ለጢሞቴዎስ የተጻፈ የመጀመሪያው ደብዳቤ
1 አዳኛችን በሆነው አምላክና ተስፋችን+ በሆነው በክርስቶስ ኢየሱስ ትእዛዝ የክርስቶስ ኢየሱስ ሐዋርያ ከሆነው ከጳውሎስ፣ 2 በእምነት እውነተኛ ልጄ+ ለሆነው ለጢሞቴዎስ፦*+
አባት ከሆነው አምላክና ከጌታችን ከክርስቶስ ኢየሱስ ጸጋ፣ ምሕረትና ሰላም ለአንተ ይሁን።
3 ወደ መቄዶንያ ልሄድ በተነሳሁበት ጊዜ በኤፌሶን እንድትቆይ እንዳበረታታሁህ ሁሉ አሁንም አንዳንዶች የሐሰት ትምህርት እንዳያስፋፉ ታዛቸው ዘንድ በዚያው እንድትቆይ አበረታታሃለሁ፤ 4 በተጨማሪም ለፈጠራ ወሬዎችና+ ለትውልድ ሐረግ ቆጠራ ትኩረት እንዳይሰጡ እዘዛቸው። እንዲህ ያሉ ነገሮች ለግምታዊ ሐሳቦች በር ከመክፈት ውጭ የሚያስገኙት ፋይዳ የለም፤+ አምላክ እምነትን ለማጠናከር ከሚሰጠው ነገር ጋር ምንም ግንኙነት የላቸውም። 5 የዚህ ትእዛዝ* ዓላማ ከንጹሕ ልብ፣ ከጥሩ ሕሊናና ግብዝነት ከሌለበት እምነት+ የሚመነጭ ፍቅር+ እንዲኖረን ነው። 6 አንዳንዶች እነዚህን ነገሮች በመተው ፍሬ ቢስ ወደሆነ ወሬ ፊታቸውን አዙረዋል።+ 7 የሕግ አስተማሪዎች+ መሆን ይፈልጋሉ፤ ሆኖም የሚናገሯቸውን ነገሮችም ሆነ አጥብቀው የሚሟገቱላቸውን ነገሮች አያስተውሉም።
8 አንድ ሰው በአግባቡ ሥራ ላይ እስካዋለው ድረስ ሕጉ መልካም ነው፤ 9 ደግሞም ሕግ የሚወጣው ለጻድቅ ሰው ሳይሆን ሕግ ለሚተላለፉና+ ለዓመፀኞች፣ ፈሪሃ አምላክ ለሌላቸውና ለኃጢአተኞች፣ ታማኞች ላልሆኑና* ቅዱስ የሆነውን ለሚንቁ፣ አባትንና እናትን ለሚገድሉ እንዲሁም ለነፍሰ ገዳዮች መሆኑን መገንዘብ ይኖርበታል፤ 10 በተጨማሪም ለሴሰኞች፣* ግብረ ሰዶም ለሚፈጽሙ ወንዶች፣* ለአፋኞች፣ ለውሸታሞችና በሐሰት ለሚምሉ* እንዲሁም ትክክለኛውን* ትምህርት+ ለሚጻረሩ ነገሮች ሁሉ ነው፤ 11 ይህ ትምህርት ደስተኛው አምላክ ከገለጸው ክብራማ ምሥራች ጋር የሚስማማ ሲሆን እሱም ምሥራቹን በአደራ ሰጥቶኛል።+
12 ለአገልግሎቱ በመሾም ታማኝ አድርጎ ስለቆጠረኝ ኃይል የሰጠኝን ጌታችን ክርስቶስ ኢየሱስን አመሰግናለሁ፤+ 13 ምንም እንኳ ቀደም ሲል አምላክን የምሳደብ፣ አሳዳጅና እብሪተኛ የነበርኩ ብሆንም ይህን አድርጎልኛል።+ ደግሞም ባለማወቅና ባለማመን ስላደረግኩት፣ ምሕረት ተደርጎልኛል። 14 የጌታችን ጸጋም ከእምነት እንዲሁም የክርስቶስ ኢየሱስ ተከታይ በመሆኔ ምክንያት ካገኘሁት ፍቅር ጋር እጅግ ተትረፍርፎልኛል። 15 ‘ክርስቶስ ኢየሱስ ኃጢአተኞችን ለማዳን+ ወደ ዓለም መጣ’ የሚለው ቃል እምነት የሚጣልበትና ሙሉ ተቀባይነት ሊያገኝ የሚገባው ነው። ከኃጢአተኞች ደግሞ እኔ ዋነኛ ነኝ።+ 16 ይሁንና ለእኔ ምሕረት የተደረገው ክርስቶስ ኢየሱስ፣ ዋነኛ ኃጢአተኛ የሆንኩትን እኔን ምሳሌ አድርጎ በመጠቀም የዘላለም ሕይወት ለማግኘት እምነታቸውን በእሱ ላይ ለሚጥሉ ሰዎች ትዕግሥቱን ሁሉ ያሳይ ዘንድ ነው።+
17 እንግዲህ ለማይጠፋውና+ ለማይታየው፣+ እሱ ብቻ አምላክ ለሆነው+ ለዘላለሙ ንጉሥ+ ክብርና ግርማ ለዘላለም ይሁን። አሜን።
18 ልጄ ጢሞቴዎስ፣ ከዚህ ቀደም ስለ አንተ በተነገሩት ትንቢቶች መሠረት ይህን ትእዛዝ* በአደራ እሰጥሃለሁ፤ ይኸውም ከእነዚህ ጋር በሚስማማ መንገድ መልካሙን ውጊያ መዋጋትህን እንድትቀጥል ነው፤+ 19 ይህን የምታደርገው እምነትንና ጥሩ ሕሊናን+ አጥብቀህ በመያዝ ነው፤ አንዳንዶች ሕሊናቸውን ወደ ጎን ገሸሽ በማድረጋቸው ባሕር ላይ አደጋ ደርሶበት እንደተሰባበረ መርከብ እምነታቸው ጠፍቷል። 20 ከእነሱም መካከል ሄሜኔዎስና+ እስክንድር ይገኙበታል፤ እነሱ ከተግሣጽ ተምረው በአምላክ ላይ የስድብ ቃል ከመናገር እንዲቆጠቡ ለሰይጣን አሳልፌ ሰጥቻቸዋለሁ።*+
2 እንግዲህ ከሁሉ አስቀድሞ ሁሉንም ዓይነት ሰዎች በተመለከተ ምልጃ፣ ጸሎት፣ ልመናና ምስጋና እንዲቀርብ አሳስባለሁ፤ 2 በተጨማሪም ነገሥታትንና በሥልጣን ላይ ያሉትን ሁሉ በተመለከተ እንዲሁ እንዲደረግ አሳስባለሁ፤+ ይህም ሙሉ በሙሉ ለአምላክ በማደርና ሁሉንም ነገር በትጋት በማከናወን* በጸጥታና በተረጋጋ ሁኔታ መኖራችንን እንቀጥል ዘንድ ነው።+ 3 ይህም አዳኛችን በሆነው አምላክ+ ፊት መልካምና ተቀባይነት ያለው ነው፤ 4 የእሱ ፈቃድ ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑና+ የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ ነው። 5 አንድ አምላክ አለና፤+ በአምላክና በሰው መካከል+ ደግሞ አንድ መካከለኛ አለ፤+ እሱም ሰው የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤+ 6 ራሱን ለሁሉ* ተመጣጣኝ ቤዛ አድርጎ ሰጠ፤+ በተወሰነለት ጊዜም የምሥክርነት ቃል የሚነገርለት ነገር ይህ ነው። 7 ሰባኪና ሐዋርያ+ ይኸውም እምነትንና እውነትን በተመለከተ የአሕዛብ አስተማሪ+ ሆኜ የተሾምኩት ለዚህ ምሥክርነት ሲባል ነው፤+ ይህን ስል እውነቱን እየተናገርኩ ነው እንጂ እየዋሸሁ አይደለም።
8 ስለዚህ በሁሉም ቦታ ወንዶች ቁጣንና+ ክርክርን+ አስወግደው ታማኝ እጆችን ወደ ላይ በማንሳት+ አዘውትረው እንዲጸልዩ እፈልጋለሁ። 9 በተመሳሳይም ሴቶች ፀጉር በመሸረብና በወርቅ ወይም በዕንቁ ወይም ደግሞ በጣም ውድ በሆነ ልብስ ሳይሆን በልከኝነትና በማስተዋል፣* ተገቢ በሆነ* ልብስ ራሳቸውን ያስውቡ፤+ 10 ለአምላክ ያደርን ነን የሚሉ ሴቶች ሊያደርጉት እንደሚገባ በመልካም ሥራ ይዋቡ።+
11 ሴት ሙሉ በሙሉ በመገዛት+ በጸጥታ* ትማር። 12 ሴት ዝም እንድትል እንጂ እንድታስተምር ወይም በወንድ ላይ ሥልጣን እንዲኖራት አልፈቅድም።+ 13 በመጀመሪያ የተፈጠረው አዳም ነውና፤ ከዚያም ሔዋን ተፈጠረች።+ 14 በተጨማሪም አዳም አልተታለለም፤ ከዚህ ይልቅ ፈጽሞ የተታለለችውና+ ሕግ የተላለፈችው ሴቷ ናት። 15 ይሁን እንጂ ሴት ጤናማ አስተሳሰብ በመያዝ* በእምነት፣ በፍቅርና በቅድስና ብትጸና ልጅ በመውለድ+ ደህንነቷ ተጠብቆ* ትኖራለች።+
3 ይህ ቃል እምነት የሚጣልበት ነው፦ የበላይ ተመልካች+ ለመሆን የሚጣጣር ሰው መልካም ሥራን ይመኛል። 2 ስለዚህ የበላይ ተመልካች የማይነቀፍ፣ የአንዲት ሚስት ባል፣ በልማዶቹ ልከኛ የሆነ፣ ጤናማ አስተሳሰብ ያለው፣*+ ሥርዓታማ፣ እንግዳ ተቀባይ፣+ የማስተማር ብቃት ያለው፣+ 3 የማይሰክር፣*+ ኃይለኛ ያልሆነ፣* ይልቁንም ምክንያታዊ የሆነ፣+ የማይጣላ፣+ ገንዘብ ወዳድ ያልሆነ፣+ 4 ታዛዥና ቁም ነገረኛ የሆኑ ልጆች ያሉትና የራሱን ቤተሰብ በተገቢው ሁኔታ የሚያስተዳድር ሊሆን ይገባዋል፤+ 5 (ደግሞስ አንድ ሰው የራሱን ቤተሰብ እንዴት እንደሚያስተዳድር ካላወቀ የአምላክን ጉባኤ እንዴት ሊንከባከብ ይችላል?) 6 በትዕቢት ተነፍቶ ዲያብሎስ የተፈረደበት ዓይነት ፍርድ እንዳይፈረድበት አዲስ ክርስቲያን አይሁን።+ 7 ከዚህም በተጨማሪ እንዳይነቀፍና* በዲያብሎስ ወጥመድ ውስጥ እንዳይወድቅ በውጭ ባሉት* ሰዎች ዘንድ በመልካም የተመሠከረለት* ሊሆን ይገባል።+
8 የጉባኤ አገልጋዮችም በተመሳሳይ ቁም ነገረኞች፣ በሁለት ምላስ የማይናገሩ፣* ብዙ የወይን ጠጅ የማይጠጡ፣ አግባብ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት የማይስገበገቡ፣+ 9 የእምነትን ቅዱስ ሚስጥር በንጹሕ ሕሊና አጥብቀው የሚይዙ መሆን ይገባቸዋል።+
10 በተጨማሪም ብቁ መሆናቸውን ለማረጋገጥ በቅድሚያ ይፈተኑ፤ ከዚያም ከክስ ነፃ ሆነው+ ከተገኙ አገልጋይ ሆነው ያገልግሉ።
11 ሴቶችም እንደዚሁ ቁም ነገረኞች፣ የሰው ስም የማያጠፉ፣+ በልማዶቻቸው ልከኞችና በሁሉም ነገር ታማኞች ሊሆኑ ይገባል።+
12 የጉባኤ አገልጋዮች የአንዲት ሚስት ባል እንዲሁም ልጆቻቸውንና የራሳቸውን ቤተሰብ በተገቢው ሁኔታ የሚያስተዳድሩ ሊሆኑ ይገባል። 13 በተገቢው ሁኔታ የሚያገለግሉ ወንዶች ለራሳቸው መልካም ስም የሚያተርፉ ከመሆናቸውም በላይ በክርስቶስ ኢየሱስ ላይ ስላላቸው እምነት አፋቸውን ሞልተው ለመናገር የሚያስችል ነፃነት ያገኛሉና።
14 በቅርቡ ወደ አንተ እንደምመጣ ተስፋ ባደርግም እነዚህን ነገሮች ጽፌልሃለሁ፤ 15 ይህን ያደረግኩት ምናልባት ብዘገይ በአምላክ ቤተሰብ+ ይኸውም የእውነት ዓምድና ድጋፍ በሆነው የሕያው አምላክ ጉባኤ ውስጥ ምን ዓይነት ምግባር ማሳየት እንዳለብህ ታውቅ ዘንድ ነው። 16 በእርግጥም ይህ ለአምላክ የማደር ቅዱስ ሚስጥር ያለጥርጥር ታላቅ ነው፦ ‘በሥጋ እንዲገለጥ ተደረገ፤+ በመንፈስ ጻድቅ ተባለ፤+ ለመላእክት ታየ፤+ በአሕዛብ መካከል ተሰበከ፤+ በዓለም ያሉ አመኑበት፤+ በክብር አረገ።’
4 ይሁን እንጂ በመንፈስ መሪነት የተነገረው ቃል በኋለኞቹ ዘመናት አንዳንዶች ከመናፍስት ለሚመነጩ አሳሳች ቃሎችና*+ ለአጋንንት ትምህርቶች ጆሯቸውን በመስጠት ከእምነት መውጣታቸው እንደማይቀር በግልጽ ይናገራል፤ 2 ይህም የሚሆነው በጋለ ብረት የተተኮሰ ያህል ሕሊናቸው የደነዘዘባቸው ግብዝ ሰዎች በሚናገሩት ውሸት የተነሳ ነው።+ 3 እነዚህ ሰዎች ጋብቻን ይከለክላሉ፤+ እንዲሁም እምነት ያላቸውና እውነትን በትክክል የተረዱ ሰዎች ምስጋና አቅርበው እንዲበሏቸው+ አምላክ የፈጠራቸውን ምግቦች+ ‘አትብሉ’ ብለው ያዛሉ።+ 4 ይሁንና አምላክ የፈጠረው ነገር ሁሉ መልካም ነው፤+ በምስጋና እስከተቀበሉት ድረስ ምንም የሚጣል ነገር የለም፤+ 5 በአምላክ ቃልና በጸሎት ተቀድሷልና።
6 ይህን ምክር ለወንድሞች በመስጠት የእምነትንና አጥብቀህ የተከተልከውን የመልካም ትምህርት ቃል በሚገባ የተመገብክ የክርስቶስ ኢየሱስ ጥሩ አገልጋይ ትሆናለህ።+ 7 ነገር ግን አሮጊቶች እንደሚያወሯቸው ካሉ አምላክን የሚጻረሩ የውሸት ታሪኮች ራቅ።+ ከዚህ ይልቅ ለአምላክ ማደርን ግብ አድርገህ ራስህን አሠልጥን። 8 የአካል ብቃት እንቅስቃሴ* በጥቂቱ ይጠቅማል፤ ለአምላክ ማደር ግን ለአሁኑም ሆነ ለወደፊቱ ሕይወት ተስፋ ስለሚሰጥ ለሁሉም ነገር ይጠቅማል።+ 9 ይህ ቃል እምነት የሚጣልበትና ሙሉ በሙሉ ሊቀበሉት የሚገባ ነው። 10 ጠንክረን በመሥራትና ብርቱ ጥረት በማድረግ ላይ ያለነውም ለዚህ ነው፤+ ምክንያቱም ሁሉንም ዓይነት ሰዎች+ በተለይ ደግሞ ታማኝ የሆኑትን በሚያድነው+ ሕያው አምላክ ላይ ተስፋችንን ጥለናል።
11 እነዚህን ትእዛዛት መስጠትህንና ማስተማርህን ቀጥል። 12 ወጣት በመሆንህ ማንም ሰው ሊንቅህ አይገባም። ከዚህ ይልቅ ታማኞች ለሆኑት በንግግር፣ በምግባር፣ በፍቅር፣ በእምነትና በንጽሕና አርዓያ ሁን። 13 እኔ እስክመጣ ድረስ ለሰዎች ለማንበብ፣+ አጥብቀህ ለመምከርና* ለማስተማር የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ። 14 የሽማግሌዎች አካል እጁን በአንተ ላይ በጫነበት+ ጊዜ በትንቢት የተሰጠህን ስጦታ ቸል አትበል። 15 እድገትህ በሁሉም ሰዎች ዘንድ በግልጽ እንዲታይ በእነዚህ ነገሮች ላይ አሰላስል፤* እንዲሁም ትኩረትህ ሙሉ በሙሉ በእነዚህ ነገሮች ላይ ያረፈ ይሁን። 16 ለራስህና ለምታስተምረው ትምህርት ምንጊዜም ትኩረት ስጥ።+ በእነዚህ ነገሮች ጽና፤ ይህን በማድረግ ራስህንም ሆነ የሚሰሙህን ታድናለህና።+
5 ሽማግሌ የሆነውን በኃይለ ቃል አትናገረው።+ ከዚህ ይልቅ እንደ አባት ቆጥረህ በደግነት ምከረው፤ ወጣት ወንዶችን እንደ ወንድሞች፣ 2 አሮጊቶችን እንደ እናቶች፣ ወጣት ሴቶችን ደግሞ እንደ እህቶች አድርገህ በፍጹም ንጽሕና ያዛቸው።
3 በእርግጥ መበለት ለሆኑ መበለቶች*+ አሳቢነት* አሳያቸው። 4 ሆኖም አንዲት መበለት ልጆች ወይም የልጅ ልጆች ካሏት እነዚህ ልጆች በመጀመሪያ በራሳቸው ቤተሰብ+ ውስጥ ለአምላክ የማደርን ባሕርይ ማንጸባረቅን እንዲሁም ለወላጆቻቸውና ለአያቶቻቸው የሚገባቸውን ብድራት መክፈልን ይማሩ፤+ ይህ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ነገር ነውና።+ 5 በእርግጥ መበለት የሆነችና ምንም የሌላት ሴት ተስፋዋን በአምላክ ላይ ትጥላለች+ እንዲሁም ሌት ተቀን ያለማሰለስ ምልጃና ጸሎት ታቀርባለች።+ 6 ለሥጋዊ ፍላጎቷ ያደረች መበለት ግን በሕይወት ብትኖርም የሞተች ናት። 7 ስለዚህ ከነቀፋ ነፃ መሆን ይችሉ ዘንድ እነዚህን መመሪያዎች* መስጠትህን ቀጥል። 8 በእርግጥም አንድ ሰው የራሱ ለሆኑት በተለይ ደግሞ ለቤተሰቡ አባላት የሚያስፈልጋቸውን ነገር የማያቀርብ ከሆነ እምነትን የካደ ከመሆኑም በላይ እምነት የለሽ ከሆነ ሰው የከፋ ነው።+
9 አንዲት መበለት ከ60 ዓመት በላይ ከሆነች በመዝገብ ላይ ትጻፍ፤ ደግሞም የአንድ ባል ሚስት የነበረች ልትሆን ይገባል፤ 10 እንዲሁም ልጆችን በማሳደግ፣+ እንግዶችን በመቀበል፣+ የቅዱሳንን እግር በማጠብ፣+ የተቸገሩትን በመርዳትና+ ማንኛውንም በጎ ተግባር በትጋት በማከናወን በመልካም ሥራ ጥሩ ስም ያተረፈች+ ልትሆን ይገባል።
11 በዕድሜ ያልገፉ መበለቶች ግን መዝገብ ላይ መጻፍ የለባቸውም፤ የፆታ ፍላጎታቸው በክርስቲያናዊ አገልግሎታቸው ላይ እንቅፋት በሚፈጥርበት ጊዜ ማግባት ይፈልጋሉና። 12 ደግሞም የመጀመሪያውን የእምነት ቃላቸውን* ስላፈረሱ በራሳቸው ላይ ፍርድ ያመጣሉ። 13 ከዚህ በተጨማሪ በየቤቱ እየዞሩ ሥራ ፈት ይሆናሉ፤ ሥራ ፈት መሆን ብቻ ሳይሆን ማውራት ስለማይገባቸው ነገሮች እያወሩ ሐሜተኞችና በሌሎች ሰዎች ጉዳይ ጣልቃ የሚገቡ ይሆናሉ።+ 14 ስለዚህ በዕድሜ ያልገፉ መበለቶች እንዲያገቡ፣+ ልጆች እንዲወልዱ፣+ ቤታቸውን እንዲያስተዳድሩና ተቃዋሚው ትችት ሊሰነዝር የሚችልበት አጋጣሚ እንዲያገኝ ከማድረግ እንዲቆጠቡ እፈልጋለሁ። 15 እንዲያውም አንዳንዶቹ ከዚህ በፊት ሰይጣንን ለመከተል ዞር ብለዋል። 16 አንዲት አማኝ የሆነች ሴት፣ መበለት የሆኑ ዘመዶች ቢኖሯት ጉባኤው ሸክም እንዳይበዛበት እሷ ትርዳቸው። በዚህ መንገድ ጉባኤው በእርግጥ መበለት የሆኑትን* መርዳት ይችላል።+
17 በመልካም ሁኔታ የሚያስተዳድሩ+ በተለይ ደግሞ በመናገርና በማስተማር ተግተው የሚሠሩ+ ሽማግሌዎች እጥፍ ክብር ሊሰጣቸው ይገባል።+ 18 የቅዱስ መጽሐፉ ቃል “እህል እያበራየ ያለውን በሬ አፉን አትሰር”፤+ እንዲሁም “ለሠራተኛ ደሞዙ ይገባዋል” ይላልና።+ 19 በሁለት ወይም በሦስት ምሥክሮች+ ማስረጃ ካልሆነ በቀር በሽማግሌ ላይ የሚቀርብን ክስ አትቀበል። 20 ለሌሎቹ ማስጠንቀቂያ እንዲሆን* ኃጢአት የመሥራት ልማድ ያላቸውን ሰዎች+ በሁሉ ፊት ውቀሳቸው።+ 21 እነዚህን መመሪያዎች መሠረተ ቢስ ከሆነ ጥላቻና ከአድልዎ በራቀ መንገድ እንድትጠብቅ በአምላክ፣ በክርስቶስ ኢየሱስና በተመረጡት መላእክት ፊት በጥብቅ አዝሃለሁ።+
22 በማንም ሰው ላይ እጅህን ለመጫን አትቸኩል፤*+ እንዲሁም በሌሎች ኃጢአት ተካፋይ አትሁን፤ ራስህን በንጽሕና ጠብቅ።
23 ከእንግዲህ ውኃ አትጠጣ፤* ከዚህ ይልቅ ለሆድህና በተደጋጋሚ ለሚነሳብህ ሕመም ጥቂት የወይን ጠጅ ጠጣ።
24 የአንዳንድ ሰዎች ኃጢአት በይፋ የታወቀ ስለሚሆን ወዲያውኑ ፍርድ ያስከትላል፤ የሌሎቹ ሰዎች ኃጢአት ደግሞ ውሎ አድሮ መታወቁ አይቀርም።+ 25 በተመሳሳይም መልካም ሥራዎች በይፋ የታወቁ ናቸው፤+ በይፋ ያልታወቁትም ቢሆኑ ተደብቀው ሊቀሩ አይችሉም።+
6 የአምላክ ስምና ትምህርት ፈጽሞ እንዳይሰደብ በባርነት ቀንበር ሥር ያሉ ሁሉ ጌቶቻቸው ሙሉ ክብር እንደሚገባቸው ይገንዘቡ።+ 2 በተጨማሪም አማኝ የሆኑ ጌቶች ያሏቸው ባሪያዎች፣ ጌቶቻቸው ወንድሞች ስለሆኑ ብቻ አክብሮት አይንፈጓቸው። ከዚህ ይልቅ እነሱ ከሚሰጡት ጥሩ አገልግሎት እየተጠቀሙ ያሉት፣ የእምነት ባልንጀሮቻቸውና የተወደዱ ወንድሞቻቸው ስለሆኑ ይበልጥ በትጋት ያገልግሏቸው።
እነዚህን ነገሮች ማስተማርህንና እነዚህን ማሳሰቢያዎች መስጠትህን ቀጥል። 3 አንድ ሰው የተለየ ትምህርት ቢያስተምርና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካስተማረው ትክክለኛ* ትምህርትም+ ሆነ ለአምላክ ማደርን ከሚያበረታታው ትምህርት+ ጋር የማይስማማ ቢሆን 4 ይህ ሰው በትዕቢት የተወጠረና ምንም የማያስተውል ነው።+ ስለ ቃላት የመጨቃጨቅና የመከራከር አባዜ* የተጠናወተው ነው።+ እንዲህ ያሉ ነገሮች ቅናት፣ ጠብ፣ ስም ማጥፋትና* መጥፎ ጥርጣሬ ያስከትላሉ፤ 5 በተጨማሪም ለአምላክ ማደር ጥቅም ማግኛ እንደሆነ አድርገው በሚያስቡ፣+ አእምሯቸው በተበላሸና+ እውነትን መረዳት ባቆሙ ሰዎች መካከል ተራ በሆኑ ጉዳዮች የማያባራ ጭቅጭቅ ያስነሳሉ። 6 እንደ እውነቱ ከሆነ ለአምላክ ያደርን+ መሆናችንና ባለን ነገር ረክተን መኖራችን ትልቅ ጥቅም ያስገኛል። 7 ወደ ዓለም ያመጣነው ምንም ነገር የለምና፤ ምንም ነገር ይዘን መሄድም አንችልም።+ 8 ስለዚህ ምግብና ልብስ* ካለን በእነዚህ ነገሮች ረክተን መኖር ይገባናል።+
9 ሀብታም ለመሆን ቆርጠው የተነሱ ግን ፈተናና ወጥመድ+ ውስጥ ይወድቃሉ፤ እንዲሁም ሰዎችን ጥፋትና ብልሽት ውስጥ በሚዘፍቁ ከንቱና ጎጂ በሆኑ ብዙ ምኞቶች ይያዛሉ።+ 10 የገንዘብ ፍቅር የብዙ ዓይነት ጎጂ ነገሮች ሥር ነውና፤ አንዳንዶች በዚህ ፍቅር ተሸንፈው ከእምነት ጎዳና ስተው ወጥተዋል፤ እንዲሁም ሁለንተናቸውን በብዙ ሥቃይ ወግተዋል።+
11 የአምላክ ሰው ሆይ፣ አንተ ግን ከእነዚህ ነገሮች ሽሽ። ከዚህ ይልቅ ጽድቅን፣ ለአምላክ ማደርን፣ እምነትን፣ ፍቅርን፣ ጽናትንና ገርነትን+ ተከታተል። 12 መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል፤ የተጠራህለትንና በብዙ ምሥክሮች ፊት በጥሩ ሁኔታ በይፋ የተናገርክለትን የዘላለም ሕይወት አጥብቀህ ያዝ።
13 ሁሉንም ነገሮች ሕያው አድርጎ በሚያኖረው አምላክና ለጳንጥዮስ ጲላጦስ+ በይፋ ግሩም ምሥክርነት በሰጠው በክርስቶስ ኢየሱስ ፊት ይህን አዝሃለሁ፦ 14 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስኪገለጥ+ ድረስ ትእዛዙን ያለእንከንና ያለነቀፋ ጠብቅ፤ 15 ደስተኛውና ብቸኛው ኃያል ገዢ በተወሰነለት ጊዜ ራሱን ይገልጣል። እሱ የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ ነው፤+ 16 ያለመሞትን ባሕርይ+ የተላበሰው እሱ ብቻ ነው፤ ሊቀረብ በማይችል ብርሃን ውስጥ ይኖራል፤+ እሱን ያየ ወይም ሊያየው የሚችል አንድም ሰው የለም።+ ክብርና ዘላለማዊ ኃይል ለእሱ ይሁን። አሜን።
17 አሁን ባለው ሥርዓት* ሀብታም የሆኑትን ሰዎች እንዳይታበዩ እንዲሁም ተስፋቸውን አስተማማኝነት በሌለው ሀብት+ ላይ ሳይሆን የሚያስደስቱንን ነገሮች ሁሉ አትረፍርፎ በሚሰጠን አምላክ ላይ እንዲጥሉ እዘዛቸው።+ 18 በተጨማሪም መልካም ነገር እንዲያደርጉ፣ በመልካም ሥራዎች ባለጸጋ እንዲሆኑ እንዲሁም ለጋሶችና ለሌሎች ለማካፈል ዝግጁ እንዲሆኑ ምከራቸው፤+ 19 እውነተኛ የሆነውን ሕይወት አጥብቀው መያዝ ይችሉ ዘንድ+ ለራሳቸው ውድ ሀብት ማከማቸታቸውን ይኸውም ለወደፊቱ ጊዜ የሚሆን መልካም መሠረት መጣላቸውን ይቀጥሉ።+
20 ጢሞቴዎስ ሆይ፣ ቅዱስ የሆነውን ነገር ከሚጻረሩ ከንቱ ንግግሮችና በውሸት “እውቀት” ተብለው ከሚጠሩ እርስ በርሳቸው ከሚቃረኑ ሐሳቦች በመራቅ+ በአደራ የተሰጠህን ነገር ጠብቅ።+ 21 አንዳንዶች እንዲህ ዓይነቱ እውቀት እንዲታይላቸው ለማድረግ ሲጣጣሩ ከእምነት ጎዳና ወጥተዋል።
የአምላክ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።
“አምላክን የሚያከብር ሰው” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “መመሪያ።”
ወይም “ታማኝ ፍቅር ለሌላቸውና።”
የቃላት መፍቻው ላይ “የፆታ ብልግና” የሚለውን ተመልከት።
ወይም “ከወንዶች ጋር የፆታ ግንኙነት ለሚፈጽሙ ወንዶች።” ቃል በቃል “ከወንዶች ጋር ለሚተኙ ወንዶች።”
ወይም “መሐላ ለሚያፈርሱ።”
ወይም “ጤናማውን፤ ጠቃሚውን።”
ወይም “መመሪያ።”
ከጉባኤ መወገዳቸውን ያመለክታል።
ወይም “ቁም ነገረኛ በመሆን።”
ወይም “ለሁሉም ዓይነት ሰዎች።”
ወይም “በጥሩ የማመዛዘን ችሎታ።”
ወይም “በሚያስከብር።”
ወይም “በዝምታ፤ በእርጋታ።”
ወይም “በጥሩ የማመዛዘን ችሎታ።”
መንፈሳዊነቷ ተጠብቆ ትኖራለች ማለት ነው።
ወይም “ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ ያለው።”
ቃል በቃል “ለወይን ጠጅ ያላደረ።”
ወይም “የማይማታ።” የግሪክኛው ቃል ሌሎችን መስደብንም ሊያመለክት ይችላል።
ወይም “እንዳይዋረድና።”
ወይም “የክርስቲያን ጉባኤ አባል ባልሆኑት።”
ወይም “ጥሩ ስም ያተረፈ።”
ወይም “በአንደበታቸው የማያታልሉ።”
ቃል በቃል “ለአሳሳች መናፍስትና።”
እዚህ ላይ የገባው ግሪክኛ ቃል የጅምናስቲክ ስፖርተኛ የሚወስደውን ዓይነት ሥልጠና ያመለክታል።
ወይም “ለማበረታታትና።”
ወይም “አውጠንጥን።”
ወይም “በእርግጥ ለተቸገሩ መበለቶች።” ረዳት የሌላቸውን መበለቶች ያመለክታል።
ቃል በቃል “አክብሮት።”
ወይም “ትእዛዛት።”
ወይም “በፊት የገቡትን ቃል።”
ወይም “በእርግጥ የተቸገሩ መበለቶችን።” ረዳት የሌላቸውን መበለቶች ያመለክታል።
ቃል በቃል “ሌሎቹ እንዲፈሩ።”
ማንኛውንም ሰው ለመሾም አትቸኩል ማለት ነው።
ወይም “ውኃ ብቻ አትጠጣ።”
ወይም “ጤናማ፤ ጠቃሚ።”
ወይም “ክፉ ጉጉት።”
ወይም “ስድብና።”
“መጠለያ” ማለትም ሊሆን ይችላል። ቃል በቃል “መሸፈኛ።”
ወይም “በአሁኑ ዘመን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።