የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • nwt ዕዝራ 1:1-10:44
  • ዕዝራ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ዕዝራ
  • አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
ዕዝራ

ዕዝራ

1 በኤርምያስ በኩል የተነገረው የይሖዋ ቃል ይፈጸም ዘንድ+ የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ+ በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት የሚከተለውን አዋጅ በመላ ግዛቱ እንዲያውጅ ይሖዋ የፋርሱን ንጉሥ የቂሮስን መንፈስ አነሳሳ፤ እሱም ይህ በጽሑፍ እንዲሰፍር አደረገ፦+

2 “የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዲህ ይላል፦ ‘የሰማይ አምላክ ይሖዋ የምድርን መንግሥታት ሁሉ ሰጥቶኛል፤+ በይሁዳ በምትገኘው በኢየሩሳሌምም ቤት እንድሠራለት አዞኛል።+ 3 ከእሱ ሕዝብ መካከል የሆነ አብሯችሁ የሚኖር ማንኛውም ሰው አምላኩ ከእሱ ጋር ይሁን፤ እሱም በይሁዳ ወደምትገኘው ወደ ኢየሩሳሌም ይውጣ፤ ቤቱ በኢየሩሳሌም የሚገኘውን* የእስራኤልን አምላክ የይሖዋን ቤትም መልሶ ይገንባ፤ እሱ እውነተኛ አምላክ ነው። 4 በየትኛውም ስፍራ የባዕድ አገር ሰው ሆኖ የሚኖረውን+ ማንኛውንም ሰው፣ ጎረቤቶቹ* በኢየሩሳሌም ለነበረው ለእውነተኛው አምላክ ቤት ከሚቀርበው የፈቃደኝነት መባ+ በተጨማሪ ብር፣ ወርቅ፣ የተለያዩ ዕቃዎችና የቤት እንስሳት በመስጠት ይርዱት።’”

5 ከዚያም የይሁዳና የቢንያም የአባቶች ቤት መሪዎች፣ ካህናቱና ሌዋውያኑ፣ እውነተኛው አምላክ መንፈሳቸውን ያነሳሳው ሰዎች ሁሉ ወጥተው በኢየሩሳሌም የነበረውን የይሖዋን ቤት መልሰው ለመገንባት ተዘጋጁ። 6 በዙሪያቸው ያሉትም ሁሉ በፈቃደኝነት ከተሰጠው መባ በተጨማሪ የብርና የወርቅ ዕቃዎችን፣ የተለያዩ ዕቃዎችን፣ የቤት እንስሳትን እንዲሁም ውድ የሆኑ ነገሮችን በመስጠት ረዷቸው።*

7 በተጨማሪም ንጉሥ ቂሮስ፣ ናቡከደነጾር ከኢየሩሳሌም ወስዶ በአምላኩ ቤት ያስቀመጣቸውን የይሖዋን ቤት ዕቃዎች አወጣ።+ 8 የፋርሱ ንጉሥ ቂሮስ በግምጃ ቤቱ ኃላፊ በሚትረዳት ተቆጣጣሪነት ዕቃዎቹ እንዲወጡ አደረገ፤ ሚትረዳትም ለይሁዳው አለቃ ለሸሽባጻር*+ ቆጥሮ አስረከበው።

9 የተቆጠሩት ዕቃዎች ዝርዝር የሚከተለው ነው፦ በቅርጫት ቅርጽ የተሠሩ 30 የወርቅ ዕቃዎች፣ በቅርጫት ቅርጽ የተሠሩ 1,000 የብር ዕቃዎችና 29 ምትክ ዕቃዎች 10 እንዲሁም 30 ትናንሽ ጎድጓዳ የወርቅ ሳህኖች፣ 410 አነስተኛ ጎድጓዳ የብር ሳህኖችና 1,000 ሌሎች ዕቃዎች። 11 የወርቅና የብር ዕቃዎቹ በአጠቃላይ 5,400 ነበሩ። ሸሽባጻርም ግዞተኞቹ+ ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለሱ እነዚህን ዕቃዎች ሁሉ ይዞ ወጣ።

2 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር ወደ ባቢሎን በግዞት ወስዷቸው+ የነበሩትና ተማርከው በግዞት ከተወሰዱት+ መካከል ወጥተው በኋላ ላይ ወደ ኢየሩሳሌምና ወደ ይሁዳ ይኸውም ወደየከተሞቻቸው የተመለሱት የአውራጃው ነዋሪዎች እነዚህ ናቸው፤+ 2 ከዘሩባቤል፣+ ከየሆሹዋ፣+ ከነህምያ፣ ከሰራያህ፣ ከረኤላያህ፣ ከመርዶክዮስ፣ ከቢልሻን፣ ከሚስጳር፣ ከቢግዋይ፣ ከረሁምና ከባአናህ ጋር የመጡት እነዚህ ናቸው።

የእስራኤላውያን ወንዶች ቁጥር የሚከተሉትንም ይጨምራል፦+ 3 የፓሮሽ ወንዶች ልጆች 2,172፣ 4 የሰፋጥያህ ወንዶች ልጆች 372፣ 5 የኤራ+ ወንዶች ልጆች 775፣ 6 የየሹዋና የኢዮዓብ ወንዶች ልጆች የሆኑት የፓሃትሞአብ+ ወንዶች ልጆች 2,812፣ 7 የኤላም ወንዶች ልጆች+ 1,254፣ 8 የዛቱ ወንዶች ልጆች+ 945፣ 9 የዛካይ ወንዶች ልጆች 760፣ 10 የባኒ ወንዶች ልጆች 642፣ 11 የቤባይ ወንዶች ልጆች 623፣ 12 የአዝጋድ ወንዶች ልጆች 1,222፣ 13 የአዶኒቃም ወንዶች ልጆች 666፣ 14 የቢግዋይ ወንዶች ልጆች 2,056፣ 15 የአዲን ወንዶች ልጆች 454፣ 16 የሕዝቅያስ ልጅ የአጤር ወንዶች ልጆች 98፣ 17 የቤጻይ ወንዶች ልጆች 323፣ 18 የዮራ ወንዶች ልጆች 112፣ 19 የሃሹም ወንዶች ልጆች+ 223፣ 20 የጊባር ወንዶች ልጆች 95፣ 21 የቤተልሔም ወንዶች ልጆች 123፣ 22 የነጦፋ ወንዶች ልጆች 56፣ 23 የአናቶት+ ሰዎች 128፣ 24 የአዝማዌት ወንዶች ልጆች 42፣ 25 የቂርያትየአሪም፣ የከፊራና የበኤሮት ወንዶች ልጆች 743፣ 26 የራማና+ የጌባ+ ወንዶች ልጆች 621፣ 27 የሚክማስ ሰዎች 122፣ 28 የቤቴልና የጋይ+ ሰዎች 223፣ 29 የነቦ ወንዶች ልጆች+ 52፣ 30 የማግቢሽ ወንዶች ልጆች 156፣ 31 የሌላኛው ኤላም ወንዶች ልጆች 1,254፣ 32 የሃሪም ወንዶች ልጆች 320፣ 33 የሎድ፣ የሃዲድና የኦኖ ወንዶች ልጆች 725፣ 34 የኢያሪኮ ወንዶች ልጆች 345፣ 35 የሰናአ ወንዶች ልጆች 3,630።

36 ካህናቱ+ የሚከተሉት ናቸው፦ ከየሹዋ+ ቤተሰብ የሆነው የየዳያህ+ ወንዶች ልጆች 973፣ 37 የኢሜር+ ወንዶች ልጆች 1,052፣ 38 የጳስኮር+ ወንዶች ልጆች 1,247፣ 39 የሃሪም+ ወንዶች ልጆች 1,017።

40 ሌዋውያኑ+ የሚከተሉት ናቸው፦ የሆዳውያህ ወንዶች ልጆች የሆኑት የየሹዋና የቃድሚኤል+ ወንዶች ልጆች 74። 41 ዘማሪዎቹ+ የአሳፍ+ ወንዶች ልጆች 128። 42 የበር ጠባቂዎቹ+ ወንዶች ልጆች የሆኑት የሻሉም ወንዶች ልጆች፣ የአጤር ወንዶች ልጆች፣ የታልሞን+ ወንዶች ልጆች፣ የአቁብ+ ወንዶች ልጆች፣ የሃጢጣ ወንዶች ልጆችና የሾባይ ወንዶች ልጆች በአጠቃላይ 139።

43 የቤተ መቅደሱ አገልጋዮች*+ የሚከተሉት ናቸው፦ የጺሃ ወንዶች ልጆች፣ የሃሱፋ ወንዶች ልጆች፣ የታባኦት ወንዶች ልጆች፣ 44 የቀሮስ ወንዶች ልጆች፣ የሲአ ወንዶች ልጆች፣ የፓዶን ወንዶች ልጆች፣ 45 የለባና ወንዶች ልጆች፣ የሃጋባ ወንዶች ልጆች፣ የአቁብ ወንዶች ልጆች፣ 46 የሃጋብ ወንዶች ልጆች፣ የሳልማይ ወንዶች ልጆች፣ የሃናን ወንዶች ልጆች፣ 47 የጊዴል ወንዶች ልጆች፣ የጋሃር ወንዶች ልጆች፣ የረአያህ ወንዶች ልጆች፣ 48 የረጺን ወንዶች ልጆች፣ የነቆዳ ወንዶች ልጆች፣ የጋዛም ወንዶች ልጆች፣ 49 የዑዛ ወንዶች ልጆች፣ የፓሰአህ ወንዶች ልጆች፣ የቤሳይ ወንዶች ልጆች፣ 50 የአስና ወንዶች ልጆች፣ የመኡኒም ወንዶች ልጆች፣ የነፉሲም ወንዶች ልጆች፣ 51 የባቅቡቅ ወንዶች ልጆች፣ የሃቁፋ ወንዶች ልጆች፣ የሃርሑር ወንዶች ልጆች፣ 52 የባጽሉት ወንዶች ልጆች፣ የመሂዳ ወንዶች ልጆች፣ የሃርሻ ወንዶች ልጆች፣ 53  የባርቆስ ወንዶች ልጆች፣ የሲሳራ ወንዶች ልጆች፣ የተማ ወንዶች ልጆች፣ 54 የነጺሃ ወንዶች ልጆችና የሃጢፋ ወንዶች ልጆች።

55 የሰለሞን አገልጋዮች ወንዶች ልጆች የሚከተሉት ናቸው፦ የሶጣይ ወንዶች ልጆች፣ የሶፈረት ወንዶች ልጆች፣ የፐሩዳ+ ወንዶች ልጆች፣ 56 የያላ ወንዶች ልጆች፣ የዳርቆን ወንዶች ልጆች፣ የጊዴል ወንዶች ልጆች፣ 57  የሰፋጥያህ ወንዶች ልጆች፣ የሃጢል ወንዶች ልጆች፣ የፖክሄሬትሃጸባይም ወንዶች ልጆችና የአሚ ወንዶች ልጆች።

58 የቤተ መቅደሱ አገልጋዮችና* የሰለሞን አገልጋዮች ወንዶች ልጆች በአጠቃላይ 392 ነበሩ።

59 ከቴልመላ፣ ከቴልሃርሻ፣ ከከሩብ፣ ከአዳንና ከኢሜር የወጡት ሆኖም ከየትኛው የአባቶች ቤትና የዘር ሐረግ እንደመጡ በውል መለየትም ሆነ እስራኤላዊ መሆን አለመሆናቸውን በትክክል ማረጋገጥ ያልቻሉት የሚከተሉት ናቸው፦+ 60 የደላያህ ወንዶች ልጆች፣ የጦብያ ወንዶች ልጆችና የነቆዳ ወንዶች ልጆች 652። 61 ከካህናቱ ወንዶች ልጆች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦ የሃባያ ወንዶች ልጆች፣ የሃቆጽ+ ወንዶች ልጆች እንዲሁም ከጊልያዳዊው ከቤርዜሊ ሴቶች ልጆች መካከል አንዷን ያገባውና በስማቸው የተጠራው የቤርዜሊ+ ወንዶች ልጆች። 62 እነዚህ የዘር ሐረጋቸውን ለማረጋገጥ በመዝገቡ ላይ የቤተሰባቸውን ስም ለማግኘት ቢጥሩም ሊያገኙት አልቻሉም፤ በመሆኑም ከክህነት አገልግሎቱ ታገዱ።*+ 63 ገዢውም* በኡሪምና ቱሚም+ አማካኝነት ምክር የሚጠይቅ ካህን እስኪገኝ ድረስ እጅግ ቅዱስ ከሆኑት ነገሮች መብላት እንደማይችሉ ነገራቸው።+

64 መላው ጉባኤ በአጠቃላይ 42,360 ነበር፤+ 65 ይህ 7,337 ወንድና ሴት ባሪያዎቻቸውን አይጨምርም፤ በተጨማሪም 200 ወንድና ሴት ዘማሪዎች ነበሯቸው። 66 ከዚህም ሌላ 736 ፈረሶች፣ 245 በቅሎዎች 67 እንዲሁም 435 ግመሎችና 6,720 አህዮች ነበሯቸው።

68 ከአባቶች ቤት መሪዎች መካከል አንዳንዶቹ ኢየሩሳሌም ወደነበረው ወደ ይሖዋ ቤት ሲደርሱ ቤቱን በቀድሞ ቦታው ላይ መልሶ ለመገንባት+ ለእውነተኛው አምላክ ቤት የፈቃደኝነት መባዎችን አቀረቡ።+ 69 እነሱም ለሥራው ማስኬጃ እንዲሆን እንደየአቅማቸው 61,000 የወርቅ ድራክማ፣* 5,000 የብር ምናን*+ እና 100 የካህናት ቀሚስ ለግምጃ ቤቱ ሰጡ። 70 ካህናቱ፣ ሌዋውያኑ፣ ከሕዝቡ መካከል አንዳንዶቹ፣ ዘማሪዎቹ፣ በር ጠባቂዎቹና የቤተ መቅደስ አገልጋዮቹ* በየከተሞቻቸው ሰፈሩ፤ የቀሩትም እስራኤላውያን በሙሉ በየከተሞቻቸው መኖር ጀመሩ።+

3 በሰባተኛው ወር+ እስራኤላውያን* በከተሞቻቸው ውስጥ ነበሩ፤ እነሱም ልክ እንደ አንድ ሰው ሆነው በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ። 2 የየሆጼዴቅ ልጅ የሹዋና+ አብረውት የሚያገለግሉት ካህናት እንዲሁም የሰላትያል+ ልጅ ዘሩባቤልና+ ወንድሞቹ በእውነተኛው አምላክ ሰው በሙሴ ሕግ+ ውስጥ በተጻፈው መሠረት በላዩ ላይ የሚቃጠሉ መሥዋዕቶችን ለማቅረብ የእስራኤልን አምላክ መሠዊያ ሠሩ።

3 በዙሪያቸው ባሉት አገሮች በሚኖሩት ሕዝቦች የተነሳ ፍርሃት አድሮባቸው+ የነበረ ቢሆንም መሠዊያውን በቀድሞ ቦታው ላይ ሠሩት፤ በላዩም ላይ ለይሖዋ የሚቃጠሉ መሥዋዕቶችን ይኸውም ጠዋትና ማታ የሚቀርቡትን የሚቃጠሉ መሥዋዕቶች ማቅረብ ጀመሩ።+ 4 ከዚያም በሕጉ ላይ በተጻፈው መሠረት የዳስ* በዓልን አከበሩ፤+ እንዲሁም በእያንዳንዱ ቀን እንዲቀርብ በታዘዘው መጠን መሠረት የሚቃጠሉ መሥዋዕቶችን አቀረቡ።+ 5 ከዚያም የተለመደውን የሚቃጠል መባ፣+ ለአዲስ ጨረቃና+ ለተቀደሱት የይሖዋ በዓላት+ የሚቀርቡትን መባዎች እንዲሁም እያንዳንዱ ሰው ለይሖዋ የሚያቀርበውን የፈቃደኝነት መባ+ አቀረቡ። 6 የይሖዋ ቤተ መቅደስ መሠረት ገና ያልተጣለ ቢሆንም ከሰባተኛው ወር የመጀመሪያ ቀን+ አንስቶ ለይሖዋ የሚቃጠሉ መሥዋዕቶችን ማቅረብ ጀመሩ።

7 ለድንጋይ ጠራቢዎቹና+ ለእጅ ጥበብ ባለሙያዎቹም+ ገንዘብ ሰጡ፤ በተጨማሪም የፋርሱ ንጉሥ ቂሮስ+ በሰጣቸው ፈቃድ መሠረት የአርዘ ሊባኖስ ሳንቃዎችን ከሊባኖስ ወደ ኢዮጴ+ ወደብ ለሚያመጡ ለሲዶና እና ለጢሮስ ሰዎች የሚበላና የሚጠጣ ነገር እንዲሁም ዘይት ሰጡ።

8 በኢየሩሳሌም ወዳለው ወደ እውነተኛው አምላክ ቤት በመጡ በሁለተኛው ዓመት፣ በሁለተኛው ወር የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤልና የየሆጼዴቅ ልጅ የሹዋ እንዲሁም ካህናቱን፣ ሌዋውያኑንና ከምርኮ ወጥተው ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሱትን+ በሙሉ ጨምሮ የቀሩት ወንድሞቻቸው ሥራውን ጀመሩ፤ የይሖዋን ቤት ሥራ በበላይነት እንዲቆጣጠሩም ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በላይ የሆኑ ሌዋውያንን ሾሙ። 9 በመሆኑም የሹዋ፣ ወንዶች ልጆቹና ወንድሞቹ፣ ቃድሚኤልና ወንዶች ልጆቹ እንዲሁም የይሁዳ ወንዶች ልጆች ሌዋውያን ከሆኑት የሄናዳድ+ ወንዶች ልጆች፣ ከእነሱ ወንዶች ልጆችና ከወንድሞቻቸው ጋር ሆነው በእውነተኛው አምላክ ቤት ውስጥ ሥራውን የሚሠሩትን ሰዎች በበላይነት ለመቆጣጠር ተባበሩ።

10 የይሖዋን ቤተ መቅደስ የሚገነቡት ሰዎች መሠረቱን ሲጥሉ+ የክህነት ልብሳቸውን የለበሱት ካህናት በመለከት፣+ ሌዋውያኑ የአሳፍ ወንዶች ልጆች ደግሞ በሲምባል* የእስራኤል ንጉሥ ዳዊት በሰጠው መመሪያ መሠረት ይሖዋን ለማወደስ ተነሱ።+ 11 “እሱ ጥሩ ነውና፤ ለእስራኤል የሚያሳየውም ታማኝ ፍቅር ለዘላለም ጸንቶ ይኖራልና”+ በማለት እየተቀባበሉ+ ይሖዋን ማወደስና ማመስገን ጀመሩ። ከዚያም ሕዝቡ ሁሉ የይሖዋ ቤት መሠረት በመጣሉ ድምፁን ከፍ አድርጎ ይሖዋን አወደሰ። 12 የቀድሞውን ቤት ያዩ ሽማግሌዎች ይኸውም ከካህናቱ፣ ከሌዋውያኑና ከአባቶች ቤት መሪዎች መካከል አብዛኞቹ የዚህ ቤት መሠረት ሲጣል ሲያዩ+ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ፤ ብዙዎቹ ግን በደስታ እልልታቸውን አቀለጡት።+ 13 ሕዝቡ ድምፁ ከሩቅ እስኪሰማ ድረስ ከፍ ባለ ድምፅ ይጮኽ ስለነበር ሰዎቹ የደስታውን እልልታ ከለቅሶው ጩኸት መለየት አልቻሉም ነበር።

4 የይሁዳና የቢንያም ጠላቶች፣+ ከግዞት የተመለሱት ሰዎች+ ለእስራኤል አምላክ ለይሖዋ ቤተ መቅደስ እየገነቡ መሆናቸውን ሲሰሙ 2 ወዲያውኑ ወደ ዘሩባቤልና ወደ አባቶች ቤት መሪዎች ቀርበው እንዲህ አሏቸው፦ “ከእናንተ ጋር እንገንባ፤ ልክ እንደ እናንተ እኛም አምላካችሁን እናመልካለን፤*+ ደግሞም ወደዚህ ካመጣን ከአሦር ንጉሥ ከኤሳርሃደን+ ዘመን ጀምሮ ለእሱ መሥዋዕት ስናቀርብ ኖረናል።”+ 3 ይሁንና ዘሩባቤል፣ የሆሹዋና የቀሩት የእስራኤል አባቶች ቤት መሪዎች እንዲህ አሏቸው፦ “የአምላካችንን ቤት በመገንባቱ ሥራ ከእኛ ጋር ተካፋይ መሆን አትችሉም፤+ ምክንያቱም የፋርሱ ንጉሥ፣ ንጉሥ ቂሮስ ባዘዘን መሠረት እኛው ራሳችን የእስራኤልን አምላክ የይሖዋን ቤት እንገነባለን።”+

4 የምድሪቱም ነዋሪዎች የይሁዳን ሕዝቦች ተስፋ ለማስቆረጥና* ወኔ ከድቷቸው የግንባታ ሥራውን እንዲያቆሙ ለማድረግ ዘወትር ይጥሩ ነበር።+ 5 ከፋርሱ ንጉሥ ከቂሮስ ዘመን አንስቶ እስከ ፋርሱ ንጉሥ እስከ ዳርዮስ+ የግዛት ዘመን ድረስ እቅዶቻቸውን ለማጨናገፍ አማካሪዎችን ቀጠሩባቸው።+ 6 በተጨማሪም በአሐሽዌሮስ የግዛት ዘመን መጀመሪያ ላይ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ላይ በጽሑፍ ክስ መሠረቱባቸው። 7 ከዚህም ሌላ በፋርስ ንጉሥ በአርጤክስስ ዘመን ቢሽላም፣ ሚትረዳት፣ ታብኤልና የቀሩት ግብረ አበሮቹ ለንጉሥ አርጤክስስ ደብዳቤ ጻፉ፤ ደብዳቤውንም ወደ አረማይክ ቋንቋ+ ተርጉመው በአረማይክ ፊደል ጻፉት።*

8 * ዋናው የመንግሥት ባለሥልጣን ረሁም እና ጸሐፊው ሺምሻይ ኢየሩሳሌምን በመክሰስ ለንጉሥ አርጤክስስ የሚከተለውን ደብዳቤ ጻፉ፦ 9 (ደብዳቤውን የላኩት ዋናው የመንግሥት ባለሥልጣን ረሁም፣ ጸሐፊው ሺምሻይና የቀሩት ግብረ አበሮቻቸው እንዲሁም ዳኞቹ፣ የበታች ገዢዎቹ፣ ጸሐፊዎቹ፣ የኤሬክ+ ሕዝቦች፣ ባቢሎናውያን፣ የሱሳ+ ነዋሪዎች ማለትም ኤላማውያን፣+ 10 ታላቁና የተከበረው አስናፈር በግዞት ወስዶ በሰማርያ ከተሞች ያሰፈራቸው+ የቀሩት ብሔራትና ከወንዙ ባሻገር* ባለው ክልል የሚኖሩት የቀሩት ሰዎች ነበሩ፤ እንግዲህ 11 የላኩለት ደብዳቤ ቅጂ ይህ ነው።)

“ለንጉሥ አርጤክስስ፣ ከወንዙ ባሻገር ባለው ክልል ከሚኖሩት አገልጋዮችህ፦ እንግዲህ 12 ከአንተ ዘንድ ወደዚህ ወደ እኛ የመጡት አይሁዳውያን ኢየሩሳሌም መድረሳቸውን ንጉሡ ይወቅ። እነዚህ ሰዎች ዓመፀኛና ክፉ የሆነችውን ከተማ መልሰው እየገነቡ ነው፤ ቅጥሮቿን ሠርተው እየጨረሱ+ ሲሆን መሠረቶቿንም እየጠገኑ ነው። 13 ከተማዋ ተመልሳ ከተገነባችና ቅጥሮቿም ተሠርተው ከተጠናቀቁ እነዚህ ሰዎች ቀረጥም ሆነ ግብር+ ወይም የኬላ ቀረጥ እንደማይከፍሉ፣ በዚህም የተነሳ ወደ ነገሥታቱ ግምጃ ቤት የሚገባው ገቢ እንደሚቀንስ ንጉሡ ይወቅ። 14 እኛ ደግሞ የቤተ መንግሥቱን ጨው እየበላን* የንጉሡ ጥቅም ሲነካ ዝም ብሎ ማየት ተገቢ መስሎ አልታየንም፤ በመሆኑም ንጉሡ ጉዳዩን እንዲያውቀው ለማድረግ ይህን ደብዳቤ ልከናል፤ 15 ስለዚህ የቀድሞ አባቶችህ መዝገብ ይመርመር።+ ይህች ከተማ ዓመፀኛና ነገሥታትንም ሆነ አውራጃዎችን ጉዳት ላይ የምትጥል፣ ከጥንት ጀምሮም ዓመፅ ቆስቋሾችን ሸሽጋ የምታኖር መሆኗን ከእነዚህ መዛግብት መረዳት ትችላለህ። ከተማዋም የተደመሰሰችው በዚህ የተነሳ ነው።+ 16 ይህች ከተማ ተመልሳ ከተገነባችና ቅጥሮቿም ተሠርተው ከተጠናቀቁ ከወንዙ+ ባሻገር ያለውን ክልል መቆጣጠር እንደማትችል* ልናሳውቅህ እንፈልጋለን።”

17 ንጉሡም ለዋናው የመንግሥት ባለሥልጣን ለረሁም፣ ለጸሐፊው ለሺምሻይ፣ በሰማርያ ለሚኖሩት ለቀሩት ግብረ አበሮቻቸውና ከወንዙ ባሻገር ላለው ለቀረው ክልል እንዲህ የሚል መልእክት ላከ፦

“ሰላምታዬ ይድረሳችሁ! እንግዲህ 18 የላካችሁልን ደብዳቤ በፊቴ ግልጽ ሆኖ ተነቧል።* 19 በሰጠሁትም ትእዛዝ መሠረት ምርመራ ተደርጎ ከተማዋ ከጥንት ጀምሮ በነገሥታት ላይ ረብሻ የምትቀሰቅስ እንዲሁም የዓመፅና የወንጀል መፍለቂያ እንደነበረች ተረጋግጧል።+ 20 ኢየሩሳሌም ከወንዙ ባሻገር ያሉትን አካባቢዎች በሙሉ የሚገዙ ኃያላን ነገሥታት ነበሯት፤ እነሱም ቀረጥ፣ ግብርና የኬላ ቀረጥ ይቀበሉ ነበር። 21 እንግዲህ እኔ ትእዛዝ እስከምሰጥ ድረስ ከተማዋ ተመልሳ እንዳትገነባ እነዚህ ሰዎች ሥራውን እንዲያቆሙ ትእዛዝ አስተላልፉ። 22 የነገሥታቱን ጥቅም ይበልጥ የሚጎዳ ነገር እንዳይከሰት ይህን ጉዳይ በተመለከተ እርምጃ ከመውሰድ ቸል እንዳትሉ ተጠንቀቁ።”+

23 ንጉሥ አርጤክስስ የላከው ደብዳቤ በረሁም፣ በጸሐፊው በሺምሻይና በተባባሪዎቻቸው ፊት ከተነበበ በኋላ ወዲያውኑ በኢየሩሳሌም ወዳሉት አይሁዳውያን በመሄድ አስገድደው ሥራውን አስቆሟቸው። 24 በኢየሩሳሌም የነበረውን የአምላክን ቤት የመገንባቱ ሥራ የተቋረጠው በዚህ ጊዜ ነበር፤ እስከ ፋርሱ ንጉሥ እስከ ዳርዮስ የንግሥና ዘመን ሁለተኛ ዓመት ድረስም ሥራው ባለበት ቆመ።+

5 ከዚያም ነቢዩ ሐጌና+ የኢዶ+ የልጅ ልጅ የሆነው ነቢዩ ዘካርያስ+ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ለነበሩ አይሁዳውያን፣ ይመራቸው በነበረው በእስራኤል አምላክ ስም ትንቢት ተናገሩ። 2 በዚህ ጊዜ የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤልና+ የየሆጼዴቅ ልጅ የሆሹዋ+ በኢየሩሳሌም የነበረውን የአምላክን ቤት መልሰው መገንባት ጀመሩ፤+ አብረዋቸው የነበሩት የአምላክ ነቢያትም ያግዟቸው ነበር።+ 3 በወቅቱ፣ ከወንዙ ባሻገር* የነበረው ክልል ገዢ የሆነው ታተናይ እና ሸታርቦዘናይ እንዲሁም ግብረ አበሮቻቸው ወደ እነሱ መጥተው “ይህን ቤት እንድትገነቡና እንድታዋቅሩ ማን ትእዛዝ ሰጣችሁ?” ሲሉ ጠየቋቸው። 4 ከዚያም “ይህን ሕንፃ እየገነቡ ያሉት ሰዎች ስም ማን ነው?” አሏቸው። 5 ሆኖም አምላክ ለአይሁዳውያን ሽማግሌዎች+ ጥበቃ ያደርግላቸው* ስለነበር መልእክቱ ለዳርዮስ ተልኮ ጉዳዩን የሚመለከት ደብዳቤ ከዚያ እስኪመጣ ድረስ ሥራውን ሊያስቆሟቸው አልቻሉም።

6 ከወንዙ ባሻገር ያለው ክልል ገዢ የሆነው ታተናይ፣ ሸታርቦዘናይና ከወንዙ ባሻገር ያለው ክልል የበታች ገዢዎች የሆኑት ግብረ አበሮቹ ለንጉሥ ዳርዮስ የላኩት ደብዳቤ ቅጂ ይህ ነው፤ 7 እንዲህ የሚል መልእክት ጽፈው ላኩለት፦

“ለንጉሥ ዳርዮስ፦

“ሰላም ለአንተ ይሁን! 8 በይሁዳ አውራጃ ወደሚገኘው ወደ ታላቁ አምላክ ቤት እንደሄድንና ቤቱ በትላልቅ ድንጋዮች እየተገነባ፣ በግንቡም ላይ ሳንቃዎች እየተነጠፉ መሆናቸውን ንጉሡ ይወቅ። ሕዝቡ ሥራውን በትጋት እያከናወነ ሲሆን ሥራውም በእነሱ ጥረት እየተፋጠነ ነው። 9 ሽማግሌዎቹንም ‘ይህን ቤት እንድትገነቡና እንድታዋቅሩ ማን ትእዛዝ ሰጣችሁ?’ አልናቸው።+ 10 በተጨማሪም ግንባር ቀደም ሆነው የሚመሩትን ሰዎች ስም ጽፈን ለአንተ ለማሳወቅ የሰዎቹን ስም እንዲነግሩን ጠየቅናቸው።

11 “እነሱም የሚከተለውን ምላሽ ሰጡን፦ ‘እኛ የሰማይና የምድር አምላክ አገልጋዮች ነን፤ አሁን መልሰን የምንገነባው ከበርካታ ዓመታት በፊት ተገንብቶ የነበረውን ይኸውም ታላቁ የእስራኤል ንጉሥ ገንብቶ ያጠናቀቀውን ቤት ነው።+ 12 ሆኖም አባቶቻችን የሰማይን አምላክ ስላስቆጡት+ ለከለዳዊው ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነጾር+ አሳልፎ ሰጣቸው፤ እሱም ይህን ቤት አፈራርሶ+ ሕዝቡን በግዞት ወደ ባቢሎን ወሰደ።+ 13 ይሁንና በባቢሎን ንጉሥ በቂሮስ የግዛት ዘመን የመጀመሪያ ዓመት ንጉሥ ቂሮስ ይህ የአምላክ ቤት ተመልሶ እንዲገነባ ትእዛዝ ሰጠ።+ 14 በተጨማሪም ንጉሥ ቂሮስ፣ ናቡከደነጾር በኢየሩሳሌም ከነበረው ቤተ መቅደስ አውጥቶ ወደ ባቢሎን ቤተ መቅደስ የወሰዳቸውን የአምላክን ቤት የወርቅና የብር ዕቃዎች ከባቢሎን ቤተ መቅደስ አወጣ።+ እነዚህም ዕቃዎች ቂሮስ ገዢ አድርጎ+ ለሾመው ሸሽባጻር*+ ለተባለ ሰው ተሰጡ። 15 ቂሮስም እንዲህ አለው፦ “እነዚህን ዕቃዎች ውሰድ። ሄደህም በኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ውስጥ አስቀምጣቸው፤ የአምላክም ቤት ቀድሞ በነበረበት ቦታ ላይ ተመልሶ ይገንባ።”+ 16 ከዚያም ሸሽባጻር መጥቶ በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የአምላክን ቤት መሠረት ጣለ፤+ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ቤቱ በመገንባት ላይ ነው፤ ሆኖም ገና አላለቀም።’+

17 “እንግዲህ አሁን፣ ንጉሡ መልካም መስሎ ከታየው ንጉሥ ቂሮስ በኢየሩሳሌም የነበረው ያ የአምላክ ቤት ተመልሶ እንዲገነባ ትእዛዝ ሰጥቶ እንደሆነና እንዳልሆነ ለማረጋገጥ በባቢሎን በሚገኘው የንጉሡ ግምጃ ቤት ምርመራ ይካሄድ፤+ ይህን በተመለከተም ንጉሡ ያስተላለፈው ውሳኔ ይላክልን።”

6 በዚያን ጊዜ ንጉሥ ዳርዮስ ትእዛዝ ሰጠ፤ እነሱም በባቢሎን የሚገኘውን ውድ ነገሮች የሚቀመጡበትን ግምጃ ቤት* መረመሩ። 2 በሜዶን አውራጃ፣ በኤክባታና* ውስጥ በሚገኘው የተመሸገ ስፍራ አንድ ጥቅልል ተገኘ፤ በላዩም ላይ የሚከተለው መልእክት ተጽፎ ነበር፦

3 “ንጉሥ ቂሮስ በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት፣ ንጉሥ ቂሮስ በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የአምላክ ቤት አስመልክቶ የሚከተለውን ትእዛዝ ሰጠ፦+ ‘መሥዋዕቶችን በዚያ ማቅረብ እንዲችሉ ቤቱ ተመልሶ ይገንባ፤ መሠረቶቹም ይጣሉ፤ ቁመቱ 60 ክንድ፣* ወርዱ 60 ክንድ+ ሆኖ 4 ትላልቅ ድንጋዮችን በሦስት ዙር በመደራረብና በላዩ ላይ አንድ ዙር ሳንቃ በማድረግ ይሠራ፤+ ወጪውም ከንጉሡ ቤት ይከፈል።+ 5 በተጨማሪም ናቡከደነጾር በኢየሩሳሌም ከነበረው ቤተ መቅደስ አውጥቶ ወደ ባቢሎን የወሰዳቸው የወርቅና የብር ዕቃዎች ይመለሱ፤+ በኢየሩሳሌም ወዳለው ቤተ መቅደስ ተወስደው በቀድሞ ቦታቸው ላይ ይደረጉ፤ በአምላክም ቤት ውስጥ ይቀመጡ።’+

6 “አሁንም ከወንዙ ባሻገር* ያለው ክልል ገዢ የሆንከው ታተናይ፣ ሸታርቦዘናይና ከወንዙ ባሻገር የሚገኙ የበታች ገዢዎች የሆኑት ግብረ አበሮቻችሁ ከዚያ ራቁ።+ 7 በአምላክ ቤት ሥራ ጣልቃ አትግቡ። የአይሁዳውያን ገዢዎችና የአይሁዳውያን ሽማግሌዎች ያንን የአምላክ ቤት በቀድሞ ቦታው ላይ መልሰው ይገንቡት። 8 በተጨማሪም እነዚህ የአይሁዳውያን ሽማግሌዎች ያን የአምላክ ቤት መልሰው ሲገነቡ ልታደርጉላቸው የሚገባውን ነገር በተመለከተ ይህን ትእዛዝ ሰጥቻለሁ፦ ሥራው እንዳይስተጓጎል ከንጉሡ ግምጃ ቤት+ ይኸውም ከወንዙ ባሻገር ካለው ክልል ከተሰበሰበው ቀረጥ ላይ ተወስዶ የእነዚህ ሰዎች ወጪ በአፋጣኝ ይሸፈንላቸው።+ 9 ለሰማይ አምላክ ለሚቀርቡት የሚቃጠሉ መባዎች የሚያስፈልጉት ነገሮች ሁሉ ይኸውም ወይፈኖች፣+ አውራ በጎች፣+ የበግ ጠቦቶች፣+ ስንዴ፣+ ጨው፣+ የወይን ጠጅና+ ዘይት+ በኢየሩሳሌም የሚገኙት ካህናት በሚጠይቁት መሠረት በየቀኑ ያለማቋረጥ ይሰጣቸው፤ 10 ይህም የሚደረገው የሰማይ አምላክን ደስ የሚያሰኙ መባዎችን ዘወትር እንዲያቀርቡ እንዲሁም ለንጉሡና ለልጆቹ ደህንነት እንዲጸልዩ ነው።+ 11 ከዚህ በተጨማሪ ይህን አዋጅ የጣሰ ማንኛውም ሰው ለዚህ ጥፋቱ ከቤቱ ምሰሶ እንዲነቀልና ወደ ላይ ከፍ ተደርጎ ላዩ ላይ እንዲቸነከር* እንዲሁም ቤቱ የሕዝብ መጸዳጃ ቤት* እንዲሆን አዝዣለሁ። 12 ስሙ በዚያ እንዲኖር ያደረገው አምላክ+ ይህን ትእዛዝ ለመቃወምና በኢየሩሳሌም የሚገኘውን ያንን የአምላክ ቤት ለማጥፋት እጁን የሚያነሳን ማንኛውንም ንጉሥም ሆነ ሕዝብ ያጥፋው። እኔ ዳርዮስ ይህን ትእዛዝ ሰጥቻለሁ። ይህም በአስቸኳይ ተግባራዊ ይደረግ።”

13 ከዚያም ከወንዙ ባሻገር ያለው ክልል ገዢ የሆነው ታተናይ፣ ሸታርቦዘናይና+ ግብረ አበሮቻቸው ንጉሥ ዳርዮስ ያዘዘውን ነገር ሁሉ ወዲያውኑ ተግባራዊ አደረጉ። 14 የአይሁዳውያን ሽማግሌዎችም ነቢዩ ሐጌና+ የኢዶ የልጅ ልጅ ዘካርያስ+ በተናገሩት ትንቢት ተበረታተው ግንባታውን ማከናወናቸውንና ሥራውን ማፋጠናቸውን ቀጠሉ፤+ በእስራኤል አምላክ ትእዛዝ መሠረት+ እንዲሁም በቂሮስ፣+ በዳርዮስና+ በፋርሱ ንጉሥ በአርጤክስስ+ ትእዛዝ መሠረት ቤቱን ገንብተው አጠናቀቁ። 15 ቤቱንም በአዳር* ወር በሦስተኛው ቀን ይኸውም ንጉሥ ዳርዮስ በነገሠ በስድስተኛው ዓመት ሠርተው አጠናቀቁ።

16 ከዚያም እስራኤላውያን፣ ካህናቱ፣ ሌዋውያኑና+ በግዞት ተወስደው የነበሩት የቀሩት ሰዎች የአምላክን ቤት ምርቃት* በደስታ አከበሩ። 17 ለአምላክ ቤት ምርቃትም 100 በሬዎችን፣ 200 አውራ በጎችንና 400 የበግ ጠቦቶችን እንዲሁም ለመላው እስራኤል የኃጢአት መባ እንዲሆኑ በእስራኤል ነገዶች ቁጥር ልክ 12 አውራ ፍየሎችን አቀረቡ።+ 18 እንዲሁም በሙሴ መጽሐፍ ውስጥ በተጻፈው መሠረት+ በኢየሩሳሌም ለሚቀርበው የአምላክ አገልግሎት ካህናቱን በየክፍላቸው፣ ሌዋውያኑንም በየምድባቸው ሾሙ።+

19 በግዞት ተወስደው የነበሩት ሰዎች በመጀመሪያው ወር በ14ኛው ቀን ላይ ፋሲካን* አከበሩ።+ 20 ካህናቱና ሌዋውያኑ በሙሉ ራሳቸውን ስላነጹ+ ሁሉም ንጹሕ ሆነው ነበር፤ እነሱም በግዞት ተወስደው ለነበሩት ሰዎች በሙሉ፣ አብረዋቸው ለሚያገለግሉት ካህናትና ለራሳቸው የፋሲካውን እርድ አረዱ። 21 ከዚያም ከግዞት የተመለሱት እስራኤላውያን በምድሪቱ ከነበሩት ብሔራት ርኩሰት ራሳቸውን በመለየት የእስራኤልን አምላክ ይሖዋን ለማምለክ* ከእነሱ ጋር ከተቀላቀሉት ሁሉ ጋር ሆነው በሉት።+ 22 በተጨማሪም ይሖዋ እንዲደሰቱ ስላደረጋቸውና የእስራኤል አምላክ የሆነውን የእውነተኛውን አምላክ ቤት ይሠሩ ዘንድ እንዲረዳቸው* የአሦርን ንጉሥ ልብ ስላራራላቸው+ የቂጣን* በዓል+ ለሰባት ቀን በደስታ አከበሩ።

7 ከእነዚህ ነገሮች በኋላ በፋርሱ ንጉሥ በአርጤክስስ+ የግዛት ዘመን ዕዝራ*+ ከባቢሎን ተመለሰ። ዕዝራ የሰራያህ+ ልጅ፣ ሰራያህ የአዛርያስ ልጅ፣ አዛርያስ የኬልቅያስ+ ልጅ፣ 2 ኬልቅያስ የሻሉም ልጅ፣ ሻሉም የሳዶቅ ልጅ፣ ሳዶቅ የአኪጡብ ልጅ፣ 3 አኪጡብ የአማርያህ ልጅ፣ አማርያህ የአዛርያስ+ ልጅ፣ አዛርያስ የመራዮት ልጅ፣ 4 መራዮት የዘራህያህ ልጅ፣ ዘራህያህ የዑዚ ልጅ፣ ዑዚ የቡቂ ልጅ፣ 5 ቡቂ የአቢሹዓ ልጅ፣ አቢሹዓ የፊንሃስ+ ልጅ፣ ፊንሃስ የአልዓዛር+ ልጅ፣ አልዓዛር የካህናት አለቃ የሆነው የአሮን+ ልጅ ነበር። 6 ይህ ዕዝራ ከባቢሎን ወጣ። እሱም የእስራኤል አምላክ ይሖዋ የሰጠውን የሙሴን ሕግ ጠንቅቆ የሚያውቅ ገልባጭ* ነበር።*+ የአምላኩ የይሖዋ እጅ በእሱ ላይ ስለነበር ንጉሡ የጠየቀውን ሁሉ ሰጠው።

7 ንጉሥ አርጤክስስ በነገሠ በሰባተኛው ዓመት ከእስራኤላውያን፣ ከካህናቱ፣ ከሌዋውያኑ፣+ ከዘማሪዎቹ፣+ ከበር ጠባቂዎቹና+ ከቤተ መቅደስ አገልጋዮቹ*+ መካከል የተወሰኑት ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ። 8 ዕዝራም ንጉሡ በነገሠ በሰባተኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ኢየሩሳሌም ደረሰ። 9 በመጀመሪያው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ከባቢሎን ተነስቶ ጉዞ ጀመረ፤ መልካም የሆነው የአምላኩ እጅ በእሱ ላይ ስለነበር+ በአምስተኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ኢየሩሳሌም ደረሰ። 10 ዕዝራ የይሖዋን ሕግ ለመመርመርና ተግባራዊ ለማድረግ+ እንዲሁም ሥርዓቱንና ፍርዱን በእስራኤል ውስጥ ለማስተማር+ ልቡን አዘጋጅቶ* ነበር።

11 ንጉሥ አርጤክስስ የይሖዋን ትእዛዛትና ለእስራኤላውያን ያወጣቸውን ሥርዓቶች በማጥናት ለተካነውና* ገልባጭ* ለሆነው ለካህኑ ዕዝራ የሰጠው ደብዳቤ ቅጂ ይህ ነው፦

12 * “ከንጉሠ ነገሥት አርጤክስስ፣+ የሰማይ አምላክ ሕግ ገልባጭ* ለሆነው ለካህኑ ዕዝራ፦ ሰላም ለአንተ ይሁን። እንግዲህ 13 በግዛቴ ውስጥ ካሉ የእስራኤል ሕዝቦች እንዲሁም ከእነሱ ካህናትና ሌዋውያን መካከል ከአንተ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ፈቃደኛ የሆነ ሰው ሁሉ እንዲሄድ ትእዛዝ ሰጥቻለሁ።+ 14 ንጉሡና ሰባቱ አማካሪዎቹ በእጅህ የሚገኘው የአምላክህ ሕግ በይሁዳና በኢየሩሳሌም በተግባር ላይ እየዋለ እንደሆነና እንዳልሆነ እንድትመረምር ልከውሃል፤ 15 እንዲሁም ንጉሡና አማካሪዎቹ በኢየሩሳሌም ለሚኖረው ለእስራኤል አምላክ በፈቃደኝነት የሰጡትን ብርና ወርቅ፣ 16 ከመላው የባቢሎን አውራጃ ከተቀበልከው* ብርና ወርቅ እንዲሁም ሕዝቡና ካህናቱ በኢየሩሳሌም ለሚገኘው ለአምላካቸው ቤት በፈቃደኝነት ከሰጡት ስጦታ ጋር ይዘህ እንድትሄድ አዘዋል።+ 17 በዚህም ገንዘብ ሳትዘገይ በሬዎችን፣+ አውራ በጎችንና+ የበግ ጠቦቶችን+ ከእህል መባዎቻቸውና+ ከመጠጥ መባዎቻቸው+ ጋር ግዛ፤ እነዚህንም በኢየሩሳሌም በሚገኘው በአምላካችሁ ቤት መሠዊያ ላይ አቅርባቸው።

18 “በተረፈው ብርና ወርቅ እንደ አምላካችሁ ፈቃድ አንተም ሆንክ ወንድሞችህ መልካም መስሎ የታያችሁን አድርጉበት። 19 በአምላክህ ቤት ለሚቀርበው አገልግሎት እንዲሆኑ የተሰጡህን ዕቃዎች በሙሉ ወደ ኢየሩሳሌም ወስደህ በአምላክ ፊት ታስቀምጣቸዋለህ።+ 20 ለአምላክህ ቤት መስጠት የሚጠበቅብህን ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ከንጉሡ ግምጃ ቤት አውጥተህ ትሰጣለህ።+

21 “እኔ ንጉሥ አርጤክስስ ከወንዙ ባሻገር* ባለው ክልል የምትገኙትን የግምጃ ቤት ኃላፊዎች በሙሉ የሰማይ አምላክ ሕግ ገልባጭ* የሆነው ካህኑ ዕዝራ+ የጠየቃችሁን ነገር ሁሉ በአስቸኳይ እንድትፈጽሙለት ትእዛዝ ሰጥቻለሁ፤ 22 እንዲሁም እስከ 100 ታላንት* ብር፣ እስከ 100 የቆሮስ* መስፈሪያ ስንዴ፣ እስከ 100 የባዶስ* መስፈሪያ የወይን ጠጅና+ እስከ 100 የባዶስ መስፈሪያ ዘይት+ ድረስ ስጡት፤ እንዲሁም የፈለገውን ያህል ጨው+ ስጡት። 23 በንጉሡ ግዛትና በልጆቹ ላይ ቁጣ እንዳይወርድ+ የሰማይ አምላክ፣ የሰማይን አምላክ ቤት አስመልክቶ ያዘዘው ሁሉ በትጋት ይፈጸም።+ 24 በተጨማሪም ከካህናቱ፣ ከሌዋውያኑ፣ ከሙዚቀኞቹ፣+ ከበር ጠባቂዎቹ፣ ከቤተ መቅደስ አገልጋዮቹም*+ ሆነ ይህን የአምላክ ቤት ከሚሠሩት ሰዎች መካከል በአንዳቸውም ላይ ምንም ዓይነት ቀረጥ፣ ግብር+ ወይም የኬላ ቀረጥ መጣል እንደማትችሉ እወቁ።

25 “አንተም ዕዝራ፣ አምላክህ የሰጠህን ጥበብ* ተጠቅመህ ከወንዙ ባሻገር ባለው ክልል ለሚኖሩት ሕዝቦች በሙሉ፣ የአምላክህን ሕጎች ለሚያውቁ ሁሉ ፍርድ የሚሰጡ ሕግ አስከባሪዎችንና ዳኞችን ሹም፤ ሕጎቹን የማያውቅ ሰው ካለም አስተምሩት።+ 26 እንዲሁም የአምላክህን ሕግና የንጉሡን ሕግ የማያከብር ማንኛውም ሰው ቅጣቱ ሞትም ይሁን ከአገር መባረር ወይም ገንዘብ አሊያም እስራት አፋጣኝ የፍርድ እርምጃ ይወሰድበት።”

27 እንዲህ ያለውን ነገር ይኸውም በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የይሖዋን ቤት የማስዋቡን ሐሳብ በንጉሡ ልብ ውስጥ ያኖረው የአባቶቻችን አምላክ ይሖዋ ይወደስ!+ 28 በንጉሡና+ በአማካሪዎቹ+ እንዲሁም ኃያላን በሆኑት የንጉሡ መኳንንት ሁሉ ፊት ታማኝ ፍቅር አሳይቶኛል። በመሆኑም የአምላኬ የይሖዋ እጅ በላዬ ስለነበር ድፍረት አገኘሁ፤* ከእኔም ጋር አብረው እንዲሄዱ ከእስራኤል መካከል መሪ* የሆኑትን ሰበሰብኩ።

8 በንጉሥ አርጤክስስ+ የግዛት ዘመን ከባቢሎን አብረውኝ የወጡት የአባቶች ቤት መሪዎች የዘር ሐረግ ዝርዝር ይህ ነው፦ 2 ከፊንሃስ+ ልጆች ጌርሳም፣ ከኢታምር+ ልጆች ዳንኤል፣ ከዳዊት ልጆች ሃጡሽ፣ 3 ከሸካንያህ ልጆች፣ ከፓሮሽ ልጆች ዘካርያስ እንዲሁም ከእሱ ጋር የተመዘገቡ 150 ወንዶች ነበሩ፤ 4 ከፓሃትሞአብ+ ልጆች የዘራህያህ ልጅ የሆነው ኤሊየሆዔናይ እንዲሁም ከእሱ ጋር 200 ወንዶች፣ 5 ከዛቱ+ ልጆች የያሃዚኤል ልጅ የሆነው ሸካንያህ እንዲሁም ከእሱ ጋር 300 ወንዶች፣ 6 ከአዲን+ ልጆች የዮናታን ልጅ የሆነው ኤቤድ እንዲሁም ከእሱ ጋር 50 ወንዶች፣ 7 ከኤላም+ ልጆች የጎቶልያ ልጅ የሆነው የሻያህ እንዲሁም ከእሱ ጋር 70 ወንዶች፣ 8 ከሰፋጥያህ+ ልጆች የሚካኤል ልጅ የሆነው ዘባድያህ እንዲሁም ከእሱ ጋር 80 ወንዶች፣ 9 ከኢዮዓብ ልጆች የየሂኤል ልጅ የሆነው አብድዩ እንዲሁም ከእሱ ጋር 218 ወንዶች፣ 10 ከባኒ ልጆች የዮሲፍያህ ልጅ የሆነው ሸሎሚት እንዲሁም ከእሱ ጋር 160 ወንዶች፣ 11 ከቤባይ+ ልጆች የቤባይ ልጅ የሆነው ዘካርያስ እንዲሁም ከእሱ ጋር 28 ወንዶች፣ 12 ከአዝጋድ+ ልጆች የሃቃጣን ልጅ የሆነው ዮሃናን እንዲሁም ከእሱ ጋር 110 ወንዶች፣ 13 ከአዶኒቃም+ ልጆች የመጨረሻዎቹ የሆኑት ስማቸው ኤሊፌሌት፣ የኢዔልና ሸማያህ ሲሆን ከእነሱም ጋር 60 ወንዶች፤ 14 ከቢግዋይ+ ልጆች ዑታይና ዛቡድ እንዲሁም ከእነሱ ጋር 70 ወንዶች።

15 እኔም ወደ አሃዋ+ በሚፈሰው ወንዝ አጠገብ ሰበሰብኳቸው፤ በዚያም ለሦስት ቀን ሰፈርን። ሆኖም ሕዝቡንና ካህናቱን ልብ ብዬ ስመለከት ከሌዋውያን መካከል ማንንም በዚያ አላገኘሁም። 16 በመሆኑም መሪዎች ለሆኑት ለኤሊዔዘር፣ ለአርዔል፣ ለሸማያህ፣ ለኤልናታን፣ ለያሪብ፣ ለኤልናታን፣ ለናታን፣ ለዘካርያስና ለመሹላም እንዲሁም ለአስተማሪዎቹ ለዮያሪብና ለኤልናታን መልእክት ላክሁባቸው። 17 ከዚያም ካሲፍያ በተባለው ቦታ መሪ ወደሆነው ወደ ኢዶ እንዲሄዱ አዘዝኳቸው። ኢዶንና በካሲፍያ የቤተ መቅደስ አገልጋዮች* የሆኑትን ወንድሞቹን በአምላካችን ቤት የሚያገለግሉ ሰዎችን ያመጡልን ዘንድ እንዲጠይቋቸው ነገርኳቸው። 18 መልካም የሆነው የአምላካችን እጅ በእኛ ላይ ስለነበር የእስራኤል ልጅ የሌዊ የልጅ ልጅ ከሆነው ከማህሊ+ ልጆች መካከል አስተዋይ የሆነውን ሸረበያህን፣+ ወንዶች ልጆቹንና ወንድሞቹን በአጠቃላይ 18 ሰዎችን አመጡልን፤ 19 እንዲሁም ሃሻብያህንና ከእሱም ጋር ከሜራራውያን+ መካከል የሻያህን፣ ወንድሞቹንና ወንዶች ልጆቻቸውን በአጠቃላይ 20 ሰዎችን አመጡልን። 20 በተጨማሪም ከቤተ መቅደሱ አገልጋዮች* መካከል ዳዊትና መኳንንቱ ሌዋውያኑ ለሚያቀርቡት አገልግሎት የሰጧቸው 220 ሰዎች ነበሩ፤ ሁሉም በየስማቸው ተመዝግበው ነበር።

21 ከዚያም ራሳችንን በአምላካችን ፊት ለማዋረድ እንዲሁም በጉዟችን ወቅት ለእኛም ሆነ ለልጆቻችንና ለንብረቶቻችን በሙሉ የሚሆን መመሪያ ከእሱ ለማግኘት እዚያው በአሃዋ ወንዝ ጾም አወጅኩ። 22 “መልካም የሆነው የአምላካችን እጅ እሱን በሚሹት ሁሉ ላይ ነው፤+ እሱን በሚተዉት ሁሉ ላይ ግን ኃይሉንና ቁጣውን ይገልጣል”+ በማለት ለንጉሡ ነግረነው ስለነበር በጉዟችን ላይ ከሚያጋጥሙን ጠላቶች የሚጠብቁን ወታደሮችና ፈረሰኞች እንዲሰጠን ንጉሡን መጠየቅ አፈርኩ። 23 ስለሆነም ጾምን፤ ይህን በተመለከተም ለአምላካችን ልመና አቀረብን፤ እሱም ልመናችንን ሰማ።+

24 እኔም ከዋነኞቹ ካህናት መካከል 12ቱን ይኸውም ሸረበያህንና ሃሻብያህን+ እንዲሁም አሥር ወንድሞቻቸውን ለየሁ። 25 ከዚያም ንጉሡ፣ አማካሪዎቹና መኳንንቱ እንዲሁም በዚያ የተገኙት እስራኤላውያን በሙሉ ለአምላካችን ቤት የሰጡትን መዋጮ ማለትም ብሩን፣ ወርቁንና ዕቃዎቹን መዘንኩላቸው።+ 26 የሚከተሉትንም ዕቃዎች መዝኜ ሰጠኋቸው፦ 650 ታላንት* ብር፣ 2 ታላንት የሚመዝኑ 100 የብር ዕቃዎች፣ 100 ታላንት ወርቅ 27 እንዲሁም 1,000 ዳሪክ* የሚመዝኑ 20 ትናንሽ ጎድጓዳ የወርቅ ሳህኖችና የወርቅ ያህል ተፈላጊ የሆኑ ከሚያብረቀርቅ ጥሩ መዳብ የተሠሩ 2 ዕቃዎች።

28 ከዚያም እንዲህ አልኳቸው፦ “እናንተ ለይሖዋ የተቀደሳችሁ ናችሁ፤+ ዕቃዎቹም የተቀደሱ ናቸው፤ ብሩና ወርቁ ለአባቶቻችሁ አምላክ ለይሖዋ የቀረበ የፈቃደኝነት መባ ነው። 29 በኢየሩሳሌም በሚገኙት በይሖዋ ቤት ክፍሎች* ውስጥ በዋነኞቹ ካህናትና ሌዋውያን እንዲሁም በእስራኤል የአባቶች ቤት መኳንንት ፊት እስክትመዝኗቸው ድረስ በጥንቃቄ ጠብቋቸው።”+ 30 ካህናቱና ሌዋውያኑም የተመዘነላቸውን ብር፣ ወርቅና ዕቃ በኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ወደ አምላካችን ቤት ለመውሰድ ተረከቡ።

31 በኋላም በመጀመሪያው ወር ከወሩም በ12ኛው ቀን+ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ከአሃዋ+ ወንዝ ተነሳን፤ የአምላካችንም እጅ በላያችን ነበር፤ እሱም በመንገድ ላይ ከጠላት እጅና ከሽምቅ ጥቃት ታደገን። 32 ወደ ኢየሩሳሌም+ መጥተን በዚያ ለሦስት ቀን ተቀመጥን። 33 በአራተኛውም ቀን ብሩን፣ ወርቁንና ዕቃዎቹን በአምላካችን ቤት+ መዝነን ለዑሪያህ ልጅ ለካህኑ ለመሬሞት+ አስረከብነው፤ ከእሱም ጋር የፊንሃስ ልጅ አልዓዛር እንዲሁም ሌዋውያን የሆኑት የየሹዋ ልጅ ዮዛባድና+ የቢኑይ+ ልጅ ኖአድያህ ነበሩ። 34 እያንዳንዱም ነገር ተቆጥሮ ተመዘነ፤ ክብደቱም ሁሉ ተመዘገበ። 35 በግዞት ተወስደው የነበሩት ከምርኮ ነፃ የወጡ ሰዎች ለእስራኤል አምላክ የሚቃጠሉ መሥዋዕቶችን አቀረቡ፤ ለመላው እስራኤል 12 በሬዎችን፣+ 96 አውራ በጎችን፣+ 77 ተባዕት የበግ ጠቦቶችንና 12 ተባዕት ፍየሎችን+ የኃጢአት መባ አድርገው አቀረቡ፤ ይህ ሁሉ ለይሖዋ የቀረበ የሚቃጠል መባ ነበር።+

36 ከዚያም ንጉሡ ያወጣቸውን ድንጋጌዎች+ ለንጉሡ የአውራጃ ገዢዎችና* ከወንዙ+ ባሻገር* ባለው ክልል ለሚገኙት ገዢዎች ሰጠናቸው፤ እነሱም ለሕዝቡና ለእውነተኛው አምላክ ቤት ድጋፍ ሰጡ።+

9 እነዚህ ነገሮች እንደተጠናቀቁ መኳንንቱ ወደ እኔ መጥተው እንዲህ አሉኝ፦ “የእስራኤል ሕዝብ፣ ካህናቱና ሌዋውያኑ በምድሪቱ ከሚኖሩት ሕዝቦች ይኸውም ከከነአናውያን፣ ከሂታውያን፣ ከፈሪዛውያን፣ ከኢያቡሳውያን፣ ከአሞናውያን፣ ከሞዓባውያን፣ ከግብፃውያንና+ ከአሞራውያን+ እንዲሁም አስጸያፊ ከሆኑት ልማዶቻቸው+ ራሳቸውን አልለዩም። 2 ከእነሱም ሴቶች ልጆች መካከል ለራሳቸውና ለወንዶች ልጆቻቸው ሚስቶች ወስደዋል።+ በመሆኑም ቅዱስ ዘር+ የሆኑት እነዚህ ሰዎች በምድሪቱ ከሚኖሩት ሕዝቦች ጋር ተቀላቅለዋል።+ ይህን ታማኝነት የጎደለው ድርጊት በመፈጸም ግንባር ቀደም የሆኑት መኳንንቱና የበታች ገዢዎቹ ናቸው።”

3 እኔም ይህን ስሰማ እጀ ጠባቤንና መደረቢያዬን ቀደድኩ፤ ፀጉሬንና ጺሜን ነጨሁ፤ በጣም ከመደንገጤም የተነሳ በተቀመጥኩበት ደርቄ ቀረሁ። 4 ምሽት ላይ እስከሚቀርበው የእህል መባ+ ድረስ እንደደነገጥኩ በዚያ ተቀምጬ ሳለሁ ለእስራኤል አምላክ ቃል አክብሮታዊ ፍርሃት ያላቸው* ሰዎች ሁሉ፣ በግዞት ተወስደው የነበሩት ሰዎች በፈጸሙት ታማኝነት የጎደለው ድርጊት የተነሳ በዙሪያዬ ተሰበሰቡ።

5 ከዚያም ምሽት ላይ የእህል መባው+ በሚቀርብበት ጊዜ እጀ ጠባቤና መደረቢያዬ እንደተቀደደ ራሴን አዋርጄ ከተቀመጥኩበት ተነሳሁ፤ በጉልበቴም ተንበርክኬ እጆቼን ወደ አምላኬ ወደ ይሖዋ ዘረጋሁ። 6 እንዲህም አልኩ፦ “አቤቱ አምላኬ ሆይ፣ ፊቴን ወደ አንተ ቀና ማድረግ አሳፈረኝ፤ አሸማቀቀኝ፤ ምክንያቱም አምላኬ ሆይ፣ የፈጸምናቸው ስህተቶች በአናታችን ላይ ተቆልለዋል፤ በደላችንም ከመብዛቱ የተነሳ እስከ ሰማይ ደርሷል።+ 7 ከአባቶቻችን ዘመን አንስቶ እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ የፈጸምነው በደል ታላቅ ነው፤+ በሠራናቸውም ስህተቶች የተነሳ ይኸው ዛሬ እንደሚታየው እኛም ሆንን ነገሥታታችንና ካህናታችን በሌሎች አገሮች ነገሥታት እጅ ወድቀን ለሰይፍ፣+ ለምርኮ፣+ ለብዝበዛና+ ለውርደት ተዳርገናል።+ 8 አሁን ግን አምላካችን ይሖዋ ቀሪዎች እንዲተርፉና በቅዱስ ስፍራው አስተማማኝ ቦታ* እንድናገኝ በማድረግ ለትንሽ ጊዜም ቢሆን ሞገስ አሳይቶናል፤+ አምላካችን ሆይ፣ ይህን ያደረግከው ዓይኖቻችን እንዲበሩና ከተጫነብን የባርነት ቀንበር ትንሽ እንድናገግም ነው። 9 ባሪያዎች+ ብንሆንም እንኳ አምላካችን ባሪያዎች ሆነን እንድንቀር አልተወንም፤ ከዚህ ይልቅ በፋርስ ነገሥታት ፊት ታማኝ ፍቅሩን አሳየን፤+ ይህን ያደረገውም ዳግም አገግመን የአምላካችንን ቤት ከወደቀበት እንድናነሳና የፈራረሱትን ቦታዎች መልሰን እንድንገነባ+ እንዲሁም በይሁዳና በኢየሩሳሌም የድንጋይ ቅጥር* እንድናገኝ ሲል ነው።

10 “አሁን ግን አምላካችን ሆይ፣ ከዚህ በኋላ ምን ማለት እንችላለን? ምክንያቱም ትእዛዛትህን ተላልፈናል፤ 11 በአገልጋዮችህ በነቢያት አማካኝነት የሰጠኸንን የሚከተለውን ትእዛዝ አላከበርንም፦ ‘ትወርሷት ዘንድ የምትገቡባት ምድር በነዋሪዎቿ ርኩሰት የተነሳ የረከሰች ናት፤ ምክንያቱም በምድሪቱ የሚኖሩት ሰዎች በአስጸያፊ ድርጊቶቻቸው ምድሪቱን ከዳር እሰከ ዳር በርኩሰታቸው ሞልተዋታል።+ 12 ስለሆነም ሴቶች ልጆቻችሁን ለወንዶች ልጆቻቸው አትስጡ፤ ሴቶች ልጆቻቸውንም ለወንዶች ልጆቻችሁ አትውሰዱ፤+ እንዲሁም ይበልጥ እየበረታችሁ እንድትሄዱ፣ የምድሪቱን መልካም ነገር እንድትበሉና ምድሪቱን የልጆቻችሁ ዘላለማዊ ርስት ማድረግ እንድትችሉ ፈጽሞ የእነሱን ሰላምና ብልጽግና አትፈልጉ።’+ 13 በተጨማሪም በመጥፎ ሥራዎቻችንና በፈጸምነው ታላቅ በደል ምክንያት ይህ ሁሉ ደረሰብን፤ አንተ ግን አምላካችን ሆይ፣ እንደ ጥፋታችን መጠን አልቀጣኸንም፤+ ከዚህ ይልቅ እኛ እዚህ ያለነው እንድንተርፍ ፈቀድክ።+ 14 ታዲያ ትእዛዛትህን እንደገና መተላለፍና እነዚህን አስጸያፊ ነገሮች ከሚፈጽሙ ሕዝቦች ጋር በጋብቻ መዛመድ ይገባናል?+ አንተስ አንድም ሰው ሳታስቀር ወይም ሳታስተርፍ ፈጽሞ እስክታጠፋን ድረስ ልትቆጣ አይገባህም? 15 የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ጻድቅ ነህ፤+ ምክንያቱም እኛ ከጥፋት ተርፈን እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ በሕይወት አለን። እንዲህ ያለ ነገር አድርጎ በፊትህ መቆም የማይቻል ቢሆንም ይኸው ከነበደላችን በፊትህ ቀርበናል።”+

10 ዕዝራ በእውነተኛው አምላክ ቤት ፊት ተደፍቶ እያለቀሰ፣ እየጸለየና+ እየተናዘዘ ሳለ በርካታ ቁጥር ያላቸው እስራኤላውያን ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች በዙሪያው ተሰበሰቡ፤ ሕዝቡም ምርር ብሎ ያለቅስ ነበር። 2 ከዚያም ከኤላም+ ልጆች መካከል የየሂኤል+ ልጅ ሸካንያህ ዕዝራን እንዲህ አለው፦ “በምድሪቱ ከሚኖሩት ሕዝቦች መካከል ባዕዳን ሴቶችን በማግባት* በአምላካችን ላይ ታማኝነት የጎደለው ድርጊት ፈጽመናል።+ ያም ሆኖ እስራኤል አሁንም ተስፋ አለው። 3 እንግዲህ ይሖዋም ሆነ ለአምላካችን ትእዛዝ አክብሮት ያላቸው* ሰዎች+ በሰጡት መመሪያ መሠረት ሚስቶቻችንን በሙሉና ከእነሱ የተወለዱትን ልጆች ለማሰናበት ከአምላካችን ጋር ቃል ኪዳን እንጋባ።+ ሕጉንም ተግባራዊ እናድርግ። 4 ይህ የአንተ ኃላፊነት ስለሆነ ተነስ፤ እኛም ከጎንህ ነን። አይዞህ፣ እርምጃ ውሰድ።”

5 በዚህ ጊዜ ዕዝራ ተነስቶ የቀረበውን ሐሳብ ተግባራዊ እንዲያደርጉ የካህናቱን፣ የሌዋውያኑንና የመላው እስራኤልን አለቆች አስማላቸው፤+ እነሱም ማሉ። 6 ከዚያም ዕዝራ ከእውነተኛው አምላክ ቤት ፊት ተነስቶ የኤልያሺብ ልጅ ወደሆነው ወደ የሆሃናን ክፍል* ሄደ። ሆኖም በግዞት የተወሰደው ሕዝብ በፈጸመው ታማኝነት የጎደለው ድርጊት+ አዝኖ ስለነበር ወደዚያ ቢሄድም እንኳ እህል አልቀመሰም፤ ውኃም አልጠጣም።

7 ከዚያም በግዞት የነበሩት ሰዎች ሁሉ በኢየሩሳሌም እንዲሰበሰቡ የሚያዝዝ አዋጅ በይሁዳና በኢየሩሳሌም አወጁ፤ 8 መኳንንቱና ሽማግሌዎቹ ባስተላለፉት ውሳኔ መሠረት በሦስት ቀን ውስጥ ያልመጣ ማንኛውም ሰው ንብረቱ በሙሉ እንዲወረስና* በግዞት ከተወሰደው ሕዝብ ጉባኤ እንዲባረር ይደረጋል።+ 9 በመሆኑም ከይሁዳና ከቢንያም ነገድ የሆኑ ወንዶች ሁሉ በሦስት ቀን ውስጥ ማለትም በዘጠነኛው ወር ከወሩም በ20ኛው ቀን በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ። ሕዝቡም ሁሉ በእውነተኛው አምላክ ቤት ግቢ ውስጥ ተቀምጠው ነበር፤ ከጉዳዩ ክብደትና ከሚዘንበው ኃይለኛ ዝናብ የተነሳም ይንቀጠቀጡ ነበር።

10 ከዚያም ካህኑ ዕዝራ ተነስቶ እንዲህ አላቸው፦ “ባዕዳን ሚስቶችን በማግባት ታማኝነት የጎደለው ድርጊት ፈጽማችኋል፤+ በዚህም የተነሳ የእስራኤል በደል እንዲበዛ አድርጋችኋል። 11 እንግዲህ አሁን ለአባቶቻችሁ አምላክ ለይሖዋ ተናዘዙ፤ ፈቃዱንም ፈጽሙ። በምድሪቱ ከሚኖሩት ሕዝቦችና ከባዕዳን ሚስቶቻችሁ ራሳችሁን ለዩ።”+ 12 በዚህ ጊዜ መላው ጉባኤ ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ልክ እንደተናገርከው ማድረግ ግዴታችን ነው። 13 ይሁንና ሕዝቡ ብዙ ነው፤ የዝናብ ወቅት ስለሆነ ውጭ መቆም አስቸጋሪ ነው። ደግሞም ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የፈጸምነው ዓመፅ እጅግ ከባድ በመሆኑ ጉዳዩ በአንድ ወይም በሁለት ቀን የሚቋጭ አይደለም። 14 ስለዚህ እባክህ መኳንንታችን ለመላው ጉባኤ ተወካይ ሆነው ያገልግሉ፤+ ባዕዳን ሴቶችን ያገቡ በከተሞቻችን በሙሉ የሚገኙ ሰዎችም ከእያንዳንዱ ከተማ ሽማግሌዎችና ፈራጆች ጋር በተወሰነው ጊዜ ይምጡ፤ በዚህ ጉዳይ የተነሳ የመጣብን የአምላካችን የሚነድ ቁጣ እስኪመለስ ድረስ እንዲህ ብናደርግ የተሻለ ነው።”

15 ይሁን እንጂ የአሳሄል ልጅ ዮናታንና የቲቅዋ ልጅ ያህዘያህ ይህን ሐሳብ ተቃወሙ፤ ሌዋውያኑ መሹላምና ሻበታይም+ ተባበሯቸው። 16 ሆኖም በግዞት የነበሩት ሰዎች በስምምነቱ መሠረት እርምጃ ወሰዱ፤ ከዚያም በአሥረኛው ወር የመጀመሪያ ቀን ካህኑ ዕዝራና በየስማቸው የተመዘገቡት የአባቶቻቸው ቤት የቤተሰብ መሪዎች ሁሉ ጉዳዩን ለመመርመር ብቻቸውን ተሰበሰቡ። 17 እነሱም ባዕዳን ሴቶችን ያገቡትን ሰዎች ጉዳይ በመጀመሪያው ወር የመጀመሪያ ቀን ላይ መርምረው ጨረሱ። 18 ባዕዳን ሴቶችን ካገቡት ሰዎችም መካከል አንዳንድ የካህናት ልጆች መኖራቸው ታወቀ፤+ እነሱም የየሆጼዴቅ ልጅ የየሆሹዋ+ ወንዶች ልጆችና ወንድሞች የሆኑት ማአሴያህ፣ ኤሊዔዘር፣ ያሪብ እና ጎዶልያስ ናቸው። 19 እነዚህ ሰዎች ሚስቶቻቸውን ለማሰናበት ቃል ገቡ፤* በደለኞች ስለሆኑም ለበደላቸው ከመንጋው መካከል አንድ አውራ በግ ያቀርባሉ።+

20 ከኢሜር+ ወንዶች ልጆች ሃናኒ እና ዘባድያህ፤ 21 ከሃሪም+ ወንዶች ልጆች ማአሴያህ፣ ኤልያስ፣ ሸማያህ፣ የሂኤል እና ዖዝያ፤ 22 ከጳስኮር+ ወንዶች ልጆች ኤሊዮዔናይ፣ ማአሴያህ፣ እስማኤል፣ ናትናኤል፣ ዮዛባድ እና ኤልዓሳ። 23 ከሌዋውያኑ መካከል ዮዛባድ፣ ሺምአይ፣ ቄላያህ (ማለትም ቀሊጣ)፣ ፐታያህ፣ ይሁዳ እና ኤሊዔዘር፤ 24 ከዘማሪዎቹ መካከል ኤልያሺብ፤ ከበር ጠባቂዎቹ መካከል ሻሉም፣ ተሌም እና ዖሪ።

25 ከእስራኤል መካከል የፓሮሽ+ ወንዶች ልጆች የሆኑት ራምያህ፣ ይዝዚያህ፣ ማልኪያህ፣ ሚያሚን፣ አልዓዛር፣ ማልኪያህ እና በናያህ ነበሩ፤ 26 ከኤላም+ ወንዶች ልጆች ማታንያህ፣ ዘካርያስ፣ የሂኤል፣+ አብዲ፣ የሬሞት እና ኤልያስ፤ 27 ከዛቱ+ ወንዶች ልጆች ኤሊዮዔናይ፣ ኤልያሺብ፣ ማታንያህ፣ የሬሞት፣ ዛባድ እና አዚዛ፤ 28 ከቤባይ+ ወንዶች ልጆች የሆሃናን፣ ሃናንያህ፣ ዛባይ እና አትላይ፤ 29 ከባኒ ወንዶች ልጆች መሹላም፣ ማሉክ፣ አዳያህ፣ ያሹብ፣ ሸአል እና የሬሞት፤ 30 ከፓሃትሞአብ+ ወንዶች ልጆች አድና፣ ከላል፣ በናያህ፣ ማአሴያህ፣ ማታንያህ፣ ባስልኤል፣ ቢኑይ እና ምናሴ፤ 31 ከሃሪም+ ወንዶች ልጆች ኤሊዔዘር፣ ይሽሺያህ፣ ማልኪያህ፣+ ሸማያህ፣ ሺምኦን፣ 32 ቢንያም፣ ማሉክ እና ሸማርያህ፤ 33 ከሃሹም+ ወንዶች ልጆች ማቴናይ፣ ማታታ፣ ዛባድ፣ ኤሊፌሌት፣ የሬማይ፣ ምናሴ እና ሺምአይ፤ 34 ከባኒ ወንዶች ልጆች ማአዳይ፣ አምራም፣ ዑኤል፣ 35 በናያህ፣ ቤድያህ፣ ከሉሂ፣ 36 ዋንያህ፣ መሬሞት፣ ኤልያሺብ፣ 37 ማታንያህ፣ ማቴናይ እና ያአሱ፤ 38 ከቢኑይ ወንዶች ልጆች ሺምአይ፣ 39 ሸሌምያህ፣ ናታን፣ አዳያህ፣ 40 ማክናደባይ፣ ሻሻይ፣ ሻራይ፣ 41 አዛርዔል፣ ሸሌምያህ፣ ሸማርያህ፣ 42 ሻሉም፣ አማርያህ እና ዮሴፍ፤ 43 ከነቦ ወንዶች ልጆች የኢዔል፣ ማቲትያህ፣ ዛባድ፣ ዘቢና፣ ያዳይ፣ ኢዩኤል እና በናያህ። 44 እነዚህ ሁሉ ባዕዳን ሚስቶችን ያገቡ ናቸው፤+ እነሱም ሚስቶቻቸውን ከነልጆቻቸው አሰናበቱ።+

“. . . ይውጣ፤ በኢየሩሳሌም ያለውን” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ቃል በቃል “የእሱ አካባቢ ሰዎች።”

ቃል በቃል “እጃቸውን አበረቱላቸው።”

በዕዝራ 2:2 እና 3:8 ላይ ዘሩባቤል የተባለው ሳይሆን አይቀርም።

ወይም “ናታኒሞቹ።” ቃል በቃል “የተሰጡ ሰዎች።”

ወይም “ናታኒሞቹ።” ቃል በቃል “የተሰጡ ሰዎች።”

ወይም “እንደረከሱ ተቆጥረው ከክህነት አገልግሎቱ ተገለሉ።”

ወይም “ቲርሻታው።” ለአንድ የአውራጃ ገዢ የሚሰጥ የፋርሳውያን የማዕረግ ስም ነው።

አብዛኛውን ጊዜ 8.4 ግራም ከሚመዝነው የፋርሳውያን የወርቅ ዳሪክ ጋር እኩል መጠን አለው። በግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ከተጠቀሰው ድራክማ የተለየ ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ አንድ ምናን 570 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ወይም “ናታኒሞቹ።” ቃል በቃል “የተሰጡ ሰዎች።”

ቃል በቃል “የእስራኤል ወንዶች ልጆች።”

ወይም “የጊዜያዊ መጠለያ።”

እዚህ ላይ የገባው የዕብራይስጥ ቃል፣ እርስ በርሱ ሲጋጭ ኃይለኛ ድምፅ የሚያወጣን ክብ ቅርጽ ያለው ከብረት የተሠራ የሙዚቃ መሣሪያ ያመለክታል።

ቃል በቃል “እንፈልጋለን።”

ቃል በቃል “እጅ ለማዛልና።”

“ደብዳቤው በአረማይክ ቋንቋ ተጽፎ የነበረ ሲሆን ከዚያም ተተረጎመ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ከዕዝራ 4:8 እስከ 6:18 ያለው በመጀመሪያ የተጻፈው በአረማይክ ቋንቋ ነበር።

ወይም “ኤፍራጥስን ተሻግሮ።”

ወይም “ደሞዛችንን ከቤተ መንግሥቱ እየተቀበልን።”

ቃል በቃል “ባለው ክልል ድርሻ እንደማይኖርህ።”

“ተተርጉሞ ተነቧል” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “ኤፍራጥስን ተሻግሮ።”

ቃል በቃል “የአምላካቸው ዓይን በአይሁዳውያን ሽማግሌዎች ላይ።”

በዕዝራ 2:2 እና 3:8 ላይ ዘሩባቤል የተባለው ሳይሆን አይቀርም።

ቃል በቃል “መዝገብ ቤት።”

ወይም “በአሕምታ።”

ወደ 26.7 ሜትር ገደማ ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ወይም “ኤፍራጥስን ተሻግሮ።”

ወይም “እንዲነቀልና ላዩ ላይ እንዲሰቀል።”

“የቆሻሻ መጣያ፤ የፋንድያ ክምር” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።

ወይም “ውሰና።”

ወይም “የማለፍን በዓል።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ቃል በቃል “ለመፈለግ።”

ቃል በቃል “እጃቸውን እንዲያበረታ።”

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

“እርዳታ” የሚል ትርጉም አለው።

ወይም “ጸሐፊ።”

ወይም “የሙሴን ሕግ በመገልበጥ የተካነ ነበር።”

ወይም “ከናታኒሞቹ።” ቃል በቃል “ከተሰጡት ሰዎች።”

ወይም “በልቡ ቆርጦ።”

ወይም “ቃላት ለሚገለብጠው።”

ወይም “ጸሐፊ።”

ከዕዝራ 7:12 እስከ 7:26 ያለው መጀመሪያ የተጻፈው በአረማይክ ቋንቋ ነበር።

ወይም “ጸሐፊ።”

ቃል በቃል “ካገኘኸው።”

ወይም “ኤፍራጥስን ተሻግሮ።”

ወይም “ጸሐፊ።”

አንድ ታላንት 34.2 ኪሎ ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

አንድ ቆሮስ 220 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

አንድ ባዶስ 22 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ወይም “ከናታኒሞቹም።” ቃል በቃል “ከተሰጡት ሰዎችም።”

ቃል በቃል “በእጅህ ባለው በአምላክህ ጥበብ።”

ወይም “ራሴን አበረታሁ።”

ቃል በቃል “ራስ።”

ወይም “ናታኒሞች።” ቃል በቃል “የተሰጡ ሰዎች።”

ወይም “ከናታኒሞቹ።” ቃል በቃል “ከተሰጡት ሰዎች።”

አንድ ታላንት 34.2 ኪሎ ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ዳሪክ የፋርስ የወርቅ ሳንቲም ነበር። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ወይም “መመገቢያ አዳራሾች።”

ይህ የማዕረግ ስም “የግዛቱ ጠባቂዎች” የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን እዚህ ላይ የተሠራበት በፋርስ ግዛት የሚገኙ የአውራጃ ገዢዎችን ለማመልከት ነው።

ወይም “ኤፍራጥስን ተሻግሮ።”

ቃል በቃል “የተንቀጠቀጡ።”

ቃል በቃል “ካስማ።”

ወይም “ከለላ የሚሆን ቅጥር።”

ወይም “ወደ ቤታችን በማስገባት።”

ቃል በቃል “የሚንቀጠቀጡ።”

ወይም “መመገቢያ አዳራሽ።”

ወይም “እንዲታገድና።”

ቃል በቃል “እጃቸውን ሰጡ።”

    የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ ጽሑፎች (2011-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ