ዘካርያስ
1 ዳርዮስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት፣+ በስምንተኛው ወር የይሖዋ ቃል ወደ ኢዶ ልጅ፣ ወደ ቤራክያህ ልጅ ወደ ነቢዩ ዘካርያስ*+ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2 “ይሖዋ በአባቶቻችሁ ላይ እጅግ ተቆጥቶ ነበር።+
3 “እንዲህ በላቸው፦ ‘የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “‘ወደ እኔ ተመለሱ’ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ፤ ‘እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ’+ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።”’
4 “‘የቀደሙት ነቢያት “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ‘እባካችሁ ከክፉ መንገዳችሁና ከክፉ ሥራችሁ ራቁ’* ይላል በማለት የነገሯቸውን አባቶቻችሁን አትምሰሉ።”’+
“‘እነሱ ግን አልሰሙም፤ ለእኔም ትኩረት አልሰጡም’+ ይላል ይሖዋ።
5 “‘አባቶቻችሁ አሁን የት አሉ? ነቢያቱስ ለዘላለም መኖር ችለዋል? 6 ይሁን እንጂ አገልጋዮቼ የሆኑትን ነቢያትን ያዘዝኳቸው ቃልና ድንጋጌ በአባቶቻችሁ ላይ ደርሶ የለም?’+ በመሆኑም ወደ እኔ ተመልሰው እንዲህ አሉ፦ ‘የሠራዊት ጌታ ይሖዋ በወሰነው መሠረት እንደ መንገዳችንና እንደ ሥራችን አደረገብን።’”+
7 ዳርዮስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት፣+ ሺባት* በተባለው በ11ኛው ወር፣ ከወሩም በ24ኛው ቀን የይሖዋ ቃል ወደ ኢዶ ልጅ፣ ወደ ቤራክያህ ልጅ፣ ወደ ነቢዩ ዘካርያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ 8 “በሌሊት ራእይ አየሁ። አንድ ሰው ቀይ ፈረስ እየጋለበ ነበር፤ እሱም በሸለቆው ውስጥ በሚገኙት የአደስ ዛፎች መካከል ቆመ፤ ከበስተ ኋላውም ቀይ፣ ቀይ ቡኒና ነጭ ፈረሶች ነበሩ።”
9 እኔም “ጌታዬ ሆይ፣ እነዚህ እነማን ናቸው?” አልኩ።
ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ “እነዚህ እነማን እንደሆኑ አሳይሃለሁ” ሲል መለሰልኝ።
10 ከዚያም በአደስ ዛፎቹ መካከል ቆሞ የነበረው ሰው “እነዚህ በምድር ላይ እንዲመላለሱ ይሖዋ የላካቸው ናቸው” አለ። 11 እነሱም በአደስ ዛፎቹ መካከል ቆሞ ለነበረው የይሖዋ መልአክ “በምድር ላይ ተመላለስን፤ እነሆም መላዋ ምድር ጸጥታና እርጋታ ሰፍኖባታል”+ አሉት።
12 የይሖዋም መልአክ እንዲህ አለ፦ “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ በእነዚህ 70 ዓመታት የተቆጣሃቸውን+ ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች ምሕረትህን የምትነፍጋቸው እስከ መቼ ነው?”+
13 ይሖዋም ሲያነጋግረኝ ለነበረው መልአክ ደግነት በተሞላባቸውና በሚያጽናኑ ቃላት መለሰለት። 14 ከዚያም ሲያነጋግረኝ የነበረው መልአክ እንዲህ አለኝ፦ “እንዲህ ብለህ አውጅ፦ ‘የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ለኢየሩሳሌምና ለጽዮን እጅግ ቀንቻለሁ።+ 15 ዘና ብለው በተቀመጡት ብሔራት ላይ እጅግ ተቆጥቻለሁ፤+ ምክንያቱም በመጠኑ ብቻ ተቆጥቼ+ እያለ እነሱ ግን ከልክ ያለፈ እርምጃ ወሰዱ።”’+
16 “ስለዚህ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘“ወደ ኢየሩሳሌም በምሕረት እመለሳለሁ፤+ የገዛ ቤቴም በውስጧ ይገነባል”+ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ፤ “በኢየሩሳሌምም ላይ የመለኪያ ገመድ ይዘረጋል።”’+
17 “በድጋሚ እንዲህ ብለህ አውጅ፦ ‘የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ከተሞቼ እንደገና መልካም ነገር ይትረፈረፍባቸዋል፤ ይሖዋም እንደገና ጽዮንን ያጽናናል፤+ ኢየሩሳሌምንም እንደገና ይመርጣል።”’”+
18 ከዚያም ቀና ብዬ ስመለከት አራት ቀንዶች አየሁ።+ 19 በመሆኑም ሲያነጋግረኝ የነበረውን መልአክ “እነዚህ ምንድን ናቸው?” አልኩት። እሱም “እነዚህ ይሁዳን፣+ እስራኤልንና+ ኢየሩሳሌምን የበታተኑ ቀንዶች ናቸው”+ ሲል መለሰልኝ።
20 ከዚያም ይሖዋ አራት የእጅ ጥበብ ባለሙያዎች አሳየኝ። 21 እኔም “እነዚህ የመጡት ምን ሊያደርጉ ነው?” ስል ጠየቅኩ።
እሱም እንዲህ አለኝ፦ “እነዚህ፣ ማንም ራሱን ቀና ማድረግ እስኪሳነው ድረስ ይሁዳን የበታተኑ ቀንዶች ናቸው። እነዚህ የእጅ ጥበብ ባለሙያዎች ደግሞ እነሱን ለማሸበር፣ ይሁዳን ይበታትኗት ዘንድ በምድሯ ላይ ቀንዶቻቸውን ያነሱትን የብሔራቱን ቀንዶች ለመጣል ይመጣሉ።”
2 እኔም ቀና ብዬ ስመለከት በእጁ የመለኪያ ገመድ+ የያዘ ሰው አየሁ። 2 ከዚያም “ወዴት እየሄድክ ነው?” ብዬ ጠየቅኩት።
እሱም “ወርዷና ርዝመቷ ምን ያህል እንደሆነ አውቅ ዘንድ ኢየሩሳሌምን ለመለካት እየሄድኩ ነው”+ ሲል መለሰልኝ።
3 እነሆም፣ ከእኔ ጋር ሲነጋገር የነበረው መልአክ ሄደ፤ ሌላም መልአክ ሊገናኘው መጣ። 4 ከዚያም እንዲህ አለው፦ “ወደዚያ ሮጠህ ሂድና ያንን ወጣት እንዲህ በለው፦ ‘“በመካከሏ ካሉት ሰዎችና መንጎች ሁሉ የተነሳ+ ኢየሩሳሌም ቅጥር እንደሌላቸው መንደሮች በነዋሪዎች ትሞላለች።+ 5 እኔም በዙሪያዋ የእሳት ቅጥር እሆንላታለሁ”+ ይላል ይሖዋ፤ “ክብሬም በመካከሏ ይሆናል።”’”+
6 “ኑ! ኑ! ከሰሜን ምድር ሽሹ”+ ይላል ይሖዋ።
“ወደ አራቱ የሰማይ ነፋሳት በትኛችኋለሁና”+ ይላል ይሖዋ።
7 “ጽዮን ሆይ፣ ነይ! ከባቢሎን ሴት ልጅ ጋር የምትኖሪ ሆይ፣ አምልጪ።+ 8 ክብር ከተጎናጸፈ በኋላ፣* እናንተን ወደዘረፏችሁ ብሔራት የላከኝ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላልና፦+ ‘እናንተን የሚነካ ሁሉ የዓይኔን ብሌን* ይነካል።+ 9 አሁን በእነሱ ላይ እጄን በዛቻ አወዛውዛለሁ፤ የገዛ ባሪያዎቻቸውም ይዘርፏቸዋል።’+ እናንተም እኔን የላከኝ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንደሆነ ታውቃላችሁ።
10 “የጽዮን ሴት ልጅ ሆይ፣ እልል በይ፤+ እኔ እመጣለሁና፤+ በመካከልሽም እኖራለሁ”+ ይላል ይሖዋ። 11 “በዚያን ቀን ብዙ ብሔራት ከይሖዋ ጋር ይተባበራሉ፤+ እነሱም ሕዝቤ ይሆናሉ፤ እኔም በመካከልሽ እኖራለሁ።” ደግሞም እኔን ወደ አንቺ የላከኝ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንደሆነ ታውቂያለሽ። 12 ይሖዋ ይሁዳን በተቀደሰው ምድር ላይ ድርሻው አድርጎ ይወርሰዋል፤ ኢየሩሳሌምንም እንደገና ይመርጣል።+ 13 የሰው ልጆች ሁሉ፣* በይሖዋ ፊት ጸጥ በሉ፤ በቅዱስ መኖሪያው ሆኖ እርምጃ እየወሰደ ነውና።
3 እሱም ሊቀ ካህናቱን ኢያሱን+ በይሖዋ መልአክ ፊት ቆሞ አሳየኝ፤ ሰይጣንም+ እሱን ለመቃወም በስተ ቀኙ ቆሞ ነበር። 2 ከዚያም የይሖዋ መልአክ ሰይጣንን እንዲህ አለው፦ “ሰይጣን፣ ይሖዋ ይገሥጽህ፤+ አዎ፣ ኢየሩሳሌምን የመረጠው+ ይሖዋ ይገሥጽህ! ይህ ሰው ከእሳት መካከል የተነጠቀ የእንጨት ጉማጅ አይደለም?”
3 ኢያሱም ያደፈ ልብስ ለብሶ በመልአኩ ፊት ቆሞ ነበር። 4 መልአኩ በፊቱ ቆመው የነበሩትን “ያደፈውን ልብሱን አውልቁለት” አላቸው። ከዚያም እሱን “እነሆ፣ ጥፋትህን* አስወግጄልሃለሁ፤ ደግሞም ጥሩ ልብስ ትለብሳለህ”*+ አለው።
5 እኔም “በራሱ ላይ ንጹሕ ጥምጥም ይደረግለት”+ አልኩ። እነሱም ንጹሑን ጥምጥም በራሱ ላይ አደረጉለት፤ ልብስም አለበሱት፤ የይሖዋም መልአክ በአጠገቡ ቆሞ ነበር። 6 ከዚያም የይሖዋ መልአክ ኢያሱን እንዲህ አለው፦ 7 “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘በመንገዶቼ ብትመላለስና በፊቴ ኃላፊነቶችህን ብትወጣ፣ በቤቴ ፈራጅ ሆነህ ታገለግላለህ፤+ ቅጥር ግቢዎቼንም ትንከባከባለህ፤* እኔም እዚህ በቆሙት መካከል በነፃነት የመቅረብ መብት እሰጥሃለሁ።’
8 “‘ሊቀ ካህናቱ ኢያሱ ሆይ፣ አንተም ሆንክ በፊትህ የሚቀመጡት ባልንጀሮችህ እባካችሁ ስሙ፤ እነዚህ ሰዎች ምልክት ሆነው ያገለግላሉና፤ እነሆ፣ ቀንበጥ+ የሚል ስም ያለውን አገልጋዬን አመጣለሁ!+ 9 በኢያሱ ፊት ያስቀመጥኩትን ድንጋይ እዩ! በአንዱ ድንጋይ ላይ ሰባት ዓይኖች አሉ፤ እኔም በላዩ ላይ ጽሑፍ እቀርጻለሁ’ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ፤ ‘የዚያችንም ምድር በደል በአንድ ቀን አስወግዳለሁ።’+
10 “‘በዚያ ቀን’ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ፣ ‘እያንዳንዳችሁ ጎረቤታችሁን ከወይናችሁና ከበለስ ዛፋችሁ ሥር እንዲቀመጥ ትጋብዛላችሁ።’”+
4 ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ ተመልሶ መጥቶ አንድን ሰው ከእንቅልፉ እንደሚቀሰቅስ ቀሰቀሰኝ። 2 ከዚያም “የምታየው ምንድን ነው?” አለኝ።
እኔም እንዲህ አልኩት፦ “እነሆ፣ ሙሉ በሙሉ በወርቅ የተሠራና ላዩ ላይ ሳህን ያለበት መቅረዝ+ ይታየኛል። በላዩ ላይ ሰባት መብራቶች፣ አዎ ሰባት መብራቶች አሉበት፤+ አናቱ ላይ ያሉት ሰባት መብራቶችም ሰባት ቱቦዎች አሏቸው። 3 ከጎኑም አንዱ ከሳህኑ በስተ ቀኝ፣ አንዱ ደግሞ በስተ ግራ የቆሙ ሁለት የወይራ ዛፎች አሉ።”+
4 ከዚያም ሲያነጋግረኝ የነበረውን መልአክ “ጌታዬ ሆይ፣ የእነዚህ ነገሮች ትርጉም ምንድን ነው?” በማለት ጠየቅኩት። 5 ከእኔ ጋር ሲነጋገር የነበረውም መልአክ “የእነዚህ ነገሮች ትርጉም ምን እንደሆነ አታውቅም?” ሲል ጠየቀኝ።
እኔም “ጌታዬ ሆይ፣ አላውቅም” ብዬ መለስኩለት።
6 በዚህ ጊዜ እንዲህ አለኝ፦ “ይሖዋ ለዘሩባቤል የተናገረው ቃል ይህ ነው፦ ‘“በመንፈሴ እንጂ፣+ በወታደራዊ ኃይል ወይም በጉልበት አይደለም”+ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ። 7 ታላቅ ተራራ ሆይ፣ አንተ ማን ነህ? በዘሩባቤል+ ፊት ደልዳላ መሬት* ትሆናለህ።+ “እንዴት ያምራል! እንዴት ያምራል!” እያሉ በሚጮኹበት ጊዜ እሱ የመደምደሚያውን ድንጋይ* ያወጣል።’”
8 የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ዳግመኛ ወደ እኔ መጣ፦ 9 “የዘሩባቤል እጆች የዚህን ቤት መሠረት ጥለዋል፤+ የገዛ እጆቹም ያጠናቅቁታል።+ እኔንም ወደ እናንተ የላከኝ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንደሆነ ታውቃላችሁ። 10 ሥራው በትንሹ የተጀመረበትን ቀን* የናቀ ማን ነው?+ እነሱ ሐሴት ያደርጋሉና፤ በዘሩባቤልም እጅ ላይ ቱምቢውን* ያያሉ። እነዚህ ሰባቱ በመላው ምድር የሚዘዋወሩ የይሖዋ ዓይኖች ናቸው።”+
11 ከዚያም “ከመቅረዙ በስተ ቀኝና በስተ ግራ ያሉት የእነዚህ ሁለት የወይራ ዛፎች ትርጉም ምንድን ነው?” በማለት ጠየቅኩት።+ 12 ለሁለተኛም ጊዜ እንዲህ ስል ጠየቅኩት፦ “በሁለቱ የወርቅ ቱቦዎች አማካኝነት ወርቃማ ፈሳሽ የሚያፈሱት የሁለቱ የወይራ ዛፎች ቅርንጫፎች* ትርጉም ምንድን ነው?”
13 እሱም “የእነዚህ ነገሮች ትርጉም ምን እንደሆነ አታውቅም?” አለኝ።
እኔም “ጌታዬ ሆይ፣ አላውቅም” ብዬ መለስኩለት።
14 እሱም “እነዚህ በምድር ሁሉ ጌታ አጠገብ የቆሙት ሁለቱ ቅቡዓን ናቸው” አለ።+
5 ዳግመኛ ቀና ብዬ ስመለከት የሚበር ጥቅልል አየሁ። 2 እሱም “የምታየው ምንድን ነው?” አለኝ።
እኔም “ርዝመቱ 20 ክንድ፣* ወርዱ ደግሞ 10 ክንድ የሆነ የሚበር ጥቅልል አያለሁ” ስል መለስኩለት።
3 ከዚያም እንዲህ አለኝ፦ “ይህ በመላው ምድር ላይ የሚወጣው እርግማን ነው፤ ምክንያቱም የሚሰርቁ ሁሉ+ በአንደኛው በኩል በተጻፈው መሠረት አልተቀጡም፤ ደግሞም በሐሰት የሚምሉ ሁሉ+ በሌላኛው በኩል በተጻፈው መሠረት አልተቀጡም። 4 ‘እኔ ልኬዋለሁ’ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ፤ ‘ወደ ሌባውም ቤት ይገባል፤ በስሜ በሐሰት ወደሚምለውም ሰው ቤት ይገባል፤ በዚያም ቤት ውስጥ ይቀመጣል፤ እንጨቱንና ድንጋዩን ጨምሮ ቤቱን ይበላዋል።’”
5 ከዚያም ሲያነጋግረኝ የነበረው መልአክ ወደ እኔ ቀርቦ “እባክህ ቀና ብለህ የምትወጣውን ነገር ተመልከት” አለኝ።
6 እኔም “ምንድን ነች?” አልኩ።
እሱም መልሶ “ይህች የምትወጣው የኢፍ መስፈሪያ* ናት” አለ። አክሎም “በምድሪቱ ሁሉ የሰዎቹ መልክ ይህ ነው” አለ። 7 እኔም ከእርሳስ የተሠራው ክቡ መክደኛ ሲነሳ አየሁ፤ በመስፈሪያዋም ውስጥ አንዲት ሴት ተቀምጣ ነበር። 8 እሱም “ይህች ሴት ክፋትን ታመለክታለች” አለኝ። ከዚያም የኢፍ መስፈሪያዋ ውስጥ መልሶ ጣላት፤ ቀጥሎም ከእርሳስ የተሠራውን ከባዱን መክደኛ መስፈሪያዋ አፍ ላይ ገጠመው።
9 ከዚያም ቀና ብዬ ስመለከት ሁለት ሴቶች ወደ ፊት ሲመጡ አየሁ፤ በነፋስም መካከል ወደ ላይ ተወነጨፉ። ክንፎቻቸው የራዛ* ዓይነት ክንፎች ነበሩ። እነሱም መስፈሪያዋን በምድርና በሰማይ መካከል አነሷት። 10 እኔም ያነጋግረኝ የነበረውን መልአክ “የኢፍ መስፈሪያዋን ወዴት እየወሰዷት ነው?” ስል ጠየቅኩት።
11 እሱም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ቤት ሊሠሩላት ወደ ሰናኦር*+ ምድር እየወሰዷት ነው፤ ቤቱም በተዘጋጀ ጊዜ በዚያ በተገቢው ቦታዋ ላይ ያስቀምጧታል።”
6 ዳግመኛም ቀና ብዬ ስመለከት አራት ሠረገሎች ከሁለት ተራሮች መካከል ሲመጡ አየሁ፤ ተራሮቹም የመዳብ ተራሮች ነበሩ። 2 የመጀመሪያውን ሠረገላ የሚጎትቱት ቀይ ፈረሶች፣ ሁለተኛውን ሠረገላ የሚጎትቱት ደግሞ ጥቁር ፈረሶች ነበሩ።+ 3 ሦስተኛውን ሠረገላ የሚጎትቱት ነጭ ፈረሶች፣ አራተኛውን ሠረገላ የሚጎትቱት ደግሞ ነጠብጣብ ያለባቸውና ዥጉርጉር ፈረሶች ነበሩ።+
4 ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረውን መልአክ “ጌታዬ ሆይ፣ እነዚህ ምንድን ናቸው?” ብዬ ጠየቅኩት።
5 መልአኩ እንዲህ ሲል መለሰልኝ፦ “እነዚህ በምድር ሁሉ ጌታ ፊት ከቆሙ በኋላ፣+ ከዚያ የሚወጡት አራቱ የሰማያት መናፍስት ናቸው።+ 6 በጥቁር ፈረሶች የሚጎተተው ሠረገላ ወደ ሰሜን ምድር ይወጣል፤+ ነጮቹ ፈረሶች ከባሕሩ ባሻገር ወዳለው ምድር ይወጣሉ፤ ነጠብጣብ ያለባቸው ፈረሶች ደግሞ ወደ ደቡብ ምድር ይወጣሉ። 7 ዥጉርጉሮቹ ፈረሶችም ወጥተው በምድር መካከል ለመመላለስ አቆብቁበው* ነበር።” እሱም “ሂዱ፤ በምድር መካከል ተመላለሱ” አለ። እነሱም በምድር መካከል ይመላለሱ ጀመር።
8 ከዚያም ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለኝ፦ “እነሆ፣ ወደ ሰሜን ምድር የሚወጡት፣ የይሖዋ መንፈስ በሰሜን ምድር እንዲያርፍ አድርገዋል።”
9 የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ዳግመኛ ወደ እኔ መጣ፦ 10 “በግዞት ከተወሰደው ሕዝብ ያመጡትን ነገር ከሄልዳይ፣ ከጦቢያህና ከየዳያህ ውሰድ፤ በዚያም ቀን፣ ከባቢሎን ከመጡት ከእነዚህ ሰዎች ጋር ወደ ሶፎንያስ ልጅ ወደ ኢዮስያስ ቤት ሂድ። 11 ብርና ወርቅ ወስደህ አክሊል* ሥራ፤ ከዚያም በየሆጼዴቅ ልጅ በሊቀ ካህናቱ በኢያሱ+ ራስ ላይ አድርገው። 12 እንዲህም በለው፦
“‘የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ቀንበጥ ተብሎ የሚጠራው ሰው ይህ ነው።+ እሱ በገዛ ቦታው ላይ ያቆጠቁጣል፤ የይሖዋንም ቤተ መቅደስ ይሠራል።+ 13 የይሖዋን ቤተ መቅደስ የሚገነባው እሱ ነው፤ ግርማ የሚጎናጸፈውም እሱ ነው። በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ይገዛል፤ ደግሞም በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ካህን ሆኖ ያገለግላል፤+ በሁለቱም መካከል* ሰላማዊ ስምምነት ይኖራል። 14 አክሊሉም* ለሄሌም፣ ለጦቢያህ፣ ለየዳያህና+ ለሶፎንያስ ልጅ ለሄን በይሖዋ ቤተ መቅደስ ውስጥ መታሰቢያ* ሆኖ ያገለግላል። 15 በሩቅ ያሉትም ይመጣሉ፤ በይሖዋ ቤተ መቅደስ የግንባታ ሥራም ይካፈላሉ።” እኔን ወደ እናንተ የላከኝ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንደሆነ ታውቃላችሁ። የአምላካችሁን የይሖዋን ቃል ብትሰሙ ይህ ይሆናል።’”
7 ንጉሥ ዳርዮስ በነገሠ በአራተኛው ዓመት፣ ኪስሌው* በተባለው በዘጠነኛው ወር፣ ከወሩም በአራተኛው ቀን የይሖዋ ቃል ወደ ዘካርያስ መጣ።+ 2 የቤቴል ሰዎች ይሖዋ ሞገስ እንዲያሳያቸው ለመለመን ሳሬጸርንና ረጌምሜሌክን ከሰዎቹ ጋር ላኩ፤ 3 እነሱም የሠራዊት ጌታን የይሖዋን ቤት* ካህናትና ነቢያቱን “ለብዙ ዓመታት እንዳደረግኩት በአምስተኛው ወር ማልቀስና+ መጾም ይኖርብኛል?” ብለው ጠየቁ።
4 የሠራዊት ጌታ የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ዳግመኛ ወደ እኔ መጣ፦ 5 “ለምድሪቱ ነዋሪዎች ሁሉና ለካህናቱ እንዲህ በላቸው፦ ‘ለ70 ዓመታት+ በአምስተኛውና በሰባተኛው ወር ስትጾሙና ዋይ ዋይ ስትሉ፣+ ትጾሙ የነበረው በእርግጥ ለእኔ ነበር? 6 ትበሉና ትጠጡ በነበረበት ጊዜስ ትበሉና ትጠጡ የነበረው ለራሳችሁ አልነበረም? 7 ኢየሩሳሌምና በዙሪያዋ ያሉት ከተሞቿ በሰዎች ተሞልተውና ሰላም ሰፍኖባቸው በነበረበት ጊዜ እንዲሁም ሰዎች በኔጌብና በሸፌላ ይኖሩ በነበረበት ወቅት ይሖዋ በቀድሞዎቹ ነቢያት አማካኝነት ያወጀውን ቃል መታዘዝ አልነበረባችሁም?’”+
8 የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ዳግመኛ ወደ ዘካርያስ መጣ፦ 9 “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘በእውነተኛ ፍትሕ ላይ ተመሥርታችሁ ፍረዱ፤+ አንዳችሁ ለሌላው ታማኝ ፍቅርና+ ምሕረት አሳዩ። 10 መበለቲቱንም ሆነ አባት የሌለውን ልጅ፣*+ ከባዕድ አገር የመጣውን ሰውም+ ሆነ ድሃውን አታታሉ፤+ ደግሞም አንዳችሁ በሌላው ላይ ክፉ ለማድረግ በልባችሁ አታሲሩ።’+ 11 እነሱ ግን ለመስማት ፈቃደኛ አልሆኑም፤+ በግትርነትም ጀርባቸውን ሰጡ፤+ ላለመስማትም ሲሉ ጆሯቸውን ደፈኑ።+ 12 ልባቸውን እንደ አልማዝ* አጠነከሩ፤+ እንዲሁም የሠራዊት ጌታ ይሖዋ በመንፈሱ አማካኝነት፣ በቀድሞዎቹ ነቢያት በኩል የላከውን ሕግና* ቃል አልታዘዙም።+ ከዚህም የተነሳ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እጅግ ተቆጣ።”+
13 “‘እኔ ስጠራቸው እንዳልሰሙኝ ሁሉ+ እነሱ ሲጣሩም አልሰማቸውም’+ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ። 14 ‘ደግሞም ወደማያውቋቸው ብሔራት ሁሉ በአውሎ ነፋስ በተንኳቸው፤+ ምድሪቱም ትተዋት ከሄዱ በኋላ ባድማ ሆነች፤ በእሷ የሚያልፍ ወይም ወደ እሷ የሚመለስ ማንም የለም፤+ የተወደደችውን ምድር አስፈሪ ቦታ አድርገዋታልና።’”
8 የሠራዊት ጌታ የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ዳግመኛ መጣ፦ 2 “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ለጽዮን በታላቅ ቅንዓት እቀናለሁ፤+ ደግሞም በታላቅ ቁጣ ለእሷ እቀናለሁ።’”
3 “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ወደ ጽዮን እመለሳለሁ፤+ በኢየሩሳሌምም እኖራለሁ፤+ ኢየሩሳሌምም የእውነት* ከተማ ተብላ ትጠራለች፤+ የሠራዊት ጌታ የይሖዋ ተራራም ቅዱስ ተራራ ተብሎ ይጠራል።’”+
4 “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ሽማግሌዎችና አሮጊቶች በኢየሩሳሌም አደባባዮች እንደገና ይቀመጣሉ፤ እያንዳንዳቸውም ከዕድሜያቸው ርዝመት የተነሳ* በእጃቸው ምርኩዝ ይይዛሉ።+ 5 የከተማዋም አደባባዮች በዚያ በሚጫወቱ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ይሞላሉ።’”+
6 “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘በዚያን ጊዜ ይህ ነገር ለዚህ ሕዝብ ቀሪዎች የማይቻል ነገር መስሎ ቢታይ እንኳ ለእኔ የማይቻል ነገር ሊመስል ይገባል?’ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።”
7 “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እነሆ፣ ሕዝቤን ከምሥራቅና ከምዕራብ አገሮች* አድናለሁ።+ 8 እኔም አመጣቸዋለሁ፤ እነሱም በኢየሩሳሌም ይኖራሉ፤+ ሕዝቤም ይሆናሉ፤ እኔም በእውነትና* በጽድቅ አምላካቸው እሆናለሁ።’”+
9 “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘በእነዚህ ቀናት በነቢያት አፍ የተነገሩትን+ እነዚህን ቃላት የምትሰሙ ሁሉ እጃችሁን አበርቱ፤*+ እነዚህ ቃላት፣ ቤተ መቅደሱን ለመገንባት፣ የሠራዊት ጌታ የይሖዋ ቤት መሠረት በተጣለበት ጊዜ ነቢያት የተናገሯቸው ናቸው። 10 ከእነዚያ ቀናት በፊት ለሰውም ሆነ ለእንስሳ የሚከፈል ደሞዝ አልነበረምና፤+ ደግሞም ከጠላት የተነሳ በሰላም መግባትና መውጣት አይቻልም ነበር፤ ሰው ሁሉ አንዱ በሌላው ላይ እንዲነሳ አድርጌ ነበርና።’
11 “‘አሁን ግን በዚህ ሕዝብ ቀሪዎች ላይ እንደቀድሞው ዘመን አላደርግም’+ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ። 12 ‘የሰላም ዘር ይዘራልና፤ የወይን ተክሉ ፍሬ ያፈራል፤ ምድርም ፍሬዋን ትሰጣለች፤+ ሰማያትም ጠል ያዘንባሉ፤ እኔም የዚህ ሕዝብ ቀሪዎች እነዚህን ነገሮች ሁሉ እንዲወርሱ አደርጋለሁ።+ 13 የይሁዳና የእስራኤል ቤት ሆይ፣ በብሔራት መካከል እርግማን ነበራችሁ፤+ አሁን ግን አድናችኋለሁ፤ እናንተም በረከት ትሆናላችሁ።+ አትፍሩ!+ እጃችሁን አበርቱ።’*+
14 “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላልና፦ ‘“አባቶቻችሁ ስላስቆጡኝ በእናንተ ላይ ጥፋት ላመጣባችሁ ቆርጬ እንደነበርና በዚያም እንዳልተጸጸትኩ ሁሉ” ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ፣+ 15 “አሁንም ለኢየሩሳሌምና ለይሁዳ ቤት መልካም ለማድረግ ቆርጫለሁ።+ አትፍሩ!”’+
16 “‘እናንተ እነዚህን ነገሮች ልታደርጉ ይገባል፦ እርስ በርሳችሁ እውነትን ተነጋገሩ፤+ በከተማዋም በሮች የምትፈርዱት ፍርድ እውነትን የሚያጠናክርና ሰላምን የሚያሰፍን ይሁን።+ 17 አንዳችሁ በሌላው ላይ ክፉ ነገር ለማድረግ በልባችሁ አታሲሩ፤+ ማንኛውንም የሐሰት መሐላ አትውደዱ፤+ እነዚህን ነገሮች ሁሉ እጠላለሁና’+ ይላል ይሖዋ።”
18 የሠራዊት ጌታ የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ዳግመኛ ወደ እኔ መጣ፦ 19 “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘የአራተኛው ወር፣+ የአምስተኛው ወር፣+ የሰባተኛው ወርና+ የአሥረኛው ወር+ ጾም ለይሁዳ ቤት የፍስሐና የደስታ ይኸውም የሐሴት በዓል ይሆናል።+ በመሆኑም እውነትንና ሰላምን ውደዱ።’
20 “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ሕዝቦችና የብዙ ከተማ ነዋሪዎች በእርግጥ ይመጣሉ፤ 21 በአንዲት ከተማ የሚኖሩ ሰዎችም በሌላ ከተማ ወደሚኖሩ ሰዎች ሄደው እንዲህ ይላሉ፦ “ይሖዋ ሞገሱን እንዲያሳየን ለመለመንና የሠራዊት ጌታ ይሖዋን ለመፈለግ ተነሱ፤ እንሂድ። እኔም እሄዳለሁ።”+ 22 ደግሞም ብዙ ሕዝቦችና ኃያላን ብሔራት የሠራዊት ጌታ ይሖዋን ለመፈለግና ይሖዋ ሞገሱን እንዲያሳያቸው ለመለመን ወደ ኢየሩሳሌም ይመጣሉ።’+
23 “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘በዚያን ጊዜ ከብሔራት ቋንቋዎች ሁሉ የተውጣጡ+ አሥር ሰዎች የአንድን አይሁዳዊ ልብስ* አጥብቀው በመያዝ “አምላክ ከእናንተ ጋር መሆኑን ስለሰማን ከእናንተ ጋር እንሄዳለን”+ ይላሉ።’”+
9 የፍርድ መልእክት፦
3 ጢሮስ የመከላከያ ግንብ* ገንብታለች።
ብርን እንደ አቧራ፣
ወርቅንም በመንገድ ላይ እንዳለ አፈር ቆልላለች።+
5 አስቀሎን ይህን አይታ ትፈራለች፤
ጋዛ በጣም ትጨነቃለች፤
ኤቅሮንም እንዲሁ ትሆናለች፤ ምክንያቱም ተስፋ የምታደርግባት ለኀፍረት ትዳረጋለች።
ከጋዛ ንጉሥ ይጠፋል፤
አስቀሎንም ሰው አልባ ትሆናለች።+
6 ዲቃላም በአሽዶድ ይቀመጣል፤
እኔም የፍልስጤምን ኩራት አስወግዳለሁ።+
7 በደም የተበከሉትን ነገሮች ከአፉ፣
አስጸያፊ የሆኑትንም ነገሮች ከጥርሱ መካከል አስወግዳለሁ፤
ከእሱም የሚተርፈው ማንኛውም ሰው የአምላካችን ይሆናል፤
ኤቅሮንም እንደ ኢያቡሳዊ ይሆናል።+
8 የሚገባም ሆነ የሚወጣ እንዳይኖር፣
ቤቴን ለመጠበቅ በውጭ በኩል ድንኳን እተክላለሁ፤*+
ከእንግዲህም ወዲህ በመካከላቸው የሚያልፍ አሠሪ* አይኖርም፤+
አሁን በገዛ ዓይኔ አይቼዋለሁና።*
9 የጽዮን ሴት ልጅ ሆይ፣ እጅግ ሐሴት አድርጊ።
የኢየሩሳሌም ሴት ልጅ ሆይ፣ በድል አድራጊነት ጩኺ።
እነሆ፣ ንጉሥሽ ወደ አንቺ ይመጣል።+
10 የጦር ሠረገላውን ከኤፍሬም፣
ፈረሱንም ከኢየሩሳሌም እወስዳለሁ።
የጦርነቱ ቀስት ይወሰዳል።
11 አንቺ ሴት፣ በእኔና በአንቺ መካከል ካለው የደም ቃል ኪዳን የተነሳ
እስረኞችሽን ውኃ ከሌለበት ጉድጓድ አውጥቼ እልካቸዋለሁ።+
12 እናንተ ተስፋ ያላችሁ እስረኞች ወደ ምሽጉ ተመለሱ።+
ዛሬ እንዲህ እልሻለሁ፦
‘ድርሻሽን እጥፍ አድርጌ እከፍልሻለሁ።+
13 ይሁዳን በእጄ እንዳለ ደጋን እወጥረዋለሁና።*
ደጋኑን በኤፍሬም እሞላዋለሁ፤*
ጽዮን ሆይ፣ ወንዶች ልጆችሽን እቀሰቅሳለሁ፤
ግሪክ ሆይ፣ በወንዶች ልጆችሽ ላይ ይነሳሉ፤
ጽዮን ሆይ፣ እንደ ተዋጊ ሰይፍም አደርግሻለሁ።’
14 ይሖዋ በእነሱ ላይ ይገለጣል፤
ፍላጻውም እንደ መብረቅ ይወነጨፋል።
ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ቀንደ መለከት ይነፋል፤+
እሱም ከደቡብ አውሎ ነፋሳት ጋር ይሄዳል።
15 የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ይከላከልላቸዋል፤
እነሱም የሚወነጨፍባቸውን ድንጋይ ውጠው ያስቀራሉ፤ ደግሞም ያመክናሉ።+
17 ጥሩነቱ ምንኛ ታላቅ ነው!+
ውበቱስ እንዴት ያማረ ነው!
እህል ወጣት ወንዶችን፣
አዲስ የወይን ጠጅም ደናግሉን ያለመልማል።”+
10 “በበልግ ዝናብ ወቅት ይሖዋ ዝናብ እንዲያዘንብላችሁ ጠይቁ።
ከንቱ ስለሆኑ ሕልሞች ይናገራሉ፤
በከንቱም ሊያጽናኑ ይሞክራሉ።
ከዚህም የተነሳ ሕዝቡ እንደ በግ ይቅበዘበዛል።
እረኛ ስለሌለ ይሠቃያል።
3 በእረኞቹ ላይ ቁጣዬ ይነዳል፤
ጨቋኞቹንም መሪዎች* ተጠያቂ አደርጋቸዋለሁ፤
የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ትኩረቱን ወደ መንጋው፣ ወደ ይሁዳ ቤት አዙሯልና፤+
ግርማ ሞገስ እንደተላበሰው የጦር ፈረሱ እነሱንም ግርማ ሞገስ አላብሷቸዋል።
5 እነሱም በጦርነት ጊዜ፣
በመንገድ ላይ ያለን ጭቃ እንደሚረግጡ ተዋጊዎች ይሆናሉ።
6 የይሁዳን ቤት ከሁሉ የላቀ አደርጋለሁ፤
የዮሴፍንም ቤት አድናለሁ።+
ምሕረት ስለማሳያቸው+
ቀድሞ ወደነበሩበት ሁኔታ እመልሳቸዋለሁ፤
እነሱም ፈጽሞ እንዳልጣልኳቸው ሰዎች ይሆናሉ፤+
እኔ ይሖዋ አምላካቸው ነኝና፤ ደግሞም እመልስላቸዋለሁ።
7 የኤፍሬም ሰዎች እንደ ኃያል ተዋጊ ይሆናሉ፤
ልባቸውም የወይን ጠጅ እንደጠጣ ሰው ሐሴት ያደርጋል።+
ልጆቻቸው ይህን አይተው ሐሴት ያደርጋሉ፤
ልባቸውም በይሖዋ ደስ ይለዋል።+
9 በሕዝቦች መካከል እንደ ዘር ብበትናቸውም፣
በሩቅ ስፍራዎች ሆነው ያስታውሱኛል፤
ከልጆቻቸው ጋር ሆነው ያንሰራራሉ፤ ደግሞም ይመለሳሉ።
የአሦር ኩራት ይዋረዳል፤
የግብፅም በትረ መንግሥት ይወገዳል።+
11 “ሊባኖስ ሆይ፣ እሳት አርዘ ሊባኖሶችህን እንድትበላ
በሮችህን ክፈት።
2 የጥድ ዛፍ ሆይ፣ አርዘ ሊባኖሱ ስለወደቀ ዋይ ዋይ በል፤
ታላላቆቹ ዛፎች ወድመዋል!
እናንተ የባሳን የባሉጥ ዛፎች፣
ጥቅጥቅ ያለው ጫካ ስለጠፋ ዋይ ዋይ በሉ!
3 ስሙ! እረኞች ግርማ ሞገሳቸው ስለተገፈፈ
ዋይ ዋይ ይላሉ።
አዳምጡ! በዮርዳኖስ አጠገብ ያሉት ጥቅጥቅ ያሉ ጥሻዎች ስለወደሙ
ደቦል አንበሶች ያገሳሉ።
4 “አምላኬ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ለእርድ የተዘጋጀውን መንጋ ጠብቅ፤+ 5 የገዟቸው ያርዷቸዋል፤+ ሆኖም ተጠያቂ አይሆኑም። የሚሸጧቸውም+ “ይሖዋ የተመሰገነ ይሁን፤ ባለጸጋ እሆናለሁና” ይላሉ። እረኞቻቸውም ምንም ዓይነት ርኅራኄ አያሳዩአቸውም።’+
6 “‘ከእንግዲህ ለምድሪቱ ነዋሪዎች አልራራላቸውም’ ይላል ይሖዋ። ‘በመሆኑም እያንዳንዱ ሰው በባልንጀራው እጅና በንጉሡ እጅ እንዲወድቅ አደርጋለሁ፤ እነሱም ምድሪቱን ያደቋታል፤ እኔም እነሱን ከእጃቸው አልታደግም።’”
7 እናንተ ጉስቁልና የደረሰባችሁ የመንጋው አባላት፣ ለመታረድ የተዘጋጀውን መንጋ መጠበቅ ጀምሬአለሁ፤+ ይህን ያደረግኩትም ለእናንተ ስል ነው። ስለዚህ ሁለት በትሮችን ወስጄ አንደኛውን በትር “ደስታ፣” ሌላኛውን ደግሞ “ኅብረት” ብዬ ጠራሁት፤+ እኔም መንጋውን መጠበቅ ጀመርኩ። 8 ደግሞም በአንድ ወር ውስጥ ሦስት እረኞችን አባረርኩ፤ ይህን ያደረግኩት እነሱን መታገሥ ስላልቻልኩና* እነሱም እኔን ስለተጸየፉኝ* ነው። 9 እንዲህም አልኩ፦ “ከእንግዲህ እረኛችሁ አልሆንም። የምትሞተው ትሙት፤ የምትጠፋውም ትጥፋ። የቀሩት ደግሞ አንዳቸው የሌላውን ሥጋ ይብሉ።” 10 ስለዚህ ከሕዝቡ ሁሉ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳኔን በማፍረስ “ደስታ” የተባለውን በትሬን+ ወስጄ ሰበርኩት። 11 በመሆኑም በዚያን ቀን ቃል ኪዳኑ ፈረሰ፤ ይመለከቱኝ የነበሩት የተጎሳቆሉት የመንጋው አባላትም ይህ የይሖዋ ቃል መሆኑን አወቁ።
12 ከዚያም “መልካም መስሎ ከታያችሁ ደሞዜን ስጡኝ፤ ካልሆነ ግን ተዉት” አልኳቸው። እነሱም ደሞዜን፣ 30 የብር ሰቅል ከፈሉኝ።*+
13 ከዚያም ይሖዋ “እኔን የገመቱበትን የከበረ ዋጋ+ ይኸውም ብሩን ግምጃ ቤት ውስጥ ጣለው” አለኝ። እኔም 30ውን የብር ሰቅል ወስጄ በይሖዋ ቤት ግምጃ ቤት ውስጥ ጣልኩት።+
14 ከዚያም በይሁዳና በእስራኤል መካከል ያለውን ወንድማማችነት በማፍረስ “ኅብረት” የተባለውን ሁለተኛውን በትሬን+ ሰበርኩት።+
15 ይሖዋም እንዲህ አለኝ፦ “እንግዲህ የሰነፍ እረኛ መሣሪያዎችን ውሰድ።+ 16 በምድሪቱ ላይ እረኛ አስነሳለሁና። እያለቁ ያሉትን በጎች አይንከባከብም፤+ ግልገሎቹን አይፈልግም ወይም የተጎዳውን አይፈውስም+ አሊያም መቆም የሚችሉትን አይቀልብም። ከዚህ ይልቅ የሰባውን በግ ሥጋ ይበላል፤+ የበጎቹንም ሰኮና ቆርጦ ይጥላል።+
17 መንጋውን ለሚተው+ የማይረባ እረኛዬ ወዮለት!+
ሰይፍ ክንዱንና ቀኝ ዓይኑን ይመታዋል።
ክንዱ ሙሉ በሙሉ ይሰልላል፤
ቀኝ ዓይኑም ሙሉ በሙሉ ይታወራል።”*
12 የፍርድ መልእክት፦
2 “እነሆ፣ ኢየሩሳሌምን በዙሪያዋ ያሉትን ሕዝቦች ሁሉ የምታንገዳግድ ጽዋ* አደርጋታለሁ፤ ጠላት ይሁዳንም ሆነ ኢየሩሳሌምን ይከባል።+ 3 በዚያ ቀን ኢየሩሳሌምን ለሕዝቦች ሁሉ ከባድ* ድንጋይ አደርጋታለሁ። ድንጋዩን የሚያነሱት ሁሉ ክፉኛ መጎዳታቸው የማይቀር ነው፤+ የምድር ብሔራትም ሁሉ በእሷ ላይ ይሰበሰባሉ።+ 4 በዚያ ቀን” ይላል ይሖዋ፣ “እያንዳንዱን ፈረስ በድንጋጤ፣ ጋላቢውንም በእብደት እመታለሁ። ዓይኖቼን በይሁዳ ቤት ላይ አደርጋለሁ፤ የሕዝቦቹን ፈረሶች ሁሉ ግን አሳውራለሁ። 5 የይሁዳም አለቆች* በልባቸው ‘የሠራዊት ጌታ ይሖዋ አምላካቸው ስለሆነ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ብርታታችን ናቸው’ ይላሉ።+ 6 በዚያን ቀን የይሁዳን አለቆች በእንጨት መካከል እንዳለ የሚነድ ምድጃና በታጨደ እህል መካከል እንዳለ የሚነድ ችቦ አደርጋቸዋለሁ፤+ እነሱም በስተ ቀኝም ሆነ በስተ ግራ፣ በዙሪያቸው ያሉትን ሕዝቦች ሁሉ ይበላሉ፤+ ኢየሩሳሌምም በገዛ ስፍራዋ* ይኸውም በኢየሩሳሌም ዳግመኛ የሰዎች መኖሪያ ትሆናለች።+
7 “የዳዊት ቤት ውበትና* የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ውበት* ከይሁዳ እጅግ የበለጠ እንዳይሆን ይሖዋ በመጀመሪያ የይሁዳን ድንኳኖች ያድናል። 8 በዚያ ቀን ይሖዋ በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ዙሪያ መከታ ይሆናል፤+ በዚያም ቀን ከእነሱ መካከል የሚሰናከለው* እንደ ዳዊት ይሆናል፤ የዳዊትም ቤት እንደ አምላክ፣ በፊታቸውም እንደሚሄደው የይሖዋ መልአክ ይሆናል።+ 9 ደግሞም በዚያ ቀን በኢየሩሳሌም ላይ የሚመጡትን ብሔራት ሁሉ ለማጥፋት ቆርጬ እነሳለሁ።+
10 “በዳዊት ቤትና በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ላይ የሞገስንና የምልጃን መንፈስ አፈሳለሁ፤ እነሱም የወጉትን ያዩታል፤+ ለአንድያ ልጅም እንደሚለቀስ ያለቅሱለታል፤ ለበኩር ልጅ እንደሚለቀሰው ያለ መራራ ለቅሶም ያለቅሱለታል። 11 በዚያን ቀን በኢየሩሳሌም የሚለቀሰው ለቅሶ በመጊዶ ሜዳ፣ በሃዳድሪሞን እንደተለቀሰው ለቅሶ ታላቅ ይሆናል።+ 12 ምድሪቱም ታለቅሳለች፤ እያንዳንዱም ቤተሰብ ለየብቻው ያለቅሳል፤ የዳዊት ቤት ቤተሰብ ለብቻው፣ ሴቶቻቸውም ለብቻቸው፣ የናታን+ ቤት ቤተሰብ ለብቻው፣ ሴቶቻቸውም ለብቻቸው፣ 13 የሌዊ+ ቤት ቤተሰብ ለብቻው፣ ሴቶቻቸውም ለብቻቸው፣ የሺምአይ+ ቤት ቤተሰብ ለብቻው፣ ሴቶቻቸውም ለብቻቸው፣ 14 የቀሩትም ቤተሰቦች በሙሉ፣ እያንዳንዱ ቤተሰብ ለብቻው፣ ሴቶቻቸውም ለብቻቸው ያለቅሳሉ።
13 “በዚያ ቀን፣ ኃጢአታቸውንና ርኩሰታቸውን ለማንጻት ለዳዊት ቤትና ለኢየሩሳሌም ነዋሪዎች የውኃ ጉድጓድ ይቆፈራል።+
2 “በዚያ ቀን” ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ፣ “የጣዖቶቹን ስም ከምድሪቱ ላይ እደመስሳለሁ፤+ እነሱም ዳግመኛ አይታወሱም፤ ደግሞም ነቢያቱንና የርኩሰት መንፈሱን ከምድሪቱ ላይ አስወግዳለሁ።+ 3 አንድ ሰው ዳግመኛ ትንቢት ቢናገር የወለዱት አባትና እናቱ ‘በይሖዋ ስም ሐሰት ስለተናገርክ በሕይወት አትኖርም’ ይሉታል። ደግሞም የወለዱት አባትና እናቱ ትንቢት በመናገሩ ይወጉታል።+
4 “በዚያ ቀን እያንዳንዱ ነቢይ ትንቢት በሚናገርበት ጊዜ ሁሉ በገዛ ራእዩ ያፍራል፤ ሰዎችንም ለማታለል የነቢያት ዓይነት ፀጉራም ልብስ+ አይለብስም። 5 ደግሞም እንዲህ ይላል፦ ‘እኔ ነቢይ አይደለሁም። ይልቁንም አራሽ ነኝ፤ ምክንያቱም አንድ ሰው ልጅ ሳለሁ ባሪያ አድርጎ ገዝቶኛል።’ 6 አንድ ሰውም ‘በትከሻዎችህ መካከል* ያሉት ቁስሎች ምንድን ናቸው?’ ብሎ ቢጠይቀው ‘በወዳጆቼ ቤት ሳለሁ የቆሰልኩት ነው’ ይላል።”
7 “ሰይፍ ሆይ፣ በእረኛዬ+ ይኸውም
በወዳጄ ላይ ንቃ” ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።
እነሱ ስሜን ይጠራሉ፤
እኔም እመልስላቸዋለሁ።
‘እነሱ ሕዝቤ ናቸው’ እላለሁ፤+
እነሱ ደግሞ ‘ይሖዋ አምላካችን ነው’ ይላሉ።”
14 “እነሆ፣ የይሖዋ ቀን ይመጣል፤ በዚያን ጊዜ ከአንቺ* የተማረከው በመካከልሽ ይከፋፈላል። 2 ኢየሩሳሌምን እንዲወጉ ብሔራትን ሁሉ እሰበስባለሁ፤ ከተማዋም ትያዛለች፤ ቤቶቹ ይዘረፋሉ፤ ሴቶቹም ይደፈራሉ። የከተማዋም እኩሌታ ለግዞት ይዳረጋል፤ ከሕዝቡ መካከል የሚቀሩት ሰዎች ግን ከከተማዋ አይወገዱም።
3 “ይሖዋ ይወጣል፤ በጦርነት ቀን እንደሚዋጋው እነዚያን ብሔራት ይዋጋል።+ 4 በዚያ ቀን እግሮቹ በስተ ምሥራቅ በኢየሩሳሌም ትይዩ በሚገኘው በደብረ ዘይት ተራራ+ ላይ ይቆማሉ፤ የደብረ ዘይት ተራራም ከምሥራቅ* አንስቶ እስከ ምዕራብ* ድረስ ለሁለት ይከፈላል፤ እጅግ ትልቅ ሸለቆም ይፈጠራል፤ የተራራው አንዱ ግማሽ ወደ ሰሜን፣ ሌላው ግማሽ ደግሞ ወደ ደቡብ ፈቀቅ ይላል። 5 እናንተ በተራሮቼ መካከል ወዳለው ሸለቆ ትሸሻላችሁ፤ በተራሮቹ መካከል ያለው ሸለቆ እስከ አዜል ድረስ ይደርሳልና። በይሁዳ ንጉሥ በዖዝያ ዘመን ከተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ የተነሳ+ ሸሽታችሁ እንደነበረ ሁሉ አሁንም ትሸሻላችሁ። አምላኬ ይሖዋም ይመጣል፤ ቅዱሳኑም ሁሉ ከእሱ ጋር ይሆናሉ።+
6 “በዚያ ቀን ደማቅ ብርሃን አይኖርም፤+ ነገሮች ሁሉ ባሉበት ይረጋሉ።* 7 ያም ቀን የይሖዋ ቀን ተብሎ የሚታወቅ ልዩ ቀን ይሆናል።+ ቀንም ሆነ ሌሊት አይሆንም፤ በመሸም ጊዜ ብርሃን ይኖራል። 8 በዚያ ቀን ከኢየሩሳሌም ሕያው ውኃዎች+ ይወጣሉ፤+ ግማሾቹ በስተ ምሥራቅ ወዳለው ባሕር፣*+ ግማሾቹ ደግሞ በስተ ምዕራብ ወዳለው ባሕር* ይፈስሳሉ።+ ይህም በበጋና በክረምት ይሆናል። 9 ይሖዋም በመላው ምድር ላይ ይነግሣል።+ በዚያ ቀን ይሖዋ አንድ፣+ ስሙም አንድ ይሆናል።+
10 “ከጌባ+ አንስቶ ከኢየሩሳሌም በስተ ደቡብ እስካለችው እስከ ሪሞን+ ድረስ መላው ምድር እንደ አረባ+ ይሆናል፤ ኢየሩሳሌም በቀድሞ ስፍራዋ ላይ ትነሳለች፤ የሰዎችም መኖሪያ ትሆናለች፤+ ደግሞም ከቢንያም በር+ አንስቶ እስከ መጀመሪያው በርና እስከ ማዕዘን በር ድረስ ያለው ስፍራ ሁሉ እንዲሁም ከሃናንኤል ማማ+ አንስቶ እስከ ንጉሡ የወይን መጭመቂያዎች* ድረስ ያለው ስፍራ ሁሉ ሰው ይኖርበታል። 11 በከተማዋም ውስጥ ሰዎች ይኖራሉ፤ ከእንግዲህም ጥፋት እንዲደርስባት አትረገምም፤+ ደግሞም ኢየሩሳሌም ሰዎች ያለስጋት የሚኖሩባት ቦታ ትሆናለች።+
12 “ይሖዋ ኢየሩሳሌምን የሚወጉ ሕዝቦችን ሁሉ የሚቀስፍበት መቅሰፍት ይህ ነው፦+ በእግራቸው ቆመው እያለ ሥጋቸው ይበሰብሳል፤ ዓይኖቻቸውም በጉድጓዶቻቸው ውስጥ ይበሰብሳሉ፤ ምላሳቸውም በአፋቸው ውስጥ ይበሰብሳል።
13 “በዚያ ቀን ከይሖዋ ዘንድ የመጣ ሽብር በመካከላቸው ይሰራጫል፤ እያንዳንዱም ሰው የባልንጀራውን እጅ ይይዛል፤ እጁንም በባልንጀራው እጅ ላይ ያነሳል።*+ 14 ይሁዳም ራሱ በኢየሩሳሌም በሚደረገው ውጊያ ይካፈላል፤ በዙሪያዋም ያሉ ብሔራት ሁሉ ሀብት ይኸውም ወርቅ፣ ብርና ልብስ በብዛት ይሰበሰባል።+
15 “በየሰፈሩ ባሉት ፈረሶች፣ በቅሎዎች፣ ግመሎች፣ አህዮችና መንጎች ሁሉ ላይ ተመሳሳይ መቅሰፍት ይወርዳል።
16 “በኢየሩሳሌም ላይ ከተነሱት ብሔራት ሁሉ የሚተርፉት ሰዎች በሙሉ ለንጉሡ ለሠራዊት ጌታ ለይሖዋ ለመስገድና*+ የዳስ* በዓልን ለማክበር+ በየዓመቱ ይወጣሉ።+ 17 ይሁንና ከምድር ብሔራት መካከል ለንጉሡ ለሠራዊት ጌታ ለይሖዋ ለመስገድ ወደ ኢየሩሳሌም የማይወጡ ቢኖሩ ዝናብ አይዘንብላቸውም።+ 18 የግብፅ ሰዎች ባይወጡና ወደ ከተማዋ ባይገቡ ዝናብ አይዘንብላቸውም። እንዲያውም ይሖዋ የዳስ በዓልን ለማክበር ባልመጡት ብሔራት ላይ በሚያመጣቸው መቅሰፍቶች ይቀሰፋሉ። 19 ግብፅ ለፈጸመችው ኃጢአትና የዳስ በዓልን ለማክበር ያልወጡት ብሔራት ሁሉ ለሠሩት ኃጢአት ይህ ቅጣት ይደርስባቸዋል።
20 “በዚያ ቀን በፈረሶቹ ቃጭል ላይ ‘ቅድስና የይሖዋ ነው!’ ተብሎ ይጻፋል።+ በይሖዋ ቤት ያሉት ድስቶች+ በመሠዊያው ፊት እንዳሉት ሳህኖች+ ይሆናሉ። 21 በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ያሉ ድስቶች በሙሉ ቅዱስና ለሠራዊት ጌታ ለይሖዋ የተወሰኑ ይሆናሉ፤ መሥዋዕት የሚያቀርቡትም ሁሉ ገብተው የተወሰኑትን ድስቶች ለመቀቀያ ይጠቀሙባቸዋል። በዚያ ቀን በሠራዊት ጌታ በይሖዋ ቤት ዳግመኛ ከነአናዊ* አይገኝም።”+
“ይሖዋ አስታውሷል” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “ተመለሱ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።
ቃል በቃል “ከክብር በኋላ።”
የመጀመሪያው ጽሑፍ “የዓይኔን ብሌን” የሚል ነበር። ሆኖም ሶፌሪም በመባል የሚታወቁት ጸሐፍት “የዓይኑን ብሌን” ብለው ቀየሩት።
ቃል በቃል “ሥጋ ሁሉ።”
ወይም “እነሆ፣ በደልህን።”
ወይም “የክት ልብስ ትለብሳለህ።”
ወይም “በቅጥር ግቢዎቼ ላይ ኃላፊ ትሆናለህ፤ ትጠብቃለህ።”
ወይም “ሜዳ።”
ወይም “ከላይ የሚቀመጠውን ድንጋይ።”
ወይም “የጥቂቱን ነገር ቀን።”
ቃል በቃል “ድንጋዩን፣ ቆርቆሮውን።”
ብዙ ፍሬ የያዙትን የዛፉን ቅርንጫፎች ያመለክታል።
አንድ ክንድ 44.5 ሴንቲ ሜትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ቃል በቃል “ኢፍ።” ይህም አንድ ኢፍ ለመለካት የሚያገለግልን መስፈሪያ ወይም ቅርጫት ያመለክታል። አንድ ኢፍ 22 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ባለ ረጃጅም እግር ትልቅ አሞራ።
ባቢሎንን ያመለክታል።
ወይም “ተዘጋጅተው፤ ቸኩለው።”
ወይም “ታላቅ አክሊል።”
ገዢና ካህን ሆኖ በሚጫወተው ሚና መካከል ማለት ነው።
ወይም “ታላቁ አክሊልም።”
ወይም “ማስታወሻ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።
ወይም “ቤተ መቅደስ።”
ወይም “ወላጅ አልባ የሆነውን ልጅ።”
“እንደ ጠንካራ ድንጋይ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “መመሪያና፤ ትምህርትና።”
ወይም “የታማኝነት።”
ቃል በቃል “ከቀናት ብዛት የተነሳ።”
ወይም “ፀሐይ ከምትወጣበት አገርና ፀሐይ ከምትጠልቅበት አገር።”
ወይም “በታማኝነትና።”
ወይም “አይዟችሁ።”
ወይም “አይዟችሁ።”
ወይም “የልብስ ዘርፍ።”
ቃል በቃል “ማረፊያ ቦታው።”
ወይም “ምሽግ።”
“ባሕሩ ላይ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “ሺክ።” የነገድ አለቃ የሆነ ሰው “ሺክ” ተብሎ ይጠራ ነበር።
ወይም “እንደ ጠባቂ ጦር እሰፍራለሁ።”
ወይም “ጨቋኝ።”
የሕዝቡን ጉስቁልና እንደተመለከተ መግለጹ ሳይሆን አይቀርም።
ወይም “ድል አድራጊም ነው፤ ደግሞም ድኗል።”
ወይም “በተባዕት አህያ።”
ኤፍራጥስን ያመለክታል።
ቃል በቃል “እረግጠዋለሁና።”
እንደ ፍላጻ አደርገዋለሁ ማለት ነው።
ወይም “በዘውድ።”
ወይም “የቤት ውስጥ አማልክት፤ ጣዖታት።”
ወይም “ምትሃታዊ ነገር፤ አስማታዊ ነገር።”
ቃል በቃል “አውራ ፍየሎች።”
ቃል በቃል “የማዕዘን ማማ።” ወሳኝ የሆነን ወይም ትልቅ ቦታ የሚሰጠውን ሰው ያመለክታል፤ አለቃ።
ቃል በቃል “ማንጠልጠያና።” ድጋፍ የሚሰጥን ሰው ያመለክታል፤ ገዢ።
ወይም “አሠሪዎች።”
ወይም “ነፍሴ እነሱን መታገሥ ስላልቻለችና።”
ወይም “የእነሱም ነፍስ እኔን ስለተጸየፈችኝ።”
ቃል በቃል “መዘኑልኝ።”
ቃል በቃል “ይጨልማል።”
ወይም “እስትንፋስ።”
ወይም “ጎድጓዳ ሳህን።”
ወይም “ለመሸከም የሚያስቸግር።”
ቃል በቃል “ሺኮች።” የነገድ አለቃ የሆነ ሰው “ሺክ” ተብሎ ይጠራ ነበር።
ወይም “በተገቢው ቦታዋ።”
ወይም “የዳዊት ቤት ግርማና።”
ወይም “ግርማ።”
ወይም “እጅግ ደካማ የሆነው።”
ቃል በቃል “በእጆችህ መካከል።” በደረቱ ወይም በጀርባው ላይ ማለት ነው።
ወይም “በጎቹም ይበተኑ።”
ወይም “ይሞታል።”
በዘካ 14:2 ላይ የተገለጸችውን ከተማ ያመለክታል።
ወይም “ከፀሐይ መውጫ።”
ቃል በቃል “ባሕሩ።”
ወይም “መንቀሳቀስ ያቅታቸዋል።” በቅዝቃዜ የደረቁ ያህል ይሆናሉ።
ሙት ባሕርን ያመለክታል።
ሜድትራንያንን ያመለክታል።
ወይም “የጭማቂ ማጠራቀሚያዎች።”
ወይም “አንዱም በሌላው ላይ ጥቃት ይሰነዝራል።”
ወይም “ይሖዋን ለማምለክና።”
ወይም “የጊዜያዊ መጠለያ።”
“ነጋዴ” ማለትም ሊሆን ይችላል።