ለቆሮንቶስ ሰዎች የተጻፈ ሁለተኛው ደብዳቤ
1 በአምላክ ፈቃድ የክርስቶስ ኢየሱስ ሐዋርያ ከሆነው ከጳውሎስና ከወንድማችን ከጢሞቴዎስ፣+ በቆሮንቶስ ለሚገኘው የአምላክ ጉባኤ እንዲሁም በመላው አካይያ+ ለሚኖሩ ቅዱሳን ሁሉ፦
2 አባታችን ከሆነው አምላክና ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።
3 የምሕረት* አባትና+ የመጽናናት+ ሁሉ አምላክ የሆነው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት+ ይወደስ፤ 4 እኛ ከአምላክ በምናገኘው መጽናኛ+ በማንኛውም ዓይነት መከራ* ውስጥ ያሉትን ሰዎች ማጽናናት እንድንችል+ እሱ በሚደርስብን መከራ ሁሉ ያጽናናናል።*+ 5 ስለ ክርስቶስ ብለን የምንቀበለው መከራ ብዙ እንደሆነ ሁሉ+ በክርስቶስ በኩል የምናገኘው መጽናኛም የዚያኑ ያህል ብዙ ነው። 6 ስለዚህ እኛ መከራ ቢደርስብን ለእናንተ መጽናኛና መዳን ያስገኛል፤ መጽናኛ ብናገኝ ደግሞ በእኛ ላይ የደረሰው መከራ በእናንተም ላይ ሲደርስ እንድትጸኑ የሚረዳ መጽናኛ ይሆንላችኋል። 7 እናንተን በተመለከተ ያለን ተስፋ የማይናወጥ ነው፤ ይህም የሆነው መከራውን ከእኛ ጋር እንደምትካፈሉ ሁሉ መጽናኛውንም እንደምትካፈሉ ስለምናውቅ ነው።+
8 ወንድሞች፣ በእስያ አውራጃ ስለደረሰብን መከራ እንድታውቁ እንፈልጋለን።+ ከአቅማችን በላይ የሆነ ከባድ ጫና ደርሶብን ስለነበር በሕይወት የመትረፍ ተስፋችን እንኳ ተሟጦ ነበር።+ 9 እንዲያውም የሞት ፍርድ ተፈርዶብናል የሚል ስሜት አድሮብን ነበር። ይህ የሆነው ግን በራሳችን ሳይሆን ሙታንን በሚያስነሳው አምላክ እንድንታመን ነው።+ 10 እሱ እንዲህ ካለ ለሞት ሊዳርግ የሚችል አደገኛ ሁኔታ አድኖናል፤ ደግሞም ያድነናል፤ ወደፊትም እንደሚያድነን በእሱ ተስፋ እናደርጋለን።+ 11 እናንተም ስለ እኛ ምልጃ በማቅረብ ልትረዱን ትችላላችሁ።+ ይህን ማድረጋችሁ ብዙዎች በሚያቀርቡት ጸሎት የተነሳ ለሚደረግልን ቸርነት ብዙዎች ስለ እኛ የምስጋና ጸሎት እንዲያቀርቡ ያነሳሳቸዋል።+
12 የምንኮራበት ነገር ይህ ነው፦ በዓለም ውስጥ በተለይም በእናንተ መካከል በቅድስናና አምላካዊ ቅንነት በማሳየት እንደኖርን ሕሊናችን ይመሠክራል፤ ይህን ያደረግነው በሥጋዊ ጥበብ ሳይሆን+ በአምላክ ጸጋ ነው። 13 ልታነብቡትና* ልትረዱት ከምትችሉት በቀር ስለ ሌላ ነገር አንጽፍላችሁም፤ ይህን ነገር በተሟላ ሁኔታ* መረዳታችሁን እንደምትቀጥሉ ተስፋ አደርጋለሁ፤ 14 አንዳንዶቻችሁ በእኛ መኩራት እንደምትችሉ እንደተገነዘባችሁ ሁሉ እኛም በጌታችን በኢየሱስ ቀን በእናንተ እንኮራለን።
15 በመሆኑም በዚህ በመተማመን ዳግመኛ እንድትደሰቱ* በመጀመሪያ ወደ እናንተ ለመምጣት አቅጄ ነበር፤ 16 ወደ መቄዶንያ ስሄድ እግረ መንገዴን እናንተን ለማየት፣ ከዚያም ከመቄዶንያ ተመልሼ ከእናንተ ጋር ለመገናኘትና ወደ ይሁዳ እንድትሸኙኝ ለማድረግ አስቤ ነበር።+ 17 እንዲህ ዓይነት ዕቅድ አውጥቼ የነበረው እንዲሁ ሳላስብበት ይመስላችኋል? ወይስ ማንኛውንም ነገር ሳቅድ በሥጋዊ አስተሳሰብ ተነድቼ በማቀድ አንዴ “አዎ፣ አዎ” ከዚያ ደግሞ “አይሆንም፣ አይሆንም” የምል ይመስላችኋል? 18 አምላክ እምነት የሚጣልበት እንደመሆኑ መጠን እኛ ለእናንተ የምንናገረውም ነገር እውነት ነው። መጀመሪያ ላይ “አዎ” ብለን ከዚያ ደግሞ “አይሆንም” አንልም። 19 ምክንያቱም እኛ ማለትም እኔ፣ ስልዋኖስና* ጢሞቴዎስ+ የሰበክንላችሁ የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ “አዎ” ሆኖ እያለ “አይደለም” ሊሆን አይችልም፤ ከዚህ ይልቅ ከእሱ ጋር በተያያዘ “አዎ” የተባለው “አዎ” ሆኗል። 20 አምላክ የሰጣቸው ተስፋዎች የቱንም ያህል ብዙ ቢሆኑም በእሱ አማካኝነት “አዎ” ሆነዋል።+ ስለዚህ እኛ ለአምላክ ክብር እንድንሰጥ በእሱ አማካኝነት ለአምላክ “አሜን” እንላለን።+ 21 ይሁንና እኛም ሆን እናንተ የክርስቶስ ለመሆናችን ዋስትና የሰጠንና የቀባን አምላክ ነው።+ 22 በተጨማሪም በማኅተሙ ያተመን+ ሲሆን ወደፊት ለሚመጣውም ነገር ማረጋገጫ* ሰጥቶናል፤ ይህም በልባችን ውስጥ ያለው መንፈስ ነው።+
23 ወደ ቆሮንቶስ እስካሁን ያልመጣሁት ለባሰ ሐዘን እንዳልዳርጋችሁ ብዬ ነው፤ ይህ እውነት ካልሆነ አምላክ በእኔ* ላይ ይመሥክርብኝ። 24 ጸንታችሁ የቆማችሁት በራሳችሁ እምነት ስለሆነ እኛ ለደስታችሁ ከእናንተ ጋር የምንሠራ ነን እንጂ በእምነታችሁ ላይ የምናዝ አይደለንም።+
2 እንደገና በምመጣበት ጊዜ ለሐዘን ምክንያት የሚሆን ነገር እንዳይፈጠር ወስኛለሁ። 2 ምክንያቱም የደስታዬ ምንጭ የሆናችሁትን እናንተን ካሳዘንኳችሁ እንግዲህ እኔን ማን ሊያስደስተኝ ነው? 3 ባለፈው ጊዜ የጻፍኩላችሁ በምመጣበት ጊዜ ልደሰትባቸው በሚገባ ሰዎች እንዳላዝን ነው፤ ምክንያቱም የእኔ ደስታ የእናንተ የሁላችሁም ደስታ እንደሚሆን እተማመናለሁ። 4 ልቤ በብዙ መከራና ጭንቀት ተውጦ በብዙ እንባ የጻፍኩላችሁ እንድታዝኑ ሳይሆን+ ለእናንተ ያለኝን ጥልቅ ፍቅር እንድታውቁ ነው።
5 ለሐዘን የሚዳርግ ነገር ያደረገ ማንም ቢኖር+ ያሳዘነው እኔን ሳይሆን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ሁላችሁንም ነው፤ እንዲህ ያልኩት ግን ነገሩን ለማክበድ ብዬ አይደለም። 6 እንዲህ ዓይነቱ ሰው ከእናንተ አብዛኞቻችሁ የሰጣችሁት ተግሣጽ ይበቃዋል፤ 7 አሁን ይህ ሰው ከልክ በላይ በሐዘን እንዳይዋጥ+ በደግነት ይቅር ልትሉትና ልታጽናኑት ይገባል።+ 8 ስለዚህ ለእሱ ያላችሁን ፍቅር እንድታረጋግጡለት አሳስባችኋለሁ።+ 9 የጻፍኩላችሁም በሁሉም ነገር ታዛዥ መሆናችሁን ታሳዩ እንደሆነ ለማረጋገጥ ነው። 10 በደሉ ምንም ይሁን ምን እናንተ ይቅር ያላችሁትን ማንኛውንም ሰው እኔም ይቅር እለዋለሁ። እንዲያውም ሁሉንም ነገር በክርስቶስ ፊት ይቅር ያልኩት (ይቅር ያልኩት ነገር ካለ) ለእናንተ ስል ነው፤ 11 ይህም ሰይጣን መግቢያ ቀዳዳ እንዳያገኝ* ነው፤+ እሱ የሚሸርበውን ተንኮል* እናውቃለንና።+
12 ስለ ክርስቶስ የሚገልጸውን ምሥራች ለማወጅ ጥሮአስ+ በደረስኩ ጊዜ የጌታን ሥራ ለማከናወን በር ተከፍቶልኝ ነበር፤ 13 ይሁንና ወንድሜን ቲቶን+ ስላላገኘሁት መንፈሴ ተረብሾ ነበር። በመሆኑም በዚያ ያሉትን ተሰናብቼ ወደ መቄዶንያ+ ሄድኩ።
14 በድል ሰልፍ ከክርስቶስ ጋር አብረን እንድንጓዝ በማድረግ ዘወትር ለሚመራንና የእውቀቱ መዓዛ በእኛ አማካኝነት በሁሉም ቦታ እንዲናኝ ለሚያደርገው አምላክ ምስጋና ይድረሰው! 15 እኛ ወደ መዳን በሚወስደው ጎዳና ላይ ባሉት መካከልና ወደ ጥፋት እያመሩ ባሉት መካከል ለአምላክ የክርስቶስ መዓዛ ነንና፤ 16 ወደ ጥፋት እያመሩ ላሉት ለሞት የሚዳርግ የሞት ሽታ፣*+ ወደ መዳን በሚወስደው ጎዳና ላይ ላሉት ደግሞ ወደ ሕይወት የሚመራ የሕይወት መዓዛ ነን። እንዲህ ላለው አገልግሎት ብቃት ያለው ማን ነው? 17 እኛ ነን፤ ምክንያቱም እኛ እንደ ብዙዎቹ ሰዎች የአምላክን ቃል አንሸቃቅጥም፤*+ ከዚህ ይልቅ በአምላክ የተላክን እንደመሆናችን መጠን በቅንነት እንናገራለን፤ ይህን የምናደርገው በአምላክ ፊት ሆነን እንዲሁም ከክርስቶስ ጋር በመተባበር ነው።
3 ብቁ መሆናችንን ለማሳየት ራሳችንን ለእናንተ እንደ አዲስ ማስተዋወቅ ያስፈልገናል? ወይስ እንደ አንዳንድ ሰዎች ለእናንተ ወይም ከእናንተ የምሥክር ወረቀት ያስፈልገን ይሆን? 2 ሰዎች ሁሉ የሚያውቁትና የሚያነብቡት በልባችን ላይ የተጻፈ ማስረጃችን እናንተ ራሳችሁ ናችሁ።+ 3 ምክንያቱም እናንተ በቀለም ሳይሆን በሕያው አምላክ መንፈስ፣ በድንጋይ ጽላቶች+ ላይ ሳይሆን በሥጋ ጽላቶች ይኸውም በልብ ላይ፣+ አገልጋዮች+ በሆንነው በእኛ አማካኝነት የተጻፋችሁ የክርስቶስ ደብዳቤ እንደሆናችሁ በግልጽ ታይቷል።
4 በክርስቶስ በኩል በአምላክ ፊት እንዲህ ያለ እምነት አለን። 5 ብቃታችንን በገዛ ራሳችን ያገኘነው እንደሆነ አድርገን አናስብም፤ ከዚህ ይልቅ አስፈላጊውን ብቃት ያገኘነው ከአምላክ ነው፤+ 6 እሱም የአዲስ ቃል ኪዳን+ አገልጋዮች ይኸውም የተጻፈ ሕግ+ ሳይሆን የመንፈስ አገልጋዮች እንድንሆን ብቁዎች አድርጎናል፤ የተጻፈው ሕግ ለሞት ፍርድ ይዳርጋልና፤+ መንፈስ ግን ሕያው ያደርጋል።+
7 የእስራኤል ልጆች፣ ከፊቱ ክብር የተነሳ የሙሴን ፊት ትኩር ብለው ማየት እስኪሳናቸው ድረስ+ የሞት ፍርድ የሚያስከትለውና በድንጋይ ላይ በፊደል የተቀረጸው ሕግ+ በክብር ይኸውም በሚጠፋ ክብር ከመጣ 8 የመንፈስ አገልግሎት+ እንዴት የላቀ ክብር አይኖረውም?+ 9 ኩነኔ የሚያስከትለው የሕግ አገልግሎት+ ክብራማ+ ከሆነ ጽድቅ የሚያስገኘው አገልግሎትማ እንዴት እጅግ የላቀ ክብር አይኖረውም!+ 10 እንዲያውም በአንድ ወቅት ክብራማ የነበረው፣ ከእሱ የላቀ ክብር ያለው በመምጣቱ ምክንያት ክብሩ ተገፏል።+ 11 የሚጠፋው በክብር ከመጣ+ ጸንቶ የሚኖረውማ እንዴት የላቀ ክብር አይኖረውም!+
12 እንዲህ ዓይነት ተስፋ ስላለን+ ታላቅ የመናገር ነፃነት አለን፤ 13 ደግሞም የእስራኤል ልጆች የዚያን የሚሻረውን ነገር መጨረሻ እንዳይመለከቱ ሙሴ ፊቱን በመሸፈኛ ይሸፍን+ በነበረበት ጊዜ ያደርግ እንደነበረው አናደርግም። 14 ሆኖም እነሱ አእምሯቸው ደንዝዟል።+ እስከ ዛሬ ድረስ፣ አሮጌው ቃል ኪዳን ሲነበብ ያው መሸፈኛ እንደጋረዳቸው ነውና፤+ ምክንያቱም መሸፈኛው የሚወገደው በክርስቶስ አማካኝነት ብቻ ነው።+ 15 እንዲያውም እስከ ዛሬ ድረስ የሙሴ መጻሕፍት በተነበቡ ቁጥር+ ልባቸው በመሸፈኛ እንደተሸፈነ ነው።+ 16 ሆኖም አንድ ሰው ወደ ይሖዋ* ሲመለስ መሸፈኛው ይወገዳል።+ 17 ይሖዋ* መንፈስ ነው፤+ የይሖዋ* መንፈስ ባለበት ደግሞ ነፃነት አለ።+ 18 እኛ ሁላችንም ባልተሸፈነ ፊት የይሖዋን* ክብር እንደ መስተዋት ስናንጸባርቅ ያንኑ መልክ ለመምሰል ከክብር ወደ ክብር* እንለወጣለን፤ በዚህ መንገድ መንፈስ የሆነው ይሖዋ* ራሱ* እንደሚያደርገን እንሆናለን።+
4 ስለዚህ በተደረገልን ምሕረት የተነሳ ይህ አገልግሎት ስላለን ተስፋ አንቆርጥም። 2 ከዚህ ይልቅ አሳፋሪ የሆኑትን ስውር ነገሮች ትተናል፤ በተንኮል አንመላለስም፤ የአምላክንም ቃል አንበርዝም፤+ ነገር ግን እውነትን በመግለጥ በአምላክ ፊት የሰውን ሁሉ ሕሊና በሚማርክ መንገድ ራሳችንን ብቁ አድርገን እናቀርባለን።+ 3 እንግዲህ የምናውጀው ምሥራች በእርግጥ የተሸፈነ ከሆነ የተሸፈነው ወደ ጥፋት እያመሩ ላሉት ነው፤ 4 የአምላክ አምሳል ስለሆነው ስለ ክርስቶስ+ የሚገልጸውና ክብራማ የሆነው ምሥራች የሚፈነጥቀው ብርሃን በእነሱ ላይ እንዳያበራ+ የዚህ ሥርዓት* አምላክ+ የማያምኑትን ሰዎች አእምሮ አሳውሯል።+ 5 እኛ የምንሰብከው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ መሆኑንና እኛም ስለ ኢየሱስ ስንል የእናንተ ባሪያዎች መሆናችንን እንጂ ስለ ራሳችን አይደለምና። 6 “በጨለማ ውስጥ ብርሃን ይብራ” ያለው አምላክ ነውና፤+ ስለሆነም በክርስቶስ ፊት አማካኝነት፣ በልባችን ውስጥ ስለ አምላክ አስደናቂ እውቀት ይፈነጥቅ ዘንድ በልባችን ላይ ብርሃን አብርቷል።+
7 ይሁን እንጂ ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነው ኃይል ከእኛ ሳይሆን ከአምላክ የመነጨ መሆኑ ይታወቅ ዘንድ+ ይህ ውድ ሀብት+ በሸክላ ዕቃ+ ውስጥ አለን። 8 በየአቅጣጫው ብንደቆስም መፈናፈኛ አናጣም፤ ግራ ብንጋባም መውጫ ቀዳዳ አናጣም፤*+ 9 ስደት ቢደርስብንም አልተተውንም፤+ በጭንቀት ብንዋጥም* አንጠፋም።+ 10 የኢየሱስ ሕይወት በእኛም ሰውነት እንዲገለጥ በኢየሱስ ላይ የደረሰውን ለሞት ሊዳርግ የሚችል መከራ ዘወትር በሰውነታችን እንሸከማለን።+ 11 የኢየሱስ ሕይወት ሟች በሆነው ሥጋችንም ይገለጥ ዘንድ እኛ ሕያዋን የሆን ለኢየሱስ ስንል ዘወትር ከሞት ጋር እንፋጠጣለንና።+ 12 ስለሆነም በእኛ ላይ ሞት፣ በእናንተ ላይ ግን ሕይወት እየሠራ ነው።
13 “አመንኩ፤ ስለዚህም ተናገርኩ” ተብሎ ተጽፏል።+ እኛም እንዲህ ዓይነት የእምነት መንፈስ ስላለን እናምናለን፤ ስለዚህም እንናገራለን፤ 14 ኢየሱስን ያስነሳው እሱ፣ እኛንም ከኢየሱስ ጋር እንደሚያስነሳንና ከእናንተ ጋር አንድ ላይ በፊቱ እንደሚያቀርበን እናውቃለን።+ 15 ይህ ሁሉ የሆነው ለእናንተ ሲባል ነውና፤ ይኸውም ብዙ ሰዎች ለአምላክ ክብር ምስጋና እያቀረቡ ስለሆነ የተትረፈረፈው ጸጋ ይበልጥ እንዲበዛ ነው።+
16 ስለዚህ ተስፋ አንቆርጥም፤ ምንም እንኳ ውጫዊው ሰውነታችን እየመነመነ ቢሄድም ውስጣዊው ሰውነታችን ከቀን ወደ ቀን እየታደሰ እንደሚሄድ ምንም ጥርጥር የለውም። 17 የሚደርስብን መከራ* ጊዜያዊና ቀላል ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄድና ዘላለማዊ የሆነ ክብር ያስገኝልናል፤+ 18 ስለዚህ ዓይናችን እንዲያተኩር የምናደርገው በሚታዩት ነገሮች ላይ ሳይሆን በማይታዩት ነገሮች ላይ ነው።+ የሚታዩት ጊዜያዊ ናቸውና፤ የማይታዩት ግን ዘላለማዊ ናቸው።
5 ምድራዊ ቤታችን* የሆነው ይህ ድንኳን ቢፈርስ+ በሰው እጅ የተሠራ ቤት ሳይሆን በሰማይ ዘላለማዊ የሆነ ሕንፃ ከአምላክ እንደምናገኝ እናውቃለን።+ 2 ከሰማይ የሆነውን መኖሪያችንን ለመልበስ እየናፈቅን በዚህ ቤት* ውስጥ ሆነን እንቃትታለን፤+ 3 ስለዚህ ይህን ስንለብስ ራቁታችንን ሆነን አንገኝም። 4 እንዲያውም በዚህ ድንኳን ውስጥ ያለነው እኛ ከባድ ሸክም ተጭኖን እንቃትታለን፤ ምክንያቱም ዘላለማዊው ሕይወት ሟች የሆነውን አካል እንዲተካ+ ይህን ድንኳን ማውለቅ ሳይሆን ሰማያዊውን መኖሪያ መልበስ እንፈልጋለን።+ 5 ለዚህ ነገር ያዘጋጀን አምላክ ነው፤+ ለሚመጣው ነገር ማረጋገጫ* አድርጎ መንፈሱን የሰጠን እሱ ነው።+
6 በመሆኑም ስለዚህ ጉዳይ ምንጊዜም እርግጠኞች ነን፤ በተጨማሪም መኖሪያችን በሆነው በዚህ አካል እስካለን ድረስ ከጌታ ጋር አብረን እንዳልሆን እናውቃለን፤+ 7 የምንመላለሰው በእምነት እንጂ በማየት አይደለምና። 8 ሆኖም እኛ እርግጠኞች ነን፤ ደግሞም ከዚህ አካል ተለይተን መኖሪያችንን ከጌታ ጋር ብናደርግ እንመርጣለን።+ 9 ስለዚህ ከእሱ ጋር አብረን ብንኖርም ሆነ ባንኖር ዓላማችን በእሱ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት ነው። 10 ምክንያቱም እያንዳንዱ በሥጋ እያለ ላደረገው ጥሩም ሆነ መጥፎ ነገር፣ እንደ ሥራው ብድራት እንዲቀበል ሁላችንም በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት ልንቀርብ* ይገባል።+
11 እንግዲህ ጌታን መፍራት እንደሚገባን ስለምናውቅ ሰዎች የምንናገረውን እንዲቀበሉ ለማሳመን ምንጊዜም እንጥራለን፤ ሆኖም አምላክ በሚገባ ያውቀናል።* የእናንተም ሕሊና እኛን በሚገባ እንድታውቁ እንደረዳችሁ ተስፋ አደርጋለሁ። 12 እኛ ብቃታችንን ለእናንተ እንደ አዲስ ማቅረባችን አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ በልብ ውስጥ ባለው ነገር ሳይሆን በውጫዊ መልክ ለሚኩራሩ+ መልስ መስጠት ትችሉ ዘንድ በእኛ እንድትኮሩ እያነሳሳናችሁ ነው። 13 አእምሯችንን ብንስት+ ለአምላክ ብለን ነውና፤ ጤናማ አእምሮ ቢኖረን ደግሞ ለእናንተ ብለን ነው። 14 አንድ ሰው ለሁሉም መሞቱን+ ስለተረዳን ክርስቶስ ያለው ፍቅር ግድ ይለናልና፤ ምክንያቱም ሁሉም ቀድሞውኑ ሞተዋል። 15 በሕይወት ያሉትም ከእንግዲህ ለራሳቸው ከመኖር ይልቅ ለእነሱ ለሞተውና ለተነሳው እንዲኖሩ እሱ ለሁሉም ሞቷል።+
16 ስለዚህ እኛ ከአሁን ጀምሮ ሰዎችን የምናውቀው ከሥጋዊ አመለካከት አንጻር አይደለም።*+ ክርስቶስን በሥጋዊ ሁኔታ እናውቀው የነበረ ቢሆንም ከዚህ በኋላ በዚህ መንገድ አናውቀውም።+ 17 በመሆኑም ማንም ከክርስቶስ ጋር አንድነት ካለው አዲስ ፍጥረት ነው፤+ አሮጌዎቹ ነገሮች አልፈዋል፤ እነሆ፣ አዳዲስ ነገሮች ወደ ሕልውና መጥተዋል! 18 ሆኖም ሁሉም ነገሮች የተገኙት በክርስቶስ አማካኝነት ከራሱ ጋር ካስታረቀንና+ የማስታረቅ አገልግሎት ከሰጠን አምላክ ነው።+ 19 ይህም፣ አምላክ በክርስቶስ አማካኝነት ዓለምን ከራሱ ጋር ከማስታረቁም በላይ+ በደላቸውን አልቆጠረባቸውም ማለት ነው፤+ ለእኛ ደግሞ የእርቁን መልእክት በአደራ ሰጥቶናል።+
20 ስለዚህ እኛ ክርስቶስን ተክተን+ የምንሠራ አምባሳደሮች ነን፤+ አምላክ በእኛ አማካኝነት እየተማጸነ ያለ ያህል ነው። ክርስቶስን ተክተን የምንሠራ እንደመሆናችን መጠን “ከአምላክ ጋር ታረቁ” ብለን እንለምናለን። 21 እኛ በእሱ አማካኝነት በአምላክ ፊት ጻድቅ እንድንሆን+ ኃጢአት የማያውቀው+ እሱ ለእኛ የኃጢአት መባ ተደረገ።
6 ደግሞም ከእሱ ጋር አብረን የምንሠራ+ እንደመሆናችን መጠን የአምላክን ጸጋ ከተቀበላችሁ በኋላ ዓላማውን እንዳትስቱ እናሳስባችኋለን።+ 2 እሱ “ሞገስ በማሳይበት ጊዜ ሰምቼሃለሁ፤ በመዳንም ቀን ረድቼሃለሁ” ይላልና።+ እነሆ፣ አምላክ ሞገስ የሚያሳይበት ልዩ ጊዜ አሁን ነው። እነሆ፣ የመዳን ቀን አሁን ነው።
3 አገልግሎታችን እንከን እንዳይገኝበት በምንም መንገድ ማሰናከያ እንዲኖር አናደርግም፤+ 4 ከዚህ ይልቅ በሁሉም ነገር ራሳችንን ብቁ የአምላክ አገልጋዮች አድርገን እናቀርባለን፤+ ይህን የምናደርገው በብዙ ነገር በመጽናት፣ በመከራ፣ በእጦት፣ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች፣+ 5 በድብደባ፣ በእስር፣+ በሁከት፣ በከባድ ሥራ፣ እንቅልፍ አጥቶ በማደርና ጾም በመዋል ነው።+ 6 የአምላክ አገልጋዮች መሆናችንን በንጽሕና፣ በእውቀት፣ በትዕግሥት፣+ በደግነት፣+ በመንፈስ ቅዱስ፣ ግብዝነት በሌለው ፍቅር፣+ 7 እውነት የሆነውን በመናገርና በአምላክ ኃይል እናሳያለን።+ እንዲሁም በቀኝ እጅና* በግራ እጅ* የጽድቅ መሣሪያዎችን በመያዝ፣+ 8 ክብርንም ሆነ ውርደትን እንዲሁም ነቀፋንም ሆነ ምስጋናን በመቀበል የአምላክ አገልጋዮች መሆናችንን እናስመሠክራለን። እውነተኞች ሆነን ሳለን እንደ አታላዮች ተቆጥረናል፤ 9 በሚገባ የታወቅን ሆነን ሳለን እንደማንታወቅ ተቆጥረናል፤ የምንሞት ስንመስል* እነሆ፣ ሕያዋን ነን፤+ ብንቀጣም ለሞት አልተዳረግንም፤+ 10 ሐዘንተኞች ተደርገን ብንታይም ምንጊዜም ደስተኞች ነን፤ እንደ ድሆች ብንቆጠርም ብዙዎችን ባለጸጋ እያደረግን ነው፤ ምንም የሌለን ብንመስልም ሁሉ ነገር አለን።+
11 የቆሮንቶስ ወንድሞች ሆይ፣ በግልጽ ነግረናችኋል፤ ልባችንም ወለል ብሎ ተከፍቶላችኋል። 12 እኛ ፍቅራችንን አልነፈግናችሁም፤+ እናንተ ግን ጥልቅ ፍቅራችሁን ነፍጋችሁናል። 13 ስለዚህ ልጆቼን እንደማናግር ሆኜ አናግራችኋለሁ፤ እናንተም በአጸፋው ልባችሁን ወለል አድርጋችሁ ክፈቱ።+
14 ከማያምኑ ጋር አቻ ባልሆነ መንገድ አትጠመዱ።*+ ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ኅብረት አለው?+ ወይስ ብርሃን ከጨለማ ጋር ምን ያገናኘዋል?+ 15 በተጨማሪም በክርስቶስና በቤልሆር* መካከል ምን ስምምነት አለ?+ ወይስ የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ድርሻ አለው?+ 16 እንዲሁም የአምላክ ቤተ መቅደስ ከጣዖቶች ጋር ምን ስምምነት አለው?+ እኛ የሕያው አምላክ ቤተ መቅደስ ነንና፤+ አምላክ “በመካከላቸው እኖራለሁ፤+ ከእነሱም ጋር እሄዳለሁ፤ እኔ አምላካቸው እሆናለሁ፣ እነሱ ደግሞ ሕዝቤ ይሆናሉ” ብሎ እንደተናገረው ነው።+ 17 “‘ስለዚህ ከመካከላቸው ውጡና ራሳችሁን ለዩ’ ይላል ይሖዋ፤* ‘ርኩስ የሆነውንም ነገር አትንኩ’”፤*+ “‘እኔም እቀበላችኋለሁ።’”+ 18 “‘እኔ አባት እሆናችኋለሁ፤+ እናንተ ደግሞ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ትሆኑኛላችሁ’+ ይላል ሁሉን ቻይ የሆነው ይሖዋ።”*
7 ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ እነዚህ ተስፋዎች ስላሉን+ ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳችንን እናንጻ፤+ እንዲሁም አምላክን በመፍራት ቅድስናችንን ፍጹም እናድርግ።
2 በልባችሁ ውስጥ ቦታ ስጡን።+ እኛ ማንንም አልበደልንም፤ ማንንም አላበላሸንም፤ ማንንም መጠቀሚያ አላደረግንም።+ 3 ይህን የምለው ልኮንናችሁ አይደለም። ከዚህ በፊት እንደነገርኳችሁ በልባችን ውስጥ ስለሆናችሁ ብንሞትም ሆነ ብንኖር አብረን ነን። 4 እናንተን በግልጽ ለማናገር ነፃነት ይሰማኛል። በእናንተ በጣም እኮራለሁ። እንዲሁም እጅግ ተጽናንቻለሁ፤ በመከራችንም ሁሉ ደስታዬ ወሰን የለውም።+
5 መቄዶንያ+ በደረስን ጊዜ በሁሉም አቅጣጫ መከራ ደረሰብን እንጂ ሰውነታችን* ምንም እረፍት አላገኘም፤ በውጭ ጠብ፣ በውስጥ ፍርሃት ነበረብን። 6 ይሁንና ያዘኑትን የሚያጽናናው አምላክ፣+ ቲቶ በመካከላችን በመገኘቱ እንድንጽናና አደረገን፤ 7 የተጽናናነውም እሱ በመካከላችን በመገኘቱ ብቻ ሳይሆን እሱ በእናንተ ምክንያት ባገኘው መጽናኛ ጭምር ነው፤ ተመልሶ በመጣ ጊዜ እኔን ስለመናፈቃችሁ፣ ስለተሰማችሁ ጥልቅ ሐዘንና ለእኔ ስላላችሁ ልባዊ አሳቢነት* ነግሮናል፤ ስለዚህ ከበፊቱ ይበልጥ ደስ ብሎኛል።
8 በደብዳቤዬ አሳዝኛችሁ ቢሆን እንኳ+ በዚህ አልጸጸትም። መጀመሪያ ላይ ብጸጸት እንኳ፣ ደብዳቤው እንድታዝኑ ያደረጋችሁ ለአጭር ጊዜ ብቻ እንደሆነ ስለተረዳሁ 9 አሁን የምደሰተው እንዲያው በማዘናችሁ ሳይሆን ሐዘናችሁ ለንስሐ ስላበቃችሁ ነው። ያዘናችሁት ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ ነውና፤ በመሆኑም በእኛ የተነሳ ምንም ጉዳት አልደረሰባችሁም። 10 ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ ማዘን ለመዳን የሚያበቃ ንስሐ ያስገኛልና፤ ይህ ደግሞ ለጸጸት አይዳርግም፤+ የዚህ ዓለም ሐዘን ግን ሞት ያስከትላል። 11 አምላካዊ በሆነ መንገድ ማዘናችሁ እንዴት ለተግባር እንዳነሳሳችሁ ተመልከቱ! አዎ፣ አቋማችሁን ለማስተካከል እርምጃ እንድትወስዱ አነሳስቷችኋል፤ ደግሞም እንዴት ያለ ቁጣ፣ እንዴት ያለ ፍርሃት፣ እንዴት ያለ ጉጉት፣ እንዴት ያለ ቅንዓት እንዳስገኘ ተመልከቱ! በእርግጥም ስህተታችሁን ለማረም እርምጃ እንድትወስዱ አድርጓችኋል።+ በዚህ ጉዳይ ንጹሕ* መሆናችሁን በሁሉም ረገድ አስመሥክራችኋል። 12 ምንም እንኳ ለእናንተ ብጽፍም የጻፍኩት በደል ለሠራው+ ወይም በደል ለተፈጸመበት ሰው ብዬ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ለመልእክታችን በጎ ምላሽ ለመስጠት የምታደርጉት ጥረት በእናንተ ዘንድና በአምላክ ፊት ግልጽ ሆኖ እንዲታይ ነው። 13 እኛም የተጽናናነው ለዚህ ነው።
ይሁን እንጂ ከመጽናናታችንም በተጨማሪ ሁላችሁም የቲቶ መንፈስ እንዲታደስ ስላደረጋችሁ በእሱ ደስታ እኛም ይበልጥ ተደስተናል። 14 ምክንያቱም ስለ እናንተ ለእሱ በኩራት ተናግሬ ቢሆን እንኳ አላሳፈራችሁኝም፤ ይሁንና ለእናንተ የተናገርነው ነገር በሙሉ እውነት እንደሆነ ሁሉ ለቲቶ በኩራት የተናገርነውም ነገር እውነት እንደሆነ ተረጋግጧል። 15 በተጨማሪም ሁላችሁም ያሳያችሁትን ታዛዥነት እንዲሁም በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ እንዴት እንደተቀበላችሁት ሲያስታውስ ለእናንተ ያለው ጥልቅ ፍቅር ጨምሯል።+ 16 እኔም በሁሉም መንገድ በእናንተ መተማመን* በመቻሌ እጅግ ደስ ብሎኛል።
8 ወንድሞች፣ በመቄዶንያ+ ላሉት ጉባኤዎች ስለተሰጠው የአምላክ ጸጋ እንድታውቁ እንፈልጋለን። 2 ከባድ ፈተና ደርሶባቸው በመከራ ውስጥ በነበሩበት ጊዜ ታላቅ ደስታ የነበራቸው ከመሆኑም በላይ ከፍተኛ* ልግስና አሳይተዋል፤ ይህን ያደረጉት በጣም ድሆች ሆነው ሳለ ነው። 3 እንደ አቅማቸው+ እንዲያውም ከአቅማቸው በላይ እንደሰጡ እመሠክርላቸዋለሁና፤+ 4 ምክንያቱም እነዚህ ወንድሞች ለቅዱሳን በልግስና በመስጠት፣ በእርዳታ አገልግሎቱ ለመካፈል መብት እንዲሰጣቸው በራሳቸው ፍላጎት ተነሳስተው ይለምኑን እንዲያውም ይማጸኑን ነበር።+ 5 ደግሞም ከጠበቅነው በላይ አድርገዋል፤ ምክንያቱም ራሳቸውን በመጀመሪያ ለጌታ ከዚያም በአምላክ ፈቃድ ለእኛ ሰጥተዋል። 6 ስለዚህ ቲቶ+ ቀደም ሲል በእናንተ መካከል የልግስና ስጦታችሁን የማሰባሰቡን ሥራ እንዳስጀመረ ሁሉ ይህንኑ ሥራ ወደ ፍጻሜ እንዲያደርስ አበረታታነው። 7 ስለዚህ በሁሉም ነገር ይኸውም በእምነት፣ በቃል፣ በእውቀት፣ በትጋት ሁሉና እኛ ለእናንተ ባለን ፍቅር ባለጸጋ እንደሆናችሁ ሁሉ በልግስና በመስጠት ረገድም ባለጸጋ ሁኑ።+
8 ይህን የምላችሁ እናንተን ለማዘዝ ሳይሆን ሌሎች የሚያሳዩትን ትጋት እንድታውቁ ለማድረግና የፍቅራችሁን እውነተኝነት ለመፈተን ነው። 9 የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ጸጋ ታውቃላችሁና፤ በእሱ ድህነት እናንተ ባለጸጋ ትሆኑ ዘንድ እሱ ባለጸጋ ሆኖ ሳለ ለእናንተ ሲል ድሃ ሆኗል።+
10 በዚህ ረገድ የምሰጠው ሐሳብ አለ፦+ ይህን ሥራ መሥራታችሁ ይጠቅማችኋል፤ ምክንያቱም ከአንድ ዓመት በፊት ሥራውን መጀመር ብቻ ሳይሆን ዳር ለማድረስም ፍላጎት እንዳላችሁ አሳይታችኋል። 11 ስለዚህ የጀመራችሁትን ሥራ ዳር አድርሱት፤ ሥራውን ለመጀመር ጓጉታችሁ እንደነበር ሁሉ፣ አሁንም እንደ አቅማችሁ በመስጠት ከፍጻሜ እንዲደርስ አድርጉ። 12 ለመስጠት ፈቃደኝነቱ ካለ ስጦታው ይበልጥ ተቀባይነት የሚኖረው አንድ ሰው ባለው መጠን ሲሰጥ+ እንጂ በሌለው መጠን ሲሰጥ አይደለምና። 13 ይህን የምለውም ሌሎች እንዲቀላቸው አድርጌ እናንተ እንዲከብዳችሁ ለማድረግ አይደለም፤ 14 ከዚህ ይልቅ በአሁኑ ጊዜ የእናንተ ትርፍ የእነሱን ጉድለት እንዲሸፍን ነው፤ የእነሱ ትርፍ ደግሞ የእናንተን ጉድለት ይሸፍናል፤ ይህም ሸክሙን እኩል እንድትጋሩ ያስችላል። 15 ይህ ደግሞ “ብዙ የሰበሰበ ብዙ አላተረፈም፤ ጥቂት የሰበሰበም ምንም አልጎደለበትም” ተብሎ እንደተጻፈው ነው።+
16 እኛ ለእናንተ ያለንን ዓይነት ልባዊ አሳቢነት በቲቶ+ ልብ ውስጥ ያሳደረ አምላክ የተመሰገነ ይሁን፤ 17 ምክንያቱም ቲቶ ወደ እናንተ የሚመጣው የእኛን ማበረታቻ በመቀበል ብቻ ሳይሆን በታላቅ ጉጉት፣ በራሱ ፈቃድ ተነሳስቶ ነው። 18 ይሁንና ከምሥራቹ ጋር በተያያዘ እያከናወነ ባለው ሥራ በጉባኤዎች ሁሉ የተመሰገነውን ወንድም ከእሱ ጋር እንልከዋለን። 19 ከዚህም በላይ ጌታን ለማስከበርና ሌሎችን ለመርዳት ዝግጁ መሆናችንን ለማሳየት ይህን የልግስና ስጦታ በምናከፋፍልበት ጊዜ ይህ ወንድም የጉዞ አጋራችን እንዲሆን በጉባኤዎች ተሹሟል። 20 ስለዚህ እኛ ከምናከፋፍለው የልግስና መዋጯችሁ ጋር በተያያዘ ማንም ሰው ምንም ዓይነት ስህተት እንዳያገኝብን እንጠነቀቃለን።+ 21 ምክንያቱም ‘በይሖዋ* ፊት ብቻ ሳይሆን በሰዎችም ፊት ሁሉንም ነገር በሐቀኝነት እናከናውናለን።’+
22 በተጨማሪም በተደጋጋሚ ጊዜ በብዙ ነገር ተፈትኖ ትጉ ሆኖ ያገኘነውን ወንድማችንን ከእነሱ ጋር እንልከዋለን፤ እንዲያውም አሁን በእናንተ ላይ ባለው ጠንካራ እምነት የተነሳ ትጋቱ እጅግ ጨምሯል። 23 ይሁን እንጂ ቲቶን በተመለከተ ጥያቄ የሚያነሳ ካለ እሱ ለእናንተ ጥቅም አብሮኝ የሚሠራ ባልደረባዬ ነው፤ ወይም ደግሞ ስለ ወንድሞቻችን ጥያቄ ካለ እነሱ የጉባኤዎች ሐዋርያትና የክርስቶስ ክብር ናቸው። 24 ስለሆነም ለእነሱ ያላችሁን ፍቅር እውነተኝነት በተጨባጭ አስመሥክሩ፤+ እንዲሁም በእናንተ የምንኮራው ለምን እንደሆነ ለጉባኤዎቹ አሳዩ።
9 ለቅዱሳን የሚደረገውን አገልግሎት* በተመለከተ+ ልጽፍላችሁ አያስፈልግም፤ 2 እርዳታ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆናችሁን አውቃለሁና፤ በመሆኑም “የአካይያ ወንድሞች ሌሎችን ለመርዳት ለአንድ ዓመት ያህል ዝግጁ ሆነው ሲጠባበቁ ቆይተዋል” ብዬ ለመቄዶንያ ወንድሞች በኩራት ተናግሬአለሁ፤ የእናንተ ቅንዓት ደግሞ አብዛኞቹን አነሳስቷል። 3 ይሁንና በዚህ ረገድ በእናንተ ላይ ያለን ትምክህት ከንቱ ሆኖ እንዳይቀር አስቀድሞ ስለ እናንተ እንደተናገርኩት ተዘጋጅታችሁ እንድትጠብቁ ወንድሞችን እልካለሁ። 4 አለዚያ የመቄዶንያ ወንድሞች ከእኔ ጋር መጥተው ዝግጁ ሳትሆኑ ቢያገኟችሁ፣ እናንተ ብቻ ሳትሆኑ እኛም በእናንተ በመተማመናችን እናፍራለን። 5 ስለዚህ ቀደም ሲል ልትሰጡ ቃል የገባችሁትን የልግስና ስጦታ አስቀድመው ያዘጋጁ ዘንድ ወንድሞች ቀደም ብለው ወደ እናንተ እንዲመጡ ማበረታታት አስፈላጊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። እንዲህ ከሆነ ስጦታው ተዘጋጅቶ ይጠብቀናል፤ ይህ ደግሞ ስጦታ የሰጣችሁት አስገድደናችሁ ሳይሆን በልግስና እንደሆነ ያሳያል።
6 ይሁንና ጥቂት የሚዘራ ሁሉ ጥቂት ያጭዳል፤ በብዛት የሚዘራ ሁሉ ደግሞ በብዛት ያጭዳል።+ 7 አምላክ በደስታ የሚሰጠውን ሰው ስለሚወድ+ እያንዳንዱ ሰው ቅር እያለው* ወይም ተገዶ ሳይሆን በልቡ ያሰበውን ይስጥ።+
8 በተጨማሪም ምንጊዜም የሚያስፈልጋችሁ ነገር በበቂ ሁኔታ እንዲኖራችሁ እንዲሁም መልካም ሥራን ሁሉ ለመሥራት የሚያስችላችሁን ነገር በብዛት እንድታገኙ አምላክ ጸጋውን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል።+ 9 (ይህም “በብዛት* አከፋፈለ፤ ለድሆችም ሰጠ። ጽድቁ ለዘላለም ይኖራል” ተብሎ እንደተጻፈው ነው።+ 10 እንግዲህ ለዘሪ ዘርን፣ ለመብል እህልን አትረፍርፎ የሚሰጠው እሱ የምትዘሩትን ዘር አትረፍርፎ ይሰጣችኋል፤ እንዲሁም የጽድቃችሁን ፍሬ ያበዛላችኋል።) 11 በሁሉም መንገድ በልግስና መስጠት እንድትችሉ አምላክ አትረፍርፎ ይባርካችኋል፤ እኛ በምናከናውነው ሥራ የተነሳ እንዲህ ያለው ልግስና ሰዎች ለአምላክ ምስጋና እንዲያቀርቡ ያነሳሳቸዋል፤ 12 ምክንያቱም ይህ የምታከናውኑት ሕዝባዊ አገልግሎት* ቅዱሳን የሚያስፈልጓቸው ነገሮች በሚገባ እንዲሟሉላቸው+ ከማድረጉም በተጨማሪ በርካታ ሰዎች ለአምላክ ብዙ ምስጋና እንዲያቀርቡ ያደርጋል። 13 በዚህ የእርዳታ አገልግሎት አማካኝነት የሚያዩት ማስረጃ አምላክን እንዲያከብሩ ያደርጋቸዋል፤ ምክንያቱም እናንተ በይፋ ለምታውጁት ስለ ክርስቶስ ለሚገልጸው ምሥራች ተገዢዎች ናችሁ፤ እንዲሁም ለእነሱም ሆነ ለሁሉም በምታደርጉት መዋጮ ለጋሶች ናችሁ።+ 14 ደግሞም አምላክ ከሰጣችሁ የላቀ ጸጋ የተነሳ ስለ እናንተ ምልጃ እያቀረቡ ለእናንተ ያላቸውን ፍቅር ይገልጻሉ።
15 በቃላት ሊገለጽ ለማይችለው ነፃ ስጦታው አምላክ የተመሰገነ ይሁን።
10 በመካከላችሁ ሆኜ ፊት ለፊት ስታይ እንደ ደካማ የምቆጠረውና+ ከእናንተ ስርቅ እንደ ደፋር የምታየው+ እኔ ጳውሎስ በክርስቶስ ገርነትና ደግነት+ እለምናችኋለሁ። 2 በመካከላችሁ በምገኝበት ጊዜ በሥጋዊ አስተሳሰብ እንደምንመላለስ አድርገው በሚቆጥሩን አንዳንድ ሰዎች ላይ በድፍረት ከባድ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስገድድ ሁኔታ እንደማይፈጠር ተስፋ አደርጋለሁ። 3 ምንም እንኳ በሥጋ የምንኖር ቢሆንም የምንዋጋው በሥጋዊ መንገድ አይደለም። 4 የምንዋጋባቸው የጦር መሣሪያዎቻችን ሥጋዊ አይደሉምና፤+ ይሁን እንጂ ምሽግን ለመደርመስ የሚያስችል መለኮታዊ ኃይል ያላቸው ናቸው።+ 5 ስለ አምላክ የሚገልጸውን እውቀት የሚጻረሩ የተሳሳቱ ሐሳቦችንና ይህን እውቀት የሚያግድን ማንኛውንም ከፍ ያለ ነገር እናፈርሳለን፤+ እንዲሁም ማንኛውንም ሐሳብ እየማረክን ለክርስቶስ እንዲታዘዝ እናደርጋለን፤ 6 ሙሉ በሙሉ ታዛዦች መሆናችሁን ካሳያችሁ በኋላ በማንኛውም መንገድ ታዛዥ በማይሆን ግለሰብ ላይ የቅጣት እርምጃ ለመውሰድ ተዘጋጅተናል።+
7 እናንተ የምትመለከቱት ውጫዊውን ነገር ብቻ ነው። ማንም ሰው የክርስቶስ ነኝ ብሎ በራሱ የሚተማመን ከሆነ እሱ የክርስቶስ እንደሆነ ሁሉ እኛም የክርስቶስ እንደሆን በድጋሚ ሊያጤን ይገባዋል። 8 ጌታ እናንተን ለማፍረስ ሳይሆን ለማነጽ በሰጠን ሥልጣን እጅግ ብኮራም እንኳ+ ለኀፍረት አልዳረግምና። 9 እናንተን በደብዳቤዎቼ ለማስፈራራት እየሞከርኩ ያለሁ ሆኖ እንዲሰማችሁ አልፈልግም። 10 አንዳንዶች “ደብዳቤዎቹ ከባድና ኃይለኛ ናቸው፤ በመካከላችን በአካል ሲገኝ ግን ደካማ ከመሆኑም በላይ ንግግሩ የተናቀ ነው” ይላሉና። 11 እንዲህ ያለው ሰው፣ በአካል ሳንኖር በደብዳቤዎቻችን የምንናገረው ቃልና በአካል ስንገኝ የምናደርገው ነገር ምንም ልዩነት እንደሌለው መገንዘብ ይገባዋል።+ 12 እኛ ራሳቸውን ብቁ አድርገው ከሚያቀርቡ ሰዎች ጋር ራሳችንን ለመመደብ ወይም ለማነጻጸር አንደፍርምና።+ ይሁንና እነሱ ራሳቸውን በራሳቸው ሲመዝኑና ራሳቸውን ከራሳቸው ጋር ሲያነጻጽሩ ማስተዋል እንደሌላቸው ያሳያሉ።+
13 እኛ ግን ከተሰጠን ወሰን ውጭ ባለው ነገር አንኩራራም፤ ከዚህ ይልቅ የምንኮራው አምላክ ለክቶ በሰጠን ክልል ውስጥ ባለው ነገር ብቻ ነው፤ ይህ ክልል ደግሞ እናንተንም ያጠቃልላል።+ 14 እናንተ ከክልላችን ውጭ ያላችሁ ይመስል እናንተ ጋር ለመድረስ ከክልላችን ውጭ መሄድ አላስፈለገንም፤ ስለ ክርስቶስ የሚገልጸውን ምሥራች በመጀመሪያ እናንተ እስካላችሁበት ድረስ ይዘን የመጣነው እኛ ነንና።+ 15 ከተመደበልን ወሰን ውጭ ሌላ ሰው በደከመበት ነገር እየተኩራራን አይደለም፤ ሆኖም እምነታችሁ እያደገ ሲሄድ በክልላችን ውስጥ ያከናወንነውን ሥራ በሚገባ እንደምትገነዘቡ ተስፋ እናደርጋለን። ይህም ይበልጥ እንድንሠራ ያደርገናል፤ 16 በመሆኑም በሌላው ሰው ክልል፣ አስቀድሞ በተሠራ ሥራ ከመኩራራት ይልቅ ከእናንተ ወዲያ ባሉት አገሮች ምሥራቹን እንሰብካለን። 17 “ሆኖም የሚኩራራ በይሖዋ* ይኩራራ።”+ 18 ተቀባይነት የሚያገኘው ራሱን ብቁ እንደሆነ አድርጎ የሚያቀርብ ሳይሆን+ ይሖዋ* ብቁ ነው የሚለው ሰው ነውና።+
11 በመጠኑ ምክንያታዊነት ቢጎድለኝ እንድትታገሡኝ እፈልጋለሁ። ደግሞም እየታገሣችሁኝ ነው! 2 በአምላክ ቅንዓት እቀናላችኋለሁና፤ እኔ ራሴ እንደ አንዲት ንጽሕት ድንግል ለክርስቶስ አቀርባችሁ ዘንድ ለአንድ ባል አጭቻችኋለሁ።+ 3 ሆኖም እባቡ ሔዋንን በተንኮሉ እንዳታለላት+ ሁሉ እናንተም አስተሳሰባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ልታሳዩ የሚገባውን ቅንነትና ንጽሕና በሆነ መንገድ እንዳታጡ እፈራለሁ።+ 4 አንድ ሰው መጥቶ እኛ የሰበክንላችሁን ሳይሆን ሌላ ኢየሱስ ቢሰብክላችሁ ወይም ከተቀበላችሁት መንፈስ የተለየ ዓይነት መንፈስ ቢያመጣ ወይም ከተቀበላችሁት ምሥራች የተለየ ሌላ ምሥራች ቢናገር+ እንዲህ ያለውን ሰው በቸልታ ታልፉታላችሁ ማለት ነው። 5 እኔ ከእናንተ የተራቀቁ ሐዋርያት በምንም ነገር የማንስ አይመስለኝም።+ 6 የተዋጣልኝ ተናጋሪ ባልሆን እንኳ+ እውቀት አይጎድለኝም፤ ይህን በሁሉም መንገድ እንዲሁም በሁሉም ነገር አሳይተናችኋል።
7 ወይስ እናንተ ከፍ እንድትሉ ራሴን ዝቅ አድርጌ የአምላክን ምሥራች ለእናንተ ያለዋጋ በደስታ መስበኬ እንደ ኃጢአት ተቆጥሮብኝ ይሆን?+ 8 እናንተን ለማገልገል ከሌሎች ጉባኤዎች ቁሳዊ እርዳታ በመቀበሌ እነሱን አራቁቻለሁ።+ 9 ከእናንተ ጋር ሳለሁ ተቸግሬ በነበረበት ጊዜ ከመቄዶንያ የመጡት ወንድሞች የጎደለኝን ነገር በሙሉ በሚገባ ስላሟሉልኝ ለማንም ሸክም አልሆንኩም።+ አዎ፣ እስካሁን ድረስ በእናንተ ላይ በምንም መንገድ ሸክም አልሆንኩም፤ ወደፊትም ሸክም አልሆንም።+ 10 የክርስቶስ እውነት በውስጤ እስካለ ድረስ በአካይያ ክልሎች ሁሉ በዚህ ነገር እንዳልኩራራ ምንም ነገር ሊያግደኝ አይችልም።+ 11 ይህን ያደረግኩት ለምንድን ነው? ስለማልወዳችሁ ነው? እንደምወዳችሁ አምላክ ያውቃል።
12 ይሁንና ከእኛ ጋር እኩል ለመሆን የሚፈልጉትና እኛም ሐዋርያት ነን ብለው የሚኩራሩት ሰዎች ለዚህ የሚሆን መሠረት* እንዳያገኙ አሁን እያደረግኩት ያለሁትን ወደፊትም አደርጋለሁ።+ 13 እንዲህ ያሉት ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት ለመምሰል ራሳቸውን የሚለውጡ ሐሰተኛ ሐዋርያትና አታላይ ሠራተኞች ናቸውና።+ 14 ይህም ምንም አያስደንቅም፤ ሰይጣን ራሱ የብርሃን መልአክ ለመምሰል ራሱን ይለዋውጣልና።+ 15 ስለዚህ አገልጋዮቹም የጽድቅ አገልጋዮች ለመምሰል ራሳቸውን ቢለዋውጡ ምንም አያስገርምም። ሆኖም ፍጻሜያቸው እንደ ሥራቸው ይሆናል።+
16 አሁንም ዳግመኛ እናገራለሁ፦ ማንም ሰው ምክንያታዊ እንዳልሆንኩ አድርጎ አያስብ። እንደዚያ አድርጋችሁ የምትመለከቱኝ ከሆነ ግን እኔም እንደ እነሱ በመጠኑ መኩራራት እንድችል ምክንያታዊነት እንደሚጎድለው ሰው አድርጋችሁ ተቀበሉኝ። 17 እንደዚህ የምናገረው የጌታን ምሳሌ በመከተል ሳይሆን ምክንያታዊ ያልሆነ ሰው እንደሚያደርገው በኩራትና በትምክህት ነው። 18 ብዙዎች በሥጋዊ ነገር ስለሚኩራሩ* እኔም እኩራራለሁ። 19 እናንተ በጣም “ምክንያታዊ” ስለሆናችሁ ምክንያታዊ ያልሆኑ ሰዎችን በደስታ ትታገሣላችሁ። 20 እንዲያውም ማንም እንደ ባሪያ ቢያደርጋችሁ፣ ማንም ንብረታችሁን ሙልጭ አድርጎ ቢወስድባችሁ፣ ማንም ያላችሁን ቢቀማችሁ፣ ማንም ራሱን ከፍ ከፍ ቢያደርግባችሁ ወይም ማንም በጥፊ ቢመታችሁ ትታገሣላችሁ።
21 ይህን መናገር ለእኛ አሳፋሪ ነው፤ ምክንያቱም አንዳንዶች በሥልጣናችን በአግባቡ መጠቀም የማንችል ደካሞች እንደሆን አድርገው ሊያስቡ ይችላሉ።
ሆኖም ምክንያታዊነት እንደሚጎድለው ሰው ልናገርና ማንም ሰው በሆነ ነገር የልብ ልብ የሚሰማው ከሆነ እኔም የልብ ልብ ሊሰማኝ ይችላል። 22 ዕብራውያን ናቸው? እኔም ነኝ።+ እስራኤላውያን ናቸው? እኔም ነኝ። የአብርሃም ዘር ናቸው? እኔም ነኝ።+ 23 የክርስቶስ አገልጋዮች ናቸው? እንደ እብድ ሰው ልናገርና እኔ ከሁሉ በላቀ ደረጃ የክርስቶስ አገልጋይ ነኝ፦ ከሁሉም ይበልጥ ሠርቻለሁ፣+ ብዙ ጊዜ ታስሬአለሁ፣+ ብዙ ጊዜ ተደብድቤአለሁ እንዲሁም ብዙ ጊዜ ሞት አፋፍ ደርሻለሁ።+ 24 አይሁዳውያን ለ40 ጅራፍ አንድ የቀረው ግርፋት አምስት ጊዜ ገርፈውኛል፤+ 25 ሦስት ጊዜ በዱላ ተደብድቤአለሁ፤+ አንድ ጊዜ በድንጋይ ተወግሬአለሁ፤+ ሦስት ጊዜ የመርከብ መሰበር አደጋ አጋጥሞኛል፤+ አንድ ሌሊትና አንድ ቀን በባሕር ላይ አሳልፌአለሁ፤ 26 ብዙ ጊዜ ተጉዣለሁ፤ ደግሞም በወንዝ ሙላት ለሚመጣ አደጋ፣ ዘራፊዎች ለሚያደርሱት አደጋ፣ የገዛ ወገኖቼ ለሚያደርሱት አደጋ፣+ ከአሕዛብ ለሚሰነዘር አደጋ፣+ በከተማ፣+ በምድረ በዳና በባሕር ላይ ለሚያጋጥም አደጋ እንዲሁም በሐሰተኛ ወንድሞች መካከል ለሚያጋጥም አደጋ ተጋልጬ ነበር፤ 27 ብዙ ጥሬአለሁ፤ ብዙ ደክሜአለሁ፤ ብዙ ጊዜ እንቅልፍ ሳልተኛ አድሬአለሁ፤+ ተርቤአለሁ፤ ተጠምቻለሁ፤+ ብዙ ጊዜ ምግብ በማጣት ተቸግሬአለሁ፤+ በብርድ ተቆራምጃለሁ፤ በልብስ እጦትም ተቸግሬአለሁ።
28 ከእነዚህ ውጫዊ ችግሮች በተጨማሪ ዕለት ዕለት የሚያስጨንቀኝ* የጉባኤዎች ሁሉ ሐሳብ ነው።+ 29 ድካም የሚሰማው አለ? እኔስ ብሆን ድካም አይሰማኝም? የተሰናከለ አለ? ይህ እኔን በጣም አያናድደኝም?
30 መኩራራት ካስፈለገ ድክመቴን በሚያሳዩ ነገሮች እኩራራለሁ። 31 ለዘላለም የሚመሰገነው የጌታ ኢየሱስ አምላክና አባት እየዋሸሁ እንዳልሆነ ያውቃል። 32 በደማስቆ የንጉሥ አሬጣስ የበታች የሆነው ገዢ ሊይዘኝ ፈልጎ የደማስቆ ሰዎችን ከተማ ያስጠብቅ ነበር፤ 33 ሆኖም በከተማዋ ግንብ ላይ በሚገኘው መስኮት በኩል በቅርጫት አውርደውኝ+ ከእጁ አመለጥኩ።
12 ልኩራራ ይገባኛል። ምንም ጥቅም ባይኖረውም እንኳ ከጌታ የተቀበልኳቸውን ተአምራዊ ራእዮችና+ ጌታ የገለጠልኝን መልእክቶች+ እናገራለሁ። 2 የክርስቶስ ደቀ መዝሙር የሆነ አንድ ሰው አውቃለሁ፤ ይህ ሰው ከ14 ዓመት በፊት ወደ ሦስተኛው ሰማይ ተነጠቀ፤ የተነጠቀው በሥጋ ይሁን ከሥጋ ውጭ አላውቅም፤ አምላክ ግን ያውቃል። 3 አዎ፣ እንዲህ ያለ ሰው አውቃለሁ፤ በሥጋ ይሁን ከሥጋ ውጭ አላውቅም፤ አምላክ ግን ያውቃል፤ 4 ይህ ሰው ወደ ገነት ተነጥቆ በአንደበት ሊገለጹ የማይችሉና ሰው እንዲናገራቸው ያልተፈቀዱ ቃላት ሰማ። 5 እንዲህ ባለው ሰው እኩራራለሁ፤ ሆኖም በድክመቶቼ ካልሆነ በስተቀር በራሴ አልኩራራም። 6 ልኮራ ብፈልግ እንኳ የምናገረው እውነት ስለሆነ ምክንያታዊነት እንደሚጎድለኝ ሆኜ ልቆጠር አይገባም። ይሁንና ማንም በእኔ ላይ ከሚያየውና ከእኔ ከሚሰማው በላይ እንደሆንኩ አድርጎ እንዳይገምተኝ ይህን ከማድረግ እቆጠባለሁ፤ 7 እንዲህ ያሉ አስደናቂ ነገሮች ስለተገለጡልኝ ብቻ ማንም ሰው ለእኔ ከፍ ያለ ግምት ሊኖረው አይገባም።
እንዳልታበይ ሥጋዬን የሚወጋ እሾህ ተሰጠኝ፤+ ይህም እንዳልታበይ ዘወትር የሚያሠቃየኝ* የሰይጣን መልአክ* ነው። 8 ይህ ነገር ከእኔ እንዲርቅ ጌታን ሦስት ጊዜ ለመንኩት። 9 እሱ ግን “ጸጋዬ ይበቃሃል፤ ምክንያቱም ኃይሌ ፍጹም የሚሆነው በምትደክምበት ጊዜ ነው” አለኝ።+ እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል በእኔ ላይ እንደ ድንኳን እንዲኖር እጅግ ደስ እያለኝ በድክመቴ እኩራራለሁ። 10 ስለሆነም ስለ ክርስቶስ ስል በድክመት፣ በስድብ፣ በእጦት፣ በስደትና በችግር ደስ እሰኛለሁ። ስደክም ያን ጊዜ ብርቱ ነኝና።+
11 ምክንያታዊነት የሚጎድለኝ ሆኛለሁ። እንዲህ እንድሆን ያስገደዳችሁኝ እናንተ ናችሁ፤ እናንተ ስለ እኔ ብቃት መመሥከር መቻል ነበረባችሁና። ምንም እንኳ እኔ ከምንም የማልቆጠር ብሆንም ከእናንተ የተራቀቁ ሐዋርያት በአንዲት ነገር እንኳ አላንስም።+ 12 ደግሞም የሐዋርያነቴን ማስረጃዎች በታላቅ ጽናት+ እንዲሁም ምልክቶችን፣ ድንቅ ነገሮችንና ተአምራትን በመፈጸም አሳይቻችኋለሁ።+ 13 እናንተ ከሌሎች ጉባኤዎች ያነሳችሁት በምንድን ነው? ምናልባት እኔ በእናንተ ላይ ሸክም ሳልሆን በመቅረቴ ሊሆን ይችላል፤+ እንዲህ ከሆነ ይህን ጥፋቴን በደግነት ይቅር በሉኝ።
14 እነሆ ወደ እናንተ ለመምጣት ስዘጋጅ ይህ ሦስተኛ ጊዜዬ ነው፤ በእናንተ ላይ ሸክም አልሆንም። እኔ የምፈልገው እናንተን እንጂ ንብረታችሁን አይደለምና፤+ ደግሞም ለልጆቻቸው+ ሀብት ማከማቸት የሚጠበቅባቸው ወላጆች ናቸው እንጂ ልጆች ለወላጆቻቸው አያከማቹም። 15 በእኔ በኩል ስለ እናንተ* ያለኝን ሁሉ፣ ራሴንም ጭምር ብሰጥ እጅግ ደስ ይለኛል።+ እኔ ይህን ያህል አጥብቄ ከወደድኳችሁ እናንተ ለእኔ ያላችሁ ፍቅር ከዚህ ያነሰ ሊሆን ይገባል? 16 የሆነ ሆኖ ሸክም አልሆንኩባችሁም።+ ነገር ግን እናንተ “መሠሪ” እንደሆንኩና “አታልዬ” እንዳጠመድኳችሁ ትናገራላችሁ። 17 ለመሆኑ ወደ እናንተ ከላክኋቸው ሰዎች መካከል በአንዱ እንኳ ተጠቅሜ ከእናንተ አላግባብ ጥቅም ለማግኘት ሞክሬአለሁ? 18 ቲቶ ወደ እናንተ እንዲመጣ ገፋፋሁት፤ ከእሱም ጋር ወንድምን ላክሁት። ለመሆኑ ቲቶ ከእናንተ አላግባብ ጥቅም ለማግኘት ሞክሮ ነበር?+ ከእሱ ጋር በአንድ መንፈስ አልተመላለስንም? አካሄዳችንስ አንድ አልነበረም?
19 እስካሁን ድረስ የምታስቡት እኛ ለእናንተ የመከላከያ መልስ እየሰጠን እንዳለን አድርጋችሁ ነው? እኛ የክርስቶስ ተከታዮች ሆነን የምንናገረው በአምላክ ፊት ነው። ይሁንና የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ ሁሉንም ነገር የምናደርገው እናንተን ለማነጽ ነው። 20 እኔ ወደ እናንተ በምመጣበት ጊዜ ምናልባት እኔ እንደምፈልገው ሳትሆኑ እንዳላገኛችሁ፣ እናንተም እኔን እንደምትፈልጉት ሆኜ ሳታገኙኝ እንዳትቀሩ እሰጋለሁ፤ እንዲያውም ጠብ፣ ቅናት፣ ኃይለኛ ቁጣ፣ ንትርክ፣ ስም ማጥፋት፣ ሐሜትና ብጥብጥ እንዲሁም በኩራት የተወጠሩ ሰዎች እንዳይኖሩ እሰጋለሁ። 21 እንደገና በምመጣበት ጊዜ ምናልባት አምላኬ በፊታችሁ ያሳፍረኝ ይሆናል፤ እንዲሁም ከዚህ ቀደም ኃጢአት ሠርተው ከፈጸሙት ርኩሰት፣ የፆታ ብልግናና* ማንአለብኝነት የሚንጸባረቅበት ድርጊት* ንስሐ ባልገቡት በርካታ ሰዎች አዝን ይሆናል ብዬ እፈራለሁ።
13 ወደ እናንተ ለመምጣት ሳስብ ይህ ሦስተኛ ጊዜዬ ነው። “ማንኛውም ጉዳይ የሚጸናው ሁለት ወይም ሦስት ምሥክሮች በሚሰጡት የምሥክርነት ቃል* ነው።”+ 2 ምንም እንኳ አሁን ከእናንተ ርቄ ያለሁ ቢሆንም ለሁለተኛ ጊዜ አብሬያችሁ እንዳለሁ አድርጋችሁ በማሰብ ቃሌን ተቀበሉ። ደግሞም ዳግመኛ ከመጣሁ ማንንም ሳልገሥጽ እንደማላልፍ ከዚህ በፊት ኃጢአት የሠሩትንም ሆነ የተቀሩትን ሁሉ አስቀድሜ አስጠነቅቃለሁ፤ 3 ይህም የሆነው በእናንተ መካከል በድካም ሳይሆን በኃይል የሚሠራው ክርስቶስ በእኔ አማካኝነት እንደሚናገር የሚያሳይ ማስረጃ ስለፈለጋችሁ ነው። 4 እርግጥ ነው፣ እሱ በእንጨት ላይ የተሰቀለው በድካም የተነሳ* ነው፤ ይሁንና በአምላክ ኃይል የተነሳ ሕያው ሆኗል።+ እርግጥ እኛም ከእሱ ጋር ደካሞች ነን፤ ሆኖም በእናንተ ላይ እየሠራ ባለው የአምላክ ኃይል+ ከእሱ ጋር እንኖራለን።+
5 በእምነት ውስጥ መሆናችሁን ለማረጋገጥ ዘወትር ራሳችሁን ፈትሹ፤ ማንነታችሁን ለማወቅ ዘወትር ራሳችሁን መርምሩ።+ ተቀባይነት አጥታችሁ ካልሆነ በስተቀር ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናንተ ጋር አንድነት እንዳለው አትገነዘቡም? 6 እኛ ግን ተቀባይነት ያለን መሆናችንን እንደምትገነዘቡ ተስፋ አደርጋለሁ።
7 መጥፎ ነገር እንዳትሠሩ ወደ አምላክ እንጸልያለን፤ ይህን የምናደርገው እኛ ተቀባይነት ያለን ሆነን እንድንታይ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ እኛ ተቀባይነት ያላገኘን መስለን ብንታይም እንኳ እናንተ መልካም የሆነውን ነገር እንድታደርጉ ነው። 8 እኛ ለእውነት የቆምን ነን እንጂ እውነትን የሚጻረር ምንም ነገር ማድረግ አንችልምና። 9 እኛ በደከምንበት ጊዜ ሁሉ እናንተ ብርቱዎች ብትሆኑ ምንጊዜም ደስተኞች ነን። ደግሞም መስተካከላችሁን እንድትቀጥሉ እንጸልያለን። 10 ከእናንተ ርቄ ሳለሁ እነዚህን ነገሮች የምጽፍላችሁ በመካከላችሁ በምሆንበት ጊዜ ጠበቅ ያለ እርምጃ እንዳልወስድ ነው፤ ጌታ ሥልጣን የሰጠኝ+ እናንተን ለማነጽ እንጂ ለማፍረስ አይደለም።
11 በተረፈ ወንድሞች፣ መደሰታችሁን፣ መስተካከላችሁን፣ ማጽናኛ መቀበላችሁን፣+ በሐሳብ መስማማታችሁንና+ በሰላም መኖራችሁን ቀጥሉ፤+ የፍቅርና የሰላም አምላክም+ ከእናንተ ጋር ይሆናል። 12 እርስ በርስ በመሳሳም* ሰላምታ ተለዋወጡ። 13 ቅዱሳን ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።
14 የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና የአምላክ ፍቅር እንዲሁም በጋራ የምንቀበለው መንፈስ ቅዱስ ከሁላችሁ ጋር ይሁን።
ወይም “ከርኅራኄ የመነጨ ምሕረት።”
ወይም “ፈተና።”
ወይም “ያበረታታናል።”
“አስቀድማችሁ በሚገባ ከምታውቁትና” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “እስከ መጨረሻው።”
“ሁለት ጊዜ መጠቀም እንድትችሉ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ሲላስ ተብሎም ይጠራል።
ወይም “ቀብድ፤ ወደፊት ለሚመጣው ነገር ዋስትና (መያዣ)።”
ወይም “በነፍሴ።”
ወይም “በሰይጣን እንዳንታለል።”
ወይም “የእሱን ሐሳብ፤ የእሱን ዕቅድ።”
ወይም “መዓዛ።”
ወይም “አንነግድም፤ በአምላክ ቃል አናተርፍም።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “ከክብር ወደላቀ ክብር።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
“የይሖዋ መንፈስ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “የዚህ ዘመን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
“ተስፋ አንቆርጥም” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “ብንወድቅም።”
ወይም “ፈተና።”
“ቤት” ወይም “መኖሪያ” የሚሉት ቃላት ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ የተሠራባቸው ሲሆን ሥጋዊ አካልን ወይም መንፈሳዊ አካልን ያመለክታሉ።
ወይም “መኖሪያ።”
ወይም “ቀብድ፤ ወደፊት ለሚመጣው ነገር ዋስትና (መያዣ)።”
ወይም “ልንገለጥ።”
ወይም “በአምላክ ፊት የተገለጥን ነን።”
ወይም “ሰዎችን ከሥጋዊ አመለካከት አንጻር አንመለከትም።”
ጥቃት ለመሰንዘር ሊሆን ይችላል።
ለመከላከል ሊሆን ይችላል።
ወይም “ሞት ይገባቸዋል ስንባል።”
ወይም “አትቆራኙ።”
“የማይረባ” የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ ቃል የመጣ ሲሆን ሰይጣንን ያመለክታል።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “መንካት አቁሙ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ቃል በቃል “ሥጋችን።”
ቃል በቃል “ለእኔ ስላላችሁ ቅንዓት።”
ወይም “ቅን።”
“መበረታታት” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “የተትረፈረፈ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “እርዳታ።”
ወይም “ያለፍላጎቱ።”
ወይም “በልግስና።”
ወይም “እርዳታ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “ሰበብ።”
በሰብዓዊ ነገር መኩራራትን ያመለክታል።
ወይም “በየዕለቱ ጫና የሚፈጥርብኝ።”
ወይም “የሚመታኝ።”
ወይም “መልእክተኛ።”
ወይም “ስለ ነፍሳችሁ።”
ግሪክኛ፣ ፖርኒያ። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “እፍረተ ቢስነት የሚንጸባረቅበት ምግባር።” ግሪክኛ፣ አሴልጊያ። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ቃል በቃል “በሁለት ወይም በሦስት ምሥክሮች አፍ።”
ሰው በመሆኑ የተነሳ።
ቃል በቃል “በተቀደሰ አሳሳም።”