ለዕብራውያን የተጻፈ ደብዳቤ
1 በጥንት ዘመን አምላክ በተለያዩ ጊዜያትና በብዙ መንገዶች በነቢያት አማካኝነት ለአባቶቻችን ተናግሯል።+ 2 አሁን ደግሞ በእነዚህ ቀናት መጨረሻ የሁሉም ነገር ወራሽ+ አድርጎ በሾመውና የተለያዩ ሥርዓቶችን* በፈጠረበት+ በልጁ+ አማካኝነት ለእኛ ተናገረ። 3 እሱ የአምላክ ክብር+ ነጸብራቅና የማንነቱ ትክክለኛ አምሳያ ነው፤+ እሱም በኃያል ቃሉ ሁሉንም ነገር ደግፎ ያኖራል። እኛን ከኃጢአታችን ካነጻ+ በኋላም በሰማይ በግርማዊው ቀኝ ተቀምጧል።+ 4 ስለዚህ ከመላእክት ስም እጅግ የላቀ ስም+ የወረሰ በመሆኑ ከእነሱ የተሻለ ሆኗል።+
5 ለምሳሌ፣ አምላክ “አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወለድኩህ”+ ደግሞም “አባት እሆነዋለሁ፤ እሱም ልጄ ይሆናል”+ ብሎ ከመላእክት መካከል ስለ የትኛው መልአክ ተናግሮ ያውቃል? 6 ሆኖም የበኩር ልጁን+ እንደገና ወደ ዓለም* የሚያመጣበትን ጊዜ በተመለከተ “የአምላክ መላእክት ሁሉ ይስገዱለት”* ይላል።
7 በተጨማሪም ስለ መላእክት ሲናገር “መላእክቱን መናፍስት፣ አገልጋዮቹን*+ ደግሞ የእሳት ነበልባል ያደርጋል”+ ይላል። 8 ስለ ልጁ ሲናገር ግን እንዲህ ይላል፦ “አምላክ ለዘላለም ዙፋንህ ነው፤+ የመንግሥትህ በትርም የቅንነት* በትረ መንግሥት ነው። 9 ጽድቅን ወደድክ፤ ዓመፅን ጠላህ። ስለዚህ አምላክ ይኸውም አምላክህ ከባልንጀሮችህ* ይበልጥ በደስታ ዘይት ቀባህ።”+ 10 ደግሞም እንዲህ ይላል፦ “ጌታ ሆይ፣ አንተ በመጀመሪያ የምድርን መሠረት ጣልክ፤ ሰማያትም የእጆችህ ሥራ ናቸው። 11 እነሱ ይጠፋሉ፤ አንተ ግን ትኖራለህ፤ ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ፤ 12 እንደ ካባ፣ እንደ ልብስም ትጠቀልላቸዋለህ፤ ደግሞም እንደ ልብስ ትለውጣቸዋለህ። አንተ ግን ያው ነህ፤ ዘመንህም ፍጻሜ የለውም።”+
13 ይሁንና “ጠላቶችህን ለእግርህ መርገጫ እስከማደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ”+ ብሎ ከመላእክት መካከል ስለ የትኛው መልአክ ተናግሮ ያውቃል? 14 ሁሉም መዳን የሚወርሱትን እንዲያገለግሉ የሚላኩ ቅዱስ አገልግሎት* የሚያከናውኑ መናፍስት አይደሉም?+
2 ቀስ በቀስ እንዳንወሰድ+ ለሰማናቸው ነገሮች ከወትሮው የበለጠ ትኩረት መስጠታችን አስፈላጊ የሆነው ለዚህ ነው።+ 2 በመላእክት አማካኝነት የተነገረው ቃል+ የጸና መሆኑ ከተረጋገጠ እንዲሁም ማንኛውም አለመታዘዝና መተላለፍ ከፍትሕ ጋር የሚስማማ ቅጣት የሚያስከትል ከሆነ+ 3 እንዲህ ያለውን ታላቅ መዳን ቸል ብንል እንዴት ከቅጣት ልናመልጥ እንችላለን?+ ይህ መዳን መጀመሪያ ጌታችን የተናገረው+ ሲሆን እሱን የሰሙት ሰዎችም ለእኛ አረጋግጠውልናል፤ 4 አምላክም በምልክቶች፣ በድንቅ ነገሮች፣ በተለያዩ ተአምራትና+ ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ ሁኔታ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎችን በማደል መሥክሯል።+
5 ይህን የምንናገርለትን መጪውን ዓለም+ያስገዛው ለመላእክት አይደለምና። 6 ነገር ግን አንድ ምሥክር፣ አንድ ቦታ ላይ እንዲህ ብሏል፦ “ታስበው ዘንድ ሰው ምንድን ነው? ወይስ ትንከባከበው ዘንድ የሰው ልጅ ምንድን ነው?+ 7 ከመላእክት ጥቂት አሳነስከው፤ የክብርና የሞገስ ዘውድ ደፋህለት፤ እንዲሁም በእጆችህ ሥራ ላይ ሾምከው። 8 ሁሉንም ነገር ከእግሩ በታች አስገዛህለት።”+ አምላክ ሁሉንም ነገር ለእሱ ስላስገዛ፣+ ያላስገዛለት ምንም ነገር የለም።+ ይሁንና በአሁኑ ጊዜ ሁሉም ነገር ተገዝቶለት አናይም።+ 9 ነገር ግን ከመላእክት በጥቂቱ እንዲያንስ ተደርጎ የነበረው ኢየሱስ+ እስከ ሞት ድረስ መከራ በመቀበሉ+ አሁን የክብርና የሞገስ ዘውድ ደፍቶ እናየዋለን፤ እሱ በአምላክ ጸጋ ለሰው ሁሉ ሲል ሞትን ቀምሷል።+
10 ሁሉ ነገር የሚኖረው ለአምላክ ነው፤ የሚኖረውም በእሱ አማካኝነት ነው። ስለዚህ አምላክ ብዙ ልጆችን ክብር ለማጎናጸፍ+ ሲል ለመዳን የሚያበቃቸውን “ዋና ወኪል”+ በመከራ አማካኝነት ፍጹም ማድረጉ የተገባ ነበር።+ 11 የሚቀድሰውም ሆነ የሚቀደሱት ሰዎች፣+ ሁሉም ከአንድ አባት የመጡ ናቸውና፤+ ከዚህም የተነሳ እነሱን ወንድሞች ብሎ ለመጥራት አያፍርም፤+ 12 ምክንያቱም “ስምህን ለወንድሞቼ አሳውቃለሁ፤ በጉባኤ መካከልም በመዝሙር አወድስሃለሁ” ይላል።+ 13 ደግሞም “እኔ እምነቴን በእሱ ላይ እጥላለሁ” ይላል።+ እንደገናም “እነሆ! እኔና ይሖዋ* የሰጠኝ ልጆች” ይላል።+
14 ስለዚህ እነዚህ “ልጆች” ሥጋና ደም ስለሆኑ እሱም ሥጋና ደም ሆነ፤+ ይህም የሆነው ለሞት የመዳረግ አቅም ያለውን+ ዲያብሎስን በሞቱ አማካኝነት እንዳልነበረ ያደርገው ዘንድ ነው፤+ 15 እንዲሁም ሞትን በመፍራታቸው በሕይወት ዘመናቸው በሙሉ በባርነት ቀንበር የተያዙትን ሁሉ ነፃ እንዲያወጣ ነው።+ 16 እሱ እየረዳ ያለው መላእክትን እንዳልሆነ የታወቀ ነውና፤ ከዚህ ይልቅ እየረዳ ያለው የአብርሃምን ዘር ነው።+ 17 ስለሆነም ለሕዝቡ ኃጢአት የማስተሰረያ መሥዋዕት ለማቅረብ*+ በአምላክ አገልግሎት መሐሪና ታማኝ ሊቀ ካህናት ይሆን ዘንድ በሁሉ ረገድ እንደ “ወንድሞቹ” መሆን አስፈለገው።+ 18 በተፈተነ ጊዜ እሱ ራሱ መከራ ስለደረሰበት+ በፈተና ላይ ላሉት ሊደርስላቸው ይችላል።+
3 ስለሆነም የሰማያዊው ጥሪ ተካፋዮች+ የሆናችሁ ቅዱሳን ወንድሞች፣ በእሱ እንደምናምን በይፋ የምንናገርለትን፣ ሐዋርያና ሊቀ ካህናት የሆነውን ኢየሱስን አስቡ።+ 2 ሙሴ በመላው የአምላክ ቤት ላይ ታማኝ እንደነበረ ሁሉ+ እሱም ለሾመው ታማኝ ነበር።+ 3 ቤቱን የሠራው፣ ከቤቱ የበለጠ ክብር ስላለው እሱ* ከሙሴ የበለጠ ክብር ይገባዋል።+ 4 እያንዳንዱ ቤት ሠሪ እንዳለው የታወቀ ነው፤ ሁሉን ነገር የሠራው ግን አምላክ ነው። 5 ሙሴም በመላው የአምላክ ቤት ላይ ታማኝ አገልጋይ ነበር። አገልግሎቱም ከጊዜ በኋላ ለሚነገሩ ነገሮች ምሥክር ነው። 6 ክርስቶስ ግን በአምላክ ቤት ላይ የተሾመ ታማኝ ልጅ ነበር።+ እኛም አፋችንን ሞልተን የመናገር ነፃነታችንንና የምንደሰትበትን ተስፋችንን እስከ መጨረሻው አጥብቀን ከያዝን የአምላክ ቤት ነን።+
7 ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦+ “ዛሬ ድምፁን የምትሰሙ ከሆነ 8 በምድረ በዳ እጅግ የሚያስቆጣ ድርጊት በተፈጸመበት በፈተና ቀን እንደሆነው ልባችሁን አታደንድኑ፤+ 9 በዚያ፣ አባቶቻችሁ ያደረግኩትን ሁሉ ለ40 ዓመት ቢያዩም እኔን በመፈተን ተገዳደሩኝ።+ 10 በዚህም ምክንያት በዚያ ትውልድ በጣም ተንገሸገሽኩ፤ እንዲህም አልኩ፦ ‘ሁልጊዜ ልባቸው ይስታል፤ መንገዴንም ሊያውቁ አልቻሉም።’ 11 በመሆኑም ‘ወደ እረፍቴ አይገቡም’ ብዬ በቁጣዬ ማልኩ።”+
12 ወንድሞች፣ ሕያው ከሆነው አምላክ በመራቅ እምነት የለሽ የሆነ ክፉ ልብ ከእናንተ መካከል በማናችሁም ውስጥ እንዳያቆጠቁጥ ተጠንቀቁ፤+ 13 ከዚህ ይልቅ ከእናንተ መካከል አንዳችሁም ኃጢአት ባለው የማታለል ኃይል እንዳትደነድኑ “ዛሬ”+ ተብሎ የሚጠራ ጊዜ እስካለ ድረስ በየዕለቱ እርስ በርሳችሁ ተበረታቱ። 14 የክርስቶስ ተካፋዮች የምንሆነው* በመጀመሪያ የነበረንን ትምክህት እስከ መጨረሻው አጽንተን ከያዝን ብቻ ነውና።+ 15 ይህም “ዛሬ ድምፁን የምትሰሙ ከሆነ እጅግ የሚያስቆጣ ድርጊት በተፈጸመበት ጊዜ እንደሆነው ልባችሁን አታደንድኑ” እንደተባለው ነው።+
16 ድምፁን ቢሰሙም እንኳ እጅግ ያስቆጡት እነማን ነበሩ? ይህን ያደረጉት ሙሴ እየመራቸው ከግብፅ የወጡት ሁሉ አይደሉም?+ 17 ከዚህም ሌላ ለ40 ዓመት አምላክ በእነሱ እንዲንገሸገሽ ያደረጉት እነማን ናቸው?+ እነዚያ ኃጢአት የሠሩትና ሬሳቸው በምድረ በዳ ወድቆ የቀረው አይደሉም?+ 18 ደግሞስ ወደ እረፍቴ አይገቡም ብሎ የማለው ስለ እነማን ነው? እነዚያን ያልታዘዙትን በተመለከተ አይደለም? 19 ስለዚህ ሊገቡ ያልቻሉት እምነት በማጣታቸው የተነሳ እንደሆነ እንረዳለን።+
4 ስለዚህ ወደ እረፍቱ የመግባት ተስፋ አሁንም ስላለ ከእናንተ መካከል ማንም ለዚያ የማይበቃ ሆኖ እንዳይገኝ እንጠንቀቅ።*+ 2 ለአባቶቻችን ተሰብኮ እንደነበረው ሁሉ ምሥራቹ ለእኛም ተሰብኳልና፤+ እነሱ ግን ሰምተው የታዘዙት ሰዎች የነበራቸው ዓይነት እምነት ስላልነበራቸው የሰሙት ቃል አልጠቀማቸውም። 3 እኛ ግን እምነት በማሳየታችን ወደዚህ እረፍት እንገባለን። ምንም እንኳ የእሱ ሥራ ዓለም ከተመሠረተበት* ጊዜ ጀምሮ የተጠናቀቀ ቢሆንም+ “‘ወደ እረፍቴ አይገቡም’ ብዬ በቁጣዬ ማልኩ” ብሏል።+ 4 በአንድ ቦታ ላይ ሰባተኛውን ቀን አስመልክቶ “አምላክም በሰባተኛው ቀን ከሥራው ሁሉ አረፈ” ብሏልና፤+ 5 እንደገና እዚህ ላይ “ወደ እረፍቴ አይገቡም” ብሏል።+
6 ስለዚህ ገና ወደ እረፍቱ የሚገቡ ስላሉና መጀመሪያ ምሥራቹ የተሰበከላቸው ባለመታዘዛቸው ምክንያት ሳይገቡ ስለቀሩ+ 7 ከረጅም ጊዜ በኋላ በዳዊት መዝሙር ላይ “ዛሬ” በማለት እንደገና አንድን ቀን መደበ፤ ይህም ቀደም ሲል “ዛሬ ድምፁን የምትሰሙ ከሆነ ልባችሁን አታደንድኑ” እንደተባለው ነው።+ 8 ኢያሱ+ ወደ እረፍት ቦታ እየመራ አስገብቷቸው ቢሆን ኖሮ አምላክ ከዚያ በኋላ ስለ ሌላ ቀን ባልተናገረ ነበር። 9 ስለዚህ የአምላክ ሕዝብ የሰንበት እረፍት ገና ይቀረዋል።+ 10 ወደ አምላክ እረፍት የገባ ሰው አምላክ ከሥራው እንዳረፈ ሁሉ እሱም ከሥራው አርፏልና።+
11 ስለዚህ ማንም የእነዚያን ያለመታዘዝ ምሳሌ ተከትሎ እንዳይወድቅ ወደዚያ እረፍት ለመግባት የተቻለንን ሁሉ እናድርግ።+ 12 የአምላክ ቃል ሕያውና ኃይለኛ ነው፤+ በሁለት በኩል ስለት ካለው ከየትኛውም ሰይፍ የበለጠ ስለታም ነው፤+ ነፍስንና* መንፈስን* እንዲሁም መገጣጠሚያንና መቅኒን እስኪለያይ ድረስ ሰንጥቆ ይገባል፤ የልብንም ሐሳብና ዓላማ መረዳት ይችላል። 13 ደግሞም ከአምላክ እይታ የተሰወረ አንድም ፍጥረት የለም፤+ ይልቁንም ተጠያቂዎች በሆንበት+ በእሱ ዓይኖች ፊት ሁሉም ነገር የተራቆተና ገሃድ የወጣ ነው።
14 እንግዲህ ወደ ሰማያት የገባ ታላቅ ሊቀ ካህናት ይኸውም የአምላክ ልጅ+ ኢየሱስ እንዳለን ስለምናውቅ በእሱ ላይ እምነት እንዳለን ምንጊዜም በይፋ እንናገር።+ 15 ያለን ሊቀ ካህናት በድካማችን ሊራራልን የማይችል አይደለምና፤+ ከዚህ ይልቅ እንደ እኛው በሁሉም ረገድ የተፈተነ ሊቀ ካህናት አለን፤ ይሁንና እሱ ኃጢአት የለበትም።+ 16 እንግዲህ እርዳታ በሚያስፈልገን ጊዜ ምሕረትና ጸጋ እናገኝ ዘንድ ያለምንም ፍርሃት* ወደ ጸጋው ዙፋን እንቅረብ።+
5 ከሰዎች መካከል የተመረጠ እያንዳንዱ ሊቀ ካህናት ለኃጢአት መባና መሥዋዕት ያቀርብ ዘንድ+ እነሱን በመወከል የአምላክን አገልግሎት ለማከናወን ይሾማል።+ 2 እሱ ራሱ ድክመት ስላለበት* አላዋቂ የሆኑትንና የሚሳሳቱትን* በርኅራኄ* ሊይዛቸው ይችላል፤ 3 በዚህም የተነሳ ለሕዝቡ የኃጢአት መባ እንደሚያቀርብ ሁሉ ለራሱም ለማቅረብ ይገደዳል።+
4 አንድ ሰው ይህን የክብር ቦታ የሚያገኘው እንደ አሮን፣ አምላክ ሲጠራው ብቻ ነው እንጂ በራሱ ፈቃድ አይደለም።+ 5 ክርስቶስም ሊቀ ካህናት በመሆን ራሱን ከፍ ከፍ አላደረገም፤+ ከዚህ ይልቅ “አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወለድኩህ”+ ብሎ ስለ እሱ የተናገረው፣ ከፍ ከፍ አደረገው። 6 ደግሞም በሌላ ቦታ ላይ “እንደ መልከጼዴቅ፣ አንተ ለዘላለም ካህን ነህ” ብሏል።+
7 ክርስቶስ በምድር ላይ በኖረበት ዘመን* ከሞት ሊያድነው ለሚችለው በከፍተኛ ጩኸትና እንባ ብዙ ምልጃና ልመና አቀረበ፤+ አምላካዊ ፍርሃት ስለነበረውም ጸሎቱ ተሰማለት። 8 ልጅ ቢሆንም እንኳ ከደረሰበት መከራ መታዘዝን ተማረ።+ 9 በዚህም ፍጹም ከሆነ በኋላ+ የሚታዘዙት ሁሉ ዘላለማዊ መዳን እንዲያገኙ ምክንያት ሆነላቸው፤+ 10 ምክንያቱም ከመልከጼዴቅ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ አምላክ ሊቀ ካህናት አድርጎ ሾሞታል።+
11 እሱን በተመለከተ ብዙ የምንናገረው ነገር አለን፤ ይሁንና ጆሯችሁ ስለደነዘዘ ለማስረዳት በጣም አስቸጋሪ ነው። 12 በአሁኑ ጊዜ* አስተማሪዎች ልትሆኑ ይገባችሁ የነበረ ቢሆንም የአምላክን ቅዱስ መልእክት መሠረታዊ ነገሮች እንደገና ከመጀመሪያ ጀምሮ የሚያስተምራችሁ ሰው ትፈልጋላችሁ፤+ ደግሞም ጠንካራ ምግብ ከመመገብ ይልቅ እንደገና ወተት መፈለግ ጀምራችኋል። 13 ወተት የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለሆነ ከጽድቅ ቃል ጋር ትውውቅ የለውም።+ 14 ጠንካራ ምግብ ግን ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት እንዲችሉ የማስተዋል ችሎታቸውን በማሠራት ላሠለጠኑ* ጎልማሳ ሰዎች ነው።
6 ስለዚህ ስለ ክርስቶስ ከተማርነው መሠረታዊ ትምህርት አልፈን ስለሄድን+ ወደ ጉልምስና ለመድረስ እንጣጣር፤+ መሠረትን ደግመን አንመሥርት፤ ይኸውም ከሞቱ ሥራዎች ንስሐ ስለ መግባት፣ በአምላክ ስለ ማመን፣ 2 እንዲሁም ስለ ጥምቀቶች፣ እጆችን ስለ መጫን፣+ ስለ ሙታን ትንሣኤና+ ስለ ዘላለማዊ ፍርድ የሚገልጹ ትምህርቶችን ደግመን አንማር። 3 አምላክ ከፈቀደ ይህን እናደርጋለን።
4 ቀደም ሲል ብርሃን በርቶላቸው የነበሩትን፣+ ሰማያዊውን ነፃ ስጦታ የቀመሱትን፣ መንፈስ ቅዱስ የተቀበሉትን፣ 5 መልካም የሆነውን የአምላክ ቃልና በሚመጣው ሥርዓት* የሚገኙትን በረከቶች* የቀመሱትን፣ 6 በኋላ ግን ከእምነት ጎዳና የራቁትን+ እንደገና ወደ ንስሐ መመለስ አይቻልም፤ ምክንያቱም የአምላክን ልጅ ለራሳቸው እንደገና በእንጨት ላይ ይቸነክሩታል፤ እንዲሁም በአደባባይ ያዋርዱታል።+ 7 በየጊዜው በላዩ ላይ የሚወርደውን ዝናብ የሚጠጣና ለአራሾቹ መብል የሚሆን አትክልት የሚያፈራ መሬት ከአምላክ በረከትን ያገኛልና። 8 እሾህና አሜኬላ የሚያበቅል ከሆነ ግን የተተወና ለመረገም የተቃረበ ይሆናል፤ በመጨረሻም በእሳት ይቃጠላል።
9 ይሁን እንጂ የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ ምንም እንኳ እንደዚህ ብለን ብንናገርም እናንተ በተሻለ ሁኔታ ላይ ይኸውም ወደ መዳን በሚያደርስ ሁኔታ ላይ እንደምትገኙ እርግጠኞች ነን። 10 አምላክ ቅዱሳንን በማገልገልም* ሆነ ወደፊትም ማገልገላችሁን በመቀጠል የምታከናውኑትን ሥራ እንዲሁም ለስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር+ በመርሳት ፍትሕ አያዛባም። 11 ይሁንና ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ የሆነውን ተስፋ+ እስከ መጨረሻው መያዝ እንድትችሉ+ እያንዳንዳችሁ ያንኑ ትጋት እንድታሳዩ እንመኛለን፤ 12 ይህም አምላክ ቃል የገባቸውን ነገሮች በእምነትና በትዕግሥት የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንዳትሆኑ ነው።+
13 አምላክ ለአብርሃም ቃል በገባለት ጊዜ ሊምልበት የሚችል ከእሱ የሚበልጥ ሌላ ማንም ስለሌለ በራሱ ስም ማለ፤+ 14 እንዲህም አለ፦ “በእርግጥ እባርክሃለሁ፤ ዘርህንም በእርግጥ አበዛዋለሁ።”+ 15 በመሆኑም አብርሃም በትዕግሥት ከጠበቀ በኋላ ይህን የተስፋ ቃል አገኘ። 16 ሰዎች ከእነሱ በሚበልጥ ይምላሉ፤ መሐላቸውም እንደ ሕጋዊ ዋስትና ስለሆነ ማንኛውም ሙግት በመሐላው ይቋጫል።+ 17 በተመሳሳይም አምላክ ዓላማው ፈጽሞ የማይለወጥ መሆኑን ለተስፋው ቃል ወራሾች+ ይበልጥ ግልጽ በሆነ ሁኔታ ለማሳየት በወሰነ ጊዜ የተስፋውን ቃል በመሐላ አረጋገጠ። 18 ይህን ያደረገው መጠጊያ ለማግኘት ወደ እሱ የሸሸን እኛ፣ አምላክ ሊዋሽ በማይችልባቸው፣+ ፈጽሞ በማይለወጡት በእነዚህ ሁለት ነገሮች አማካኝነት በፊታችን ያለውን ተስፋ አጥብቀን እንድንይዝ የሚረዳንን ከፍተኛ ማበረታቻ እንድናገኝ ነው። 19 እኛ ለነፍሳችን* እንደ መልሕቅ አስተማማኝና ጽኑ የሆነ ይህ ተስፋ አለን፤+ ተስፋውም መጋረጃውን አልፈን ወደ ውስጥ እንድንገባ ያስችለናል፤+ 20 ከመልከጼዴቅ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ለዘላለም ሊቀ ካህናት+ የሆነው ኢየሱስ+ ፈር ቀዳጅ ሆኖ ስለ እኛ ወደዚያ ገብቷል።
7 አብርሃም ነገሥታትን ድል አድርጎ ሲመለስ የሳሌም ንጉሥና የልዑሉ አምላክ ካህን የሆነው ይህ መልከጼዴቅ አግኝቶት ባረከው፤+ 2 አብርሃም ደግሞ ከሁሉ ነገር አንድ አሥረኛ ሰጠው።* በመጀመሪያ ስሙ “የጽድቅ ንጉሥ” ማለት ነው፤ ደግሞም የሳሌም ንጉሥ ማለትም “የሰላም ንጉሥ” ነው። 3 አባትና እናትም ሆነ የዘር ሐረግ እንዲሁም ለዘመኑ መጀመሪያ፣ ለሕይወቱም መጨረሻ የለውም፤ ከዚህ ይልቅ የአምላክን ልጅ እንዲመስል በመደረጉ ለዘላለም ካህን ሆኖ ይኖራል።+
4 እንግዲህ የቤተሰብ ራስ* የሆነው አብርሃም ምርጥ ከሆነው ምርኮ ላይ አንድ አሥረኛውን የሰጠው+ ይህ ሰው ምን ያህል ታላቅ እንደነበረ ተመልከቱ። 5 እርግጥ የክህነት ኃላፊነት የሚቀበሉ ከሌዊ ልጆች ወገን የሆኑት ሰዎች+ ምንም እንኳ ወንድሞቻቸው የአብርሃም ዘሮች ቢሆኑም ከሕዝቡ ማለትም ከገዛ ወንድሞቻቸው አሥራት እንዲሰበስቡ ሕጉ ያዛል።+ 6 ሆኖም ከእነሱ የትውልድ ሐረግ ያልመጣው ይህ ሰው ከአብርሃም አሥራት የተቀበለ ሲሆን የተስፋ ቃል የተሰጠውን ሰው ባርኮታል።+ 7 እንግዲህ አነስተኛ የሆነው ከእሱ በሚበልጠው እንደተባረከ ምንም ጥርጥር የለውም። 8 በአንድ በኩል አሥራት የሚቀበሉት ሟች የሆኑ ሰዎች ሲሆኑ በሌላ በኩል ግን አሥራት የሚቀበለው ሕያው ሆኖ እንደሚኖር የተመሠከረለት ሰው ነው።+ 9 እንግዲህ አሥራት የሚቀበለው ሌዊ እንኳ በአብርሃም በኩል አሥራት ከፍሏል ማለት ይቻላል፤ 10 መልከጼዴቅ አብርሃምን ባገኘው ጊዜ ሌዊ ገና በአባቱ በአብርሃም አብራክ ውስጥ* ነበርና።+
11 እንግዲህ ፍጽምና ሊገኝ የሚችለው በሌዊ ክህነት አማካኝነት ቢሆን ኖሮ+ (ክህነቱ ለሕዝቡ የተሰጠው ሕግ አንዱ ገጽታ ስለሆነ)፣ እንደ አሮን ሥርዓት ሳይሆን እንደ መልከጼዴቅ ሥርዓት+ ያለ ተብሎ የተነገረለት ሌላ ካህን መነሳቱ ምን ያስፈልግ ነበር? 12 ክህነቱ ስለሚለወጥ ሕጉም የግድ መለወጥ ያስፈልገዋልና።+ 13 ይህ ሁሉ ነገር የተነገረለት ሰው ከሌላ ነገድ የመጣ ነውና፤ ከዚህ ነገድ ማንም ወደ መሠዊያው ቀርቦ ያገለገለ የለም።+ 14 ጌታችን ከይሁዳ ነገድ እንደወጣ የታወቀ ነውና፤+ ይሁንና ሙሴ ከዚህ ነገድ ካህናት እንደሚገኙ የተናገረው ነገር የለም።
15 ደግሞም እንደ መልከጼዴቅ ያለ ሌላ ካህን+ ሲነሳ ይህ ጉዳይ ይበልጥ ግልጽ ይሆናል፤+ 16 እሱ ካህን የሆነው በሥጋዊ ትውልድ ላይ በተመካውና ሕጉ በያዘው መሥፈርት ሳይሆን የማይጠፋ ሕይወት+ እንዲኖረው ባስቻለው ኃይል ነው። 17 “እንደ መልከጼዴቅ፣ አንተ ለዘላለም ካህን ነህ” ተብሎ ተመሥክሮለታልና።+
18 እንግዲህ የቀድሞው ትእዛዝ ደካማና ፍሬ ቢስ በመሆኑ ተሽሯል።+ 19 ሕጉ የትኛውንም ነገር ወደ ፍጽምና አላደረሰምና፤+ ወደ አምላክ የምንቀርብበት የተሻለ ተስፋ+ መሰጠቱ ግን ይህን ማድረግ ችሏል።+ 20 በተጨማሪም ይህ ያለመሐላ እንዳልሆነ ሁሉ 21 (ያለመሐላ ካህናት የሆኑ ሰዎች አሉና፤ እሱ ግን በመሐላ ካህን ሆኗል፤ ይህም የሆነው “ይሖዋ* ‘አንተ ለዘላለም ካህን ነህ’ ብሎ ምሏል፤ ደግሞም ሐሳቡን አይለውጥም”* በማለት ስለ እሱ የተናገረው አምላክ በማለው መሐላ መሠረት ነው፤)+ 22 እንደዚሁም ኢየሱስ ለተሻለ ቃል ኪዳን ዋስትና* ሆኗል።+ 23 ከዚህም በተጨማሪ ካህናት አገልግሎታቸውን እንዳይቀጥሉ ሞት ስለሚያግዳቸው አንዱ ሌላውን እየተካ እንዲያገለግል ብዙዎች ካህናት መሆን ነበረባቸው፤+ 24 እሱ ግን ለዘላለም+ ሕያው ሆኖ ስለሚኖር ክህነቱ ተተኪ የለውም። 25 ስለሆነም ለእነሱ ለመማለድ ሁልጊዜ ሕያው ሆኖ ስለሚኖር በእሱ አማካኝነት ወደ አምላክ የሚቀርቡትን ፈጽሞ ሊያድናቸውም ይችላል።+
26 እኛ የሚያስፈልገን ታማኝ፣ ቅን የሆነ፣ ያልረከሰ፣+ ከኃጢአተኞች የተለየና ከሰማያት በላይ ከፍ ያለ እንደዚህ ያለ ሊቀ ካህናት ነው።+ 27 እነዚያ ሊቃነ ካህናት ያደርጉ እንደነበረው፣ በመጀመሪያ ለራሱ ኃጢአት ከዚያም ለሕዝቡ ኃጢአት+ በየዕለቱ መሥዋዕት ማቅረብ አያስፈልገውም፤+ ምክንያቱም ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ባቀረበ ጊዜ ይህን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ፈጽሞታል።+ 28 ሕጉ ድክመት ያለባቸውን ሰዎች ሊቃነ ካህናት አድርጎ ይሾማልና፤+ ከሕጉ በኋላ የመጣው የመሐላ ቃል+ ግን ለዘላለም ፍጹም የተደረገውን ልጅ+ ይሾማል።
8 እንግዲህ የምንናገረው ነገር ዋና ነጥብ ይህ ነው፦ በሰማያት በግርማዊው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ+ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን፤+ 2 እሱም የቅዱሱ ስፍራና*+ የእውነተኛው ድንኳን አገልጋይ* ነው፤ ይህም ድንኳን በሰው ሳይሆን በይሖዋ* የተተከለ ነው። 3 እያንዳንዱ ሊቀ ካህናት የሚሾመው ስጦታና መሥዋዕት ለማቅረብ ነውና፤ በመሆኑም ይሄኛው ሊቀ ካህናትም የሚያቀርበው ነገር ያስፈልገዋል።+ 4 እሱ ምድር ላይ ቢሆን ኖሮ ካህን ባልሆነ ነበር፤+ ምክንያቱም ሕጉ በሚያዘው መሠረት ስጦታ የሚያቀርቡ ሰዎች አሉ። 5 እነዚህ ሰዎች ለሰማያዊ ነገሮች+ ዓይነተኛ አምሳያና ጥላ+ የሆነ ቅዱስ አገልግሎት ያቀርባሉ፤ ይህም የሆነው ሙሴ ድንኳኑን ለመሥራት በተዘጋጀ ጊዜ “በተራራው ላይ ተገልጦልህ ባየኸው ንድፍ መሠረት ሁሉንም ነገር በጥንቃቄ ሥራ” ተብሎ ከተሰጠው መለኮታዊ ትእዛዝ ጋር በሚስማማ ሁኔታ ነው።+ 6 ይሁንና ኢየሱስ እጅግ የላቀ አገልግሎት* ተቀብሏል፤ ልክ እንደዚሁም ለተሻለ ቃል ኪዳን+ መካከለኛ ሆኗል፤+ ይህም ቃል ኪዳን በተሻሉ ተስፋዎች ላይ በሕግ የጸና ነው።+
7 የመጀመሪያው ቃል ኪዳን ምንም ጉድለት ባይኖረው ኖሮ ሁለተኛ ቃል ኪዳን ባላስፈለገ ነበር።+ 8 አምላክ በሕዝቡ ላይ ጉድለት ስላገኘ እንዲህ ብሎ ተናግሯልና፦ “‘እነሆ፣ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ጊዜ ይመጣል’ ይላል ይሖዋ።* 9 ‘ይህም ቃል ኪዳን አባቶቻቸውን እጃቸውን ይዤ ከግብፅ ምድር እየመራሁ ባወጣኋቸው ቀን+ ከእነሱ ጋር እንደገባሁት ዓይነት ቃል ኪዳን አይሆንም፤ ምክንያቱም እነሱ በቃል ኪዳኔ አልጸኑም፤ በመሆኑም ችላ አልኳቸው’ ይላል ይሖዋ።*
10 “‘ከዚያ ጊዜ በኋላ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነውና’ ይላል ይሖዋ።* ‘ሕግጋቴን በአእምሯቸው ውስጥ አኖራለሁ፤ በልባቸውም ላይ እጽፋቸዋለሁ።+ እኔም አምላካቸው እሆናለሁ፤ እነሱም ሕዝቤ ይሆናሉ።+
11 “‘እነሱም እያንዳንዳቸው የአገራቸውን ሰው፣ እያንዳንዳቸውም ወንድማቸውን “ይሖዋን* እወቅ!” ብለው ከእንግዲህ አያስተምሩም። ከትንሹ አንስቶ እስከ ትልቁ ድረስ ሁሉም ያውቁኛልና። 12 ለክፉ ሥራቸው ምሕረት አደርግላቸዋለሁና፤ ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ ወዲህ አላስታውስም።’”+
13 “አዲስ ቃል ኪዳን” ሲል የቀድሞውን ቃል ኪዳን ጊዜ ያለፈበት አድርጎታል።+ ስለዚህ ጊዜ ያለፈበትና እያረጀ ያለው ቃል ኪዳን ሊጠፋ ተቃርቧል።+
9 የቀድሞው ቃል ኪዳን በበኩሉ ቅዱስ አገልግሎት የሚከናወንባቸው ደንቦችና በምድር ላይ የራሱ ቅዱስ ስፍራ+ ነበረው። 2 መቅረዙ፣+ ጠረጴዛውና በአምላክ ፊት የቀረበው ኅብስት+ የሚገኙበት የድንኳኑ የመጀመሪያው ክፍል ተሠርቶ ነበር፤ ይህም ቅድስት ይባላል።+ 3 ከሁለተኛው መጋረጃ+ በስተ ኋላ ግን ቅድስተ ቅዱሳን የሚባለው የድንኳኑ ክፍል ይገኝ ነበር።+ 4 በዚህ ክፍል ውስጥ የወርቅ ጥና+ እና ሙሉ በሙሉ በወርቅ የተለበጠው+ የቃል ኪዳኑ ታቦት+ ይገኙ ነበር፤ በታቦቱ ውስጥም መና የያዘው የወርቅ ማሰሮ፣+ ያቆጠቆጠችው የአሮን በትርና+ የቃል ኪዳኑ ጽላቶች+ ነበሩ፤ 5 በላዩ ላይ ደግሞ የስርየት መክደኛውን* የሚጋርዱ ክብራማ ኪሩቦች ነበሩ።+ ይሁንና ስለ እነዚህ ነገሮች በዝርዝር ለመናገር አሁን ጊዜው አይደለም።
6 እነዚህ ነገሮች በዚህ መንገድ ከተሠሩ በኋላ ካህናቱ ቅዱስ አገልግሎቶችን ለማከናወን ወደ ድንኳኑ የመጀመሪያ ክፍል ሁልጊዜ ይገባሉ፤+ 7 ወደ ሁለተኛው ክፍል የሚገባው ግን ሊቀ ካህናቱ ብቻ ነበር፤ የሚገባውም በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ነው፤+ ደግሞም ለራሱና+ ሕዝቡ+ ባለማወቅ ለፈጸመው ኃጢአት የሚያቀርበውን ደም ሳይዝ አይገባም።+ 8 በዚህ መንገድ፣ የመጀመሪያው ድንኳን* ተተክሎ ሳለ ወደ ቅዱሱ ስፍራ* የሚወስደው መንገድ ገና እንዳልተገለጠ መንፈስ ቅዱስ ግልጽ አድርጓል።+ 9 ይህ ድንኳን ለአሁኑ ዘመን ምሳሌ+ ሲሆን ከዚህ ዝግጅት ጋር በሚስማማ ሁኔታ ስጦታዎችና መሥዋዕቶች ይቀርባሉ።+ ይሁን እንጂ እነዚህ ነገሮች ቅዱስ አገልግሎት የሚያቀርበው ሰው ፍጹም በሆነ መንገድ ንጹሕ ሕሊና እንዲኖረው ሊያደርጉ አይችሉም።+ 10 እነዚህ ነገሮች ከምግብ፣ ከመጠጥና ከተለያዩ የመንጻት ሥርዓቶች* ጋር ብቻ የተያያዙ ናቸው።+ ደግሞም አካልን የሚመለከቱ ደንቦች+ ሲሆኑ በሥራ ላይ የዋሉትም፣ ሁኔታዎች የሚስተካከሉበት የተወሰነው ጊዜ እስኪመጣ ድረስ ነበር።
11 ይሁን እንጂ ክርስቶስ አሁን ላሉት መልካም ነገሮች ሊቀ ካህናት ሆኖ በመጣ ጊዜ በሰው እጅ ወዳልተሠራው ይኸውም ከዚህ ፍጥረት ወዳልሆነው ይበልጥ ታላቅና ፍጹም ወደሆነው ድንኳን ገብቷል። 12 ወደ ቅዱሱ ስፍራ የገባው የፍየሎችንና የወይፈኖችን ደም ይዞ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ የገዛ ራሱን ደም ይዞ+ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ገባ፤ ደግሞም ለእኛ ዘላለማዊ መዳን* አስገኘልን።+ 13 የፍየሎችና የኮርማዎች ደም+ እንዲሁም በረከሱ ሰዎች ላይ የሚረጭ የጊደር አመድ ሥጋን በማንጻት የሚቀድስ ከሆነ+ 14 በዘላለማዊ መንፈስ አማካኝነት ራሱን ያላንዳች እንከን ለአምላክ ያቀረበው የክርስቶስ ደም+ ሕያው ለሆነው አምላክ ቅዱስ አገልግሎት እንድናቀርብ+ ሕሊናችንን ከሞቱ ሥራዎች እንዴት አብልጦ አያነጻም?+
15 የአዲስ ቃል ኪዳን መካከለኛ የሆነው በዚህ ምክንያት ነው።+ መካከለኛ የሆነውም የተጠሩት የዘላለማዊውን ውርሻ+ ተስፋ ይቀበሉ ዘንድ ነው። ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለው በሞቱ የተነሳ ሲሆን በእሱ ሞት አማካኝነት በቀድሞው ቃል ኪዳን ሥር ሆነው ሕግ በመተላለፍ ከፈጸሟቸው ድርጊቶች በቤዛ ነፃ ወጥተዋል።+ 16 ቃል ኪዳን ሲኖር ቃል ኪዳኑን የፈጸመው ሰው* መሞቱ መረጋገጥ አለበት፤ 17 ምክንያቱም ቃል ኪዳኑን የፈጸመው ሰው በሕይወት እስካለ ድረስ ቃል ኪዳኑ መቼም ተፈጻሚ ሊሆን ስለማይችል ቃል ኪዳን የሚጸናው ሞትን መሠረት በማድረግ ነው። 18 ከዚህም የተነሳ የቀድሞው ቃል ኪዳንም ያለደም ሥራ ላይ መዋል አልጀመረም።* 19 ሙሴ በሕጉ ላይ የሰፈረውን እያንዳንዱን ትእዛዝ ለሕዝቡ ሁሉ ከተናገረ በኋላ የወይፈኖችንና የፍየሎችን ደም ከውኃ፣ ከቀይ ሱፍና ከሂሶጵ ጋር ወስዶ መጽሐፉንና* ሕዝቡን ሁሉ ረጭቷል፤ 20 የረጨውም “አምላክ እንድትጠብቁት ያዘዛችሁ የቃል ኪዳኑ ደም ይህ ነው” ብሎ ነው።+ 21 በተመሳሳይም በድንኳኑና ቅዱስ አገልግሎት* በሚቀርብባቸው ዕቃዎች ሁሉ ላይ ደም ረጭቷል።+ 22 አዎ፣ በሕጉ መሠረት ሁሉም ነገር ማለት ይቻላል በደም ይነጻል፤+ ደም ካልፈሰሰ በስተቀር ይቅርታ ማግኘት አይቻልም።+
23 ስለዚህ በሰማያት ላሉት ነገሮች ዓይነተኛ አምሳያ+ የሆኑት ሁሉ በዚህ መንገድ መንጻታቸው+ የግድ አስፈላጊ ነበር፤ በሰማያት ያሉት ነገሮች ግን የተሻሉ መሥዋዕቶች ያስፈልጓቸዋል። 24 ክርስቶስ የገባው በሰው እጅ ወደተሠራውና የእውነተኛው ቅዱስ ስፍራ አምሳያ+ ወደሆነው ስፍራ አይደለምና፤+ ከዚህ ይልቅ አሁን ስለ እኛ በአምላክ ፊት ይታይ ዘንድ+ ወደ ሰማይ ገብቷል።+ 25 የገባው ግን ሊቀ ካህናቱ የራሱን ሳይሆን የእንስሳ ደም ይዞ በየዓመቱ ወደ ቅዱሱ ስፍራ ይገባ እንደነበረው ራሱን ብዙ ጊዜ መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ አይደለም።+ 26 አለዚያማ ዓለም ከተመሠረተ* ጀምሮ ብዙ ጊዜ መከራ መቀበል ባስፈለገው ነበር። አሁን ግን ራሱን መሥዋዕት አድርጎ በማቅረብ ኃጢአትን ለማስወገድ በሥርዓቶቹ* መደምደሚያ ላይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ራሱን ገልጧል።+ 27 ሰው ሁሉ አንድ ጊዜ መሞቱ አይቀርም፤ ከዚያ በኋላ ግን ፍርድ ይቀበላል፤ 28 በተመሳሳይም ክርስቶስ የብዙዎችን ኃጢአት ለመሸከም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መሥዋዕት ሆኖ ቀርቧል፤+ ለሁለተኛ ጊዜ የሚገለጠውም ኃጢአትን ለማስወገድ አይደለም፤ መዳን ለማግኘት እሱን በጉጉት የሚጠባበቁትም ያዩታል።+
10 ሕጉ ወደፊት ለሚመጡት መልካም ነገሮች ጥላ+ ነው እንጂ የእነዚህ ነገሮች እውነተኛ አካል አይደለም፤ ስለዚህ ሕጉ ከዓመት ዓመት እነዚያኑ መሥዋዕቶች በማቅረብ አምላክን የሚያመልኩትን ሰዎች ፍጹም ሊያደርጋቸው አይችልም።*+ 2 ቢችልማ ኖሮ መሥዋዕት ማቅረቡን ይተዉት አልነበረም? ምክንያቱም ቅዱስ አገልግሎት የሚያቀርቡት ሰዎች አንዴ ከነጹ በኋላ ሕሊናቸው በጥፋተኝነት ስሜት አይወቅሳቸውም ነበር። 3 ይሁንና እነዚህ መሥዋዕቶች ከዓመት ዓመት ኃጢአት እንዲታወስ ያደርጋሉ፤+ 4 የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን ማስወገድ አይችልምና።
5 ስለዚህ ወደ ዓለም በመጣ ጊዜ እንዲህ አለ፦ “‘መሥዋዕትንና መባን አልፈለግክም፤ ከዚህ ይልቅ አካል አዘጋጀህልኝ። 6 ሙሉ በሙሉ በሚቃጠል መባና ለኃጢአት በሚቀርብ መባ ደስ አልተሰኘህም።’+ 7 በዚህ ጊዜ ‘እነሆ፣ አምላክ ሆይ፣ (ስለ እኔ በመጽሐፍ ጥቅልል እንደተጻፈ) ፈቃድህን ለማድረግ መጥቻለሁ’ አልኩ።”+ 8 በመጀመሪያ እንዲህ አለ፦ “መሥዋዕትን፣ መባን፣ ሙሉ በሙሉ የሚቃጠል መባንና ለኃጢአት የሚቀርብ መባን አልፈለግክም፤ እንዲሁም ደስ አልተሰኘህበትም።” እነዚህ መሥዋዕቶች ሕጉ በሚያዝዘው መሠረት የሚቀርቡ ናቸው። 9 ከዚያም “እነሆ፣ ፈቃድህን ለማድረግ መጥቻለሁ” አለ።+ ሁለተኛውን ለማቋቋም የመጀመሪያውን ያስወግዳል። 10 በዚህ “ፈቃድ”+ መሠረት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መሥዋዕት ሆኖ በቀረበው የኢየሱስ ክርስቶስ አካል አማካኝነት ተቀድሰናል።+
11 በተጨማሪም እያንዳንዱ ካህን ቅዱስ አገልግሎት ለማቅረብና*+ ኃጢአትን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ የማይችሉትን+ እነዚያኑ መሥዋዕቶች በየጊዜው ለማቅረብ+ ዕለት ዕለት በቦታው ይገኛል። 12 ይህ ሰው ግን ስለ ኃጢአት ለሁልጊዜ የሚሆን አንድ መሥዋዕት አቅርቦ በአምላክ ቀኝ ተቀምጧል፤+ 13 ከዚያን ጊዜ አንስቶ ጠላቶቹ የእግሩ መርገጫ እስኪደረጉ ድረስ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል።+ 14 እነዚያን የሚቀደሱትን ለሁልጊዜ ፍጹማን ያደረጋቸው አንድ መሥዋዕት በማቅረብ ነውና።+ 15 ከዚህ በተጨማሪ መንፈስ ቅዱስም ስለ እኛ ይመሠክራል፤ በመጀመሪያ እንዲህ ይላልና፦ 16 “‘ከዚያ ጊዜ በኋላ ከእነሱ ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነው’ ይላል ይሖዋ።* ‘ሕግጋቴን በልባቸው ውስጥ አኖራለሁ፤ በአእምሯቸውም ላይ እጽፋቸዋለሁ።’”+ 17 በመቀጠልም “ኃጢአታቸውንና የዓመፅ ድርጊታቸውንም ከእንግዲህ ወዲህ አላስታውስም” ይላል።+ 18 እንግዲህ እነዚህ ይቅር ከተባሉ፣ ከዚህ በኋላ ለኃጢአት መባ ማቅረብ አያስፈልግም።
19 ስለዚህ ወንድሞች፣ በኢየሱስ ደም አማካኝነት ወደ ቅዱሱ ስፍራ በሚወስደው መንገድ ለመግባት የሚያስችል ድፍረት* አግኝተናል፤+ 20 እሱ የከፈተልን* ይህ መንገድ ወደ ሕይወት የሚመራ አዲስ መንገድ ነው። ይህን ያደረገው በመጋረጃው+ ማለትም በሥጋው በኩል በማለፍ ነው፤ 21 በተጨማሪም በአምላክ ቤት ላይ የተሾመ ታላቅ ሊቀ ካህናት ስላለን+ 22 ከክፉ ሕሊና ለመንጻት+ ልባችንን ተረጭተን እንዲሁም ሰውነታችንን በንጹሕ ውኃ ታጥበን+ በቅን ልቦና እና በሙሉ እምነት ወደ አምላክ እንቅረብ። 23 የተስፋን ቃል የሰጠው የታመነ ስለሆነ ተስፋችንን በይፋ ለማወጅ የሚያስችለንን አጋጣሚ ያላንዳች ማወላወል አጥብቀን እንያዝ።+ 24 እንዲሁም እርስ በርስ ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች መነቃቃት* እንድንችል አንዳችን ለሌላው ትኩረት እንስጥ፤*+ 25 አንዳንዶች ልማድ እንዳደረጉት መሰብሰባችንን* ቸል አንበል፤+ ከዚህ ይልቅ እርስ በርስ እንበረታታ፤+ ደግሞም ቀኑ እየቀረበ መምጣቱን ስናይ ከበፊቱ ይበልጥ ይህን እናድርግ።+
26 የእውነትን ትክክለኛ እውቀት ካገኘን በኋላ ሆን ብለን በኃጢአት ጎዳና ብንመላለስ+ ለኃጢአታችን የሚቀርብ ሌላ መሥዋዕት አይኖርም፤+ 27 ከዚህ ይልቅ አስፈሪ ፍርድ ይጠብቀናል፤ አምላክን የሚቃወሙትን የሚበላ የሚነድ ቁጣም ይኖራል።+ 28 የሙሴን ሕግ የጣሰ ማንኛውም ሰው ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች ከመሠከሩበት ያለርኅራኄ ይገደል ነበር።+ 29 ታዲያ የአምላክን ልጅ የረገጠ፣ የተቀደሰበትን የቃል ኪዳኑን ደም+ እንደ ተራ ነገር የቆጠረና የጸጋን መንፈስ በንቀት ያጥላላ ሰው ምን ያህል የከፋ ቅጣት የሚገባው ይመስላችኋል?+ 30 “በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ” ያለውን እናውቀዋለንና። ደግሞም “ይሖዋ* ሕዝቡን ይዳኛል።”+ 31 በሕያው አምላክ እጅ መውደቅ የሚያስፈራ ነገር ነው።
32 ይሁን እንጂ ብርሃን ከበራላችሁ በኋላ+ በመከራ ውስጥ በከፍተኛ ተጋድሎ የጸናችሁበትን የቀድሞውን ጊዜ ዘወትር አስታውሱ። 33 በአደባባይ ለነቀፋና ለመከራ የተጋለጣችሁባቸው* ጊዜያት ነበሩ፤ ደግሞም እንዲህ ዓይነት ሁኔታ የደረሰባቸውን ሰዎች መከራ የተጋራችሁባቸው* ጊዜያት ነበሩ። 34 እናንተ ራሳችሁ የተሻለና ዘላቂ የሆነ ንብረት እንዳላችሁ ስለምታውቁ+ በእስር ላይ ላሉት ራራችሁላቸው፤ እንዲሁም ንብረታችሁ ሲዘረፍ ሁኔታውን በደስታ ተቀበላችሁ።+
35 እንግዲህ ትልቅ ወሮታ የሚያስገኘውን በድፍረት የመናገር ነፃነታችሁን አሽቀንጥራችሁ አትጣሉት።+ 36 የአምላክን ፈቃድ ከፈጸማችሁ በኋላ የተስፋው ቃል ሲፈጸም ማየት እንድትችሉ መጽናት ያስፈልጋችኋልና።+ 37 ምክንያቱም “ለጥቂት ጊዜ ነው”+ እንጂ “የሚመጣው እሱ ይመጣል፤ ደግሞም አይዘገይም።”+ 38 “ሆኖም ጻድቅ አገልጋዬ በእምነት ይኖራል”፤+ ደግሞም “ወደኋላ ቢያፈገፍግ በእሱ ደስ አልሰኝም።”*+ 39 እንግዲህ እኛ በሕይወት የሚያኖር* እምነት እንዳላቸው ሰዎች ነን እንጂ ወደ ጥፋት እንደሚያፈገፍጉ ሰዎች አይደለንም።+
11 እምነት ተስፋ የተደረጉትን ነገሮች በእርግጠኝነት መጠበቅ ማለት ነው፤+ በተጨማሪም የምናምንበት ነገር በዓይን የሚታይ ባይሆንም እውን መሆኑን የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ ነው። 2 በጥንት ዘመን የኖሩት ሰዎች* የተመሠከረላቸው በዚህ አማካኝነት ነው።
3 ሥርዓቶቹ* የተቋቋሙት በአምላክ ቃል መሆኑን የምንረዳው በእምነት ነው፤ በመሆኑም የሚታየው ነገር ወደ ሕልውና የመጣው ከማይታዩ ነገሮች ነው።
4 አቤል፣ ቃየን ካቀረበው የበለጠ ዋጋ ያለው መሥዋዕት ለአምላክ በእምነት አቀረበ፤+ አምላክ ስጦታውን ስለተቀበለ* በዚህ እምነቱ የተነሳ ጻድቅ እንደሆነ ተመሥክሮለታል፤+ ቢሞትም እንኳ በእምነቱ አማካኝነት አሁንም ይናገራል።+
5 ሄኖክ+ ሞትን እንዳያይ በእምነት ወደ ሌላ ቦታ ተወሰደ፤ አምላክ ወደ ሌላ ቦታ ስለወሰደውም የትም ቦታ ሊገኝ አልቻለም፤+ ከመወሰዱ በፊት አምላክን በሚገባ ደስ እንዳሰኘ ተመሥክሮለት ነበርና። 6 በተጨማሪም ያለእምነት አምላክን በሚገባ ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ አምላክ የሚቀርብ ሁሉ እሱ መኖሩንና ከልብ ለሚፈልጉትም ወሮታ ከፋይ መሆኑን ማመን ይኖርበታልና።+
7 ኖኅ+ ገና ስላልታዩት ነገሮች መለኮታዊ ማስጠንቀቂያ ከተቀበለ በኋላ+ አምላካዊ ፍርሃት ያሳየውና ቤተሰቡን ለማዳን መርከብ የሠራው በእምነት ነበር፤+ በዚህ እምነት አማካኝነትም ዓለምን ኮንኗል፤+ እንዲሁም በእምነት የሚገኘውን ጽድቅ ለመውረስ በቅቷል።
8 አብርሃም+ በተጠራ ጊዜ ወደፊት ርስት አድርጎ ወደሚቀበለው ስፍራ በመሄድ በእምነት ታዘዘ፤ ወዴት እንደሚሄድ ባያውቅም ይኖርበት የነበረውን ስፍራ ለቆ ወጣ።+ 9 በባዕድ አገር እንደሚኖር እንግዳ በተስፋይቱ ምድር በእምነት ኖረ፤+ ደግሞም አብረውት የዚሁ ተስፋ ቃል ወራሾች ከሆኑት ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር+ በድንኳን ኖረ።+ 10 አምላክ ንድፍ ያወጣላትንና የገነባትን፣ እውነተኛ መሠረት ያላትን ከተማ ይጠባበቅ ነበርና።+
11 ሣራም የተስፋን ቃል የሰጠው እሱ ታማኝ* እንደሆነ አድርጋ ስላሰበች ዕድሜዋ ካለፈ በኋላም እንኳ ዘር ለመፀነስ በእምነት ኃይል አገኘች።+ 12 ከዚህም የተነሳ እንደሞተ ያህል ከሚቆጠረው+ ከአንድ ሰው እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዙና በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ የማይቆጠሩ ልጆች ተወለዱ።+
13 እነዚህ ሁሉ የተስፋውን ቃል ፍጻሜ ባያዩም እምነታቸውን እንደጠበቁ ሞቱ፤+ ሆኖም ከሩቅ አይተው በደስታ ተቀበሉት፤+ በምድሩም ላይ እንግዶችና ጊዜያዊ ነዋሪዎች መሆናቸውን በይፋ ተናገሩ። 14 እንዲህ ብለው የሚናገሩት ሰዎች የራሳቸው የሆነ ቦታ ለማግኘት ከልብ እንደሚሹ ያሳያሉ። 15 ይሁንና ትተውት የወጡትን ቦታ ሁልጊዜ ቢያስቡ ኖሮ+ መመለስ የሚችሉበት አጋጣሚ በኖራቸው ነበር። 16 አሁን ግን የተሻለውን ይኸውም ከሰማይ የሆነውን ስፍራ ለማግኘት ይጣጣራሉ። ስለዚህ አምላክ፣ እሱን አምላካችን ብለው ቢጠሩት አያፍርባቸውም፤+ ከተማን አዘጋጅቶላቸዋልና።+
17 አብርሃም በተፈተነ ጊዜ+ ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ እስከ ማቅረብ ድረስ እምነት አሳይቷል፤ የተስፋን ቃል በደስታ የተቀበለው ይህ ሰው አንድያ ልጁን መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ ተዘጋጅቶ ነበር፤+ 18 ይህን ያደረገው “ዘርህ የሚጠራልህ በይስሐቅ በኩል ይሆናል” ተብሎ ተነግሮት እያለ ነው።+ 19 ይሁንና አምላክ ከሞት እንኳ ሳይቀር ሊያስነሳው እንደሚችል ተገንዝቦ ነበር፤ ልጁንም ከሞት አፋፍ መልሶ አገኘው፤ ይህም እንደ ምሳሌ ሆኖ አገልግሏል።+
20 ይስሐቅም ወደፊት ከሚሆኑት ነገሮች ጋር በተያያዘ ያዕቆብንና+ ኤሳውን+ በእምነት ባረካቸው።
21 ያዕቆብ መሞቻው በተቃረበ ጊዜ+ የዮሴፍን ልጆች እያንዳንዳቸውን የባረካቸውና+ የበትሩን ጫፍ ተመርኩዞ ለአምላክ የሰገደው በእምነት ነበር።+
22 ዮሴፍ ሊሞት በተቃረበ ጊዜ ስለ እስራኤል ልጆች ከግብፅ መውጣት* በእምነት ተናገረ፤ ስለ አፅሙም* መመሪያ* ሰጣቸው።+
23 ሙሴ ከተወለደ በኋላ ወላጆቹ መልኩ የሚያምር ሕፃን+ መሆኑን ስላዩ የንጉሡን ትእዛዝ ሳይፈሩ+ ለሦስት ወር የሸሸጉት+ በእምነት ነበር። 24 ሙሴ ካደገ በኋላ+ የፈርዖን የልጅ ልጅ* ተብሎ ለመጠራት በእምነት እንቢ አለ፤+ 25 በኃጢአት ከሚገኝ ጊዜያዊ ደስታ ይልቅ ከአምላክ ሕዝብ ጋር መንገላታትን መረጠ፤ 26 ምክንያቱም ቅቡዕ* ሆኖ የሚደርስበት ነቀፋ በግብፅ ከሚገኝ ውድ ሀብት የላቀ እንደሆነ አስቧል፤ የሚከፈለውን ወሮታ በትኩረት ተመልክቷልና። 27 ደግሞም በእምነት ግብፅን ለቆ ወጣ፤+ ሆኖም ይህን ያደረገው የንጉሡን ቁጣ ፈርቶ አይደለም፤+ የማይታየውን አምላክ+ እንደሚያየው አድርጎ በጽናት ቀጥሏልና። 28 አጥፊው የበኩር ልጆቻቸውን እንዳይገድል* ሙሴ ፋሲካን* ያከበረውና መቃኖቹ ላይ ደም የረጨው በእምነት ነው።+
29 እስራኤላውያን በደረቅ ምድር የሚሄዱ ያህል ቀይ ባሕርን በእምነት ተሻገሩ፤+ ይሁንና ግብፃውያን እንዲህ ለማድረግ በሞከሩ ጊዜ ሰመጡ።+
30 እስራኤላውያን የኢያሪኮን ግንብ ሰባት ቀን ከዞሩት በኋላ በእምነት ወደቀ።+ 31 ዝሙት አዳሪዋ ረዓብ ታዛዥ ሳይሆኑ ከቀሩት ሰዎች ጋር ከመጥፋት የዳነችው በእምነት ነው፤ ምክንያቱም ሰላዮቹን በሰላም ተቀብላለች።+
32 እንግዲህ ከዚህ በላይ ምን እላለሁ? ስለ ጌድዮን፣+ ስለ ባርቅ፣+ ስለ ሳምሶን፣+ ስለ ዮፍታሔ፣+ ስለ ዳዊት+ እንዲሁም ስለ ሳሙኤልና+ ስለ ሌሎቹ ነቢያት እንዳልተርክ ጊዜ ያጥረኛል። 33 እነዚህ ሰዎች በእምነት መንግሥታትን ድል አድርገዋል፤+ ጽድቅን አስፍነዋል፤ የተስፋን ቃል ተቀብለዋል፤+ የአንበሶችን አፍ ዘግተዋል፤+ 34 የእሳትን ኃይል አጥፍተዋል፤+ ከሰይፍ ስለት አምልጠዋል፤+ ደካማ የነበሩት ብርታት አግኝተዋል፤+ በጦርነት ኃያላን ሆነዋል፤+ ወራሪ ሠራዊትን አባረዋል።+ 35 ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀብለዋል፤+ ሌሎች ወንዶች ግን ቤዛ ተከፍሎላቸው ነፃ መሆን ስላልፈለጉ ከባድ ሥቃይ ደርሶባቸዋል፤ ይህን ያደረጉት የተሻለ ትንሣኤ ለማግኘት ሲሉ ነው። 36 አዎ፣ ሌሎች ደግሞ መዘባበቻ በመሆንና በመገረፍ ይባስ ብሎም በመታሰርና ወህኒ ቤት በመጣል+ ፈተና ደርሶባቸዋል። 37 በድንጋይ ተወግረዋል፤+ ተፈትነዋል፤ በመጋዝ ለሁለት ተሰንጥቀዋል፤ በሰይፍ ተቀልተዋል፤+ እየተቸገሩ፣ መከራ እየተቀበሉና+ እየተንገላቱ+ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ተንከራተዋል፤+ 38 ዓለም እንዲህ ዓይነት ሰዎች የሚገቡት ሆኖ አልተገኘም። በየበረሃው፣ በየተራራው፣ በየዋሻውና+ በምድር ውስጥ ባሉ ጉድጓዶች ተቅበዝብዘዋል።
39 ይሁንና እነዚህ ሁሉ በእምነታቸው ምክንያት በመልካም የተመሠከረላቸው ቢሆኑም እንኳ የተስፋውን ቃል ፍጻሜ አላዩም፤ 40 ምክንያቱም አምላክ ያለእኛ ወደ ፍጽምና እንዲደርሱ ዓላማው ስላልነበረ ለእኛ የተሻለ ነገር ለመስጠት አስቀድሞ አስቧል።+
12 እንግዲያው እንዲህ ያለ ታላቅ የምሥክሮች ደመና በዙሪያችን ስላለልን እኛም ማንኛውንም ሸክምና በቀላሉ ተብትቦ የሚይዘንን ኃጢአት+ ከላያችን አንስተን እንጣል፤ ከፊታችን የሚጠብቀንን ሩጫም በጽናት እንሩጥ፤+ 2 የምንሮጠውም የእምነታችን “ዋና ወኪል”* እና “ፍጹም አድራጊ” የሆነውን ኢየሱስን በትኩረት በመመልከት ነው።+ እሱ ከፊቱ ለሚጠብቀው ደስታ ሲል፣ የሚደርስበትን ውርደት ከምንም ሳይቆጥር በመከራ እንጨት* ላይ እስከ መሞት ድረስ ጸንቷል፤ እንዲሁም በአምላክ ዙፋን ቀኝ ተቀምጧል።+ 3 እንግዲህ እንዳትደክሙና ተስፋ እንዳትቆርጡ*+ ኃጢአተኞች የራሳቸውን ጥቅም በመጻረር የሚያሰሙትን እንዲህ ዓይነቱን የተቃውሞ ንግግር በጽናት የተቋቋመውን+ እሱን በጥሞና አስቡ።
4 እናንተ ከዚህ ኃጢአት ጋር እያደረጋችሁ ባላችሁት ትግል ደማችሁ እስኪፈስ ድረስ ገና አልታገላችሁም። 5 ደግሞም ልጆች እንደመሆናችሁ መጠን የተሰጣችሁን የሚከተለውን ማሳሰቢያ ሙሉ በሙሉ ረስታችኋል፦ “ልጄ ሆይ፣ ይሖዋ* የሚሰጥህን ተግሣጽ አቅልለህ አትመልከት፤ በሚያርምህም ጊዜ ተስፋ አትቁረጥ፤ 6 ይሖዋ* የሚወዳቸውን ይገሥጻልና፤ እንዲያውም እንደ ልጁ አድርጎ የሚቀበለውን ሁሉ ይቀጣል።”*+
7 ተግሣጽ የምትቀበሉበት* አንዱ መንገድ ይህ ስለሆነ መከራ ሲደርስባችሁ መጽናት ያስፈልጋችኋል። አምላክ የያዛችሁ እንደ ልጆቹ አድርጎ ነው።+ ለመሆኑ አባቱ የማይገሥጸው ልጅ ማን ነው?+ 8 ሆኖም ሁላችሁም ይህን ተግሣጽ ካልተቀበላችሁ ዲቃላዎች ናችሁ እንጂ ልጆች አይደላችሁም። 9 ከዚህም በላይ ሰብዓዊ አባቶቻችን ይገሥጹን ነበር፤ እኛም እናከብራቸው ነበር። ታዲያ የመንፈሳዊ ሕይወታችን አባት ለሆነው ይበልጥ በፈቃደኝነት በመገዛት በሕይወት ልንኖር አይገባም?+ 10 እነሱ መልካም መስሎ በታያቸው መንገድ ለጥቂት ጊዜ ገሥጸውናል፤ እሱ ግን ከቅድስናው ተካፋዮች እንድንሆን+ ለጥቅማችን ሲል ይገሥጸናል። 11 እርግጥ ነው፣ ማንኛውም ተግሣጽ ለጊዜው የሚያስደስት አይመስልም፤ ይልቁንም ያስከፋል፤* በኋላ ግን በተግሣጽ ሥልጠና ላገኙ ሰዎች የጽድቅን ሰላማዊ ፍሬ ያፈራላቸዋል።
12 ስለዚህ የዛሉትን እጆችና የተብረከረኩትን ጉልበቶች አበርቱ፤+ 13 የተጎዳው የአካል ክፍል እንዲፈወስ እንጂ እንዳይናጋ እግራችሁ ዘወትር ቀና በሆነ መንገድ እንዲጓዝ አድርጉ።+ 14 ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር ጥረት አድርጉ፤+ ቅድስናንም ፈልጉ፤+ ያለቅድስና ማንም ሰው ጌታን ማየት አይችልም። 15 ማንም የአምላክን ጸጋ እንዳያጣ ብሎም መርዛማ ሥር በቅሎ ችግር እንዳይፈጥርና ብዙዎችን እንዳይበክል ተጠንቀቁ፤+ 16 በተጨማሪም በመካከላችሁ ሴሰኛ* ሰውም ሆነ ለአንድ ጊዜ መብል ሲል የብኩርና መብቱን አሳልፎ እንደሰጠው እንደ ኤሳው ቅዱስ ነገሮችን የማያደንቅ ሰው እንዳይገኝ ተጠንቀቁ።+ 17 ኤሳው የኋላ ኋላ በረከቱን ለመውረስ በፈለገ ጊዜ እንደተከለከለ ታውቃላችሁና፤ ሐሳብ ለማስቀየር* እያለቀሰ ብርቱ ጥረት ቢያደርግም+ እንኳ አልተሳካለትም።
18 እናንተ እኮ የቀረባችሁት ሊዳሰስ ወደሚችለውና+ በእሳት ወደተያያዘው ተራራ፣+ ወደ ጥቁሩ ደመና፣ ወደ ድቅድቁ ጨለማ፣ ወደ አውሎ ነፋሱ፣+ 19 ወደ መለከት ድምፁና+ ቃል ያሰማ ወደነበረው ድምፅ+ አይደለም፤ ሕዝቡ ይህን ሲሰሙ ሌላ ተጨማሪ ነገር እንዳይነገራቸው ለምነው ነበር።+ 20 “እንስሳ እንኳ ተራራውን ቢነካ በድንጋይ ተወግሮ ይሙት” የሚለው ትእዛዝ በጣም አስፈርቷቸው ነበርና።+ 21 በተጨማሪም በዚያ ይታይ የነበረው ነገር በጣም አስፈሪ ስለነበረ ሙሴ “ፈራሁ፤ ተንቀጠቀጥኩም” ሲል ተናግሯል።+ 22 እናንተ ግን የቀረባችሁት ወደ ጽዮን ተራራና+ የሕያው አምላክ ከተማ ወደሆነችው ወደ ሰማያዊቱ ኢየሩሳሌም፣+ አንድ ላይ ወደተሰበሰቡ አእላፋት* መላእክት፣ 23 በሰማያት ወደተመዘገበው የበኩራት ጉባኤ፣+ የሁሉ ፈራጅ ወደሆነው አምላክ፣+ ፍጽምና እንዲያገኙ ወደተደረጉት+ ጻድቃን መንፈሳዊ ሕይወት፣+ 24 የአዲስ ቃል ኪዳን+ መካከለኛ ወደሆነው ወደ ኢየሱስና+ ከአቤል ደም በተሻለ ሁኔታ ወደሚናገረው ወደተረጨው ደም ነው።+
25 እየተናገረ ያለውን እሱን ከመስማት ወደኋላ እንዳትሉ* ተጠንቀቁ። በምድር ላይ መለኮታዊ ማስጠንቀቂያ ይሰጣቸው የነበረውን ከመስማት ወደኋላ ያሉት ሰዎች ከቅጣት ካላመለጡ ታዲያ እኛ ከሰማይ የሚናገረውን እሱን ከመስማት ዞር ብንል እንዴት እናመልጣለን?+ 26 በዚያን ጊዜ ድምፁ ምድርን አናውጦ ነበር፤+ አሁን ግን “ምድርን ብቻ ሳይሆን ሰማይን ጭምር እንደገና አናውጣለሁ” ሲል ቃል ገብቷል።+ 27 እንግዲህ “እንደገና” የሚለው አባባል የማይናወጡት ነገሮች ጸንተው ይኖሩ ዘንድ የሚናወጡት ይኸውም የተሠሩት ነገሮች የሚወገዱ መሆናቸውን ያመለክታል። 28 ስለዚህ እኛ ሊናወጥ የማይችል መንግሥት ልንቀበል እንደሆነ ስለምናውቅ ጸጋውን መቀበላችንን እንቀጥል፤ ይህም በጸጋው አማካኝነት በአምላካዊ ፍርሃትና በጥልቅ አክብሮት፣ ተቀባይነት ባለው መንገድ ለአምላክ ቅዱስ አገልግሎት ማቅረብ እንችል ዘንድ ነው። 29 አምላካችን የሚባላ እሳት ነውና።+
13 እርስ በርሳችሁ እንደ ወንድማማች መዋደዳችሁን ቀጥሉ።+ 2 እንግዳ መቀበልን* አትርሱ፤+ አንዳንዶች ይህን ሲያደርጉ ሳያውቁት መላእክትን አስተናግደዋልና።+ 3 በእስር ላይ ያሉትን ከእነሱ ጋር ታስራችሁ እንዳላችሁ አድርጋችሁ በማሰብ+ ሁልጊዜ አስታውሷቸው፤+ እናንተም ራሳችሁ ገና በሥጋ ያላችሁ በመሆናችሁ* እንግልት እየደረሰባቸው ያሉትን አስቡ። 4 ጋብቻ በሁሉ ዘንድ ክቡር፣ መኝታውም ከርኩሰት የጸዳ ይሁን፤+ አምላክ ሴሰኞችንና* አመንዝሮችን ይፈርድባቸዋልና።+ 5 አኗኗራችሁ ከገንዘብ ፍቅር ነፃ ይሁን፤+ ባሏችሁ ነገሮች ረክታችሁ ኑሩ።+ እሱ “ፈጽሞ አልተውህም፤ በምንም ዓይነት አልጥልህም” ብሏልና።+ 6 ስለዚህ በሙሉ ልብ “ይሖዋ* ረዳቴ ነው፤ አልፈራም። ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?” እንላለን።+
7 የአምላክን ቃል የነገሯችሁን በመካከላችሁ ሆነው አመራር የሚሰጡትን አስቡ፤+ ደግሞም ምግባራቸው ያስገኘውን ውጤት በሚገባ በማጤን በእምነታቸው ምሰሏቸው።+
8 ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትም፣ ዛሬም፣ ለዘላለምም ያው ነው።
9 በልዩ ልዩና እንግዳ በሆኑ ትምህርቶች አትወሰዱ፤ ልባችን በምግብ* ሳይሆን በአምላክ ጸጋ ቢጠናከር መልካም ነውና፤ በዚህ የተጠመዱ ምንም አልተጠቀሙም።+
10 እኛ መሠዊያ ያለን ሲሆን በድንኳኑ ውስጥ ቅዱስ አገልግሎት የሚያቀርቡት ከመሠዊያው ላይ ወስደው መብላት አይፈቀድላቸውም።+ 11 ምክንያቱም ሊቀ ካህናቱ የእንስሳቱን ደም የኃጢአት መባ አድርጎ ወደ ቅዱሱ ስፍራ* የሚወስደው ሲሆን ሥጋው ግን ከሰፈሩ ውጭ ይቃጠላል።+ 12 ስለዚህ ኢየሱስም ሕዝቡን በገዛ ራሱ ደም ለመቀደስ+ ከከተማው በር ውጭ መከራ ተቀበለ።+ 13 እንግዲህ እኛም እሱ የተሸከመውን ነቀፋ ተሸክመን ከሰፈር ውጭ እሱ ወዳለበት እንሂድ፤+ 14 በዚህ ቋሚ ከተማ የለንምና፤ ከዚህ ይልቅ ወደፊት የምትመጣዋን ከተማ በጉጉት እንጠባበቃለን።+ 15 ስለዚህ በኢየሱስ አማካኝነት የውዳሴ መሥዋዕት ዘወትር ለአምላክ እናቅርብ፤+ ይህም ስሙን በይፋ የምናውጅበት+ የከንፈራችን ፍሬ ነው።+ 16 በተጨማሪም መልካም ማድረግንና ያላችሁን ነገር ለሌሎች ማካፈልን አትርሱ፤+ አምላክ እንዲህ ባሉት መሥዋዕቶች እጅግ ይደሰታልና።+
17 ተግተው ስለሚጠብቋችሁና* ይህን በተመለከተ ስሌት ስለሚያቀርቡ+ በመካከላችሁ ሆነው አመራር ለሚሰጧችሁ ታዘዙ+ እንዲሁም ተገዙ፤+ ይህን የምታደርጉት ሥራቸውን በደስታ እንጂ በሐዘን እንዳያከናውኑ ነው፤ አለዚያ ሥራቸውን የሚያከናውኑት በሐዘን ይሆናል፤ ይህ ደግሞ እናንተን ይጎዳችኋል።
18 ለእኛ መጸለያችሁን ቀጥሉ፤ ምክንያቱም ሐቀኛ* ሕሊና እንዳለን እናምናለን፤ ደግሞም በሁሉም ነገር በሐቀኝነት ለመኖር እንፈልጋለን።+ 19 በተለይ ደግሞ ወደ እናንተ በፍጥነት ተመልሼ እንድመጣ ትጸልዩልኝ ዘንድ አሳስባችኋለሁ።
20 እንግዲያው ታላቅ የበጎች እረኛ+ የሆነው ጌታችን ኢየሱስ የዘላለማዊውን ቃል ኪዳን ደም ይዞ ከሞት እንዲነሳ ያደረገው የሰላም አምላክ 21 ፈቃዱን እንድታደርጉ በመልካም ነገር ሁሉ ያስታጥቃችሁ፤ እሱ በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን ነገር እንድናደርግ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ያነሳሳናል። ለእሱ ለዘላለም ክብር ይሁን። አሜን።
22 እንግዲህ ወንድሞች፣ የጻፍኩላችሁ ደብዳቤ አጭር ስለሆነ ይህን የማበረታቻ ቃል በትዕግሥት እንድታዳምጡ አሳስባችኋለሁ። 23 ወንድማችን ጢሞቴዎስ መፈታቱን እንድታውቁ እፈልጋለሁ። ቶሎ ከመጣ አብረን መጥተን እናያችኋለን።
24 በመካከላችሁ ሆነው አመራር ለሚሰጧችሁ ሁሉና ለቀሩት ቅዱሳን ሁሉ ሰላምታ አቅርቡልኝ። በጣሊያን+ ያሉት ሰላምታ ልከውላችኋል።
25 የአምላክ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን።
ወይም “ዘመናትን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ቃል በቃል “ሰዎች ወደሚኖሩበት ምድር።”
ወይም “እጅ ይንሱት።”
ወይም “የሕዝብ አገልጋዮቹን።”
ወይም “የፍትሕ።”
በዳዊት የዘር ሐረግ የነበሩ ሌሎች ነገሥታትን ያመለክታል።
ወይም “ሕዝባዊ አገልግሎት።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “የሕዝቡን ኃጢአት ለማስተሰረይ።”
ኢየሱስን ያመለክታል።
ወይም “ከክርስቶስ ጋር አብረን የምንካፈለው።”
ቃል በቃል “እንፍራ።”
ይህ አባባል የአዳምንና የሔዋንን ዘሮች ያመለክታል።
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “የመናገር ነፃነት ተሰምቶን።”
ወይም “ለድክመት የተጋለጠ ስለሆነ።”
ወይም “በሥርዓት የማይሄዱትን።”
ወይም “በደግነት፤ በአግባቡ።”
ቃል በቃል “በሥጋው ቀናት።”
ቃል በቃል “ከጊዜው አንጻር።”
የግሪክኛው ቃል የጅምናስቲክ ስፖርተኛ የሚወስደውን ዓይነት ሥልጠና ያመለክታል።
ወይም “በሚመጣው ዘመን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ቃል በቃል “ኃይሎች።”
ወይም “በመርዳትም።”
ወይም “እኛ ለሕይወታችን።”
ቃል በቃል “አካፈለው።”
ወይም “ፓትሪያርክ።”
ወይም “ወደፊት የሚወለድ የአባቱ የአብርሃም ዘር።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “አይጸጸትም።”
ወይም “እንደ መያዣ የተሰጠ።”
ቅድስተ ቅዱሳኑን ያመለክታል።
ወይም “የሕዝብ አገልጋይ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “ሕዝባዊ አገልግሎት።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “የስርየት ስፍራውን።”
በምድር ላይ የነበረውን ድንኳን ያመለክታል።
በሰማይ የሚገኘውን ቅዱስ ስፍራ የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም።
ቃል በቃል “ከተለያዩ ጥምቀቶች።”
ቃል በቃል “ቤዛነት።”
ወይም “ቃል ኪዳን የሚያጋባው ወገን።”
ቃል በቃል “አልተመረቀም።”
ወይም “ጥቅልሉንና።”
ወይም “ሕዝባዊ አገልግሎት።”
ይህ አባባል የአዳምንና የሔዋንን ዘሮች ያመለክታል።
ወይም “በዘመናቱ።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
“ስለዚህ ሰዎች . . . ሊያደርጓቸው አይችሉም” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ሕዝባዊ አገልግሎት ለመስጠትና።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “የመተማመን ስሜት።”
ቃል በቃል “የመረቀልን።”
ወይም “አንዳችን ሌላውን ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች መቀስቀስ ወይም ማነሳሳት።”
ወይም “እናስብ።”
ለአምልኮ መሰብሰብን ያመለክታል።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ቃል በቃል “ቲያትር ላይ የቀረባችሁ ያህል የተጋለጣችሁባቸው።”
ወይም “እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ከደረሰባቸው ሰዎች ጎን የቆማችሁባቸው።”
ወይም “ነፍሴ በእሱ ደስ አትሰኝም።”
ወይም “ነፍስን ጠብቆ የሚያኖር።”
ወይም “አባቶቻችን።”
ወይም “ዘመናቱ።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “በመቀበል ምሥክርነት ስለሰጠ።”
ወይም “እምነት የሚጣልበት።”
እዚህ ላይ የገባው ግሪክኛ ቃል ለዘፀአት መጽሐፍ ከተሰጠው ግሪክኛ ስያሜ ጋር ተዛማጅነት አለው።
ወይም “ስለ ቀብሩም።”
ወይም “ትእዛዝ።”
ወይም “የፈርዖን ሴት ልጅ፣ ልጅ።”
በግሪክኛ “ክርስቶስ።”
ቃል በቃል “እንዳይነካ።”
ወይም “የማለፍ በዓልን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ቃል በቃል “ዋና መሪ።”
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “በነፍሳችሁ እንዳትዝሉ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ቃል በቃል “ይገርፋል።”
ወይም “ሥልጠና የምታገኙበት።”
ወይም “ያሳዝናል።”
የቃላት መፍቻው ላይ “የፆታ ብልግና” የሚለውን ተመልከት።
የአባቱን ሐሳብ ለማስቀየር ማለት ነው።
ወይም “በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ።”
ወይም “ላለመስማት ሰበብ እንዳትፈጥሩ፤ ከመስማት ቸል እንዳትሉ።”
ወይም “ለእንግዶች ደግነት ማሳየትን።”
“ከእነሱ ጋር መከራ የምትቀበሉ ያህል ሆናችሁ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
የቃላት መፍቻው ላይ “የፆታ ብልግና” የሚለውን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከምግብ ጋር የተያያዙ ደንቦችን ያመለክታል።
ቅድስተ ቅዱሳኑን ያመለክታል።
ወይም “ነፍሳችሁን ተግተው ስለሚጠብቁና።”
ቃል በቃል “ጥሩ።”