ለገላትያ ሰዎች የተጻፈ ደብዳቤ
1 ከሰዎች ወይም በሰው ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስ+ እንዲሁም እሱን ከሞት ባስነሳውና አባታችን በሆነው አምላክ+ አማካኝነት ሐዋርያ ከሆነው ከጳውሎስ፣ 2 እንዲሁም አብረውኝ ካሉት ወንድሞች ሁሉ፣ በገላትያ ላሉት ጉባኤዎች፦
3 አባታችን ከሆነው አምላክና ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። 4 ኢየሱስ እንደ አምላካችንና እንደ አባታችን ፈቃድ+ አሁን ካለው ክፉ ሥርዓት*+ እኛን ለመታደግ ስለ ኃጢአታችን ራሱን ሰጠ፤+ 5 ለዘላለም ለአምላክ ክብር ይሁን። አሜን።
6 አምላክ በክርስቶስ ጸጋ ከጠራችሁ በኋላ እንዲህ በፍጥነት ከእሱ ዞር ማለታችሁና* ለሌላ ዓይነት ምሥራች ጆሯችሁን መስጠታችሁ ደንቆኛል።+ 7 እንደ እውነቱ ከሆነ ሌላ ምሥራች የለም፤ ሆኖም እናንተን የሚረብሹና+ ስለ ክርስቶስ የሚናገረውን ምሥራች ለማጣመም የሚፈልጉ አንዳንድ ሰዎች አሉ። 8 ይሁን እንጂ ከመካከላችን አንዱ ወይም ከሰማይ የወረደ መልአክ፣ እኛ ከሰበክንላችሁ ምሥራች የተለየ ምሥራች ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን። 9 ቀደም ሲል እንደተናገርነው፣ አሁንም ደግሜ እላለሁ፣ ማንም ይሁን ማን ከተቀበላችሁት የተለየ ምሥራች ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን።
10 አሁን እኔ ጥረት የማደርገው የሰውን ሞገስ ለማግኘት ነው ወይስ የአምላክን? ደግሞስ ሰዎችን ለማስደሰት እየሞከርኩ ነው? አሁንም ሰዎችን እያስደሰትኩ ከሆነ የክርስቶስ ባሪያ አይደለሁም ማለት ነው። 11 ወንድሞች፣ እኔ የሰበክሁላችሁ ምሥራች ከሰው የመነጨ ምሥራች እንዳልሆነ ላሳውቃችሁ እወዳለሁ፤+ 12 ኢየሱስ ክርስቶስ በራእይ ገለጠልኝ እንጂ የተቀበልኩትም ሆነ የተማርኩት ከሰው አይደለምና።
13 በእርግጥ፣ በአይሁዳውያን ሃይማኖት+ ሳለሁ ምን ዓይነት ሰው እንደነበርኩ ሰምታችኋል፤ የአምላክን ጉባኤ ክፉኛ* አሳድድና ለማጥፋት ጥረት አደርግ ነበር፤+ 14 ለአባቶቼ ወግ ከፍተኛ ቅንዓት ስለነበረኝ ከወገኖቼ መካከል በእኔ ዕድሜ ካሉት ከብዙዎቹ የበለጠ በአይሁዳውያን ሃይማኖት የላቀ እድገት እያደረግኩ ነበር።+ 15 ሆኖም ከእናቴ ማህፀን እንድለይ* ያደረገኝና በጸጋው አማካኝነት የጠራኝ አምላክ+ 16 ስለ ክርስቶስ የሚገልጸውን ምሥራች ለአሕዛብ እንዳውጅ+ ልጁን በእኔ አማካኝነት ለመግለጥ በወደደ ጊዜ ከማንም ሰው* ጋር ወዲያው አልተማከርኩም፤ 17 በኢየሩሳሌም ወደሚገኙት ከእኔ በፊት ሐዋርያት ወደሆኑትም አልሄድኩም፤ ከዚህ ይልቅ ወደ ዓረብ አገር ሄድኩ፤ ከዚያም ወደ ደማስቆ+ ተመለስኩ።
18 ከዚያም ከሦስት ዓመት በኋላ ኬፋን*+ ለመጠየቅ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣሁ፤+ ከእሱም ጋር 15 ቀን ተቀመጥኩ። 19 ሆኖም ከጌታ ወንድም ከያዕቆብ+ በስተቀር ከሌሎቹ ሐዋርያት መካከል ማንንም አላየሁም። 20 እንግዲህ እየጻፍኩላችሁ ያለሁት ነገር ውሸት እንዳልሆነ በአምላክ ፊት ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ።
21 ከዚያ በኋላ በሶርያና በኪልቅያ ወዳሉ ክልሎች ሄድኩ።+ 22 ሆኖም በይሁዳ ያሉ የክርስቲያን ጉባኤዎች በአካል አይተውኝ አያውቁም ነበር። 23 ይሁንና “ከዚህ ቀደም ያሳድደን የነበረው ሰው፣+ ሊያጠፋው ይፈልግ ስለነበረው እምነት+ የሚገልጸውን ምሥራች አሁን እየሰበከ ነው” የሚል ወሬ ብቻ ይሰሙ ነበር። 24 ስለዚህ በእኔ ምክንያት አምላክን ከፍ ከፍ ያደርጉ ጀመር።
2 ከዚያም ከ14 ዓመት በኋላ ዳግመኛ ወደ ኢየሩሳሌም ስወጣ በርናባስ አብሮኝ ነበር፤+ ቲቶንም ይዤው ሄድኩ።+ 2 ሆኖም የሄድኩት በተገለጠልኝ ራእይ መሠረት ነበር፤ ከዚያም በአሕዛብ መካከል እየሰበክሁ ያለሁትን ምሥራች ከፍ ተደርገው በሚታዩት ወንድሞች ፊት አቀረብኩ። ይሁን እንጂ እየሮጥኩ ያለሁት ወይም የሮጥኩት ምናልባት በከንቱ እንዳይሆን ስለሰጋሁ ይህን ያስታወቅኳቸው ለብቻቸው ነበር። 3 ይሁንና ከእኔ ጋር የነበረው ቲቶ+ እንኳ ግሪካዊ ቢሆንም እንዲገረዝ አልተገደደም።+ 4 ሆኖም ይህ ጉዳይ የተነሳው ሙሉ በሙሉ ባሪያዎች ሊያደርጉን በማሰብ+ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር ባለን አንድነት ያገኘነውን ነፃነት+ ሊሰልሉ ሾልከው በስውር በገቡት ሐሰተኛ ወንድሞች ምክንያት ነው፤+ 5 እኛ ግን የምሥራቹ እውነት በእናንተ ዘንድ ጸንቶ እንዲኖር በማለት ለአንድ አፍታ* እንኳ እሺ ብለን አልተገዛንላቸውም።+
6 ወሳኝ ሰዎች ተደርገው የሚታዩትን+ በተመለከተ ግን እነዚህ ሰዎች ለእኔ የጨመሩልኝ አዲስ ነገር የለም። አዎ፣ አምላክ የሰውን ውጫዊ ማንነት አይቶ ስለማያዳላ እነዚህ ከፍ ተደርገው የሚታዩት ሰዎች ቀደም ሲል ምንም ይሁኑ ምን ለእኔ የሚያመጣው ለውጥ የለም። 7 በአንጻሩ ግን ጴጥሮስ ለተገረዙት እንዲሰብክ ምሥራቹ በአደራ እንደተሰጠው ሁሉ እኔም ላልተገረዙት እንድሰብክ ምሥራቹ በአደራ እንደተሰጠኝ በተገነዘቡ ጊዜ+ 8 (ጴጥሮስ ለተገረዙት ሐዋርያ ሆኖ እንዲያገለግል ኃይል የሰጠው አምላክ ለእኔም ከአሕዛብ ወገን የሆኑትን እንዳገለግል ኃይል ሰጥቶኛልና፤)+ 9 እንዲሁም እንደ ዓምድ የሚታዩት ያዕቆብ፣+ ኬፋና* ዮሐንስ የተሰጠኝን ጸጋ በተረዱ ጊዜ+ እነሱ ወደተገረዙት እኛ ደግሞ ወደ አሕዛብ እንድንሄድ ለእኔና ለበርናባስ+ ቀኝ እጃቸውን በመስጠት አጋርነታቸውን* ገለጹልን። 10 ይሁንና ድሆችን ማሰባችንን እንዳናቋርጥ አደራ አሉን፤ እኔም ብሆን ይህን ለመፈጸም ትጋት የተሞላበት ጥረት ሳደርግ ነበር።+
11 ይሁን እንጂ ኬፋ*+ ወደ አንጾኪያ+ በመጣ ጊዜ ፊት ለፊት ተቃወምኩት፤* ምክንያቱም ግልጽ የሆነ ስህተት ሠርቶ* ነበር። 12 የተወሰኑ ሰዎች ከያዕቆብ+ ዘንድ ከመምጣታቸው በፊት ከአሕዛብ ወገን ከሆኑ ሰዎች ጋር ይበላ ነበር፤+ እነሱ ከመጡ በኋላ ግን ከተገረዙት ወገን የሆኑትን በመፍራት ይህን ማድረጉን አቁሞ ራሱን ከአሕዛብ አገለለ።+ 13 የቀሩት አይሁዳውያንም በዚህ የግብዝነት ድርጊት* ከእሱ ጋር ተባበሩ፤ በርናባስም እንኳ በእነሱ የግብዝነት ድርጊት* ተሸንፎ ነበር። 14 ሆኖም ከምሥራቹ እውነት ጋር በሚስማማ መንገድ እየተጓዙ እንዳልሆኑ ባየሁ ጊዜ+ ኬፋን* በሁሉም ፊት እንዲህ አልኩት፦ “አንተ አይሁዳዊ ሆነህ ሳለህ እንደ አይሁዳውያን ሳይሆን እንደ አሕዛብ የምትኖር ከሆነ ከአሕዛብ ወገን የሆኑ ሰዎች እንደ አይሁዳውያን ልማድ እንዲኖሩ እንዴት ልታስገድዳቸው ትችላለህ?”+
15 በትውልዳችን አይሁዳውያን እንጂ ከአሕዛብ ወገን እንደሆኑት ኃጢአተኞች ያልሆንነው እኛ፣ 16 አንድ ሰው የሚጸድቀው ሕግን በመጠበቅ ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን+ ብቻ እንደሆነ እንገነዘባለን።+ ስለዚህ ሕግን በመጠበቅ ሳይሆን በክርስቶስ በማመን እንድንጸድቅ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነናል፤ ምክንያቱም ሕግን በመጠበቅ መጽደቅ የሚችል ሰው* የለም።+ 17 እኛ በክርስቶስ አማካኝነት መጽደቅ በመፈለጋችን እንደ ኃጢአተኞች ተደርገን ከታየን፣ ታዲያ ክርስቶስ የኃጢአት አገልጋይ ነው ማለት ነው? በጭራሽ! 18 በአንድ ወቅት እኔው ራሴ ያፈረስኳቸውን እነዚያኑ ነገሮች መልሼ የምገነባ ከሆነ ሕግ ተላላፊ መሆኔን አሳያለሁ ማለት ነው። 19 ለአምላክ ሕያው መሆን እችል ዘንድ በሕጉ በኩል ለሕጉ ሞቻለሁና።*+ 20 እኔ አሁን ከክርስቶስ ጋር በእንጨት ላይ ተቸንክሬአለሁ።+ ከዚህ በኋላ የምኖረው እኔ ሳልሆን+ ከእኔ ጋር አንድ ሆኖ የሚኖረው ክርስቶስ ነው። አሁን በሥጋ የምኖረውን ሕይወት የምኖረው በወደደኝና ለእኔ ሲል ራሱን አሳልፎ በሰጠው+ በአምላክ ልጅ ላይ ባለኝ እምነት ነው።+ 21 የአምላክን ጸጋ+ ወደ ጎን ገሸሽ አላደርግም፤* ጽድቅ የሚገኘው በሕግ አማካኝነት ከሆነማ ክርስቶስ የሞተው እንዲያው በከንቱ ነው።+
3 እናንተ ማስተዋል የጎደላችሁ የገላትያ ሰዎች! ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በእንጨት ላይ ተቸንክሮ ፊት ለፊት ያያችሁት ያህል በዓይነ ሕሊናችሁ ተስሎ ነበር፤+ ታዲያ አሁን አፍዝ አደንግዝ ያደረገባችሁ ማን ነው?+ 2 እስቲ አንድ ነገር ልጠይቃችሁ፦ መንፈስን የተቀበላችሁት ሕግን በመጠበቅ ነው ወይስ የሰማችሁትን በማመን?+ 3 ይህን ያህል ማስተዋል የጎደላችሁ ናችሁ? በመንፈሳዊ መንገድ መጓዝ ከጀመራችሁ በኋላ በሥጋዊ መንገድ ልታጠናቅቁ ታስባላችሁ?+ 4 ብዙ መከራ የተቀበላችሁት እንዲያው በከንቱ ነው? መቼም በከንቱ ነው ብዬ አላስብም። 5 መንፈስን የሚሰጣችሁና በመካከላችሁ ተአምራት የሚፈጽመው+ እሱ ይህን የሚያደርገው ሕግን በመጠበቃችሁ ነው ወይስ የሰማችሁትን በማመናችሁ? 6 ይህም አብርሃም “በይሖዋ* አመነ፤ ጽድቅም ሆኖ ተቆጠረለት” እንደተባለው ነው።+
7 የአብርሃም ልጆች የሆኑት እምነትን አጥብቀው የሚከተሉት መሆናቸውን እንደምታውቁ የተረጋገጠ ነው።+ 8 ቅዱስ መጽሐፉ፣ አምላክ ከብሔራት ወገን የሆኑ ሰዎችን በእምነት አማካኝነት ጸድቃችኋል እንደሚላቸው አስቀድሞ ተረድቶ “ብሔራት ሁሉ በአንተ አማካኝነት ይባረካሉ” በማለት ምሥራቹን ለአብርሃም አስቀድሞ አስታውቆታል።+ 9 በመሆኑም እምነትን አጥብቀው የሚይዙ በእምነት ከተመላለሰው ከአብርሃም ጋር የበረከቱ ተካፋዮች ሆነዋል።+
10 ሕግን በመጠበቅ የሚታመኑ ሁሉ የተረገሙ ናቸው፤ “በሕጉ የመጽሐፍ ጥቅልል የተጻፉትን ነገሮች ሁሉ በመፈጸም እነሱን ተግባራዊ ማድረጉን የማይቀጥል ሰው ሁሉ የተረገመ ነው” ተብሎ ተጽፏልና።+ 11 በተጨማሪም “ጻድቅ በእምነት ይኖራል” ተብሎ ስለተጻፈ+ በአምላክ ፊት ማንም በሕግ አማካኝነት ጻድቅ ሊባል እንደማይችል ግልጽ ነው።+ 12 ሕጉ በእምነት ላይ የተመሠረተ አይደለም። ከዚህ ይልቅ “ትእዛዛቱን የሚጠብቅ ማንኛውም ሰው በእነሱ አማካኝነት በሕይወት ይኖራል” ይላል።+ 13 ክርስቶስ በእኛ ፋንታ የተረገመ ሆኖ እኛን ከሕጉ እርግማን ነፃ በማውጣት+ ዋጅቶናል፤+ ምክንያቱም “በእንጨት ላይ የተሰቀለ ሰው ሁሉ የተረገመ ነው” ተብሎ ተጽፏል።+ 14 ይህም የሆነው ለአብርሃም ቃል የተገባው በረከት በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ለብሔራት እንዲደርስና+ እኛም በእምነታችን አማካኝነት ቃል የተገባውን መንፈስ ማግኘት እንድንችል ነው።+
15 ወንድሞች፣ በሰው ዕለታዊ ሕይወት የተለመደ አንድ ምሳሌ ልጠቀም፦ አንድ ቃል ኪዳን፣ በሰውም እንኳ ቢሆን አንዴ ከጸደቀ በኋላ ማንም ሊሽረው ወይም ምንም ነገር ሊጨምርበት አይችልም። 16 የተስፋው ቃል የተነገረው ለአብርሃምና ለዘሩ ነው።+ ቅዱስ መጽሐፉ ስለ ብዙዎች እንደሚናገር “ለዘሮችህ” አይልም። ከዚህ ይልቅ ስለ አንድ እንደሚናገር “ለዘርህ” ይላል፤ እሱም ክርስቶስ ነው።+ 17 በተጨማሪም ይህን እላለሁ፦ ከ430 ዓመታት በኋላ+ የተሰጠው ሕግ ቀደም ሲል አምላክ የገባውን ቃል ኪዳን አፍርሶ የተስፋውን ቃል አይሽርም። 18 ውርሻው የሚገኘው በሕግ አማካኝነት ቢሆን ኖሮ በተስፋ ቃል አማካኝነት መሆኑ በቀረ ነበርና፤ ሆኖም አምላክ ውርሻውን ለአብርሃም በደግነት የሰጠው በተስፋ ቃል አማካኝነት ነው።+
19 ታዲያ ሕግ የተሰጠው ለምንድን ነው? ሕጉ የተጨመረው፣ ቃል የተገባለት ዘር እስኪመጣ ድረስ+ ሕግ ተላላፊነትን ይፋ ለማድረግ ነው፤+ ሕጉ የተሰጠውም በመላእክት አማካኝነት+ በአንድ መካከለኛ እጅ ነው።+ 20 ይሁንና አንድ ወገን ብቻ ባለበት መካከለኛ አይኖርም፤ አምላክ ደግሞ አንድ ወገን ብቻ ነው። 21 ታዲያ ሕጉ የአምላክን የተስፋ ቃል ይጻረራል ማለት ነው? በጭራሽ! ሕይወት ሊያስገኝ የሚችል ሕግ ተሰጥቶ ቢሆን ኖሮ ጽድቅ የሚገኘው በሕግ አማካኝነት በሆነ ነበር። 22 ሆኖም ቅዱስ መጽሐፉ ሁሉም ነገሮች የኃጢአት እስረኛ እንዲሆኑ አሳልፎ ሰጥቷቸዋል፤ ይህም የሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው የተስፋ ቃል ለሚያምኑ ሁሉ ይሰጥ ዘንድ ነው።
23 ይሁን እንጂ እምነት ከመምጣቱ በፊት፣ ሊገለጥ ያለውን እምነት እየተጠባበቅን በሕግ ጥበቃ ሥር እስረኞች እንድንሆን አልፈን ተሰጥተናል።+ 24 በመሆኑም በእምነት አማካኝነት መጽደቅ እንችል ዘንድ+ ሕጉ ወደ ክርስቶስ የሚያደርስ ሞግዚታችን* ሆኗል።+ 25 አሁን ግን ያ እምነት ስለመጣ+ ከእንግዲህ ወዲህ በሞግዚት* ሥር አይደለንም።+
26 እንደ እውነቱ ከሆነ ሁላችሁም በክርስቶስ ኢየሱስ ላይ ባላችሁ እምነት የተነሳ+ የአምላክ ልጆች ናችሁ።+ 27 ወደ ክርስቶስ የተጠመቃችሁ ሁላችሁም ክርስቶስን ለብሳችኋልና።*+ 28 ሁላችሁም ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድነት በመፍጠር አንድ በመሆናችሁ+ በአይሁዳዊና በግሪካዊ፣+ በባሪያና በነፃ ሰው+ እንዲሁም በወንድና በሴት+ መካከል ልዩነት የለም። 29 በተጨማሪም የክርስቶስ ከሆናችሁ በእርግጥም የአብርሃም ዘር ናችሁ፤+ በተስፋውም ቃል መሠረት+ ወራሾች ናችሁ።+
4 እንግዲህ ይህን እላለሁ፦ ወራሹ የሁሉም ነገር ጌታ ቢሆንም እንኳ ሕፃን እስከሆነ ድረስ ከባሪያ በምንም አይለይም፤ 2 ይልቁንም አባቱ አስቀድሞ የወሰነው ቀን እስኪደርስ ድረስ በሞግዚቶችና በመጋቢዎች ሥር ሆኖ ይቆያል። 3 በተመሳሳይ እኛም ልጆች በነበርንበት ጊዜ በዓለም ውስጥ ላሉ ተራ ነገሮች ባሪያ ሆነን ቆይተናል።+ 4 ሆኖም ዘመኑ ሙሉ በሙሉ የሚጠናቀቅበት ጊዜ ሲደርስ አምላክ ከሴት የተወለደውንና+ በሕግ ሥር የነበረውን ልጁን ላከ፤+ 5 ይህን ያደረገው እኛን ልጆቹ አድርጎ መውሰድ ይችል ዘንድ+ በሕግ ሥር ያሉትን ዋጅቶ ነፃ ለማውጣት ነው።+
6 አሁን እናንተ ልጆች ስለሆናችሁ አምላክ የልጁን መንፈስ ወደ ልባችን+ ልኳል፤+ ይህም መንፈስ “አባ፣* አባት!” እያለ ይጣራል።+ 7 በመሆኑም ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ ነህ እንጂ ባሪያ አይደለህም፤ ልጅ ከሆንክ ደግሞ አምላክ ወራሽም አድርጎሃል።+
8 ይሁንና አምላክን ከማወቃችሁ በፊት በእርግጥ አማልክት ላልሆኑ ባሪያዎች ሆናችሁ ትገዙ ነበር። 9 አሁን ግን አምላክን አውቃችኋል፤ እንዲያውም አምላክ እናንተን አውቋችኋል፤ ታዲያ ደካማና ከንቱ ወደሆኑ ተራ ነገሮች መመለስና+ እንደገና ለእነዚህ ነገሮች ባሪያ መሆን ትፈልጋላችሁ?+ 10 ቀናትን፣ ወራትን፣+ ወቅቶችንና ዓመታትን በጥንቃቄ እየጠበቃችሁ ታከብራላችሁ። 11 የእናንተ ሁኔታ ያሳስበኛል፤ ምክንያቱም ለእናንተ የደከምኩት በከንቱ እንዳይሆን እሰጋለሁ።
12 ወንድሞች፣ እንደ እኔ ሁኑ ብዬ እለምናችኋለሁ፤ ምክንያቱም እኔም በአንድ ወቅት እንደ እናንተ ነበርኩ።+ እናንተ ምንም የበደላችሁኝ ነገር የለም። 13 በተጨማሪም ለመጀመሪያ ጊዜ ለእናንተ ምሥራቹን ለመስበክ አጋጣሚ ያገኘሁት በመታመሜ የተነሳ እንደነበር ታውቃላችሁ። 14 ሕመሜ ፈተና ሆኖባችሁ የነበረ ቢሆንም እንኳ አልናቃችሁኝም ወይም አልተጸየፋችሁኝም፤* ከዚህ ይልቅ እንደ አምላክ መልአክ ወይም እንደ ክርስቶስ ኢየሱስ ተቀበላችሁኝ። 15 ታዲያ ያ ሁሉ ደስታችሁ የት ጠፋ? የሚቻል ቢሆን ኖሮ ዓይናችሁን እንኳ አውጥታችሁ ትሰጡኝ እንደነበር እርግጠኛ ነኝ።+ 16 ታዲያ እውነቱን ስለምነግራችሁ ጠላት ሆንኩባችሁ ማለት ነው? 17 እነሱ ወደ ራሳቸው ሊስቧችሁ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ፤ ይህን የሚያደርጉት ግን ለበጎ ሳይሆን እናንተን ከእኔ በማራቅ እነሱን አጥብቃችሁ እንድትከተሏቸው ለማድረግ ነው። 18 ይሁን እንጂ አንድ ሰው ምንጊዜም እናንተን አጥብቆ የሚፈልገው ለበጎ ዓላማ ከሆነ ጥሩ ነው፤ ይህም መሆን ያለበት እኔ ከእናንተ ጋር ስሆን ብቻ አይደለም፤ 19 የምወዳችሁ ልጆቼ፣+ ክርስቶስ በውስጣችሁ እስኪቀረጽ ድረስ በእናንተ ምክንያት እንደገና ምጥ ይዞኛል። 20 በእናንተ ግራ ስለተጋባሁ አሁን በመካከላችሁ ተገኝቼ ለየት ባለ መንገድ ላነጋግራችሁ ብችል ደስ ባለኝ ነበር።
21 እናንተ በሕግ ሥር መኖር የምትፈልጉ እስቲ ንገሩኝ፤ ሕጉ የሚለውን አትሰሙም? 22 ለምሳሌ ያህል፣ አብርሃም አንዱ ከአገልጋዪቱ፣+ ሌላው ደግሞ ከነፃዪቱ ሴት+ የተወለዱ ሁለት ወንዶች ልጆች እንደነበሩት ተጽፏል፤ 23 ሆኖም ከአገልጋዪቱ የተገኘው ልጅ የተወለደው በሥጋዊ መንገድ*+ ሲሆን ከነፃዪቱ ሴት የተገኘው ልጅ ደግሞ የተወለደው በተስፋ ቃል መሠረት ነው።+ 24 እነዚህ ሴቶች ሁለት ቃል ኪዳኖችን ስለሚወክሉ እነዚህ ነገሮች ምሳሌያዊ ትርጉም አላቸው፤ አንደኛው ቃል ኪዳን የተገባው በሲና ተራራ+ ሲሆን በዚህ ቃል ኪዳን ሥር ያሉት ልጆች ሁሉ ባሪያዎች ናቸው፤ ይህ ቃል ኪዳን ደግሞ አጋርን ያመለክታል። 25 አጋር፣ በዓረብ አገር የሚገኘውን የሲና ተራራ+ የምትወክል ሲሆን ዛሬ ካለችው ኢየሩሳሌም ጋር ትመሳሰላለች፤ ኢየሩሳሌም ከልጆቿ ጋር በባርነት ሥር ናትና። 26 ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም ግን ነፃ ናት፤ እሷም እናታችን ናት።
27 “አንቺ የማትወልጂ መሃን ሴት፣ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ ምጥ የማታውቂ ሴት፣ እልል በይ፣ ጩኺም፤ ምክንያቱም ባል ካላት ሴት ይልቅ የተተወችው ሴት ልጆች እጅግ በዝተዋል” ተብሎ ተጽፏልና።+ 28 እንግዲህ ወንድሞች፣ እንደ ይስሐቅ የተስፋው ቃል ልጆች ናችሁ።+ 29 ሆኖም ያን ጊዜ በሥጋዊ መንገድ* የተወለደው በመንፈስ የተወለደውን ማሳደድ እንደጀመረ+ ሁሉ አሁንም እንደዚያው ነው።+ 30 ይሁንና ቅዱስ መጽሐፉ ምን ይላል? “የአገልጋዪቱ ልጅ ከነፃዪቱ ልጅ ጋር በምንም ዓይነት አብሮ ስለማይወርስ አገልጋዪቱን ከነልጅዋ አባር።”+ 31 ስለዚህ ወንድሞች፣ እኛ የነፃዪቱ ልጆች እንጂ የአገልጋዪቱ ልጆች አይደለንም።
5 ክርስቶስ ነፃ ያወጣን እንዲህ ዓይነት ነፃነት እንድናገኝ ነው። ስለዚህ ጸንታችሁ ቁሙ፤+ ዳግመኛ ራሳችሁን በባርነት ቀንበር አታስጠምዱ።+
2 እኔ ጳውሎስ፣ የምትገረዙ ከሆነ ክርስቶስ ለእናንተ ምንም እንደማይጠቅማችሁ አሳውቃችኋለሁ።+ 3 የሚገረዝ እያንዳንዱ ሰው መላውን ሕግ የመጠበቅ ግዴታ እንዳለበት ዳግመኛ አሳስበዋለሁ።+ 4 እናንተ በሕግ አማካኝነት ለመጽደቅ ስለምትጥሩ ከክርስቶስ ተለይታችኋል፤+ ከጸጋውም ርቃችኋል። 5 እኛ ግን ተስፋ የምናደርገውን በእምነት የሚገኘውን ጽድቅ በመንፈስ አማካኝነት በጉጉት እንጠባበቃለን። 6 ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድነት ላላቸው በፍቅር የሚመራ እምነት እንጂ መገረዝ ወይም አለመገረዝ ፋይዳ የለውም።+
7 በአግባቡ ትሮጡ ነበር፤+ ታዲያ ለእውነት መታዘዛችሁን እንዳትቀጥሉ እንቅፋት የሆነባችሁ ማን ነው? 8 እንዲህ ያለው ማግባቢያ እየጠራችሁ ካለው የመጣ አይደለም። 9 ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ ያቦካል።+ 10 ከጌታ ጋር አንድነት ያላችሁ ሁሉ+ የተለየ ሐሳብ እንደማይኖራችሁ እተማመናለሁ፤ ሆኖም እያወካችሁ+ ያለው ማንም ይሁን ማን የሚገባውን ፍርድ ይቀበላል። 11 ወንድሞች፣ እኔ አሁንም ስለ መገረዝ እየሰበክሁ ከሆነ እስካሁን ለምን ስደት ይደርስብኛል? እንደዚያማ ቢሆን ኖሮ የመከራው እንጨት* እንቅፋት+ መሆኑ በቀረ ነበር። 12 ሊያውኳችሁ እየሞከሩ ያሉት ሰዎች ከናካቴው ቢሰለቡ* ደስታዬ ነው።
13 ወንድሞች፣ የተጠራችሁት ነፃ እንድትወጡ ነው፤ ብቻ ይህን ነፃነት የሥጋን ፍላጎት ለማርካት አትጠቀሙበት፤+ ይልቁንም አንዳችሁ ሌላውን በፍቅር አገልግሉ።+ 14 መላው ሕግ “ባልንጀራህን* እንደ ራስህ ውደድ” በሚለው አንድ ትእዛዝ ተፈጽሟልና።*+ 15 ይሁንና እርስ በርሳችሁ መነካከሳችሁንና መባላታችሁን ካልተዋችሁ+ እርስ በርስ ልትጠፋፉ ስለምትችሉ ተጠንቀቁ።+
16 እኔ ግን በመንፈስ መመላለሳችሁን ቀጥሉ እላለሁ፤+ እንዲህ ካደረጋችሁ የሥጋን ምኞት ከቶ አትፈጽሙም።+ 17 የሥጋ ፍላጎት ከመንፈስ ፍላጎት ጋር፣ የመንፈስ ፍላጎት ደግሞ ከሥጋ ፍላጎት ጋር አይጣጣምም፤ እነዚህ እርስ በርሳቸው ይቃረናሉ። ስለሆነም ማድረግ የምትፈልጉትን አታደርጉም።+ 18 በተጨማሪም በመንፈስ የምትመሩ ከሆነ በሕግ ሥር አይደላችሁም።
19 የሥጋ ሥራዎች በግልጽ የታወቁ ናቸው፤ እነሱም፦ የፆታ ብልግና፣*+ ርኩሰት፣ ማንአለብኝነት፣*+ 20 ጣዖት አምልኮ፣ መናፍስታዊ ድርጊት፣*+ ጥላቻ፣ ጠብ፣ ቅናት፣ በቁጣ መገንፈል፣ ጭቅጭቅ፣ መከፋፈል፣ መናፍቅነት፣ 21 ምቀኝነት፣ ሰካራምነት፣+ መረን የለቀቀ ፈንጠዝያና እነዚህን የመሳሰሉ ናቸው።+ እነዚህን በተመለከተ አስቀድሜ እንዳስጠነቀቅኳችሁ ሁሉ አሁንም አስጠነቅቃችኋለሁ፤ እንዲህ ያሉትን ነገሮች የሚፈጽሙ* የአምላክን መንግሥት አይወርሱም።+
22 በሌላ በኩል ግን የመንፈስ ፍሬ ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ደግነት፣ ጥሩነት፣+ እምነት፣ 23 ገርነት፣* ራስን መግዛት ነው።+ እንዲህ ያሉትን ነገሮች የሚከለክል ሕግ የለም። 24 ከዚህም በተጨማሪ የክርስቶስ ኢየሱስ የሆኑት ሥጋን ከመጥፎ ምኞቱና ፍላጎቱ ጋር በእንጨት ላይ ቸንክረውታል።*+
25 በመንፈስ የምንኖር ከሆነ መንፈስ የሚሰጠንን አመራር በመከተል ምንጊዜም በሥርዓት እንመላለስ።+ 26 በመካከላችን የፉክክር መንፈስ በማነሳሳትና+ አንዳችን ሌላውን በመመቅኘት በከንቱ አንመካ።+
6 ወንድሞች፣ አንድ ሰው ሳያውቅ የተሳሳተ ጎዳና ቢከተል መንፈሳዊ ብቃት ያላችሁ እናንተ እንዲህ ዓይነቱን ሰው በገርነት* መንፈስ ለማስተካከል ጥረት አድርጉ።+ ይሁንና እናንተም ፈተና ላይ እንዳትወድቁ+ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።+ 2 አንዳችሁ የሌላውን ከባድ ሸክም ተሸከሙ፤+ በዚህ መንገድ የክርስቶስን ሕግ ትፈጽማላችሁ።+ 3 አንድ ሰው ምንም ሳይሆን ራሱን ከፍ አድርጎ የሚመለከት ከሆነ+ ራሱን እያታለለ ነው። 4 ከዚህ ይልቅ እያንዳንዱ ሰው የራሱን ተግባር ይመርምር፤+ ከዚያም ራሱን ከሌላ ሰው ጋር ሳያወዳድር+ ከራሱ ጋር ብቻ በተያያዘ እጅግ የሚደሰትበት ነገር ያገኛል። 5 እያንዳንዱ የራሱን የኃላፊነት ሸክም ይሸከማልና።+
6 ከዚህም በተጨማሪ ቃሉን በመማር ላይ ያለ ማንኛውም ሰው፣ ይህን ትምህርት* ከሚያስተምረው ሰው ጋር መልካም ነገሮችን ሁሉ ይካፈል።+
7 አትታለሉ፤ አምላክ አይዘበትበትም። አንድ ሰው ምንም ዘራ ምን ያንኑ መልሶ ያጭዳል፤+ 8 ምክንያቱም ለሥጋው ብሎ የሚዘራ ከሥጋው መበስበስን ያጭዳል፤ ለመንፈስ ብሎ የሚዘራ ግን ከመንፈስ የዘላለም ሕይወት ያጭዳል።+ 9 ካልታከትን* ጊዜው ሲደርስ ስለምናጭድ ተስፋ ቆርጠን መልካም ሥራ መሥራታችንን አንተው።+ 10 እንግዲያው ይህን ለማድረግ የሚያስችል አጋጣሚ* እስካገኘን ድረስ ለሁሉም፣ በተለይ ደግሞ በእምነት ለሚዛመዱን ሰዎች መልካም እናድርግ።
11 በራሴ እጅ እንዴት ባሉ ትላልቅ ፊደላት እንደጻፍኩላችሁ ተመልከቱ።
12 በሥጋ ተቀባይነት ለማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ* እንድትገረዙ ሊያስገድዷችሁ ይሞክራሉ፤ ይህን የሚያደርጉት ግን በክርስቶስ የመከራ እንጨት* ሳቢያ ስደት እንዳይደርስባቸው ነው። 13 እነሱ እንድትገረዙ የሚፈልጉት በእናንተ ሥጋ ለመኩራራት ብለው ነው እንጂ የተገረዙት ራሳቸውም እንኳ ሕጉን አይጠብቁም።+ 14 ይሁንና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የመከራ እንጨት* ካልሆነ በስተቀር በሌላ ነገር ፈጽሞ መኩራራት አልፈልግም፤+ በእሱ የተነሳ፣ በእኔ አመለካከት ዓለም ሞቷል፤* በዓለም አመለካከት ደግሞ እኔ ሞቻለሁ።* 15 መገረዝም ሆነ አለመገረዝ ምንም አይጠቅምም፤+ ከዚህ ይልቅ የሚጠቅመው አዲስ ፍጥረት መሆን ነው።+ 16 ይህን የሥነ ምግባር ደንብ በመከተል በሥርዓት በሚመላለሱ ሁሉ ይኸውም በአምላክ እስራኤል+ ላይ ሰላምና ምሕረት ይሁን።
17 የኢየሱስ ባሪያ መሆኔን የሚያሳይ መለያ ምልክት በሰውነቴ ላይ ስላለ+ ከእንግዲህ ወዲህ ማንም አያስቸግረኝ።
18 ወንድሞች፣ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከምታሳዩት መንፈስ ጋር ይሁን። አሜን።
ወይም “ክፉ ዘመን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “እንዲህ በፍጥነት ከእሱ እየራቃችሁ መሄዳችሁና።”
ቃል በቃል “ያለልክ።”
ወይም “እንድወለድ።”
ቃል በቃል “ከሥጋና ከደም።”
ጴጥሮስ ተብሎም ይጠራል።
ቃል በቃል “ለአንድ ሰዓት።”
ጴጥሮስ ተብሎም ይጠራል።
ወይም “ትብብራቸውን።”
ጴጥሮስ ተብሎም ይጠራል።
ወይም “ተጋፈጥኩት።”
ወይም “ሊወገዝ ይገባው።”
ወይም “የማስመሰል ድርጊት።”
ወይም “የማስመሰል ድርጊት።”
ጴጥሮስ ተብሎም ይጠራል።
ቃል በቃል “ሥጋ።”
ወይም “ከሕጉ ነፃ ወጥቻለሁና።”
ወይም “አሽቀንጥሬ አልጥልም።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “አስተማሪያችን።”
ወይም “በአስተማሪ።”
ወይም “እንደ ክርስቶስ ሆናችኋልና።”
“አባት ሆይ!” የሚል ትርጉም ያለው የአረማይክ ቃል ነው።
ወይም “እንትፍ አላላችሁብኝም።”
ወይም “እንደ ማንኛውም ሰው።”
ወይም “እንደ ማንኛውም ሰው።”
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ጃንደረባ ቢሆኑ።” እንዲህ መሆናቸው የሚደግፉትን ሕግ ለመፈጸም ብቃት እንዳይኖራቸው ያደርጋቸዋል።
“ባልንጀራ” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል የአንድን ሰው የቅርብ ጓደኛ ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም ሰው ሊያመለክት ይችላል።
“ተጠቃሏልና” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ግሪክኛ፣ ፖርኒያ። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “እፍረተ ቢስነት የሚንጸባረቅበት ምግባር።” ግሪክኛ፣ አሴልጊያ። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ጥንቆላ፤ መድኃኒተኝነት።”
እንዲህ ያሉ ነገሮችን የመሥራት ልማድ ያላቸውን ያመለክታል።
“ልዝብ፤ ለስላሳ፤ ሸካራ ያልሆነ” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “ገድለውታል።”
“ልዝብ፤ ለስላሳ፤ ሸካራ ያልሆነ” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “ይህን የቃል ትምህርት።”
ወይም “ተስፋ ካልቆረጥን።”
ቃል በቃል “የተቀጠረ ጊዜ።”
ወይም “ከውጭ ሲያዩአቸው ጥሩ መስለው መታየት የሚፈልጉ ሁሉ።”
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “በእንጨት ላይ ተሰቅሏል።”
ወይም “በእንጨት ላይ ተሰቅያለሁ።”