መሳፍንት
1 ኢያሱ+ ከሞተ በኋላ እስራኤላውያን* “ከከነአናውያን ጋር ለመዋጋት ከመካከላችን ማን ቀድሞ ይውጣ?” በማለት ይሖዋን ጠየቁ።+ 2 ይሖዋም “ይሁዳ ይውጣ።+ እኔም ምድሪቱን በእጁ አሳልፌ እሰጠዋለሁ”* አለ። 3 ከዚያም ይሁዳ ወንድሙን ስምዖንን “ከከነአናውያን ጋር ለመዋጋት ወደተመደበልኝ ርስት* + አብረኸኝ ውጣ። እኔም ደግሞ በዕጣ ወደደረሰህ ርስት አብሬህ እሄዳለሁ” አለው። ስለዚህ ስምዖን አብሮት ሄደ።
4 ይሁዳም በወጣ ጊዜ ይሖዋ ከነአናውያንንና ፈሪዛውያንን በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው፤+ በመሆኑም ቤዜቅ ላይ 10,000 ሰዎችን ድል አደረጉ። 5 አዶኒቤዜቅን ቤዜቅ ላይ ባገኙት ጊዜ በዚያ ከእሱ ጋር ተዋጉ፤ ከነአናውያንንና+ ፈሪዛውያንንም+ ድል አደረጉ። 6 አዶኒቤዜቅም በሸሸ ጊዜ አሳደው ያዙት፤ ከዚያም የእጆቹንና የእግሮቹን አውራ ጣቶች ቆረጡ። 7 አዶኒቤዜቅም እንዲህ አለ፦ “የእጃቸውና የእግራቸው አውራ ጣቶች የተቆረጡባቸው ከገበታዬ ሥር ሆነው ፍርፋሪ የሚለቃቅሙ 70 ነገሥታት ነበሩ። አምላክም ልክ እኔ እንዳደረግኩት አደረገብኝ።” ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም አመጡት፤+ እሱም በዚያ ሞተ።
8 በተጨማሪም የይሁዳ ሰዎች ኢየሩሳሌምን ወግተው በቁጥጥር ሥር አዋሏት፤+ ከተማዋንም በሰይፍ መትተው በእሳት አቃጠሏት። 9 ከዚያም የይሁዳ ሰዎች በተራራማው አካባቢ፣ በኔጌብና በሸፌላ+ ከሚኖሩት ከነአናውያን ጋር ለመዋጋት ወረዱ። 10 በመሆኑም ይሁዳ በኬብሮን ይኖሩ በነበሩት ከነአናውያን ላይ ዘመተ (ኬብሮን ቀደም ሲል ቂርያትአርባ ተብላ ትጠራ ነበር)፤ እነሱም ሸሻይን፣ አሂማንን እና ታልማይን መቱ።+
11 ከዚያም ተነስተው በደቢር ነዋሪዎች ላይ ዘመቱ።+ (ደቢር ቀደም ሲል ቂርያትሰፈር ትባል ነበር።)+ 12 ካሌብም+ “ቂርያትሰፈርን መትቶ በቁጥጥር ሥር ላደረጋት ሰው ሴት ልጄን አክሳን እድርለታለሁ” አለ።+ 13 የካሌብ ታናሽ ወንድም የሆነው የቀናዝ+ ልጅ ኦትኒኤልም+ ከተማዋን በቁጥጥር ሥር አደረጋት። ስለሆነም ካሌብ ሴት ልጁን አክሳን ዳረለት። 14 እሷም ወደ ባሏ ቤት እየሄደች ሳለ ባሏን ከአባቷ መሬት እንዲጠይቅ ወተወተችው። ከዚያም ከአህያዋ ላይ ወረደች።* በዚህ ጊዜ ካሌብ “ምን ፈለግሽ?” ሲል ጠየቃት። 15 እሷም “የሰጠኸኝ በስተ ደቡብ* ያለ ቁራሽ መሬት ስለሆነ እባክህ ባርከኝ፤ ጉሎትማይምንም* ስጠኝ” አለችው። በመሆኑም ካሌብ ላይኛውን ጉሎት እና ታችኛውን ጉሎት ሰጣት።
16 የቄናዊው+ የሙሴ አማት+ ዘሮች ከይሁዳ ሰዎች ጋር በመሆን ከዘንባባ ዛፎች ከተማ+ ወጥተው ከአራድ+ በስተ ደቡብ ወደሚገኘው ወደ ይሁዳ ምድረ በዳ አቀኑ። እነሱም ወደዚያ ሄደው ከሕዝቡ ጋር መኖር ጀመሩ።+ 17 ይሁዳም ከወንድሙ ከስምዖን ጋር በመዝመት በጸፋት በሚኖሩት ከነአናውያን ላይ ጥቃት ሰነዘሩ፤ ከተማዋንም ሙሉ በሙሉ ደመሰሱ።+ በመሆኑም ከተማዋን ሆርማ* + ብለው ሰየሟት። 18 ከዚያም ይሁዳ ጋዛንና+ ግዛቶቿን፣ አስቀሎንንና+ ግዛቶቿን እንዲሁም ኤቅሮንንና+ ግዛቶቿን ተቆጣጠረ። 19 ይሖዋ ከይሁዳ ጋር ስለነበር ይሁዳ ተራራማውን አካባቢ ወረሰ፤ በሜዳው* ላይ የሚኖሩትን ሰዎች ግን ማባረር አልቻሉም፤ ምክንያቱም እነሱ የብረት ማጭድ የተገጠመላቸው የጦር ሠረገሎች* ነበሯቸው።+ 20 ሙሴ ቃል በገባው መሠረት ኬብሮንን ለካሌብ ሰጡት፤+ እሱም ሦስቱን የኤናቅ ልጆች ከዚያ አባረራቸው።+
21 ቢንያማውያን ግን በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ኢያቡሳውያን ከዚያ አላስወጧቸውም ነበር፤ በመሆኑም ኢያቡሳውያኑ ከቢንያማውያን ጋር እስከ ዛሬ ድረስ በኢየሩሳሌም አብረው ይኖራሉ።+
22 በዚህ ጊዜ የዮሴፍ ቤት+ ቤቴልን ለመውጋት ወጣ፤ ይሖዋም ከእነሱ ጋር ነበር።+ 23 የዮሴፍ ቤት ቤቴልን እየሰለለ ነበር (ቤቴል ቀደም ሲል ሎዛ ተብላ ትጠራ ነበር)፤+ 24 ሰላዮቹም አንድ ሰው ከከተማዋ ሲወጣ አዩ። በመሆኑም “እባክህ ወደ ከተማዋ የሚያስገባውን መንገድ አሳየን፤ እኛም ደግነት እናደርግልሃለን”* አሉት። 25 በመሆኑም ሰውየው ወደ ከተማዋ የሚያስገባውን መንገድ አሳያቸው፤ እነሱም የከተማዋን ነዋሪዎች በሰይፍ መቱ፤ ይሁንና ሰውየውንና ቤተሰቡን በሙሉ ነፃ ለቀቋቸው።+ 26 ሰውየውም ወደ ሂታውያን ምድር ሄዶ ከተማ ገነባ፤ ከተማዋንም ሎዛ ብሎ ጠራት፤ እስከ ዛሬም ድረስ ስሟ ይኸው ነው።
27 ምናሴ ቤትሼንንና በሥሯ* ያሉትን ከተሞች፣ ታአናክንና+ በሥሯ ያሉትን ከተሞች፣ የዶርን ነዋሪዎችና በሥሯ ያሉትን ከተሞች፣ የይብለአምን ነዋሪዎችና በሥሯ ያሉትን ከተሞች እንዲሁም የመጊዶን ነዋሪዎችና በሥሯ ያሉትን ከተሞች አልወረሰም ነበር።+ ከነአናውያን ይህን ምድር ላለመልቀቅ ቆርጠው ነበር። 28 እስራኤላውያንም እያየሉ በሄዱ ጊዜ ከነአናውያንን የግዳጅ ሥራ እንዲሠሩ አስገደዷቸው+ እንጂ ሙሉ በሙሉ አላባረሯቸውም።+
29 ኤፍሬምም ቢሆን በጌዜር ይኖሩ የነበሩትን ከነአናውያን አላባረራቸውም። ከነአናውያን በጌዜር አብረዋቸው ይኖሩ ነበር።+
30 ዛብሎንም የቂትሮንን ነዋሪዎችና የናሃሎልን+ ነዋሪዎች አላባረራቸውም። ከነአናውያን አብረዋቸው ይኖሩ የነበረ ሲሆን የግዳጅ ሥራም እንዲሠሩ ተገደው ነበር።+
31 አሴር የአኮን ነዋሪዎች እንዲሁም የሲዶናን፣+ የአህላብን፣ የአክዚብን፣+ የሄልባን፣ የአፊቅን+ እና የሬሆብን+ ነዋሪዎች አላባረራቸውም። 32 በመሆኑም አሴራውያን በምድሩ ይኖሩ ከነበሩት ከነአናውያን ጋር አብረው መኖራቸውን ቀጠሉ፤ ምክንያቱም አላባረሯቸውም ነበር።
33 ንፍታሌም የቤትሼሜሽን ነዋሪዎችና የቤትአናትን ነዋሪዎች+ አላባረራቸውም፤ ከዚህ ይልቅ በምድሩ ይኖሩ ከነበሩት ከነአናውያን ጋር አብረው ኖሩ።+ የቤትሼሜሽ ነዋሪዎችና የቤትአናት ነዋሪዎች የግዳጅ ሥራ ይሠሩላቸው ነበር።
34 ዳናውያን ወደ ሜዳው* እንዲወርዱ አሞራውያን ስላልፈቀዱላቸው በተራራማው አካባቢ ተወስነው ለመኖር ተገደዱ።+ 35 አሞራውያን የሃሬስ ተራራን፣ አይሎንን+ እና ሻአልቢምን+ አንለቅም በማለት በዚያ መኖራቸውን ቀጠሉ። ይሁንና የዮሴፍ ቤት ኃይሉ* እየጨመረ* በመጣ ጊዜ የጉልበት ሥራ ለመሥራት ተገደዱ። 36 የአሞራውያን ክልል ከአቅራቢም አቀበትና+ ከሴላ አንስቶ ወደ ላይ ያለው ነበር።
2 የይሖዋም መልአክ+ ከጊልጋል+ ወደ ቦኪም ወጣ፤ እንዲህም አለ፦ “ከግብፅ አውጥቼ ለአባቶቻችሁ ወደማልኩላቸው ምድር አስገባኋችሁ።+ በተጨማሪም እንዲህ አልኩ፦ ‘እኔ ከእናንተ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን ፈጽሞ አላፈርስም።+ 2 እናንተም ከዚህች ምድር ነዋሪዎች ጋር ቃል ኪዳን አትግቡ፤+ መሠዊያዎቻቸውንም አፈራርሱ።’+ እናንተ ግን ቃሌን አልሰማችሁም።+ እንዲህ ያደረጋችሁት ለምንድን ነው? 3 በዚህም የተነሳ ‘እነሱን ከፊታችሁ አላስወጣቸውም፤+ ለእናንተም ወጥመድ ይሆኑባችኋል፤+ አማልክታቸውም ያታልሏችኋል’+ አልኩ።”
4 የይሖዋም መልአክ ለእስራኤላውያን በሙሉ ይህን በተናገረ ጊዜ ሕዝቡ ድምፁን ከፍ አድርጎ አለቀሰ። 5 ስለሆነም የዚያን ስፍራ ስም ቦኪም* አሉት፤ በዚያም ለይሖዋ መሥዋዕት አቀረቡ።
6 ኢያሱ ሕዝቡን ካሰናበተ በኋላ እያንዳንዱ እስራኤላዊ ምድሪቱን ለመውረስ ወደየርስቱ ሄደ።+ 7 ሕዝቡም ኢያሱ በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ እንዲሁም ከኢያሱ በኋላ በሕይወት በኖሩትና ይሖዋ ለእስራኤል ሲል ያደረገውን ታላቅ ነገር በሙሉ በተመለከቱት ሽማግሌዎች ዘመን ሁሉ ይሖዋን አገለገለ።+ 8 ከዚያም የይሖዋ አገልጋይ የሆነው የነዌ ልጅ ኢያሱ በ110 ዓመቱ ሞተ።+ 9 እነሱም ከጋአሽ ተራራ+ በስተ ሰሜን በኤፍሬም ተራራማ አካባቢ በሚገኘው ርስቱ በቲምናትሄረስ+ ቀበሩት። 10 ያም ትውልድ ሁሉ ወደ አያቶቹ ተሰበሰበ፤* ከእነሱም በኋላ ይሖዋንም ሆነ እሱ ለእስራኤል ያደረገውን ነገር የማያውቅ ሌላ ትውልድ ተነሳ።
11 በመሆኑም እስራኤላውያን በይሖዋ ፊት መጥፎ ነገር አደረጉ፤ ባአልንም አገለገሉ።* + 12 በዚህ መንገድ ከግብፅ ምድር ያወጣቸውን የአባቶቻቸውን አምላክ ይሖዋን ተዉ።+ በዙሪያቸው ያሉት ሕዝቦች የሚያመልኳቸውን ሌሎች አማልክት ተከተሉ፤+ ለእነሱም በመስገድ ይሖዋን አስቆጡት።+ 13 ይሖዋን ትተው ባአልንና የአስታሮትን ምስሎች አገለገሉ።+ 14 በዚህ ጊዜ የይሖዋ ቁጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፤ በመሆኑም ለሚዘርፏቸው ዘራፊዎች አሳልፎ ሰጣቸው።+ በዙሪያቸው ላሉ ጠላቶቻቸው ሸጣቸው፤+ ከዚያ ወዲህ ጠላቶቻቸውን መቋቋም አልቻሉም።+ 15 ይሖዋ አስቀድሞ በተናገረውና ይሖዋ ለእነሱ በማለው መሠረት+ በሄዱበት ቦታ ሁሉ ጥፋት ያመጣባቸው+ ዘንድ የይሖዋ እጅ በእነሱ ላይ ነበር፤ እነሱም በከባድ ጭንቀት ተውጠው ነበር።+ 16 በመሆኑም ይሖዋ ከዘራፊዎቻቸው እጅ የሚያድኗቸውን መሳፍንት አስነሳላቸው።+
17 እነሱ ግን መሳፍንቱን እንኳ ለመስማት ፈቃደኞች አልሆኑም፤ እንዲያውም ከሌሎች አማልክት ጋር አመነዘሩ፤ ለእነሱም ሰገዱ። የይሖዋን ትእዛዛት ያከብሩ የነበሩ አባቶቻቸው ከሄዱበት መንገድ ፈጥነው ዞር አሉ።+ እነሱ እንዳደረጉት ማድረግ ሳይችሉ ቀሩ። 18 ይሖዋ መሳፍንትን በሚያስነሳላቸው+ ጊዜ ሁሉ ይሖዋ ከመስፍኑ ጋር ይሆን ነበር፤ በመስፍኑም ዘመን ሁሉ ከጠላቶቻቸው እጅ ያድናቸው ነበር፤ ምክንያቱም ይሖዋ በሚጨቁኗቸውና+ በሚያንገላቷቸው ሰዎች የተነሳ ሲቃትቱ ያዝናል።*+
19 መስፍኑ በሚሞትበት ጊዜ ግን ሌሎች አማልክትን በመከተልና በማገልገል እንዲሁም ለእነሱ በመስገድ በድጋሚ ከአባቶቻቸው ይበልጥ መጥፎ ድርጊት ይፈጽማሉ።+ መጥፎ ሥራቸውን ያልተዉ ከመሆኑም ሌላ በእንቢተኝነታቸው ገፍተውበታል። 20 በመጨረሻም የይሖዋ ቁጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፤+ እንዲህም አለ፦ “ይህ ብሔር ከአባቶቻቸው ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን ስላፈረሰና+ ቃሌን ስላልሰማ+ 21 እኔም ኢያሱ በሞተ ጊዜ ሳያጠፋ ከተዋቸው ብሔራት መካከል አንዳቸውንም ከፊቱ አላባርርም።+ 22 ይህን የማደርገው እስራኤላውያን አባቶቻቸው እንዳደረጉት እነሱም በይሖዋ መንገድ በመሄድ መንገዱን ይጠብቁ እንደሆነና እንዳልሆነ ለመፈተን ነው።”+ 23 ስለዚህ ይሖዋ እነዚህ ብሔራት እዚያው እንዲኖሩ ፈቀደ። ወዲያውኑም አላስወጣቸውም፤ ለኢያሱም አሳልፎ አልሰጣቸውም።
3 ይሖዋ ከከነአን ጋር በተደረገው ጦርነት ያልተካፈሉትን እስራኤላውያን ሁሉ እንዲፈትኗቸው+ ሲል በምድሪቱ ላይ እንዲኖሩ የፈቀደላቸው ብሔራት እነዚህ ናቸው 2 (ይህን ያደረገው ከዚህ በፊት ተዋግተው የማያውቁት በኋላ ላይ የመጡት የእስራኤላውያን ትውልዶች የውጊያ ልምድ እንዲያገኙ ነው)፦ 3 አምስቱ የፍልስጤም+ ገዢዎች፣ ከነአናውያን በሙሉ፣ ሲዶናውያን+ እንዲሁም ከበዓልሄርሞን ተራራ አንስቶ እስከ ሌቦሃማት* + ድረስ በሚዘልቀው የሊባኖስ+ ተራራ የሚኖሩት ሂዋውያን።+ 4 እነዚህ ብሔራት እስራኤላውያን ይሖዋ በሙሴ አማካኝነት ለአባቶቻቸው የሰጣቸውን ትእዛዛት ይጠብቁ እንደሆነና እንዳልሆነ ለማወቅ የእስራኤላውያን መፈተኛ ሆነው አገልግለዋል።+ 5 በመሆኑም እስራኤላውያን በከነአናውያን፣ በሂታውያን፣ በአሞራውያን፣ በፈሪዛውያን፣ በሂዋውያን እና በኢያቡሳውያን መካከል ይኖሩ ነበር።+ 6 እነሱም ሴቶች ልጆቻቸውን ያገቡ፣ የራሳቸውንም ሴቶች ልጆች ለእነሱ ወንዶች ልጆች ይድሩ የነበረ ሲሆን የእነሱን አማልክትም ማገልገል ጀመሩ።+
7 ስለዚህ እስራኤላውያን በይሖዋ ፊት መጥፎ ነገር አደረጉ፤ አምላካቸውን ይሖዋንም ረሱ፤ ባአልንና+ የማምለኪያ ግንዶችን* + አገለገሉ። 8 በዚህ ጊዜ የይሖዋ ቁጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፤ ለሜሶጶጣሚያው* ንጉሥ ለኩሻንሪሻታይምም አሳልፎ ሸጣቸው። እስራኤላውያን ኩሻንሪሻታይምን ለስምንት ዓመት አገለገሉት። 9 ይሖዋ እንዲረዳቸው ወደ እሱ በጮኹም ጊዜ+ ይሖዋ እስራኤላውያንን እንዲያድናቸው የካሌብ ታናሽ ወንድም የሆነውን የቀናዝን ልጅ ኦትኒኤልን+ አዳኝ አድርጎ አስነሳው።+ 10 የይሖዋም መንፈስ በእሱ ላይ ወረደ፤+ እሱም የእስራኤል መስፍን ሆነ። ለጦርነት በወጣም ጊዜ ይሖዋ የሜሶጶጣሚያውን* ንጉሥ ኩሻንሪሻታይምን በእጁ አሳልፎ ሰጠው፤ እሱም በኩሻንሪሻታይም ላይ በረታበት። 11 ከዚያ በኋላ ምድሪቱ ለ40 ዓመት አረፈች።* ከዚያም የቀናዝ ልጅ ኦትኒኤል ሞተ።
12 እስራኤላውያንም እንደገና በይሖዋ ፊት መጥፎ ነገር ማድረግ ጀመሩ።+ ስለዚህ ይሖዋ የሞዓብ+ ንጉሥ ኤግሎን በእስራኤላውያን ላይ እንዲበረታባቸው አደረገ፤ ምክንያቱም በይሖዋ ፊት መጥፎ ነገር አድርገው ነበር። 13 በተጨማሪም አሞናውያንንና+ አማሌቃውያንን+ በእነሱ ላይ አመጣባቸው። እነሱም በእስራኤላውያን ላይ ጥቃት በመሰንዘር የዘንባባ ዛፎች ከተማን+ ያዙ። 14 እስራኤላውያንም የሞዓብን ንጉሥ ኤግሎንን 18 ዓመት አገለገሉ።+ 15 ከዚያም እስራኤላውያን ይሖዋ እንዲረዳቸው ወደ እሱ ጮኹ፤+ ይሖዋም ግራኝ+ የሆነውን ቢንያማዊውን+ የጌራን ልጅ ኤሁድን+ አዳኝ አድርጎ አስነሳላቸው።+ ከጊዜ በኋላ እስራኤላውያን በእሱ በኩል ለሞዓብ ንጉሥ ለኤግሎን ግብር ላኩ። 16 በዚህ ጊዜ ኤሁድ ርዝመቱ አንድ ክንድ* የሆነ በሁለት በኩል ስለት ያለው ሰይፍ ሠርቶ ከልብሱ ሥር በቀኝ ጭኑ ላይ አሰረው። 17 ከዚያም ግብሩን ለሞዓብ ንጉሥ ለኤግሎን አቀረበ። ኤግሎን በጣም ወፍራም ነበር።
18 ኤሁድ ግብሩን ሰጥቶ እንደጨረሰ ግብሩን ተሸክመው የመጡትን ሰዎች አሰናበታቸው። 19 እሱ ግን በጊልጋል+ የሚገኙት የተቀረጹ ምስሎች* ጋ ሲደርስ ተመልሶ በመሄድ “ንጉሥ ሆይ፣ በሚስጥር የምነግርህ አንድ መልእክት አለኝ” አለ። ንጉሡም “እስቲ አንዴ ጸጥታ!” አለ። በዚህ ጊዜ አገልጋዮቹ ሁሉ ጥለውት ወጡ። 20 ንጉሡ፣ ሰገነት ላይ በሚገኘው ቀዝቀዝ ያለ የግል ክፍሉ ውስጥ ብቻውን ተቀምጦ ሳለ ኤሁድ ወደ እሱ ቀረበ። ከዚያም ኤሁድ “ከአምላክ ዘንድ ለአንተ የመጣ መልእክት አለኝ” አለው። በዚህ ጊዜ ንጉሡ ከዙፋኑ* ተነሳ። 21 ስለዚህ ኤሁድ ግራ እጁን ሰዶ በቀኝ ጭኑ በኩል የነበረውን ሰይፍ በመምዘዝ በንጉሡ ሆድ ውስጥ ሻጠው። 22 ከስለቱ በኋላም እጀታው ሆዱ ውስጥ ገባ፤ ኤሁድ ሰይፉን ከሆዱ መልሶ ስላላወጣው ስለቱ በስብ ተሸፈነ፤ ፈርሱም ተዘረገፈ። 23 ኤሁድም በበረንዳው* በኩል ወጣ፤ ሰገነት ላይ ያለውን ክፍል በሮች ግን ዘግቶ ቆልፏቸው ነበር። 24 እሱም ከሄደ በኋላ አገልጋዮቹ መጥተው ሲያዩ ሰገነት ላይ ያለው ክፍል በሮች ተቆልፈው ነበር። በመሆኑም “ቀዝቀዝ ባለው ውስጠኛ ክፍል እየተጸዳዳ* ይሆናል” አሉ። 25 እነሱም እስኪያፍሩ ድረስ ጠበቁ፤ ሆኖም ሰገነት ላይ የሚገኘውን ክፍል በሮች እንዳልከፈተ ባዩ ጊዜ ቁልፉን ወስደው በሮቹን ከፈቱ፤ በዚያም ጌታቸው ሞቶ ወለል ላይ ተዘርሮ ተመለከቱ!
26 ኤሁድ ግን እነሱ ቆመው ሲጠባበቁ ሳለ አመለጠ፤ በተቀረጹት ምስሎች* + በኩል አድርጎም በሰላም ወደ ሰኢራ ደረሰ። 27 እዚያም እንደደረሰ በኤፍሬም ተራራማ አካባቢ+ ቀንደ መለከት ነፋ፤+ እስራኤላውያንም ከተራራማው አካባቢ ወጥተው በእሱ መሪነት አብረውት ወረዱ። 28 ከዚያም “ይሖዋ ጠላቶቻችሁን ሞዓባውያንን በእጃችሁ አሳልፎ ስለሰጣችሁ ተከተሉኝ” አላቸው። እነሱም ተከትለውት በመሄድ ሞዓባውያን እንዳይሻገሩ የዮርዳኖስን መልካዎች* ያዙባቸው፤ አንድም ሰው እንዲሻገር አልፈቀዱም። 29 በዚያን ጊዜም ጠንካራና ጀግና የሆኑ 10,000 ሞዓባውያንን ገደሉ፤+ አንድም ሰው አላመለጠም።+ 30 በዚያ ቀን ሞዓብ በእስራኤል እጅ ተንበረከከ፤ ምድሪቱም ለ80 ዓመት አረፈች።* +
31 ከእሱ በኋላ፣ 600 ፍልስጤማውያንን+ በከብት መውጊያ+ የገደለው የአናት ልጅ ሻምጋር+ ተነሳ፤ እሱም እስራኤልን አዳነ።
4 ሆኖም ኤሁድ ከሞተ በኋላ እስራኤላውያን እንደገና በይሖዋ ፊት መጥፎ ነገር አደረጉ።+ 2 በመሆኑም ይሖዋ በሃጾር ሆኖ ይገዛ ለነበረው ለከነአን ንጉሥ ለያቢን አሳልፎ ሸጣቸው።+ የሠራዊቱም አለቃ በሃሮሼትጎይም+ የሚኖረው ሲሳራ ነበር። 3 ያቢን* የብረት ማጭድ የተገጠመላቸው 900 የጦር ሠረገሎች* + ስለነበሩትና ለ20 ዓመት ክፉኛ ስለጨቆናቸው+ እስራኤላውያን ወደ ይሖዋ ጮኹ።+
4 በዚያን ጊዜ የላጲዶት ሚስት ነቢዪቱ ዲቦራ+ በእስራኤል ውስጥ ፈራጅ ሆና ታገለግል ነበር። 5 እሷም በኤፍሬም ተራራማ አካባቢ፣ በራማና+ በቤቴል+ መካከል ባለው የዲቦራ ዘንባባ ዛፍ ሥር ትቀመጥ ነበር፤ እስራኤላውያንም ለፍርድ ወደ እሷ ይወጡ ነበር። 6 እሷም የአቢኖዓምን ልጅ ባርቅን+ ከቃዴሽንፍታሌም+ አስጠርታ እንዲህ አለችው፦ “የእስራኤል አምላክ ይሖዋ እንዲህ የሚል ትእዛዝ ሰጥቶ የለም? ‘ሂድና ወደ ታቦር ተራራ ዝመት፤* ከአንተም ጋር ከንፍታሌምና ከዛብሎን 10,000 ወንዶችን ውሰድ። 7 እኔም የያቢን ሠራዊት አለቃ የሆነውን ሲሳራን ከጦር ሠረገሎቹና ከሠራዊቱ ጋር ወደ ቂሾን ጅረት* + ወደ አንተ አመጣዋለሁ፤ እሱንም በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ።’”+
8 በዚህ ጊዜ ባርቅ “አብረሽኝ የምትሄጂ ከሆነ እሄዳለሁ፤ አብረሽኝ የማትሄጂ ከሆነ ግን አልሄድም” አላት። 9 እሷም እንዲህ አለችው፦ “በእርግጥ አብሬህ እሄዳለሁ። ይሁንና ይሖዋ ሲሳራን በሴት እጅ አሳልፎ ስለሚሰጠው የምታካሂደው ዘመቻ ለአንተ ክብር አያስገኝልህም።”+ ከዚያም ዲቦራ ተነስታ ከባርቅ ጋር ወደ ቃዴሽ+ ሄደች። 10 ባርቅም ዛብሎንንና ንፍታሌምን+ ወደ ቃዴሽ ጠራቸው፤ 10,000 ሰዎችም የእሱን ዱካ ተከተሉ። ዲቦራም አብራው ወጣች።
11 እንደ አጋጣሚ ሆኖ ቄናዊው+ ሄቤር፣ የሙሴ አማት+ የሆባብ ዘሮች ከሆኑት ከቄናውያን ተለይቶ በቃዴሽ በሚገኘው በጻናኒም ትልቅ ዛፍ አጠገብ ድንኳኑን ተክሎ ነበር።
12 ከዚያም የአቢኖዓም ልጅ ባርቅ ወደ ታቦር ተራራ+ እንደወጣ ለሲሳራ ነገሩት። 13 ሲሳራም ወደ ቂሾን ጅረት* + ለመሄድ ወዲያውኑ የጦር ሠረገሎቹን በሙሉ ይኸውም የብረት ማጭድ የተገጠመላቸውን 900 የጦር ሠረገሎች* እንዲሁም ከእሱ ጋር የነበረውን ሠራዊት ሁሉ ከሃሮሼትጎይም አሰባሰበ። 14 በዚህ ጊዜ ዲቦራ ባርቅን እንዲህ አለችው፦ “ይሖዋ ሲሳራን በእጅህ አሳልፎ የሚሰጥበት ቀን ይህ ስለሆነ ተነስ! ይሖዋ በፊትህ ቀድሞ ይወጣ የለም?” ባርቅም 10,000 ሰዎችን አስከትሎ ከታቦር ተራራ ወረደ። 15 ይሖዋም ሲሳራንና የጦር ሠረገሎቹን በሙሉ እንዲሁም ሠራዊቱን ሁሉ ግራ እንዲጋቡ አደረጋቸው፤+ በባርቅም ሰይፍ አጠፋቸው። በመጨረሻም ሲሳራ ከሠረገላው ላይ ወርዶ በእግሩ መሸሽ ጀመረ። 16 ባርቅም የጦር ሠረገሎቹንና ሠራዊቱን እስከ ሃሮሼትጎይም ድረስ አሳደዳቸው። በመሆኑም የሲሳራ ሠራዊት በሙሉ በሰይፍ ወደቀ፤ አንድም የተረፈ ሰው አልነበረም።+
17 ሆኖም ሲሳራ የቄናዊው የሄቤር ሚስት ወደሆነችው ወደ ኢያዔል+ ድንኳን በእግሩ ሸሸ፤ ምክንያቱም በሃጾር ንጉሥ በያቢንና+ በቄናዊው በሄቤር+ ቤት መካከል ሰላማዊ ግንኙነት ነበር። 18 ኢያዔልም ሲሳራን ልትቀበለው ወጣች፤ ከዚያም “ጌታዬ ና፤ ወደዚህ ግባ። አትፍራ” አለችው። በመሆኑም ወደ እሷ ድንኳን ገባ። እሷም ብርድ ልብስ አለበሰችው። 19 ከዚያም “እባክሽ ስለጠማኝ የምጠጣው ትንሽ ውኃ ስጪኝ” አላት። እሷም የወተት አቁማዳውን ፈትታ የሚጠጣውን ሰጠችው፤+ ከዚያም በድጋሚ ሸፈነችው። 20 እሱም “ድንኳኑ በር ላይ ቁሚ፤ ማንም ሰው መጥቶ ‘እዚህ ሰው አለ?’ ብሎ ቢጠይቅሽ ‘የለም!’ በይ” አላት።
21 የሄቤር ሚስት ኢያዔል ግን የድንኳን ካስማና መዶሻ ወሰደች። ከዚያም ሲሳራ ደክሞት ድብን ያለ እንቅልፍ ወስዶት ሳለ በቀስታ ወደ እሱ ሄዳ ካስማውን ሰሪሳራዎቹ* ላይ በመቸንከር ከመሬት ጋር አጣበቀችው። እሱም ሞተ።+
22 ባርቅ ሲሳራን እያሳደደ ወደዚያ አካባቢ ሄደ፤ ኢያዔልም እሱን ለማግኘት ወጣች፤ ከዚያም “ና፣ የምትፈልገውን ሰው አሳይሃለሁ” አለችው። እሱም ከእሷ ጋር ወደ ውስጥ ገባ፤ ሲሳራንም ካስማው ሰሪሳራዎቹ ላይ እንደተቸነከረ ሞቶ አገኘው።
23 በመሆኑም አምላክ በዚያን ዕለት የከነአን ንጉሥ ያቢን ለእስራኤላውያን እንዲንበረከክ አደረገ።+ 24 እስራኤላውያን የከነአንን+ ንጉሥ ያቢንን እስኪያጠፉት ድረስ እጃቸው በከነአን ንጉሥ በያቢን ላይ ይበልጥ እየበረታ ሄደ።+
5 በዚያን ቀን ዲቦራ+ ከአቢኖዓም ልጅ ከባርቅ+ ጋር ሆና ይህን መዝሙር ዘመረች፦+
3 እናንተ ነገሥታት ስሙ! እናንተ ገዢዎች ጆሯችሁን ስጡ!
ለይሖዋ እዘምራለሁ።
ለእስራኤል አምላክ+ ለይሖዋ የውዳሴ መዝሙር እዘምራለሁ።+
በ40,000 የእስራኤል ወንዶች መካከል፣
አንድ ጋሻ ወይም አንድ ጦር ሊታይ አልቻለም።
ይሖዋን አወድሱ!
10 እናንተ፣ ነጣ ባሉ ቡናማ አህዮች የምትጋልቡ፣
እናንተ፣ ባማሩ ምንጣፎች ላይ የምትቀመጡ፣
እናንተ፣ በመንገድ ላይ የምትሄዱ፣
ይህን ልብ በሉ!
11 የውኃ ቀጂዎች ድምፅ በውኃ መቅጃው ስፍራ ተሰማ፤
እነሱም በዚያ የይሖዋን የጽድቅ ሥራዎች፣
በእስራኤል መንደሮች ውስጥ የሚኖሩ ሕዝቦቹን የጽድቅ ሥራዎች መተረክ ጀመሩ።
የይሖዋም ሕዝቦች ወደ በሮቹ ወረዱ።
12 ዲቦራ+ ሆይ፣ ንቂ፣ ንቂ!
ንቂ፣ ንቂ፣ መዝሙርም ዘምሪ!+
የአቢኖዓም ልጅ ባርቅ+ ሆይ፣ ተነስ! ምርኮኞችህን እየመራህ ሂድ!
13 የተረፉትም ሰዎች ወደ መኳንንቱ ወረዱ፤
የይሖዋ ሕዝቦች ኃያላኑን ለመውጋት ወደ እኔ ወረዱ።
14 በሸለቆው* የነበሩ ሰዎች ምንጫቸው ኤፍሬም ነበር፤
ቢንያም ሆይ፣ እነሱ በሕዝቦችህ መካከል እየተከተሉህ ነው።
15 የይሳኮር መኳንንት ከዲቦራ ጋር ነበሩ፤
እንደ ይሳኮር ሁሉ ባርቅም+ ከእሷ ጋር ነበር።
የሮቤል ቡድኖች ልባቸው በእጅጉ አመንትቶ ነበር።
16 አንተ በመንታ ጭነት መካከል የተቀመጥከው ለምንድን ነው?
ለመንጎቹ ዋሽንታቸውን ሲነፉ ለማዳመጥ ነው?+
የሮቤል ቡድኖች እንደሆነ ልባቸው በእጅጉ አመንትቷል።
አሴር በባሕር ዳርቻ ላይ ሥራ ፈቶ ተቀምጧል፤
በወደቦቹም ላይ ይኖራል።+
ምንም ብር ማርከው አልወሰዱም።+
20 ከዋክብት ከሰማይ ተዋጉ፤
በምሕዋራቸው ላይ ሆነው ከሲሳራ ጋር ተዋጉ።
21 የቂሾን ወንዝ፣
ጥንታዊው ወንዝ፣ የቂሾን ወንዝ ጠራርጎ ወሰዳቸው።+
ነፍሴ* ሆይ፣ ብርቱዎቹን ረገጥሽ።
22 የፈረሶች ኮቴ ሲረግጥ የተሰማው ያን ጊዜ ነበር፣
ድንጉላ ፈረሶቹ በኃይል ይጋልቡ ነበር።+
23 የይሖዋ መልአክ እንዲህ አለ፦ ‘መሮዝን እርገሙ፤
ነዋሪዎቿንም እርገሙ፣
ይሖዋን ለመርዳት አልመጡምና፣
ይሖዋን ለመርዳት ከኃያላኑ ጋር አልመጡም።’
በድንኳን ከሚኖሩ ሴቶች ሁሉ ይልቅ የተባረከች ነች።
25 ውኃ ጠየቀ፣ ወተት ሰጠችው።
ለመኳንንት በሚቀርብበት ጎድጓዳ ሳህን እርጎ ሰጠችው።+
26 እጇን ዘርግታ የድንኳን ካስማ አነሳች፣
በቀኝ እጇም የሠራተኛ መዶሻ ያዘች።
ሲሳራንም ቸነከረችው፣ ጭንቅላቱንም ፈረከሰችው፣
ሰሪሳራውንም ተረከከችው፤ በሳችው።+
27 እሱም በእግሮቿ መካከል ተደፋ፤ በወደቀበት በዚያው ቀረ፤
በእግሮቿ መካከል ተደፋ፣ ወደቀ፤
እዚያው በተደፋበት ተሸንፎ ቀረ።
28 አንዲት ሴት በመስኮት ተመለከተች፣
የሲሳራ እናት በፍርግርጉ አጮልቃ ወደ ውጭ ተመለከተች፣
‘የጦር ሠረገሎቹ ሳይመጡ ለምን ዘገዩ?
የሠረገሎቹ ኮቴ ድምፅስ ምነው ይህን ያህል ዘገየ?’+
29 ጥበበኛ የሆኑት የተከበሩ ወይዛዝርቷ ይመልሱላታል፤
አዎ፣ እሷም ለራሷ እንዲህ ትላለች፣
30 ‘ያገኙትን ምርኮ እየተከፋፈሉ መሆን አለበት፣
ለእያንዳንዱ ተዋጊ አንድ ልጃገረድ* እንዲያውም ሁለት ልጃገረዶች፣*
ለሲሳራም ከምርኮው ላይ ቀለም የተነከሩ ልብሶች፣ አዎ ቀለም የተነከሩ ልብሶች፣
ምርኮውን ለማረኩት ሰዎች አንገት፣
ቀለም የተነከረ ባለ ጥልፍ ልብስ፣ እንዲያውም ሁለት ባለ ጥልፍ ልብስ እየተሰጠ ነው።’
31 ይሖዋ ሆይ፣ ጠላቶችህ ሁሉ ይጥፉ፣+
አንተን የሚወዱ ግን ደምቃ እንደምትወጣ ፀሐይ ይሁኑ።”
6 እስራኤላውያን ግን እንደገና በይሖዋ ፊት መጥፎ ነገር አደረጉ፤+ በመሆኑም ይሖዋ ለሰባት ዓመት ለምድያማውያን አሳልፎ ሰጣቸው።+ 2 የምድያማውያን እጅ በእስራኤል ላይ በረታ።+ እስራኤላውያን በምድያማውያን የተነሳ በተራሮች ላይ፣ በዋሻዎች ውስጥና በቀላሉ በማይደረስባቸው ስፍራዎች ለመደበቂያ የሚሆኑ ቦታዎችን* ለራሳቸው አዘጋጁ።+ 3 እነሱም ዘር በሚዘሩበት ጊዜ ሁሉ ምድያማውያን፣ አማሌቃውያንና+ የምሥራቅ ሰዎች+ ጥቃት ይሰነዝሩባቸው ነበር። 4 እንዲሁም በዙሪያቸው በመስፈር እስከ ጋዛ ድረስ ያለውን የምድሩን ሰብል ያጠፉ ነበር፤ ለእስራኤላውያን የሚበሉት ምንም ነገር አያስተርፉላቸውም፤ በግም ሆነ ከብት ወይም አህያ አያስቀሩላቸውም ነበር።+ 5 ምክንያቱም ከብቶቻቸውንና ድንኳኖቻቸውን ይዘው እንደ አንበጣ መንጋ ብዙ ሆነው ይመጡ ነበር፤+ እነሱም ሆኑ ግመሎቻቸው ለቁጥር የሚያታክቱ ነበሩ፤+ ወደዚያም የሚመጡት ምድሪቱን ለማጥፋት ነበር። 6 በመሆኑም እስራኤላውያን በምድያማውያን የተነሳ ለከፍተኛ ድህነት ተዳረጉ፤ እነሱም ይሖዋ እንዲረዳቸው መጮኽ ጀመሩ።+
7 እስራኤላውያን በምድያማውያን የተነሳ ለእርዳታ ወደ ይሖዋ በጮኹ ጊዜ+ 8 ይሖዋ ነቢይ ላከላቸው፤ እሱም እንዲህ አላቸው፦ “የእስራኤል አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ከግብፅ አወጣኋችሁ፤ በዚህ መንገድ ከባርነት ቤት አላቀኳችሁ።+ 9 ከግብፅ እጅና ከሚጨቁኗችሁ ሁሉ ታደግኳችሁ፤ እነሱንም ከፊታችሁ በማባረር ምድራቸውን ሰጠኋችሁ።+ 10 እንዲሁም “እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ።+ በምድራቸው ላይ የምትኖሩባቸው አሞራውያን የሚያመልኳቸውን አማልክት አትፍሩ” አልኳችሁ።+ እናንተ ግን ቃሌን አልሰማችሁም።’”+
11 በኋላም የይሖዋ መልአክ መጥቶ+ በኦፍራ በሚገኘው በአቢዔዜራዊው+ በዮአስ ትልቅ ዛፍ ሥር ተቀመጠ። የዮአስም ልጅ ጌድዮን+ ከምድያማውያን ተደብቆ በወይን መጭመቂያው ስፍራ ስንዴ እየወቃ ነበር። 12 ከዚያም የይሖዋ መልአክ ተገለጠለትና “አንተ ኃያል ተዋጊ፣ ይሖዋ ከአንተ ጋር ነው”+ አለው። 13 ጌድዮንም እንዲህ አለው፦ “ይቅርታ ጌታዬ፤ ታዲያ ይሖዋ ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ሁሉ የሚደርስብን ለምንድን ነው?+ አባቶቻችን ‘ይሖዋ ከግብፅ ምድር አላወጣንም?’+ እያሉ ይነግሩን የነበረው ድንቅ ሥራው ሁሉ የት አለ?+ አሁን ይሖዋ ትቶናል፤+ ለምድያማውያንም እጅ አሳልፎ ሰጥቶናል።” 14 ይሖዋም ፊት ለፊቱ ቆመና እንዲህ አለው፦ “በል ባለህ ኃይል ሂድ፤ እስራኤልንም ከምድያማውያን እጅ ታድናለህ።+ የምልክህ እኔ አይደለሁም?” 15 ጌድዮንም መልሶ እንዲህ አለው፦ “ይሖዋ ሆይ፣ ይቅርታ አድርግልኝ፤ እኔ እንዴት እስራኤልን ላድን እችላለሁ? የእኔ ጎሳ* እንደሆነ ከምናሴ ነገድ የመጨረሻው ነው፤ እኔም ብሆን በአባቴ ቤት ውስጥ እዚህ ግባ የምባል አይደለሁም።” 16 ሆኖም ይሖዋ “እኔ ከአንተ ጋር ስለምሆን+ ምድያማውያንን ልክ እንደ አንድ ሰው ትመታቸዋለህ” አለው።
17 ከዚያም ጌድዮን እንዲህ አለው፦ “እንግዲህ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ ከእኔ ጋር እየተነጋገርክ ያለኸው አንተ ስለመሆንህ አንድ ምልክት አሳየኝ። 18 ደግሞም ተመልሼ መጥቼ ስጦታዬን በፊትህ እስካቀርብ ድረስ እባክህ ከዚህ አትሂድ”+ አለው። እሱም “እስክትመለስ ድረስ እዚሁ እጠብቅሃለሁ” አለው። 19 ጌድዮንም ገብቶ አንድ የፍየል ጠቦትና ከአንድ ኢፍ* ዱቄት ቂጣ* አዘጋጀ።+ ሥጋውን በቅርጫት፣ መረቁን ደግሞ በድስት አድርጎ ወደ እሱ ይዞ በመምጣት በትልቁ ዛፍ ሥር አቀረበለት።
20 የእውነተኛው አምላክ መልአክም “ሥጋውንና ቂጣውን ወስደህ እዚያ ባለው ዓለት ላይ አስቀምጣቸው፤ መረቁንም አፍስሰው” አለው። እሱም እንዲሁ አደረገ። 21 ከዚያም የይሖዋ መልአክ በእጁ ይዞት የነበረውን በትር ዘርግቶ በጫፉ ሥጋውንና ቂጣውን ነካ፤ በዚህ ጊዜ እሳት ከዓለቱ ወጥቶ ሥጋውንና ቂጣውን በላ።+ ከዚያም የይሖዋ መልአክ ከእይታው ተሰወረ። 22 በዚህ ጊዜ ጌድዮን የይሖዋ መልአክ እንደነበር አስተዋለ።+
ወዲያውኑም “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ፣ የይሖዋን መልአክ ፊት ለፊት አይቻለሁና ወዮልኝ!” አለ።+ 23 ሆኖም ይሖዋ “ሰላም ለአንተ ይሁን። አትፍራ፤+ አትሞትም” አለው። 24 ጌድዮንም በዚያ ለይሖዋ መሠዊያ ሠራ፤ መሠዊያውም እስከ ዛሬ ድረስ ‘ይሖዋ ሻሎም’* + ተብሎ ይጠራል። አሁንም ድረስ የአቢዔዜራውያን በሆነችው በኦፍራ ይገኛል።
25 በዚያ ምሽት ይሖዋ ጌድዮንን እንዲህ አለው፦ “የአባትህ ንብረት የሆነውን ሰባት ዓመት የሞላውን ሁለተኛውን ወይፈን ውሰድ፤ የአባትህ የሆነውን የባአልን መሠዊያም አፈራርስ፤ አጠገቡም የሚገኘውን የማምለኪያ ግንድ* ሰባብር።+ 26 በዚህ ምሽግ አናት ላይ ድንጋይ ደርድረህ ለአምላክህ ለይሖዋ መሠዊያ ከሠራህ በኋላ ሁለተኛውን ወይፈን ወስደህ በምትሰባብረው የማምለኪያ ግንድ* እንጨት ላይ የሚቃጠል መባ አድርገህ አቅርበው።” 27 ስለዚህ ጌድዮን ከአገልጋዮቹ መካከል አሥር ሰዎችን ወስዶ ልክ ይሖዋ እንዳለው አደረገ። ይሁንና የአባቱን ቤትና የከተማዋን ሰዎች በጣም ስለፈራ ይህን ያደረገው በቀን ሳይሆን በሌሊት ነበር።
28 የከተማዋ ሰዎች በማግስቱ በማለዳ ሲነሱ የባአል መሠዊያ ፈራርሶ፣ አጠገቡ የነበረው የማምለኪያ ግንድም* ተሰባብሮ እንዲሁም ሁለተኛው ወይፈን በተሠራው መሠዊያ ላይ ተሠውቶ ተመለከቱ። 29 እነሱም እርስ በርሳቸው “ይህን ያደረገው ማን ነው?” ተባባሉ። ሁኔታውንም ካጣሩ በኋላ “ይህን ያደረገው የዮአስ ልጅ ጌድዮን ነው” አሉ። 30 በመሆኑም የከተማዋ ሰዎች ዮአስን “ልጅህ የባአልን መሠዊያ ስላፈራረሰና አጠገቡ የነበረውን የማምለኪያ ግንድ* ስለሰባበረ ወደዚህ አውጣው፤ መሞት አለበት” አሉት። 31 ከዚያም ዮአስ+ እሱን የሚቃወሙትን ሰዎች ሁሉ እንዲህ አላቸው፦ “ለባአል መሟገት ይኖርባችኋል? እሱን ለማዳን መሞከርስ ይገባችኋል? ለእሱ የሚሟገት ማንኛውም ሰው በዚህ ጠዋት መሞት ይገባዋል።+ እሱ አምላክ ከሆነ አንድ ሰው መሠዊያውን ስላፈረሰበት ለራሱ ይሟገት።”+ 32 እሱም “ባአል አንድ ሰው መሠዊያውን ስላፈረሰበት ለራሱ ይሟገት” በማለት ጌድዮንን በዚያ ቀን የሩባአል* ብሎ ጠራው።
33 ምድያማውያን፣+ አማሌቃውያንና+ የምሥራቅ ሰዎች በሙሉ ግንባር ፈጥረው+ ወደ ኢይዝራኤል ሸለቆ* በመሻገር በዚያ ሰፈሩ። 34 የይሖዋም መንፈስ በጌድዮን ላይ ወረደ፤* + እሱም ቀንደ መለከት ነፋ፤+ አቢዔዜራውያንም+ እሱን በመደገፍ ተከትለውት ወጡ። 35 ከዚያም በመላው ምናሴ መልእክተኞችን ላከ፤ እነሱም እሱን በመደገፍ ተከትለውት ወጡ። በተጨማሪም ወደ አሴር፣ ወደ ዛብሎንና ወደ ንፍታሌም መልእክተኞችን ላከ፤ እነሱም ከእሱ ጋር ለመገናኘት ወጡ።
36 ከዚያም ጌድዮን እውነተኛውን አምላክ እንዲህ አለው፦ “ቃል በገባኸው መሠረት በእኔ አማካኝነት እስራኤልን የምታድን ከሆነ+ 37 ይኸው አውድማው ላይ የተባዘተ የበግ ፀጉር አስቀምጣለሁ። በዙሪያው ያለው ምድር በሙሉ ደረቅ ሆኖ የበግ ፀጉሩ ላይ ብቻ ጤዛ ከተገኘ ቃል በገባኸው መሠረት በእኔ አማካኝነት እስራኤልን እንደምታድን አውቃለሁ።” 38 ልክ እንደዚሁም ሆነ። በማግስቱ በማለዳ ተነስቶ የበግ ፀጉሩን ሲጨምቀው ከበግ ፀጉሩ ላይ የወጣው ውኃ በትልቅ ጎድጓዳ ሳህን ሙሉ ሆነ። 39 ሆኖም ጌድዮን እውነተኛውን አምላክ እንዲህ አለው፦ “እባክህ ቁጣህ በእኔ ላይ አይንደድ፤ አንድ ጊዜ ብቻ እንድናገር ፍቀድልኝ። ከበግ ፀጉሩ ጋር በተያያዘ አንድ ሌላ ሙከራ ብቻ ላድርግ። እባክህ የበግ ፀጉሩ ብቻ ደረቅ ሆኖ ምድሩ በሙሉ ጤዛ እንዲሆን አድርግ።” 40 በመሆኑም አምላክ በዚያ ሌሊት እንደዚሁ አደረገ፤ የበግ ፀጉሩ ብቻ ደረቅ ሆኖ ምድሩ በሙሉ ጤዛ ሆነ።
7 ከዚያም የሩባአል የተባለው ጌድዮንና+ ከእሱ ጋር የነበሩት ሰዎች በሙሉ በማለዳ ተነስተው በሃሮድ ምንጭ አጠገብ ሰፈሩ፤ የምድያማውያን ሰፈር ደግሞ ከእሱ በስተ ሰሜን በሞሬ ኮረብታ በሸለቋማው ሜዳ* ላይ ይገኝ ነበር። 2 ይሖዋም ጌድዮንን እንዲህ አለው፦ “ምድያማውያንን በእጃቸው አሳልፌ እንዳልሰጥ አብረውህ ያሉት ሰዎች በጣም ብዙ ናቸው።+ ይህን ባደርግ እስራኤላውያን ‘የገዛ እጄ አዳነኝ’+ ብለው ይታበዩብኛል። 3 በመሆኑም እባክህ ሕዝቡ በተሰበሰበበት ‘ከመካከላችሁ የፈራና የተሸበረ ካለ ወደ ቤት ይመለስ’ ብለህ ተናገር።”+ ስለዚህ ጌድዮን ፈተናቸው። በዚህ ጊዜ ከሕዝቡ መካከል 22,000 ሰዎች ወደ ቤታቸው ተመለሱና 10,000 ብቻ ቀሩ።
4 ይሖዋም እንደገና ጌድዮንን እንዲህ አለው፦ “አሁንም ሰዎቹ በጣም ብዙ ናቸው። በዚያ እነሱን እንድፈትንልህ ወደ ውኃው ይዘሃቸው ውረድ። እኔም ‘ይህ ከአንተ ጋር ይሄዳል’ የምልህ ከአንተ ጋር ይሄዳል፤ ‘ይህ ከአንተ ጋር አይሄድም’ የምልህ ግን ከአንተ ጋር አይሄድም።” 5 እሱም ሰዎቹን ወደ ውኃው ይዟቸው ወረደ።
ከዚያም ይሖዋ ጌድዮንን “ልክ እንደ ውሻ ውኃውን በምላሱ እየጨለፈ የሚጠጣውን ሁሉ በጉልበታቸው ተንበርክከው ከሚጠጡት ለይ” አለው። 6 ውኃውን በእጃቸው እየጨለፉ የሚጠጡት ሰዎች ቁጥር 300 ነበር። የቀሩት ሰዎች ሁሉ ግን ውኃ ለመጠጣት በጉልበታቸው ተንበረከኩ።
7 ይሖዋም ጌድዮንን እንዲህ አለው፦ “ውኃውን በእጃቸው እየጨለፉ በጠጡት 300 ሰዎች አድናችኋለሁ፤ ምድያማውያንንም በእጃችሁ አሳልፌ እሰጣችኋለሁ።+ የቀሩት ሰዎች ሁሉ ግን ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ አሰናብታቸው።” 8 በመሆኑም ከሕዝቡ ላይ ስንቃቸውንና ቀንደ መለከታቸውን ከተቀበሉ በኋላ ጌድዮን 300ዎቹን ብቻ አስቀርቶ ሌሎቹን እስራኤላውያን በሙሉ ወደ ቤታቸው አሰናበታቸው። የምድያማውያኑ ሰፈር የሚገኘው ከእሱ በታች በሸለቋማው ሜዳ ላይ ነበር።+
9 በዚያ ምሽት ይሖዋ ጌድዮንን እንዲህ አለው፦ “ተነስ፤ በእጅህ አሳልፌ ስለሰጠሁህ በሰፈሩ ላይ ጥቃት ሰንዝር።+ 10 በሰፈሩ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ከፈራህ ግን ከአገልጋይህ ከፑራ ጋር ወደ ሰፈሩ ውረድ። 11 የሚናገሩትንም ነገር አዳምጥ፤ ከዚያም በሰፈሩ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ድፍረት ታገኛለህ።”* ስለዚህ እሱና አገልጋዩ ፑራ ወርደው ሠራዊቱ ወደሰፈረበት ቦታ ተጠጉ።
12 ምድያማውያንና አማሌቃውያን እንዲሁም የምሥራቅ ሰዎች በሙሉ+ ሸለቋማውን ሜዳ ልክ እንደ አንበጣ መንጋ ወረውት ነበር፤ ግመሎቻቸውም በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ ለቁጥር የሚያታክቱ ነበሩ።+ 13 ጌድዮንም እዚያ ደረሰ፤ በዚህ ጊዜ አንድ ሰው ለጓደኛው እንዲህ በማለት አንድ ሕልም እየነገረው ነበር፦ “ያለምኩት ሕልም ይህ ነው። አንድ የገብስ ዳቦ እየተንከባለለ ወደ ምድያም ሰፈር መጣ። ከዚያም ወደ አንድ ድንኳን በመምጣት በኃይል መትቶ ጣለው።+ ድንኳኑንም ገለበጠው፤ ድንኳኑም መሬት ላይ ተነጠፈ።” 14 ጓደኛውም እንዲህ አለው፦ “ይሄማ ከዮአስ ልጅ ከእስራኤላዊው ከጌድዮን ሰይፍ በስተቀር ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም።+ አምላክ ምድያማውያንንና ሰፈሩን በሙሉ በእጁ አሳልፎ ሰጥቶታል።”+
15 ጌድዮንም ሕልሙንና ፍቺውን ሲሰማ ለአምላክ ሰገደ።+ ከዚያም ወደ እስራኤላውያን ሰፈር ተመልሶ “ተነሱ፤ ይሖዋ የምድያማውያንን ሰፈር በእጃችሁ አሳልፎ ሰጥቷችኋል” አላቸው። 16 በመቀጠልም 300ዎቹን ሰዎች በሦስት ቡድን ከፈላቸው፤ ለሁሉም ቀንደ መለከትና+ በውስጣቸው ችቦ ያለባቸው ትላልቅ ባዶ ማሰሮዎች ሰጣቸው። 17 ከዚያም እንዲህ አላቸው፦ “ልብ ብላችሁ ተመልከቱኝ፤ እኔ የማደርገውንም አድርጉ። ወደ ሰፈሩ ዳርቻ በምጠጋበት ጊዜ ልክ እኔ እንደማደርገው አድርጉ። 18 እኔና ከእኔ ጋር ያሉት ሁሉ ቀንደ መለከቶቻችንን ስንነፋ እናንተም በሰፈሩ ዙሪያ ሁሉ ቀንደ መለከቶቻችሁን ነፍታችሁ ‘ለይሖዋና ለጌድዮን!’ ብላችሁ ጩኹ።”
19 ከዚያም ጌድዮንና ከእሱ ጋር የነበሩት 100 ሰዎች በመካከለኛው ክፍለ ሌሊት* መጀመሪያ ላይ ዘብ ጠባቂዎቹ ገና እንደተቀያየሩ ወደ ሰፈሩ ዳርቻ ተጠጉ። እነሱም ቀንደ መለከቶቻቸውን ነፉ፤+ የያዟቸውንም ትላልቅ የውኃ ማሰሮዎች ሰባበሩ።+ 20 በዚህ ጊዜ ሦስቱም ቡድኖች ቀንደ መለከቶቻቸውን ነፉ፤ ትላልቆቹንም ማሰሮዎች ሰባበሩ። ችቦዎቹን በግራ እጃቸው ይዘው በቀኝ እጃቸው የያዟቸውን ቀንደ መለከቶች እየነፉ “የይሖዋና የጌድዮን ሰይፍ!” በማለት ጮኹ። 21 እያንዳንዱም ሰው በሰፈሩ ዙሪያ ቦታ ቦታውን ይዞ ቆሞ ነበር፤ ሠራዊቱም ሁሉ ሮጠ፤ እየጮኸም ሸሸ።+ 22 ሦስት መቶዎቹ ሰዎችም ቀንደ መለከቶቹን መንፋታቸውን ቀጠሉ፤ ይሖዋም በሰፈሩ ውስጥ ያለው እያንዳንዱ ሰው አንዱ በሌላው ላይ ሰይፉን እንዲመዝበት አደረገ፤+ ሠራዊቱም በጸሬራህ አቅጣጫ እስከ ቤትሺጣ እንዲሁም ከጣባት አጠገብ እስከምትገኘው እስከ አቤልምሆላ+ ዳርቻ ድረስ ሸሸ።
23 እስራኤላውያንም ከንፍታሌም፣ ከአሴርና ከመላው ምናሴ+ ተጠርተው አንድ ላይ በመሰባሰብ ምድያማውያንን አሳደዷቸው። 24 ጌድዮንም በኤፍሬም ተራራማ አካባቢዎች ለሚኖሩ ሁሉ “በምድያማውያን ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ውረዱ፤ እስከ ቤትባራ ድረስ ያሉትን ውኃዎችና ዮርዳኖስን ያዙ” ብለው እንዲነግሯቸው መልእክተኞችን ላከ። በመሆኑም የኤፍሬም ሰዎች በሙሉ ተጠሩ፤ እነሱም እስከ ቤትባራ ድረስ ያሉትን ውኃዎችና ዮርዳኖስን ያዙ። 25 በተጨማሪም ሁለቱን የምድያም መኳንንት ማለትም ኦሬብን+ እና ዜብን ያዙ፤ ኦሬብን በኦሬብ ዓለት ላይ ገደሉት፤ ዜብን ደግሞ በዜብ የወይን መጭመቂያ ላይ ገደሉት። ምድያማውያንንም ማሳደዳቸውን ተያያዙት፤+ የኦሬብን እና የዜብን ጭንቅላት በዮርዳኖስ አካባቢ ወደነበረው ወደ ጌድዮን አመጡ።
8 ከዚያም የኤፍሬም ሰዎች ጌድዮንን “እንዴት እንዲህ ያለ ነገር ታደርግብናለህ? ከምድያማውያን ጋር ለመዋጋት ስትወጣ ያልጠራኸን ለምንድን ነው?”+ አሉት። የመረረ ጥልም ተጣሉት።+ 2 እሱ ግን እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ ካደረጋችሁት ጋር ሲነጻጸር እኔ ምን አደረግኩ? የኤፍሬም ቃርሚያ+ ከአቢዔዜር+ የወይን መከር አይሻልም? 3 አምላክ የምድያማውያንን መኳንንት ኦሬብን እና ዜብን አሳልፎ የሰጠው ለእናንተ ነው፤+ ታዲያ እናንተ ካደረጋችሁት ጋር ሲነጻጸር እኔ ምን አደረግኩ?” እነሱም በዚህ መንገድ ሲያነጋግራቸው* ቁጣቸው በረደ።*
4 ከዚያም ጌድዮን ወደ ዮርዳኖስ መጥቶ ወንዙን ተሻገረ። እሱም ሆነ ከእሱ ጋር የነበሩት 300 ሰዎች ደክሟቸው የነበረ ቢሆንም ጠላቶቻቸውን ከማሳደድ ወደኋላ አላሉም ነበር። 5 ስለዚህ ጌድዮን የሱኮትን ሰዎች “የምድያማውያን ነገሥታት የሆኑትን ዘባህን እና ጻልሙናን በማሳደድ ላይ ስለሆንኩና የሚከተሉኝም ሰዎች ስለደከማቸው እባካችሁ ዳቦ ስጧቸው” አላቸው። 6 የሱኮት መኳንንት ግን “ለሠራዊትህ ዳቦ የምንሰጠው ለመሆኑ የዘባህ እና የጻልሙና መዳፍ እጅህ ገብቷል?” አሉት። 7 በዚህ ጊዜ ጌድዮን “እንግዲያው ይሖዋ ዘባህን እና ጻልሙናን በእጄ አሳልፎ ሲሰጠኝ በምድረ በዳ እሾህና አሜኬላ ሥጋችሁን እተለትላለሁ”+ አላቸው። 8 ከዚያም ወደ ጰኑኤል ወጣ፤ ለእነሱም ተመሳሳይ ጥያቄ አቀረበላቸው፤ የጰኑኤል ሰዎችም የሱኮት ሰዎች የሰጡትን ዓይነት መልስ ሰጡት። 9 ስለዚህ የጰኑኤልንም ሰዎች “በሰላም በምመለስበት ጊዜ ይህን ግንብ አፈርሰዋለሁ”+ አላቸው።
10 በዚህ ጊዜ ዘባህ እና ጻልሙና ከሠራዊታቸው ጋር በቃርቆር ሰፍረው ነበር፤ የሠራዊቱም ቁጥር ወደ 15,000 ገደማ ነበር። ቀደም ሲል 120,000 የሚያህሉ ሰይፍ የታጠቁ ወንዶች ተገድለው ስለነበር ከመላው የምሥራቅ ሰዎች+ ሠራዊት የቀሩት እነዚህ ብቻ ነበሩ። 11 ጌድዮንም ከኖባህ እና ከዮግበሃ+ በስተ ምሥራቅ የሚኖሩ ዘላኖች የሚሄዱበትን መንገድ ተከትሎ ወጣ፤ የጠላት ሠራዊት ተዘናግቶ ባለበትም ወቅት በሰፈሩ ላይ ጥቃት ሰነዘረ። 12 ሁለቱ ምድያማውያን ነገሥታት ማለትም ዘባህ እና ጻልሙና በሸሹም ጊዜ አሳዶ ያዛቸው፤ መላውን ሠራዊትም አሸበረው።
13 ከዚያም የዮአስ ልጅ ጌድዮን ወደ ሄሬስ ሽቅብ በሚያስወጣው መንገድ በኩል አድርጎ ከውጊያው ተመለሰ። 14 እሱም በመንገድ ላይ የሱኮት ሰው የሆነ አንድ ወጣት ያዘ፤ እሱንም መረመረው። በመሆኑም ወጣቱ የሱኮት መኳንንትና ሽማግሌዎች የሆኑ የ77 ሰዎችን ስም ጻፈለት። 15 ጌድዮንም ወደ ሱኮት ሰዎች ሄዶ “‘ለደከሙት ሰዎችህ ዳቦ የምንሰጠው ለመሆኑ የዘባህ እና የጻልሙና መዳፍ እጅህ ገብቷል?’ በማለት የተሳለቃችሁብኝ ዘባህ እና ጻልሙና እነዚሁላችሁ” አላቸው።+ 16 ከዚያም የከተማዋን ሽማግሌዎች ወሰደ፤ በምድረ በዳ እሾህና አሜኬላም ለሱኮት ሰዎች ትምህርት ሰጣቸው።+ 17 እንዲሁም የጰኑኤልን ግንብ አፈረሰ፤+ የከተማዋንም ሰዎች ገደለ።
18 ጌድዮንም ዘባህን እና ጻልሙናን “ለመሆኑ በታቦር የገደላችኋቸው ሰዎች ምን ዓይነት ነበሩ?” አላቸው። እነሱም መልሰው “እንደ አንተ ዓይነት ነበሩ፤ እያንዳንዳቸውም የንጉሥ ልጅ ይመስሉ ነበር” አሉት። 19 በዚህ ጊዜ “እነሱ የእናቴ ልጆች ወንድሞቼ ነበሩ። ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ፣ በሕይወት ትታችኋቸው ቢሆን ኖሮ አልገድላችሁም ነበር” አላቸው። 20 ከዚያም የበኩር ልጁን የቴርን “ተነስ፤ ግደላቸው” አለው። ወጣቱ ግን ሰይፉን አልመዘዘም፤ ምክንያቱም ገና ወጣት ስለሆነ ፈርቶ ነበር። 21 በመሆኑም ዘባህ እና ጻልሙና “የሰው ማንነት የሚለካው በኃይሉ ስለሆነ አንተው ራስህ ተነስና ግደለን” አሉት። በመሆኑም ጌድዮን ተነስቶ ዘባህን እና ጻልሙናን+ ገደላቸው፤ በግመሎቻቸው አንገት ላይ የነበሩትንም የሩብ ጨረቃ ቅርጽ ያላቸው ጌጣጌጦች ወሰደ።
22 ከጊዜ በኋላም የእስራኤል ሰዎች ጌድዮንን “ከምድያማውያን እጅ ስለታደግከን አንተ፣ ልጆችህና የልጅ ልጆችህ ግዙን” አሉት።+ 23 ጌድዮን ግን “እኔ አልገዛችሁም፤ ልጄም ቢሆን አይገዛችሁም። የሚገዛችሁ ይሖዋ ነው”+ አላቸው። 24 ከዚያም ጌድዮን “አንድ ነገር ልጠይቃችሁ፦ እያንዳንዳችሁ በምርኮ ካገኛችሁት ላይ የአፍንጫ ሎቲዎችን ስጡኝ” አላቸው። (ምክንያቱም ድል የሆኑት ሕዝቦች እስማኤላውያን+ ስለነበሩ የወርቅ የአፍንጫ ሎቲዎች ነበሯቸው።) 25 እነሱም “በደስታ እንሰጣለን” አሉት። ከዚያም መጎናጸፊያ አነጠፉ፤ እያንዳንዱም ሰው በምርኮ ካገኘው ውስጥ የአፍንጫ ሎቲውን እዚያ ላይ ጣለ። 26 የሩብ ጨረቃ ቅርጽ ካላቸው ጌጣጌጦች፣ ከአንገት ሐብል ማጫወቻዎች፣ የምድያም ነገሥታት ይለብሷቸው ከነበሩት ቀይ ሐምራዊ ቀለም የተነከሩ የሱፍ ልብሶች እንዲሁም በግመሎቹ ላይ ከነበሩት የአንገት ጌጦች በተጨማሪ እንዲሰጡት የጠየቃቸው የወርቅ የአፍንጫ ሎቲዎች ክብደት 1,700 የወርቅ ሰቅል* ነበር።+
27 ጌድዮንም በወርቁ ኤፉድ+ ሠራ፤ ሰዎች እንዲያዩትም በከተማው በኦፍራ+ አስቀመጠው፤ እስራኤላውያንም በሙሉ በዚያ ከእሱ ጋር መንፈሳዊ ምንዝር ፈጸሙ፤+ ኤፉዱም ለጌድዮንና ለቤተሰቡ ወጥመድ ሆነ።+
28 በዚህ መንገድ ምድያማውያን+ ለእስራኤላውያን ተገዙ፤ ከዚያ በኋላም ተገዳድረዋቸው አያውቁም፤* በጌድዮን ዘመን ምድሪቱ ለ40 ዓመት አረፈች።* +
29 የዮአስ ልጅ የሩባአልም+ ወደ ቤቱ ተመልሶ በዚያ መኖሩን ቀጠለ።
30 ጌድዮንም ብዙ ሚስቶች ስለነበሩት 70 ወንዶች ልጆች* ነበሩት። 31 በሴኬም የነበረችው ቁባቱም ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ እሱም ስሙን አቢሜሌክ+ አለው። 32 የዮአስ ልጅ ጌድዮንም ዕድሜ ጠግቦ ሞተ፤ የአቢዔዜራውያን+ በሆነችው በኦፍራ በሚገኘው በአባቱ በዮአስ መቃብር ተቀበረ።
33 እስራኤላውያን ጌድዮን ከሞተ ብዙም ሳይቆይ እንደገና ከባአል ጋር መንፈሳዊ ምንዝር ፈጸሙ፤+ ባአልበሪትንም አምላካቸው አደረጉት።+ 34 እስራኤላውያንም በዙሪያቸው ከነበሩት ጠላቶቻቸው ሁሉ እጅ የታደጋቸውን+ አምላካቸውን ይሖዋን አላስታወሱም፤+ 35 እንዲሁም የሩባአል የተባለው ጌድዮን ለእስራኤል ያደረገውን ጥሩ ነገር ሁሉ አስበው ለቤተሰቡ ታማኝ ፍቅር አላሳዩም።+
9 ከጊዜ በኋላ የየሩባአል ልጅ አቢሜሌክ+ በሴኬም ወደሚገኙት የእናቱ ወንድሞች ሄዶ እነሱንና የአያቱን ቤተሰብ* በሙሉ እንዲህ አላቸው፦ 2 “እባካችሁ የሴኬምን መሪዎች* ሁሉ እንዲህ ብላችሁ ጠይቋቸው፦ ‘70ዎቹ የየሩባአል ልጆች+ በሙሉ ቢገዟችሁ ይሻላችኋል ወይስ አንድ ሰው ቢገዛችሁ? ደግሞም እኔ የአጥንታችሁ ፍላጭ፣ የሥጋችሁ ቁራጭ* መሆኔን አስታውሱ።’”
3 በመሆኑም የእናቱ ወንድሞች እሱን ወክለው ለሴኬም መሪዎች በሙሉ ይህንኑ ነገሯቸው፤ እነሱም “እሱ እኮ የገዛ ወንድማችን ነው” በማለት ልባቸው አቢሜሌክን ወደመከተል አዘነበለ። 4 እነሱም ከባአልበሪት+ ቤት* 70 የብር ሰቅል ሰጡት፤ አቢሜሌክም ተከታዮቹ እንዲሆኑ በዚህ ገንዘብ ሥራ ፈቶችንና ወሮበሎችን ቀጠረበት። 5 ከዚያም በኦፍራ+ ወደሚገኘው ወደ አባቱ ቤት ሄዶ ወንድሞቹን ማለትም 70ዎቹን የየሩባአል ልጆች በአንድ ድንጋይ ላይ ገደላቸው።+ በሕይወት የተረፈው የሁሉም ታናሽ የሆነው የየሩባአል ልጅ ኢዮዓታም ብቻ ነበር፤ ምክንያቱም እሱ ተደብቆ ነበር።
6 ከዚያም የሴኬም መሪዎች ሁሉ እንዲሁም የቤትሚሎ ሰዎች በሙሉ በአንድነት ተሰብስበው በመሄድ አቢሜሌክን በትልቁ ዛፍ አጠገብ ይኸውም በሴኬም በነበረው ዓምድ አጠገብ አነገሡት።+
7 ኢዮዓታምም ይህን በነገሩት ጊዜ ወዲያውኑ ሄዶ በገሪዛን ተራራ+ አናት ላይ ቆመ፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ የሴኬም መሪዎች እኔን ስሙኝ፤ ከዚያም አምላክ ይሰማችኋል።
8 “ከዕለታት አንድ ቀን ዛፎች በላያቸው የሚነግሥ ንጉሥ ለመቀባት ሄዱ። በመሆኑም የወይራ ዛፍን ‘በእኛ ላይ ንገሥ’+ አሉት። 9 ሆኖም የወይራ ዛፍ ‘ሄጄ ከሌሎች ዛፎች በላይ ለመወዛወዝ ስል አምላክንና ሰዎችን ለማክበር የሚጠቀሙበትን ዘይቴን* መስጠት ልተው?’ አላቸው። 10 ከዚያም ዛፎቹ የበለስን ዛፍ ‘መጥተህ በእኛ ላይ ንገሥ’ አሉት። 11 የበለስ ዛፍ ግን ‘ሄጄ ከሌሎች ዛፎች በላይ ለመወዛወዝ ስል ጣፋጭና መልካም ፍሬዬን መስጠት ልተው?’ አላቸው። 12 በመቀጠልም ዛፎቹ የወይን ተክልን ‘መጥተህ በእኛ ላይ ንገሥ’ አሉት። 13 የወይን ተክልም መልሶ ‘ሄጄ ከሌሎች ዛፎች በላይ ለመወዛወዝ ስል አምላክንና ሰዎችን የሚያስደስተውን አዲስ የወይን ጠጅ መስጠቴን ልተው?’ አላቸው። 14 በመጨረሻም ሌሎቹ ዛፎች ሁሉ የእሾህ ቁጥቋጦን ‘መጥተህ በእኛ ላይ ንገሥ’+ አሉት። 15 በዚህ ጊዜ የእሾህ ቁጥቋጦው ዛፎቹን እንዲህ አላቸው፦ ‘በእናንተ ላይ ንጉሥ እንድሆን የምትቀቡኝ እውነት ከልባችሁ ከሆነ መጥታችሁ በጥላዬ ሥር ተጠለሉ። ካልሆነ ግን እሳት ከእሾህ ቁጥቋጦው ወጥቶ አርዘ ሊባኖሶችን ያቃጥል።’
16 “ለመሆኑ አቢሜሌክን ንጉሥ ያደረጋችሁት+ በየዋህነትና በቅንነት ነው? ለየሩባአልና ለቤተሰቡ ጥሩነት አሳይታችኋል? የሚገባውን ውለታስ መልሳችሁለታል? 17 አባቴ ለእናንተ ሲል በተዋጋ ጊዜ+ እናንተን ከምድያማውያን እጅ ለመታደግ ሕይወቱን* አደጋ ላይ ጥሏል።+ 18 እናንተ ግን ዛሬ በአባቴ ቤተሰብ ላይ ተነሳችሁ፤ 70 ልጆቹንም በአንድ ድንጋይ ላይ ገደላችኋቸው።+ ወንድማችሁ ስለሆነ ብቻ ከባሪያይቱ የወለደውን ልጁን አቢሜሌክን+ በሴኬም መሪዎች ላይ አነገሣችሁት። 19 በዛሬው ዕለት ለየሩባአልና ለቤተሰቡ ይህን ያደረጋችሁት በየዋህነትና በቅንነት ከሆነ በአቢሜሌክ ደስ ይበላችሁ፤ እሱም በእናንተ ደስ ይበለው። 20 ይህ ካልሆነ ግን እሳት ከአቢሜሌክ ወጥቶ የሴኬምን መሪዎችና ቤትሚሎን+ ያቃጥል፤ እንዲሁም እሳት ከሴኬም መሪዎችና ከቤትሚሎ ወጥቶ አቢሜሌክን ያቃጥል።”+
21 ከዚያም ኢዮዓታም+ ወደ በኤር ሸሽቶ አመለጠ፤ በወንድሙ በአቢሜሌክ የተነሳም በዚያ ኖረ።
22 አቢሜሌክም በእስራኤል ላይ ሦስት ዓመት ገዛ።* 23 ከዚያም አምላክ በአቢሜሌክና በሴኬም መሪዎች መካከል ቅራኔ እንዲፈጠር አደረገ፤* እነሱም በአቢሜሌክ ላይ ተንኮል አሴሩበት። 24 ይህም የሆነው ወንድሞቹን የገደለውን አቢሜሌክንና ወንድሞቹን እንዲገድል የረዱትን የሴኬምን መሪዎች በሞቱት ሰዎች ደም ተጠያቂ በማድረግ+ በ70ዎቹ የየሩባአል ልጆች ላይ የተፈጸመውን ግፍ ለመበቀል ነው። 25 በመሆኑም የሴኬም መሪዎች አድብተው እሱን የሚጠባበቁ ሰዎችን በተራሮች አናት ላይ መደቡ፤ እነሱም በአጠገባቸው የሚያልፈውን መንገደኛ ሁሉ ይዘርፉ ነበር። በኋላም ሁኔታው ለአቢሜሌክ ተነገረው።
26 ከዚያም የኤቤድ ልጅ ገአል ከወንድሞቹ ጋር ወደ ሴኬም ተሻገረ፤+ የሴኬምም መሪዎች እምነት ጣሉበት። 27 እነሱም ወደ እርሻ ወጥተው የወይን ፍሬያቸውን ከሰበሰቡ በኋላ ጨመቁት፤ በዓልም አከበሩ፤ ከዚያም ወደ አምላካቸው+ ቤት ገብተው በሉ፤ ጠጡም፤ አቢሜሌክንም ረገሙ። 28 ከዚያም የኤቤድ ልጅ ገአል እንዲህ አለ፦ “ለመሆኑ አቢሜሌክ ማን ነው? እናገለግለውስ ዘንድ ሴኬም ማን ነው? እሱ የየሩባአል+ ልጅ አይደለም? የእሱ ተወካይስ ዘቡል አይደለም? የሴኬምን አባት የኤሞርን ሰዎች አገልግሉ! አቢሜሌክን የምናገለግለው ለምንድን ነው? 29 ይህን ሕዝብ የማዘው እኔ ብሆን ኖሮ አቢሜሌክን አስወግደው ነበር።” ከዚያም አቢሜሌክን “ብዙ ሠራዊት አሰባስበህ ና ውጣ” አለው።
30 የከተማዋ ገዢ የሆነው ዘቡል የኤቤድ ልጅ ገአል የተናገረውን ነገር በሰማ ጊዜ ቁጣው ነደደ። 31 በመሆኑም ለአቢሜሌክ እንዲህ ብለው እንዲነግሩት በሚስጥር መልእክተኞችን ላከ፦* “እነሆ፣ የኤቤድ ልጅ ገአልና ወንድሞቹ ወደ ሴኬም መጥተዋል፤ ከተማዋም በአንተ ላይ እንድታምፅ እያነሳሱ ነው። 32 በመሆኑም አንተም ሆንክ አብረውህ ያሉት ሰዎች በሌሊት ወጥታችሁ ሜዳው ላይ አድፍጡ። 33 ጠዋት ላይ ልክ ፀሐይ ስትወጣ፣ ማልደህ በመነሳት በከተማዋ ላይ ጥቃት ሰንዝር፤ እሱና አብረውት ያሉት ሰዎች አንተን ለመውጋት ሲወጡም እሱን ድል ለመምታት የቻልከውን ሁሉ አድርግ።”*
34 በመሆኑም አቢሜሌክና አብረውት ያሉት ሰዎች በሙሉ በሌሊት ተነሱ፤ በአራት ቡድንም ሆነው በሴኬም ላይ አደፈጡ። 35 የኤቤድ ልጅ ገአል ወጥቶ በከተማዋ መግቢያ በር ላይ በቆመ ጊዜ አቢሜሌክና አብረውት ያሉት ሰዎች ካደፈጡበት ቦታ ተነሱ። 36 ገአልም ሰዎቹን ባያቸው ጊዜ ዘቡልን “ተመልከት፣ ከተራሮቹ አናት ላይ ሰዎች እየወረዱ ነው” አለው። ዘቡል ግን “ሰው መስሎ የታየህ የተራሮቹ ጥላ ነው” አለው።
37 በኋላም ገአል “ተመልከት፤ ከምድሩ መሃል ሰዎች እየወረዱ ነው፤ አንደኛው ቡድን በመኦነኒም ትልቅ ዛፍ በኩል አድርጎ እየመጣ ነው” አለ። 38 ዘቡልም “‘እናገለግለው ዘንድ አቢሜሌክ ማን ነው?’+ እያልክ ጉራህን ስትነዛ አልነበረም? የናቅከው ሕዝብ ይህ አይደለም? እስቲ አሁን ውጣና ግጠማቸው” ሲል መለሰለት።
39 በመሆኑም ገአል ከሴኬም መሪዎች ፊት ፊት በመሄድ ከአቢሜሌክ ጋር ተዋጋ። 40 አቢሜሌክም አሳደደው፤ ገአልም ከፊቱ ሸሸ፤ እስከ ከተማዋም መግቢያ በር ድረስ ብዙ ሰው ተረፈረፈ።
41 አቢሜሌክም በአሩማ መኖሩን ቀጠለ፤ ዘቡልም+ ገአልንና ወንድሞቹን ከሴኬም አስወጣቸው። 42 በማግስቱም ሕዝቡ ከከተማዋ ወጣ፤ ይህም ለአቢሜሌክ ተነገረው። 43 እሱም ሰዎቹን ወስዶ በሦስት ቡድን በመክፈል ሜዳ ላይ አድፍጦ ይጠባበቅ ጀመር። ሕዝቡም ከከተማዋ መውጣቱን ተመለከተ፤ በዚህ ጊዜም በእነሱ ላይ ጥቃት ሰነዘረ፤ መታቸውም። 44 አቢሜሌክና አብረውት የነበሩት ቡድኖች በፍጥነት ወደ ፊት በመገስገስ በከተማዋ መግቢያ በር ላይ ቆሙ፤ ሁለቱ ቡድኖች ደግሞ ከከተማዋ ውጭ ባሉት ሰዎች ሁሉ ላይ ጥቃት ሰነዘሩ፤ መቷቸውም። 45 አቢሜሌክም ያን ቀን ሙሉ ከተማዋን ሲወጋ ዋለ፤ በመጨረሻም በቁጥጥሩ ሥር አዋላት። በከተማዋም ውስጥ የነበሩትን ሰዎች ገደለ፤ ከዚያም ከተማዋን አፈራረሳት፤+ በላይዋም ጨው ዘራባት።
46 የሴኬም ግንብ መሪዎች በሙሉ ይህን ሲሰሙ ወዲያውኑ በኤልበሪት+ ቤት* ወደሚገኘው መሸሸጊያ ቦታ* ሄዱ። 47 የሴኬም ግንብ መሪዎች በሙሉ አንድ ላይ እንደተሰባሰቡ ለአቢሜሌክ በተነገረውም ጊዜ 48 አቢሜሌክና አብረውት የነበሩት ሰዎች በሙሉ ወደ ጻልሞን ተራራ ወጡ። አቢሜሌክም መጥረቢያ ይዞ የዛፍ ቅርንጫፍ ከቆረጠ በኋላ አንስቶ በትከሻው ተሸከመው፤ አብረውት የነበሩትንም ሰዎች “እኔ ሳደርግ ያያችሁትን ፈጥናችሁ አድርጉ!” አላቸው። 49 በመሆኑም ሰዎቹ ሁሉ ቅርንጫፎች ቆርጠው በመያዝ አቢሜሌክን ተከተሉት። ከዚያም ቅርንጫፎቹን መሸሸጊያ ቦታው ላይ በመቆለል መሸሸጊያ ቦታውን በእሳት አያያዙት። በዚህም የተነሳ የሴኬም ግንብ ሰዎች በሙሉ ይኸውም 1,000 ገደማ የሚሆኑ ወንዶችና ሴቶች ሞቱ።
50 ከዚያም አቢሜሌክ ወደ ቴቤጽ ሄደ፤ ቴቤጽንም ከቦ በቁጥጥር ሥር አዋላት። 51 በከተማዋ መሃል ጠንካራ ግንብ ስለነበር ወንዶችና ሴቶች በሙሉ እንዲሁም የከተማዋ መሪዎች በሙሉ ወደዚያ ሸሹ። እነሱም ከውስጥ ሆነው በሩን ከዘጉት በኋላ የግንቡ አናት ላይ ወጡ። 52 አቢሜሌክም ወደ ግንቡ ሄደ፤ ጥቃትም ሰነዘረበት። ግንቡንም በእሳት ለማቃጠል ወደ መግቢያው ተጠጋ። 53 ከዚያም አንዲት ሴት በአቢሜሌክ ራስ ላይ የወፍጮ መጅ በመልቀቅ ጭንቅላቱን ፈረከሰችው።+ 54 እሱም ጋሻ ጃግሬውን ወዲያውኑ ጠርቶ “‘ሴት ገደለችው’ እንዳይሉኝ ሰይፍህን ምዘዝና ግደለኝ” አለው። ጋሻ ጃግሬውም ወጋው፤ እሱም ሞተ።
55 የእስራኤል ሰዎች አቢሜሌክ መሞቱን ሲያዩ ሁሉም ወደቤታቸው ተመለሱ። 56 በዚህ መንገድ አምላክ፣ አቢሜሌክ 70 ወንድሞቹን በመግደል በአባቱ ላይ ለፈጸመው ክፉ ነገር የእጁን እንዲያገኝ አደረገ።+ 57 በተጨማሪም አምላክ የሴኬም ሰዎች ክፋት ሁሉ በራሳቸው ላይ እንዲደርስ አደረገ። በመሆኑም የየሩባአል+ ልጅ የኢዮዓታም+ እርግማን ደረሰባቸው።
10 ከአቢሜሌክ በኋላ የዶዶ ልጅ፣ የፑሃ ልጅ የይሳኮር ሰው የሆነው ቶላ እስራኤልን ለማዳን ተነሳ።+ እሱም በኤፍሬም ተራራማ አካባቢዎች በምትገኘው በሻሚር ይኖር ነበር። 2 በእስራኤልም ውስጥ ለ23 ዓመት ፈራጅ ሆኖ አገለገለ። ከዚያም ሞተ፤ በሻሚርም ተቀበረ።
3 ከእሱም በኋላ ጊልያዳዊው ያኢር ተነሳ፤ በእስራኤልም ውስጥ ለ22 ዓመት ፈራጅ ሆኖ አገለገለ። 4 ያኢር በ30 አህዮች የሚጋልቡ 30 ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ እነሱም እስከ ዛሬ ድረስ ሃዎትያኢር+ ተብለው የሚጠሩ 30 ከተሞች ነበሯቸው፤ ከተሞቹም የሚገኙት በጊልያድ ምድር ነው። 5 ከዚያም ያኢር ሞተ፤ በቃሞንም ተቀበረ።
6 እስራኤላውያንም በይሖዋ ፊት እንደገና መጥፎ ነገር አደረጉ፤+ ባአልን፣+ የአስታሮትን ምስሎች፣ የአራምን* አማልክት፣ የሲዶናን አማልክት፣ የሞዓብን አማልክት፣+ የአሞናውያንን አማልክትና+ የፍልስጤማውያንን አማልክት+ ማገልገል ጀመሩ። ይሖዋን ተዉት፤ እሱንም አላገለገሉም። 7 የይሖዋም ቁጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፤ እነሱንም ለፍልስጤማውያንና ለአሞናውያን ሸጣቸው።+ 8 ስለሆነም በዚያ ዓመት እስራኤላውያንን አደቀቋቸው፤ ክፉኛም ጨቆኗቸው፤ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ በጊልያድ በሚገኘው በአሞራውያን ምድር የነበሩትን እስራኤላውያን በሙሉ ለ18 ዓመት ጨቆኗቸው። 9 በተጨማሪም አሞናውያን ይሁዳን፣ ቢንያምንና የኤፍሬምን ቤት ለመውጋት ዮርዳኖስን ይሻገሩ ነበር፤ እስራኤላውያንም እጅግ ተጨንቀው ነበር። 10 ከዚያም እስራኤላውያን “አንተን አምላካችንን ትተን ባአልን በማገልገላችን+ በአንተ ላይ ኃጢአት ሠርተናል” በማለት ይሖዋ እንዲረዳቸው ጮኹ።+
11 ሆኖም ይሖዋ እስራኤላውያንን እንዲህ አላቸው፦ “ግብፃውያን፣+ አሞራውያን፣+ አሞናውያን፣ ፍልስጤማውያን፣+ 12 ሲዶናውያን፣ አማሌቃውያንና ምድያማውያን በጨቆኗችሁ ጊዜ አላዳንኳችሁም? ወደ እኔ ስትጮኹ ከእጃቸው ታደግኳችሁ። 13 እናንተ ግን እኔን ትታችሁ ሌሎች አማልክትን አገለገላችሁ።+ ዳግመኛ የማላድናችሁም በዚህ የተነሳ ነው።+ 14 ወደመረጣችኋቸው አማልክት ሂዱና እንዲረዷችሁ ጠይቋቸው።+ በጭንቀታችሁ ጊዜ እነሱ ያድኗችሁ።”+ 15 እስራኤላውያን ግን ይሖዋን “ኃጢአት ሠርተናል። መልካም መስሎ የታየህን ማንኛውንም ነገር አድርግብን። እባክህ፣ የዛሬን ብቻ አድነን” አሉት። 16 እነሱም ከመካከላቸው ባዕዳን አማልክትን አስወግደው ይሖዋን አገለገሉ፤+ በመሆኑም በእስራኤል ላይ እየደረሰ የነበረውን መከራ ሊታገሥ አልቻለም።* +
17 ከጊዜ በኋላም አሞናውያን+ ተሰባስበው በጊልያድ ሰፈሩ። በመሆኑም እስራኤላውያን ተሰባስበው በምጽጳ ሰፈሩ። 18 የጊልያድ ሕዝብና መኳንንት እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፦ “ከአሞናውያን ጋር የሚደረገውን ውጊያ ግንባር ቀደም ሆኖ የሚመራው ማን ነው?+ ይህ ሰው በጊልያድ ነዋሪዎች ሁሉ ላይ አለቃ ይሁን።”
11 ጊልያዳዊው ዮፍታሔ+ ኃያል ተዋጊ ነበር፤ እሱም የአንዲት ዝሙት አዳሪ ልጅ የነበረ ሲሆን አባቱ ጊልያድ ነበር። 2 ይሁንና የጊልያድ ሚስትም ለጊልያድ ወንዶች ልጆች ወለደችለት። የዚህችኛዋ ሚስቱ ልጆች ሲያድጉም ዮፍታሔን “አንተ ከሌላ ሴት የተወለድክ ስለሆንክ በአባታችን ቤት ምንም ውርሻ አይኖርህም” በማለት አባረሩት። 3 በመሆኑም ዮፍታሔ ከወንድሞቹ ሸሽቶ በጦብ ምድር መኖር ጀመረ። ሥራ ፈት ሰዎችም ከእሱ ጋር በመተባበር ተከተሉት።
4 ከተወሰነ ጊዜ በኋላም አሞናውያን ከእስራኤላውያን ጋር ተዋጉ።+ 5 አሞናውያን ከእስራኤላውያን ጋር በሚዋጉበት ጊዜ የጊልያድ ሽማግሌዎች ዮፍታሔን ከጦብ ምድር መልሰው ለማምጣት ወዲያውኑ ወደዚያ ሄዱ። 6 ዮፍታሔንም “አሞናውያንን መውጋት እንድንችል መጥተህ አዛዣችን ሁን” አሉት። 7 ዮፍታሔ ግን የጊልያድን ሽማግሌዎች “እኔን እጅግ ከመጥላታችሁ የተነሳ ከአባቴ ቤት ያባረራችሁኝ እናንተ አይደላችሁም?+ ታዲያ አሁን ጭንቅ ውስጥ ስትገቡ ወደ እኔ የምትመጡት ለምንድን ነው?” አላቸው። 8 በዚህ ጊዜ የጊልያድ ሽማግሌዎች ዮፍታሔን እንዲህ አሉት፦ “አሁን ወደ አንተ ተመልሰን የመጣነውም ለዚህ ነው። ከእኛ ጋር አብረኸን በመሄድ ከአሞናውያን ጋር የምትዋጋ ከሆነ ለጊልያድ ነዋሪዎች በሙሉ መሪ ትሆናለህ።”+ 9 ዮፍታሔም የጊልያድን ሽማግሌዎች “እንግዲህ ከአሞናውያን ጋር እንድዋጋ ወደዚያ ብትመልሱኝና ይሖዋ እነሱን ድል ቢያደርግልኝ በእርግጥ እኔ መሪያችሁ እሆናለሁ!” አላቸው። 10 የጊልያድ ሽማግሌዎችም ዮፍታሔን “እንዳልከው ካላደረግን ይሖዋ በመካከላችን ምሥክር* ይሁን” አሉት። 11 በመሆኑም ዮፍታሔ ከጊልያድ ሽማግሌዎች ጋር ሄደ፤ ሕዝቡም መሪና አዛዥ አደረገው። ዮፍታሔም የተናገረውን ነገር ሁሉ በምጽጳ+ በይሖዋ ፊት ደገመው።
12 ከዚያም ዮፍታሔ ለአሞናውያን+ ንጉሥ “ምድሬን ልትወጋ የመጣኸው ከእኔ ጋር ምን ጠብ ቢኖርህ ነው?”* ብለው እንዲነግሩት መልእክተኞች ላከ። 13 የአሞናውያን ንጉሥም የዮፍታሔን መልእክተኞች እንዲህ አላቸው፦ “ይህን ያደረግኩት እስራኤል ከግብፅ በወጣበት ጊዜ ከአርኖን+ አንስቶ እስከ ያቦቅና እስከ ዮርዳኖስ+ ድረስ ያለውን መሬቴን ስለወሰደብኝ ነው።+ አሁንም መሬቴን በሰላም መልሱልኝ።” 14 ዮፍታሔ ግን መልእክተኞቹን እንደገና ወደ አሞናውያን ንጉሥ በመላክ 15 እንዲህ አለው፦
“ዮፍታሔ እንዲህ ይላል፦ ‘እስራኤል የሞዓባውያንን+ ምድርና የአሞናውያንን+ ምድር አልወሰደም፤ 16 ምክንያቱም እስራኤላውያን ከግብፅ በወጡ ጊዜ በምድረ በዳው አልፈው እስከ ቀይ ባሕርና+ እስከ ቃዴስ+ ድረስ መጡ። 17 ከዚያም እስራኤል ለኤዶም+ ንጉሥ “እባክህ ምድርህን አቋርጠን እንድናልፍ ፍቀድልን” ብለው እንዲነግሩት መልእክተኞችን ላከ፤ የኤዶም ንጉሥ ግን ለመስማት ፈቃደኛ አልሆነም። ለሞዓብም+ ንጉሥ መልእክት ላኩ፤ እሱም ቢሆን በዚህ ሐሳብ አልተስማማም። ስለዚህ እስራኤል በቃዴስ+ ተቀመጠ። 18 በምድረ በዳው በተጓዙበት ጊዜ በኤዶም ምድርና በሞዓብ ምድር ዳርቻ አልፈው ሄዱ።+ ከሞዓብ ምድር በስተ ምሥራቅ ተጉዘውም+ በአርኖን ክልል ሰፈሩ፤ ወደ ሞዓብ ወሰንም አልገቡም፤+ ምክንያቱም አርኖን የሞዓብ ወሰን ነበር።
19 “‘ከዚያም እስራኤል ወደ አሞራውያን ንጉሥ ማለትም ወደ ሃሽቦን ንጉሥ ወደ ሲሖን መልእክተኞችን ላከ፤ እስራኤልም “እባክህ ምድርህን አቋርጠን ወደ ገዛ ስፍራችን እንድናልፍ ፍቀድልን” አለው።+ 20 ሲሖን ግን በግዛቱ አቋርጦ እንዲያልፍ ለመፍቀድ እስራኤልን አላመነውም፤ በመሆኑም ሕዝቡን ሁሉ በአንድነት ሰብስቦ በያሃጽ ሰፈረ፤ ከእስራኤልም ጋር ውጊያ ገጠመ።+ 21 በዚህ ጊዜ የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ሲሖንንና ሕዝቡን ሁሉ ለእስራኤላውያን አሳልፎ ሰጣቸው፤ በመሆኑም ድል አደረጓቸው፤ እስራኤላውያንም በዚያ የሚኖሩትን የአሞራውያንን ምድር በሙሉ ወረሱ።+ 22 በዚህ መንገድ ከአርኖን አንስቶ እስከ ያቦቅ እንዲሁም ከምድረ በዳው አንስቶ እስከ ዮርዳኖስ ድረስ ያለውን የአሞራውያንን ግዛት በሙሉ ወረሱ።+
23 “‘እንግዲህ አሞራውያንን ከሕዝቡ ከእስራኤላውያን ፊት ያባረራቸው የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ነው፤+ እና አሁን አንተ ደግሞ እነሱን ልታባርራቸው ነው? 24 አንተስ ብትሆን አምላክህ ከሞሽ+ እንድትወርሰው የሰጠህን ሁሉ አትወርስም? ስለዚህ እኛም አምላካችን ይሖዋ ከፊታችን ያባረራቸውን ሁሉ እናባርራለን።+ 25 ደግሞስ አንተ የሞዓብ ንጉሥ ከሆነው ከሴፎር ልጅ ከባላቅ+ ትበልጣለህ? ለመሆኑ እሱ እስራኤልን ለመገዳደር ሞክሮ ያውቃል? ወይስ ከእነሱ ጋር ውጊያ ገጥሞ ያውቃል? 26 እስራኤል በሃሽቦንና በሥሯ* ባሉት ከተሞች፣+ በአሮዔርና በሥሯ ባሉት ከተሞች እንዲሁም በአርኖን ሸለቆ ዳርቻ በሚገኙት ከተሞች ሁሉ ለ300 ዓመት ተቀምጦ በነበረበት ጊዜ እነዚያን ቦታዎች መልሳችሁ ለመውሰድ ያልሞከራችሁት ለምንድን ነው?+ 27 እንግዲህ እኔ ምንም የበደልኩህ ነገር የለም፤ አንተም ብትሆን በእኔ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር መነሳትህ ተገቢ አይደለም። ፈራጁ ይሖዋ+ በእስራኤል ሕዝብና በአሞን ሕዝብ መካከል ዛሬ ይፍረድ።’”
28 የአሞናውያን ንጉሥ ግን ዮፍታሔ የላከበትን መልእክት ለመስማት ፈቃደኛ አልሆነም።
29 የይሖዋ መንፈስ በዮፍታሔ ላይ ወረደ፤+ እሱም በጊልያድ ወደምትገኘው ወደ ምጽጳ+ ለመሄድ ጊልያድንና ምናሴን አቋርጦ አለፈ፤ በጊልያድ ከምትገኘው ምጽጳም ተነስቶ ወደ አሞናውያን ሄደ።
30 ከዚያም ዮፍታሔ እንዲህ ሲል ለይሖዋ ስእለት ተሳለ፦+ “አሞናውያንን በእጄ አሳልፈህ ከሰጠኸኝ 31 ከአሞናውያን ዘንድ በሰላም በምመለስበት ጊዜ ሊቀበለኝ ከቤቴ በር የሚወጣው ማንኛውም ሰው የይሖዋ ይሆናል፤+ እኔም የሚቃጠል መባ አድርጌ አቀርበዋለሁ።”+
32 በመሆኑም ዮፍታሔ ከአሞናውያን ጋር ለመዋጋት ሄደ፤ ይሖዋም እነሱን በእጁ አሳልፎ ሰጠው። 33 እሱም ከአሮዔር አንስቶ እስከ ሚኒት ድረስ ማለትም 20 ከተሞችን፣ ከዚያም አልፎ እስከ አቤልከራሚም ድረስ ፈጽሞ ደመሰሳቸው። በዚህ መንገድ አሞናውያን ለእስራኤላውያን ተገዙ።
34 በመጨረሻም ዮፍታሔ በምጽጳ+ ወደሚገኘው ቤቱ መጣ፤ በዚህ ጊዜ ሴት ልጁ አታሞ እየመታችና እየጨፈረች ልትቀበለው ወጣች! ልጁ እሷ ብቻ ነበረች። ከእሷ ሌላ ወንድም ሆነ ሴት ልጅ አልነበረውም። 35 እሱም ባያት ጊዜ ልብሱን ቀደደ፤ እንዲህም አለ፦ “ወዮ፣ ልጄ! ልቤን ሰበርሽው፤* እንግዲህ ከቤት የማስወጣው አንቺን ነው። አንዴ ለይሖዋ ቃል ገብቻለሁ፤ ልመልሰውም አልችልም።”+
36 እሷም እንዲህ አለችው፦ “አባቴ ሆይ፣ ለይሖዋ ቃል ከገባህ፣ የገባኸውን ቃል በእኔ ላይ ፈጽምብኝ፤+ ምክንያቱም ይሖዋ ጠላቶችህን አሞናውያንን ተበቅሎልሃል።” 37 እሷም በመቀጠል አባቷን እንዲህ አለችው፦ “እንዲህ ይደረግልኝ፦ ለሁለት ወር ያህል ብቻዬን ልሁን፤ ወደ ተራሮቹም ልሂድ፤ ከሴት ባልንጀሮቼም ጋር ሆኜ ስለ ድንግልናዬ ላልቅስ።”*
38 በዚህ ጊዜ “እሺ ሂጂ!” አላት፤ ለሁለት ወርም አሰናበታት፤ እሷም ስለ ድንግልናዋ ለማልቀስ ከባልንጀሮቿ ጋር ወደ ተራሮቹ ሄደች። 39 ከሁለት ወር በኋላም ወደ አባቷ ተመለሰች፤ አባቷም እሷን በተመለከተ የተሳለውን ስእለት ፈጸመ።+ እሷም ከወንድ ጋር ግንኙነት ፈጽማ አታውቅም ነበር። ይህም በእስራኤል ውስጥ ልማድ* ሆነ፦ 40 የእስራኤል ወጣት ሴቶች የጊልያዳዊውን የዮፍታሔን ሴት ልጅ ለማመስገን በየዓመቱ ለአራት ቀን ያህል ይሄዱ ነበር።
12 ከዚያም የኤፍሬም ሰዎች አንድ ላይ ተሰባስበው ወደ ጻፎን* በመሻገር ዮፍታሔን “አሞናውያንን ለመውጋት ስትሻገር አብረንህ እንድንሄድ ያልጠራኸን ለምንድን ነው?+ ቤትህን በላይህ ላይ በእሳት እናቃጥለዋለን” አሉት። 2 ዮፍታሔ ግን እንዲህ አላቸው፦ “እኔና ሕዝቤ ከአሞናውያን ጋር በከፍተኛ ሁኔታ ተጋጭተን ነበር። እኔም እንድትረዱኝ ጠርቻችሁ ነበር፤ እናንተ ግን ከእጃቸው አላዳናችሁኝም። 3 እኔም እንደማታድኑኝ ስመለከት ሕይወቴን አደጋ ላይ ጥዬ* በአሞናውያን ላይ ለመዝመት ወሰንኩ፤+ ይሖዋም እነሱን በእጄ አሳልፎ ሰጣቸው። ታዲያ ዛሬ ልትወጉኝ የወጣችሁት ለምንድን ነው?”
4 ከዚያም ዮፍታሔ የጊልያድን+ ሰዎች ሁሉ አሰባስቦ ከኤፍሬም ጋር ተዋጋ፤ የጊልያድም ሰዎች ኤፍሬማውያንን ድል አደረጓቸው፤ ኤፍሬማውያን የጊልያድን ሰዎች “በኤፍሬምና በምናሴ የምትኖሩ እናንተ የጊልያድ ሰዎች፣ እናንተ እኮ ከኤፍሬም ሸሽታችሁ ያመለጣችሁ ስደተኞች ናችሁ” ይሏቸው ነበር። 5 ጊልያዳውያንም ከኤፍሬማውያን ፊት ለፊት የሚገኘውን የዮርዳኖስን+ መልካ* ተቆጣጠሩ፤ የኤፍሬምም ሰዎች ለማምለጥ በሚሞክሩበት ጊዜ “እንድሻገር ፍቀዱልኝ” ይላሉ፤ በዚህ ጊዜ የጊልያድ ሰዎች እያንዳንዱን ሰው “አንተ ኤፍሬማዊ ነህ?” ብለው ይጠይቁታል፤ እሱም “አይ፣ አይደለሁም” ብሎ ሲመልስላቸው 6 “እስቲ ሺቦሌት በል” ይሉታል። እሱ ግን ቃሉን በትክክል መጥራት ስለማይችል “ሲቦሌት” ይላል። እነሱም ይዘው እዚያው ዮርዳኖስ መልካ ላይ ይገድሉታል። በመሆኑም በዚያን ጊዜ 42,000 ኤፍሬማውያን አለቁ።
7 ዮፍታሔም በእስራኤል ውስጥ ለስድስት ዓመት ፈራጅ ሆኖ አገለገለ፤ ከዚያም ጊልያዳዊው ዮፍታሔ ሞተ፤ በጊልያድ በምትገኘው ከተማውም ተቀበረ።
8 ከእሱም በኋላ የቤተልሔሙ ኢብጻን በእስራኤል ውስጥ ፈራጅ ሆኖ አገለገለ።+ 9 ኢብጻን 30 ወንዶችና 30 ሴቶች ልጆች ነበሩት። እሱም ሴቶች ልጆቹን ከጎሳው ውጭ የሆኑ ሰዎችን እንዲያገቡ ላካቸው፤ እንዲሁም ከወንዶች ልጆቹ ጋር እንዲጋቡ ከጎሳው ውጭ የሆኑ 30 ሴቶችን አስመጣ። በእስራኤልም ውስጥ ለሰባት ዓመት ፈራጅ ሆኖ አገለገለ። 10 ከዚያም ኢብጻን ሞተ፤ በቤተልሔምም ተቀበረ።
11 ከእሱም በኋላ ዛብሎናዊው ኤሎን በእስራኤል ውስጥ ፈራጅ ሆኖ አገለገለ። እሱም በእስራኤል ውስጥ ለአሥር ዓመት ፈራጅ ሆኖ አገለገለ። 12 ከዚያም ዛብሎናዊው ኤሎን ሞተ፤ በዛብሎን ምድር በአይሎንም ተቀበረ።
13 ከእሱም በኋላ የጲራቶናዊው የሂሌል ልጅ አብዶን በእስራኤል ውስጥ ፈራጅ ሆኖ አገለገለ። 14 እሱም በ70 አህዮች የሚጋልቡ 40 ወንዶች ልጆችና 30 የልጅ ልጆች ነበሩት። በእስራኤልም ውስጥ ለስምንት ዓመት ፈራጅ ሆኖ አገለገለ። 15 ከዚያም የጲራቶናዊው የሂሌል ልጅ አብዶን ሞተ፤ በአማሌቃውያን+ ተራራ በኤፍሬም ምድር በምትገኘው በጲራቶንም ተቀበረ።
13 እስራኤላውያን እንደገና በይሖዋ ፊት መጥፎ ነገር አደረጉ፤+ ይሖዋም ለ40 ዓመት በፍልስጤማውያን እጅ አሳልፎ ሰጣቸው።+
2 በዚህ ጊዜ ከዳናውያን+ ቤተሰብ የሆነ ስሙ ማኑሄ+ የሚባል አንድ የጾራ+ ሰው ነበር። ሚስቱ መሃን ስለነበረች ልጅ አልነበራትም።+ 3 ከጊዜ በኋላ የይሖዋ መልአክ ለሴቲቱ ተገለጠላትና እንዲህ አላት፦ “እነሆ አንቺ መሃን ነሽ፤ ልጅም የለሽም። ነገር ግን ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ።+ 4 እንግዲህ ተጠንቀቂ፤ የወይን ጠጅ ወይም ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አትጠጪ፤+ እንዲሁም ምንም ዓይነት ርኩስ ነገር አትብዪ።+ 5 እነሆ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ይህ ልጅ ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ* የአምላክ ናዝራዊ* ስለሚሆን ራሱን ምላጭ አይንካው፤+ እሱም እስራኤልን ከፍልስጤማውያን እጅ በማዳን ረገድ ግንባር ቀደም ይሆናል።”+
6 ከዚያም ሴቲቱ ሄዳ ባሏን እንዲህ አለችው፦ “የእውነተኛው አምላክ ሰው ወደ እኔ መጥቶ ነበር፤ መልኩም የእውነተኛውን አምላክ መልአክ ይመስላል፤ በጣም የሚያስፈራ ነበር። ከየት እንደመጣ አልጠየቅኩትም፤ እሱም ቢሆን ስሙን አልነገረኝም።+ 7 ሆኖም እንዲህ አለኝ፦ ‘እነሆ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ። እንግዲህ የወይን ጠጅ ወይም ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አትጠጪ፤ እንዲሁም ምንም ዓይነት ርኩስ ነገር አትብዪ፤ ምክንያቱም ልጁ ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ* እስከሚሞትበት ዕለት ድረስ የአምላክ ናዝራዊ ይሆናል።’”
8 ማኑሄም “ይቅርታ አድርግልኝ ይሖዋ። እባክህ ልከኸው የነበረው ያ የእውነተኛው አምላክ ሰው እንደገና ወደ እኛ ይምጣና የሚወለደውን ልጅ በተመለከተ ምን ማድረግ እንዳለብን መመሪያ ይስጠን” በማለት ይሖዋን ተማጸነ። 9 በመሆኑም እውነተኛው አምላክ የማኑሄን ቃል ሰማ፤ የእውነተኛው አምላክ መልአክም ሴቲቱ ሜዳ ላይ ተቀምጣ ሳለ ዳግመኛ ወደ እሷ መጣ፤ ባሏ ማኑሄ ግን አብሯት አልነበረም። 10 ሴቲቱም በፍጥነት እየሮጠች ሄዳ ባሏን “ባለፈው ጊዜ ወደ እኔ መጥቶ የነበረው ሰው ተገለጠልኝ” አለችው።+
11 ከዚያም ማኑሄ ተነስቶ ከሚስቱ ጋር ሄደ። ሰውየውንም ሲያገኘው “ሚስቴን ያነጋገርካት አንተ ነህ?” አለው፤ እሱም “አዎ፣ እኔ ነኝ” አለ። 12 ማኑሄም “እንግዲህ እንደ ቃልህ ይሁንልን! ይሁንና ልጁን ማሳደግ የሚኖርብን እንዴት ነው? የእሱስ ሥራ ምን ይሆናል?” አለው።+ 13 የይሖዋም መልአክ ማኑሄን እንዲህ አለው፦ “ሚስትህ ከነገርኳት ነገር ሁሉ ራሷን ትጠብቅ።+ 14 ከወይን ተክል የሚገኝ ማንኛውንም ነገር አትብላ፤ የወይን ጠጅም ሆነ ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አትጠጣ፤+ እንዲሁም ምንም ዓይነት ርኩስ ነገር አትብላ።+ ያዘዝኳትን ሁሉ ትጠብቅ።”
15 ማኑሄም የይሖዋን መልአክ “እባክህ አንድ የፍየል ጠቦት አዘጋጅተን እስክናቀርብልህ ድረስ ቆይ” አለው።+ 16 ሆኖም የይሖዋ መልአክ ማኑሄን “ብቆይም እንኳ የምታቀርበውን ምግብ አልበላም፤ ይሁንና ለይሖዋ የሚቃጠል መባ ማቅረብ የምትፈልግ ከሆነ እሱን አቅርበው” አለው። ማኑሄ ይህ ሰው የይሖዋ መልአክ መሆኑን አላወቀም ነበር። 17 ከዚያም ማኑሄ የይሖዋን መልአክ “የተናገርከው ቃል ሲፈጸም እንድናከብርህ ስምህ ማን ነው?”+ በማለት ጠየቀው። 18 ሆኖም የይሖዋ መልአክ “ስሜ የሚያስደንቅ ሆኖ ሳለ ለምን ስሜን ትጠይቀኛለህ?” አለው።
19 ከዚያም ማኑሄ የፍየል ጠቦቱንና የእህል መባውን ወስዶ በዓለቱ ላይ ለይሖዋ አቀረበው። እሱም ማኑሄና ሚስቱ እየተመለከቱ አስደናቂ ነገር አደረገ። 20 የእሳቱ ነበልባል ከመሠዊያው ወደ ሰማይ ሲወጣ የይሖዋ መልአክ ማኑሄና ሚስቱ እያዩት ከመሠዊያው በወጣው ነበልባል ውስጥ ሆኖ አረገ። እነሱም ወዲያውኑ በግንባራቸው መሬት ላይ ተደፉ። 21 የይሖዋም መልአክ ለማኑሄና ለሚስቱ ዳግመኛ አልተገለጠላቸውም። ማኑሄ ሰውየው የይሖዋ መልአክ እንደነበር የተገነዘበው ያን ጊዜ ነበር።+ 22 ከዚያም ማኑሄ ሚስቱን “ያየነው አምላክን ስለሆነ መሞታችን አይቀርም” አላት።+ 23 ሚስቱ ግን “ይሖዋ ሊገድለን ቢፈልግማ ኖሮ የሚቃጠል መባና የእህል መባ ከእጃችን ባልተቀበለ ነበር፤+ ደግሞም ይህን ሁሉ ነገር ባላሳየንና እንዲህ ያለውንም ነገር ባልነገረን ነበር” አለችው።
24 በኋላም ሴቲቱ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ሳምሶን+ አለችው፤ ልጁም እያደገ ሄደ፤ ይሖዋም ባረከው። 25 ከጊዜ በኋላም በጾራ እና በኤሽታዖል+ መካከል በምትገኘው በማሃነህዳን+ ሳለ የይሖዋ መንፈስ ይገፋፋው ጀመር።+
14 ከዚያም ሳምሶን ወደ ቲምና ወረደ፤ በቲምናም አንዲት ፍልስጤማዊት ሴት አየ። 2 ወጥቶም አባቱንና እናቱን “በቲምና ያለች አንዲት ፍልስጤማዊት ዓይኔን ማርካዋለች፤ እሷን እንድታጋቡኝ እፈልጋለሁ” አላቸው። 3 ሆኖም አባቱና እናቱ “ከዘመዶችህና ከእኛ ሕዝብ መካከል ለአንተ የምትሆን ሴት አጥተህ ነው?+ የግድ ሄደህ ካልተገረዙት ፍልስጤማውያን መካከል ሚስት ማግባት አለብህ?” አሉት። ሳምሶን ግን አባቱን “ልቤን የማረከችው እሷ ስለሆነች እሷን አጋባኝ” አለው። 4 በዚያን ጊዜ በእስራኤል ላይ ይገዙ የነበሩት ፍልስጤማውያን ስለነበሩ አባቱና እናቱ ነገሩ ከይሖዋ መሆኑንና እሱም ከፍልስጤማውያን ጋር ግጭት የሚፈጠርበትን አጋጣሚ እየፈለገ እንደነበር አላወቁም።+
5 ስለዚህ ሳምሶን ከአባቱና ከእናቱ ጋር ወደ ቲምና ወረደ። በቲምና ወዳለው የወይን እርሻ ሲደርስም አንድ ደቦል አንበሳ እያገሳ መጣበት። 6 ከዚያም የይሖዋ መንፈስ ኃይል ሰጠው፤+ አንድ ሰው በባዶ እጁ የፍየልን ጠቦት ለሁለት እንደሚገነጥል እሱም አንበሳውን ለሁለት ገነጠለው። ሆኖም ያደረገውን ነገር ለአባቱም ሆነ ለእናቱ አልነገራቸውም። 7 ከዚያም ወርዶ ሴቲቱን አነጋገራት፤ አሁንም የሳምሶን ልብ በእሷ እንደተማረከ ነበር።+
8 ከተወሰነ ጊዜ በኋላም ወደ ቤቱ ሊያመጣት+ ተመልሶ ሲሄድ የአንበሳውን በድን ለማየት ከመንገድ ዞር አለ፤ በአንበሳውም በድን ውስጥ የንብ መንጋና ማር ነበር። 9 እሱም ማሩን ዛቅ አድርጎ መዳፉ ላይ በማድረግ በመንገድ ላይ እየበላ ሄደ። ከአባቱና ከእናቱ ጋር እንደተገናኘም ከማሩ ሰጣቸው፤ እነሱም በሉ። ሆኖም ማሩን የወሰደው ከአንበሳ በድን ውስጥ እንደሆነ አልነገራቸውም ነበር።
10 አባቱም ወደ ሴቲቱ ወረደ፤ ሳምሶንም በዚያ ግብዣ አዘጋጀ፤ ምክንያቱም ወጣቶች እንዲህ የማድረግ ልማድ ነበራቸው። 11 እነሱም ባዩት ጊዜ አብረውት እንዲሆኑ 30 ሚዜዎችን አመጡ። 12 ሳምሶንም እንዲህ አላቸው፦ “እስቲ አንድ እንቆቅልሽ ልንገራችሁ። ግብዣው በሚቆይበት በዚህ ሰባት ቀን ውስጥ ፍቺውን ካወቃችሁና መልሱን ከነገራችሁኝ 30 የበፍታ ልብሶችንና 30 የክት ልብሶችን እሰጣችኋለሁ። 13 መልሱን ልትነግሩኝ ካልቻላችሁ ግን 30 የበፍታ ልብሶችንና 30 የክት ልብሶችን ትሰጡኛላችሁ።” እነሱም “እንቆቅልሽህን ንገረን፤ እስቲ እንስማው” አሉት። 14 እሱም እንዲህ አላቸው፦
“ከበላተኛው መብል ወጣ፤
ከብርቱውም ውስጥ ጣፋጭ ነገር ወጣ።”+
እነሱም እስከ ሦስት ቀን ድረስ እንቆቅልሹን ሊፈቱት አልቻሉም። 15 በአራተኛውም ቀን የሳምሶንን ሚስት እንዲህ አሏት፦ “ባልሽን አታለሽ+ የእንቆቅልሹን ፍቺ እንዲነግረን አድርጊ። አለዚያ አንቺንም ሆነ የአባትሽን ቤት በእሳት እናቃጥላለን። እዚህ የጋበዛችሁን ንብረታችንን ልትዘርፉን ነው?” 16 የሳምሶንም ሚስት ላዩ ላይ እያለቀሰች “አንተ ትጠላኛለህ፤ ደግሞም አትወደኝም።+ ለሕዝቤ አንድ እንቆቅልሽ ነግረሃቸው ነበር፤ መልሱን ግን ለእኔ አልነገርከኝም” አለችው። እሱም በዚህ ጊዜ “እንዴ፣ ለገዛ አባቴና እናቴ እንኳ አልነገርኳቸውም! ታዲያ ለአንቺ ለምን እነግርሻለሁ?” አላት። 17 እሷ ግን ግብዣው እስከቆየበት እስከ ሰባተኛው ቀን ድረስ ስታለቅስበት ሰነበተች። በመጨረሻም አጥብቃ ስለነዘነዘችው በሰባተኛው ቀን ነገራት። እሷም የእንቆቅልሹን ፍቺ ለሕዝቧ ነገረች።+ 18 የከተማዋም ሰዎች ሳምሶንን በሰባተኛው ቀን ፀሐይዋ ከመጥለቋ በፊት* እንዲህ አሉት፦
“ከማር ይልቅ የሚጣፍጥ ምን ተገኝቶ?
ከአንበሳስ ይልቅ የበረታ ከየት መጥቶ?”+
እሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፦
“በጊደሬ ባላረሳችሁ፣+
እንቆቅልሼን ባልፈታችሁ።”
19 ከዚያም የይሖዋ መንፈስ ለሳምሶን ኃይል ሰጠው፤+ እሱም ወደ አስቀሎን+ ወርዶ ከሰዎቻቸው መካከል 30ውን ገደለ፤ ልብሳቸውንም ገፎ እንቆቅልሹን ለፈቱት ሰዎች ሰጣቸው።+ ቁጣው እንደነደደም ወደ አባቱ ቤት ወጣ።
20 የሳምሶንም ሚስት+ አብረውት ከነበሩት ሚዜዎች ለአንዱ ተዳረች።+
15 ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በስንዴ መከር ወቅት ሳምሶን አንድ የፍየል ጠቦት ይዞ ሚስቱን ሊጠይቅ ሄደ። እሱም “ሚስቴ ወዳለችበት መኝታ ቤት* መግባት እፈልጋለሁ” አለ። አባቷ ግን እንዲገባ አልፈቀደለትም። 2 ከዚያም አባትየው እንዲህ አለው፦ “እኔ እኮ ‘ፈጽሞ ጠልተሃታል’ ብዬ አስቤ ነበር።+ ስለሆነም ለሚዜህ ዳርኳት።+ ታናሽ እህቷ ከእሷ ይልቅ ቆንጆ አይደለችም? እባክህ በዚያችኛዋ ፋንታ ይህችኛዋን አግባት።” 3 ሳምሶን ግን “ከእንግዲህ ፍልስጤማውያን ለማደርስባቸው ጉዳት ተጠያቂ ሊያደርጉኝ አይችሉም” አላቸው።
4 ሳምሶንም ሄዶ 300 ቀበሮዎችን ያዘ። ከዚያም ችቦዎች አመጣ፤ ቀበሮዎቹንም ፊታቸውን አዙሮ ጭራና ጭራቸውን አንድ ላይ ካሰረ በኋላ በጭራቸው መሃል አንድ አንድ ችቦ አደረገ። 5 በመቀጠልም ችቦዎቹን በእሳት በመለኮስ ቀበሮዎቹን በፍልስጤማውያን እርሻ ላይ ባለው ያልታጨደ እህል ውስጥ ለቀቃቸው። ከነዶው አንስቶ እስካልታጨደው እህል ድረስ እንዲሁም የወይን እርሻዎችንና የወይራ ዛፎችን አቃጠለ።
6 ፍልስጤማውያኑም “ይህን ያደረገው ማን ነው?” ብለው ጠየቁ። እነሱም “የቲምናዊው አማች ሳምሶን ነው፤ ይህን ያደረገውም ሚስቱን ወስዶ ለሚዜው ስለሰጠበት ነው” ተብሎ ተነገራቸው።+ በዚህ ጊዜ ፍልስጤማውያን ሄደው እሷንና አባቷን በእሳት አቃጠሉ።+ 7 ሳምሶንም “እንግዲህ እናንተ ይህን ካደረጋችሁ እኔ ደግሞ እናንተን ሳልበቀል አርፌ አልቀመጥም” አላቸው።+ 8 ከዚያም አንድ በአንድ እየመታ* ረፈረፋቸው፤ ከዚህ በኋላ ወርዶ በኤጣም በሚገኝ አንድ የዓለት ዋሻ* ውስጥ ተቀመጠ።
9 በኋላም ፍልስጤማውያን ወጥተው በይሁዳ ሰፈሩ፤ የሊሃይንም+ አካባቢ ያስሱ ጀመር። 10 የይሁዳም ሰዎች “እኛን ልትወጉ የመጣችሁት ለምንድን ነው?” አሏቸው፤ እነሱም መልሰው “እኛ የመጣነው ሳምሶንን ለመያዝና* እሱ እንዳደረገብን ሁሉ እኛም እንድናደርግበት ነው” አሉ። 11 በመሆኑም 3,000 የይሁዳ ሰዎች በኤጣም ወደሚገኘው የዓለት ዋሻ* ወርደው ሳምሶንን “ፍልስጤማውያን ገዢዎቻችን መሆናቸውን አታውቅም?+ ታዲያ እንዲህ ያለ ነገር የፈጸምክብን ለምንድን ነው?” አሉት። እሱም “እነሱ እንዳደረጉብኝ እኔም አደረግኩባቸው” አላቸው። 12 እነሱ ግን “አሁን የመጣነው ይዘን* ለፍልስጤማውያን ልናስረክብህ ነው” አሉት። ከዚያም ሳምሶን “እናንተ ራሳችሁ ምንም ጥቃት እንደማታደርሱብኝ ማሉልኝ” አላቸው። 13 እነሱም “አስረን ብቻ ለእነሱ እናስረክብሃለን እንጂ አንገድልህም” አሉት።
በመሆኑም በሁለት አዳዲስ ገመዶች አስረው ከዓለቱ ውስጥ አወጡት። 14 እሱም ሊሃይ ሲደርስ ፍልስጤማውያኑ እሱን በማግኘታቸው በድል አድራጊነት ጮኹ። በዚህ ጊዜ የይሖዋ መንፈስ ኃይል ሰጠው፤+ እጆቹ የታሰሩባቸውም ገመዶች እሳት እንደበላው የበፍታ ክር ሆኑ፤ ማሰሪያዎቹም ከእጆቹ ላይ ቀልጠው ወደቁ።+ 15 እሱም በቅርቡ የሞተ የአንድ አህያ መንጋጋ አገኘ፤ መንጋጋውንም አንስቶ በእሱ 1,000 ሰው ገደለ።+ 16 ከዚያም ሳምሶን እንዲህ አለ፦
“በአህያ መንጋጋ በክምር ላይ ክምር አነባባሪ፤
በአህያ መንጋጋ 1,000 ሰው ዘራሪ!”+
17 እሱም ይህን ተናግሮ ሲጨርስ የአህያውን መንጋጋ ወረወረው፤ ያንንም ቦታ ራማትሊሃይ* + ብሎ ጠራው። 18 ከዚያም በጣም ተጠማ፤ ወደ ይሖዋም እንዲህ ሲል ጮኸ፦ “ይህ ታላቅ መዳን በአገልጋይህ እጅ እንዲፈጸም ያደረግከው አንተ ነበርክ። ታዲያ አሁን በውኃ ጥም ልሙት? በእነዚህ ባልተገረዙ ሰዎች እጅስ ልውደቅ?” 19 በመሆኑም አምላክ በሊሃይ የሚገኝ አንድ ዓለት ነደለ፤ ውኃም ከዓለቱ መውጣት ጀመረ።+ እሱም በጠጣ ጊዜ መንፈሱ* ተመለሰ፤ ብርታትም አገኘ። እስከ ዛሬ ድረስ በሊሃይ የሚገኘውን ያንን ቦታ ኤንሃቆሬ* ሲል የጠራው ለዚህ ነው።
20 እሱም በፍልስጤማውያን ዘመን ለ20 ዓመት በእስራኤል ውስጥ ፈራጅ ሆኖ አገለገለ።+
16 አንድ ቀን ሳምሶን ወደ ጋዛ ሄደ፤ በዚያም አንዲት ዝሙት አዳሪ አይቶ ወደ እሷ ገባ። 2 ከዚያም ጋዛውያን “ሳምሶን እዚህ መጥቷል” የሚል ወሬ ደረሳቸው። እነሱም ከበውት በከተማዋ በር ላይ ሌሊቱን ሙሉ አድፍጠው ሲጠባበቁ አደሩ። ለራሳቸውም “ጎህ ሲቀድ እንገድለዋለን” በማለት ሌሊቱን ሙሉ ድምፃቸውን አጥፍተው አደሩ።
3 ይሁንና ሳምሶን እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ተኛ። ከዚያም እኩለ ሌሊት ላይ ተነስቶ የከተማዋን በሮች ያዘ፤ በሮቹን ከነመቃኖቹና ከነመቀርቀሪያዎቹ ነቀለ። በትከሻው ከተሸከማቸውም በኋላ በኬብሮን ትይዩ እስከሚገኘው ተራራ አናት ድረስ ይዟቸው ወጣ።
4 ከዚህ በኋላ ሳምሶን በሶረቅ ሸለቆ* የምትገኝ ደሊላ+ የምትባል አንዲት ሴት ወደደ። 5 የፍልስጤም ገዢዎችም ወደ እሷ ቀርበው እንዲህ አሏት፦ “እስቲ አታለሽ* + እንዲህ ያለ ከፍተኛ ጥንካሬ የሰጠው ምን እንደሆነ እንዲሁም እንዴት ልናሸንፈው፣ ልናስረውና በቁጥጥር ሥር ልናውለው እንደምንችል ለማወቅ ሞክሪ። ይህን ካደረግሽ እያንዳንዳችን 1,100 የብር ሰቅል እንሰጥሻለን።”
6 ከጊዜ በኋላም ደሊላ ሳምሶንን “የታላቅ ኃይልህ ሚስጥር ምን እንደሆነ እንዲሁም አንተን በምን ማሰርና በቁጥጥር ሥር ማዋል እንደሚቻል እስቲ ንገረኝ” አለችው። 7 ሳምሶንም “ገና እርጥብ በሆኑ ባልደረቁ ሰባት ጅማቶች ቢያስሩኝ እንደ ማንኛውም ሰው ደካማ እሆናለሁ” አላት። 8 በመሆኑም የፍልስጤም ገዢዎች ገና እርጥብ የሆኑ ያልደረቁ ሰባት ጅማቶች አመጡላት፤ እሷም በጅማቶቹ አሰረችው። 9 እነሱም በውስጠኛው ክፍል ውስጥ አድፍጠው ይጠባበቁ ነበር፤ እሷም “ሳምሶን፣ ፍልስጤማውያን መጡብህ!” ብላ ጮኸች። በዚህ ጊዜ ሳምሶን የተፈተለ የበፍታ ክር* እሳት ሲነካው በቀላሉ እንደሚበጣጠስ ጅማቶቹን በጣጠሳቸው።+ የኃይሉም ሚስጥር ሊታወቅ አልቻለም።
10 ደሊላም ሳምሶንን “አሞኝተኸኛል፣ ደግሞም ዋሽተኸኛል።* እሺ አሁን በምን ልትታሰር እንደምትችል እባክህ ንገረኝ” አለችው። 11 እሱም “ሥራ ላይ ባልዋሉ አዲስ ገመዶች ቢያስሩኝ እንደ ማንኛውም ሰው ደካማ እሆናለሁ” አላት። 12 ደሊላም አዲስ ገመዶች ወስዳ አሰረችው፤ ከዚያም “ሳምሶን፣ ፍልስጤማውያን መጡብህ!” ብላ ጮኸች። (በዚህ ጊዜ ሁሉ በውስጠኛው ክፍል ውስጥ አድፍጠው የሚጠባበቁ ሰዎች ነበሩ።) ሳምሶንም ገመዶቹን ልክ እንደ ክር ከእጆቹ ላይ በጣጠሳቸው።+
13 ከዚህ በኋላ ደሊላ ሳምሶንን “አሁንም አሞኘኸኝ፤ ዋሸኸኝ።+ በምን ልትታሰር እንደምትችል ንገረኝ” አለችው። እሱም “የራስ ፀጉሬን ሰባት ጉንጉኖች በመሸመኛ ላይ ከድር ጋር አብረሽ ሸምኛቸው” አላት። 14 በመሆኑም ደሊላ ጉንጉኖቹን በሸማኔ ዘንግ አጠበቀቻቸው፤ ከዚያም “ሳምሶን፣ ፍልስጤማውያን መጡብህ!” ብላ ጮኸች። እሱም ከእንቅልፉ ነቃ፤ ዘንጉንና ድሩንም መዞ አወጣው።
15 እሷም “ልብህ ከእኔ ጋር ሳይሆን እንዴት ‘እወድሻለሁ’+ ትለኛለህ? ይኸው ሦስት ጊዜ አሞኘኸኝ፤ የታላቁ ኃይልህን ሚስጥር አልነገርከኝም”+ አለችው። 16 ዕለት ዕለት ስለነዘነዘችውና ለጭንቀት ስለዳረገችው ሞቱን እስኪመኝ ድረስ ተመረረ።* + 17 በመጨረሻም የልቡን ሁሉ አውጥቶ እንዲህ ሲል ነገራት፦ “ከተወለድኩበት ጊዜ አንስቶ* ለአምላክ ናዝራዊ ስለሆንኩ ራሴን ምላጭ ነክቶት አያውቅም።+ ፀጉሬን ከተላጨሁ ኃይሌን አጣለሁ፤ አቅምም አይኖረኝም፤ እንደ ሌሎች ሰዎች ሁሉ እሆናለሁ።”
18 ደሊላም ሳምሶን የልቡን ሁሉ አውጥቶ እንደነገራት ስታውቅ “የልቡን ሁሉ አውጥቶ ስለነገረኝ በቃ አሁን መምጣት ትችላላችሁ” በማለት የፍልስጤም ገዢዎችን+ ወዲያውኑ አስጠራቻቸው። የፍልስጤም ገዢዎችም ገንዘቡን ይዘው ወደ እሷ መጡ። 19 እሷም ሳምሶንን ጭኗ ላይ አስተኛችው፤ ሰውየውንም ጠርታ የራስ ፀጉሩን ሰባት ጉንጉኖች እንዲላጫቸው አደረገች። ከዚያ በኋላ ኃይሉ ከእሱ ስለተለየ በቁጥጥሯ ሥር አዋለችው። 20 እሷም “ሳምሶን፣ ፍልስጤማውያን መጡብህ!” አለችው። በዚህ ጊዜ ከእንቅልፉ ነቅቶ “እንደ ሌላው ጊዜ እወጣለሁ፤+ ራሴንም ነፃ አደርጋለሁ” አለ። ሆኖም ይሖዋ እንደተወው አላወቀም ነበር። 21 በመሆኑም ፍልስጤማውያን ይዘው ዓይኖቹን አወጡ። ከዚያም ወደ ጋዛ ይዘውት በመውረድ ከመዳብ በተሠሩ ሁለት የእግር ብረቶች አሰሩት፤ እሱም እስር ቤት ውስጥ እህል ፈጪ ሆነ። 22 ሆኖም ተላጭቶ የነበረው የሳምሶን ፀጉር እንደገና ማደግ ጀመረ።+
23 የፍልስጤም ገዢዎች “አምላካችን ጠላታችንን ሳምሶንን በእጃችን አሳልፎ ሰጠን!” በማለት ለአምላካቸው ለዳጎን+ ታላቅ መሥዋዕት ለመሠዋትና ለመደሰት አንድ ላይ ተሰብስበው ነበር። 24 ሕዝቡም ሳምሶንን ባዩት ጊዜ “አምላካችን ምድራችንን ያጠፋውንና+ ብዙ ወገኖቻችንን የገደለብንን+ ጠላታችንን በእጃችን አሳልፎ ሰጠን” በማለት አምላካቸውን አወደሱ።
25 እነሱም ልባቸው ሐሴት በማድረጉ “እስቲ ሳምሶንን ጥሩትና ትንሽ ያዝናናን” አሉ። በመሆኑም እንዲያዝናናቸው ሳምሶንን ከእስር ቤት ጠሩት፤ በዓምዶቹም መካከል አቆሙት። 26 ከዚያም ሳምሶን እጁን ይዞት የነበረውን ልጅ “ቤቱ የቆመባቸውን ዓምዶች አስይዘኝና ልደገፍባቸው” አለው። 27 (እንደ አጋጣሚ ሆኖ ቤቱ በወንዶችና በሴቶች ተሞልቶ ነበር። የፍልስጤም ገዢዎችም በሙሉ እዚያ ነበሩ፤ በተጨማሪም ሳምሶን ሕዝቡን ሲያዝናና ይመለከቱ የነበሩ 3,000 ወንዶችና ሴቶች ጣሪያው ላይ ነበሩ።)
28 ሳምሶንም+ እንዲህ በማለት ወደ ይሖዋ ጮኸ፦ “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ እባክህ አስበኝ፤ አምላክ ሆይ፣ እባክህ ለአሁን ብቻ አንድ ጊዜ ብርታት ስጠኝና+ ከሁለቱ ዓይኖቼ+ ስለ አንዱ ፍልስጤማውያንን ልበቀላቸው።”
29 ከዚያም ሳምሶን ቤቱን ደግፈው ያቆሙትን መሃል ላይ የሚገኙትን ሁለቱን ዓምዶች፣ አንዱን በቀኝ እጁ ሌላውን ደግሞ በግራ እጁ አቅፎ ተደገፈባቸው። 30 እሱም “ከፍልስጤማውያን ጋር ልሙት!”* ብሎ ጮኸ። ከዚያም ዓምዶቹን ባለ በሌለ ኃይሉ ገፋቸው፤ ቤቱም በገዢዎቹና በውስጡ በነበሩት ሰዎች ሁሉ ላይ ወደቀ።+ በመሆኑም ሳምሶን በሕይወት ሳለ ከገደላቸው ሰዎች ይልቅ በሞተበት ጊዜ የገደላቸው ሰዎች በለጡ።+
31 በኋላም ወንድሞቹና የአባቱ ቤተሰቦች በሙሉ ሊወስዱት ወደዚያ ወረዱ። እነሱም ወስደው በጾራ+ እና በኤሽታዖል መካከል በሚገኘው በአባቱ በማኑሄ+ የመቃብር ስፍራ ቀበሩት። እሱም በእስራኤል ውስጥ ለ20 ዓመት ፈራጅ ሆኖ አገለገለ።+
17 በኤፍሬም ተራራማ አካባቢ+ የሚኖር ሚክያስ የተባለ አንድ ሰው ነበር። 2 እሱም እናቱን እንዲህ አላት፦ “1,100 የብር ሰቅል ተወስዶብሽ የሰረቀውን ሰው ስትራገሚ ሰምቼ ነበር፤ ብሩ ያለው እኔ ጋ ነው። የወሰድኩት እኔ ነበርኩ።” በዚህ ጊዜ እናቱ “ልጄ፣ ይሖዋ ይባርክህ” አለችው። 3 በመሆኑም 1,100ውን የብር ሰቅል ለእናቱ መለሰላት፤ እናቱ ግን “የተቀረጸ ምስልና ከብረት የተሠራ ሐውልት* + እንዲሠራበት ለልጄ ስል ብሩን ከእጄ ለይሖዋ እቀድሰዋለሁ። ለአንተም መልሼ እሰጥሃለሁ” አለችው።
4 እሱም ብሩን ለእናቱ ከመለሰላት በኋላ እናቱ 200 የብር ሰቅል ወስዳ ለብር አንጥረኛው ሰጠችው። እሱም የተቀረጸ ምስልና ከብረት የተሠራ ሐውልት* ሠራበት፤ እነሱም በሚክያስ ቤት ተቀመጡ። 5 ሚክያስ የተባለው ይህ ሰው የአማልክት ቤት ነበረው፤ እሱም ኤፉድና+ የተራፊም ቅርጻ ቅርጾች* + ሠራ፤ ከወንዶች ልጆቹም መካከል አንዱን ካህን ሆኖ እንዲያገለግለው ሾመው።* + 6 በዚያ ዘመን በእስራኤል ንጉሥ አልነበረም።+ እያንዳንዱም ሰው ለራሱ ትክክል መስሎ የታየውን ያደርግ ነበር።+
7 በዚያ ጊዜ በይሁዳ በምትገኘው በቤተልሔም+ የሚኖር ከይሁዳ ቤተሰብ የሆነ አንድ ወጣት ነበር። እሱም ሌዋዊ+ ሲሆን በዚያ ለተወሰነ ጊዜ ተቀምጦ ነበር። 8 ይህም ሰው የሚኖርበት ስፍራ ለመፈለግ በይሁዳ የምትገኘውን የቤተልሔምን ከተማ ለቆ ሄደ። እየተጓዘም ሳለ በኤፍሬም ተራራማ አካባቢ ወደሚገኘው ወደ ሚክያስ+ ቤት ደረሰ። 9 ከዚያም ሚክያስ “ከየት ነው የመጣኸው?” ሲል ጠየቀው። እሱም መልሶ “በይሁዳ ከምትገኘው ከቤተልሔም የመጣሁ ሌዋዊ ነኝ፤ የምኖርበት ስፍራ ለመፈለግ እየሄድኩ ነው” አለው። 10 በመሆኑም ሚክያስ “እንግዲያው እኔ ጋ ተቀመጥ፤ እንደ አባትና* እንደ ካህንም ሆነህ አገልግለኝ። እኔ ደግሞ በዓመት አሥር የብር ሰቅል እንዲሁም ልብስና ምግብህን እሰጥሃለሁ” አለው። ስለዚህ ሌዋዊው ገባ። 11 በዚህ መንገድ ሌዋዊው ከሰውየው ጋር ለመኖር ተስማማ፤ ወጣቱም ከልጆቹ እንደ አንዱ ሆነለት። 12 በተጨማሪም ሚክያስ ሌዋዊውን ካህን ሆኖ እንዲያገለግለው ሾመው፤* + እሱም በሚክያስ ቤት ኖረ። 13 ከዚያም ሚክያስ “ሌዋዊው፣ ካህን ስለሆነልኝ ይሖዋ መልካም እንደሚያደርግልኝ አሁን ተረድቻለሁ” አለ።
18 በዚያ ዘመን በእስራኤል ንጉሥ አልነበረም።+ በዚያ ጊዜ የዳናውያን ነገድ+ የሚሰፍርበት ርስት እየፈለገ ነበር፤ ምክንያቱም ዳናውያን እስከዚያ ጊዜ ድረስ በእስራኤል ነገዶች መካከል ርስት አልተሰጣቸውም ነበር።+
2 ዳናውያን ከቤተሰባቸው መካከል ብቃት ያላቸውን አምስት ወንዶች መርጠው ምድሪቱን እንዲሰልሉና እንዲቃኙ ከጾራና ከኤሽታዖል+ ላኳቸው። እነሱንም “ሂዱ፣ ምድሪቱን ቃኙ” አሏቸው። እነሱም በኤፍሬም ተራራማ አካባቢ ወደሚገኘው ወደ ሚክያስ+ ቤት ሲደርሱ እዚያ አደሩ። 3 ወደ ሚክያስ ቤት በቀረቡም ጊዜ የወጣቱን ሌዋዊ ድምፅ* ለዩት፤ በመሆኑም ወደ እሱ ገብተው “ለመሆኑ እዚህ ማን አመጣህ? ደግሞስ እዚህ ምን ትሠራለህ? እዚህ እንድትቆይ ያደረገህስ ምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት። 4 እሱም መልሶ “ሚክያስ ይህን ይህን አደረገልኝ፤ ካህን ሆኜ እንዳገለግለውም ቀጠረኝ”+ አላቸው። 5 ከዚያም እነሱ “መንገዳችን የተቃና መሆን አለመሆኑን እባክህ አምላክን ጠይቅልን” አሉት። 6 ካህኑም “በሰላም ሂዱ። በመንገዳችሁ ሁሉ ይሖዋ ከእናንተ ጋር ነው” አላቸው።
7 ስለሆነም አምስቱ ሰዎች ጉዟቸውን በመቀጠል ወደ ላይሽ+ መጡ። የከተማዋም ሰዎች ልክ እንደ ሲዶናውያን ራሳቸውን ችለው እንደሚኖሩ ተመለከቱ። እነዚህ ሰዎች ያለምንም ስጋት ተረጋግተው የተቀመጡ+ ከመሆናቸውም ሌላ በምድሪቱ ላይ እነሱን የሚያውክ ጨቋኝ ቅኝ ገዢ አልነበረም። በተጨማሪም የሚኖሩት ከሲዶናውያን ርቀው ነበር፤ ከማንም ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት አልነበራቸውም።
8 እነሱም በጾራና በኤሽታዖል+ ወደሚገኙት ወንድሞቻቸው በተመለሱ ጊዜ ወንድሞቻቸው “የሄዳችሁበት ጉዳይ እንዴት ሆነ?” በማለት ጠየቋቸው። 9 እነሱም እንዲህ ሲሉ መለሱ፦ “ምድሪቱ በጣም ጥሩ ምድር መሆኗን ስላየን ተነሱ፣ እንዝመትባቸው። ለምን ታመነታላችሁ? ገብታችሁ ምድሪቱን ለመውረስ አትዘግዩ። 10 እዚያ ስትደርሱ ያለምንም ስጋት የተቀመጠ+ ሕዝብ ታገኛላችሁ፤ ምድሪቱም በጣም ሰፊ ነች። አምላክም በምድር ላይ ያለ ማንኛውም ነገር የማይታጣበትን ስፍራ በእጃችሁ አሳልፎ ሰጥቷችኋል።”+
11 ከዚያም ከዳናውያን ቤተሰብ የሆኑና ለጦርነት የታጠቁ 600 ሰዎች ከጾራና ከኤሽታዖል+ ተንቀሳቀሱ። 12 እነሱም ወጥተው በይሁዳ በምትገኘው በቂርያትየአሪም+ ሰፈሩ። ከቂርያትየአሪም በስተ ምዕራብ የሚገኘው ያ ስፍራ እስከ ዛሬ ድረስ ማሃነህዳን* + ተብሎ የሚጠራው በዚህ የተነሳ ነው። 13 ከዚያም ተነስተው ወደ ኤፍሬም ተራራማ አካባቢ ተጓዙ፤ ወደ ሚክያስም+ ቤት መጡ።
14 በኋላም ላይሽን+ ለመሰለል ሄደው የነበሩት አምስቱ ሰዎች ወንድሞቻቸውን “እነዚህ ቤቶች ውስጥ ኤፉድ፣ የተራፊም ቅርጻ ቅርጾች፣* የተቀረጸ ምስልና ከብረት የተሠራ ሐውልት* እንዳለ ታውቃላችሁ?+ እንግዲህ ምን ማድረግ እንዳለባችሁ አስቡ” አሏቸው። 15 እነሱም በሚክያስ ቤት ወደሚገኘው ወደ ወጣቱ ሌዋዊ+ ቤት ጎራ ብለው ስለ ደህንነቱ ጠየቁት። 16 በዚህ ጊዜ ሁሉ ለጦርነት የታጠቁት 600ዎቹ የዳን ሰዎች+ መግቢያው በር ላይ ቆመው ነበር። 17 ምድሪቱን ለመሰለል+ ሄደው የነበሩት አምስቱ ሰዎችም የተቀረጸውን ምስል፣ ኤፉዱን፣+ የተራፊም ቅርጻ ቅርጾቹንና* + ከብረት የተሠራውን ምስል* + ለመውሰድ ወደ ውስጥ ገቡ። (ካህኑም+ ለጦርነት ከታጠቁት 600 ሰዎች ጋር መግቢያው በር ላይ ቆሞ ነበር።) 18 እነሱም ወደ ሚክያስ ቤት ገብተው የተቀረጸውን ምስል፣ ኤፉዱን፣ የተራፊም ቅርጻ ቅርጾቹንና* ከብረት የተሠራውን ምስል* ወሰዱ። ካህኑም “ምን እያደረጋችሁ ነው?” አላቸው። 19 እነሱ ግን እንዲህ አሉት፦ “ዝም በል። ምንም ቃል አትናገር፤ ይልቅስ ከእኛ ጋር ሄደህ አባትና* ካህን ሁነን። ለአንድ ሰው ቤት ካህን ብትሆን ይሻልሃል+ ወይስ በእስራኤል ለሚገኝ አንድ ነገድና+ ቤተሰብ ካህን ብትሆን?” 20 በዚህ ጊዜ የካህኑ ልብ ደስ ተሰኘ፤ እሱም ኤፉዱን፣ የተራፊም ቅርጻ ቅርጾቹንና* የተቀረጸውን ምስል+ ይዞ ከሕዝቡ ጋር ሄደ።
21 ከዚያም ልጆቹን፣ ከብቶቹንና ውድ የሆኑትን ነገሮች ከፊት አስቀድመው ጉዟቸውን ለመቀጠል ተነሱ። 22 ከሚክያስ ቤት የተወሰነ መንገድ ርቀው ከሄዱም በኋላ በሚክያስ ቤት አቅራቢያ በሚገኙ ቤቶች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች አንድ ላይ ተሰበሰቡ፤ ዳናውያንንም ተከታትለው ደረሱባቸው። 23 ከዚያም ጮኸው ሲጠሯቸው ዳናውያኑ ዞር በማለት ሚክያስን “ምን ሆነሃል? ተሰባስባችሁ የመጣችሁትስ ለምንድን ነው?” አሉት። 24 እሱም “የሠራኋቸውን አማልክቴን ወሰዳችሁ፤ ካህኑንም ይዛችሁ ሄዳችሁ። እንግዲህ ምን ቀረኝ? ታዲያ እንዴት ‘ምን ሆነሃል?’ ትሉኛላችሁ?” አላቸው። 25 በዚህ ጊዜ ዳናውያኑ “አትጩኽብን፤ አለዚያ የተቆጡ ሰዎች* ጉዳት ያደርሱባችኋል፤ ይህም የገዛ ሕይወትህንና* የቤተሰብህን ሕይወት* ሊያሳጣህ ይችላል” አሉት። 26 ዳናውያኑም ጉዟቸውን ቀጠሉ፤ ሚክያስም እነሱ ከእሱ ይልቅ ብርቱዎች እንደሆኑ ስለተረዳ ተመልሶ ወደ ቤቱ ሄደ።
27 እነሱም ሚክያስ የሠራቸውን ነገሮችና የእሱን ካህን ከወሰዱ በኋላ ወደ ላይሽ+ ይኸውም ያለምንም ስጋት ተረጋግተው ይኖሩ ወደነበሩት+ ሰዎች ሄዱ። እነሱንም በሰይፍ መቷቸው፤ ከተማዋንም በእሳት አቃጠሉ። 28 ከተማዋ የምትገኘው ከሲዶና ርቃ ስለነበርና ነዋሪዎቿም ከማንኛውም ሕዝብ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ስላልነበራቸው ማንም የሚያድናት አልነበረም፤ ላይሽ የምትገኘው በቤትሬሆብ+ ባለው ሸለቋማ ሜዳ* ላይ ነበር። እነሱም ከተማዋን ዳግመኛ ገንብተው በዚያ መኖር ጀመሩ። 29 በተጨማሪም ከተማዋን ለእስራኤል በተወለደለት+ በአባታቸው በዳን ስም ዳን+ ብለው ጠሯት። የከተማዋ የቀድሞ ስም ግን ላይሽ ነበር።+ 30 ከዚያም ዳናውያን የተቀረጸውን ምስል+ ለራሳቸው አቆሙት፤ የሙሴ ልጅ የሆነው የጌርሳም+ ልጅ ዮናታንና+ ወንዶች ልጆቹ የምድሪቱ ነዋሪዎች በግዞት እስከተወሰዱበት ጊዜ ድረስ የዳናውያን ነገድ ካህናት ሆኑ። 31 ሚክያስ የሠራውንም የተቀረጸ ምስል አቆሙት፤ ምስሉም የእውነተኛው አምላክ ቤት በሴሎ በነበረበት ጊዜ ሁሉ በዚያ ነበር።+
19 በእስራኤል ንጉሥ ባልነበረበት+ በዚያ ዘመን በኤፍሬም ተራራማ አካባቢ+ ራቅ ብሎ በሚገኝ ስፍራ የሚኖር አንድ ሌዋዊ በይሁዳ ካለችው ከቤተልሔም+ አንዲት ቁባት አገባ። 2 ቁባቱ ግን ለእሱ ታማኝ አልነበረችም፤ ከዚያም ትታው በይሁዳ ባለችው ቤተልሔም ወደሚገኘው ወደ አባቷ ቤት ሄደች። እሷም በዚያ ለአራት ወር ተቀመጠች። 3 ባሏም እንድትመለስ ሊያግባባት ተነስቶ ወደ እሷ ሄደ፤ ወደዚያም የሄደው አገልጋዩንና ሁለት አህዮቹን ይዞ ነበር። እሷም ወደ አባቷ ቤት አስገባችው። አባቷም ባየው ጊዜ እሱን በማግኘቱ ተደሰተ። 4 ስለሆነም አማቱ ማለትም የወጣቷ አባት ሰውየውን ለሦስት ቀን እሱ ጋ እንዲቆይ አግባባው፤ እነሱም በሉ፣ ጠጡም፤ እሱም እዚያው አደረ።
5 በአራተኛው ቀን በማለዳ ለመሄድ ሲነሱ የወጣቷ አባት አማቹን “ብርታት እንድታገኙ* ትንሽ እህል ቅመሱ፤ ከዚያ በኋላ ትሄዳላችሁ” አለው። 6 በመሆኑም ተቀመጡ፤ እነሱም አብረው በሉ፤ ጠጡም፤ ከዚያም የወጣቷ አባት ሰውየውን “እባክህ እዚሁ እደር፤ ልብህም ደስ ይበለው” አለው። 7 ሰውየውም ለመሄድ ሲነሳ አማቱ ይለምነው ነበር፤ ስለዚህ ዳግመኛ እዚያው አደረ።
8 በአምስተኛውም ቀን ለመሄድ በማለዳ ሲነሳ የወጣቷ አባት “ብርታት እንድታገኝ* እባክህ ትንሽ እህል ቅመስ” አለው። እነሱም ቀኑ እስኪገባደድ ድረስ እዚያው ዋሉ፤ አብረውም ሲበሉ ቆዩ። 9 ሰውየውም ከቁባቱና ከአገልጋዩ ጋር ለመሄድ ሲነሳ አማቱ ማለትም የወጣቷ አባት እንዲህ አለው፦ “አሁን እኮ እየመሸ ነው! እባካችሁ እዚሁ እደሩ። ቀኑ እየተገባደደ ነው። እዚሁ እደሩና ልባችሁ ደስ ይበለው። ነገ በማለዳ ተነስታችሁ ትጓዛላችሁ፤ ወደ ቤታችሁም* ትሄዳላችሁ።” 10 ሆኖም ሰውየው እዚያ ለማደር አልፈለገም፤ ስለሆነም ተነስቶ እስከ ኢያቡስ ማለትም እስከ ኢየሩሳሌም ድረስ ተጓዘ።+ ከእሱም ጋር ጭነት የተጫኑት ሁለቱ አህዮች፣ ቁባቱና አገልጋዩ ነበሩ።
11 ወደ ኢያቡስም በቀረቡ ጊዜ ቀኑ መሸትሸት ብሎ ነበር። በመሆኑም አገልጋዩ ጌታውን “ወደዚህች የኢያቡሳውያን ከተማ ጎራ ብለን ብናድር አይሻልም?” አለው። 12 ጌታው ግን “እስራኤላውያን ወዳልሆኑ ባዕድ ሰዎች ከተማ መግባት የለብንም። ከዚህ ይልቅ እስከ ጊብዓ+ ድረስ እንሂድ” አለው። 13 ከዚያም አገልጋዩን “ና፣ ከእነዚህ ስፍራዎች ወደ አንዱ ለመድረስ እንሞክር፤ ጊብዓ ወይም ራማ+ እናድራለን” አለው። 14 በመሆኑም ጉዟቸውን ቀጠሉ፤ የቢንያም ወደሆነችው ወደ ጊብዓ በተቃረቡም ጊዜ ፀሐይዋ መጥለቅ ጀመረች።
15 ስለዚህ በጊብዓ ለማደር ወደዚያ ጎራ አሉ። ገብተውም በከተማዋ አደባባይ ተቀመጡ፤ ሆኖም ሊያሳድራቸው ወደ ቤቱ የወሰዳቸው ማንም ሰው አልነበረም።+ 16 በመጨረሻም ምሽት ላይ ከእርሻ ሥራው እየተመለሰ ያለ አንድ አረጋዊ ሰው መጣ። ይህ ሰው የኤፍሬም ተራራማ አካባቢ+ ሰው ነበር፤ በጊብዓም መኖር ከጀመረ የተወሰነ ጊዜ ሆኖታል፤ የከተማዋ ነዋሪዎች ግን ቢንያማውያን+ ነበሩ። 17 አረጋዊውም ቀና ብሎ መንገደኛውን ሰው በከተማዋ አደባባይ ሲያየው “ወዴት ነው የምትሄደው? የመጣኸውስ ከየት ነው?” አለው። 18 እሱም መልሶ እንዲህ አለው፦ “እኛ በይሁዳ ከምትገኘው ቤተልሔም ተነስተን በኤፍሬም ተራራማ አካባቢዎች ራቅ ብሎ ወደሚገኝ ስፍራ እየተጓዝን ነው፤ እኔ የዚያ አካባቢ ሰው ነኝ። በይሁዳ ወደምትገኘው ቤተልሔም+ ሄጄ ነበር፤ አሁን ወደ ይሖዋ ቤት እየሄድኩ ነው፤* ይሁንና ወደ ቤቱ የሚያስገባኝ ሰው አላገኘሁም። 19 ለአህዮቻችን የሚሆን በቂ ገለባና ገፈራ አለን፤+ በተጨማሪም ለእኔም ሆነ ለሴትየዋ እንዲሁም ለአገልጋያችን የሚሆን ምግብና+ የወይን ጠጅ አለን። ምንም የጎደለ ነገር የለም።” 20 ሆኖም አረጋዊው ሰው “ሰላም ለአንተ ይሁን! የሚያስፈልጋችሁን ማንኛውንም ነገር እኔ አሟላላችኋለሁ። ብቻ እዚህ አደባባይ ላይ አትደሩ” አለው። 21 ስለዚህ ወደ ቤቱ ይዞት ገባ፤ ለአህዮቹም ገፈራ ሰጣቸው። ሰዎቹም እግራቸውን ታጠቡ፤ በሉ፣ ጠጡም።
22 እነሱም እየተደሰቱ ሳለ በከተማዋ ውስጥ የሚኖሩ የተወሰኑ ጋጠወጥ ወንዶች ቤቱን ከበው እርስ በርስ እየተገፈታተሩ በሩን ይደበድቡ ጀመር፤ የቤቱ ባለቤት የሆነውንም አረጋዊ “ከእሱ ጋር የፆታ ግንኙነት እንድንፈጽም ቤትህ የገባውን ሰው ወደ ውጭ አውጣልን” ይሉት ነበር።+ 23 በዚህ ጊዜ የቤቱ ባለቤት ወደ እነሱ ወጥቶ እንዲህ አላቸው፦ “ወንድሞቼ ተዉ፤ ይህን መጥፎ ድርጊት አትፈጽሙ። እባካችሁ ይህ ሰው የእኔ እንግዳ ነው። እንዲህ ያለውን አሳፋሪ ድርጊት አትፈጽሙ። 24 ይኸው ድንግል የሆነች ልጄና የሰውየው ቁባት አሉ። እንግዲህ አሻፈረኝ ካላችሁ እነሱን ላውጣላችሁና ልታዋርዷቸው ትችላላችሁ።* + በዚህ ሰው ላይ ግን እንዲህ ያለውን አሳፋሪ ድርጊት አትፈጽሙ።”
25 ሰዎቹ ግን ሊሰሙት ፈቃደኞች አልሆኑም፤ በመሆኑም ሰውየው ቁባቱን+ ይዞ ወደ ውጭ አወጣላቸው። እነሱም ደፈሯት፤ እስኪነጋም ድረስ ሌሊቱን ሙሉ ሲጫወቱባት አደሩ። ከዚያም ጎህ ሲቀድ ለቀቋት። 26 ሴትየዋም በማለዳ መጥታ ጌታዋ ባለበት የሰውየው ቤት በር ላይ ተዘረረች፤ ብርሃን እስኪሆንም ድረስ እዚያው ወድቃ ቀረች። 27 በኋላም ጌታዋ ጉዞውን ለመቀጠል በጠዋት ተነስቶ የቤቱን በሮች ሲከፍት ሴትየዋ ማለትም ቁባቱ እጇ ደፉ ላይ ተዘርግቶ የቤቱ በር ላይ ወድቃ ተመለከተ። 28 እሱም “ተነሽ፤ እንሂድ” አላት። ነገር ግን ምንም መልስ አልነበረም። ከዚያም ሰውየው እሷን በአህያው ላይ አድርጎ ወደ ቤቱ ሄደ።
29 ቤቱም እንደደረሰ ቢላ አንስቶ ቁባቱን በአጥንቶቿ መገጣጠሚያ ላይ 12 ቦታ ቆራረጣት፤ ከዚያም ወደ እያንዳንዱ የእስራኤል ክልል አንድ ቁራጭ ላከ። 30 ይህን ያየ ሰው ሁሉ እንዲህ ይል ነበር፦ “እስራኤላውያን ከግብፅ ምድር ከወጡበት ጊዜ አንስቶ እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ ታይቶም፣ ተሰምቶም አያውቅም። ይህን ጉዳይ በቁም ነገር አስቡበት፤* ተመካከሩበት፤+ ከዚያም ምን መደረግ እንዳለበት ንገሩን።”
20 በመሆኑም ከዳን+ አንስቶ እስከ ቤርሳቤህ ድረስ እንዲሁም በጊልያድ ምድር+ ያሉ እስራኤላውያን በሙሉ አንድ ላይ* በመውጣት በምጽጳ+ በይሖዋ ፊት ተሰበሰቡ። 2 የሕዝቡና የእስራኤል ነገዶች አለቆች ሁሉ በእውነተኛው አምላክ ሕዝብ ጉባኤ መካከል ቦታ ቦታቸውን ይዘው ቆሙ፤ ሰይፍ የታጠቁት እግረኛ ወታደሮች 400,000 ነበሩ።+
3 ቢንያማውያንም የእስራኤል ሰዎች ወደ ምጽጳ መውጣታቸውን ሰሙ።
ከዚያም የእስራኤል ሰዎች “ይህ ክፉ ነገር እንዴት ሊፈጸም እንደቻለ እስቲ ንገሩን?”+ አሏቸው። 4 በዚህ ጊዜ የተገደለችው ሴት ባል የሆነው ሌዋዊ+ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “እኔና ቁባቴ የቢንያም በሆነችው በጊብዓ ለማደር ወደዚያ መጥተን ነበር።+ 5 የጊብዓ ነዋሪዎችም* በእኔ ላይ ተነሱብኝ፤ በሌሊት መጥተውም ቤቱን ከበቡ። ለመግደል ያሰቡት እኔን ነበር፤ ሆኖም ቁባቴን ደፈሯት፤ እሷም ሞተች።+ 6 እኔም የቁባቴን አስከሬን ወስጄ ቆራረጥኩት፤ ከዚያም ወደ እያንዳንዱ የእስራኤል ርስት ላክሁት፤+ ምክንያቱም እነሱ በእስራኤል ውስጥ አሳፋሪና አስነዋሪ ድርጊት ፈጽመዋል። 7 እንግዲህ እናንተ እስራኤላውያን ሁሉ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ያላችሁን ሐሳብና አስተያየት ስጡ።”+
8 ከዚያም ሕዝቡ ሁሉ አንድ ላይ* ሆኖ በመነሳት እንዲህ አለ፦ “ከመካከላችን ማንም ሰው ወደ ድንኳኑ አይሄድም ወይም ወደ ቤቱ አይመለስም። 9 እንግዲህ በጊብዓ ላይ የምናደርገው ይህ ነው፦ ዕጣ እናወጣና እንዘምትባታለን።+ 10 የቢንያም ግዛት የሆነችው የጊብዓ ነዋሪዎች በእስራኤል ውስጥ በፈጸሙት አሳፋሪ ድርጊት የተነሳ በእሷ ላይ ዘምቶ ተገቢውን እርምጃ ለሚወስደው ሠራዊት ስንቅ እንዲያዘጋጁ ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ መካከል ከ100ው 10፣ ከ1,000ው 100፣ ከ10,000ው ደግሞ 1,000 ሰዎችን እንወስዳለን።” 11 በዚህ መንገድ የእስራኤል ሰዎች በሙሉ ግንባር በመፍጠር በከተማዋ ላይ በአንድነት* ወጡ።
12 ከዚያም የእስራኤል ነገዶች ወደ ቢንያም ነገድ መሪዎች ሁሉ እንዲህ በማለት መልእክተኞችን ላኩ፦ “በመካከላችሁ የተፈጸመው ይህ ዘግናኝ ድርጊት ምንድን ነው? 13 በሉ አሁን በጊብዓ ያሉትን እነዚያን ጋጠወጥ ሰዎች+ እንድንገድላቸውና ክፉ የሆነውን ከእስራኤል መካከል እንድናስወግድ ሰዎቹን አሳልፋችሁ ስጡን።”+ ቢንያማውያን ግን ወንድሞቻቸውን እስራኤላውያንን ለመስማት ፈቃደኞች አልሆኑም።
14 ከዚያም ቢንያማውያን ከእስራኤል ሰዎች ጋር ለመዋጋት ከየከተሞቹ ወጥተው በጊብዓ ተሰባሰቡ። 15 ከተመረጡት 700 የጊብዓ ሰዎች በተጨማሪ በዚያ ቀን ሰይፍ የታጠቁ 26,000 ቢንያማውያን ከየከተሞቻቸው ተሰባሰቡ። 16 በሠራዊቱም መካከል የተመረጡ 700 ግራኞች ነበሩ። እያንዳንዳቸውም ድንጋይ ወንጭፈው ፀጉር እንኳ የማይስቱ ነበሩ።
17 የእስራኤል ሰዎች ደግሞ ቢንያምን ሳይጨምር ሰይፍ የታጠቁ 400,000 ሰዎች አሰባሰቡ፤+ እያንዳንዳቸውም ልምድ ያላቸው ተዋጊዎች ነበሩ። 18 እነሱም አምላክን ለመጠየቅ ተነስተው ወደ ቤቴል ወጡ።+ ከዚያም የእስራኤል ሰዎች “ከቢንያማውያን ጋር ለሚደረገው ውጊያ ከመካከላችን ማን ቀድሞ ይውጣ?” ሲሉ ጠየቁ። ይሖዋም “ይሁዳ ቀድሞ ይውጣ” ሲል መለሰ።
19 ከዚያም እስራኤላውያን በማለዳ ተነስተው ጊብዓን ከበቡ።
20 የእስራኤል ሰዎችም ቢንያምን ለመውጋት ወጡ፤ የእስራኤል ሰዎች እነሱን ጊብዓ ላይ ለመውጋት የጦርነት አሰላለፍ ይዘው ቆሙ። 21 ቢንያማውያንም ከጊብዓ በመውጣት በዚያን ቀን ከእስራኤላውያን መካከል 22,000 ሰዎችን ገደሉ። 22 ሆኖም የእስራኤላውያን ሠራዊት ልክ እንደ መጀመሪያው ቀን የጦርነት አሰላለፍ ይዞ አሁንም እዚያው ቦታ ላይ በድፍረት ቆመ። 23 ከዚያም እስራኤላውያን ወጥተው እስኪመሽ ድረስ በይሖዋ ፊት አለቀሱ፤ ይሖዋንም “ከወንድሞቻችን ከቢንያም ሰዎች ጋር ለመዋጋት እንደገና እንውጣ?” በማለት ጠየቁ።+ ይሖዋም “አዎ፣ በእነሱ ላይ ውጡ” አላቸው።
24 በመሆኑም እስራኤላውያን በሁለተኛው ቀን ወደ ቢንያማውያን ተጠጉ። 25 ቢንያማውያንም በሁለተኛው ቀን እነሱን ለመግጠም ከጊብዓ ወጡ፤ ከእስራኤላውያንም መካከል ሰይፍ የታጠቁ ተጨማሪ 18,000 ሰዎችን ገደሉ።+ 26 በዚህ ጊዜ የእስራኤል ሰዎች በሙሉ ወደ ቤቴል ወጡ። በዚያም እያለቀሱ በይሖዋ ፊት ተቀመጡ፤+ እንዲሁም በዚያ ቀን እስኪመሽ ድረስ ጾሙ፤+ በይሖዋም ፊት የሚቃጠሉ መባዎችንና+ የኅብረት መባዎችን+ አቀረቡ። 27 ከዚያም የእስራኤል ሰዎች ይሖዋን ጠየቁ፤+ ምክንያቱም በዚያ ዘመን የእውነተኛው አምላክ የቃል ኪዳን ታቦት የሚገኘው እዚያ ነበር። 28 የአሮን ልጅ፣ የአልዓዛር ልጅ ፊንሃስም+ በዚያ ዘመን በታቦቱ ፊት ያገለግል* ነበር። እነሱም “ወንድሞቻችንን የቢንያምን ሰዎች ለመውጋት እንደገና እንውጣ ወይስ እንቅር?” ሲሉ ጠየቁ።+ ይሖዋም “በነገው ዕለት እነሱን በእጃችሁ አሳልፌ ስለምሰጣችሁ ውጡ” በማለት መለሰላቸው። 29 ከዚያም እስራኤላውያን በጊብዓ ዙሪያ አድፍጠው የሚጠባበቁ+ ሰዎች አስቀመጡ።
30 በሦስተኛውም ቀን እስራኤላውያን ቢንያማውያንን ለመውጋት ወጡ፤ እንደ ሌሎቹ ጊዜያት ሁሉ ጊብዓን ለመውጋት የጦርነት አሰላለፍ ይዘው ቆሙ።+ 31 ቢንያማውያንም ሠራዊቱን ለመግጠም በወጡ ጊዜ ከከተማዋ ራቁ።+ ከዚያም እንደ ሌሎቹ ጊዜያት ሁሉ በአውራ ጎዳናዎቹ ማለትም ወደ ቤቴልና ወደ ጊብዓ በሚወስዱት አውራ ጎዳናዎች ላይ በነበሩት ሰዎች ላይ ጥቃት በመሰንዘር የተወሰኑ ሰዎችን ገደሉ፤ ወደ 30 ገደማ የሚሆኑ የእስራኤል ሰዎችን በሜዳው ላይ ገደሉ።+ 32 በመሆኑም ቢንያማውያን “እንደ በፊቱ ሁሉ አሁንም ድል እያደረግናቸው ነው” አሉ።+ እስራኤላውያን ግን “እየሸሸን ከከተማው ርቀው ወደ አውራ ጎዳናዎቹ እንዲመጡ እናድርጋቸው” አሉ። 33 ስለሆነም የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ከነበሩበት ተነስተው በመሄድ በዓልታማር ላይ የጦርነት አሰላለፍ ይዘው ቆሙ፤ በዚህ ጊዜ አድፍጠው የነበሩት እስራኤላውያን ተደብቀውበት ከነበረው ከጊብዓ አቅራቢያ ተንደርድረው ወጡ። 34 በዚህ መንገድ ከመላው እስራኤል የተውጣጡ 10,000 የተመረጡ ወንዶች ወደ ጊብዓ ፊት ለፊት መጡ፤ ከባድ ውጊያም ተካሄደ። ሆኖም ቢንያማውያን ጥፋት እያንዣበበባቸው መሆኑን አላወቁም ነበር።
35 ይሖዋ ቢንያምን በእስራኤል ፊት ድል አደረገው፤+ በዚያም ቀን እስራኤላውያን ሰይፍ የታጠቁ 25,100 ቢንያማውያንን ገደሉ።+
36 ይሁንና ቢንያማውያን የእስራኤል ሰዎች ከእነሱ ሲያፈገፍጉ ድል እያደረጓቸው ያሉ መስሏቸው ነበር፤+ ሆኖም እስራኤላውያን ያፈገፈጉት በጊብዓ ላይ ባደፈጡት ሰዎች ተማምነው ነበር።+ 37 አድፍጠው የነበሩትም ሰዎች በፍጥነት እየተንደረደሩ ወደ ጊብዓ ሄዱ። ከዚያም በየቦታው ተሰራጭተው ከተማዋን በሙሉ በሰይፍ መቱ።
38 የእስራኤልም ሰዎች አድፍጠው በከተማዋ ላይ ጥቃት የሚሰነዝሩት ተዋጊዎች ከከተማዋ ጭስ እንዲወጣ በማድረግ ምልክት እንዲያሳዩአቸው ተስማምተው ነበር።
39 እስራኤላውያንም ከውጊያው ሲያፈገፍጉ የቢንያም ሰዎች ጥቃት በመሰንዘር ከእስራኤላውያን መካከል ወደ 30 ገደማ የሚሆኑ ሰዎችን ገደሉ፤+ እነሱም “ልክ እንደ መጀመሪያው ውጊያ ሁሉ አሁንም ድል እያደረግናቸው መሆኑ ግልጽ ነው” ይሉ ነበር።+ 40 ሆኖም ምልክት ሆኖ የሚያገለግለው ጭስ እንደ ዓምድ በመሆን ከከተማዋ ይወጣ ጀመር። የቢንያምም ሰዎች ዞር ብለው ሲመለከቱ የመላ ከተማዋ ነበልባል ወደ ሰማይ ሲንቀለቀል አዩ። 41 ከዚያም የእስራኤል ሰዎች ወደ ኋላ ተመለሱ፤ የቢንያምም ሰዎች መጥፊያቸው እንደቀረበ ስላወቁ ተደናገጡ። 42 በመሆኑም ከእስራኤል ሰዎች በመሸሽ ወደ ምድረ በዳው ሄዱ፤ ሆኖም ከከተሞቹ የወጡትም ሰዎች በእነሱ ላይ ጥቃት መሰንዘር ስለጀመሩ ከውጊያው ማምለጥ አልቻሉም። 43 እነሱም ቢንያማውያኑን ከበቧቸው፤ ያለእረፍትም አሳደዷቸው። ከዚያም ጊብዓ ፊት ለፊት በስተ ምሥራቅ አቅጣጫ ባለው ስፍራ ደመሰሷቸው። 44 በመጨረሻም 18,000 የቢንያም ሰዎች ረገፉ፤ ሁሉም ኃያል ተዋጊዎች ነበሩ።+
45 የቢንያም ሰዎችም ዞረው በምድረ በዳው ወደሚገኘው የሪሞን ዓለት+ ሸሹ፤ እስራኤላውያንም 5,000 ሰዎችን በአውራ ጎዳናዎቹ ላይ ገደሉባቸው፤* እስከ ጊድኦምም ድረስ አሳደዷቸው፤ በመሆኑም ተጨማሪ 2,000 ሰዎችን ገደሉ። 46 በዚያ ቀን የተገደሉት ሰይፍ የታጠቁ ቢንያማውያን ቁጥር በአጠቃላይ 25,000 ደረሰ፤+ ሁሉም ኃያል ተዋጊዎች ነበሩ። 47 ሆኖም 600 ሰዎች በምድረ በዳው ወደሚገኘው የሪሞን ዓለት ሸሹ፤ በሪሞን ዓለትም ለአራት ወር ተቀመጡ።
48 የእስራኤልም ሰዎች በቢንያማውያን ላይ ተመልሰው በመምጣት ከሰው አንስቶ እስከ እንስሳ ድረስ በከተማዋ ውስጥ የቀረውን ሁሉ በሰይፍ መቱ። በተጨማሪም በመንገዳቸው ላይ ያገኟቸውን ከተሞች በሙሉ በእሳት አቃጠሉ።
21 የእስራኤል ሰዎች በምጽጳ+ ተሰብስበው “ከእኛ መካከል ማንም ሰው ሴት ልጁን ከቢንያም ወገን ለሆነ ሰው መዳር የለበትም” በማለት ተማምለው ነበር።+ 2 በመሆኑም እስራኤላውያን ወደ ቤቴል+ መጥተው በዚያ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አምርረው እያለቀሱ በእውነተኛው አምላክ ፊት እስከ ምሽት ድረስ ተቀመጡ። 3 እነሱም “የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ሆይ፣ በእስራኤል ውስጥ እንዲህ ያለ ነገር እንዲከሰት ለምን ፈቀድክ? ዛሬ ከእስራኤል መካከል አንድ ነገድ እንዴት ይጥፋ?” ይሉ ነበር። 4 በማግስቱም ሕዝቡ በማለዳ ተነስቶ የሚቃጠሉ መባዎችንና የኅብረት መባዎችን+ ለማቅረብ በዚያ መሠዊያ ሠራ።
5 የእስራኤል ሰዎችም በምጽጳ በይሖዋ ፊት ያልተገኘ ሰው ሁሉ ያለምንም ጥርጥር መገደል አለበት በማለት በጥብቅ ተማምለው ስለነበር “ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ መካከል በይሖዋ ፊት ለመሰብሰብ ያልወጣው ማን ነው?” በማለት ጠየቁ። 6 የእስራኤል ሰዎችም በወንድማቸው በቢንያም ላይ በደረሰው ነገር አዘኑ። እንዲህም አሉ፦ “እነሆ ዛሬ ከእስራኤል መካከል አንድ ነገድ ተቆርጧል። 7 እንግዲህ እኛ ሴት ልጆቻችንን ለእነሱ ላለመዳር በይሖዋ ምለናል፤+ ታዲያ የተረፉት ወንዶች ሚስት ማግኘት እንዲችሉ ምን ብናደርግ ይሻላል?”+
8 እነሱም “ከእስራኤል ነገዶች መካከል በምጽጳ በይሖዋ ፊት ለመቅረብ ያልወጣው የትኛው ነው?”+ በማለት ጠየቁ። ከኢያቢስጊልያድ ጉባኤው ወደነበረበት ሰፈር የመጣ ማንም ሰው አልነበረም። 9 ሕዝቡ በተቆጠረበት ጊዜ ከኢያቢስጊልያድ ነዋሪዎች መካከል አንድም ሰው እንዳልነበር ተገነዘቡ። 10 በመሆኑም ማኅበረሰቡ እጅግ ኃያል ከሆኑት ተዋጊዎች መካከል 12,000 ሰዎችን ወደዚያ ላከ። እንዲህም ሲሉ አዘዟቸው፦ “ሂዱ፤ የኢያቢስጊልያድን ነዋሪዎች በሰይፍ ምቱ፤ ሴቶችንና ልጆችንም እንኳ አታስቀሩ።+ 11 እንግዲህ እንዲህ አድርጉ፦ እያንዳንዱን ወንድ እንዲሁም ከወንድ ጋር የፆታ ግንኙነት ፈጽመው የሚያውቁ ሴቶችን ሁሉ ፈጽማችሁ አጥፉ።” 12 እነሱም ከኢያቢስጊልያድ ነዋሪዎች መካከል ከወንድ ጋር የፆታ ግንኙነት ፈጽመው የማያውቁ 400 ደናግል ሴቶችን አገኙ። እነሱንም በከነአን ምድር በሴሎ+ ወደሚገኘው ሰፈር አመጧቸው።
13 ከዚያም መላው ማኅበረሰብ በሪሞን በሚገኘው ዓለት+ ወዳሉት ቢንያማውያን መልእክት በመላክ የሰላም ጥሪ አቀረበላቸው። 14 በመሆኑም በዚህ ጊዜ ቢንያማውያን ወደ ምድራቸው ተመለሱ። ከኢያቢስጊልያድ ሴቶች መካከል በሕይወት እንዲተርፉ የተዉአቸውንም ሴቶች ሰጧቸው፤+ ሆኖም በቂ ሴቶች አላገኙላቸውም። 15 ሕዝቡም ይሖዋ በእስራኤል ነገዶች መካከል ክፍፍል እንዲኖር በማድረጉ የተነሳ በቢንያማውያን ላይ በደረሰው ነገር አዘነ።+ 16 የማኅበረሰቡም ሽማግሌዎች “ቢንያማውያን ሴቶች በሙሉ ስላለቁ ለተረፉት ወንዶች ሚስት ለማግኘት ምን ብናደርግ ይሻላል?” አሉ። 17 እነሱም እንዲህ በማለት መለሱ፦ “ከእስራኤል መካከል አንድ ነገድ ሙሉ በሙሉ እንዳይጠፋ በሕይወት ለተረፉት ቢንያማውያን ርስት ሊኖራቸው ይገባል። 18 ሆኖም እኛ ሴቶች ልጆቻችንን ለእነሱ መዳር አይፈቀድልንም፤ ምክንያቱም የእስራኤል ሰዎች ‘ለቢንያም ልጁን የሚድር የተረገመ ነው’ ብለው ምለዋል።”+
19 ከዚያም “ከቤቴል በስተ ሰሜንና ከቤቴል ወደ ሴኬም ከሚወስደው አውራ ጎዳና በስተ ምሥራቅ እንዲሁም ከለቦና በስተ ደቡብ በምትገኘው በሴሎ+ በየዓመቱ ለይሖዋ የሚከበር በዓል አለ” አሉ። 20 በመሆኑም የቢንያምን ሰዎች እንዲህ በማለት አዘዟቸው፦ “ሂዱና በወይን እርሻው ውስጥ አድፍጣችሁ ጠብቁ። 21 የሴሎ ወጣት ሴቶች ክብ ሠርተው ለመጨፈር ሲወጡ ስታዩ እያንዳንዳችሁ ከወይን እርሻው ውስጥ ወጥታችሁ ከሴሎ ወጣት ሴቶች መካከል ለራሳችሁ ሚስት ጠልፋችሁ ውሰዱ፤ ከዚያም ወደ ቢንያም ምድር ተመለሱ። 22 አባቶቻቸው ወይም ወንድሞቻቸው መጥተው በእኛ ላይ ስሞታ ቢያሰሙ እንዲህ እንላቸዋለን፦ ‘ባደረግነው ጦርነት ለእያንዳንዳቸው የሚሆኑ ሚስቶችን ማግኘት ስላልቻልን ለእነሱ ስትሉ ውለታ ዋሉልን፤+ እናንተም ብትሆኑ ሴቶቹን ፈቅዳችሁ ስላልሰጣችኋቸው በጥፋተኝነት አትጠየቁም።’”+
23 በመሆኑም የቢንያም ሰዎች እንደተባሉት አደረጉ፤ እያንዳንዳቸውም ከሚጨፍሩት ሴቶች መካከል ሚስቶችን ጠልፈው ወሰዱ። ከዚያም ወደየርስታቸው ተመልሰው በመሄድ ከተሞቻቸውን በድጋሚ ገንብተው+ በዚያ መኖር ጀመሩ።
24 በዚያን ጊዜ እስራኤላውያን እያንዳንዳቸው ወደየነገዳቸውና ወደየቤተሰባቸው በመሄድ ከዚያ አካባቢ ተበተኑ፤ እያንዳንዳቸውም ከዚያ ተነስተው ወደየርስታቸው ሄዱ።
25 በዚያ ዘመን በእስራኤል ንጉሥ አልነበረም።+ እያንዳንዱም ሰው ለራሱ ትክክል መስሎ የታየውን ያደርግ ነበር።
ቃል በቃል “የእስራኤል ወንዶች ልጆች።”
ወይም “ሰጥቼዋለሁ።”
ቃል በቃል “ወደ ዕጣዬ።”
“በአህያዋ ላይ እያለች አጨበጨበች” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “በኔጌብ።”
“የውኃ ምንጮች” የሚል ትርጉም አለው።
“ለጥፋት መዳረግ” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “በረባዳማው ሜዳ።”
ቃል በቃል “የብረት ሠረገሎች።”
ቃል በቃል “ታማኝ ፍቅር እናሳይሃለን።”
ወይም “በዙሪያዋ።”
ወይም “ረባዳማው ሜዳ።”
ቃል በቃል “እጁ።”
ቃል በቃል “እየከበደ።”
“አልቃሽ” የሚል ትርጉም አለው።
ይህ ሞትን የሚያመለክት ቅኔያዊ አነጋገር ነው።
ወይም “አመለኩ።”
ወይም “ይጸጸታል።”
ወይም “ሃማት መግቢያ።”
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ቃል በቃል “ለአራምናሃራይም።”
ቃል በቃል “የአራምን።”
ወይም “ሰላም አገኘች።”
ወደ 38 ሴንቲ ሜትር ገደማ ርዝመት ያለውን አጭር ክንድ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
“የድንጋይ ካባዎች” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ከተቀመጠበት።”
“በአየር ማስገቢያው” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “እግሩን እየሸፈነ።”
“በድንጋይ ካባዎቹ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወንዝ ማቋረጥ የሚቻልበት ጥልቀት የሌለው የወንዝ ክፍል።
ወይም “ሰላም አገኘች።”
ቃል በቃል “እሱም።”
ቃል በቃል “የብረት ሠረገሎች።”
ወይም “ሰዎችህን በታቦር ተራራ አሰማራ።”
ወይም “ደረቅ ወንዝ።”
ወይም “ደረቅ ወንዝ።”
ቃል በቃል “የብረት ሠረገሎች።”
በዓይንና በጆሮ መካከል ያለውን የአካል ክፍል ያመለክታል።
ወይም “ፀጉራቸውን ስለለቀቁት ተዋጊዎች።”
“ተናወጡ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “በረባዳማው ሜዳ።”
“የጸሐፊ መሣሪያ የሚይዙ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ረባዳማው ሜዳ።”
ወይም “ነፍሱን የሚንቅ።”
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ቃል በቃል “ማህፀን።”
ቃል በቃል “ማህፀኖች።”
ወይም “ሰላም አገኘች።”
“የምድር ውስጥ ዕቃ ማከማቻዎች” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “ሺህ።”
አንድ ኢፍ 22 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
“ይሖዋ ሰላም ነው” የሚል ትርጉም አለው።
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
“ባአል በሕግ ይሟገት (ይከራከር)” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”
ቃል በቃል “ጌድዮንን አለበሰው።”
ወይም “በረባዳማው ሜዳ።”
ቃል በቃል “እጅህ ይበረታል።”
ከምሽቱ 4 ሰዓት ገደማ ጀምሮ እስከ ሌሊቱ 8 ሰዓት ገደማ ድረስ።
ቃል በቃል “ይህን ቃል ሲነግራቸው።”
ቃል በቃል “መንፈሳቸው እሱን ከመቃወም በረደ።”
አንድ ሰቅል 11.4 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ቃል በቃል “ራሳቸውን ቀና አላደረጉም።”
ወይም “ሰላም አገኘች።”
ቃል በቃል “ከጭኑ የወጡ 70 ወንዶች ልጆች።”
ቃል በቃል “የእናቱን አባት ቤት ቤተሰብ።”
“ባለርስቶች” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “የሥጋ ዘመዳችሁ።”
ወይም “ቤተ መቅደስ።”
ወይም “ፍሬዬን።”
ወይም “ነፍሱን።”
ወይም “ራሱን እንደ አለቃ አድርጎ ገዛ።”
ቃል በቃል “መጥፎ መንፈስ ላከ።”
ወይም “በተንኮል መልእክተኞችን ላከ።”
ወይም “እጅህ የቻለውን ሁሉ አድርግበት።”
ወይም “በኤልበሪት ቤተ መቅደስ።”
ወይም “ምሽግ።”
ወይም “የሶርያን።”
ወይም “ነፍሱ ልትታገሥ አልቻለችም።”
ቃል በቃል “አዳማጭ።”
ቃል በቃል “ለእኔም ሆነ ለአንተ ምንድን ነው?”
ወይም “በዙሪያዋ።”
ቃል በቃል “በጣም ዝቅ አደረግሽኝ።”
ወይም “ከእንግዲህ ስለማላገባ ከጓደኞቼ ጋር ላልቅስ።”
ወይም “ሥርዓት።”
“ወደ ሰሜን” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ነፍሴን በእጄ ይዤ።”
ወንዝ ማቋረጥ የሚቻልበት ጥልቀት የሌለው የወንዝ ክፍል።
ቃል በቃል “ከማህፀን ጀምሮ።”
“የተወሰነ ወይም የተለየ” የሚል ትርጉም አለው።
ቃል በቃል “ከማህፀን ጀምሮ።”
“ወደ ውስጠኛው ክፍል ከመግባቱ በፊት” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ወደ ውስጠኛው ክፍል።”
ቃል በቃል “እግር ጭናቸው ላይ እየመታ።”
ወይም “ስንጥቅ።”
ወይም “ለማሰርና።”
ወይም “ስንጥቅ።”
ወይም “አስረን።”
“የመንጋጋ ከፍ ያለ ቦታ” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “ጥንካሬው።”
“የጠሪው ምንጭ” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “ደረቅ ወንዝ።”
ወይም “አግባቢው።”
ወይም “ገመድ።”
ወይም “ተጫውተህብኛል።”
ወይም “ነፍሱ ተመረረች።”
ቃል በቃል “ከእናቴ ማህፀን ጀምሮ።”
ወይም “ነፍሴ ከፍልስጤማውያን ጋር ትሙት።”
ወይም “ቀልጦ የተሠራ ሐውልት።”
ወይም “ቀልጦ የተሠራ ሐውልት።”
ወይም “የቤት ውስጥ አማልክት፤ ጣዖታት።”
ቃል በቃል “እጁን ሞላው።”
ወይም “አማካሪና።”
ቃል በቃል “እጁን ሞላው።”
ወይም “አነጋገር።”
“የዳን ሰፈር” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “የቤት ውስጥ አማልክት፤ ጣዖታት።”
ወይም “ቀልጦ የተሠራ ሐውልት።”
ወይም “የቤት ውስጥ አማልክቱንና፤ ጣዖታቱንና።”
ወይም “ቀልጦ የተሠራውን ሐውልት።”
ወይም “የቤት ውስጥ አማልክቱንና፤ ጣዖታቱንና።”
ወይም “ቀልጦ የተሠራውን ሐውልት።”
ወይም “አማካሪና።”
ወይም “የቤት ውስጥ አማልክቱንና፤ ጣዖታቱንና።”
ወይም “በነፍሳቸው የተመረሩ ሰዎች።”
ወይም “ነፍስህንና።”
ወይም “ነፍስ።”
ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”
ወይም “ልባችሁን ለመደገፍ።”
ወይም “ልብህን ለመደገፍ።”
ቃል በቃል “ድንኳናችሁ።”
“አሁን በይሖዋ ቤት አገለግላለሁ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “አስነውሯቸው፤ መልካም መስሎ የታያችሁንም አድርጉባቸው።”
ወይም “ልብ በሉት።”
ቃል በቃል “እንደ አንድ ሰው ሆነው።”
“ባለርስቶች” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “እንደ አንድ ሰው።”
ቃል በቃል “እንደ አንድ ሰው ሆነው።”
ቃል በቃል “ይቆም።”
ቃል በቃል “ቃረሙ።”