የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • nwt ዮሐንስ 1:1-21:25
  • ዮሐንስ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ዮሐንስ
  • አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
ዮሐንስ

የዮሐንስ ወንጌል

1 በመጀመሪያ ቃል+ ነበረ፤ ቃልም ከአምላክ ጋር ነበር፤+ ቃልም አምላክ*+ ነበር። 2 እሱም በመጀመሪያ ከአምላክ ጋር ነበር። 3 ሁሉም ነገሮች ወደ ሕልውና የመጡት በእሱ በኩል ነው፤+ ያለእሱ ወደ ሕልውና የመጣ አንድም ነገር የለም።

4 በእሱ አማካኝነት ሕይወት ወደ ሕልውና መጥቷል፤ ይህ ሕይወት ደግሞ የሰው ብርሃን ነበር።+ 5 ብርሃኑም በጨለማ እየበራ ነው፤+ ጨለማውም አላሸነፈውም።

6 ከአምላክ የተላከ አንድ ሰው ነበር፤ እሱም ዮሐንስ+ ይባላል። 7 ይህ ሰው ስለ ብርሃኑ ይመሠክር ዘንድ ምሥክር ሆኖ መጣ፤+ ይህን ያደረገው ሁሉም ዓይነት ሰዎች በእሱ በኩል እንዲያምኑ ነው። 8 ያ ብርሃን እሱ አልነበረም፤+ ከዚህ ይልቅ እሱ የመጣው ስለ ብርሃኑ ሊመሠክር ነው።

9 ለሁሉም ዓይነት ሰው ብርሃን የሚሰጠው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም የሚመጣበት ጊዜ ደርሶ ነበር።+ 10 እሱም በዓለም ነበረ፤+ ዓለምም ወደ ሕልውና የመጣው በእሱ በኩል ነው፤+ ሆኖም ዓለም አላወቀውም። 11 ወደ ገዛ አገሩ መጣ፤ ነገር ግን የገዛ ወገኖቹ አልተቀበሉትም። 12 ለተቀበሉት ሁሉ ግን በስሙ ስላመኑ+ የአምላክ ልጆች+ የመሆን መብት ሰጣቸው። 13 እነሱም የተወለዱት ከአምላክ እንጂ+ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አይደለም።

14 ቃልም ሥጋ ሆነ፤+ በመካከላችንም ኖረ፤ አንድያ ልጅ+ ከአባቱ እንደሚያገኘው ክብር ያለ ክብሩን አየን፤ እሱም መለኮታዊ ሞገስንና* እውነትን ተሞልቶ ነበር። 15 (ዮሐንስ ስለ እሱ መሥክሯል፤ እንዲያውም ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “‘ከእኔ ኋላ የሚመጣው ከእኔ በፊት ስለነበረ ከእኔ ይበልጣል’ ብዬ የተናገርኩት ስለ እሱ ነው።”)+ 16 ከእሱ የጸጋ ሙላት የተነሳ ሁላችንም በጸጋ ላይ ጸጋን ተቀብለናል። 17 ምክንያቱም ሕጉ የተሰጠው በሙሴ በኩል ነበር፤+ ጸጋና+ እውነት ግን የመጣው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ነው።+ 18 በየትኛውም ጊዜ ቢሆን አምላክን ያየው አንድም ሰው የለም፤+ ስለ እሱ የገለጸልን+ ከአብ ጎን* ያለውና+ አምላክ+ የሆነው አንድያ ልጁ ነው።

19 አይሁዳውያን “አንተ ማን ነህ?”+ ብለው እንዲጠይቁት ከኢየሩሳሌም ካህናትንና ሌዋውያንን በላኩ ጊዜ ዮሐንስ የሰጠው ምሥክርነት ይህ ነው፤ 20 “እኔ ክርስቶስ አይደለሁም” ብሎ በግልጽ ተናገረ እንጂ ጥያቄውን ከመመለስ ወደኋላ አላለም። 21 እነሱም “ታዲያ ማን ነህ? ኤልያስ ነህ?”+ ሲሉ ጠየቁት። እሱም መልሶ “አይደለሁም” አለ። “ነቢዩ ነህ?”+ አሉት። እሱም “አይደለሁም!” ሲል መለሰ። 22 በዚህ ጊዜ “ለላኩን ሰዎች መልስ መስጠት እንድንችል ታዲያ አንተ ማን ነህ? ስለ ራስህስ ምን ትላለህ?” አሉት። 23 እሱም “ነቢዩ ኢሳይያስ እንደተናገረው ‘የይሖዋን* መንገድ አቅኑ’ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኸው ሰው እኔ ነኝ” አለ።+ 24 ሰዎቹን የላኳቸውም ፈሪሳውያን ነበሩ። 25 በመሆኑም “ታዲያ ክርስቶስ ወይም ኤልያስ ወይም ነቢዩ ካልሆንክ ለምን ታጠምቃለህ?” ሲሉ ጠየቁት። 26 ዮሐንስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “እኔ በውኃ አጠምቃለሁ። እናንተ የማታውቁት ግን በመካከላችሁ ቆሟል፤ 27 እሱም ከኋላዬ ይመጣል፤ እኔ የጫማውን ማሰሪያ እንኳ ለመፍታት አልበቃም።”+ 28 ይህ የሆነው ዮሐንስ ሲያጠምቅ+ ከነበረበት ከዮርዳኖስ ማዶ በሚገኘው በቢታንያ ነበር።

29 በማግስቱ ኢየሱስ ወደ እሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ፦ “የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግደው+ የአምላክ በግ+ ይኸውላችሁ!+ 30 ‘ከኋላዬ አንድ ሰው ይመጣል፤ ከእኔ በፊት ስለነበረ ከእኔ ይበልጣል’ ያልኳችሁ እሱ ነው።+ 31 እኔም እንኳ አላውቀውም ነበር፤ እኔ በውኃ እያጠመቅኩ የመጣሁበት ምክንያት ግን እሱ ለእስራኤል እንዲገለጥ ነው።”+ 32 በተጨማሪም ዮሐንስ እንዲህ ሲል ምሥክርነት ሰጥቷል፦ “መንፈስ ከሰማይ ወጥቶ እንደ ርግብ ሲወርድ አይቻለሁ፤ በእሱም ላይ አረፈ።+ 33 እኔም እንኳ አላውቀውም ነበር፤ ሆኖም በውኃ እንዳጠምቅ የላከኝ ራሱ ‘በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቀው፣+ መንፈስ ሲወርድበትና ሲያርፍበት+ የምታየው ያ ሰው ነው’ አለኝ። 34 እኔም አይቻለሁ፤ እሱም የአምላክ ልጅ መሆኑን መሥክሬአለሁ።”+

35 በማግስቱም ዮሐንስ ከሁለት ደቀ መዛሙርቱ ጋር እንደገና በዚያ ቆሞ ነበር፤ 36 ኢየሱስ ሲያልፍ አይቶም “የአምላክ በግ+ ይኸውላችሁ!” አለ። 37 ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ይህን ሲናገር በሰሙ ጊዜ ኢየሱስን ተከተሉት። 38 ከዚያም ኢየሱስ ዞር ብሎ ሲከተሉት አየና “ምን ፈልጋችሁ ነው?” አላቸው። እነሱም “ረቢ፣ የት ነው የምትኖረው?” አሉት (ረቢ ማለት “መምህር” ማለት ነው)፤ 39 እሱም “ኑና እዩ” አላቸው። ስለዚህ ሄደው የት እንደሚኖር አዩ፤ ጊዜውም አሥር ሰዓት ገደማ ነበር፤ በዚያም ዕለት አብረውት ዋሉ። 40 ዮሐንስ የተናገረውን ከሰሙትና ኢየሱስን ከተከተሉት ሁለት ሰዎች አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ+ ነበር። 41 እንድርያስ በመጀመሪያ የራሱን ወንድም ስምዖንን አገኘውና “መሲሑን አገኘነው”+ አለው (መሲሕ ማለት “ክርስቶስ” ማለት ነው)፤ 42 ወደ ኢየሱስም ወሰደው። ኢየሱስም ባየው ጊዜ “አንተ የዮሐንስ ልጅ ስምዖን+ ነህ፤ ኬፋ ተብለህ ትጠራለህ” አለው (ኬፋ ማለት “ጴጥሮስ” ማለት ነው)።+

43 በማግስቱ ኢየሱስ ወደ ገሊላ ለመሄድ ፈለገ። ከዚያም ፊልጶስን+ አግኝቶ “ተከታዬ ሁን” አለው። 44 ፊልጶስም እንደ እንድርያስና እንደ ጴጥሮስ የቤተሳይዳ ከተማ ሰው ነበረ። 45 ፊልጶስ ናትናኤልን+ አግኝቶ “ሙሴ በሕጉ፣ ነቢያት ደግሞ በመጻሕፍት የጻፉለትን የዮሴፍን+ ልጅ የናዝሬቱን ኢየሱስን አገኘነው” አለው። 46 ናትናኤል ግን “ደግሞ ከናዝሬት ጥሩ ነገር ሊገኝ ይችላል?” አለው። ፊልጶስም “መጥተህ እይ” አለው። 47 ኢየሱስም ናትናኤል ወደ እሱ ሲመጣ አይቶ ስለ እሱ “ተንኮል የሌለበት እውነተኛ እስራኤላዊ ይኸውላችሁ!” አለ።+ 48 ናትናኤልም “እንዴት ልታውቀኝ ቻልክ?” አለው። ኢየሱስም መልሶ “ገና ፊልጶስ ሳይጠራህ ከበለስ ዛፍ ሥር ሳለህ አይቼሃለሁ” አለው። 49 ናትናኤልም “ረቢ፣ አንተ የአምላክ ልጅ ነህ፤ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ” ሲል መለሰለት።+ 50 ኢየሱስም መልሶ “ያመንከው ከበለስ ዛፍ ሥር አየሁህ ስላልኩህ ነው? ከዚህ የሚበልጥ ነገር ገና ታያለህ” አለው። 51 ከዚያም “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ሰማይ ተከፍቶ የአምላክ መላእክት ወደዚያ ሲወጡና የሰው ልጅ ወዳለበት ሲወርዱ ታያላችሁ” አለው።+

2 በሦስተኛውም ቀን በገሊላ በምትገኘው በቃና የሠርግ ድግስ ነበር፤ የኢየሱስ እናትም በዚያ ነበረች። 2 ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሠርጉ ተጠርተው ነበር።

3 የወይን ጠጁ እያለቀ ሲሄድ የኢየሱስ እናት “የወይን ጠጅ አልቆባቸዋል” አለችው። 4 ኢየሱስ ግን “አንቺ ሴት፣ ይህ ጉዳይ እኔንና አንቺን ምን ይመለከተናል?* ሰዓቴ ገና አልደረሰም” አላት። 5 እናቱም በዚያ የሚያገለግሉትን ሰዎች “የሚላችሁን ነገር ሁሉ አድርጉ” አለቻቸው። 6 የአይሁዳውያን የመንጻት ሥርዓት በሚያዘው መሠረት+ እያንዳንዳቸው ሁለት ወይም ሦስት የፈሳሽ መለኪያዎች* የሚይዙ ከድንጋይ የተሠሩ ስድስት የውኃ ጋኖች በዚያ ተቀምጠው ነበር። 7 ኢየሱስም “ጋኖቹን ውኃ ሙሏቸው” አላቸው። እነሱም እስከ አፋቸው ድረስ ሞሏቸው። 8 ከዚያም “አሁን ቀድታችሁ ለድግሱ አሳዳሪ ስጡት” አላቸው። እነሱም ወስደው ሰጡት። 9 የድግሱ አሳዳሪም ወደ ወይን ጠጅ የተለወጠውን ውኃ ቀመሰ፤ ሆኖም ከየት እንደመጣ አላወቀም፤ ውኃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር፤ አሳዳሪውም ሙሽራውን ጠርቶ 10 እንዲህ አለው፦ “ሰው ሁሉ በቅድሚያ ጥሩውን የወይን ጠጅ ያቀርብና ሰዎቹ ከሰከሩ በኋላ መናኛውን ያቀርባል። አንተ ግን ጥሩውን የወይን ጠጅ እስካሁን ድረስ አስቀምጠሃል።” 11 ኢየሱስ ከምልክቶቹ የመጀመሪያ የሆነውን ይህን ተአምር በገሊላ በምትገኘው በቃና ፈጸመ፤ ክብሩንም ገለጠ፤+ ደቀ መዛሙርቱም በእሱ አመኑ።

12 ከዚህ በኋላ እሱና እናቱ እንዲሁም ወንድሞቹና+ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ቅፍርናሆም+ ወረዱ፤ ሆኖም በዚያ ብዙ ቀን አልቆዩም።

13 በዚህ ጊዜ የአይሁዳውያን ፋሲካ*+ ቀርቦ ነበር፤ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። 14 በቤተ መቅደሱ ውስጥ ከብት፣ በግና ርግብ+ የሚሸጡ ሰዎችን እንዲሁም በዚያ የተቀመጡ ገንዘብ መንዛሪዎችን አገኘ። 15 በዚህ ጊዜ የገመድ ጅራፍ ሠርቶ ሁሉንም ከበጎቻቸውና ከከብቶቻቸው ጋር አስወጣ፤ የገንዘብ ለዋጮችንም ሳንቲሞች በተነ፤ ጠረጴዛዎቻቸውንም ገለባበጠ።+ 16 ርግብ ሻጮቹንም “እነዚህን ከዚህ አስወጡ! የአባቴን ቤት የንግድ ቤት* ማድረጋችሁ ይብቃ!” አላቸው።+ 17 ደቀ መዛሙርቱም “ለቤትህ ያለኝ ቅንዓት ይበላኛል”+ ተብሎ የተጻፈው ትዝ አላቸው።

18 በዚህ ጊዜ አይሁዳውያን መልሰው “እነዚህን ነገሮች ለማድረግ ሥልጣን እንዳለህ የሚያረጋግጥ ምን ምልክት ታሳየናለህ?” አሉት።+ 19 ኢየሱስም መልሶ “ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፤ እኔም በሦስት ቀን ውስጥ አነሳዋለሁ” አላቸው።+ 20 አይሁዳውያኑም “ቤተ መቅደሱን ለመገንባት 46 ዓመት ፈጅቷል፤ ታዲያ አንተ በሦስት ቀን ታነሳዋለህ?” አሉት። 21 እሱ ግን ቤተ መቅደስ ሲል ስለ ራሱ ሰውነት መናገሩ ነበር።+ 22 ከሙታን በተነሳ ጊዜም፣ ደቀ መዛሙርቱ ይህን ደጋግሞ ይናገር እንደነበር አስታወሱ፤+ ቅዱሳን መጻሕፍትንና ኢየሱስ የተናገረውንም ቃል አመኑ።

23 ይሁንና በፋሲካ በዓል፣ በኢየሩሳሌም በነበረበት ጊዜ ብዙ ሰዎች የሚያከናውናቸውን ተአምራዊ ምልክቶች ሲያዩ በስሙ አመኑ። 24 ኢየሱስ ግን ሁሉንም ያውቃቸው ስለነበር አይተማመንባቸውም ነበር፤ 25 እንዲሁም በሰው ውስጥ ያለውን ያውቅ ስለነበር ማንም ስለ ሰው እንዲመሠክርለት አላስፈለገውም።+

3 ከፈሪሳውያን ወገን፣ የአይሁዳውያን ገዢ የሆነ ኒቆዲሞስ+ የሚባል ሰው ነበር። 2 ይህ ሰው በማታ ወደ ኢየሱስ መጥቶ+ እንዲህ አለው፦ “ረቢ፣+ አንተ ከአምላክ ዘንድ የመጣህ አስተማሪ እንደሆንክ እናውቃለን፤ ምክንያቱም አምላክ ከእሱ ጋር ካልሆነ በቀር+ አንተ የምትፈጽማቸውን ተአምራዊ ምልክቶች መፈጸም የሚችል አንድም ሰው የለም።”+ 3 ኢየሱስም መልሶ “እውነት እውነት እልሃለሁ፣ አንድ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ*+ በቀር የአምላክን መንግሥት ሊያይ አይችልም”+ አለው። 4 ኒቆዲሞስም “ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ዳግም ወደ እናቱ ማህፀን ገብቶ ሊወለድ ይችላል?” አለው። 5 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “እውነት እውነት እልሃለሁ፣ ሰው ከውኃና+ ከመንፈስ+ ካልተወለደ በቀር ወደ አምላክ መንግሥት ሊገባ አይችልም። 6 ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፤ ከመንፈስ የተወለደ ደግሞ መንፈስ ነው። 7 ‘ዳግመኛ መወለድ አለባችሁ’ ስላልኩህ አትገረም። 8 ነፋስ ወደፈለገው አቅጣጫ ይነፍሳል፤ ድምፁንም ትሰማለህ፤ ሆኖም ከየት እንደሚመጣና ወዴት እንደሚሄድ አታውቅም። ከመንፈስ የተወለደም ሁሉ እንደዚሁ ነው።”+

9 ኒቆዲሞስም መልሶ “ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” አለው። 10 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “አንተ የእስራኤል አስተማሪ ሆነህ ሳለህ እነዚህን ነገሮች አታውቅም? 11 እውነት እውነት እልሃለሁ፣ እኛ የምናውቀውን እንናገራለን፤ ያየነውንም እንመሠክራለን፤ እናንተ ግን እኛ የምንሰጠውን ምሥክርነት አትቀበሉም። 12 ስለ ምድራዊ ነገሮች ነግሬአችሁ የማታምኑ ከሆነ ስለ ሰማያዊ ነገሮች ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ? 13 ደግሞም ከሰማይ ከወረደው+ ከሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም።+ 14 ሙሴ በምድረ በዳ እባቡን እንደሰቀለ፣+ የሰው ልጅም እንዲሁ ሊሰቀል ይገባዋል፤+ 15 ይኸውም በእሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው ነው።+

16 “አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ+ በልጁ የሚያምን* ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።+ 17 ምክንያቱም አምላክ ልጁን ወደ ዓለም የላከው በዓለም ላይ እንዲፈርድ ሳይሆን ዓለም በእሱ አማካኝነት እንዲድን ነው።+ 18 በእሱ የሚያምን ሁሉ አይፈረድበትም።+ በእሱ የማያምን ሁሉ ግን በአምላክ አንድያ ልጅ ስም ስለማያምን ቀድሞውኑም ተፈርዶበታል።+ 19 እንግዲህ የሚፈረድባቸው በዚህ መሠረት ነው፦ ብርሃን ወደ ዓለም መጣ፤+ ሰዎች ግን ሥራቸው ክፉ ስለነበረ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ወደዱ። 20 መጥፎ ነገር የሚያደርግ* ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፤ እንዲሁም ሥራው እንዳይጋለጥበት ወደ ብርሃን አይመጣም። 21 ትክክል የሆነውን የሚያደርግ ሁሉ ግን ያደረገው ነገር ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ የተከናወነ መሆኑ እንዲታይ ወደ ብርሃን ይመጣል።”+

22 ከዚህ በኋላ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ይሁዳ ገጠራማ ክልል ሄዱ፤ በዚያም ከእነሱ ጋር ለተወሰነ ጊዜ ቆየ፤ ያጠምቅም ነበር።+ 23 ይሁንና ዮሐንስም በሳሊም አቅራቢያ በሄኖን ብዙ ውኃ በመኖሩ+ በዚያ እያጠመቀ ነበር፤ ሰዎችም እየመጡ ይጠመቁ ነበር፤+ 24 በዚህ ጊዜ ዮሐንስ ገና እስር ቤት አልገባም ነበር።+

25 የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት የመንጻት ሥርዓትን በተመለከተ ከአንድ አይሁዳዊ ጋር ተከራከሩ። 26 ከዚያ በኋላ ወደ ዮሐንስ መጥተው “ረቢ፣ በዮርዳኖስ ማዶ ከአንተ ጋር የነበረውና ስለ እሱ የመሠከርክለት ሰው+ እያጠመቀ ነው፤ ሰዉም ሁሉ ወደ እሱ እየሄደ ነው” አሉት። 27 ዮሐንስም መልሶ እንዲህ አለ፦ “አንድ ሰው ከሰማይ ካልተሰጠው በቀር አንዳች ነገር ሊያገኝ አይችልም። 28 ‘እኔ ክርስቶስ አይደለሁም፤+ ከዚህ ይልቅ ከእሱ በፊት የተላክሁ ነኝ’+ እንዳልኩ እናንተ ራሳችሁ ትመሠክራላችሁ። 29 ሙሽራይቱ የሙሽራው ናት።+ ይሁን እንጂ የሙሽራው ጓደኛ በዚያ ቆሞ ሲሰማው በሙሽራው ድምፅ የተነሳ እጅግ ደስ ይለዋል። በመሆኑም የእኔ ደስታ ተፈጽሟል። 30 እሱ እየጨመረ መሄድ አለበት፤ እኔ ግን እየቀነስኩ መሄድ አለብኝ።”

31 ከላይ የሚመጣው+ ከሌሎች ሁሉ በላይ ነው። ከምድር የሆነው ምድራዊ ነው፤ የሚናገረውም ስለ ምድራዊ ነገሮች ነው። ከሰማይ የሚመጣው ከሌሎች ሁሉ በላይ ነው።+ 32 ስላየውና ስለሰማው ነገር ይመሠክራል፤+ ነገር ግን ምሥክርነቱን የሚቀበል ሰው የለም።+ 33 ምሥክርነቱን የተቀበለ ሰው ሁሉ አምላክ እውነተኛ መሆኑን አረጋግጧል።*+ 34 ምክንያቱም አምላክ የላከው የአምላክን ቃል ይናገራል፤+ አምላክ መንፈሱን ቆጥቦ* አይሰጥምና። 35 አብ ወልድን ይወዳል፤+ ደግሞም ሁሉንም ነገር በእጁ ሰጥቶታል።+ 36 በወልድ የሚያምን* የዘላለም ሕይወት አለው፤+ ወልድን የማይታዘዝ ግን የአምላክ ቁጣ በላዩ ይኖራል+ እንጂ ሕይወትን አያይም።+

4 ጌታ፣ ከዮሐንስ ይበልጥ ብዙ ደቀ መዛሙርት እያፈራና እያጠመቀ+ መሆኑን ፈሪሳውያን እንደሰሙ ባወቀ ጊዜ፣ 2 (እርግጥ ደቀ መዛሙርቱ እንጂ ኢየሱስ ራሱ አላጠመቀም) 3 ይሁዳን ለቆ እንደገና ወደ ገሊላ ሄደ። 4 ሆኖም በሰማርያ በኩል ማለፍ ነበረበት። 5 ስለሆነም ያዕቆብ ለልጁ ለዮሴፍ በሰጠው መሬት አጠገብ+ ወዳለችው ሲካር ወደተባለች የሰማርያ ከተማ መጣ። 6 ደግሞም በዚያ የያዕቆብ የውኃ ጉድጓድ ነበረ።+ ኢየሱስም ከጉዞው የተነሳ ደክሞት ስለነበር በውኃ ጉድጓዱ* አጠገብ ተቀመጠ። ጊዜው ስድስት ሰዓት ገደማ ነበር።

7 አንዲት የሰማርያ ሴት ውኃ ልትቀዳ መጣች። ኢየሱስም “እባክሽ፣ የምጠጣው ውኃ ስጪኝ” አላት። 8 (ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ሊገዙ ወደ ከተማዋ ሄደው ነበር።) 9 ሳምራዊቷም “አንተ አይሁዳዊ ሆነህ ሳለ እኔን ሳምራዊቷን እንዴት የምጠጣው ውኃ ስጪኝ ትለኛለህ?” አለችው። (ይህን ያለችው አይሁዳውያን ከሳምራውያን ጋር ምንም ግንኙነት ስላልነበራቸው ነው።)+ 10 ኢየሱስም መልሶ “የአምላክን ነፃ ስጦታ+ ብታውቂና ‘የምጠጣው ውኃ ስጪኝ’ የሚልሽ ማን መሆኑን ብትረጂ ኖሮ አንቺ ራስሽ ትጠይቂው ነበር፤ እሱም ሕያው ውኃ ይሰጥሽ ነበር”+ አላት። 11 እሷም እንዲህ አለችው፦ “ጌታዬ፣ አንተ ውኃ መቅጃ እንኳ የለህም፤ ጉድጓዱ ደግሞ ጥልቅ ነው። ታዲያ ይህን ሕያው ውኃ ከየት ታገኛለህ? 12 አንተ ይህን የውኃ ጉድጓድ ከሰጠን እንዲሁም ከልጆቹና ከከብቶቹ ጋር ከዚህ ጉድጓድ ከጠጣው ከአባታችን ከያዕቆብ ትበልጣለህ?” 13 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላት፦ “ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ሁሉ እንደገና ይጠማል። 14 እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ፈጽሞ አይጠማም፤+ ከዚህ ይልቅ እኔ የምሰጠው ውኃ በውስጡ የሚፈልቅ የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝ የውኃ ምንጭ ይሆናል።”+ 15 ሴትየዋም “ጌታዬ፣ እንዳልጠማም ሆነ ውኃ ለመቅዳት ወደዚህ ቦታ እንዳልመላለስ ይህን ውኃ ስጠኝ” አለችው።

16 እሱም “ሂጂና ባልሽን ጠርተሽ ተመልሰሽ ነይ” አላት። 17 ሴትየዋም “ባል የለኝም” ብላ መለሰችለት። ኢየሱስም እንዲህ አላት፦ “‘ባል የለኝም’ ማለትሽ ትክክል ነው። 18 ምክንያቱም አምስት ባሎች ነበሩሽ፤ አሁን አብሮሽ ያለው ሰው ደግሞ ባልሽ አይደለም። ስለዚህ የተናገርሽው እውነት ነው።” 19 ሴትየዋም እንዲህ አለችው፦ “ጌታዬ፣ አንተ ነቢይ እንደሆንክ አሁን ተረዳሁ።+ 20 አባቶቻችን በዚህ ተራራ ላይ አምልኳቸውን ያካሂዱ ነበር፤ እናንተ አይሁዳውያን ግን ሰዎች ማምለክ ያለባቸው በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ።”+ 21 ኢየሱስም እንዲህ አላት፦ “አንቺ ሴት፣ እመኚኝ፤ በዚህ ተራራም ሆነ በኢየሩሳሌም አብን የማታመልኩበት ሰዓት ይመጣል። 22 እናንተ የማታውቁትን ታመልካላችሁ፤+ እኛ ግን መዳን የሚጀምረው ከአይሁዳውያን ስለሆነ የምናውቀውን እናመልካለን።+ 23 ይሁንና እውነተኛ አምላኪዎች አብን በመንፈስና በእውነት የሚያመልኩበት ሰዓት ይመጣል፤ ያም ሰዓት አሁን ነው፤ ምክንያቱም አብ እንዲያመልኩት የሚፈልገው እንዲህ ያሉ ሰዎችን ነው።+ 24 አምላክ መንፈስ ነው፤+ የሚያመልኩትም በመንፈስና በእውነት ሊያመልኩት ይገባል።”+ 25 ሴትየዋም “ክርስቶስ የተባለ መሲሕ እንደሚመጣ አውቃለሁ። እሱ ሲመጣ ሁሉንም ነገር ግልጥልጥ አድርጎ ይነግረናል” አለችው። 26 ኢየሱስም “እያነጋገርኩሽ ያለሁት እኔ፣ እሱ ነኝ” አላት።+

27 በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ መጡ፤ ከሴት ጋር ሲነጋገር አይተውም ተደነቁ። ይሁን እንጂ “ምን ፈልገህ ነው?” ወይም “ከእሷ ጋር የምትነጋገረው ለምንድን ነው?” ያለው ማንም አልነበረም። 28 ሴትየዋም እንስራዋን ትታ ወደ ከተማዋ በመሄድ ሰዎቹን እንዲህ አለቻቸው፦ 29 “ያደረግኩትን ሁሉ የነገረኝን ሰው መጥታችሁ እዩ። ይህ ሰው ክርስቶስ ይሆን እንዴ?” 30 እነሱም ከከተማዋ ወጥተው ወደ እሱ መጡ።

31 በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ “ረቢ፣+ ብላ እንጂ” እያሉ ጎተጎቱት። 32 እሱ ግን “እናንተ የማታውቁት የምበላው ምግብ አለኝ” አላቸው። 33 ደቀ መዛሙርቱም እርስ በርሳቸው “ምግብ ያመጣለት ይኖር ይሆን እንዴ?” ተባባሉ። 34 ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “የእኔ ምግብ የላከኝን ፈቃድ ማድረግና+ እንዳከናውነው የሰጠኝን ሥራ መፈጸም ነው።+ 35 እናንተ መከር ሊገባ ገና አራት ወር ይቀረዋል ትሉ የለም? እነሆ እላችኋለሁ፣ ዓይናችሁን ወደ ማሳው አቅንታችሁ አዝመራው እንደነጣ ተመልከቱ።+ 36 አሁንም እንኳ አጫጁ ደሞዙን እየተቀበለና ለዘላለም ሕይወት ፍሬ እየሰበሰበ ነው፤ ስለዚህ ዘሪውም ሆነ አጫጁ በአንድነት ደስ ይላቸዋል።+ 37 ከዚህም የተነሳ ‘አንዱ ይዘራል፤ ሌላኛውም ያጭዳል’ የሚለው አባባል እውነት ነው። 38 እኔም ያልደከማችሁበትን እንድታጭዱ ላክኋችሁ። ሌሎች በደከሙበት እናንተ የድካማቸው ፍሬ ተካፋዮች ሆናችሁ።”

39 ሴትየዋ “ያደረግኩትን ሁሉ ነገረኝ”+ ብላ ስለመሠከረች ከዚያች ከተማ ብዙ ሳምራውያን በእሱ አመኑ። 40 ሳምራውያኑም ወደ እሱ በመጡ ጊዜ አብሯቸው እንዲቆይ ለመኑት፤ እሱም በዚያ ሁለት ቀን ቆየ። 41 በመሆኑም ሌሎች ብዙ ሰዎች ከተናገረው ቃል የተነሳ አመኑ፤ 42 ሴትየዋንም “ከእንግዲህ የምናምነው አንቺ ስለነገርሽን ብቻ አይደለም፤ ምክንያቱም እኛ ራሳችን ሰምተናል፤ እንዲሁም ይህ ሰው በእርግጥ የዓለም አዳኝ+ እንደሆነ አውቀናል” አሏት።

43 ከሁለት ቀናት በኋላ ከዚያ ተነስቶ ወደ ገሊላ ሄደ። 44 ይሁንና ኢየሱስ ራሱ፣ ነቢይ በገዛ አገሩ እንደማይከበር+ ተናግሮ ነበር። 45 ገሊላ በደረሰ ጊዜም የገሊላ ሰዎች በጥሩ ሁኔታ ተቀበሉት፤ ምክንያቱም በኢየሩሳሌም በበዓሉ ላይ ተገኝተው+ በዚያ ያከናወናቸውን ነገሮች ሁሉ አይተው ነበር።+

46 ከዚያም ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ ወደለወጠባት በገሊላ ወደምትገኘው ወደ ቃና በድጋሚ መጣ።+ በዚህ ጊዜ በቅፍርናሆም፣ ልጁ የታመመበት የቤተ መንግሥት ባለሥልጣን የሆነ አንድ ሰው ነበር። 47 ይህ ሰው ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ መምጣቱን ሲሰማ ወደ እሱ ሄደና ወደ ቅፍርናሆም ወርዶ በሞት አፋፍ ላይ ያለውን ልጁን እንዲፈውስለት ለመነው። 48 ኢየሱስ ግን “መቼም እናንተ ተአምራዊ ምልክቶችና ድንቅ ነገሮች ካላያችሁ ፈጽሞ አታምኑም” አለው።+ 49 የቤተ መንግሥት ባለሥልጣኑም “ጌታዬ፣ ልጄ ከመሞቱ በፊት እባክህ በቶሎ ድረስ” አለው። 50 ኢየሱስም “ሂድ፤ ልጅህ ድኗል” አለው።+ ሰውየውም ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አምኖ ሄደ። 51 ሆኖም ሰውየው ወደዚያ እየወረደ ሳለ ባሪያዎቹ አገኙትና ልጁ በሕይወት እንዳለ* ነገሩት። 52 እሱም ልጁ ስንት ሰዓት ላይ እንደተሻለው ጠየቃቸው። እነሱም “ትናንት ሰባት ሰዓት ላይ ትኩሳቱ ለቀቀው” ብለው መለሱለት። 53  በዚህ ጊዜ አባትየው ልጁ የዳነው ልክ ኢየሱስ “ልጅህ ድኗል” ባለው ሰዓት ላይ መሆኑን አወቀ።+ እሱና መላው ቤተሰቡም አማኞች ሆኑ። 54 ይህም ደግሞ ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ ሲመጣ ያከናወነው ሁለተኛው ተአምራዊ ምልክት ነው።+

5 ከዚህ በኋላ የአይሁዳውያን በዓል+ ስለነበረ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። 2 በኢየሩሳሌም በበጎች በር+ አጠገብ አምስት ባለ መጠለያ መተላለፊያዎች ያሉት በዕብራይስጥ ቤተዛታ ተብሎ የሚጠራ አንድ የውኃ ገንዳ ነበር። 3 በእነዚህ መተላለፊያዎች ውስጥ ብዙ ሕመምተኞች፣ ዓይነ ስውሮች፣ አንካሶችና ሽባዎች* ይተኙ ነበር። 4 *—— 5 በዚያም ለ38 ዓመት ሕመምተኛ ሆኖ የኖረ አንድ ሰው ነበር። 6 ኢየሱስ ይህን ሰው በዚያ ተኝቶ አየውና ለረጅም ጊዜ ሕመምተኛ ሆኖ እንደኖረ አውቆ “መዳን ትፈልጋለህ?”+ አለው። 7 ሕመምተኛውም “ጌታዬ፣ ውኃው በሚናወጥበት ጊዜ ገንዳው ውስጥ የሚያስገባኝ ሰው የለኝም፤ ወደ ገንዳው ስሄድ ደግሞ ሌላው ቀድሞኝ ይገባል” ሲል መለሰለት። 8 ኢየሱስም “ተነስ! ምንጣፍህን* ተሸክመህ ሂድ” አለው።+ 9 ሰውየውም ወዲያውኑ ተፈወሰ፤ ምንጣፉንም* አንስቶ መሄድ ጀመረ።

ቀኑም ሰንበት ነበር። 10 በመሆኑም አይሁዳውያን የተፈወሰውን ሰው “ሰንበት እኮ ነው፤ ምንጣፍህን* እንድትሸከም ሕጉ አይፈቅድልህም” አሉት።+ 11 እሱ ግን “የፈወሰኝ ሰው ራሱ ‘ምንጣፍህን* ተሸክመህ ሂድ’ ብሎኛል” ሲል መለሰላቸው። 12 እነሱም “‘ምንጣፍህን* ተሸክመህ ሂድ’ ያለህ ሰው ማን ነው?” ሲሉ ጠየቁት። 13 ሆኖም ኢየሱስ ከቦታው ዞር ብሎ ከሕዝቡ ጋር ተቀላቅሎ ስለነበር ሰውየው የፈወሰውን ሰው ማንነት ማወቅ አልቻለም።

14 ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ሰውየውን በቤተ መቅደሱ ውስጥ አገኘውና “አሁን ደህና ሆነሃል። የባሰ ነገር እንዳይደርስብህ ከእንግዲህ ኃጢአት አትሥራ” አለው። 15 ሰውየውም ሄዶ የፈወሰው ኢየሱስ መሆኑን ለአይሁዳውያኑ ነገራቸው። 16 ከዚህም የተነሳ አይሁዳውያኑ በኢየሱስ ላይ ስደት ያደርሱበት ጀመር፤ ይህን ያደረጉት በሰንበት ቀን እነዚህን ነገሮች ይፈጽም ስለነበረ ነው። 17 እሱ ግን “አባቴ እስካሁን እየሠራ ነው፤ እኔም እሠራለሁ”+ ሲል መለሰላቸው። 18 ከዚህም የተነሳ አይሁዳውያኑ ሰንበትን ስለጣሰ ብቻ ሳይሆን አምላክን የገዛ አባቱ እንደሆነ አድርጎ በመጥራት+ ራሱን ከአምላክ ጋር እኩል ስላደረገ+ እሱን ለመግደል ይበልጥ ተነሳሱ።

19 ስለሆነም ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ወልድ፣ አብ ሲያደርግ ያየውን ብቻ እንጂ በራሱ ተነሳስቶ አንድም ነገር ሊያደርግ አይችልም።+ አብ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድም በተመሳሳይ መንገድ ያንኑ ያደርጋል። 20 ምክንያቱም አብ ወልድን ይወደዋል፤+ እንዲሁም እሱ ራሱ የሚያደርገውን ነገር ሁሉ ያሳየዋል፤ እናንተም ትደነቁ ዘንድ ከእነዚህም የሚበልጥ ሥራ ያሳየዋል።+ 21 አብ ሙታንን እንደሚያስነሳቸውና ሕያው እንደሚያደርጋቸው+ ሁሉ ወልድም እንዲሁ የፈለገውን ሰው ሕያው ያደርጋል።+ 22 አብ በማንም ላይ አይፈርድምና፤ ከዚህ ይልቅ የመፍረዱን ሥልጣን ሁሉ ለወልድ ሰጥቶታል፤+ 23 ይህን ያደረገውም ሁሉም አብን እንደሚያከብሩ ሁሉ ወልድንም እንዲያከብሩ ነው። ወልድን የማያከብር ሁሉ እሱን የላከውን አብንም አያከብርም።+ 24 እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ቃሌን የሚሰማና የላከኝን የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት አለው፤+ ወደ ፍርድም አይመጣም፤ ከዚህ ይልቅ ከሞት ወደ ሕይወት ተሻግሯል።+

25 “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ሙታን የአምላክን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ ያም ሰዓት አሁን ነው፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ። 26 አብ በራሱ ሕይወት እንዳለው* ሁሉ፣+ ወልድም በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታልና።+ 27 እሱ የሰው ልጅ+ ስለሆነ የመፍረድ ሥልጣን ሰጥቶታል።+ 28 በዚህ አትደነቁ፤ በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣልና፤+ 29 መልካም የሠሩ ለሕይወት ትንሣኤ፣ ክፉ የሠሩ* ደግሞ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉ።+ 30 በራሴ ተነሳስቼ አንድም ነገር ማድረግ አልችልም። እንደሰማሁ እፈርዳለሁ፤ የራሴን ፈቃድ ሳይሆን የላከኝን ፈቃድ+ መፈጸም ስለምፈልግ የምፈርደው የጽድቅ ፍርድ ነው።+

31 “እኔ ብቻ ስለ ራሴ ብመሠክር ምሥክርነቴ እውነት አይደለም።+ 32 ስለ እኔ የሚመሠክር ሌላ አለ፤ ደግሞም እሱ ስለ እኔ የሚሰጠው ምሥክርነት እውነት እንደሆነ አውቃለሁ።+ 33 ወደ ዮሐንስ ሰዎች ልካችሁ ነበር፤ እሱም ለእውነት መሥክሯል።+ 34 ይሁን እንጂ እኔ የሰው ምሥክርነት አያስፈልገኝም፤ ይህን የምናገረው ግን እናንተ እንድትድኑ ነው። 35 ያ ሰው የሚነድና የሚያበራ መብራት ነበር፤ እናንተም ለጥቂት ጊዜ በእሱ ብርሃን እጅግ ለመደሰት ፈቃደኞች ነበራችሁ።+ 36 እኔ ግን ከዮሐንስ የበለጠ ምሥክር አለኝ፤ ምክንያቱም አባቴ እንዳከናውነው የሰጠኝ ሥራ ማለትም እየሠራሁት ያለው ይህ ሥራ አብ እንደላከኝ ይመሠክራል።+ 37 የላከኝ አብም ራሱ ስለ እኔ መሥክሯል።+ እናንተ መቼም ቢሆን ድምፁን አልሰማችሁም፤ መልኩንም አላያችሁም፤+ 38 እሱ የላከውንም ስለማታምኑ ቃሉ በልባችሁ ውስጥ አይኖርም።

39 “እናንተ በቅዱሳን መጻሕፍት የዘላለም ሕይወት የምታገኙ ስለሚመስላችሁ እነሱን ትመረምራላችሁ፤+ እነዚሁ መጻሕፍት ስለ እኔ የሚመሠክሩ ናቸው።+ 40 ሆኖም ሕይወት እንድታገኙ ወደ እኔ መምጣት አትፈልጉም።+ 41 እኔ ከሰው ክብር መቀበል አልፈልግም፤ 42 ይሁንና እናንተ የአምላክ ፍቅር በውስጣችሁ እንደሌለ በሚገባ አውቃለሁ። 43 እኔ በአባቴ ስም መጣሁ፤ እናንተ ግን አልተቀበላችሁኝም። ሌላው ግን በራሱ ስም ቢመጣ ትቀበሉታላችሁ። 44 እናንተ እርስ በርሳችሁ ክብር የምትሰጣጡና ከአንዱ አምላክ የሚገኘውን ክብር የማትፈልጉ ሆናችሁ ሳላችሁ እንዴት ልታምኑ ትችላላችሁ?+ 45 እኔ በአብ ፊት የምከሳችሁ አይምሰላችሁ፤ የሚከሳችሁ ሌላ አለ፤ እሱም ተስፋ የጣላችሁበት ሙሴ ነው።+ 46 ደግሞም ሙሴን ብታምኑት ኖሮ እኔንም ታምኑኝ ነበር፤ እሱ ስለ እኔ ጽፏልና።+ 47 ሆኖም እሱ የጻፈውን ካላመናችሁ እኔ የምናገረውን እንዴት ታምናላችሁ?”

6 ከዚህ በኋላ ኢየሱስ የገሊላን ማለትም የጥብርያዶስን ባሕር* አቋርጦ ወደ ማዶ ተሻገረ።+ 2 ብዙ ሰዎችም ኢየሱስ የታመሙትን በመፈወስ+ የፈጸማቸውን ተአምራዊ ምልክቶች ስላዩ ተከተሉት።+ 3 ስለዚህ ኢየሱስ ወደ ተራራ ወጥቶ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በዚያ ተቀመጠ። 4 በዚያን ጊዜ የአይሁዳውያን በዓል የሆነው ፋሲካ+ ተቃርቦ ነበር። 5 ኢየሱስም ቀና ብሎ ብዙ ሕዝብ ወደ እሱ እየመጣ እንዳለ ሲመለከት ፊልጶስን “እነዚህ ሰዎች የሚበሉት ዳቦ ከየት ብንገዛ ይሻላል?” አለው።+ 6 ሆኖም ይህን ያለው ሊፈትነው ብሎ እንጂ ለማድረግ ያሰበውን ያውቅ ነበር። 7 ፊልጶስም “እያንዳንዱ ሰው ትንሽ ትንሽ እንዲደርሰው ለማድረግ እንኳ የ200 ዲናር* ዳቦ አይበቃም” ሲል መለሰለት። 8 ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ የሆነው የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ እንዲህ አለው፦ 9 “አምስት የገብስ ዳቦና ሁለት ትናንሽ ዓሣ የያዘ አንድ ትንሽ ልጅ እዚህ አለ። ይህ ግን ለዚህ ሁሉ ሕዝብ እንዴት ይበቃል?”+

10 ኢየሱስም “ሰዎቹ እንዲቀመጡ አድርጉ” አለ። በስፍራው ብዙ ሣር ስለነበር ሰዎቹ በዚያ ተቀመጡ፤ ወንዶቹም 5,000 ያህል ነበሩ።+ 11 ኢየሱስ ዳቦዎቹን ወስዶ ካመሰገነ በኋላ በዚያ ለተቀመጡት ሰዎች አከፋፈለ፤ ትናንሾቹን ዓሣዎችም ልክ እንደዚሁ አደለ፤ እነሱም የሚፈልጉትን ያህል ወሰዱ። 12 በልተው ከጠገቡም በኋላ ደቀ መዛሙርቱን “ምንም እንዳይባክን የተረፈውን ቁርስራሽ ሁሉ ሰብስቡ” አላቸው። 13 ስለዚህ ከአምስቱ የገብስ ዳቦ ሰዎቹ በልተው የተረፈውን ቁርስራሽ ሰበሰቡ፤ ቁርስራሹም 12 ቅርጫት ሙሉ ሆነ።

14 ሰዎቹም ኢየሱስ የፈጸመውን ተአምራዊ ምልክት ባዩ ጊዜ “ወደ ዓለም እንደሚመጣ ትንቢት የተነገረለት ነቢይ በእርግጥ ይህ ነው” አሉ።+ 15 ከዚያም ኢየሱስ ሰዎቹ መጥተው ሊይዙትና ሊያነግሡት እንዳሰቡ ስላወቀ ብቻውን ዳግመኛ ወደ ተራራ ገለል አለ።+

16 በመሸ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ባሕሩ ወረዱ፤+ 17 በጀልባም ተሳፍረው ባሕሩን በማቋረጥ ወደ ቅፍርናሆም ለመሻገር ተነሱ። በዚያን ሰዓት ጨልሞ የነበረ ቢሆንም ኢየሱስ ገና ወደ እነሱ አልመጣም ነበር።+ 18 በተጨማሪም ኃይለኛ ነፋስ ይነፍስ ስለነበረ ባሕሩ ይናወጥ ጀመር።+ 19 ይሁን እንጂ አምስት ወይም ስድስት ኪሎ ሜትር ገደማ* እንደቀዘፉ ኢየሱስ በባሕሩ ላይ እየተራመደ ወደ ጀልባዋ ሲቃረብ ተመልክተው ፈሩ። 20 እሱ ግን “እኔ ነኝ፤ አትፍሩ!” አላቸው።+ 21 ከዚያም ወዲያው ጀልባዋ ላይ አሳፈሩት፤ ጀልባዋም ሊሄዱ ወዳሰቡበት ቦታ በፍጥነት ደረሰች።+

22 በማግስቱም፣ በባሕሩ ማዶ የቀሩት ሰዎች በዚያ ምንም ጀልባ እንዳልነበረ አስተዋሉ። አንዲት ትንሽ ጀልባ በዚያ ነበረች፤ ኢየሱስ ግን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በዚህች ጀልባ አልተሳፈረም። ምክንያቱም ደቀ መዛሙርቱ ብቻቸውን ሄደው ነበር። 23 ሆኖም ከጥብርያዶስ የተነሱ ጀልባዎች፣ ሕዝቡ ጌታ የባረከውን ዳቦ ወደበሉበት አካባቢ መጡ። 24 ሕዝቡ ኢየሱስም ሆነ ደቀ መዛሙርቱ በዚያ አለመኖራቸውን ባወቁ ጊዜ በጀልባዎቻቸው ተሳፍረው ኢየሱስን ፍለጋ ወደ ቅፍርናሆም መጡ።

25 ከባሕሩ ማዶ ባገኙትም ጊዜ “ረቢ፣+ መቼ ወደዚህ መጣህ?” አሉት። 26 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ የምትፈልጉኝ ተአምራዊ ምልክት ስላያችሁ ሳይሆን ዳቦ ስለበላችሁና ስለጠገባችሁ ነው።+ 27 ለሚጠፋ ምግብ ሳይሆን የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ዘላቂ ለሆነውና የዘላለም ሕይወት+ ለሚያስገኘው ምግብ ሥሩ፤ ምክንያቱም አብ ይኸውም አምላክ ራሱ እሱን እንደተቀበለው አሳይቷል።”*+

28 እነሱም “ታዲያ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለውን ሥራ ለመሥራት ምን ብናደርግ ይሻላል?” አሉት። 29 ኢየሱስም መልሶ “አምላክ የሚቀበለው ሥራማ እሱ በላከው ሰው ማመን ነው” አላቸው።+ 30 በዚህ ጊዜ እንዲህ አሉት፦ “ታዲያ አይተን እንድናምንብህ ምን ተአምራዊ ምልክት ትፈጽማለህ?+ ምን ነገርስ ትሠራለህ? 31 ‘ይበሉ ዘንድ ከሰማይ ምግብ ሰጣቸው’+ ተብሎ በተጻፈው መሠረት አባቶቻችን በምድረ በዳ መና በሉ።”+ 32 ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ከሰማይ የወረደውን ምግብ የሰጣችሁ ሙሴ አይደለም፤ አባቴ ግን እውነተኛውን ምግብ ከሰማይ ይሰጣችኋል። 33 ምክንያቱም አምላክ የሚሰጠው ምግብ ከሰማይ የሚወርድና ለዓለም ሕይወት የሚያስገኝ ነው።” 34 እነሱም “ጌታ ሆይ፣ ይህን ምግብ ሁልጊዜ ስጠን” አሉት።

35 ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “ሕይወት የሚያስገኘው ምግብ እኔ ነኝ። ወደ እኔ የሚመጣ ሁሉ ፈጽሞ አይራብም፤ እንዲሁም በእኔ የሚያምን ሁሉ ፈጽሞ አይጠማም።+ 36 ነገር ግን “አይታችሁኝም እንኳ አታምኑም” ብያችሁ ነበር።+ 37 አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፤ ወደ እኔ የሚመጣውንም ፈጽሞ አላባርረውም፤+ 38 ከሰማይ የመጣሁት+ የራሴን ፈቃድ ሳይሆን የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ነውና።+ 39 የላከኝም ፈቃድ፣ ከሰጠኝ ሁሉ አንዱም እንኳ እንዳይጠፋብኝና በመጨረሻው ቀን ሁሉንም ከሞት እንዳስነሳቸው+ ነው። 40 ምክንያቱም የአባቴ ፈቃድ ወልድን የሚያውቅና በእሱ የሚያምን* ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው ነው፤+ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሳዋለሁ።”+

41 ከዚያም አይሁዳውያን “ከሰማይ የወረደው ምግብ እኔ ነኝ”+ በማለቱ በኢየሱስ ላይ ያጉረመርሙ ጀመር። 42 ደግሞም “ይህ የዮሴፍ ልጅ ኢየሱስ አይደለም? አባቱንና እናቱንስ እናውቃቸው የለም እንዴ?+ ታዲያ እንዴት ‘ከሰማይ ወረድኩ’ ይላል?” አሉ። 43 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “እርስ በርሳችሁ አታጉረምርሙ። 44 የላከኝ አብ ካልሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል ሰው የለም፤+ እኔም በመጨረሻው ቀን ከሞት አስነሳዋለሁ።+ 45 ነቢያት በጻፏቸው ጽሑፎች ላይ ‘ሁሉም ከይሖዋ* የተማሩ ይሆናሉ’+ ተብሎ ተጽፏል። ከአብ የሰማና የተማረ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል። 46 ከአምላክ ዘንድ ከመጣው በስተቀር አብን ያየ አንድም ሰው የለም፤+ እሱ አብን አይቶታል።+ 47 እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት አለው።+

48 “ሕይወት የሚያስገኘው ምግብ እኔ ነኝ።+ 49 አባቶቻችሁ በምድረ በዳ መና በሉ፤ ይሁን እንጂ ሞቱ።+ 50 ከሰማይ የወረደውን ምግብ የሚበላ ሁሉ ግን አይሞትም። 51 ከሰማይ የወረደው ሕያው ምግብ እኔ ነኝ። ከዚህ ምግብ የሚበላ ሁሉ ለዘላለም ይኖራል፤ ምግቡ ደግሞ ለዓለም ሕይወት ስል የምሰጠው ሥጋዬ ነው።”+

52 አይሁዳውያንም “ይህ ሰው እንዴት ሥጋውን እንድንበላ ሊሰጠን ይችላል?” በማለት እርስ በርሳቸው ይከራከሩ ጀመር። 53  በመሆኑም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁና ደሙን ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም።+ 54 ሥጋዬን የሚበላና ደሜን የሚጠጣ ሁሉ የዘላለም ሕይወት አለው፤ በመጨረሻውም ቀን ከሞት አስነሳዋለሁ፤+ 55 ሥጋዬ እውነተኛ ምግብ፣ ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና። 56 ሥጋዬን የሚበላና ደሜን የሚጠጣ ሁሉ ከእኔ ጋር አንድነት ይኖረዋል፤ እኔም ከእሱ ጋር አንድነት ይኖረኛል።+ 57  ሕያው የሆነው አብ እንደላከኝና እኔም ከእሱ የተነሳ በሕይወት እንደምኖር ሁሉ የእኔን ሥጋ የሚበላም ከእኔ የተነሳ በሕይወት ይኖራል።+ 58 ከሰማይ የወረደው ምግብ ይህ ነው። ይህም አባቶቻችሁ በበሉበት ጊዜ እንደነበረው አይደለም፤ እነሱ ቢበሉም እንኳ ሞተዋል። ይህን ምግብ የሚበላ ሁሉ ግን ለዘላለም ይኖራል።”+ 59 ይህን የተናገረው በቅፍርናሆም በምኩራብ* እያስተማረ ሳለ ነበር።

60 ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎቹ ይህን ሲሰሙ “ይህ የሚሰቀጥጥ ንግግር ነው፤ ማን ሊሰማው ይችላል?” አሉ። 61 ኢየሱስ ግን ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ ጉዳይ እያጉረመረሙ እንዳሉ ስለገባው እንዲህ አላቸው፦ “ይህ ያሰናክላችኋል? 62 ታዲያ የሰው ልጅ ቀድሞ ወደነበረበት ሲወጣ ብታዩ ምን ልትሉ ነው?+ 63 ሕይወትን የሚሰጠው መንፈስ ነው፤+ ሥጋ ምንም አይጠቅምም። እኔ የነገርኳችሁ ቃል መንፈስም ሕይወትም ነው።+ 64 ነገር ግን ከእናንተ መካከል የማያምኑ አንዳንዶች አሉ።” ኢየሱስ ይህን ያለው የማያምኑት እነማን እንደሆኑና ማን አሳልፎ እንደሚሰጠው ከመጀመሪያው ያውቅ ስለነበረ ነው።+ 65 ከዚያም “አብ ካልፈቀደለት በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም ያልኳችሁ ለዚህ ነው” አላቸው።+

66 ከዚህም የተነሳ ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎቹ ትተውት ወደነበረው ነገር ተመለሱ፤+ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም እሱን መከተላቸውን አቆሙ። 67 በዚህ ጊዜ ኢየሱስ አሥራ ሁለቱን “እናንተም መሄድ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። 68 ስምዖን ጴጥሮስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ጌታ ሆይ፣ ወደ ማን እንሄዳለን?+ አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ።+ 69 አንተ የአምላክ ቅዱስ አገልጋይ እንደሆንክ አምነናል፤ ደግሞም አውቀናል።”+ 70 ኢየሱስም መልሶ “አሥራ ሁለታችሁንም የመረጥኳችሁ እኔ አይደለሁም?+ ይሁንና ከመካከላችሁ አንዱ ስም አጥፊ* ነው” አላቸው።+ 71 ይህን ሲል የአስቆሮቱ ስምዖን ልጅ ስለሆነው ስለ ይሁዳ መናገሩ ነበር፤ ምክንያቱም ይሁዳ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ቢሆንም አሳልፎ የሚሰጠው እሱ ነበር።+

7 ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በገሊላ መዘዋወሩን* ቀጠለ፤ ምክንያቱም አይሁዳውያን ሊገድሉት ይፈልጉ+ ስለነበር በይሁዳ ምድር መዘዋወር አልፈለገም። 2 ይሁን እንጂ የአይሁዳውያን በዓል የሆነው የዳስ በዓል+ ተቃርቦ ነበር። 3 ስለዚህ ወንድሞቹ+ እንዲህ አሉት፦ “ደቀ መዛሙርትህም የምታከናውነውን ሥራ ማየት እንዲችሉ ከዚህ ተነስተህ ወደ ይሁዳ ሂድ። 4 በይፋ እንዲታወቅ እየፈለገ በስውር የሚሠራ ሰው የለምና። እነዚህን ነገሮች የምትሠራ ከሆነ ራስህን ለዓለም ግለጥ።” 5 ወንድሞቹም ቢሆኑ አላመኑበትም ነበር።+ 6 ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “ጊዜዬ ገና አልደረሰም፤+ ለእናንተ ግን ማንኛውም ጊዜ ተስማሚ ነው። 7 ዓለም እናንተን የሚጠላበት ምንም ምክንያት የለውም፤ እኔ ግን ሥራው ክፉ እንደሆነ ስለምመሠክርበት ይጠላኛል።+ 8 እናንተ ወደ በዓሉ ሂዱ፤ እኔ ግን ገና ጊዜዬ ስላልደረሰ+ ወደ በዓሉ አልሄድም።” 9 ይህን ከነገራቸው በኋላ በገሊላ ቆየ።

10 ሆኖም ወንድሞቹ ወደ በዓሉ ከሄዱ በኋላ እሱም በግልጽ ሳይሆን በስውር ወደዚያው ሄደ። 11 በበዓሉም ላይ አይሁዳውያን “ያ ሰው የት አለ?” እያሉ ይፈልጉት ጀመር። 12 በሕዝቡም መካከል ስለ እሱ ብዙ ጉምጉምታ ነበር። አንዳንዶች “እሱ ጥሩ ሰው ነው” ሲሉ ሌሎች ደግሞ “አይደለም። እሱ ሕዝቡን ያሳስታል” ይሉ ነበር።+ 13 እርግጥ አይሁዳውያንን* ይፈሩ ስለነበረ ስለ እሱ በግልጽ የሚናገር ሰው አልነበረም።+

14 በበዓሉም አጋማሽ ላይ ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደሱ ሄዶ ያስተምር ጀመር። 15 አይሁዳውያንም በጣም ተገርመው “ይህ ሰው ትምህርት ቤት* ገብቶ ሳይማር ቅዱሳን መጻሕፍትን* እንዴት እንዲህ ሊያውቅ ቻለ?” አሉ።+ 16 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “የማስተምረው ትምህርት የራሴ ሳይሆን ከላከኝ የመጣ ነው።+ 17 ማንም የእሱን ፈቃድ ማድረግ የሚፈልግ ከሆነ ይህ ትምህርት ከአምላክ የመጣ+ ይሁን ከራሴ ለይቶ ያውቃል። 18 ከራሱ አመንጭቶ የሚናገር ሁሉ ራሱ እንዲከበር ይፈልጋል፤ የላከው እንዲከበር+ የሚፈልግ ሁሉ ግን እሱ እውነተኛ ነው፤ በእሱም ዘንድ ዓመፅ የለም። 19 ሕጉን የሰጣችሁ ሙሴ አይደለም?+ ሆኖም አንዳችሁም ሕጉን አትታዘዙም። እኔን ለመግደል የምትፈልጉት ለምንድን ነው?”+ 20 ሕዝቡም “አንተ ጋኔን አለብህ። ሊገድልህ የፈለገው ደግሞ ማን ነው?” ብለው መለሱለት። 21 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “አንድ ነገር ስለሠራሁ ሁላችሁም ተደነቃችሁ። 22 እስቲ ይህን ልብ በሉ፦ ሙሴ የግርዘትን ሕግ ሰጣችሁ+ (ይህ ሕግ የተሰጠው ከአባቶች ነው+ እንጂ ከሙሴ አይደለም)፤ እናንተም በሰንበት ሰው ትገርዛላችሁ። 23 የሙሴ ሕግ እንዳይጣስ ሲባል በሰንበት ቀን ሰው የሚገረዝ ከሆነ እኔ በሰንበት አንድን ሰው መፈወሴ ይህን ያህል ሊያስቆጣችሁ ይገባል?+ 24 የሰውን ውጫዊ ገጽታ በማየት አትፍረዱ፤* ከዚህ ይልቅ በጽድቅ ፍረዱ።”+

25 በዚህ ጊዜ ከኢየሩሳሌም ነዋሪዎች መካከል አንዳንዶቹ እንዲህ አሉ፦ “ሊገድሉት የሚፈልጉት ሰው ይህ አይደለም እንዴ?+ 26 እሱ ግን ይኸው በአደባባይ እየተናገረ ነው፤ እነሱም ምንም አላሉትም። ገዢዎቹ ይህ ሰው በእርግጥ ክርስቶስ እንደሆነ አስበው ይሆን? 27 ሆኖም እኛ ይህ ሰው ከየት እንደመጣ እናውቃለን፤+ ክርስቶስ ሲመጣ ግን ከየት እንደመጣ ማንም አያውቅም።” 28 ከዚያም ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ እያስተማረ ሳለ ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፦ “እኔ ማን እንደሆንኩም ሆነ ከየት እንደመጣሁ ታውቃላችሁ። የመጣሁትም በራሴ ተነሳስቼ አይደለም፤+ ሆኖም የላከኝ በእውን ያለ ነው፤ እናንተም አታውቁትም።+ 29 እኔ ግን የእሱ ተወካይ ሆኜ የመጣሁ ስለሆንኩ አውቀዋለሁ፤+ የላከኝም እሱ ነው።” 30 በመሆኑም ሊይዙት ፈለጉ፤+ ሆኖም ሰዓቱ ገና ስላልደረሰ ማንም አልያዘውም።+ 31 ይሁንና ከሕዝቡ መካከል ብዙዎች በእሱ አምነው+ “ክርስቶስስ በሚመጣበት ጊዜ ይህ ሰው ካደረገው የበለጠ ብዙ ተአምራዊ ምልክት ያደርጋል እንዴ?” ይሉ ነበር።

32 ፈሪሳውያን ሕዝቡ በጉምጉምታ ስለ እሱ የሚያወራውን ነገር ሰሙ፤ የካህናት አለቆቹና ፈሪሳውያኑም ይይዙት* ዘንድ የቤተ መቅደስ ጠባቂዎችን ላኩ። 33 በዚህ ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ከእናንተ ጋር የምቆየው ለጥቂት ጊዜ ነው፤ ከዚያም ወደ ላከኝ እሄዳለሁ።+ 34 እናንተ ትፈልጉኛላችሁ፤ ግን አታገኙኝም፤ ወደምሄድበትም ልትመጡ አትችሉም።”+ 35 በዚህ ጊዜ አይሁዳውያን እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፦ “ይህ ሰው ልናገኘው የማንችለው ወዴት ሊሄድ ቢያስብ ነው? በግሪካውያን መካከል ተበታትነው ወደሚገኙት አይሁዳውያን ሄዶ ግሪካውያንን ሊያስተምር አስቦ ይሆን እንዴ? 36 ‘ትፈልጉኛላችሁ፤ ግን አታገኙኝም፤ ወደምሄድበትም ልትመጡ አትችሉም’ ሲል ምን ማለቱ ይሆን?”

37 የበዓሉ+ መጨረሻ በሆነው በታላቁ ቀን ኢየሱስ ቆሞ ከፍ ባለ ድምፅ እንዲህ አለ፦ “የተጠማ ካለ ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ።+ 38 በእኔ የሚያምን ሁሉ ቅዱስ መጽሐፉ እንደሚለው ‘የሕያው ውኃ ጅረቶች ከውስጡ ይፈስሳሉ።’”+ 39 ይሁን እንጂ ይህን ሲል በእሱ የሚያምኑ ስለሚቀበሉት መንፈስ መናገሩ ነበር፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ክብሩን ገና ስላልተጎናጸፈ+ መንፈስ አልተሰጠም ነበር።+ 40 ከሕዝቡ መካከል አንዳንዶች ይህን ቃል ሲሰሙ “ይህ ሰው በእርግጥ ነቢዩ ነው” ይሉ ጀመር።+ 41 ሌሎችም “ይህ ክርስቶስ ነው”+ ይሉ ነበር። አንዳንዶች ግን እንዲህ አሉ፦ “ክርስቶስ የሚመጣው ከገሊላ ነው እንዴ?+ 42 ቅዱስ መጽሐፉ ክርስቶስ ከዳዊት ዘርና+ ዳዊት ከኖረበት መንደር+ ከቤተልሔም+ እንደሚመጣ ይናገር የለም?” 43 ስለዚህ እሱን በተመለከተ በሕዝቡ መካከል ክፍፍል ተፈጠረ። 44 ይሁንና አንዳንዶቹ ሊይዙት* ፈልገው ነበር፤ ሆኖም አንድም ሰው አልያዘውም።

45 ከዚያም የቤተ መቅደሱ ጠባቂዎች ወደ ካህናት አለቆቹና ወደ ፈሪሳውያኑ ተመልሰው ሄዱ፤ እነሱም ጠባቂዎቹን “ለምን ይዛችሁት አልመጣችሁም?” አሏቸው። 46 ጠባቂዎቹም “ማንም ሰው እንደዚህ ተናግሮ አያውቅም” ብለው መለሱ።+ 47 ፈሪሳውያኑ ግን እንዲህ አሏቸው፦ “እናንተም ተታለላችሁ? 48 ከገዢዎች ወይም ከፈሪሳውያን መካከል በእሱ ያመነ አለ?+ 49 ሕጉን የማያውቀው ይህ ሕዝብ ግን የተረገመ ነው።” 50 ቀደም ሲል ወደ ኢየሱስ መጥቶ የነበረውና ከእነሱ አንዱ የሆነው ኒቆዲሞስ እንዲህ አላቸው፦ 51 “ሕጋችን በመጀመሪያ ግለሰቡ የሚለውን ሳይሰማና ምን እያደረገ እንዳለ ሳያውቅ ይፈርድበታል?”+ 52 እነሱም “አንተም ደግሞ ከገሊላ ነህ? ከገሊላ አንድም ነቢይ እንደማይነሳ ቅዱሳን መጻሕፍትን መርምረህ ተረዳ” አሉት።*

8 12 ደግሞም ኢየሱስ ሰዎቹን እንዲህ አላቸው፦ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ።+ እኔን የሚከተል ሁሉ በምንም ዓይነት በጨለማ አይሄድም፤ ከዚህ ይልቅ የሕይወት ብርሃን ያገኛል።”+ 13 ፈሪሳውያንም “አንተ ስለ ራስህ ትመሠክራለህ፤ ምሥክርነትህም እውነት አይደለም” አሉት። 14 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “ስለ ራሴ ብመሠክር እንኳ ከየት እንደመጣሁና ወዴት እንደምሄድ ስለማውቅ+ ምሥክርነቴ እውነት ነው። እናንተ ግን ከየት እንደመጣሁና ወዴት እንደምሄድ አታውቁም። 15 እናንተ በሥጋዊ አስተሳሰብ* ትፈርዳላችሁ፤+ እኔ በማንም ላይ አልፈርድም። 16 እኔ ብፈርድ እንኳ ፍርዴ እውነተኛ ነው፤ ምክንያቱም የምፈርደው ብቻዬን አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ የላከኝ አብ ከእኔ ጋር ነው።+ 17 በሕጋችሁም ላይ ‘የሁለት ሰዎች ምሥክርነት እውነት ነው’+ ተብሎ ተጽፏል። 18 ስለ ራሴ የምመሠክር አንዱ እኔ ነኝ፤ ደግሞም የላከኝ አብ ስለ እኔ ይመሠክራል።”+ 19 በዚህ ጊዜ “አባትህ የት ነው?” አሉት። ኢየሱስም “እናንተ እኔንም ሆነ አባቴን አታውቁም።+ እኔን ብታውቁኝ ኖሮ አባቴንም ባወቃችሁት ነበር”+ ሲል መለሰላቸው። 20 ኢየሱስ ይህን የተናገረው በቤተ መቅደስ፣ ግምጃ ቤቱ+ አካባቢ ሆኖ ሲያስተምር ነበር። ሆኖም ሰዓቱ ገና ስላልደረሰ ማንም አልያዘውም።+

21 ኢየሱስም እንደገና “እኔ እሄዳለሁ፤ እናንተም ትፈልጉኛላችሁ፤ ይሁንና ኃጢአተኛ እንደሆናችሁ ትሞታላችሁ።+ እኔ ወደምሄድበት ልትመጡ አትችሉም”+ አላቸው። 22 አይሁዳውያኑም “‘እኔ ወደምሄድበት ልትመጡ አትችሉም’ የሚለው ራሱን ሊገድል አስቦ ይሆን እንዴ?” አሉ። 23 እሱም እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ ከምድር ናችሁ፤ እኔ ከላይ ነኝ።+ እናንተ ከዚህ ዓለም ናችሁ፤ እኔ ከዚህ ዓለም አይደለሁም። 24 በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁ ያልኳችሁ ለዚህ ነው። እኔ እሱ እንደሆንኩ ካላመናችሁ በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁ።” 25 እነሱም “ለመሆኑ አንተ ማን ነህ?” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ድሮውንም እኔ ከእናንተ ጋር የምነጋገረው እንዲያው በከንቱ ነው። 26 ስለ እናንተ ብዙ የምናገረው ነገር አለኝ፤ ፍርድ የምሰጥበትም ብዙ ነገር አለኝ። በመሠረቱ የላከኝ እውነተኛ ነው፤ እኔም ከእሱ የሰማሁትን ያንኑ ነገር ለዓለም እየተናገርኩ ነው።”+ 27 እነሱ ግን ስለ አብ እየነገራቸው እንደሆነ አልተረዱም ነበር። 28 ከዚያም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “የሰውን ልጅ ከሰቀላችሁት+ በኋላ እኔ እሱ+ እንደሆንኩና በራሴ ተነሳስቼ አንዳች ነገር እንደማላደርግ+ ከዚህ ይልቅ እነዚህን ነገሮች የምናገረው ልክ አብ እንዳስተማረኝ መሆኑን ታውቃላችሁ። 29 እኔን የላከኝ ከእኔ ጋር ነው፤ ሁልጊዜ እሱን ደስ የሚያሰኘውን ስለማደርግ+ ብቻዬን አልተወኝም።” 30 ይህን በተናገረ ጊዜ ብዙዎች በእሱ አመኑ።

31 ከዚያም ኢየሱስ በእሱ ላመኑት አይሁዳውያን እንዲህ አለ፦ “ቃሌን ጠብቃችሁ ብትኖሩ በእርግጥ ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ 32 እውነትንም ታውቃላችሁ፤+ እውነትም ነፃ ያወጣችኋል።”+ 33 እነሱም መልሰው “እኛ የአብርሃም ዘር ነን፤ ለማንም ባሪያዎች ሆነን አናውቅም። ታዲያ አንተ ‘ነፃ ትወጣላችሁ’ እንዴት ትለናለህ?” አሉት። 34 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ኃጢአት የሚያደርግ ሁሉ የኃጢአት ባሪያ ነው።+ 35 ደግሞም ባሪያ በጌታው ቤት ለዘለቄታው አይኖርም፤ ልጅ ከሆነ ግን ሁልጊዜ ይኖራል። 36 ስለዚህ ወልድ ነፃ ካወጣችሁ፣ በእርግጥ ነፃ ትሆናላችሁ። 37 የአብርሃም ዘር እንደሆናችሁ አውቃለሁ። ሆኖም ቃሌ በእናንተ ውስጥ ሥር ስለማይሰድ ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ። 38 እኔ ከአባቴ ጋር ሳለሁ ያየሁትን ነገር እናገራለሁ፤+ እናንተ ግን ከአባታችሁ የሰማችሁትን ነገር ታደርጋላችሁ።” 39 እነሱም መልሰው “አባታችን አብርሃም ነው” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “የአብርሃም ልጆች+ ብትሆኑ ኖሮ አብርሃም የሠራውን ትሠሩ ነበር። 40 እናንተ ግን ከአምላክ የሰማሁትን እውነት የነገርኳችሁን+ እኔን ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ። አብርሃም እንዲህ አላደረገም። 41 እናንተ እየሠራችሁ ያላችሁት የአባታችሁን ሥራ ነው።” እነሱም “እኛስ በዝሙት* የተወለድን አይደለንም፤ እኛ አንድ አባት አለን፤ እሱም አምላክ ነው” አሉት።

42 ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “አምላክ አባታችሁ ቢሆን ኖሮ እኔ ወደዚህ የመጣሁት ከእሱ ዘንድ ስለሆነ በወደዳችሁኝ ነበር።+ እሱ ላከኝ እንጂ እኔ በራሴ ተነሳስቼ አልመጣሁም።+ 43 እየተናገርኩት ያለው ነገር የማይገባችሁ ለምንድን ነው? ቃሌን መስማት ስለማትችሉ ነው። 44 እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ፤ የአባታችሁንም ፍላጎት መፈጸም ትሻላችሁ።+ እሱ በራሱ መንገድ መሄድ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ* ነፍሰ ገዳይ ነበር፤+ በእሱ ዘንድ እውነት ስለሌለ በእውነት ውስጥ ጸንቶ አልቆመም። ውሸታምና የውሸት አባት ስለሆነ ውሸት ሲናገር ከራሱ አመንጭቶ ይናገራል።+ 45 በሌላ በኩል ግን እኔ እውነትን ስለምናገር አታምኑኝም። 46 ከመካከላችሁ እኔን ኃጢአት ሠርተሃል ብሎ በማስረጃ ሊወነጅለኝ የሚችል ማን ነው? የምናገረው እውነት ከሆነ ደግሞ የማታምኑኝ ለምንድን ነው? 47 ከአምላክ የሆነ የአምላክን ቃል ይሰማል።+ እናንተ ግን ከአምላክ ስላልሆናችሁ አትሰሙም።”+

48 አይሁዳውያኑም መልሰው “‘አንተ ሳምራዊ+ ነህ፤ ደግሞም ጋኔን አድሮብሃል’+ ማለታችን ትክክል አይደለም?” አሉት። 49 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “እኔ አባቴን አከብራለሁ እንጂ ጋኔን የለብኝም፤ እናንተ ግን ታቃልሉኛላችሁ። 50 እኔ ለራሴ ክብር እየፈለግኩ አይደለም፤+ ይሁንና ይህን የሚፈልግና የሚፈርድ አለ። 51 እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ማንም ሰው ቃሌን የሚጠብቅ ከሆነ ፈጽሞ ሞትን አያይም።”+ 52 አይሁዳውያኑም እንዲህ አሉት፦ “አሁን በእርግጥ ጋኔን እንዳለብህ ተረዳን። አብርሃም ሞቷል፤ ነቢያትም ሞተዋል፤ አንተ ግን ‘ማንም ሰው ቃሌን የሚጠብቅ ከሆነ ፈጽሞ ሞትን አይቀምስም’ ትላለህ። 53  አንተ ከሞተው ከአባታችን ከአብርሃም ትበልጣለህ እንዴ? ነቢያትም ሞተዋል። ለመሆኑ አንተ ማን ነኝ ልትል ነው?” 54 ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “እኔ ራሴን የማከብር ከሆነ ክብሬ ከንቱ ነው። እኔን የሚያከብረኝ እናንተ አምላካችን ነው የምትሉት አባቴ ነው።+ 55 ሆኖም እናንተ አላወቃችሁትም፤+ እኔ ግን አውቀዋለሁ።+ አላውቀውም ብል እንደ እናንተ ውሸታም መሆኔ ነው። ይሁንና እኔ አውቀዋለሁ፤ ቃሉንም እጠብቃለሁ። 56 አባታችሁ አብርሃም ቀኔን እንደሚያይ ተስፋ በማድረግ እጅግ ተደሰተ፤ አይቶትም ደስ ተሰኘ።”+ 57  አይሁዳውያኑም “አንተ ገና 50 ዓመት እንኳ ያልሞላህ፣ አብርሃምን አይቼዋለሁ ትላለህ?” አሉት። 58 ኢየሱስም “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ አብርሃም ከመወለዱ በፊት እኔ ነበርኩ” አላቸው።+ 59 በዚህ ጊዜ ሊወግሩት ድንጋይ አነሱ፤ ኢየሱስ ግን ተሰወረና ከቤተ መቅደሱ ወጥቶ ሄደ።

9 በመንገድ እያለፈ ሳለም ሲወለድ ጀምሮ ዓይነ ስውር የሆነ አንድ ሰው አየ። 2 ደቀ መዛሙርቱም “ረቢ፣+ ይህ ሰው ዓይነ ስውር ሆኖ የተወለደው ማን በሠራው ኃጢአት ነው? በራሱ ኃጢአት ነው ወይስ በወላጆቹ?” ሲሉ ጠየቁት። 3 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “እሱም ሆነ ወላጆቹ ኃጢአት አልሠሩም፤ ሆኖም ይህ የሆነው የአምላክ ሥራ በእሱ እንዲገለጥ ነው።+ 4 ቀን ሳለ፣ የላከኝን የእሱን ሥራ መሥራት አለብን፤+ ማንም ሊሠራ የማይችልበት ሌሊት ይመጣል። 5 በዓለም እስካለሁ ድረስ የዓለም ብርሃን ነኝ።”+ 6 ይህን ካለ በኋላ መሬት ላይ እንትፍ በማለት በምራቁ ጭቃ ለወሰ፤ ጭቃውንም በሰውየው ዓይኖች ላይ ቀባ፤+ 7 ሰውየውንም “ሄደህ በሰሊሆም ገንዳ ታጠብ” አለው (ሰሊሆም ማለት “ተላከ” ማለት ነው)። ሰውየውም ሄዶ ታጠበ፤ ዓይኑም በርቶለት መጣ።+

8 ከዚያም ጎረቤቶቹና ቀደም ሲል ሲለምን ያዩት የነበሩ ሰዎች “ይህ ሰው ተቀምጦ ይለምን የነበረው አይደለም እንዴ?” አሉ። 9 አንዳንዶች “አዎ፣ እሱ ነው” ሲሉ ሌሎች ደግሞ “አይ፣ እሱን ይመስላል እንጂ እሱ አይደለም” ይሉ ነበር። ሰውየው ግን “እኔው ነኝ” ይል ነበር። 10 በመሆኑም “ታዲያ ዓይኖችህ እንዴት ተከፈቱ?” ሲሉ ጠየቁት። 11 እሱም “ኢየሱስ የተባለው ሰው ጭቃ ለውሶ ዓይኖቼን ቀባና ‘ወደ ሰሊሆም ሄደህ ታጠብ’ አለኝ።+ እኔም ሄጄ ታጠብኩ፤ ዓይኔም በራልኝ” ሲል መለሰ። 12 በዚህ ጊዜ “ሰውየው የት አለ?” አሉት። እሱም “እኔ አላውቅም” አለ።

13 እነሱም ዓይነ ስውር የነበረውን ሰው ወደ ፈሪሳውያን ወሰዱት። 14 እንደ አጋጣሚ ሆኖ ኢየሱስ ጭቃውን የለወሰበትና የሰውየውን ዓይኖች ያበራበት ቀን+ ሰንበት ነበር።+ 15 በዚህ ጊዜ ፈሪሳውያኑም እንዴት ማየት እንደቻለ ጠየቁት። እሱም “ሰውየው ዓይኖቼን ጭቃ ቀባ፤ እኔም ታጠብኩ፤ ከዚያም ማየት ቻልኩ” አላቸው። 16 ከፈሪሳውያንም መካከል አንዳንዶቹ “ይህ ሰው ሰንበትን ስለማያከብር ከአምላክ የመጣ አይደለም” አሉ።+ ሌሎቹ ደግሞ “ኃጢአተኛ የሆነ ሰው እንዲህ ያሉ ተአምራዊ ምልክቶችን እንዴት ሊፈጽም ይችላል?” አሉ።+ በመሆኑም በመካከላቸው ክፍፍል ተፈጠረ።+ 17 በድጋሚም ዓይነ ስውሩን “ይህ ሰው ዓይኖችህን ስላበራልህ ስለ እሱ ምን ትላለህ?” አሉት። ሰውየውም “እሱ ነቢይ ነው” አለ።

18 ይሁን እንጂ አይሁዳውያኑ ማየት የቻለውን ሰው ወላጆች እስከጠሩበት ጊዜ ድረስ ሰውየው ዓይነ ስውር እንደነበረና በኋላ ዓይኑ እንደበራለት አላመኑም ነበር። 19 ወላጆቹንም “ዓይነ ስውር ሆኖ ተወልዷል የምትሉት ልጃችሁ ይህ ነው? ታዲያ አሁን እንዴት ሊያይ ቻለ?” ሲሉ ጠየቋቸው። 20 ወላጆቹም እንዲህ ሲሉ መለሱ፦ “ይህ ልጃችን እንደሆነና ዓይነ ስውር ሆኖ እንደተወለደ እናውቃለን። 21 አሁን ግን እንዴት ሊያይ እንደቻለ የምናውቀው ነገር የለም፤ ዓይኖቹን ማን እንዳበራለትም አናውቅም። እሱን ጠይቁት፤ ሙሉ ሰው ነው። ስለ ራሱ መናገር ያለበት እሱ ነው።” 22 ወላጆቹ ይህን ያሉት አይሁዳውያኑን* ስለፈሩ ነው፤+ ምክንያቱም አይሁዳውያን ኢየሱስን፣ ‘ክርስቶስ ነው’ ብሎ የተቀበለ ማንኛውም ሰው ከምኩራብ እንዲባረር አስቀድመው ወስነው ነበር።+ 23 ወላጆቹ “ሙሉ ሰው ነው። እሱን ጠይቁት” ያሉት ለዚህ ነበር።

24 ስለዚህ ዓይነ ስውር የነበረውን ሰው ለሁለተኛ ጊዜ ጠርተው “እውነቱን በመናገር ለአምላክ ክብር ስጥ፤ እኛ ይህ ሰው ኃጢአተኛ መሆኑን እናውቃለን” አሉት። 25 እሱም መልሶ “ኃጢአተኛ ይሁን አይሁን የማውቀው ነገር የለም። እኔ የማውቀው ዓይነ ስውር እንደነበርኩና አሁን ግን ማየት እንደቻልኩ ነው” አለ። 26 በዚህ ጊዜ “ምንድን ነው ያደረገልህ? ዓይንህን ያበራልህስ እንዴት ነው?” አሉት። 27 እሱም “ነገርኳችሁ እኮ፤ እናንተ ግን አትሰሙም። እንደገና መስማት የፈለጋችሁት ለምንድን ነው? እናንተም የእሱ ደቀ መዝሙር መሆን ፈለጋችሁ እንዴ?” ሲል መለሰላቸው። 28 እነሱም ሰውየውን በንቀት እንዲህ አሉት፦ “የዚያ ሰው ደቀ መዝሙር አንተ ነህ፤ እኛ ግን የሙሴ ደቀ መዛሙርት ነን። 29 አምላክ ሙሴን እንዳነጋገረው እናውቃለን፤ ይህ ሰው ግን ከየት እንደመጣ አናውቅም።” 30 ሰውየውም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ከየት እንደመጣ አለማወቃችሁ በጣም የሚያስገርም ነገር ነው፤ ያም ሆነ ይህ ዓይኖቼን አብርቶልኛል። 31 አምላክ ኃጢአተኞችን እንደማይሰማ እናውቃለን፤+ ፈሪሃ አምላክ ያለውንና ፈቃዱን የሚያደርገውን ሁሉ ግን ይሰማዋል።+ 32 ዓይነ ስውር ሆኖ የተወለደን ሰው ዓይኖች የከፈተ አለ ሲባል ከጥንት ዘመን ጀምሮ ተሰምቶ አይታወቅም። 33 ይህ ሰው ከአምላክ ባይሆን ኖሮ ምንም ነገር ሊያደርግ አይችልም ነበር።”+ 34 እነሱም መልሰው “አንተ ሁለመናህ በኃጢአት ተበክሎ የተወለድክ! እኛን ልታስተምር ትፈልጋለህ?” አሉት። ከዚያም አባረሩት!+

35 ኢየሱስም ሰውየውን እንዳባረሩት ሰማ፤ ባገኘውም ጊዜ “በሰው ልጅ ላይ እምነት አለህ?” አለው። 36 ሰውየውም “ጌታዬ፣ አምንበት ዘንድ እሱ ማን ነው?” ሲል መለሰ። 37 ኢየሱስም “አይተኸዋል፤ ደግሞም እያነጋገረህ ያለው እሱ ነው” አለው። 38 እሱም “ጌታ ሆይ፣ በእሱ አምናለሁ” አለ። ከዚያም ሰገደለት።* 39 ኢየሱስም “የማያዩ ማየት እንዲችሉ፣+ የሚያዩም እንዲታወሩ፣+ ለዚህ ፍርድ ወደዚህ ዓለም መጥቻለሁ” አለ። 40 በዚያ የነበሩ ፈሪሳውያንም ይህን ሰምተው “እናንተም ዕውሮች ናችሁ እያልከን ነው?” አሉት። 41 ኢየሱስም “ዕውሮች ብትሆኑማ ኖሮ ኃጢአት ባልሆነባችሁ ነበር። አሁን ግን ‘እናያለን’ ትላላችሁ። ስለዚህ ኃጢአታችሁ እንዳለ ይኖራል” አላቸው።+

10 “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ በበሩ ሳይሆን በሌላ በኩል ዘሎ ወደ በጎቹ ጉረኖ የሚገባ ሌባና ዘራፊ ነው።+ 2 በበሩ በኩል የሚገባ ግን የበጎቹ እረኛ ነው።+ 3 በር ጠባቂውም ለእሱ ይከፍትለታል፤+ በጎቹም ድምፁን ይሰማሉ።+ የራሱን በጎች በየስማቸው ጠርቶ እየመራ ያወጣቸዋል። 4 የራሱ የሆኑትን ሁሉ ካወጣ በኋላ ከፊት ከፊታቸው ይሄዳል፤ በጎቹም ድምፁን ስለሚያውቁ ይከተሉታል። 5 እንግዳ የሆነውን ግን ይሸሹታል እንጂ በምንም ዓይነት አይከተሉትም፤ ምክንያቱም የእንግዳ ሰዎችን ድምፅ አያውቁም።” 6 ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ እነሱ ግን ምን እያላቸው እንዳለ አልገባቸውም።

7 ስለዚህ ኢየሱስ እንደገና እንዲህ አለ፦ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ በጎቹ የሚገቡበት በር እኔ ነኝ።+ 8 አስመሳይ ሆነው በእኔ ስም የመጡ ሁሉ ሌቦችና ዘራፊዎች ናቸው፤ በጎቹ ግን አልሰሟቸውም። 9 በሩ እኔ ነኝ፤ በእኔ በኩል የሚገባ ሁሉ ይድናል፤ ይገባል፤ ይወጣል፤ መሰማሪያም ያገኛል።+ 10 ሌባው ለመስረቅ፣ ለመግደልና ለማጥፋት ካልሆነ በቀር ለሌላ አይመጣም።+ እኔ የመጣሁት ሕይወት እንዲኖራቸውና እንዲትረፈረፍላቸው ነው። 11 እኔ ጥሩ እረኛ ነኝ፤+ ጥሩ እረኛ ሕይወቱን* ለበጎቹ ሲል አሳልፎ ይሰጣል።+ 12 እረኛ ያልሆነና በጎቹ የራሱ ያልሆኑ ተቀጣሪ ሠራተኛ ተኩላ ሲመጣ ሲያይ በጎቹን ጥሎ ይሸሻል (ተኩላውም በጎቹን ይነጥቃል እንዲሁም ይበታትናል)፤ 13 ሠራተኛው እንዲህ የሚያደርገው ተቀጣሪ ስለሆነና ለበጎቹ ደንታ ስለሌለው ነው። 14 እኔ ጥሩ እረኛ ነኝ። በጎቼን አውቃቸዋለሁ፤ በጎቼም ያውቁኛል፤+ 15 ይህም አብ እኔን እንደሚያውቀኝና እኔም አብን እንደማውቀው ነው፤+ ሕይወቴንም* ለበጎቹ ስል አሳልፌ እሰጣለሁ።+

16 “ከዚህ ጉረኖ ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤+ እነሱንም ማምጣት አለብኝ፤ ድምፄንም ይሰማሉ፤ ሁሉም አንድ መንጋ ይሆናሉ፤ አንድ እረኛም ይኖራቸዋል።+ 17 ሕይወቴን* መልሼ አገኛት ዘንድ አሳልፌ ስለምሰጣት+ አብ ይወደኛል።+ 18 በራሴ ተነሳስቼ አሳልፌ እሰጣታለሁ እንጂ ማንም ሰው ከእኔ አይወስዳትም። ሕይወቴን* አሳልፌ ለመስጠት ሥልጣን አለኝ፤ መልሼ ለመቀበልም ሥልጣን አለኝ።+ ይህን ትእዛዝ የተቀበልኩት ከአባቴ ነው።”

19 ከዚህ ንግግር የተነሳ በአይሁዳውያኑ መካከል እንደገና ክፍፍል ተፈጠረ።+ 20 ብዙዎቹም “ይህ ሰው ጋኔን አለበት፤ አእምሮውን ስቷል። ለምን ትሰሙታላችሁ?” አሉ። 21 ሌሎቹ ደግሞ “ጋኔን የያዘው ሰው እንዲህ አይናገርም። ጋኔን የዓይነ ስውራንን ዓይን ሊከፍት ይችላል እንዴ?” አሉ።

22 በዚያ ጊዜ በኢየሩሳሌም የመታደስ በዓል* ይከበር ነበር። ወቅቱም ክረምት ነበር፤ 23 ኢየሱስም በቤተ መቅደሱ በሚገኘውና መጠለያ ባለው የሰለሞን መተላለፊያ+ ውስጥ እያለፈ ነበር። 24 በዚህ ጊዜ አይሁዳውያን ከበውት “እስከ መቼ ድረስ ልባችንን* ታንጠለጥላለህ? አንተ ክርስቶስ ከሆንክ በግልጽ ንገረን” አሉት። 25 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እኔ ነግሬአችኋለሁ፤ እናንተ ግን አታምኑም። በአባቴ ስም እየሠራኋቸው ያሉት ሥራዎች ስለ እኔ ይመሠክራሉ።+ 26 ሆኖም እናንተ በጎቼ ስላልሆናችሁ አታምኑም።+ 27 በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ፤ እኔም አውቃቸዋለሁ፤ እነሱም ይከተሉኛል።+ 28 የዘላለም ሕይወት እሰጣቸዋለሁ፤+ መቼም ቢሆን ጥፋት አይደርስባቸውም፤ ከእጄ የሚነጥቃቸውም የለም።+ 29 አባቴ የሰጠኝ በጎች ከሌሎች ነገሮች ሁሉ ይበልጣሉ፤ እነሱንም ከአባቴ እጅ ሊነጥቃቸው የሚችል የለም።+ 30 እኔና አብ አንድ ነን።”*+

31 በዚህ ጊዜም አይሁዳውያኑ ሊወግሩት ድንጋይ አነሱ። 32 ኢየሱስም መልሶ “ከአብ ዘንድ ብዙ መልካም ሥራዎች አሳየኋችሁ። ታዲያ የምትወግሩኝ ከእነዚህ ሥራዎች መካከል በየትኛው የተነሳ ነው?” አላቸው። 33 አይሁዳውያኑም “እኛ የምንወግርህ ስለ መልካም ሥራህ ሳይሆን አንተ ሰው ሆነህ ሳለህ ራስህን አምላክ በማድረግ አምላክን ስለተዳፈርክ ነው”+ ሲሉ መለሱለት። 34 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “በሕጋችሁ ላይ ‘“እናንተ አማልክት* ናችሁ” አልኩ’+ ተብሎ ተጽፎ የለም? 35 የአምላክ ቃል ያወገዛቸውን እሱ ‘አማልክት’+ ብሎ ከጠራቸውና ቅዱስ መጽሐፉ ሊሻር የማይችል ከሆነ 36 አብ የቀደሰኝንና ወደ ዓለም የላከኝን እኔን፣ ‘የአምላክ ልጅ ነኝ’+ ስላልኩ ‘አምላክን ትዳፈራለህ’ ትሉኛላችሁ? 37 እኔ የአባቴን ሥራ እየሠራሁ ካልሆነ አትመኑኝ። 38 የአባቴን ሥራ እየሠራሁ ከሆነ ግን እኔን ባታምኑኝ እንኳ ሥራዬን እመኑ፤+ ይህም አብ ከእኔ ጋር አንድነት እንዳለው እንዲሁም እኔም ከአብ ጋር አንድነት እንዳለኝ እንድታውቁና ይህን ይበልጥ እያወቃችሁ እንድትሄዱ ነው።”+ 39 ስለዚህ እንደገና ሊይዙት ሞከሩ፤ እሱ ግን አመለጣቸው።

40 ከዚያም ዮሐንስ ቀደም ሲል ያጠምቅ ወደነበረበት ከዮርዳኖስ ማዶ ወዳለው ቦታ+ ዳግመኛ ሄደ፤ በዚያም ለተወሰነ ጊዜ ቆየ። 41 ብዙ ሰዎችም ወደ እሱ መጥተው እርስ በርሳቸው “ዮሐንስ አንድም ተአምራዊ ምልክት አላደረገም፤ ሆኖም ዮሐንስ ስለዚህ ሰው የተናገረው ነገር ሁሉ እውነት ነበር” ተባባሉ።+ 42 በዚያም ብዙዎች በእሱ አመኑ።

11 ማርያምና እህቷ ማርታ+ በሚኖሩበት መንደር በቢታንያ አልዓዛር የተባለ ሰው ታሞ ነበር። 2 ማርያም በጌታ ላይ ጥሩ መዓዛ ያለው ዘይት ያፈሰሰችውና በፀጉሯ እግሩን ያበሰችው+ ሴት ስትሆን የታመመውም፣ ወንድሟ አልዓዛር ነበር። 3 ስለዚህ እህቶቹ “ጌታ ሆይ፣ የምትወደው ሰው ታሟል” ሲሉ መልእክት ላኩበት። 4 ኢየሱስ ግን ይህን በሰማ ጊዜ “ይህ ሕመም ለአምላክ ክብር የሚያመጣ ነው+ እንጂ በሞት የሚያበቃ አይደለም፤ ይህም የአምላክ ልጅ በዚህ አማካኝነት ክብር ይጎናጸፍ ዘንድ ነው” አለ።

5 ኢየሱስ ማርታንና እህቷን እንዲሁም አልዓዛርን ይወዳቸው ነበር። 6 ይሁን እንጂ አልዓዛር መታመሙን ከሰማ በኋላ በዚያው በነበረበት ቦታ ሁለት ቀን ቆየ። 7 ከዚያም ደቀ መዛሙርቱን “ተመልሰን ወደ ይሁዳ እንሂድ” አላቸው። 8 ደቀ መዛሙርቱ ግን “ረቢ፣+ በቅርቡ እኮ የይሁዳ ሰዎች በድንጋይ ሊወግሩህ ፈልገው ነበር፤+ ታዲያ ወደዚያ ተመልሰህ ልትሄድ ነው?” አሉት። 9 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “በቀን ውስጥ ብርሃን የሚሆንበት 12 ሰዓት አለ አይደል?+ ማንም ሰው በቀን ብርሃን የሚሄድ ከሆነ የዚህን ዓለም ብርሃን ስለሚያይ ምንም ነገር አያደናቅፈውም። 10 ሆኖም በሌሊት የሚሄድ ሰው በእሱ ዘንድ ብርሃን ስለሌለ ይደናቀፋል።”

11 ይህን ከነገራቸው በኋላም “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቷል፤+ እኔም ልቀሰቅሰው ወደዚያ እሄዳለሁ” አላቸው። 12 በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ “ጌታ ሆይ፣ ተኝቶ ከሆነ ይሻለዋል” አሉት። 13 ይሁንና ኢየሱስ የተናገረው ስለመሞቱ ነበር። እነሱ ግን ለማረፍ ብሎ እንቅልፍ ስለመተኛቱ የተናገረ መሰላቸው። 14 በዚህ ጊዜ ኢየሱስ በግልጽ እንዲህ አላቸው፦ “አልዓዛር ሞቷል፤+ 15 ታምኑ ዘንድ በዚያ ባለመኖሬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል። ያም ሆነ ይህ ወደ እሱ እንሂድ።” 16 በዚህ ጊዜ ዲዲሞስ* የሚባለው ቶማስ ለተቀሩት ደቀ መዛሙርት “ከእሱ ጋር እንድንሞት አብረነው እንሂድ” አላቸው።+

17 ኢየሱስ እዚያ በደረሰ ጊዜ አልዓዛር በመቃብር ውስጥ አራት ቀን እንደሆነው አወቀ። 18 ቢታንያ ለኢየሩሳሌም ቅርብ የነበረች ሲሆን ሦስት ኪሎ ሜትር ያህል* ርቀት ላይ ትገኝ ነበር። 19 ወንድማቸውን በሞት ያጡትን ማርታንና ማርያምን ለማጽናናት ብዙ አይሁዳውያን መጥተው ነበር። 20 ማርታ፣ ኢየሱስ እየመጣ መሆኑን ስትሰማ ልትቀበለው ወጣች፤ ማርያም+ ግን እዚያው ቤት ቀረች። 21 ማርታም ኢየሱስን እንዲህ አለችው፦ “ጌታ ሆይ፣ አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተ ነበር። 22 አሁንም ቢሆን አምላክ የጠየቅከውን ነገር ሁሉ እንደሚሰጥህ አምናለሁ።” 23 ኢየሱስም “ወንድምሽ ይነሳል” አላት። 24 ማርታም “በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንደሚነሳ አውቃለሁ” አለችው።+ 25 ኢየሱስም እንዲህ አላት፦ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ።+ በእኔ የሚያምን* ሁሉ ቢሞት እንኳ እንደገና ሕያው ይሆናል፤ 26 በሕይወት ያለና በእኔ የሚያምን ሁሉ ደግሞ ፈጽሞ አይሞትም።+ ይህን ታምኛለሽ?” 27 እሷም “አዎ፣ ጌታ ሆይ፣ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው የአምላክ ልጅ ክርስቶስ መሆንህን አምናለሁ” አለችው። 28 ይህን ካለች በኋላም ሄዳ እህቷን ማርያምን ለብቻዋ ጠርታት “መምህሩ+ መጥቷል፤ እየጠራሽ ነው” አለቻት። 29 ማርያምም ይህን ስትሰማ በፍጥነት ተነስታ ወደ እሱ ሄደች።

30 ይሁንና ኢየሱስ እዚያው ማርታ ያገኘችው ቦታ ነበር እንጂ ገና ወደ መንደሩ አልገባም ነበር። 31 እሷን እያጽናኑ በቤት አብረዋት የነበሩ አይሁዳውያንም ማርያም ፈጥና ተነስታ ስትወጣ ሲያዩ ወደ መቃብሩ+ ሄዳ ልታለቅስ መስሏቸው ተከተሏት። 32 ማርያምም ኢየሱስ የነበረበት ቦታ ደርሳ ባየችው ጊዜ እግሩ ላይ ተደፋች፤ ከዚያም “ጌታ ሆይ፣ አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተ ነበር” አለችው። 33 ኢየሱስ እሷ ስታለቅስና አብረዋት የመጡት አይሁዳውያን ሲያለቅሱ ሲያይ እጅግ አዘነ፤* ተረበሸም። 34 እሱም “የት ነው ያኖራችሁት?” አለ። እነሱም “ጌታ ሆይ፣ መጥተህ እይ” አሉት። 35 ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ።+ 36 በዚህ ጊዜ አይሁዳውያኑ “እንዴት ይወደው እንደነበር ተመልከቱ!” አሉ። 37 ሆኖም ከእነሱ መካከል አንዳንዶች “የዓይነ ስውሩን ዓይን ያበራው ይህ ሰው+ ይሄኛውንም እንዳይሞት ማድረግ አይችልም ነበር?” አሉ።

38 ከዚያም ኢየሱስ ልቡ ዳግመኛ በሐዘን ታውኮ ወደ መቃብሩ መጣ። መቃብሩ ዋሻ ሲሆን በድንጋይም ተዘግቶ ነበር። 39 ኢየሱስ “ድንጋዩን አንሱት” አለ። የሟቹ እህት ማርታም “ጌታ ሆይ፣ አራት ቀን ስለሆነው አሁን ይሸታል” አለችው። 40 ኢየሱስም “ካመንሽ የአምላክን ክብር ታያለሽ ብዬ አልነገርኩሽም?” አላት።+ 41 ስለዚህ ድንጋዩን አነሱት። ከዚያም ኢየሱስ ወደ ሰማይ ተመልክቶ+ እንዲህ አለ፦ “አባት ሆይ፣ ስለሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ። 42 እውነት ነው፣ ሁልጊዜ እንደምትሰማኝ አውቃለሁ፤ ይህን ያልኩት ግን እዚህ የቆሙት ሰዎች አንተ እንደላክኸኝ ያምኑ ዘንድ ነው።”+ 43 ይህን ከተናገረ በኋላ በታላቅ ድምፅ “አልዓዛር፣ ና ውጣ!” አለ።+ 44 የሞተው ሰው እጆቹና እግሮቹ በመግነዝ እንደተገነዙ ወጣ፤ ፊቱም በጨርቅ ተጠምጥሞ ነበር። ኢየሱስም “ፍቱትና ይሂድ” አላቸው።

45 በመሆኑም ወደ ማርያም መጥተው ከነበሩትና ያደረገውን ነገር ካዩት አይሁዳውያን መካከል ብዙዎቹ በእሱ አመኑ፤+ 46 አንዳንዶቹ ግን ወደ ፈሪሳውያን ሄደው ኢየሱስ ያደረገውን ነገር ነገሯቸው። 47 ስለዚህ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን የሳንሄድሪንን ሸንጎ ሰብስበው እንዲህ አሉ፦ “ይህ ሰው ብዙ ተአምራዊ ምልክቶች እያደረገ ስለሆነ ምን ብናደርግ ይሻላል?+ 48 እንዲሁ ብንተወው ሁሉም በእሱ ያምናሉ፤ ሮማውያንም መጥተው ቦታችንንና* ሕዝባችንን ይወስዱብናል።” 49 ሆኖም ከመካከላቸው አንዱ፣ በዚያ ዓመት ሊቀ ካህናት የነበረው ቀያፋ+ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ ምንም አታውቁም፤ 50 ደግሞም ሕዝቡ ሁሉ ከሚጠፋ፣ አንድ ሰው ስለ ሕዝቡ ቢሞት እንደሚሻል ማሰብ ተስኗችኋል።” 51 ይሁንና ይህን የተናገረው ከራሱ አመንጭቶ አልነበረም፤ ከዚህ ይልቅ በዚያ ዓመት ሊቀ ካህናት ስለነበረ ኢየሱስ ለሕዝቡ እንደሚሞት ትንቢት መናገሩ ነበር፤ 52 የሚሞተውም ለሕዝቡ ብቻ ሳይሆን ተበታትነው ያሉትን የአምላክ ልጆችም አንድ ላይ መሰብሰብ ይችል ዘንድ ነው። 53  ስለዚህ ከዚያን ቀን አንስቶ ሊገድሉት አሴሩ።

54 በመሆኑም ኢየሱስ ከዚያን ጊዜ አንስቶ በአይሁዳውያን መካከል በይፋ መንቀሳቀስ አቆመ፤ ከዚህ ይልቅ በምድረ በዳ አቅራቢያ ወዳለ ስፍራ ሄደ፤ በዚያም ኤፍሬም+ ተብላ በምትጠራ ከተማ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተቀመጠ። 55 በዚህ ወቅት የአይሁዳውያን ፋሲካ+ ቀርቦ ነበር፤ ብዙ ሰዎችም ከፋሲካ በፊት የመንጻት ሥርዓት ለመፈጸም ከገጠር ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ። 56 ኢየሱስንም ይፈልጉት ጀመር፤ በቤተ መቅደሱም ቆመው እርስ በርሳቸው “ምን ይመስላችኋል? ጭራሽ ወደ በዓሉ አይመጣ ይሆን?” ይባባሉ ነበር። 57  የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ግን ኢየሱስን መያዝ* እንዲችሉ እሱ ያለበትን ቦታ የሚያውቅ ሁሉ እንዲጠቁማቸው አዘው ነበር።

12 የፋሲካ በዓል ከመድረሱ ከስድስት ቀን በፊት ኢየሱስ፣ ከሞት ያስነሳው አልዓዛር+ ወደሚኖርባት ወደ ቢታንያ መጣ። 2 በዚያም የራት ግብዣ አዘጋጁለት፤ ማርታ ታገለግላቸው የነበረ+ ሲሆን አልዓዛር ግን ከእሱ ጋር ከሚበሉት አንዱ ነበር። 3 ከዚያም ማርያም ግማሽ ሊትር ገደማ* የሚሆን እጅግ ውድ የሆነና ጥሩ መዓዛ ያለው ዘይት ይኸውም ንጹሕ ናርዶስ አምጥታ በኢየሱስ እግር ላይ አፈሰሰች፤ እግሩንም በፀጉሯ አብሳ አደረቀች። ቤቱም በዘይቱ መዓዛ ታወደ።+ 4 ሆኖም ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ የሆነውና አሳልፎ የሚሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ+ እንዲህ አለ፦ 5 “ይህ ዘይት በ300 ዲናር* ተሸጦ ገንዘቡ ለድሆች ያልተሰጠው ለምንድን ነው?” 6 እንዲህ ያለው ግን ለድሆች አስቦ ሳይሆን ሌባ ስለነበረ ነው፤ የገንዘብ ሣጥኑን ይይዝ የነበረው እሱ በመሆኑ ወደ ሣጥኑ ከሚገባው ገንዘብ የመስረቅ ልማድ ነበረው። 7 በዚህ ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ለቀብሬ ቀን ለማዘጋጀት+ ብላ ያደረገችው ስለሆነ ይህን ልማድ እንዳትፈጽም አትከልክሏት። 8 ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ናቸው፤+ እኔን ግን ሁልጊዜ አታገኙኝም።”+

9 በዚህ ጊዜ ብዙ አይሁዳውያን ኢየሱስ እዚያ መኖሩን አውቀው መጡ፤ የመጡትም ኢየሱስን ለማየት ብቻ ሳይሆን እሱ ከሞት ያስነሳውን አልዓዛርንም ለማየት ነበር።+ 10 በመሆኑም የካህናት አለቆቹ አልዓዛርንም ለመግደል አሴሩ፤ 11 ምክንያቱም በእሱ የተነሳ ብዙ አይሁዳውያን ወደዚያ እየሄዱ በኢየሱስ ያምኑ ነበር።+

12 በማግስቱም ወደ በዓሉ የመጡ እጅግ ብዙ ሰዎች ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እየመጣ መሆኑን ሰሙ። 13 በመሆኑም የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው ሊቀበሉት ወጡ። እንዲህ እያሉም ይጮኹ ጀመር፦ “እንድታድነው እንለምንሃለን!* በይሖዋ* ስም የሚመጣው የእስራኤል ንጉሥ+ የተባረከ ነው!”+ 14 ኢየሱስ የአህያ ውርንጭላ አግኝቶ ተቀመጠበት፤+ ይህም የሆነው እንዲህ ተብሎ በተጻፈው መሠረት ነው፦ 15 “የጽዮን ልጅ ሆይ፣ አትፍሪ። እነሆ ንጉሥሽ በአህያ ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ ይመጣል።”+ 16 ደቀ መዛሙርቱ በመጀመሪያ እነዚህን ነገሮች አላስተዋሉም ነበር፤ ኢየሱስ ክብር በተጎናጸፈ ጊዜ+ ግን እነዚህ ነገሮች የተጻፉት ስለ እሱ እንደሆነና እነዚህን ነገሮች ለእሱ እንዳደረጉለት ትዝ አላቸው።+

17 ኢየሱስ አልዓዛርን ከመቃብር ጠርቶ+ ከሞት ባስነሳበት ጊዜ አብረውት የነበሩት ሰዎች ስላዩት ነገር ይመሠክሩ ነበር።+ 18 ከዚህም የተነሳ ይህን ተአምራዊ ምልክት መፈጸሙን የሰማው ሕዝብ ሊቀበለው ወጣ። 19 ስለዚህ ፈሪሳውያን እርስ በርሳቸው “ምንም ማድረግ እንዳልቻልን አያችሁ! ተመልከቱ፣ ዓለሙ ሁሉ ግልብጥ ብሎ ተከትሎታል” ተባባሉ።+

20 ለአምልኮ ወደ በዓሉ ከመጡት ሰዎች መካከል አንዳንድ ግሪካውያን ነበሩ። 21 እነሱም በገሊላ የምትገኘው የቤተሳይዳ ሰው ወደሆነው ወደ ፊልጶስ+ ቀርበው “ጌታ ሆይ፣ ኢየሱስን ማየት እንፈልጋለን” ብለው ጠየቁት። 22 ፊልጶስ መጥቶ ለእንድርያስ ነገረው። ከዚያም እንድርያስና ፊልጶስ መጥተው ለኢየሱስ ነገሩት።

23 ኢየሱስ ግን እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “የሰው ልጅ ክብር የሚያገኝበት ሰዓት ደርሷል።+ 24 እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ አንዲት የስንዴ ዘር መሬት ላይ ወድቃ ካልሞተች አንድ ዘር ብቻ ሆና ትቀራለች፤ ከሞተች ግን+ ብዙ ፍሬ ታፈራለች። 25 ሕይወቱን የሚወድ ሁሉ* ያጠፋታል፤ በዚህ ዓለም ሕይወቱን* የሚጠላ+ ሁሉ ግን ለዘላለም ሕይወት ይጠብቃታል።+ 26 እኔን ሊያገለግል የሚፈልግ ቢኖር ይከተለኝ፤ እኔ ባለሁበት አገልጋዬም በዚያ ይሆናል።+ የሚያገለግለኝንም ሁሉ አብ ያከብረዋል። 27 አሁን ተጨንቄአለሁ፤*+ እንግዲህ ምን ማለት እችላለሁ? አባት ሆይ፣ ከዚህ ሰዓት አድነኝ።+ ይሁንና የመጣሁት ለዚህ ሰዓት ነው። 28 አባት ሆይ፣ ስምህን አክብረው።” በዚህ ጊዜ “ስሜን አክብሬዋለሁ፤ ደግሞም አከብረዋለሁ”+ የሚል ድምፅ+ ከሰማይ መጣ።

29 በዚያ ቆመው የነበሩት ብዙ ሰዎች ድምፁን በሰሙ ጊዜ ‘ነጎድጓድ ነው’ አሉ። ሌሎች ደግሞ “መልአክ አናገረው” አሉ። 30 ኢየሱስ ግን እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ይህ ድምፅ የተሰማው ለእኔ ሳይሆን ለእናንተ ሲባል ነው። 31 ይህ ዓለም የሚፈረድበት ጊዜ አሁን ነው፤ የዚህ ዓለም ገዢ+ አሁን ይባረራል።+ 32 እኔ ግን ከምድር ወደ ላይ ከፍ ከተደረግኩ+ ሁሉንም ዓይነት ሰዎች ወደ ራሴ እስባለሁ።” 33 ይህን የተናገረው በቅርብ ጊዜ ውስጥ ምን ዓይነት አሟሟት እንደሚሞት ለማመልከት ነው።+ 34 በዚህ ጊዜ ሕዝቡ “ክርስቶስ ለዘላለም እንደሚኖር ከሕጉ ሰምተናል።+ ታዲያ አንተ የሰው ልጅ ከፍ ማለት አለበት እንዴት ትላለህ?+ ይህ የሰው ልጅ ማን ነው?” ብለው መለሱለት። 35 ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “ብርሃኑ ለጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር ይቆያል። ጨለማ እንዳይውጣችሁ ብርሃኑ እያለላችሁ በብርሃን ሂዱ፤ በጨለማ የሚሄድ ሁሉ ወዴት እንደሚሄድ አያውቅም።+ 36 የብርሃን ልጆች+ እንድትሆኑ ብርሃኑ እያለላችሁ በብርሃኑ እመኑ።”

ኢየሱስ ይህን ተናግሮ እንደጨረሰ ሄደ፤ ከእነሱም ተሰወረ። 37 በፊታቸው ብዙ ተአምራዊ ምልክቶች ቢፈጽምም በእሱ አላመኑም፤ 38 ይህም ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው፦ “ይሖዋ* ሆይ፣ ከእኛ የሰማውን* ነገር ያመነ ማን ነው?+ የይሖዋስ* ክንድ ለማን ተገለጠ?”+ 39 ደግሞም ኢሳይያስ ሊያምኑ ያልቻሉበትን ምክንያት እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ 40 “በዓይናቸው አይተውና በልባቸው አስተውለው እንዳይመለሱና እንዳይፈውሳቸው ዓይናቸውን አሳውሯል፤ ልባቸውንም አደንድኗል።”+ 41 ኢሳይያስ ይህን የተናገረው ክብሩን ስላየ ነው፤ ስለ እሱም ተናገረ።+ 42 ያም ሆኖ ከገዢዎችም እንኳ ሳይቀር ብዙዎች በእሱ አመኑ፤+ ይሁንና ፈሪሳውያን ከምኩራብ እንዳያባርሯቸው ስለፈሩ በእሱ ማመናቸውን በግልጽ አይናገሩም ነበር፤+ 43 ይህም የሆነው ከሰው የሚገኘውን ክብር ከአምላክ ከሚገኘው ክብር አስበልጠው ስለወደዱ ነው።+

44 ይሁን እንጂ ኢየሱስ ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፦ “በእኔ የሚያምን ሁሉ በእኔ ብቻ ሳይሆን በላከኝም ጭምር ያምናል፤+ 45 እኔን የሚያይ ሁሉ የላከኝንም ያያል።+ 46 በእኔ የሚያምን ሁሉ በጨለማ እንዳይኖር+ ብርሃን ሆኜ ወደ ዓለም መጥቻለሁ።+ 47 ይሁንና ማንም ቃሌን ሰምቶ የማይጠብቅ ከሆነ የምፈርድበት እኔ አይደለሁም፤ እኔ የመጣሁት ዓለምን ለማዳን እንጂ በዓለም ላይ ለመፍረድ አይደለምና።+ 48 እኔን የሚንቀውንና ቃሌን የማይቀበለውን ሁሉ የሚፈርድበት አለ። በመጨረሻው ቀን የሚፈርድበት የተናገርኩት ቃል ነው። 49 እኔ የተናገርኩት በራሴ ተነሳስቼ አይደለምና፤ ከዚህ ይልቅ ምን እንደምልና ምን እንደምናገር ያዘዘኝ የላከኝ አብ ራሱ ነው።+ 50 ደግሞም የእሱ ትእዛዝ የዘላለም ሕይወት እንደሚያስገኝ አውቃለሁ።+ ስለዚህ ምንጊዜም የምናገረው ልክ አባቴ በነገረኝ መሠረት ነው።”+

13 የፋሲካ በዓል ተቃርቦ በነበረበት ወቅት ኢየሱስ ይህን ዓለም ትቶ ወደ አብ የሚሄድበት+ ሰዓት እንደደረሰ+ ስላወቀ በዓለም የነበሩትንና የወደዳቸውን ተከታዮቹን* እስከ መጨረሻው ወደዳቸው።+ 2 በዚህ ጊዜ ራት እየበሉ ነበር። ዲያብሎስ በስምዖን ልጅ በአስቆሮቱ ይሁዳ+ ልብ ውስጥ ኢየሱስን አሳልፎ የመስጠት ሐሳብ አሳድሮ ነበር።+ 3 ኢየሱስ፣ አብ ሁሉን ነገር በእጁ እንደሰጠው እንዲሁም ከአምላክ እንደመጣና ወደ አምላክ እንደሚሄድ+ ያውቅ ስለነበር 4 ከራት ተነስቶ መደረቢያውን አስቀመጠ። ፎጣ ወስዶም ወገቡ ላይ አሸረጠ።+ 5 ከዚያም በመታጠቢያ ዕቃ ውስጥ ውኃ ጨምሮ የደቀ መዛሙርቱን እግር ማጠብና ባሸረጠው ፎጣ ማድረቅ ጀመረ። 6 ከዚያም ወደ ስምዖን ጴጥሮስ መጣ። ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ፣ እግሬን ልታጥብ ነው?” አለው። 7 ኢየሱስም መልሶ “እያደረግኩት ያለውን ነገር አሁን አትረዳውም፤ በኋላ ግን ትረዳዋለህ” አለው። 8 ጴጥሮስም “በፍጹም እግሬን አታጥብም” አለው። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “ካላጠብኩህ+ ከእኔ ጋር ምንም ድርሻ አይኖርህም” ሲል መለሰለት። 9 ስምዖን ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ፣ እግሬን ብቻ ሳይሆን እጄንና ራሴንም እጠበኝ” አለው። 10 ኢየሱስም “ገላውን የታጠበ ሁለመናው ንጹሕ በመሆኑ ከእግሩ በስተቀር መታጠብ አያስፈልገውም። እናንተ ንጹሐን ናችሁ፤ ሁላችሁም ግን አይደላችሁም” አለው። 11 ምክንያቱም አሳልፎ የሚሰጠው ሰው ማን እንደሆነ ያውቅ ነበር።+ “ሁላችሁም ንጹሐን አይደላችሁም” ያለው ለዚህ ነው።

12 እግራቸውን አጥቦ ካበቃና መደረቢያውን ለብሶ ዳግመኛ በማዕድ ከተቀመጠ በኋላ እንዲህ አላቸው፦ “ምን እንዳደረግኩላችሁ አስተዋላችሁ? 13 እናንተ ‘መምህር’ እና ‘ጌታ’ ብላችሁ ትጠሩኛላችሁ፤ እንደዚያ ስለሆንኩም እንዲህ ብላችሁ መጥራታችሁ ትክክል ነው።+ 14 ስለዚህ እኔ ጌታና መምህር ሆኜ ሳለሁ እግራችሁን ካጠብኩ+ እናንተም እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ልትተጣጠቡ ይገባችኋል።*+ 15 እኔ እንዳደረግኩላችሁ እናንተም እንደዚሁ እንድታደርጉ አርዓያ ሆኜላችኋለሁ።+ 16 እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ባሪያ ከጌታው አይበልጥም፤ የተላከም ከላከው አይበልጥም። 17 እነዚህን ነገሮች ስለምታውቁ ብትፈጽሟቸው ደስተኞች ናችሁ።+ 18 ይህን ስል ስለ ሁላችሁም መናገሬ አይደለም፤ የመረጥኳቸውን አውቃለሁ። ይሁንና ‘ከማዕዴ ይበላ የነበረ ተረከዙን በእኔ ላይ አነሳ’*+ የሚለው የቅዱሳን መጻሕፍት ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው።+ 19 ገና ሳይፈጸም በፊት አሁን የምነግራችሁ፣ በሚፈጸምበት ጊዜ እኔ እሱ መሆኔን እንድታምኑ ነው።+ 20 እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ እኔ የምልከውን የሚቀበል ሁሉ እኔንም ይቀበላል፤+ እኔን የሚቀበል ሁሉ ደግሞ የላከኝንም ይቀበላል።”+

21 ኢየሱስ እነዚህን ነገሮች ከተናገረ በኋላ መንፈሱ ተረብሾ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል”+ ሲል በግልጽ ተናገረ። 22 ደቀ መዛሙርቱም ስለ ማን እየተናገረ እንዳለ ግራ ገብቷቸው እርስ በርሳቸው ይተያዩ ጀመር።+ 23 ከእነሱ አንዱ ይኸውም ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀ መዝሙር+ ኢየሱስ አጠገብ ጋደም ብሎ ነበር። 24 ስምዖን ጴጥሮስም ለዚህ ደቀ መዝሙር ምልክት በመስጠት “ስለ ማን እየተናገረ እንዳለ ንገረን” አለው። 25 እሱም ወደ ኢየሱስ ደረት ጠጋ ብሎ “ጌታ ሆይ፣ ማን ነው?” አለው።+ 26 ኢየሱስም “ይህን የማጠቅሰውን ቁራሽ ዳቦ የምሰጠው ሰው ነው” ሲል መለሰ።+ ከዚያም ዳቦውን አጥቅሶ ለአስቆሮቱ ስምዖን ልጅ ለይሁዳ ሰጠው። 27 ይሁዳም ቁራሹን ከተቀበለ በኋላ ሰይጣን ገባበት።+ ስለዚህ ኢየሱስ “እያደረግከው ያለኸውን ነገር ቶሎ አድርገው” አለው። 28 ይሁን እንጂ በማዕድ ከተቀመጡት መካከል አንዳቸውም ለምን እንዲህ እንዳለው አልገባቸውም። 29 እንዲያውም አንዳንዶቹ ይሁዳ የገንዘብ ሣጥኑን ይይዝ ስለነበር+ ለበዓሉ የሚያስፈልጉትን ነገሮች እንዲገዛ ወይም ለድሆች የሆነ ነገር እንዲሰጥ ኢየሱስ ያዘዘው መስሏቸው ነበር። 30 ስለዚህ ይሁዳ ቁራሹን ዳቦ ከተቀበለ በኋላ ወዲያውኑ ወጣ። ጊዜውም ሌሊት ነበር።+

31 ይሁዳ ከሄደ በኋላ ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “አሁን የሰው ልጅ ክብር ተጎናጸፈ፤+ አምላክም በእሱ አማካኝነት ከበረ። 32 አምላክ ራሱም ያከብረዋል፤+ ደግሞም ወዲያውኑ ያከብረዋል። 33 ልጆቼ ሆይ፣ ጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር እቆያለሁ። እናንተም ትፈልጉኛላችሁ፤ ለአይሁዳውያን ‘ወደምሄድበት ልትመጡ አትችሉም’+ እንዳልኳቸው ሁሉ አሁን ደግሞ ለእናንተ ይህንኑ እላችኋለሁ። 34 እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ እኔ እንደወደድኳችሁ+ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ።+ 35 እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ+ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።”

36 ስምዖን ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ፣ ወዴት ልትሄድ ነው?” አለው። ኢየሱስም “እኔ ወደምሄድበት አሁን ልትከተለኝ አትችልም፤ በኋላ ግን ትከተለኛለህ” ሲል መለሰ።+ 37 ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ፣ አሁን ልከተልህ የማልችለው ለምንድን ነው? ሕይወቴን* ስለ አንተ አሳልፌ ለመስጠት ፈቃደኛ ነኝ” አለው።+ 38 ኢየሱስም “ሕይወትህን* ስለ እኔ አሳልፈህ ትሰጣለህ? እውነት እውነት እልሃለሁ፣ ዶሮ ከመጮኹ በፊት ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ሲል መለሰ።+

14 “ልባችሁ አይረበሽ።+ በአምላክ እመኑ፤+ በእኔም ደግሞ እመኑ። 2 በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ ቦታ አለ። ይህ ባይሆን ኖሮ በግልጽ እነግራችሁ ነበር፤ ለእናንተ ቦታ ለማዘጋጀት እሄዳለሁና።+ 3 ደግሞም ሄጄ ቦታ ባዘጋጀሁላችሁ ጊዜ እኔ ባለሁበት እናንተም እንድትሆኑ እንደገና መጥቼ እኔ ወዳለሁበት እወስዳችኋለሁ።*+ 4 እኔ ወደምሄድበትም ቦታ የሚወስደውን መንገድ ታውቃላችሁ።”

5 ቶማስም+ “ጌታ ሆይ፣ ወዴት እንደምትሄድ አናውቅም። ታዲያ መንገዱን እንዴት ማወቅ እንችላለን?” አለው።

6 ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ “እኔ መንገድ፣+ እውነትና+ ሕይወት+ ነኝ። በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።+ 7 እኔን ብታውቁኝ ኖሮ አባቴንም ታውቁት ነበር፤ ከዚህ ጊዜ አንስቶ ታውቁታላችሁ፤ ደግሞም አይታችሁታል።”+

8 ፊልጶስም “ጌታ ሆይ፣ አብን አሳየንና ይበቃናል” አለው።

9 ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ “ፊልጶስ፣ ከእናንተ ጋር ይህን ያህል ረጅም ጊዜ ኖሬም እንኳ አላወቅከኝም? እኔን ያየ ሁሉ አብንም አይቷል።+ ታዲያ እንዴት ‘አብን አሳየን’ ትላለህ? 10 እኔ ከአብ ጋር አንድነት እንዳለኝና አብ ከእኔ ጋር አንድነት እንዳለው አታምንም?+ የምነግራችሁን ነገር የምናገረው ከራሴ አመንጭቼ አይደለም፤+ ሆኖም ሥራውን እየሠራ ያለው ከእኔ ጋር አንድነት ያለው አብ ነው። 11 እኔ ከአብ ጋር አንድነት እንዳለኝ አብም ከእኔ ጋር አንድነት እንዳለው እመኑኝ፤ ካልሆነ ደግሞ ከተሠሩት ሥራዎች የተነሳ እመኑ።+ 12 እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ በእኔ የሚያምን ሁሉ እኔ የምሠራቸውን ሥራዎች ይሠራል፤ እንዲያውም እኔ ወደ አብ ስለምሄድ+ እሱ ከእነዚህ የበለጡ ሥራዎች ይሠራል።+ 13 በተጨማሪም አብ በወልድ አማካኝነት እንዲከበር በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ።+ 14 ማንኛውንም ነገር በስሜ ከለመናችሁ እኔ አደርገዋለሁ።

15 “የምትወዱኝ ከሆነ ትእዛዛቴን ትጠብቃላችሁ።+ 16 እኔም አብን እጠይቃለሁ፤ እሱም ለዘላለም ከእናንተ ጋር የሚሆን ሌላ ረዳት* ይሰጣችኋል፤+ 17 እሱም የእውነት መንፈስ ነው፤+ ዓለም ስለማያየውና ስለማያውቀው ሊቀበለው አይችልም።+ እናንተ ግን አብሯችሁ ስለሚኖርና በውስጣችሁ ስላለ ታውቁታላችሁ። 18 ሐዘን ላይ* ትቻችሁ አልሄድም። ወደ እናንተ እመጣለሁ።+ 19 ከጥቂት ጊዜ በኋላ ዓለም ከቶ አያየኝም፤ እናንተ ግን ታዩኛላችሁ፤+ ምክንያቱም እኔ እኖራለሁ፤ እናንተም ትኖራላችሁ። 20 እኔ ከአባቴ ጋር አንድነት እንዳለኝ፣ እናንተ ከእኔ ጋር አንድነት እንዳላችሁና እኔም ከእናንተ ጋር አንድነት እንዳለኝ በዚያን ቀን ታውቃላችሁ።+ 21 እኔን የሚወደኝ ትእዛዛቴን የሚቀበልና የሚጠብቅ ነው። እኔን የሚወደኝን ሁሉ ደግሞ አባቴ ይወደዋል፤ እኔም እወደዋለሁ፤ ራሴንም እገልጥለታለሁ።”

22 የአስቆሮቱ ሳይሆን ሌላው ይሁዳ+ “ጌታ ሆይ፣ ለዓለም ሳይሆን ለእኛ ራስህን ለመግለጥ ያሰብከው ለምንድን ነው?” አለው።

23 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ማንም ሰው እኔን የሚወደኝ ከሆነ ቃሌን ይጠብቃል፤+ አባቴም ይወደዋል፣ እኛም ወደ እሱ መጥተን መኖሪያችንን ከእሱ ጋር እናደርጋለን።+ 24 እኔን የማይወደኝ ሁሉ ቃሌን አይጠብቅም። ይህ እየሰማችሁት ያለው ቃል ደግሞ የላከኝ የአብ ነው እንጂ የእኔ አይደለም።+

25 “አሁን ከእናንተ ጋር እያለሁ እነዚህን ነገሮች ነግሬአችኋለሁ። 26 ሆኖም አብ በስሜ የሚልከው ረዳት* ይኸውም መንፈስ ቅዱስ ሁሉንም ነገር ያስተምራችኋል እንዲሁም የነገርኳችሁን ነገር ሁሉ እንድታስታውሱ ያደርጋችኋል።+ 27 ሰላምን እተውላችኋለሁ፤ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ።+ እኔ ሰላም የምሰጣችሁ ዓለም በሚሰጥበት መንገድ አይደለም። ልባችሁ አይረበሽ፤ በፍርሃትም አይዋጥ። 28 ‘እሄዳለሁ ወደ እናንተም ተመልሼ እመጣለሁ’ እንዳልኳችሁ ሰምታችኋል። ብትወዱኝስ ወደ አብ በመሄዴ ደስ ባላችሁ ነበር፤ ከእኔ አብ ይበልጣልና።+ 29 በመሆኑም በሚፈጸምበት ጊዜ እንድታምኑ ከመፈጸሙ በፊት አሁን ነግሬአችኋለሁ።+ 30 የዚህ ዓለም ገዢ+ እየመጣ ስለሆነ ከዚህ በኋላ ከእናንተ ጋር ብዙ አልነጋገርም፤ እሱም በእኔ ላይ ምንም ኃይል የለውም።+ 31 ይሁን እንጂ እኔ አብን እንደምወድ ዓለም እንዲያውቅ አብ ባዘዘኝ መሠረት+ እየሠራሁ ነው። ተነሱ ከዚህ እንሂድ።

15 “እኔ እውነተኛው የወይን ተክል ነኝ፤ አትክልተኛው ደግሞ አባቴ ነው። 2 በእኔ ላይ ያለውን፣ ፍሬ የማያፈራውን ቅርንጫፍ ሁሉ ቆርጦ ይጥለዋል፤ ፍሬ የሚያፈራውን ቅርንጫፍ ሁሉ ደግሞ ይበልጥ እንዲያፈራ ያጠራዋል።*+ 3 እናንተ ከነገርኳችሁ ቃል የተነሳ አሁን ንጹሐን ናችሁ።+ 4 ከእኔ ጋር ያላችሁን አንድነት ጠብቃችሁ ኑሩ፤ እኔም ከእናንተ ጋር ያለኝን አንድነት ጠብቄ እኖራለሁ። ቅርንጫፉ ከወይኑ ተክል ጋር ተጣብቆ ካልኖረ በራሱ ፍሬ ማፍራት አይችልም፤ እናንተም ከእኔ ጋር ያላችሁን አንድነት ጠብቃችሁ ካልኖራችሁ+ ፍሬ ልታፈሩ አትችሉም። 5 እኔ የወይኑ ተክል ነኝ፤ እናንተ ደግሞ ቅርንጫፎቹ ናችሁ። ማንኛውም ሰው ከእኔ ጋር ያለውን አንድነት ጠብቆ ከኖረና እኔም ከእሱ ጋር አንድ ሆኜ ከኖርኩ ብዙ ፍሬ ያፈራል፤+ እናንተ ከእኔ ተለይታችሁ ምንም ነገር ልታደርጉ አትችሉምና። 6 አንድ ሰው ከእኔ ጋር ያለውን አንድነት ጠብቆ ካልኖረ እንደ ቅርንጫፍ ይጣልና ይደርቃል። ሰዎችም እንዲህ ያሉትን ቅርንጫፎች ሰብስበው እሳት ውስጥ በመጣል ያቃጥሏቸዋል። 7 እናንተ ከእኔ ጋር ያላችሁን አንድነት ከጠበቃችሁና ቃሌ በልባችሁ ከኖረ የምትፈልጉትን ማንኛውንም ነገር ብትጠይቁ ይፈጸምላችኋል።+ 8 ብዙ ፍሬ ብታፈሩና ደቀ መዛሙርቴ መሆናችሁን ብታሳዩ በዚህ አባቴ ይከበራል።+ 9 አብ እኔን እንደወደደኝ፣+ እኔም እናንተን እንዲሁ ወድጃችኋለሁ። እናንተም በፍቅሬ ኑሩ። 10 እኔ የአብን ትእዛዛት ጠብቄ በፍቅሩ እንደምኖር እናንተም ትእዛዛቴን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ።

11 “እነዚህን ነገሮች የነገርኳችሁ እኔ ያገኘሁትን ደስታ እንድታገኙና የእናንተም ደስታ የተሟላ እንዲሆን ነው።+ 12 ትእዛዜ ይህ ነው፤ እኔ እንደወደድኳችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ።+ 13 ሕይወቱን* ለወዳጆቹ ሲል አሳልፎ ከሚሰጥ ሰው የበለጠ ፍቅር ያለው ማንም የለም።+ 14 የማዛችሁን ነገር የምትፈጽሙ ከሆነ ወዳጆቼ ናችሁ።+ 15 ከእንግዲህ ባሪያዎች ብዬ አልጠራችሁም፤ ምክንያቱም ባሪያ ጌታው የሚያደርገውን ነገር አያውቅም። እኔ ግን ከአባቴ የሰማሁትን ነገር ሁሉ ስላሳወቅኳችሁ ወዳጆች ብዬ ጠርቻችኋለሁ። 16 እኔ መረጥኳችሁ እንጂ እናንተ አልመረጣችሁኝም፤ ሄዳችሁ ፍሬ እንድታፈሩና ፍሬያችሁ ጸንቶ እንዲኖር ሾሜያችኋለሁ፤ የመረጥኳችሁ አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ እንዲሰጣችሁ ነው።+

17 “እነዚህን ነገሮች የማዛችሁ እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ነው።+ 18 ዓለም ቢጠላችሁ፣ እናንተን ከመጥላቱ በፊት እኔን እንደጠላኝ ታውቃላችሁ።+ 19 የዓለም ክፍል ብትሆኑ ኖሮ ዓለም የራሱ የሆነውን በወደደ ነበር። አሁን ግን እኔ ከዓለም መረጥኳችሁ እንጂ የዓለም ክፍል ስላልሆናችሁ+ ከዚህ የተነሳ ዓለም ይጠላችኋል።+ 20 ባሪያ ከጌታው አይበልጥም ብዬ የነገርኳችሁን ቃል አስታውሱ። እኔን ስደት አድርሰውብኝ ከሆነ እናንተንም ስደት ያደርሱባችኋል፤+ ቃሌን ጠብቀው ከሆነ ደግሞ የእናንተንም ቃል ይጠብቃሉ። 21 ሆኖም የላከኝን ስለማያውቁት በስሜ ምክንያት እነዚህን ነገሮች ሁሉ ያደርጉባችኋል።+ 22 መጥቼ ባልነግራቸው ኖሮ ኃጢአት ባልሆነባቸው ነበር።+ አሁን ግን ለኃጢአታቸው የሚያቀርቡት ሰበብ የለም።+ 23 እኔን የሚጠላ ሁሉ አባቴንም ይጠላል።+ 24 ሌላ ማንም ያላደረገውን ነገር በመካከላቸው ባላደርግ ኖሮ ኃጢአት ባልሆነባቸው ነበር፤+ አሁን ግን እኔን አይተዋል እንዲሁም እኔንም ሆነ አባቴን ጠልተዋል። 25 ይሁን እንጂ ይህ የሆነው ‘ያለምክንያት ጠሉኝ’+ ተብሎ በሕጋቸው የተጻፈው ቃል እንዲፈጸም ነው። 26 ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ ከአብ የሚወጣው ረዳት* ይኸውም የእውነት መንፈስ+ ሲመጣ እሱ ስለ እኔ ይመሠክራል፤+ 27 እናንተም ደግሞ ትመሠክራላችሁ፤+ ምክንያቱም ከመጀመሪያ አንስቶ ከእኔ ጋር ነበራችሁ።

16 “ይህን ሁሉ የነገርኳችሁ እንዳትሰናከሉ ብዬ ነው። 2 ሰዎች ከምኩራብ ያባርሯችኋል።+ እንዲያውም እናንተን የሚገድል+ ሁሉ ለአምላክ ቅዱስ አገልግሎት እንዳቀረበ አድርጎ የሚያስብበት ሰዓት ይመጣል። 3 ሆኖም እነዚህን ነገሮች የሚያደርጉት አብንም ሆነ እኔን ስላላወቁ ነው።+ 4 ይሁንና እነዚህን ነገሮች የነገርኳችሁ የሚፈጸሙበት ሰዓት ሲደርስ አስቀድሜ ነግሬአችሁ እንደነበረ እንድታስታውሱ ነው።+

“ከእናንተ ጋር ስለነበርኩ እነዚህን ነገሮች በመጀመሪያ አልነገርኳችሁም። 5 አሁን ግን ወደ ላከኝ ልሄድ ነው፤+ ሆኖም ከመካከላችሁ ‘ወዴት ነው የምትሄደው?’ ብሎ የጠየቀኝ የለም። 6 እነዚህን ነገሮች ስለነገርኳችሁ ልባችሁ በሐዘን ተሞልቷል።+ 7 ይሁንና እውነቱን ለመናገር እኔ የምሄደው ለእናንተው ጥቅም ነው። ምክንያቱም እኔ ካልሄድኩ ረዳቱ*+ በምንም ዓይነት ወደ እናንተ አይመጣም፤ ከሄድኩ ግን እሱን ወደ እናንተ እልከዋለሁ። 8 እሱ ሲመጣ ስለ ኃጢአት፣ ስለ ጽድቅና ስለ ፍርድ ለዓለም አሳማኝ ማስረጃ ያቀርባል፦ 9 በመጀመሪያ ደረጃ ስለ ኃጢአት+ የተባለው፣ ሰዎች በእኔ ስላላመኑ ነው፤+ 10 ከዚያም ስለ ጽድቅ የተባለው፣ እኔ ወደ አብ ስለምሄድና እናንተ ከእንግዲህ ስለማታዩኝ ነው፤ 11 ስለ ፍርድ የተባለው ደግሞ የዚህ ዓለም ገዢ ስለተፈረደበት ነው።+

12 “ገና ብዙ የምነግራችሁ ነገር አለኝ፤ አሁን ግን ልትሸከሙት አትችሉም። 13 ይሁን እንጂ እሱ* ይኸውም የእውነት መንፈስ+ ሲመጣ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ ምክንያቱም የሚናገረው ከራሱ አመንጭቶ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ የሰማውን ይናገራል፤ እንዲሁም ወደፊት የሚሆኑትን ነገሮች ያሳውቃችኋል።+ 14 የሚያሳውቃችሁ+ የእኔ ከሆነው ወስዶ ስለሆነ እሱ እኔን ያከብረኛል።+ 15 አብ ያለው ነገር ሁሉ የእኔ ነው።+ የእኔ ከሆነው ወስዶ ያሳውቃችኋል ያልኳችሁ ለዚህ ነው። 16 ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤+ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ታዩኛላችሁ።”

17 በዚህ ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ አንዳንዶቹ እርስ በርሳቸው “‘ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ታዩኛላችሁ’ እንዲሁም ‘ወደ አብ ልሄድ ነውና’ ሲለን ምን ማለቱ ነው?” ተባባሉ። 18 ስለዚህ “‘ከጥቂት ጊዜ በኋላ’ ሲል ምን ማለቱ ነው? ስለ ምን ነገር እየተናገረ እንደሆነ አልገባንም” አሉ። 19 ኢየሱስ ሊጠይቁት እንደፈለጉ ተረድቶ እንዲህ አላቸው፦ “እርስ በርሳችሁ ስለዚህ ጉዳይ የምትጠያየቁት ‘ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ታዩኛላችሁ’ ስላልኩ ነው? 20 እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ እናንተ ታለቅሳላችሁ እንዲሁም ዋይ ዋይ ትላላችሁ፤ ዓለም ግን ይደሰታል፤ እናንተ ታዝናላችሁ፤ ሆኖም ሐዘናችሁ ወደ ደስታ ይለወጣል።+ 21 አንዲት ሴት የመውለጃዋ ሰዓት ደርሶ ስታምጥ ትጨነቃለች፤ ሕፃኑን ከወለደች በኋላ ግን አንድ ሰው ወደ ዓለም በመምጣቱ ከደስታዋ የተነሳ ሥቃይዋን ሁሉ ትረሳለች። 22 ስለዚህ እናንተም አሁን አዝናችኋል፤ ሆኖም እንደገና ስለማያችሁ ልባችሁ በደስታ ይሞላል፤+ ደስታችሁን ደግሞ ማንም አይነጥቃችሁም። 23 በዚያን ጊዜ እኔን ምንም ጥያቄ አትጠይቁኝም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ አብን ማንኛውንም ነገር በስሜ ብትጠይቁት+ ይሰጣችኋል።+ 24 እስካሁን ድረስ በስሜ አንድም ነገር አልጠየቃችሁም። ደስታችሁ የተሟላ እንዲሆን ጠይቁ፤ ትቀበላላችሁ።

25 “እነዚህን ነገሮች የነገርኳችሁ በምሳሌ ነው። ይሁንና ለእናንተ በምሳሌ የማልናገርበት ሰዓት ይመጣል፤ ከዚህ ይልቅ ስለ አብ በግልጽ እነግራችኋለሁ። 26 በዚያ ቀን አብን በስሜ ትለምናላችሁ፤ ይህን ስል ስለ እናንተ አብን እጠይቃለሁ ማለቴ አይደለም። 27 ምክንያቱም እናንተ እኔን ስለወደዳችሁኝና+ የአምላክ ተወካይ ሆኜ እንደመጣሁ ስላመናችሁ+ አብ ራሱ ይወዳችኋል። 28 እኔ የአብ ተወካይ ሆኜ ወደ ዓለም መጥቻለሁ። አሁን ደግሞ ዓለምን ትቼ ወደ አብ ልሄድ ነው።”+

29 ደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አሉ፦ “አሁን እኮ በግልጽ እየተናገርክ ነው፤ በምሳሌም አልተናገርክም። 30 አሁን ሁሉን ነገር እንደምታውቅና ማንም ጥያቄ እስኪጠይቅህ ድረስ መጠበቅ እንደማያስፈልግህ ተረዳን። ስለሆነም ከአምላክ ዘንድ እንደመጣህ እናምናለን።” 31 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “አሁን አመናችሁ? 32 እነሆ፣ ሁላችሁም ወደየቤታችሁ የምትበታተኑበትና እኔን ብቻዬን ትታችሁ የምትሄዱበት ሰዓት ቀርቧል፤+ እንዲያውም ደርሷል። ይሁንና አብ ከእኔ ጋር ስላለ ብቻዬን አይደለሁም።+ 33 እነዚህን ነገሮች የነገርኳችሁ በእኔ አማካኝነት ሰላም እንዲኖራችሁ ነው።+ በዓለም ሳላችሁ መከራ ይደርስባችኋል፤ ነገር ግን አይዟችሁ! እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።”+

17 ኢየሱስ እነዚህን ነገሮች ከተናገረ በኋላ ወደ ሰማይ ቀና ብሎ እንዲህ ሲል ጸለየ፦ “አባት ሆይ፣ ሰዓቱ ደርሷል። ልጅህ ያከብርህ ዘንድ ልጅህን አክብረው፤+ 2 ይህም በሥጋ ለባሽ* ሁሉ ላይ ሥልጣን እንደሰጠኸው+ ሁሉ እሱም አንተ ለሰጠኸው ሰው+ ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲሰጥ ነው።+ 3 ብቸኛው* እውነተኛ አምላክ+ የሆንከውን አንተንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ*+ የዘላለም ሕይወት+ ነው። 4 እንድሠራው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ+ በምድር ላይ አከበርኩህ።+ 5 ስለዚህ አባት ሆይ፣ ዓለም ከመመሥረቱ በፊት በጎንህ ሆኜ ክብር እንደነበረኝ+ ሁሉ አሁንም በጎንህ አድርገህ አክብረኝ።

6 “ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገልጬላቸዋለሁ።*+ እነሱ የአንተ ነበሩ፤ አንተም ለእኔ ሰጠኸኝ፤ ደግሞም ቃልህን ጠብቀዋል።* 7 የሰጠኸኝ ነገር ሁሉ ከአንተ የተገኘ መሆኑን አሁን አውቀዋል፤ 8 ምክንያቱም የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸዋለሁ፤+ እነሱም ተቀብለውታል፤ እንዲሁም የአንተ ተወካይ ሆኜ መምጣቴን በእርግጥ አውቀዋል፤+ አንተ እንደላክኸኝም አምነዋል።+ 9 ስለ እነሱ እለምንሃለሁ፤ የምለምንህ ስለ ዓለም ሳይሆን አንተ ስለሰጠኸኝ ሰዎች ነው፤ ምክንያቱም እነሱ የአንተ ናቸው፤ 10 ደግሞም የእኔ የሆነው ነገር ሁሉ የአንተ ነው፤+ የአንተ የሆነውም ሁሉ የእኔ ነው፤ እኔም በእነሱ መካከል ከብሬአለሁ።

11 “ከእንግዲህ እኔ በዓለም ውስጥ አልኖርም፤ እነሱ ግን በዓለም ውስጥ ናቸው፤+ እኔ ወደ አንተ መምጣቴ ነው። ቅዱስ አባት ሆይ፣ እኛ አንድ እንደሆንን* ሁሉ እነሱም አንድ እንዲሆኑ፣*+ ስለሰጠኸኝ ስለ ራስህ ስም ስትል ጠብቃቸው።+ 12 እኔ ከእነሱ ጋር ሳለሁ፣ ስለሰጠኸኝ ስለ ራስህ ስም ስል ስጠብቃቸው ቆይቻለሁ፤+ ደግሞም ጠብቄአቸዋለሁ፤ የቅዱስ መጽሐፉ ቃል ይፈጸም ዘንድ+ ከጥፋት ልጅ በቀር+ አንዳቸውም አልጠፉም።+ 13 አሁን ግን ወደ አንተ መምጣቴ ነው፤ ደስታዬ በውስጣቸው ሙሉ እንዲሆን+ አሁን በዓለም ላይ እያለሁ እነዚህን ነገሮች እናገራለሁ። 14 ቃልህን ሰጥቻቸዋለሁ፤ ሆኖም እኔ የዓለም ክፍል እንዳልሆንኩ ሁሉ እነሱም የዓለም ክፍል ስላልሆኑ ዓለም ጠላቸው።+

15 “የምለምንህ ከዓለም እንድታወጣቸው ሳይሆን ከክፉው* እንድትጠብቃቸው ነው።+ 16 እኔ የዓለም ክፍል እንዳልሆንኩ+ ሁሉ እነሱም የዓለም ክፍል አይደሉም።+ 17 በእውነትህ ቀድሳቸው፤*+ ቃልህ እውነት ነው።+ 18 አንተ ወደ ዓለም እንደላክኸኝ ሁሉ እኔም ወደ ዓለም ልኬአቸዋለሁ።+ 19 እነሱም በእውነት እንዲቀደሱ እኔ ራሴም ስለ እነሱ ስል ቅድስናዬን እጠብቃለሁ።

20 “የምለምንህ ስለ እነዚህ ብቻ ሳይሆን በእነሱ ቃል አማካኝነት በእኔ ለሚያምኑ ጭምር ነው፤ 21 ይህን ልመና የማቀርበውም ሁሉም አንድ እንዲሆኑ ነው፤+ ይኸውም ዓለም አንተ እንደላክኸኝ ያምን ዘንድ አባት ሆይ፣ አንተ ከእኔ ጋር አንድነት እንዳለህና እኔም ከአንተ ጋር አንድነት እንዳለኝ+ ሁሉ እነሱም ከእኛ ጋር አንድነት እንዲኖራቸው ነው። 22 እኛ አንድ እንደሆንን ሁሉ እነሱም አንድ እንዲሆኑ+ ለእኔ የሰጠኸኝን ክብር ሰጥቻቸዋለሁ። 23 እኔ ከእነሱ ጋር አንድነት አለኝ፤ አንተም ከእኔ ጋር አንድነት አለህ፤ ይህ ደግሞ እነሱም ፍጹም አንድ እንዲሆኑ* ነው፤ በተጨማሪም ዓለም አንተ እንደላክኸኝ እንዲሁም እኔን እንደወደድከኝ ሁሉ እነሱንም እንደወደድካቸው ያውቅ ዘንድ ነው። 24 አባት ሆይ፣ እነዚህ የሰጠኸኝ፣ እኔ ባለሁበት እነሱም ከእኔ ጋር እንዲሆኑ እፈልጋለሁ፤+ ይህም ዓለም ከመመሥረቱ* በፊት ስለወደድከኝ የሰጠኸኝን ክብር እንዲያዩ ነው።+ 25 ጻድቅ አባት ሆይ፣ በእርግጥ ዓለም አላወቀህም፤+ እኔ ግን አውቅሃለሁ፤+ እነዚህ ደግሞ አንተ እንደላክኸኝ አውቀዋል። 26 እኔን የወደድክበት ፍቅር እነሱም እንዲኖራቸው እንዲሁም እኔ ከእነሱ ጋር አንድነት እንዲኖረኝ+ ስምህን አሳውቄአቸዋለሁ፤ ደግሞም አሳውቃለሁ።”+

18 ኢየሱስ ስለ እነዚህ ነገሮች ከጸለየ በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የቄድሮንን ሸለቆ*+ ተሻግሮ ወደ አንድ የአትክልት ስፍራ ሄደ፤ እሱና ደቀ መዛሙርቱም ወደ አትክልት ስፍራው ገቡ።+ 2 ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ብዙ ጊዜ በዚህ ስፍራ ይገናኝ ስለነበር አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም ቦታውን ያውቅ ነበር። 3 ስለዚህ ይሁዳ አንድ የወታደሮች ቡድን እንዲሁም ከካህናት አለቆችና ከፈሪሳውያን የተላኩ የቤተ መቅደስ ጠባቂዎች አስከትሎ መጣ፤ እነሱም ችቦና መብራት እንዲሁም መሣሪያ ይዘው ነበር።+ 4 በዚህ ጊዜ ኢየሱስ የሚደርስበትን ነገር ሁሉ ስላወቀ ወደ ፊት ራመድ ብሎ “ማንን ነው የምትፈልጉት?” አላቸው። 5 እነሱም “የናዝሬቱን ኢየሱስ”+ ሲሉ መለሱለት። እሱም “እኔ ነኝ” አላቸው። አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም ከእነሱ ጋር ቆሞ ነበር።+

6 ይሁን እንጂ ኢየሱስ “እኔ ነኝ” ሲላቸው ወደ ኋላ አፈግፍገው መሬት ላይ ወደቁ።+ 7 ዳግመኛም “ማንን ነው የምትፈልጉት?” ሲል ጠየቃቸው። እነሱም “የናዝሬቱን ኢየሱስ” አሉት። 8 ኢየሱስም መልሶ “እኔ ነኝ አልኳችሁ እኮ። የምትፈልጉት እኔን ከሆነ እነዚህን ተዉአቸው ይሂዱ” አለ። 9 ይህም የሆነው “ከሰጠኸኝ ከእነዚህ መካከል አንዱም እንኳ አልጠፋብኝም”+ ብሎ የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው።

10 በዚህ ጊዜ ሰይፍ ይዞ የነበረው ስምዖን ጴጥሮስ ሰይፉን በመምዘዝ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቆረጠው።+ የባሪያውም ስም ማልኮስ ነበር። 11 ይሁን እንጂ ኢየሱስ ጴጥሮስን “ሰይፉን ወደ ሰገባው መልስ።+ አብ የሰጠኝን ጽዋ መጠጣት አይኖርብኝም?” አለው።+

12 ከዚያም ወታደሮቹና የጦር አዛዡ እንዲሁም ከአይሁዳውያን የተላኩት የቤተ መቅደስ ጠባቂዎች ኢየሱስን ይዘው አሰሩት። 13 በመጀመሪያም ወደ ሐና ወሰዱት፤ ምክንያቱም ሐና በዚያ ዓመት ሊቀ ካህናት+ የነበረው የቀያፋ+ አማት ነበር። 14 ቀያፋ ደግሞ አንድ ሰው ስለ ሕዝቡ ቢሞት ለእነሱ የተሻለ እንደሚሆን ለአይሁዳውያን ምክር የሰጠው ሰው ነው።+

15 ስምዖን ጴጥሮስና አንድ ሌላ ደቀ መዝሙር ኢየሱስን እየተከተሉ ነበር።+ ይህን ደቀ መዝሙር ሊቀ ካህናቱ ያውቀው ስለነበር ከኢየሱስ ጋር ወደ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ገባ፤ 16 ጴጥሮስ ግን ውጭ በር ላይ ቆሞ ነበር። ስለሆነም ሊቀ ካህናቱ የሚያውቀው ይህ ደቀ መዝሙር ወጥቶ በር ጠባቂዋን አነጋገራትና ጴጥሮስን አስገባው። 17 በር ጠባቂ የነበረችውም አገልጋይ ጴጥሮስን “አንተም ከዚህ ሰው ደቀ መዛሙርት አንዱ ነህ አይደል?” አለችው። እሱም “አይደለሁም” አለ።+ 18 ብርድ ስለነበር ባሪያዎቹና የቤተ መቅደሱ ጠባቂዎች ባቀጣጠሉት ከሰል ዙሪያ ቆመው እየሞቁ ነበር። ጴጥሮስም ከእነሱ ጋር ቆሞ እሳት ይሞቅ ነበር።

19 በዚህ ጊዜ የካህናት አለቃው ኢየሱስን ስለ ደቀ መዛሙርቱና ስለ ትምህርቱ ጠየቀው። 20 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “እኔ ለዓለም በግልጽ ተናግሬአለሁ። አይሁዳውያን ሁሉ በሚሰበሰቡበት በምኩራብና በቤተ መቅደሱ ሁልጊዜ አስተምር ነበር፤+ በስውር የተናገርኩት ምንም ነገር የለም። 21 እኔን ለምን ትጠይቀኛለህ? እኔ የነገርኳቸውን ነገር የሰሙትን ሰዎች ጠይቃቸው። እነዚህ የተናገርኩትን ያውቃሉ።” 22 ኢየሱስ ይህን በተናገረ ጊዜ አጠገቡ ቆመው ከነበሩት የቤተ መቅደስ ጠባቂዎች አንዱ በጥፊ መታውና+ “ለካህናት አለቃው የምትመልሰው እንዲህ ነው?” አለው። 23 ኢየሱስም “የተሳሳተ ነገር ተናግሬ ከሆነ ስህተቴ ምን እንደሆነ ንገረኝ፤* የተናገርኩት ነገር ትክክል ከሆነ ግን ለምን ትመታኛለህ?” ሲል መለሰለት። 24 ከዚያም ሐና ኢየሱስን እንደታሰረ ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ላከው።+

25 ስምዖን ጴጥሮስም ቆሞ እሳት እየሞቀ ነበር። በዚህ ጊዜ ሰዎቹ “አንተም ከእሱ ደቀ መዛሙርት አንዱ ነህ አይደል?” አሉት። እሱም “አይደለሁም” ሲል ካደ።+ 26 ከሊቀ ካህናቱ ባሪያዎች አንዱ ይኸውም ጴጥሮስ ጆሮውን የቆረጠው+ ሰው ዘመድ “በአትክልቱ ስፍራ ከእሱ ጋር አይቼህ አልነበረም?” አለው። 27 ይሁን እንጂ ጴጥሮስ እንደገና ካደ፤ ወዲያውም ዶሮ ጮኸ።+

28 ከዚያም ኢየሱስን ከቀያፋ ቤት ወደ ገዢው መኖሪያ ወሰዱት።+ ጊዜውም ማለዳ ነበር። ሆኖም እነሱ ፋሲካን መብላት ይችሉ ዘንድ እንዳይረክሱ+ ወደ ገዢው መኖሪያ አልገቡም። 29 ስለዚህ ጲላጦስ እነሱ ወዳሉበት ወጥቶ “በዚህ ሰው ላይ የምታቀርቡት ክስ ምንድን ነው?” አላቸው። 30 እነሱም መልሰው “ይህ ሰው ጥፋተኛ* ባይሆን ኖሮ ለአንተ አሳልፈን አንሰጠውም ነበር” አሉት። 31 ስለዚህ ጲላጦስ “እናንተ ራሳችሁ ወስዳችሁ በሕጋችሁ መሠረት ፍረዱበት” አላቸው።+ አይሁዳውያኑም “እኛ ማንንም ሰው ለመግደል ሕግ አይፈቅድልንም” አሉት።+ 32 ይህ የሆነው ኢየሱስ በምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚሞት ለማመልከት የተናገረው ቃል እንዲፈጸም ነው።+

33 ስለሆነም ጲላጦስ ወደ ገዢው መኖሪያ ተመልሶ ገባና ኢየሱስን ጠርቶ “አንተ የአይሁዳውያን ንጉሥ ነህ?” አለው።+ 34 ኢየሱስም መልሶ “ይህ የራስህ ጥያቄ ነው ወይስ ሌሎች ስለ እኔ ነግረውህ ነው?” አለው። 35 ጲላጦስም “እኔ አይሁዳዊ ነኝ እንዴ? ለእኔ አሳልፈው የሰጡህ የራስህ ሕዝብና የካህናት አለቆች ናቸው። ያደረግከው ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው። 36 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፦+ “መንግሥቴ የዚህ ዓለም ክፍል አይደለም።+ መንግሥቴ የዚህ ዓለም ክፍል ቢሆን ኖሮ በአይሁዳውያን እጅ እንዳልወድቅ አገልጋዮቼ ይዋጉልኝ ነበር።+ አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለም።” 37 በዚህ ጊዜ ጲላጦስ “እንግዲያው አንተ ንጉሥ ነህ?” አለው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “እኔ ንጉሥ እንደሆንኩ አንተ ራስህ እየተናገርክ ነው።+ እኔ የተወለድኩትና ወደ ዓለም የመጣሁት ስለ እውነት ለመመሥከር ነው።+ ከእውነት ጎን የቆመ ሁሉ ቃሌን ይሰማል።” 38 ጲላጦስም “እውነት ምንድን ነው?” አለው።

ይህን ከተናገረ በኋላ እንደገና አይሁዳውያኑ ወዳሉበት ወጥቶ እንዲህ አላቸው፦ “እኔ ምንም ጥፋት አላገኘሁበትም።+ 39 ከዚህም በላይ በልማዳችሁ መሠረት በፋሲካ አንድ ሰው ለእናንተ መፍታቴ አይቀርም።+ ስለዚህ የአይሁዳውያንን ንጉሥ እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁ?” 40 እነሱም እንደገና በመጮኽ “ይህን ሰው አንፈልግም፤ በርባንን ፍታልን!” አሉ። በርባን ግን ወንበዴ ነበር።+

19 ከዚያም ጲላጦስ ኢየሱስን ወስዶ ገረፈው።+ 2 ወታደሮቹም የእሾህ አክሊል ጎንጉነው በራሱ ላይ ደፉበት፤ እንዲሁም ሐምራዊ ልብስ አለበሱት፤+ 3 ወደ እሱ እየቀረቡም “የአይሁዳውያን ንጉሥ ሆይ፣ ሰላም ለአንተ ይሁን!” ይሉት ነበር። ደግሞም በጥፊ ይመቱት ነበር።+ 4 ጲላጦስም ዳግመኛ ወደ ውጭ ወጥቶ “ምንም ጥፋት እንዳላገኘሁበት ታውቁ ዘንድ እነሆ ወደ ውጭ አወጣላችኋለሁ” አላቸው።+ 5 በመሆኑም ኢየሱስ የእሾህ አክሊል እንደደፋና ሐምራዊ ልብስ እንደለበሰ ወደ ውጭ ወጣ። ጲላጦስም “እነሆ፣ ሰውየው!” አላቸው። 6 ይሁን እንጂ የካህናት አለቆቹና የቤተ መቅደስ ጠባቂዎቹ ባዩት ጊዜ “ይሰቀል! ይሰቀል!”*+ እያሉ ጮኹ። ጲላጦስም “እኔ ምንም ጥፋት ስላላገኘሁበት ራሳችሁ ወስዳችሁ ግደሉት”* አላቸው።+ 7 አይሁዳውያኑም “እኛ ሕግ አለን፤ ይህ ሰው ደግሞ ራሱን የአምላክ ልጅ ስላደረገ+ በሕጉ መሠረት መሞት አለበት”+ ሲሉ መለሱለት።

8 ጲላጦስ ያሉትን ነገር ሲሰማ ይበልጥ ፍርሃት አደረበት፤ 9 ዳግመኛም ወደ ገዢው መኖሪያ ገብቶ ኢየሱስን “ለመሆኑ ከየት ነው የመጣኸው?” አለው። ኢየሱስ ግን ምንም መልስ አልሰጠውም።+ 10 ስለሆነም ጲላጦስ “መልስ አትሰጠኝም? ልፈታህም ሆነ ልገድልህ* ሥልጣን እንዳለኝ አታውቅም?” አለው። 11 ኢየሱስም “ከላይ ባይሰጥህ ኖሮ በእኔ ላይ ምንም ሥልጣን አይኖርህም ነበር። ለአንተ አሳልፎ የሰጠኝ ሰው የባሰ ኃጢአት ያለበት ለዚህ ነው” ሲል መለሰለት።

12 ከዚህ የተነሳ ጲላጦስ ኢየሱስን መፍታት የሚችልበትን መንገድ ያስብ ጀመር፤ አይሁዳውያኑ ግን “ይህን ሰው ከፈታኸው አንተ የቄሳር ወዳጅ አይደለህም። ራሱን ንጉሥ የሚያደርግ ሰው ሁሉ የቄሳር ተቃዋሚ ነው” እያሉ ጮኹ።+ 13 ጲላጦስ ይህን ከሰማ በኋላ ኢየሱስን ወደ ውጭ አውጥቶ የድንጋይ ንጣፍ በተባለ ቦታ በፍርድ ወንበር ተቀመጠ፤ ይህ ቦታ በዕብራይስጥ ጋባታ ይባላል። 14 ጊዜው የፋሲካ* የዝግጅት ቀን+ ነበር፤ ሰዓቱ ደግሞ ስድስት ሰዓት ገደማ ነበር። ጲላጦስም አይሁዳውያኑን “እነሆ፣ ንጉሣችሁ!” አላቸው። 15 እነሱ ግን “አስወግደው! አስወግደው! ስቀለው!”* እያሉ ጮኹ። ጲላጦስም “ንጉሣችሁን ልግደለው?” አላቸው። የካህናት አለቆቹም “ከቄሳር በቀር ሌላ ንጉሥ የለንም” ሲሉ መለሱ። 16 በዚህ ጊዜ እንጨት ላይ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጣቸው።+

እነሱም ኢየሱስን ይዘው ወሰዱት። 17 ኢየሱስም የመከራውን እንጨት* ራሱ ተሸክሞ የራስ ቅል ቦታ+ ወደተባለ ስፍራ ወጣ፤ ይህ ቦታ በዕብራይስጥ ጎልጎታ ይባላል።+ 18 በዚያም በእንጨት ላይ ቸነከሩት፤+ ከእሱም ጋር ሁለት ሰዎችን የሰቀሉ ሲሆን ኢየሱስን በመካከል አድርገው አንዱን በዚህ ሌላውን በዚያ ጎን ሰቀሉ።+ 19 በተጨማሪም ጲላጦስ ጽሑፍ ጽፎ በመከራው እንጨት* ላይ አንጠለጠለው። ጽሑፉም “የአይሁዳውያን ንጉሥ፣ የናዝሬቱ ኢየሱስ” የሚል ነበር።+ 20 ኢየሱስ በእንጨት ላይ የተቸነከረበት ቦታ በከተማዋ አቅራቢያ የሚገኝ በመሆኑ ብዙ አይሁዳውያን ይህን ጽሑፍ አነበቡት፤ ጽሑፉም የተጻፈው በዕብራይስጥ፣ በላቲንና በግሪክኛ ነበር። 21 ይሁን እንጂ የአይሁድ የካህናት አለቆች ጲላጦስን “እሱ ‘የአይሁዳውያን ንጉሥ ነኝ’ እንዳለ ጻፍ እንጂ ‘የአይሁዳውያን ንጉሥ’ ብለህ አትጻፍ” አሉት። 22 ጲላጦስም “እንግዲህ የጻፍኩትን ጽፌአለሁ” ሲል መለሰ።

23 ወታደሮቹ ኢየሱስን በእንጨት ላይ ከቸነከሩት በኋላ መደረቢያዎቹን ወስደው እያንዳንዱ ወታደር አንድ አንድ ቁራጭ እንዲደርሰው አራት ቦታ ቆራረጧቸው፤ ከውስጥ ለብሶት የነበረውንም ልብስ ወሰዱ። ሆኖም ልብሱ ከላይ እስከ ታች አንድ ወጥ ሆኖ ያለስፌት የተሠራ ነበር። 24 ስለዚህ እርስ በርሳቸው “ከምንቀደው ዕጣ ተጣጥለን ለማን እንደሚደርስ እንወስን” ተባባሉ።+ ይህም የሆነው “መደረቢያዎቼን እርስ በርሳቸው ተከፋፈሉ፤ በልብሴም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ” የሚለው የቅዱስ መጽሐፉ ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው።+ ወታደሮቹም ያደረጉት ይህንኑ ነበር።

25 ይሁንና ኢየሱስ በተሰቀለበት የመከራ እንጨት* አጠገብ እናቱ፣+ የእናቱ እህት፣ የቀልዮጳ ሚስት ማርያምና መግደላዊቷ ማርያም ቆመው ነበር።+ 26 ስለዚህ ኢየሱስ እናቱንና የሚወደውን ደቀ መዝሙር+ በአቅራቢያው ቆመው ሲያያቸው እናቱን “አንቺ ሴት፣ ልጅሽ ይኸውልሽ!” አላት። 27 ከዚያም ደቀ መዝሙሩን “እናትህ ይህችውልህ!” አለው። ደቀ መዝሙሩም ከዚያ ሰዓት አንስቶ ወደ ራሱ ቤት ወሰዳት።

28 ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ሁሉም ነገር እንደተፈጸመ አውቆ የቅዱስ መጽሐፉ ቃል እንዲፈጸም “ተጠማሁ”+ አለ። 29 በዚያም የኮመጠጠ ወይን ጠጅ የሞላበት ዕቃ ተቀምጦ ነበር። በመሆኑም ወይን ጠጁ ውስጥ የተነከረ ሰፍነግ፣* በሂሶጵ* አገዳ ላይ አድርገው ወደ አፉ አቀረቡለት።+ 30 ኢየሱስ የኮመጠጠውን ወይን ጠጅ ከቀመሰ በኋላ “ተፈጸመ!”+ አለ፤ ራሱንም ዘንበል አድርጎ መንፈሱን ሰጠ።*+

31 ዕለቱ የዝግጅት ቀን+ ስለነበር አይሁዳውያን በሰንበት (ያ ሰንበት ታላቅ ሰንበት* ስለነበር)+ አስከሬኖቹ በመከራ እንጨቶቹ ላይ ተሰቅለው እንዳይቆዩ+ ሲሉ እግራቸው ተሰብሮ እንዲወርዱ ጲላጦስን ጠየቁት። 32 ስለዚህ ወታደሮቹ መጥተው ከእሱ ጋር የተሰቀሉትን የመጀመሪያውን ሰውና የሌላኛውን ሰው እግሮች ሰበሩ። 33 ወደ ኢየሱስ በመጡ ጊዜ ግን ቀደም ብሎ መሞቱን ስላዩ እግሮቹን አልሰበሩም። 34 ሆኖም ከወታደሮቹ አንዱ ጎኑን በጦር ወጋው፤+ ወዲያውም ደምና ውኃ ፈሰሰ። 35 ይህን ያየው ሰውም ምሥክርነት ሰጥቷል፤ ምሥክርነቱም እውነት ነው፤ እናንተም እንድታምኑ ይህ ሰው የሚናገራቸው ነገሮች እውነት እንደሆኑ ያውቃል።+ 36 ይህም የሆነው “ከእሱ አንድ አጥንት እንኳ አይሰበርም”+ የሚለው የቅዱስ መጽሐፉ ቃል እንዲፈጸም ነው። 37 ደግሞም ሌላ የቅዱስ መጽሐፉ ቃል “የወጉትን ያዩታል”+ ይላል።

38 ይህ ከሆነ በኋላ፣ የአርማትያሱ ዮሴፍ የኢየሱስን አስከሬን ለመውሰድ ጲላጦስን ጠየቀ፤ ዮሴፍ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ነበር። ሆኖም አይሁዳውያንን* ይፈራ ስለነበር+ ይህን ለማንም አልተናገረም። ጲላጦስ ከፈቀደለት በኋላ መጥቶ የኢየሱስን አስከሬን ወሰደ።+ 39 ቀደም ሲል በማታ ወደ ኢየሱስ መጥቶ የነበረው ኒቆዲሞስም+ 30 ኪሎ ግራም* ገደማ የሚሆን የከርቤና የእሬት* ድብልቅ * ይዞ መጣ።+ 40 የኢየሱስንም አስከሬን ወስደው በአይሁዳውያን የአገናነዝ ልማድ መሠረት ጥሩ መዓዛ ባላቸው በእነዚህ ቅመሞች ተጠቅመው በበፍታ ጨርቅ ገነዙት።+ 41 እሱ በተገደለበት* ቦታ አቅራቢያ አንድ የአትክልት ስፍራ ነበር፤ በአትክልት ስፍራው ውስጥ ደግሞ ገና ማንም ያልተቀበረበት አዲስ መቃብር ነበር።+ 42 ዕለቱ አይሁዳውያን ለበዓሉ የሚዘጋጁበት ቀን+ ስለነበርና መቃብሩም በአቅራቢያው ይገኝ ስለነበር ኢየሱስን በዚያ አኖሩት።

20 በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን መግደላዊቷ ማርያም በማለዳ፣ ገና ጨለማ ሳለ ወደ መቃብሩ መጣች፤+ መቃብሩ የተዘጋበትም ድንጋይ ተንከባሎ አየች።+ 2 ስለዚህ ወደ ስምዖን ጴጥሮስና ኢየሱስ ይወደው ወደነበረው ወደ ሌላው ደቀ መዝሙር+ እየሮጠች መጥታ “ጌታን ከመቃብሩ ውስጥ ወስደውታል፤+ የት እንዳኖሩትም አናውቅም” አለቻቸው።

3 በዚህ ጊዜ ጴጥሮስና ሌላው ደቀ መዝሙር ወደ መቃብሩ አመሩ። 4 ሁለቱም አብረው ይሮጡ ጀመር፤ ሆኖም ሌላው ደቀ መዝሙር ጴጥሮስን ቀድሞ በመሮጥ መቃብሩ ጋ ደረሰ። 5 ጎንበስ ብሎ ወደ ውስጥ ሲመለከት የበፍታ ጨርቆቹ እዚያ ተቀምጠው አየ፤+ ወደ ውስጥ ግን አልገባም። 6 ከዚያም ስምዖን ጴጥሮስ ተከትሎት መጥቶ መቃብሩ ውስጥ ገባ። የበፍታ ጨርቆቹም በዚያ ተቀምጠው አየ። 7 በራሱ ላይ የነበረው ጨርቅ፣ ከመግነዝ ጨርቆቹ ጋር ሳይሆን ለብቻው ተጠቅልሎ አንድ ቦታ ላይ ተቀምጦ አየ። 8 ከዚያም ቀድሞ ወደ መቃብሩ ደርሶ የነበረው ሌላው ደቀ መዝሙርም ወደ ውስጥ ገባ፤ እሱም አይቶ አመነ። 9 ከሞት መነሳት እንዳለበት የሚናገረውን የቅዱስ መጽሐፉን ቃል ገና አልተረዱም ነበር።+ 10 ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ ወደየቤታቸው ተመልሰው ሄዱ።

11 ይሁን እንጂ ማርያም እዚያው መቃብሩ አጠገብ ቆማ ታለቅስ ነበር። እያለቀሰችም ወደ መቃብሩ ውስጥ ለማየት ጎንበስ አለች፤ 12 ነጭ ልብስ የለበሱ ሁለት መላእክትም+ የኢየሱስ አስከሬን አርፎበት በነበረው ቦታ አንዱ በራስጌው ሌላው በግርጌው ተቀምጠው አየች። 13 እነሱም “አንቺ ሴት፣ ለምን ታለቅሻለሽ?” አሏት። እሷም “ጌታዬን ወስደውታል፤ የት እንዳደረጉትም አላውቅም” አለቻቸው። 14 ይህን ካለች በኋላ ዞር ስትል ኢየሱስን በዚያ ቆሞ አየችው፤ ነገር ግን ኢየሱስ መሆኑን አላወቀችም።+ 15 ኢየሱስም “አንቺ ሴት፣ ለምን ታለቅሻለሽ? የምትፈልጊው ማንን ነው?” አላት። እሷም አትክልተኛው ስለመሰላት “ጌታዬ፣ አንተ ከዚህ ወስደኸው ከሆነ የት እንዳደረግከው ንገረኝ፤ እኔም እወስደዋለሁ” አለችው። 16 ኢየሱስም “ማርያም!” አላት። እሷም ዞር ብላ በዕብራይስጥ “ራቦኒ!” አለችው (ትርጉሙም “መምህር!” ማለት ነው)። 17 ኢየሱስም እንዲህ አላት፦ “ጥብቅ አድርገሽ አትያዥኝ፤ ገና ወደ አባቴ አላረግኩምና። ይልቁንስ ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ+ ‘ወደ አባቴና+ ወደ አባታችሁ፣ ወደ አምላኬና+ ወደ አምላካችሁ ላርግ ነው’ ብለሽ ንገሪያቸው።” 18 መግደላዊቷ ማርያም መጥታ “ጌታን አየሁት!” ብላ ለደቀ መዛሙርቱ አበሰረቻቸው፤ እሱ ያላትንም ነገረቻቸው።+

19 የሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን በነበረው በዚያው ቀን ምሽት ላይ ደቀ መዛሙርቱ አይሁዳውያኑን* በመፍራታቸው በሮቹን ቆልፈው ተቀምጠው ሳለ ኢየሱስ መጥቶ በመካከላቸው ቆመና “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው።+ 20 ይህን ካለ በኋላ እጆቹንና ጎኑን አሳያቸው።+ ደቀ መዛሙርቱም ጌታን በማየታቸው እጅግ ተደሰቱ።+ 21 ኢየሱስም ዳግመኛ “ሰላም ለእናንተ ይሁን።+ አብ እኔን እንደላከኝ፣+ እኔም እናንተን እልካችኋለሁ”+ አላቸው። 22 ይህን ካለ በኋላ እፍ አለባቸውና እንዲህ አላቸው፦ “መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ።+ 23 የማንንም ሰው ኃጢአት ይቅር ብትሉ ኃጢአቱ ይቅር ይባላል፤ ይቅር የማትሉት ሰው ሁሉ ደግሞ ኃጢአቱ እንዳለ ይጸናል።”

24 ይሁን እንጂ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው ዲዲሞስ* የሚባለው ቶማስ+ ኢየሱስ በመጣበት ጊዜ አብሯቸው አልነበረም። 25 ስለዚህ ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት “ጌታን አየነው!” አሉት። እሱ ግን “በእጆቹ ላይ ምስማሮቹ የተቸነከሩበትን ምልክት ካላየሁ እንዲሁም ጣቴን ምስማሮቹ በነበሩበት ቦታ ካላስገባሁና እጄን በጎኑ ካላስገባሁ+ ፈጽሞ አላምንም” አላቸው።

26 እንደገናም ከስምንት ቀን በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ቤት ውስጥ ነበሩ፤ ቶማስም ከእነሱ ጋር ነበር። በሮቹ ተቆልፈው የነበሩ ቢሆንም ኢየሱስ መጣና በመካከላቸው ቆሞ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አለ።+ 27 ከዚያም ቶማስን “ጣትህን እዚህ ክተት፤ እጆቼንም ተመልከት፤ እጅህንም አምጣና በጎኔ አስገባ። መጠራጠርህን* ተውና እመን” አለው። 28 ቶማስም መልሶ “ጌታዬ፣ አምላኬ!” አለው። 29 ኢየሱስ “ስላየኸኝ አመንክ? ሳያዩ የሚያምኑ ደስተኞች ናቸው” አለው።

30 እርግጥ ኢየሱስ በዚህ ጥቅልል ውስጥ ያልተጻፉ ሌሎች ብዙ ተአምራዊ ምልክቶችም በደቀ መዛሙርቱ ፊት አድርጓል።+ 31 ሆኖም እነዚህ የተጻፉት ኢየሱስ በእርግጥ ክርስቶስ እንዲሁም የአምላክ ልጅ እንደሆነ እንድታምኑና በማመናችሁም በስሙ አማካኝነት ሕይወት እንዲኖራችሁ ነው።+

21 ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በጥብርያዶስ* ባሕር እንደገና ለደቀ መዛሙርቱ ተገለጠ።* የተገለጠውም በዚህ መንገድ ነበር፤ 2 ስምዖን ጴጥሮስ፣ ዲዲሞስ* የሚባለው ቶማስ፣+ የገሊላ ቃና ሰው የሆነው ናትናኤል፣+ የዘብዴዎስ ልጆችና+ ሌሎች ሁለት ደቀ መዛሙርቱ አብረው ነበሩ። 3 ስምዖን ጴጥሮስ “ዓሣ ላጠምድ መሄዴ ነው” አላቸው። እነሱም “እኛም አብረንህ እንሄዳለን” አሉት። ወጥተው ሄዱና ጀልባ ላይ ተሳፈሩ፤ በዚያ ሌሊት ግን አንድም ዓሣ አልያዙም።+

4 ይሁን እንጂ ጎህ ሲቀድ ኢየሱስ መጥቶ በባሕሩ ዳርቻ ቆመ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ኢየሱስ መሆኑን አላወቁም ነበር።+ 5 ከዚያም ኢየሱስ “ልጆቼ፣ የሚበላ ነገር* አላችሁ?” አላቸው። እነሱም “የለንም!” ብለው መለሱለት። 6 እሱም “መረቡን ከጀልባዋ በስተ ቀኝ ጣሉት፤ ዓሣ ታገኛላችሁ” አላቸው። እነሱም መረቡን ጣሉ፤ ከዓሣውም ብዛት የተነሳ መረቡን መጎተት አቃታቸው።+ 7 በዚህ ጊዜ፣ ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀ መዝሙር+ ጴጥሮስን “ጌታ እኮ ነው!” አለው። ስምዖን ጴጥሮስም ጌታ መሆኑን ሲሰማ ከወገቡ በላይ ራቁቱን* ስለነበር መደረቢያውን ለበሰና* ዘሎ ባሕሩ ውስጥ ገባ። 8 ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ግን ከባሕሩ ዳርቻ ብዙም ሳይርቁ 90 ሜትር ገደማ* ርቀት ላይ ስለነበሩ በዓሣዎች የተሞላውን መረብ እየጎተቱ በትንሿ ጀልባ መጡ።

9 ወደ ባሕሩ ዳርቻ በደረሱ ጊዜ በከሰል ፍም ላይ የተቀመጠ ዓሣ እንዲሁም ዳቦ አዩ። 10 ኢየሱስ “አሁን ከያዛችሁት ዓሣ የተወሰነ አምጡ” አላቸው። 11 ስለዚህ ስምዖን ጴጥሮስ ጀልባዋ ላይ ወጥቶ በትላልቅ ዓሣዎች የተሞላውን መረብ ወደ ባሕሩ ዳርቻ ጎተተው፤ የዓሣዎቹም ብዛት 153 ነበር። መረቡ ይህን ያህል ብዙ ዓሣ ቢይዝም አልተቀደደም። 12 ኢየሱስ “ኑ፣ ቁርሳችሁን ብሉ” አላቸው። ጌታ መሆኑን አውቀው ስለነበር ከደቀ መዛሙርቱ መካከል “አንተ ማን ነህ?” ብሎ ሊጠይቀው የደፈረ አልነበረም። 13 ኢየሱስም መጥቶ ዳቦውን አነሳና ሰጣቸው፤ ዓሣውንም አንስቶ እንዲሁ አደረገ። 14 ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ሲገለጥ ይህ ለሦስተኛ ጊዜ ነበር።+

15 ቁርስ በልተው ከጨረሱም በኋላ ኢየሱስ፣ ስምዖን ጴጥሮስን “የዮሐንስ ልጅ ስምዖን፣ ከእነዚህ አስበልጠህ ትወደኛለህ?” አለው። እሱም “አዎ፣ ጌታ ሆይ፣ በጣም እንደምወድህ ታውቃለህ” ሲል መለሰለት። ኢየሱስም “ጠቦቶቼን መግብ” አለው።+ 16 ደግሞም ለሁለተኛ ጊዜ “የዮሐንስ ልጅ ስምዖን፣ ትወደኛለህ?” አለው። እሱም “አዎ፣ ጌታ ሆይ፣ በጣም እንደምወድህ ታውቃለህ” ሲል መለሰለት። ኢየሱስም “ግልገሎቼን ጠብቅ” አለው።+ 17 ለሦስተኛ ጊዜም “የዮሐንስ ልጅ ስምዖን፣ በጣም ትወደኛለህ?” አለው። ጴጥሮስ ለሦስተኛ ጊዜ “በጣም ትወደኛለህ?” ብሎ ስለጠየቀው አዘነ። በመሆኑም “ጌታ ሆይ፣ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ በጣም እንደምወድህ ታውቃለህ” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ “ግልገሎቼን መግብ።+ 18 እውነት እውነት እልሃለሁ፣ ወጣት ሳለህ ራስህ ለብሰህ ወደፈለግክበት ቦታ ትሄድ ነበር። ስታረጅ ግን እጅህን ትዘረጋለህ፤ ሌላ ሰውም ያለብስሃል፤ ወደማትፈልግበትም ቦታ ይወስድሃል።” 19 ይህን የተናገረው፣ ጴጥሮስ በምን ዓይነት አሟሟት አምላክን እንደሚያከብር ለማመልከት ነበር። ይህን ካለ በኋላ “እኔን መከተልህን ቀጥል” አለው።+

20 ጴጥሮስ ዞር ሲል ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀ መዝሙር+ ሲከተላቸው አየ፤ ይህ ደቀ መዝሙር ራት በበሉ ጊዜ ወደ ኢየሱስ ደረት ተጠግቶ “ጌታ ሆይ፣ አሳልፎ የሚሰጥህ ማን ነው?” ብሎ የጠየቀው ነው። 21 ጴጥሮስም ባየው ጊዜ ኢየሱስን “ጌታ ሆይ፣ ይህስ ሰው ምን ይሆናል?” አለው። 22 ኢየሱስም “እኔ እስክመጣ ድረስ እንዲቆይ ብፈቅድ አንተ ምን ቸገረህ? አንተ እኔን መከተልህን ቀጥል” አለው። 23 በመሆኑም ይህ ደቀ መዝሙር አይሞትም የሚል ወሬ በወንድሞች መካከል ተሰራጨ። ይሁንና ኢየሱስ “እኔ እስክመጣ ድረስ እንዲቆይ ብፈቅድ አንተ ምን ቸገረህ?” አለው እንጂ አይሞትም አላለውም።

24 ስለ እነዚህ ነገሮች የሚመሠክረውና እነዚህን ነገሮች የጻፈው ይህ ደቀ መዝሙር ነው፤+ እሱ የሚሰጠው ምሥክርነትም እውነት እንደሆነ እናውቃለን።

25 እርግጥ ኢየሱስ ያደረጋቸው ሌሎች ብዙ ነገሮችም አሉ፤ እነዚህ ሁሉ በዝርዝር ቢጻፉ ዓለም ራሱ የተጻፉትን ጥቅልሎች ለማስቀመጥ የሚበቃ ቦታ የሚኖረው አይመስለኝም።+

ወይም “መለኮት።”

ወይም “ጸጋንና።”

ወይም “በአብ እቅፍ።” ይህ አባባል ልዩ ሞገስ ማግኘትን ያመለክታል።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ቃል በቃል “አንቺ ሴት፣ ለእኔና ለአንቺ ምንድን ነው?” ይህ በአንድ ጉዳይ አለመስማማትን የሚያሳይ ፈሊጣዊ አነጋገር ነው። “አንቺ ሴት” የሚለው አገላለጽ አክብሮት እንደጎደለው የሚያሳይ አይደለም።

እዚህ ላይ የተጠቀሰው የፈሳሽ መለኪያ ባዶስ ሊሆን ይችላል፤ አንድ ባዶስ 22 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ወይም “የማለፍ በዓል።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “ገበያ።”

“ከላይ ካልተወለደ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “በልጁ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ።”

መጥፎ ነገር መሥራትን ልማድ የሚያደርግን ሰው ያመለክታል።

ቃል በቃል “በማኅተም አጽንቷል።”

ወይም “ለክቶ።”

ወይም “በወልድ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ።”

ወይም “ምንጩ።”

ወይም “መዳኑን።”

ወይም “እግራቸው ወይም እጃቸው የሰለለ።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ3ን ተመልከት።

ወይም “መኝታህን።”

ወይም “መኝታውንም።”

ወይም “መኝታህን።”

ወይም “መኝታህን።”

ወይም “መኝታህን።”

ወይም “በራሱ የሕይወት ስጦታ እንዳለው።”

መጥፎ ነገር መሥራትን ልማድ ያደረጉ ሰዎችን ያመለክታል።

ማቴ 4:18 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ቃል በቃል “25 ወይም 30 ስታዲዮን ገደማ።” ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ቃል በቃል “የማረጋገጫ ማኅተሙን አትሟል።”

ወይም “በእሱ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

“ሕዝብ በተሰበሰበበት” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “ዲያብሎስ።”

ወይም “መመላለሱን።”

የአይሁዳውያን ሃይማኖታዊ መሪዎችን ያመለክታል።

የረቢዎችን ትምህርት ቤት ያመለክታል።

ቃል በቃል “ጽሑፎችን።”

ወይም “መፍረዳችሁን ተዉ።”

ወይም “ያስሩት።”

ወይም “ሊያስሩት።”

በእጅ የተጻፉ በርካታ ጥንታዊና ከፍተኛ ተአማኒነት ያላቸው ቅጂዎች ከዮሐ 7:53 እስከ 8:11 ድረስ ያለውን ሐሳብ አይጨምሩም።

ወይም “በሰው መሥፈርት።”

ወይም “በፆታ ብልግና።” ግሪክኛ፣ ፖርኒያ። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “እሱ ከመጀመሪያው አንስቶ።”

ዮሐ 7:13 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።

ወይም “እጅ ነሳው።”

ወይም “ነፍሱን።”

ወይም “ነፍሴንም።”

ወይም “ነፍሴን።”

ወይም “ነፍሴን።”

ወይም “ቤተ መቅደሱ ለአምላክ የተወሰነበት በዓል (ሃኑካ)።”

ወይም “ነፍሳችንን።”

ወይም “እኔና አብ አንድነት አለን።”

ወይም “እንደ አምላክ ያላችሁ።”

ወይም “መንትያ።”

ቃል በቃል “15 ስታዲዮን ገደማ።” ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ወይም “በእኔ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ።”

ቃል በቃል “በመንፈሱ ቃተተ።”

ቤተ መቅደሱን ያመለክታል።

ወይም “ማሰር።”

ክብደቱ አንድ የሮማውያን ፓውንድ ሲሆን 327 ግራም ገደማ ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ግሪክኛ፣ ሆሳዕና።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “ነፍሱን የሚወድ ሁሉ።”

ወይም “ነፍሱን።”

ወይም “ነፍሴ ተጨንቃለች።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “እኛ የተናገርነውን።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “የራሱ የሆኑትን።”

ወይም “የመተጣጠብ ግዴታ አለባችሁ።”

ወይም “በእኔ ላይ ተነሳ።”

ወይም “ነፍሴን።”

ወይም “ነፍስህን።”

ወይም “ወደ ቤቴ እወስዳችኋለሁ።”

ወይም “አጽናኝ።”

ወይም “ወላጅ አልባ እንደሆኑ ልጆች።”

ወይም “አጽናኝ።”

ወይም “ይገርዘዋል።”

ወይም “ነፍሱን።”

ወይም “አጽናኝ።”

ወይም “አጽናኙ።”

ዮሐ 16:13, 14 ላይ የተጠቀሰው “እሱ” የሚለው ቃል፣ ቁጥር 7 ላይ “ረዳቱ” ተብሎ የተጠቀሰውን ያመለክታል። ኢየሱስ “ረዳቱ” (እዚህ ላይ በግሪክኛ በተባዕታይ ፆታ ተጠቅሷል) የሚለውን ቃል የተጠቀመው አካል የሌለውን ኃይል ይኸውም መንፈስ ቅዱስን በሰውኛ ዘይቤ ለመግለጽ ነው፤ ግሪክኛው ቋንቋ መንፈስ ቅዱስን ሲገልጽ ተባዕታይም ሆነ አንስታይ ፆታ አይጠቀምም።

ወይም “በሰው ዘር፤ በሰዎች።”

እውነተኛው አምላክ እሱ ብቻ መሆኑን ያመለክታል።

ወይም “እውቀት መቅሰም።” እዚህ ላይ የገባው የግሪክኛ ግስ ቀጣይነት ያለውን ድርጊት ያመለክታል።

ወይም “አሳውቄአቸዋለሁ።”

ወይም “ታዘዋል።”

ወይም “አንድነት እንዳለን።”

ወይም “አንድነት እንዲኖራቸው።”

ሰይጣንን ያመለክታል።

ወይም “ለያቸው።”

ወይም “ፍጹም አንድነት እንዲኖራቸው።”

ይህ አባባል የአዳምንና የሔዋንን ዘሮች ያመለክታል።

ወይም “የቄድሮንን የክረምት ወንዝ።”

ወይም “መሥክር።”

ወይም “ወንጀለኛ።”

ወይም “እንጨት ላይ ይሰቀል! እንጨት ላይ ይሰቀል!”

ወይም “እንጨት ላይ ስቀሉት!”

ወይም “በእንጨት ላይ ልሰቅልህ።”

እዚህ ላይ “ፋሲካ” የሚለው ቃል ለሰባት ቀናት የሚከበረውን የቂጣ በዓል ጨምሮ የፋሲካን ሳምንት ያመለክታል።

ወይም “እንጨት ላይ ስቀለው!”

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ስፖንጅ ተብሎ ከሚጠራ የባሕር እንስሳ የሚገኝ ውኃን መምጠጥና መያዝ የሚችል ነገር።

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “ሞተ።”

የቂጣ በዓል የሚከበርበት የመጀመሪያው ቀን ምንጊዜም የሰንበት ቀን እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠር ነበር። ይህ ሰንበት ከሳምንቱ የሰንበት ቀን ጋር ሲገጣጠም ደግሞ ታላቅ ሰንበት ተብሎ ይጠራል።

የአይሁዳውያን ሃይማኖታዊ መሪዎችን ያመለክታል።

ወይም “100 የሮማውያን ፓውንድ።” ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ሽቶ ለመሥራት የሚያገለግል ጥሩ መዓዛ ያለው ንጥረ ነገር የሚገኝበትን ዛፍ ያመለክታል።

“ጥቅልል” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “እንጨት ላይ በተሰቀለበት።”

የአይሁዳውያን ሃይማኖታዊ መሪዎችን ያመለክታል።

ወይም “መንትያ።”

ቃል በቃል “አለማመንህን።”

ማቴ 4:18 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።

ወይም “ታየ።”

ወይም “መንትያ።”

ወይም “ዓሣ።”

ወይም “ከውስጥ በለበሳት ልብስ ብቻ።”

ወይም “ታጠቀና።”

ቃል በቃል “200 ክንድ ገደማ።” ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

    የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ ጽሑፎች (2011-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ