኝ ፍቅርን ታሳያለህ።+

ሚካኤል (“እንደ አምላክ ያለ ማን ነው?” የሚል ትርጉም አለው) ወይም ሚካያህ (“እንደ ይሖዋ ያለ ማን ነው?” የሚል ትርጉም አለው) የሚሉት ስሞች አጭር መጠሪያ።

ወይም “ረባዳማ ሜዳዎቹም።”

ቃል በቃል “ሸለቆ ውስጥ አፈሳለሁ።”

ወይም “የተከፈላት ደሞዝ ሁሉ በእሳት ይቃጠላል።”

ወይም “በአፍራ ቤት።”

ወይም “በዝባዡን።”

ቃል በቃል “አንገታችሁን አታወጡም።”

“ከልብሱ ላይ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ቃል በቃል “በራሳቸው ላይ ይሆናል።”

ወይም “በትልቅ ድስት።”

“የሚያላምጡት ነገር ሲያገኙ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ቃል በቃል “ጦርነትን በሚቀድሱ።”

ወይም “አፍንጫቸው ሥር ያለውን ጢም።”

ቃል በቃል “ራሶቿ።”

ወይም “በብር።”

ወይም “በይሖዋ እንደሚመኩ ይናገራሉ።”

ወይም “የቤተ መቅደሱም።”

ወይም “በዛፍ እንደተሸፈነ ተረተር።”

ወይም “በመጨረሻዎቹ ቀኖች።”

ወይም “መመሪያ፤ ትምህርት።”

ወይም “ያስተካክላል።”

ወይም “ይኖራል።”

ቃል በቃል “የምታነክሰውን።”

ቃል በቃል “የምታነክሰው ቀሪዎች እንዲኖሯት።”

ወይም “የቀድሞው።”

ወይም “ጎሳዎች።”

ወይም “መሪዎችን።”

ቃል በቃል “ከእጅህ አስወግዳለሁ።”

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “ነፍሴ ለሠራችውም።”

ወይም “ትክክል የሆነውን ነገር እንድታደርግ።”

ወይም “ደግነትና ታማኝነት የሚንጸባረቅበት ፍቅር እንድታሳይና።” ቃል በቃል “ታማኝ ፍቅርን እንድትወድና።”

ወይም “ማስተዋል የታከለበት ጥበብ ያላቸው።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ወይም “ሐሰተኛ ሚዛንና፤ ትክክል ያልሆነ ሚዛንና።”

ወይም “ለማጭበርበር የሚያገለግሉ።”

ወይም “ቅን ልሆን እችላለሁ?”

የበጋ ፍሬ በዋነኝነት የሚያመለክተው “በለስን” ሲሆን “ቴምርንም” ሊጨምር ይችላል።

ወይም “ነፍሴ በጣም የምትመኘውን።”

ወይም “ደብዛው ጠፍቷል።”

ወይም “የነፍሱን ምኞት ይገልጻል።”

ቃል በቃል “ይጎነጉናሉ።”

ወይም “በትዕግሥት የመጠበቅ ዝንባሌ አሳያለሁ።”

“ድንጋጌው ይርቃል” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ኤፍራጥስን ያመለክታል።

ቃል በቃል “ከሥራቸው ፍሬ።”

ወይም “ይረግጣል፤ ያሸንፋል።”

    የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ ጽሑፎች (2011-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ