ለቆሮንቶስ ሰዎች የተጻፈ የመጀመሪያው ደብዳቤ
1 በአምላክ ፈቃድ የክርስቶስ ኢየሱስ ሐዋርያ+ እንዲሆን ከተጠራው ከጳውሎስና ከወንድማችን ከሶስቴንስ፣ 2 በቆሮንቶስ ለሚገኘው የአምላክ ጉባኤ+ ይኸውም ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር ባላችሁ አንድነት ለተቀደሳችሁ፣+ እንዲሁም የእነሱም ሆነ የእኛ ጌታ የሆነውን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም+ በየስፍራው ሆነው ከሚጠሩ ሁሉ ጋር ቅዱሳን ለመሆን ለተጠራችሁ፦
3 ከአባታችን ከአምላክና ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።
4 በክርስቶስ ኢየሱስ ለእናንተ በሰጠው ጸጋ የተነሳ አምላኬን ሁልጊዜ ስለ እናንተ አመሰግናለሁ፤ 5 ምክንያቱም በሁሉም ነገር ይኸውም በመናገር ችሎታ ሁሉና በእውቀት ሁሉ በክርስቶስ በልጽጋችኋል፤+ 6 ደግሞም ስለ ክርስቶስ የተሰጠው ምሥክርነት+ በእናንተ መካከል በሚገባ ሥር ሰዷል፤ 7 ስለዚህ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ በጉጉት ስትጠባበቁ ማንኛውም ስጦታ ፈጽሞ አይጎድልባችሁም።+ 8 በተጨማሪም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቀን+ ከማንኛውም ክስ ነፃ መሆን እንድትችሉ እስከ መጨረሻው ያጸናችኋል። 9 ከልጁ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ* የጠራችሁ አምላክ ታማኝ ነው።+
10 እንግዲህ ወንድሞች፣ ሁላችሁም ንግግራችሁ አንድ እንዲሆንና በመካከላችሁ መከፋፈል እንዳይኖር፣+ ከዚህ ይልቅ በአስተሳሰብም ሆነ በዓላማ ፍጹም አንድነት እንዲኖራችሁ+ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አጥብቄ አሳስባችኋለሁ። 11 ወንድሞቼ ሆይ፣ የቀሎኤ ቤተሰብ አባላት የሆኑ አንዳንዶች በመካከላችሁ አለመግባባት እንዳለ ነግረውኛል። 12 ይኸውም እያንዳንዳችሁ “እኔ የጳውሎስ ነኝ፣” “እኔ ግን የአጵሎስ+ ነኝ፣” “እኔ ደግሞ የኬፋ* ነኝ፣” “እኔ የክርስቶስ ነኝ” ትላላችሁ። 13 ታዲያ የክርስቶስ ጉባኤ ተከፋፍሏል ማለት ነው? ጳውሎስ ለእናንተ ሲል በእንጨት ላይ ተሰቅሏል እንዴ? ወይስ የተጠመቃችሁት በጳውሎስ ስም ነው? 14 ከቀርስጶስና+ ከጋይዮስ+ በስተቀር ከእናንተ አንዳችሁንም ባለማጥመቄ አምላክን አመሰግናለሁ፤ 15 በመሆኑም ከእናንተ መካከል በእኔ ስም እንደተጠመቀ ሊናገር የሚችል ማንም የለም። 16 እርግጥ የእስጢፋናስን+ ቤተሰብም አጥምቄአለሁ። ከእነዚህ ሌላ ግን ያጠመቅኩት ሰው መኖሩን አላስታውስም። 17 ክርስቶስ የላከኝ እንዳጠምቅ ሳይሆን ምሥራቹን እንዳውጅ ነው፤+ ደግሞም የክርስቶስ የመከራ እንጨት* ከንቱ እንዳይሆን ምሥራቹን የማውጀው በንግግር ጥበብ* አይደለም።
18 ስለ መከራው እንጨት* የሚነገረው መልእክት ወደ ጥፋት እያመሩ ላሉት ሞኝነት፣+ ወደ መዳን በሚወስደው ጎዳና ላይ ላለነው ለእኛ ግን የአምላክ ኃይል መገለጫ ነው።+ 19 “የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ፤ የሊቃውንትንም ማስተዋል ወዲያ እጥላለሁ” ተብሎ ተጽፏልና።+ 20 የዚህ ሥርዓት* ጥበበኞች የት አሉ? ጸሐፍትስ* የት አሉ? ተሟጋቾችስ የት አሉ? አምላክ የዓለምን ጥበብ ሞኝነት አላደረገም? 21 ዓለም በራሱ ጥበብ+ አምላክን ሊያውቀው ስላልቻለ+ አምላክ በጥበቡ፣ እንደ ሞኝነት በሚቆጠረውና+ እየተሰበከ ባለው መልእክት አማካኝነት የሚያምኑትን ሰዎች ለማዳን መርጧል።
22 አይሁዳውያን ተአምራዊ ምልክቶች ማየት ይፈልጋሉ፤+ ግሪካውያን ደግሞ ጥበብን ይሻሉ፤ 23 እኛ ግን በእንጨት ላይ የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁዳውያን መሰናክል ለአሕዛብ ደግሞ ሞኝነት ነው።+ 24 ይሁን እንጂ ክርስቶስ ለተጠሩት፣ ለአይሁዳውያንም ሆነ ለግሪካውያን የአምላክ ኃይልና የአምላክ ጥበብ ነው።+ 25 ምክንያቱም የአምላክ ሞኝነት እንደሆነ ተደርጎ የሚታሰበው ነገር ከሰዎች ጥበብ ይበልጣል፤ የአምላክ ድክመት እንደሆነ ተደርጎ የሚታሰበው ነገር ደግሞ ከሰዎች ብርታት ይበልጣል።+
26 ወንድሞች፣ ከራሳችሁ ሁኔታ መረዳት እንደምትችሉት በሰብዓዊ አመለካከት* ጥበበኞች የሆኑ ብዙዎች፣+ ኃያላን የሆኑ ብዙዎች እንዲሁም ከትልቅ ቤተሰብ የተወለዱ ብዙዎች አልተጠሩም፤+ 27 ከዚህ ይልቅ አምላክ ጥበበኞችን ያሳፍር ዘንድ የዓለምን ሞኝ ነገር መረጠ፤ ብርቱውንም ነገር ያሳፍር ዘንድ የዓለምን ደካማ ነገር መረጠ፤+ 28 አምላክ በሰዎች ዘንድ ትልቅ ግምት የሚሰጠውን ነገር ከንቱ ያደርግ ዘንድ በዚህ ዓለም ዝቅ ተደርጎ የሚታየውንና የተናቀውን ነገር ይኸውም ከንቱ መስሎ የሚታየውን ነገር መረጠ፤+ 29 ይህን ያደረገው ማንም ሰው* በአምላክ ፊት እንዳይኩራራ ነው። 30 ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድነት ሊኖራችሁ የቻለው በእሱ ምክንያት ነው፤ ክርስቶስ ደግሞ ለእኛ ከአምላክ የመጣ ጥበብ፣ ጽድቅና+ ቅድስና+ ሆኖልናል፤ እንዲሁም በቤዛው ነፃ አውጥቶናል፤+ 31 ይህም “የሚኩራራ በይሖዋ* ይኩራራ” ተብሎ እንደተጻፈው ነው።+
2 ስለዚህ ወንድሞች፣ የአምላክን ቅዱስ ሚስጥር+ ለእናንተ ለመግለጽ በመጣሁ ጊዜ በንግግር ችሎታ+ ወይም በጥበብ እናንተን ለማስደመም አልሞከርኩም። 2 ከእናንተ ጋር በነበርኩ ጊዜ ትኩረቴን በኢየሱስ ክርስቶስና በእሱ መሰቀል ላይ ብቻ ለማድረግ ወስኜ ነበርና።+ 3 ወደ እናንተም የመጣሁት ደካማ ሆኜ እንዲሁም በፍርሃትና እጅግ በመንቀጥቀጥ ነበር፤ 4 ንግግሬም ሆነ የሰበክሁላችሁ መልእክት የሚያባብል የጥበብ ቃል አልነበረም፤ ከዚህ ይልቅ የአምላክን መንፈስና ኃይል የሚያሳይ ነበር፤+ 5 ይኸውም እምነታችሁ በአምላክ ኃይል ላይ እንጂ በሰው ጥበብ ላይ የተመሠረተ እንዳይሆን ነው።
6 በመሆኑም በጎለመሱት+ መካከል ስለ ጥበብ እንናገራለን፤ ሆኖም የምንናገረው የዚህን ሥርዓት* ጥበብ ወይም የሚጠፉትን የዚህን ሥርዓት ገዢዎች+ ጥበብ አይደለም። 7 ከዚህ ይልቅ የምንናገረው በቅዱስ ሚስጥር+ የተገለጠውን የአምላክ ጥበብ ይኸውም አምላክ ለእኛ ክብር ከዘመናት በፊት* አስቀድሞ የወሰነውን የተሰወረ ጥበብ ነው። 8 ይህን ጥበብ ከዚህ ሥርዓት* ገዢዎች መካከል አንዳቸውም አላወቁትም፤+ ቢያውቁትማ ኖሮ ታላቅ ክብር ያለውን ጌታ ባልሰቀሉት* ነበር። 9 ይሁንና “አምላክ ለሚወዱት ያዘጋጃቸውን ነገሮች ዓይን አላየም፣ ጆሮም አልሰማም፣ የሰውም ልብ አላሰበም” ተብሎ እንደተጻፈው ነው።+ 10 አምላክ እነዚህን ነገሮች በመንፈሱ+ አማካኝነት የገለጠው ለእኛ ነውና፤+ ምክንያቱም መንፈስ ሁሉንም ነገሮች አልፎ ተርፎም የአምላክን ጥልቅ ነገሮች ይመረምራል።+
11 ከሰዎች መካከል በአንድ ሰው ውስጥ ያለውን ነገር በውስጡ ካለው የሰውየው መንፈስ በቀር ማን ሊያውቅ ይችላል? በተመሳሳይም በአምላክ ውስጥ ያለውን ነገር ከአምላክ መንፈስ በቀር ማንም አያውቅም። 12 እኛ አምላክ በደግነት የሰጠንን ነገሮች ማወቅ እንድንችል ከአምላክ የሆነውን መንፈስ+ ተቀበልን እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም። 13 ደግሞም እነዚህን ነገሮች እንናገራለን፤ የምንናገረው ግን ከሰው ጥበብ+ በተማርነው ቃል አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ መንፈሳዊ ጉዳዮችን በመንፈሳዊ ቃል ስናብራራ* ከመንፈስ በተማርነው ቃል እንናገራለን።+
14 ዓለማዊ ሰው ግን ከአምላክ መንፈስ የሆኑትን ነገሮች አይቀበልም፤ እንዲህ ያሉት ነገሮች ለእሱ ሞኝነት ናቸውና፤ በመንፈስ የሚመረመሩ ስለሆኑም ሊረዳቸው አይችልም። 15 ይሁን እንጂ መንፈሳዊ ሰው ሁሉንም ነገር ይመረምራል፤+ እሱ ራሱ ግን በማንም ሰው አይመረመርም። 16 “ያስተምረው ዘንድ የይሖዋን* አስተሳሰብ ያወቀ ማን ነው?” ተብሏልና፤+ እኛ ግን የክርስቶስ አስተሳሰብ አለን።+
3 በመሆኑም ወንድሞች፣ ከክርስቶስ ጋር በተያያዘ ገና ሕፃናት+ እንደሆኑ እንደ ሥጋውያን ሰዎች እንጂ እንደ መንፈሳውያን ሰዎች+ ላነጋግራችሁ አልቻልኩም። 2 ጠንካራ ስላልነበራችሁ ወተት እንጂ ጠንካራ ምግብ አልመገብኳችሁም። አሁንም ቢሆን ገና አልጠነከራችሁም፤+ 3 ደግሞም ገና ሥጋውያን ናችሁ።+ ቅናትና ጠብ በመካከላችሁ ስላለ ሥጋውያን መሆናችሁ፣+ ደግሞም በዓለም እንዳሉ ሰዎች መመላለሳችሁ አይደለም? 4 አንዱ “እኔ የጳውሎስ ነኝ፣” ሌላው ደግሞ “እኔ የአጵሎስ+ ነኝ” ሲል እንደ ማንኛውም ሰው መሆናችሁ አይደለም?
5 ለመሆኑ አጵሎስ ምንድን ነው? ጳውሎስስ ምንድን ነው? ጌታ የሰጣቸውን ሥራ የሚያከናውኑ አገልጋዮች+ ናቸው፤ እናንተም አማኞች የሆናችሁት በእነሱ አማካኝነት ነው። 6 እኔ ተከልኩ፤+ አጵሎስ አጠጣ፤+ ያሳደገው ግን አምላክ ነው፤ 7 ስለዚህ ምስጋና የሚገባው የሚያሳድገው አምላክ እንጂ የሚተክለውም ሆነ የሚያጠጣው አይደለም።+ 8 የሚተክለውም ሆነ የሚያጠጣው በኅብረት የሚሠሩ ናቸው፤* ሆኖም እያንዳንዱ ሰው እንደ ሥራው መጠን የራሱን ወሮታ ይቀበላል።+ 9 እኛ ከአምላክ ጋር አብረን የምንሠራ ነንና። እናንተ በመልማት ላይ ያለ የአምላክ እርሻ ናችሁ፤ የአምላክ ሕንፃ ናችሁ።+
10 በተሰጠኝ የአምላክ ጸጋ መሠረት በሙያው እንደተካነ ግንበኛ* እኔ መሠረት ጣልኩ፤+ ሌላው ደግሞ በዚያ ላይ ይገነባል። ሆኖም እያንዳንዱ በዚያ ላይ እንዴት እንደሚገነባ በጥንቃቄ ሊያስብ ይገባል። 11 ማንም ሰው ከተጣለው መሠረት ሌላ አዲስ መሠረት መጣል አይችልምና፤ ይህም መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።+ 12 ማንም በዚህ መሠረት ላይ በወርቅ፣ በብር፣ በከበሩ ድንጋዮች፣ በእንጨት፣ በሣር ወይም በአገዳ ቢገነባ 13 የፈተናው ቀን ሲመጣ የእያንዳንዱ ሥራ ይገለጣል፤ እሳቱ+ ሁሉንም ነገር ይገልጣልና፤ እንዲሁም እያንዳንዱ ሰው ምን ዓይነት ግንባታ እንዳከናወነ እሳቱ ራሱ ፈትኖ ያሳያል። 14 ማንም በመሠረቱ ላይ የገነባው ነገር ቢጸናለት ወሮታ ያገኛል፤ 15 ይሁንና ማንም ሰው የሠራው ሥራ ቢቃጠል ኪሳራ ይደርስበታል፤ እሱ ግን ይተርፋል፤ ሆኖም በእሳት ውስጥ አልፎ የመትረፍ ያህል ይሆናል።
16 እናንተ ራሳችሁ የአምላክ ቤተ መቅደስ+ እንደሆናችሁና የአምላክ መንፈስ በእናንተ ውስጥ እንደሚያድር አታውቁም?+ 17 ማንም የአምላክን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ አምላክ ያፈርሰዋል፤ የአምላክ ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፤ ቤተ መቅደሱም እናንተ ናችሁ።+
18 ማንም ራሱን አያታል፤ ከእናንተ መካከል ማንም በዚህ ሥርዓት* ጥበበኛ እንደሆነ ቢያስብ፣ ጥበበኛ መሆን ይችል ዘንድ ሞኝ ይሁን። 19 ምክንያቱም የዚህ ዓለም ጥበብ በአምላክ ፊት ሞኝነት ነው፤ “ጥበበኞችን በራሳቸው ተንኮል ይይዛቸዋል” ተብሎ ተጽፏልና።+ 20 ደግሞም “ይሖዋ* የጥበበኞች ሐሳብ ከንቱ እንደሆነ ያውቃል” ተብሏል።+ 21 በመሆኑም ማንም በሰዎች አይኩራራ፤ ሁሉም ነገር የእናንተ ነውና፤ 22 ጳውሎስም ቢሆን አጵሎስም ቢሆን ኬፋም*+ ቢሆን ዓለምም ቢሆን ሕይወትም ቢሆን ሞትም ቢሆን አሁን ያሉት ነገሮችም ቢሆኑ የሚመጡትም ነገሮች ቢሆኑ ሁሉም ነገር የእናንተ ነው፤ 23 እናንተም የክርስቶስ ናችሁ፤+ ክርስቶስ ደግሞ የአምላክ ነው።
4 እንግዲህ ሰው እኛን የክርስቶስ አገልጋዮችና* የአምላክ ቅዱስ ሚስጥር በአደራ የተሰጠን መጋቢዎች እንደሆን አድርጎ ሊቆጥረን ይገባል።+ 2 በዚህ ረገድ መጋቢዎች ታማኝ ሆነው መገኘት ይጠበቅባቸዋል። 3 በእናንተም ሆነ በሰዎች ሸንጎ* ብመረመር ለእኔ ምንም ትርጉም የለውም። እኔም እንኳ ራሴን አልመረምርም። 4 ምክንያቱም ሕሊናዬ በሁሉም ነገር ንጹሕ ነው። ሆኖም ይህ ጻድቅ መሆኔን ያረጋግጣል ማለት አይደለም፤ እኔን የሚመረምረኝ ይሖዋ* ነው።+ 5 ስለዚህ ጊዜው ከመድረሱ በፊት በምንም ነገር ላይ አትፍረዱ፤+ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ጠብቁ። እሱ በጨለማ ውስጥ የተሰወረውን ነገር ወደ ብርሃን ያወጣዋል፤ እንዲሁም በልብ ውስጥ ያለውን ሐሳብ ይገልጣል፤ በዚያን ጊዜ እያንዳንዱ ሰው ከአምላክ ምስጋናውን ይቀበላል።+
6 እንግዲህ ወንድሞች፣ አንዱን ከሌላው በማስበለጥ እንዳትታበዩ፣+ ለእናንተው ጥቅም ራሴንና አጵሎስን+ ምሳሌ አድርጌ በማቅረብ እነዚህን ነገሮች የተናገርኩት “ከተጻፈው አትለፍ” የሚለውን ደንብ እንድትማሩ ነው። 7 ለመሆኑ አንተን ከሌላው የተለየህ እንድትሆን ያደረገህ ማን ነው? ደግሞስ ያልተቀበልከው ምን ነገር አለ?+ ከተቀበልክ ደግሞ እንዳልተቀበልክ ሆነህ የምትኩራራው ለምንድን ነው?
8 እንግዲህ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ አግኝታችኋል ማለት ነዋ! ባለጠጎች ሆናችኋላ! ያለእኛ ነግሣችኋል+ ማለት ነዋ! እኛም ከእናንተ ጋር መንገሥ እንድንችል ነገሥታት ሆናችሁ መግዛት ጀምራችሁ ቢሆን ምንኛ ደስ ባለኝ ነበር!+ 9 አምላክ እኛን ሐዋርያቱን ሞት እንደተፈረደባቸው+ ሰዎች መጨረሻ ላይ ወደ መድረክ እንድንወጣ ያደረገን ይመስለኛል፤ ምክንያቱም ለዓለም፣ ለመላእክትና ለሰዎች ትርዒት ሆነናል።+ 10 እኛ በክርስቶስ የተነሳ ሞኞች ነን፤+ እናንተ ግን በክርስቶስ የተነሳ ልባሞች ናችሁ፤ እኛ ደካሞች ነን፤ እናንተ ግን ጠንካሮች ናችሁ፤ እናንተ የተከበራችሁ ናችሁ፤ እኛ ግን ተዋርደናል። 11 እስከዚህ ሰዓት ድረስ እየተራብንና+ እየተጠማን፣+ እየተራቆትን፣ እየተደበደብንና*+ ቤት አጥተን እየተንከራተትን እንገኛለን፤ 12 እንዲሁም በገዛ እጃችን እየሠራን እንለፋለን።+ ሲሰድቡን እንባርካለን፤+ ስደት ሲያደርሱብን በትዕግሥት እናሳልፋለን፤+ 13 ስማችንን ሲያጠፉ በለዘበ አንደበት እንመልሳለን፤*+ እስካሁን ድረስ የዓለም ጉድፍና* የሁሉ ነገር ጥራጊ እንደሆንን ተደርገን እንታያለን።
14 እነዚህን ነገሮች የምጽፍላችሁ ላሳፍራችሁ ብዬ ሳይሆን እንደተወደዳችሁ ልጆቼ አድርጌ ልመክራችሁ ነው። 15 ምንም እንኳ በክርስቶስ 10,000 ሞግዚቶች* ሊኖሯችሁ ቢችልም ብዙ አባቶች እንደሌሏችሁ ግን የተረጋገጠ ነው፤ በምሥራቹ አማካኝነት በክርስቶስ ኢየሱስ እኔ አባታችሁ ሆኛለሁና።+ 16 ስለዚህ እኔን እንድትመስሉ እለምናችኋለሁ።+ 17 በጌታ ልጄ የሆነውን የምወደውንና ታማኝ የሆነውን ጢሞቴዎስን የምልክላችሁ ለዚህ ነው። እሱም በየስፍራው በሚገኙ ጉባኤዎች ሁሉ ሳስተምር የምጠቀምባቸውን ይኸውም ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር በተያያዘ አገልግሎቴን የማከናውንባቸውን ዘዴዎች* ያሳስባችኋል።+
18 አንዳንዶች እኔ ወደ እናንተ የማልመጣ መስሏቸው በኩራት ተወጥረዋል። 19 ይሁንና ይሖዋ* ከፈቀደ በቅርቡ ወደ እናንተ እመጣለሁ፤ በዚያን ጊዜም እነዚህ በኩራት የተወጠሩ ሰዎች የሚናገሩትን ነገር ሳይሆን የአምላክ ኃይል ይኖራቸው እንደሆነ ማወቅ እፈልጋለሁ። 20 የአምላክ መንግሥት የወሬ ጉዳይ ሳይሆን የኃይል ጉዳይ ነውና። 21 ለመሆኑ የትኛው ይሻላችኋል? ዱላ+ ይዤ ልምጣ ወይስ በፍቅርና በገርነት መንፈስ ልምጣ?
5 በመካከላችሁ የፆታ ብልግና*+ እንደተፈጸመ ይወራል፤ እንዲህ ዓይነቱ ብልግና* ደግሞ በአሕዛብ መካከል እንኳ ታይቶ አይታወቅም፤ ከአባቱ ሚስት ጋር የሚኖር ሰው አለ ተብሏል።+ 2 ታዲያ በዚህ ትኩራራላችሁ? ይልቁንም በዚህ ማዘንና+ ድርጊቱን የፈጸመውን ሰው ከመካከላችሁ ማስወጣት አይገባችሁም?+ 3 ምንም እንኳ እኔ በአካል ከእናንተ ጋር ባልሆንም በመንፈስ ከእናንተ ጋር ነኝ፤ ደግሞም እንዲህ ያለ ድርጊት በፈጸመው ሰው ላይ አብሬያችሁ ያለሁ ያህል ሆኜ ፈርጄበታለሁ። 4 በጌታችን በኢየሱስ ስም አንድ ላይ በምትሰበሰቡበት ጊዜ እኔም በጌታችን በኢየሱስ ኃይል በመንፈስ ከእናንተ ጋር እንደምሆን በመገንዘብ 5 እንዲህ ያለውን ሰው ለሰይጣን አሳልፋችሁ ልትሰጡት ይገባል፤+ ይህም እሱ በጉባኤው ላይ ያሳደረው መጥፎ ተጽዕኖ እንዲወገድና* የጉባኤው መንፈስ በጌታ ቀን ባለበት ሁኔታ እንዲቀጥል ነው።+
6 መመካታችሁ መልካም አይደለም። ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ እንደሚያቦካው አታውቁም?+ 7 አዲስ ሊጥ እንድትሆኑ አሮጌውን እርሾ አስወግዱ፤ ምክንያቱም የፋሲካችን በግ+ የሆነው ክርስቶስ ስለተሠዋ+ ከእርሾ ነፃ ናችሁ። 8 ስለዚህ በዓሉን+ በአሮጌ እርሾ እንዲሁም በክፋትና በኃጢአት እርሾ ሳይሆን እርሾ በሌለበት በቅንነትና በእውነት ቂጣ እናክብር።
9 ከሴሰኞች* ጋር መግጠማችሁን እንድትተዉ* በደብዳቤዬ ላይ ጽፌላችሁ ነበር፤ 10 እንዲህ ስል ግን በአጠቃላይ ከዚህ ዓለም+ ሴሰኞች፣* ስግብግብ ሰዎች፣ ቀማኞች ወይም ጣዖት አምላኪዎች ጋር አትገናኙ ማለቴ አይደለም። እንዲህ ቢሆንማ ኖሮ ጨርሶ ከዓለም መውጣት ያስፈልጋችሁ ነበር።+ 11 አሁን ግን የጻፍኩላችሁ፣ ወንድም ተብሎ እየተጠራ ሴሰኛ* ወይም ስግብግብ+ ወይም ጣዖት አምላኪ ወይም ተሳዳቢ ወይም ሰካራም+ ወይም ቀማኛ+ ከሆነ ማንኛውም ሰው ጋር መግጠማችሁን እንድትተዉ*+ አልፎ ተርፎም እንዲህ ካለው ሰው ጋር ምግብ እንኳ እንዳትበሉ ነው። 12 በውጭ ባሉ* ሰዎች ላይ የምፈርደው እኔ ምን አግብቶኝ ነው? በውስጥ ባሉት ሰዎች ላይ እናንተ አትፈርዱም? 13 በውጭ ባሉት ላይ አምላክ ይፈርዳል።+ “ክፉውን ሰው ከመካከላችሁ አስወግዱት።”+
6 ከእናንተ መካከል አንዱ ከሌላው ጋር የሚከራከርበት ጉዳይ ቢኖረው፣+ ጉዳዩን በቅዱሳን ፊት በማቅረብ ፋንታ በዓመፀኛ ሰዎች ፊት ለማቅረብ ፍርድ ቤት ለመሄድ እንዴት ይደፍራል? 2 ወይስ ቅዱሳን በዓለም ላይ እንደሚፈርዱ አታውቁም?+ ታዲያ እናንተ በዓለም ላይ የምትፈርዱ ከሆነ በጣም ተራ የሆኑ ጉዳዮችን ለመዳኘት አትበቁም? 3 በመላእክት ላይ እንኳ እንደምንፈርድ አታውቁም?+ ታዲያ በአሁኑ ሕይወት በሚያጋጥሙ ጉዳዮች ላይ ለምን አትፈርዱም? 4 ደግሞስ በአሁኑ ሕይወት የሚያጋጥሙ ዳኝነት የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ካሉ+ ጉባኤው የሚንቃቸው ሰዎች እንዲዳኙት ታደርጋላችሁ? 5 ይህን የምለው ኀፍረት እንዲሰማችሁ ብዬ ነው። ወንድሞቹን መዳኘት የሚችል አንድ እንኳ ጥበበኛ ሰው በመካከላችሁ የለም? 6 አንድ ወንድም ሌላውን ወንድም ፍርድ ቤት ይወስዳል፤ ያውም የማያምኑ ሰዎች ፊት!
7 እንግዲህ እርስ በርስ ተካስሳችሁ ፍርድ ቤት መሄዳችሁ ለእናንተ ትልቅ ሽንፈት ነው። ከዚህ ይልቅ እናንተ ራሳችሁ ብትበደሉ አይሻልም?+ ደግሞስ እናንተ ራሳችሁ ብትታለሉ አይሻልም? 8 እናንተ ግን ትበድላላችሁ እንዲሁም ታታልላላችሁ፤ ያውም የገዛ ወንድሞቻችሁን!
9 ወይስ ዓመፀኞች የአምላክን መንግሥት እንደማይወርሱ አታውቁም?+ አትታለሉ፤ ሴሰኞችም*+ ሆኑ ጣዖት አምላኪዎች+ ወይም አመንዝሮች+ ወይም ቀላጮች*+ ወይም ግብረ ሰዶማውያን*+ 10 ወይም ሌቦች ወይም ስግብግቦች+ ወይም ሰካራሞች+ ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ቀማኞች የአምላክን መንግሥት አይወርሱም።+ 11 አንዳንዶቻችሁም እንደዚህ ነበራችሁ። ሆኖም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስምና በአምላካችን መንፈስ ታጥባችሁ ነጽታችኋል፣+ ተቀድሳችኋል+ እንዲሁም ጻድቃን ተብላችኋል።+
12 ሁሉም ነገር ተፈቅዶልኛል፤ ሆኖም ሁሉም ነገር ይጠቅማል ማለት አይደለም።+ ሁሉም ነገር ተፈቅዶልኛል፤ ሆኖም ለምንም ነገር ተገዢ መሆን አልሻም። 13 ምግብ ለሆድ፣ ሆድም ለምግብ ነው፤ አምላክ ግን ሁለቱንም ያጠፋቸዋል።+ አካል ለጌታ ነው እንጂ ለፆታ ብልግና* አይደለም፤+ ጌታ ደግሞ ለአካል ነው። 14 ይሁን እንጂ አምላክ በኃይሉ+ አማካኝነት ጌታን እንዳስነሳው+ እኛንም ከሞት ያስነሳናል።+
15 ሰውነታችሁ የክርስቶስ አካል ክፍል እንደሆነ አታውቁም?+ ታዲያ የክርስቶስ አካል ክፍል የሆነውን ወስጄ ከዝሙት አዳሪ ጋር ላጣምረው? በፍጹም! 16 ከዝሙት አዳሪ ጋር የሚጣመር ሁሉ ከእሷ ጋር አንድ አካል እንደሚሆን አታውቁም? አምላክ “ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” ብሏልና።+ 17 ሆኖም ከጌታ ጋር የተቆራኘ ሁሉ በመንፈስ ከእሱ ጋር አንድ ነው።+ 18 ከፆታ ብልግና* ሽሹ!+ አንድ ሰው የሚፈጽመው ሌላ ኃጢአት ሁሉ ከአካሉ ውጭ ነው፤ የፆታ ብልግና የሚፈጽም ሁሉ ግን በራሱ አካል ላይ ኃጢአት እየሠራ ነው።+ 19 የእናንተ አካል ከአምላክ ለተቀበላችሁት፣ በውስጣችሁ ላለው መንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ+ እንደሆነ አታውቁም?+ በተጨማሪም እናንተ የራሳችሁ አይደላችሁም፤+ 20 በዋጋ ተገዝታችኋልና።+ ስለዚህ በሰውነታችሁ+ አምላክን አክብሩ።+
7 በደብዳቤያችሁ ላይ ያነሳችኋቸውን ጥያቄዎች በተመለከተ፣ አንድ ወንድ አንዲትን ሴት ባይነካ* ይሻላል፤ 2 ይሁንና የፆታ ብልግና* ስለተስፋፋ እያንዳንዱ ወንድ የራሱ ሚስት ትኑረው፤+ እያንዳንዷም ሴት የራሷ ባል ይኑራት።+ 3 ባል ለሚስቱ የሚገባትን ያድርግላት፤ ሚስትም ብትሆን ለባሏ እንደዚሁ ታድርግለት።+ 4 ሚስት በራሷ አካል ላይ ሥልጣን የላትም፤ ሥልጣን ያለው ባሏ ነው፤ በተመሳሳይም ባል በራሱ አካል ላይ ሥልጣን የለውም፤ ሥልጣን ያላት ሚስቱ ናት። 5 አንዳችሁ ለሌላው የሚገባውን አትከልክሉ፤ እንዲህ ማድረግ የምትችሉት በጋራ ስምምነት የተወሰነ ጊዜ ለጸሎት ለማዋል ካሰባችሁ ብቻ ነው፤ ደግሞም ራሳችሁን መግዛት አቅቷችሁ ሰይጣን እንዳይፈታተናችሁ እንደገና አብራችሁ ሁኑ። 6 ይሁን እንጂ ይህን ያልኩት እንዲህ ማድረግ እንደሚቻል ለመግለጽ ነው እንጂ ለማዘዝ አይደለም። 7 ይሁንና ሰው ሁሉ እንደ እኔ ቢሆን ደስ ባለኝ ነበር። ነገር ግን እያንዳንዱ ሰው ከአምላክ ያገኘው የራሱ ስጦታ አለው፤+ አንዱ አንድ ዓይነት ስጦታ ሲኖረው ሌላው ደግሞ ሌላ ዓይነት ስጦታ አለው።
8 ሆኖም ላላገቡና መበለት ለሆኑ እንደ እኔ ሆነው ቢኖሩ የተሻለ ነው እላለሁ።+ 9 ራሳቸውን መግዛት ካቃታቸው ግን ያግቡ፤ በፍትወት ከመቃጠል ማግባት ይሻላልና።+
10 ላገቡት ሰዎች ይህን መመሪያ እሰጣለሁ፤ ይህ መመሪያ የጌታ እንጂ የእኔ አይደለም፤ ሚስት ከባሏ አትለያይ።+ 11 ብትለያይ ግን ሳታገባ ትኑር ወይም ከባሏ ጋር ትታረቅ፤ ባልም ሚስቱን መተው የለበትም።+
12 ለሌሎች ደግሞ እንዲህ እላለሁ፤ ይህን የምለው እኔ እንጂ ጌታ አይደለም፦+ አንድ ወንድም አማኝ ያልሆነች ሚስት ካለችውና አብራው ለመኖር ከተስማማች አይተዋት፤ 13 እንዲሁም አንዲት ሴት አማኝ ያልሆነ ባል ካላትና ባሏ አብሯት ለመኖር ከተስማማ አትተወው። 14 አማኝ ያልሆነ ባል ከሚስቱ ጋር ባለው ዝምድና የተነሳ ተቀድሷልና፤ አማኝ ያልሆነች ሚስትም ከወንድም ጋር ባላት ዝምድና የተነሳ ተቀድሳለች፤ እንዲህ ባይሆን ኖሮ ልጆቻችሁ ርኩሳን በሆኑ ነበር፤ አሁን ግን ቅዱሳን ናቸው። 15 ይሁንና አማኝ ያልሆነው ወገን ለመለየት ከመረጠ ይለይ፤ እንዲህ ያለ ሁኔታ በሚፈጠርበት ጊዜ አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት ምንም ዓይነት ግዴታ የለባቸውም፤ አምላክ የጠራችሁ ለሰላም ነውና።+ 16 አንቺ ሚስት፣ ባልሽን ታድኚው እንደሆነ ምን ታውቂያለሽ?+ ወይስ አንተ ባል፣ ሚስትህን ታድን እንደሆነ ምን ታውቃለህ?
17 ያም ሆነ ይህ እያንዳንዱ ሰው ይሖዋ* በሰጠው ድርሻና አምላክ ሲጠራው በነበረበት ሁኔታ ይመላለስ።+ ለጉባኤዎችም ሁሉ ይህን መመሪያ እሰጣለሁ። 18 አንድ ሰው የተጠራው ተገርዞ እያለ ነው?+ እንዳልተገረዘ ሰው አይሁን። አንድ ሰው የተጠራው ሳይገረዝ ነው? ከሆነ አይገረዝ።+ 19 መገረዝ ምንም ማለት አይደለም፤ አለመገረዝም ቢሆን ምንም ማለት አይደለም፤+ ዋናው ነገር የአምላክን ትእዛዛት መጠበቅ ነው።+ 20 እያንዳንዱ ሰው በተጠራበት ጊዜ የነበረበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን በዚያው ይቀጥል።+ 21 የተጠራኸው ባሪያ እያለህ ነው? ይሄ አያስጨንቅህ፤+ ሆኖም ነፃ መውጣት የምትችል ከሆነ አጋጣሚውን ተጠቀምበት። 22 ባሪያ እያለ የተጠራ ማንኛውም የጌታ ደቀ መዝሙር ነፃ የወጣ የጌታ ሰው ነውና፤+ በተመሳሳይም ነፃ እያለ የተጠራ ሰው የክርስቶስ ባሪያ ነው። 23 በዋጋ ተገዝታችኋል፤+ የሰው ባሪያ መሆናችሁ ይብቃ። 24 ወንድሞች፣ እያንዳንዱ ሰው በተጠራበት ጊዜ የነበረበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን በአምላክ ፊት በዚያው ሁኔታ ይቀጥል።
25 ድንግል የሆኑትን* በተመለከተ ከጌታ የተቀበልኩት ትእዛዝ የለኝም፤ ይሁን እንጂ ጌታ ካሳየኝ ምሕረት የተነሳ እንደ ታማኝ ሰው የራሴን ሐሳብ እሰጣለሁ።+ 26 ስለዚህ አሁን ካለው ችግር አንጻር አንድ ሰው ባለበት ሁኔታ ቢቀጥል የተሻለ ይመስለኛል። 27 በሚስት ታስረሃል? ከሆነ መፈታትን አትሻ።+ ሚስት የሌለህ ነህ? ከሆነ ሚስት ለማግባት አትፈልግ። 28 ይሁንና ብታገባም ኃጢአት ይሆንብሃል ማለት አይደለም። እንዲሁም ድንግል የሆነ ሰው ቢያገባ ኃጢአት ይሆንበታል ማለት አይደለም። ይሁን እንጂ የሚያገቡ ሰዎች በሥጋቸው ላይ መከራ ይደርስባቸዋል። ነገር ግን የእኔ ምኞት ከዚህ እንድትድኑ ነው።
29 ከዚህም በላይ ወንድሞች፣ የቀረው ጊዜ አጭር መሆኑን ልነግራችሁ እወዳለሁ።+ ከእንግዲህ ወዲህ ሚስት ያላቸው እንደሌላቸው ይሁኑ፤ 30 የሚያለቅሱም እንደማያለቅሱ፣ የሚደሰቱም እንደማይደሰቱ፣ የሚገዙም ምንም እንደሌላቸው 31 እንዲሁም በዓለም የሚጠቀሙ ሰዎች ሙሉ በሙሉ እንደማይጠቀሙበት ይሁኑ፤ የዚህ ዓለም ትእይንት እየተለዋወጠ ነውና። 32 በመሆኑም ከጭንቀት ነፃ እንድትሆኑ እፈልጋለሁ። ያላገባ ሰው ጌታን እንዴት ደስ ማሰኘት እንደሚችል በማሰብ ስለ ጌታ ነገር ይጨነቃል። 33 ያገባ ሰው ግን ሚስቱን እንዴት ደስ ማሰኘት እንደሚችል በማሰብ ስለ ዓለም ነገር ይጨነቃል፤+ 34 በመሆኑም ሐሳቡ ተከፋፍሏል። በተጨማሪም ያላገባች ሴትም ሆነች ድንግል በአካሏም ሆነ በመንፈሷ ቅዱስ መሆን ትችል ዘንድ ስለ ጌታ ነገር ትጨነቃለች።+ ይሁን እንጂ ያገባች ሴት ባሏን እንዴት ደስ ማሰኘት እንደምትችል በማሰብ ስለ ዓለም ነገር ትጨነቃለች። 35 ይህን የምለው ግን ለእናንተው ጥቅም ብዬ ነው እንጂ ነፃነት ላሳጣችሁ* ብዬ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ተስማሚ የሆነውን ነገር እንድታደርጉና ሐሳባችሁ ሳይከፋፈል ዘወትር ለጌታ ያደራችሁ እንድትሆኑ ላነሳሳችሁ ብዬ ነው።
36 ይሁንና አንድ ሰው ሳያገባ ቀርቶ ራሱን መቆጣጠር* እንደተሳነው ከተሰማው፣ በተለይ ደግሞ አፍላ የጉርምስና ዕድሜን ያለፈ ከሆነና ማግባቱ የሚመረጥ ከሆነ የፈለገውን ያድርግ፤ ኃጢአት አይሆንበትም። እንዲህ ያሉ ሰዎች ያግቡ።+ 37 ሆኖም አንድ ሰው ልቡ ከቆረጠና ይህን ማድረግ እንደማያስፈልገው ከተሰማው፣ ደግሞም ራሱን መግዛት የሚችል ከሆነና ሳያገባ* ለመኖር በልቡ ከወሰነ መልካም ያደርጋል።+ 38 ስለዚህ የሚያገባ* ሁሉ መልካም ያደርጋል፤ ሳያገባ የሚኖር ሁሉ ደግሞ የተሻለ ያደርጋል።+
39 አንዲት ሚስት ባሏ በሕይወት ባለበት ዘመን ሁሉ የታሰረች ናት።+ ባሏ በሞት ካንቀላፋ ግን በጌታ ብቻ ይሁን እንጂ ከፈለገችው ሰው ጋር ለመጋባት ነፃ ናት።+ 40 እንደ እኔ ከሆነ ግን እንዳለች ብትቀጥል ይበልጥ ደስተኛ ትሆናለች፤ እኔ ደግሞ የአምላክ መንፈስ እንዳለኝ እርግጠኛ ነኝ።
8 ለጣዖቶች የቀረበን ምግብ በተመለከተ፣+ ሁላችንም እውቀት እንዳለን እናውቃለን።+ እውቀት ያስታብያል፤ ፍቅር ግን ያንጻል።+ 2 አንድ ሰው ስለ አንድ ነገር አውቃለሁ ብሎ የሚያስብ ከሆነ ስለዚያ ነገር ማወቅ የሚገባውን ያህል ገና አያውቅም። 3 ሆኖም አንድ ሰው አምላክን የሚወድ ከሆነ በእሱ ዘንድ የታወቀ ነው።
4 ለጣዖቶች የቀረበ ምግብ መብላትን በተመለከተ፣ በዓለም ላይ ጣዖት ከንቱ እንደሆነና+ ከአንዱ በቀር አምላክ እንደሌለ እናውቃለን።+ 5 ብዙ “አማልክት” እና ብዙ “ጌቶች” እንደመኖራቸው መጠን በሰማይም ሆነ በምድር አማልክት ተብለው የሚጠሩ+ ቢኖሩም እንኳ 6 እኛ ግን ሁሉም ነገር ከእሱ የሆነ እኛም ለእሱ የሆን+ አንድ አምላክ+ አብ+ አለን፤ እንዲሁም ሁሉም ነገር በእሱ በኩል የሆነና እኛም በእሱ በኩል የሆን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለ።+
7 ይሁንና ይህ እውቀት ያላቸው ሁሉም ሰዎች አይደሉም።+ አንዳንዶች ግን ቀደም ሲል ጣዖት ያመልኩ ስለነበር የሚበሉት ምግብ ለጣዖት የተሠዋ እንደሆነ አድርገው ያስባሉ፤+ ሕሊናቸው ደካማ ስለሆነም ይረክሳል።+ 8 ይሁን እንጂ ምግብ ከአምላክ ጋር አያቀራርበንም፤+ ባንበላ የሚጎድልብን ነገር የለም፤ ብንበላም የምናተርፈው ነገር የለም።+ 9 ነገር ግን የመምረጥ መብታችሁ፣ ደካማ የሆኑትን በሆነ መንገድ እንዳያሰናክላቸው ተጠንቀቁ።+ 10 አንተ እውቀት ያለህ በጣዖት ቤተ መቅደስ ውስጥ ስትበላ አንድ ሰው ቢያይህ ደካማ የሆነው ይህ ሰው ሕሊናው ለጣዖት የቀረበውን ምግብ እንዲበላ አያደፋፍረውም? 11 እንግዲህ ክርስቶስ የሞተለት ይህ ደካማ የሆነው ወንድምህ በአንተ እውቀት ሳቢያ ጠፋ* ማለት ነው።+ 12 በዚህ መንገድ ወንድሞቻችሁን ስትበድሉና ደካማ የሆነውን ሕሊናቸውን ስታቆስሉ+ በክርስቶስ ላይ ኃጢአት እየሠራችሁ ነው። 13 ስለዚህ ምግብ ወንድሜን የሚያሰናክለው ከሆነ ወንድሜን ላለማሰናከል ስል ከእንግዲህ ፈጽሞ ሥጋ አልበላም።+
9 እኔ ነፃ ሰው አይደለሁም? ሐዋርያስ አይደለሁም? ደግሞስ ጌታችንን ኢየሱስን አላየሁትም?+ እናንተ በጌታ የሥራዬ ውጤት አይደላችሁም? 2 ለሌሎች ሐዋርያ ባልሆን እንኳ ለእናንተ ሐዋርያ እንደሆንኩ የተረጋገጠ ነው! እናንተ የጌታ ሐዋርያ መሆኔን የሚያረጋግጥ ማኅተም ናችሁና።
3 ለሚመረምሩኝ የማቀርበው የመከላከያ መልስ ይህ ነው፦ 4 እኛ የመብላትና የመጠጣት መብት* የለንም እንዴ? 5 እንደ ሌሎቹ ሐዋርያትና እንደ ጌታ ወንድሞች+ እንዲሁም እንደ ኬፋ*+ አማኝ የሆነች ሚስት ይዘን የመዞር መብት የለንም?+ 6 ወይስ ሰብዓዊ ሥራ የመተው መብት የሌለን እኔና በርናባስ+ ብቻ ነን? 7 ለመሆኑ በራሱ ወጪ ወታደር ሆኖ የሚያገለግል ማን ነው? ወይን ተክሎ ፍሬውን የማይበላ ማን ነው?+ ወይስ መንጋ እየጠበቀ ከመንጋው ወተት የተወሰነ ድርሻ የማያገኝ ማን ነው?
8 ይህን የምለው ከሰብዓዊ አመለካከት አንጻር ነው? ሕጉስ ቢሆን እንዲህ አይልም? 9 በሙሴ ሕግ “እህል እያበራየ ያለውን በሬ አፉን አትሰር” ተብሎ ተጽፏልና።+ አምላክ ይህን የተናገረው ስለ በሬዎች ተጨንቆ ነው? 10 እንዲህ ያለው ስለ እኛ በማሰብ አይደለም? እንዲህ ተብሎ የተጻፈው በእርግጥ ስለ እኛ ነው፤ ምክንያቱም አራሹም ሆነ የሚያበራየው ሰው ሥራቸውን የሚያከናውኑት ከምርቱ ድርሻ እንደሚኖራቸው ተስፋ በማድረግ ነው።
11 እኛ በእናንተ መካከል መንፈሳዊ ነገሮች ከዘራን ከእናንተ ሥጋዊ ነገሮች ብናጭድ ትልቅ ነገር መሆኑ ነው?+ 12 ሌሎች የእናንተን ድጋፍ የማግኘት መብት ካላቸው እኛ ከእነሱ የበለጠ መብት የለንም? ይሁንና እኛ በዚህ መብት* አልተጠቀምንም፤+ ከዚህ ይልቅ ስለ ክርስቶስ የሚሰበከውን ምሥራች የሚያደናቅፍ ምንም ነገር ላለመፍጠር ሁሉን ችለን እንኖራለን።+ 13 ቅዱስ አገልግሎት የሚያከናውኑት ሰዎች ከቤተ መቅደስ የሚያገኙትን ምግብ እንደሚመገቡ እንዲሁም ዘወትር በመሠዊያው የሚያገለግሉ ከመሠዊያው የራሳቸውን ድርሻ እንደሚያገኙ አታውቁም?+ 14 በተመሳሳይም ምሥራቹን የሚያውጁ ሰዎች በምሥራቹ አማካኝነት በሚያገኙት ነገር እንዲኖሩ ጌታ አዟል።+
15 ይሁን እንጂ እኔ ከእነዚህ ዝግጅቶች በአንዱም አልተጠቀምኩም።+ እርግጥ ይህን የጻፍኩት እንዲህ ሊደረግልኝ ይገባል ለማለት አይደለም፤ ማንም ሰው የምኮራበትን ነገር ከሚያሳጣኝ ብሞት ይሻለኛልና!+ 16 አሁን ምሥራቹን እየሰበክሁ ብሆንም ለመኩራራት ምክንያት አይሆነኝም፤ እንዲህ የማድረግ ግዴታ ተጥሎብኛልና። እንዲያውም ምሥራቹን ባልሰብክ ወዮልኝ!+ 17 ይህን በፈቃደኝነት ካከናወንኩ ሽልማት አለኝ፤ ይሁንና ሳልወድ ባደርገውም እንኳ የመጋቢነት አደራ ተጥሎብኛል።+ 18 ታዲያ ሽልማቴ ምንድን ነው? ከምሥራቹ ጋር በተያያዘ ሥልጣኔን* አላግባብ እንዳልጠቀምበት ምሥራቹን በምሰብክበት ጊዜ ምሥራቹን ያለክፍያ ማቅረብ ነው።
19 እኔ ከሰው ሁሉ ነፃ ነኝ፤ ሆኖም በተቻለ መጠን ብዙዎችን እማርክ ዘንድ ራሴን ለሁሉ ባሪያ አደረግኩ። 20 አይሁዳውያንን እማርክ ዘንድ ለአይሁዳውያን እንደ አይሁዳዊ ሆንኩ፤+ እኔ ራሴ በሕግ ሥር ባልሆንም እንኳ በሕግ ሥር ያሉትን እማርክ ዘንድ በሕግ ሥር ላሉት በሕግ ሥር እንዳለሁ ሆንኩ።+ 21 በአምላክ ፊት ከሕግ ነፃ ያልሆንኩና በክርስቶስ ፊት በሕግ ሥር ያለሁ ብሆንም እንኳ ሕግ የሌላቸውን እማርክ ዘንድ ሕግ ለሌላቸው ሕግ እንደሌለው ሰው ሆንኩ።+ 22 ደካሞችን እማርክ ዘንድ ለደካሞች ደካማ ሆንኩ።+ በተቻለ መጠን የተወሰኑ ሰዎችን አድን ዘንድ ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ሁሉንም ነገር ሆንኩ። 23 ምሥራቹን ለሌሎች አካፍል ዘንድ ለምሥራቹ ስል ሁሉን ነገር አደርጋለሁ።+
24 በሩጫ ውድድር ሁሉም እንደሚሮጡ፣ ሽልማቱን የሚያገኘው ግን አንዱ ብቻ እንደሆነ አታውቁም? እናንተም ሽልማቱን እንድታገኙ በዚሁ ሁኔታ ሩጡ።+ 25 በውድድር የሚሳተፍ ማንኛውም ሰው* በሁሉም ነገር ራሱን ይገዛል። እነሱ ይህን የሚያደርጉት የሚጠፋውን አክሊል+ ለማግኘት ሲሆን እኛ ግን የማይጠፋውን አክሊል ለማግኘት ነው።+ 26 ስለዚህ እኔ ያለግብ አልሮጥም፤+ ቡጢ የምሰነዝረውም አየር ለመምታት አይደለም፤ 27 ከዚህ ይልቅ ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ እኔ ራሴ በሆነ መንገድ ተቀባይነት እንዳላጣ* ሰውነቴን እየጎሰምኩ*+ እንደ ባሪያ እንዲገዛልኝ አደርገዋለሁ።
10 እንግዲህ ወንድሞች፣ አባቶቻችን ሁሉ ከደመና በታች+ እንደነበሩና ሁሉም በባሕር መካከል እንዳለፉ+ ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ፤ 2 ሁሉም ከሙሴ ጋር በመተባበር በደመናውና በባሕሩ ተጠመቁ፤ 3 ደግሞም ሁሉም አንድ ዓይነት መንፈሳዊ ምግብ ተመገቡ፤+ 4 በተጨማሪም ሁሉም አንድ ዓይነት መንፈሳዊ መጠጥ ጠጡ።+ ይከተላቸው ከነበረው መንፈሳዊ ዓለት ይጠጡ ነበርና፤ ይህም ዓለት ክርስቶስን ያመለክታል።*+ 5 ይሁንና አምላክ በአብዛኞቹ ስላልተደሰተ በምድረ በዳ ወድቀው ቀርተዋል።+
6 እነሱ ጎጂ የሆኑ ነገሮችን እንደተመኙ እኛም እንዳንመኝ እነዚህ ነገሮች ለእኛ ምሳሌ ሆነውልናል።+ 7 “ሕዝቡ ሊበሉና ሊጠጡ ተቀመጡ። ከዚያም ሊጨፍሩ ተነሱ” ተብሎ እንደተጻፈው ከእነሱ አንዳንዶቹ እንዳደረጉት ጣዖት አምላኪዎች አትሁኑ።+ 8 ከእነሱ አንዳንዶቹ የፆታ ብልግና* ፈጽመው ከመካከላቸው 23,000 የሚሆኑት በአንድ ቀን እንደረገፉ እኛም የፆታ ብልግና* አንፈጽም።+ 9 ከእነሱ አንዳንዶቹ ይሖዋን* ተፈታትነው በእባቦች እንደጠፉ እኛም አንፈታተነው።+ 10 በተጨማሪም ከእነሱ አንዳንዶቹ በማጉረምረማቸው+ በአጥፊው እንደጠፉ+ አጉረምራሚዎች አትሁኑ። 11 እነዚህ ነገሮች ምሳሌ ይሆኑ ዘንድ በእነሱ ላይ ደረሱ፤ የተጻፉትም የሥርዓቶቹ ፍጻሜ የደረሰብንን እኛን ለማስጠንቀቅ ነው።+
12 በመሆኑም የቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ።+ 13 በሰው ሁሉ ላይ ከሚደርሰው ፈተና የተለየ ፈተና አልደረሰባችሁም።+ ይሁንና አምላክ ታማኝ ነው፤ ልትሸከሙት ከምትችሉት በላይ ፈተና እንዲደርስባችሁ አይፈቅድም፤+ ከዚህ ይልቅ ፈተናውን በጽናት መቋቋም እንድትችሉ ፈተና ሲደርስባችሁ መውጫ መንገዱን ያዘጋጅላችኋል።+
14 ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ ከጣዖት አምልኮ ሽሹ።+ 15 ይህን የምናገረው ማስተዋል ላላቸው ሰዎች ነው፤ የምናገረው ነገር ትክክል ይሁን አይሁን እናንተ ራሳችሁ ፍረዱ። 16 የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም መቋደስ አይደለም?+ የምንቆርሰውስ ቂጣ ከክርስቶስ አካል መቋደስ አይደለም?+ 17 ምክንያቱም እኛ ብዙ ብንሆንም ቂጣው አንድ ስለሆነ አንድ አካል ነን፤+ ሁላችንም የምንካፈለው ከዚሁ አንድ ቂጣ ነውና።
18 እስቲ ሥጋዊ እስራኤላውያንን ተመልከቱ፦ መሥዋዕቱን የሚበሉት ከመሠዊያው ጋር ተቋዳሾች አይደሉም?+ 19 እንግዲህ ምን እያልኩ ነው? ለጣዖት የተሠዋ ነገር የተለየ ፋይዳ አለው ማለቴ ነው? ወይስ ጣዖት ዋጋ አለው ማለቴ ነው? 20 እንዲህ ማለቴ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ አሕዛብ መሥዋዕት አድርገው የሚያቀርቧቸውን ነገሮች የሚሠዉት ለአምላክ ሳይሆን ለአጋንንት ነው ማለቴ ነው፤+ ከአጋንንት ጋር እንድትተባበሩ ደግሞ አልፈልግም።+ 21 የይሖዋን* ጽዋና የአጋንንትን ጽዋ መጠጣት አትችሉም፤ “ከይሖዋ* ማዕድ”+ እና ከአጋንንት ማዕድ መካፈል አትችሉም። 22 ወይስ ‘ይሖዋን* እያስቀናነው ነው’?+ እኛ ከእሱ ይበልጥ ብርቱዎች ነን እንዴ?
23 ሁሉም ነገር ተፈቅዷል፤ ሆኖም ሁሉም ነገር ይጠቅማል ማለት አይደለም። ሁሉም ነገር ተፈቅዷል፤ ሆኖም ሁሉም ነገር ያንጻል ማለት አይደለም።+ 24 እያንዳንዱ ሰው ምንጊዜም የራሱን ጥቅም ሳይሆን የሌላውን ሰው ጥቅም ይፈልግ።+
25 ከሕሊናችሁ የተነሳ ምንም ጥያቄ ሳታነሱ በሥጋ ገበያ የሚሸጠውን ማንኛውንም ነገር ብሉ፤ 26 “ምድርና በውስጧ ያለው ነገር ሁሉ የይሖዋ* ነውና።”+ 27 አማኝ ያልሆነ ሰው ቢጋብዛችሁና መሄድ ብትፈልጉ ከሕሊናችሁ የተነሳ ምንም ጥያቄ ሳታነሱ የቀረበላችሁን ሁሉ ብሉ። 28 ይሁንና አንድ ሰው “ይህ መሥዋዕት ሆኖ የቀረበ ነው” ቢላችሁ ይህን ለነገራችሁ ሰውና ለሕሊና ስትሉ አትብሉ።+ 29 እንዲህ ስል ስለ ራሳችሁ ሕሊና ሳይሆን ስለ ሌላው ሰው ሕሊና መናገሬ ነው። ነፃነቴ በሌላው ሰው ሕሊና ለምን ይፈረድበት?+ 30 አመስግኜ የምበላ ከሆነ ባመሰገንኩበት ነገር ለምን እነቀፋለሁ?+
31 ስለዚህ ስትበሉም ሆነ ስትጠጡ ወይም ማንኛውንም ነገር ስታደርጉ ሁሉንም ነገር ለአምላክ ክብር አድርጉ።+ 32 ለአይሁዳውያንም ሆነ ለግሪካውያን እንዲሁም ለአምላክ ጉባኤ እንቅፋት አትሁኑ፤+ 33 እኔ ብዙዎች እንዲድኑ የእነሱን እንጂ የራሴን ጥቅም ሳልፈልግ በማደርገው ነገር ሁሉ፣+ ሁሉንም ሰው ለማስደሰት እንደምጥር እናንተም እንዲሁ አድርጉ።+
11 እኔ የክርስቶስን አርዓያ እንደምከተል እናንተም የእኔን አርዓያ ተከተሉ።+
2 በሁሉም ነገር ስለምታስቡኝና ለእናንተ ያስተላለፍኳቸውን ወጎች አጥብቃችሁ ስለያዛችሁ አመሰግናችኋለሁ። 3 ይሁንና የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፣+ የሴትም ራስ ወንድ፣+ የክርስቶስ ራስ ደግሞ አምላክ እንደሆነ እንድታውቁ እወዳለሁ።+ 4 ራሱን ሸፍኖ የሚጸልይ ወይም ትንቢት የሚናገር ወንድ ሁሉ የእሱን ራስ ያዋርዳል፤ 5 ራሷን ሳትሸፍን የምትጸልይ ወይም ትንቢት የምትናገር+ ሴት ሁሉ ደግሞ የእሷን ራስ ታዋርዳለች፤ እንዲህ የምታደርግ ሴት ራሷን እንደተላጨች ሴት ትቆጠራለች። 6 አንዲት ሴት ራሷን የማትሸፍን ከሆነ ፀጉሯን ትቆረጥ፤ ፀጉሯን መቆረጧ ወይም መላጨቷ የሚያሳፍራት ከሆነ ግን ትሸፈን።
7 ወንድ የአምላክ አምሳልና+ ክብር ስለሆነ ራሱን መሸፈን የለበትም፤ ሴት ግን የወንድ ክብር ናት። 8 ሴት ከወንድ ተገኘች እንጂ ወንድ ከሴት አልተገኘምና።+ 9 ከዚህም በተጨማሪ ሴት ለወንድ ተፈጠረች እንጂ ወንድ ለሴት አልተፈጠረም።+ 10 ከዚህ የተነሳም ሆነ ለመላእክት ሲባል ሴት በሥልጣን ሥር መሆኗን የሚያሳይ ምልክት በራሷ ላይ ታድርግ።+
11 ይሁንና በጌታ ተከታዮች ዘንድ ሴት ያለወንድ አትኖርም፤ ወንድም ያለሴት አይኖርም። 12 ሴት ከወንድ እንደተገኘች ሁሉ+ ወንድም የተገኘው በሴት አማካኝነት ነውና፤ ሆኖም ሁሉም ነገሮች የተገኙት ከአምላክ ነው።+ 13 እስቲ እናንተ ራሳችሁ ፍረዱ፦ ሴት ሳትሸፈን ወደ አምላክ ብትጸልይ ተገቢ ይሆናል? 14 ወንድ ፀጉሩን ቢያስረዝም ውርደት እንደሚሆንበት ተፈጥሮ ራሱ እንኳ አያስተምራችሁም? 15 ሴት ግን ፀጉሯን ብታስረዝም ለእሷ ክብር አይደለም? ፀጉሯ የተሰጣት በመሸፈኛ ምትክ ነውና። 16 ይሁን እንጂ ማንም ሰው ሌላ ልማድ መከተል አለብን በሚል ለመከራከር ቢፈልግ እኛም ሆን የአምላክ ጉባኤ ከዚህ የተለየ ልማድ የለንም።
17 ሆኖም ስብሰባችሁ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ስለሚያመዝን እነዚህን መመሪያዎች ስሰጣችሁ ላመሰግናችሁ አልፈልግም። 18 በመጀመሪያ ደረጃ፣ በጉባኤ በምትሰበሰቡበት ጊዜ በመካከላችሁ ክፍፍል እንዳለ እሰማለሁ፤ ደግሞም ይህ በተወሰነ መጠን እውነትነት እንዳለው አምናለሁ። 19 በዚህ ሁኔታ በእናንተ መካከል ኑፋቄዎች ብቅ ማለታቸው አይቀርም፤+ ይህም መሆኑ ከእናንተ መካከል ተቀባይነት የሚያገኙት ሰዎች ተለይተው እንዲታወቁ ያስችላል።
20 አንድ ላይ በምትሰበሰቡበት ጊዜ፣ የምትሰበሰቡት የጌታ ራትን+ ለመብላት ነው ለማለት አያስደፍርም። 21 የጌታ ራትን በምትበሉበት ጊዜ አንዳንዶች አስቀድመው የራሳቸውን ራት ስለሚበሉ አንዱ ይራባል ሌላው ደግሞ ይሰክራል። 22 የምትበሉበትና የምትጠጡበት ቤት የላችሁም? ወይስ የአምላክን ጉባኤ በመናቅ ምንም የሌላቸውን ታሳፍራላችሁ? እንግዲህ ምን ልበላችሁ? ላመስግናችሁ? በዚህ ነገርስ አላመሰግናችሁም።
23 እኔ ከጌታ የተቀበልኩትን ለእናንተ አስተላልፌአለሁና፤ ጌታ ኢየሱስ አልፎ በተሰጠበት ሌሊት+ ቂጣ አንስቶ 24 ካመሰገነ በኋላ ቆርሶ “ይህ ስለ እናንተ የሚሰጠውን ሥጋዬን ያመለክታል።+ ይህን ሁልጊዜ ለመታሰቢያዬ አድርጉት” አለ።+ 25 በተጨማሪም ራት ከበሉ በኋላ ጽዋውን+ አንስቶ ልክ እንደዚሁ አደረገ፤ እንዲህም አለ፦ “ይህ ጽዋ በደሜ+ አማካኝነት የሚመሠረተውን አዲሱን ቃል ኪዳን+ ያመለክታል። ከዚህ ጽዋ በጠጣችሁ ቁጥር ይህን ሁልጊዜ ለመታሰቢያዬ አድርጉት።”+ 26 ይህን ቂጣ በበላችሁና ከዚህ ጽዋ በጠጣችሁ ቁጥር ጌታ እስከሚመጣ ድረስ ሞቱን ታውጃላችሁ።
27 እንግዲህ የማይገባው ሆኖ ሳለ ከቂጣው የሚበላ ወይም ከጌታ ጽዋ የሚጠጣ ከጌታ አካልና ደም ጋር በተያያዘ ተጠያቂ ይሆናል። 28 አንድ ሰው የሚገባው እንደሆነ ለማወቅ በቅድሚያ ራሱን ይመርምር፤+ ቂጣውን መብላትና ጽዋውን መጠጣት የሚችለው ይህን ካደረገ ብቻ ነው። 29 ምክንያቱም አካሉ ምን ትርጉም እንዳለው ሳይገነዘብ የሚበላና የሚጠጣ በራሱ ላይ ፍርድ የሚያመጣበትን ነገር መብላትና መጠጣት ይሆንበታል። 30 ከእናንተ መካከል ብዙዎቹ የተዳከሙትና ታማሚ የሆኑት እንዲሁም ጥቂት የማይባሉት በሞት ያንቀላፉት* በዚህ ምክንያት ነው።+ 31 ሆኖም ራሳችንን መርምረን ብናውቅ ኖሮ ባልተፈረደብን ነበር። 32 ይሁን እንጂ በሚፈረድብን ጊዜ፣ ከዓለም ጋር አብረን እንዳንኮነን+ ሲል ይሖዋ* ይገሥጸናል።+ 33 ስለዚህ ወንድሞቼ፣ ይህን ራት ለመብላት በምትሰበሰቡበት ጊዜ እርስ በርሳችሁ ተጠባበቁ። 34 የምትሰበሰቡት ለፍርድ እንዳይሆን የራበው ሰው ካለ እዚያው ቤቱ ይብላ።+ የቀሩትን ጉዳዮች ግን ስመጣ አስተካክላለሁ።
12 ወንድሞች፣ አሁን ደግሞ ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች+ በሚገባ እንድታውቁ እፈልጋለሁ። 2 አሕዛብ* በነበራችሁበት ጊዜ ድምፅ የሌላቸው ጣዖቶች+ ካሳደሩባችሁ ተጽዕኖ የተነሳ ወደመሯችሁ ቦታ ሁሉ በመሄድ እነሱን ተከትላችሁ ትባዝኑ ነበር። 3 ስለዚህ ይህን እንድታውቁ እወዳለሁ፦ በአምላክ መንፈስ ተመርቶ “ኢየሱስ የተረገመ ነው!” የሚል ማንም የለም፤ እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ካልሆነ በቀር ማንም “ኢየሱስ ጌታ ነው!” ብሎ ሊናገር አይችልም።+
4 ልዩ ልዩ ስጦታዎች አሉ፤ ምንጩ ግን ያው መንፈስ ነው፤+ 5 ልዩ ልዩ አገልግሎቶች አሉ፤+ ሁሉም አገልግሎት የሚቀርበው ግን ለአንድ ጌታ ነው፤ 6 በተጨማሪም ልዩ ልዩ ሥራዎች* አሉ፤ ሆኖም ሁሉም ሰዎች እነዚህን ሁሉ ነገሮች እንዲያከናውኑ የሚያስችለው አንድ አምላክ ብቻ ነው።+ 7 ይሁን እንጂ መንፈስ በእያንዳንዱ ሰው አማካኝነት ጠቃሚ ለሆነ ዓላማ ይገለጣል።+ 8 ለአንዱ በመንፈስ አማካኝነት በጥበብ የመናገር ችሎታ* ይሰጠዋልና፤ ለሌላው ደግሞ በዚያው መንፈስ በእውቀት የመናገር ችሎታ ይሰጠዋል፤ 9 ለሌላው በዚያው መንፈስ እምነት ይሰጠዋል፤+ ለሌላው ደግሞ በዚያው መንፈስ፣ የመፈወስ ስጦታ ይሰጠዋል፤+ 10 እንዲሁም ለሌላው ተአምራት የመሥራት፣+ ለሌላው ትንቢት የመናገር፣ ለሌላው በመንፈስ መሪነት የተነገረን ቃል የመረዳት፣+ ለሌላው በተለያዩ ልሳኖች* የመናገር፣+ ለሌላው ደግሞ ልሳኖችን የመተርጎም ችሎታ ይሰጠዋል።+ 11 ሆኖም ለእያንዳንዱ በግለሰብ ደረጃ እነዚህን ስጦታዎች እንደፈቀደ በማከፋፈል እነዚህን ሁሉ ነገሮች የሚያከናውነው ያው አንድ መንፈስ ነው።
12 አካል አንድ ቢሆንም ብዙ የአካል ክፍሎች እንዳሉትና የዚህ አካል ክፍሎች በሙሉ ብዙ ቢሆኑም አንድ አካል+ እንደሆኑ ሁሉ ክርስቶስም እንደዚሁ ነው። 13 አይሁዳውያንም ሆን ግሪካውያን፣ ባሪያዎችም ሆን ነፃ ሰዎች ሁላችንም አንድ አካል ለመሆን በአንድ መንፈስ ተጠምቀናልና፤ እንዲሁም ሁላችንም አንድ መንፈስ እንድንጠጣ ተሰጥቶናል።
14 አካል በአንድ ብቻ ሳይሆን በብዙ የአካል ክፍሎች የተገነባ ነውና።+ 15 እግር “እኔ እጅ ስላልሆንኩ የአካል ክፍል አይደለሁም” ቢል ይህን በማለቱ የአካል ክፍል መሆኑ አይቀርም። 16 እንዲሁም ጆሮ “እኔ ዓይን ስላልሆንኩ የአካል ክፍል አይደለሁም” ቢል ይህን በማለቱ የአካል ክፍል መሆኑ አይቀርም። 17 አካል በሙሉ ዓይን ቢሆን ኖሮ እንዴት መስማት ይቻል ነበር? አካል በሙሉ ጆሮ ቢሆን ኖሮስ እንዴት ማሽተት ይቻል ነበር? 18 ሆኖም አምላክ እያንዳንዱን የአካል ክፍል እሱ በፈለገው ቦታ መድቦታል።
19 የአካል ክፍሎች ሁሉ አንድ ዓይነት ቢሆኑ ኖሮ ሙሉ አካል ከየት ይገኝ ነበር? 20 አሁን ግን የአካል ክፍሎች ብዙ ቢሆኑም አካል ግን አንድ ነው። 21 ዓይን እጅን “አንተ አታስፈልገኝም” ሊለው አይችልም፤ ወይም ደግሞ ራስ እግርን “አንተ አታስፈልገኝም” ሊለው አይችልም። 22 እንዲያውም ደካማ የሚመስሉት የአካል ክፍሎች በጣም አስፈላጊ ናቸው፤ 23 እምብዛም ክብር የላቸውም ብለን የምናስባቸውን የአካል ክፍሎች የበለጠ ክብር እንሰጣቸዋለን፤+ በመሆኑም የምናፍርባቸውን የአካል ክፍሎች ይበልጥ በክብር እንይዛቸዋለን፤ 24 በአንጻሩ ደግሞ የሚያምሩት የአካል ክፍሎቻችን ምንም አያስፈልጋቸውም። ይሁንና አምላክ ክብር የሚጎድለውን የአካል ክፍል ታላቅ ክብር በማልበስ አካልን ገንብቷል፤ 25 ይህን ያደረገው በአካል መካከል ክፍፍል እንዳይኖር፣ ከዚህ ይልቅ የአካል ክፍሎች በእኩል ደረጃ አንዳቸው ለሌላው አሳቢነት እንዲያሳዩ ነው።+ 26 አንድ የአካል ክፍል ቢሠቃይ ሌሎቹ የአካል ክፍሎች በሙሉ አብረውት ይሠቃያሉ፤+ ወይም አንድ የአካል ክፍል ክብር ቢያገኝ ሌሎቹ የአካል ክፍሎች በሙሉ አብረውት ይደሰታሉ።+
27 እንግዲህ እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ፤+ እያንዳንዳችሁም በግለሰብ ደረጃ የአካሉ ክፍል ናችሁ።+ 28 አምላክ የተለያዩ የአካል ክፍሎችን ይኸውም አንደኛ ሐዋርያትን፣+ ሁለተኛ ነቢያትን፣+ ሦስተኛ አስተማሪዎችን፣+ ከዚያም ተአምር የሚፈጽሙትን፣+ ከዚያም የመፈወስ ስጦታ ያላቸውን፣+ ጠቃሚ አገልግሎት የሚያከናውኑትን፣ የመምራት ችሎታ ያላቸውንና+ በተለያዩ ልሳኖች የሚናገሩትን+ በጉባኤ ውስጥ መድቧል። 29 ሁሉ ሐዋርያት ናቸው? ሁሉስ ነቢያት ናቸው? ሁሉስ አስተማሪዎች ናቸው? ሁሉስ ተአምር ይሠራሉ? 30 ሁሉስ የመፈወስ ስጦታ አላቸው? ሁሉስ በልሳን ይናገራሉ?+ ሁሉስ ተርጓሚዎች ናቸው?+ 31 ይሁንና ብልጫ ያላቸውን ስጦታዎች ለማግኘት ጥረት* ማድረጋችሁን ቀጥሉ።+ ደግሞም ከሁሉ የላቀውን መንገድ አሳያችኋለሁ።+
13 በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ በኃይል እንደሚጮኽ ደወል* ወይም ሲምባል* ሆኛለሁ። 2 የመተንበይ ስጦታ ቢኖረኝ፣ ቅዱስ ሚስጥርን ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ+ እንዲሁም ተራራን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ማንቀሳቀስ የሚያስችል እምነት ቢኖረኝ፣ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ።*+ 3 ሌሎችን ለመመገብ ያለኝን ሁሉ ብሰጥ+ እንዲሁም እኩራራ ዘንድ ሰውነቴን አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ+ ምንም የማገኘው ጥቅም የለም።
4 ፍቅር+ ታጋሽና+ ደግ+ ነው። ፍቅር አይቀናም።+ ጉራ አይነዛም፣ አይታበይም፣+ 5 ጨዋነት የጎደለው ምግባር አያሳይም፣*+ የራሱን ፍላጎት አያስቀድምም፣+ በቀላሉ አይበሳጭም።+ ፍቅር የበደል መዝገብ የለውም።+ 6 ፍቅር በዓመፅ አይደሰትም፤+ ከዚህ ይልቅ ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል። 7 ሁሉን ችሎ ያልፋል፣+ ሁሉን ያምናል፣+ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፣+ ሁሉን ነገር በጽናት ይቋቋማል።+
8 ፍቅር ለዘላለም ይኖራል።* ሆኖም የመተንበይ፣ በልሳን የመናገርም* ሆነ የእውቀት ስጦታ ይቀራል። 9 እውቀታችን ከፊል ነውና፤+ ትንቢት የምንናገረውም በከፊል ነው፤ 10 የተሟላው ሲመጣ ግን ከፊል የሆነው ይቀራል። 11 ልጅ በነበርኩበት ጊዜ እንደ ልጅ እናገር፣ እንደ ልጅ አስብ እንዲሁም እንደ ልጅ አመዛዝን ነበር፤ አሁን ሙሉ ሰው ከሆንኩ በኋላ ግን የልጅነትን ጠባይ ትቻለሁ። 12 አሁን በብረት መስተዋት ብዥ ያለ* ምስል ይታየናል፤ በዚያን ጊዜ ግን ፊት ለፊት የማየት ያህል በግልጽ ይታየናል። አሁን ስለ አምላክ የማውቀው በከፊል ነው፤ በዚያን ጊዜ ግን እሱ እኔን በትክክል የሚያውቀኝን ያህል የተሟላ* እውቀት ይኖረኛል። 13 ይሁን እንጂ እምነት፣ ተስፋ፣ ፍቅር፣ እነዚህ ሦስቱ ይቀጥላሉ፤ ከእነዚህ መካከል የሚበልጠው ግን ፍቅር ነው።+
14 ፍቅርን ተከታተሉ፤ ሆኖም መንፈሳዊ ስጦታዎችን ይልቁንም ትንቢት የመናገር ስጦታን ለማግኘት ጥረት* አድርጉ።+ 2 በልሳን የሚናገር ለአምላክ እንጂ ለሰው አይናገርምና፤ በመንፈስ አማካኝነት ቅዱስ ሚስጥሮችን ቢናገርም+ እንኳ ማንም አይሰማውም።+ 3 ይሁን እንጂ ትንቢት የሚናገር በንግግሩ ሰዎችን ያንጻል፣ ያበረታታል እንዲሁም ያጽናናል። 4 በልሳን የሚናገር ራሱን ያንጻል፤ ትንቢት የሚናገር ግን ጉባኤን ያንጻል። 5 ሁላችሁም በልሳን ብትናገሩ እወድ ነበር፤+ ሆኖም ትንቢት ብትናገሩ እመርጣለሁ።+ ደግሞም ትንቢት የሚናገር በልሳን ከሚናገር ይበልጣል። ምክንያቱም በልሳን የሚናገር የተናገረውን ካልተረጎመው ጉባኤው ሊታነጽ አይችልም። 6 አሁን ግን ወንድሞች፣ ወደ እናንተ መጥቼ ራእይን በመግለጥ+ ወይም በእውቀት+ ወይም በትንቢት ወይም በትምህርት ካልነገርኳችሁ በስተቀር በልሳን ብነግራችሁ ምን እጠቅማችኋለሁ?
7 እንደ ዋሽንትና በገና ካሉ ድምፅ የሚያወጡ ግዑዝ ነገሮች ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። የሚያወጡት የድምፅ ቃና ግልጽ የሆነ ልዩነት ከሌለው ከዋሽንቱም ሆነ ከበገናው የሚወጣው ዜማ እንዴት ይለያል? 8 ደግሞም መለከት ለመለየት የሚያስቸግር ድምፅ ቢያሰማ ለጦርነት ማን ይዘጋጃል? 9 ልክ እንደዚሁም ከአንደበታችሁ የሚወጣው ቃል በቀላሉ የሚገባ ካልሆነ ስለ ምን እየተናገራችሁ እንዳለ ማን ሊያውቅ ይችላል? እንዲህ ከሆነ ለነፋስ የምትናገሩ ትሆናላችሁ። 10 በዓለም ላይ ብዙ ዓይነት ቋንቋዎች አሉ፤ ሆኖም ትርጉም የሌለው ቋንቋ የለም። 11 አንድ ሰው የሚናገረውን ቋንቋ ትርጉም ካላወቅኩ እኔ ለሚናገረው ሰው የባዕድ አገር ሰው እሆንበታለሁ፤ እሱም ለእኔ የባዕድ አገር ሰው ይሆንብኛል። 12 ስለዚህ እናንተም የመንፈስን ስጦታዎች እጅግ ስለምትፈልጉ ጉባኤውን የሚያንጹ ስጦታዎች በብዛት ለማግኘት ጥረት አድርጉ።+
13 ስለሆነም በልሳን የሚናገር ሰው የሚናገረውን መተርጎም እንዲችል ይጸልይ።+ 14 ምክንያቱም በልሳን የምጸልይ ከሆነ፣ የሚጸልየው የተቀበልኩት የመንፈስ ስጦታ ነው፤ አእምሮዬ ግን ምንም የሚያከናውነው ነገር የለም። 15 ታዲያ ምን ማድረግ ይሻላል? በመንፈስ ስጦታ እጸልያለሁ፤ ሆኖም የምጸልየው ትርጉሙ ገብቶኝ ነው። በመንፈስ ስጦታ የውዳሴ መዝሙር እዘምራለሁ፤ ሆኖም የምዘምረው ትርጉሙ ገብቶኝ ነው። 16 እንዲህ ካልሆነ በመንፈስ ስጦታ ውዳሴ ብታቀርብ በመካከልህ ያለው ምንም የማያውቅ ሰው ምን እየተናገርክ እንዳለህ ስለማይገባው ላቀረብከው ምስጋና እንዴት “አሜን” ሊል ይችላል? 17 እርግጥ አንተ ግሩም በሆነ መንገድ ምስጋና ታቀርብ ይሆናል፤ ሌላው ሰው ግን እየታነጸበት አይደለም። 18 ከሁላችሁ የበለጠ በብዙ ልሳኖች ስለምናገር አምላክን አመሰግናለሁ። 19 ይሁንና በጉባኤ ውስጥ አሥር ሺህ ቃላት በልሳን ከምናገር ሌሎችንም ማስተማር* እችል ዘንድ አምስት ቃላት በአእምሮዬ* ብናገር እመርጣለሁ።+
20 ወንድሞች፣ በማስተዋል ችሎታችሁ እንደ ሕፃናት አትሁኑ፤+ ለክፋት ግን ሕፃናት ሁኑ፤+ በማስተዋል ችሎታችሁም የጎለመሳችሁ ሁኑ።+ 21 በሕጉ ላይ “‘በባዕዳን አንደበትና እንግዳ በሆኑ ሰዎች ቋንቋዎች ለዚህ ሕዝብ እናገራለሁ፤ እነሱ ግን በዚያን ጊዜም እንኳ አይሰሙኝም’ ይላል ይሖዋ”* ተብሎ ተጽፏል።+ 22 በመሆኑም ልሳን ለአማኞች ሳይሆን አማኝ ላልሆኑት ምልክት ነው፤+ ትንቢት ግን አማኝ ላልሆኑት ሳይሆን ለአማኞች ነው። 23 ስለዚህ ጉባኤው በሙሉ አንድ ላይ ተሰብስቦ ባለበት ወቅት ሁሉም በልሳኖች ቢናገሩና በዚህ መሃል ምንም የማያውቁ ሰዎች ወይም አማኞች ያልሆኑ ቢገቡ እነዚህ ሰዎች ‘አእምሯችሁን ስታችኋል’ አይሏችሁም? 24 ሆኖም ሁላችሁም ትንቢት እየተናገራችሁ ሳለ አማኝ ያልሆነ ወይም ምንም የማያውቅ ሰው ቢገባ ሁላችሁም የምትናገሩት ቃል እንደ ወቀሳ የሚያገለግለው ከመሆኑም በላይ ራሱን በሚገባ እንዲመረምር ያነሳሳዋል። 25 በዚህ ጊዜ በልቡ የተሰወረው ነገር ይገለጣል፤ በመሆኑም “አምላክ በእርግጥ በመካከላችሁ ነው” እያለ በግንባሩ ተደፍቶ ለአምላክ ይሰግዳል።+
26 እንግዲህ ወንድሞች፣ ምን ማድረግ ይሻላል? አንድ ላይ በምትሰበሰቡበት ጊዜ አንዱ ይዘምራል፣ ሌላው ያስተምራል፣ ሌላው ራእይን ይገልጣል፣ ሌላው በልሳን ይናገራል፣ ሌላው ደግሞ ይተረጉማል።+ ሁሉም ነገር ለማነጽ ይሁን። 27 በልሳን የሚናገሩ ካሉ ከሁለት ወይም ከሦስት አይብለጡ፤ በየተራም ይናገሩ፤ የሚናገሩትንም ሌላ ሰው ይተርጉም።+ 28 የሚተረጉም ሰው ከሌለ ግን በጉባኤ መካከል ዝም ይበሉና ለራሳቸውና ለአምላክ ይናገሩ። 29 ሁለት ወይም ሦስት ነቢያት+ ይናገሩ፤ ሌሎቹ ደግሞ ትርጉሙን ለመረዳት ይጣሩ። 30 ሆኖም አንድ ሰው እዚያ ተቀምጦ ሳለ ራእይ ቢገለጥለት የመጀመሪያው ተናጋሪ ዝም ይበል። 31 ሁሉም እንዲማሩና ሁሉም እንዲበረታቱ ሁላችሁም በየተራ ትንቢት መናገር ትችላላችሁ።+ 32 ነቢያት የመንፈስ ስጦታዎችን በአግባቡ ሊጠቀሙባቸው ይገባል። 33 አምላክ የሰላም እንጂ የሁከት አምላክ አይደለምና።+
በቅዱሳን ጉባኤዎች ሁሉ እንደሚደረገው 34 ሴቶች በጉባኤ ውስጥ እንዲናገሩ ስላልተፈቀደላቸው ዝም ይበሉ።+ ከዚህ ይልቅ ሕጉም እንደሚለው ይገዙ።+ 35 ያልገባቸው ነገር ካለ በቤታቸው ባሎቻቸውን ይጠይቁ፤ ምክንያቱም ሴት በጉባኤ መካከል ብትናገር የሚያሳፍር ነው።
36 የአምላክ ቃል የመጣው ከእናንተ ነው? ወይስ የአምላክ ቃል የደረሰው ወደ እናንተ ብቻ ነው?
37 ነቢይ እንደሆነ ወይም የመንፈስ ስጦታ እንዳለው የሚያስብ ሰው ካለ እነዚህ የጻፍኩላችሁ ነገሮች የጌታ ትእዛዛት መሆናቸውን አምኖ ይቀበል። 38 ሆኖም ይህን ችላ የሚል ካለ እሱም ችላ ይባላል።* 39 ስለዚህ ወንድሞቼ፣ ትንቢት ለመናገር ጥረት አድርጉ፤+ ይሁንና በልሳኖች መናገርንም አትከልክሉ።+ 40 ሆኖም ሁሉም ነገር በአግባብና በሥርዓት ይሁን።+
15 አሁን ደግሞ ወንድሞች፣ የነገርኳችሁን ምሥራች ላስታውሳችሁ እወዳለሁ፤+ ይህ ምሥራች እናንተም የተቀበላችሁትና የቆማችሁለት ነው። 2 በተጨማሪም እኔ የነገርኳችሁን ምሥራች አጥብቃችሁ የምትይዙ ከሆነ በምሥራቹ ትድናላችሁ፤ አለዚያ አማኝ የሆናችሁት በከንቱ ነው ማለት ነው።
3 እኔ የተቀበልኩትን ከሁሉ በላይ የሆነውን ነገር ለእናንተ አስተላልፌአለሁና፤ ይኸውም ቅዱሳን መጻሕፍት እንደሚሉት ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፤+ 4 ደግሞም ተቀበረ፤+ ቅዱሳን መጻሕፍት+ እንደሚሉትም በሦስተኛው ቀን+ ተነሳ፤+ 5 ለኬፋ*+ ከዚያም ለአሥራ ሁለቱ ታየ።+ 6 በኋላ ደግሞ በአንድ ጊዜ ከ500 ለሚበልጡ ወንድሞች የታየ+ ሲሆን አንዳንዶቹ በሞት ቢያንቀላፉም አብዛኞቹ ግን አሁንም ከእኛ ጋር አሉ። 7 ከዚያም ለያዕቆብ ታየ፤+ ቀጥሎም ለሐዋርያቱ በሙሉ ታየ።+ 8 በመጨረሻ ደግሞ እንደ ጭንጋፍ ለምቆጠር ለእኔ ተገለጠልኝ።+
9 እኔ የአምላክን ጉባኤ አሳድድ ስለነበር ከሐዋርያት ሁሉ የማንስና ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ ነኝ።+ 10 ሆኖም አሁን የሆንኩትን ለመሆን የበቃሁት በአምላክ ጸጋ ነው። አምላክ ለእኔ ያሳየው ጸጋም ከንቱ ሆኖ አልቀረም፤ እንዲያውም ከሁሉም የበለጠ በትጋት ሠርቻለሁ፤ ይሁንና ይህን ያደረገው ከእኔ ጋር ያለው የአምላክ ጸጋ ነው እንጂ እኔ አይደለሁም። 11 እንግዲህ እኔም ሆንኩ እነሱ የምንሰብከው በዚህ መንገድ ነው፤ እናንተም ያመናችሁት በዚህ መንገድ ነው።
12 ታዲያ ክርስቶስ ከሞት እንደተነሳ እየተሰበከ ከሆነ+ ከእናንተ መካከል አንዳንዶቹ እንዴት የሙታን ትንሣኤ የለም ይላሉ? 13 የሙታን ትንሣኤ ከሌለማ ክርስቶስም አልተነሳም ማለት ነዋ! 14 ክርስቶስ ካልተነሳ ደግሞ ስብከታችን ከንቱ ነው፤ እምነታችሁም ከንቱ ነው። 15 ከዚህም በተጨማሪ ሙታን በእርግጥ የማይነሱ ከሆነ አምላክ ክርስቶስን ከሞት ስላላስነሳው፣ ክርስቶስን አስነስቶታል+ ብለን ስንመሠክር ሐሰተኞች የአምላክ ምሥክሮች ሆነን ተገኝተናል ማለት ነው።+ 16 ምክንያቱም ሙታን የማይነሱ ከሆነ ክርስቶስም ከሞት አልተነሳም ማለት ይሆናል። 17 ክርስቶስ ካልተነሳ ደግሞ እምነታችሁ ከንቱ ነው፤ እናንተም ከነኃጢአታችሁ ትኖራላችሁ።+ 18 ከክርስቶስ ጋር አንድነት ኖሯቸው በሞት ያንቀላፉትም ጠፍተው ቀርተዋል ማለት ነው።+ 19 በክርስቶስ ተስፋ ያደረግነው ለዚህ ሕይወት ብቻ ከሆነ ከሰው ሁሉ ይልቅ የምናሳዝን ነን።
20 ይሁንና ክርስቶስ በሞት ካንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሞት ተነስቷል።+ 21 ሞት የመጣው በአንድ ሰው በኩል+ ስለሆነ የሙታን ትንሣኤም በአንድ ሰው በኩል ነው።+ 22 ሁሉም በአዳም እንደሚሞቱ+ ሁሉም በክርስቶስ ሕያው ይሆናሉና።+ 23 ሆኖም እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፦ ክርስቶስ በኩራት ነው፤+ በመቀጠል ደግሞ ክርስቶስ በሚገኝበት ጊዜ የእሱ የሆኑት ሕያዋን ይሆናሉ።+ 24 ከዚያም ማንኛውንም መስተዳድር እንዲሁም ሥልጣንን ሁሉና ኃይልን አጥፍቶ መንግሥቱን ለአምላኩና ለአባቱ በሚያስረክብበት ጊዜ ፍጻሜ ይሆናል።+ 25 አምላክ ጠላቶችን ሁሉ ከእግሩ በታች እስኪያደርግለት ድረስ ንጉሥ ሆኖ ሊገዛ ይገባዋልና።+ 26 የመጨረሻው ጠላት፣ ሞት ይደመሰሳል።+ 27 አምላክ “ሁሉንም ነገር ከእግሩ በታች አስገዝቶለታልና።”+ ሆኖም ‘ሁሉም ነገር ተገዝቷል’+ ሲል ሁሉንም ነገር ያስገዛለትን እንደማይጨምር ግልጽ ነው።+ 28 ይሁንና ሁሉም ነገር ከተገዛለት በኋላ ወልድ ራሱ ሁሉን ነገር ላስገዛለት ራሱን ያስገዛል፤+ ይህም አምላክ ለሁሉም ሁሉንም ነገር እንዲሆን ነው።+
29 አለዚያማ ለመሞት ብለው በመጠመቅ ምን የሚያተርፉት ነገር ይኖራል?+ ሙታን ፈጽሞ የማይነሱ ከሆነ እነሱም ለመሞት ብለው የሚጠመቁበት ምን ምክንያት አለ? 30 እኛስ ሁልጊዜ ለአደጋ ተጋልጠን የምንኖረው ለምንድን ነው?+ 31 እኔ በየቀኑ ሞትን እጋፈጣለሁ። ወንድሞች፣ ይህ እውነት መሆኑን የጌታችን የክርስቶስ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በሆናችሁት በእናንተ ላይ ባለኝ ትምክህት አረጋግጥላችኋለሁ። 32 እንደ ሌሎች ሰዎች* በኤፌሶን ከአውሬዎች ጋር ከታገልኩ፣+ እንዲህ ማድረጌ ለእኔ ምን ይጠቅመኛል? ሙታን የማይነሱ ከሆነማ “ነገ ስለምንሞት እንብላ፣ እንጠጣ።”+ 33 አትታለሉ። መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን አመል* ያበላሻል።+ 34 ጽድቅ የሆነውን በማድረግ ወደ ልቦናችሁ ተመለሱ፤ ኃጢአት መሥራትን ልማድ አታድርጉ፤ አንዳንዶች ስለ አምላክ አያውቁምና። ይህን የምላችሁ ላሳፍራችሁ ብዬ ነው።
35 ይሁንና አንድ ሰው “ሙታን የሚነሱት እንዴት ነው? ከሞት የሚነሱትስ ምን ዓይነት አካል ይዘው ነው?” ይል ይሆናል።+ 36 አንተ ማስተዋል የጎደለህ! የምትዘራው መጀመሪያ ካልሞተ ሕያው ሊሆን አይችልም። 37 ደግሞም ስንዴም ሆነ ሌላ ዓይነት እህል ስትዘራ የምትዘራው ዘሩን እንጂ በኋላ የሚያድገውን አካል አይደለም፤ 38 ሆኖም አምላክ የፈለገውን አካል ይሰጠዋል፤ ለእያንዳንዱም ዘር የራሱን አካል ይሰጠዋል። 39 ሥጋ ሁሉ አንድ ዓይነት አይደለም፤ በመሆኑም የሰው ሥጋ አለ፣ የከብት ሥጋ አለ፣ የወፎች ሥጋ አለ እንዲሁም የዓሣ ሥጋ አለ። 40 በተጨማሪም ሰማያዊ አካላት አሉ፤+ ምድራዊ አካላትም አሉ፤+ ሆኖም የሰማይ አካላት የራሳቸው ክብር አላቸው፤ የምድር አካላት ደግሞ ሌላ ዓይነት ክብር አላቸው። 41 ፀሐይ የራሷ ክብር አላት፤ ጨረቃ ደግሞ ሌላ ዓይነት ክብር አላት፤+ ከዋክብትም ሌላ ዓይነት ክብር አላቸው፤ እንዲያውም የአንዱ ኮከብ ክብር ከሌላው ኮከብ ክብር ይለያል።
42 ስለዚህ የሙታን ትንሣኤም እንደዚሁ ነው። የሚዘራው የሚበሰብስ ነው፤ የሚነሳው የማይበሰብስ ነው።+ 43 የሚዘራው በውርደት ነው፤ የሚነሳው በክብር ነው።+ የሚዘራው በድካም ነው፤ የሚነሳው በኃይል ነው።+ 44 የሚዘራው ሥጋዊ አካል ነው፤ የሚነሳው መንፈሳዊ አካል ነው። ሥጋዊ አካል ካለ መንፈሳዊ አካልም አለ። 45 ስለዚህ “የመጀመሪያው ሰው አዳም ሕያው ሰው* ሆነ” ተብሎ ተጽፏል።+ የኋለኛው አዳም ሕይወት የሚሰጥ መንፈስ ሆነ።+ 46 ይሁንና የመጀመሪያው መንፈሳዊው አይደለም። የመጀመሪያው ሥጋዊው ነው፤ የኋለኛው ደግሞ መንፈሳዊው ነው። 47 የመጀመሪያው ሰው ከምድር የተገኘና ከአፈር የተሠራ ነው፤+ ሁለተኛው ሰው ደግሞ ከሰማይ ነው።+ 48 ከአፈር የተሠሩት ከአፈር እንደተሠራው ናቸው፤ ሰማያዊ የሆኑትም ከሰማይ እንደመጣው ናቸው።+ 49 ከአፈር የተሠራውን ሰው መልክ እንደመሰልን ሁሉ+ የሰማያዊውንም መልክ እንመስላለን።+
50 ይሁን እንጂ ወንድሞች ይህን እነግራችኋለሁ፦ ሥጋና ደም የአምላክን መንግሥት አይወርስም፤ የሚበሰብሰውም የማይበሰብሰውን አይወርስም። 51 እነሆ፣ አንድ ቅዱስ ሚስጥር እነግራችኋለሁ፦ በሞት የምናንቀላፋው ሁላችንም አይደለንም፤ ነገር ግን ሁላችንም እንለወጣለን፤+ 52 የመጨረሻው መለከት በሚነፋበት ወቅት ድንገት፣ በቅጽበተ ዓይን* እንለወጣለን። መለከት ይነፋል፤+ ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሳሉ፤ እኛም እንለወጣለን። 53 ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሊለብስ ይገባዋልና፤+ ይህ ሟች የሆነው የማይሞተውን ሊለብስ ይገባዋል።+ 54 ሆኖም ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሲለብስና ይህ ሟች የሆነው የማይሞተውን ሲለብስ “ሞት ለዘላለም ተዋጠ” ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸማል።+ 55 “ሞት ሆይ፣ ድል አድራጊነትህ የት አለ? ሞት ሆይ፣ መንደፊያህ የት አለ?”+ 56 ለሞት የሚዳርገው መንደፊያ ኃጢአት ነው፤+ ለኃጢአት ኃይል የሚሰጠው ደግሞ ሕጉ ነው።+ 57 ሆኖም አምላክ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ድል ስለሚያጎናጽፈን የተመሰገነ ይሁን!+
58 ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ ጸንታችሁ ቁሙ፤+ አትነቃነቁ፤ እንዲሁም ከጌታ ጋር በተያያዘ በትጋት የምታከናውኑት ሥራ ከንቱ አለመሆኑን አውቃችሁ+ ምንጊዜም የጌታ ሥራ የበዛላችሁ ሁኑ።+
16 ለቅዱሳን መዋጮ ማሰባሰብን በተመለከተ+ ደግሞ በገላትያ ለሚገኙ ጉባኤዎች የሰጠሁትን መመሪያ መከተል ትችላላችሁ። 2 መዋጮ የሚሰባሰበው እኔ በምመጣበት ጊዜ እንዳይሆን ከእናንተ እያንዳንዱ በየሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን አቅሙ በሚፈቅድለት መጠን የተወሰነ ገንዘብ ያስቀምጥ። 3 ስመጣም የመረጣችኋቸውንና የድጋፍ ደብዳቤ የጻፋችሁላቸውን ሰዎች+ የልግስና ስጦታችሁን ኢየሩሳሌም እንዲያደርሱ እልካቸዋለሁ። 4 ይሁን እንጂ የእኔም መሄድ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ አብረውኝ ይሄዳሉ።
5 ይሁንና በመቄዶንያ በኩል ማለፌ ስለማይቀር በዚያ ሳልፍ ወደ እናንተ እመጣለሁ፤+ 6 ወደምሄድበትም ቦታ የተወሰነ መንገድ እንድትሸኙኝ ምናልባት እናንተ ጋ ልቆይ እችላለሁ፤ እንዲያውም ክረምቱን ከእናንተ ጋር አሳልፍ ይሆናል። 7 ይሖዋ* ቢፈቅድ ከእናንተ ጋር የተወሰነ ጊዜ አሳልፋለሁ ብዬ ተስፋ ስለማደርግ አሁን እግረ መንገዴን ሳልፍ ላያችሁ አልፈልግም።+ 8 ይሁንና እስከ ጴንጤቆስጤ በዓል ድረስ በኤፌሶን+ እቆያለሁ፤ 9 ምክንያቱም ትልቅ የሥራ በር ተከፍቶልኛል፤+ ሆኖም ብዙ ተቃዋሚዎች አሉ።
10 ጢሞቴዎስ+ ከመጣ በመካከላችሁ በሚቆይበት ጊዜ ፍርሃት እንዳይሰማው ተባበሩት፤ እሱም እንደ እኔ የይሖዋን* ሥራ የሚሠራ ነውና።+ 11 ስለዚህ ማንም አይናቀው። ከወንድሞች ጋር እየጠበቅኩት ስለሆነ ወደ እኔ እንዲመጣ በሰላም ሸኙት።
12 ወንድማችንን አጵሎስን+ በተመለከተ ደግሞ ከወንድሞች ጋር ወደ እናንተ እንዲመጣ አጥብቄ ለምኜው ነበር። እሱ አሁን የመምጣት ሐሳብ የለውም፤ ሆኖም ሁኔታው ሲመቻችለት ይመጣል።
13 ነቅታችሁ ኑሩ፤+ በእምነት ጸንታችሁ ቁሙ፤+ ወንድ ሁኑ፤*+ ብርቱዎች ሁኑ።+ 14 የምታደርጉትን ነገር ሁሉ በፍቅር አድርጉ።+
15 እንግዲህ ወንድሞች ይህን አሳስባችኋለሁ፦ የእስጢፋናስ ቤተሰብ በአካይያ የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት* እንደሆኑና ቅዱሳንን ለማገልገል ራሳቸውን እንደሰጡ ታውቃላችሁ። 16 እናንተም እንደ እነሱ ላሉት እንዲሁም ከእኛ ጋር ለሚተባበሩትና በትጋት ለሚሠሩት ሁሉ ተገዙ።+ 17 እስጢፋናስ+ እና ፈርጡናጦስ እንዲሁም አካይቆስ እዚህ በመገኘታቸው እጅግ ተደስቻለሁ፤ ምክንያቱም የእናንተ እዚህ አለመኖር በእነሱ ተካክሷል። 18 እነሱ የእኔንም ሆነ የእናንተን መንፈስ አድሰዋልና። ስለዚህ እንዲህ ላሉት ሰዎች እውቅና ስጡ።
19 በእስያ ያሉ ጉባኤዎች ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። አቂላና ጵርስቅላ እንዲሁም በቤታቸው ያለው ጉባኤ+ ሞቅ ያለ ክርስቲያናዊ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። 20 ወንድሞች ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። እርስ በርሳችሁ በተቀደሰ አሳሳም ሰላምታ ተለዋወጡ።
21 እኔ ጳውሎስ በገዛ እጄ የጻፍኩላችሁ ሰላምታ ይድረሳችሁ።
22 ጌታን የማይወድ ቢኖር የተረገመ ይሁን። ጌታችን ሆይ፣ ና! 23 የጌታ ኢየሱስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን። 24 የክርስቶስ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የሆናችሁ ሁሉ፣ ፍቅሬ ይድረሳችሁ።
ወይም “ተካፋይ እንድትሆኑ።”
ጴጥሮስ ተብሎም ይጠራል።
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “በአፈ ጮሌነት።”
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “የዚህ ዘመን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ሕጉን ጠንቅቀው የተማሩ ሰዎችን ያመለክታል።
ቃል በቃል “በሥጋዊ መንገድ።”
ቃል በቃል “ሥጋ ሁሉ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “የዚህን ዘመን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ከዓለም ሥርዓቶች በፊት።”
ወይም “ከዚህ ዘመን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “በእንጨት ላይ ባልሰቀሉት።”
ወይም “ከመንፈሳዊ ቃላት ጋር በማዛመድ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ቃል በቃል “አንድ ናቸው።” ወይም “አንድ ዓላማ አላቸው።”
ወይም “በሙያው እንደተካነ መሐንዲስ።”
ወይም “በዚህ ዘመን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ጴጥሮስ ተብሎም ይጠራል።
ወይም “የበታቾችና።”
ወይም “ፍርድ ቤት።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “በቡጢ እየተመታንና።”
ቃል በቃል “እንለማመጣለን።”
ወይም “ቆሻሻና፤ ትርኪ ምርኪና።”
ወይም “አስተማሪዎች።”
ቃል በቃል “መንገዶች።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ግሪክኛ፣ ፖርኒያ። የቃላት መፍቻው ላይ “የፆታ ብልግና” የሚለውን ተመልከት።
ግሪክኛ፣ ፖርኒያ። የቃላት መፍቻው ላይ “የፆታ ብልግና” የሚለውን ተመልከት።
ቃል በቃል “ሥጋው እንዲጠፋና።”
የቃላት መፍቻው ላይ “የፆታ ብልግና” የሚለውን ተመልከት።
ወይም “እንዳትቀራረቡ።”
የቃላት መፍቻው ላይ “የፆታ ብልግና” የሚለውን ተመልከት።
የቃላት መፍቻው ላይ “የፆታ ብልግና” የሚለውን ተመልከት።
ወይም “እንዳትቀራረቡ።”
ወይም “የክርስቲያን ጉባኤ አባል ባልሆኑ።”
የቃላት መፍቻው ላይ “የፆታ ብልግና” የሚለውን ተመልከት።
ግብረ ሰዶማውያን ሆነው የሴት ዓይነት ሚና ያላቸውን ወንዶች ያመለክታል።
ወይም “ከወንዶች ጋር የፆታ ግንኙነት የሚፈጽሙ ወንዶች።” ቃል በቃል “ከወንዶች ጋር የሚተኙ ወንዶች።”
ግሪክኛ፣ ፖርኒያ። የቃላት መፍቻው ላይ “የፆታ ብልግና” የሚለውን ተመልከት።
ግሪክኛ፣ ፖርኒያ። የቃላት መፍቻው ላይ “የፆታ ብልግና” የሚለውን ተመልከት።
በፆታ ስሜት መንካትን ያመለክታል።
ፖርኒያ የተባለው ግሪክኛ ቃል ብዙ ቁጥር። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “አግብተው የማያውቁትን።”
ቃል በቃል “ማነቆ ውስጥ ላስገባችሁ።”
ወይም “ከድንግልናው ጋር በሚስማማ ሁኔታ በአግባቡ መኖር።”
ወይም “ድንግልናውን ጠብቆ።”
ወይም “ድንግልናውን በጋብቻ የሚሰጥ።”
እምነቱ ወይም የዘላለም ሕይወት ተስፋው መጥፋቱን ያመለክታል።
ቃል በቃል “ሥልጣን።”
ጴጥሮስ ተብሎም ይጠራል።
ቃል በቃል “ሥልጣን።”
ወይም “መብቴን።”
ወይም “አትሌት።”
ወይም “ብቃቱን እንዳላጓድል።”
ወይም “እየቀጣሁ፤ አጥብቄ እየገሠጽኩ።”
ወይም “ክርስቶስ ነበር።”
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ይህ አባባል በመንፈሳዊ መሞትን ሊያመለክት ይችላል።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
አማኝ እንዳልነበሩ ያመለክታል።
ወይም “አሠራሮች።”
ወይም “ጥበብ የሚንጸባረቅበት መልእክት።”
ወይም “ቋንቋዎች።”
ወይም “ቅንዓት የተሞላበት ጥረት።”
ቃል በቃል “ነሐስ።”
እዚህ ላይ የገባው ግሪክኛ ቃል፣ እርስ በርሱ ሲጋጭ ኃይለኛ ድምፅ የሚያወጣን ክብ ቅርጽ ያለው ከብረት የተሠራ የሙዚቃ መሣሪያ ያመለክታል።
ወይም “ዋጋ ቢስ ነኝ።”
ወይም “ሥርዓት የለሽ አይደለም።”
ወይም “መቼም ቢሆን አይጠፋም።”
ሌሎች ቋንቋዎችን የመናገር ተአምራዊ ስጦታን ያመለክታል።
ወይም “ለመለየት የሚያስቸግር።”
ወይም “ትክክለኛ።”
ወይም “ቅንዓት የተሞላበት ጥረት።”
ወይም “በቃል ማስተማር።”
ወይም “በማስተዋል።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
“ይህን የማያውቅ ካለ ያለእውቀት ይኖራል” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ጴጥሮስ ተብሎም ይጠራል።
“ከሰው አመለካከት አንጻር” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ጥሩውን ሥነ ምግባር።”
ወይም “ነፍስ።”
ወይም “ወዲያው።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “ደፋሮች ሁኑ።”
ቃል በቃል “የአካይያ በኩራት።”