ለሮም ሰዎች የተጻፈ ደብዳቤ
1 የክርስቶስ ኢየሱስ ባሪያ ከሆነው፣ ሐዋርያ እንዲሆን ከተጠራውና የአምላክን ምሥራች እንዲያውጅ ከተሾመው* ከጳውሎስ፤+ 2 ይህ ምሥራች አምላክ በነቢያቱ አማካኝነት በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ አስቀድሞ የሰጠው የተስፋ ቃል ሲሆን 3 በሥጋ ከዳዊት ዘር+ ስለተወለደው ልጁ የሚገልጽ ነው፤ 4 ይሁንና እሱ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የአምላክ ልጅ+ መሆኑ እንዲታወቅ ተደርጓል። ይህም የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት በተነሳ+ ጊዜ ነው። 5 ለስሙ ክብር በብሔራት ሁሉ መካከል+ በእምነት የሚታዘዙ ሰዎች እንዲገኙ ሲባል በእሱ አማካኝነት ጸጋና ሐዋርያነት+ ተቀብለናል፤* 6 የኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሆኑ ከአሕዛብ ከተጠሩት መካከል እናንተም ትገኙበታላችሁ። 7 ቅዱሳን እንድትሆኑ ለተጠራችሁና በአምላክ ለተወደዳችሁ በሮም ለምትኖሩ ሁሉ፦
አባታችን ከሆነው አምላክና ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።
8 ከሁሉ አስቀድሜ፣ ስለ እምነታችሁ በመላው ዓለም ስለሚወራ ስለ ሁላችሁም በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለአምላኬ ምስጋና አቀርባለሁ። 9 ያለማቋረጥ ዘወትር በጸሎቴ እናንተን ሳልጠቅስ እንደማላልፍ፣+ ስለ ልጁ የሚገልጸውን ምሥራች በማወጅ በሙሉ ልቤ ቅዱስ አገልግሎት የማቀርብለት አምላክ ምሥክሬ ነው፤ 10 ደግሞም በአምላክ ፈቃድ አሁን በመጨረሻ እንደ ምንም ተሳክቶልኝ ወደ እናንተ መምጣት እንድችል ልመና እያቀረብኩ ነው። 11 ለመጽናት የሚያስችላችሁን መንፈሳዊ ስጦታ እንዳካፍላችሁ ላያችሁ እጓጓለሁና፤ 12 ይህን ስል እኔ በእናንተ እምነት እናንተም በእኔ እምነት እርስ በርሳችን እንድንበረታታ+ ነው።
13 ይሁንና ወንድሞች፣ በሌሎች አሕዛብ መካከል ፍሬ እንዳፈራሁ ሁሉ በእናንተም መካከል ፍሬ አፈራ ዘንድ ወደ እናንተ ለመምጣት ብዙ ጊዜ አቅጄ እንደነበር እንድታውቁ እፈልጋለሁ። ሆኖም ለመምጣት ባሰብኩ ቁጥር የሆነ እንቅፋት ያጋጥመኛል። 14 ለግሪካውያንም ሆነ ግሪካውያን ላልሆኑ* እንዲሁም ለጠቢባንም ሆነ ላልተማሩ ዕዳ አለብኝ፤ 15 በመሆኑም በሮም ላላችሁት ለእናንተም ምሥራቹን ለማወጅ እጓጓለሁ።+ 16 እኔ በምሥራቹ አላፍርምና፤+ እንዲያውም ለሚያምን ሁሉ+ ይኸውም በመጀመሪያ ለአይሁዳዊ+ ከዚያም ለግሪካዊ+ ምሥራቹ መዳን የሚያስገኝ የአምላክ ኃይል ነው። 17 ምክንያቱም “ጻድቅ ግን በእምነት ይኖራል”+ ተብሎ እንደተጻፈ ሁሉ እምነት ያላቸው+ ሰዎች፣ አምላክ በምሥራቹ አማካኝነት ጽድቁን እንደሚገልጥ ይረዳሉ፤ ይህ ደግሞ እምነታቸውን ያጠነክርላቸዋል።
18 እውነትን ለማፈን+ የተንኮል ዘዴ የሚጠቀሙ ሰዎች በሚፈጽሙት አምላክን የሚጻረር ድርጊትና ክፋት ሁሉ ላይ የአምላክ ቁጣ+ ከሰማይ እየተገለጠ ነው፤ 19 ምክንያቱም ስለ አምላክ ሊታወቅ የሚችለው ነገር በእነሱ ዘንድ በግልጽ የታወቀ ነው፤ ይህም የሆነው አምላክ ይህን ግልጽ ስላደረገላቸው ነው።+ 20 የማይታዩት ባሕርያቱ ይኸውም ዘላለማዊ ኃይሉና+ አምላክነቱ+ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ በግልጽ ይታያሉ፤+ ምክንያቱም ባሕርያቱን ከተሠሩት ነገሮች ማስተዋል ይቻላል፤ ስለሆነም የሚያመካኙበት ነገር የላቸውም። 21 አምላክን የሚያውቁ ቢሆኑም እንኳ እንደ አምላክነቱ አላከበሩትም ብሎም አላመሰገኑትም፤ ከዚህ ይልቅ አስተሳሰባቸው ከንቱ ሆነ፤ የማያስተውለው ልባቸውም ጨለመ።+ 22 ጥበበኞች ነን ቢሉም ሞኞች ሆኑ፤ 23 ሊጠፋ የማይችለውን አምላክ ክብር ጠፊ በሆነው ሰው፣ በወፎች፣ አራት እግር ባላቸው እንስሳትና በምድር ላይ በሚሳቡ ፍጥረታት ምስል ለወጡት።+
24 ስለሆነም አምላክ እንደ ልባቸው ምኞት የገዛ ራሳቸውን አካል እንዲያስነውሩ ለርኩሰት አሳልፎ ሰጣቸው። 25 እነዚህ ሰዎች የአምላክን እውነት በሐሰት ለውጠዋል፤ በፈጣሪ ፋንታ ለፍጥረት ክብር ሰጥተዋል፤* እንዲሁም ቅዱስ አገልግሎት አቅርበዋል፤ ይሁንና ለዘላለም ሊወደስ የሚገባው ፈጣሪ ብቻ ነው። አሜን። 26 አምላክ አሳፋሪ ለሆነ የፆታ ምኞት+ አሳልፎ የሰጣቸው በዚህ ምክንያት ነው፤ ሴቶቻቸውም ተፈጥሯዊ የሆነውን ግንኙነት ከተፈጥሮ ውጭ በሆነ ግንኙነት ለወጡ፤+ 27 ወንዶቹም ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ ከሴቶች ጋር መገናኘት ትተው እርስ በርሳቸው ኃይለኛ በሆነ የፆታ ስሜት ተቃጠሉ፤ ወንዶች ከወንዶች ጋር አስነዋሪ ነገር ፈጸሙ፤+ እነሱ ራሳቸውም ለጥፋታቸው የሚገባውን ቅጣት* እየተቀበሉ ነው።+
28 ለአምላክ እውቅና መስጠት ተገቢ መስሎ ስላልታያቸው* መደረግ የማይገባውን ነገር እንዲያደርጉ አምላክ በእሱ ዘንድ ተቀባይነት ለሌለው አስተሳሰብ አሳልፎ ሰጣቸው።+ 29 ደግሞም እነዚህ ሰዎች በዓመፅ፣+ በኃጢአተኝነት፣ በስግብግብነት፣*+ በክፋት፣ በቅናት፣+ በነፍሰ ገዳይነት፣+ በጥል፣ በማታለልና+ በተንኮል+ የተሞሉ ናቸው፤ እንዲሁም ስም አጥፊዎች፣* 30 ሐሜተኞች፣+ አምላክን የሚጠሉ፣ ተሳዳቢዎች፣ ትዕቢተኞች፣ ጉረኞች፣ ክፋት ጠንሳሾች፣ ለወላጆች የማይታዘዙ፣+ 31 የማያስተውሉ፣+ ቃላቸውን የማይጠብቁ፣ ተፈጥሯዊ ፍቅር የሌላቸውና ምሕረት የለሾች ናቸው። 32 እነዚህ ሰዎች ‘እንዲህ ያሉ ነገሮችን የሚያደርጉ* ሁሉ ሞት ይገባቸዋል’+ የሚለውን የአምላክን የጽድቅ ሕግ በሚገባ የሚያውቁ ቢሆኑም በዚህ ድርጊታቸው መግፋት ብቻ ሳይሆን ይህን የሚያደርጉትንም ይደግፋሉ።
2 ስለዚህ አንተ ሰው፣ ማንም ሆንክ ማን+ በሌላው ላይ የምትፈርድ ከሆነ ምንም የምታመካኝበት ነገር የለህም፤ በሌላው ላይ ስትፈርድ ራስህንም ኮነንክ ማለት ነው፤ ምክንያቱም በሌላው ላይ የምትፈርድ አንተ ራስህ እነዚያኑ ነገሮች በተደጋጋሚ ታደርጋለህ።+ 2 አምላክ እንዲህ ያሉትን ነገሮች በሚፈጽሙ ሰዎች ላይ እንደሚፈርድ እናውቃለን፤ ፍርዱ ደግሞ ከእውነት ጋር የሚስማማ ነው።
3 ይሁን እንጂ አንተ ሰው፣ እንዲህ ያሉትን ነገሮች በሚፈጽሙ ሰዎች ላይ እየፈረድክ አንተ ግን እነዚያኑ ነገሮች የምታደርግ ከሆነ ከአምላክ ፍርድ አመልጣለሁ ብለህ ታስባለህ? 4 ወይስ አምላክ በደግነቱ ወደ ንስሐ ሊመራህ+ እየሞከረ እንዳለ ሳታውቅ የደግነቱን፣+ የቻይነቱንና+ የትዕግሥቱን+ ብዛት ትንቃለህ? 5 እንግዲህ በግትርነትህና ንስሐ በማይገባው ልብህ የተነሳ በራስህ ላይ ቁጣ ታከማቻለህ። ይህ ቁጣ አምላክ የጽድቅ ፍርድ በሚፈርድበት ቀን ይገለጣል።+ 6 እሱም ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ይከፍለዋል፦+ 7 በመልካም ሥራ በመጽናት ክብርን፣ ሞገስንና ሊጠፋ የማይችል ሕይወትን+ ለሚፈልጉ የዘላለም ሕይወት ይሰጣቸዋል፤ 8 ይሁን እንጂ ጠብ ወዳዶች በሆኑትና ለእውነት ከመታዘዝ ይልቅ ለዓመፅ በሚታዘዙት ላይ ቁጣና መዓት ይወርድባቸዋል።+ 9 ክፉ ሥራ በሚሠራ ሰው ሁሉ* ላይ ይኸውም በመጀመሪያ በአይሁዳዊ ከዚያም በግሪካዊ ላይ መከራና ጭንቀት ይመጣል፤ 10 ሆኖም መልካም ሥራ የሚሠራ ሁሉ ይኸውም በመጀመሪያ አይሁዳዊ+ ከዚያም ግሪካዊ+ ክብር፣ ሞገስና ሰላም ያገኛል። 11 በአምላክ ዘንድ አድልዎ የለምና።+
12 ሕግ ሳይኖራቸው ኃጢአት የሠሩ ሁሉ ያለሕግ ይጠፋሉና፤+ ሆኖም ሕግ እያላቸው ኃጢአት የሠሩ ሁሉ በሕግ ይፈረድባቸዋል።+ 13 ምክንያቱም በአምላክ ፊት ጻድቅ የሆኑት ሕግን የሚሰሙ አይደሉም፤ ከዚህ ይልቅ ጻድቃን ናችሁ የሚባሉት ሕግን የሚፈጽሙ ናቸው።+ 14 ሕግ የሌላቸው+ አሕዛብ በተፈጥሮ በሕጉ ውስጥ ያሉትን ነገሮች ሲያደርጉ እነዚህ ሰዎች ሕግ ባይኖራቸውም እንኳ እነሱ ለራሳቸው ሕግ ናቸውና። 15 የሕጉ መሠረታዊ ሐሳብ በልባቸው እንደተጻፈ የሚያሳዩት እነሱ ራሳቸው ናቸው፤ ሕሊናቸው ከእነሱ ጋር ሆኖ በሚመሠክርበት ጊዜ ሐሳባቸው በውስጣቸው* እየተሟገተ አንዴ ይከሳቸዋል፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ጥፋተኛ አይደላችሁም ይላቸዋል። 16 ይህ የሚሆነው እኔ በማውጀው ምሥራች መሠረት አምላክ በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ሰዎች በስውር በሚያስቧቸውና በሚያደርጓቸው ነገሮች ላይ በሚፈርድበት+ ቀን ነው።
17 አንተ አይሁዳዊ ተብለህ የምትጠራ፣+ በሕጉ የምትመካ፣ ከአምላክ ጋር ባለህ ዝምድና የምትኩራራ፣ 18 ፈቃዱን የምታውቅ፣ በሕጉ ውስጥ ያለውን ነገር የተማርክ*+ በመሆንህ የላቀ ዋጋ ያላቸውን ነገሮች በሚገባ የምትገነዘብ፣ 19 ለዕውር መሪ፣ በጨለማ ላሉት ብርሃን ነኝ ብለህ የምታምን፣ 20 ማስተዋል የጎደላቸውን የማሠለጥንና ሕፃናትን የማስተምር ነኝ የምትል እንዲሁም በሕጉ ውስጥ ያሉትን የእውቀትና የእውነት መሠረታዊ ገጽታዎች የምታውቅ ከሆንክ፣ 21 ታዲያ አንተ ሌላውን የምታስተምር ራስህን አታስተምርም?+ አንተ “አትስረቅ”+ ብለህ የምትሰብክ ትሰርቃለህ? 22 አንተ “አታመንዝር”+ የምትል ታመነዝራለህ? አንተ ጣዖትን የምትጸየፍ ቤተ መቅደስን ትዘርፋለህ? 23 አንተ በሕግ የምትኩራራ ሕጉን በመተላለፍ አምላክን ታዋርዳለህ? 24 ይህም “በእናንተ ምክንያት የአምላክ ስም በአሕዛብ መካከል ይሰደባል” ተብሎ እንደተጻፈው ነው።+
25 መገረዝ+ ጥቅም የሚኖረው ሕጉን እስካከበርክ ድረስ ነው፤+ ሕጉን የምትተላለፍ ከሆነ ግን መገረዝህ እንደ አለመገረዝ ይቆጠራል። 26 ያልተገረዘ ሰው+ በሕጉ ውስጥ ያሉትን የጽድቅ መሥፈርቶች የሚጠብቅ ከሆነ አለመገረዙ እንደ መገረዝ አይቆጠርም?+ 27 እንግዲህ አንተ የተጻፈ ሕግ ያለህና የተገረዝክ ሆነህ ሳለ ሕግን የምትጥስ ከሆነ በሥጋ ያልተገረዘ ሆኖ ሕግን የሚፈጽም ሰው ይፈርድብሃል። 28 ምክንያቱም እውነተኛ አይሁዳዊነት በውጫዊ ገጽታ የሚገለጽ አይደለም፤+ ግርዘቱም ውጫዊና ሥጋዊ ግርዘት አይደለም።+ 29 ከዚህ ይልቅ በውስጡ አይሁዳዊ የሆነ እሱ አይሁዳዊ ነው፤+ ግርዘቱም በተጻፈ ሕግ ሳይሆን በመንፈስ+ የሆነ የልብ ግርዘት ነው።+ እንዲህ ዓይነቱ ሰው ውዳሴ የሚያገኘው ከሰው ሳይሆን ከአምላክ ነው።+
3 ታዲያ አይሁዳዊ መሆን ጥቅሙ ምኑ ላይ ነው? ግርዘትስ ፋይዳው ምንድን ነው? 2 በሁሉም መንገድ ትልቅ ጥቅም አለው። በመጀመሪያ ደረጃ የአምላክ ቅዱስ ቃል+ በአደራ ተሰጥቷቸዋል። 3 አንዳንድ አይሁዳውያን እምነት ቢጎድላቸውስ? የእነሱ እምነት ማጣት ሰዎች በአምላክ እንዳይታመኑ ሊያደርግ ይችላል? 4 በፍጹም! ከዚህ ይልቅ “በቃልህ ጻድቅ ሆነህ ትገኝ ዘንድ፣ በፍርድም ፊት ትረታ ዘንድ”+ ተብሎ እንደተጻፈ ሰው ሁሉ ሐሰተኛ ሆኖ ቢገኝ+ እንኳ የአምላክ እውነተኝነት የተረጋገጠ ነው።+ 5 ይሁን እንጂ የእኛ ክፋት የአምላክን ጽድቅ አጉልቶ የሚያሳይ ከሆነ ምን ማለት እንችላለን? አምላክ ቁጣውን መግለጹ ኢፍትሐዊ ያሰኘዋል እንዴ? (አንዳንድ ሰዎች እንደሚያስቡት ማለት ነው።) 6 በፍጹም! አለዚያ አምላክ በዓለም ላይ እንዴት ይፈርዳል?+
7 ይሁንና በእኔ ውሸት የተነሳ የአምላክ እውነት ለእሱ ክብር በሚያመጣ መንገድ ይበልጥ ጎልቶ የሚወጣ ከሆነ ታዲያ እኔ ለምን ኃጢአተኛ ተብዬ ይፈረድብኛል? 8 እንዲህ ከሆነማ አንዳንድ ሰዎች “ጥሩ ነገር እንዲገኝ መጥፎ ነገር እንሥራ” ይላሉ በማለት በሐሰት እንደሚያስወሩብን ለምን አንልም? በእነዚህ ሰዎች ላይ የሚበየነው ፍርድ ፍትሐዊ ነው።+
9 እንግዲህ ምን ማለት ይቻላል? እኛ የተሻልን ነን ማለት ነው? በፍጹም! ምክንያቱም አይሁዳውያንም ሆኑ ግሪካውያን ሁሉም የኃጢአት ተገዢዎች+ እንደሆኑ በመናገር አስቀድመን ከሰናቸዋል፤ 10 ይህም እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈው ነው፦ “ጻድቅ ሰው የለም፤ አንድም እንኳ የለም፤+ 11 ማስተዋል ያለው አንድም ሰው የለም፤ ደግሞም አምላክን የሚፈልግ አንድም ሰው የለም። 12 ሁሉም መንገድ ስተዋል፤ ሁሉም የማይረቡ ሆነዋል፤ ደግነት የሚያሳይ አንድም ሰው የለም፤ አንድም እንኳ አይገኝም።”+ 13 “ጉሮሯቸው የተከፈተ መቃብር ነው፤ በምላሳቸው ያታልላሉ።”+ “ከከንፈራቸው ሥር የእባብ መርዝ አለ።”+ 14 “አፋቸውም በእርግማንና በምሬት የተሞላ ነው።”+ 15 “እግሮቻቸው ደም ለማፍሰስ ፈጣኖች ናቸው።”+ 16 “በመንገዳቸው ላይ ጥፋትና መከራ አለ፤ 17 የሰላምንም መንገድ አያውቁም።”+ 18 “በዓይኖቻቸው ፊት አምላክን መፍራት የሚባል ነገር የለም።”+
19 እንግዲህ አፍ ሁሉ እንዲዘጋና ዓለም በሙሉ በአምላክ ፊት ተጠያቂ እንዲሆን+ ሕግ የሚናገረው ሁሉ ከሕግ በታች ላሉት እንደሆነ እናውቃለን። 20 ስለዚህ ሕግን በመጠበቅ ማንም ሰው* በፊቱ ጻድቅ ነህ ሊባል አይችልም፤+ ምክንያቱም ስለ ኃጢአት ትክክለኛ ግንዛቤ* የሚገኘው በሕጉ አማካኝነት ነው።+
21 አሁን ግን ሕግ ሳያስፈልግ፣ በሕጉና በነቢያት የተመሠከረለት+ የአምላክ ጽድቅ ግልጽ ሆኗል፤+ 22 እምነት ያላቸው ሁሉ ደግሞ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ባላቸው እምነት አማካኝነት የአምላክን ጽድቅ ያገኛሉ። ይህም የሆነው በሰዎች መካከል ምንም ልዩነት ስለሌለ ነው።+ 23 ምክንያቱም ሁሉም ኃጢአት ሠርተዋል፤ የአምላክንም ክብር ማንጸባረቅ ተስኗቸዋል፤+ 24 ይሁንና ክርስቶስ ኢየሱስ የከፈለው ቤዛ+ በሚያስገኘው ነፃነት አማካኝነት በጸጋው+ ጻድቃን ናችሁ መባላቸው እንዲሁ የተገኘ ነፃ ስጦታ ነው።+ 25 በኢየሱስ ደም የሚያምኑ+ ሁሉ ማስተሰረያ ያገኙ*+ ዘንድ አምላክ እሱን መባ አድርጎ አቅርቦታል። አምላክ ይህን ያደረገው የራሱን ጽድቅ ለማሳየት ነው፤ ምክንያቱም አምላክ ቻይ በመሆን በቀደሙት ዘመናት የተፈጸሙትን ኃጢአቶች ይቅር ብሏል። 26 ይህን ያደረገው በዚህም ዘመን የራሱን ጽድቅ ለማሳየት ነው፤+ ይህም በኢየሱስ የሚያምነውን ሰው ጻድቅ ነህ በማለት እሱ ራሱ ጻድቅ ይሆን ዘንድ ነው።+
27 ታዲያ እንድንኮራ የሚያደርገን ነገር ይኖራል? ምንም ነገር የለም። እንዳንኮራ የሚያደርገን ሕግ የትኛው ነው? የሥራ ሕግ ነው?+ በፍጹም አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ እንዳንኮራ የሚያደርገን የእምነት ሕግ ነው። 28 ምክንያቱም አንድ ሰው ጻድቅ ነህ የሚባለው የሕግን ሥራ በመፈጸም ሳይሆን በእምነት እንደሆነ እንረዳለን።+ 29 ወይስ አምላክ የአይሁዳውያን አምላክ ብቻ ነው?+ የአሕዛብስ አምላክ አይደለም?+ አዎ፣ የአሕዛብም አምላክ ነው።+ 30 አምላክ አንድ ስለሆነ+ የተገረዙትን ከእምነት የተነሳ ጻድቃን ይላቸዋል፤+ ያልተገረዙትንም በእምነታቸው አማካኝነት ጻድቃን ናችሁ ይላቸዋል።+ 31 ታዲያ በእምነታችን አማካኝነት ሕግን እንሽራለን ማለት ነው? በፍጹም! እንዲያውም ሕግን እንደግፋለን።+
4 እንዲህ ከሆነ ታዲያ በሥጋ አባታችን የሆነው አብርሃም ምን አገኘ እንላለን? 2 ለምሳሌ አብርሃም ጻድቅ የተባለው በሥራ ቢሆን ኖሮ የሚመካበት ነገር በኖረው ነበር፤ ሆኖም በአምላክ ፊት ሊመካ አይችልም። 3 የቅዱስ መጽሐፉስ ቃል ምን ይላል? “አብርሃም በይሖዋ* አመነ፤ ይህም ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት።”+ 4 ይሁንና ለሚሠራ ሰው ደሞዙ እንደ ሥራው ዋጋ* እንጂ እንደ ጸጋ ስጦታ ተደርጎ አይቆጠርለትም። 5 በሌላ በኩል ግን በራሱ ሥራ ከመመካት ይልቅ ኃጢአተኛውን ጻድቅ ነህ ብሎ በሚጠራው አምላክ የሚያምን እምነቱ እንደ ጽድቅ ይቆጠርለታል።+ 6 ይህም ዳዊት፣ አምላክ ያለሥራ እንደ ጻድቅ አድርጎ የሚቆጥረው ሰው ስለሚያገኘው ደስታ እንዲህ ብሎ እንደተናገረው ነው፦ 7 “የዓመፅ ሥራቸው ይቅር የተባለላቸው፣ ኃጢአታቸውም የተሸፈነላቸው* ደስተኞች ናቸው፤ 8 ይሖዋ* ኃጢአቱን የማይቆጥርበት ሰው ደስተኛ ነው።”+
9 ታዲያ ይህን ደስታ የሚያገኙት የተገረዙ ሰዎች ብቻ ናቸው ወይስ ያልተገረዙትም ጭምር?+ ምክንያቱም “አብርሃም እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት” ብለናል።+ 10 ታዲያ እምነቱ እንደ ጽድቅ የተቆጠረው በምን ዓይነት ሁኔታ እያለ ነው? ተገርዞ እያለ ነው ወይስ ከመገረዙ በፊት? ተገርዞ እያለ ሳይሆን ከመገረዙ በፊት ነው። 11 ገና ከመገረዙ በፊት በነበረው እምነት ላገኘው ጽድቅ ምልክት ሆኖ የሚያገለግለውን+ ግርዘትን እንደ ማኅተም* ተቀበለ፤ ስለዚህ ባይገረዙም እንኳ በእምነታቸው የተነሳ እንደ ጻድቃን ለተቆጠሩት ሁሉ አባት ሆኗል፤+ 12 ለተገረዙት ዘሮቹም አባት ነው፤ ይሁንና ግርዘትን አጥብቀው ለሚከተሉት ብቻ ሳይሆን አባታችን አብርሃም+ ከመገረዙ በፊት የነበረውን እምነት ተከትለው በሥርዓት ለሚመላለሱ ሰዎችም ሁሉ አባት ነው።
13 ምክንያቱም አብርሃም ወይም ዘሩ የዓለም ወራሽ+ እንደሚሆን ተስፋ የተሰጠው በሕግ አማካኝነት ሳይሆን በእምነት በሚገኘው ጽድቅ ነው።+ 14 ወራሾች የሚሆኑት ሕጉን በጥብቅ የሚከተሉ ቢሆኑ ኖሮ እምነት ከንቱ በሆነ ነበርና፤ የተስፋውም ቃል ባከተመ ነበር። 15 እንደ እውነቱ ከሆነ ሕጉ ቁጣ ያስከትላል፤+ ሆኖም ሕግ ከሌለ ሕግን መተላለፍ የሚባል ነገር አይኖርም።+
16 በመሆኑም ተስፋው በእምነት የተገኘ ነው፤ ይህም የሆነው ተስፋው በጸጋ+ ላይ የተመሠረተ እንዲሆንና ለዘሩ ሁሉ+ ይኸውም ሕጉን በጥብቅ ለሚከተል ብቻ ሳይሆን የሁላችንም አባት+ የሆነውን የአብርሃምን እምነት በጥብቅ ለሚከተል ጭምር የተረጋገጠ እንዲሆን ነው። 17 (ይህም “ለብዙ ብሔራት አባት አድርጌሃለሁ” ተብሎ እንደተጻፈው ነው።)+ ይህ የሆነው እሱ ባመነበት ማለትም ሙታንን ሕያው በሚያደርገውና የሌለውን እንዳለ አድርጎ በሚጠራው* አምላክ ፊት ነው። 18 ተስፋ ለማድረግ የሚያበቃ ምንም መሠረት ባይኖርም እንኳ “የአንተም ዘር እጅግ ይበዛል”+ ተብሎ በተነገረው መሠረት የብዙ ብሔራት አባት እንደሚሆን በተሰጠው ተስፋ አምኗል። 19 እምነቱ ባይዳከምም እንኳ 100 ዓመት ገደማ+ ሆኖት ስለነበር የሞተ ያህል ስለሆነው የገዛ ራሱ አካል እንዲሁም ሙት* ስለሆነው የሣራ ማህፀን አሰበ።+ 20 ሆኖም አምላክ ከሰጠው የተስፋ ቃል የተነሳ ለአምላክ ክብር በመስጠት በእምነት በረታ እንጂ እምነት በማጣት አልወላወለም፤ 21 ደግሞም አምላክ የሰጠውን ተስፋ መፈጸም እንደሚችል ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነበር።+ 22 በመሆኑም “ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት።”+
23 ሆኖም “ተቆጠረለት” ተብሎ የተጻፈው ስለ እሱ ብቻ አይደለም፤+ 24 ከዚህ ይልቅ እንደ ጻድቃን ስለምንቆጠረው ስለ እኛም ጭምር ነው፤ ምክንያቱም ጌታችንን ኢየሱስን ከሞት ባስነሳው በእሱ እናምናለን።+ 25 ኢየሱስ ስለ በደላችን ለሞት አልፎ ተሰጠ፤+ አምላክ ጻድቃን ናችሁ ብሎ እንዲያስታውቅልንም ከሞት ተነሳ።+
5 ስለዚህ አሁን በእምነት አማካኝነት ጻድቃን ናችሁ+ ስለተባልን በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኩል+ ከአምላክ ጋር ያለንን ሰላም ጠብቀን እንኑር፤* 2 ደግሞም በኢየሱስ አማካኝነት የአምላክን ጸጋ ለማግኘት በእምነት ወደ እሱ መቅረብ የቻልን ሲሆን ይህን ጸጋ አሁን አግኝተናል፤+ የአምላክንም ክብር እንደምናገኝ ተስፋ በማድረግ እጅግ እንደሰት።* 3 በዚህ ብቻ ሳይሆን በመከራ ውስጥ እያለንም እጅግ እንደሰት፤*+ ምክንያቱም መከራ ጽናትን እንደሚያስገኝ እናውቃለን፤+ 4 ጽናትም በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንድናገኝ+ ያስችለናል፤ ተቀባይነት ማግኘት ደግሞ ተስፋን+ ያጎናጽፋል፤ 5 ተስፋውም ሳይፈጸም ቀርቶ ለሐዘን* አይዳርገንም፤+ ምክንያቱም የአምላክ ፍቅር፣ በተሰጠን መንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በልባችን ውስጥ ፈሷል።+
6 ገና ደካሞች ሳለን+ ክርስቶስ አስቀድሞ የተወሰነው ጊዜ ሲደርስ ለኃጢአተኞች ሞቷልና። 7 ለጻድቅ ሰው የሚሞት ማግኘት በጣም አዳጋች ነው፤ ለጥሩ ሰው ለመሞት የሚደፍር ግን ምናልባት ይገኝ ይሆናል። 8 ሆኖም አምላክ ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ እንዲሞትልን በማድረግ ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር አሳይቷል።+ 9 ከእንግዲህ በደሙ ጻድቃን ናችሁ ስለተባልን+ በእሱ አማካኝነት ከአምላክ ቁጣ እንደምንድን ይበልጥ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።+ 10 ጠላቶች ሆነን ሳለን በልጁ ሞት አማካኝነት ከአምላክ ጋር ከታረቅን አሁን ታርቀን ሳለንማ+ በእሱ ሕይወት እንደምንድን የተረጋገጠ ነው። 11 ይህም ብቻ ሳይሆን አሁን እርቅ ባገኘንበት+ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት በአምላክ ሐሴት እያደረግን ነው።
12 ስለሆነም በአንድ ሰው አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤+ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ፤ ሁሉም ኃጢአት ስለሠሩም ሞት ለሰው ሁሉ ተዳረሰ።+ 13 ሕጉ ከመሰጠቱ በፊት ኃጢአት በዓለም ላይ ነበርና፤ ሆኖም ሕግ በሌለበት ማንም በኃጢአት አይጠየቅም።+ 14 ይሁንና አዳም ትእዛዝ በመተላለፍ የሠራውን ዓይነት ኃጢአት ባልሠሩት ላይም እንኳ ሳይቀር ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ ድረስ ሞት በሁሉ ላይ ነገሠ፤ አዳም በኋላ ለሚመጣው አምሳያ ነበር።+
15 ሆኖም ስጦታው ያስገኘው ነገር በደሉ ካስከተለው ነገር የተለየ ነው። ምክንያቱም በአንድ ሰው በደል ብዙዎች ሞተዋል፤ ይሁንና የአምላክ ጸጋና ነፃ ስጦታው በአንዱ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ+ አማካኝነት ለብዙ ሰዎች ወደር የሌለው* ጥቅም አስገኝቷል!+ 16 በተጨማሪም ነፃ ስጦታው ያስገኘው ውጤት የአንዱ ሰው ኃጢአት+ ካመጣው ውጤት የተለየ ነው። ምክንያቱም አንድን በደል ተከትሎ የመጣው ፍርድ ኩነኔን አስከትሏል፤+ ብዙዎች በደል ከፈጸሙ በኋላ ግን አምላክ ጻድቃን እንዲባሉ የሚያስችል ስጦታ ሰጥቷል።+ 17 በአንድ ሰው በደል የተነሳ ሞት በዚህ ሰው በኩል ከነገሠ+ የአምላክን የተትረፈረፈ ጸጋና የጽድቅን ነፃ ስጦታ የሚቀበሉትማ+ በአንዱ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት+ ሕይወት አግኝተው ነገሥታት+ ሆነው እንደሚገዙ ይበልጥ የተረጋገጠ ነው!
18 ስለዚህ አንድ በደል ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲኮነኑ እንዳደረገ ሁሉ+ አንድ የጽድቅ ድርጊትም* ሁሉም ዓይነት ሰዎች ጻድቃን ናችሁ ተብለው ለሕይወት እንዲበቁ ያስችላል።+ 19 ምክንያቱም በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጢአተኞች እንደሆኑ ሁሉ+ በአንዱ ሰው መታዘዝም ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ።+ 20 ሕጉ የመጣው ሰዎች ብዙ በደል እንደሚፈጽሙ ለማሳየት ነው።+ ይሁን እንጂ ሰዎች ብዙ ኃጢአት ሲፈጽሙ አምላክ ታላቅ ጸጋ አሳያቸው። 21 ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ኃጢአት ከሞት ጋር እንደነገሠ+ ሁሉ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የዘላለም ሕይወት ይገኝ ዘንድ ጸጋ በጽድቅ አማካኝነት እንዲነግሥ ነው።+
6 እንግዲህ ምን እንበል? ጸጋ እንዲበዛ ኃጢአት መሥራታችንን እንቀጥል? 2 በፍጹም! እኛ ለኃጢአት የሞትን+ ሆነን ሳለን ከእንግዲህ እንዴት በኃጢአት ውስጥ መኖራችንን እንቀጥላለን?+ 3 ወይስ ክርስቶስ ኢየሱስ ውስጥ የተጠመቅን+ ሁላችን እሱ ሞት ውስጥ እንደተጠመቅን+ አታውቁም? 4 ስለዚህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሞት እንደተነሳ ሁሉ እኛም አዲስ ሕይወት እንድንኖር+ እሱ ሞት ውስጥ በመጠመቅ ከእሱ ጋር ተቀብረናል።+ 5 ሞቱን በሚመስል ሞት ከእሱ ጋር አንድ ከሆንን+ ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ+ ደግሞ ከእሱ ጋር አንድ እንደምንሆን ጥርጥር የለውም። 6 ምክንያቱም ኃጢአተኛው ሰውነታችን በእኛ ላይ ምንም ኃይል እንዳይኖረውና+ ከእንግዲህ የኃጢአት ባሪያዎች ሆነን እንዳንኖር+ አሮጌው ስብዕናችን ከእሱ ጋር በእንጨት ላይ እንደተቸነከረ እናውቃለን።+ 7 የሞተ ከኃጢአቱ ነፃ ወጥቷልና።*
8 በተጨማሪም ከክርስቶስ ጋር ከሞትን ከእሱ ጋር እንደምንኖር እናምናለን። 9 ክርስቶስ አሁን ከሞት እንደተነሳና+ ዳግመኛ እንደማይሞት+ እናውቃለን፤ ከእንግዲህ ሞት በእሱ ላይ እንደ ጌታ ሊሠለጥን አይችልም። 10 ምክንያቱም እሱ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለኃጢአት ሞቷል፤*+ ሆኖም አሁን እየኖረ ያለውን ሕይወት የሚኖረው ለአምላክ ነው። 11 በተመሳሳይም እናንተ ለኃጢአት እንደሞታችሁ ሆኖም በክርስቶስ ኢየሱስ ለአምላክ እንደምትኖሩ አድርጋችሁ አስቡ።+
12 በመሆኑም ኃጢአት ለሰውነታችሁ ምኞት ተገዢ እንድትሆኑ በማድረግ ሟች በሆነው ሰውነታችሁ ላይ መንገሡን እንዲቀጥል አትፍቀዱ።+ 13 በተጨማሪም ሰውነታችሁን* የክፋት መሣሪያ* አድርጋችሁ ለኃጢአት አታቅርቡ፤ ከዚህ ይልቅ ከሞት ወደ ሕይወት እንደተሻገሩ ሰዎች አድርጋችሁ ራሳችሁን ለአምላክ አቅርቡ፤ ሰውነታችሁንም* የጽድቅ መሣሪያ አድርጋችሁ ለአምላክ አቅርቡ።+ 14 ምክንያቱም በጸጋ+ ሥር እንጂ በሕግ ሥር ስላልሆናችሁ+ ኃጢአት በእናንተ ላይ ጌታ ሊሆን አይገባም።
15 እንግዲህ ከዚህ በመነሳት ምን ማለት እንችላለን? በጸጋ ሥር እንጂ በሕግ ሥር ስላልሆንን ኃጢአት እንሥራ ማለት ነው?+ በፍጹም! 16 ለማንም ቢሆን ታዛዥ ባሪያዎች ሆናችሁ ራሳችሁን ካቀረባችሁ ለዚያ ለምትታዘዙለት ባሪያዎች+ እንደሆናችሁ አታውቁም? በመሆኑም ሞት+ ለሚያስከትለው ለኃጢአት+ አለዚያም ጽድቅ ለሚያስገኘው ለታዛዥነት ባሪያዎች ናችሁ። 17 ሆኖም እናንተ በአንድ ወቅት የኃጢአት ባሪያዎች የነበራችሁ ቢሆንም እንድትከተሉት ለተሰጣችሁ ለእንዲህ ዓይነቱ ትምህርት ከልብ ስለታዘዛችሁ አምላክ የተመሰገነ ይሁን። 18 አዎ፣ ከኃጢአት ነፃ ስለወጣችሁ+ የጽድቅ ባሪያዎች ሆናችኋል።+ 19 እኔ ሰዎች በሚረዱት ቋንቋ የምናገረው በሥጋችሁ ድክመት የተነሳ ነው፤ የአካል ክፍሎቻችሁን ክፉ ድርጊት ለመፈጸም ለርኩሰትና ለክፋት ባሪያዎች አድርጋችሁ አቅርባችሁ እንደነበረ ሁሉ አሁን ደግሞ የአካል ክፍሎቻችሁን ቅዱስ ሥራ ለመሥራት የጽድቅ ባሪያዎች አድርጋችሁ አቅርቡ።+ 20 የኃጢአት ባሪያዎች በነበራችሁበት ጊዜ በጽድቅ ሥር አልነበራችሁምና።
21 ታዲያ በዚያን ጊዜ ታፈሯቸው የነበሩት ፍሬዎች ምን ዓይነት ነበሩ? አሁን የምታፍሩባቸው ነገሮች ናቸው። የእነዚህ ነገሮች መጨረሻ ሞት ነውና።+ 22 ይሁን እንጂ አሁን ከኃጢአት ነፃ ወጥታችሁ የአምላክ ባሪያዎች ስለሆናችሁ በቅድስና ጎዳና ፍሬ እያፈራችሁ ነው፤+ የዚህም መጨረሻ የዘላለም ሕይወት ነው።+ 23 የኃጢአት ደሞዝ ሞት ነውና፤*+ አምላክ የሚሰጠው ስጦታ ግን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ+ የዘላለም ሕይወት ነው።+
7 ወንድሞች፣ (እየተናገርኩ ያለሁት ሕግ ለሚያውቁ ሰዎች ነው፤) ሕጉ በአንድ ሰው ላይ ሥልጣን የሚኖረው በሕይወት እስከኖረ ድረስ ብቻ እንደሆነ አታውቁም? 2 ለምሳሌ ያህል፣ ያገባች ሴት ባሏ በሕይወት እስካለ ድረስ በሕግ ለእሱ የታሰረች ናት፤ ባሏ ከሞተ ግን ከባሏ ሕግ ነፃ ትወጣለች።+ 3 በመሆኑም ባሏ በሕይወት እያለ የሌላ ወንድ ብትሆን አመንዝራ ትባላለች።+ ባሏ ከሞተ ግን ከእሱ ሕግ ነፃ ስለምትሆን የሌላ ወንድ ብትሆን አመንዝራ አትባልም።+
4 ስለዚህ ወንድሞቼ፣ እናንተም የሌላ ይኸውም ከሞት የተነሳው+ የክርስቶስ እንድትሆኑ+ በእሱ አካል አማካኝነት ለሕጉ ሞታችኋል፤* ይህም የሆነው ለአምላክ ፍሬ እንድናፈራ ነው።+ 5 ምክንያቱም እንደ ሥጋ ፍላጎት እንኖር በነበረበት ጊዜ ሕጉ ይፋ ያወጣቸው የኃጢአት ምኞቶች ለሞት ፍሬ እንድናፈራ በሰውነታችን* ውስጥ ይሠሩ ነበር።+ 6 አሁን ግን አሮጌ በሆነው በተጻፈው ሕግ+ ሳይሆን በአዲስ መልክ በመንፈስ ባሪያዎች+ እንሆን ዘንድ አስሮ ይዞን ለነበረው ሕግ ስለሞትን ከሕጉ ነፃ ወጥተናል።+
7 እንግዲህ ምን እንበል? ሕጉ ጉድለት አለበት ማለት ነው?* በፍጹም! እንደ እውነቱ ከሆነ ሕጉ ባይኖር ኖሮ ኃጢአት ምን እንደሆነ ባላወቅኩ ነበር።+ ለምሳሌ ሕጉ “አትጎምጅ”+ ባይል ኖሮ መጎምጀት ምን እንደሆነ ባላወቅኩ ነበር። 8 ሆኖም ኃጢአት፣ ይህ ትእዛዝ ባስገኘው አጋጣሚ ተጠቅሞ ማንኛውንም ዓይነት ነገር የመጎምጀት ፍላጎት በውስጤ እንዲያድር አደረገ፤ ሕግ ባልነበረበት ጊዜ ኃጢአት የሞተ ነበርና።+ 9 በእርግጥ ሕግ ባልነበረበት ጊዜ ሕያው ነበርኩ። ትእዛዙ ሲመጣ ግን ኃጢአት ዳግመኛ ሕያው ሆነ፤ እኔ ግን ሞትኩ።+ 10 ወደ ሕይወት እንዲመራ የታሰበውም ትእዛዝ+ ሞት እንዳመጣ ተገነዘብኩ። 11 ምክንያቱም ኃጢአት ትእዛዙ ባስገኘው አጋጣሚ ተጠቅሞ አታሎኛል፤ እንዲሁም በትእዛዙ አማካኝነት ገድሎኛል። 12 ስለዚህ ሕጉ በራሱ ቅዱስ ነው፤ ትእዛዙም ቅዱስ፣ ጻድቅና ጥሩ ነው።+
13 ታዲያ ይህ ጥሩ የሆነው ነገር* ሞት አመጣብኝ ማለት ነው? በፍጹም! ከዚህ ይልቅ የገደለኝ ኃጢአት ነው። የኃጢአት ምንነት እንዲገለጥ ጥሩ በሆነው ነገር አማካኝነት ሞት ያመጣብኝ ኃጢአት ነው።+ ትእዛዙም ኃጢአት ምን ያህል ክፉ እንደሆነ አሳይቷል።+ 14 ሕጉ መንፈሳዊ* እንደሆነ እናውቃለንና፤ እኔ ግን ለኃጢአት የተሸጥኩ ሥጋዊ ነኝ።+ 15 ለምን እንዲህ እንደማደርግ አላውቅም። ለማድረግ የምፈልገውን ነገር አላደርግምና፤ ከዚህ ይልቅ የማደርገው የምጠላውን ነገር ነው። 16 ይሁን እንጂ የማደርገው የማልፈልገውን ከሆነ ሕጉ መልካም ነው በሚለው እስማማለሁ። 17 ሆኖም አሁን ይህን የሚያደርገው በእኔ ውስጥ የሚኖረው ኃጢአት ነው+ እንጂ እኔ አይደለሁም። 18 ምክንያቱም በውስጤ ማለትም በሥጋዬ ውስጥ የሚኖር ምንም ጥሩ ነገር የለም፤ መልካም የሆነውን ነገር የማድረግ ፍላጎት እንጂ የመፈጸም ችሎታ የለኝም።+ 19 የምመኘውን መልካም ነገር አላደርግምና፤ የማልፈልገውን መጥፎ ነገር ግን አደርጋለሁ። 20 እንግዲህ የማደርገው የማልፈልገውን ነገር ከሆነ ይህን የማደርገው እኔ ሳልሆን በውስጤ የሚኖረው ኃጢአት ነው።
21 እንግዲያው ይህ ሕግ በራሴ ላይ ሲሠራ አያለሁ፦ ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ስፈልግ ከእኔ ጋር ያለው ግን መጥፎ ነገር ነው።+ 22 በውስጤ በአምላክ ሕግ እጅግ ደስ ይለኛል፤+ 23 በሰውነቴ* ውስጥ ግን ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋውንና+ በሰውነቴ* ውስጥ ላለው የኃጢአት ሕግ ምርኮኛ አድርጎ የሚሰጠኝን+ ሌላ ሕግ አያለሁ። 24 እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ! እንዲህ ወዳለው ሞት ከሚመራኝ ሰውነት ማን ይታደገኛል? 25 በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የሚታደገኝ አምላክ የተመሰገነ ይሁን! ስለዚህ እኔ ራሴ በአእምሮዬ ለአምላክ ሕግ ባሪያ ስሆን በሥጋዬ ግን ለኃጢአት ሕግ ባሪያ ነኝ።+
8 ስለዚህ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድነት ያላቸው ኩነኔ የለባቸውም። 2 ምክንያቱም ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድነት ላላቸው ሰዎች ሕይወት የሚያስገኘው መንፈስ ሕግ፣ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ ነፃ አውጥቷችኋል።+ 3 ሕጉ ከሰብዓዊ አለፍጽምና የተነሳ ደካማ በመሆኑ+ ሊፈጽመው ያልቻለውን+ ነገር አምላክ ኃጢአትን ለማስወገድ የገዛ ራሱን ልጅ ኃጢአተኛ በሆኑ ሰዎች አምሳል+ በመላክ+ ፈጽሞታል። እንዲህ በማድረግም የሥጋን ኃጢአት ኮንኗል፤ 4 ይህም የሆነው የሕጉ የጽድቅ መሥፈርት እንደ ሥጋ ፈቃድ ሳይሆን እንደ መንፈስ ፈቃድ+ በምንመላለሰው በእኛ እንዲፈጸም ነው።+ 5 እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ አእምሯቸው በሥጋዊ ነገሮች ላይ ያተኮረ ነው፤+ እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን አእምሯቸው በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ያተኮረ ነው።+ 6 በሥጋዊ ነገሮች ላይ ማተኮር ሞት ያስከትላልና፤+ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማተኮር ግን ሕይወትና ሰላም ያስገኛል፤+ 7 ሥጋ ለአምላክ ሕግ ስለማይገዛና ደግሞም ሊገዛ ስለማይችል በሥጋዊ ነገሮች ላይ ማተኮር የአምላክ ጠላት ያደርጋል።+ 8 ስለሆነም እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚመላለሱ አምላክን ማስደሰት አይችሉም።
9 ይሁን እንጂ የአምላክ መንፈስ በእርግጥ በውስጣችሁ የሚኖር ከሆነ ከሥጋ ጋር ሳይሆን ከመንፈስ+ ጋር ስምም ናችሁ። ሆኖም አንድ ሰው የክርስቶስ መንፈስ ከሌለው ይህ ሰው የክርስቶስ አይደለም። 10 ይሁንና ክርስቶስ ከእናንተ ጋር አንድነት ካለው፣+ ሰውነታችሁ በኃጢአት ምክንያት የሞተ ቢሆንም እንኳ መንፈስ ከጽድቅ የተነሳ ሕይወት ያስገኛል። 11 እንግዲህ ኢየሱስን ከሞት ያስነሳው የአምላክ መንፈስ በእናንተ ውስጥ የሚኖር ከሆነ ክርስቶስ ኢየሱስን ከሞት ያስነሳው+ እሱ በእናንተ ውስጥ በሚኖረው መንፈሱ አማካኝነት ሟች ሰውነታችሁንም ሕያው ያደርገዋል።+
12 ስለዚህ ወንድሞች ግዴታ አለብን፤ ይሁንና ግዴታችን እንደ ሥጋ ፈቃድ መኖር አይደለም፤+ 13 እንደ ሥጋ ፈቃድ የምትኖሩ ከሆነ መሞታችሁ የማይቀር ነውና፤ ይሁን እንጂ ሰውነታችሁ የሚፈጽመውን ሥራ በመንፈስ ብትገድሉ+ በሕይወት ትኖራላችሁ።+ 14 በአምላክ መንፈስ የሚመሩ ሁሉ በእርግጥ የአምላክ ልጆች ናቸውና።+ 15 ዳግመኛ ለፍርሃት የሚዳርጋችሁን የባርነት መንፈስ አልተቀበላችሁም፤ ከዚህ ይልቅ አምላክ ልጆቹ አድርጎ እንዲወስዳችሁ የሚያስችል መንፈስ አግኝታችኋል፤ ይህም መንፈስ “አባ፣* አባት!”+ ብለን እንድንጣራ ይገፋፋናል። 16 የአምላክ ልጆች+ መሆናችንን ይህ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ሆኖ ይመሠክራል።+ 17 እንግዲህ ልጆች ከሆን ወራሾች ነን፤ ይኸውም ከአምላክ ውርሻ እንቀበላለን፤ ይሁንና የምንወርሰው ከክርስቶስ ጋር ነው፤+ አሁን አብረነው መከራ ከተቀበልን፣+ በኋላ ደግሞ አብረነው ክብር እንጎናጸፋለን።+
18 በአሁኑ ጊዜ የሚደርስብን መከራ በእኛ ላይ ከሚገለጠው ክብር ጋር ሲነጻጸር ከምንም ሊቆጠር እንደማይችል አምናለሁ።+ 19 ፍጥረት የአምላክን ልጆች መገለጥ በከፍተኛ ጉጉት እየተጠባበቀ ነው።+ 20 ፍጥረት ለከንቱነት ተገዝቷልና፤+ የተገዛው ግን በገዛ ፈቃዱ ሳይሆን በተስፋ እንዲገዛ ባደረገው በእሱ አማካኝነት ነው፤ 21 ተስፋውም ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከመበስበስ ባርነት ነፃ ወጥቶ+ የአምላክ ልጆች የሚያገኙት ዓይነት ክብራማ ነፃነት ማግኘት ነው። 22 ፍጥረት ሁሉ እስካሁን ድረስ አብሮ በመቃተትና በመሠቃየት ላይ እንደሚገኝ እናውቃለን። 23 ይህም ብቻ ሳይሆን የውርሻችንን በኩራት ይኸውም መንፈስን ያገኘን እኛ ራሳችንም በቤዛው አማካኝነት ከሥጋዊ አካላችን ነፃ በመውጣት አምላክ ልጆቹ አድርጎ እንዲወስደን+ በጉጉት እየተጠባበቅን በውስጣችን እንቃትታለን።+ 24 በዚህ ተስፋ ድነናል፤ ነገር ግን ተስፋ የሚደረገው ነገር የሚታይ ከሆነ ተስፋ መሆኑ ይቀራል፤ ደግሞስ አንድ ሰው የሚያየውን ነገር ተስፋ ያደርጋል? 25 የማናየውን ነገር+ ተስፋ የምናደርግ ከሆነ+ ግን ጸንተን በጉጉት እንጠባበቀዋለን።+
26 በተመሳሳይም መንፈስ በድካማችን ይረዳናል።+ ምን ብለን መጸለይ እንዳለብን ግራ የምንጋባበት ጊዜ ሊኖር ይችላል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥመንና ስሜታችንን በቃላት መግለጽ ተስኖን ስንቃትት መንፈስ ራሱ ስለ እኛ ይማልዳል። 27 ይሁንና ልብን የሚመረምረው+ አምላክ የመንፈስን ዓላማ ያውቃል፤ ምክንያቱም መንፈስ ለቅዱሳን የሚማልደው ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ ነው።
28 አምላክ ለሚወዱት ይኸውም ከእሱ ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ ለተጠሩት ሥራውን ሁሉ አቀናጅቶ ለበጎ እንዲሆንላቸው እንደሚያደርግ እናውቃለን፤+ 29 ምክንያቱም መጀመሪያ እውቅና የሰጣቸው ሰዎች የልጁን መልክ እንዲመስሉ+ አስቀድሞ ወስኗል፤ ይኸውም ልጁ ከብዙ ወንድሞች+ መካከል በኩር+ እንዲሆን ነው። 30 ከዚህም በተጨማሪ አስቀድሞ የወሰናቸውን+ እነዚህን ጠራቸው፤+ የጠራቸውን እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው።+ በመጨረሻም ያጸደቃቸውን እነዚህን አከበራቸው።+
31 እንግዲህ ስለ እነዚህ ነገሮች ምን እንበል? አምላክ ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ሊቃወመን ይችላል?+ 32 ለገዛ ልጁ እንኳ ያልሳሳው፣ ከዚህ ይልቅ ለእኛ ለሁላችን አሳልፎ የሰጠው+ አምላክ፣ ከእሱ ጋር አብሮ ሌሎች ነገሮችን ሁሉ እንዴት በደግነት አይሰጠንም? 33 አምላክ የመረጣቸውን ማን ሊከሳቸው ይችላል?+ ምክንያቱም የሚያጸድቃቸው አምላክ ራሱ ነው።+ 34 እነሱን የሚኮንን ማን ነው? ምክንያቱም የሞተው ብሎም ከሞት የተነሳውና በአምላክ ቀኝ የተቀመጠው+ እንዲሁም ስለ እኛ የሚማልደው+ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው።
35 ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል?+ መከራ ወይስ ጭንቀት ወይስ ስደት ወይስ ረሃብ ወይስ ራቁትነት ወይስ አደጋ ወይስ ሰይፍ?+ 36 ይህም “ስለ አንተ ቀኑን ሙሉ ሞትን እንጋፈጣለን፤ እንደ እርድ በጎችም ተቆጠርን”+ ተብሎ እንደተጻፈው ነው። 37 ከዚህ ይልቅ በወደደን በእሱ አማካኝነት እነዚህን ነገሮች ሁሉ ሙሉ በሙሉ በድል አድራጊነት እንወጣለን።+ 38 ምክንያቱም ሞትም ቢሆን፣ ሕይወትም ቢሆን፣ መላእክትም ቢሆኑ፣ መንግሥታትም ቢሆኑ፣ አሁን ያሉት ነገሮችም ቢሆኑ፣ ወደፊት የሚመጡት ነገሮችም ቢሆኑ፣ ማንኛውም ኃይል+ ቢሆን፣ 39 ከፍታም ቢሆን፣ ዝቅታም ቢሆን፣ ሌላ ማንኛውም ፍጥረት ቢሆን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ከተገለጸው የአምላክ ፍቅር ሊለየን እንደማይችል ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነኝ።
9 የክርስቶስ ተከታይ እንደመሆኔ መጠን የምናገረው እውነት ነው፤ ሕሊናዬ በመንፈስ ቅዱስ እየተመራ ከእኔ ጋር ሆኖ ስለሚመሠክር አልዋሽም፤ 2 ታላቅ ሐዘንና የማያቋርጥ ሥቃይ በልቤ ውስጥ አለ። 3 የሥጋ ዘመዶቼ ስለሆኑት ስለ ወንድሞቼ ስል እኔ ራሴ የተረገምኩ ሆኜ ከክርስቶስ ብለይ በወደድኩ ነበርና። 4 እነሱ እስራኤላውያን ናቸው፤ አምላክ ልጆቹ አድርጎ የወሰዳቸው፣+ ክብር ያገኙት፣ ቃል ኪዳን የተገባላቸው፣+ ሕግ የተሰጣቸው፣+ ቅዱስ አገልግሎት የማቅረብ መብት ያገኙትና+ ተስፋ የተሰጣቸው+ እነሱ ናቸው። 5 አባቶችም የእነሱ ናቸው፤+ ክርስቶስም በሥጋ የተገኘው ከእነሱ ነው።+ የሁሉ የበላይ የሆነው አምላክ ለዘላለም ይወደስ። አሜን።
6 ይሁን እንጂ የአምላክ ቃል ከንቱ ሆኖ ቀርቷል ማለት አይደለም። ከእስራኤል የተወለደ ሁሉ በእርግጥ “እስራኤል” አይደለምና።+ 7 በተጨማሪም የአብርሃም ዘር ስለሆኑ+ ሁሉም ልጆቹ ናቸው ማለት አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ “ዘርህ የሚጠራልህ በይስሐቅ በኩል ይሆናል” ተብሎ ተጽፏል።+ 8 ይህም ሲባል በሥጋ ልጆች የሆኑ በእርግጥ የአምላክ ልጆች አይደሉም፤+ በተስፋው ልጆች+ የሆኑት ግን ዘሩ እንደሆኑ ተደርገው ይቆጠራሉ። 9 የተስፋው ቃል “የዛሬ ዓመት በዚህ ጊዜ እመጣለሁ፤ ሣራም ወንድ ልጅ ትወልዳለች” ይላልና።+ 10 ተስፋው የተሰጠው በዚያን ጊዜ ብቻ ሳይሆን ርብቃ ከአባታችን ከይስሐቅ መንታ ልጆች በፀነሰች ጊዜ ጭምር ነው፤+ 11 ምርጫውን በተመለከተ የአምላክ ዓላማ በሥራ ሳይሆን በጠሪው ላይ የተመካ ሆኖ ይቀጥል ዘንድ ልጆቹ ከመወለዳቸውና ጥሩም ሆነ ክፉ ከማድረጋቸው በፊት 12 ርብቃ “ታላቁ የታናሹ ባሪያ ይሆናል” ተብሎ ተነግሯት ነበር።+ 13 ይህም “ያዕቆብን ወደድኩ፤ ኤሳውን ግን ጠላሁ” ተብሎ እንደተጻፈው ነው።+
14 እንግዲህ ምን እንበል? አምላክ ፍትሕ ያዛባል ማለት ነው? በፍጹም!+ 15 ሙሴን “ልምረው የምፈልገውን እምረዋለሁ፤ ልራራለት የምፈልገውን ደግሞ እራራለታለሁ” ብሎታልና።+ 16 ስለዚህ ይህ የተመካው በአንድ ሰው ፍላጎት ወይም ጥረት* ሳይሆን ምሕረት በሚያደርገው አምላክ ላይ ነው።+ 17 ቅዱስ መጽሐፉ ስለ ፈርዖን ሲናገር “በሕይወት ያቆየሁህ ኃይሌን በአንተ ለማሳየትና ስሜ በመላው ምድር እንዲታወጅ ለማድረግ ነው” ይላል።+ 18 ስለዚህ አምላክ የፈለገውን ይምራል፤ የፈለገውን ደግሞ ግትር እንዲሆን ይፈቅዳል።+
19 በመሆኑም “እንደዚህ ከሆነ ታዲያ ሰዎችን ለምን ይወቅሳል?* ደግሞስ ፈቃዱን ማን መቃወም ይችላል?” ትለኝ ይሆናል። 20 ለመሆኑ ለአምላክ የምትመልሰው አንተ ማን ነህ?+ አንድ ዕቃ ቅርጽ አውጥቶ የሠራውን ሰው “ለምን እንዲህ አድርገህ ሠራኸኝ?” ይለዋል?+ 21 ሸክላ ሠሪው ከዚያው ከአንዱ ጭቃ፣ አንዱን ዕቃ ክቡር ለሆነ አገልግሎት ሌላውን ዕቃ ደግሞ ክብር ለሌለው አገልግሎት ለመሥራት በጭቃው ላይ ሥልጣን እንዳለው+ አታውቅም? 22 አምላክ ቁጣውን ለማሳየትና ኃይሉ እንዲታወቅ ለማድረግ ቢፈልግም እንኳ ጥፋት የሚገባቸውን የቁጣ ዕቃዎች በብዙ ትዕግሥት ችሏቸው እንደሆነስ ምን ታውቃለህ? 23 ይህን ያደረገው ታላቅ ክብሩን አስቀድሞ ለክብር ባዘጋጃቸው የምሕረት ዕቃዎች+ ላይ ለመግለጥ 24 ይኸውም ከአይሁዳውያን ብቻ ሳይሆን ከአሕዛብም+ በጠራን በእኛ ላይ ታላቅ ክብሩን ለመግለጥ ቢሆንስ? 25 ይህም በሆሴዕ መጽሐፍ ላይ እንዲህ ብሎ እንደተናገረው ነው፦ “ሕዝቤ ያልሆኑትን+ ‘ሕዝቤ’ ብዬ፣ ያልተወደደችውንም ‘የተወደደች’+ ብዬ እጠራለሁ፤ 26 ‘ሕዝቤ አይደላችሁም’ ተብሎ በተነገራቸው ስፍራም በዚያ ‘የሕያው አምላክ ልጆች’ ተብለው ይጠራሉ።”+
27 ከዚህም በተጨማሪ ኢሳይያስ ስለ እስራኤል እንዲህ ሲል ድምፁን ከፍ አድርጎ ይናገራል፦ “የእስራኤል ልጆች ቁጥር እንደ ባሕር አሸዋ ቢሆንም እንኳ የሚድኑት ቀሪዎች ብቻ ናቸው።+ 28 ይሖዋ* በምድር የሚኖሩትን ይፋረዳልና፤ ይህን ደግሞ ሳይዘገይ* ይፈጽመዋል።”+ 29 ደግሞም ኢሳይያስ አስቀድሞ እንደተናገረው “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ* ዘር ባያስቀርልን ኖሮ እንደ ሰዶም በሆን፣ ገሞራንም በመሰልን ነበር።”+
30 እንግዲህ ምን እንበል? አሕዛብ ጽድቅን ባይከታተሉም እንኳ ጽድቅን ይኸውም በእምነት አማካኝነት የሚገኘውን ጽድቅ አገኙ፤+ 31 ሆኖም እስራኤል የጽድቅን ሕግ ቢከታተልም ግቡ ላይ አልደረሰም፤ ይኸውም ሕጉን አልፈጸመም። 32 ይህ የሆነው ለምንድን ነው? በእምነት ሳይሆን በሥራ የሚገኝ እንደሆነ አድርገው ስለተከታተሉት ነው። ስለዚህ “በማሰናከያ ድንጋይ” ተሰናከሉ፤+ 33 ይህም “እነሆ፣ በጽዮን የሚያደናቅፍ ድንጋይና የሚያሰናክል ዓለት አኖራለሁ፤+ በእሱ ላይ እምነት የሚጥል ግን አያፍርም”+ ተብሎ እንደተጻፈው ነው።
10 ወንድሞች፣ ለእስራኤላውያን ከልቤ የምመኘውና ስለ እነሱ ለአምላክ ምልጃ የማቀርበው እንዲድኑ ነው።+ 2 ለአምላክ ቅንዓት እንዳላቸው እመሠክርላቸዋለሁና፤+ ሆኖም ቅንዓታቸው በትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ አይደለም። 3 የአምላክን ጽድቅ ሳያውቁ+ የራሳቸውን ጽድቅ ለመመሥረት+ ስለፈለጉ ራሳቸውን ለአምላክ ጽድቅ አላስገዙም።+ 4 የሚያምን* ሁሉ መጽደቅ ይችል ዘንድ+ ክርስቶስ የሕግ ፍጻሜ ነውና።+
5 ሙሴ በሕጉ አማካኝነት ስለሚገኘው ጽድቅ ሲገልጽ “እነዚህን ነገሮች የሚያደርግ ሰው በእነሱ አማካኝነት በሕይወት ይኖራል” ሲል ጽፏል።+ 6 ሆኖም በእምነት የሚገኘውን ጽድቅ በተመለከተ እንዲህ ተብሏል፦ “በልብህ+ ‘ወደ ሰማይ ማን ይወጣል?’ አትበል፤+ ይህም ክርስቶስን ለማውረድ ነው፤ 7 ወይም ‘ወደ ጥልቁ ማን ይወርዳል?’ አትበል፤+ ይህም ክርስቶስን ከሞት ለማስነሳት ነው።” 8 ይሁንና ቅዱስ መጽሐፉ ምን ይላል? “ቃሉ ለአንተ ቅርብ ነው፤ ደግሞም በአፍህና በልብህ ውስጥ ነው”፤+ ይህም እኛ የምንሰብከው የእምነት “ቃል” ነው። 9 ኢየሱስ ጌታ እንደሆነ በአፍህ በይፋ ብትናገር+ እንዲሁም አምላክ ከሞት እንዳስነሳው በልብህ ብታምን ትድናለህና። 10 ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና፤ በአፉ ደግሞ እምነቱን በይፋ ተናግሮ ይድናል።+
11 ቅዱስ መጽሐፉ “በእሱ ላይ እምነት የሚጥል ሁሉ አያፍርም” ይላል።+ 12 በአይሁዳዊና በግሪካዊ መካከል ምንም ልዩነት የለምና።+ የሁሉም ጌታ አንድ ነው፤ እሱም የሚለምኑትን ሁሉ አብዝቶ ይባርካል።* 13 “የይሖዋን* ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና።”+ 14 ይሁንና ካላመኑበት እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ስለ እሱ ሳይሰሙስ እንዴት ያምኑበታል? ደግሞስ የሚሰብክላቸው ሳይኖር እንዴት ይሰማሉ? 15 ካልተላኩስ እንዴት ይሰብካሉ?+ ይህም “የተሻለ ነገር እንደሚመጣ ምሥራች የሚናገሩ ሰዎች እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው!”+ ተብሎ እንደተጻፈው ነው።
16 ሆኖም ምሥራቹን የታዘዙት ሁሉም አይደሉም። ኢሳይያስ “ይሖዋ* ሆይ፣ ከእኛ የሰማውን* ነገር ያመነ ማን ነው?” ብሏልና።+ 17 ስለዚህ እምነት የሚገኘው ቃሉን ከመስማት ነው።+ ቃሉን መስማት የሚቻለው ደግሞ ስለ ክርስቶስ የሚናገር ሰው ሲኖር ነው። 18 ይሁንና ‘ሳይሰሙ ቀርተው ይሆን?’ ብዬ እጠይቃለሁ። በእርግጥ ሰምተዋል፤ “ጩኸታቸው ወደ መላው ምድር ወጣ፤ መልእክታቸውም እስከ ዓለም ዳርቻዎች ተሰማ” ተብሏልና።+ 19 ይሁንና ‘እስራኤላውያን ሳያውቁ ቀርተው ይሆን?’ ብዬ እጠይቃለሁ።+ ሙሴ አስቀድሞ “እናንተን፣ ሕዝብ ባልሆኑት አስቀናችኋለሁ፤ ሞኝ በሆነ ብሔር አማካኝነትም ክፉኛ አስቆጣችኋለሁ” ብሏል።+ 20 ኢሳይያስም በድፍረት “ያልፈለጉኝ ሰዎች አገኙኝ፤+ እኔን ለማግኘት ባልጠየቁ ሰዎችም ዘንድ የታወቅኩ ሆንኩ” ብሏል።+ 21 እስራኤልን በተመለከተ ግን “ወደማይታዘዝና ልበ ደንዳና ወደሆነ ሕዝብ ቀኑን ሙሉ እጆቼን ዘረጋሁ” ብሏል።+
11 እንግዲያው ‘አምላክ ሕዝቡን ትቷል ማለት ነው?’ ብዬ እጠይቃለሁ፤+ በፍጹም! ምክንያቱም እኔም ራሴ እስራኤላዊ ነኝ፤ ከአብርሃም ዘር፣ ከቢንያም ነገድ ነኝ። 2 አምላክ መጀመሪያ እውቅና የሰጣቸውን ሰዎች አልተዋቸውም።+ ቅዱስ መጽሐፉ ኤልያስ እስራኤልን በአምላክ ፊት በከሰሰበት ጊዜ የሆነውን ነገር በተመለከተ ምን እንደሚል አታውቁም? 3 “ይሖዋ* ሆይ፣ ነቢያትህን ገድለዋል፤ መሠዊያዎችህንም አፍርሰዋል፤ እኔ ብቻ ቀረሁ፤ አሁንም ሕይወቴን* ለማጥፋት ጥረት እያደረጉ ነው።”+ 4 ይሁንና አምላክ የሰጠው መልስ ምን ነበር? “ለባአል ያልተንበረከኩ 7,000 ሰዎች አሉኝ።”+ 5 ስለዚህ በዚህ መንገድ በጸጋ የተመረጡ ቀሪዎች+ በአሁኑ ዘመንም አሉ። 6 የተመረጡት በጸጋ+ ከሆነ በሥራ መሆኑ ቀርቷል፤+ አለዚያ ጸጋው ጸጋ መሆኑ በቀረ ነበር።
7 እንግዲህ ምን ማለት እንችላለን? እስራኤል አጥብቆ ይፈልገው የነበረውን ነገር አላገኘም፤ የተመረጡት ግን አገኙት።+ የቀሩት የማስተዋል ስሜታቸው ደነዘዘ፤+ 8 ይህም “አምላክ እስከ ዛሬ ኃይለኛ የእንቅልፍ መንፈስ ጣለባቸው፤+ የማያይ ዓይንና የማይሰማ ጆሮ ሰጣቸው” ተብሎ እንደተጻፈው ነው።+ 9 በተጨማሪም ዳዊት እንዲህ ብሏል፦ “ማዕዳቸው ወጥመድና አሽክላ እንዲሁም እንቅፋትና ቅጣት ይሁንባቸው። 10 ዓይኖቻቸው ማየት እንዳይችሉ ይጨልሙ፤ ጀርባቸውም ጎብጦ እንዲቀር አድርግ።”+
11 በመሆኑም ‘የተሰናከሉት ወድቀው እንዲቀሩ ነው?’ ብዬ እጠይቃለሁ፤ በፍጹም! ከዚህ ይልቅ እነሱ ሕጉን በመተላለፋቸው ለአሕዛብ የመዳን መንገድ ተከፈተ፤ ይህም የሆነው እነሱን ለማስቀናት ነው።+ 12 እነሱ ሕጉን መተላለፋቸው ለዓለም በረከት ከሆነና የእነሱ ማነስ ለአሕዛብ በረከት ካስገኘ+ ቁጥራቸው መሙላቱማ ምን ያህል ታላቅ በረከት ያስገኝ ይሆን!
13 አሁን ደግሞ የምናገረው ከአሕዛብ ወገን ለሆናችሁት ነው። ለአሕዛብ የተላክሁ ሐዋርያ+ እንደመሆኔ መጠን አገልግሎቴን አከብራለሁ፤*+ 14 ይህን የማደርገው የገዛ ወገኖቼ* የሆኑትን በማስቀናት ከእነሱ መካከል አንዳንዶቹን ማዳን እችል እንደሆነ ብዬ ነው። 15 የእነሱ መጣል+ ለዓለም እርቅ ካስገኘ፣ ተቀባይነት ማግኘታቸውማ ከሞት ወደ ሕይወት መሻገር ማለት አይሆንም? 16 በተጨማሪም በኩራት ተደርጎ የተወሰደው የሊጡ ክፍል ቅዱስ ከሆነ ሊጡ በሙሉ ቅዱስ ነው፤ እንዲሁም ሥሩ ቅዱስ ከሆነ ቅርንጫፎቹም ቅዱሳን ናቸው።
17 ይሁን እንጂ ከቅርንጫፎቹ መካከል አንዳንዶቹ ቢሰበሩና አንተ የዱር ወይራ ሆነህ ሳለህ በእነሱ መካከል ከተጣበቅክ እንዲሁም ከወይራው ዛፍ ሥር ከሚገኘው በረከት ተካፋይ ከሆንክ 18 በተሰበሩት ቅርንጫፎች ላይ አትታበይ።* በእነሱ ላይ የምትታበይ+ ከሆነ ግን አንተን የተሸከመህ ሥሩ ነው እንጂ አንተ ሥሩን እንዳልተሸከምከው አስታውስ። 19 ይሁንና “ቅርንጫፎቹ የተሰበሩት እኔ በቦታቸው እንድጣበቅ ነው”+ ብለህ ታስብ ይሆናል። 20 እውነት ነው! እነሱ ባለማመናቸው ተሰብረዋል፤+ አንተ ግን በእምነት ቆመሃል።+ ቢሆንም መፍራት እንጂ መታበይ አይገባህም። 21 አምላክ በተፈጥሮ ቅርንጫፎች ለሆኑት ካልራራ ለአንተም አይራራምና። 22 ስለዚህ አምላክ ደግም+ ጥብቅም እንደሆነ ተመልከት። በወደቁት ላይ ጥብቅ ይሆናል፤+ አንተ ግን የአምላክ ደግነት የሚገባህ ሆነህ እስከተገኘህ ድረስ ደግነቱን ያሳይሃል፤ አለዚያ ግን አንተም ተቆርጠህ ትጣላለህ። 23 እነሱም እምነት የለሽ ሆነው ካልቀጠሉ ይጣበቃሉ፤ አምላክ መልሶ ሊያጣብቃቸው+ ይችላልና። 24 አንተ በተፈጥሮ የዱር ከሆነው የወይራ ዛፍ ተቆርጠህ፣ ከተፈጥሮ ውጭ በሆነ መንገድ በጓሮ የወይራ ዛፍ ላይ መጣበቅ ከቻልክ እነዚህ ተፈጥሯዊ የሆኑት ቅርንጫፎችማ በራሳቸው የወይራ ዛፍ ላይ ተመልሰው መጣበቅ እንደሚችሉ የታወቀ ነው!
25 ወንድሞች፣ በራሳችሁ ዓይን ጥበበኞች የሆናችሁ እንዳይመስላችሁ ይህን ቅዱስ ሚስጥር እንድታውቁ እፈልጋለሁ፦+ የአሕዛብ ቁጥር እስኪሞላ ድረስ የእስራኤል ሕዝብ በከፊል ስሜቱ ደንዝዟል፤ 26 በዚህም መንገድ እስራኤል ሁሉ+ ይድናል። ይህም እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈው ነው፦ “አዳኝ* ከጽዮን ይወጣል፤+ የያዕቆብም ዘሮች የክፋት ድርጊታቸውን እንዲተዉ ያደርጋል። 27 ኃጢአታቸውንም በማስወግድበት ጊዜ+ ከእነሱ ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነው።”+ 28 እርግጥ ከምሥራቹ ጋር በተያያዘ ለእናንተ ጥቅም ሲባል የአምላክ ጠላቶች ናቸው፤ በአምላክ ምርጫ መሠረት ግን ለአባቶቻቸው በተገባው የተስፋ ቃል የተነሳ በአምላክ ዘንድ የተወደዱ ናቸው።+ 29 አምላክ በስጦታውና በጠራቸው ሰዎች አይጸጸትምና። 30 በአንድ ወቅት እናንተ አምላክን የማትታዘዙ ነበራችሁ፤+ አሁን ግን በእነሱ አለመታዘዝ+ ምክንያት ምሕረት አግኝታችኋል።+ 31 ስለዚህ አይሁዳውያን ሳይታዘዙ በመቅረታቸው አምላክ ለእናንተ ምሕረት አሳይቷችኋል፤ ከዚህም የተነሳ ለእነሱም ምሕረት ሊያሳያቸው ይችላል። 32 አምላክ ለሁሉም ምሕረት ያሳይ ዘንድ+ ሁሉም ያለመታዘዝ እስረኞች+ እንዲሆኑ ፈቅዷልና።
33 የአምላክ ብልጽግና፣ ጥበብና እውቀት እንዴት ጥልቅ ነው! ፍርዱም ፈጽሞ የማይመረመር ነው! መንገዱም የማይደረስበት ነው! 34 እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፦ “የይሖዋን* ሐሳብ ማወቅ የቻለ ማን ነው? አማካሪውስ የሆነ ማን ነው?”+ 35 ወይስ “መልሶ ይከፍለው ዘንድ ለእሱ ያበደረ ማን ነው?”+ 36 ምክንያቱም ሁሉም ነገር የተገኘው ከእሱ፣ በእሱና ለእሱ ነው። ለእሱ ለዘላለም ክብር ይሁን። አሜን።
12 እንግዲህ ወንድሞች፣ ሰውነታችሁን ሕያው፣ ቅዱስና+ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት አድርጋችሁ እንድታቀርቡ+ በአምላክ ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፤ ይህም የማሰብ ችሎታችሁን ተጠቅማችሁ የምታቀርቡት ቅዱስ አገልግሎት ነው።+ 2 በተጨማሪም ይህ ሥርዓት* እንዲቀርጻችሁ አትፍቀዱ፤ ከዚህ ይልቅ ጥሩ የሆነውን፣ ተቀባይነት ያለውንና ፍጹም የሆነውን የአምላክ ፈቃድ መርምራችሁ ማረጋገጥ ትችሉ ዘንድ+ አእምሯችሁን በማደስ ተለወጡ።+
3 እያንዳንዱ ሰው ከሚገባው በላይ ስለ ራሱ በማሰብ ራሱን ከፍ አድርጎ አይመልከት፤+ ከዚህ ይልቅ አምላክ ለእያንዳንዱ በሰጠው* እምነት መሠረት ጤናማ አስተሳሰብ እንዳለው በሚያሳይ መንገድ እንዲያስብ፣ በመካከላችሁ ያለውን እያንዳንዱን ሰው በተሰጠኝ ጸጋ እመክራለሁ።+ 4 በአንድ አካል ላይ ብዙ የአካል ክፍሎች አሉን፤+ ደግሞም ሁሉም የአካል ክፍሎች አንድ ዓይነት ተግባር አያከናውኑም፤ 5 ልክ እንደዚሁ እኛም ብዙ ብንሆንም እንኳ ከክርስቶስ ጋር ባለን አንድነት አንድ አካል ነን፤ ደግሞም አንዳችን የሌላው የአካል ክፍል ነን።+ 6 በመሆኑም በተሰጠን ጸጋ መሠረት+ የተለያዩ ስጦታዎች ስላሉን ስጦታችን ትንቢት መናገር ከሆነ በተሰጠን እምነት መሠረት ትንቢት እንናገር፤ 7 ማገልገል ከሆነ ማገልገላችንን እንቀጥል፤ የሚያስተምርም ቢሆን ማስተማሩን ይቀጥል፤+ 8 የሚያበረታታም* ቢሆን ማበረታቻ መስጠቱን ይቀጥል፤+ የሚሰጥ* በልግስና ይስጥ፤+ የሚያስተዳድር* በትጋት ያስተዳድር፤+ የሚምር በደስታ ይማር።+
9 ፍቅራችሁ ግብዝነት የሌለበት ይሁን።+ ክፉ የሆነውን ተጸየፉ፤+ ጥሩ የሆነውን አጥብቃችሁ ያዙ። 10 በወንድማማች ፍቅር እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ። አንዳችሁ ሌላውን ለማክበር ቀዳሚ ሁኑ።*+ 11 ታታሪዎች* ሁኑ እንጂ አትስነፉ።*+ በመንፈስ የምትቃጠሉ ሁኑ።+ ይሖዋን* እንደ ባሪያ አገልግሉ።+ 12 በተስፋው ደስ ይበላችሁ። መከራን በጽናት ተቋቋሙ።+ ሳትታክቱ ጸልዩ።+ 13 ለቅዱሳን እንደየችግራቸው ያላችሁን አካፍሉ።+ የእንግዳ ተቀባይነትን ባሕል አዳብሩ።+ 14 ስደት የሚያደርሱባችሁን መርቁ፤+ መርቁ እንጂ አትርገሙ።+ 15 ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ፤ ከሚያለቅሱ ጋር አልቅሱ። 16 ለራሳችሁ ያላችሁ ዓይነት አመለካከት ለሌሎችም ይኑራችሁ፤ የትዕቢት ዝንባሌ እንዳያድርባችሁ ተጠንቀቁ፤ ትሕትና የሚንጸባረቅበት አስተሳሰብ ይኑራችሁ።+ ጥበበኞች እንደሆናችሁ አድርጋችሁ አታስቡ።+
17 ለማንም በክፉ ፋንታ ክፉ አትመልሱ።+ በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን ነገር ለማድረግ ጥረት አድርጉ። 18 ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር በእናንተ በኩል የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ።+ 19 የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ ራሳችሁ አትበቀሉ፤ ከዚህ ይልቅ “‘በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ’ ይላል ይሖዋ”*+ ተብሎ ስለተጻፈ ለቁጣው* ዕድል ስጡ።+ 20 ነገር ግን “ጠላትህ ቢራብ አብላው፤ ቢጠማ አጠጣው፤ ይህን በማድረግ በራሱ ላይ ፍም ትከምራለህ።”*+ 21 በክፉ አትሸነፍ፤ ከዚህ ይልቅ ምንጊዜም ክፉውን በመልካም አሸንፍ።+
13 ሰው* ሁሉ ለበላይ ባለሥልጣናት ይገዛ፤+ ሥልጣን ሁሉ የሚገኘው ከአምላክ ነውና፤+ ያሉት ባለሥልጣናት አንጻራዊ ቦታቸውን ያገኙት ከአምላክ ነው።+ 2 ስለዚህ ባለሥልጣንን የሚቃወም ሁሉ አምላክ ያደረገውን ዝግጅት ይቃወማል፤ ይህን ዝግጅት የሚቃወሙ በራሳቸው ላይ ፍርድ ያመጣሉ። 3 ገዢዎች የሚያስፈሩት ክፉ ለሚያደርጉ እንጂ መልካም ለሚያደርጉ አይደለምና።+ እንግዲያው ባለሥልጣንን መፍራት የማትፈልግ ከሆነ መልካም ማድረግህን ቀጥል፤+ ከእሱም ምስጋና ታገኛለህ፤ 4 ለአንተ ጥቅም ሲባል የተሾመ የአምላክ አገልጋይ ነውና። ክፉ የምታደርግ ከሆነ ግን ልትፈራ ይገባሃል፤ ምክንያቱም ሰይፍ የሚታጠቀው እንዲያው በከንቱ አይደለም። ክፉ የሚሠራን በመቅጣት* የሚበቀል የአምላክ አገልጋይ ነው።
5 ስለዚህ ቁጣውን በመፍራት ብቻ ሳይሆን ስለ ሕሊናችሁ ስትሉም መገዛታችሁ አስፈላጊ ነው።+ 6 ቀረጥ የምትከፍሉትም ለዚሁ ነው፤ ምክንያቱም እነሱ ሕዝባዊ አገልግሎት የሚያከናውኑ የአምላክ አገልጋዮች ናቸው፤ የዘወትር ተግባራቸውም ይኸው ነው። 7 ለሁሉም የሚገባውን አስረክቡ፤ ቀረጥ ለሚጠይቅ ቀረጥ፣+ ግብር ለሚጠይቅ ግብር ስጡ፤ መፈራት የሚፈልገውን ፍሩ፤+ መከበር የሚፈልገውን አክብሩ።+
8 እርስ በርስ ከመዋደድ በቀር በማንም ላይ ምንም ዕዳ አይኑርባችሁ፤+ ሰውን የሚወድ ሁሉ ሕጉን ፈጽሟልና።+ 9 ምክንያቱም “አታመንዝር፣+ አትግደል፣+ አትስረቅ፣+ አትጎምጅ”+ የሚሉት ሕጎችና ሌሎች ትእዛዛት በሙሉ “ባልንጀራህን* እንደ ራስህ ውደድ”+ በሚለው በዚህ ቃል ተጠቃለዋል። 10 ፍቅር በባልንጀራው ላይ ክፉ አያደርግም፤+ ስለዚህ ፍቅር የሕግ ፍጻሜ ነው።+
11 ምን ዓይነት ዘመን ላይ እንደምንገኝ ስለምታውቁም ይህን አድርጉ፤ አማኞች ከሆንበት ጊዜ ይልቅ አሁን መዳናችን ይበልጥ ስለቀረበ ከእንቅልፍ የምትነቁበት ሰዓት አሁን ነው።+ 12 ሌሊቱ እየተገባደደ ነው፤ ቀኑም ቀርቧል። ስለዚህ ከጨለማ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን አውልቀን+ የብርሃንን የጦር ዕቃዎች እንልበስ።+ 13 መረን በለቀቀ ፈንጠዝያና በስካር፣ ልቅ በሆነ የፆታ ግንኙነትና ማንአለብኝነት በሚንጸባረቅበት ድርጊት*+ እንዲሁም በጠብና በቅናት+ ሳይሆን በቀን ብርሃን እንደምንመላለስ በጨዋነት እንመላለስ።+ 14 ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት፤+ የሥጋ ፍላጎታችሁን ለማርካት ዕቅድ አታውጡ።+
14 በእምነቱ ጠንካራ ያልሆነውን ሰው ተቀበሉት+ እንጂ በአመለካከት ልዩነት* ላይ ተመሥርታችሁ አትፍረዱ። 2 አንድ ሰው እምነቱ ማንኛውንም ነገር እንዲበላ ይፈቅድለታል፤ በእምነቱ ጠንካራ ያልሆነ ሰው ግን አትክልት ብቻ ይበላል። 3 ማንኛውንም ነገር የሚበላ የማይበላውን አይናቅ፤ የማይበላው ደግሞ በሚበላው ላይ አይፍረድ፤+ ይህን ሰው አምላክ ተቀብሎታልና። 4 በሌላው አገልጋይ ላይ የምትፈርድ አንተ ማን ነህ?+ እሱ ቢቆምም ሆነ ቢወድቅ ለጌታው ነው።+ እንዲያውም ይሖዋ* እንዲቆም ሊያደርገው ስለሚችል ይቆማል።
5 አንድ ሰው አንዱ ቀን ከሌላው ቀን የበለጠ እንደሆነ አድርጎ ያስባል፤+ ሌላው ደግሞ አንዱ ቀን ከሌሎቹ ቀናት ሁሉ የተለየ እንዳልሆነ ያስባል፤+ እያንዳንዱ ሰው ሙሉ በሙሉ ያመነበትን ውሳኔ ያድርግ። 6 አንድን ቀን የሚያከብር ለይሖዋ* ብሎ ያከብራል። ማንኛውንም ነገር የሚበላም አምላክን ስለሚያመሰግን ለይሖዋ* ብሎ ይበላል፤+ የማይበላም ለይሖዋ* ብሎ አይበላም፤ ይሁንና አምላክን ያመሰግናል።+ 7 እንዲያውም ከመካከላችን ለራሱ ብቻ ብሎ የሚኖር የለም፤+ ለራሱ ብቻ ብሎም የሚሞት የለም። 8 ብንኖር የምንኖረው ለይሖዋ* ነውና፤+ ብንሞትም የምንሞተው ለይሖዋ* ነው። ስለዚህ ብንኖርም ሆነ ብንሞት የይሖዋ* ነን።+ 9 ክርስቶስ የሞተውና ዳግም ሕያው የሆነው ለዚህ ዓላማ ይኸውም በሙታንም ሆነ በሕያዋን ላይ ጌታ ይሆን ዘንድ ነውና።+
10 ታዲያ አንተ በወንድምህ ላይ ለምን ትፈርዳለህ?+ አንተ ደግሞ ወንድምህን ለምን ትንቃለህ? ሁላችንም በአምላክ የፍርድ ወንበር ፊት እንቆማለንና።+ 11 “‘በሕያውነቴ እምላለሁ’+ ይላል ይሖዋ፣* ‘ጉልበት ሁሉ ለእኔ ይንበረከካል፤ ምላስም ሁሉ እኔ አምላክ መሆኔን በይፋ ይመሠክራል’” ተብሎ ተጽፏልና።+ 12 ስለዚህ እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለአምላክ መልስ እንሰጣለን።+
13 ስለሆነም ከእንግዲህ አንዳችን በሌላው ላይ አንፍረድ፤+ ከዚህ ይልቅ በአንድ ወንድም ፊት የሚያደናቅፍ ወይም የሚያሰናክል ነገር ላለማስቀመጥ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።+ 14 የጌታ ኢየሱስ ተከታይ እንደመሆኔ መጠን ማንኛውም ነገር በራሱ ርኩስ እንዳልሆነ አውቄአለሁ ደግሞም አምኛለሁ፤+ አንድ ነገር ለአንድ ሰው ርኩስ የሚሆነው ያ ነገር ርኩስ ነው ብሎ ሲያስብ ብቻ ነው። 15 አንተ በምግብ የተነሳ ወንድምህ ቅር እንዲሰኝ ካደረግክ በፍቅር መመላለስህን ትተሃል ማለት ነው።+ ስለዚህ ክርስቶስ የሞተለት ይህ ሰው በምትበላው ምግብ ምክንያት እንዲጠፋ አታድርግ።*+ 16 በመሆኑም መልካም ነው ብላችሁ የምታደርጉት ነገር በሌሎች ዘንድ በመጥፎ እንዳይነሳ ተጠንቀቁ። 17 የአምላክ መንግሥት በመንፈስ ቅዱስ የሚገኝ ጽድቅ፣ ሰላምና ደስታ ነው እንጂ የመብልና የመጠጥ ጉዳይ አይደለም።+ 18 በዚህ መንገድ ክርስቶስን እንደ ባሪያ የሚያገለግል ሁሉ በአምላክ ፊት ተቀባይነት፣ በሰዎችም ዘንድ ሞገስ ያገኛልና።
19 ስለዚህ ሰላም የሚገኝበትንና+ እርስ በርሳችን የምንተናነጽበትን+ ነገር ለማድረግ የተቻለንን ሁሉ ጥረት እናድርግ። 20 ለምግብ ብለህ የአምላክን ሥራ ማፍረስ ተው።+ እርግጥ ነው፣ ሁሉም ነገር ንጹሕ ነው፤ ሆኖም አንድ ሰው መብላቱ ሌሎችን የሚያደናቅፍ ከሆነ ጎጂ* ነው።+ 21 ወንድምህ የሚሰናከልበት ከሆነ ሥጋ አለመብላት፣ የወይን ጠጅ አለመጠጣት ወይም ማንኛውንም የሚያሰናክል ነገር አለማድረግ የተሻለ ነው።+ 22 እንግዲህ እምነትህ በአንተና በአምላክ መካከል ያለ ጉዳይ ይሁን። ትክክል ነው ብሎ ያመነበትን ነገር ካደረገ በኋላ መልሶ ራሱን የማይኮንን ሰው ደስተኛ ነው። 23 እየተጠራጠረ ከበላ ግን የበላው በእምነት ስላልሆነ ቀድሞውንም ተኮንኗል። ደግሞም በእምነት ያልተደረገ ነገር ሁሉ ኃጢአት ነው።
15 እኛ በእምነት ጠንካሮች የሆን ጠንካሮች ያልሆኑትን ሰዎች ድክመት ልንሸከም ይገባል+ እንጂ ራሳችንን የምናስደስት መሆን የለብንም።+ 2 እያንዳንዳችን ባልንጀራችንን* የሚጠቅመውንና የሚያንጸውን ነገር በማድረግ እናስደስተው።+ 3 ክርስቶስ እንኳ ራሱን አላስደሰተምና፤+ ይህም “ሰዎች አንተን ይነቅፉበት የነበረው ነቀፋ በእኔ ላይ ደረሰ” ተብሎ እንደተጻፈው ነው።+ 4 በምናሳየው ጽናትና+ ከቅዱሳን መጻሕፍት በምናገኘው መጽናኛ ተስፋ ይኖረን ዘንድ+ ቀደም ብሎ የተጻፈው ነገር ሁሉ ለእኛ ትምህርት እንዲሆን ተጽፏልና።+ 5 ጽናትንና መጽናኛን የሚሰጠው አምላክ፣ ሁላችሁም ክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ዓይነት አስተሳሰብ እንዲኖራችሁ ያድርግ፤ 6 ይኸውም በኅብረትና+ በአንድ ድምፅ* የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክና አባት እንድታከብሩ ነው።
7 ስለዚህ ክርስቶስ እኛን እንደተቀበለን+ ሁሉ አምላክ እንዲከበር እናንተም አንዳችሁ ሌላውን ተቀበሉ።+ 8 ክርስቶስ፣ አምላክ እውነተኛ መሆኑን ለማሳየት ሲል ለተገረዙት አገልጋይ እንደሆነ ልነግራችሁ እወዳለሁ፤+ በተጨማሪም አገልጋይ የሆነው፣ አምላክ ለአባቶቻቸው የገባውን ቃል ለማረጋገጥ+ 9 እንዲሁም ብሔራት አምላክን ስለ ምሕረቱ ያከብሩት ዘንድ ነው።+ ይህም “ስለዚህ በብሔራት መካከል በይፋ አወድስሃለሁ፤ ለስምህም የውዳሴ መዝሙር እዘምራለሁ” ተብሎ እንደተጻፈው ነው።+ 10 ደግሞም “እናንተ ብሔራት፣ ከሕዝቡ ጋር ደስ ይበላችሁ” ይላል።+ 11 እንደገናም “ብሔራት ሁሉ፣ ይሖዋን* አወድሱት፤ ሕዝቦችም ሁሉ ያወድሱት” ይላል።+ 12 እንዲሁም ኢሳይያስ “የእሴይ ሥር ይገለጣል፤+ ብሔራትንም የሚገዛው ይነሳል፤+ ብሔራትም ተስፋቸውን በእሱ ላይ ይጥላሉ” ይላል።+ 13 በእሱ በመታመናችሁ የተነሳ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተስፋ እንዲትረፈረፍላችሁ* ተስፋ የሚሰጠው አምላክ ደስታንና ሰላምን ሁሉ ይሙላባችሁ።+
14 ወንድሞቼ ሆይ፣ እናንተ ራሳችሁ በጥሩነት የተሞላችሁ እንደሆናችሁ፣ የተሟላ እውቀት እንዳላችሁና አንዳችሁ ሌላውን መምከር* እንደምትችሉ እኔ ራሴ ስለ እናንተ እርግጠኛ መሆን ችያለሁ። 15 ይሁን እንጂ አንዳንድ ጉዳዮችን ግልጥልጥ አድርጌ የጻፍኩላችሁ ተጨማሪ ማሳሰቢያ ልሰጣችሁ ስለፈለግኩ ነው። ይህን የማደርገው ከአምላክ በተሰጠኝ ጸጋ የተነሳ ነው። 16 ይህ ጸጋ የተሰጠኝም ለአሕዛብ የክርስቶስ ኢየሱስ አገልጋይ እንድሆን ነው።+ የአምላክን ምሥራች በማወጁ ቅዱስ ሥራ+ የምካፈለው እነዚህ አሕዛብ በመንፈስ ቅዱስ የተቀደሰ፣ ተቀባይነት ያለው መባ ሆነው ለአምላክ እንዲቀርቡ ነው።
17 ስለዚህ ለአምላክ ከማቀርበው አገልግሎት ጋር በተያያዘ በክርስቶስ ኢየሱስ ሐሴት የማደርግበት ምክንያት አለኝ። 18 አሕዛብ ታዛዦች እንዲሆኑ ክርስቶስ በእኔ አማካኝነት ስላከናወነው ነገር ካልሆነ በቀር ስለ ሌላ ነገር ለመናገር አልደፍርም። ይህን ያከናወነው እኔ በተናገርኩትና ባደረግኩት ነገር 19 እንዲሁም በተአምራዊ ምልክቶችና ድንቅ ነገሮች+ ደግሞም በአምላክ መንፈስ ኃይል ነው፤ በመሆኑም ከኢየሩሳሌም አንስቶ ዙሪያውን እስከ እልዋሪቆን ድረስ ስለ ክርስቶስ የሚገልጸውን ምሥራች በተሟላ ሁኔታ ሰብኬአለሁ።+ 20 በዚህ መንገድ የክርስቶስ ስም አስቀድሞ በታወቀበት ቦታ ምሥራቹን ላለመስበክ የተቻለኝን ሁሉ ጥረት አድርጌአለሁ፤ ይህን ያደረግኩት ሌላ ሰው በጣለው መሠረት ላይ መገንባት ስላልፈለግኩ ነው፤ 21 ይህም “ከዚህ በፊት ስለ እሱ ምንም ያልተነገራቸው ያያሉ፤ ያልሰሙም ያስተውላሉ” ተብሎ እንደተጻፈው ነው።+
22 በተደጋጋሚ ጊዜያት ወደ እናንተ መምጣት ሳልችል የቀረሁትም በዚህ ምክንያት ነው። 23 አሁን ግን በዚህ አካባቢ ባሉት አገሮች ያልሰበክሁበት ክልል የለም፤ ደግሞም ለብዙ ዓመታት* ወደ እናንተ ለመምጣት ስጓጓ ቆይቻለሁ። 24 በመሆኑም ወደ ስፔን በምጓዝበት ጊዜ እንደማገኛችሁና እናንተ ጋ ለተወሰነ ጊዜ ቆይቼ ናፍቆቴን ከተወጣሁ በኋላ ጥቂት መንገድ እንደምትሸኙኝ ተስፋ አደርጋለሁ። 25 አሁን ግን ቅዱሳንን ለማገልገል* ወደ ኢየሩሳሌም ልጓዝ ነው።+ 26 በመቄዶንያና በአካይያ ያሉት ወንድሞች በኢየሩሳሌም ባሉት ቅዱሳን መካከል ለሚገኙት ድሆች መዋጮ በመስጠት ያላቸውን ነገር በደስታ አካፍለዋልና።+ 27 አዎ፣ ይህን ያደረጉት በፈቃደኝነት ነው፤ ደግሞም የእነሱ ዕዳ ነበረባቸው፤ ምክንያቱም አሕዛብ የእነሱን መንፈሳዊ ነገር ከተካፈሉ እነሱ ደግሞ ለሚያስፈልጓቸው ቁሳዊ ነገሮች የማዋጣት ዕዳ አለባቸው።+ 28 ስለሆነም ይህን ሥራ ካከናወንኩና መዋጮውን ካስረከብኳቸው* በኋላ በእናንተ በኩል አድርጌ ወደ ስፔን እሄዳለሁ። 29 ደግሞም ወደ እናንተ በምመጣበት ጊዜ የክርስቶስን የተትረፈረፈ በረከት ይዤላችሁ እንደምመጣ አውቃለሁ።
30 እንግዲህ ወንድሞች፣ ስለ እኔ አምላክን በመለመን ከእኔ ጋር አብራችሁ በጸሎት እንድትተጉ+ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስና ከመንፈስ በሚገኘው ፍቅር አበረታታችኋለሁ፤ 31 በይሁዳ ካሉት የማያምኑ ሰዎች እጅ እንድድንና+ በኢየሩሳሌም ለሚገኙት ቅዱሳን+ የማቀርበው አገልግሎት* በእነሱ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ጸልዩልኝ፤ 32 ይኸውም አምላክ ከፈቀደ ወደ እናንተ በደስታ እንድመጣና ከእናንተ ጋር በመሆን መንፈሴ እንዲታደስ ነው። 33 ሰላም የሚሰጠው አምላክ ከሁላችሁ ጋር ይሁን።+ አሜን።
16 በክንክራኦስ+ ጉባኤ የምታገለግለውን እህታችንን ፌበንን ላስተዋውቃችሁ እወዳለሁ፤ 2 በጌታ የእምነት ባልደረባችሁ እንደመሆኗ መጠን ለቅዱሳን በሚገባ ሁኔታ* ተቀበሏት፤ የምትፈልገውንም እርዳታ ሁሉ አድርጉላት፤+ ምክንያቱም እሷ እኔን ጨምሮ ለብዙ ወንድሞች ድጋፍ ሆናለች።
3 በክርስቶስ ኢየሱስ አብረውኝ ለሚሠሩት ለጵርስቅላና ለአቂላ+ ሰላምታ አቅርቡልኝ፤ 4 እነሱ ለእኔ* ሲሉ ሕይወታቸውን* ለአደጋ አጋልጠዋል፤+ እኔ ብቻ ሳልሆን በአሕዛብ መካከል የሚገኙ ጉባኤዎችም ሁሉ ያመሰግኗቸዋል። 5 በቤታቸው ላለው ጉባኤም ሰላምታ አቅርቡልኝ።+ በእስያ ከመጀመሪያዎቹ የክርስቶስ ተከታዮች አንዱ የሆነውን የምወደውን ኤጲኔጦስን ሰላም በሉልኝ። 6 ለእናንተ ብዙ የደከመችውን ማርያምን ሰላም በሉልኝ። 7 ዘመዶቼ+ የሆኑትንና አብረውኝ የታሰሩትን እንዲሁም በሐዋርያት ዘንድ ስመጥር የሆኑትንና ከእኔ ቀደም ብለው የክርስቶስ ተከታዮች የሆኑትን አንድሮኒኮስንና ዩኒያስን ሰላም በሉልኝ።
8 በጌታ ለምወደው ለአምጵልያጦስ ሰላምታዬን አቅርቡልኝ። 9 በክርስቶስ አብሮን የሚሠራውን ኡርባኖስንና የምወደውን እስጣኩስን ሰላም በሉልኝ። 10 በክርስቶስ ዘንድ መልካም ስም ያተረፈውን አጵሌስን ሰላም በሉልኝ። የአርስጦቡሉስ ቤተሰብ ለሆኑት ሰላምታ አቅርቡልኝ። 11 ዘመዴን ሄሮድዮንን ሰላም በሉልኝ። የጌታ ተከታዮች የሆኑትን የናርኪሰስን ቤተሰቦች ሰላም በሉልኝ። 12 በጌታ ሆነው በትጋት የሚሠሩትን ጥራይፊናና ጥራይፎሳ የተባሉትን ሴቶች ሰላም በሉልኝ። የምንወዳትን ጰርሲስን ሰላም በሉልኝ፤ በጌታ ሥራ ብዙ ደክማለችና። 13 የጌታ ምርጥ አገልጋይ ለሆነው ለሩፎስ እንዲሁም እኔም እንደ እናቴ ለማያት ለእናቱ ሰላምታ አቅርቡልኝ። 14 አሲንክሪጦስን፣ ፍሌጎንን፣ ሄርሜስን፣ ጳጥሮባን፣ ሄርማስንና ከእነሱ ጋር ያሉትን ወንድሞች ሰላም በሉልኝ። 15 ፊሎሎጎስንና ዩልያን፣ ኔርዩስንና እህቱን፣ ኦሊምጳስን እንዲሁም ከእነሱ ጋር ያሉትን ቅዱሳን ሁሉ ሰላም በሉልኝ። 16 በተቀደሰ አሳሳም ሰላምታ ተለዋወጡ። የክርስቶስ ጉባኤዎች በሙሉ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።
17 እንግዲህ ወንድሞች፣ ክፍፍል ከሚፈጥሩና ለእንቅፋት ምክንያት የሚሆኑ ነገሮችን ከሚያመጡ ሰዎች እንድትጠነቀቁ አሳስባችኋለሁ፤ እነዚህ ነገሮች የተማራችሁትን ትምህርት የሚጻረሩ ናቸው፤ ይህን ከሚያደርጉ ሰዎች ራቁ።+ 18 እንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች ለጌታችን ለክርስቶስ ሳይሆን ለራሳቸው ፍላጎት* ባሪያዎች ናቸው፤ በለሰለሰ አንደበትና በሽንገላ ቃላት የየዋሆችን ልብ ያታልላሉ። 19 ታዛዥነታችሁ በሁሉ ዘንድ የታወቀ ሆኗል፤ ስለዚህ እኔ በእናንተ እጅግ እደሰታለሁ። ይሁንና ለመልካም ነገር ጥበበኞች እንድትሆኑ፣ ለክፉ ነገር ደግሞ አላዋቂዎች እንድትሆኑ እፈልጋለሁ።+ 20 ሰላም የሚሰጠው አምላክ በቅርቡ ሰይጣንን ከእግራችሁ በታች ይጨፈልቀዋል።+ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።
21 የሥራ አጋሬ ጢሞቴዎስ ሰላምታ ያቀርብላችኋል፤ ዘመዶቼ+ የሆኑት ሉክዮስ፣ ያሶንና ሶሲጳጥሮስም ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።
22 ይህን ደብዳቤ በጽሑፍ ያሰፈርኩት እኔ ጤርጥዮስም በጌታ ሰላምታ አቀርብላችኋለሁ።
23 እኔንም ሆነ መላውን ጉባኤ የሚያስተናግደው ጋይዮስ+ ሰላም ይላችኋል። የከተማዋ የግምጃ ቤት ሹም* ኤርስጦስ ሰላምታ ያቀርብላችኋል፤ ወንድሙ ቁአስጥሮስም ሰላም ይላችኋል። 24 *——
25 አምላክ ለረጅም ዘመናት ተሰውሮ ከቆየው ቅዱስ ሚስጥር+ መገለጥ ጋር በሚስማማ ሁኔታ እኔ በማውጀው ምሥራችና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚሰበከው መልእክት መሠረት ሊያጸናችሁ ይችላል። 26 አሁን ግን ሕዝቦች ሁሉ እምነት እንዲኖራቸውና እሱን እንዲታዘዙ ቅዱሱ ሚስጥር፣ በዘላለማዊው አምላክ ትእዛዝ መሠረት ትንቢታዊ በሆኑ ቅዱሳን መጻሕፍት አማካኝነት በሕዝቦች ሁሉ መካከል እንዲገለጥና እንዲታወቅ ተደርጓል፤ 27 እሱ ብቻ ጥበበኛ+ ለሆነው አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለዘላለም ክብር ይሁን። አሜን።
ቃል በቃል “ከተለየው።”
ወይም “ተቀብያለሁ።” እዚህ ላይ ጳውሎስ በብዙ ቁጥር የተጠቀመው ራሱን ለማመልከት ሊሆን ይችላል።
ወይም “ለባዕዳን።” ቃል በቃል “ላልሠለጠኑ።”
ወይም “ፍጥረትን አምልከዋል።”
ወይም “ብድራት።”
ወይም “ስለ አምላክ ትክክለኛ እውቀት ማግኘት ስላልፈለጉ።”
ወይም “በመጎምጀት።”
ወይም “አሾክሿኪዎች።”
እንዲህ ያሉ ነገሮችን የመሥራት ልማድ ያላቸውን ሰዎች ያመለክታል።
ወይም “ሰው ነፍስ ሁሉ።”
ቃል በቃል “እርስ በርሱ።”
ወይም “በቃል የተማርክ።”
ቃል በቃል “ሥጋ ሁሉ።”
ወይም “እውቀት።”
ወይም “እርቅ ይፈጥሩ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “እንደ ዕዳ።”
ወይም “ይቅር የተባለላቸው።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “ዋስትና፤ ማረጋገጫ።”
“ሕልውና የሌለውን ነገር ወደ ሕልውና በሚያመጣው” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ፍሬ አልባ።”
“ከአምላክ ጋር ሰላም አለን” ማለትም ሊሆን ይችላል።
“እጅግ እንደሰታለን” ማለትም ሊሆን ይችላል።
“እጅግ እንደሰታለን” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ለኀፍረት።”
ወይም “የተትረፈረፈ።”
ወይም “ከበደል ነፃ የሚያደርግ አንድ ድርጊትም።” ሰዎች ጻድቃን እንዲባሉ የሚያስችል ድርጊት ማለት ነው።
ወይም “ኃጢአቱ ይቅር ተብሏልና።”
ኃጢአትን ለማስወገድ ሞቷል ማለት ነው።
ቃል በቃል “የአካል ክፍሎቻችሁን።”
ቃል በቃል “የጦር መሣሪያ።”
ቃል በቃል “የአካል ክፍሎቻችሁንም።”
ወይም “ኃጢአት የሚከፍለው ደሞዝ ሞት ነውና።”
ወይም “ከሕጉ ነፃ ወጥታችኋል።”
ቃል በቃል “በአካል ክፍሎቻችን።”
ቃል በቃል “ሕጉ ኃጢአት ነው?”
“ጥሩ የሆነው ነገር” የሚለው የአምላክን ሕግ ያመለክታል።
ወይም “ከአምላክ የተገኘ።”
ቃል በቃል “በአካል ክፍሎቼ።”
ቃል በቃል “በአካል ክፍሎቼ።”
“አባት ሆይ!” የሚል ትርጉም ያለው የዕብራይስጥ ወይም የአረማይክ ቃል ነው።
ቃል በቃል “በተመኘ ወይም በሮጠ።”
ወይም “በሰዎች ላይ ለምን ስህተት ይፈላልጋል?”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “በፍጥነት።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “እምነቱን በተግባር የሚያሳይ።”
ወይም “እሱም ለሚለምኑት ሁሉ በልግስና ይሰጣል።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “እኛ የተናገርነውን።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “ነፍሴን።”
ወይም “ከፍ ከፍ አደርጋለሁ።”
ቃል በቃል “ሥጋዬ።”
ወይም “ጉራ አትንዛ።”
ወይም “ነፃ አውጪ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “ይህ ዘመን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “በመደበው፤ ባከፋፈለው።”
ወይም “የሚመክርም።”
ወይም “የሚያዋጣ።”
ወይም “አመራር የሚሰጥ።”
ወይም “ተነሳሽነት ይኑራችሁ።”
ወይም “ትጉዎች፤ ቀናተኞች።”
ወይም “በሥራችሁ አትለግሙ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
የአምላክን ቁጣ ያመለክታል።
የሰውየው ልብ እንዲለሰልስና ቁጣው እንዲበርድ ማድረግን ያመለክታል።
ወይም “ነፍስ።”
ወይም “ክፉ በሚሠራ ላይ የአምላክን ቁጣ በመግለጽ።”
“ባልንጀራ” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል የአንድን ሰው የቅርብ ጓደኛ ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም ሰው ሊያመለክት ይችላል።
ወይም “እፍረተ ቢስነት በሚንጸባረቅበት ምግባር።” እዚህ ላይ የገባው አሴልጊያ የሚለው ግሪክኛ ቃል ብዙ ቁጥር ነው። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
“በውስጥ በሚጉላሉ ጥያቄዎች” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
እምነቱ ወይም የዘላለም ሕይወት ተስፋው እንዲጠፋ አለማድረግን ያመለክታል።
ወይም “ስህተት።”
“ባልንጀራ” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል የአንድን ሰው የቅርብ ጓደኛ ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም ሰው ሊያመለክት ይችላል።
ቃል በቃል “አፍ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “እንዲበዛላችሁ።”
ወይም “ማስተማር።”
“ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ለመርዳት።”
ቃል በቃል “ፍሬውን ከሰጠኋቸው።”
ወይም “እርዳታ።”
ወይም “ቅዱሳን ሌሎችን በሚቀበሉበት መንገድ።”
ወይም “ለነፍሴ።”
ቃል በቃል “አንገታቸውን።”
ወይም “ለገዛ ሆዳቸው።”
ወይም “መጋቢ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ3ን ተመልከት።