ዳንኤል
1 የይሁዳ ንጉሥ ኢዮዓቄም+ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ከበባት።+ 2 ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ይሖዋ የይሁዳን ንጉሥ ኢዮዓቄምንና በእውነተኛው አምላክ ቤት* ውስጥ ካሉት ዕቃዎች መካከል የተወሰኑትን በእጁ አሳልፎ ሰጠው፤+ እሱም በሰናኦር+ ምድር* ወደሚገኘው ወደ አምላኩ ቤት* አመጣቸው። ዕቃዎቹን በአምላኩ ግምጃ ቤት ውስጥ አስቀመጣቸው።+
3 ከዚያም ንጉሡ የቤተ መንግሥቱ ዋና ባለሥልጣን የሆነውን አሽፈኔዝን ከንጉሡና ከመሳፍንቱ ዘር የሆኑትን ጨምሮ አንዳንድ እስራኤላውያንን* እንዲያመጣ አዘዘው።+ 4 እነሱም ምንም እንከን የሌለባቸው፣ መልከ መልካሞች፣ ጥበብ፣ እውቀትና ማስተዋል ያላቸው+ እንዲሁም በንጉሡ ቤተ መንግሥት ውስጥ ማገልገል የሚችሉ ወጣቶች* መሆን ነበረባቸው። የከለዳውያንን ጽሑፍና ቋንቋም እንዲያስተምራቸው አዘዘው። 5 በተጨማሪም ንጉሡ ለእሱ ከሚቀርበው ምርጥ ምግብና ከሚጠጣው የወይን ጠጅ ላይ የዕለት ቀለብ እንዲሰጣቸው አደረገ። እነዚህ ወጣቶች ለሦስት ዓመት ከሠለጠኑ በኋላ* ንጉሡን ለማገልገል የሚሰማሩ ናቸው።
6 ከእነሱ መካከል ከይሁዳ ነገድ የሆኑት ዳንኤል፣*+ ሃናንያህ፣* ሚሳኤልና* አዛርያስ* ይገኙበታል።+ 7 ዋናው ባለሥልጣንም ስም* አወጣላቸው፤ ዳንኤልን ብልጣሶር፣+ ሃናንያህን ሲድራቅ፣ ሚሳኤልን ሚሳቅ፣ አዛርያስን ደግሞ አብደናጎ ብሎ ጠራቸው።+
8 ዳንኤል ግን በንጉሡ ምርጥ ምግብ ወይም በሚጠጣው የወይን ጠጅ ላለመርከስ በልቡ ቁርጥ ውሳኔ አደረገ። በመሆኑም በዚህ መንገድ ራሱን እንዳያረክስ ዋናውን ባለሥልጣን ፈቃድ ጠየቀው። 9 እውነተኛው አምላክም ዋናው ባለሥልጣን ለዳንኤል ሞገስና* ምሕረት እንዲያሳየው አደረገ።+ 10 ሆኖም ዋናው ባለሥልጣን ዳንኤልን እንዲህ አለው፦ “የምትበሉትንና የምትጠጡትን የመደበላችሁን ጌታዬን ንጉሡን እፈራለሁ። እኩዮቻችሁ ከሆኑት ከሌሎቹ ወጣቶች* ይልቅ ፊታችሁ ተጎሳቁሎ ቢያይስ? እኔን* በንጉሡ ፊት በደለኛ ታደርጉኛላችሁ።” 11 ዳንኤል ግን ዋናው ባለሥልጣን በዳንኤል፣ በሃናንያህ፣ በሚሳኤልና በአዛርያስ ላይ ጠባቂ አድርጎ የሾመውን ሰው እንዲህ አለው፦ 12 “እባክህ አገልጋዮችህን ለአሥር ቀን ያህል ፈትነን፤ የምንበላው አትክልትና የምንጠጣው ውኃ ይሰጠን፤ 13 ከዚያም የእኛን ቁመና የንጉሡን ምርጥ ምግብ ከሚበሉት ወጣቶች* ቁመና ጋር አወዳድር፤ በኋላም ባየኸው መሠረት በአገልጋዮችህ ላይ የፈለግከውን ነገር አድርግ።”
14 እሱም በሐሳባቸው ተስማማ፤ ለአሥር ቀንም ፈተናቸው። 15 ከአሥር ቀን በኋላም የንጉሡን ምርጥ ምግብ ከሚበሉት ወጣቶች* ሁሉ ይበልጥ ቁመናቸው የተሻለና ጤናማ ሆነው* ተገኙ። 16 ስለዚህ ጠባቂው ምርጥ በሆነው ምግባቸውና በወይን ጠጃቸው ምትክ አትክልት ይሰጣቸው ነበር። 17 እውነተኛው አምላክም ለእነዚህ አራት ወጣቶች* በሁሉም ዓይነት የጽሑፍና የጥበብ መስክ እውቀትና ጥልቅ ማስተዋል ሰጣቸው፤ ዳንኤልም ሁሉንም ዓይነት ራእዮችና ሕልሞች የመረዳት ችሎታ ተሰጠው።+
18 ንጉሡ በፊቱ እንዲያቀርቧቸው የቀጠረው ጊዜ ሲደርስ+ ዋናው ባለሥልጣን ናቡከደነጾር ፊት አቀረባቸው። 19 ንጉሡ ሲያነጋግራቸው ከወጣቶቹ መካከል እንደ ዳንኤል፣ ሃናንያህ፣ ሚሳኤልና አዛርያስ ያለ አልተገኘም፤+ እነሱም በንጉሡ ፊት ማገልገላቸውን ቀጠሉ። 20 ንጉሡ ጥበብና ማስተዋል የሚጠይቁ ጉዳዮችን ሁሉ አንስቶ በጠየቃቸው ጊዜ በመላ ግዛቱ ካሉት አስማተኛ ካህናትና ጠንቋዮች ሁሉ+ አሥር እጅ በልጠው አገኛቸው። 21 ዳንኤልም እስከ ንጉሥ ቂሮስ+ የመጀመሪያ ዓመት ድረስ በዚያ ቆየ።
2 ናቡከደነጾር በነገሠ በሁለተኛው ዓመት ሕልሞችን አለመ፤ መንፈሱም እጅግ ከመታወኩ የተነሳ+ እንቅልፍ ሊወስደው አልቻለም። 2 ስለዚህ ንጉሡ ሕልሞቹን እንዲነግሩት አስማተኞቹ ካህናት፣ ጠንቋዮቹ፣ መተተኞቹና ከለዳውያኑ* እንዲጠሩ አዘዘ። በዚህም መሠረት ገብተው በንጉሡ ፊት ቆሙ።+ 3 ከዚያም ንጉሡ “ሕልም አልሜ ነበር፤ ሕልሙ ምን እንደሆነ ማወቅ ስለፈለግኩ መንፈሴ ታውኳል” አላቸው። 4 ከለዳውያኑም በአረማይክ ቋንቋ*+ ለንጉሡ እንዲህ ሲሉ መለሱ፦ “ንጉሥ ሆይ፣ ለዘላለም ኑር። ያየኸውን ሕልም ለአገልጋዮችህ ንገረን፤ እኛም ትርጉሙን እናሳውቅሃለን።”
5 ንጉሡም ለከለዳውያኑ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “የመጨረሻ ውሳኔዬ ይህ ነው፦ ሕልሙን ከነትርጉሙ የማታሳውቁኝ ከሆነ ሰውነታችሁ ይቆራረጣል፤ ቤቶቻችሁም የሕዝብ መጸዳጃ* ይሆናሉ። 6 ሕልሙንና ትርጉሙን ብታሳውቁኝ ግን ስጦታ፣ ሽልማትና ታላቅ ክብር እሰጣችኋለሁ።+ ስለዚህ ሕልሙንና ትርጉሙን አሳውቁኝ።”
7 እነሱም በድጋሚ መልሰው “ንጉሡ ሕልሙን ለአገልጋዮቹ ይንገረን፤ እኛም ትርጉሙን እንናገራለን” አሉት።
8 ንጉሡም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “የመጨረሻ ውሳኔዬን ስላወቃችሁ ጊዜ ለማራዘም እየሞከራችሁ እንደሆነ በሚገባ ተረድቻለሁ። 9 ሕልሙን የማታሳውቁኝ ከሆነ ሁላችሁም የሚጠብቃችሁ ቅጣት አንድ ነው። እናንተ ግን ሁኔታው እስኪለወጥ ድረስ፣ የሆነ ውሸትና ማታለያ ልትነግሩኝ ተስማምታችኋል። ስለዚህ ሕልሙን ንገሩኝ፤ እኔም ትርጉሙን ልታብራሩ እንደምትችሉ በዚህ አውቃለሁ።”
10 ከለዳውያኑም ለንጉሡ እንዲህ ሲሉ መለሱ፦ “ንጉሡ የሚጠይቀውን ነገር መፈጸም የሚችል አንድም ሰው በምድር ላይ የለም፤ የትኛውም ታላቅ ንጉሥ ወይም ገዢ፣ ከማንኛውም አስማተኛ ካህን ወይም ጠንቋይ ወይም ከለዳዊ እንዲህ ዓይነት ነገር ጠይቆ አያውቅም። 11 ንጉሡ እየጠየቀ ያለው ነገር በጣም አስቸጋሪ ነው፤ በሰዎች መካከል* ከማይኖሩት አማልክት በስተቀር ይህን ለንጉሡ ሊገልጽለት የሚችል የለም።”
12 በዚህ ጊዜ ንጉሡ በቁጣ ቱግ አለ፤ በባቢሎን ያሉት ጥበበኛ ሰዎች ሁሉ እንዲገደሉም አዘዘ።+ 13 ትእዛዙ ሲወጣና ጠቢባኑ ሊገደሉ ሲሉ ዳንኤልንና ጓደኞቹንም ለመግደል ይፈልጓቸው ጀመር።
14 በዚህ ጊዜ ዳንኤል በባቢሎን የሚገኙትን ጥበበኛ ሰዎች ለመግደል የወጣውን የንጉሡን የክብር ዘብ አለቃ አርዮክን በጥበብና በዘዴ አናገረው። 15 የንጉሡ ባለሥልጣን የሆነውን አርዮክን “ንጉሡ እንዲህ ያለ ከባድ ትእዛዝ ያወጣው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው። አርዮክም ጉዳዩን ለዳንኤል ገለጸለት።+ 16 ዳንኤልም ወደ ንጉሡ ገብቶ የሕልሙን ትርጉም ለእሱ የሚያስታውቅበት ጊዜ እንዲሰጠው ንጉሡን ጠየቀው።
17 ከዚያም ዳንኤል ወደ ቤቱ ሄደ፤ ጉዳዩንም ለጓደኞቹ ለሃናንያህ፣ ለሚሳኤልና ለአዛርያስ ነገራቸው። 18 ደግሞም ዳንኤልንና ጓደኞቹን ከቀሩት የባቢሎን ጠቢባን ጋር እንዳይገድሏቸው የሰማይ አምላክ ምሕረት እንዲያሳያቸውና ሚስጥሩን እንዲገልጥላቸው ይጸልዩ ዘንድ ነገራቸው።
19 ከዚያም ሚስጥሩ በሌሊት ለዳንኤል በራእይ ተገለጠለት።+ በመሆኑም ዳንኤል የሰማይን አምላክ አወደሰ። 20 ዳንኤልም እንዲህ አለ፦
“የአምላክ ስም ከዘላለም እስከ ዘላለም ይወደስ፤
ጥበብና ኃይል የእሱ ብቻ ነውና።+
23 የአባቶቼ አምላክ ሆይ፣ ለአንተ ምስጋናና ውዳሴ አቀርባለሁ፤
ምክንያቱም ጥበብንና ኃይልን ሰጥተኸኛል።
አሁን ደግሞ ከአንተ የጠየቅነውን ነገር አሳውቀኸኛል፤
ንጉሡ ያሳሰበውን ጉዳይ አሳውቀኸናል።”+
24 ከዚያም ዳንኤል የባቢሎንን ጠቢባን እንዲያጠፋ ንጉሡ ወደ ሾመው ወደ አርዮክ ሄዶ+ “ከባቢሎን ጠቢባን መካከል አንዳቸውንም አትግደል። በንጉሡ ፊት አቅርበኝ፤ እኔም የሕልሙን ትርጉም ለንጉሡ አሳውቃለሁ” አለው።
25 አርዮክም ዳንኤልን ወዲያውኑ በንጉሡ ፊት አቅርቦ “ከይሁዳ ግዞተኞች መካከል የሕልሙን ትርጉም ለንጉሡ ማሳወቅ የሚችል ሰው አግኝቻለሁ”+ አለው። 26 ንጉሡም ብልጣሶር የተባለውን ዳንኤልን+ “ያየሁትን ሕልምና ትርጉሙን በእርግጥ ልትነግረኝ ትችላለህ?” አለው።+ 27 ዳንኤልም ለንጉሡ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ከጠቢባኑ፣ ከጠንቋዮቹ፣ አስማተኛ ከሆኑት ካህናት ወይም ከኮከብ ቆጣሪዎቹ መካከል ንጉሡ የጠየቀውን ሚስጥር መግለጥ የሚችል የለም።+ 28 ይሁንና ሚስጥርን የሚገልጥ አምላክ በሰማያት አለ፤+ እሱም በመጨረሻዎቹ ቀናት የሚሆነውን ነገር ለንጉሥ ናቡከደነጾር አሳውቆታል። በአልጋህ ላይ ተኝተህ ሳለህ ያየኸው ሕልምና የተመለከትካቸው ራእዮች እነዚህ ናቸው፦
29 “ንጉሥ ሆይ፣ በአልጋህ ላይ ተኝተህ ሳለ ወደፊት የሚሆነውን ነገር ታስብ ነበር፤ ሚስጥርን የሚገልጠውም አምላክ ወደፊት የሚሆነውን ነገር አሳውቆሃል። 30 ይህ ሚስጥር ለእኔ የተገለጠልኝ ከሰው ሁሉ የላቀ ጥበብ ስላለኝ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ በልብህ ታስባቸው የነበሩትን ነገሮች ታውቅ ዘንድ የሕልሙ ትርጉም ለንጉሡ እንዲገለጥ ነው።+
31 “ንጉሥ ሆይ፣ በትኩረት እየተመለከትክ ሳለ አንድ ግዙፍ ምስል* አየህ። ግዙፍ የሆነውና እጅግ የሚያብረቀርቀው ይህ ምስል በፊትህ ቆሞ ነበር፤ መልኩም በጣም የሚያስፈራ ነበር። 32 የምስሉ ራስ ከጥሩ ወርቅ፣+ ደረቱና ክንዶቹ ከብር፣+ ሆዱና ጭኖቹ ከመዳብ፣+ 33 ቅልጥሞቹ ከብረት የተሠሩ+ ሲሆን እግሮቹ ከፊሉ ብረት፣ ከፊሉ ደግሞ ሸክላ* ነበሩ።+ 34 አንተም አንድ ድንጋይ የሰው እጅ ሳይነካው ተፈንቅሎ ከብረትና ከሸክላ የተሠሩትን የምስሉን እግሮች ሲመታቸውና ሲያደቅቃቸው አየህ።+ 35 በዚህ ጊዜ ብረቱ፣ ሸክላው፣ መዳቡ፣ ብሩና ወርቁ ሁሉም በአንድነት ተሰባበሩ፤ በበጋ ወቅት በአውድማ ላይ እንደሚቀር ገለባም ሆኑ፤ ነፋስም አንዳች ሳያስቀር ጠራርጎ ወሰዳቸው። ምስሉን የመታው ድንጋይ ግን ትልቅ ተራራ ሆነ፤ ምድርንም ሁሉ ሞላ።
36 “ሕልሙ ይህ ነው፤ አሁን ደግሞ ትርጉሙን ለንጉሡ እናሳውቃለን። 37 ንጉሥ ሆይ፣ አንተ የነገሥታት ንጉሥ ነህ፤ የሰማይ አምላክ መንግሥትን፣ ኃይልን፣ ብርታትንና ክብርን ሰጥቶሃል፤+ 38 ደግሞም በየትኛውም ቦታ የሚኖሩትን ሰዎችም ሆነ የዱር እንስሳትና የሰማይ ወፎች በእጅህ አሳልፎ ሰጥቶሃል፤ በሁሉም ላይ ገዢ አድርጎሃል፤+ የወርቁ ራስ አንተ ራስህ ነህ።+
39 “ይሁንና ከአንተ በኋላ፣ ከአንተ ያነሰ ሌላ መንግሥት ይነሳል፤+ ከዚያም መላውን ምድር የሚገዛ ሌላ ሦስተኛ የመዳብ መንግሥት ይነሳል።+
40 “አራተኛው መንግሥት ደግሞ እንደ ብረት የጠነከረ ይሆናል።+ ብረት ሁሉንም ነገር እንደሚሰባብርና እንደሚፈጭ ሁሉ፣ እሱም እንደሚያደቅ ብረት እነዚህን መንግሥታት ሁሉ ይሰባብራቸዋል፤ ደግሞም ያደቅቃቸዋል።+
41 “እግሮቹና ጣቶቹ ከፊሉ ሸክላ፣ ከፊሉ ደግሞ ብረት ሆነው እንዳየህ ሁሉ መንግሥቱም የተከፋፈለ ይሆናል፤ ሆኖም ብረቱና የሸክላ ጭቃው ተደባልቆ እንዳየህ ሁሉ በተወሰነ መጠን የብረት ጥንካሬ ይኖረዋል። 42 የእግሮቹ ጣቶች ከፊሉ ብረት፣ ከፊሉ ሸክላ እንደሆኑ ሁሉ ይህም መንግሥት በከፊል ብርቱ፣ በከፊል ደግሞ ደካማ ይሆናል። 43 ብረቱና የሸክላ ጭቃው ተደባልቀው እንዳየህ ሁሉ እነሱም ከሕዝቡ* ጋር ይደባለቃሉ፤ ሆኖም ብረት ከሸክላ ጋር እንደማይዋሃድ ሁሉ እነሱም አንዱ ከሌላው ጋር አይጣበቁም።
44 “በእነዚያ ነገሥታት ዘመን የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይጠፋ+ መንግሥት ያቋቁማል።+ ይህም መንግሥት ለሌላ ሕዝብ አይሰጥም።+ እነዚህን መንግሥታት ሁሉ ያደቅቃል፤ ፈጽሞም ያጠፋቸዋል፤+ እሱም ብቻውን ለዘላለም ይቆማል፤+ 45 አንድ ድንጋይ የሰው እጅ ሳይነካው ከተራራው ተፈንቅሎ ብረቱን፣ መዳቡን፣ ሸክላውን፣ ብሩንና ወርቁን ሲያደቅ እንዳየህ ሁሉ እንዲሁ ይሆናል።+ ታላቁ አምላክ ወደፊት የሚሆነውን ነገር ለንጉሡ አሳውቆታል።+ ሕልሙ እውነት፣ ትርጉሙም አስተማማኝ ነው።”
46 ከዚያም ንጉሥ ናቡከደነጾር በዳንኤል ፊት መሬት ላይ በግንባሩ ተደፋ፤ ዳንኤልንም እጅግ አከበረው። ደግሞም ስጦታና ዕጣን እንዲቀርብለት አዘዘ። 47 ንጉሡም ዳንኤልን እንዲህ አለው፦ “በእርግጥም አምላካችሁ የአማልክት አምላክና የነገሥታት ጌታ እንዲሁም ሚስጥርን የሚገልጥ ነው፤ ምክንያቱም አንተ ይህን ሚስጥር መግለጥ ችለሃል።”+ 48 ከዚያም ንጉሡ ዳንኤልን ከፍ ከፍ አደረገው፤ ብዙ የከበሩ ስጦታዎችም ሰጠው፤ የመላው ባቢሎን አውራጃ ገዢና የባቢሎን ጠቢባን ሁሉ ዋና አስተዳዳሪ አደረገው።+ 49 ዳንኤልም ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ንጉሡ ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን+ በባቢሎን አውራጃ አስተዳዳሪዎች አድርጎ ሾማቸው፤ ዳንኤል ግን በንጉሡ ቤተ መንግሥት ውስጥ ያገለግል ነበር።
3 ንጉሥ ናቡከደነጾር ቁመቱ 60 ክንድ፣* ወርዱ 6 ክንድ* የሆነ የወርቅ ምስል* ሠራ። ምስሉን በባቢሎን አውራጃ በዱራ ሜዳ አቆመው። 2 ከዚያም ንጉሥ ናቡከደነጾር የአውራጃ ገዢዎቹ፣ አስተዳዳሪዎቹ፣ አገረ ገዢዎቹ፣ አማካሪዎቹ፣ የግምጃ ቤት ኃላፊዎቹ፣ ዳኞቹ፣ ሕግ አስከባሪዎቹና የየአውራጃዎቹ አስተዳዳሪዎች በሙሉ ንጉሥ ናቡከደነጾር ላቆመው ምስል የምረቃ ሥነ ሥርዓት እንዲሰበሰቡ ጥሪ አስተላለፈ።
3 በመሆኑም የአውራጃ ገዢዎቹ፣ አስተዳዳሪዎቹ፣ አገረ ገዢዎቹ፣ አማካሪዎቹ፣ የግምጃ ቤት ኃላፊዎቹ፣ ዳኞቹ፣ ሕግ አስከባሪዎቹና የየአውራጃዎቹ አስተዳዳሪዎች በሙሉ ንጉሥ ናቡከደነጾር ላቆመው ምስል የምረቃ ሥነ ሥርዓት ተሰበሰቡ። ናቡከደነጾር ባቆመውም ምስል ፊት ቆሙ። 4 አዋጅ ነጋሪው ከፍ ባለ ድምፅ እንዲህ አለ፦ “እናንተ ከተለያዩ ብሔራትና ቋንቋዎች የተውጣጣችሁ ሕዝቦች ሆይ፣ እንዲህ እንድታደርጉ ታዛችኋል፦ 5 የቀንደ መለከት፣ የእምቢልታ፣ የተለያዩ ባለ አውታር መሣሪያዎች፣ የባለ ሦስት ማዕዘን በገና፣ የባለ ከረጢት ዋሽንትና የሌሎቹን የሙዚቃ መሣሪያዎች ሁሉ ድምፅ ስትሰሙ በግንባራችሁ ተደፍታችሁ ንጉሥ ናቡከደነጾር ላቆመው የወርቅ ምስል ስገዱ። 6 ተደፍቶ የማይሰግድ ማንኛውም ሰው ወዲያውኑ ወደሚንበለበለው የእቶን እሳት ይጣላል።”+ 7 ስለዚህ ከተለያዩ ብሔራትና ቋንቋዎች የተውጣጡት ሕዝቦች በሙሉ የቀንደ መለከት፣ የእምቢልታ፣ የተለያዩ ባለ አውታር መሣሪያዎች፣ የባለ ሦስት ማዕዘን በገናና የሌሎቹን የሙዚቃ መሣሪያዎች ሁሉ ድምፅ ሲሰሙ ተደፍተው ንጉሥ ናቡከደነጾር ላቆመው የወርቅ ምስል ሰገዱ።
8 በዚህ ጊዜ አንዳንድ ከለዳውያን ወደ ፊት ቀርበው አይሁዳውያንን ከሰሱ።* 9 ንጉሥ ናቡከደነጾርን እንዲህ አሉት፦ “ንጉሥ ሆይ፣ ለዘላለም ኑር። 10 ንጉሥ ሆይ፣ ማንኛውም ሰው የቀንደ መለከት፣ የእምቢልታ፣ የተለያዩ ባለ አውታር መሣሪያዎች፣ የባለ ሦስት ማዕዘን በገና፣ የባለ ከረጢት ዋሽንትና የሌሎቹን የሙዚቃ መሣሪያዎች ሁሉ ድምፅ ሲሰማ ተደፍቶ ለወርቁ ምስል እንዲሰግድ ትእዛዝ አስተላልፈሃል፤ 11 ተደፍቶ የማይሰግድ ሁሉ ወደሚንበለበለው የእቶን እሳት እንደሚጣል ተናግረሃል።+ 12 ሆኖም በባቢሎን አውራጃ አስተዳዳሪዎች አድርገህ የሾምካቸው ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ የሚባሉ አይሁዳውያን አሉ።+ ንጉሥ ሆይ፣ እነዚህ ሰዎች ለአንተ አክብሮት የላቸውም። አማልክትህን አያገለግሉም እንዲሁም ላቆምከው የወርቅ ምስል ለመስገድ እንቢተኞች ሆነዋል።”
13 በዚህ ጊዜ ናቡከደነጾር እጅግ ተቆጥቶ ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን እንዲያመጧቸው አዘዘ። እነሱንም በንጉሡ ፊት አቀረቧቸው። 14 ናቡከደነጾርም እንዲህ አላቸው፦ “ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ፣ አማልክቴን አለማገልገላችሁና+ ላቆምኩት የወርቅ ምስል አንሰግድም ማለታችሁ እውነት ነው? 15 አሁንም የቀንደ መለከት፣ የእምቢልታ፣ የተለያዩ ባለ አውታር መሣሪያዎች፣ የባለ ሦስት ማዕዘን በገና፣ የባለ ከረጢት ዋሽንትና የሌሎቹን የሙዚቃ መሣሪያዎች ሁሉ ድምፅ ስትሰሙ ለሠራሁት ምስል ተደፍታችሁ ለመስገድ ፈቃደኞች ከሆናችሁ፣ መልካም! የማትሰግዱ ከሆነ ግን ወዲያውኑ ወደሚንበለበለው የእቶን እሳት ትጣላላችሁ። ለመሆኑ ከእጄ ሊያስጥላችሁ የሚችል አምላክ ማን ነው?”+
16 ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ ለንጉሡ መልሰው እንዲህ አሉ፦ “ናቡከደነጾር ሆይ፣ በዚህ ጉዳይ ለአንተ መልስ መስጠት አያስፈልገንም። 17 ወደ እሳቱ የምንጣል ከሆነ የምናገለግለው አምላካችን ከሚንበለበለው የእቶን እሳት ሊያስጥለን ይችላል፤ ንጉሥ ሆይ፣ ከእጅህም ያስጥለናል።+ 18 ሆኖም እሱ ባያስጥለንም እንኳ ንጉሥ ሆይ፣ የአንተን አማልክት እንደማናገለግልና ላቆምከው የወርቅ ምስል እንደማንሰግድ እወቅ።”+
19 በዚህ ጊዜ ናቡከደነጾር በሲድራቅ፣ በሚሳቅና በአብደናጎ እጅግ ተቆጣ፤ የፊቱም ገጽታ ተለወጠባቸው፤* የእቶኑም እሳት ከወትሮው ይበልጥ ሰባት እጥፍ እንዲነድ አዘዘ። 20 ከዚያም በሠራዊቱ መካከል ያሉ ኃያላን ሰዎች ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን አስረው ወደሚንበለበለው የእቶን እሳት እንዲጥሏቸው አዘዘ።
21 በመሆኑም እነዚህ ሰዎች ልብሳቸውን እንደለበሱ ማለትም መጎናጸፊያቸውን፣ ከውስጥም ሆነ ከላይ ያደረጉትን ልብስና ጥምጥማቸውን በሙሉ እንደለበሱ ታስረው ወደሚንበለበለው የእቶን እሳት ተጣሉ። 22 የንጉሡ ትእዛዝ እጅግ ጥብቅ ስለነበረና የእቶኑ እሳት በኃይል ስለተቀጣጠለ ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን የወሰዷቸው ሰዎች በእሳቱ ወላፈን ተቃጥለው ሞቱ። 23 ይሁንና ሦስቱ ሰዎች ይኸውም ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ እንደታሰሩ በሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ ወደቁ።
24 ከዚያም ንጉሥ ናቡከደነጾር በድንጋጤ ከተቀመጠበት ዘሎ ተነሳ፤ ከፍተኛ ባለሥልጣናቱንም “አስረን እሳት ውስጥ የጣልናቸው ሦስት ሰዎች አልነበሩም እንዴ?” ሲል ጠየቃቸው፤ እነሱም “አዎ፣ ንጉሥ ሆይ” ብለው መለሱ። 25 እሱም እንዲህ አላቸው፦ “እነሆ፣ ያልታሰሩ አራት ሰዎች በእሳቱ መካከል ሲመላለሱ አያለሁ፤ ጉዳትም አልደረሰባቸውም፤ አራተኛውም የአማልክትን ልጅ ይመስላል።”
26 ናቡከደነጾር የሚንበለበል እሳት ወዳለበት እቶን በር ቀርቦ “እናንተ የልዑል አምላክ አገልጋዮች፣+ ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ ወጥታችሁ ወደዚህ ኑ!” አለ። ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎም ከእሳቱ ውስጥ ወጡ። 27 በዚያ ተሰብስበው የነበሩት የአውራጃ ገዢዎቹ፣ አስተዳዳሪዎቹ፣ አገረ ገዢዎቹና የንጉሡ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣+ እሳቱ ሰውነታቸውን እንዳልጎዳው፣*+ ከራሳቸው ፀጉር አንዲቷ እንኳ እንዳልተቃጠለች፣ መጎናጸፊያቸው መልኩ እንዳልተለወጠና የእሳቱ ሽታ በላያቸው እንዳልነበረ ተመለከቱ።
28 ከዚያም ናቡከደነጾር እንዲህ አለ፦ “መልአኩን ልኮ አገልጋዮቹን የታደገው የሲድራቅ፣ የሚሳቅና የአብደናጎ አምላክ የተመሰገነ ይሁን።+ እነሱ በእሱ በመታመን የንጉሡን ትእዛዝ ለመቀበል ፈቃደኞች አልሆኑም፤ የራሳቸውን አምላክ ትተው ሌላ አምላክ ከማገልገል ወይም ከማምለክ ይልቅ ሞትን መርጠዋል።*+ 29 ስለዚህ በሲድራቅ፣ በሚሳቅና በአብደናጎ አምላክ ላይ ማንኛውንም መጥፎ ነገር የሚናገር ከየትኛውም ብሔርና ቋንቋ የሆነ ሕዝብ ሁሉ እንዲቆራረጥ፣ ቤቱም የሕዝብ መጸዳጃ* እንዲሆን አዝዣለሁ፤ እንደ እሱ ማዳን የሚችል ሌላ አምላክ የለምና።”+
30 ከዚያም ንጉሡ ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ በባቢሎን አውራጃ ውስጥ የደረጃ እድገት እንዲያገኙ አደረገ።+
4 “ከንጉሥ ናቡከደነጾር፣ በመላው ምድር ለሚኖሩ ከተለያዩ ብሔራትና ቋንቋዎች ለተውጣጡ ሕዝቦች፦ ሰላም ይብዛላችሁ! 2 ልዑሉ አምላክ ለእኔ ያደረጋቸውን ተአምራዊ ምልክቶችና ድንቅ ሥራዎች ስነግራችሁ ደስ ይለኛል። 3 ተአምራዊ ምልክቱ እንዴት ታላቅ ነው! ድንቅ ሥራውም በዓይነቱ ልዩ ነው! መንግሥቱ የዘላለም መንግሥት ነው፤ የመግዛት ሥልጣኑም ከትውልድ እስከ ትውልድ ይዘልቃል።+
4 “እኔ ናቡከደነጾር በቤቴ ዘና ብዬ፣ በቤተ መንግሥቴም ደልቶኝ እኖር ነበር። 5 አንድ አስፈሪ ሕልም አየሁ። በአልጋዬ ላይ ተኝቼ ሳለሁ ወደ አእምሮዬ ይመጡ የነበሩት ምስሎችና ራእዮች አስፈሩኝ።+ 6 ስለዚህ ያየሁትን ሕልም ትርጉም እንዲያሳውቁኝ የባቢሎንን ጠቢባን ሁሉ በፊቴ እንዲያቀርቧቸው አዘዝኩ።+
7 “በዚህ ጊዜ አስማተኞቹ ካህናት፣ ጠንቋዮቹ፣ ከለዳውያኑና* ኮከብ ቆጣሪዎቹ+ ገቡ። ያየሁትን ሕልም ስነግራቸው ትርጉሙን ሊያሳውቁኝ አልቻሉም።+ 8 በመጨረሻም በአምላኬ ስም+ ብልጣሶር ተብሎ የተጠራውና+ የቅዱሳን አማልክት መንፈስ ያለበት ዳንኤል በፊቴ ቀረበ፤+ እኔም ያየሁትን ሕልም ነገርኩት፦
9 “‘የአስማተኛ ካህናት አለቃ የሆንከው ብልጣሶር ሆይ፣+ የቅዱሳን አማልክት መንፈስ በአንተ ውስጥ እንዳለና+ ለመግለጥ የሚያስቸግርህ ምንም ዓይነት ሚስጥር እንደሌለ በሚገባ አውቃለሁ።+ በመሆኑም በሕልሜ ያየኋቸውን ራእዮችና ትርጉማቸውን ግለጽልኝ።
10 “‘በአልጋዬ ላይ ተኝቼ ሳለሁ ባየኋቸው ራእዮች ላይ፣ በምድር መካከል ቁመቱ እጅግ ረጅም የሆነ አንድ ዛፍ+ ቆሞ ተመለከትኩ።+ 11 ዛፉም አድጎ ጠንካራ ሆነ፤ ጫፉም እስከ ሰማያት ደረሰ፤ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስም ይታይ ነበር። 12 ቅጠሉ ያማረ፣ ፍሬውም በጣም ብዙ ሲሆን ዛፉ ላይ ለሁሉ የሚሆን መብል ነበር። የዱር እንስሳት በጥላው ሥር ያርፉ፣ የሰማይ ወፎችም በቅርንጫፎቹ ላይ ይቀመጡ ነበር፤ ፍጥረታትም ሁሉ ከእሱ ይመገቡ ነበር።*
13 “‘በአልጋዬ ላይ ተኝቼ ራእዮቹን ስመለከት ቅዱስ የሆነ አንድ ጠባቂ ከሰማያት ሲወርድ አየሁ።+ 14 እሱም ከፍ ባለ ድምፅ እንዲህ አለ፦ “ዛፉን ቁረጡ፤+ ቅርንጫፎቹን ጨፍጭፉ፤ ቅጠሎቹን አራግፉ፤ ፍሬውንም በትኑ! የዱር እንስሳቱ ከሥሩ፣ ወፎቹም ከቅርንጫፎቹ ላይ ይሽሹ። 15 ጉቶው ግን በብረትና በመዳብ ታስሮ በሜዳ ሣር መካከል ከነሥሩ መሬት ውስጥ ይቆይ። በሰማያትም ጠል ይረስርስ፤ ዕጣ ፋንታውም በምድር ተክሎች መካከል ከአራዊት ጋር ይሁን።+ 16 ልቡ ከሰው ልብ ይለወጥ፤ የአውሬም ልብ ይሰጠው፤ ሰባት ዘመናትም+ ይለፉበት።+ 17 ይህ ነገር በጠባቂዎች ታውጇል፤+ የፍርድ ውሳኔውም በቅዱሳኑ ተነግሯል፤ ይህም ልዑሉ አምላክ በሰው ልጆች መንግሥት ላይ እንደሚገዛ+ እንዲሁም መንግሥቱን ለወደደው እንደሚሰጥና ከሰዎች ሁሉ የተናቀውን እንደሚሾምበት በሕይወት ያሉ ሁሉ ያውቁ ዘንድ ነው።”
18 “‘እኔ ንጉሥ ናቡከደነጾር ያየሁት ሕልም ይህ ነው፤ አሁንም ብልጣሶር ሆይ፣ በመንግሥቴ ውስጥ የሚኖሩት ሌሎቹ ጠቢባን ሁሉ ትርጉሙን ሊያሳውቁኝ ስላልቻሉ አንተ ትርጉሙን ንገረኝ።+ የቅዱሳን አማልክት መንፈስ በውስጥህ ስላለ ትርጉሙን ልታሳውቀኝ ትችላለህ።’
19 “በዚህ ጊዜ ብልጣሶር የተባለው ዳንኤል+ ለጥቂት ጊዜ በድንጋጤ ተዋጠ፤ ወደ አእምሮው የመጣው ሐሳብም በጣም አስፈራው።
“ንጉሡም ‘ብልጣሶር ሆይ፣ ሕልሙና ትርጉሙ አያስፈራህ’ አለው።
“ብልጣሶርም መልሶ እንዲህ አለው፦ ‘ጌታዬ ሆይ፣ ሕልሙ ለሚጠሉህ፣ ትርጉሙም ለጠላቶችህ ይሁን።
20 “‘አንተ ያየኸው ዛፍ ይኸውም በጣም ያደገውና የጠነከረው፣ ጫፉ እስከ ሰማያት የደረሰውና ከየትኛውም የምድር ክፍል የሚታየው፣+ 21 ቅጠሉ ያማረውና ፍሬው የበዛው፣ ለሁሉም የሚሆን መብል ያለበት፣ የዱር እንስሳት መጠለያ የሆነውና በቅርንጫፎቹ ላይ የሰማይ ወፎች የሚኖሩበት ዛፍ፣+ 22 ንጉሥ ሆይ፣ አንተ ነህ፤ ምክንያቱም አንተ ታላቅና ብርቱ ሆነሃል፤ ታላቅነትህ ገንኖ እስከ ሰማያት ደርሷል፤+ ግዛትህም እስከ ምድር ዳርቻ ተንሰራፍቷል።+
23 “‘ንጉሡም አንድ ቅዱስ ጠባቂ+ “ዛፉን ቆርጣችሁ አጥፉት፤ ጉቶው ግን በብረትና በመዳብ ታስሮ በሜዳ ሣር መካከል ከነሥሩ መሬት ውስጥ ይቆይ። በሰማያትም ጠል ይረስርስ፤ ሰባት ዘመናትም እስኪያልፉበት ድረስ ዕጣ ፋንታው ከዱር አራዊት ጋር ይሁን” እያለ ከሰማያት ሲወርድ አይቷል።+ 24 ንጉሥ ሆይ፣ ትርጉሙ ይህ ነው፤ ልዑሉ አምላክ በጌታዬ በንጉሡ ላይ ይደርሳል ብሎ ያወጀው ነገር ይህ ነው። 25 ከሰዎች መካከል ትሰደዳለህ፤ ከዱር አራዊትም ጋር ትኖራለህ፤ እንደ በሬም ሣር ትበላለህ፤ በሰማያትም ጠል ትረሰርሳለህ፤+ ልዑሉ አምላክ በሰው ልጆች መንግሥት ላይ እንደሚገዛና መንግሥቱንም ለወደደው እንደሚሰጥ እስክታውቅ ድረስ+ ሰባት ዘመናት+ ያልፉብሃል።+
26 “‘ይሁንና የዛፉን ጉቶ ከነሥሩ እንዲተዉት+ ስለተነገራቸው፣ አምላክ በሰማያት እንደሚገዛ ካወቅክ በኋላ መንግሥትህ ይመለስልሃል። 27 ስለዚህ ንጉሥ ሆይ፣ ምክሬ በአንተ ዘንድ ተቀባይነት ያግኝ። ኃጢአት መሥራትህን ትተህ ትክክል የሆነውን አድርግ፤ ግፍ መፈጸምህን ትተህ ለድሆች ምሕረት አሳይ። ምናልባት የተደላደለ ሕይወት የምትኖርበት ዘመን ይራዘምልህ ይሆናል።’”+
28 ይህ ሁሉ በንጉሥ ናቡከደነጾር ላይ ደረሰ።
29 ከ12 ወራት በኋላ በባቢሎን ቤተ መንግሥት ሰገነት ላይ እየተመላለሰ ነበር። 30 ንጉሡም “ይህች፣ ንጉሣዊ መኖሪያ እንድትሆን ለግርማዬ ክብር፣ በገዛ ብርታቴና ኃይሌ የገነባኋት ታላቂቱ ባቢሎን አይደለችም?” አለ።
31 ንጉሡ ንግግሩን ገና ከአፉ ሳይጨርስ እንዲህ የሚል ድምፅ ከሰማያት መጣ፦ “ንጉሥ ናቡከደነጾር ሆይ፣ የተላከልህ መልእክት ይህ ነው፦ ‘መንግሥትህ ከአንተ ተወስዷል፤+ 32 ከሰዎች መካከል ትሰደዳለህ። ከዱር አራዊት ጋር ትኖራለህ፤ እንደ በሬም ሣር ትበላለህ፤ ልዑሉ አምላክ በሰው ልጆች መንግሥት ላይ እንደሚገዛና መንግሥቱንም ለወደደው እንደሚሰጥ እስክታውቅ ድረስ ሰባት ዘመናት ያልፉብሃል።’”+
33 ወዲያውኑ ይህ ቃል በናቡከደነጾር ላይ ተፈጸመ። ከሰው ልጆች መካከል ተሰደደ፤ እንደ በሬም ሣር መብላት ጀመረ፤ ፀጉሩ እንደ ንስር ላባ እስኪረዝም፣ ጥፍሮቹም እንደ ወፍ ጥፍሮች እስኪያድጉ ድረስ ሰውነቱ በሰማያት ጠል ረሰረሰ።+
34 “ዘመኑ በተፈጸመ ጊዜ+ እኔ ናቡከደነጾር ወደ ሰማያት ተመለከትኩ፤ አእምሮዬም ተመለሰልኝ፤ ልዑሉንም አምላክ አመሰገንኩ፤ ለዘላለም የሚኖረውንም አወደስኩ፤ አከበርኩትም፤ ምክንያቱም የመግዛት ሥልጣኑ ዘላለማዊ ነው፤ መንግሥቱም ከትውልድ እስከ ትውልድ ይኖራል።+ 35 የምድር ነዋሪዎች ሁሉ እንደ ኢምንት ይቆጠራሉ፤ በሰማያት ሠራዊትና በምድር ነዋሪዎች ላይ እንደ ፈቃዱ ያደርጋል። ሊያግደው* ወይም ‘ምን ማድረግህ ነው?’ ብሎ ሊጠይቀው የሚችል ማንም የለም።+
36 “በዚህ ጊዜ አእምሮዬ ተመለሰልኝ፤ ደግሞም የመንግሥቴ ክብር፣ ግርማዊነቴና ሞገሴ ተመለሰልኝ።+ ከፍተኛ ባለሥልጣናቴና መኳንንቴ አጥብቀው ፈለጉኝ፤ እኔም ወደ መንግሥቴ ተመለስኩ፤ ከቀድሞውም የበለጠ ታላቅ ሆንኩ።
37 “አሁንም እኔ ናቡከደነጾር የሰማያትን ንጉሥ አወድሰዋለሁ፣ ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ እንዲሁም አከብረዋለሁ፤+ ምክንያቱም ሥራው ሁሉ እውነት፣ መንገዶቹም ትክክል ናቸው፤+ በኩራት የሚመላለሱትንም ማዋረድ ይችላል።”+
5 ንጉሥ ቤልሻዛር+ ለሺህ መኳንንቱ ታላቅ ግብዣ አደረገ፤ በእነሱም ፊት የወይን ጠጅ እየጠጣ ነበር።+ 2 ቤልሻዛር የወይን ጠጅ ጠጥቶ ሞቅ ሲለው አባቱ ናቡከደነጾር በኢየሩሳሌም ከነበረው ቤተ መቅደስ የወሰዳቸውን የወርቅና የብር ዕቃዎች፣+ ንጉሡና መኳንንቱ እንዲሁም ቁባቶቹና ቅምጦቹ ይጠጡባቸው ዘንድ እንዲያመጧቸው አዘዘ። 3 በዚህ ጊዜ በኢየሩሳሌም፣ በአምላክ ቤት ከነበረው ቤተ መቅደስ የወሰዷቸውን የወርቅ ዕቃዎች አመጡ፤ ንጉሡና መኳንንቱ እንዲሁም ቁባቶቹና ቅምጦቹ ጠጡባቸው። 4 እነሱም የወይን ጠጅ እየጠጡ ከወርቅ፣ ከብር፣ ከመዳብ፣ ከብረት፣ ከእንጨትና ከድንጋይ የተሠሩ አማልክትን አወደሱ።
5 ወዲያውኑም የሰው እጅ ጣቶች ብቅ ብለው በንጉሡ ቤተ መንግሥት፣ በመቅረዙ ትይዩ ባለው ግድግዳ ልስን ላይ መጻፍ ጀመሩ፤ ንጉሡም የሚጽፈውን እጅ አየ። 6 በዚህ ጊዜ ንጉሡ ፊቱ ገረጣ፤* ወደ አእምሮው የመጣው ሐሳብ አሸበረው፤ ወገቡም ተንቀጠቀጠ፤+ ጉልበቶቹም ይብረከረኩ ጀመር።
7 ንጉሡ ድምፁን ከፍ አድርጎ ጠንቋዮቹን፣ ከለዳውያኑንና* ኮከብ ቆጣሪዎቹን እንዲያመጧቸው አዘዘ።+ ንጉሡም የባቢሎንን ጠቢባን እንዲህ አላቸው፦ “ይህን ጽሑፍ የሚያነብና ትርጉሙን የሚነግረኝ ማንኛውም ሰው ሐምራዊ ልብስ ይለብሳል፤ አንገቱ ላይ የወርቅ ሐብል ይደረግለታል፤+ በመንግሥትም ላይ ሦስተኛ ገዢ ይሆናል።”+
8 በዚህ ጊዜ የንጉሡ ጠቢባን ሁሉ ገቡ፤ ሆኖም ጽሑፉን ማንበብም ሆነ ትርጉሙን ለንጉሡ ማሳወቅ አልቻሉም።+ 9 በመሆኑም ንጉሥ ቤልሻዛር እጅግ ፈራ፤ ፊቱም ገረጣ፤ መኳንንቱም ግራ ተጋቡ።+
10 ንግሥቲቱም ንጉሡና መኳንንቱ የተናገሩትን በሰማች ጊዜ ወደ ግብዣው አዳራሽ ገባች። እንዲህም አለች፦ “ንጉሥ ሆይ፣ ለዘላለም ኑር። በፍርሃት አትዋጥ፤ ፊትህም አይለዋወጥ። 11 በመንግሥትህ ውስጥ የቅዱሳን አማልክት መንፈስ ያለበት ሰው* አለ። በአባትህ ዘመን እንደ አማልክት ጥበብ ያለ ጥበብ፣ የእውቀት ብርሃንና ጥልቅ ማስተዋል ተገኝቶበት ነበር።+ አባትህ ንጉሥ ናቡከደነጾር የአስማተኛ ካህናቱ፣ የጠንቋዮቹ፣ የከለዳውያኑና* የኮከብ ቆጣሪዎቹ አለቃ አድርጎ ሾመው፤+ ንጉሥ ሆይ፣ ይህን ያደረገው አባትህ ነው። 12 ንጉሡ፣ ብልጣሶር ብሎ የሰየመው ዳንኤል+ ሕልምን በመተርጎም ረገድ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ችሎታ፣ እውቀትና ጥልቅ ማስተዋል እንዲሁም እንቆቅልሽንና የተወሳሰቡ ችግሮችን የመፍታት* ችሎታ ነበረው።+ እንግዲህ ዳንኤል ይጠራ፤ እሱም ትርጉሙን ይነግርሃል።”
13 በመሆኑም ዳንኤልን በንጉሡ ፊት አቀረቡት። ንጉሡም ዳንኤልን እንዲህ ሲል ጠየቀው፦ “ንጉሡ አባቴ ከይሁዳ ምድር ካመጣቸው+ የይሁዳ ግዞተኞች አንዱ የሆንከው ዳንኤል አንተ ነህ?+ 14 የአማልክት መንፈስ በውስጥህ እንዳለ+ እንዲሁም የእውቀት ብርሃን፣ ጥልቅ ማስተዋልና በዓይነቱ ልዩ የሆነ ጥበብ እንደተገኘብህ ስለ አንተ ሰምቻለሁ።+ 15 ይህን ጽሑፍ አንብበው ትርጉሙን እንዲያሳውቁኝ ጥበበኞችንና ጠንቋዮችን በፊቴ አቅርበዋቸው ነበር፤ እነሱ ግን የመልእክቱን ትርጉም መናገር አልቻሉም።+ 16 አንተ ግን የመተርጎምና የተወሳሰቡ ችግሮችን የመፍታት* ችሎታ እንዳለህ ሰምቻለሁ።+ አሁንም ይህን ጽሑፍ አንብበህ ትርጉሙን ልታሳውቀኝ ከቻልክ ሐምራዊ ልብስ ትለብሳለህ፤ አንገትህ ላይ የወርቅ ሐብል ይደረግልሃል፤ በመንግሥትም ላይ ሦስተኛ ገዢ ትሆናለህ።”+
17 በዚህ ጊዜ ዳንኤል ለንጉሡ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ስጦታህ ለራስህ ይሁን፤ ገጸ በረከቶችህንም ለሌሎች ስጥ። ይሁንና ጽሑፉን ለንጉሡ አነባለሁ፤ ትርጉሙንም አሳውቀዋለሁ። 18 ንጉሥ ሆይ፣ ልዑሉ አምላክ ለአባትህ ለናቡከደነጾር መንግሥት፣ ታላቅነት፣ ክብርና ግርማ ሰጠው።+ 19 ታላቅነትን ስላጎናጸፈው ከተለያዩ ብሔራትና ቋንቋዎች የተውጣጡ ሕዝቦች ሁሉ በፊቱ በፍርሃት ይንቀጠቀጡ ነበር።+ የፈለገውን ይገድል ወይም በሕይወት እንዲኖር ይፈቅድ፣ የፈለገውን ከፍ ከፍ ያደርግ ወይም ያዋርድ ነበር።+ 20 ሆኖም ልቡ ታብዮና አንገተ ደንዳና ሆኖ የእብሪተኝነት መንፈስ ባሳየ ጊዜ+ ከመንግሥቱ ዙፋን እንዲወርድ ተደረገ፤ ክብሩንም ተገፈፈ። 21 ከሰው ልጆች መካከል ተሰደደ፤ ልቡም ወደ አውሬ ልብ ተለወጠ፤ መኖሪያውም ከዱር አህዮች ጋር ሆነ። ልዑሉ አምላክ በሰው ልጆች መንግሥት ላይ እንደሚገዛና የፈለገውን በመንግሥቱ ላይ እንደሚያስቀምጥ እስኪያውቅ ድረስ እንደ በሬ ሣር በላ፤ ሰውነቱም በሰማያት ጠል ረሰረሰ።+
22 “ቤልሻዛር ሆይ፣ አንተ ግን ልጁ እንደመሆንህ መጠን ይህን ሁሉ ብታውቅም ትሕትና አላሳየህም። 23 ይልቁንም በሰማያት ጌታ ላይ ታበይክ፤+ የቤተ መቅደሱንም ዕቃ አስመጣህ።+ ከዚያም አንተና መኳንንትህ እንዲሁም ቁባቶችህና ቅምጦችህ በእነዚህ ዕቃዎች የወይን ጠጅ ጠጣችሁ፤ አንዳች ነገር ማየትም ሆነ መስማት ወይም ማወቅ የማይችሉትን ከብር፣ ከወርቅ፣ ከመዳብ፣ ከብረት፣ ከእንጨትና ከድንጋይ የተሠሩ አማልክት አወደሳችሁ።+ እስትንፋስህንና መንገድህን ሁሉ በእጁ የያዘውን አምላክ ግን አላከበርክም።+ 24 ስለዚህ ይህን እጅ የላከው እሱ ነው፤ ይህም ጽሑፍ ተጻፈ።+ 25 የተጻፈውም ጽሑፍ፣ ‘ሚኒ፣ ሚኒ፣ ቲቄል እና ፋርሲን’ ይላል።
26 “የቃላቱ ትርጉም ይህ ነው፦ ሚኒ ማለት አምላክ የመንግሥትህን ዘመን ቆጠረው፤ ወደ ፍጻሜም አመጣው ማለት ነው።+
27 “ቲቄል ማለት በሚዛን ተመዘንክ፤ ጉድለትም ተገኘብህ ማለት ነው።
28 “ፊሬስ ማለት ደግሞ መንግሥትህ ተከፈለ፤ ለሜዶናውያንና ለፋርሳውያን ተሰጠ ማለት ነው።”+
29 በዚህ ጊዜ ቤልሻዛር ትእዛዝ አስተላለፈ፤ ዳንኤልንም ሐምራዊ ልብስ አለበሱት፤ በአንገቱም ላይ የወርቅ ሐብል አጠለቁለት፤ በመንግሥትም ላይ ሦስተኛ ገዢ ሆኖ መሾሙን አወጁ።+
30 በዚያኑ ሌሊት ከለዳዊው ንጉሥ ቤልሻዛር ተገደለ።+ 31 ሜዶናዊው ዳርዮስም+ መንግሥቱን ተረከበ፤ ዕድሜውም 62 ዓመት ገደማ ነበር።
6 ዳርዮስ በመላው ንጉሣዊ ግዛቱ ላይ 120 የአውራጃ ገዢዎችን ለመሾም ወሰነ።+ 2 በእነሱ ላይ ሦስት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሾመ፤ ከእነዚህም አንዱ ዳንኤል ነበር፤+ ንጉሡ ለኪሳራ እንዳይዳረግ እነዚህ የአውራጃ ገዢዎች+ ተጠሪነታቸው ለባለሥልጣናቱ እንዲሆን ተደረገ። 3 ዳንኤልም በዓይነቱ ልዩ የሆነ መንፈስ ስለነበረው ከከፍተኛ ባለሥልጣናቱና ከአውራጃ ገዢዎቹ ይበልጥ ብቃት እንዳለው አስመሠከረ፤+ ንጉሡም በመላው ንጉሣዊ ግዛቱ ላይ ከፍ ያለ ቦታ ሊሰጠው አሰበ።
4 በዚህ ጊዜ ከፍተኛ ባለሥልጣናቱና የአውራጃ ገዢዎቹ ከመንግሥት ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ዳንኤልን ለመክሰስ የሚያስችል ሰበብ ለማግኘት ይከታተሉት ነበር፤ ሆኖም ዳንኤል እምነት የሚጣልበት ስለነበርና ምንም ዓይነት እንከንና ጉድለት ስላልነበረበት በእሱ ላይ አንዳች ሰበብ ወይም ጉድለት ሊያገኙ አልቻሉም። 5 በመሆኑም “ከአምላኩ ሕግ ጋር በተያያዘ ካልሆነ በቀር ዳንኤልን ለመክሰስ ምንም ዓይነት ሰበብ ልናገኝ አንችልም” አሉ።+
6 ስለዚህ ከፍተኛ ባለሥልጣናቱና የአውራጃ ገዢዎቹ ተሰብስበው ወደ ንጉሡ በመግባት እንዲህ አሉት፦ “ንጉሥ ዳርዮስ ሆይ፣ ለዘላለም ኑር። 7 ንጉሥ ሆይ፣ ለ30 ቀናት ያህል ለአንተ ካልሆነ በስተቀር ለአምላክም ሆነ ለሰው ልመና የሚያቀርብ ማንኛውም ግለሰብ ወደ አንበሶች ጉድጓድ እንዲወረወር+ የሚያዝዝ ንጉሣዊ ድንጋጌ እንዲወጣና እገዳ እንዲጣል የመንግሥት ባለሥልጣናቱ፣ አስተዳዳሪዎቹ፣ የአውራጃ ገዢዎቹ፣ የንጉሡ አማካሪዎችና አገረ ገዢዎቹ ሁሉ በአንድነት ተስማምተዋል። 8 አሁንም ንጉሥ ሆይ፣ ሊሻር በማይችለው የሜዶናውያንና የፋርሳውያን ሕግ+ መሠረት ድንጋጌው እንዳይለወጥ አጽናው፤ በጽሑፉም ላይ ፈርምበት።”+
9 ስለዚህ ንጉሥ ዳርዮስ እገዳውን በያዘው ድንጋጌ ላይ ፈረመ።
10 ዳንኤል ግን ድንጋጌው በፊርማ መጽደቁን እንዳወቀ ወደ ቤቱ ገባ፤ በሰገነት ላይ ባለው ክፍሉ ውስጥ በኢየሩሳሌም አቅጣጫ ያሉት መስኮቶች ተከፍተው ነበር።+ ከዚህ በፊት አዘውትሮ ያደርግ እንደነበረውም በቀን ሦስት ጊዜ በጉልበቱ ተንበርክኮ ጸለየ፤ ለአምላኩም ውዳሴ አቀረበ። 11 ሰዎቹ በሩን በርግደው በገቡ ጊዜ ዳንኤል በአምላኩ ፊት ሞገስ ለማግኘት ልመና ሲያቀርብና ሲማጸን አገኙት።
12 በመሆኑም ወደ ንጉሡ ቀርበው “ንጉሥ ሆይ፣ ለ30 ቀናት ያህል ለአንተ ካልሆነ በስተቀር ለአምላክም ሆነ ለሰው ልመና የሚያቀርብ ማንኛውም ግለሰብ ወደ አንበሶች ጉድጓድ እንዲወረወር የሚደነግገውን እገዳ በፊርማህ አጽድቀህ አልነበረም?” በማለት ንጉሡ የጣለውን እገዳ አስታወሱት። ንጉሡም “ጉዳዩ ሊሻር በማይችለው በሜዶናውያንና በፋርሳውያን ሕግ መሠረት በሚገባ የጸና ነው” ሲል መለሰላቸው።+ 13 እነሱም ቀበል አድርገው ንጉሡን እንዲህ አሉት፦ “ንጉሥ ሆይ፣ ከይሁዳ ግዞተኞች አንዱ የሆነው ዳንኤል፣+ ለአንተም ሆነ በፊርማህ ላጸደቅከው እገዳ አክብሮት የለውም፤ ይልቁንም በቀን ሦስት ጊዜ ይጸልያል።”+ 14 ንጉሡም ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ ተጨነቀ፤ ዳንኤልንም መታደግ የሚችልበትን መንገድ ያወጣና ያወርድ ጀመር፤ ፀሐይ እስክትጠልቅም ድረስ እሱን ለማዳን የተቻለውን ሁሉ ጥረት ሲያደርግ ቆየ። 15 በመጨረሻም እነዚህ ሰዎች አንድ ላይ ሆነው ወደ ንጉሡ በመግባት ንጉሡን እንዲህ አሉት፦ “ንጉሥ ሆይ፣ በሜዶናውያንና በፋርሳውያን ሕግ መሠረት ንጉሡ ያጸናው ማንኛውም እገዳ ወይም ድንጋጌ ሊለወጥ እንደማይችል አትርሳ።”+
16 ስለዚህ ንጉሡ ትእዛዝ አስተላለፈ፤ እነሱም ዳንኤልን አምጥተው አንበሶች ጉድጓድ ውስጥ ጣሉት።+ ንጉሡም ዳንኤልን “ሁልጊዜ የምታገለግለው አምላክህ ይታደግሃል” አለው። 17 ከዚያም ድንጋይ አምጥተው በጉድጓዱ አፍ* ላይ ገጠሙት፤ ንጉሡም በዳንኤል ላይ የተወሰደው እርምጃ እንዳይለወጥ፣ በራሱ የማኅተም ቀለበትና በመኳንንቱ የማኅተም ቀለበት በድንጋዩ ላይ አተመበት።
18 ከዚያም ንጉሡ ወደ ቤተ መንግሥቱ ሄደ። ጾሙንም አደረ፤ በምንም ነገር መዝናናት አልፈለገም፤* እንቅልፍም በዓይኑ አልዞረም።* 19 በመጨረሻም ንጉሡ ገና ጎህ ሲቀድ ተነስቶ እየተጣደፈ ወደ አንበሶቹ ጉድጓድ ሄደ። 20 ወደ ጉድጓዱ በቀረበ ጊዜ ሐዘን በተቀላቀለበት ድምፅ ጮክ ብሎ ዳንኤልን ተጣራ። ንጉሡም ዳንኤልን “የሕያው አምላክ አገልጋይ ዳንኤል ሆይ፣ ሁልጊዜ የምታገለግለው አምላክህ ከአንበሶቹ ሊታደግህ ችሏል?” አለው። 21 ዳንኤልም ንጉሡን እንዲህ አለው፦ “ንጉሥ ሆይ፣ ለዘላለም ኑር። 22 አምላኬ መልአኩን ልኮ የአንበሶቹን አፍ ዘጋ፤+ እነሱም አልጎዱኝም፤+ በፊቱ ንጹሕ ሆኜ ተገኝቻለሁና፤ ንጉሥ ሆይ፣ በአንተም ላይ የሠራሁት በደል የለም።”
23 ንጉሡ እጅግ ተደሰተ፤ ዳንኤልንም ከጉድጓዱ እንዲያወጡት አዘዘ። እነሱም ከጉድጓዱ አወጡት፤ ዳንኤል በአምላኩ ታምኖ ስለነበር ምንም ጉዳት አልደረሰበትም።+
24 ከዚያም በንጉሡ ትእዛዝ መሠረት፣ የዳንኤልን ከሳሾች* አምጥተው ከነልጆቻቸውና ከነሚስቶቻቸው ወደ አንበሶቹ ጉድጓድ ጣሏቸው። ገና ወደ ጉድጓዱ መጨረሻ ሳይደርሱ አንበሶቹ ተቀራመቷቸው፤ አጥንቶቻቸውንም ሁሉ አደቀቁ።+
25 ከዚያም ንጉሥ ዳርዮስ በመላው ምድር ለሚኖሩ ከተለያዩ ብሔራትና ቋንቋዎች ለተውጣጡ ሕዝቦች ሁሉ እንዲህ ሲል ጻፈ፦+ “ሰላም ይብዛላችሁ! 26 በየትኛውም የመንግሥቴ ግዛት የሚኖሩ ሰዎች የዳንኤልን አምላክ ፈርተው እንዲንቀጠቀጡ ትእዛዝ አስተላልፌአለሁ።+ እሱ ለዘላለም የሚኖር ሕያው አምላክ ነውና። መንግሥቱ ፈጽሞ አይጠፋም፤ የመግዛት ሥልጣኑም* ዘላለማዊ ነው።+ 27 እሱ ይታደጋል፤+ ደግሞም ያድናል፤ በሰማያትና በምድርም ተአምራዊ ምልክቶችንና ድንቅ ነገሮችን ያደርጋል፤+ ዳንኤልን ከአንበሶች መዳፍ ታድጎታልና።”
28 ስለዚህ ዳንኤል በዳርዮስ+ መንግሥት እንዲሁም በፋርሳዊው በቂሮስ+ መንግሥት ሁሉ ነገር ተሳካለት።
7 የባቢሎን ንጉሥ ቤልሻዛር+ በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት ዳንኤል በአልጋው ላይ ተኝቶ ሳለ ሕልምና ራእዮች አየ።+ ከዚያም ያየውን ሕልም ጻፈ፤+ ጉዳዩንም በዝርዝር አሰፈረ። 2 ዳንኤልም እንዲህ ሲል ገለጸ፦
“በሌሊት ባየኋቸው ራእዮች ላይ አራቱ የሰማያት ነፋሳት የተንጣለለውን ባሕር ሲያናውጡት ተመለከትኩ።+ 3 አራት ግዙፍ አራዊትም+ ከባሕር ውስጥ ወጡ፤ እያንዳንዳቸውም አንዱ ከሌላው የተለዩ ነበሩ።
4 “የመጀመሪያው አንበሳ ይመስል ነበር፤+ የንስር ክንፎችም ነበሩት።+ እኔም እየተመለከትኩ ሳለ ክንፎቹ ተነቃቀሉ፤ ከምድር እንዲነሳና ልክ እንደ ሰው በሁለት እግሩ እንዲቆም ተደረገ፤ የሰውም ልብ ተሰጠው።
5 “እነሆ፣ ሁለተኛው አውሬ ድብ ይመስል ነበር።+ በአንድ ጎኑም ተነስቶ ነበር፤ በአፉም ውስጥ በጥርሶቹ መካከል ሦስት የጎድን አጥንቶች ይዞ ነበር፤ ‘ተነስተህ ብዙ ሥጋ ብላ’ ተባለ።+
6 “ከዚህም በኋላ አየሁ፤ እነሆ ነብር የሚመስል ሌላ አውሬ ነበር፤+ ሆኖም ጀርባው ላይ አራት የወፍ ክንፎች ነበሩት። አውሬውም አራት ራሶች ነበሩት፤+ የመግዛት ሥልጣንም ተሰጠው።
7 “ከዚህ በኋላ በሌሊት ባየኋቸው ራእዮች ላይ የሚያስፈራ፣ የሚያስደነግጥና ለየት ያለ ጥንካሬ ያለው አራተኛ አውሬ ተመለከትኩ፤ ትላልቅ የብረት ጥርሶችም ነበሩት። ይበላና ያደቅ እንዲሁም የቀረውን በእግሮቹ ይረጋግጥ ነበር።+ ከእሱ በፊት ከነበሩት አራዊት ሁሉ የተለየ ሲሆን አሥር ቀንዶች ነበሩት። 8 ቀንዶቹን እየተመለከትኩ ሳለ፣ እነሆ ሌላ ትንሽ ቀንድ በመካከላቸው ወጣ፤+ ከመጀመሪያዎቹ ቀንዶች መካከል ሦስቱ በፊቱ ተነቃቀሉ። እነሆ፣ በዚህ ቀንድ ላይ የሰው ዓይኖች የሚመስሉ ዓይኖች ነበሩ፤ በእብሪት* የሚናገርም አፍ ነበረው።+
9 “እኔም እየተመለከትኩ ሳለ ዙፋኖች ተዘጋጁ፤ ከዘመናት በፊት የነበረውም+ ተቀመጠ።+ ልብሱ እንደ በረዶ ነጭ፣+ የራሱም ፀጉር እንደጠራ ሱፍ ነበር። ዙፋኑ የእሳት ነበልባል፣ መንኮራኩሮቹም የሚነድ እሳት ነበሩ።+ 10 ከፊቱ የእሳት ጅረት ይፈልቅና ይፈስ ነበር።+ ሺህ ጊዜ ሺዎች ያገለግሉት ነበር፤ እልፍ ጊዜ እልፍም* በፊቱ ቆመው ነበር።+ ችሎቱ+ ተሰየመ፤ መጻሕፍትም ተከፈቱ።
11 “በዚህ ጊዜ ቀንዱ ከሚናገረው የእብሪት* ቃል የተነሳ መመልከቴን ቀጠልኩ፤+ እኔም እየተመለከትኩ ሳለ አውሬው ተገደለ፤ አካሉም ወደሚንበለበል እሳት ተጥሎ እንዲጠፋ ተደረገ። 12 የቀሩት አራዊት+ ግን የገዢነት ሥልጣናቸውን ተቀሙ፤ ሆኖም ለተወሰነ ጊዜና ወቅት ዕድሜያቸው ተራዘመ።
13 “በሌሊት የተገለጡልኝን ራእዮች ማየቴን ቀጠልኩ፤ እነሆ የሰው ልጅ+ የሚመስል ከሰማያት ደመና ጋር መጣ፤ ከዘመናት በፊት ወደነበረውም+ እንዲገባ ተፈቀደለት፤ ወደ ፊቱም አቀረቡት። 14 ከተለያዩ ብሔራትና ቋንቋዎች የተውጣጡ ሕዝቦች ሁሉ እንዲያገለግሉት የገዢነት ሥልጣን፣+ ክብርና+ መንግሥት ተሰጠው።+ የገዢነት ሥልጣኑ የማያልፍና ዘላለማዊ፣ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው።+
15 “እኔ ዳንኤል ያየኋቸው ራእዮች ፍርሃት ስላሳደሩብኝ በውስጤ መንፈሴ ታወከ።+ 16 ከቆሙት መካከል ወደ አንዱ ቀርቤ የዚህ ሁሉ ትክክለኛ ትርጉም ምን እንደሆነ ጠየቅኩት። እሱም መለሰልኝ፤ ደግሞም የእነዚህን ነገሮች ትርጉም ገለጸልኝ።
17 “‘እነዚህ አራት ግዙፍ አራዊት+ ከምድር የሚነሱ አራት ነገሥታት ናቸው።+ 18 ይሁንና ከሁሉ የላቀው አምላክ ቅዱሳን፣+ መንግሥቱን ይቀበላሉ፤+ መንግሥቱን ለዘላለም፣ አዎ ለዘላለም ዓለም ይወርሳሉ።’+
19 “ከዚያም ከሌሎቹ ሁሉ የተለየ ስለሆነው ስለ አራተኛው አውሬ ይበልጥ ማወቅ ፈለግኩ፤ የብረት ጥርሶችና የመዳብ ጥፍሮች ያሉት እጅግ አስፈሪ አውሬ ነበር፤ ይበላና ያደቅ እንዲሁም የቀረውን በእግሩ ይረጋግጥ ነበር፤+ 20 ደግሞም በራሱ ላይ ስለነበሩት አሥር ቀንዶች+ እንዲሁም በኋላ ስለወጣውና ሦስቱ በፊቱ እንዲወድቁ ስላደረገው ስለ ሌላኛው ቀንድ+ ይኸውም ዓይኖችና በእብሪት* የሚናገር አፍ ስላሉት እንዲሁም ከሌሎቹ ስለበለጠው ቀንድ ማወቅ ፈለግኩ።
21 “እየተመለከትኩ ሳለ ይህ ቀንድ በቅዱሳኑ ላይ ጦርነት ከፈተ፤ በእነሱም ላይ አየለባቸው፤+ 22 ይህም የሆነው ከዘመናት በፊት የነበረው+ እስኪመጣና ከሁሉ የላቀው አምላክ ቅዱሳን አገልጋዮች+ እስኪፈረድላቸው ድረስ ነበር፤ ቅዱሳኑም መንግሥቱን የሚወርሱበት የተወሰነው ዘመን መጣ።+
23 “እሱም እንዲህ አለ፦ ‘አራተኛው አውሬ በምድር ላይ የሚነሳ አራተኛ መንግሥት ነው። ከሌሎቹ መንግሥታት ሁሉ የተለየ ይሆናል፤ መላዋን ምድር ያወድማል፣ ይረግጣል እንዲሁም ያደቃል።+ 24 አሥሩ ቀንዶች ከዚህ መንግሥት የሚነሱ አሥር ነገሥታት ናቸው፤ ከእነሱም በኋላ ሌላ ይነሳል፤ እሱም ከመጀመሪያዎቹ የተለየ ይሆናል፤ ሦስት ነገሥታትንም ያዋርዳል።+ 25 በልዑሉ አምላክ ላይ የተቃውሞ ቃል ይናገራል፤+ ከሁሉ በላቀው አምላክ ቅዱሳንም ላይ ያለማቋረጥ ችግር ያደርስባቸዋል። ዘመናትንና ሕግን ለመለወጥ ያስባል፤ እነሱም ለዘመን፣ ለዘመናትና ለዘመን እኩሌታ* በእጁ አልፈው ይሰጣሉ።+ 26 ይሁንና ችሎቱ ተሰየመ፤ የገዢነት ሥልጣኑንም ቀሙት፤ ከዚያም አስወገዱት፤ ፈጽሞም አጠፉት።+
27 “‘ከሰማያት በታች ያለ መንግሥት፣ የገዢነት ሥልጣንና የመንግሥታት ግርማ በሙሉ ከሁሉ የላቀው አምላክ ቅዱሳን ለሆኑት ሰዎች ተሰጠ።+ መንግሥታቸው ዘላለማዊ መንግሥት ነው፤+ መንግሥታትም ሁሉ ያገለግሏቸዋል፤ ደግሞም ይታዘዟቸዋል።’
28 “የነገሩ ፍጻሜ ይህ ነው። እኔም ዳንኤል ሳስበው የነበረው ነገር በጣም አስፈራኝ፤ ፊቴም ገረጣ፤* ነገሩን ግን በልቤ ያዝኩት።”
8 ንጉሥ ቤልሻዛር+ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት፣ ቀደም ሲል ከተገለጠልኝ ራእይ በኋላ ለእኔ፣ ለዳንኤል ሌላ ራእይ ተገለጠልኝ።+ 2 እኔም ራእዩን ተመለከትኩ፤ በራእዩም ላይ ራሴን፣ በኤላም+ አውራጃ በሚገኘው በሹሻን*+ ግንብ* አየሁት፤ ደግሞም ራእዩን ተመለከትኩ፤ እኔም በኡላይ የውኃ መውረጃ አጠገብ ነበርኩ። 3 ዓይኔን አንስቼ ስመለከት፣ እነሆ በውኃ መውረጃው አጠገብ ሁለት ቀንዶች ያሉት+ አንድ አውራ በግ+ ቆሞ ነበር። ሁለቱ ቀንዶች ረጃጅም ነበሩ፤ ይሁንና አንደኛው ከሌላው ይረዝማል፤ ይበልጥ ረጅም የሆነው ቀንድ የበቀለው በኋላ ነው።+ 4 አውራ በጉ ወደ ምዕራብ፣ ወደ ሰሜንና ወደ ደቡብ በቀንዱ ሲወጋ ተመለከትኩ፤ አንድም አውሬ ሊቋቋመው አልቻለም፤ ከእጁም መታደግ የሚችል ማንም አልነበረም።+ የፈለገውን ያደርግ ነበር፤ ራሱንም ከፍ ከፍ አደረገ።
5 እየተመለከትኩ ሳለ፣ እነሆ አንድ አውራ ፍየል+ ከምዕራብ* ተነስቶ መሬት ሳይነካ መላዋን ምድር እያቋረጠ መጣ። አውራውም ፍየል በዓይኖቹ መካከል ጎልቶ የሚታይ ቀንድ ነበረው።+ 6 እሱም በውኃ መውረጃው አጠገብ ቆሞ ወዳየሁት ሁለት ቀንድ ወዳለው አውራ በግ አመራ፤ በታላቅ ቁጣም ተንደርድሮ መጣበት።
7 ወደ አውራው በግ ሲቀርብ አየሁት፤ በበጉም እጅግ ተመርሮ ነበር። በጉን መትቶ ሁለቱንም ቀንዶቹን ሰባበራቸው፤ አውራውም በግ ሊቋቋመው የሚችልበት አቅም አልነበረውም። በጉን መሬት ላይ ጥሎ ረጋገጠው፤ አውራ በጉንም ከእጁ የሚያስጥለው አልነበረም።
8 ከዚያም አውራው ፍየል እጅግ ታበየ፤ ሆኖም ኃያል በሆነ ጊዜ ትልቁ ቀንድ ተሰበረ፤ በምትኩም ጎልተው የሚታዩ አራት ቀንዶች ወደ አራቱ የሰማይ ነፋሳት በቀሉ።+
9 ከእነሱ መካከል ከአንደኛው፣ አንድ ሌላ ትንሽ ቀንድ በቀለ፤ ወደ ደቡብ፣ ወደ ምሥራቅና* ውብ ወደሆነችው ምድር*+ በጣም እያደገ ሄደ። 10 ወደ ሰማይ ሠራዊት እስከሚደርስ ድረስ እያደገ ሄደ፤ ከሠራዊቱና ከከዋክብቱ መካከልም የተወሰኑትን ወደ ምድር ጣለ፤ ረጋገጣቸውም። 11 በሠራዊቱ አለቃ ላይ እንኳ ሳይቀር ራሱን ከፍ ከፍ አደረገ፤ የዘወትሩም መሥዋዕት ከአለቃው ተወሰደ፤ ጽኑ የሆነው የመቅደሱ ስፍራም ፈረሰ።+ 12 ከተፈጸመው በደል የተነሳ ሠራዊቱ ከዘወትሩ መሥዋዕት ጋር ለቀንዱ አልፎ ተሰጠ፤ እውነትን ወደ ምድር ጣለ፤ እንደ ፈቃዱ አደረገ፤ ደግሞም ተሳካለት።
13 ከቅዱሳኑም አንዱ ሲናገር ሰማሁ፤ ሌላውም ቅዱስ እየተናገረ ለነበረው ቅዱስ እንዲህ አለው፦ “ስለ ዘወትሩ መሥዋዕትና ጥፋት ስለሚያመጣው በደል+ እንዲሁም ቅዱሱ ስፍራና ሠራዊቱ እንዲረገጡ ስለመተዋቸው በሚገልጸው ራእይ ላይ የታየው ነገር የሚቆየው እስከ መቼ ነው?” 14 እሱም “2,300 ምሽቶችና ንጋቶች እስኪያልፉ ድረስ ነው፤ ቅዱሱም ስፍራ ወደ ትክክለኛው ሁኔታ በእርግጥ ይመለሳል” አለኝ።
15 እኔ ዳንኤል ራእዩን እየተመለከትኩና ለመረዳት እየጣርኩ ሳለ፣ ሰው የሚመስል ድንገት ከፊት ለፊቴ ቆሞ አየሁ። 16 ከዚያም ከኡላይ+ መካከል የሰው ድምፅ ሰማሁ፤ እሱም ጮክ ብሎ “ገብርኤል፣+ ለዚህ ሰው ያየውን ነገር አስረዳው” አለ።+ 17 በመሆኑም እኔ ወደቆምኩበት ስፍራ ቀረበ፤ ሆኖም ወደ እኔ ሲመጣ፣ በጣም ከመደንገጤ የተነሳ በግንባሬ ተደፋሁ። እሱም “የሰው ልጅ ሆይ፣ ራእዩ የሚፈጸመው በዘመኑ ፍጻሜ መሆኑን ተረዳ” አለኝ።+ 18 እኔ ግን እያናገረኝ ሳለ መሬት ላይ በግንባሬ ተደፋሁ፤ ከባድ እንቅልፍም ወሰደኝ። ስለዚህ ዳሰሰኝና ቆሜበት በነበረው ቦታ እንድቆም አደረገኝ።+ 19 ከዚያም እንዲህ አለኝ፦ “እነሆ፣ በቁጣው ዘመን ማብቂያ ላይ የሚሆነውን ነገር አሳውቅሃለሁ፤ ምክንያቱም ራእዩ በተወሰነው የፍጻሜ ዘመን ይፈጸማል።+
20 “ያየኸው ሁለት ቀንዶች ያሉት አውራ በግ የሜዶንንና የፋርስን ነገሥታት ያመለክታል።+ 21 ፀጉራሙ አውራ ፍየል የግሪክን ንጉሥ ያመለክታል፤+ በዓይኖቹ መካከል ያለው ትልቁ ቀንድ የመጀመሪያውን ንጉሥ ያመለክታል።+ 22 ቀንዱ ተሰብሮ በምትኩ አራት ቀንዶች እንደወጡ ሁሉ+ ከእሱ ብሔር የሚነሱ አራት መንግሥታት ይኖራሉ፤ ሆኖም የእሱን ያህል ኃይል አይኖራቸውም።
23 “በዘመነ መንግሥታቸውም መገባደጃ ላይ በደለኞቹ እስከ መጨረሻ* በደል ሲፈጽሙ፣ ግራ የሚያጋቡ አባባሎችን የሚረዳ* አስፈሪ መልክ ያለው ንጉሥ ይነሳል። 24 ኃይሉ እጅግ ታላቅ ይሆናል፤ በገዛ ኃይሉ ግን አይደለም። ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ጥፋት* ያደርሳል፤ የሚያደርገው ነገር ሁሉ ይሳካለታል። በኃያላን ሰዎችና በቅዱሳኑ ሕዝብ ላይ ጥፋት ያደርሳል።+ 25 መሠሪ ዘዴ ተጠቅሞ ብዙዎችን በማታለል ረገድ ይሳካለታል፤ በልቡም ራሱን ከፍ ከፍ ያደርጋል፤ ሰዎች ተረጋግተው በሚኖሩበት ጊዜም* በብዙዎች ላይ ጥፋት ያደርሳል። አልፎ ተርፎም የልዑላን ልዑል በሆነው ላይ ይነሳል፤ ሆኖም የሰው እጅ ሳይነካው ይሰበራል።
26 “ምሽቶቹንና ንጋቶቹን በተመለከተ በራእይ የተነገረው ነገር እውነት ነው፤ አንተ ግን ራእዩን በሚስጥር ያዝ፤ ከብዙ ዘመን በኋላ* የሚሆነውን ነገር የሚያመለክት ነውና።”+
27 እኔም ዳንኤል ኃይሌ ተሟጠጠ፤ ለተወሰኑ ቀናትም ታመምኩ።+ ከዚያም ተነስቼ ለንጉሡ የማከናውነውን ሥራ መሥራት ጀመርኩ፤+ ሆኖም ባየሁት ነገር የተነሳ ደንዝዤ ነበር፤ ራእዩንም ማንም ሰው ሊረዳው አልቻለም።+
9 በከለዳውያን መንግሥት ላይ ንጉሥ ሆኖ የተሾመውና የሜዶናውያን ተወላጅ የሆነው የአሐሽዌሮስ ልጅ ዳርዮስ+ በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት፣+ 2 አዎ፣ በዘመነ መንግሥቱ የመጀመሪያ ዓመት እኔ ዳንኤል ለነቢዩ ኤርምያስ በተነገረው የይሖዋ ቃል ላይ በተጠቀሰው መሠረት ኢየሩሳሌም ፈራርሳ የምትቆየው+ ለ70 ዓመት+ እንደሆነ ከመጻሕፍቱ* አስተዋልኩ። 3 በመሆኑም ወደ እውነተኛው አምላክ ወደ ይሖዋ ፊቴን አዞርኩ፤ ማቅ ለብሼና በራሴ ላይ አመድ ነስንሼ በጸሎትና በጾም ተማጸንኩት።+ 4 ወደ አምላኬ ወደ ይሖዋ ጸለይኩ፤ ደግሞም ተናዘዝኩ፤ እንዲህም አልኩ፦
“እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ለሚወዱህ፣ ትእዛዛትህንም ለሚያከብሩ ቃል ኪዳንህን የምትጠብቅና ታማኝ ፍቅር የምታሳይ+ ታላቅና የምትፈራ አምላክ ነህ፤+ 5 እኛ ኃጢአት ሠርተናል፤ በደል ፈጽመናል፤ ክፋት ሠርተናል እንዲሁም ዓምፀናል፤+ ከትእዛዛትህና ከድንጋጌዎችህ ዞር ብለናል። 6 ለነገሥታታችን፣ ለመኳንንታችን፣ ለአባቶቻችንና ለምድሪቱ ሕዝብ ሁሉ በስምህ የተናገሩትን አገልጋዮችህን ነቢያትን አልሰማንም።+ 7 ይሖዋ ሆይ፣ ጽድቅ የአንተ ነው፤ እኛ ግን ይኸውም የይሁዳ ሰዎች፣ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች እንዲሁም በቅርብም ይሁን በሩቅ ባሉ አገራት ሁሉ የበተንካቸው የእስራኤል ቤት ሰዎች በሙሉ ዛሬ እንደሆነው ሁሉ ኀፍረት* ተከናንበናል፤ ምክንያቱም እነሱ ለአንተ ታማኝ ሳይሆኑ ቀርተዋል።+
8 “ይሖዋ ሆይ፣ እኛ፣ ነገሥታታችን፣ መኳንንታችንና አባቶቻችን በአንተ ላይ ኃጢአት በመሥራታችን ኀፍረት* ተከናንበናል። 9 ምሕረትና ይቅር ባይነት የአምላካችን የይሖዋ ነው፤+ እኛ በእሱ ላይ ዓምፀናልና።+ 10 የአምላካችንን የይሖዋን ቃል አልታዘዝንም፤ አገልጋዮቹ በሆኑት በነቢያት አማካኝነት የሰጠንን ሕጎችም አላከበርንም።+ 11 የእስራኤል ቤት ሰዎች ሁሉ ሕግህን ተላልፈዋል፤ ቃልህን ባለመታዘዝም ለአንተ ጀርባቸውን ሰጥተዋል፤ በዚህም የተነሳ የእውነተኛው አምላክ አገልጋይ በሆነው በሙሴ ሕግ የተጻፈውን እርግማንና መሐላ በእኛ ላይ አወረድክ፤+ በአንተ ላይ ኃጢአት ሠርተናልና። 12 በእኛ ላይ ታላቅ ጥፋት በማምጣት በእኛ ላይና እኛን በገዙት ገዢዎቻችን ላይ* የተናገረውን ቃል ፈጸመብን፤+ በኢየሩሳሌም ላይ እንደተፈጸመው ያለ ነገር ከሰማይ በታች ታይቶ አያውቅም።+ 13 በሙሴ ሕግ እንደተጻፈው ይህ ሁሉ ጥፋት ደረሰብን፤+ ያም ሆኖ ከበደላችን በመመለስና ለእውነትህ* ትኩረት በመስጠት የአምላካችንን የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት አልተማጸንም።+
14 “በመሆኑም ይሖዋ በትኩረት ሲከታተል ቆይቶ ጥፋት አመጣብን፤ አምላካችን ይሖዋ በሥራው ሁሉ ጻድቅ ነውና፤ እኛ ግን ቃሉን አልታዘዝንም።+
15 “አሁንም ሕዝብህን ከግብፅ ምድር በኃያል እጅ ያወጣህና+ እስከዚህ ቀን ድረስ ስምህ እንዲታወቅ ያደረግክ አምላካችን ይሖዋ ሆይ፣+ እኛ ኃጢአት ሠርተናል፤ ክፉ ድርጊትም ፈጽመናል። 16 ይሖዋ ሆይ፣ እንደ ጽድቅ ሥራህ መጠን፣+ እባክህ ቁጣህንና ንዴትህን ከከተማህ ከኢየሩሳሌም ይኸውም ከቅዱስ ተራራህ መልስ፤ ምክንያቱም በኃጢአታችንና አባቶቻችን በፈጸሙት በደል የተነሳ ኢየሩሳሌምና ሕዝብህ በዙሪያችን ባሉት ሁሉ ዘንድ መሳለቂያ ሆነዋል።+ 17 አሁንም አምላካችን ሆይ፣ የአገልጋይህን ጸሎትና ልመና ስማ፤ ይሖዋ ሆይ፣ ለራስህ ስትል ለፈረሰው+ መቅደስህ ሞገስ አሳይ።+ 18 አምላኬ ሆይ፣ ጆሮህን አዘንብለህ ስማ! ዓይንህን ገልጠህ በስምህ በተጠራችው ከተማችን ላይ የደረሰውን ጥፋት ተመልከት፤ ልመናችንን በፊትህ የምናቀርበው ከእኛ ጽድቅ የተነሳ ሳይሆን ከታላቅ ምሕረትህ የተነሳ ነው።+ 19 ይሖዋ ሆይ፣ ስማ። ይሖዋ ሆይ፣ ይቅር በል።+ ይሖዋ ሆይ፣ ትኩረት ስጥ፤ እርምጃም ውሰድ! አምላኬ ሆይ፣ ለራስህ ስትል አትዘግይ፤ ስምህ በከተማህና በሕዝብህ ላይ ተጠርቷልና።”+
20 እኔም ገና እየተናገርኩና እየጸለይኩ፣ የራሴንና የሕዝቤን የእስራኤልን ኃጢአት እየተናዘዝኩ እንዲሁም በአምላኬ ቅዱስ ተራራ+ ላይ ሞገሱን እንዲያደርግ አምላኬን ይሖዋን እየለመንኩ፣ 21 አዎ፣ እየጸለይኩ ሳለ፣ ቀደም ሲል በራእዩ+ ላይ አይቼው የነበረው ሰው ገብርኤል፣+ በጣም ተዳክሜ ሳለ የምሽቱ የስጦታ መባ በሚቀርብበት ጊዜ ወደ እኔ መጣ። 22 እሱም እንዲህ በማለት እንዳስተውል ረዳኝ፦
“ዳንኤል ሆይ፣ አሁን ጥልቅ ማስተዋልና የመረዳት ችሎታ ልሰጥህ መጥቻለሁ። 23 ልመናህን ገና ማቅረብ ስትጀምር ትእዛዝ ተሰጥቷል፤ እኔም ልነግርህ መጥቻለሁ፤ ምክንያቱም አንተ እጅግ የተወደድክ* ነህ።+ ስለዚህ ለጉዳዩ ትኩረት ስጥ፤ ራእዩንም አስተውል።
24 “መተላለፍን ለማስቆም፣ ኃጢአትን ለመደምሰስ፣+ በደልን ለማስተሰረይ፣+ የዘላለም ጽድቅ ለማምጣት፣+ ራእዩንና ትንቢቱን* ለማተም+ እንዲሁም ቅድስተ ቅዱሳኑን ለመቀባት ለሕዝብህና ለቅድስቲቱ ከተማህ+ 70 ሳምንታት* ተወስኗል። 25 ኢየሩሳሌምን ለማደስና መልሶ ለመገንባት+ ትእዛዝ ከሚወጣበት ጊዜ አንስቶ መሪ+ የሆነው መሲሕ*+ እስከሚገለጥበት ጊዜ ድረስ 7 ሳምንታትና 62 ሳምንታት እንደሚሆን እወቅ፤ አስተውልም።+ ኢየሩሳሌም ትታደሳለች፤ ዳግመኛም ትገነባለች፤ አደባባይዋና የመከላከያ ቦይዋ እንደገና ይሠራል፤ ይህ የሚሆነው ግን በአስጨናቂ ወቅት ነው።
26 “ከ62ቱ ሳምንታት በኋላ መሲሑ ይቆረጣል፤*+ ትቶት የሚያልፈው ምንም ነገር አይኖርም።+
“የሚመጣውም መሪ ሠራዊት፣ ከተማዋንና ቅዱሱን ስፍራ ያጠፋል።+ ፍጻሜው በጎርፍ ይሆናል። እስከ ፍጻሜውም ድረስ ጦርነት ይሆናል፤ ጥፋትም ተወስኗል።+
27 “እሱም ለብዙዎች ቃል ኪዳኑን ለአንድ ሳምንት ያጸናል፤ በሳምንቱም አጋማሽ ላይ መሥዋዕትንና የስጦታ መባን ያስቀራል።+
“ጥፋት የሚያመጣውም በአስጸያፊ ነገሮች ክንፍ ላይ ሆኖ ይመጣል፤+ ጥፋት እስኪመጣም ድረስ የተወሰነው ነገር በወደመው ነገር ላይ ይፈስሳል።”
10 የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ+ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት ብልጣሶር ተብሎ የተጠራው ዳንኤል+ አንድ ራእይ ተሰጠው፤ ይህም መልእክት እውነት ነው፤ መልእክቱም ስለ አንድ ታላቅ ውጊያ ይገልጻል። እሱም መልእክቱን ተረድቶት ነበር፤ ያየውንም ነገር ማስተዋል ችሎ ነበር።
2 በዚያን ጊዜ እኔ ዳንኤል ሦስት ሳምንት ሙሉ በሐዘን ላይ ነበርኩ።+ 3 ሦስቱ ሳምንታት እስኪያበቁ ድረስ ምርጥ ምግብ አልበላሁም፤ ሥጋም ሆነ የወይን ጠጅ አልቀመስኩም እንዲሁም ሰውነቴን ቅባት አልተቀባሁም። 4 በመጀመሪያው ወር በ24ኛው ቀን በታላቁ ወንዝ ይኸውም በጤግሮስ*+ ዳርቻ ሳለሁ፣ 5 ቀና ብዬ ስመለከት በፍታ የለበሰና+ ወገቡ ላይ በዑፋዝ ወርቅ የተሠራ ቀበቶ የታጠቀ አንድ ሰው አየሁ። 6 ሰውነቱ እንደ ክርስቲሎቤ፣+ ፊቱ እንደ መብረቅ፣ ዓይኖቹ እንደሚንቦገቦግ ችቦ፣ ክንዶቹና እግሮቹ እንደሚያብረቀርቅ መዳብ፣+ ድምፁም እንደ ብዙ ሕዝብ ድምፅ ነበር። 7 ራእዩን ያየሁት እኔ ዳንኤል ብቻ ነበርኩ፤ ከእኔ ጋር የነበሩት ሰዎች ግን ራእዩን አላዩም።+ ነገር ግን እጅግ ስለተሸበሩ ሸሽተው ተደበቁ።
8 እኔም ብቻዬን ቀረሁ፤ ይህን ታላቅ ራእይ በተመለከትኩ ጊዜም በውስጤ ምንም ኃይል አልቀረም፤ ግርማ ሞገስ የተላበሰው ቁመናዬ ተለወጠ፤ ኃይሌም በሙሉ ተሟጠጠ።+ 9 ከዚያም ሲናገር ድምፁን ሰማሁ፤ ሆኖም ሲናገር እየሰማሁት ሳለ በግንባሬ መሬት ላይ ተደፍቼ ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ወሰደኝ።+ 10 በዚህ ጊዜ አንድ እጅ ዳሰሰኝ፤+ ከቀሰቀሰኝ በኋላ በእጄና በጉልበቴ ተደግፌ እንድነሳ አደረገኝ። 11 ከዚያም እንዲህ አለኝ፦
“እጅግ የተወደድክ*+ ዳንኤል ሆይ፣ የምነግርህን ቃል አስተውል። በነበርክበት ቦታ ላይ ቁም፤ ወደ አንተ ተልኬ መጥቼአለሁና።”
ይህን ሲለኝ እየተንቀጠቀጥኩ ቆምኩ።
12 ከዚያም እንዲህ አለኝ፦ “ዳንኤል ሆይ፣ አትፍራ።+ እነዚህን ነገሮች ለመረዳት ልባዊ ጥረት ማድረግና በአምላክህ ፊት ራስህን ዝቅ ማድረግ ከጀመርክበት ቀን አንስቶ ቃልህ ተሰምቷል፤ እኔም የመጣሁት ከቃልህ የተነሳ ነው።+ 13 ሆኖም የፋርስ ንጉሣዊ ግዛት አለቃ+ ለ21 ቀናት ተቋቋመኝ። በኋላ ግን ከዋነኞቹ አለቆች* አንዱ የሆነው ሚካኤል*+ ሊረዳኝ መጣ፤ እኔም በዚያን ጊዜ ከፋርስ ነገሥታት ጋር በዚያ ቆየሁ። 14 ራእዩ ከብዙ ዘመን በኋላ የሚፈጸም ስለሆነ+ በዘመኑ መጨረሻ በሕዝብህ ላይ የሚደርሰውን ነገር አስረዳህ ዘንድ መጥቻለሁ።”+
15 ይህን ቃል በነገረኝ ጊዜ ወደ መሬት አቀረቀርኩ፤ መናገርም ተሳነኝ። 16 በዚህ ጊዜ የሰው ልጅ የሚመስል ከንፈሮቼን ዳሰሰ፤+ እኔም አፌን ከፍቼ በፊቴ ቆሞ የነበረውን እንዲህ አልኩት፦ “ጌታዬ ሆይ፣ ከራእዩ የተነሳ እየተንቀጠቀጥኩ ነው፤ ኃይሌም ተሟጥጧል።+ 17 ስለዚህ የጌታዬ አገልጋይ ከጌታዬ ጋር እንዴት መነጋገር ይችላል?+ አሁን ምንም ኃይል የለኝምና፤ በውስጤም የቀረ እስትንፋስ የለም።”+
18 ሰው የሚመስለው እንደገና ዳሰሰኝ፤ አበረታኝም።+ 19 ከዚያም “አንተ እጅግ የተወደድክ* ሰው+ ሆይ፣ አትፍራ።+ ሰላም ለአንተ ይሁን።+ በርታ፣ አይዞህ በርታ” አለኝ። እንዲህ ባለኝ ጊዜ ተበረታትቼ “ጌታዬ ሆይ፣ ብርታት ሰጥተኸኛልና ተናገር” አልኩት።
20 እሱም እንዲህ አለኝ፦ “ወደ አንተ የመጣሁት ለምን እንደሆነ ታውቃለህ? አሁን ከፋርስ አለቃ ጋር ለመዋጋት ተመልሼ እሄዳለሁ።+ እኔ ስሄድ የግሪክ አለቃ ይመጣል። 21 ሆኖም በእውነት መጽሐፍ ላይ የሠፈሩትን ነገሮች እነግርሃለሁ። ከእነዚህ ነገሮች ጋር በተያያዘ የሕዝብህ አለቃ+ ከሆነው ከሚካኤል+ በስተቀር በእጅጉ ሊረዳኝ የሚችል የለም።
11 “እኔም ሜዶናዊው ዳርዮስ+ በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት፣ እሱን ለማበረታታትና ለማጠናከር* ቆሜ ነበር። 2 አሁን የምነግርህ ነገር እውነት ነው፦
“እነሆ፣ ሦስት ተጨማሪ ነገሥታት በፋርስ ምድር ይነሳሉ፤* አራተኛውም ከሌሎቹ ሁሉ ይበልጥ ብዙ ሀብት ያከማቻል። በሀብቱም በበረታ ጊዜ፣ ሁሉንም ነገር በግሪክ መንግሥት ላይ ያስነሳል።+
3 “አንድ ኃያል ንጉሥ ይነሳል፤ በታላቅ ኃይልም ይገዛል፤+ የፈለገውንም ያደርጋል። 4 ሆኖም በተነሳ ጊዜ መንግሥቱ ይፈራርሳል፤ ወደ አራቱ የሰማይ ነፋሳት አቅጣጫ ይከፋፈላል፤+ ለልጆቹ* ግን አይተላለፍም፤ ግዛታቸው እንደ እሱ ግዛት አይሆንም፤ መንግሥቱ ይነቀላልና፤ ከእነሱም ለሌሎች ይተላለፋል።
5 “የደቡቡ ንጉሥ ይኸውም ከገዢዎቹ አንዱ ብርቱ ይሆናል፤ ይሁንና አንዱ በእሱ ላይ ያይላል፤ ከዚያኛው የገዢነት ሥልጣንም በላቀ ኃይል ይገዛል።
6 “ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ኅብረት ይፈጥራሉ፤ የደቡቡ ንጉሥ ሴት ልጅ ስምምነት ለማድረግ ወደ ሰሜኑ ንጉሥ ትመጣለች። ሆኖም የክንዷ ኃይል አይጸናም፤ ደግሞም እሱም ሆነ ክንዱ አይጸናም፤ እሷም አልፋ ትሰጣለች፤ እሷና ያመጧት ሰዎች፣ የወለዳትና በዚያ ዘመን ብርቱ እንድትሆን ያደረጋት አልፈው ይሰጣሉ። 7 ከሥሮቿም ከሚበቅለው ቀንበጥ አንዱ በእሱ ቦታ ይነሳል፤ እሱም ወደ ሠራዊቱ ይመጣል፤ በሰሜኑ ንጉሥ ምሽግም ላይ ይዘምታል፤ በእነሱም ላይ እርምጃ ይወስዳል፤ ያሸንፋቸዋልም። 8 በተጨማሪም አማልክታቸውን፣ ከብረት የተሠሩ ምስሎቻቸውን፣* ከብርና ከወርቅ የተሠሩ ጠቃሚ* ዕቃዎቻቸውንና ምርኮኞቹን ይዞ ወደ ግብፅ ይመጣል። ለተወሰኑ ዓመታት ከሰሜኑ ንጉሥ ርቆ ይቆማል፤ 9 የሰሜኑም ንጉሥ የደቡቡን ንጉሥ መንግሥት ይወርራል፤ ሆኖም ወደ ገዛ ምድሩ ይመለሳል።
10 “ወንዶች ልጆቹም ለጦርነት ይዘጋጃሉ፤ እጅግ ታላቅ ሠራዊትም ያሰባስባሉ። እሱ በእርግጥ ይገሰግሳል፤ እንደ ጎርፍም ምድሪቱን እያጥለቀለቀ ያልፋል። ሆኖም ይመለሳል፤ ወደ ምሽጉም እስከሚደርስ ድረስ ይዋጋል።
11 “የደቡቡም ንጉሥ በምሬት ተሞልቶ ይወጣል፤ ደግሞም ከእሱ ይኸውም ከሰሜኑ ንጉሥ ጋር ይዋጋል፤ ይሄኛውም ታላቅ ሠራዊት ያሰልፋል፤ ይሁንና ሠራዊቱ ለዚያኛው እጅ አልፎ ይሰጣል። 12 ሠራዊቱም ተጠራርጎ ይወሰዳል። ልቡም ይታበያል፤ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ያጠፋል፤ ሆኖም ያገኘውን ጥሩ አጋጣሚ አይጠቀምበትም።
13 “የሰሜኑም ንጉሥ ይመለሳል፤ ከመጀመሪያውም የሚበልጥ ሠራዊት ያሰባስባል፤ ከተወሰነ ጊዜ ይኸውም ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ በሚገባ የታጠቀ ታላቅ ሠራዊት ይዞ ይመጣል። 14 በዚያ ዘመን ብዙዎች በደቡቡ ንጉሥ ላይ ይነሳሉ።
“በሕዝብህ መካከል ያሉ ዓመፀኛ ሰዎች* ይነሳሉ፤ ደግሞም ራእይን ለመፈጸም ይጥራሉ፤ ሆኖም አይሳካላቸውም።
15 “የሰሜኑም ንጉሥ ይመጣል፤ የአፈር ቁልልም ይደለድላል፤ የተመሸገችንም ከተማ ይይዛል። የደቡቡ ክንዶችም ሆኑ* የተመረጡት ተዋጊዎቹ አይቋቋሙትም፤ ለመቋቋም የሚያስችል ኃይልም አይኖራቸውም። 16 በእሱ ላይ የሚመጣው እንደፈለገው ያደርጋል፤ በፊቱም የሚቆም አይኖርም። ውብ በሆነችው* ምድር+ ላይ ይቆማል፤ የማጥፋትም ኃይል ይኖረዋል። 17 የመንግሥቱን ወታደራዊ ኃይል በሙሉ አሰባስቦ ለመምጣት ፊቱን ያቀናል፤* ከእሱም ጋር ስምምነት ያደርጋል፤ እርምጃም ይወስዳል። የሴቶችንም ሴት ልጅ እንዲያጠፋ ይፈቀድለታል። እሷም አትጸናም፤ የእሱም ሆና አትቀጥልም። 18 እሱም ፊቱን ወደ ባሕር ዳርቻዎች በመመለስ ብዙ ቦታዎችን ይይዛል። አንድ አዛዥ ከእሱ የደረሰበትን ነቀፋ ያስቀራል፤ ከዚያ በኋላ የሚሰነዘርበት ነቀፋ ይቆማል። ነቀፋውንም በራሱ ላይ ይመልስበታል። 19 ከዚያም ፊቱን በገዛ ምድሩ ወደሚገኙት ምሽጎች ይመልሳል፤ ተሰናክሎም ይወድቃል፤ ደግሞም አይገኝም።
20 “በእሱም ቦታ የሚነሳው ዕፁብ ድንቅ በሆነው ግዛቱ የሚያልፍ አስገባሪ* ይልካል፤ ይሁንና በቁጣ ወይም በጦርነት ባይሆንም እንኳ በጥቂት ቀናት ውስጥ ይሰበራል።
21 “በእሱም ቦታ የተናቀ* ሰው ይነሳል፤ እነሱም ንጉሣዊ ክብር አይሰጡትም፤ እሱም ሰዎች ተረጋግተው በሚኖሩበት ጊዜ* ይመጣል፤ መንግሥቱንም በብልጠት* ይይዛል። 22 የጎርፉም ክንዶች* በእሱ የተነሳ ተጠራርገው ይወሰዳሉ፤ ደግሞም ይሰበራሉ፤ የቃል ኪዳኑም+ መሪ+ ይሰበራል። 23 እነሱም ከእሱ ጋር በማበራቸው ማታለሉን ይቀጥላል፤ ደግሞም ይነሳል፤ በጥቂት ሕዝብ አማካኝነትም ኃያል ይሆናል። 24 ሰዎች ተረጋግተው በሚኖሩበት ጊዜ* ወደበለጸገው* የአውራጃው ክፍል ይገባል፤ አባቶቹና የአባቶቹ አባቶች ያላደረጉትን ነገር ያደርጋል። ብዝበዛን፣ ምርኮንና ንብረትን በሕዝቡ መካከል ያከፋፍላል፤ በተመሸጉት ቦታዎችም ላይ ሴራ ይጠነስሳል፤ ይህን የሚያደርገው ግን ለጊዜው ብቻ ነው።
25 “እሱም ታላቅ ሠራዊት አሰባስቦ ኃይሉንና ልቡን በደቡቡ ንጉሥ ላይ ያነሳሳል፤ የደቡቡም ንጉሥ እጅግ ታላቅና ኃያል የሆነ ሠራዊት አሰባስቦ ለጦርነቱ ይዘጋጃል። ሴራ ስለሚጠነስሱበትም መቋቋም አይችልም። 26 የእሱን ምርጥ ምግብ የሚበሉም ለውድቀት ይዳርጉታል።
“ሠራዊቱ ተጠራርጎ* ይወሰዳል፤ ብዙዎችም ተገድለው ይወድቃሉ።
27 “እነዚህ ሁለት ነገሥታት ልባቸው መጥፎ ነገር ለመሥራት ይነሳሳል፤ በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው እርስ በርስ ውሸት ይነጋገራሉ። ሆኖም ፍጻሜው እስከተወሰነው ጊዜ+ ድረስ ስለሚቆይ ምንም ነገር አይሳካላቸውም።
28 “እሱም በጣም ብዙ ንብረት ሰብስቦ ወደ አገሩ ይመለሳል፤ ልቡም በቅዱሱ ቃል ኪዳን ላይ ይነሳል። እርምጃ ይወስዳል፤ ወደ አገሩም ይመለሳል።
29 “በተወሰነው ጊዜ ይመለሳል፤ በደቡቡ ላይም ይነሳል። በዚህ ጊዜ ግን ቀድሞ እንደነበረው አይሆንም፤ 30 የኪቲም+ መርከቦች በእሱ ላይ ይመጡበታልና፤ ይዋረዳልም።
“ወደ ኋላ ይመለሳል፤ በቅዱሱ ቃል ኪዳንም ላይ የውግዘት ቃል* ይሰነዝራል፤+ እርምጃም ይወስዳል፤ ተመልሶም ትኩረቱን ቅዱስ ቃል ኪዳኑን በተዉት ላይ ያደርጋል። 31 ከእሱ የሚወጡ ክንዶች ይቆማሉ፤* እነሱም ምሽጉን ይኸውም መቅደሱን ያረክሳሉ፤+ የዘወትሩንም መሥዋዕት ያስቀራሉ።+
“ጥፋት የሚያመጣውንም ርኩስ ነገር በዚያ ያኖራሉ።+
32 “ክፋት የሚሠሩትንና ቃል ኪዳኑን የሚያፈርሱትን በማታለል* ወደ ክህደት ጎዳና ይመራቸዋል። አምላካቸውን የሚያውቁት ሰዎች ግን ይበረታሉ፤ እርምጃም ይወስዳሉ። 33 በሕዝቡም መካከል ያሉ ጥልቅ ማስተዋል ያላቸው ሰዎች+ ብዙዎች ማስተዋል እንዲኖራቸው ያደርጋሉ። እነሱም ለተወሰነ ጊዜ የሰይፍ፣ የእሳት፣ የምርኮና የብዝበዛ ሰለባ በመሆን ይወድቃሉ። 34 ሆኖም በሚወድቁበት ጊዜ መጠነኛ እርዳታ ያገኛሉ፤ ብዙዎችም አታላይ በሆነ አንደበት* ከእነሱ ጋር ይተባበራሉ። 35 እስከ ፍጻሜው ዘመን ድረስ በእነሱ የተነሳ የማጥራት፣ የማጽዳትና የማንጻት ሥራ+ ይከናወን ዘንድ ጥልቅ ማስተዋል ካላቸው ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ እንዲወድቁ ይደረጋል፤ ምክንያቱም ይህ እስከተወሰነው ጊዜ ድረስ ይቆያል።
36 “ንጉሡ እንደፈለገው ያደርጋል፤ ከአማልክትም ሁሉ በላይ ራሱን ከፍ ከፍ ያደርጋል፤ እጅግም ይኩራራል፤ በአማልክትም አምላክ+ ላይ አስደንጋጭ ነገር ይናገራል። ቁጣው እስኪፈጸም ድረስ ይሳካለታል፤ ምክንያቱም የተወሰነው ነገር መፈጸም አለበት። 37 ለአባቶቹ አምላክ ምንም ቦታ አይሰጥም፤ ደግሞም ለሴቶች ፍላጎትም ሆነ ለሌላ ለማንኛውም አምላክ ምንም ቦታ አይሰጥም፤ ራሱን ግን በሁሉም ላይ ከፍ ከፍ ያደርጋል። 38 ይልቁንም* ለምሽጎች አምላክ ክብር ይሰጣል፤ አባቶቹም ለማያውቁት አምላክ በወርቅ፣ በብር፣ በከበሩ ድንጋዮችና ተፈላጊ* በሆኑ ነገሮች ክብር ይሰጣል። 39 ከባዕድ አምላክ ጋር ሆኖ* እጅግ ጠንካራ በሆኑት ምሽጎች ላይ እርምጃ ይወስዳል። ለእሱ እውቅና የሚሰጡትን ሁሉ* ከፍተኛ ክብር ያጎናጽፋቸዋል፤ በብዙዎችም መካከል እንዲገዙ ያደርጋል፤ ምድሩንም በዋጋ ያከፋፍላል።*
40 “በፍጻሜው ዘመን የደቡቡ ንጉሥ ከእሱ ጋር ይጋፋል፤* የሰሜኑም ንጉሥ ከሠረገሎች፣ ከፈረሰኞችና ከብዙ መርከቦች ጋር እንደ አውሎ ነፋስ ይመጣበታል፤ ወደ ብዙ አገሮችም ይገባል፤ እንደ ጎርፍም እያጥለቀለቀ ያልፋል። 41 ውብ* ወደሆነችውም ምድር+ ይገባል፤ ብዙ አገሮችም ይወድቃሉ። ሆኖም ኤዶም፣ ሞዓብና የአሞናውያን ዋነኛ ክፍል ከእጁ ያመልጣሉ። 42 እጁንም በብዙ አገሮች ላይ ይዘረጋል፤ የግብፅም ምድር አታመልጥም። 43 እሱም በተደበቁ ውድ ሀብቶች፣ በወርቅና በብር እንዲሁም በግብፅ የከበሩ* ነገሮች ሁሉ ላይ ይሠለጥናል። ሊቢያውያንና ኢትዮጵያውያንም ይከተሉታል።
44 “ሆኖም ከምሥራቅና* ከሰሜን የሚመጣ ወሬ ይረብሸዋል፤ እሱም ለማጥፋትና ብዙዎችን ለመደምሰስ በታላቅ ቁጣ ይወጣል። 45 ንጉሣዊ* ድንኳኖቹንም በታላቁ ባሕርና ቅዱስ በሆነው ውብ* ተራራ+ መካከል ይተክላል፤ እሱም ወደ ፍጻሜው ይመጣል፤ የሚረዳውም አይኖርም።
12 “በዚያ ዘመን ለሕዝብህ* የሚቆመው ታላቁ አለቃ+ ሚካኤል*+ ይነሳል።* ብሔራት ከተቋቋሙበት ጊዜ አንስቶ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ሆኖ የማያውቅ የጭንቀት ጊዜ ይመጣል። በዚያን ወቅት ሕዝብህ ይኸውም በመጽሐፍ ላይ ተጽፎ የተገኘ+ እያንዳንዱ ሰው ይተርፋል።+ 2 በምድር አፈር ውስጥ ካንቀላፉትም መካከል ብዙዎቹ ይነሳሉ፤ አንዳንዶቹ ለዘላለም ሕይወት፣ ሌሎቹ ደግሞ ለነቀፋና ለዘላለማዊ ውርደት ይነሳሉ።
3 “ደግሞም ጥልቅ ማስተዋል ያላቸው ሰዎች እንደ ሰማይ ጸዳል ያበራሉ፤ የጽድቅን ጎዳና እንዲከተሉ ብዙ ሰዎችን የሚረዱም ለዘላለም እንደ ከዋክብት ያበራሉ።
4 “አንተም ዳንኤል ሆይ፣ እስከ ፍጻሜው ዘመን ድረስ ቃሉን በሚስጥር ያዝ፤ መጽሐፉንም አትመው።+ ብዙዎች መጽሐፉን በሚገባ ይመረምራሉ፤* እውነተኛው እውቀትም ይበዛል።”+
5 ከዚያም እኔ ዳንኤል ስመለከት ሌሎች ሁለት በዚያ ቆመው አየሁ፤ አንደኛው ከወንዙ በዚህኛው ዳር ቆሞ የነበረ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ከወንዙ በዚያኛው ዳር ቆሞ ነበር።+ 6 ከዚያም አንዱ፣ ከወንዙ ውኃ በላይ ያለውንና በፍታ የለበሰውን+ ሰው “እነዚህ አስደናቂ ነገሮች ፍጻሜያቸውን የሚያገኙት ከምን ያህል ጊዜ በኋላ ነው?” አለው። 7 ከዚያም ከወንዙ ውኃ በላይ ያለውና በፍታ የለበሰው ሰው መልስ ሲሰጥ ሰማሁ። እሱም ቀኝ እጁንና ግራ እጁን ወደ ሰማያት ዘርግቶ ለዘላለም ሕያው በሆነው+ በመማል እንዲህ ሲል መልስ ሰጠ፦ “ከተወሰነ ዘመን፣ ዘመናትና የዘመን እኩሌታ* በኋላ ነው። የቅዱሱ ሕዝብ ኃይል ተደምስሶ እንዳበቃ+ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ።”
8 እኔም ሰማሁ፤ ሆኖም ሊገባኝ አልቻለም፤+ ስለዚህ “ጌታዬ ሆይ፣ የእነዚህ ነገሮች መጨረሻ ምን ይሆን?” አልኩት።
9 እሱም እንዲህ አለኝ፦ “ዳንኤል ሆይ፣ ሂድ፤ ምክንያቱም የፍጻሜው ዘመን እስኪመጣ ድረስ ቃሉ በሚስጥር የተያዘና የታተመ ይሆናል።+ 10 ብዙዎች ራሳቸውን ያጸዳሉ፣ ያነጻሉ እንዲሁም ይጠራሉ።+ ክፉዎች ደግሞ ክፉ ድርጊት ይፈጽማሉ፤ ከክፉዎች መካከል አንዳቸውም አይረዱትም፤ ጥልቅ ማስተዋል ያላቸው ግን ይረዱታል።+
11 “የዘወትሩ መሥዋዕት+ ከተቋረጠበትና ጥፋት የሚያመጣው ርኩስ ነገር ከቆመበት+ ጊዜ አንስቶ 1,290 ቀን ይሆናል።
12 “ደግሞም 1,335ቱ ቀን እስከሚያልፍ ድረስ በትዕግሥት የሚጠባበቅ* ሰው ደስተኛ ነው!
13 “አንተ ግን እስከ ፍጻሜው ድረስ ሂድ። ታርፋለህ፤ ሆኖም በዘመኑ ፍጻሜ ዕጣ ፋንታህን ለመቀበል* ትነሳለህ።”+
ወይም “ቤተ መቅደስ።”
የባቢሎንን ምድር ያመለክታል።
ወይም “ቤተ መቅደስ።”
ቃል በቃል “አንዳንድ የእስራኤል ወንዶች ልጆችን።”
ቃል በቃል “ልጆች።”
“እንክብካቤ ከተደረገላቸው በኋላ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
“አምላክ ፈራጄ ነው” የሚል ትርጉም አለው።
“ይሖዋ ሞገስ አሳየ” የሚል ትርጉም አለው።
“እንደ አምላክ ያለ ማን ነው?” ማለት ሊሆን ይችላል።
“ይሖዋ ረድቶናል” የሚል ትርጉም አለው።
የባቢሎናውያን ስም።
ወይም “ደግነትና።”
ቃል በቃል “ልጆች።”
ቃል በቃል “ራሴን።”
ቃል በቃል “ልጆች።”
ቃል በቃል “ልጆች።”
ቃል በቃል “ቁመናቸው ተሽሎና ሥጋቸው ወፍሮ።”
ቃል በቃል “ልጆች።”
በሟርትና በኮከብ ቆጠራ የተካኑ ሰዎችን ያቀፈ ቡድንን ያመለክታል።
ከዳን 2:4ለ እስከ 7:28 ድረስ በመጀመሪያ የተጻፈው በአረማይክ ነበር።
“ቆሻሻ መጣያ፤ የፋንድያ ክምር” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “ከሥጋ ጋር።”
ወይም “ሐውልት።”
ወይም “የተተኮሰ (ቅርጽ የወጣለት) ሸክላ።”
ወይም “ከሰው ዘር።” ተራውን ሕዝብ ያመለክታል።
ወደ 27 ሜትር ገደማ ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወደ 2.7 ሜትር ገደማ ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ሐውልት።”
ወይም “የአይሁዳውያንን ስም አጠፉ።”
ወይም “መንፈሱ ሙሉ በሙሉ ተለወጠባቸው።”
ወይም “በሰውነታቸው ላይ ኃይል እንዳልነበረው።”
ወይም “ሰውነታቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል።”
“ቆሻሻ መጣያ፤ የፋንድያ ክምር” ማለትም ሊሆን ይችላል።
በሟርትና በኮከብ ቆጠራ የተካኑ ሰዎችን ያቀፈ ቡድንን ያመለክታል።
ቃል በቃል “ሥጋም ሁሉ ከእሱ ይመገብ ነበር።”
ወይም “እጁን ሊከለክል።”
ወይም “የንጉሡ ፊት ተለወጠ።”
በሟርትና በኮከብ ቆጠራ የተካኑ ሰዎችን ያቀፈ ቡድንን ያመለክታል።
ወይም “ጥሩ ችሎታ ያለው ሰው።”
በሟርትና በኮከብ ቆጠራ የተካኑ ሰዎችን ያቀፈ ቡድንን ያመለክታል።
ቃል በቃል “የተቋጠረውን የመፍታት።”
ቃል በቃል “የተቋጠረውን የመፍታት።”
ወይም “መግቢያ።”
“በፊቱ አንድም ሙዚቀኛ አልቀረበም” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “እንቅልፉም ከእሱ ሸሸ።”
ወይም “የዳንኤልን ስም ያጠፉትን ሰዎች።”
ወይም “ሉዓላዊነቱም።”
ወይም “በጉራ።”
ወይም “አንድ መቶ ሚሊዮን።”
ወይም “የጉራ።”
ወይም “በጉራ።”
ሦስት ዘመን ተኩልን ያመለክታል።
ወይም “ፊቴም ተለዋወጠ።”
ወይም “በሱሳ።”
ወይም “ቤተ መንግሥት፤ ምሽግ።”
ወይም “ፀሐይ ከምትጠልቅበት።”
ወይም “ፀሐይ መውጫና።”
ወይም “ወደ ጌጧ።”
ወይም “እስኪበቃቸው ድረስ።”
ወይም “ሴራ በመጠንሰስ የተካነ።”
ወይም “አሰቃቂ ጥፋት።”
“ሳያስጠነቅቅም” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ወደፊት።”
ቅዱሳን መጻሕፍቱን ያመለክታል።
ቃል በቃል “የፊት ኀፍረት።”
ቃል በቃል “የፊት ኀፍረት።”
ቃል በቃል “በእኛ ላይ በፈረዱት በፈራጆቻችን ላይ።”
ወይም “ለታማኝነትህ።”
ወይም “ትልቅ ግምት የሚሰጥህ፤ እጅግ የተከበርክ።”
ቃል በቃል “ነቢዩን።”
የዓመታት ሳምንታትን ያመለክታል።
ወይም “ቅቡዕ።”
ወይም “ይገደላል።”
ቃል በቃል “በሂዲኬል።”
ወይም “ትልቅ ግምት የሚሰጥህ፤ እጅግ የተከበርክ።”
ወይም “የመጀመሪያውን ደረጃ ከያዙት አለቆች።”
“እንደ አምላክ ያለ ማን ነው?” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “ትልቅ ግምት የሚሰጥህ፤ እጅግ የተከበርክ።”
ወይም “ለእሱ እንደ ምሽግ ሆኜ።”
ወይም “በፋርስ ምድር ይቆማሉ።”
ወይም “ለዘሩ።”
ወይም “ቀልጠው የተሠሩ ሐውልቶቻቸውን።”
ወይም “ውድ።”
ወይም “የዘራፊዎች ወንዶች ልጆች።”
ወይም “ሠራዊትም ሆነ።”
ወይም “ጌጥ በሆነችው።”
ወይም “ቁርጥ ውሳኔ ያደርጋል።”
“አስገባሪ” የሚለው ቃል ቀረጥ የሚሰበስብን ሰው ሊያመለክት ይችላል። ወይም “ተቆጣጣሪ።”
ወይም “የተጠላ።”
“ያለማስጠንቀቂያ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “በተንኮል።”
ወይም “ሠራዊት።”
“ያለማስጠንቀቂያ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “ስብ ወደሆነው።”
ወይም “ተጥለቅልቆ።”
ወይም “ቁጣውን።”
ወይም “የሚወጣ ሠራዊት ይቆማል።”
ወይም “በሽንገላ፤ በግብዝነት።”
ወይም “በሽንገላ፤ በግብዝነት።”
ወይም “በእሱ ቦታ።”
ወይም “ውድ።”
ወይም “በባዕድ አምላክ እርዳታ።”
“እሱ እውቅና የሚሰጣቸውን ሁሉ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ያድላል።”
ወይም “ይጣላል።”
ወይም “ጌጥ።”
ወይም “ውድ።”
ወይም “ከፀሐይ መውጫና።”
ወይም “ዕፁብ ድንቅ የሆኑ።”
ወይም “የጌጥ።”
ቃል በቃል “ለሕዝብህ ወንዶች ልጆች።”
“እንደ አምላክ ያለ ማን ነው?” የሚል ትርጉም አለው።
ቃል በቃል “ይቆማል።”
ቃል በቃል “ወዲያ ወዲህ ይላሉ።”
ሦስት ዘመን ተኩልን ያመለክታል።
ወይም “በጉጉት የሚጠባበቅ።”
ወይም “በተመደበልህ ቦታ።”