የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • nwt ኢያሱ 1:1-24:33
  • ኢያሱ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ኢያሱ
  • አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
ኢያሱ

ኢያሱ

1 የይሖዋ አገልጋይ ሙሴ ከሞተ በኋላ ይሖዋ የሙሴ አገልጋይ+ የነበረውን የነዌን ልጅ ኢያሱን*+ እንዲህ አለው፦ 2 “አገልጋዬ ሙሴ ሞቷል።+ እንግዲህ አንተም ሆንክ ይህ ሕዝብ ተነስታችሁ ዮርዳኖስን በመሻገር ለእስራኤላውያን ወደምሰጣቸው ምድር ግቡ።+ 3 ለሙሴ በገባሁት ቃል መሠረት እግራችሁ የሚረግጠውን ቦታ ሁሉ እሰጣችኋለሁ።+ 4 ግዛታችሁም ከምድረ በዳው እስከ ሊባኖስና እስከ ታላቁ ወንዝ እስከ ኤፍራጥስ ድረስ ይኸውም መላው የሂታውያን+ ምድር እንዲሁም በስተ ምዕራብ* እስካለው እስከ ታላቁ ባሕር* ድረስ ይሆናል።+ 5 በሕይወት ዘመንህ ሁሉ ማንም አይቋቋምህም።+ ከሙሴ ጋር እንደነበርኩ ሁሉ ከአንተም ጋር እሆናለሁ።+ አልጥልህም ወይም አልተውህም።+ 6 ይህን ሕዝብ ለአባቶቻቸው ልሰጣቸው ወደማልኩላቸው ምድር+ የምታስገባው አንተ ስለሆንክ ደፋርና ብርቱ ሁን።+

7 “ብቻ አንተ ደፋርና ብርቱ ሁን፤ አገልጋዬ ሙሴ ያዘዘህን ሕግ በሙሉ በጥንቃቄ ፈጽም። በምትሄድበት በየትኛውም ቦታ ማንኛውንም ነገር በጥበብ ማከናወን እንድትችል+ ከዚህ ሕግ ወደ ቀኝም ሆነ ወደ ግራ ዞር አትበል።+ 8 ይህ የሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፤+ በውስጡ የተጻፈውንም በጥንቃቄ መፈጸም እንድትችል ቀንም ሆነ ሌሊት በለሆሳስ አንብበው፤*+ እንዲህ ካደረግክ መንገድህ ይቃናልሃል፤ እንዲሁም ማንኛውንም ነገር በጥበብ ማከናወን ትችላለህ።+ 9 ደፋርና ብርቱ ሁን ብዬ አዝዤህ አልነበረም? አምላክህ ይሖዋ በምትሄድበት ሁሉ ከአንተ ጋር ስለሆነ አትሸበር፤ አትፍራ።”+

10 ከዚያም ኢያሱ የሕዝቡን አለቆች እንዲህ ሲል አዘዛቸው፦ 11 “በሰፈሩ ውስጥ በመዘዋወር ሕዝቡን እንዲህ በማለት እዘዙ፦ ‘አምላካችሁ ይሖዋ ርስት አድርጎ የሚሰጣችሁን ምድር ገብታችሁ ለመውረስ በሦስት ቀን ውስጥ ዮርዳኖስን ስለምትሻገሩ ስንቃችሁን አዘጋጁ።’”+

12 ኢያሱም ለሮቤላውያን፣ ለጋዳውያንና ለምናሴ ነገድ እኩሌታ እንዲህ አላቸው፦ 13 “የይሖዋ አገልጋይ ሙሴ እንዲህ በማለት ያዘዛችሁን ቃል አስታውሱ፦+ ‘አምላካችሁ ይሖዋ እረፍት ሰጥቷችኋል፤ ይህን ምድር አውርሷችኋል። 14 ሚስቶቻችሁ፣ ልጆቻችሁና ከብቶቻችሁ ሙሴ በሰጣችሁ ከዮርዳኖስ ወዲህ ባለው ምድር* ላይ ይቀመጣሉ፤+ ሆኖም ብርቱ የሆናችሁት ተዋጊዎች በሙሉ+ የጦርነት አሰላለፍ በመከተል ወንድሞቻችሁን ቀድማችሁ ትሻገራላችሁ።+ እነሱን መርዳት ይገባችኋል፤ 15 ይሖዋ ለእናንተ እንዳደረገው ሁሉ ለወንድሞቻችሁም እረፍት እስከሚሰጣቸውና አምላካችሁ ይሖዋ የሚሰጣቸውን ምድር እስከሚወርሱ ድረስ ይህን ማድረግ ይኖርባችኋል። ከዚያም እንድትይዟትና እንድትወርሷት ወደተሰጠቻችሁ ይኸውም የይሖዋ አገልጋይ ሙሴ ወደሰጣችሁ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ወደምትገኘው ምድር ትመለሳላችሁ።’”+

16 እነሱም ለኢያሱ እንዲህ ሲሉ መለሱለት፦ “የምታዘንን ሁሉ እንፈጽማለን፤ ወደምትልከንም ሁሉ እንሄዳለን።+ 17 ሙሴ የሚለንን ማንኛውንም ነገር እንሰማ እንደነበር ሁሉ አንተንም እንሰማለን። ብቻ አምላክህ ይሖዋ ከሙሴ ጋር እንደነበረ ሁሉ ከአንተም ጋር ይሁን።+ 18 መመሪያህን አልታዘዝም የሚልና የምትሰጠውን ትእዛዝ ሁሉ የማይሰማ ማንኛውም ሰው ይገደል።+ ብቻ አንተ ደፋርና ብርቱ ሁን።”+

2 ከዚያም የነዌ ልጅ ኢያሱ ከሺቲም+ ሁለት ሰላዮችን በድብቅ ላከ። እነሱንም “እስቲ ሄዳችሁ ምድሪቱን በተለይም ኢያሪኮን አይታችሁ ኑ” አላቸው። ሰዎቹም ሄደው ረዓብ+ ወደተባለች አንዲት ዝሙት አዳሪ ቤት ገቡ፤ በዚያም አረፉ። 2 የኢያሪኮም ንጉሥ “እስራኤላውያን የሆኑ ሰዎች ምድሪቱን ለመሰለል ዛሬ ማታ ወደዚህ መጥተዋል” ተብሎ ተነገረው። 3 በዚህ ጊዜ የኢያሪኮ ንጉሥ ወደ ረዓብ እንዲህ የሚል መልእክት ላከባት፦ “ቤትሽ መጥተው ያረፉትን ሰዎች አውጪ፤ ምክንያቱም ወደዚህ የመጡት ምድሪቱን በሙሉ ለመሰለል ነው።”

4 ሴትየዋ ግን ሁለቱን ሰዎች ደበቀቻቸው። ከዚያም እንዲህ አለች፦ “በእርግጥ ሰዎቹ ወደ እኔ መጥተው ነበር፤ ሆኖም ከየት እንደመጡ አላወቅኩም። 5 ምሽት ላይ የከተማዋ በር ሊዘጋ ሲል ወጥተው ሄደዋል። ወዴት እንደሄዱ አላውቅም፤ ሆኖም ፈጥናችሁ ከተከታተላችኋቸው ልትደርሱባቸው ትችላላችሁ።” 6 (ይሁንና ሰዎቹን ጣሪያ ላይ ይዛቸው ወጥታ በተረበረበ የተልባ እግር ውስጥ ደብቃቸው ነበር።) 7 ሰዎቹም ሰላዮቹን በመከታተል ወደ ዮርዳኖስ አቅጣጫ በመልካው*+ በኩል ሄዱ፤ አሳዳጆቹ ወጥተው እንደሄዱም የከተማዋ በር ተዘጋ።

8 እሷም ሰላዮቹ ከመተኛታቸው በፊት እነሱ ወዳሉበት ወደ ጣሪያው ወጣች። 9 እንዲህም አለቻቸው፦ “ይሖዋ ምድሪቱን እንደሚሰጣችሁ አውቃለሁ፤+ እኛም እናንተን በመፍራት ተሸብረናል።+ የምድሪቱ ነዋሪዎች በሙሉ በእናንተ የተነሳ ልባቸው ከድቷቸዋል፤+ 10 ምክንያቱም ከግብፅ በወጣችሁ ጊዜ ይሖዋ ቀይ ባሕርን በፊታችሁ እንዴት እንዳደረቀው+ እንዲሁም ከዮርዳኖስ ማዶ* በደመሰሳችኋቸው በሁለቱ የአሞራውያን ነገሥታት፣ በሲሖንና+ በኦግ+ ላይ ምን እንዳደረጋችሁ ሰምተናል። 11 ይህን ስንሰማ ልባችን ቀለጠ፤ በእናንተም የተነሳ ወኔ ያልከዳው ማንም አልነበረም፤ ምክንያቱም አምላካችሁ ይሖዋ በላይ በሰማይ በታችም በምድር አምላክ ነው።+ 12 እንግዲህ እኔ ታማኝ ፍቅር እንዳሳየኋችሁ ሁሉ እናንተም ለአባቴ ቤት ታማኝ ፍቅር እንደምታሳዩ እባካችሁ በይሖዋ ማሉልኝ፤ እንዲሁም አስተማማኝ ምልክት ስጡኝ። 13 አባቴን፣ እናቴን፣ ወንድሞቼን፣ እህቶቼንና የእነሱ የሆነውን ሁሉ አትርፉልኝ፤ ከሞትም ታደጉን።”*+

14 በዚህ ጊዜ ሰዎቹ እንዲህ አሏት፦ “በእናንተ ምትክ ሕይወታችንን እንሰጣለን!* ስለ ተልእኳችን ካልተናገራችሁ ይሖዋ ምድሪቱን በሚሰጠን ጊዜ ታማኝ ፍቅርና ታማኝነት እናሳያችኋለን።” 15 እሷም ሰዎቹን በመስኮት በኩል በገመድ አወረደቻቸው፤ ምክንያቱም ቤቷ ከከተማው ቅጥር ጋር ተያይዞ የተሠራ ነበር። እንዲያውም የምትኖረው ቅጥሩ ላይ ነበር።+ 16 ከዚያም እንዲህ አለቻቸው፦ “የሚያሳድዷችሁ ሰዎች እንዳያገኟችሁ ወደ ተራራማው አካባቢ ሄዳችሁ ለሦስት ቀን ተደበቁ። ከዚያም የሚያሳድዷችሁ ሰዎች ከተመለሱ በኋላ ወደምትፈልጉት ቦታ መሄድ ትችላላችሁ።”

17 ሰዎቹም እንዲህ አሏት፦ “እንደሚከተለው ካላደረግሽ ባስማልሽን በዚህ መሐላ ተጠያቂ አንሆንም፦+ 18 ወደ ምድሪቱ በምንገባበት ጊዜ ይህን ቀይ ገመድ እኛን ባወረድሽበት መስኮት በኩል አንጠልጥይው። እንዲሁም አባትሽ፣ እናትሽ፣ ወንድሞችሽና የአባትሽ ቤት በሙሉ ቤትሽ ውስጥ እንዲሰበሰቡ ማድረግ አለብሽ።+ 19 ከቤትሽ ወጥቶ ደጅ የሚገኝ ማንኛውም ሰው ደሙ በራሱ ላይ ይሆናል፤ እኛም ከበደል ነፃ እንሆናለን። ሆኖም ከአንቺ ጋር ቤት ውስጥ ያለ ማንኛውም ሰው ጉዳት ቢደርስበት* ደሙ በእኛ ላይ ይሆናል። 20 ስለ ተልእኳችን ከተናገርሽ+ ግን ባስማልሽን በዚህ መሐላ ተጠያቂ አንሆንም።” 21 እሷም “እንዳላችሁት ይሁን” አለቻቸው።

ከዚያም አሰናበተቻቸው፤ እነሱም ሄዱ። እሷም ቀዩን ገመድ መስኮቱ ላይ አሰረችው። 22 እነሱም ወደ ተራራማው አካባቢ ሄደው አሳዳጆቹ እስኪመለሱ ድረስ በዚያ ለሦስት ቀን ተቀመጡ። አሳዳጆቹም በየመንገዱ ሁሉ ፈለጓቸው፤ ሆኖም አላገኟቸውም። 23 ከዚያም ሁለቱ ሰዎች ከተራራማው አካባቢ ወርደው ወንዙን በመሻገር ወደ ነዌ ልጅ ወደ ኢያሱ መጡ። ያጋጠማቸውንም ሁሉ ነገሩት። 24 ኢያሱንም እንዲህ አሉት፦ “ይሖዋ ምድሪቱን በሙሉ በእጃችን ሰጥቶናል።+ እንዲያውም የምድሪቱ ነዋሪዎች ሁሉ በእኛ የተነሳ ልባቸው ከድቷቸዋል።”+

3 ከዚያም ኢያሱ በማለዳ ተነሳ፤ እሱም ሆነ እስራኤላውያን* በሙሉ ከሺቲም+ ተነስተው ወደ ዮርዳኖስ መጡ። ወደ ማዶም ሳይሻገሩ እዚያው አደሩ።

2 ከሦስት ቀን በኋላም አለቆቹ+ በሰፈሩ ውስጥ በመዘዋወር 3 ሕዝቡን እንዲህ በማለት አዘዙ፦ “ሌዋውያን የሆኑት ካህናት+ የአምላካችሁን የይሖዋን የቃል ኪዳን ታቦት ተሸክመው ስታዩ ከሰፈራችሁበት ቦታ ተነስታችሁ ታቦቱን ተከተሉት። 4 ሆኖም ወደ እሱ አትቅረቡ፤ በእናንተና በታቦቱ መካከል 2,000 ክንድ* ያህል ርቀት ይኑር፤ ከዚህ በፊት በዚህ አቅጣጫ ሄዳችሁ ስለማታውቁ በየትኛው መንገድ መሄድ እንዳለባችሁ በዚህ ትረዳላችሁ።”

5 ኢያሱም ሕዝቡን “ይሖዋ በነገው ዕለት በመካከላችሁ ድንቅ ነገሮችን ስለሚያደርግ+ ራሳችሁን ቀድሱ”+ አላቸው።

6 ከዚያም ኢያሱ ካህናቱን “የቃል ኪዳኑን ታቦት አንስታችሁ+ ከሕዝቡ ቀድማችሁ ሂዱ” አላቸው። በመሆኑም ካህናቱ የቃል ኪዳኑን ታቦት በማንሳት ከሕዝቡ ቀድመው ሄዱ።

7 ይሖዋም ኢያሱን እንዲህ አለው፦ “ከሙሴ ጋር እንደነበርኩ ሁሉ+ ከአንተም ጋር መሆኔን እንዲያውቁ+ በዛሬው ዕለት አንተን በእስራኤላውያን ሁሉ ፊት ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ።+ 8 አንተም የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙትን ካህናት ‘ዮርዳኖስ ውኃ ዳር ስትደርሱ እዚያው ዮርዳኖስ ውስጥ ባላችሁበት ቁሙ’ ብለህ እዘዛቸው።”+

9 ኢያሱም እስራኤላውያንን “ወደዚህ ቀርባችሁ የአምላካችሁን የይሖዋን ቃል ስሙ” አላቸው። 10 ከዚያም እንዲህ አላቸው፦ “እንግዲህ በመካከላችሁ ሕያው አምላክ እንዳለና+ እሱም ከነአናውያንን፣ ሂታውያንን፣ ሂዋውያንን፣ ፈሪዛውያንን፣ ገርጌሻውያንን፣ አሞራውያንንና ኢያቡሳውያንን በእርግጥ ከፊታችሁ እንደሚያባርራቸው በዚህ ታውቃላችሁ።+ 11 የምድር ሁሉ ጌታ የቃል ኪዳን ታቦት ቀድሟችሁ ወደ ዮርዳኖስ ይገባል። 12 እናንተም ከእስራኤል ነገዶች 12 ሰዎችን ይኸውም ከእያንዳንዱ ነገድ አንድ አንድ ሰው ምረጡ፤+ 13 የምድር ሁሉ ጌታ የሆነውን የይሖዋን የቃል ኪዳን ታቦት የተሸከሙት ካህናት እግር የዮርዳኖስን ውኃ ሲነካ* ከላይ የሚወርደው ውኃ ይቋረጣል፤ ውኃውም ልክ እንደ ግድብ* ቀጥ ብሎ ይቆማል።”+

14 ስለዚህ ሕዝቡ ዮርዳኖስን ለመሻገር ድንኳኑን ነቅሎ ሲነሳ የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙት ካህናት+ ሕዝቡን ቀድመው ሄዱ። 15 ታቦቱን የተሸከሙት ካህናት ዮርዳኖስ ጋ ሲደርሱና እግራቸውን ውኃው ዳር ሲያጠልቁ (ወቅቱ መከር ስለነበር በመከር ጊዜ እንደሚሆነው ሁሉ የዮርዳኖስ ወንዝ ሞልቶ ዳርቻውን አጥለቅልቆት ነበር)+ 16 ከላይ ይወርድ የነበረው ውኃ ቆመ። ውኃውም በሩቅ ይኸውም በጻረታን አጠገብ በምትገኘው በአዳም ከተማ እንደ ግድብ* ተቆልሎ ቆመ፤ በአረባ ወደሚገኘው ባሕር ይኸውም ወደ ጨው ባሕር* የሚወርደውም ውኃ ደረቀ። ውኃው ተቋርጦ ስለነበር ሕዝቡ ከኢያሪኮ ማዶ ወዳለው ስፍራ ተሻገረ። 17 እስራኤላውያን በሙሉ በደረቅ መሬት እስኪሻገሩ+ ይኸውም መላው ብሔር ዮርዳኖስን ተሻግሮ እስኪያበቃ ድረስ የይሖዋን የቃል ኪዳን ታቦት የተሸከሙት ካህናት በዮርዳኖስ መካከል በደረቅ መሬት ላይ ባሉበት ቆመው ነበር።+

4 መላው ብሔር ዮርዳኖስን እንደተሻገረ ይሖዋ ኢያሱን እንዲህ አለው፦ 2 “ከሕዝቡ መካከል 12 ሰዎችን ይኸውም ከእያንዳንዱ ነገድ አንድ አንድ ሰው ምረጥ፤+ 3 እነሱንም እንዲህ ብለህ እዘዛቸው፦ ‘ከዮርዳኖስ ወንዝ መሃል ይኸውም የካህናቱ እግር ከቆመበት ስፍራ+ 12 ድንጋዮችን ውሰዱ፤ ድንጋዮቹንም ይዛችሁ በመሄድ በምታድሩበት ስፍራ አስቀምጧቸው።’”+

4 በመሆኑም ኢያሱ ከእስራኤላውያን መካከል የሾማቸውን 12 ሰዎች ይኸውም ከእያንዳንዱ ነገድ አንድ አንድ ሰው ጠራ፤ 5 ኢያሱም እንዲህ አላቸው፦ “የአምላካችሁን የይሖዋን ታቦት ቀድማችሁ ወደ ዮርዳኖስ መሃል ሂዱ፤ እያንዳንዳችሁም በእስራኤላውያን ነገዶች ቁጥር ልክ አንድ አንድ ድንጋይ አንስታችሁ በትከሻችሁ ተሸከሙ፤ 6 ይህም በመካከላችሁ እንደ ምልክት ሆኖ ያገለግላል። ምናልባት ወደፊት ልጆቻችሁ* ‘እነዚህን ድንጋዮች እዚህ ያስቀመጣችኋቸው ለምንድን ነው?’ ብለው ቢጠይቋችሁ+ 7 እንዲህ በሏቸው፦ ‘የዮርዳኖስ ውኃ በይሖዋ የቃል ኪዳን ታቦት ፊት ተቋርጦ ስለነበር ነው።+ ታቦቱ ዮርዳኖስን ሲሻገር የዮርዳኖስ ውኃ ተቋረጠ። እነዚህ ድንጋዮች ለእስራኤላውያን በዘላቂነት እንደ መታሰቢያ* ሆነው ያገለግላሉ።’”+

8 እስራኤላውያንም ኢያሱ እንዳዘዛቸው አደረጉ። እነሱም ይሖዋ ኢያሱን ባዘዘው መሠረት ከዮርዳኖስ መሃል በእስራኤላውያን ነገዶች ቁጥር ልክ 12 ድንጋዮችን አነሱ። ከዚያም ወደሚያድሩበት ስፍራ ይዘዋቸው በመሄድ እዚያ አስቀመጧቸው።

9 በተጨማሪም ኢያሱ የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙት ካህናት እግር ቆሞበት በነበረው በዮርዳኖስ መሃል ባለው ቦታ+ ላይ 12 ድንጋዮችን አስቀምጦ ነበር፤ እነዚህም ድንጋዮች እስከ ዛሬ ድረስ በዚያ ይገኛሉ።

10 ሙሴ ለኢያሱ በሰጠው መመሪያ መሠረት ይሖዋ፣ ኢያሱ ለሕዝቡ እንዲናገር ያዘዘው ነገር በሙሉ እስኪፈጸም ድረስ ታቦቱን የተሸከሙት ካህናት በዮርዳኖስ መሃል ቆመው ነበር። በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ፈጥኖ ተሻገረ። 11 ሕዝቡ ሁሉ ተሻግሮ እንዳበቃ የይሖዋ ታቦትና ካህናቱ ሕዝቡ እያያቸው ተሻገሩ።+ 12 ሮቤላውያን፣ ጋዳውያንና የምናሴ ነገድ እኩሌታ ሙሴ በሰጣቸው መመሪያ መሠረት+ የጦርነት አሰላለፍ ተከትለው+ ሌሎቹን እስራኤላውያን ቀድመው ተሻገሩ። 13 ወደ 40,000 የሚሆኑ ለጦርነት የታጠቁ ሰዎች ወደ ኢያሪኮ በረሃማ ሜዳ በይሖዋ ፊት ተሻገሩ።

14 በዚያ ዕለት ይሖዋ ኢያሱን በእስራኤላውያን ሁሉ ፊት ከፍ ከፍ አደረገው፤+ እነሱም ሙሴን በጥልቅ ያከብሩት እንደነበር ሁሉ እሱንም በሕይወት ዘመኑ ሁሉ በጥልቅ አከበሩት።*+

15 ከዚያም ይሖዋ ኢያሱን እንዲህ አለው፦ 16 “የምሥክሩን ታቦት+ የተሸከሙትን ካህናት ከዮርዳኖስ እንዲወጡ እዘዛቸው።” 17 በመሆኑም ኢያሱ ካህናቱን “ከዮርዳኖስ ውጡ” በማለት አዘዛቸው። 18 የይሖዋን የቃል ኪዳን ታቦት የተሸከሙት ካህናት+ ከዮርዳኖስ መሃል ሲወጡና የካህናቱ እግር ከውኃው ወጥቶ ደረቁን መሬት ሲረግጥ የዮርዳኖስ ውኃ እንደቀድሞው መፍሰሱንና ዳርቻውን ሁሉ ማጥለቅለቁን ቀጠለ።+

19 ሕዝቡም በመጀመሪያው ወር በአሥረኛው ቀን ላይ ከዮርዳኖስ ወጥቶ በኢያሪኮ ምሥራቃዊ ወሰን ላይ በምትገኘው በጊልጋል ሰፈረ።+

20 ኢያሱም ከዮርዳኖስ ያወጧቸውን 12 ድንጋዮች በጊልጋል አቆማቸው።+ 21 ከዚያም እስራኤላውያንን እንዲህ አላቸው፦ “ወደፊት ልጆቻችሁ ‘እነዚህ ድንጋዮች ምንድን ናቸው?’ ብለው በሚጠይቋችሁ ጊዜ+ 22 ልጆቻችሁን እንዲህ በሏቸው፦ ‘እስራኤል ዮርዳኖስን በደረቅ ምድር ተሻገረ፤+ 23 ይህም የሆነው አምላካችሁ ይሖዋ ቀይ ባሕርን እስኪሻገሩ ድረስ ባሕሩን በፊታቸው እንዳደረቀው ሁሉ እኛም ዮርዳኖስን እስክንሻገር ድረስ አምላካችሁ ይሖዋ የዮርዳኖስን ውኃ በፊታችን ስላደረቀው ነው።+ 24 ይህን ያደረገው የምድር ሕዝቦች ሁሉ የይሖዋ ክንድ ምን ያህል ኃያል መሆኑን እንዲያውቁና+ እናንተም አምላካችሁን ይሖዋን ሁልጊዜ እንድትፈሩ ነው።’”

5 ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ* የሚገኙት የአሞራውያን+ ነገሥታት ሁሉ እንዲሁም በባሕሩ አጠገብ ያሉት የከነአናውያን+ ነገሥታት በሙሉ ይሖዋ እስራኤላውያን ዮርዳኖስን እስኪሻገሩ ድረስ የወንዙን ውኃ በፊታቸው እንዳደረቀው ሲሰሙ ልባቸው ቀለጠ፤+ በእስራኤላውያንም የተነሳ ወኔ ከድቷቸው ነበር።*+

2 በዚያን ጊዜ ይሖዋ ኢያሱን “የባልጩት ቢላ ሠርተህ እስራኤላውያን ወንዶችን እንደገና ለሁለተኛ ጊዜ ግረዛቸው”+ አለው። 3 ስለሆነም ኢያሱ የባልጩት ቢላ ሠርቶ እስራኤላውያን ወንዶችን ጊብዓትሃራሎት* በተባለ ስፍራ ገረዛቸው።+ 4 ኢያሱ የገረዛቸው በዚህ የተነሳ ነው፦ ከግብፅ በወጣው ሕዝብ መካከል የነበሩት ወንዶች ሁሉ ይኸውም ለውጊያ ብቁ የሆኑት* ወንዶች በሙሉ ከግብፅ ከወጡ በኋላ በጉዞ ላይ ሳሉ በምድረ በዳ ሞተዋል።+ 5 ከግብፅ የወጣው ሕዝብ ሁሉ ተገርዞ ነበር፤ ከግብፅ ከወጡ በኋላ በጉዞ ላይ ሳሉ በምድረ በዳ የተወለደው ሕዝብ ግን አልተገረዘም ነበር። 6 መላው ብሔር ይኸውም የይሖዋን ቃል ያልታዘዙት+ ከግብፅ የወጡት ለውጊያ ብቁ የሆኑ ወንዶች ሁሉ ሞተው እስኪያልቁ ድረስ እስራኤላውያን በምድረ በዳ 40 ዓመት ተጓዙ።+ ይሖዋም ለእኛ ለመስጠት ለአባቶቻቸው የማለላቸውን ምድር+ ይኸውም ወተትና ማር የምታፈሰውን ምድር+ እንዲያዩ ፈጽሞ እንደማይፈቅድላቸው ይሖዋ ምሎ ነበር።+ 7 በመሆኑም በእነሱ ምትክ ወንዶች ልጆቻቸውን አስነሳ።+ ኢያሱም እነዚህን ገረዛቸው፤ ምክንያቱም በጉዞ ላይ ሳሉ ስላልገረዟቸው ከነሸለፈታቸው ነበሩ።

8 እነሱም መላውን ብሔር ገርዘው ሲጨርሱ የተገረዙት ከቁስላቸው እስኪያገግሙ ድረስ እዚያው በሰፈሩበት ቦታ ቆዩ።

9 ከዚያም ይሖዋ ኢያሱን “በዛሬው ዕለት የግብፅን ነውር ከእናንተ ላይ አንከባልያለሁ” አለው። በመሆኑም የዚያ ስፍራ ስም ጊልጋል*+ ተባለ፤ እስከ ዛሬም ድረስ የሚታወቀው በዚሁ ስሙ ነው።

10 እስራኤላውያንም በጊልጋል እንደሰፈሩ ቆዩ፤ ወሩ በገባ በ14ኛው ቀን ምሽት ላይም በኢያሪኮ በረሃማ ሜዳ የፋሲካን* በዓል አከበሩ።+ 11 ከፋሲካውም ቀን በኋላ በዚያው ዕለት የምድሪቱን ፍሬ ማለትም ቂጣና*+ የተጠበሰ እሸት በሉ። 12 ከምድሪቱ ፍሬ በበሉበት ቀን ማግስት መናው ተቋረጠ፤+ ከዚያ በኋላ እስራኤላውያን መና አልወረደላቸውም፤ ከዚህ ይልቅ በዚያ ዓመት የከነአንን ምድር ፍሬ መብላት ጀመሩ።+

13 ኢያሱ በኢያሪኮ አቅራቢያ ሳለ፣ ቀና ብሎ ሲመለከት የተመዘዘ ሰይፍ በእጁ የያዘ+ አንድ ሰው ፊት ለፊቱ ቆሞ አየ።+ ኢያሱም ወደ እሱ ሄዶ “ከእኛ ወገን ነህ ወይስ ከጠላቶቻችን?” ሲል ጠየቀው። 14 እሱም መልሶ እንዲህ አለው፦ “አይደለሁም፤ እኔ አሁን የመጣሁት የይሖዋ ሠራዊት አለቃ ሆኜ ነው።”+ በዚህ ጊዜ ኢያሱ በግንባሩ መሬት ላይ ተደፍቶ በመስገድ “ታዲያ ጌታዬ ለአገልጋዩ የሚነግረው ምንድን ነው?” አለው። 15 የይሖዋ ሠራዊት አለቃም ኢያሱን “የቆምክበት ስፍራ ቅዱስ ስለሆነ ጫማህን አውልቅ” አለው። ኢያሱም ወዲያውኑ እንደተባለው አደረገ።+

6 ኢያሪኮ በእስራኤላውያን የተነሳ ጥርቅም ተደርጋ ተዘግታ ነበር፤ ወደ ውጭ የሚወጣም ሆነ ወደ ውስጥ የሚገባ አልነበረም።+

2 ይሖዋም ኢያሱን እንዲህ አለው፦ “እንግዲህ ኢያሪኮን፣ ንጉሥዋንና ኃያል ተዋጊዎቿን በእጅህ አሳልፌ ሰጥቼሃለሁ።+ 3 ተዋጊ የሆናችሁት ወንዶችም ሁሉ ከተማዋን ዙሪያዋን በመሄድ አንድ ጊዜ ዙሯት። ለስድስት ቀን እንዲህ አድርጉ። 4 ሰባት ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት* ይዘው በታቦቱ ፊት ይሂዱ። በሰባተኛው ቀን ግን ከተማዋን ሰባት ጊዜ ዙሯት፤ ካህናቱም ቀንደ መለከቱን ይንፉ።+ 5 ቀንደ መለከቱ ሲነፋና የቀንደ መለከቱን ድምፅ* ስትሰሙ ሕዝቡ ሁሉ ታላቅ የጦርነት ጩኸት ያሰማ። ከዚያም የከተማዋ ቅጥር ይፈራርሳል፤+ ሕዝቡም ሁሉ፣ እያንዳንዱም ሰው ቀጥ ብሎ ወደ ፊት ይሂድ።”

6 ስለዚህ የነዌ ልጅ ኢያሱ ካህናቱን አንድ ላይ ጠርቶ “የቃል ኪዳኑን ታቦት አንሱ፤ ሰባት ካህናትም ሰባት ቀንደ መለከት ይዘው በይሖዋ ታቦት ፊት ይሂዱ” አላቸው።+ 7 ሕዝቡንም “እናንተ ተነሱና ከተማዋን ዙሩ፤ የታጠቁት ተዋጊዎችም+ ከይሖዋ ታቦት ቀድመው ይሄዳሉ” አላቸው። 8 ኢያሱ ለሕዝቡ በተናገረው መሠረት ሰባት ቀንደ መለከት የያዙት ሰባት ካህናት በይሖዋ ፊት ቀድመው በመሄድ ቀንደ መለከታቸውን ነፉ፤ የይሖዋ የቃል ኪዳን ታቦትም ይከተላቸው ነበር። 9 የታጠቁትም ተዋጊዎች ቀንደ መለከቱን ከሚነፉት ካህናት ቀድመው ሄዱ፤ የኋላው ደጀን ደግሞ ታቦቱን ይከተል ነበር፤ በዚህ ጊዜ ሁሉ ቀንደ መለከቱ ያለማቋረጥ ይነፋ ነበር።

10 ኢያሱም ሕዝቡን እንዲህ ሲል አዘዘ፦ “መጮኽም ሆነ ድምፃችሁን ማሰማት የለባችሁም። እኔ ‘ጩኹ!’ ብዬ እስከማዛችሁ ቀን ድረስ ከአፋችሁ አንድም ቃል መውጣት የለበትም። ከዚያ በኋላ ትጮኻላችሁ።” 11 እሱም የይሖዋ ታቦት በከተማዋ ዙሪያ በመሄድ ከተማዋን አንድ ጊዜ እንዲዞር አደረገ፤ ከዚያም ወደ ሰፈሩ ተመልሰው በዚያ አደሩ።

12 በሚቀጥለው ቀን ኢያሱ በማለዳ ተነሳ፤ ካህናቱም የይሖዋን ታቦት አነሱ፤+ 13 ሰባት ቀንደ መለከት የያዙ ሰባት ካህናት ያለማቋረጥ መለከታቸውን እየነፉ ከይሖዋ ታቦት ፊት ፊት ይሄዱ ነበር። የታጠቁት ተዋጊዎችም ከእነሱ ፊት ይሄዱ ነበር፤ የኋላው ደጀን ደግሞ የይሖዋን ታቦት ይከተል ነበር፤ በዚህ ጊዜ ሁሉ ቀንደ መለከቱ ያለማቋረጥ ይነፋ ነበር። 14 በሁለተኛውም ቀን ከተማዋን አንድ ጊዜ ዞሯት፤ ከዚያም ወደ ሰፈሩ ተመለሱ። ለስድስት ቀን ልክ እንደዚሁ አደረጉ።+

15 በሰባተኛው ቀን ገና ጎህ ሲቀድ ተነስተው ከተማዋን በዚሁ መንገድ ሰባት ጊዜ ዞሯት። ከተማዋን ሰባት ጊዜ የዞሯት በዚያ ቀን ብቻ ነበር።+ 16 በሰባተኛው ዙር ላይ ካህናቱ ቀንደ መለከቱን ነፉ፤ ኢያሱም ሕዝቡን እንዲህ አለ፦ “ይሖዋ ከተማዋን አሳልፎ ስለሰጣችሁ ጩኹ!+ 17 ከተማዋም ሆነች በውስጧ ያለው ነገር ሁሉ ሙሉ በሙሉ መጥፋት አለበት፤+ ከተማዋ ሙሉ በሙሉ የይሖዋ ነች። በሕይወት የሚተርፉት ዝሙት አዳሪዋ ረዓብና+ ከእሷ ጋር በቤቱ ውስጥ ያሉት ብቻ ናቸው፤ ምክንያቱም እሷ የላክናቸውን መልእክተኞች ደብቃለች።+ 18 እናንተ ግን ለጥፋት የተለየው ነገር እንዳያጓጓችሁና እንዳትወስዱት፣ በእስራኤልም ሰፈር ላይ መዓት* በማምጣት ሰፈሩን ለጥፋት የተለየ እንዳታደርጉት+ ለጥፋት ከተለየው ነገር ራቁ።+ 19 ሆኖም ብሩ፣ ወርቁ እንዲሁም ከመዳብና ከብረት የተሠሩት ዕቃዎች ሁሉ ለይሖዋ የተቀደሱ ናቸው።+ ወደ ይሖዋ ግምጃ ቤት መግባት አለባቸው።”+

20 ከዚያም ቀንደ መለከቱ ሲነፋ ሕዝቡ ጮኸ።+ ሕዝቡ የቀንደ መለከቱን ድምፅ ሰምቶ ታላቅ የጦርነት ጩኸት ሲያሰማ ቅጥሩ ፈረሰ።+ ከዚያም ሕዝቡ ሁሉ፣ እያንዳንዱም ሰው በቀጥታ ወደ ከተማዋ በመግባት ከተማዋን ያዛት። 21 እነሱም በከተማዋ ውስጥ የነበረውን በሙሉ ይኸውም ወንዱንና ሴቱን፣ ወጣቱንና ሽማግሌውን እንዲሁም በሬውን፣ በጉንና አህያውን በሰይፍ ሙሉ በሙሉ አጠፉ።+

22 ኢያሱም ምድሪቱን የሰለሉትን ሁለቱን ሰዎች “ወደ ዝሙት አዳሪዋ ቤት ገብታችሁ በማላችሁላት መሠረት ሴትየዋንና የእሷ የሆነውን ሁሉ ከዚያ አውጡ” አላቸው።+ 23 በመሆኑም ወጣቶቹ ሰላዮች ገብተው ረዓብን፣ አባቷን፣ እናቷን፣ ወንድሞቿንና የእሷ የሆነውን ሁሉ አዎ፣ ቤተሰቧን በሙሉ+ አውጥተው ከእስራኤል ሰፈር ውጭ ወዳለ ስፍራ በሰላም አመጧቸው።

24 ከዚያም ከተማዋንና በውስጧ የነበረውን ሁሉ በእሳት አቃጠሉ። ብሩን፣ ወርቁን እንዲሁም ከመዳብና ከብረት የተሠሩትን ዕቃዎች ግን ወደ ይሖዋ ግምጃ ቤት አስገቡ።+ 25 ኢያሱ በሕይወት እንዲተርፉ ያደረገው ዝሙት አዳሪዋን ረዓብን፣ የአባቷን ቤተሰብና የእሷ የሆነውን ብቻ ነበር፤+ እሷም እስከ ዛሬ ድረስ በእስራኤል መካከል ትኖራለች፤+ ምክንያቱም ኢያሱ ኢያሪኮን እንዲሰልሉ የላካቸውን መልእክተኞች ደብቃ ነበር።+

26 በዚያን ጊዜ ኢያሱ ይህን ቃለ መሐላ አወጀ፦* “ይህችን የኢያሪኮን ከተማ ለመገንባት የሚነሳ ሰው በይሖዋ ፊት የተረገመ ይሁን። የከተማዋን መሠረት ሲጥል የበኩር ልጁ ይጥፋ፤ በሮቿንም ሲያቆም የመጨረሻ ልጁ ይጥፋ።”+

27 ይሖዋም ከኢያሱ ጋር ነበር፤+ በመላውም ምድር ላይ ዝነኛ ሆነ።+

7 ይሁን እንጂ ከይሁዳ ነገድ የሆነው የዛራ ልጅ፣ የዛብዲ ልጅ፣ የካርሚ ልጅ አካን+ ለጥፋት ከተለየው ነገር ላይ በመውሰዱ እስራኤላውያን ለጥፋት ከተለየው ነገር ጋር በተያያዘ ታማኝነት የጎደለው ድርጊት ፈጸሙ።+ በዚህም የተነሳ የይሖዋ ቁጣ በእስራኤላውያን ላይ ነደደ።+

2 ከዚያም ኢያሱ “ወጥታችሁ ምድሪቱን ሰልሉ” በማለት ከቤቴል+ በስተ ምሥራቅ በቤትአዌን አቅራቢያ ወደምትገኘው ወደ ጋይ+ ሰዎችን ላከ። በመሆኑም ሰዎቹ ወጥተው ጋይን ሰለሉ። 3 ሰዎቹም ወደ ኢያሱ ተመልሰው እንዲህ አሉት፦ “ሕዝቡ ሁሉ መውጣት አያስፈልገውም። ጋይን ድል ለማድረግ ሁለት ሺህ ወይም ሦስት ሺህ ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ብቻ ይበቃሉ። ነዋሪዎቿ ጥቂት ስለሆኑ መላው ሕዝብ እንዲሄድ በማድረግ ሕዝቡን አታድክም።”

4 በመሆኑም 3,000 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ወደዚያ ወጡ፤ ይሁን እንጂ ከጋይ ሰዎች ፊት ለመሸሽ ተገደዱ።+ 5 የጋይ ሰዎችም 36 ሰዎችን ገደሉ፤ ከከተማዋ በር አንስቶ እስከ ሸባሪም* ድረስ በማሳደድ ቁልቁለቱ ላይ መቷቸው። በዚህም የተነሳ የሕዝቡ ልብ ቀለጠ፤ እንደ ውኃም ፈሰሰ።

6 በዚህ ጊዜ ኢያሱ ልብሱን ቀደደ፤ እስከ ምሽትም ድረስ በይሖዋ ታቦት ፊት በግንባሩ መሬት ላይ ተደፋ፤ እሱም ሆነ የእስራኤል ሽማግሌዎች እንዲሁ አደረጉ፤ በራሳቸውም ላይ አቧራ ይበትኑ ነበር። 7 ኢያሱም እንዲህ አለ፦ “ወዮ! ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ፤ ይህን ሁሉ ሕዝብ ዮርዳኖስን አሻግረህ እዚህ ድረስ ያመጣኸው ለአሞራውያን አሳልፈህ በመስጠት እንድንጠፋ ለማድረግ ነው? እዚያው በዮርዳኖስ ማዶ* አርፈን ብንቀመጥ ይሻለን ነበር! 8 አቤቱ ይሖዋ ሆይ ይቅር በለኝ፣ እንግዲህ እስራኤል ከጠላቶቹ ፊት እንዲህ የሚሸሽ* ከሆነ ምን ማለት እችላለሁ? 9 ከነአናውያንና የምድሪቱ ነዋሪዎች በሙሉ ይህን ሲሰሙ መጥተው ይከቡንና ስማችንን ከምድር ገጽ ያጠፉታል፤ ታዲያ አንተ ለታላቁ ስምህ ስትል ምን ታደርግ ይሆን?”+

10 ይሖዋም ለኢያሱ እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ተነስ! በግንባርህ የተደፋኸው ለምንድን ነው? 11 እስራኤላውያን ኃጢአት ሠርተዋል። እንዲጠብቁት ያዘዝኳቸውን ቃል ኪዳኔን አፍርሰዋል።+ ለጥፋት ከተለየው ነገር ላይም ሰርቀው+ ወስደዋል፤+ ከራሳቸው ዕቃዎችም ጋር በመቀላቀል ደብቀው አስቀምጠውታል።+ 12 ስለዚህ እስራኤላውያን ጠላቶቻቸውን መቋቋም አይችሉም። ዞረውም ከጠላቶቻቸው ፊት ይሸሻሉ፤ ምክንያቱም እነሱ ራሳቸው ለጥፋት የተለዩ ሆነዋል። ለጥፋት የተለየውን ነገር ከመካከላችሁ ካላስወገዳችሁ በስተቀር ከእንግዲህ እኔ ከእናንተ ጋር አልሆንም።+ 13 ተነስና ሕዝቡን ቀድስ!+ እንዲህም በላቸው፦ ‘ለነገ ራሳችሁን ቀድሱ፤ ምክንያቱም የእስራኤል አምላክ ይሖዋ እንዲህ ብሏል፦ “እስራኤል ሆይ፣ በመካከልህ ለጥፋት የተለየ ነገር አለ። ለጥፋት የተለየውን ነገር ከመካከልህ ካላስወገድክ ጠላቶችህን መቋቋም አትችልም። 14 ማለዳ ላይ በነገድ በነገድ ሆናችሁ ትቀርባላችሁ፤ ይሖዋ የሚመርጠውም ነገድ+ ወደ ፊት ይቀርባል፤ ከዚያም በወገን በወገኑ ሆኖ ይቀርባል፤ ይሖዋ የሚመርጠውም ወገን ወደ ፊት ይቀርባል፤ ከዚያም በቤተሰብ በቤተሰብ ሆኖ ይቀርባል፤ ይሖዋ የሚመርጠውም ቤተሰብ ወደ ፊት ይቀርባል፤ ከዚያም በግለሰብ በግለሰብ ሆኖ ይቀርባል። 15 ለጥፋት የተለየውን ነገር ወስዶ የተገኘውም ሰው በእሳት ይቃጠላል፤+ እሱም ሆነ የእሱ የሆነው ሁሉ ይቃጠላሉ፤ ምክንያቱም ይህ ሰው የይሖዋን ቃል ኪዳን አፍርሷል፤+ እንዲሁም በእስራኤል ውስጥ አሳፋሪ ተግባር ፈጽሟል።”’”

16 ስለሆነም ኢያሱ በሚቀጥለው ቀን በማለዳ ተነስቶ እስራኤላውያን በነገድ በነገድ ሆነው ወደ ፊት እንዲቀርቡ አደረገ፤ የይሁዳም ነገድ ተመረጠ። 17 የይሁዳ ወገኖች ወደ ፊት እንዲቀርቡ አደረገ፤ ከመካከላቸውም የዛራውያን+ ወገን ተመረጠ፤ ከዚያም ከዛራውያን ወገን የሆኑት ሰዎች በግለሰብ ደረጃ ወደ ፊት እንዲቀርቡ አደረገ፤ ከዚያም ዛብዲ ተመረጠ። 18 በመጨረሻም የዛብዲ ቤተሰብ በግለሰብ በግለሰብ ሆኖ ወደ ፊት እንዲቀርብ አደረገ፤ ከዚያም ከይሁዳ ነገድ የዛራ ልጅ፣ የዛብዲ ልጅ፣ የካርሚ ልጅ አካን ተመረጠ።+ 19 ኢያሱም አካንን እንዲህ አለው፦ “ልጄ ሆይ፣ እባክህ የእስራኤልን አምላክ ይሖዋን አክብር፤ ለእሱም ተናዘዝ። እባክህ ያደረግከውን ንገረኝ። አትደብቀኝ።”

20 አካንም ለኢያሱ እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “በእርግጥም በእስራኤል አምላክ በይሖዋ ላይ ኃጢአት የሠራሁት እኔ ነኝ፤ እንግዲህ ያደረግኩት ይህ ነው፦ 21 ከምርኮው መካከል ከሰናኦር+ የመጣ የሚያምር የክብር ልብስ፣ 200 ሰቅል* ብርና 50 ሰቅል የሚመዝን ጥፍጥፍ ወርቅ አይቼ ስለተመኘሁ ወሰድኳቸው። አሁንም ገንዘቡ ከታች ሆኖ ድንኳኔ ውስጥ መሬት ውስጥ ተቀብረው ይገኛሉ።”

22 ኢያሱም ወዲያውኑ መልእክተኞች ላከ፤ እነሱም ወደ ድንኳኑ እየሮጡ ሄዱ፤ ልብሱንም ድንኳኑ ውስጥ ተደብቆ አገኙት፤ ገንዘቡም ከልብሱ ሥር ነበር። 23 ከዚያም ከድንኳኑ አውጥተው ወደ ኢያሱና ወደ እስራኤላውያን ሁሉ አመጧቸው፤ በይሖዋም ፊት አስቀመጧቸው። 24 በኋላም ኢያሱና ከእሱ ጋር የነበሩት እስራኤላውያን በሙሉ የዛራን ልጅ አካንን፣+ ብሩን፣ የክብር ልብሱን፣ ጥፍጥፍ ወርቁን፣+ ወንዶች ልጆቹን፣ ሴቶች ልጆቹን፣ በሬውን፣ አህያውን፣ መንጋውን፣ ድንኳኑንና የእሱ የሆነውን ሁሉ ወደ አኮር ሸለቆ*+ አመጡ። 25 ኢያሱም አካንን “መዓት* ያመጣህብን ለምንድን ነው?+ ይሖዋም በዛሬው ዕለት መዓት ያመጣብሃል” አለው። ከዚያም እስራኤላውያን በሙሉ በድንጋይ ወገሩት፤+ በእሳትም አቃጠሏቸው።+ በዚህ መንገድ ሁሉንም በድንጋይ ወግረው ገደሏቸው። 26 በእሱም ላይ እስከ ዛሬ ድረስ የሚታየውን የድንጋይ ቁልል ከመሩበት። በዚህ ጊዜ የይሖዋ ታላቅ ቁጣ በረደ።+ የዚያ ቦታ ስም እስከ ዛሬ ድረስ የአኮር* ሸለቆ የሚባለው በዚህ የተነሳ ነው።

8 ከዚያም ይሖዋ ኢያሱን እንዲህ አለው፦ “አትፍራ ወይም አትሸበር።+ ተዋጊዎቹን ሁሉ ይዘህ በጋይ ላይ ዝመት። እነሆ፣ የጋይን ንጉሥ፣ ሕዝቡን፣ ከተማውንና ምድሩን በእጅህ አሳልፌ ሰጥቼሃለሁ።+ 2 በኢያሪኮና በንጉሥዋ ላይ ያደረግከውን ሁሉ በጋይና በንጉሥዋም ላይ አድርግ፤+ የማረካችኋቸውን ነገሮችና ከብቶቿን ግን ለራሳችሁ ውሰዱ። ከከተማዋም በስተ ጀርባ የደፈጣ ተዋጊዎችን አስቀምጥ።”

3 ስለዚህ ኢያሱና ተዋጊዎቹ በሙሉ ጋይን ለመውጋት ወጡ። ኢያሱም 30,000 ኃያል ተዋጊዎችን መርጦ በሌሊት ላካቸው። 4 እንዲህም ሲል አዘዛቸው፦ “እንግዲህ እናንተ ከከተማዋ በስተ ጀርባ አድፍጣችሁ ትጠብቃላችሁ። ከከተማዋ ብዙ አትራቁ፤ ሁላችሁም በተጠንቀቅ ጠብቁ። 5 እኔና አብሮኝ ያለው ሕዝብ ሁሉ ወደ ከተማዋ እንቀርባለን፤ እነሱም ከዚህ በፊት እንዳደረጉት ሁሉ ሊወጉን ሲወጡ+ እኛ ከፊታቸው እንሸሻለን። 6 እነሱም ‘ከዚህ በፊት እንዳደረጉት አሁንም ከፊታችን እየሸሹ ነው’+ በማለት ይከታተሉናል፤ በዚህ መንገድ ከከተማዋ እንዲርቁ እናደርጋቸዋለን። እኛም ከእነሱ እንሸሻለን። 7 እናንተም ካደፈጣችሁበት ቦታ ተነስታችሁ ከተማዋን ትቆጣጠራላችሁ፤ አምላካችሁ ይሖዋም ከተማዋን በእጃችሁ አሳልፎ ይሰጣችኋል። 8 ከተማዋን እንደያዛችሁም በእሳት አቃጥሏት።+ ይሖዋ ባዘዘው መሠረት አድርጉ። እንግዲህ እኔ አዝዣችኋለሁ።”

9 ከዚያም ኢያሱ ሰዎቹን ላካቸው፤ እነሱም አድፍጠው ወደሚጠባበቁበት ቦታ ሄዱ፤ ከጋይ በስተ ምዕራብ በቤቴልና በጋይ መካከል በሚገኘው ስፍራም አደፈጡ፤ ኢያሱ ግን ያን ሌሊት እዚያው ከሕዝቡ ጋር አደረ።

10 ከዚያም ኢያሱ በማለዳ ተነስቶ ሠራዊቱን ከሰበሰበ በኋላ እሱና የእስራኤል ሽማግሌዎች እየመሯቸው ወደ ጋይ ይዘዋቸው ሄዱ። 11 ከእሱም ጋር የነበሩት ተዋጊዎች በሙሉ+ ገስግሰው ወደ ከተማዋ ፊት ቀረቡ። እነሱም ከጋይ በስተ ሰሜን ሰፈሩ፤ በእነሱና በጋይ መካከልም ሸለቆ ነበር። 12 በዚህ ጊዜ ኢያሱ 5,000 ገደማ የሚሆኑ ሰዎችን ወስዶ ከከተማዋ በስተ ምዕራብ በኩል በቤቴልና+ በጋይ መካከል አድፍጠው እንዲጠብቁ+ አድርጎ ነበር። 13 ሕዝቡም ዋና ሰፈሩን ከከተማዋ በስተ ሰሜን አደረገ፤+ የኋላ ደጀን የሆነውን ሠራዊት ደግሞ ከከተማዋ በስተ ምዕራብ አደረገ፤+ ኢያሱም በዚያ ሌሊት ወደ ሸለቆው* መሃል ሄደ።

14 የጋይም ንጉሥ ይህን ባየ ጊዜ እሱና የከተማዋ ሰዎች ማልደው በመነሳት ከእስራኤል ጋር ለመዋጋት በረሃማውን ሜዳ ቁልቁል ማየት ወደሚያስችላቸው ስፍራ በፍጥነት ገሰገሱ። ሆኖም ንጉሡ ከከተማዋ በስተ ጀርባ በእሱ ላይ ያደፈጠ ሠራዊት መኖሩን አላወቀም ነበር። 15 የጋይ ሰዎችም ጥቃት በሰነዘሩ ጊዜ ኢያሱና መላው እስራኤል ድል የተመቱ በማስመሰል ወደ ምድረ በዳው የሚወስደውን መንገድ ይዘው ሸሹ።+ 16 ከዚያም በከተማዋ ውስጥ የነበረው ሕዝብ በሙሉ ወጥቶ እንዲያሳድዳቸው ተጠራ፤ እነሱም ኢያሱን እያሳደዱ ከከተማዋ ርቀው ሄዱ። 17 ከጋይም ሆነ ከቤቴል እስራኤልን ለማሳደድ ያልወጣ አንድም ወንድ አልነበረም። ከተማዋንም ወለል አድርገው ከፍተው በመሄድ እስራኤልን ማሳደዳቸውን ተያያዙት።

18 በዚህ ጊዜ ይሖዋ ኢያሱን “ከተማዋን በእጅህ አሳልፌ ስለምሰጥህ+ የያዝከውን ጦር ወደ ጋይ አቅጣጫ ሰንዝር”+ አለው። ኢያሱም ይዞት የነበረውን ጦር ወደ ከተማዋ አቅጣጫ ሰነዘረ። 19 ያደፈጠውም ሠራዊት ኢያሱ እጁን በሰነዘረበት ቅጽበት ወዲያውኑ ከቦታው ተነስቶ ወደ ከተማዋ ሮጦ በመግባት ያዛት። ከዚያም በፍጥነት ከተማዋን በእሳት አያያዟት።+

20 የጋይ ሰዎች ዞረው ሲመለከቱ የከተማዋ ጭስ ወደ ሰማይ ሲወጣ አዩ፤ ወደየትኛውም አቅጣጫ መሸሽ የሚችሉበት አቅም አልነበራቸውም። ወደ ምድረ በዳው እየሸሹ የነበሩትም ሰዎች ወደ አሳዳጆቻቸው ዞሩ። 21 ኢያሱና እስራኤላውያን በሙሉ፣ አድፍጦ የነበረው ሠራዊት ከተማዋን በቁጥጥር ሥር ማዋሉንና የከተማዋ ጭስ ወደ ላይ መውጣቱን ሲመለከቱ ወደ ኋላ ተመልሰው የጋይን ሰዎች ማጥቃት ጀመሩ። 22 ከተማዋን ተቆጣጥረው የነበሩትም ሰዎች እነሱን ለመግጠም ከከተማዋ ወጡ፤ በመሆኑም የጋይ ሰዎች በሁለቱም በኩል ባሉት እስራኤላውያን መካከል አጣብቂኝ ውስጥ ገቡ፤ እነሱም ፈጇቸው፤ ከመካከላቸው የተረፈም ሆነ ያመለጠ አንድም እንኳ አልነበረም።+ 23 የጋይን ንጉሥ+ ግን ከነሕይወቱ ይዘው ወደ ኢያሱ አመጡት።

24 እስራኤላውያን የጋይን ነዋሪዎች በሙሉ ሜዳ ላይ ይኸውም ሲያሳድዷቸው በነበረው ምድረ በዳ ላይ ፈጇቸው፤ አንድም ሳይቀር ሁሉም በሰይፍ አለቁ። ከዚያም እስራኤላውያን በሙሉ ወደ ጋይ ተመልሰው ከተማዋን በሰይፍ መቱ። 25 ወንድ ሴት ሳይል በዚያን ቀን የሞቱት የጋይ ሰዎች በጠቅላላ 12,000 ነበሩ። 26 ኢያሱም የጋይን ነዋሪዎች በሙሉ ፈጽሞ እስኪያጠፋ ድረስ+ ጦር የሰነዘረበትን እጁን አልመለሰውም።+ 27 እስራኤላውያንም ይሖዋ ለኢያሱ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት የከተማዋን ምርኮና ከብቶች ለራሳቸው ወሰዱ።+

28 ኢያሱም ጋይን በእሳት አጋያት፤ ከተማዋንም የፍርስራሽ ክምር ሆና እንድትቀር አደረጋት፤+ እስከ ዛሬም ድረስ ባድማ ናት። 29 የጋይንም ንጉሥ እስከ ማታ ድረስ እንጨት* ላይ ሰቀለው፤ ከዚያም ኢያሱ ፀሐይ ልትጠልቅ ስትል በድኑን ከእንጨቱ ላይ እንዲያወርዱት ትእዛዝ ሰጠ።+ እነሱም በድኑን በከተማዋ በር ላይ ጣሉት፤ በእሱም ላይ ትልቅ የድንጋይ ቁልል ከመሩበት፤ ይህም እስከ ዛሬ ድረስ እዚያው ይገኛል።

30 ኢያሱም በኤባል ተራራ+ ላይ ለእስራኤል አምላክ ለይሖዋ መሠዊያ የሠራው በዚያን ጊዜ ነበር፤ 31 መሠዊያውንም የሠራው የይሖዋ አገልጋይ ሙሴ ለእስራኤላውያን በሰጠው ትእዛዝና በሙሴ የሕግ መጽሐፍ+ ላይ በተጻፈው “መሠዊያው የብረት መሣሪያ ካልነካው ያልተጠረበ ድንጋይ የተሠራ ይሁን”+ በሚለው መመሪያ መሠረት ነው። በዚያም ላይ የሚቃጠሉ መባዎችንና የኅብረት መሥዋዕቶችን ለይሖዋ አቀረቡ።+

32 ከዚያም በድንጋዮቹ ላይ ሙሴ በእስራኤላውያን ፊት የጻፈውን ሕግ ቅጂ+ ጻፈባቸው።+ 33 እስራኤላውያን በሙሉ፣ ሽማግሌዎቻቸው፣ አለቆቻቸውና ዳኞቻቸው የይሖዋን የቃል ኪዳን ታቦት በሚሸከሙት በሌዋውያን ካህናት ፊት ከታቦቱ ወዲህና ወዲያ ቆመው ነበር። የባዕድ አገር ሰዎችም ሆኑ የአገሬው ተወላጆች በዚያ ነበሩ።+ የእስራኤልን ሕዝብ ለመባረክ (የይሖዋ አገልጋይ ሙሴ ቀደም ሲል ባዘዘው መሠረት)+ ግማሾቹ በገሪዛን ተራራ ፊት ለፊት፣ ግማሾቹ ደግሞ በኤባል ተራራ ፊት ለፊት ቆሙ።+ 34 ከዚህ በኋላ ኢያሱ በሕጉ መጽሐፍ+ ላይ በተጻፈው መሠረት የሕጉን ቃላት በሙሉ ይኸውም በረከቱንና+ እርግማኑን+ ድምፁን ከፍ አድርጎ አነበበ። 35 ኢያሱ፣ ሙሴ ከሰጠው ትእዛዝ ውስጥ፣ ሴቶችንና ልጆችን እንዲሁም በመካከላቸው የሚኖሩ+ የባዕድ አገር ሰዎችን+ ጨምሮ በመላው የእስራኤል ጉባኤ ፊት ድምፁን ከፍ አድርጎ ያላነበበው አንድም ቃል አልነበረም።+

9 ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ+ በተራራማው አካባቢ፣ በሸፌላ፣ በመላው የታላቁ ባሕር*+ ዳርቻ እንዲሁም በሊባኖስ ፊት ለፊት የነበሩት ነገሥታት ሁሉ ይኸውም ሂታውያን፣ አሞራውያን፣ ከነአናውያን፣ ፈሪዛውያን፣ ሂዋውያንና ኢያቡሳውያን ይህን ሲሰሙ+ 2 ኢያሱንና እስራኤልን ለመውጋት ግንባር ፈጠሩ።+

3 የገባኦን+ ነዋሪዎችም ኢያሱ በኢያሪኮና+ በጋይ+ ላይ ምን እንዳደረገ ሰሙ። 4 በመሆኑም ብልሃት ፈጠሩ፤ ስንቃቸውን ባረጁ ከረጢቶች ውስጥ ከከተቱ በኋላ ተቀዳደው ከተጠጋገኑ ያረጁ የወይን ጠጅ አቁማዳዎች ጋር በአህያዎቻቸው ላይ ጫኑ፤ 5 በተጨማሪም ያደረጉት ነጠላ ጫማ ያለቀና የተጠጋገነ፣ የለበሱትም ልብስ ያረጀ ነበር። ለስንቅ የያዙትም ዳቦ በሙሉ የደረቀና የተፈረፈረ ነበር። 6 እነሱም በጊልጋል+ በሚገኘው ሰፈር ወደነበረው ወደ ኢያሱ ሄደው እሱንና የእስራኤልን ሰዎች “የመጣነው ከሩቅ አገር ነው። እንግዲህ ከእኛ ጋር ቃል ኪዳን ግቡ” አሏቸው። 7 ይሁን እንጂ የእስራኤል ሰዎች ሂዋውያኑን+ “ይህን ጊዜ እኮ የምትኖሩት እዚሁ አጠገባችን ይሆናል። ታዲያ ከእናንተ ጋር እንዴት ቃል ኪዳን እንገባለን?” አሏቸው።+ 8 እነሱም መልሰው ኢያሱን “እኛ የአንተ አገልጋዮች* ነን” አሉት።

ከዚያም ኢያሱ “እናንተ እነማን ናችሁ? የመጣችሁትስ ከየት ነው?” አላቸው። 9 በዚህ ጊዜ እንዲህ አሉት፦ “እኛ አገልጋዮችህ ለአምላክህ ለይሖዋ ስም ካለን አክብሮት የተነሳ ከሩቅ አገር የመጣን ነን፤+ ምክንያቱም ዝናውንና በግብፅ ያደረገውን ሁሉ ሰምተናል፤+ 10 እንዲሁም ከዮርዳኖስ ማዶ* በነበሩት በሁለቱ የአሞራውያን ነገሥታት ይኸውም በሃሽቦን ንጉሥ በሲሖንና+ በአስታሮት በነበረው በባሳን ንጉሥ በኦግ+ ላይ ያደረገውን ሁሉ ሰምተናል። 11 በመሆኑም ሽማግሌዎቻችንና የአገራችን ነዋሪዎች በሙሉ እንዲህ አሉን፦ ‘ለጉዟችሁ የሚሆን ስንቅ ይዛችሁ ወደ እነዚህ ሰዎች ሂዱ። ከዚያም “አገልጋዮቻችሁ እንሆናለን።+ ከእኛ ጋር ቃል ኪዳን ግቡ”+ በሏቸው።’ 12 ለስንቅ እንዲሆነን የያዝነው ይህ ዳቦ ወደዚህ ወደ እናንተ ለመምጣት ከቤታችን በወጣንበት ቀን ትኩስ ነበር። አሁን ግን ይኸው እንደምታዩት ደርቋል፤ ደግሞም ተፈርፍሯል።+ 13 እነዚህ የወይን ጠጅ አቁማዳዎች ያን ጊዜ ስንሞላቸው አዲስ ነበሩ፤ አሁን ግን ይኸው እንደምታዩአቸው ተቀዳደዋል።+ ልብሶቻችንና ጫማዎቻችንም ረጅም መንገድ ከመጓዛችን የተነሳ አልቀዋል።”

14 በዚህ ጊዜ የእስራኤል ሰዎች ከስንቃቸው ላይ ጥቂት ወሰዱ፤* ስለ ጉዳዩ ግን ይሖዋን አልጠየቁም።+ 15 በመሆኑም ኢያሱ ከእነሱ ጋር በሰላም ለመኖር ተስማማ፤+ እንደማያጠፋቸውም ቃል ኪዳን ገባላቸው፤ የማኅበረሰቡም አለቆች ይህንኑ በመሐላ አጸኑላቸው።+

16 እስራኤላውያንም ከእነሱ ጋር ቃል ኪዳን ከገቡ ከሦስት ቀን በኋላ እነዚህ ሰዎች እዚያው በአቅራቢያቸው የሚኖሩ የአካባቢው ነዋሪዎች መሆናቸውን ሰሙ። 17 ከዚያም እስራኤላውያን ተጉዘው በሦስተኛው ቀን ወደ ከተሞቻቸው ደረሱ፤ ከተሞቻቸውም ገባኦን፣+ ከፊራ፣ በኤሮት እና ቂርያትየአሪም+ ነበሩ። 18 ይሁን እንጂ የማኅበረሰቡ አለቆች በእስራኤል አምላክ በይሖዋ ምለውላቸው+ ስለነበር እስራኤላውያን ጥቃት አልሰነዘሩባቸውም። ስለሆነም መላው ማኅበረሰብ በአለቆቹ ላይ ማጉረምረም ጀመረ። 19 በዚህ ጊዜ አለቆቹ በሙሉ መላውን ማኅበረሰብ እንዲህ አሉ፦ “በእስራኤል አምላክ በይሖዋ ስም ስለማልንላቸው ጉዳት ልናደርስባቸው አንችልም። 20 እንግዲህ የምናደርገው ነገር ቢኖር በማልንላቸው መሐላ የተነሳ ቁጣ እንዳይመጣብን በሕይወት እንዲኖሩ መተው ብቻ ነው።”+ 21 ከዚያም አለቆቹ “በሕይወት ይኑሩ፤ ሆኖም ለማኅበረሰቡ በሙሉ እንጨት ለቃሚዎችና ውኃ ቀጂዎች ይሁኑ” አሉ። አለቆቹም ይህንኑ ቃል ገቡላቸው።

22 ኢያሱም እነሱን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “የምትኖሩት እዚሁ አጠገባችን ሆኖ ሳለ ‘የምንኖረው ከእናንተ በጣም ርቆ በሚገኝ ቦታ ነው’ በማለት ያታለላችሁን ለምንድን ነው?+ 23 ስለዚህ ከአሁን ጀምሮ የተረገማችሁ ናችሁ፤+ ለአምላኬም ቤት እንጨት ለቃሚዎችና ውኃ ቀጂዎች በመሆን ምንጊዜም እንደ ባሪያ ታገለግላላችሁ።” 24 እነሱም መልሰው ኢያሱን እንዲህ አሉት፦ “ይህን ያደረግነው አምላክህ ይሖዋ አገልጋዩን ሙሴን ምድሪቱን በሙሉ ለእናንተ እንዲሰጣችሁና ነዋሪዎቿን በሙሉ ከፊታችሁ እንዲያጠፋላችሁ አዞት እንደነበር ለእኛ ለአገልጋዮችህ በግልጽ ስለተነገረን ነው።+ ስለሆነም በእናንተ የተነሳ ለሕይወታችን* በጣም ፈራን፤+ ይህን ያደረግነው በዚህ ምክንያት ነው።+ 25 ይኸው አሁን በእጅህ ነን። መልካምና ትክክል መስሎ የታየህን ሁሉ አድርግብን።” 26 እሱም እንዲሁ አደረገባቸው፤ ከእስራኤላውያን እጅ አዳናቸው፤ እነሱም አልገደሏቸውም። 27 ሆኖም በዚያን ዕለት ኢያሱ አምላክ በሚመርጠው ስፍራ+ ለማኅበረሰቡና ለይሖዋ መሠዊያ እንጨት ለቃሚዎችና ውኃ ቀጂዎች አደረጋቸው፤+ እነሱም እስከ ዛሬ ድረስ ይህንኑ ያደርጋሉ።+

10 የኢየሩሳሌም ንጉሥ አዶኒጼዴቅ፣ ኢያሱ ጋይን እንደተቆጣጠራትና እንደደመሰሳት፣ በኢያሪኮና በንጉሥዋ+ ላይ እንዳደረገው ሁሉ በጋይና በንጉሥዋም+ ላይ እንዳደረገ እንዲሁም የገባኦን ነዋሪዎች ከእስራኤላውያን ጋር ሰላማዊ ግንኙነት+ ፈጥረው በመካከላቸው እየኖሩ እንዳሉ ሲሰማ 2 በጣም ደነገጠ፤+ ምክንያቱም ገባኦን በንጉሥ እንደሚተዳደሩት ከተሞች ሁሉ ታላቅ ከተማ ነበረች። ይህች ከተማ ከጋይ+ ትበልጥ የነበረ ሲሆን ነዋሪዎቿም በሙሉ ጦረኞች ነበሩ። 3 በመሆኑም የኢየሩሳሌም ንጉሥ አዶኒጼዴቅ ለኬብሮን+ ንጉሥ ለሆሐም፣ ለያርሙት ንጉሥ ለፒራም፣ ለለኪሶ ንጉሥ ለያፊአ እና ለኤግሎን ንጉሥ+ ለደቢር እንዲህ የሚል መልእክት ላከ፦ 4 “መጥታችሁ እርዱኝና በገባኦን ላይ ጥቃት እንሰንዝር፤ ምክንያቱም ገባኦን ከኢያሱና ከእስራኤላውያን ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ፈጥራለች።”+ 5 በዚህ ጊዜ አምስቱ የአሞራውያን+ ነገሥታት ይኸውም የኢየሩሳሌም ንጉሥ፣ የኬብሮን ንጉሥ፣ የያርሙት ንጉሥ፣ የለኪሶ ንጉሥና የኤግሎን ንጉሥ ከነሠራዊታቸው አንድ ላይ ተሰብስበው በመዝመት ገባኦንን ለመውጋት ከበቧት።

6 የገባኦን ሰዎችም በጊልጋል+ በሚገኘው ሰፈር ወደነበረው ወደ ኢያሱ እንዲህ የሚል መልእክት ላኩበት፦ “እኛን ባሪያዎችህን አትተወን።+ ፈጥነህ ድረስልን! አድነን፤ እርዳን! በተራራማው አካባቢ የሚኖሩት የአሞራውያን ነገሥታት በሙሉ እኛን ለመውጋት ተሰብስበዋል።” 7 በመሆኑም ኢያሱ ተዋጊዎቹንና ኃያላን የሆኑትን ጦረኞች+ በሙሉ ይዞ ከጊልጋል ወጣ።

8 ከዚያም ይሖዋ ኢያሱን “በእጅህ አሳልፌ ስለሰጠኋቸው+ አትፍራቸው።+ አንዳቸውም እንኳ ሊቋቋሙህ አይችሉም”+ አለው። 9 ኢያሱም ከጊልጋል በመነሳት ሌሊቱን ሙሉ ሲገሰግስ አድሮ ድንገት መጣባቸው። 10 ይሖዋም በእስራኤላውያን ፊት ግራ እንዲጋቡ አደረጋቸው፤+ እነሱም ገባኦን ላይ ክፉኛ ጨፈጨፏቸው፤ ወደ ቤትሆሮን አቀበት በሚወስደው መንገድ ላይ በማሳደድ እስከ አዜቃ እና እስከ መቄዳ ድረስ መቷቸው። 11 እነሱም ከእስራኤላውያን በመሸሽ የቤትሆሮንን ቁልቁለት እየወረዱ ሳሉ እስከ አዜቃ ድረስ ይሖዋ ከሰማይ ትላልቅ የበረዶ ድንጋይ አወረደባቸው፤ እነሱም ሞቱ። እንዲያውም በእስራኤላውያን ሰይፍ ከሞቱት ይልቅ በበረዶ ድንጋይ የሞቱት ይበልጣሉ።

12 ይሖዋ አሞራውያንን ከእስራኤላውያን ፊት ባባረረበት ዕለት ኢያሱ በእስራኤላውያን ፊት ይሖዋን እንዲህ አለው፦

“ፀሐይ ሆይ፣ በገባኦን ላይ ቁሚ፤+

አንቺም ጨረቃ ሆይ፣ በአይሎን ሸለቆ* ላይ ቀጥ በይ!”

13 በመሆኑም ብሔሩ ጠላቶቹን እስኪበቀል ድረስ ፀሐይ ባለችበት ቆመች፤ ጨረቃም አልተንቀሳቀሰችም። ይህስ በያሻር መጽሐፍ+ ላይ ተጽፎ የሚገኝ አይደለም? ፀሐይ በሰማይ መካከል ባለችበት ቆመች፤ ለአንድ ቀን ያህል ለመጥለቅ አልቸኮለችም። 14 ይሖዋ የሰውን ቃል የሰማበት+ እንደዚያ ያለ ቀን ከዚያ በፊትም ሆነ ከዚያ በኋላ ፈጽሞ አልነበረም፤ ምክንያቱም ይሖዋ ለእስራኤል እየተዋጋ ነበር።+

15 ከዚያ በኋላ ኢያሱና መላው እስራኤል በጊልጋል ወደሚገኘው ሰፈር+ ተመለሱ።

16 በዚህ ጊዜ አምስቱ ነገሥታት ሸሽተው በመቄዳ+ በሚገኝ ዋሻ ውስጥ ተደብቀው ነበር። 17 ከዚያም ኢያሱ “አምስቱ ነገሥታት በመቄዳ+ በሚገኘው ዋሻ ውስጥ ተደብቀው ተገኝተዋል” የሚል መልእክት ደረሰው። 18 እሱም እንዲህ አለ፦ “ትላልቅ ድንጋዮች አንከባላችሁ የዋሻውን አፍ ግጠሙትና እነሱን የሚጠብቁ ሰዎች መድቡ። 19 የተቀራችሁት ግን ዝም ብላችሁ አትቁሙ። ጠላቶቻችሁን እያሳደዳችሁ ከኋላ ምቷቸው።+ አምላካችሁ ይሖዋ በእጃችሁ አሳልፎ ስለሰጣቸው ወደ ከተሞቻቸው እንዲገቡ አትፍቀዱላቸው።”

20 ኢያሱና እስራኤላውያን፣ አምልጠው ወደተመሸጉት ከተሞች ከገቡት ጥቂት ሰዎች በቀር ጠላቶቻቸውን እስኪጠፉ ድረስ ክፉኛ ከጨፈጨፏቸው በኋላ 21 ሕዝቡ ሁሉ በመቄዳ በሚገኘው ሰፈር ወደነበረው ወደ ኢያሱ በሰላም ተመለሰ። በእስራኤላውያን ላይ አንዲት ቃል ሊናገር የደፈረ* ሰው አልነበረም። 22 ከዚያም ኢያሱ “የዋሻውን አፍ ከፍታችሁ አምስቱን ነገሥታት ከዋሻው አውጥታችሁ ወደ እኔ አምጧቸው” አለ። 23 ስለሆነም እነዚህን አምስት ነገሥታት ማለትም የኢየሩሳሌምን ንጉሥ፣ የኬብሮንን ንጉሥ፣ የያርሙትን ንጉሥ፣ የለኪሶን ንጉሥና የኤግሎንን ንጉሥ ከዋሻው አውጥተው ወደ እሱ አመጧቸው።+ 24 ኢያሱም እነዚህን ነገሥታት ወደ እሱ ባመጧቸው ጊዜ የእስራኤልን ሰዎች በሙሉ ጠርቶ አብረውት የሄዱትን የሠራዊቱን አዛዦች “ወደዚህ ቅረቡ። እግራችሁን በእነዚህ ነገሥታት ማጅራት ላይ አድርጉ” አላቸው። እነሱም ቀርበው እግራቸውን በማጅራታቸው ላይ አደረጉ።+ 25 ከዚያም ኢያሱ እንዲህ አላቸው፦ “አትፍሩ ወይም አትሸበሩ።+ ይሖዋ በምትዋጓቸው ጠላቶቻችሁ ሁሉ ላይ እንዲህ ስለሚያደርግ ደፋርና ብርቱ ሁኑ።”+

26 ከዚያም ኢያሱ መትቶ ገደላቸው፤ በአምስት እንጨቶችም* ላይ ሰቀላቸው፤ በእንጨቶቹም ላይ እንደተሰቀሉ እስከ ምሽት ድረስ ቆዩ። 27 ፀሐይም ልትጠልቅ ስትቃረብ ኢያሱ፣ አስከሬኖቻቸው ከእንጨቶቹ ላይ እንዲወርዱና+ ተደብቀውበት በነበረው ዋሻ ውስጥ እንዲጣሉ ትእዛዝ ሰጠ። ከዚያም በዋሻው አፍ ላይ ትላልቅ ድንጋዮችን አደረጉ፤ እነዚህም እስከ ዛሬ ድረስ እዚያው ይገኛሉ።

28 ኢያሱም በዚያን ዕለት መቄዳን+ በመቆጣጠር ሕዝቡን በሰይፍ ፈጀ። ንጉሥዋንና በውስጧ ያለውን ሰው* ሁሉ አንድም ሳያስቀር ፈጽሞ አጠፋ።+ በኢያሪኮ ንጉሥ ላይ እንዳደረገውም ሁሉ በመቄዳ ንጉሥ+ ላይ አደረገ።

29 ከዚያም ኢያሱና ከእሱ ጋር የነበሩት እስራኤላውያን በሙሉ ከመቄዳ ወደ ሊብና በመሄድ ሊብናን+ ወጓት። 30 ይሖዋም ከተማዋንና ንጉሥዋን+ በእስራኤላውያን እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነሱም ከተማዋንና በውስጧ ያለውን ሰው* ሁሉ አንድም ሳያስቀሩ በሰይፍ መቱ። በኢያሪኮ ንጉሥ ላይ እንዳደረጉትም ሁሉ በንጉሥዋ ላይ አደረጉ።+

31 በመቀጠልም ኢያሱና ከእሱ ጋር የነበሩት እስራኤላውያን በሙሉ ከሊብና ወደ ለኪሶ+ ሄዱ፤ እሷንም ከበው ወጓት። 32 ይሖዋም ለኪሶን ለእስራኤላውያን አሳልፎ ሰጣት፤ እነሱም በሁለተኛው ቀን ያዟት። በሊብና ላይ እንዳደረጉትም ሁሉ ከተማዋንና በውስጧ ያለውን ሰው* ሁሉ በሰይፍ መቱ።+

33 በዚህ ጊዜ የጌዜር+ ንጉሥ ሆራም ለኪሶን ለመርዳት ወጣ፤ ሆኖም ኢያሱ እሱንና ሕዝቡን አንድም ሳያስቀር መታቸው።

34 በመቀጠልም ኢያሱና ከእሱ ጋር የነበሩት እስራኤላውያን በሙሉ ከለኪሶ ወደ ኤግሎን+ በመሄድ ከበው ወጓት። 35 እነሱም በዚያን ቀን ከተማዋን በመቆጣጠር በሰይፍ መቷት። በለኪሶ ላይ እንዳደረጉት ሁሉ በውስጧ ያለውን ሰው* ሁሉ በዚያኑ ዕለት ሙሉ በሙሉ አጠፉ።+

36 ከዚያም ኢያሱና ከእሱ ጋር የነበሩት እስራኤላውያን በሙሉ ከኤግሎን ወደ ኬብሮን+ በመውጣት ኬብሮንን ወጓት። 37 እሷንም ተቆጣጥረው ከተማዋን፣ ንጉሥዋንና በዙሪያዋ ያሉትን አነስተኛ ከተሞች እንዲሁም በውስጧ ያለውን ሰው* ሁሉ አንድም ሳያስቀሩ በሰይፍ መቱ። በኤግሎንም ላይ እንዳደረገው ሁሉ ከተማዋንና በውስጧ ያለውን ሰው* ሁሉ ሙሉ በሙሉ አጠፋ።

38 በመጨረሻም ኢያሱና ከእሱ ጋር የነበሩት እስራኤላውያን በሙሉ ወደ ደቢር+ በመዞር ወጓት። 39 ከተማዋን፣ ንጉሥዋንና በዙሪያዋ ያሉትን አነስተኛ ከተሞች ተቆጣጠረ፤ እነሱንም በሰይፍ መቷቸው፤ በውስጧ ያለውንም ሰው* ሁሉ አንድም ሳያስቀሩ+ ፈጽመው አጠፉ።+ በኬብሮን እንዲሁም በሊብና እና በንጉሥዋ ላይ እንዳደረገው ሁሉ በደቢርና በንጉሥዋ ላይ አደረገ።

40 ኢያሱም ምድሩን ሁሉ ይኸውም ተራራማውን አካባቢ፣ ኔጌብን፣ ሸፌላን፣+ ሸንተረሮቹንና ነገሥታታቸውን በሙሉ ድል አደረገ፤ አንድም ሰው አላስቀረም፤ የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ባዘዘውም መሠረት+ እስትንፋስ ያለውን ሁሉ ፈጽሞ አጠፋ።+ 41 ኢያሱ ከቃዴስበርኔ+ አንስቶ እስከ ጋዛ+ ድረስ እንዲሁም የጎሸንን+ ምድር በሙሉ እስከ ገባኦን+ ድረስ ድል አደረገ። 42 ኢያሱ እነዚህን ሁሉ ነገሥታትና ምድራቸውን በሙሉ በአንድ ጊዜ ተቆጣጠረ፤ ምክንያቱም የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ለእስራኤላውያን እየተዋጋላቸው ነበር።+ 43 ከዚያም ኢያሱና እስራኤላውያን በሙሉ በጊልጋል+ ወደሚገኘው ሰፈር ተመለሱ።

11 የሃጾር ንጉሥ ያቢን ይህን ሲሰማ ወደ ማዶን ንጉሥ+ ወደ ዮባብ፣ ወደ ሺምሮን ንጉሥ፣ ወደ አክሻፍ ንጉሥ+ 2 እንዲሁም በስተ ሰሜን በሚገኘው ተራራማ አካባቢ፣ በደቡብ ኪኔሬት ባሉት ሜዳዎችና* በሸፌላ ወደሚገኙት እንዲሁም በስተ ምዕራብ በዶር+ ሸንተረሮች ወዳሉት ነገሥታት፣ 3 በስተ ምሥራቅና በስተ ምዕራብ ወዳሉት ከነአናውያን፣+ ወደ አሞራውያን፣+ ወደ ሂታውያን፣ ወደ ፈሪዛውያን፣ በተራራማው አካባቢ ወደሚኖሩት ወደ ኢያቡሳውያን እንዲሁም በምጽጳ ምድር በሄርሞን+ ግርጌ ወደሚገኙት ወደ ሂዋውያን+ መልእክት ላከ። 4 እነሱም በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ ብዙ ከሆነው ሠራዊታቸው ሁሉ ጋር ወጡ፤ እጅግ ብዙ ፈረሶችና የጦር ሠረገሎችም ነበሯቸው። 5 እነዚህም ነገሥታት በሙሉ አንድ ላይ ለመገናኘት ተስማሙ፤ ከዚያም እስራኤልን ለመውጋት መጥተው በመሮም ውኃ አጠገብ አንድ ላይ ሰፈሩ።

6 በዚህ ጊዜ ይሖዋ ኢያሱን እንዲህ አለው፦ “ነገ በዚህ ሰዓት ገደማ ሁሉንም ለእስራኤላውያን አሳልፌ ስለምሰጣቸው አትፍሯቸው፤+ እናንተም ትፈጇቸዋላችሁ። የፈረሶቻቸውን ቋንጃ ቁረጡ፣+ ሠረገሎቻቸውንም በእሳት አቃጥሉ።” 7 ከዚያም ኢያሱና አብረውት የነበሩት ተዋጊዎች በሙሉ በመሮም ውኃ አጠገብ ድንገተኛ ጥቃት ሰነዘሩባቸው። 8 ይሖዋም ለእስራኤላውያን አሳልፎ ሰጣቸው፤+ እነሱም ድል አደረጓቸው፤ እስከ ታላቋ ሲዶና፣+ እስከ ሚስረፎትማይምና+ በስተ ምሥራቅ እስካለው እስከ ምጽጳ ሸለቆ ድረስም አሳደዷቸው፤ አንድም ሰው በሕይወት ሳያስቀሩ መቷቸው።+ 9 ከዚያም ኢያሱ ልክ ይሖዋ እንደነገረው አደረገባቸው፤ የፈረሶቻቸውን ቋንጃ ቆረጠ፤ ሠረገሎቻቸውንም በእሳት አቃጠለ።+

10 ከዚህም በተጨማሪ ኢያሱ ተመልሶ ሃጾርን ተቆጣጠረ፤ ንጉሥዋንም በሰይፍ መትቶ ገደለው፤+ ምክንያቱም ሃጾር ቀደም ሲል የእነዚህ መንግሥታት ሁሉ የበላይ ነበረች። 11 እነሱም በውስጧ ያለውን ሰው* ሁሉ በሰይፍ በመምታት ፈጽመው አጠፉ።+ እስትንፋስ ያለው አንድም ነገር አላስቀሩም።+ ከዚያም ሃጾርን በእሳት አቃጠላት። 12 ኢያሱ የእነዚህን ነገሥታት ከተሞች በሙሉ በቁጥጥር ሥር አዋለ፤ ነገሥታታቸውንም ሁሉ በሰይፍ ድል አደረገ።+ የይሖዋ አገልጋይ ሙሴ ባዘዘውም መሠረት ፈጽሞ አጠፋቸው።+ 13 ሆኖም እስራኤላውያን ኢያሱ ካቃጠላት ከሃጾር በስተቀር በኮረብቶቻቸው ላይ ካሉት ከተሞች አንዱንም አላቃጠሉም ነበር። 14 እስራኤላውያን ከእነዚህ ከተሞች ያገኙትን ምርኮና የቤት እንስሳ ሁሉ ለራሳቸው ወሰዱ።+ ሰዎቹን ግን አንድ በአንድ በሰይፍ መተው ሁሉንም አጠፏቸው።+ እስትንፋስ ያለው አንድም ሰው አላስቀሩም።+ 15 ይሖዋ አገልጋዩን ሙሴን እንዳዘዘው ሁሉ ሙሴም ኢያሱን አዞት ነበር፤+ ኢያሱም እንደተባለው አደረገ። ኢያሱ፣ ይሖዋ ሙሴን ካዘዘው ሁሉ ሳይፈጽም የቀረው አንድም ነገር አልነበረም።+

16 ኢያሱ ይህን ምድር በሙሉ ይኸውም ተራራማውን አካባቢ፣ ኔጌብን+ በሙሉ፣ የጎሸንን ምድር ሁሉ፣ ሸፌላን፣+ አረባን፣+ የእስራኤልን ተራራማና ቆላማ አካባቢዎች በሙሉ ድል አደረገ፤ 17 ወደ ሴይር ሽቅብ ከሚወጣው ከሃላቅ ተራራ አንስቶ በሄርሞን ተራራ+ ግርጌ በሊባኖስ ሸለቆ እስከሚገኘው እስከ በዓልጋድ+ ድረስ ያለውን አካባቢ በሙሉ ድል አደረገ፤ ነገሥታታቸውን ሁሉ በቁጥጥር ሥር አዋለ፤ ድል አደረጋቸው፤ ገደላቸውም። 18 ኢያሱ ከእነዚህ ሁሉ ነገሥታት ጋር ለተወሰነ ጊዜ ተዋጋ። 19 በገባኦን ከሚኖሩት ሂዋውያን በስተቀር ከእስራኤላውያን ጋር ሰላማዊ ግንኙነት የፈጠረ አንድም ከተማ አልነበረም።+ ሌሎቹን ሁሉ በጦርነት ድል አደረጓቸው።+ 20 በእስራኤል ላይ ጦርነት እንዲከፍቱና ምንም ሳይራራላቸው ፈጽሞ ያጠፋቸው+ ዘንድ ልባቸው እንዲደነድን የፈቀደው ይሖዋ ነው።+ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት ሙሉ በሙሉ መጥፋት ነበረባቸው።+

21 በዚያን ጊዜ ኢያሱ ከተራራማው አካባቢ ከኬብሮን፣ ከደቢር፣ ከአናብ እንዲሁም ከይሁዳ ተራራማ አካባቢዎች ሁሉና ከእስራኤል ተራራማ አካባቢዎች ሁሉ ኤናቃውያንን+ ጠራርጎ አጠፋ። ኢያሱ እነሱንም ሆነ ከተሞቻቸውን ሙሉ በሙሉ አጠፋቸው።+ 22 በእስራኤላውያን ምድር የተረፈ አንድም ኤናቃዊ አልነበረም፤ ኤናቃውያን የነበሩት በጋዛ፣+ በጌት+ እና በአሽዶድ+ ብቻ ነበር።+ 23 ስለዚህ ኢያሱ ይሖዋ ለሙሴ በገባው ቃል መሠረት ምድሩን ሁሉ ተቆጣጠረ፤+ ከዚያም ኢያሱ ለእስራኤላውያን በየነገዳቸው ድርሻቸውን ርስት አድርጎ ሰጣቸው።+ ምድሪቱም ከጦርነት አረፈች።+

12 እንግዲህ እስራኤላውያን ድል ያደረጓቸውና ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ የሚገኘውን ምድራቸውን ይኸውም ከአርኖን ሸለቆ*+ አንስቶ እስከ ሄርሞን ተራራ+ ድረስ ያለውን እንዲሁም በስተ ምሥራቅ የሚገኘውን አረባን በሙሉ የወረሱባቸው ነገሥታት እነዚህ ናቸው፦+ 2 በሃሽቦን የሚኖረውና በአርኖን ሸለቆ* ዳርቻ ላይ በምትገኘው በአሮዔር+ ሆኖ የሚገዛው የአሞራውያን ንጉሥ ሲሖን፤+ እሱም በአርኖን ሸለቆ+ መሃል ካለው ስፍራ አንስቶ የአሞናውያን ወሰን እስከሆነው እስከ ያቦቅ ሸለቆ* ድረስ ያለውን የጊልያድን እኩሌታ ይገዛ ነበር። 3 በተጨማሪም ምሥራቃዊ አረባን እስከ ኪኔሬት ባሕር*+ ድረስ፣ በስተ ምሥራቅ በቤትየሺሞት አቅጣጫ እስካለው የአረባ ባሕር ይኸውም እስከ ጨው ባሕር* ድረስና በስተ ደቡብ እስከ ጲስጋ+ ሸንተረር ድረስ ያለውን አካባቢ ይገዛ ነበር።

4 እንዲሁም በአስታሮትና በኤድራይ ይኖር የነበረውንና ከመጨረሻዎቹ የረፋይም+ ወገኖች አንዱ የሆነውን የባሳንን ንጉሥ የኦግን+ ግዛት፤ 5 እሱም የሄርሞንን ተራራ፣ ሳልካን፣ ባሳንን+ በሙሉ እስከ ገሹራውያንና እስከ ማአካታውያን+ ወሰን ድረስ እንዲሁም እስከ ሃሽቦን+ ንጉሥ እስከ ሲሖን ግዛት ድረስ ያለውን የጊልያድን እኩሌታ ይገዛ ነበር።

6 የይሖዋ አገልጋይ ሙሴና እስራኤላውያን እነዚህን ነገሥታት ድል አደረጓቸው፤+ ከዚያም የይሖዋ አገልጋይ ሙሴ ምድራቸውን ለሮቤላውያን፣ ለጋዳውያንና ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ርስት አድርጎ ሰጠ።+

7 ኢያሱና እስራኤላውያን ድል ያደረጓቸው ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ ያሉት የምድሪቱ ነገሥታት እነዚህ ናቸው፤ ግዛታቸውም በሊባኖስ ሸለቆ+ ከሚገኘው ከበዓልጋድ+ አንስቶ ወደ ሴይር+ ሽቅብ እስከሚወጣው እስከ ሃላቅ ተራራ+ ድረስ ነው፤ ከዚያም ኢያሱ ምድራቸውን ለእስራኤል ነገዶች እንደየድርሻቸው ርስት አድርጎ ሰጠ፤+ 8 ይህም በተራራማው አካባቢ፣ በሸፌላ፣ በአረባ፣ በሸንተረሮቹ ላይ፣ በምድረ በዳውና በኔጌብ+ የሚኖሩት የሂታውያን፣ የአሞራውያን፣+ የከነአናውያን፣ የፈሪዛውያን፣ የሂዋውያንና የኢያቡሳውያን+ ምድር ነው፤ ነገሥታቱም የሚከተሉት ናቸው፦

 9 የኢያሪኮ ንጉሥ፣+ አንድ፤ በቤቴል አጠገብ የነበረችው የጋይ ንጉሥ፣+ አንድ፤

10 የኢየሩሳሌም ንጉሥ፣ አንድ፤ የኬብሮን ንጉሥ፣+ አንድ፤

11 የያርሙት ንጉሥ፣ አንድ፤ የለኪሶ ንጉሥ፣ አንድ፤

12 የኤግሎን ንጉሥ፣ አንድ፤ የጌዜር ንጉሥ፣+ አንድ፤

13 የደቢር ንጉሥ፣+ አንድ፤ የጌዴር ንጉሥ፣ አንድ፤

14 የሆርማ ንጉሥ፣ አንድ፤ የአራድ ንጉሥ፣ አንድ፤

15 የሊብና ንጉሥ፣+ አንድ፤ የአዱላም ንጉሥ፣ አንድ፤

16 የመቄዳ ንጉሥ፣+ አንድ፤ የቤቴል ንጉሥ፣+ አንድ፤

17 የታጱአ ንጉሥ፣ አንድ፤ የሄፌር ንጉሥ፣ አንድ፤

18 የአፌቅ ንጉሥ፣ አንድ፤ የላሻሮን ንጉሥ፣ አንድ፤

19 የማዶን ንጉሥ፣ አንድ፤ የሃጾር ንጉሥ፣+ አንድ፤

20 የሺምሮንመሮን ንጉሥ፣ አንድ፤ የአክሻፍ ንጉሥ፣ አንድ፤

21 የታአናክ ንጉሥ፣ አንድ፤ የመጊዶ ንጉሥ፣ አንድ፤

22 የቃዴሽ ንጉሥ፣ አንድ፤ በቀርሜሎስ የምትገኘው የዮቅነአም ንጉሥ፣+ አንድ፤

23 በዶር+ ሸንተረሮች የምትገኘው የዶር ንጉሥ፣ አንድ፤ በጊልጋል የምትገኘው የጎይም ንጉሥ፣ አንድ፤

24 የቲርጻ ንጉሥ፣ አንድ፤ በአጠቃላይ 31 ነገሥታት ናቸው።

13 ኢያሱም ዕድሜው ገፍቶና አርጅቶ ነበር።+ በመሆኑም ይሖዋ እንዲህ አለው፦ “እንግዲህ አንተ ዕድሜህ ገፍቷል፤ አርጅተሃል፤ ሆኖም መወረስ* ያለበት ገና ሰፊ ምድር ይቀራል። 2 የሚቀረውም ምድር ይህ ነው፦+ የፍልስጤማውያንና የገሹራውያን+ ምድር በሙሉ 3 (ከግብፅ ፊት ለፊት ከሚገኘው ከአባይ ወንዝ ቅርንጫፍ* አንስቶ በሰሜን እስከ ኤቅሮን ወሰን ድረስ ያለው ክልል የከነአናውያን ግዛት እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠር ነበር)+ እንዲሁም በጋዛ፣ በአሽዶድ፣+ በአስቀሎን፣+ በጌት+ እና በኤቅሮን+ የሚኖሩትን የአምስቱን የፍልስጤም ገዢዎች+ ምድር የሚጨምር ሲሆን የአዊም+ ሰዎችንም ምድር ያካትታል፤ 4 እነሱም በደቡብ በኩል ይኖሩ ነበር፤ መላው የከነአናውያን ምድር፤ የሲዶናውያን+ ይዞታ የሆነችው መአራ፣ እንዲሁም በአሞራውያን ወሰን ላይ እስከሚገኘው እስከ አፌቅ ድረስ ያለው አካባቢ፤ 5 የጌባላውያን+ ምድር፣ በስተ ምሥራቅ አቅጣጫ ያለው መላው ሊባኖስ ይኸውም በሄርሞን ተራራ ግርጌ ከሚገኘው ከበዓልጋድ አንስቶ እስከ ሌቦሃማት*+ ድረስ ያለው አካባቢ፤ 6 በተራራማው አካባቢ፣ ከሊባኖስ+ እስከ ሚስረፎትማይም+ ባለው ምድር የሚኖሩት ነዋሪዎች በሙሉ እንዲሁም ሲዶናውያን+ በሙሉ ናቸው። እነሱንም ከእስራኤላውያን ፊት አባርራቸዋለሁ።+ አንተም ባዘዝኩህ መሠረት ምድሩን ለእስራኤላውያን ርስት አድርገህ ስጥ።+ 7 እንግዲህ ይህን ምድር ለዘጠኙ ነገዶችና ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ርስት አድርገህ አከፋፍል።”+

8 የተቀረው የምናሴ ነገድ እኩሌታና ሮቤላውያን እንዲሁም ጋዳውያን የይሖዋ አገልጋይ ሙሴ በሰጣቸው መሠረት ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ርስታቸውን ወስደዋል፤+ 9 ይህም በአርኖን ሸለቆ*+ መካከል የምትገኘውን ከተማና የመደባን አምባ በሙሉ ጨምሮ በሸለቆው ዳርቻ ላይ ከምትገኘው ከአሮዔር+ አንስቶ እስከ ዲቦን ድረስ ያለውን አካባቢ፣ 10 በሃሽቦን ሆኖ ይገዛ የነበረውን የአሞራውያንን ንጉሥ የሲሖንን ከተሞች በሙሉ እስከ አሞናውያን+ ወሰን ድረስ፣ 11 ጊልያድን፣ የገሹራውያንንና የማአካታውያንን+ ግዛት፣ የሄርሞንን ተራራ በሙሉ፣ ባሳንን+ በሙሉ እስከ ሳልካ+ ድረስ 12 እንዲሁም በአስታሮት እና በኤድራይ ሆኖ ይገዛ የነበረውን በባሳን ያለውን የኦግን ንጉሣዊ ግዛት በሙሉ ያጠቃልላል። (እሱም በሕይወት ከተረፉት የመጨረሻዎቹ የረፋይም ዘሮች አንዱ ነበር።)+ ሙሴም ድል አድርጎ አባረራቸው።+ 13 ሆኖም እስራኤላውያን ገሹራውያንንና ማአካታውያንን ከምድራቸው አላስለቀቋቸውም፤+ ምክንያቱም ገሹራውያንና ማአካታውያን እስከ ዛሬ ድረስ በእስራኤል መካከል አሉ።

14 ውርስ ያልሰጠው ለሌዋውያን ነገድ ብቻ ነበር።+ የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ቃል በገባላቸው መሠረት+ ለእሱ በእሳት የሚቀርቡት መባዎች የእነሱ ውርሻ ናቸው።+

15 ከዚያም ሙሴ ለሮቤላውያን ነገድ በየቤተሰባቸው ርስት ሰጣቸው፤ 16 ግዛታቸውም በአርኖን ሸለቆ* ዳርቻ ላይ ከምትገኘው ከአሮዔር አንስቶ ያለው ሲሆን በሸለቆው መካከል የምትገኘውን ከተማ፣ የመደባን አምባ በሙሉ፣ 17 ሃሽቦንንና በአምባው ላይ ያሉትን ከተሞቿን በሙሉ፣+ ዲቦንን፣ ባሞትበዓልን፣ ቤትበዓልመዖንን፣+ 18 ያሃጽን፣+ ቀደሞትን፣+ መፋአትን፣+ 19 ቂርያታይምን፣ ሲብማን፣+ በሸለቆው* አጠገብ ባለው ኮረብታ ላይ የምትገኘውን ጸሬትሻሃርን፣ 20 ቤትጰኦርን፣ የጲስጋን ሸንተረሮች፣+ ቤትየሺሞትን፣+ 21 በአምባው ላይ የሚገኙትን ከተሞች ሁሉ እንዲሁም በሃሽቦን+ ሆኖ ይገዛ የነበረውን የአሞራውያንን ንጉሥ የሲሖንን ንጉሣዊ ግዛት በሙሉ ያጠቃልላል። ሙሴም ይህን ንጉሥና+ በምድሪቱ ይኖሩ የነበሩትን የምድያም አለቆች፣ ኤዊን፣ ራቄምን፣ ጹርን፣ ሁርን እና ረባን+ እንዲሁም የሲሖንን መሳፍንት* ድል አድርጓቸው ነበር። 22 እስራኤላውያን በሰይፍ ከገደሏቸው መካከል ሟርተኛው+ የቢዖር ልጅ በለዓም+ ይገኝበታል። 23 የሮቤላውያን ወሰን ዮርዳኖስ ነበር፤ ከተሞቹንና መንደሮቹን ጨምሮ ይህ ግዛት ሮቤላውያን በየቤተሰባቸው የያዙት ርስት ነው።

24 በተጨማሪም ሙሴ ለጋድ ነገድ ይኸውም ለጋዳውያን በየቤተሰባቸው ርስት ሰጣቸው፤ 25 ግዛታቸውም ያዜርን፣+ የጊልያድን ከተሞች በሙሉ፣ ከራባ+ ፊት ለፊት እስከምትገኘው እስከ አሮዔር የሚደርሰውን የአሞናውያንን+ ምድር እኩሌታ፣ 26 ከሃሽቦን+ እስከ ራማትምጽጳ እና እስከ በጦኒም እንዲሁም ከማሃናይም+ እስከ ደቢር ወሰን ድረስ ያለውን አካባቢ፣ 27 በሸለቆው ውስጥ* ደግሞ ቤትሃራምን፣ ቤትኒምራን፣+ ሱኮትን፣+ ጻፎንን እና ወሰኑ ዮርዳኖስ ሆኖ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ከሚገኘው ከኪኔሬት ባሕር*+ የታችኛው ጫፍ ጀምሮ ያለውን ቀሪውን የሃሽቦንን ንጉሥ የሲሖንን ንጉሣዊ ግዛት+ ያጠቃልላል። 28 ከተሞቹንና መንደሮቹን ጨምሮ ጋዳውያን በየቤተሰባቸው የያዙት ርስት ይህ ነው።

29 በተጨማሪም ሙሴ ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ይኸውም ለግማሹ የምናሴ ነገድ በየቤተሰባቸው ርስት ሰጠ።+ 30 ግዛታቸውም ከማሃናይም+ አንስቶ ያለው ሲሆን ባሳንን በሙሉ፣ የባሳንን ንጉሥ የኦግን ንጉሣዊ ግዛት በሙሉ፣ በባሳን የሚገኙትን የያኢር+ የድንኳን ሰፈሮች በሙሉ፣ 60 ከተሞችን ያጠቃልላል። 31 የጊልያድ እኩሌታ እንዲሁም በባሳን የሚገኙት የኦግ ንጉሣዊ ግዛት ከተሞች ማለትም አስታሮትና ኤድራይ+ የምናሴ ልጅ ለሆነው ለማኪር+ ልጆች ይኸውም ለማኪር ልጆች እኩሌታ በየቤተሰባቸው ተሰጡ።

32 ሙሴ ከዮርዳኖስ ማዶ ከኢያሪኮ በስተ ምሥራቅ በሞዓብ በረሃማ ሜዳ የሰጣቸው ርስት ይህ ነበር።+

33 ሆኖም ሙሴ ለሌዋውያን ነገድ ርስት አልሰጠም።+ የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ቃል በገባላቸው መሠረት ርስታቸው እሱ ነው።+

14 እንግዲህ እስራኤላውያን በከነአን ምድር ርስት አድርገው የወረሱት ይኸውም ካህኑ አልዓዛር፣ የነዌ ልጅ ኢያሱና የእስራኤል ነገዶች የአባቶች ቤት መሪዎች ያወረሷቸው ምድር ይህ ነው።+ 2 ይሖዋ ዘጠኙን ነገድና ግማሹን ነገድ+ አስመልክቶ በሙሴ አማካኝነት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ርስታቸው የተከፋፈለው በዕጣ ነበር።+ 3 ሙሴ ለሌሎቹ ሁለት ነገዶችና ለሌላኛው ግማሽ ነገድ ከዮርዳኖስ ማዶ* ርስት ሰጥቷቸው ነበር፤+ ለሌዋውያኑ ግን በእነሱ መካከል ርስት አልሰጣቸውም።+ 4 የዮሴፍ ዘሮች እንደ ሁለት ነገድ ተደርገው ይቆጠሩ+ የነበረ ሲሆን እነሱም ምናሴና ኤፍሬም ናቸው፤+ ለሌዋውያኑም ከሚኖሩባቸው ከተሞች እንዲሁም ለከብቶቻቸውና ለንብረቶቻቸው ከሚሆን መሬት በስተቀር በምድሪቱ ውስጥ ድርሻ አልሰጧቸውም።+ 5 በመሆኑም እስራኤላውያን ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት ምድሪቱን ተከፋፈሉ።

6 ከዚያም የይሁዳ ሰዎች በጊልጋል+ ወደ ኢያሱ ቀረቡ፤ የቀኒዛዊው የየፎኒ ልጅ ካሌብም+ እንዲህ አለው፦ “ይሖዋ በቃዴስበርኔ+ ስለ እኔና ስለ አንተ ለእውነተኛው አምላክ ሰው ለሙሴ+ ምን እንዳለው በሚገባ ታውቃለህ።+ 7 የይሖዋ አገልጋይ ሙሴ ምድሪቱን እንድሰልል ከቃዴስበርኔ ሲልከኝ የ40 ዓመት ሰው ነበርኩ፤+ እኔም ትክክለኛውን መረጃ* ይዤ መጣሁ።+ 8 አብረውኝ የወጡት ወንድሞቼ የሕዝቡ ልብ እንዲቀልጥ ቢያደርጉም እኔ ግን አምላኬን ይሖዋን በሙሉ ልቤ ተከተልኩት።+ 9 ሙሴም በዚያ ዕለት ‘አምላኬን ይሖዋን በሙሉ ልብህ ስለተከተልከው እግርህ የረገጣት ምድር ለዘለቄታው የአንተና የልጆችህ ርስት ትሆናለች’ ብሎ ማለ።+ 10 እስራኤል በምድረ በዳ እየተጓዘ ሳለ+ ይሖዋ ለሙሴ ይህን ቃል ከገባለት ጊዜ አንስቶ ይሖዋ በገባው ቃል መሠረት+ እነዚህን 45 ዓመታት በሕይወት አቆይቶኛል፤+ ይኸው ዛሬ 85 ዓመት ሆኖኛል። 11 ደግሞም ሙሴ በላከኝ ጊዜ የነበረኝ ብርታት ዛሬም አለኝ። ልክ እንደዚያን ጊዜ ሁሉ አሁንም ወደ ጦርነት ለመሄድም ሆነ ሌሎች ነገሮችን ለማከናወን የሚያስችል ጥንካሬ አለኝ። 12 ስለዚህ ይሖዋ በዚያ ዕለት ቃል የገባውን ይህን ተራራማ አካባቢ ስጠኝ። የተመሸጉ ታላላቅ ከተሞች+ ያሏቸው ኤናቃውያን+ በአካባቢው እንደሚኖሩ በዚያ ቀን ሰምተህ የነበረ ቢሆንም ይሖዋ ከእኔ ጋር እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፤+ ይሖዋም በገባው ቃል መሠረት ድል አድርጌ አባርራቸዋለሁ።”+

13 በመሆኑም ኢያሱ ባረከው፤ ኬብሮንንም ለየፎኒ ልጅ ለካሌብ ርስት አድርጎ ሰጠው።+ 14 ኬብሮን ለቀኒዛዊው ለየፎኒ ልጅ ለካሌብ እስከ ዛሬ ድረስ ርስት የሆነችው ለዚህ ነው፤ ምክንያቱም እሱ የእስራኤልን አምላክ ይሖዋን በሙሉ ልቡ ተከትሏል።+ 15 ኬብሮን ከዚያ በፊት ቂርያትአርባ+ ተብላ ትጠራ ነበር (አርባ በኤናቃውያን መካከል ታላቅ ሰው ነበር)። ምድሪቱም ከጦርነት አረፈች።+

15 ለይሁዳ ነገድ ለየቤተሰቡ በዕጣ የተሰጠው ርስት+ እስከ ኤዶም+ ይኸውም እስከ ጺን ምድረ በዳና እስከ ኔጌብ ደቡባዊ ጫፍ ድረስ ይዘልቃል። 2 ደቡባዊው ወሰናቸው ከጨው ባሕር* ዳርቻ+ ይኸውም ከባሕሩ ደቡባዊ ወሽመጥ ይነሳል። 3 ከዚያም በስተ ደቡብ እስከ አቅራቢም አቀበት+ ድረስ ይዘልቅና ወደ ጺን ይሻገራል፤ በመቀጠልም ከደቡብ ወደ ቃዴስበርኔ+ ይወጣና በኤስሮን በኩል አልፎ ወደ አዳር ከሄደ በኋላ ወደ ቃርቃ ይዞራል። 4 ከዚያም ወደ አጽሞን+ ይዘልቅና ወደ ግብፅ ሸለቆ*+ ይቀጥላል፤ ወሰኑም ባሕሩ* ጋ ሲደርስ ያበቃል። ደቡባዊ ወሰናቸው ይህ ነበር።

5 ምሥራቃዊው ወሰን ደግሞ ጨው ባሕር* ሲሆን ይህም እስከ ዮርዳኖስ ጫፍ ይደርሳል፤ በስተ ሰሜን በኩል ያለው ወሰን በዮርዳኖስ ጫፍ ላይ የሚገኘው የባሕሩ ወሽመጥ ነበር።+ 6 ከዚያም ወሰኑ ወደ ቤትሆግላ+ ይወጣና ከቤትአረባ+ በስተ ሰሜን በኩል ያልፋል፤ የሮቤል ልጅ የቦሃን ድንጋይ+ እስካለበትም ድረስ ይዘልቃል። 7 በመቀጠልም በአኮር ሸለቆ*+ ወደምትገኘው ወደ ደቢር ይወጣና በስተ ሰሜን ወደ ጊልጋል+ ይኸውም ከሸለቆው በስተ ደቡብ ከሚገኘው ከአዱሚም አቀበት ፊት ለፊት ወዳለው ቦታ ይታጠፋል፤ ከዚያም ወደ ኤንሼሜሽ+ ውኃዎች ይሄድና ኤንሮጌል+ ላይ ያበቃል። 8 ወሰኑ እስከ ሂኖም ልጅ ሸለቆ+ ይኸውም በስተ ደቡብ እስከሚገኘው እስከ ኢያቡሳውያን+ ሸንተረር ማለትም እስከ ኢየሩሳሌም+ ድረስ ይወጣል፤ በተጨማሪም በረፋይም ሸለቆ* ሰሜናዊ ጫፍ ላይ እስከሚገኘውና ከሂኖም ሸለቆ ምዕራባዊ ክፍል ትይዩ እስካለው ተራራ አናት ድረስ ይዘልቃል። 9 ከዚያም ከተራራው አናት ተነስቶ እስከ ነፍቶአ+ የውኃ ምንጮች ድረስ ይሄዳል፤ እንዲሁም በኤፍሮን ተራራ ላይ እስካሉት ከተሞች ይዘልቃል፤ በመቀጠልም እስከ ባዓላ ማለትም እስከ ቂርያትየአሪም+ ይሄዳል። 10 ወሰኑ ከባዓላ ተነስቶ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ በመዞር ወደ ሴይር ተራራ ይሄዳል፤ ከዚያም በስተ ሰሜን ወደ የአሪም ተራራ ሸንተረር ማለትም ወደ ከሳሎን ያልፋል፤ በመቀጠልም ወደ ቤትሼሜሽ+ በመውረድ ወደ ቲምና+ ይዘልቃል። 11 ወደ ሰሜን አቅጣጫ ወደ ኤቅሮን+ ሸንተረር ከወጣም በኋላ ወደ ሺከሮን ይሄዳል፤ ከዚያም ባዓላ ተራራን አልፎ ወደ ያብነኤል ይወጣል፤ ባሕሩም ጋ ሲደርስ ያበቃል።

12 ምዕራባዊው ወሰን ታላቁ ባሕርና*+ ዳርቻው ነበር። እንግዲህ የይሁዳ ዘሮች በየቤተሰባቸው ወሰናቸው ዙሪያውን ይህ ነበር።

13 ኢያሱ ይሖዋ ባዘዘው መሠረት ለየፎኒ ልጅ ለካሌብ+ በይሁዳ ዘሮች መካከል የምትገኘውን ኬብሮን+ የተባለችውን ቂርያትአርባን ድርሻ አድርጎ ሰጠው (አርባ የኤናቅ አባት ነበር)። 14 በመሆኑም ካሌብ የኤናቅ+ ዘሮች የሆኑትን ሦስቱን የኤናቅ ልጆች ማለትም ሸሻይን፣ አሂማንን እና ታልማይን+ ከዚያ አባረራቸው። 15 ከዚያ ተነስቶም በደቢር ነዋሪዎች ላይ ዘመተ።+ (ደቢር ቀደም ሲል ቂርያትሰፈር ትባል ነበር።) 16 ካሌብም “ቂርያትሰፈርን መትቶ በቁጥጥር ሥር ላደረጋት ሰው ሴት ልጄን አክሳን እድርለታለሁ” አለ። 17 የካሌብ ወንድም የሆነው የቀናዝ+ ልጅ ኦትኒኤልም+ ከተማዋን በቁጥጥር ሥር አደረጋት። ስለሆነም ካሌብ ሴት ልጁን አክሳን+ ዳረለት። 18 እሷም ወደ ባሏ ቤት እየሄደች ሳለ ባሏን ከአባቷ መሬት እንዲጠይቅ ወተወተችው። ከዚያም ከአህያዋ ላይ ወረደች።* በዚህ ጊዜ ካሌብ “ምን ፈለግሽ?” ሲል ጠየቃት።+ 19 እሷም “የሰጠኸኝ በስተ ደቡብ* ያለ ቁራሽ መሬት ስለሆነ እባክህ ባርከኝ፤ ጉሎትማይምንም* ስጠኝ” አለችው። ስለዚህ ላይኛውን ጉሎት እና ታችኛውን ጉሎት ሰጣት።

20 የይሁዳ ነገድ በየቤተሰባቸው የተሰጣቸው ርስት ይህ ነበር።

21 በኤዶም+ ወሰን በኩል ባለው የይሁዳ ነገድ ክልል ደቡባዊ ጫፍ ላይ የሚገኙት ከተሞች እነዚህ ናቸው፦ ቃብጽኤል፣ ኤዴር፣ ያጉር፣ 22 ቂና፣ ዲሞና፣ አድዓዳ፣ 23 ቃዴሽ፣ ሃጾር፣ ይትናን፣ 24 ዚፍ፣ ተሌም፣ በዓሎት፣ 25 ሃጾርሃዳታ፣ ቀሪዮትሄጽሮን ማለትም ሃጾር፣ 26 አማም፣ ሼማ፣ ሞላዳ፣+ 27 ሃጻርጋዳ፣ ሄሽሞን፣ ቤትጳሌጥ፣+ 28 ሃጻርሹአል፣ ቤርሳቤህ፣+ ቢዝዮትያ፣ 29 ባዓላ፣ ኢዪም፣ ኤጼም፣ 30 ኤልቶላድ፣ ከሲል፣ ሆርማ፣+ 31 ጺቅላግ፣+ ማድማና፣ ሳንሳና፣ 32 ለባኦት፣ ሺልሂም፣ አይን እና ሪሞን፤+ በአጠቃላይ 29 ከተሞች ከነመንደሮቻቸው ነበሩ።

33 በሸፌላ+ የነበሩት ከተሞች እነዚህ ናቸው፦ ኤሽታዖል፣ ጾራ፣+ አሽና፣ 34 ዛኖሃ፣ ኤንጋኒም፣ ታጱአ፣ ኤናም፣ 35 ያርሙት፣ አዱላም፣+ ሶኮህ፣ አዜቃ፣+ 36 ሻአራይም፣+ አዲታይም፣ ገዴራ እና ገዴሮታይም፤* በአጠቃላይ 14 ከተሞች ከነመንደሮቻቸው ነበሩ።

37 ጸናን፣ ሃዳሻ፣ ሚግዳልጋድ፣ 38 ዲልአን፣ ምጽጳ፣ ዮቅተኤል፣ 39 ለኪሶ፣+ ቦጽቃት፣ ኤግሎን፣ 40 ካቦን፣ ላህማም፣ ኪትሊሽ፣ 41 ገዴሮት፣ ቤትዳጎን፣ ናዕማ እና መቄዳ፤+ በአጠቃላይ 16 ከተሞች ከነመንደሮቻቸው ነበሩ።

42 ሊብና፣+ ኤቴር፣ አሻን፣+ 43 ይፍታህ፣ አሽና፣ ነጺብ፣ 44 ቀኢላ፣ አክዚብ እና ማሬሻህ፤ በአጠቃላይ ዘጠኝ ከተሞች ከነመንደሮቻቸው ነበሩ።

45 ኤቅሮን እንዲሁም በሥሯ* ያሉት ከተሞችና መንደሮቿ። 46 ከኤቅሮን በስተ ምዕራብ በአሽዶድ በኩል ያሉት አካባቢዎች በሙሉና መንደሮቻቸው።

47 አሽዶድ+ እንዲሁም በሥሯ* ያሉት ከተሞችና መንደሮቿ፤ ጋዛ+ እንዲሁም በሥሯ ያሉት ከተሞችና መንደሮቿ እስከ ግብፅ ሸለቆ፣ እስከ ታላቁ ባሕርና* በባሕሩ ጠረፍ እስካለው አካባቢ ድረስ።+

48 በተራራማው አካባቢ የነበሩት ከተሞች እነዚህ ናቸው፦ ሻሚር፣ ያቲር፣+ ሶኮህ፣ 49 ዳና፣ ቂርያትሳና ማለትም ደቢር፣ 50 አናብ፣ ኤሽተሞህ፣+ አኒም፣ 51 ጎሸን፣+ ሆሎን እና ጊሎ፤+ በአጠቃላይ 11 ከተሞች ከነመንደሮቻቸው ነበሩ።

52 ዓረብ፣ ዱማ፣ ኤሽዓን፣ 53  ያኒም፣ ቤትታጱአ፣ አፌቃ፣ 54 ሁምጣ፣ ቂርያትአርባ ማለትም ኬብሮን+ እና ጺኦር፤ በአጠቃላይ ዘጠኝ ከተሞች ከነመንደሮቻቸው ነበሩ።

55 ማኦን፣+ ቀርሜሎስ፣ ዚፍ፣+ ዩጣ፣ 56 ኢይዝራኤል፣ ዮቅደአም፣ ዛኖሃ፣ 57  ቄይን፣ ጊብዓ እና ቲምና፤+ በአጠቃላይ አሥር ከተሞች ከነመንደሮቻቸው ነበሩ።

58 ሃልሁል፣ ቤትጹር፣ ጌዶር፣ 59 ማአራት፣ ቤትአኖት እና ኤልተቆን፤ በአጠቃላይ ስድስት ከተሞች ከነመንደሮቻቸው ነበሩ።

60 ቂርያትበኣል ማለትም ቂርያትየአሪም+ እና ራባ፤ በአጠቃላይ ሁለት ከተሞች ከነመንደሮቻቸው ነበሩ።

61 በምድረ በዳው የነበሩት ከተሞች እነዚህ ናቸው፦ ቤትአረባ፣+ ሚዲን፣ ሰካካ፣ 62 ኒብሻን፣ የጨው ከተማ እና ኤንገዲ፤+ በአጠቃላይ ስድስት ከተሞች ከነመንደሮቻቸው ነበሩ።

63 የይሁዳ ሰዎች በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩትን+ ኢያቡሳውያንን+ ሊያባርሯቸው አልቻሉም ነበር፤+ ስለሆነም ኢያቡሳውያን እስከ ዛሬ ድረስ ከይሁዳ ሰዎች ጋር በኢየሩሳሌም ይኖራሉ።

16 ለዮሴፍ ዘሮች+ በዕጣ የተሰጣቸው ምድር+ በኢያሪኮ አጠገብ ካለው ከዮርዳኖስ አንስቶ ከኢያሪኮ በስተ ምሥራቅ እስካሉት ውኃዎች ድረስ ሲሆን ከኢያሪኮ ሽቅብ የሚወጣውን ምድረ በዳ አቋርጦ እስከ ተራራማው የቤቴል አካባቢ ድረስ ይዘልቃል።+ 2 እንዲሁም በሎዛ ከምትገኘው ከቤቴል አንስቶ በአጣሮት እስካለው የአርካውያን ወሰን ድረስ ይሄዳል፤ 3 ከዚያም በስተ ምዕራብ ወደ ያፍለጣውያን ወሰን ቁልቁል በመውረድ እስከ ታችኛው ቤትሆሮን+ ወሰንና እስከ ጌዜር+ ይደርሳል፤ ባሕሩም ጋ ሲደርስ ያበቃል።

4 ስለሆነም የዮሴፍ ዘሮች+ ምናሴና ኤፍሬም ርስታቸው የሆነውን መሬት ወሰዱ።+ 5 የኤፍሬም ዘሮች ወሰን በየቤተሰባቸው የሚከተለው ነው፦ በስተ ምሥራቅ በኩል የርስታቸው ወሰን አጣሮትዓዳር+ ሲሆን እስከ ላይኛው ቤትሆሮንም+ ይደርሳል፤ 6 ከዚያም እስከ ባሕሩ ድረስ ይዘልቃል። ወሰኑ በስተ ሰሜን ሚክመታት+ ሲሆን በስተ ምሥራቅ በኩል ዞሮ ወደ ታአናትሺሎ ይሄድና በስተ ምሥራቅ አቅጣጫ ወደ ያኖአህ ይዘልቃል። 7 ከያኖአህ ተነስቶም ወደ አጣሮትና ወደ ናዕራ ቁልቁል በመውረድ ኢያሪኮ+ ይደርስና ወደ ዮርዳኖስ ይዘልቃል። 8 ከዚያም ከታጱአ+ ተነስቶ በስተ ምዕራብ በኩል እስከ ቃና ሸለቆ በመዝለቅ ባሕሩ ጋ ሲደርስ ያበቃል።+ የኤፍሬም ነገድ በየቤተሰቡ ያገኘው ርስት ይህ ነው፤ 9 የኤፍሬም ዘሮች በምናሴ+ ርስት ውስጥም የተከለሉ ከተሞች ነበሯቸው፤ ከተሞቹ በሙሉ ከነመንደሮቻቸው የእነሱ ነበሩ።

10 ሆኖም በጌዜር+ ይኖሩ የነበሩትን ከነአናውያን አላባረሯቸውም፤ ከነአናውያንም እስከ ዛሬ ድረስ በኤፍሬም መካከል ይኖራሉ፤+ የግዳጅ ሥራ የመሥራት ግዴታም ተጥሎባቸዋል።+

17 ከዚያም ዕጣው+ ለምናሴ+ ነገድ ወጣ፤ ምክንያቱም እሱ የዮሴፍ የበኩር ልጅ ነበር።+ የጊልያድ አባት የሆነው የምናሴ የበኩር ልጅ ማኪር+ ጦረኛ ሰው ስለነበር ጊልያድን እና ባሳንን+ ወሰደ። 2 ለቀሩት የምናሴ ዘሮችም በየቤተሰባቸው ይኸውም ለአቢዔዜር+ ልጆች፣ ለሄሌቅ ልጆች፣ ለአስሪዔል ልጆች፣ ለሴኬም ልጆች፣ ለሄፌር ልጆችና ለሸሚዳ ልጆች ዕጣ ወጣ። የዮሴፍ ልጅ የምናሴ ዘሮች ወንዶቹ በየቤተሰባቸው እነዚህ ነበሩ።+ 3 ሆኖም የምናሴ ልጅ፣ የማኪር ልጅ፣ የጊልያድ ልጅ፣ የሄፌር ልጅ ሰለጰአድ+ ሴቶች እንጂ ወንዶች ልጆች አልነበሩትም፤ የሴቶች ልጆቹም ስም ማህላ፣ ኖኅ፣ ሆግላ፣ ሚልካ እና ቲርጻ ነበር። 4 እነሱም ወደ ካህኑ አልዓዛር፣+ ወደ ነዌ ልጅ ወደ ኢያሱና ወደ አለቆቹ ቀርበው “ይሖዋ በወንድሞቻችን መካከል ርስት እንዲሰጠን ሙሴን አዞት ነበር” አሏቸው።+ ስለዚህ ኢያሱ ይሖዋ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት በአባታቸው ወንድሞች መካከል ርስት ሰጣቸው።+

5 ምናሴ በዮርዳኖስ ማዶ* ከነበሩት ከጊልያድና ከባሳን በተጨማሪ አሥር ድርሻዎች ወጡለት፤+ 6 ምክንያቱም የምናሴ ሴቶች ልጆች በወንዶች ልጆቹ መካከል ርስት ተሰጥቷቸው ነበር፤ የጊልያድም ምድር የቀሩት የምናሴ ዘሮች ርስት ሆነ።

7 የምናሴ ወሰን ከአሴር አንስቶ ከሴኬም+ ፊት ለፊት እስከምትገኘው እስከ ሚክመታት+ ድረስ ነበር፤ ወሰኑ በስተ ደቡብ* በኩል የኤንታጱአ ነዋሪዎች እስከሚገኙበት ምድር ይዘልቃል። 8 የታጱአ+ ምድር የምናሴ ሆነች፤ በምናሴ ወሰን ላይ የምትገኘው የታጱአ ከተማ ግን የኤፍሬም ዘሮች ነበረች። 9 ወሰኑ ወደ ቃና ሸለቆ ይኸውም ከሸለቆው በስተ ደቡብ ቁልቁል ይወርዳል። በምናሴ ከተሞች መካከል የሚገኙ የኤፍሬም ከተሞች የነበሩ ሲሆን+ የምናሴ ወሰን በሸለቆው ሰሜናዊ ክፍል አድርጎ ባሕሩ ጋ ሲደርስ ያበቃል።+ 10 በስተ ደቡብ በኩል ያለው የኤፍሬም፣ በስተ ሰሜን በኩል ያለው ደግሞ የምናሴ ነበር፤ ባሕሩም የእሱ ወሰን ነበር፤+ እነሱም* በስተ ሰሜን እስከ አሴር፣ በስተ ምሥራቅ ደግሞ እስከ ይሳኮር ይደርሱ ነበር።

11 በይሳኮርና በአሴር ግዛቶች ውስጥ ለምናሴ የተሰጡት የሚከተሉት ናቸው፦ ቤትሼንና በሥሯ* ያሉት ከተሞች፣ ይብለአምና+ በሥሯ ያሉት ከተሞች፣ የዶር+ ነዋሪዎችና በሥሯ ያሉት ከተሞች እንዲሁም የኤንዶር+ ነዋሪዎችና በሥሯ ያሉት ከተሞች፣ የታአናክ+ ነዋሪዎችና በሥሯ ያሉት ከተሞች፣ የመጊዶ ነዋሪዎችና በሥሯ ያሉት ከተሞች፣ ሦስቱ ኮረብታማ አካባቢዎች።

12 ሆኖም የምናሴ ዘሮች እነዚህን ከተሞች መውረስ አልቻሉም፤ ከነአናውያን ይህን ምድር ላለመልቀቅ ቆርጠው ነበር።+ 13 እስራኤላውያን እያየሉ በሄዱ ጊዜ ከነአናውያንን የግዳጅ ሥራ እንዲሠሩ አስገደዷቸው፤+ ይሁን እንጂ ሙሉ በሙሉ አላባረሯቸውም።*+

14 የዮሴፍ ዘሮችም ኢያሱን “አንድ ዕጣና+ አንድ ድርሻ ብቻ ርስት አድርገህ የሰጠኸን ለምንድን ነው?* ይሖዋ እስካሁን ድረስ ስለባረከን የሕዝባችን ቁጥር በዝቷል”+ አሉት። 15 ኢያሱም “ቁጥራችሁ ይህን ያህል ብዙ ከሆነ የኤፍሬም ተራራማ አካባቢ+ በጣም ስለሚጠብባችሁ ወደ ጫካው በመውጣት በፈሪዛውያንና+ በረፋይም+ ምድር የሚገኘውን አካባቢ ለራሳችሁ መንጥሩ” አላቸው። 16 ከዚያም የዮሴፍ ዘሮች እንዲህ አሉት፦ “ተራራማው አካባቢ አይበቃንም፤ ደግሞም በሸለቆው* ምድር ማለትም በቤትሼን+ እና በሥሯ* በሚገኙት ከተሞች እንዲሁም በኢይዝራኤል ሸለቆ+ ውስጥ* የሚኖሩት ከነአናውያን በሙሉ የብረት ማጭድ የተገጠመላቸው የጦር ሠረገሎች* አሏቸው።”+ 17 በመሆኑም ኢያሱ ለዮሴፍ ቤት ይኸውም ለኤፍሬምና ለምናሴ እንዲህ አለ፦ “እናንተ ብዙ ሕዝብ ናችሁ፤ ታላቅ ኃይልም አላችሁ። ድርሻችሁ አንድ ዕጣ ብቻ አይሆንም፤+ 18 ከዚህ ይልቅ ተራራማው አካባቢ የእናንተ ይሆናል።+ አካባቢው ጫካ ቢሆንም ትመነጥሩታላችሁ፤ የግዛታችሁም ወሰን ይሆናል። ምክንያቱም ከነአናውያን የብረት ማጭድ የተገጠመላቸው የጦር ሠረገሎች* ያሏቸውና ብርቱዎች ቢሆኑም እንኳ ከምድሩ ታባርሯቸዋላችሁ።”+

18 ከዚያም መላው የእስራኤላውያን ማኅበረሰብ በሴሎ+ ተሰበሰበ፤ በዚህ ጊዜ ምድሪቱ በፊታቸው ተገዝታላቸው+ ስለነበር የመገናኛ ድንኳኑን በዚያ ተከሉ።+ 2 ይሁንና ከእስራኤላውያን መካከል ገና ርስት ያልተሰጣቸው ሰባት ነገዶች ነበሩ። 3 በመሆኑም ኢያሱ እስራኤላውያንን እንዲህ አላቸው፦ “የአባቶቻችሁ አምላክ ይሖዋ የሰጣችሁን ምድር ገብታችሁ ለመውረስ ችላ የምትሉት እስከ መቼ ነው?+ 4 ከእያንዳንዱ ነገድ ሦስት ሦስት ወንዶችን ስጡኝ፤ እኔም እልካቸዋለሁ፤ እነሱም ሄደው ምድሪቱን ተዘዋውረው ከተመለከቱ በኋላ በሚወርሱት ድርሻ መሠረት ይሸነሽኗታል። ከዚያም ተመልሰው ወደ እኔ ይመጣሉ። 5 ምድሪቱንም ሰባት ቦታ ይከፋፈሏታል።+ ይሁዳ በስተ ደቡብ ያለውን ክልሉን ይዞ ይኖራል፤+ የዮሴፍ ቤት ደግሞ በስተ ሰሜን ያለውን ክልሉን ይዞ ይኖራል።+ 6 እናንተ ግን ምድሪቱን ሰባት ቦታ ትሸነሽኗታላችሁ፤ ከዚያም የሸነሸናችሁትን ይዛችሁ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም እዚህ በአምላካችን በይሖዋ ፊት ዕጣ አወጣላችኋለሁ።+ 7 ሌዋውያኑ ግን ለይሖዋ የሚያቀርቡት የክህነት አገልግሎት ውርሻቸው ስለሆነ+ በመካከላችሁ ድርሻ አይሰጣቸውም፤+ ጋድ፣ ሮቤልና የምናሴ ነገድ እኩሌታም+ ቢሆኑ የይሖዋ አገልጋይ ሙሴ በሰጣቸው መሠረት ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ርስታቸውን አስቀድመው ወስደዋል።”

8 ሰዎቹም ለመሄድ ተነሱ፤ ኢያሱም ምድሪቱን ለመሸንሸን የሚሄዱትን ሰዎች “ሂዱና ምድሪቱን ተዘዋውራችሁ በማየት ሸንሽኗት፤ ከዚያም ተመልሳችሁ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም እዚሁ በሴሎ በይሖዋ ፊት ዕጣ አወጣላችኋለሁ”+ ሲል አዘዛቸው። 9 ሰዎቹም ሄደው በምድሪቱ ተዘዋወሩ፤ ከዚያም በከተማ በከተማ ሰባት ቦታ ሸንሽነው በመጽሐፍ አሰፈሩት። በኋላም በሴሎ ባለው ሰፈር ወደሚገኘው ወደ ኢያሱ ተመልሰው መጡ። 10 ኢያሱም በሴሎ በይሖዋ ፊት ዕጣ አወጣላቸው።+ በዚያም ኢያሱ ምድሪቱን ለእስራኤላውያን በየድርሻቸው አከፋፈላቸው።+

11 የመጀመሪያውም ዕጣ ለቢንያም ነገድ በየቤተሰቡ ወጣ፤ በዕጣ የደረሳቸውም ክልል በይሁዳ ሰዎችና+ በዮሴፍ ሰዎች+ መካከል የሚገኘው ነበር። 12 በሰሜን በኩል ያለው ወሰናቸው ከዮርዳኖስ ተነስቶ በስተ ሰሜን ወዳለው የኢያሪኮ+ ሸንተረር ይወጣና በስተ ምዕራብ ወደ ተራራው ያቀናል፤ ከዚያም ወደ ቤትአዌን+ ምድረ በዳ ይዘልቃል። 13 ከዚያ ደግሞ ወሰኑ ቤቴል+ ወደምትባለው ወደ ሎዛ ማለትም ወደ ሎዛ ደቡባዊ ሸንተረር ያቀናል፤ በመቀጠልም ከታችኛው ቤትሆሮን+ በስተ ደቡብ በሚገኘው ተራራ ላይ አድርጎ ወደ አጣሮትዓዳር+ ይወርዳል። 14 በስተ ምዕራብ ያለው ወሰንም በስተ ደቡብ በኩል ከቤትሆሮን ትይዩ ከሆነው ተራራ በመነሳት ወደ ደቡብ ይታጠፋል፤ ከዚያም የይሁዳ ከተማ የሆነችው ቂርያትበአል ይኸውም ቂርያትየአሪም + ጋ ሲደርስ ያበቃል። ይህ ምዕራባዊው ወሰን ነው።

15 በስተ ደቡብ ያለው ወሰን ደግሞ ከቂርያትየአሪም ጫፍ ተነስቶ ወደ ምዕራብ ይዘልቃል፤ ከዚያም ወደ ነፍቶአ+ የውኃ ምንጭ ይወጣል። 16 ከዚያም ከሂኖም ልጅ ሸለቆ+ ፊት ለፊት ወደሚገኘውና በረፋይም ሸለቆ*+ ሰሜናዊ ጫፍ ወዳለው ተራራ ግርጌ ይወርዳል፤ በመቀጠልም ወደ ሂኖም ሸለቆ ይኸውም በስተ ደቡብ ወደሚገኘው ወደ ኢያቡሳውያን+ ሸንተረር ይወርድና እስከ ኤንሮጌል+ ይዘልቃል። 17 ከዚያም ወደ ሰሜን በማቅናት ወደ ኤንሼሜሽ ያልፍና ከአዱሚም አቀበት+ ፊት ለፊት እስከምትገኘው እስከ ገሊሎት ይደርሳል፤ በመቀጠልም የሮቤል ልጅ የቦሃን+ ድንጋይ+ እስካለበት ድረስ ይወርዳል። 18 ወሰኑ አረባ ፊት ለፊት ወዳለው ሰሜናዊ ሸንተረር ይሄድና ቁልቁል ወደ አረባ ይወርዳል። 19 ከዚያም ወደ ቤትሆግላ+ ሰሜናዊ ሸንተረር ይዘልቅና በዮርዳኖስ ደቡባዊ ጫፍ፣ የጨው ባሕር*+ ሰሜናዊ ዳርቻ ላይ ሲደርስ ያበቃል። ደቡባዊው ወሰን ይህ ነበር። 20 በስተ ምሥራቅ በኩል ወሰኑ ዮርዳኖስ ነበር። የቢንያም ዘሮች በየቤተሰባቸው ያገኙት ርስት ወሰን ዙሪያውን ይህ ነበር።

21 የቢንያም ነገድ በየቤተሰቡ ያገኛቸው ከተሞች እነዚህ ናቸው፦ ኢያሪኮ፣ ቤትሆግላ፣ ኤሜቀጺጽ፣ 22 ቤትአረባ፣+ ጸማራይም፣ ቤቴል፣+ 23 አዊም፣ ጳራ፣ ኦፍራ፣ 24 ከፋርአሞናይ፣ ኦፍኒ እና ጌባ፤+ በአጠቃላይ 12 ከተሞች ከነመንደሮቻቸው ነበሩ።

25 ገባኦን፣+ ራማ፣ በኤሮት፣ 26 ምጽጳ፣ ከፊራ፣ ሞጻ፣ 27 ራቄም፣ ይርጰኤል፣ ታራላ፣ 28 ጸላህ፣+ ኤሌፍ፣ ኢያቡስ ማለትም ኢየሩሳሌም፣+ ጊብዓ+ እና ቂርያት፤ በአጠቃላይ 14 ከተሞች ከነመንደሮቻቸው ነበሩ።

የቢንያም ዘሮች በየቤተሰባቸው ያገኙት ርስት ይህ ነበር።

19 ከዚያም ሁለተኛው ዕጣ+ ለስምዖን ይኸውም ለስምዖን+ ነገድ በየቤተሰቡ ወጣ። ርስታቸውም በይሁዳ ርስት መካከል ነበር።+ 2 ርስታቸውም የሚከተለው ነበር፦ ቤርሳቤህ+ ከሳባ ጋር፣ ሞላዳ፣+ 3 ሃጻርሹአል፣+ ባላህ፣ ኤጼም፣+ 4 ኤልቶላድ፣+ በቱል፣ ሆርማ፣ 5 ጺቅላግ፣+ ቤትማርካቦት፣ ሃጻርሱሳ፣ 6 ቤትለባኦት+ እና ሻሩሄን፤ በአጠቃላይ 13 ከተሞች ከነመንደሮቻቸው፤ 7 አይን፣ ሪሞን፣ ኤቴር እና አሻን፤+ በአጠቃላይ አራት ከተሞች ከነመንደሮቻቸው፤ 8 እንዲሁም በእነዚህ ከተሞች ዙሪያ የነበሩትን መንደሮች በሙሉ እስከ ባዓላትበኤር ይኸውም በስተ ደቡብ እስከምትገኘው እስከ ራማ ድረስ ያሉትን አካባቢዎች ይጨምራል። የስምዖን ነገድ ርስት በየቤተሰቡ ይህ ነበር። 9 ለስምዖን ዘሮች ርስት የተሰጠው ከይሁዳ ልጆች ድርሻ ላይ ተወስዶ ነበር፤ ምክንያቱም የይሁዳ ዘሮች ድርሻቸው በጣም በዝቶባቸው ነበር። በመሆኑም የስምዖን ልጆች ርስት ያገኙት በእነሱ ርስት መካከል ነው።+

10 በመቀጠል ሦስተኛው ዕጣ+ ለዛብሎን+ ዘሮች በየቤተሰባቸው ወጣ፤ የርስታቸውም ወሰን እስከ ሳሪድ ድረስ ይዘልቃል። 11 በስተ ምዕራብም ወደ ማረአል ይወጣና እስከ ዳባሼት ይደርሳል፤ ከዚያም በዮቅነአም ፊት ለፊት እስካለው ሸለቆ* ድረስ ይሄዳል። 12 ከሳሪድ ተነስቶ በስተ ምሥራቅ ወደ ፀሐይ መውጫ አቅጣጫ እስከ ኪስሎትታቦር ድንበር ድረስ ይሄድና ወደ ዳብራት+ ከዚያም ወደ ያፊአ ይወጣል። 13 ከዚያም ተነስቶ በስተ ምሥራቅ በፀሐይ መውጫ አቅጣጫ ወደ ጋትሔፌር፣+ ወደ ኢትቃጺን ከሄደ በኋላ ወደ ሪሞን ወጥቶ እስከ ኒአ ይዘልቃል። 14 በመቀጠልም በስተ ሰሜን ዞሮት ወደ ሃናቶን ያመራል፤ ወሰኑ የሚያበቃው ይፍታህኤል ሸለቆ፣ 15 ቃጣት፣ ናሃላል፣ ሺምሮን፣+ ይዳላ እና ቤተልሔም + ጋ ሲደርስ ነው፤ በአጠቃላይ 12 ከተሞች ከነመንደሮቻቸው ነበሩ። 16 የዛብሎን ዘሮች ርስት በየቤተሰባቸው ይህ ነበር።+ ከተሞቹና መንደሮቻቸው እነዚህ ነበሩ።

17 አራተኛው ዕጣ+ የወጣው ለይሳኮር+ ይኸውም ለይሳኮር ዘሮች በየቤተሰባቸው ነበር። 18 ወሰናቸውም እስከ ኢይዝራኤል፣+ ከሱሎት፣ ሹነም፣+ 19 ሃፋራይም፣ ሺኦን፣ አናሃራት፣ 20 ራቢት፣ ቂሾን፣ ኤቤጽ፣ 21 ረመት፣ ኤንጋኒም፣+ ኤንሃዳ እና ቤትጳጼጽ ድረስ ነበር። 22 ከዚያም እስከ ታቦር፣+ ሻሃጺማ እና ቤትሼሜሽ ይዘልቅ ነበር፤ ወሰናቸውም ዮርዳኖስ ጋ ሲደርስ ያበቃል፤ በአጠቃላይ 16 ከተሞች ከነመንደሮቻቸው ነበሩ። 23 የይሳኮር ነገድ ርስት በየቤተሰቡ ይህ ነበር፤+ ከተሞቹና መንደሮቻቸው እነዚህ ነበሩ።

24 ከዚያም አምስተኛው ዕጣ+ ለአሴር+ ነገድ በየቤተሰቡ ወጣ። 25 ወሰናቸውም ሄልቃት፣+ ሃሊ፣ ቤጤን፣ አክሻፍ፣ 26 አላሜሌክ፣ አምዓድ እና ሚሽአል ነበር። በስተ ምዕራብም እስከ ቀርሜሎስና+ እስከ ሺሆርሊብናት ይደርስ ነበር፤ 27 ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ ወደ ቤትዳጎን ተመልሶ እስከ ዛብሎን እንዲሁም በስተ ሰሜን እስከ ይፍታህኤል ሸለቆ ይደርስና እስከ ቤትኤሜቅ እንዲሁም እስከ ነኢኤል ይዘልቃል፤ በመቀጠልም በስተ ግራ በኩል ወደ ካቡል ይሄዳል፤ 28 ከዚያም ወደ ኤብሮን፣ ሬሆብ፣ ሃሞን እና ቃና ሄዶ እስከ ታላቋ ሲዶና+ ድረስ ይደርሳል። 29 ወሰኑ ወደ ራማ ተመልሶ እስከተመሸገችው ከተማ እስከ ጢሮስ+ ይዘልቃል። ከዚያም ወደ ሆሳ ይመለስና በአክዚብ ክልል የሚገኘው ባሕር፣ 30 ዑማ፣ አፌቅ+ እና ሬሆብ+ ጋ ሲደርስ ያበቃል፤ በአጠቃላይ 22 ከተሞች ከነመንደሮቻቸው ነበሩ። 31 የአሴር ነገድ ርስት በየቤተሰቡ ይህ ነው።+ ከተሞቹና መንደሮቻቸው እነዚህ ነበሩ።

32 ስድስተኛው ዕጣ+ የወጣው ለንፍታሌም ዘሮች ይኸውም ለንፍታሌም ዘሮች በየቤተሰባቸው ነበር። 33 ወሰናቸውም ከሄሌፍ፣ በጻናኒም ከሚገኘው ትልቅ ዛፍ፣+ ከአዳሚኔቄብ እና ከያብነኤል አንስቶ እስከ ላቁም ይደርሳል፤ ዮርዳኖስ ጋ ሲደርስም ያበቃል። 34 ወሰኑ በስተ ምዕራብ ወደ አዝኖትታቦር ይመለሳል፤ ከዚያም በመነሳት ወደ ሁቆቃ ይሄድና በስተ ደቡብ እስከ ዛብሎን፣ በስተ ምዕራብ እስከ አሴር፣ በስተ ምሥራቅ ደግሞ በዮርዳኖስ እስከሚገኘው እስከ ይሁዳ ይደርሳል። 35 የተመሸጉት ከተሞች እነዚህ ነበሩ፦ ጺዲም፣ ጸር፣ ሃማት፣+ ራቃት፣ ኪኔሬት፣ 36 አዳማ፣ ራማ፣ ሃጾር፣+ 37 ቃዴሽ፣+ ኤድራይ፣ ኤንሃጾር፣ 38 ይርኦን፣ ሚግዳልኤል፣ ሆሬም፣ ቤትአናት እና ቤትሼሜሽ፤+ በአጠቃላይ 19 ከተሞች ከነመንደሮቻቸው ነበሩ። 39 የንፍታሌም ነገድ ርስት በየቤተሰቡ ይህ ነበር፤+ ከተሞቹና መንደሮቻቸው እነዚህ ነበሩ።

40 ሰባተኛው ዕጣ+ ለዳን+ ነገድ በየቤተሰቡ ወጣ። 41 የርስታቸውም ወሰን ጾራ፣+ ኤሽታዖል፣ ኢርሻሜሽ፣ 42 ሻአላቢን፣+ አይሎን፣+ ይትላ፣ 43 ኤሎን፣ ቲምና፣+ ኤቅሮን፣+ 44 ኤልተቄ፣ ጊበቶን፣+ ባዓላት፣ 45 የሁድ፣ ብኔበራቅ፣ ጋትሪሞን፣+ 46 መሃይያርቆን፣ ራቆን እና ከኢዮጴ+ ትይዩ ያለው ድንበር ነበር። 47 የዳን ዘሮች ርስታቸው በጣም ጠቧቸው ነበር።+ በመሆኑም ወጥተው ለሸምን+ ወጉ፤ ከተማዋንም በመቆጣጠር በሰይፍ መቷት። ከዚያም ከተማዋን ርስት አድርገው በመያዝ በዚያ መኖር ጀመሩ፤ ለሸምንም በአባታቸው በዳን ስም ዳን ብለው ጠሯት።+ 48 የዳን ነገድ ርስት በየቤተሰቡ ይህ ነበር። ከተሞቹና መንደሮቻቸው እነዚህ ነበሩ።

49 በዚህ መንገድ ምድሪቱን በየክልሉ በርስትነት አከፋፍለው ጨረሱ። ከዚያም እስራኤላውያን ለነዌ ልጅ ለኢያሱ በመካከላቸው ርስት ሰጡት። 50 እነሱም የጠየቀውን ከተማ ማለትም በኤፍሬም ተራራማ አካባቢ የምትገኘውን ቲምናትሰራን+ በይሖዋ ትእዛዝ መሠረት ሰጡት፤ እሱም ከተማዋን ገንብቶ በዚያ ተቀመጠ።

51 ካህኑ አልዓዛር፣ የነዌ ልጅ ኢያሱና የእስራኤል ነገዶች የአባቶች ቤት መሪዎች በሴሎ+ በይሖዋ ፊት በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ላይ+ ርስት አድርገው በዕጣ ያከፋፈሉት ድርሻ ይህ ነበር።+ በዚህ ሁኔታ ምድሪቱን አከፋፍለው ጨረሱ።

20 ከዚያም ይሖዋ ኢያሱን እንዲህ አለው፦ 2 “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፦ ‘በሙሴ አማካኝነት በነገርኳችሁ መሠረት ለራሳችሁ የመማጸኛ ከተሞችን+ ምረጡ፤ 3 ሳያስበው ወይም በድንገት* ሰው የገደለ* ግለሰብ ወደነዚህ ከተሞች መሸሽ ይችላል። እነሱም ከደም ተበቃዩ+ መሸሸጊያ ሆነው ያገለግሏችኋል። 4 ገዳዩ ከእነዚህ ከተሞች ወደ አንዱ በመሸሽ+ በከተማዋ በር ላይ ቆሞ+ ለከተማዋ ሽማግሌዎች ጉዳዩን ይናገር። እነሱም ወደ ከተማቸው አስገብተው መኖሪያ ይስጡት፤ እሱም አብሯቸው ይኖራል። 5 ደም ተበቃዩ ቢያሳድደው ሰዎቹ ነፍሰ ገዳዩን አሳልፈው አይስጡት፤ ምክንያቱም ግለሰቡ ባልንጀራውን የገደለው የቆየ ጥላቻ ኖሮት ሳይሆን በድንገት* ነው።+ 6 ስለሆነም በማኅበረሰቡ ፊት ለፍርድ እስኪቀርብ+ ድረስ በከተማዋ ውስጥ ይኑር፤ በዚያ ጊዜ የሚያገለግለው ሊቀ ካህናት እስኪሞት ድረስም ከዚያ መውጣት የለበትም።+ ከዚያ በኋላ ገዳዩ ሸሽቶ ወደወጣባት ከተማ መመለስ እንዲሁም ወደ ከተማውና ወደ ቤቱ መግባት ይችላል።’”+

7 በመሆኑም በንፍታሌም ተራራማ አካባቢ በገሊላ የምትገኘውን ቃዴሽን፣+ በኤፍሬም ተራራማ አካባቢ የምትገኘውን ሴኬምንና+ በይሁዳ ተራራማ አካባቢ የምትገኘውን ቂርያትአርባን+ ማለትም ኬብሮንን ለዚህ ዓላማ ቀደሱ።* 8 ከኢያሪኮ በስተ ምሥራቅ ባለው የዮርዳኖስ ክልል ደግሞ ከሮቤል ነገድ ርስት በአምባው ላይ በሚገኘው ምድረ በዳ ላይ ያለችውን ቤጼርን፣+ ከጋድ ነገድ ርስት በጊልያድ የምትገኘውን ራሞትን+ እንዲሁም ከምናሴ ነገድ ርስት በባሳን የምትገኘውን ጎላንን+ መረጡ።+

9 ሳያስበው ሰው* የገደለ ማንኛውም ግለሰብ በማኅበረሰቡ ፊት ለፍርድ ከመቅረቡ በፊት ደም ተበቃዩ አግኝቶ እንዳይገድለው ሸሽቶ እንዲሸሸግባቸው+ ለእስራኤላውያን በሙሉ ወይም በመካከላቸው ለሚኖር የባዕድ አገር ሰው የተለዩት ከተሞች እነዚህ ናቸው።+

21 የሌዋውያን አባቶች ቤቶች መሪዎች ወደ ካህኑ ወደ አልዓዛር፣+ ወደ ነዌ ልጅ ወደ ኢያሱና ወደ እስራኤል ነገዶች አባቶች ቤቶች መሪዎች ቀርበው 2 በከነአን ምድር በሴሎ+ እንዲህ አሏቸው፦ “ይሖዋ የምንኖርባቸው ከተሞች ለከብቶቻችን ከሚሆኑት የግጦሽ መሬቶቻቸው ጋር እንዲሰጡን በሙሴ በኩል አዝዞ ነበር።”+ 3 በመሆኑም እስራኤላውያን ይሖዋ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ከራሳቸው ርስት ላይ እነዚህን ከተሞችና የግጦሽ መሬቶቻቸውን ለሌዋውያኑ ሰጡ።+

4 ከዚያም ዕጣው ለቀአታውያን ቤተሰቦች+ ወጣ፤ የካህኑ የአሮን ዘሮች የሆኑት ሌዋውያንም ከይሁዳ ነገድ፣+ ከስምዖን ነገድና+ ከቢንያም ነገድ+ ላይ 13 ከተሞች በዕጣ ተሰጧቸው።

5 ለቀሩት ቀአታውያንም ከኤፍሬም ነገድ፣+ ከዳን ነገድና ከምናሴ ነገድ+ እኩሌታ ቤተሰቦች ላይ አሥር ከተሞች በዕጣ ተሰጧቸው።

6 ለጌድሶናውያንም+ ከይሳኮር ነገድ፣ ከአሴር ነገድ፣ ከንፍታሌም ነገድና በባሳን+ ከሚገኘው ከምናሴ ነገድ እኩሌታ ቤተሰቦች ላይ 13 ከተሞች በዕጣ ተሰጧቸው።

7 ለሜራራውያንም+ በየቤተሰባቸው ከሮቤል ነገድ፣ ከጋድ ነገድና ከዛብሎን ነገድ+ ላይ 12 ከተሞች ተሰጧቸው።

8 በመሆኑም እስራኤላውያን ይሖዋ በሙሴ አማካኝነት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ለሌዋውያኑ እነዚህን ከተሞችና የግጦሽ መሬቶቻቸውን በዕጣ ሰጧቸው።+

9 ከይሁዳ ነገድና ከስምዖን ነገድ ላይ ደግሞ እዚህ ላይ በስም የተጠቀሱትን እነዚህን ከተሞች ሰጧቸው፤+ 10 እነዚህም ከሌዋውያን መካከል የቀአታውያን ቤተሰብ ለሆኑት ለአሮን ልጆች ተሰጡ፤ ምክንያቱም የመጀመሪያው ዕጣ የወጣው ለእነሱ ነበር። 11 እነሱም በይሁዳ ተራራማ አካባቢ የምትገኘውን ቂርያትአርባን+ (አርባ የኤናቅ አባት ነበር) ይኸውም ኬብሮንን+ እና በዙሪያዋ ያለውን የግጦሽ መሬት ሰጧቸው። 12 ይሁንና የከተማዋን እርሻና መንደሮቿን ለየፎኒ ልጅ ለካሌብ ርስት አድርገው ሰጡት።+

13 ለካህኑ ለአሮን ልጆችም ነፍስ ላጠፋ ሰው የመማጸኛ ከተማ+ የሆነችውን ኬብሮንን+ ከነግጦሽ መሬቷ፣ ሊብናን+ ከነግጦሽ መሬቷ፣ 14 ያቲርን+ ከነግጦሽ መሬቷ፣ ኤሽተሞዓን+ ከነግጦሽ መሬቷ፣ 15 ሆሎንን+ ከነግጦሽ መሬቷ፣ ደቢርን+ ከነግጦሽ መሬቷ፣ 16 አይንን+ ከነግጦሽ መሬቷ፣ ዩጣን+ ከነግጦሽ መሬቷ እንዲሁም ቤትሼሜሽን ከነግጦሽ መሬቷ ሰጡ፤ ከእነዚህ ሁለት ነገዶች ላይ ዘጠኝ ከተሞችን ሰጡ።

17 ከቢንያም ነገድ ገባኦንን+ ከነግጦሽ መሬቷ፣ ጌባን ከነግጦሽ መሬቷ፣+ 18 አናቶትን+ ከነግጦሽ መሬቷ እንዲሁም አልሞንን ከነግጦሽ መሬቷ ይኸውም አራት ከተሞችን ሰጧቸው።

19 ለካህናቱ ለአሮን ዘሮች የተሰጡት ከተሞች በአጠቃላይ 13 ከተሞች ከነግጦሽ መሬቶቻቸው ነበሩ።+

20 ከሌዋውያን መካከል ለሆኑት ለቀሩት የቀአታውያን ቤተሰቦች ደግሞ ከኤፍሬም ነገድ ርስት ላይ ከተሞች በዕጣ ተሰጧቸው። 21 ነፍስ ላጠፋ ሰው የመማጸኛ ከተማ የሆነችውን+ በኤፍሬም ተራራማ አካባቢ የምትገኘውን ሴኬምን+ ከነግጦሽ መሬቷ፣ ጌዜርን+ ከነግጦሽ መሬቷ፣ 22 ቂብጻይምን ከነግጦሽ መሬቷ እንዲሁም ቤትሆሮንን+ ከነግጦሽ መሬቷ ይኸውም አራት ከተሞችን ሰጧቸው።

23 ከዳን ነገድ ላይ ኤልተቄን ከነግጦሽ መሬቷ፣ ጊበቶንን ከነግጦሽ መሬቷ፣ 24 አይሎንን+ ከነግጦሽ መሬቷ እንዲሁም ጋትሪሞንን ከነግጦሽ መሬቷ ይኸውም አራት ከተሞችን ሰጧቸው።

25 ከምናሴ ነገድ እኩሌታ ላይ ታአናክን+ ከነግጦሽ መሬቷ እንዲሁም ጋትሪሞንን ከነግጦሽ መሬቷ ይኸውም ሁለት ከተሞችን ሰጧቸው።

26 ለቀሩት የቀአታውያን ቤተሰቦች የተሰጧቸው ከተሞች ከነግጦሽ መሬቶቻቸው በአጠቃላይ አሥር ነበሩ።

27 የሌዋውያን ቤተሰቦች የሆኑት ጌድሶናውያንም+ ከምናሴ ነገድ እኩሌታ ላይ ነፍስ ላጠፋ ሰው የመማጸኛ ከተማ የሆነችውን በባሳን የምትገኘውን ጎላንን+ ከነግጦሽ መሬቷ እንዲሁም በኤሽተራን ከነግጦሽ መሬቷ ይኸውም ሁለት ከተሞችን ወሰዱ።

28 ከይሳኮር ነገድ+ ላይ ቂሾንን ከነግጦሽ መሬቷ፣ ዳብራትን+ ከነግጦሽ መሬቷ፣ 29 ያርሙትን ከነግጦሽ መሬቷ እንዲሁም ኤንጋኒምን ከነግጦሽ መሬቷ ይኸውም አራት ከተሞችን ሰጡ።

30 ከአሴር ነገድ+ ላይ ሚሽአልን ከነግጦሽ መሬቷ፣ አብዶንን ከነግጦሽ መሬቷ፣ 31 ሄልቃትን+ ከነግጦሽ መሬቷ እንዲሁም ሬሆብን+ ከነግጦሽ መሬቷ ይኸውም አራት ከተሞችን ሰጡ።

32 ከንፍታሌም ነገድ ላይ ነፍስ ላጠፋ ሰው የመማጸኛ ከተማ+ የሆነችውን በገሊላ የምትገኘውን ቃዴሽን+ ከነግጦሽ መሬቷ፣ ሃሞትዶርን ከነግጦሽ መሬቷ እንዲሁም ቃርታንን ከነግጦሽ መሬቷ ይኸውም ሦስት ከተሞችን ሰጡ።

33 የጌድሶናውያን ከተሞች በየቤተሰባቸው በአጠቃላይ 13 ከተሞች ከነግጦሽ መሬቶቻቸው ነበሩ።

34 የሜራራውያን ቤተሰቦች+ የሆኑት የቀሩት ሌዋውያን ደግሞ ከዛብሎን ነገድ+ ላይ ዮቅነአምን+ ከነግጦሽ መሬቷ፣ ቃርታን ከነግጦሽ መሬቷ፣ 35 ዲምናን ከነግጦሽ መሬቷ እንዲሁም ናሃላልን+ ከነግጦሽ መሬቷ ይኸውም አራት ከተሞችን ወሰዱ።

36 ከሮቤል ነገድ ላይ ቤጼርን+ ከነግጦሽ መሬቷ፣ ያሃጽን ከነግጦሽ መሬቷ፣+ 37 ቀደሞትን ከነግጦሽ መሬቷ እንዲሁም መፋአትን ከነግጦሽ መሬቷ ይኸውም አራት ከተሞችን ሰጡ።

38 ከጋድ ነገድ+ ላይ ደግሞ ነፍስ ላጠፋ ሰው የመማጸኛ ከተማ የሆነችውን በጊልያድ የምትገኘውን ራሞትን+ ከነግጦሽ መሬቷ፣ ማሃናይምን+ ከነግጦሽ መሬቷ፣ 39 ሃሽቦንን+ ከነግጦሽ መሬቷ እንዲሁም ያዜርን+ ከነግጦሽ መሬቷ በአጠቃላይ አራት ከተሞችን ሰጡ።

40 ከሌዋውያን ቤተሰቦች ለቀሩት ሜራራውያን በየቤተሰባቸው በዕጣ የተሰጧቸው ከተሞች በአጠቃላይ 12 ከተሞች ነበሩ።

41 በእስራኤላውያን ርስት መካከል የነበሩት የሌዋውያን ከተሞች በአጠቃላይ 48 ከተሞች ከነግጦሽ መሬቶቻቸው ነበሩ።+ 42 እነዚህ ከተሞች በሙሉ እያንዳንዳቸው በዙሪያቸው የግጦሽ መሬት ነበራቸው።

43 በመሆኑም ይሖዋ ለእስራኤላውያን፣ ለአባቶቻቸው ለመስጠት የማለላቸውን ምድር+ በሙሉ ሰጣቸው፤ እነሱም ምድሪቱን ወርሰው በዚያ መኖር ጀመሩ።+ 44 በተጨማሪም ይሖዋ ለአባቶቻቸው በማለላቸው+ በእያንዳንዱ ነገር መሠረት በዙሪያቸው ካሉት ጠላቶቻቸው ሁሉ እረፍት ሰጣቸው፤ ከጠላቶቻቸው መካከል ሊቋቋማቸው የቻለ አንድም አልነበረም።+ ይሖዋ ጠላቶቻቸውን ሁሉ በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው።+ 45 ይሖዋ ለእስራኤል ቤት ከገባው መልካም ቃል ሁሉ ሳይፈጸም የቀረ አንድም ቃል የለም፤ ሁሉም ተፈጽሟል።+

22 ከዚያም ኢያሱ ሮቤላውያንን፣ ጋዳውያንንና የምናሴን ነገድ እኩሌታ ጠርቶ 2 እንዲህ አላቸው፦ “የይሖዋ አገልጋይ ሙሴ ያዘዛችሁን ሁሉ ፈጽማችኋል፤+ እኔም ባዘዝኳችሁ ነገር ሁሉ ቃሌን ሰምታችኋል።+ 3 በእነዚህ ሁሉ ጊዜያት እስከ ዛሬ ድረስ ወንድሞቻችሁን አልተዋችሁም፤+ አምላካችሁ ይሖዋ ከሰጣችሁ ትእዛዝ ጋር በተያያዘ ግዴታችሁን ተወጥታችኋል።+ 4 እንግዲህ አሁን አምላካችሁ ይሖዋ ለወንድሞቻችሁ ቃል በገባላቸው መሠረት እረፍት ሰጥቷቸዋል።+ በመሆኑም የይሖዋ አገልጋይ ሙሴ ከዮርዳኖስ ማዶ* ርስት አድርጎ በሰጣችሁ ምድር ወደሚገኙት ድንኳኖቻችሁ መመለስ ትችላላችሁ።+ 5 ብቻ እናንተ አምላካችሁን ይሖዋን በመውደድ፣+ በመንገዶቹ ሁሉ በመሄድ፣+ ትእዛዛቱን በመጠበቅ፣+ ከእሱ ጋር በመጣበቅ+ እንዲሁም በሙሉ ልባችሁና በሙሉ ነፍሳችሁ*+ እሱን በማገልገል+ የይሖዋ አገልጋይ ሙሴ የሰጣችሁን ትእዛዝና ሕግ በጥንቃቄ ፈጽሙ።”+

6 ከዚያም ኢያሱ ባረካቸውና አሰናበታቸው፤ እነሱም ወደ ድንኳኖቻቸው ሄዱ። 7 ሙሴ ለምናሴ ነገድ እኩሌታ በባሳን ርስት ሰጥቶ ነበር፤+ ኢያሱ ደግሞ ለቀረው የነገዱ እኩሌታ ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ ከወንድሞቻቸው ጋር መሬት ሰጣቸው።+ በተጨማሪም ኢያሱ ወደ ድንኳኖቻቸው እንዲሄዱ ባሰናበታቸው ጊዜ ባረካቸው፤ 8 እንዲህም አላቸው፦ “ብዙ ሀብት፣ እጅግ ብዙ ከብት፣ ብር፣ ወርቅ፣ መዳብ፣ ብረትና እጅግ ብዙ ልብስ ይዛችሁ ወደየድንኳኖቻችሁ ተመለሱ።+ ከጠላቶቻችሁ ያገኛችሁትን ምርኮ ወስዳችሁ ከወንድሞቻችሁ ጋር ተካፈሉ።”+

9 ከዚህ በኋላ ሮቤላውያን፣ ጋዳውያንና የምናሴ ነገድ እኩሌታ በከነአን ምድር በምትገኘው በሴሎ ከነበሩት ከሌሎቹ እስራኤላውያን ተለይተው ወደ ጊልያድ ምድር+ ይኸውም ይሖዋ በሙሴ አማካኝነት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ርስት አድርገው ወደሰፈሩባት ምድር ተመለሱ።+ 10 ሮቤላውያን፣ ጋዳውያንና የምናሴ ነገድ እኩሌታ በከነአን ምድር ወዳለው የዮርዳኖስ ክልል ሲደርሱ በዮርዳኖስ አጠገብ ግዙፍ የሆነ አስደናቂ መሠዊያ ሠሩ። 11 በኋላም ሌሎቹ እስራኤላውያን “እነሆ፣ ሮቤላውያን፣ ጋዳውያንና የምናሴ ነገድ እኩሌታ የእስራኤላውያን ክልል በሆነው በከነአን ምድር ወሰን ላይ በሚገኘው የዮርዳኖስ ክልል መሠዊያ ሠርተዋል” የሚል ወሬ ሰሙ።+ 12 እስራኤላውያንም ይህን በሰሙ ጊዜ መላው የእስራኤላውያን ማኅበረሰብ እነሱን ለመውጋት በሴሎ+ ተሰበሰበ።

13 ከዚያም እስራኤላውያን የካህኑን የአልዓዛርን ልጅ ፊንሃስን+ በጊልያድ ምድር ወዳሉት ወደ ሮቤላውያን፣ ወደ ጋዳውያን እና ወደ ምናሴ ነገድ እኩሌታ ላኩት፤ 14 ከእሱም ጋር አሥር አለቆችን ይኸውም ከሁሉም የእስራኤል ነገዶች ከእያንዳንዱ የአባቶች ቤት አንድ አንድ አለቃ አብረው ላኩ፤ እነዚህም እያንዳንዳቸው ከእስራኤል የሺህ አለቆች* መካከል የሆኑ የአባቶች ቤት መሪዎች ነበሩ።+ 15 እነሱም በጊልያድ ምድር ወዳሉት ወደ ሮቤላውያን፣ ወደ ጋዳውያንና ወደ ምናሴ ነገድ እኩሌታ መጥተው እንዲህ አሏቸው፦

16 “መላው የይሖዋ ጉባኤ እንዲህ ይላል፦ ‘በእስራኤል አምላክ ላይ እንዲህ ያለ ታማኝነት የጎደለው ድርጊት የፈጸማችሁት ለምንድን ነው?+ ለራሳችሁ መሠዊያ በመሥራትና በይሖዋ ላይ በማመፅ ይኸው ዛሬ ይሖዋን ከመከተል ዞር ብላችኋል።+ 17 በፌጎር የሠራነው ስህተት አንሶ ነው? ምንም እንኳ ያኔ በይሖዋ ጉባኤ ላይ መቅሰፍት ቢወርድም ይኸው እስከ ዛሬ ድረስ ከዚህ ነገር ራሳችንን አላነጻንም።+ 18 እናንተ ደግሞ ዛሬ ይሖዋን ከመከተል ዞር ትላላችሁ! ዛሬ እናንተ በይሖዋ ላይ ብታምፁ ነገ ደግሞ እሱ በመላው የእስራኤል ማኅበረሰብ ላይ ይቆጣል።+ 19 የወረሳችኋት ምድር ረክሳ ከሆነ የይሖዋ የማደሪያ ድንኳን ወደሚገኝበት+ የይሖዋ ርስት ወደሆነው ምድር ተሻግራችሁ+ በመካከላችን ኑሩ፤ ሆኖም ከአምላካችን ከይሖዋ መሠዊያ ሌላ ለራሳችሁ መሠዊያ በመሥራት በይሖዋ ላይ አታምፁ፣ እኛንም ዓመፀኞች አታድርጉን።+ 20 የዛራ ልጅ አካን+ ለጥፋት ከተለየው ነገር ጋር በተያያዘ ታማኝነት የጎደለው ድርጊት በፈጸመ ጊዜ በመላው የእስራኤል ማኅበረሰብ ላይ ቁጣ አልወረደም?+ በሠራው ስህተት የሞተው እሱ ብቻ አልነበረም።’”+

21 በዚህ ጊዜ ሮቤላውያን፣ ጋዳውያንና የምናሴ ነገድ እኩሌታ ለእስራኤል የሺህ* አለቆች እንዲህ ሲሉ መለሱላቸው፦+ 22 “የአማልክት አምላክ፣ ይሖዋ!* የአማልክት አምላክ፣ ይሖዋ!+ እሱ ያውቃል፤ እስራኤልም ቢሆን ያውቃል። በይሖዋ ላይ ዓምፀንና ታማኝነት የጎደለው ድርጊት ፈጽመን ከሆነ ዛሬ አይታደገን። 23 ለራሳችን መሠዊያ የሠራነው ይሖዋን ከመከተል ዞር ለማለት ወይም በላዩ ላይ የሚቃጠሉ መባዎችንና የእህል መባዎችን ለማቅረብ አሊያም የኅብረት መሥዋዕቶችን ለመሠዋት ብለን ከሆነ ይሖዋ ይቅጣን።+ 24 እኛ ግን ይህን ያደረግነው ወደፊት ልጆቻችሁ ልጆቻችንን እንዲህ ማለታቸው አይቀርም ብለን ስለሰጋን ነው፦ ‘ከእስራኤል አምላክ ከይሖዋ ጋር ምን ግንኙነት አላችሁ? 25 ይሖዋ ሮቤላውያንና ጋዳውያን በሆናችሁት በእናንተና በእኛ መካከል ዮርዳኖስን ድንበር አድርጓል። እናንተ በይሖዋ ዘንድ ምንም ድርሻ የላችሁም።’ ልጆቻችሁም ልጆቻችን ይሖዋን እንዳያመልኩ* እንቅፋት ይሆኑባቸዋል።”

26 “በመሆኑም እንዲህ አልን፦ ‘እንግዲህ አንድ እርምጃ መውሰድ አለብን፤ መሠዊያ እንሥራ፤ ይህም የሚቃጠል መባ ወይም መሥዋዕት የሚቀርብበት አይደለም፤ 27 ከዚህ ይልቅ የሚቃጠሉ መባዎቻችንን፣ መሥዋዕቶቻችንንና የኅብረት መሥዋዕቶቻችንን+ ይዘን በመምጣት በይሖዋ ፊት አገልግሎት እንደምናቀርብ ለማሳየት በእኛና በእናንተ እንዲሁም ከእኛ በኋላ በሚመጡት ዘሮቻችን* መካከል ምሥክር የሚሆን ነው፤+ ስለዚህ ወደፊት ልጆቻችሁ ልጆቻችንን “እናንተ በይሖዋ ዘንድ ምንም ድርሻ የላችሁም” አይሏቸውም።’ 28 ስለዚህ እኛ እንዲህ አልን፦ ‘ወደፊት እኛንም ሆነ ዘሮቻችንን* እንዲህ ቢሉ እኛ ደግሞ “የሚቃጠል መባ ወይም መሥዋዕት የሚቀርብበት ሳይሆን በእኛና በእናንተ መካከል ምሥክር እንዲሆን አባቶቻችን የይሖዋን መሠዊያ አስመስለው የሠሩት መሠዊያ ይኸውና” እንላቸዋለን።’ 29 በማደሪያ ድንኳኑ ፊት ካለው ከአምላካችን ከይሖዋ መሠዊያ ሌላ የሚቃጠል መባ፣ የእህል መባና መሥዋዕት የሚቀርብበት መሠዊያ በመሥራት+ ዛሬ በይሖዋ ላይ ማመፅና ይሖዋን ከመከተል ወደኋላ ማለት+ በእኛ በኩል ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነው!”

30 ካህኑ ፊንሃስና ከእሱ ጋር የነበሩት የማኅበረሰቡ አለቆች ይኸውም የእስራኤል የሺህ* አለቆች የሮቤል፣ የጋድና የምናሴ ዘሮች የተናገሩትን በሰሙ ጊዜ ነገሩን አሳማኝ ሆኖ አገኙት።+ 31 በመሆኑም የካህኑ የአልዓዛር ልጅ ፊንሃስ የሮቤልን፣ የጋድንና የምናሴን ዘሮች እንዲህ አላቸው፦ “በይሖዋ ላይ እንዲህ ያለ ታማኝነት የጎደለው ድርጊት ስላልፈጸማችሁ ይሖዋ በመካከላችን እንዳለ ዛሬ አውቀናል። እነሆ እስራኤላውያንን ከይሖዋ እጅ ታድጋችኋል።”

32 ከዚያም የካህኑ የአልዓዛር ልጅ ፊንሃስና አለቆቹ በጊልያድ ምድር ከሰፈሩት ከሮቤላውያንና ከጋዳውያን ዘንድ ተመልሰው በከነአን ምድር ወደሚገኙት ወደ ሌሎቹ እስራኤላውያን በመምጣት ስለ ሁኔታው ነገሯቸው። 33 እስራኤላውያንም ነገሩን አሳማኝ ሆኖ አገኙት። ከዚያም እስራኤላውያን አምላክን ባረኩ፤ ከዚያ በኋላም በሮቤላውያንና በጋዳውያን ላይ ስለመዝመትም ሆነ የሚኖሩባትን ምድር ስለማጥፋት አንስተው አያውቁም።

34 ስለሆነም ሮቤላውያንና ጋዳውያን “ይህ መሠዊያ ይሖዋ እውነተኛ አምላክ ስለመሆኑ በመካከላችን ያለ ምሥክር ነው” በማለት ለመሠዊያው ስም* አወጡለት።

23 ይሖዋ እስራኤላውያንን በዙሪያቸው ካሉት ጠላቶቻቸው ሁሉ ካሳረፋቸው+ ከብዙ ጊዜ በኋላ፣ ኢያሱም አርጅቶና ዕድሜው ገፍቶ ሳለ+ 2 ኢያሱ እስራኤላውያንን በሙሉ፣ ሽማግሌዎቻቸውን፣ መሪዎቻቸውን፣ ዳኞቻቸውንና አለቆቻቸውን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦+ “እንግዲህ እኔ አርጅቻለሁ፤ ዕድሜዬም ገፍቷል። 3 አምላካችሁ ይሖዋ ለእናንተ ሲል በእነዚህ ብሔራት ላይ ያደረገውን ሁሉ ራሳችሁ አይታችኋል፤ ምክንያቱም ለእናንተ እየተዋጋላችሁ የነበረው አምላካችሁ ይሖዋ ነው።+ 4 እኔም ከዮርዳኖስ አንስቶ በስተ ምዕራብ* እስከሚገኘው እስከ ታላቁ ባሕር* ድረስ ያጠፋኋቸውን ብሔራት ሁሉ ምድር+ ጨምሮ የቀሩትን ብሔራት ምድር+ ለየነገዶቻችሁ ርስት እንዲሆን በዕጣ አከፋፍዬ+ ሰጥቻችኋለሁ። 5 እነሱን ከፊታችሁ ያባረራቸው አምላካችሁ ይሖዋ ነው፤+ እሱም ለእናንተ ሲል አባረራቸው፤* እናንተም አምላካችሁ ይሖዋ በገባላችሁ ቃል መሠረት ምድራቸውን ወረሳችሁ።+

6 “እንግዲህ በሙሴ የሕግ መጽሐፍ+ ውስጥ ከተጻፈው ወደ ቀኝም ሆነ ወደ ግራ ፈጽሞ ዞር ሳትሉ+ ሕጉን ሁሉ ለመጠበቅና ለመፈጸም ደፋሮች ሁኑ፤ 7 እንዲሁም በመካከላችሁ ከቀሩት ከእነዚህ ብሔራት ጋር አትቀላቀሉ።+ ሌላው ቀርቶ የአማልክታቸውን ስም አታንሱ፤+ በእነሱም አትማሉ፤ ፈጽሞ አታገልግሏቸው እንዲሁም አትስገዱላቸው።+ 8 ከዚህ ይልቅ እስከዚህ ቀን ድረስ እንዳደረጋችሁት ሁሉ ከአምላካችሁ ከይሖዋ ጋር ተጣብቃችሁ ኑሩ።+ 9 ይሖዋ ታላላቅና ኃያላን ብሔራትን ከፊታችሁ ያባርራቸዋል፤+ እስከዚህ ቀን ድረስ አንድም ሰው ሊቋቋማችሁ አልቻለም።+ 10 አምላካችሁ ይሖዋ በገባላችሁ ቃል መሠረት+ ለእናንተ ስለሚዋጋላችሁ+ ከእናንተ አንዱ፣ ሺህ ሰው ያሳድዳል።+ 11 ስለዚህ አምላካችሁን ይሖዋን በመውደድ+ ዘወትር ነቅታችሁ ጠብቁ።*+

12 “ይሁንና ወደ ኋላ ዞር ብትሉና ከእነዚህ ብሔራት መካከል ተርፈው ከእናንተ ጋር ከቀሩት+ ሰዎች ጋር የጠበቀ ግንኙነት ብትመሠርቱ፣ በጋብቻ ብትዛመዱ+ እንዲሁም እናንተ ከእነሱ ጋር ብትወዳጁ፣ እነሱም ከእናንተ ጋር ወዳጅነት ቢመሠርቱ 13 አምላካችሁ ይሖዋ ከዚህ በኋላ ለእናንተ ሲል እነዚህን ብሔራት እንደማያባርራቸው* በእርግጥ እወቁ።+ እነሱም አምላካችሁ ይሖዋ ከሰጣችሁ ከዚህች መልካም ምድር ላይ እስክትጠፉ ድረስ ወጥመድ፣ አሽክላ፣ ለጀርባችሁ ጅራፍ እንዲሁም በዓይናችሁ ውስጥ እንዳለ እሾህ ይሆኑባችኋል።+

14 “እንግዲህ እኔ መሞቻዬ ተቃርቧል፤* አምላካችሁ ይሖዋ ከገባላችሁ መልካም ቃል ሁሉ አንዲቷም እንኳ ሳትፈጸም እንዳልቀረች በሙሉ ልባችሁና በሙሉ ነፍሳችሁ* ታውቃላችሁ። ሁሉም ተፈጽሞላችኋል። ከመካከላቸው ሳይፈጸም የቀረ አንድም ቃል የለም።+ 15 ሆኖም አምላካችሁ ይሖዋ የገባላችሁ መልካም ቃል በሙሉ እንደተፈጸመላችሁ ሁሉ ይሖዋ አመጣባችኋለሁ ብሎ+ የተናገረውን ጥፋት ሁሉ* ያመጣባችኋል፤ አምላካችሁ ይሖዋ ከሰጣችሁ ከዚህች መልካም ምድርም ያጠፋችኋል።+ 16 አምላካችሁ ይሖዋ እንድትጠብቁት ያዘዛችሁን ቃል ኪዳን ካፈረሳችሁ እንዲሁም ሄዳችሁ ሌሎች አማልክትን ካገለገላችሁና ለእነሱ ከሰገዳችሁ የይሖዋ ቁጣ በእናንተ ላይ ይነድዳል፤+ ከሰጣችሁም መልካም ምድር ላይ በፍጥነት ትጠፋላችሁ።”+

24 ከዚያም ኢያሱ የእስራኤልን ነገዶች በሙሉ በሴኬም አንድ ላይ ሰበሰባቸው፤ የእስራኤልንም ሽማግሌዎች፣ መሪዎች፣ ዳኞችና አለቆች+ ጠራ፤ እነሱም በእውነተኛው አምላክ ፊት ቆሙ። 2 ኢያሱም ሕዝቡን ሁሉ እንዲህ አላቸው፦ “የእስራኤል አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘የአብርሃምና የናኮር አባት የሆነውን ታራን ጨምሮ አባቶቻችሁ+ ከረጅም ጊዜ በፊት+ ከወንዙ* ማዶ ይኖሩ ነበር፤ እነሱም ሌሎች አማልክትን ያገለግሉ ነበር።+

3 “‘እኔም ከጊዜ በኋላ አባታችሁን አብርሃምን+ ከወንዙ* ማዶ አምጥቼ በመላው የከነአን ምድር እንዲዘዋወር አደረግኩት፤ ዘሩንም አበዛሁለት።+ ይስሐቅን ሰጠሁት፤+ 4 ከዚያም ለይስሐቅ ያዕቆብንና ኤሳውን ሰጠሁት።+ በኋላም ለኤሳው ሴይር ተራራን ርስት አድርጌ ሰጠሁት፤+ ያዕቆብና ልጆቹ ደግሞ ወደ ግብፅ ወረዱ።+ 5 በኋላም ሙሴንና አሮንን ላክኋቸው፤+ ግብፅንም በመካከላቸው በፈጸምኩት ነገር በመቅሰፍት መታኋት፤+ ከዚያም እናንተን አወጣኋችሁ። 6 አባቶቻችሁን ከግብፅ ባወጣኋቸውና+ ወደ ባሕሩ በደረሳችሁ ጊዜ ግብፃውያኑ የጦር ሠረገሎችንና ፈረሰኞችን አሰልፈው አባቶቻችሁን እየተከታተሉ እስከ ቀይ ባሕር ድረስ መጡ።+ 7 እነሱም ወደ ይሖዋ መጮኽ ጀመሩ፤+ በመሆኑም በእናንተና በግብፃውያን መካከል ጨለማ እንዲኖር አደረገ፤ ባሕሩንም በላያቸው ላይ በመመለስ አሰመጣቸው፤+ በግብፅ ያደረግኩትንም የገዛ ዓይኖቻችሁ አይተዋል።+ ከዚያም በምድረ በዳ ለብዙ ዓመታት* ኖራችሁ።+

8 “‘ከዮርዳኖስ ማዶ* ይኖሩ ወደነበሩት ወደ አሞራውያንም ምድር አመጣኋችሁ፤ እነሱም ተዋጓችሁ።+ ሆኖም ምድራቸውን እንድትወርሱ እነሱን በእጃችሁ አሳልፌ ሰጠኋችሁ፤ ከፊታችሁም አጠፋኋቸው።+ 9 ከዚያም የሞዓብ ንጉሥ የሆነው የሴፎር ልጅ ባላቅ ተነስቶ ከእስራኤል ጋር ተዋጋ። የቢዖርን ልጅ በለዓምንም እናንተን እንዲረግም አስጠራው።+ 10 እኔ ግን በለዓምን ልሰማው አልፈለግኩም።+ በመሆኑም ደጋግሞ ባረካችሁ፤+ እኔም ከእጁ አዳንኳችሁ።+

11 “‘ከዚያም ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ+ ወደ ኢያሪኮ መጣችሁ።+ የኢያሪኮ መሪዎች* የሆኑት አሞራውያን፣ ፈሪዛውያን፣ ከነአናውያን፣ ሂታውያን፣ ገርጌሻውያን፣ ሂዋውያንና ኢያቡሳውያን ተዋጓችሁ፤ እኔ ግን እነሱን በእጃችሁ አሳልፌ ሰጠኋችሁ።+ 12 ከእናንተ አስቀድሜ ጭንቀት* ላክሁ፤ ሁለቱንም የአሞራውያን ነገሥታት ከፊታችሁ አባረራቸው።+ ይህም የሆነው በሰይፋችሁ ወይም በቀስታችሁ አይደለም።+ 13 ስለዚህ ያልደከማችሁበትን ምድር፣ ያልገነባችኋቸውንም ከተሞች ሰጠኋችሁ፤+ እናንተም በዚያ መኖር ጀመራችሁ። ካልተከላችሁት የወይን ተክልና የወይራ ዛፍ እየበላችሁ ነው።’+

14 “ስለዚህ ይሖዋን ፍሩ፤ በንጹሕ አቋምና* በታማኝነትም* አገልግሉት፤+ አባቶቻችሁ ከወንዙ* ማዶና በግብፅ ምድር ያገለገሏቸውን አማልክት አስወግዱ፤+ ይሖዋን አገልግሉ። 15 ይሖዋን ማገልገል መጥፎ መስሎ ከታያችሁ ደግሞ የምታገለግሉትን ዛሬውኑ ምረጡ፤+ ከወንዙ* ማዶ የነበሩት አባቶቻችሁ ያገለገሏቸውን አማልክትም+ ይሁን አሁን በምትኖሩበት ምድር ያሉት አሞራውያን የሚያገለግሏቸውን አማልክት+ መምረጥ ትችላላችሁ። እኔና ቤተሰቤ ግን ይሖዋን እናገለግላለን።”

16 በዚህ ጊዜ ሕዝቡ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “በእኛ በኩል ይሖዋን መተውና ሌሎች አማልክትን ማገልገል ፈጽሞ የማይታሰብ ነው። 17 እኛንም ሆነ አባቶቻችንን ከግብፅ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣን፣+ እነዚህን ታላላቅ ምልክቶች በፊታችን የፈጸመው+ እንዲሁም በሄድንበት መንገድ ሁሉና አቋርጠን ባለፍናቸው ሕዝቦች ሁሉ መካከል የጠበቀን+ አምላካችን ይሖዋ ነው። 18 ይሖዋ አሞራውያንን ጨምሮ ከእኛ በፊት በምድሪቱ ላይ ይኖሩ የነበሩትን ሕዝቦች በሙሉ አባረረ። ስለዚህ እኛም ይሖዋን እናገለግላለን፤ ምክንያቱም እሱ አምላካችን ነው።”

19 ከዚያም ኢያሱ ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ አምላክን ማገልገል አትችሉም፤ ምክንያቱም እሱ ቅዱስ አምላክ ነው፤+ እንዲሁም እሱ ብቻ እንዲመለክ የሚፈልግ አምላክ ነው።+ መተላለፋችሁንና* ኃጢአታችሁን ይቅር አይልም።+ 20 ይሖዋን ትታችሁ ባዕዳን አማልክትን ብታገለግሉ እሱም መልካም ነገር ካደረገላችሁ በኋላ በእናንተ ላይ ይዞርባችኋል፤ ደግሞም ያጠፋችኋል።”+

21 ሕዝቡ ግን ኢያሱን “በፍጹም፣ እኛ ይሖዋን እናገለግላለን!” አሉት።+ 22 ስለዚህ ኢያሱ ሕዝቡን “በራሳችሁ ፍላጎት ይሖዋን ለማገልገል ስለመረጣችሁ እናንተ በራሳችሁ ላይ ምሥክሮች ናችሁ” አላቸው።+ እነሱም “አዎ፣ ምሥክሮች ነን” አሉ።

23 “እንግዲህ አሁን በመካከላችሁ ያሉትን ባዕዳን አማልክት አስወግዱ፤ ልባችሁንም ወደ እስራኤል አምላክ ወደ ይሖዋ አዘንብሉ።” 24 ሕዝቡም ኢያሱን “አምላካችንን ይሖዋን እናገለግላለን፤ ቃሉንም እንሰማለን!” አለው።

25 በመሆኑም ኢያሱ በዚያ ቀን ከሕዝቡ ጋር ቃል ኪዳን ገባ፤ ለእነሱም በሴኬም ሥርዓትና ደንብ ደነገገላቸው። 26 ከዚያም ኢያሱ እነዚህን ቃላት በአምላክ የሕግ መጽሐፍ+ ላይ ጻፋቸው፤ ትልቅ ድንጋይም ወስዶ+ በይሖዋ መቅደስ አጠገብ በሚገኘው ትልቅ ዛፍ ሥር አቆመው።

27 ኢያሱ ሕዝቡን ሁሉ እንዲህ አላቸው፦ “እንግዲህ ይህ ድንጋይ ይሖዋ የነገረንን ሁሉ ስለሰማ በእኛ ላይ እንደ ምሥክር ሆኖ ያገለግላል፤+ እንዲሁም አምላካችሁን እንዳትክዱ በእናንተ ላይ እንደ ምሥክር ሆኖ ያገለግላል።” 28 ከዚያም ኢያሱ ሕዝቡን ሁሉ፣ እያንዳንዱን ወደየርስቱ አሰናበተ።+

29 ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ፣ የይሖዋ አገልጋይ የሆነው የነዌ ልጅ ኢያሱ በ110 ዓመቱ ሞተ።+ 30 እነሱም ከጋአሽ ተራራ በስተ ሰሜን በኤፍሬም ተራራማ አካባቢ በሚገኘው ርስቱ ውስጥ በቲምናትሰራ+ ቀበሩት። 31 እስራኤላውያን ኢያሱ በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ እንዲሁም ከኢያሱ በኋላ በሕይወት በኖሩትና ይሖዋ ለእስራኤላውያን ሲል ያደረገውን ነገር በሙሉ በሚያውቁት ሽማግሌዎች ሁሉ ዘመን ይሖዋን ማገልገላቸውን ቀጠሉ።+

32 እስራኤላውያን ከግብፅ ይዘውት የወጡት የዮሴፍ አፅም + ያዕቆብ ከሴኬም አባት ከኤሞር+ ልጆች ላይ በ100 ጥሬ ገንዘብ በገዛው+ በሴኬም በሚገኘው እርሻ ውስጥ ተቀብሮ ነበር፤ ይህም የዮሴፍ ልጆች ርስት ሆነ።+

33 የአሮን ልጅ አልዓዛርም ሞተ።+ እነሱም በኤፍሬም ተራራማ አካባቢ ለልጁ ለፊንሃስ+ ተሰጥቶት በነበረው ኮረብታ ቀበሩት።

ወይም “የሆሹአን።” “ይሖዋ አዳኝ ነው” የሚል ትርጉም አለው።

ወይም “በፀሐይ መግቢያ።”

ሜድትራንያንን ያመለክታል።

ወይም “አሰላስልበት።”

በስተ ምሥራቅ ያለውን ምድር ያመለክታል።

ወንዝ ማቋረጥ የሚቻልበት ጥልቀት የሌለው የወንዝ ክፍል።

በስተ ምሥራቅ ያለውን ያመለክታል።

ወይም “ነፍሳችንን ከሞት ታደጉ።”

ወይም “በእናንተ ምትክ ነፍሳችን ትሞታለች!”

ወይም “እጅ ቢያርፍበት።”

ቃል በቃል “የእስራኤል ወንዶች ልጆች።”

ወደ 890 ሜትር ገደማ ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ቃል በቃል “የዮርዳኖስ ውኃ ላይ ሲያርፍ።”

ወይም “ግድግዳ።”

ወይም “ግድግዳ።”

ሙት ባሕርን ያመለክታል።

ቃል በቃል “ወንዶች ልጆቻችሁ።”

ወይም “ማስታወሻ።”

ቃል በቃል “ፈሩት።”

ቃል በቃል “በባሕሩ በኩል ባለው አቅጣጫ።”

ቃል በቃል “በውስጣቸው ምንም መንፈስ አልቀረም።”

“የሸለፈት ኮረብታ” የሚል ትርጉም አለው።

ወይም “ዕድሜያቸው ለውትድርና የደረሰው።”

“ማንከባለል” የሚል ትርጉም አለው።

ወይም “የማለፍን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ቃል በቃል “ከአውራ በግ ቀንድ የተሠራ መለከት።”

ወይም “ቀንደ መለከቱ በረጅሙ ሲነፋ።”

ወይም “ችግር፤ መጠላት።”

“ሕዝቡ ይህን ቃለ መሐላ እንዲምል አደረገ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

“የድንጋይ ካባ” የሚል ትርጉም አለው።

በስተ ምሥራቅ ያለውን ያመለክታል።

ወይም “ለጠላቶቹ ጀርባውን የሚሰጥ።”

አንድ ሰቅል 11.4 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”

ወይም “ችግር፤ መጠላት።”

“መዓት፤ መጠላት” የሚል ትርጉም አለው።

ወይም “ረባዳማው ሜዳ።”

ወይም “ዛፍ።”

ሜድትራንያንን ያመለክታል።

ወይም “ባሪያዎች።”

በስተ ምሥራቅ ያለውን ያመለክታል።

ወይም “ጥቂት ወስደው መረመሩ።”

ወይም “ለነፍሳችን።”

ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”

ቃል በቃል “ምላሱን ያሾለ።”

ወይም “ዛፎችም።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “በአረባና።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ደረቅ ወንዝ።”

ወይም “ደረቅ ወንዝ።”

ወይም “ደረቅ ወንዝ።”

ጌንሴሬጥ ሐይቅን ወይም ገሊላ ባሕርን ያመለክታል።

ሙት ባሕርን ያመለክታል።

ወይም “ድል መደረግ።”

ወይም “ከሺሆር።”

ወይም “ሃማት መግቢያ።”

ወይም “ደረቅ ወንዝ።”

ወይም “ደረቅ ወንዝ።”

ወይም “በረባዳማው ሜዳ።”

ለሲሖን ይገዙ የነበሩ ነገሥታትን ያመለክታል።

ወይም “በረባዳማው ሜዳ ላይ።”

ጌንሴሬጥ ሐይቅን ወይም ገሊላ ባሕርን ያመለክታል።

በስተ ምሥራቅ ያለውን ያመለክታል።

ቃል በቃል “ከልቤ ጋር ያለውን ቃል።”

ሙት ባሕርን ያመለክታል።

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ታላቁን ባሕር፣ ሜድትራንያንን ያመለክታል።

ሙት ባሕርን ያመለክታል።

ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”

ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”

ሜድትራንያንን ያመለክታል።

“በአህያዋ ላይ እያለች አጨበጨበች” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “በኔጌብ።”

“የውኃ ምንጮች” የሚል ትርጉም አለው።

“ገዴራና የበግ ጉረኖዎቿ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “በዙሪያዋ።”

ወይም “በዙሪያዋ።”

ሜድትራንያንን ያመለክታል።

በስተ ምሥራቅ ያለውን ያመለክታል።

ቃል በቃል “በስተ ቀኝ።”

የምናሴን ሰዎች ወይም የምናሴን ክልል ያመለክታል።

ወይም “በዙሪያዋ።”

ወይም “አላስለቀቋቸውም።”

ቃል በቃል “የሰጠኸኝ ለምንድን ነው?”

ወይም “በረባዳማው ሜዳ።”

ወይም “በዙሪያዋ።”

ወይም “ረባዳማ ሜዳ ላይ።”

ቃል በቃል “የብረት ሠረገሎች።”

ቃል በቃል “የብረት ሠረገሎች።”

ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”

ሙት ባሕርን ያመለክታል።

ወይም “ደረቅ ወንዝ።”

ወይም “ባለማወቅ።”

ወይም “ነፍስ መትቶ የገደለ።”

ወይም “ባለማወቅ።”

ወይም “ለዩ።”

ወይም “ነፍስ።”

በስተ ምሥራቅ ያለውን ያመለክታል።

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “ጎሳዎች።”

ወይም “የጎሳ።”

ወይም “መለኮታዊው አምላክ፣ ይሖዋ።”

ቃል በቃል “እንዳይፈሩ።”

ቃል በቃል “ትውልዶቻችን።”

ቃል በቃል “ትውልዶቻችንን።”

ወይም “የጎሳ።”

ከተሰጠው ማብራሪያ መረዳት እንደሚቻለው የመሠዊያው ስም ‘ምሥክር’ ሳይሆን አይቀርም።

ወይም “በፀሐይ መግቢያ።”

ሜድትራንያንን ያመለክታል።

ወይም “አስለቀቃቸው።”

ወይም “ነፍሳችሁን በጥንቃቄ ጠብቁ።”

ወይም “እንደማያስለቅቃቸው።”

ቃል በቃል “ዛሬ የምድርን ሁሉ መንገድ ልሄድ ነው።”

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “ክፉ ቃል ሁሉ።”

ኤፍራጥስን ያመለክታል።

ኤፍራጥስን ያመለክታል።

ቃል በቃል “ቀናት።”

በስተ ምሥራቅ ያለውን ያመለክታል።

“ባለ ርስት” ማለትም ሊሆን ይችላል።

“ድንጋጤ፤ ሽብር” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “ያለነቀፋና።”

ወይም “በእውነትም።”

ኤፍራጥስን ያመለክታል።

ኤፍራጥስን ያመለክታል።

ወይም “ዓመፃችሁንና።”

    የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ ጽሑፎች (2011-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ