ሁለተኛ ሳሙኤል
1 ሳኦል ከሞተ በኋላ ዳዊት አማሌቃውያንን ድል አድርጎ* ሲመለስ በጺቅላግ+ ሁለት ቀን ቆየ። 2 በሦስተኛውም ቀን አንድ ሰው ልብሱን ቀዶና በራሱ ላይ አቧራ ነስንሶ ከሳኦል ሰፈር መጣ። እሱም ዳዊት ጋ ሲደርስ መሬት ላይ ተደፍቶ ሰገደ።
3 ዳዊትም “ከየት ነው የመጣኸው?” ሲል ጠየቀው፤ እሱም “ከእስራኤል ሰፈር አምልጬ ነው” በማለት መለሰለት። 4 ዳዊትም “እስቲ የሆነውን ነገር ንገረኝ” አለው። እሱም “ሰዎቹ ከውጊያው ሸሽተዋል፤ ብዙዎቹም ወድቀዋል፤ ሞተዋል። ሳኦልና ልጁ ዮናታንም እንኳ ሞተዋል” አለው።+ 5 ከዚያም ዳዊት ወሬውን ያመጣለትን ወጣት “ለመሆኑ ሳኦልና ልጁ ዮናታን መሞታቸውን እንዴት አወቅክ?” ሲል ጠየቀው። 6 ወጣቱም እንዲህ አለው፦ “እንደ አጋጣሚ ሆኖ ጊልቦአ+ ተራራ ላይ ነበርኩ፤ እዚያም ሳኦል ጦሩን ተመርኩዞ ቆሞ ነበር፤ ሠረገሎቹና ፈረሰኞቹም ደረሱበት።+ 7 ወደ ኋላም ዞር ብሎ ሲያየኝ ጠራኝ፤ እኔም ‘አቤት!’ አልኩት። 8 እሱም ‘አንተ ማን ነህ?’ አለኝ፤ እኔም ‘አማሌቃዊ+ ነኝ’ አልኩት። 9 ከዚያም ‘ሕይወቴ ያላለፈች* ቢሆንም ከባድ ሥቃይ ላይ ስለሆንኩ እባክህ ላዬ ላይ ቁምና ግደለኝ’ አለኝ። 10 በመሆኑም መቼም ቆስሎ ከወደቀ በኋላ እንደማይተርፍ ስላወቅኩ ላዩ ላይ ቆሜ ገደልኩት።+ ከዚያም ራሱ ላይ ያለውን ዘውድና ክንዱ ላይ የነበረውን አምባር ወስጄ ወደ ጌታዬ ይዤ መጣሁ።”
11 በዚህ ጊዜ ዳዊት ልብሱን ቀደደ፤ አብረውት ያሉትም ሰዎች ሁሉ እንደዚሁ አደረጉ። 12 ከዚያም ለሳኦል፣ ለልጁ ለዮናታን፣ ለይሖዋ ሕዝብና ለእስራኤል ቤት+ እስከ ማታ ድረስ ጮኹ፣ አለቀሱ እንዲሁም ጾሙ፤+ በሰይፍ ወድቀዋልና።
13 ዳዊትም ወሬውን ያመጣለትን ወጣት “የየት አገር ሰው ነህ?” አለው። እሱም “የባዕድ አገር ሰው የሆነ የአንድ አማሌቃዊ ልጅ ነኝ” አለው። 14 ከዚያም ዳዊት “ይሖዋ የቀባውን ለመግደል እጅህን ስታነሳ እንዴት አልፈራህም?” አለው።+ 15 ዳዊትም ከወጣቶቹ መካከል አንዱን ጠርቶ “በል ቅረብና ምታው” አለው። እሱም መታው፤ ወጣቱም ሞተ።+ 16 ከዚያም ዳዊት “‘ይሖዋ የቀባውን እኔ ራሴ ገድዬዋለሁ’ በማለት የገዛ አፍህ ስለመሠከረብህ ደምህ በራስህ ላይ ነው” አለው።+
17 ዳዊትም ለሳኦልና ለልጁ ለዮናታን ይህን የሐዘን እንጉርጉሮ ተቀኘ፤+ 18 እንዲሁም በያሻር መጽሐፍ+ ተጽፎ የሚገኘውን “ቀስት” የተባለውን ሙሾ* የይሁዳ ልጆች እንዲማሩ አዘዘ።
19 “እስራኤል ሆይ፣ ውበት በኮረብቶችህ ላይ ተገድሎ ተጋድሟል።+
ኃያላኑ እንዴት እንዲህ ይውደቁ!
21 እናንተ የጊልቦአ ተራሮች፣+
ጠል አያረስርሳችሁ ወይም ዝናብ አይዝነብባችሁ፣
ለቅዱስ መዋጮዎች የሚሆን እህል የሚያበቅሉ ማሳዎችም አይገኙባችሁ፣+
በዚያ የኃያላኑ ጋሻ ረክሷልና፣
የሳኦልም ጋሻ ከእንግዲህ በዘይት አይወለወልም።
24 እናንተ የእስራኤል ሴቶች ልጆች፣
የተንቆጠቆጡ ደማቅ ቀይ ልብሶችን ላለበሳችሁ፣
ልብሶቻችሁንም በወርቅ ላስጌጠላችሁ ለሳኦል አልቅሱ።
25 ኃያላኑ በጦርነት ላይ እንዴት እንዲህ ይውደቁ!
ዮናታን በኮረብቶችህ ላይ ተገድሎ ተጋድሟል!+
26 ወንድሜ ዮናታን፣ በአንተ የተነሳ ተጨንቄአለሁ፤
አንተ በእኔ ዘንድ እጅግ የተወደድክ ነበርክ።+
የአንተ ፍቅር ለእኔ ከሴት ፍቅር ይበልጥ ነበር።+
27 ኃያላኑ እንዴት እንዲህ ይውደቁ፤
የጦር መሣሪያዎቹስ እንዴት እንዲህ ይጥፉ!”
2 ከዚህ በኋላ ዳዊት “ከይሁዳ ከተሞች ወደ አንዱ ልውጣ?” በማለት ይሖዋን ጠየቀ።+ ይሖዋም “ውጣ” አለው። ዳዊትም “ወዴት ብሄድ ይሻላል?” አለ። እሱም “ወደ ኬብሮን”+ አለው። 2 በመሆኑም ዳዊት ከሁለቱ ሚስቶቹ ማለትም ከኢይዝራኤላዊቷ ከአኪኖዓም+ እና የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት ከነበረችው ከአቢጋኤል+ ጋር ወደዚያ ወጣ። 3 በተጨማሪም ዳዊት አብረውት የነበሩትን ሰዎች+ እያንዳንዳቸውን ከነቤተሰባቸው ይዞ ወጣ፤ እነሱም በኬብሮን ዙሪያ በሚገኙ ከተሞች ውስጥ መኖር ጀመሩ። 4 ከዚያም የይሁዳ ሰዎች መጥተው በዚያ ዳዊትን በይሁዳ ቤት ላይ ንጉሥ አድርገው ቀቡት።+
ለዳዊትም “ሳኦልን የቀበሩት የኢያቢስጊልያድ ሰዎች ናቸው” ብለው ነገሩት። 5 በመሆኑም ዳዊት ወደ ኢያቢስጊልያድ ሰዎች መልእክተኞችን በመላክ እንዲህ አላቸው፦ “ጌታችሁን ሳኦልን በመቅበር ለእሱ ታማኝ ፍቅር ስላሳያችሁ ይሖዋ ይባርካችሁ።+ 6 ይሖዋ ታማኝ ፍቅርና ታማኝነት ያሳያችሁ። እኔም ይህን ስላደረጋችሁ ደግነት አደርግላችኋለሁ።+ 7 እንግዲህ አሁን ጌታችሁ ሳኦል ስለሞተና የይሁዳም ቤት እኔን በላያቸው ንጉሥ አድርገው ስለቀቡኝ እጆቻችሁን አበርቱ፤ ደፋሮችም ሁኑ።”
8 የሳኦል ሠራዊት አለቃ የሆነው የኔር ልጅ አበኔር+ ግን የሳኦልን ልጅ ኢያቡስቴን+ ወስዶ ወደ ማሃናይም+ አሻገረው፤ 9 እሱንም በጊልያድ፣+ በአሱራውያን፣ በኢይዝራኤል፣+ በኤፍሬምና+ በቢንያም እንዲሁም በእስራኤል ሁሉ ላይ አነገሠው። 10 የሳኦል ልጅ ኢያቡስቴ በእስራኤል ላይ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 40 ዓመት ነበር፤ እሱም ለሁለት ዓመት ገዛ። የይሁዳ ቤት ግን ዳዊትን ደገፈ።+ 11 ዳዊት በኬብሮን ንጉሥ ሆኖ በይሁዳ ቤት ላይ የገዛበት ጊዜ* ሰባት ዓመት ከስድስት ወር ነበር።+
12 ከጊዜ በኋላ የኔር ልጅ አበኔርና የሳኦል ልጅ የኢያቡስቴ አገልጋዮች ከማሃናይም+ ወደ ገባኦን+ ወጡ። 13 የጽሩያ+ ልጅ ኢዮዓብና+ የዳዊት አገልጋዮችም ወጥተው በገባኦን ኩሬ አጠገብ አገኟቸው፤ አንደኛው ቡድን ከኩሬው በዚህኛው በኩል ሌላኛው ቡድን ደግሞ ከኩሬው በዚያኛው በኩል ተቀመጠ። 14 በመጨረሻም አበኔር ኢዮዓብን “እስቲ ወጣቶቹ ይነሱና በፊታችን ይፋለሙ”* አለው። ኢዮዓብም “እሺ ይነሱ” አለ። 15 በመሆኑም ተነሱ፤ ከሳኦል ልጅ ከኢያቡስቴ 12 ቢንያማውያን፣ ከዳዊት አገልጋዮችም 12 ሰዎች ተቆጥረው ተሻገሩ። 16 ከዚያም አንዱ የሌላውን ራስ በመያዝ ሰይፉን በባላጋራው ጎን እየሻጠ ሁሉም ተያይዘው ወደቁ። ስለዚህ በገባኦን የሚገኘው ያ ቦታ ሄልቃትሃጽጹሪም ተባለ።
17 በዚያን ዕለት የተነሳው ውጊያ እጅግ ከባድ ነበር፤ በመጨረሻም አበኔርና የእስራኤል ሰዎች በዳዊት አገልጋዮች ፊት ተሸነፉ። 18 ሦስቱ የጽሩያ+ ልጆች ኢዮዓብ፣+ አቢሳ+ እና አሳሄል+ እዚያ ነበሩ፤ አሳሄል በመስክ ላይ እንዳለች የሜዳ ፍየል ፈጣን ሯጭ ነበር። 19 አሳሄልም አበኔርን ማሳደዱን ተያያዘው፤ እሱን ከማሳደድ ወደ ቀኝም ሆነ ወደ ግራ ዞር አላለም። 20 አበኔርም ወደ ኋላ ዞር ብሎ ተመለከተና “አሳሄል፣ አንተ ነህ?” ሲል ጠየቀ፤ እሱም “አዎ፣ እኔ ነኝ” አለው። 21 ከዚያም አበኔር “ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ዞር ብለህ ከወጣቶቹ መካከል አንዱን ያዝና ያለውን ነጥቀህ ለራስህ ውሰድ” አለው። አሳሄል ግን እሱን ማሳደዱን መተው አልፈለገም። 22 በመሆኑም አበኔር አሳሄልን እንደገና “እኔን ማሳደድህን ተው። እኔስ ለምን ልግደልህ? የወንድምህን የኢዮዓብንስ ፊት እንዴት ብዬ አያለሁ?” አለው። 23 እሱ ግን ለመተው ፈቃደኛ አልሆነም፤ በመሆኑም አበኔር በጦሩ የኋላ ጫፍ ሆዱን ወጋው፤+ ጦሩም በጀርባው ዘልቆ ወጣ፤ እሱም እዚያው ወድቆ ወዲያውኑ ሞተ። በዚያ የሚያልፍ ሰው ሁሉ አሳሄል ወድቆ የሞተበት ስፍራ ሲደርስ ቆም ይል ነበር።
24 ከዚያም ኢዮዓብና አቢሳ አበኔርን ማሳደድ ጀመሩ። ወደ ገባኦን ምድረ በዳ በሚወስደው መንገድ ላይ ከጊያህ ፊት ለፊት ያለው የአማ ኮረብታ ጋ ሲደርሱ ፀሐይ ጠለቀች። 25 ቢንያማውያንም በአበኔር ዙሪያ ተሰበሰቡ፤ እነሱም ግንባር በመፍጠር በአንድ ኮረብታ አናት ላይ ቆሙ። 26 ከዚያም አበኔር ኢዮዓብን ጠርቶ እንዲህ አለው፦ “ይህ ሰይፍ ያለገደብ ሰው መብላት አለበት? ውጤቱስ መራራ እንደሚሆን አንተ ራስህ ሳታውቀው ቀርተህ ነው? ሰዎቹ ወንድሞቻቸውን ከማሳደድ እንዲመለሱ የማትነግራቸው እስከ መቼ ነው?” 27 በዚህ ጊዜ ኢዮዓብ “ሕያው በሆነው በእውነተኛው አምላክ እምላለሁ፣ አንተ ይህን ባትናገር ኖሮ ሰዎቹ እስኪነጋ ድረስ ወንድሞቻቸውን ማሳደዳቸውን አያቆሙም ነበር” አለ። 28 ኢዮዓብም ቀንደ መለከት ነፋ፤ የእሱ ሰዎችም እስራኤልን ማሳደዳቸውን ተዉ፤ ውጊያውም አቆመ።
29 ከዚያም አበኔርና ሰዎቹ ሌሊቱን ሙሉ በአረባ+ ሲጓዙ አደሩ፤ ዮርዳኖስንም በመሻገር ሸለቆውን* ሁሉ አቋርጠው በመጨረሻ ማሃናይም+ደረሱ። 30 ኢዮዓብም አበኔርን ከማሳደድ ተመልሶ ሕዝቡን በሙሉ አንድ ላይ ሰበሰበ። ከዳዊትም አገልጋዮች መካከል አሳሄልን ጨምሮ 19 ሰዎች መጉደላቸው ታወቀ። 31 የዳዊት አገልጋዮች ግን ቢንያማውያንንና የአበኔርን ሰዎች ድል ያደረጓቸው ከመሆኑም ሌላ ከእነሱ መካከል 360 ሰዎችን ገድለው ነበር። 32 እነሱም አሳሄልን+ ወስደው በቤተልሔም+ በሚገኘው በአባቱ የመቃብር ቦታ ቀበሩት። ከዚያም ኢዮዓብና ሰዎቹ ሌሊቱን ሙሉ ሲገሰግሱ አድረው ንጋት ላይ ኬብሮን+ ደረሱ።
3 በሳኦል ቤትና በዳዊት ቤት መካከል የሚደረገው ውጊያ ለረጅም ጊዜ ዘለቀ፤ ዳዊት እየበረታ+ ሲሄድ የሳኦል ቤት ግን እየተዳከመ+ መጣ።
2 በዚህ መሃል ዳዊት በኬብሮን ወንዶች ልጆች ተወለዱለት።+ የበኩር ልጁ ከኢይዝራኤላዊቷ ከአኪኖዓም+ የወለደው አምኖን+ ነበር። 3 ሁለተኛው ልጁ የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት ከነበረችው ከአቢጋኤል+ የወለደው ኪልአብ ሲሆን ሦስተኛው ልጁ ደግሞ የገሹር ንጉሥ የታልማይ+ ልጅ የሆነችው የማአካ ልጅ አቢሴሎም+ ነበር። 4 አራተኛው ልጁ የሃጊት ልጅ አዶንያስ፣+ አምስተኛው ልጁ ደግሞ የአቢጣል ልጅ ሰፋጥያህ ነበር። 5 ስድስተኛው ልጁ ኤግላ ከተባለችው ሚስቱ የወለደው ይትረአም ነበር። እነዚህ ዳዊት በኬብሮን ሳለ የተወለዱለት ናቸው።
6 በሳኦል ቤትና በዳዊት ቤት መካከል የነበረው ጦርነት በቀጠለበት ወቅት አበኔር+ በሳኦል ቤት ውስጥ የነበረውን ቦታ እያጠናከረ ሄደ። 7 ሳኦል የአያ ልጅ የሆነች ሪጽፋ+ የተባለች ቁባት ነበረችው። በኋላም ኢያቡስቴ+ አበኔርን “ከአባቴ ቁባት ጋር ግንኙነት የፈጸምከው ለምንድን ነው?” አለው።+ 8 አበኔርም በኢያቡስቴ ንግግር እጅግ ተቆጥቶ እንዲህ አለ፦ “እኔ ከይሁዳ ወገን የሆንኩ የውሻ ጭንቅላት ነኝ? እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ ለአባትህ ለሳኦል ቤት፣ ለወንድሞቹና ለቅርብ ወዳጆቹ ታማኝ ፍቅር ከማሳየት ወደኋላ አላልኩም፤ አንተንም ለዳዊት አሳልፌ አልሰጠሁህም፤ ይኸው አንተ ግን ዛሬ በአንዲት ሴት የተነሳ ጥፋተኛ አድርገህ ትከሰኛለህ። 9 ይሖዋ ለዳዊት እንደማለለት+ ሳላደርግለት ብቀር አምላክ በአበኔር ላይ ይህን ያድርግበት፤ ከዚህ የከፋም ያምጣበት፤ 10 አምላክ መንግሥትን ከሳኦል ቤት እንደሚወስድ እንዲሁም የዳዊትን ዙፋን በእስራኤልና በይሁዳ ላይ ከዳን አንስቶ እስከ ቤርሳቤህ+ ድረስ እንደሚያጸና ምሏል።” 11 ኢያቡስቴም አበኔርን ስለፈራው አንዲት ቃል እንኳ ሊመልስለት አልደፈረም።+
12 አበኔርም ወዲያውኑ ወደ ዳዊት መልእክተኞችን ልኮ “ምድሪቱ የማን ናት? ከእኔ ጋር ቃል ኪዳን ግባ፤ መላው እስራኤል ከአንተ ጎን እንዲቆም የቻልኩትን ሁሉ አደርጋለሁ”* አለው።+ 13 እሱም እንዲህ አለው፦ “መልካም! ከአንተ ጋር ቃል ኪዳን እገባለሁ። ብቻ አንድ ነገር እንድታደርግልኝ እጠይቅሃለሁ፤ ወደ እኔ ስትመጣ የሳኦልን ልጅ ሜልኮልን+ ይዘህ ካልመጣህ በቀር ፊቴን እንደማታይ እወቅ” አለው። 14 ከዚያም ዳዊት ለሳኦል ልጅ ለኢያቡስቴ+ “በ100 የፍልስጤማውያን ሸለፈት ያጨኋትን ሚስቴን ሜልኮልን ስጠኝ” ብለው እንዲነግሩት መልእክተኞችን ላከ።+ 15 በመሆኑም ኢያቡስቴ መልእክተኛ ልኮ ሜልኮልን የላይሽ ልጅ ከሆነው ከባሏ ከፓልጢኤል+ ወሰዳት። 16 ባሏ ግን እስከ ባሁሪም+ ድረስ እያለቀሰ ተከትሏት ሄደ። ከዚያም አበኔር “በቃ ሂድ፣ ተመለስ!” አለው። እሱም ተመለሰ።
17 ይህ በእንዲህ እንዳለ አበኔር ለእስራኤል ሽማግሌዎች እንዲህ የሚል መልእክት ላከ፦ “ቀድሞውንም ቢሆን ዳዊት በላያችሁ እንዲነግሥ ትፈልጉ ነበር። 18 ይሖዋ ዳዊትን ‘ሕዝቤን እስራኤልን ከፍልስጤማውያንና ከጠላቶቻቸው ሁሉ እጅ የምታደገው በአገልጋዬ በዳዊት እጅ ነው’+ ስላለው በሉ አሁን እርምጃ ውሰዱ።” 19 ከዚያም አበኔር ቢንያማውያንን+ አነጋገራቸው። በተጨማሪም አበኔር እስራኤልና መላው የቢንያም ቤት ለማድረግ የተስማሙትን ነገር በኬብሮን ላለው ለዳዊት በግል ሊነግረው ወደ እሱ ሄደ።
20 አበኔር ከ20 ሰዎች ጋር ሆኖ በኬብሮን ወዳለው ወደ ዳዊት ሲመጣ ዳዊት ለአበኔርና አብረውት ለነበሩት ሰዎች ግብዣ አደረገላቸው። 21 ከዚያም አበኔር ዳዊትን “እስራኤላውያን ከአንተ ጋር ቃል ኪዳን እንዲገቡ ተነስቼ ልሂድና ሁሉንም ወደ ጌታዬ ወደ ንጉሡ ልሰብስባቸው፤ አንተም በፈለግከው* ሁሉ ላይ ንጉሥ ትሆናለህ” አለው። በመሆኑም ዳዊት አበኔርን አሰናበተው፤ እሱም በሰላም ሄደ።
22 በዚህ ጊዜ የዳዊት አገልጋዮችና ኢዮዓብ በጣም ብዙ ምርኮ ይዘው ከዘመቻ ተመለሱ። አበኔር ግን ዳዊት በሰላም አሰናብቶት ስለሄደ በኬብሮን ከእሱ ጋር አልነበረም። 23 ኢዮዓብና+ አብሮት የነበረው ሠራዊት ሁሉ እዚያ ሲደርስ “የኔር+ ልጅ አበኔር+ ወደ ንጉሡ መጥቶ ነበር፤ ንጉሡም አሰናበተው፤ እሱም በሰላም ሄደ” ብለው ለኢዮዓብ ነገሩት። 24 በመሆኑም ኢዮዓብ ወደ ንጉሡ ገብቶ እንዲህ አለው፦ “ምን ማድረግህ ነው? አበኔር ወደ አንተ መጥቶ ነበር። ታዲያ በሰላም እንዲሄድ ያሰናበትከው ለምንድን ነው? 25 የኔርን ልጅ አበኔርን በሚገባ ታውቀዋለህ! ወደዚህ የመጣው አንተን ለማታለል እንዲሁም መውጫ መግቢያህን ለማወቅና የምታደርገውን ነገር ሁሉ ለመሰለል ነው።”
26 በመሆኑም ኢዮዓብ ከዳዊት ዘንድ ወጥቶ መልእክተኞችን ወደ አበኔር ላከ፤ እነሱም ሲራ ከተባለው የውኃ ማጠራቀሚያ ጉድጓድ ጋ መለሱት፤ ዳዊት ግን ስለዚህ ጉዳይ ምንም የሚያውቀው ነገር አልነበረም። 27 አበኔር ወደ ኬብሮን+ በተመለሰ ጊዜ ኢዮዓብ ከእሱ ጋር በግል ለመነጋገር ነጠል አድርጎ ወደ ቅጥሩ በር ይዞት ገባ። ሆኖም በዚያ ሳሉ ሆዱ ላይ ወግቶ ገደለው፤+ ይህን ያደረገው የወንድሙን የአሳሄልን ደም ለመበቀል ነው።+ 28 ዳዊትም ይህን ሲሰማ እንዲህ አለ፦ “እኔም ሆንኩ መንግሥቴ በኔር ልጅ በአበኔር ደም በይሖዋ ፊት ለዘላለም ተጠያቂ አይደለንም።+ 29 ደሙ በኢዮዓብ ራስና በመላው የአባቱ ቤት ራስ ላይ ይሁን።+ ከኢዮዓብም ቤት ፈሳሽ የሚወጣው+ ሰው ወይም የሥጋ ደዌ+ ያለበት አሊያም እንዝርት የሚያሾር ወንድ* ወይም በሰይፍ የሚወድቅ አሊያም የሚበላው ያጣ ረሃብተኛ አይጥፋ!”+ 30 በመሆኑም ኢዮዓብና ወንድሙ አቢሳ+ በገባኦን በተደረገው ውጊያ ላይ ወንድማቸውን አሳሄልን ስለገደለባቸው+ አበኔርን+ ገደሉት።
31 ከዚያም ዳዊት ኢዮዓብንና አብረውት የነበሩትን ሰዎች በሙሉ “ልብሳችሁን ቀድዳችሁና ማቅ አሸርጣችሁ ለአበኔር አልቅሱለት” አላቸው። ንጉሥ ዳዊትም ራሱ ከቃሬዛው ኋላ ይሄድ ነበር። 32 አበኔርንም በኬብሮን ቀበሩት፤ ንጉሡም በአበኔር መቃብር ላይ ድምፁን ከፍ አድርጎ አለቀሰ፤ ሕዝቡም ሁሉ አለቀሰ። 33 ንጉሡም ለአበኔር ይህን የሐዘን እንጉርጉሮ ተቀኘ፦
“አበኔርም እንደማይረባ ሰው ይሙት?
34 እጆችህ አልታሰሩም፤
እግሮችህም እግር ብረት* ውስጥ አልገቡም።
በወንጀለኞች* ፊት እንደሚወድቅ ሰው ወደቅክ።”+
በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ ለእሱ እንደገና አለቀሱ።
35 በኋላም ሕዝቡ ሁሉ ገና ቀን ሳለ፣ ዳዊትን ለማጽናናት ምግብ* ይዞ መጣ፤ ሆኖም ዳዊት “ፀሐይ ከመጥለቋ በፊት ምግብ ወይም ማንኛውንም ነገር ብቀምስ አምላክ እንዲህ ያድርግብኝ፤ ከዚህ የከፋም ነገር ያምጣብኝ!” በማለት ማለ።+ 36 ሕዝቡም ሁሉ የሆነውን ነገር ተመለከተ፤ ይህም ደስ አሰኛቸው። ንጉሡ ያደረገው ማንኛውም ነገር እንዳስደሰታቸው ሁሉ ይህም ደስ አሰኛቸው። 37 በመሆኑም ሰዎቹ ሁሉና መላው እስራኤል ንጉሡ በኔር ልጅ በአበኔር ሞት እጁ እንደሌለበት በዚያ ቀን አወቁ።+ 38 ከዚያም ንጉሡ አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው፦ “በዛሬው ዕለት በእስራኤል ውስጥ አለቃና ታላቅ ሰው እንደወደቀ አታውቁም?+ 39 ምንም እንኳ ንጉሥ ሆኜ የተቀባሁ+ ብሆንም እኔ ዛሬ ደካማ ነኝ፤ እነዚህ የጽሩያ+ ልጆች እጅግ ጨካኝ ሆነውብኛል።+ ይሖዋ ለክፉ አድራጊው እንደ ክፋቱ ይመልስለት።”+
4 የሳኦል ልጅ ኢያቡስቴ፣*+ አበኔር በኬብሮን መሞቱን+ ሲሰማ ወኔ ከዳው፤* እስራኤላውያንም በሙሉ ተረበሹ። 2 የሳኦል ልጅ የሚመራቸው ወራሪ ቡድኖች አለቃ የሆኑ ሁለት ሰዎች ነበሩ፤ የአንደኛው ስም ባአናህ ሲሆን የሌላኛው ስም ደግሞ ሬካብ ነበር። እነሱም ከቢንያም ነገድ የሆነው የበኤሮታዊው የሪሞን ልጆች ነበሩ። (ምክንያቱም በኤሮት+ ከቢንያም ወገን እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠር ነበር። 3 በኤሮታውያን ወደ ጊታይም+ ሸሹ፤ እስከ ዛሬም ድረስ በዚያ የባዕድ አገር ሰው ሆነው ይኖራሉ።)
4 የሳኦል ልጅ ዮናታን+ እግሮቹ ሽባ የሆኑ አንድ ልጅ ነበረው።+ እሱም ስለ ሳኦልና ስለ ዮናታን የሚገልጸው ወሬ ከኢይዝራኤል+ በመጣ ጊዜ የአምስት ዓመት ልጅ ነበር፤ ሞግዚቱም አንስታው መሸሽ ጀመረች፤ ሆኖም በድንጋጤ ሸሽታ ስትሮጥ ከእጇ ላይ ወድቆ ሽባ ሆነ። ስሙም ሜፊቦስቴ+ ነበር።
5 የበኤሮታዊው የሪሞን ልጆች ሬካብ እና ባአናህ ሞቃታማ በሆነው የቀኑ ክፍለ ጊዜ ወደ ኢያቡስቴ ቤት ሄዱ፤ እሱም ቀትር ላይ አረፍ ብሎ ነበር። 6 እነሱም ስንዴ የሚወስዱ ሰዎች መስለው ወደ ቤቱ ውስጥ ዘልቀው ገቡ፤ ኢያቡስቴንም ሆዱ ላይ ወጉት፤ ከዚያም ሬካብ እና ወንድሙ ባአናህ+ ሸሽተው አመለጡ። 7 ወደ ቤት ሲገቡ ኢያቡስቴ መኝታ ቤቱ ውስጥ አልጋው ላይ ጋደም ብሎ ነበር፤ እነሱም መትተው ገደሉት፤ ከዚያም ራሱን ቆርጠው በመውሰድ ወደ አረባ በሚወስደው መንገድ ሌሊቱን ሙሉ ሲጓዙ አደሩ። 8 የኢያቡስቴንም+ ራስ በኬብሮን ወዳለው ወደ ዳዊት አምጥተው ንጉሡን “ሕይወትህን* ሲፈልጋት+ የነበረው የጠላትህ+ የሳኦል ልጅ የኢያቡስቴ ራስ ይኸውልህ። ይሖዋ በዛሬው ዕለት ሳኦልንና ዘሮቹን ለጌታዬ ለንጉሡ ተበቀለለት” አሉት።
9 ሆኖም ዳዊት ለበኤሮታዊው ለሪሞን ልጆች ለሬካብ እና ለወንድሙ ለባአናህ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ሕይወቴን ከመከራ ሁሉ በታደገልኝ*+ ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ፣ 10 አንድ ሰው ምሥራች ያበሰረኝ መስሎት ‘ሳኦል እኮ ሞተ’+ ብሎ በነገረኝ ጊዜ ጺቅላግ ላይ ገደልኩት።+ መልእክተኛው ከእኔ ያገኘው ሽልማት ይህ ነበር! 11 ታዲያ በገዛ ቤቱ አልጋው ላይ ተኝቶ የነበረውን ጻድቅ ሰው የገደሉ ክፉ ሰዎችማ እንዴት ከዚህ የባሰ ነገር አይጠብቃቸው! እና አሁን ደሙን ከእጃችሁ መጠየቅም+ ሆነ እናንተን ከምድር ገጽ ማጥፋት አይገባኝም?” 12 ከዚያም ዳዊት እንዲገድሏቸው ለወጣቶቹ ትእዛዝ ሰጠ።+ እነሱም እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን ቆርጠው በኬብሮን በሚገኘው ኩሬ አጠገብ ሰቀሏቸው።+ የኢያቡስቴን ራስ ግን ወስደው በኬብሮን ባለው በአበኔር የመቃብር ቦታ ቀበሩት።
5 ከጊዜ በኋላ የእስራኤል ነገዶች በሙሉ በኬብሮን+ ወደሚገኘው ወደ ዳዊት መጥተው እንዲህ አሉት፦ “እንግዲህ እኛ የአጥንትህ ፍላጭ፣ የሥጋህም ቁራጭ ነን።*+ 2 ባለፉት ዘመናት ሳኦል ንጉሣችን በነበረበት ጊዜ እስራኤል ወደ ጦርነት ሲወጣ የምትመራው* አንተ ነበርክ።+ ይሖዋም ‘ሕዝቤን እስራኤልን እረኛ ሆነህ ትጠብቃለህ፣ በእስራኤልም ላይ መሪ ትሆናለህ’ ብሎህ ነበር።”+ 3 በመሆኑም የእስራኤል ሽማግሌዎች በሙሉ ንጉሡ ወዳለበት ወደ ኬብሮን መጡ፤ ንጉሥ ዳዊትም በኬብሮን ከእነሱ ጋር በይሖዋ ፊት ቃል ኪዳን ገባ።+ እነሱም ዳዊትን በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርገው ቀቡት።+
4 ዳዊት በነገሠ ጊዜ 30 ዓመቱ ነበር፤ ለ40 ዓመትም ገዛ።+ 5 በኬብሮን ተቀምጦ በይሁዳ ላይ ለ7 ዓመት ከ6 ወር ገዛ፤ በኢየሩሳሌም+ ሆኖ ደግሞ በመላው እስራኤልና ይሁዳ ላይ ለ33 ዓመት ገዛ። 6 ዳዊትና ሰዎቹም በምድሪቱ የሚኖሩትን ኢያቡሳውያን+ ለመውጋት ወደ ኢየሩሳሌም ዘመቱ። እነሱም ዳዊትን “ፈጽሞ ወደዚህ አትገባም! ዕውሮችና ሽባዎች እንኳ ያባርሩሃል” በማለት ተሳለቁበት። ይህን ያሉት ‘ዳዊት ፈጽሞ ወደዚህ አይገባም’ ብለው ስላሰቡ ነበር።+ 7 ይሁን እንጂ ዳዊት በአሁኑ ጊዜ የዳዊት ከተማ+ ተብላ የምትጠራውን የጽዮንን ምሽግ ያዘ። 8 ስለሆነም በዚያን ቀን ዳዊት “በኢያቡሳውያን ላይ ጥቃት የሚሰነዝር ማንኛውም ሰው ዳዊት የሚጠላቸውን* ‘ሽባዎችንና ዕውሮችን’ ለመምታት በውኃ መውረጃው ቦይ በኩል ማለፍ አለበት!” አለ። “ዕውርና ሽባ ፈጽሞ ወደ ቤት አይገቡም” የሚባለውም በዚህ የተነሳ ነው። 9 ከዚያም ዳዊት በምሽጉ ውስጥ መኖር ጀመረ፤ ስፍራውም የዳዊት ከተማ ተብሎ ይጠራ ነበር፤* እሱም ከጉብታው*+ አንስቶ ወደ ውስጥ ዙሪያውን መገንባት ጀመረ።+ 10 በዚህ ሁኔታ ዳዊት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረታ ሄደ፤+ የሠራዊት አምላክ ይሖዋም ከእሱ ጋር ነበር።+
11 የጢሮስ ንጉሥ ኪራም+ መልእክተኞችን ወደ ዳዊት ላከ፤ እንዲሁም የአርዘ ሊባኖስ ሳንቃዎችን፣+ አናጺዎችንና ለቅጥር የሚሆን ድንጋይ የሚጠርቡ ሰዎችን ላከ፤ እነሱም ለዳዊት ቤት* መሥራት ጀመሩ።+ 12 ዳዊትም ይሖዋ በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርጎ እንዳጸናውና+ ስለ ሕዝቡ ስለ እስራኤል ሲል+ መንግሥቱን ከፍ ከፍ እንዳደረገለት+ አወቀ።
13 ዳዊት ከኬብሮን ከመጣ በኋላ በኢየሩሳሌም ተጨማሪ ቁባቶችን+ አስቀመጠ፤ እንዲሁም ሌሎች ሚስቶችን አገባ፤ ተጨማሪ ወንዶችና ሴቶች ልጆችም ተወለዱለት።+ 14 በኢየሩሳሌም ሳለ የተወለዱለት ልጆች ስም ይህ ነው፦ ሻሙአ፣ ሾባብ፣ ናታን፣+ ሰለሞን፣+ 15 ይብሃር፣ ኤሊሹዓ፣ ኔፌግ፣ ያፊአ፣ 16 ኤሊሻማ፣ ኤሊያዳ እና ኤሊፌሌት።
17 ፍልስጤማውያንም በሙሉ ዳዊት በእስራኤል ላይ ንጉሥ ሆኖ መቀባቱን+ ሲሰሙ እሱን ፍለጋ ወጡ።+ ዳዊትም ይህን ሲሰማ ወደ ምሽጉ ወረደ።+ 18 ከዚያም ፍልስጤማውያን መጥተው በረፋይም ሸለቆ*+ ተበታትነው ሰፈሩ። 19 ዳዊትም “ወጥቼ ፍልስጤማውያንን ልግጠም? አንተስ በእጄ አሳልፈህ ትሰጣቸዋለህ?” ሲል ይሖዋን ጠየቀ።+ ይሖዋም ዳዊትን “አዎ ውጣ፤ እኔም በእርግጥ ፍልስጤማውያንን በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ” አለው።+ 20 በመሆኑም ዳዊት ወደ በዓልጰራጺም መጥቶ በዚያ መታቸው። እሱም “ይሖዋ፣ ውኃ እንደጣሰው ግድብ ጠላቶቼን በፊቴ ደረማመሳቸው” አለ።+ ከዚህም የተነሳ ያን ቦታ በዓልጰራጺም*+ ብሎ ጠራው። 21 ፍልስጤማውያንም ጣዖቶቻቸውን በዚያ ጥለው ሸሹ፤ ዳዊትና ሰዎቹም ወሰዷቸው።*
22 ከጊዜ በኋላ ፍልስጤማውያን እንደገና ወደ ረፋይም ሸለቆ*+ መጥተው ተበታትነው ሰፈሩ። 23 ዳዊትም ይሖዋን ጠየቀ፤ እሱ ግን እንዲህ አለው፦ “በቀጥታ አትውጣ። ይልቁንም ከኋላቸው ዞረህ በባካ* ቁጥቋጦዎቹ ፊት ለፊት ግጠማቸው። 24 በባካ ቁጥቋጦዎቹ አናት ላይ የሰልፍ ድምፅ ስትሰማ ቆራጥ እርምጃ ውሰድ፤ ምክንያቱም ይህ በሚሆንበት ጊዜ ይሖዋ የፍልስጤማውያንን ሠራዊት ለመምታት በፊትህ ወጥቷል ማለት ነው።” 25 በመሆኑም ዳዊት ልክ ይሖዋ እንዳዘዘው አደረገ፤ ፍልስጤማውያንንም ከጌባ+ አንስቶ እስከ ጌዜር+ ድረስ መታቸው።+
6 ዳዊትም በእስራኤል ውስጥ ያሉትን ምርጥ የሆኑ ተዋጊዎች በሙሉ በድጋሚ ሰበሰበ፤ ብዛታቸውም 30,000 ነበር። 2 ከዚያም አብሮት ከነበረው ሕዝብ ሁሉ ጋር ተነስቶ የእውነተኛውን አምላክ ታቦት+ ለማምጣት በዙፋን ላይ ከኪሩቤል በላይ የተቀመጠው*+ የሠራዊት ጌታ የይሖዋ+ ስም ወደተጠራበት ወደ በዓለይሁዳ ሄደ። 3 ይሁን እንጂ የእውነተኛውን አምላክ ታቦት በኮረብታ ላይ ካለው ከአቢናዳብ+ ቤት ለማምጣት በአዲስ ሠረገላ ላይ ጫኑት፤+ የአቢናዳብ ልጆች የሆኑት ዖዛ እና አሂዮም አዲሱን ሠረገላ ይነዱ ነበር።
4 በመሆኑም የእውነተኛውን አምላክ ታቦት በኮረብታ ላይ ከነበረው ከአቢናዳብ ቤት ይዘው ጉዞ ጀመሩ፤ አሂዮም ከታቦቱ ፊት ፊት ይሄድ ነበር። 5 ዳዊትና መላው የእስራኤል ቤት ከጥድ እንጨት በተሠሩ የተለያዩ መሣሪያዎች፣ በበገና፣ በባለ አውታር መሣሪያዎች፣+ በአታሞ፣+ በጸናጽልና በሲምባል*+ ታጅበው በይሖዋ ፊት በደስታ ይጨፍሩ ነበር። 6 ወደ ናኮን አውድማ ሲደርሱ ግን ከብቶቹ ታቦቱን ሊጥሉት ተቃርበው ስለነበር ዖዛ እጁን ዘርግቶ የእውነተኛውን አምላክ ታቦት ያዘ።+ 7 በዚህ ጊዜ የይሖዋ ቁጣ በዖዛ ላይ ነደደ፤ በመሆኑም ዖዛ እንዲህ ያለ የድፍረት ድርጊት+ በመፈጸሙ እውነተኛው አምላክ እዚያው ቀሰፈው፤+ እሱም በእውነተኛው አምላክ ታቦት አጠገብ እዚያው ሞተ። 8 ሆኖም የይሖዋ ቁጣ በዖዛ ላይ ስለነደደ ዳዊት ተበሳጨ፤* ያም ቦታ እስከ ዛሬ ድረስ ጴሬዝዖዛ* ተብሎ ይጠራል። 9 ዳዊትም በዚያን ዕለት ይሖዋን ፈርቶ+ “ታዲያ የይሖዋ ታቦት እንዴት ወደ እኔ ይመጣል?” አለ።+ 10 ዳዊትም የይሖዋ ታቦት እሱ ወዳለበት ወደ ዳዊት ከተማ+ እንዲመጣ አልፈለገም። ይልቁንም ታቦቱ የጌት ሰው ወደሆነው ወደ ኦቤድዔዶም+ ቤት እንዲወሰድ አደረገ።
11 የይሖዋም ታቦት የጌት ሰው በሆነው በኦቤድዔዶም ቤት ለሦስት ወር ተቀመጠ፤ ይሖዋም ኦቤድዔዶምን እና ቤተሰቡን በሙሉ ባረከ።+ 12 በመጨረሻም ዳዊት “ይሖዋ በእውነተኛው አምላክ ታቦት የተነሳ የኦቤድዔዶምን ቤትና የእሱ የሆነውን ነገር ሁሉ ባርኳል” ተብሎ ተነገረው። ስለሆነም ዳዊት የእውነተኛውን አምላክ ታቦት ከኦቤድዔዶም ቤት ወደ ዳዊት ከተማ በታላቅ ደስታ ለማምጣት ሄደ።+ 13 የይሖዋን ታቦት የተሸከሙት+ ሰዎች ስድስት እርምጃ ከተራመዱ በኋላ ዳዊት አንድ በሬና አንድ የሰባ ጥጃ ሠዋ።
14 ዳዊትም በሙሉ ኃይሉ በይሖዋ ፊት ይጨፍር ነበር፤ በዚህ ጊዜ ሁሉ ከበፍታ የተሠራ ኤፉድ ለብሶ* ነበር።+ 15 ዳዊትና የእስራኤል ቤት በሙሉ የይሖዋን ታቦት+ በእልልታና+ በቀንደ መለከት+ አጅበው አመጡት። 16 ይሁንና የይሖዋ ታቦት ወደ ዳዊት ከተማ በመጣ ጊዜ የሳኦል ልጅ ሜልኮል+ በመስኮት ሆና ወደ ታች ተመለከተች፤ እሷም ንጉሥ ዳዊት በይሖዋ ፊት ሲዘልና ሲጨፍር አይታ በልቧ ናቀችው።+ 17 በዚህ መንገድ የይሖዋን ታቦት አምጥተው ዳዊት በተከለለት ድንኳን ውስጥ በተዘጋጀለት ቦታ ላይ አስቀመጡት።+ ከዚያም ዳዊት የሚቃጠሉ መባዎችንና+ የኅብረት መሥዋዕቶችን+ በይሖዋ ፊት አቀረበ።+ 18 ዳዊት የሚቃጠሉትን መባዎችና የኅብረት መሥዋዕቶቹን አቅርቦ ሲጨርስ ሕዝቡን በሠራዊት ጌታ በይሖዋ ስም ባረከ። 19 በተጨማሪም ለሕዝቡ ሁሉ ይኸውም ለተሰበሰቡት እስራኤላውያን በሙሉ፣ ለእያንዳንዱ ወንድና ሴት አንድ ዳቦ፣ አንድ የቴምር ጥፍጥፍና አንድ የዘቢብ ጥፍጥፍ አከፋፈለ፤ ከዚያም ሕዝቡ ሁሉ ወደየቤቱ ሄደ።
20 በዚህ ጊዜ ዳዊት የራሱን ቤት ለመባረክ ተመለሰ፤ የሳኦል ልጅ ሜልኮልም+ ዳዊትን ልትቀበለው ወጥታ “ዛሬ የእስራኤል ንጉሥ እንደ አንድ ተራ ሰው በአገልጋዮቹ ሴት ባሪያዎች ፊት እርቃኑን በመሆኑ እንዴት ራሱን አስከብሯል!” አለችው።+ 21 በዚህ ጊዜ ዳዊት ሜልኮልን እንዲህ አላት፦ “የጨፈርኩት እኮ ከአባትሽና በቤቱ ካሉት ሁሉ ይልቅ እኔን መርጦ በይሖዋ ሕዝብ በእስራኤል ላይ መሪ አድርጎ በሾመኝ በይሖዋ ፊት ነው፤+ አሁንም ቢሆን በይሖዋ ፊት እጨፍራለሁ። 22 እንዲያውም ከዚህ የባሰ ራሴን አዋርዳለሁ፤ ራሴንም እንቃለሁ። ሆኖም አንቺ በጠቀስሻቸው ሴት ባሪያዎች ፊት እከበራለሁ።” 23 የሳኦል ልጅ ሜልኮልም+ እስከሞተችበት ቀን ድረስ ልጅ አልወለደችም።
7 ንጉሡ በራሱ ቤት* መኖር በጀመረና+ ይሖዋም በዙሪያው ካሉት ጠላቶቹ ሁሉ እረፍት በሰጠው ጊዜ 2 ነቢዩ ናታንን+ “የእውነተኛው አምላክ ታቦት በድንኳን ውስጥ+ ተቀምጦ ሳለ ይኸው እኔ ከአርዘ ሊባኖስ በተሠራ+ ቤት ውስጥ እየኖርኩ ነው” አለው። 3 ናታንም ንጉሡን “ይሖዋ ከአንተ ጋር ስለሆነ ሄደህ በልብህ ያለውን ነገር ሁሉ አድርግ” አለው።+
4 በዚያው ሌሊት የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ወደ ናታን መጣ፦ 5 “ሂድና አገልጋዬን ዳዊትን እንዲህ በለው፦ ‘ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “አንተ የምኖርበትን ቤት መሥራት ይኖርብሃል?+ 6 እስራኤላውያንን ከግብፅ ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በድንኳንና በማደሪያ ድንኳን እጓዝ ነበር እንጂ በቤት ውስጥ አልኖርኩም።+ 7 ከእስራኤላውያን* ሁሉ ጋር በተጓዝኩበት ጊዜ በሙሉ ሕዝቤን እስራኤልን እረኛ ሆነው እንዲጠብቁ ከሾምኳቸው የነገድ መሪዎች መካከል ‘በአርዘ ሊባኖስ ቤት ያልሠራህልኝ ለምንድን ነው?’ ያልኩት ማን አለ?”’ 8 አሁንም አገልጋዬን ዳዊትን እንዲህ በለው፦ ‘የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መሪ እንድትሆን+ መንጋ ከምትጠብቅበት ስፍራ+ ወሰድኩህ። 9 እኔም በምትሄድበት ሁሉ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤+ ጠላቶችህንም ሁሉ ከፊትህ አጠፋለሁ፤+ ስምህንም በምድር ላይ እንዳሉ ታላላቅ ሰዎች ስም ገናና አደርገዋለሁ።+ 10 ለሕዝቤ ለእስራኤል ቦታ እሰጣቸዋለሁ፤ ተረጋግተው እንዲቀመጡም አደርጋለሁ፤ በዚያም ይኖራሉ፤ ከእንግዲህም የሚረብሻቸው አይኖርም፤ ክፉዎች እንደቀድሞው ዳግመኛ አይጨቁኗቸውም፤+ 11 በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መሳፍንትን ከሾምኩበት+ ጊዜ አንስቶ ሲያደርጉ እንደነበሩት አያደርጉባቸውም። እኔም ከጠላቶችህ ሁሉ እረፍት እሰጥሃለሁ።+
“‘“በተጨማሪም ይሖዋ ቤት* እንደሚሠራልህ ይሖዋ ራሱ ነግሮሃል።+ 12 የሕይወት ዘመንህ አብቅቶ+ ከአባቶችህ ጋር በምታንቀላፋበት ጊዜ ከአንተ በኋላ ከአብራክህ የሚወጣውን ዘርህን አስነሳለሁ፤ መንግሥቱንም አጸናለሁ።+ 13 ለስሜ የሚሆን ቤት የሚሠራልኝ እሱ ነው፤+ እኔም የመንግሥቱን ዙፋን ለዘላለም አጸናለሁ።+ 14 አባት እሆነዋለሁ፤ እሱም ልጄ ይሆናል።+ ጥፋት በሚያጠፋበት ጊዜም በሰዎች በትር፣ በሰው* ልጆች አለንጋ እቀጣዋለሁ።+ 15 ከፊትህ ካስወገድኩት ከሳኦል ላይ ታማኝ ፍቅሬን እንደወሰድኩ+ ከእሱ ላይ አይወሰድም። 16 ቤትህና መንግሥትህ ለዘላለም በፊትህ ጸንቶ ይኖራል፤ ዙፋንህም ለዘላለም የጸና ይሆናል።”’”+
17 ናታንም ይህን ቃል ሁሉና ይህን ራእይ በሙሉ ለዳዊት ነገረው።+
18 በዚህ ጊዜ ንጉሥ ዳዊት ገብቶ በይሖዋ ፊት ተቀመጠ፤ እንዲህም አለ፦ “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ ኧረ ለመሆኑ እኔ ማን ነኝ? እስከዚህ ድረስ ያደረስከኝስ ቤቴ ምን ስለሆነ ነው?+ 19 ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ ይህ ሳያንስ ስለ አገልጋይህ ቤት ገና ወደፊት የሚሆነውንም ነገር ተናገርክ፤ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ ይህ ለሰው ዘር ሁሉ የተሰጠ መመሪያ* ነው። 20 ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ ታዲያ አገልጋይህ ዳዊት ከዚህ በላይ ምን ሊልህ ይችላል? አንተ በሚገባ ታውቀኝ የለ?+ 21 ለቃልህ ስትል፣ ከልብህ ጋር በሚስማማ ሁኔታ* እነዚህን ሁሉ ታላላቅ ነገሮች ፈጽመሃል፤ እንዲሁም ለአገልጋይህ ገልጠህለታል።+ 22 ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ አንተ በእርግጥም ታላቅ+ የሆንከው ለዚህ ነው። እንደ አንተ ያለ ማንም የለም፤+ ከአንተ በቀር አምላክ የለም፤+ በጆሯችን የሰማነው ነገር ሁሉ ይህን ያረጋግጣል። 23 በምድር ላይ እንደ ሕዝብህ እንደ እስራኤል ያለ ሌላ ብሔር ማን አለ?+ አምላክ ሄዶ ለእነሱ ሲል ታላላቅና አስፈሪ ነገሮችን+ በመፈጸም እንዲሁም ስሙን በማስጠራት+ ሕዝቡ አድርጎ ዋጃቸው።+ ከግብፅ ለዋጀኸው ሕዝብ ስትል ብሔራትንና አማልክታቸውን አባረርክ። 24 ሕዝብህን እስራኤልን እስከ ወዲያኛው የራስህ ሕዝብ አድርገህ አጸናኸው፤+ ይሖዋ ሆይ፣ አንተም አምላኩ ሆንክ።+
25 “አሁንም ይሖዋ አምላክ ሆይ፣ አገልጋይህንና ቤቱን በተመለከተ የገባኸውን ቃል እስከ ወዲያኛው ፈጽም፤ ቃል እንደገባኸውም አድርግ።+ 26 ሰዎች ‘የሠራዊት ጌታ ይሖዋ በእስራኤል ላይ አምላክ ነው’ እንዲሉ ስምህ ለዘላለም ከፍ ከፍ ይበል፤+ የአገልጋይህም የዳዊት ቤት በፊትህ የጸና ይሁን።+ 27 የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ‘ለአንተ ቤት* እሠራልሃለሁ’+ በማለት ለአገልጋይህ ራእይ ገልጠህለታል። አገልጋይህ ይህን ጸሎት ወደ አንተ ለማቅረብ ድፍረት* ያገኘው በዚህ ምክንያት ነው። 28 አሁንም ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ እውነተኛው አምላክ አንተ ነህ፤ ቃልህ እውነት ነው፤+ ለአገልጋይህም እነዚህን መልካም ነገሮች ለማድረግ ቃል ገብተህለታል። 29 በመሆኑም የአገልጋይህን ቤት እባክህ ባርክ፤ በፊትህም ለዘላለም የጸና ይሁን፤+ ምክንያቱም ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ራስህ ቃል ገብተሃል፤ በአንተም በረከት የአገልጋይህ ቤት ለዘላለም የተባረከ ይሁን።”+
8 ከጊዜ በኋላም ዳዊት ፍልስጤማውያንን+ ድል በማድረግ በቁጥጥር ሥር አዋላቸው፤+ መተግአማህንም ከፍልስጤማውያን እጅ ወሰደ።
2 ሞዓባውያንንም ድል አደረጋቸው፤+ እነሱንም መሬት ላይ አጋድሞ በገመድ ለካቸው። ይህን ያደረገው በገመዱ ርዝመት ሁለት እጅ የሚሆኑትን ለመግደል እንዲሁም በገመዱ ርዝመት አንድ እጅ የሚሆኑትን በሕይወት ለመተው ነው።+ ሞዓባውያንም የዳዊት አገልጋዮች ሆኑ፤ ግብርም ገበሩለት።+
3 የሬሆብ ልጅ የሆነው የጾባህ+ ንጉሥ ሃዳድኤዜር በኤፍራጥስ ወንዝ+ ላይ ያለውን የበላይነት ዳግመኛ ለማረጋገጥ በሄደ ጊዜ ዳዊት ድል አደረገው። 4 ዳዊትም ከእሱ ላይ 1,700 ፈረሰኞችንና 20,000 እግረኛ ወታደሮችን ማረከ። ከዚያም ዳዊት 100 የሠረገላ ፈረሶችን ብቻ አስቀርቶ ሌሎቹን በሙሉ ቋንጃቸውን ቆረጠ።+
5 የደማስቆዎቹ ሶርያውያን፣+ የጾባህን ንጉሥ ሃዳድኤዜርን ለመርዳት በመጡ ጊዜ ዳዊት ከሶርያውያን መካከል 22,000 ሰዎችን ገደለ።+ 6 ከዚያም ዳዊት በደማስቆ ሶርያ የጦር ሰፈሮች አቋቋመ፤ ሶርያውያንም የዳዊት አገልጋዮች ሆኑ፤ ግብርም ገበሩለት። ይሖዋ ዳዊትን በሄደበት ሁሉ ድል አቀዳጀው።*+ 7 በተጨማሪም ዳዊት ከሃዳድኤዜር አገልጋዮች ላይ ከወርቅ የተሠሩ ክብ ጋሻዎችን ወሰደ፤ ወደ ኢየሩሳሌምም አመጣቸው።+ 8 ደግሞም ንጉሥ ዳዊት የሃዳድኤዜር ከተሞች ከሆኑት ከቤጣህ እና ከበሮታይ እጅግ ብዙ መዳብ ወሰደ።
9 በዚህ ጊዜ የሃማት+ ንጉሥ ቶአይ ዳዊት የጾባህን ንጉሥ የሃዳድኤዜርን+ ሠራዊት በሙሉ ድል እንዳደረገ ሰማ። 10 በመሆኑም ቶአይ የንጉሥ ዳዊትን ደህንነት እንዲጠይቅና ከሃዳድኤዜር ጋር ተዋግቶ ድል በማድረጉ የተሰማውን ደስታ እንዲገልጽለት ልጁን ዮራምን ወደ ዳዊት ላከው (ምክንያቱም ሃዳድኤዜር ከቶአይ ጋር ብዙ ጊዜ ይዋጋ ነበር)፤ እሱም ከብር፣ ከወርቅና ከመዳብ የተሠሩ ዕቃዎችን ይዞ መጣ። 11 ንጉሥ ዳዊት እነዚህን ዕቃዎች ተገዢዎቹ ካደረጋቸው ብሔራት ሁሉ ላይ ወስዶ ከቀደሰው ብርና ወርቅ ጋር አብሮ ለይሖዋ ቀደሳቸው፤+ 12 ዕቃዎቹም ከሶርያ፣ ከሞዓብ፣+ ከአሞናውያን፣ ከፍልስጤማውያንና+ ከአማሌቃውያን+ ላይ የወሰዳቸው እንዲሁም የሬሆብ ልጅ ከሆነው ከጾባህ ንጉሥ ከሃዳድኤዜር+ ላይ የማረካቸው ናቸው። 13 ዳዊት በጨው ሸለቆ 18,000 ኤዶማውያንን ገድሎ ከተመለሰ በኋላ ስሙ ገነነ።+ 14 በኤዶምም የጦር ሰፈሮችን አቋቋመ። በመላው ኤዶም የጦር ሰፈሮችን ከማቋቋሙም ሌላ ኤዶማውያን ሁሉ የዳዊት አገልጋዮች ሆኑ።+ ይሖዋም ዳዊትን በሄደበት ሁሉ ድል አቀዳጀው።*+
15 ዳዊት በመላው እስራኤል ላይ መግዛቱን ቀጠለ፤+ ለሕዝቡም ሁሉ+ ፍትሕንና ጽድቅን አሰፈነላቸው።+ 16 የጽሩያ ልጅ ኢዮዓብ+ የሠራዊቱ አዛዥ ነበር፤ የአሂሉድ ልጅ ኢዮሳፍጥ+ ታሪክ ጸሐፊ ነበር። 17 የአኪጡብ ልጅ ሳዶቅና+ የአብያታር ልጅ አሂሜሌክ ካህናት ነበሩ፤ ሰራያህ ደግሞ ጸሐፊ ነበር። 18 የዮዳሄ ልጅ በናያህ+ የከሪታውያንና የጴሌታውያን+ አዛዥ ነበር። የዳዊት ወንዶች ልጆችም ዋና ኃላፊዎች* ሆኑ።
9 ከዚያም ዳዊት “ለመሆኑ ለዮናታን ስል ታማኝ ፍቅር ላሳየው የምችል ከሳኦል ቤት የቀረ ሰው ይኖራል?” አለ።+ 2 በዚህ ጊዜ የሳኦል ቤት አገልጋይ የሆነ ሲባ+ የሚባል ሰው ነበር። እሱንም ወደ ዳዊት እንዲመጣ ጠሩት፤ ንጉሡም “ሲባ የምትባለው አንተ ነህ?” ሲል ጠየቀው። እሱም “አዎ፣ እኔ አገልጋይህ ሲባ ነኝ” በማለት መለሰ። 3 ከዚያም ንጉሡ “እንደው የአምላክን ታማኝ ፍቅር ላሳየው የምችል ከሳኦል ቤት የቀረ ሰው ይኖራል?” አለው። ሲባም ንጉሡን “ሁለቱም እግሮቹ ሽባ+ የሆኑ አንድ የዮናታን ልጅ አለ” አለው። 4 ንጉሡም “ለመሆኑ የት ነው ያለው?” አለው። ሲባም ንጉሡን “ሎደባር ባለው በአሚዔል ልጅ በማኪር+ ቤት ይገኛል” አለው።
5 ንጉሥ ዳዊትም ወዲያውኑ መልእክተኞችን ልኮ ሎደባር ከሚገኘው ከአሚዔል ልጅ ከማኪር ቤት አስመጣው። 6 የሳኦል ልጅ፣ የዮናታን ልጅ ሜፊቦስቴ ወደ ዳዊት ሲገባ ወዲያውኑ በግንባሩ ተደፍቶ ሰገደ። ከዚያም ዳዊት “ሜፊቦስቴ!” ብሎ ጠራው፤ እሱም “አቤት ጌታዬ” አለ። 7 ዳዊትም “ለአባትህ ለዮናታን ስል ታማኝ ፍቅር ስለማሳይህ አትፍራ፤+ የአያትህን የሳኦልንም መሬት በሙሉ እመልስልሃለሁ፤ አንተም ዘወትር ከማዕዴ ትበላለህ”+ አለው።
8 እሱም ከሰገደ በኋላ “እንደ እኔ ላለ የሞተ ውሻ+ ሞገስ ታሳይ ዘንድ ለመሆኑ እኔ አገልጋይህ ማን ነኝ?” አለው። 9 ከዚያም ንጉሡ ለሳኦል አገልጋይ ለሲባ እንዲህ የሚል መልእክት ላከ፦ “የሳኦልና የቤተሰቡ የሆነውን ነገር ሁሉ ለጌታህ የልጅ ልጅ ሰጥቼዋለሁ።+ 10 አንተ፣ ልጆችህና አገልጋዮችህ መሬቱን ታርሱለታላችሁ፤ ምርቱንም ታስገቡለታላችሁ፤ ይህም ለጌታህ የልጅ ልጅ ቤተሰቦች መብል ይሆናል። የጌታህ የልጅ ልጅ ሜፊቦስቴ ግን ዘወትር ከማዕዴ ይመገባል።”+
ሲባ 15 ልጆችና 20 አገልጋዮች ነበሩት።+ 11 ከዚያም ሲባ ንጉሡን “እኔ አገልጋይህ፣ ጌታዬ ንጉሡ ያዘዘኝን ሁሉ እፈጽማለሁ” አለው። ስለዚህ ሜፊቦስቴ ከንጉሡ ልጆች እንደ አንዱ ከዳዊት* ማዕድ በላ። 12 ሜፊቦስቴም ሚካ+ የሚባል ትንሽ ልጅ ነበረው፤ በሲባ ቤት የሚኖሩም ሁሉ የሜፊቦስቴ አገልጋዮች ሆኑ። 13 ሜፊቦስቴም ዘወትር ከንጉሡ ማዕድ ይበላ+ ስለነበር የሚኖረው በኢየሩሳሌም ነበር፤ ሁለቱም እግሮቹ ሽባ ነበሩ።+
10 ከጊዜ በኋላ የአሞናውያን+ ንጉሥ ሞተ፤ ልጁ ሃኑንም በእሱ ፋንታ ነገሠ።+ 2 በዚህ ጊዜ ዳዊት “አባቱ ታማኝ ፍቅር እንዳሳየኝ ሁሉ እኔም ለናሃሽ ልጅ ለሃኑን ታማኝ ፍቅር አሳየዋለሁ” አለ። ስለሆነም ዳዊት፣ በአባቱ ሞት ከደረሰበት ሐዘን እንዲያጽናኑት አገልጋዮቹን ወደ ሃኑን ላከ። ሆኖም የዳዊት አገልጋዮች ወደ አሞናውያን ምድር ሲደርሱ 3 የአሞናውያን መኳንንት ጌታቸውን ሃኑንን “ዳዊት አጽናኞችን ወደ አንተ የላከው አባትህን አክብሮ ይመስልሃል? ዳዊት አገልጋዮቹን ወደ አንተ የላከው ከተማዋን በሚገባ ለማጥናት፣ ለመሰለልና ለመገልበጥ አይደለም?” አሉት። 4 በመሆኑም ሃኑን የዳዊትን አገልጋዮች ወስዶ ግማሹን ጢማቸውን ላጫቸው፤+ ልብሳቸውንም እስከ መቀመጫቸው ድረስ አሳጥሮ በመቁረጥ መልሶ ላካቸው። 5 ዳዊትም ይህን ሲሰማ ወዲያውኑ መልእክተኞችን ወደ ሰዎቹ ላከ፤ ምክንያቱም በኀፍረት ተውጠው ነበር፤ ንጉሡም “ጢማችሁ እስኪያድግ ድረስ በኢያሪኮ+ ቆዩ፤ ከዚያ በኋላ ተመለሱ” አላቸው።
6 ውሎ አድሮ አሞናውያን በዳዊት ዘንድ እንደ ጥንብ እንደተቆጠሩ ተገነዘቡ፤ በመሆኑም አሞናውያን፣ ሰዎችን በመላክ ከቤትሬሆብ+ ሶርያውያንና ከጾባህ+ ሶርያውያን 20,000 እግረኛ ተዋጊዎችን፣ የማአካን+ ንጉሥ ከ1,000 ሰዎች ጋር እንዲሁም ከኢሽጦብ* 12,000 ሰዎችን ቀጠሩ።+ 7 ዳዊትም ይህን በሰማ ጊዜ ኢዮአብን እንዲሁም እጅግ ኃያላን የሆኑትን ተዋጊዎቹን+ ጨምሮ መላውን ሠራዊት ላከ። 8 አሞናውያንም ወጥተው በከተማዋ መግቢያ ላይ ለውጊያ ተሰለፉ፤ የጾባህና የሬሆብ ሶርያውያን ደግሞ ከኢሽጦብና* ከማአካ ጋር ሆነው ለብቻቸው ሜዳ ላይ ተሰለፉ።
9 ኢዮዓብ ወታደሮቹ ከፊትና ከኋላ ጥቃት ለመሰንዘር ወደ እሱ እየገሰገሱ መምጣታቸውን ሲያይ በእስራኤል ካሉት ምርጥ የሆኑ ተዋጊዎች መካከል የተወሰኑትን መርጦ ሶርያውያንን እንዲገጥሙ አሰለፋቸው።+ 10 የቀሩትን ሰዎች ደግሞ በወንድሙ በአቢሳ+ አመራር ሥር* ሆነው አሞናውያንን+ እንዲገጥሙ አሰለፋቸው። 11 ከዚያም እንዲህ አለው፦ “ሶርያውያን ከበረቱብኝ አንተ ትደርስልኛለህ፤ አሞናውያን ከበረቱብህ ደግሞ እኔ እደርስልሃለሁ። 12 ለሕዝባችንና ለአምላካችን ከተሞች ስንል ብርቱና ደፋር መሆን አለብን፤+ ይሖዋም በፊቱ መልካም የሆነውን ነገር ያደርጋል።”+
13 ከዚያም ኢዮዓብና አብረውት የነበሩት ሰዎች ሶርያውያንን ለመግጠም ወደ እነሱ ሲገሰግሱ ሶርያውያኑ ከፊታቸው ሸሹ።+ 14 አሞናውያንም ሶርያውያን እንደ ሸሹ ሲያዩ ከአቢሳ ፊት ሸሽተው ወደ ከተማዋ ገቡ። ከዚያም ኢዮዓብ አሞናውያንን ከመውጋት ተመልሶ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ።
15 ሶርያውያንም በእስራኤላውያን ድል እንደተመቱ ሲያዩ በአዲስ መልክ ተደራጁ።+ 16 በመሆኑም ሃዳድኤዜር+ በወንዙ*+ አካባቢ ወደነበሩት ሶርያውያን መልእክተኞችን ላከ፤ እነሱም የሃዳድኤዜር ሠራዊት አለቃ በሆነው በሾባክ መሪነት ወደ ሄላም መጡ።
17 ዳዊት ወሬው በተነገረው ጊዜ ወዲያውኑ እስራኤላውያንን ሁሉ ሰብስቦ ዮርዳኖስን በመሻገር ወደ ሄላም መጣ። ሶርያውያንም ዳዊትን ለመግጠም ተሰለፉ፤ ከእሱም ጋር ተዋጉ።+ 18 ሆኖም ሶርያውያን ከእስራኤላውያን ፊት ሸሹ፤ ዳዊትም ከሶርያውያን መካከል 700 ሠረገለኞችንና 40,000 ፈረሰኞችን ገደለ፤ የሠራዊታቸው አለቃ የሆነውን ሾባክንም መታው፤ እሱም እዚያው ሞተ።+ 19 የሃዳድኤዜር አገልጋዮች የሆኑት ነገሥታት በሙሉ እስራኤላውያን እንዳሸነፏቸው ባዩ ጊዜ ወዲያውኑ ከእስራኤላውያን ጋር እርቅ በመፍጠር ለእነሱ ተገዙ፤+ ሶርያውያንም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አሞናውያንን መርዳት ፈሩ።
11 በዓመቱ መባቻ፣* ነገሥታት ለውጊያ በሚዘምቱበት ወቅት ዳዊት አሞናውያንን እንዲያጠፉ ኢዮዓብን፣ አገልጋዮቹንና መላውን የእስራኤል ሠራዊት ላከ፤ እነሱም ራባን+ ከበቡ፤ በዚህ ጊዜ ዳዊት ኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር።+
2 አንድ ቀን ምሽት፣* ዳዊት ከአልጋው ተነስቶ በንጉሡ ቤት* ሰገነት ላይ ይንጎራደድ ነበር። በሰገነቱ ላይ ሳለም አንዲት ሴት ገላዋን ስትታጠብ አየ፤ እሷም በጣም ውብ ነበረች። 3 ዳዊትም ስለ ሴትየዋ ማንነት እንዲጠይቅ አንድ ሰው ላከ፤ ሰውየውም “ሴቲቱ የኤሊያም+ ልጅ፣ የሂታዊው+ የኦርዮ+ ሚስት ቤርሳቤህ+ ናት” ብሎ ነገረው። 4 ከዚያም ዳዊት ሴትየዋን እንዲያመጧት መልእክተኞችን ላከ።+ እሷም ወደ እሱ ገባች፤ አብሯትም ተኛ።+ (ይህ የሆነው ራሷን ከርኩሰቷ* እያነጻች ሳለ ነበር።)+ በኋላም ሴትየዋ ወደ ቤቷ ተመለሰች።
5 ሴትየዋም ፀነሰች፤ ለዳዊትም “አርግዣለሁ” የሚል መልእክት ላከችበት። 6 በዚህ ጊዜ ዳዊት “ሂታዊውን ኦርዮን ወደ እኔ ላከው” በማለት ወደ ኢዮዓብ መልእክት ላከበት። በመሆኑም ኢዮዓብ ኦርዮን ወደ ዳዊት ላከው። 7 ኦርዮም በመጣ ጊዜ ዳዊት ስለ ኢዮዓብ ደህንነት፣ ስለ ሠራዊቱ ሁኔታና ጦርነቱ እንዴት እየተካሄደ እንዳለ ጠየቀው። 8 ከዚያም ዳዊት ኦርዮን “እንግዲህ ወደ ቤትህ ውረድና ዘና በል”* አለው። ኦርዮ ከንጉሡ ቤት ወጥቶ በሄደ ጊዜ የንጉሡ የደግነት ስጦታ* ተላከለት። 9 ኦርዮ ግን ከሌሎቹ የጌታው አገልጋዮች ጋር በንጉሡ ቤት ደጃፍ ላይ ተኛ እንጂ ወደ ቤቱ አልወረደም። 10 በመሆኑም ለዳዊት “ኦርዮ እኮ ወደ ቤቱ አልወረደም” ብለው ነገሩት። በዚህ ጊዜ ዳዊት ኦርዮን “ከመንገድ ገና መግባትህ አይደለም እንዴ? ታዲያ ወደ ቤትህ ያልወረድከው ለምንድን ነው?” አለው። 11 ኦርዮም ዳዊትን እንዲህ አለው፦ “ታቦቱም+ ሆነ እስራኤልና ይሁዳ ያሉት ዳስ ውስጥ ነው፤ ጌታዬ ኢዮዓብና የጌታዬ አገልጋዮችም አውላላ ሜዳ ላይ ሰፍረዋል። ታዲያ እኔ ለመብላትና ለመጠጣት፣ ከሚስቴም ጋር ለመተኛት ወደ ቤቴ ልሂድ?+ በአንተና በሕያውነትህ* እምላለሁ ይህን ፈጽሞ አላደርገውም!”
12 ከዚያም ዳዊት ኦርዮን “እንግዲያውስ ዛሬን እዚህ ቆይና ነገ አሰናብትሃለሁ” አለው። በመሆኑም ኦርዮ ያን ቀንና ቀጣዩን ቀን ኢየሩሳሌም ቆየ። 13 ዳዊትም አብሮት እንዲበላና እንዲጠጣ አስጠራው፤ አሰከረውም። ሆኖም ኦርዮ ምሽት ላይ ከጌታው አገልጋዮች ጋር ለመተኛት ወጥቶ ወደ መኝታው ሄደ እንጂ ወደ ቤቱ አልወረደም። 14 ሲነጋም ዳዊት ለኢዮዓብ ደብዳቤ ጽፎ በኦርዮ እጅ ላከለት። 15 በደብዳቤውም ላይ “ኦርዮን ውጊያው በተፋፋመበት ግንባር መድበው። እሱም ተመቶ እንዲሞት እናንተ ከኋላው አፈግፍጉ” ብሎ ጻፈ።+
16 ኢዮዓብም ከተማዋን በጥንቃቄ ይመለከት ነበር፤ ኦርዮንም ኃይለኛ ተዋጊዎች እንዳሉበት በሚያውቀው ግንባር መደበው። 17 የከተማዋም ሰዎች ወጥተው ከኢዮዓብ ጋር ሲዋጉ ከዳዊት አገልጋዮች መካከል አንዳንዶቹ ወደቁ፤ ከሞቱትም ሰዎች መካከል ሂታዊው ኦርዮ ይገኝበታል።+ 18 ከዚያም ኢዮዓብ የጦርነቱን አጠቃላይ ሁኔታ የሚገልጽ ወሬ ለዳዊት ላከ። 19 መልእክተኛውንም እንዲህ ሲል አዘዘው፦ “አጠቃላይ የጦርነቱን ሁኔታ ለንጉሡ ነግረህ ስትጨርስ 20 ንጉሡ ሊቆጣና እንዲህ ሊልህ ይችላል፦ ‘ከተማዋን ለመውጋት ይህን ያህል የተጠጋችሁት ለምንድን ነው? ቅጥሩ አናት ላይ ሆነው እንደሚወነጭፉባችሁ አታውቁም? 21 የየሩቤሼትን+ ልጅ አቢሜሌክን የገደለው ማን ሆነና ነው?+ በቅጥሩ አናት ላይ ሆና መጅ በመልቀቅ በቴቤጽ የገደለችው አንዲት ሴት አይደለችም? ታዲያ እናንተ ይህን ያህል ወደ ቅጥሩ የተጠጋችሁት ለምንድን ነው?’ በዚህ ጊዜ ‘አገልጋይህ ሂታዊው ኦርዮም ሞቷል’ በለው።”
22 በመሆኑም መልእክተኛው ተነስቶ ሄደ፤ ኢዮዓብ የላከውንም መልእክት ሁሉ ለዳዊት ነገረው። 23 መልእክተኛውም ዳዊትን እንዲህ አለው፦ “ሰዎቹ አየሉብን፤ እኛንም ለመውጋት ወደ ሜዳው ወጡ፤ እኛ ግን እስከ ከተማው መግቢያ ድረስ እንዲያፈገፍጉ አደረግናቸው። 24 ቀስተኞቹም ቅጥሩ አናት ላይ ሆነው በአገልጋዮችህ ላይ ቀስት ያስወነጭፉ ጀመር፤ በዚህም የተነሳ ከንጉሡ አገልጋዮች መካከል አንዳንዶቹ ተገደሉ፤ አገልጋይህ ሂታዊው ኦርዮም ሞተ።”+ 25 በዚህ ጊዜ ዳዊት መልእክተኛውን “ኢዮዓብን እንዲህ በለው፦ ‘መቼም ሰይፍ አንዱን እንደሚበላ ሁሉ ሌላውንም ስለሚበላ ይህ ሁኔታ አይረብሽህ። ብቻ አንተ በከተማዋ ላይ ውጊያህን በማፋፋም በቁጥጥር ሥር አውላት።’+ አንተም አበረታታው” አለው።
26 የኦርዮ ሚስት ባሏ መሞቱን ስትሰማ ለባለቤቷ አለቀሰችለት። 27 የሐዘኑ ጊዜ እንዳበቃም ዳዊት ልኮ ወደ ቤቱ አስመጣት፤ እሷም ሚስቱ ሆነች፤+ ወንድ ልጅም ወለደችለት። ሆኖም ዳዊት ያደረገው ነገር ይሖዋን በጣም አሳዝኖት* ነበር።+
12 በመሆኑም ይሖዋ ናታንን+ ወደ ዳዊት ላከው። እሱም ወደ ዳዊት መጥቶ+ እንዲህ አለው፦ “በአንዲት ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ሁለት ሰዎች ነበሩ፤ አንደኛው ሀብታም ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ድሃ ነበር። 2 ሀብታሙ ሰው እጅግ ብዙ በጎችና ከብቶች ነበሩት፤+ 3 ድሃው ሰው ግን ከገዛት አንዲት ትንሽ የበግ ጠቦት ሌላ ምንም አልነበረውም።+ እሱም ይንከባከባት ነበር፤ እሷም ከእሱና ከወንዶች ልጆቹ ጋር አብራ እየኖረች አደገች። ያለችውን ጥቂት ምግብ አብራ ትበላ፣ ከጽዋውም ትጠጣ እንዲሁም በእቅፉ ትተኛ ነበር። ለእሱም እንደ ሴት ልጁ ነበረች። 4 አንድ ቀን ሀብታሙ ሰው እንግዳ መጣበት፤ ሆኖም ይህ ሰው ወደ እሱ ለመጣው መንገደኛ የሚበላ ነገር ለማዘጋጀት ከራሱ በጎችና ከብቶች ላይ አልወሰደም። ከዚህ ይልቅ የድሃውን ሰው የበግ ጠቦት ወስዶ ወደ እሱ ለመጣው እንግዳ አዘጋጅቶ አቀረበለት።”+
5 በዚህ ጊዜ ዳዊት በሰውየው ላይ እጅግ ተቆጥቶ ናታንን እንዲህ አለው፦ “ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ፣+ ይህን ያደረገው ሰው ሞት ይገባዋል! 6 ይህ ሰው እንዲህ ያለውን ነገር ስላደረገና ርኅራኄ ስላላሳየ በበግ ጠቦቷ ምትክ አራት እጥፍ መክፈል አለበት።”+
7 ከዚያም ናታን ዳዊትን እንዲህ አለው፦ “ያ ሰው አንተ ነህ! የእስራኤል አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘በእስራኤል ላይ ንጉሥ እንድትሆን እኔ ራሴ ቀባሁህ፤+ ከሳኦልም እጅ ታደግኩህ።+ 8 የጌታህን ቤት ልሰጥህ፣+ የጌታህንም ሚስቶች+ በእቅፍህ ላደርግልህ ፈቃደኛ ነበርኩ፤ የእስራኤልንና የይሁዳንም ቤት ሰጠሁህ።+ ይህም ሁሉ አንሶህ ቢሆን ኖሮ ከዚህ የበለጠ ነገር ላደርግልህ ፈቃደኛ ነበርኩ።+ 9 ታዲያ በፊቱ መጥፎ ነገር በመሥራት የይሖዋን ቃል ያቃለልከው ለምንድን ነው? ሂታዊውን ኦርዮን በሰይፍ መታኸው!+ በአሞናውያን ሰይፍ ከገደልከውም+ በኋላ ሚስቱን ወስደህ ሚስትህ አደረግካት።+ 10 ስለዚህ የሂታዊውን የኦርዮን ሚስት ወስደህ ሚስትህ በማድረግ እኔን ስለናቅክ ሰይፍ ከቤትህ ፈጽሞ አይለይም።’+ 11 ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ከገዛ ቤትህ መከራ አመጣብሃለሁ፤+ ዓይንህ እያየም ሚስቶችህን ወስጄ ለሌላ ሰው* እሰጣቸዋለሁ፤+ እሱም በቀን ብርሃን* ከሚስቶችህ ጋር ይተኛል።+ 12 አንተ ይህን በድብቅ ብታደርገውም+ እኔ ግን በመላው እስራኤል ፊት በቀን ብርሃን* አደርገዋለሁ።’”
13 ከዚያም ዳዊት ናታንን “በይሖዋ ላይ ኃጢአት ሠርቻለሁ” አለው።+ ናታንም ዳዊትን እንዲህ አለው፦ “ይሖዋም ኃጢአትህን ይቅር ይላል።*+ አትሞትም።+ 14 ይሁንና ይህን ድርጊት በመፈጸም ይሖዋን እጅግ ስለናቅክ አሁን የተወለደልህ ልጅ ይሞታል።”
15 ከዚያም ናታን ወደ ቤቱ ሄደ።
ይሖዋም የኦርዮ ሚስት ለዳዊት የወለደችለትን ልጅ በመቅሰፍት መታው፤ ልጁም ታመመ። 16 ዳዊትም ስለ ልጁ እውነተኛውን አምላክ ተማጸነ። ምንም ነገር ሳይቀምስም ጾመ፤ ወደ ክፍሉ ገብቶም ሌሊቱን ሙሉ መሬት ላይ ተኝቶ አደረ።+ 17 በቤቱ ያሉ ሽማግሌዎችም መጥተው አጠገቡ ቆሙ፤ ከመሬት ሊያነሱትም ሞከሩ። እሱ ግን ፈቃደኛ አልሆነም፤ አብሯቸውም ምግብ አልበላም። 18 በሰባተኛው ቀን ልጁ ሞተ፤ የዳዊት አገልጋዮች ግን የልጁን መሞት ለእሱ መንገር ፈሩ። እነሱም እንዲህ አሉ፦ “ልጁ በሕይወት ሳለ ዳዊትን አነጋግረነው ነበር፤ እሱ ግን ሊሰማን ፈቃደኛ አልሆነም። ታዲያ አሁን ልጁ መሞቱን እንዴት እንነግረዋለን? መቼም ይህን ብንነግረው መጥፎ ነገር ሊያደርግ ይችላል።”
19 ዳዊት አገልጋዮቹ በሹክሹክታ ሲነጋገሩ ሲያይ ልጁ እንደሞተ ገባው። በመሆኑም አገልጋዮቹን “ልጁ ሞተ?” አላቸው። እነሱም “አዎ፣ ሞቷል” ብለው መለሱለት። 20 በዚህ ጊዜ ዳዊት ከመሬት ተነሳ። ከታጠበ፣ ዘይት ከተቀባና+ ልብሱን ከቀየረ በኋላም ወደ ይሖዋ ቤት+ ሄዶ ሰገደ። ወደ ቤቱም* ሄዶ ምግብ እንዲያቀርቡለት ጠየቀ፤ ከዚያም በላ። 21 አገልጋዮቹም “እንዲህ ያደረግከው ለምንድን ነው? ልጁ በሕይወት ሳለ ስትጾምና ስታለቅስ ነበር፤ ልጁ ሲሞት ግን ወዲያውኑ ተነሳህ፤ ምግብም በላህ” አሉት። 22 እሱም እንዲህ አለ፦ “ልጁ በሕይወት ሳለ ‘ማን ያውቃል፣ ይሖዋ ይራራልኝና ልጁን በሕይወት ያኖርልኝ ይሆናል’+ ብዬ ስላሰብኩ ጾምኩ፤+ እንዲሁም አለቀስኩ። 23 አሁን ግን ልጁ ሞቷል፤ ታዲያ የምጾመው ለምንድን ነው? መልሼ ላመጣው እችላለሁ?+ እኔ ወደ እሱ እሄዳለሁ+ እንጂ እሱ ወደ እኔ አይመለስም።”+
24 ከዚያም ዳዊት ሚስቱን ቤርሳቤህን+ አጽናናት። ወደ እሷም ገብቶ አብሯት ተኛ። ከጊዜ በኋላም ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙም ሰለሞን*+ ተባለ። ይሖዋም ወደደው፤+ 25 በነቢዩ ናታን+ በኩል መልእክት ልኮም ለይሖዋ ሲል ስሙን ይዲድያህ* አለው።
26 ኢዮአብ የአሞናውያን+ ከተማ የሆነችውን ራባን+ መውጋቱን ቀጠለ፤ የነገሥታቱንም* ከተማ ተቆጣጠረ።+ 27 በመሆኑም ኢዮአብ እንዲህ ብለው እንዲነግሩት መልእክተኞችን ወደ ዳዊት ላከ፦ “ከራባ+ ጋር ተዋግቼ የውኃዎችን ከተማ* ይዣለሁ። 28 በል አሁን የቀረውን ሠራዊት ሰብስብና ከተማዋን ከበህ በቁጥጥርህ ሥር አድርጋት። አለዚያ ከተማዋን እይዛትና ክብሩ ለእኔ ይሆናል።”*
29 በመሆኑም ዳዊት ሠራዊቱን ሁሉ ሰብስቦ ወደ ራባ ሄደ፤ ከተማዋንም ወግቶ በቁጥጥር ሥር አደረጋት። 30 ከዚያም የማልካምን* ዘውድ ከራሱ ላይ ወሰደ። የዘውዱም ክብደት አንድ ታላንት* ወርቅ ነበር፤ በላዩም ላይ የከበሩ ድንጋዮች ነበሩ፤ ዘውዱም በዳዊት ራስ ላይ ተደረገ። በተጨማሪም ከከተማዋ+ በጣም ብዙ ምርኮ ወሰደ።+ 31 ነዋሪዎቿንም አውጥቶ ድንጋይ እንዲቆርጡ፣ ስለት ባላቸው የብረት መሣሪያዎችና በብረት መጥረቢያዎች እንዲሠሩ እንዲሁም ጡብ እንዲያመርቱ አደረጋቸው። በአሞናውያን ከተሞች ሁሉ እንዲሁ አደረገ። በመጨረሻም ዳዊትና ሠራዊቱ ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።
13 የዳዊት ልጅ አቢሴሎም ትዕማር+ የምትባል ቆንጆ እህት ነበረችው፤ የዳዊት ልጅ አምኖንም+ ወደዳት። 2 አምኖን በእህቱ በትዕማር ምክንያት በጣም ከመጨነቁ የተነሳ ታመመ፤ ምክንያቱም ድንግል ስለነበረች በእሷ ላይ ምንም ነገር ማድረግ እንደማይችል ሆኖ ተሰምቶት ነበር። 3 አምኖን፣ ኢዮናዳብ+ የተባለ ጓደኛ ነበረው፤ እሱም የዳዊት ወንድም የሆነው የሺምአህ+ ልጅ ነው፤ ኢዮናዳብም ብልህ ሰው ነበር። 4 እሱም አምኖንን “አንተ የንጉሥ ልጅ፣ በየቀኑ እንዲህ የምትጨነቀው ለምንድን ነው? ለምን አትነግረኝም?” አለው። አምኖንም “የወንድሜን የአቢሴሎምን እህት+ ትዕማርን አፍቅሬ ነው” አለው። 5 በዚህ ጊዜ ኢዮናዳብ እንዲህ አለው፦ “የታመምክ መስለህ አልጋህ ላይ ተኛ። አባትህም ሊጠይቅህ ሲመጣ ‘እባክህ፣ እህቴ ትዕማር መጥታ ምግብ ትስጠኝ። ለታመመ ሰው የሚሆነውን ምግብ* እዚሁ እያየኋት ታዘጋጅልኝና በእጇ ታጉርሰኝ’ በለው።”
6 ስለዚህ አምኖን የታመመ መስሎ ተኛ፤ ንጉሡም ሊጠይቀው መጣ። ከዚያም አምኖን ንጉሡን “እባክህ፣ እህቴ ትዕማር ትምጣና እዚሁ እያየኋት ሁለት ቂጣ* ጋግራ በእጇ ታጉርሰኝ” አለው። 7 ዳዊትም “እባክሽ፣ ወደ ወንድምሽ ወደ አምኖን ቤት ሄደሽ ምግብ* አዘጋጂለት” ብለው ለትዕማር እንዲነግሯት ወደ ቤት መልእክት ላከ። 8 በመሆኑም ትዕማር ወደ ወንድሟ ወደ አምኖን ቤት ሄደች፤ እሱም እዚያ ተኝቶ ነበር። እሷም ሊጥ ካቦካች በኋላ እዚያው እያየ ጠፍጥፋ ጋገረችው። 9 ከዚያም መጋገሪያውን አውጥታ ቂጣውን አቀረበችለት። አምኖን ግን ለመብላት ፈቃደኛ አልሆነም፤ እሱም “ሁሉንም ሰው ከዚህ አስወጡልኝ!” አለ። ስለዚህ ሁሉም ሰው ትቶት ወጣ።
10 በዚህ ጊዜ አምኖን ትዕማርን “በእጅሽ እንድታጎርሺኝ ምግቡን* ወደ መኝታ ክፍል አምጪልኝ” አላት። ትዕማርም የጋገረችውን ቂጣ ይዛ ወንድሟ አምኖን ወደነበረበት መኝታ ክፍል ገባች። 11 እሷም ምግቡን እንዲበላ ስታቀርብለት አፈፍ አድርጎ ያዛትና “እህቴ ሆይ፣ ነይ፣ አብረሽኝ ተኚ” አላት። 12 እሷ ግን እንዲህ አለችው፦ “ወንድሜ ሆይ፣ ይሄማ ፈጽሞ አይሆንም! እባክህ አታዋርደኝ፤ በእስራኤል ውስጥ እንዲህ ያለ ነገር ተደርጎ አያውቅም።+ ይህን አሳፋሪ ድርጊት አትፈጽም።+ 13 እኔስ ብሆን ይህን ነውሬን ተሸክሜ እንዴት እኖራለሁ? አንተም ብትሆን በእስራኤል ውስጥ ካሉት ወራዳ ሰዎች እንደ አንዱ ትቆጠራለህ። ስለዚህ አሁን፣ እባክህ ንጉሡን አነጋግረው፤ እሱም ቢሆን እኔን አይከለክልህም።” 14 እሱ ግን ሊሰማት ፈቃደኛ አልሆነም፤ ከዚህ ይልቅ ኃይል ተጠቅሞ በማስነወር አዋረዳት። 15 ከዚያም አምኖን እጅግ በጣም ጠላት፤ ለእሷ ያደረበት ጥላቻም ለእሷ ከነበረው ፍቅር በለጠ። አምኖንም “ተነሽ ውጭልኝ!” አላት። 16 በዚህ ጊዜ “ወንድሜ ሆይ፣ ይሄማ አይሆንም፤ አሁን እኔን ማባረርህ ቀደም ሲል ከፈጸምክብኝ ነገር የከፋ ይሆናል!” አለችው። እሱ ግን ሊሰማት ፈቃደኛ አልሆነም።
17 ከዚያም አምኖን የሚያገለግለውን ወጣት ጠርቶ “እባክህ ይህችን ሴት ከፊቴ አስወጣና በሩን ዝጋባት” አለው። 18 (እሷም የሚያምር* ልብስ ለብሳ ነበር፤ ምክንያቱም ድንግል የሆኑት የንጉሡ ሴቶች ልጆች እንዲህ ዓይነት ልብስ ይለብሱ ነበር።) በመሆኑም አገልጋዩ ወደ ውጭ አስወጥቶ በሩን ዘጋባት። 19 ከዚያም ትዕማር ራሷ ላይ አመድ ነሰነሰች፤+ የለበሰችውንም የሚያምር ቀሚስ ቀደደች፤ በእጇም ራሷን ይዛ እያለቀሰች ሄደች።
20 በዚህ ጊዜ ወንድሟ አቢሴሎም+ “ወንድምሽ አምኖን ከአንቺ ጋር ነበር? እህቴ ሆይ፣ በቃ አሁን ዝም በይ። እንግዲህ እሱ ወንድምሽ ነው።+ ይህን ነገር በልብሽ አታብሰልስዪው” አላት። ከዚያም ትዕማር ከሌሎች ተገልላ በወንድሟ በአቢሴሎም ቤት ተቀመጠች። 21 ንጉሥ ዳዊት የሆነውን ነገር ሁሉ ሲሰማ እጅግ ተቆጣ።+ ሆኖም አምኖን የበኩር ልጁ በመሆኑ በጣም ይወደው ስለነበር ሊያስቀይመው አልፈለገም። 22 አቢሴሎምም አምኖንን ክፉም ሆነ ደግ አልተናገረውም፤ ምክንያቱም አቢሴሎም፣ አምኖን እህቱን ትዕማርን ስላዋረዳት+ ጠልቶት ነበር።+
23 ድፍን ሁለት ዓመት ካለፈ በኋላ እንዲህ ሆነ፤ አቢሴሎም በኤፍሬም+ አቅራቢያ ባለችው በበዓልሃጾር በጎቹን ያሸልት ነበር፤ አቢሴሎምም የንጉሡን ወንዶች ልጆች በሙሉ ጋበዘ።+ 24 በመሆኑም አቢሴሎም ወደ ንጉሡ ገብቶ “አገልጋይህ በጎቹን እያሸለተ ነው። እባክህ፣ ንጉሡና አገልጋዮቹ ከእኔ ጋር ይሂዱ” አለው። 25 ንጉሡ ግን አቢሴሎምን “የእኔ ልጅ፣ ይሄማ አይሆንም! ሁላችንም ከሄድን ሸክም እንሆንብሃለን” አለው። አቢሴሎም አጥብቆ ቢለምነውም ንጉሡ ለመሄድ ፈቃደኛ አልሆነም፤ ከዚህ ይልቅ ባረከው። 26 ከዚያም አቢሴሎም “እሺ አንተ ካልሄድክ እባክህ ወንድሜ አምኖን አብሮን ይሂድ”+ አለው። ንጉሡም “ከአንተ ጋር የሚሄደው ለምንድን ነው?” አለው። 27 አቢሴሎም ግን አጥብቆ ለመነው፤ በመሆኑም ዳዊት አምኖንንና የንጉሡን ወንዶች ልጆች በሙሉ ላካቸው።
28 ከዚያም አቢሴሎም አገልጋዮቹን እንዲህ ሲል አዘዛቸው፦ “ልብ ብላችሁ ተመልከቱ፣ እኔም አምኖን የወይን ጠጅ ጠጥቶ ሞቅ ሲለው ‘አምኖንን ምቱት!’ እላችኋለሁ። እናንተም ትገድሉታላችሁ። አትፍሩ፤ የማዛችሁ እኔ አይደለሁም? በርቱ! ደፋሮች ሁኑ!” 29 በመሆኑም የአቢሴሎም አገልጋዮች በአምኖን ላይ ልክ አቢሴሎም እንዳዘዛቸው አደረጉበት፤ ከዚያም ሌሎቹ የንጉሡ ልጆች በሙሉ ተነስተው በየበቅሏቸው ላይ በመቀመጥ ሸሹ። 30 ገና በመንገድ ላይ ሳሉም ዳዊት “አቢሴሎም የንጉሡን ልጆች በሙሉ ፈጃቸው፤ አንድም የተረፈ ሰው የለም” የሚል ወሬ ደረሰው። 31 በዚህ ጊዜ ንጉሡ ተነሳ፤ ልብሱንም ቀዶ መሬት ላይ ተዘረረ፤ አገልጋዮቹም በሙሉ ልብሳቸውን ቀደው አጠገቡ ቆመው ነበር።
32 ሆኖም የዳዊት ወንድም የሺምአህ+ ልጅ የሆነው ኢዮናዳብ+ እንዲህ አለ፦ “ጌታዬ ወጣቶቹን የንጉሡን ወንዶች ልጆች በሙሉ እንደገደሏቸው አድርጎ አያስብ፤ ምክንያቱም የሞተው አምኖን ብቻ ነው።+ ይህም በአቢሴሎም ትእዛዝ የተፈጸመ ነው፤ እሱ፣ አምኖን እህቱን+ ትዕማርን+ ካስነወረበት ቀን አንስቶ ይህን ነገር ለማድረግ ወስኖ ነበር።+ 33 አሁንም ጌታዬ ንጉሡ ‘የንጉሡ ወንዶች ልጆች በሙሉ አልቀዋል’ ለሚለው ወሬ ጆሮ አይስጥ፤ የሞተው አምኖን ብቻ ነው።”
34 ይህ በእንዲህ እንዳለ አቢሴሎም ሸሸ።+ በኋላም ጠባቂው ቀና ብሎ ሲመለከት ከኋላው ባለው ከተራራው አጠገብ በሚገኘው መንገድ ላይ ብዙ ሰዎች ሲመጡ አየ። 35 በዚህ ጊዜ ኢዮናዳብ+ ንጉሡን “ይኸው፣ የንጉሡ ወንዶች ልጆች ተመልሰው መጥተዋል። የሆነውም ነገር ልክ አገልጋይህ እንደተናገረው ነው” አለው። 36 እሱም ተናግሮ እንደጨረሰ የንጉሡ ወንዶች ልጆች ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እያለቀሱ ገቡ፤ ንጉሡና አገልጋዮቹም በሙሉ አምርረው አለቀሱ። 37 አቢሴሎም ግን ኮብልሎ የገሹር ንጉሥ ወደሆነው ወደ አሚሁድ ልጅ ወደ ታልማይ+ ሄደ። ዳዊትም ለልጁ ብዙ ቀናት አለቀሰ። 38 አቢሴሎም ሸሽቶ ወደ ገሹር+ ከሄደ በኋላ በዚያ ሦስት ዓመት ተቀመጠ።
39 በመጨረሻም የንጉሥ ዳዊት ነፍስ አቢሴሎምን ለማየት ናፈቀች፤ ምክንያቱም ዳዊት የአምኖን ሞት ካስከተለበት ሐዘን ተጽናንቶ ነበር።
14 የጽሩያ+ ልጅ ኢዮዓብ የንጉሡ ልብ አቢሴሎምን እንደናፈቀ ተረዳ።+ 2 በመሆኑም ኢዮአብ ወደ ተቆአ፣+ ሰው ልኮ አንዲት ብልህ ሴት አስመጣ፤ እንዲህም አላት፦ “እባክሽ፣ ሐዘንተኛ ምሰዪ፤ የሐዘን ልብስ ልበሺ፤ ዘይትም አትቀቢ።+ ሰው ሞቶባት ለረጅም ጊዜ እንዳዘነች ሴት ሁኚ። 3 ወደ ንጉሡም ገብተሽ እንዲህ በይው።” ከዚያም ኢዮዓብ ምን እንደምትል ነገራት።
4 ተቆአዊቷም ሴት ወደ ንጉሡ ከገባች በኋላ በግንባሯ ተደፍታ በመስገድ “ንጉሥ ሆይ፣ እርዳኝ!” አለች። 5 ንጉሡም “ምን ሆነሽ ነው?” አላት። እሷም እንዲህ አለችው፦ “እኔ ባሌ የሞተብኝ መበለት ነኝ። 6 እኔ አገልጋይህ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩኝ፤ እነሱም ሜዳ ላይ ተደባደቡ። ገላጋይም ስላልነበረ አንደኛው ሌላኛውን መትቶ ገደለው። 7 በኋላም ቤተ ዘመድ ሁሉ በእኔ በአገልጋይህ ላይ ተነስቶ ‘ወራሹን ማጥፋት ቢሆንብንም እንኳ የወንድሙን ሕይወት* ስላጠፋ እሱን እንድንገድለው ገዳዩን አሳልፈሽ ስጪን’ ይለኝ ጀመር።+ በመሆኑም የቀረችኝን አንዲት ፍም* በማጥፋት ባሌን በምድር ላይ ያለስምና ያለዘር ሊያስቀሩት ነው።”
8 ከዚያም ንጉሡ ሴትየዋን “በቃ አንቺ ወደ ቤትሽ ሂጂ፤ የአንቺን ጉዳይ በተመለከተ ትእዛዝ እሰጣለሁ” አላት። 9 በዚህ ጊዜ ተቆአዊቷ ሴት ንጉሡን “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ ንጉሡና ዙፋኑ ንጹሐን ስለሆኑ በደሉ በእኔና በአባቴ ቤት ላይ ይሁን” አለችው። 10 ከዚያም ንጉሡ “ከዚህ በኋላ ማንም ሰው ቢናገርሽ ወደ እኔ አምጪው፤ ዳግመኛም አያስቸግርሽም” አላት። 11 እሷ ግን “ደም ተበቃዩ+ በልጄ ላይ ጉዳት እንዳያደርስበትና እንዳይገድለው እባክህ ንጉሡ አምላኩን ይሖዋን ያስብ” አለችው። እሱም “ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ፣+ ከልጅሽ ራስ ላይ አንዲት ፀጉር እንኳ መሬት ላይ አትወድቅም” አላት። 12 ሴትየዋም “እባክህ አገልጋይህ ለጌታዬ ለንጉሡ አንዲት ቃል እንድትናገር ፍቀድላት” አለች። እሱም “እሺ፣ ተናገሪ!” አላት።
13 ከዚያም ሴትየዋ እንዲህ አለች፦ “ታዲያ አንተ በአምላክ ሕዝብ ላይ እንዲህ ያለ ነገር ለማድረግ ያሰብከው ለምንድን ነው?+ ንጉሡ የተሰደደውን የገዛ ልጁን ባለመመለሱ እንዲህ ብሎ ሲናገር ራሱን በደለኛ እያደረገ ነው።+ 14 ሁላችንም መሞታችን አይቀርም፤ የፈሰሰ ውኃ እንደማይታፈስ ሁሉ እኛም እንደዚሁ እንሆናለን። ሆኖም አምላክ ሕይወት* አያጠፋም፤ እንዲሁም የተሰደደ ሰው ከእሱ ርቆ በዚያው ተሰዶ እንዳይቀር እሱን ለመመለስ ምክንያት ይፈልጋል። 15 አሁንም ለጌታዬ ለንጉሡ ይህን ነገር ለመናገር የመጣሁት ሕዝቡ ስላስፈራኝ ነው። በመሆኑም አገልጋይህ እንዲህ ብላ አሰበች፦ ‘እንግዲህ አሁን ንጉሡን ላነጋግረው። ምናልባትም ንጉሡ ባሪያው የጠየቀችውን ነገር ይፈጽምላት ይሆናል። 16 ንጉሡ ቃሌን ሰምቶ እኔንም ሆነ አንድ ልጄን አምላክ ከሰጠን ርስት ላይ ሊያጠፋን ከሚፈልገው ሰው እጅ ባሪያውን ይታደጋት ይሆናል።’+ 17 ከዚያም አገልጋይህ ‘የጌታዬ የንጉሡ ቃል እረፍት ይስጠኝ’ አለች፤ ምክንያቱም ጌታዬ ንጉሡ ጥሩውን ከመጥፎው በመለየት ረገድ እንደ እውነተኛው አምላክ መልአክ ነው። አምላክህ ይሖዋም ከአንተ ጋር ይሁን።”
18 ንጉሡም መልሶ ሴትየዋን “እባክሽ፣ የምጠይቅሽን ነገር አንድም ሳትደብቂ ንገሪኝ” አላት። ሴትየዋም “እሺ፣ ንጉሡ ጌታዬ ይናገር” አለች። 19 ከዚያም ንጉሡ “በዚህ ሁሉ ነገር ውስጥ የኢዮዓብ እጅ አለበት?” ሲል ጠየቃት።+ ሴትየዋም እንዲህ ስትል መለሰች፦ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ በሕያውነትህ* እምላለሁ፣ ጌታዬ ንጉሡ እንደተናገረው ነው፤* ይህን እንዳደርግ ያዘዘኝና አገልጋይህ የተናገረችውን ነገር ሁሉ የነገራት አገልጋይህ ኢዮዓብ ነው። 20 አገልጋይህ ኢዮዓብ ይህን ያደረገው ሁኔታውን ለመለወጥ ሲል ነው፤ ሆኖም ጌታዬ እንደ እውነተኛው አምላክ መልአክ ዓይነት ጥበብ አለው፤ በምድሪቱ ላይ የሚከናወነውንም ነገር ሁሉ ያውቃል።”
21 ከዚያም ንጉሡ ኢዮዓብን “እሺ፣ ይህን አደርጋለሁ።+ በል ሂድና ወጣቱን አቢሴሎምን መልሰህ አምጣው” አለው።+ 22 በዚህ ጊዜ ኢዮዓብ በግንባሩ መሬት ላይ ተደፍቶ በመስገድ ንጉሡን አመሰገነ። ከዚያም “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ ንጉሡ አገልጋዩ የጠየቀውን ነገር ስለፈጸመለት ዛሬ እኔ አገልጋይህ በፊትህ ሞገስ እንዳገኘሁ አወቅኩ” አለ። 23 ኢዮዓብም ተነስቶ ወደ ገሹር+ ሄደ፤ አቢሴሎምንም ወደ ኢየሩሳሌም አመጣው። 24 ሆኖም ንጉሡ “ወደ ራሱ ቤት ይመለስ፤ ፊቴን እንዳያይ” አለ። በመሆኑም አቢሴሎም ወደ ራሱ ቤት ተመለሰ፤ የንጉሡንም ፊት አላየም።
25 መቼም በመልኩ ማማር የአቢሴሎምን ያህል የተወደሰ አንድም ወንድ በመላው እስራኤል አልነበረም። ከእግር ጥፍሩ አንስቶ እስከ ራስ ፀጉሩ ድረስ ምንም እንከን አይወጣለትም ነበር። 26 የራስ ፀጉሩን ሲቆረጠው ፀጉሩ በቤተ መንግሥቱ የድንጋይ ሚዛን* 200 ሰቅል* ይመዝን ነበር፤ ፀጉሩም በጣም ስለሚከብደው ሁልጊዜ በዓመቱ መጨረሻ ላይ መቆረጥ ነበረበት። 27 አቢሴሎም ትዕማር የምትባል አንዲት ሴት ልጅና ሦስት ወንዶች ልጆች ነበሩት።+ ትዕማር በጣም ቆንጆ ነበረች።
28 አቢሴሎምም በኢየሩሳሌም ድፍን ሁለት ዓመት ተቀመጠ፤ ሆኖም የንጉሡን ፊት አላየም።+ 29 በመሆኑም አቢሴሎም ወደ ንጉሡ ሊልከው ስለፈለገ ኢዮዓብን አስጠራው፤ ኢዮዓብ ግን ወደ እሱ ሳይመጣ ቀረ። ለሁለተኛ ጊዜም ሰው ላከበት፤ እሱ ግን አሁንም ለመምጣት ፈቃደኛ አልሆነም። 30 በመጨረሻም አቢሴሎም አገልጋዮቹን “የኢዮዓብ እርሻ የሚገኘው ከእኔ እርሻ አጠገብ ነው፤ በእርሻው ላይም የገብስ አዝመራ አለ። ሂዱና እሳት ልቀቁበት” አላቸው። በመሆኑም የአቢሴሎም አገልጋዮች በእርሻው ላይ እሳት ለቀቁበት። 31 በዚህ ጊዜ ኢዮዓብ ተነስቶ ወደ አቢሴሎም ቤት በመምጣት “አገልጋዮችህ እርሻዬን በእሳት ያቃጠሉት ለምንድን ነው?” አለው። 32 አቢሴሎምም ኢዮዓብን እንዲህ አለው፦ “ወደ እኔ ናና ለንጉሡ ‘“ከገሹር የመጣሁት ለምንድን ነው?+ እዚያው ብሆን ይሻለኝ ነበር። አሁንም ቢሆን የንጉሡን ፊት ማየት እፈልጋለሁ፤ ጥፋት ከተገኘብኝም ይግደለኝ” ብለህ እንድትነግርልኝ ልላክህ’ ብዬ መልእክት ላክሁብህ።”
33 በመሆኑም ኢዮዓብ ወደ ንጉሡ ገብቶ ይህንኑ ነገረው። ንጉሡም አቢሴሎምን ጠራው፤ አቢሴሎምም ወደ ንጉሡ ገብቶ በንጉሡ ፊት በግንባሩ መሬት ላይ በመደፋት ሰገደ። ንጉሡም አቢሴሎምን ሳመው።+
15 ከዚህ ሁሉ በኋላ አቢሴሎም ሠረገላ፣ ፈረሶችና ከፊቱ የሚሮጡ 50 ሰዎች አዘጋጀ።+ 2 አቢሴሎምም በጠዋት ተነስቶ ወደ ከተማዋ በር+ በሚወስደው መንገድ ዳር ይቆም ነበር። ማንም ሰው ሙግት ኖሮት ፍርድ ለማግኘት+ ወደ ንጉሡ በሚመጣበት ጊዜ አቢሴሎም ይጠራውና “ለመሆኑ አንተ የየትኛው ከተማ ሰው ነህ?” ይለው ነበር፤ እሱም “አገልጋይህ ከእስራኤል ነገዶች መካከል ከአንዱ ነው” ይለዋል። 3 አቢሴሎምም “አቤቱታህ ትክክልና ተገቢ ነው፤ ግን ምን ያደርጋል፣ ከንጉሡ ዘንድ ጉዳይህን የሚሰማልህ አንድም ሰው አታገኝም” ይለው ነበር። 4 ከዚያም አቢሴሎም “ምነው በምድሪቱ ላይ ዳኛ ሆኜ በተሾምኩ! ሙግት ያለው ወይም ፍርድ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ወደ እኔ መጥቶ ፍትሕ ማግኘት ይችል ነበር” ይል ነበር።
5 እንዲሁም አንድ ሰው ሊሰግድለት ወደ እሱ በሚቀርብበት ጊዜ አቢሴሎም እጁን ዘርግቶ ይይዘውና ይስመው ነበር።+ 6 አቢሴሎምም ፍርድ ለማግኘት ወደ ንጉሡ ለሚመጣው እስራኤላዊ በሙሉ እንዲህ ያደርግ ነበር፤ በዚህ መንገድ አቢሴሎም የእስራኤልን ሰዎች ልብ ሰረቀ።+
7 በአራቱ* ዓመት ማብቂያ ላይ አቢሴሎም ንጉሡን እንዲህ አለው፦ “እባክህ፣ ለይሖዋ የተሳልኩትን ስእለት ለማድረስ ወደ ኬብሮን+ ልሂድ። 8 ምክንያቱም እኔ አገልጋይህ በሶርያ ባለችው በገሹር+ በነበርኩበት ጊዜ ‘ይሖዋ ወደ ኢየሩሳሌም ከመለሰኝ ለይሖዋ መባ* አቀርባለሁ’ በማለት ተስዬ+ ነበር።” 9 በመሆኑም ንጉሡ “በሰላም ሂድ” አለው። እሱም ተነስቶ ወደ ኬብሮን ሄደ።
10 አቢሴሎምም “የቀንደ መለከት ድምፅ ስትሰሙ ‘አቢሴሎም በኬብሮን ነገሠ!’+ ብላችሁ አውጁ” በማለት በመላው የእስራኤል ነገዶች መካከል ሰላዮችን አሰማራ። 11 በዚህ ጊዜ ከኢየሩሳሌም 200 ሰዎች ከአቢሴሎም ጋር ወደዚያ ሄደው ነበር፤ ጥሪ ቀርቦላቸው የሄዱት እነዚህ ሰዎች ምንም የጠረጠሩትና የሚያውቁት ነገር አልነበረም። 12 በተጨማሪም አቢሴሎም መሥዋዕቶቹን በሚያቀርብበት ጊዜ የዳዊትን አማካሪ+ ጊሎአዊውን አኪጦፌልን+ ከከተማው ከጊሎ+ ልኮ አስጠራው። አቢሴሎም የጠነሰሰው ሴራ እየተጠናከረ ሄደ፤ ከአቢሴሎም ጎን የተሰለፈውም ሕዝብ ቁጥር እየጨመረ መጣ።+
13 በኋላም አንድ ሰው ወደ ዳዊት መጥቶ “የእስራኤል ሰዎች ልብ ወደ አቢሴሎም ሸፍቷል” ሲል ነገረው። 14 ዳዊትም በኢየሩሳሌም አብረውት የነበሩትን አገልጋዮቹን በሙሉ ወዲያውኑ እንዲህ አላቸው፦ “ተነሱ፣ እንሽሽ፤+ አለዚያ አንዳችንም ከአቢሴሎም እጅ አናመልጥም! በፍጥነት መጥቶ እንዳይዘንና እንዳያጠፋን፣ ከተማዋንም በሰይፍ እንዳይመታ ቶሎ ብለን ከዚህ እንሂድ!”+ 15 የንጉሡ አገልጋዮችም ንጉሡን “እኛ አገልጋዮችህ ጌታዬ ንጉሡ የወሰነውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነን” አሉት።+ 16 በመሆኑም ንጉሡ ቤተሰቡን ሁሉ አስከትሎ ወጣ፤ ሆኖም ቤቱን* እንዲጠብቁ አሥር ቁባቶቹን እዚያው አስቀረ።+ 17 ንጉሡም ሕዝቡን ሁሉ አስከትሎ ተጓዘ፤ እነሱም ቤትሜርሃቅ ሲደርሱ ቆሙ።
18 ከዚያም አብረውት የሄዱት* አገልጋዮቹ በሙሉ፣ ከሪታውያን በሙሉ፣ ጴሌታውያን+ በሙሉ እንዲሁም ከጌት+ ተከትለውት የመጡት 600 ጌታውያን+ ንጉሡ እያያቸው አለፉ።* 19 ንጉሡም ጌታዊውን ኢታይን+ እንዲህ አለው፦ “ከእኛ ጋር የምትሄደው ለምንድን ነው? በል ተመለስና ከአዲሱ ንጉሥ ጋር ተቀመጥ፤ አንተ ለራስህ ከአገርህ ተሰደህ የመጣህ የባዕድ አገር ሰው ነህ። 20 የመጣኸው ገና ትናንት ነው፤ ታዲያ ዛሬ እኔ ወደምሄድበት ቦታ ሁሉ አብረህ እንድትሄድ በማድረግ ከእኛ ጋር እንድትንከራተት ላድርግ? በል አሁን ወንድሞችህን ይዘህ ተመለስ፤ ይሖዋም ታማኝ ፍቅርና ታማኝነት ያሳይህ!”+ 21 ኢታይ ግን ለንጉሡ “ሕያው በሆነው በይሖዋና ሕያው በሆነው በጌታዬ በንጉሡ እምላለሁ፣ በሕይወት ብኖርም ሆነ ብሞት ጌታዬ ንጉሡ በሚገኝበት በማንኛውም ቦታ ሁሉ እኔ አገልጋይህም በዚያ እሆናለሁ!” ሲል መለሰ።+ 22 በዚህ ጊዜ ዳዊት ኢታይን+ “እሺ፣ እለፍ” አለው። በመሆኑም ጌታዊው ኢታይ ከሰዎቹና ከልጆቹ ሁሉ ጋር አለፈ።
23 እነዚህ ሁሉ ሰዎች በሚያልፉበት ጊዜ በአካባቢው ያሉ ሰዎች በሙሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ያለቅሱ ነበር፤ ንጉሡም በቄድሮን ሸለቆ+ አጠገብ ቆሞ ነበር፤ ሕዝቡም ሁሉ ወደ ምድረ በዳው ወደሚወስደው መንገድ ተሻገረ። 24 ሳዶቅም+ በዚያ ነበር፤ የእውነተኛውን አምላክ የቃል ኪዳን ታቦት+ የተሸከሙት ሌዋውያንም+ በሙሉ ከእሱ ጋር ነበሩ፤ እነሱም የእውነተኛውን አምላክ ታቦት አስቀመጡት፤ ሕዝቡ ሁሉ ከተማዋን ለቆ ከተሻገረም በኋላ አብያታር+ ወጣ። 25 ሆኖም ንጉሡ ሳዶቅን እንዲህ አለው፦ “የእውነተኛውን አምላክ ታቦት ወደ ከተማዋ መልሱት።+ በይሖዋ ፊት ሞገስ ካገኘሁ እንድመለስና ታቦቱንም ሆነ ማደሪያ ስፍራውን እንዳይ ያደርገኝ ይሆናል።+ 26 ይሁንና እሱ ‘በአንተ አልተደሰትኩም’ ካለኝ መልካም መስሎ የታየውን ያድርግብኝ።” 27 ንጉሡም ካህኑን ሳዶቅን እንዲህ አለው፦ “አንተ ባለ ራእይ አይደለህም?+ በል እንግዲህ ወደ ከተማዋ በሰላም ተመለስ፤ ሁለቱን ልጆቻችሁን ማለትም የገዛ ልጅህን አኪማዓስንና የአብያታርን ልጅ ዮናታንን+ ይዘህ ተመለስ። 28 እኔም ከእናንተ አንድ መልእክት እስኪመጣልኝ ድረስ በምድረ በዳው በሚገኙት መልካዎች* አጠገብ እቆያለሁ።”+ 29 ስለዚህ ሳዶቅና አብያታር የእውነተኛውን አምላክ ታቦት ይዘው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ እነሱም በዚያ ተቀመጡ።
30 ዳዊት የደብረ ዘይትን ተራራ*+ ሽቅብ ሲወጣ እያለቀሰ ነበር፤ እሱም ራሱን ተከናንቦ ባዶ እግሩን ይሄድ ነበር። አብረውት የነበሩት ሰዎችም ሁሉ ራሳቸውን ተከናንበው እያለቀሱ ሽቅብ ወጡ። 31 ከዚያም ዳዊት “ከአቢሴሎም+ ጋር ካሴሩት+ ሰዎች አንዱ እኮ አኪጦፌል ነው” ተብሎ ተነገረው። በዚህ ጊዜ ዳዊት “ይሖዋ ሆይ፣+ እባክህ የአኪጦፌልን ምክር የሞኝ ምክር+ አድርገው!” አለ።
32 ዳዊት ሕዝቡ ለአምላክ ይሰግድበት ወደነበረው የተራራ ጫፍ ሲደርስ አርካዊው+ ኩሲ+ ልብሱን ቀዶና በራሱ ላይ አቧራ ነስንሶ እሱን ለማግኘት በዚያ ይጠባበቅ ነበር። 33 ዳዊት ግን እንዲህ አለው፦ “አብረኸኝ የምትሻገር ከሆነ ሸክም ትሆንብኛለህ። 34 ከዚህ ይልቅ ወደ ከተማዋ ተመልሰህ አቢሴሎምን ‘ንጉሥ ሆይ፣ እኔ የአንተ አገልጋይ ነኝ።+ ቀደም ሲል የአባትህ አገልጋይ ነበርኩ፤ አሁን ግን የአንተ አገልጋይ ነኝ’ ብትለው የአኪጦፌልን ምክር ታከሽፍልኛለህ።+ 35 ካህናት የሆኑት ሳዶቅና አብያታር እዚያው ከአንተ ጋር አይደሉም? ከንጉሡ ቤት የምትሰማውን ነገር ሁሉ ካህናት ለሆኑት ለሳዶቅና ለአብያታር ንገራቸው።+ 36 ከእነሱም ጋር ሁለቱ ልጆቻቸው ማለትም የሳዶቅ ልጅ አኪማዓስና+ የአብያታር ልጅ ዮናታን+ አሉ፤ እናንተም የምትሰሙትን ማንኛውንም ነገር በእነሱ በኩል ልካችሁ አሳውቁኝ።” 37 በመሆኑም አቢሴሎም ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ የዳዊት ወዳጅ*+ የሆነው ኩሲ ወደ ከተማዋ ሄደ።
16 ዳዊት የተራራውን ጫፍ+ አልፎ ጥቂት እንደሄደ ሲባ+ የተባለው የሜፊቦስቴ+ አገልጋይ 200 ዳቦዎች፣ 100 የዘቢብ ቂጣዎች፣ ከበጋ ፍሬ* የተዘጋጁ 100 ቂጣዎችና አንድ እንስራ የወይን ጠጅ የተጫነባቸው ሁለት አህዮች እየነዳ ሊያገኘው መጣ።+ 2 ንጉሡም ሲባን “እነዚህን ነገሮች ያመጣኸው ለምንድን ነው?” አለው። ሲባም “አህዮቹን የንጉሡ ቤተሰብ እንዲቀመጥባቸው፣ ዳቦውንና የበጋ ፍሬውን ደግሞ ወጣቶቹ እንዲበሏቸው፣ የወይን ጠጁንም በምድረ በዳ የደከሙ ሰዎች እንዲጠጡት ነው” ሲል መለሰ።+ 3 ንጉሡም “የጌታህ ልጅ* የት አለ?” አለው።+ በዚህ ጊዜ ሲባ ንጉሡን “‘ዛሬ የእስራኤል ቤት የአባቴን ንጉሣዊ ሥልጣን ይመልስልኛል’ ብሎ ስላሰበ ኢየሩሳሌም ቀርቷል” አለው።+ 4 ንጉሡም ሲባን “እንግዲህ የሜፊቦስቴ የሆነው ሁሉ የአንተ ነው” አለው።+ ሲባም “በፊትህ እሰግዳለሁ። ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ በአንተ ዘንድ ሞገስ ላግኝ” ሲል መለሰ።+
5 ንጉሥ ዳዊትም ባሁሪም ሲደርስ ከሳኦል ቤት የሆነ ሺምአይ+ የተባለ ሰው ከዚያ ወጥቶ እየተራገመ+ ወደ እነሱ ቀረበ፤ እሱም የጌራ ልጅ ነበር። 6 ሺምአይ በንጉሥ ዳዊትና በአገልጋዮቹ ሁሉ ላይ እንዲሁም በንጉሡ ግራና ቀኝ በነበረው ሕዝብ ሁሉና በኃያላኑ ላይ ድንጋይ ይወረውር ነበር። 7 ሺምአይም እንዲህ እያለ ይራገም ነበር፦ “ውጣ፣ ከዚህ ውጣ፣ አንተ የደም ሰው! አንተ የማትረባ ሰው! 8 ንግሥናውን በወሰድክበት በሳኦል ቤት የተነሳ ያለብህን የደም ዕዳ በሙሉ ይሖዋ በአንተ ላይ እያመጣብህ ነው፤ ይሖዋም መንግሥትህን ለልጅህ ለአቢሴሎም አሳልፎ ይሰጠዋል። የደም ሰው ስለሆንክ ይኸው መከራህን እያየህ ነው!”+
9 ከዚያም የጽሩያ+ ልጅ አቢሳ ንጉሡን “ይህ የሞተ ውሻ+ ጌታዬን ንጉሡን የሚራገመው ለምንድን ነው?+ እባክህ ልሂድና ራሱን ልቁረጠው”+ አለው። 10 ንጉሡ ግን “እናንተ የጽሩያ ልጆች፣ ከእናንተ ጋር ምን የሚያገናኘኝ ጉዳይ አለ?+ ተዉት ይርገመኝ፤+ ምክንያቱም ይሖዋ ‘ዳዊትን እርገመው!’ ብሎታል።+ ታዲያ ‘ለምን እንዲህ ታደርጋለህ?’ ማን ሊለው ይችላል?” አለው። 11 ከዚያም ዳዊት አቢሳንና አገልጋዮቹን በሙሉ እንዲህ አላቸው፦ “ከአብራኬ የወጣው የገዛ ልጄ እንኳ ይኸው ሕይወቴን* እየፈለገ አይደል?+ ታዲያ አንድ ቢንያማዊ+ እንዲህ ቢያደርግ ምን ያስደንቃል! ተዉት ይርገመኝ፤ ይሖዋ እርገመው ብሎት ነው! 12 ምናልባትም ይሖዋ መከራዬን ያይልኝና+ በዛሬው እርግማን ፋንታ ይሖዋ መልካም ነገር ያደርግልኝ ይሆናል።”+ 13 ከዚያም ዳዊትና ሰዎቹ መንገዱን ይዘው ቁልቁል ወረዱ፤ ሺምአይም በተራራው ጥግ ከዳዊት ጎን ጎን እየሄደ ይራገም፣+ ድንጋይ ይወረውርና አቧራ ይበትን ነበር።
14 በኋላም ንጉሡና አብሮት የነበረው ሕዝብ በሙሉ ወዳሰቡበት ቦታ ደረሱ፤ እነሱም በጣም ደክሟቸው ነበር፤ በዚያም አረፉ።
15 ይህ በእንዲህ እንዳለ አቢሴሎምና የእስራኤል ሰዎች በሙሉ ኢየሩሳሌም ደረሱ፤ አኪጦፌልም+ አብሮት ነበር። 16 የዳዊት ወዳጅ* አርካዊው+ ኩሲም+ ልክ ወደ አቢሴሎም እንደገባ አቢሴሎምን “ንጉሡ ለዘላለም ይኑር!+ ንጉሡ ለዘላለም ይኑር!” አለው። 17 በዚህ ጊዜ አቢሴሎም ኩሲን “ለወዳጅህ ታማኝ ፍቅር የምታሳየው በዚህ መንገድ ነው? ከወዳጅህ ጋር አብረህ ያልሄድከው ለምንድን ነው?” አለው። 18 ኩሲም አቢሴሎምን እንዲህ አለው፦ “በጭራሽ፣ እንዲህማ አላደርግም፤ ይሖዋ፣ ይህ ሕዝብና የእስራኤል ሰዎች በሙሉ ከመረጡት ሰው ጎን እቆማለሁ። ከእሱም ጋር እቀመጣለሁ። 19 ደግሜ ይህን እናገራለሁ፣ ማገልገል ያለብኝ ማንን ነው? ልጁን አይደለም? አባትህን እንዳገለገልኩ ሁሉ አንተንም አገለግላለሁ።”+
20 ከዚያም አቢሴሎም አኪጦፌልን “እስቲ ምክር ስጡኝ።+ ምን ብናደርግ ይሻላል?” አለው። 21 አኪጦፌልም አቢሴሎምን “አባትህ፣ ቤቱን* እንዲጠብቁ ከተዋቸው+ ቁባቶቹ ጋር ግንኙነት ፈጽም።+ ከዚያም እስራኤላውያን ሁሉ ራስህን በአባትህ ዘንድ እንደ ጥንብ እንዳስቆጠርክ ይሰማሉ፤ አንተንም የሚደግፉ ብርታት ያገኛሉ” አለው። 22 በመሆኑም ለአቢሴሎም በጣሪያው ላይ ድንኳን ተከሉለት፤+ አቢሴሎምም እስራኤላውያን ሁሉ እያዩት+ ከአባቱ ቁባቶች ጋር ግንኙነት ፈጸመ።+
23 በዚያ ዘመን አኪጦፌል+ የሚሰጠው ምክር እንደ እውነተኛው አምላክ ቃል ተደርጎ* ይቆጠር ነበር። ዳዊትም ሆነ አቢሴሎም የአኪጦፌልን ምክር ሁሉ የሚያዩት እንደዚያ ነበር።
17 ከዚያም አኪጦፌል አቢሴሎምን እንዲህ አለው፦ “እባክህ፣ 12,000 ሰዎች ልምረጥና ተነስቼ ዛሬ ማታ ዳዊትን ላሳደው። 2 በደከመውና አቅም ባጣ* ጊዜ ድንገት እደርስበታለሁ፤+ ሽብርም እለቅበታለሁ፤ አብረውት ያሉት ሰዎችም ሁሉ ይሸሻሉ፤ ንጉሡን ብቻ እመታለሁ።+ 3 ከዚያም ሕዝቡን ሁሉ ወደ አንተ እመልሳለሁ። የሕዝቡ ሁሉ መመለስ የተመካው አንተ የምትፈልገው ሰው በሚደርስበት ነገር ላይ ነው። ከዚያ በኋላ ሕዝቡ ሁሉ ሰላም ያገኛል።” 4 ይህ ሐሳብም በአቢሴሎምና በእስራኤል ሽማግሌዎች ሁሉ ፊት መልካም ሆኖ ተገኘ።
5 ሆኖም አቢሴሎም “እስቲ አርካዊውን ኩሲን+ ጥሩትና እሱ ደግሞ የሚለውን እንስማ” አለ። 6 በመሆኑም ኩሲ ወደ አቢሴሎም ገባ። ከዚያም አቢሴሎም “አኪጦፌል እንዲህ የሚል ምክር ሰጥቷል። ታዲያ እሱ እንዳለው እናድርግ? ካልሆነ የአንተን ሐሳብ ንገረን” አለው። 7 ኩሲም አቢሴሎምን “እዚህ ላይ እንኳ አኪጦፌል የሰጠው ምክር የሚያዋጣ አይደለም!” አለው።+
8 አክሎም ኩሲ እንዲህ አለ፦ “መቼም አባትህም ሆነ አብረውት ያሉት ሰዎች ኃያል ተዋጊዎችና+ በሜዳ እንዳለች ግልገሎቿን ያጣች ድብ+ ምንም ነገር ከማድረግ የማይመለሱ* መሆናቸውን በሚገባ ታውቃለህ። ደግሞም አባትህ ጦረኛ ነው፤+ ሌሊት ከሕዝቡ ጋር አያድርም። 9 ይህን ጊዜ እኮ አንድ ዋሻ* ውስጥ ወይም ሌላ ቦታ ተደብቋል፤+ እሱ ቀድሞ ጥቃት ከሰነዘረ ይህን የሰሙ ሁሉ ‘አቢሴሎምን የተከተሉት ሰዎች ድል ተመቱ!’ ብለው ያወራሉ። 10 ልቡ እንደ አንበሳ+ የሆነ ደፋር ሰው እንኳ በፍርሃት መራዱ አይቀርም፤ ምክንያቱም አባትህ ኃያል ተዋጊ፣ አብረውት ያሉትም ሰዎች ጀግኖች+ መሆናቸውን መላው እስራኤል ያውቃል። 11 እንግዲህ እኔ የምመክርህ ይህ ነው፦ ከብዛቱ የተነሳ በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ+ የሆነው ከዳን አንስቶ እስከ ቤርሳቤህ+ ድረስ ያለው የእስራኤል ሕዝብ በሙሉ ወደ አንተ ይሰብሰብ፤ አንተ ራስህም እየመራህ ወደ ውጊያ ውሰዳቸው። 12 እኛም የገባበት ገብተን ጥቃት እንሰነዝርበታለን፤ በመሬት ላይ እንደሚወርድ ጤዛም እንወርድበታለን፤ እሱም ሆነ ከእሱ ጋር ያሉት ሰዎች አንዳቸውም አያመልጡም። 13 ወደ አንድ ከተማ ቢሸሽ እንኳ መላው እስራኤል ወደ ከተማዋ ገመድ ይዞ በመሄድ፣ ከተማዋን ጎትተን አንዲት ጠጠር ሳናስቀር ሸለቆ ውስጥ እንከታታለን።”
14 ከዚያም አቢሴሎምና የእስራኤል ሰዎች በሙሉ “ከአኪጦፌል ምክር ይልቅ የአርካዊው የኩሲ ምክር ይሻላል!” አሉ።+ ምክንያቱም ይሖዋ በአቢሴሎም ላይ ጥፋት ለማምጣት ሲል ይሖዋ መልካም የሆነውን የአኪጦፌልን+ ምክር ለማክሸፍ ወስኖ* ነበር።+
15 በኋላም ኩሲ ካህናት የሆኑትን ሳዶቅንና አብያታርን+ እንዲህ አላቸው፦ “አኪጦፌል እንዲህ እንዲህ በማለት አቢሴሎምንና የእስራኤልን ሽማግሌዎች መክሯቸው ነበር፤ እኔ ደግሞ እንዲህ እንዲህ ብዬ መክሬያቸዋለሁ። 16 አሁንም ለዳዊት ፈጥናችሁ መልእክት በመላክ እንዲህ ብላችሁ አስጠንቅቁት፦ ‘ዛሬ ሌሊት በምድረ በዳው ባሉት መልካዎች* እንዳታድር፤ የግድ መሻገር አለብህ፤ አለዚያ ንጉሡና አብሮት ያለው ሕዝብ በሙሉ ያልቃል።’”*+
17 ዮናታንና+ አኪማዓስም+ በኤንሮጌል+ ተቀምጠው ነበር፤ በመሆኑም አንዲት አገልጋይ ሄዳ መልእክቱን ነገረቻቸው፤ እነሱም ሁኔታውን ለንጉሥ ዳዊት ለመንገር ሄዱ። ምክንያቱም ወደ ከተማዋ ከገባን እንታያለን ብለው ፈርተው ነበር። 18 ይሁንና አንድ ወጣት አያቸውና ለአቢሴሎም ነገረው። ስለሆነም ሁለቱም በፍጥነት ከዚያ በመሄድ በባሁሪም+ ወደሚገኝ አንድ ሰው ቤት መጡ፤ እሱም ግቢው ውስጥ የውኃ ጉድጓድ ነበረው። እነሱም እዚያ ውስጥ ገቡ፤ 19 የሰውየውም ሚስት በጉድጓዱ አፍ ላይ ማስጫ ዘርግታ የተከካ እህል አሰጣችበት፤ ይህን ያወቀ ማንም ሰው አልነበረም። 20 የአቢሴሎም አገልጋዮችም ወደ ሴትየዋ ቤት መጥተው “አኪማዓስና ዮናታን የት አሉ?” አሏት። እሷም “በዚህ አልፈው ወደ ወንዙ ሄደዋል” አለቻቸው።+ ሰዎቹም ፍለጋቸውን ቀጠሉ፤ ሆኖም ሊያገኟቸው አልቻሉም፤ ስለዚህ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።
21 ሰዎቹ ከሄዱም በኋላ አኪማዓስና ዮናታን ከጉድጓዱ ወጥተው ወደ ንጉሥ ዳዊት በመሄድ “እናንተ ሰዎች፣ ተነስታችሁ በፍጥነት ወንዙን ተሻገሩ፤ ምክንያቱም አኪጦፌል ስለ እናንተ እንዲህ እንዲህ የሚል ምክር ሰጥቷል” አሉት።+ 22 ዳዊትና አብሮት የነበረው ሕዝብ በሙሉ ወዲያውኑ ተነስተው ዮርዳኖስን ተሻገሩ። ጎህ ሲቀድም ዮርዳኖስን ሳይሻገር የቀረ አንድም ሰው አልነበረም።
23 አኪጦፌል፣ የሰጠው ምክር ተቀባይነት እንዳላገኘ ሲያይ አህያውን ጭኖ በሚኖርባት ከተማ ወደሚገኘው ቤቱ ሄደ።+ ከዚያም ለቤተሰቡ አንዳንድ መመሪያዎችን ከሰጠ+ በኋላ ታንቆ ሞተ።+ በአባቶቹም የመቃብር ቦታ ተቀበረ።
24 ይህ በእንዲህ እንዳለ ዳዊት ወደ ማሃናይም+ ሄደ፤ አቢሴሎም ደግሞ ከእስራኤል ሰዎች ሁሉ ጋር ዮርዳኖስን ተሻገረ። 25 አቢሴሎም በኢዮዓብ+ ቦታ አሜሳይን+ በሠራዊቱ ላይ ሾመው፤ አሜሳይ የእስራኤላዊው የይትራ ልጅ ነበር፤ ይትራ የኢዮዓብ እናት ከሆነችው ከጽሩያ እህት ከአቢጋኤል+ ጋር ግንኙነት ነበረው፤ አቢጋኤል የናሃሽ ልጅ ነበረች። 26 እስራኤላውያንና አቢሴሎም በጊልያድ+ ምድር ሰፈሩ።
27 ዳዊት ማሃናይም ሲደርስ የአሞናውያን ከተማ ከሆነችው ከራባ+ የመጣው የናሃሽ ልጅ ሾባይ፣ ከሎደባር የመጣው የአሚዔል ልጅ ማኪርና+ ከሮገሊም የመጣው ጊልያዳዊው ቤርዜሊ+ 28 ለመኝታ የሚሆኑ ነገሮች፣ ጎድጓዳ ሳህኖች፣ የሸክላ ዕቃዎች፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ ዱቄት፣ ቆሎ፣ ባቄላ፣ ምስር፣ የተጠበሰ እሸት፣ 29 ማር፣ ቅቤ፣ በግና አይብ* ይዘው መጡ። ይህን ሁሉ ይዘው የመጡት “መቼም ሕዝቡ በምድረ በዳ ተርቧል፣ ደክሟል፣ ተጠምቷል” ብለው በማሰብ ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች እንዲበሉት ነው።+
18 ከዚያም ዳዊት አብረውት የነበሩትን ሰዎች ቆጠረ፤ በእነሱም ላይ የሺህ አለቆችና የመቶ አለቆች ሾመ።+ 2 በተጨማሪም ዳዊት ከሰዎቹ መካከል አንድ ሦስተኛውን በኢዮዓብ+ አመራር* ሥር፣ አንድ ሦስተኛውን ደግሞ የኢዮዓብ ወንድም በሆነው በጽሩያ+ ልጅ በአቢሳ+ አመራር ሥር እንዲሁም አንድ ሦስተኛውን በጌታዊው በኢታይ+ አመራር ሥር አድርጎ ላከ። ንጉሡም ሰዎቹን “እኔም አብሬያችሁ እወጣለሁ” አላቸው። 3 እነሱ ግን እንዲህ አሉት፦ “አንተማ መውጣት የለብህም፤+ ለመሸሽ ብንገደድ እንኳ እነሱ ስለ እኛ ደንታ አይሰጣቸውም፤* ግማሾቻችን ብንሞትም ግድ የላቸውም፤ ምክንያቱም አንተ ከእኛ ከአሥሩ ሺህ ትበልጣለህ።+ ስለዚህ ከተማው ውስጥ ሆነህ ድጋፍ ብትሰጠን ይሻላል።” 4 ንጉሡም “እሺ፣ እናንተ የተሻለ ነው ያላችሁትን አደርጋለሁ” አላቸው። በመሆኑም ንጉሡ በከተማዋ በር አጠገብ ቆመ፤ ሰዎቹም ሁሉ በመቶዎችና በሺዎች እየሆኑ ወጡ። 5 ንጉሡም ኢዮዓብን፣ አቢሳንና ኢታይን “ለእኔ ስትሉ በወጣቱ በአቢሴሎም ላይ አትጨክኑበት” ሲል አዘዛቸው።+ ንጉሡ አቢሴሎምን አስመልክቶ ለአለቆቹ በሙሉ ትእዛዝ ሲሰጥ ሰዎቹ ሁሉ ሰሙ።
6 ሰዎቹም ከእስራኤላውያን ጋር ለመዋጋት ወደ ሜዳው ወጡ፤ ውጊያውም በኤፍሬም ጫካ ውስጥ ተካሄደ።+ 7 በዚያም የእስራኤል ሰዎች+ በዳዊት አገልጋዮች ድል ተመቱ፤+ በዚያም ቀን ታላቅ እልቂት ሆነ፤ ከመካከላቸውም 20,000 ሰው ተገደለ። 8 ውጊያውም በአካባቢው ሁሉ ተዛመተ። በዚያን ቀን ሰይፍ ከበላው ይልቅ ጫካ የበላው ሰው በለጠ።
9 በኋላም አቢሴሎም ከዳዊት አገልጋዮች ጋር ድንገት ተገናኘ። አቢሴሎም በበቅሎ ላይ ተቀምጦ ይሄድ ነበር፤ በቅሎዋም ጥቅጥቅ ያለ ቅርንጫፍ ባለው አንድ ትልቅ ዛፍ ሥር ስታልፍ ዛፉ የአቢሴሎምን ፀጉር ያዘው፤ በመሆኑም የተቀመጠባት በቅሎ ስታልፍ እሱ አየር ላይ* ተንጠልጥሎ ቀረ። 10 ከዚያም አንድ ሰው ይህን አይቶ ለኢዮዓብ+ “አቢሴሎምን አንድ ትልቅ ዛፍ ላይ ተንጠልጥሎ አየሁት!” ብሎ ነገረው። 11 በዚህ ጊዜ ኢዮዓብ ይህን የነገረውን ሰው “እና ካየኸው ያኔውኑ መትተህ መሬት ላይ ያልጣልከው ለምንድን ነው? እንዲህ ብታደርግ ኖሮ አሥር ሰቅል ብርና ቀበቶ እሸልምህ ነበር” አለው። 12 ሰውየው ግን ኢዮዓብን እንዲህ አለው፦ “1,000 የብር ሰቅል ቢሰጠኝ* እንኳ በንጉሡ ልጅ ላይ እጄን አላነሳም፤ ምክንያቱም ንጉሡ አንተን፣ አቢሳንና ኢታይን ‘ማናችሁም ብትሆኑ በወጣቱ በአቢሴሎም ላይ ጉዳት እንዳታደርሱበት ተጠንቀቁ’ ብሎ ሲያዛችሁ ሰምተናል።+ 13 ትእዛዙን በመተላለፍ የልጁን ሕይወት አጥፍቼ* ቢሆን ኖሮ ይህ ጉዳይ ከንጉሡ ተሰውሮ ሊቀር አይችልም ነበር፤ አንተም ብትሆን ልታስጥለኝ አትችልም።” 14 ኢዮዓብም “ከዚህ በላይ ከአንተ ጋር ጊዜ አላጠፋም!” አለው። ከዚያም ሦስት ቀስቶች* ይዞ በመሄድ አቢሴሎም በትልቁ ዛፍ መሃል ተንጠልጥሎ ገና በሕይወት እያለ ቀስቶቹን ልቡ ላይ ሰካቸው። 15 ከዚያም ከኢዮዓብ ጋሻ ጃግሬዎች አሥሩ መጥተው አቢሴሎምን መትተው ገደሉት።+ 16 ኢዮዓብም ቀንደ መለከት ነፋ፤ ሰዎቹም እስራኤላውያንን ከማሳደድ ተመለሱ፤ በዚህ መንገድ ኢዮዓብ ሰዎቹን አስቆማቸው። 17 እነሱም አቢሴሎምን ወስደው ጫካው ውስጥ በሚገኝ አንድ ትልቅ ጉድጓድ ውስጥ ጣሉት፤ በላዩም ላይ በጣም ትልቅ የድንጋይ ቁልል ከመሩበት።+ እስራኤላውያንም በሙሉ ወደየቤታቸው ሸሹ።
18 አቢሴሎም በሕይወት ሳለ “ስሜ የሚታወስበት ልጅ የለኝም”+ በማለት በንጉሡ ሸለቆ*+ ለራሱ ዓምድ አቁሞ ነበር። ዓምዱንም በራሱ ስም ሰይሞት ነበር፤ እስከ ዛሬም ድረስ የአቢሴሎም ሐውልት በመባል ይጠራል።
19 የሳዶቅ ልጅ አኪማዓስም+ “ይሖዋ ንጉሡን ከጠላቶቹ እጅ ነፃ በማውጣት ስለፈረደለት+ እባክህ እየሮጥኩ ሄጄ ወሬውን ልንገረው” አለ። 20 ኢዮዓብ ግን “ዛሬ ወሬውን የምትነግረው አንተ አይደለህም። ወሬውን ሌላ ቀን ትነግረዋለህ፤ የንጉሡ ልጅ ስለ ሞተ ዛሬ ወሬውን መናገር የለብህም” አለው።+ 21 ከዚያም ኢዮዓብ አንድ ኩሻዊ+ ጠርቶ “ሂድ፣ ያየኸውን ነገር ለንጉሡ ንገረው” አለው። በዚህ ጊዜ ኩሻዊው ለኢዮዓብ ከሰገደ በኋላ እየሮጠ ሄደ። 22 የሳዶቅ ልጅ አኪማዓስም እንደገና ኢዮዓብን “እባክህ፣ የመጣው ይምጣ እኔም ኩሻዊውን ተከትዬ ልሩጥ” አለው። ሆኖም ኢዮዓብ “ልጄ ሆይ፣ የምትናገረው ነገር ሳይኖር ለምን ትሮጣለህ?” አለው። 23 እሱ ግን አሁንም “ምንም ይሁን ምን፣ እባክህ ልሩጥ” አለው። ስለዚህ ኢዮዓብ “በቃ ሩጥ!” አለው። አኪማዓስም የዮርዳኖስን አውራጃ* አቋርጦ የሚያልፈውን መንገድ ይዞ መሮጥ ጀመረ፤ በኋላም ኩሻዊውን አልፎት ሄደ።
24 በዚህ ጊዜ ዳዊት በሁለቱ የከተማዋ በሮች+ መካከል ተቀምጦ ነበር፤ ጠባቂውም+ ከቅጥሩ ጋር ተያይዞ ወደተሠራው የበሩ ሰገነት ወጣ። ቀና ብሎም ሲመለከት ብቻውን የሚሮጥ አንድ ሰው አየ። 25 ጠባቂውም ተጣርቶ ይህንኑ ለንጉሡ ነገረው፤ ንጉሡም “ብቻውን ከሆነ ወሬ ይዞ የመጣ መሆን አለበት” አለ። ሰውየውም እየቀረበ ሲመጣ 26 ጠባቂው ሌላ ሰው ሲሮጥ ተመለከተ። በመሆኑም የበር ጠባቂውን ተጣርቶ “ይኸው ሌላም ሰው ብቻውን እየሮጠ በመምጣት ላይ ነው!” አለው። ንጉሡም “ይህም ሰው ቢሆን ወሬ ይዞ የመጣ መሆን አለበት” አለ። 27 ጠባቂውም “የመጀመሪያው ሰው አሯሯጥ የሳዶቅን ልጅ የአኪማዓስን+ አሯሯጥ ይመስላል” አለ፤ በመሆኑም ንጉሡ “እሱማ ጥሩ ሰው ነው፤ ምሥራች ሳይዝ አይመጣም” አለው። 28 አኪማዓስም ንጉሡን ተጣርቶ “ሁሉም ነገር ሰላም ነው!” አለው። ከዚያም በግንባሩ መሬት ላይ ተደፍቶ ለንጉሡ ሰገደ። ቀጥሎም “በጌታዬ በንጉሡ ላይ ያመፁትን* ሰዎች አሳልፎ የሰጠህ አምላክህ ይሖዋ ይወደስ!” አለ።+
29 ሆኖም ንጉሡ “ለመሆኑ ወጣቱ አቢሴሎም ደህና ነው?” አለው። በዚህ ጊዜ አኪማዓስ “ኢዮዓብ የንጉሡን አገልጋይና እኔን አገልጋይህን በላከ ጊዜ ከፍተኛ ትርምስ አይቻለሁ፤ ምን እንደሆነ ግን አላወቅኩም” አለ።+ 30 ንጉሡም “እሺ፣ እልፍ በልና እዚያ ቁም” አለው። እሱም እልፍ ብሎ ቆመ።
31 ከዚያም ኩሻዊው ደረሰ፤+ እሱም “ጌታዬ ንጉሡ፣ ያመጣሁትን ይህን ወሬ ይስማ፦ ዛሬ ይሖዋ፣ በአንተ ላይ ካመፁብህ ሰዎች ሁሉ እጅ ነፃ በማውጣት ፈርዶልሃል” አለ።+ 32 ይሁንና ንጉሡ ኩሻዊውን “ለመሆኑ ወጣቱ አቢሴሎም ደህና ነው?” አለው። በዚህ ጊዜ ኩሻዊው “የጌታዬ የንጉሡ ጠላቶች ሁሉና በአንተ ላይ ጉዳት ለማድረስ ያመፁብህ ሁሉ እንደዚያ ወጣት ይሁኑ!” አለ።+
33 ይህም ንጉሡን ረበሸው፤ በውጭው በር ሰገነት ላይ ወዳለው ክፍልም ወጥቶ አለቀሰ፤ ወዲያ ወዲህ እያለም “ልጄ አቢሴሎም፣ ልጄ፣ ልጄ አቢሴሎም! ምነው በአንተ ፋንታ እኔ በሞትኩ፤ ልጄ አቢሴሎም፣ ልጄ!” ይል ነበር።+
19 ለኢዮዓብ “ንጉሡ ለአቢሴሎም እያለቀሰና እያዘነ ነው” ተብሎ ተነገረው።+ 2 ሕዝቡ ሁሉ ንጉሡ በልጁ ምክንያት ማዘኑን ሲሰማ ያን ዕለት የተገኘው ድል* ወደ ሐዘን ተለወጠ። 3 በዚያን ቀን ሕዝቡ ከጦርነት በመሸሹ ምክንያት በኀፍረት እንደተሸማቀቀ ሕዝብ ድምፁን አጥፍቶ ወደ ከተማዋ ገባ።+ 4 ንጉሡም ፊቱን ተከናንቦ “ልጄ አቢሴሎም! ልጄ አቢሴሎም፣ ልጄ!” እያለ ድምፁን ከፍ አድርጎ ያለቅስ ነበር።+
5 ከዚያም ኢዮዓብ ቤቱ ውስጥ ወደነበረው ወደ ንጉሡ ገብቶ እንዲህ አለው፦ “በዛሬው ዕለት የአንተን፣ የወንዶች ልጆችህን፣+ የሴቶች ልጆችህን፣+ የሚስቶችህንና የቁባቶችህን+ ሕይወት* የታደጉትን አገልጋዮችህን ሁሉ አሳፍረሃቸዋል። 6 አንተ የሚጠሉህን ትወዳለህ፣ የሚወዱህን ደግሞ ትጠላለህ፤ የጦር አለቆችህም ሆኑ አገልጋዮችህ ለአንተ ምንህም እንዳይደሉ ይኸው ዛሬ በግልጽ አሳይተሃል፤ በዛሬው ቀን አቢሴሎም ብቻ በሕይወት ተርፎ እኛ ሁላችን አልቀን ቢሆን ኖሮ ደስ ይልህ እንደነበር እርግጠኛ ነኝ። 7 በል አሁን ተነስተህ ውጣና አገልጋዮችህን አበረታታቸው፤* ባትወጣ ግን በይሖዋ እምላለሁ፣ ዛሬ አንድም ሰው አብሮህ አያድርም። ይህ ደግሞ ከልጅነትህ አንስቶ እስካሁን ድረስ ከደረሰብህ ጉዳት ሁሉ የከፋ ይሆናል።” 8 በመሆኑም ንጉሡ ተነስቶ በከተማዋ በር አጠገብ ተቀመጠ፤ ለሕዝቡም ሁሉ “ንጉሡ በሩ አጠገብ ተቀምጧል” ተብሎ ተነገረው። ከዚያም ሕዝቡ ሁሉ ወደ ንጉሡ መጣ።
እስራኤላውያን ግን ወደየቤታቸው ሸሽተው ነበር።+ 9 በመላው የእስራኤል ነገዶች መካከል ያለው ሕዝብ እንዲህ በማለት ይከራከር ነበር፦ “ንጉሡ ከጠላቶቻችን አዳነን፤+ ከፍልስጤማውያንም ታደገን፤ አሁን ግን በአቢሴሎም የተነሳ ከአገሩ ሸሽቶ ሄዷል።+ 10 በላያችን እንዲነግሥ የቀባነው+ አቢሴሎም እንደሆነ በውጊያው ሞቷል።+ ታዲያ ንጉሡን ለመመለስ አንድ ነገር የማታደርጉት ለምንድን ነው?”
11 ንጉሥ ዳዊት ለካህናቱ ለሳዶቅና+ ለአብያታር+ እንዲህ የሚል መልእክት ላከባቸው፦ “የይሁዳን ሽማግሌዎች+ እንዲህ በሏቸው፦ ‘እስራኤላውያን በሙሉ የተናገሩት ነገር በቤቱ ውስጥ ወዳለው ወደ ንጉሡ ደርሶ ሳለ እናንተ ንጉሡን ወደ ቤቱ ለመመለስ እንዴት የመጨረሻዎቹ ሰዎች ትሆናላችሁ? 12 እናንተ ወንድሞቼ ናችሁ፤ የአጥንቴ ፍላጭና የሥጋዬ ቁራጭ* ናችሁ። ታዲያ ንጉሡን ለመመለስ እንዴት የመጨረሻዎቹ ሰዎች ትሆናላችሁ?’ 13 አሜሳይንም+ ‘አንተ የአጥንቴ ፍላጭና የሥጋዬ ቁራጭ አይደለህም? ከአሁን ጀምሮ በኢዮዓብ+ ምትክ የሠራዊቴ አለቃ ባትሆን አምላክ እንዲህ ያድርግብኝ፤ ከዚህ የባሰም ያምጣብኝ’ በሉት።”
14 በመሆኑም የይሁዳን ሰዎች ሁሉ ልብ ልክ እንደ አንድ ሰው ልብ ማረከ፤* እነሱም ወደ ንጉሡ “አንተም ሆንክ አገልጋዮችህ በሙሉ ተመለሱ” የሚል መልእክት ላኩበት።
15 ንጉሡም ለመመለስ ጉዞ ጀመረ፤ እስከ ዮርዳኖስም ድረስ መጣ፤ የይሁዳም ሰዎች ንጉሡን ለመቀበልና እስከ ዮርዳኖስ ማዶ ድረስ ለመሸኘት ወደ ጊልጋል+ መጡ። 16 የባሁሪም ሰው የሆነው ቢንያማዊው የጌራ ልጅ ሺምአይ+ ንጉሥ ዳዊትን ለማግኘት ከይሁዳ ሰዎች ጋር በፍጥነት ወረደ፤ 17 ከእሱም ጋር ከቢንያም የመጡ 1,000 ሰዎች ነበሩ። በተጨማሪም የሳኦል ቤት አገልጋይ የሆነው ሲባ+ ከ15 ወንዶች ልጆቹና ከ20 አገልጋዮቹ ጋር በመሆን ከንጉሡ ቀድሞ በፍጥነት ወደ ዮርዳኖስ ወረደ። 18 እሱም* የንጉሡን ቤተሰብ ለማሻገርና ንጉሡ ደስ የሚያሰኘውን ለማድረግ መልካውን* ተሻገረ። የጌራ ልጅ ሺምአይ ግን ንጉሡ ዮርዳኖስን ሊሻገር ሲል በፊቱ ተደፋ። 19 ንጉሡንም እንዲህ አለው፦ “ጌታዬ በደሌን አይቁጠርብኝ፤ ጌታዬ ንጉሡ ከኢየሩሳሌም በወጣበት ቀን አገልጋይህ የፈጸመውን በደል አያስብ።+ ንጉሡም በልቡ አይያዘው፤ 20 ምክንያቱም እኔ አገልጋይህ ኃጢአት እንደሠራሁ በሚገባ አውቃለሁ፤ በመሆኑም ዛሬ ጌታዬን ንጉሡን ወርጄ ለመቀበል ከመላው የዮሴፍ ቤት ቀድሜ መጥቻለሁ።”
21 በዚህ ጊዜ የጽሩያ+ ልጅ አቢሳ+ “ሺምአይ ይሖዋ የቀባውን በመራገም ለፈጸመው በደል ሞት አይገባውም?” አለ።+ 22 ዳዊት ግን እንዲህ አለ፦ “እናንተ የጽሩያ ልጆች፣+ ይህ ጉዳይ ምን ይመለከታችኋልና ነው ዛሬ እኔን ተቃውማችሁ የተነሳችሁት? በዛሬው ዕለት እስራኤል ውስጥ ሰው መገደል ይገባዋል? በእስራኤል ላይ ንጉሥ መሆኔን ያወቅኩት ዛሬ አይደለም?” 23 ንጉሡ አክሎ ሺምአይን “አይዞህ፣ አትሞትም” አለው። ከዚያም ንጉሡ ማለለት።+
24 የሳኦል የልጅ ልጅ የሆነው ሜፊቦስቴም+ ንጉሡን ለመቀበል ወረደ። እሱም ንጉሡ ከሄደበት ቀን አንስቶ በሰላም እስከተመለሰበት ዕለት ድረስ ለእግሩ ተገቢውን እንክብካቤ አላደረገም፣ ጢሙን አልተከረከመም፤ ልብሱንም አላጠበም። 25 እሱም ንጉሡን ለማግኘት ወደ ኢየሩሳሌም* በመጣ ጊዜ ንጉሡ “ሜፊቦስቴ፣ አብረኸኝ ያልሄድከው ለምንድን ነው?” አለው። 26 በዚህ ጊዜ እንዲህ አለው፦ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ አገልጋዬ+ አታለለኝ። እኔ አገልጋይህ ሽባ+ ስለሆንኩ ‘በአህያዬ ላይ ተቀምጬ ከንጉሡ ጋር እንድሄድ አህያዬን ጫኑልኝ’ ብዬ ነበር። 27 ሆኖም እሱ በጌታዬ በንጉሡ ፊት የእኔን የአገልጋይህን ስም አጥፍቷል።+ ይሁን እንጂ ጌታዬ ንጉሡ እንደ እውነተኛው አምላክ መልአክ ስለሆነ መልካም መስሎ የታየህን አድርግ። 28 የአባቴ ቤት በሙሉ በንጉሡ በጌታዬ ሞት ሊፈረድበት ይገባ ነበር፤ አንተ ግን አገልጋይህን ከማዕድህ ከሚበሉት አንዱ አደረግከው።+ ታዲያ ንጉሡን ተጨማሪ ነገር የመጠየቅ ምን መብት አለኝ?”
29 ሆኖም ንጉሡ “ለምን ዝም ብለህ ነገር ታስረዝማለህ? እርሻውን አንተና ሲባ እንድትካፈሉ ወስኛለሁ” አለው።+ 30 በዚህ ጊዜ ሜፊቦስቴ ንጉሡን “ጌታዬ ንጉሡ ወደ ቤቱ እንኳን በሰላም ተመለሰ እንጂ እሱ ሁሉንም ይውሰደው” አለው።
31 ከዚያም ጊልያዳዊው ቤርዜሊ+ ንጉሡን ወደ ዮርዳኖስ ለመሸኘት ከሮገሊም ወደ ዮርዳኖስ ወረደ። 32 ቤርዜሊ የ80 ዓመት አረጋዊ ነበር፤ እጅግ ባለጸጋም ስለነበር ንጉሡ በማሃናይም ይኖር በነበረበት ጊዜ ቀለብ አምጥቶለት ነበር።+ 33 በመሆኑም ንጉሡ ቤርዜሊን “አብረኸኝ ተሻገር፤ እኔም በኢየሩሳሌም ቀለብ እሰጥሃለሁ” አለው።+ 34 ቤርዜሊ ግን ንጉሡን እንዲህ አለው፦ “ከንጉሡ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም የምወጣው ለየትኛው ዕድሜዬ ብዬ ነው? 35 አሁን የ80 ዓመት ሰው ነኝ።+ ታዲያ መልካምና መጥፎውን መለየት እችላለሁ? እኔ አገልጋይህ የምበላውንና የምጠጣውን ማጣጣም እችላለሁ? ደግሞስ የወንድና የሴት ዘፋኞችን ድምፅ መስማት እችላለሁ?+ ታዲያ አገልጋይህ ለጌታዬ ለንጉሡ ለምን ተጨማሪ ሸክም ይሆናል? 36 አገልጋይህ ንጉሡን እስከ ዮርዳኖስ ድረስ መሸኘት ከቻለ ይበቃዋል። ታዲያ ንጉሡ ይህን ወሮታ የሚመልስልኝ ለምንድን ነው? 37 እባክህ እኔ አገልጋይህ ልመለስና በገዛ ከተማዬ በአባቴና በእናቴ መቃብር አጠገብ ልሙት።+ ሆኖም አገልጋይህ ኪምሃም+ ይኸውልህ። እሱ ከጌታዬ ከንጉሡ ጋር ይሻገር፤ አንተም መልካም መስሎ የታየህን አድርግለት።”
38 በመሆኑም ንጉሡ “እንግዲያው ኪምሃም አብሮኝ ይሻገራል፤ እኔም መልካም መስሎ የታየህን አደርግለታለሁ፤ ለአንተም የምትጠይቀኝን ማንኛውንም ነገር አደርግልሃለሁ” አለው። 39 በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ ዮርዳኖስን መሻገር ጀመረ፤ ንጉሡም ሊሻገር ሲል ቤርዜሊን ስሞ ባረከው፤+ ቤርዜሊም ወደ ቤቱ ተመለሰ። 40 ንጉሡ ወደ ጊልጋል+ ሲሻገር ኪምሃምም አብሮት ተሻገረ። እንዲሁም የይሁዳ ሰዎች በሙሉና ግማሹ የእስራኤል ሕዝብ ንጉሡን አሻገሩት።+
41 ከዚያም የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ወደ ንጉሡ ቀርበው “ወንድሞቻችን የሆኑት የይሁዳ ሰዎች ሹልክ ብለው ይዘውህ በመሄድ ንጉሡንና ቤተሰቡን ከዳዊት ሰዎች ሁሉ ጋር ዮርዳኖስን ያሻገሩት ለምንድን ነው?” አሉት።+ 42 በዚህ ጊዜ የይሁዳ ሰዎች ሁሉ የእስራኤልን ሰዎች “ይህን ያደረግነው ንጉሡ ዘመዳችን ስለሆነ ነው።+ ታዲያ ይህ እናንተን ያስቆጣችሁ ለምንድን ነው? በንጉሡ ወጪ የበላነው ነገር አለ? ወይስ ስጦታ መጥቶልን ያውቃል?” አሏቸው።
43 ሆኖም የእስራኤል ሰዎች የይሁዳን ሰዎች እንዲህ አሏቸው፦ “እኛ እኮ ከንጉሡ አሥር እጅ ድርሻ አለን፤ ስለሆነም በዳዊት ላይ ከእናንተ የበለጠ መብት ያለን እኛ ነን። ታዲያ የናቃችሁን ለምንድን ነው? ንጉሣችንን ለመመለስ ቅድሚያ ሊሰጠን አይገባም ነበር?” ይሁንና ከእስራኤል ሰዎች ቃል ይልቅ የይሁዳ ሰዎች ቃል አሸነፈ።*
20 በዚህ ጊዜ የቢንያማዊው የቢክሪ ልጅ የሆነ ሳባ+ የሚባል አንድ አስቸጋሪ ሰው ነበር። እሱም ቀንደ መለከት በመንፋት+ “እኛ ከዳዊት ጋር ምንም ድርሻ የለንም፤ ከእሴይም ልጅ ጋር ምንም ውርሻ የለንም።+ እስራኤል ሆይ፣ እያንዳንድህ ወደ አማልክትህ* ተመለስ!” አለ።+ 2 ስለዚህ የእስራኤል ሰዎች በሙሉ ዳዊትን መከተል ትተው የቢክሪን ልጅ ሳባን መከተል ጀመሩ፤+ የይሁዳ ሰዎች ግን ከዮርዳኖስ አንስቶ እስከ ኢየሩሳሌም ድረስ ከንጉሣቸው አልተለዩም።+
3 ዳዊት በኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ቤቱ*+ ሲመጣ ንጉሡ ቤቱን እንዲጠብቁ ትቷቸው ሄዶ የነበሩትን አሥሩን ቁባቶቹን+ ወስዶ በዘብ በሚጠበቅ አንድ ቤት ውስጥ አስገባቸው። በየጊዜው ቀለብ ይሰጣቸው የነበረ ቢሆንም ከእነሱ ጋር ምንም ግንኙነት አልፈጸመም።+ እነሱም ባላቸው በሕይወት ያለ ቢሆንም እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ እንደ መበለት ሆነው ኖሩ።
4 ንጉሡም አሜሳይን+ “የይሁዳን ሰዎች በሦስት ቀን ውስጥ ጠርተህ ወደ እኔ ሰብስብልኝ፤ አንተም እዚህ መገኘት ይኖርብሃል” አለው። 5 ስለዚህ አሜሳይ የይሁዳን ሕዝብ ለመሰብሰብ ሄደ፤ ሆኖም ንጉሡ ከቀጠረለት ጊዜ ዘገየ። 6 ከዚያም ዳዊት አቢሳን+ “ከአቢሴሎም ይልቅ የቢክሪ ልጅ ሳባ+ የከፋ ጉዳት ሊያደርስብን ይችላል።+ ስለሆነም የተመሸጉ ከተሞች አግኝቶ እንዳያመልጠን የጌታህን አገልጋዮች ይዘህ አሳደው” አለው። 7 በመሆኑም የኢዮዓብ+ ሰዎች፣ ከሪታውያን፣ ጴሌታውያን+ እና ኃያላን የሆኑት ሰዎች በሙሉ ተከትለውት ሄዱ፤ የቢክሪን ልጅ ሳባን ለማሳደድም ከኢየሩሳሌም ወጡ። 8 እነሱም በገባኦን+ በሚገኘው ትልቅ ድንጋይ አጠገብ ሲደርሱ አሜሳይ+ ሊገናኛቸው መጣ። ኢዮዓብ የጦር ልብሱን ለብሶ፣ ወገቡም ላይ ሰይፉን ከነሰገባው ታጥቆ ነበር። ወደ ፊት ራመድ ሲልም ሰይፉ ከሰገባው ወደቀ።
9 ኢዮዓብም አሜሳይን “ወንድሜ ሆይ፣ ደህና ነህ?” አለው። ከዚያም ኢዮዓብ የሚስመው አስመስሎ በቀኝ እጁ የአሜሳይን ጢም ያዘ። 10 አሜሳይ፣ በኢዮዓብ እጅ ከነበረው ሰይፍ ራሱን አልጠበቀም፤ ኢዮዓብም በሰይፉ ሆዱ ላይ ወጋው፤+ አንጀቱም መሬት ላይ ተዘረገፈ። ዳግመኛ መውጋት እንኳ ሳያስፈልገው አንዴ ብቻ ወግቶ ገደለው። ከዚያም ኢዮዓብና ወንድሙ አቢሳ የቢክሪን ልጅ ሳባን ማሳደዳቸውን ቀጠሉ።
11 ከኢዮዓብ ወጣቶች መካከል አንዱ አሜሳይ አጠገብ ቆሞ “ከኢዮዓብ ጎን የሚቆምና የዳዊት የሆነ ማንኛውም ሰው ኢዮዓብን ይከተል!” ይል ነበር። 12 በዚህ ጊዜ አሜሳይ መንገዱ መሃል ላይ በደም ተጨማልቆ ይንፈራገጥ ነበር። ሰውየውም ሰዉ ሁሉ እዚያ ሲደርስ እንደሚቆም ሲያይ አሜሳይን ከመንገዱ ላይ ወደ ሜዳው ገለል አደረገው። ይሁንና ሰዉ ሁሉ አሁንም እሱ ጋ ሲደርስ እንደሚቆም ሲያይ ልብስ ጣል አደረገበት። 13 አሜሳይን ከመንገዱ ላይ ካነሳው በኋላ ሰዉ ሁሉ የቢክሪን ልጅ ሳባን+ ለማሳደድ ኢዮዓብን ተከትሎ ሄደ።
14 ሳባም የእስራኤልን ነገዶች በሙሉ አልፎ ወደ ቤትማዓካዋ አቤል+ ሄደ። ቢክሪያውያንም ተሰብስበው ተከተሉት።
15 ኢዮዓብና ሰዎቹም* መጥተው ሳባን በቤትማዓካዋ አቤል እንዳለ ከበቡት፤ በከተማዋም ዙሪያ የአፈር ቁልል ደለደሉ፤ ከተማዋም በአፈር ቁልሉ መሃል ነበረች። ከኢዮዓብም ጋር የነበሩት ሰዎች ሁሉ የከተማዋን ቅጥር ለመጣል ከሥሩ ይሰረስሩ ነበር። 16 ከከተማዋም ውስጥ አንዲት ብልህ ሴት ድምፅዋን ከፍ አድርጋ “ስሙ፣ እናንተ ሰዎች ስሙ! እባካችሁ ኢዮዓብን ‘ወደዚህ ቅረብና ላነጋግርህ’ በሉት” አለች። 17 እሱም ወደ እሷ ቀረበ፤ ከዚያም ሴትየዋ “ኢዮዓብ አንተ ነህ?” አለችው፤ እሱም “አዎ፣ እኔ ነኝ” አላት። በዚህ ጊዜ “አገልጋይህ የምትልህን ስማ” አለችው። እሱም መልሶ “እሺ እየሰማሁ ነው” አላት። 18 እሷም እንዲህ አለች፦ “ቀደም ባሉት ጊዜያት ሰዎች ‘በአቤል ከተማ ይጠይቁ፤ ጉዳያቸውም እልባት ያገኛል’ ይሉ ነበር። 19 እኔ የእስራኤልን ሰላማዊና ታማኝ ሰዎች እወክላለሁ። አንተ በእስራኤል ውስጥ እንደ እናት የሆነችን ከተማ ልትደመስስ ትፈልጋለህ። የይሖዋን ውርሻ የምታጠፋው* ለምንድን ነው?”+ 20 ኢዮዓብም መልሶ እንዲህ አላት፦ “ከተማዋን ማጥፋትም ሆነ መደምሰስ ፈጽሞ የማላስበው ነገር ነው። 21 ነገሩ እንደዚያ አይደለም። ሆኖም ከኤፍሬም ተራራማ አካባቢ+ የመጣውና የቢክሪ ልጅ የሆነው ሳባ+ በንጉሥ ዳዊት ላይ ዓምፆአል።* ይህን ሰው አሳልፋችሁ ከሰጣችሁኝ ከተማዋን ትቼ እሄዳለሁ።” ከዚያም ሴትየዋ ኢዮዓብን “እንግዲህ የሰውየው ራስ በቅጥሩ ላይ ይወረወርልሃል!” አለችው።
22 ብልህ የሆነችው ሴትም ወዲያውኑ ወደ ሕዝቡ ሄደች፤ እነሱም የቢክሪን ልጅ የሳባን ራስ ቆርጠው ለኢዮዓብ ወረወሩለት። በዚህ ጊዜ ኢዮዓብ ቀንደ መለከት ነፋ፤ እነሱም ከተማዋን ትተው በየአቅጣጫው ተበታተኑ፤ እያንዳንዱም ሰው ወደቤቱ ሄደ፤+ ኢዮዓብም ወደ ኢየሩሳሌም ወደ ንጉሡ ተመለሰ።
23 ኢዮዓብ የመላው የእስራኤል ሠራዊት አዛዥ ነበር፤+ የዮዳሄ+ ልጅ በናያህ+ ደግሞ በከሪታውያንና በጴሌታውያን+ ላይ የበላይ ነበር። 24 አዶራም+ የግዳጅ ሥራ እንዲሠሩ በተመለመሉት ላይ የበላይ ነበር፤ የአሂሉድ ልጅ ኢዮሳፍጥ+ ደግሞ ታሪክ ጸሐፊ ነበር። 25 ሻዌ ጸሐፊ ነበር፤ ሳዶቅና+ አብያታር+ ደግሞ ካህናት ነበሩ። 26 በተጨማሪም ያኢራዊው ኢራ ዋና ኃላፊ* ሆኖ ዳዊትን ያገለግል ነበር።
21 በዳዊት ዘመን ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ረሃብ ሆነ፤+ ስለዚህ ዳዊት ይሖዋን ምክር ጠየቀ፤ ይሖዋም “ሳኦል ገባኦናውያንን ስለገደለ እሱም ሆነ ቤቱ የደም ዕዳ አለባቸው” አለ።+ 2 በመሆኑም ንጉሡ ገባኦናውያንን+ ጠርቶ አነጋገራቸው። (እርግጥ ገባኦናውያን ከአሞራውያን+ የተረፉ ናቸው እንጂ እስራኤላውያን አልነበሩም፤ እስራኤላውያንም እንደማያጠፏቸው ምለውላቸው ነበር፤+ ይሁንና ሳኦል ለእስራኤልና ለይሁዳ ሕዝብ ባለው ቅንዓት ተነሳስቶ ሊያጠፋቸው ፈልጎ ነበር።) 3 ዳዊትም ገባኦናውያንን “የይሖዋን ርስት እንድትባርኩ ምን ላድርግላችሁ? ማስተሰረይስ የምችለው እንዴት ነው?” አላቸው። 4 ገባኦናውያንም “ከሳኦልና ከእሱ ቤት ጋር በተያያዘ የተፈጠረው ችግር በብርና በወርቅ የሚፈታ አይደለም፤+ ደግሞም በእስራኤል ውስጥ ማንንም ሰው የመግደል መብት የለንም” አሉት። በዚህ ጊዜ ዳዊት “ያላችሁትን ሁሉ አደርግላችኋለሁ” አላቸው። 5 እነሱም ንጉሡን እንዲህ አሉት፦ “ለጥፋት ከዳረገንና በየትኛውም የእስራኤል ግዛት ውስጥ እንዳንኖር እኛን ለመደምሰስ ሴራ ከጠነሰሰብን ሰው+ 6 ወንዶች ልጆች መካከል ሰባቱ ይሰጡን። እኛም በይሖዋ የተመረጠው የሳኦል+ አገር በሆነችው በጊብዓ+ በድናቸውን በይሖዋ ፊት እንሰቅላለን።”*+ ከዚያም ንጉሡ “እሺ፣ እሰጣችኋለሁ” አላቸው።
7 ሆኖም ንጉሡ እሱና የሳኦል ልጅ ዮናታን በይሖዋ ፊት በተማማሉት መሐላ የተነሳ የሳኦል ልጅ ለሆነው ለዮናታን+ ልጅ ለሜፊቦስቴ+ ራራለት። 8 በመሆኑም ንጉሡ የአያ ልጅ ሪጽፋ+ ለሳኦል የወለደችለትን ሁለት ወንዶች ልጆች ማለትም አርሞኒንና ሜፊቦስቴን እንዲሁም የሳኦል ልጅ ሜልኮል*+ የመሆላታዊው የቤርዜሊ ልጅ ለሆነው ለአድሪዔል+ የወለደችለትን አምስት ወንዶች ልጆች ወሰደ። 9 ከዚያም ለገባኦናውያኑ አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነሱም በድናቸውን በተራራው ላይ በይሖዋ ፊት ሰቀሉ።+ ሰባቱም አንድ ላይ ሞቱ፤ የተገደሉትም አዝመራ በሚሰበሰብባቸው የመጀመሪያዎቹ ቀናት ይኸውም የገብስ አዝመራ መሰብሰብ በሚጀምርበት ጊዜ ነበር። 10 ከዚያም የአያ ልጅ ሪጽፋ+ ከመከር ወቅት መጀመሪያ አንስቶ በበድኖቹ ላይ ከሰማይ ዝናብ እስከሚወርድበት ጊዜ ድረስ ማቅ ወስዳ በዓለቱ ላይ አነጠፈች፤ ቀን የሰማይ አሞሮች እንዲያርፉባቸው፣ ሌሊት ደግሞ የዱር አራዊት እንዲጠጓቸው አልፈቀደችም።
11 በኋላም የሳኦል ቁባት የሆነችው የአያ ልጅ ሪጽፋ ያደረገችው ነገር ለዳዊት ተነገረው። 12 ስለዚህ ዳዊት ሄዶ የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን አፅም ከኢያቢስጊልያድ+ መሪዎች* ላይ ወሰደ፤ እነዚህ ሰዎች አፅሙን ፍልስጤማውያን ሳኦልን በጊልቦአ+ በገደሉበት ቀን እሱንና ዮናታንን ከሰቀሉበት ከቤትሻን አደባባይ ሰርቀው ወስደው ነበር። 13 እሱም የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን አፅም ከዚያ አመጣ፤ በተጨማሪም የተገደሉትን* ሰዎች አፅም ሰበሰቡ።+ 14 ከዚያም የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን አፅም በቢንያም ምድር በጸላ+ በሚገኘው በሳኦል አባት በቂስ+ የመቃብር ስፍራ ቀበሩት። ንጉሡ ያዘዘውን ነገር ሁሉ ከፈጸሙም በኋላ አምላክ ስለ ምድሪቱ ያቀረቡትን ልመና ሰማ።+
15 በፍልስጤማውያንና በእስራኤላውያን መካከል እንደገና ጦርነት ተነሳ።+ በመሆኑም ዳዊትና አገልጋዮቹ ወርደው ፍልስጤማውያንን ወጉ፤ በዚህ ጊዜ ዳዊት ዛለ። 16 ከረፋይም+ ዘር የሆነው እንዲሁም 300 ሰቅል*+ የሚመዝን የመዳብ ጦርና አዲስ ሰይፍ የታጠቀው ይሽቢብኖብ ዳዊትን ለመግደል አሰበ። 17 የጽሩያ ልጅ አቢሳም+ ወዲያውኑ ደረሰለት፤+ ፍልስጤማዊውንም መትቶ ገደለው። በዚያን ጊዜ የዳዊት ሰዎች “ከአሁን በኋላ ከእኛ ጋር ወደ ውጊያ መውጣት የለብህም!+ የእስራኤልን መብራት አታጥፋ!”+ በማለት ማሉለት።
18 ከዚህም በኋላ እንደገና ከፍልስጤማውያን ጋር በጎብ ጦርነት ተከፈተ።+ በዚህ ጊዜ ሁሻዊው ሲበካይ+ የረፋይም+ ዘር የሆነውን ሳፍን ገደለው።
19 ዳግመኛም ከፍልስጤማውያን ጋር በጎብ ጦርነት ተቀሰቀሰ፤+ የቤተልሔማዊው የያአሬዖርጊም ልጅ ኤልሃናን የሸማኔ መጠቅለያ የሚመስል ዘንግ ያለው ጦር ይዞ የነበረውን ጌታዊውን ጎልያድን ገደለው።+
20 እንደገናም በጌት ጦርነት ተቀሰቀሰ፤ በዚያም በእጆቹ ላይ ስድስት ስድስት ጣቶች በእግሮቹም ላይ ስድስት ስድስት ጣቶች፣ በድምሩ 24 ጣቶች ያሉት በጣም ግዙፍ የሆነ ሰው ነበር፤ እሱም የረፋይም ዘር ነበር።+ 21 ይህ ሰው እስራኤልን ይገዳደር+ ስለነበር የዳዊት ወንድም የሺምአይ+ ልጅ ዮናታን ገደለው።
22 እነዚህ አራቱ በጌት የሚኖሩ የረፋይም ዘሮች ነበሩ፤ እነሱም በዳዊት እጅና በአገልጋዮቹ እጅ ወደቁ።+
22 ዳዊት፣ ይሖዋ ከጠላቶቹ ሁሉ እጅና ከሳኦል እጅ+ በታደገው+ ቀን የዚህን መዝሙር ቃል ለይሖዋ ዘመረ።+ 2 እንዲህም አለ፦
4 ውዳሴ የሚገባውን ይሖዋን እጠራለሁ፤
ከጠላቶቼም እድናለሁ።
7 በጭንቅ ውስጥ ሳለሁ ይሖዋን ጠራሁት፤+
አምላኬን ደጋግሜ ጠራሁት።
እሱም በመቅደሱ ሆኖ ድምፄን ሰማ፣
እርዳታ ለማግኘት የማሰማውም ጩኸት ወደ ጆሮው ደረሰ።+
11 በኪሩብ ላይ ተቀምጦ+ እየበረረ መጣ።
12 ከዚያም ጨለማን በዙሪያው እንደ መጠለያ አደረገ፣+
ጨለማውም ጥቁር ውኃና ጥቅጥቅ ያለ ደመና ነበረው።
13 በፊቱ ካለው ብርሃን ፍም ፈለቀ።
17 ከላይ ሆኖ እጁን ሰደደ፤
ከጥልቅ ውኃ ውስጥም አወጣኝ።+
18 ከብርቱ ጠላቴ አዳነኝ፤+
ከእኔ ይበልጥ ብርቱዎች ከሆኑት፣ ከሚጠሉኝ ሰዎች ታደገኝ።
19 ችግር ላይ በወደቅኩበት ቀን ተነሱብኝ፤+
ይሖዋ ግን ድጋፍ ሆነልኝ።
22 የይሖዋን መንገድ ጠብቄአለሁና፤
አምላኬን በመተው ክፉ ድርጊት አልፈጸምኩም።
30 በአንተ እርዳታ ወራሪውን ቡድን መጋፈጥ እችላለሁ፤
በአምላክ ኃይል ቅጥር መውጣት እችላለሁ።+
እሱ መጠጊያ ለሚያደርጉት ሁሉ ጋሻቸው ነው።+
32 ደግሞስ ከይሖዋ ሌላ አምላክ ማን ነው?+
ከአምላካችንስ በቀር ዓለት ማን ነው?+
34 እግሮቼን እንደ ዋልያ እግሮች ያደርጋል፤
በከፍታ ቦታዎች ላይ ያቆመኛል።+
35 እጆቼን ለጦርነት ያሠለጥናል፤
ክንዶቼ የመዳብ ደጋን ማጠፍ ይችላሉ።
36 የመዳን ጋሻህን ትሰጠኛለህ፤
ትሕትናህም ታላቅ ያደርገኛል።+
38 ጠላቶቼን አሳድጄ አጠፋቸዋለሁ፤
ተጠራርገው እስኪጠፉ ድረስ ወደ ኋላ አልመለስም።
39 እንዳያንሰራሩም ጠራርጌ አጠፋቸዋለሁ፣ አደቃቸዋለሁ፤+
እግሬ ሥር ይወድቃሉ።
42 እርዳታ ለማግኘት ይጮኻሉ፤ ሆኖም የሚያድናቸው የለም፤
ወደ ይሖዋም ይጮኻሉ፤ እሱ ግን አይመልስላቸውም።+
43 በምድር ላይ እንዳለ አቧራ አደቃቸዋለሁ፤
በመንገድ ላይ እንዳለ ጭቃ እረግጣቸዋለሁ፤ አደቃቸዋለሁ።
44 ስህተት ከሚለቃቅሙት ሕዝቦቼ ታድነኛለህ።+
46 የባዕድ አገር ሰዎች ወኔ ይከዳቸዋል፤*
ከምሽጎቻቸው እየተንቀጠቀጡ ይወጣሉ።
47 ይሖዋ ሕያው ነው! ዓለቴ ይወደስ!+
የመዳኔ ዓለት የሆነው አምላክ ከፍ ከፍ ይበል።+
23 የዳዊት የመጨረሻ ቃላት እነዚህ ናቸው፦+
3 የእስራኤል አምላክ ተናገረ፣
የእስራኤል ዓለት+ እንዲህ አለኝ፦
4 ፀሐይ በምትፈነጥቅበት ጊዜ እንደሚኖረው የማለዳ ብርሃን፣+
ደመና እንደሌለበት ማለዳ ይሆናል።
ሣርን ከምድር እንደሚያበቅል፣+
ዝናብ ካባራ በኋላ ፍንትው ብሎ እንደሚወጣ የፀሐይ ብርሃን ነው።’
5 የእኔስ ቤት በአምላክ ፊት እንዲሁ አይደለም?
እሱ ከእኔ ጋር ዘላለማዊ ቃል ኪዳን ገብቷልና፤+
ቃል ኪዳኑም የተስተካከለና አስተማማኝ ነው።
ምክንያቱም ይህ ለእኔ የተሟላ መዳንና ፍጹም ደስታ ነው፤
ደግሞስ ቤቴ እንዲለመልም የሚያደርገው ለዚህ አይደለም?+
6 የማይረቡ ሰዎች ሁሉ ልክ እንደ እሾህ ቁጥቋጦ ወዲያ ይጣላሉ፤+
በእጅ ሊሰበሰቡ አይችሉምና።
7 የሚነካቸው ሰው
የብረት መሣሪያ መታጠቅና የጦር ዘንግ መያዝ አለበት፤
እነሱም ባሉበት ሙሉ በሙሉ በእሳት መቃጠል አለባቸው።”
8 የዳዊት ኃያላን ተዋጊዎች+ ስም ይህ ነው፦ የሦስቱ መሪ+ የሆነው ታህክሞናዊው ዮሼብባሼቤት። እሱም ጦሩን ሰብቆ በአንድ ጊዜ 800 ሰው ገደለ። 9 ከእሱ ቀጥሎ የአሆሐይ ልጅ የሆነው የዶዶ+ ልጅ አልዓዛር+ ነበር፤ እሱም ፍልስጤማውያንን በተገዳደሩበት ጊዜ ከዳዊት ጋር ከነበሩት ሦስት ኃያላን ተዋጊዎች አንዱ ነው። ፍልስጤማውያንም በዚያ ለጦርነት ተሰብስበው ነበር፤ የእስራኤል ሰዎች ባፈገፈጉ ጊዜ 10 እሱ ካለበት ንቅንቅ ሳይል እጁ እስኪዝልና ከጨበጠው ሰይፍ ላይ መላቀቅ እስኪያቅተው ድረስ ፍልስጤማውያንን ጨፈጨፋቸው።+ በመሆኑም ይሖዋ በዚያ ቀን ታላቅ ድል አጎናጸፈ፤*+ ሕዝቡም ከተገደሉት ሰዎች ላይ ለመግፈፍ ከእሱ ኋላ ተመልሶ መጣ።
11 ከእሱ ቀጥሎ የሃራራዊው የአጌ ልጅ ሻማህ ነበር። ፍልስጤማውያን ሊሃይ በተባለ ስፍራ ምስር በሞላበት አንድ ማሳ ውስጥ ተሰብስበው ነበር፤ ሕዝቡም በፍልስጤማውያን የተነሳ ሸሸ። 12 እሱ ግን በእርሻው መካከል ካለበት ንቅንቅ ሳይል መሬቱ እንዳይያዝ አደረገ፤ ፍልስጤማውያንንም መታቸው፤ በመሆኑም ይሖዋ ታላቅ ድል አጎናጸፈ።*+
13 በመከር ወቅት ከ30ዎቹ መሪዎች መካከል ሦስቱ ዳዊት ወደሚገኝበት ወደ አዱላም+ ዋሻ ወረዱ፤ አንድ የፍልስጤማውያን ቡድንም* በረፋይም ሸለቆ*+ ሰፍሮ ነበር። 14 በዚህ ጊዜ ዳዊት በምሽጉ+ ውስጥ ነበር፤ የፍልስጤማውያንም የጦር ሰፈር በቤተልሔም ነበር። 15 ከዚያም ዳዊት “በቤተልሔም በር አቅራቢያ ካለው የውኃ ማጠራቀሚያ ጉድጓድ የምጠጣው ውኃ ባገኝ ምንኛ ደስ ባለኝ!” በማለት ምኞቱን ገለጸ። 16 በዚህ ጊዜ ሦስቱ ኃያላን ተዋጊዎች ወደ ፍልስጤማውያን ሰፈር ጥሰው በመግባት በቤተልሔም በር አቅራቢያ ከሚገኘው የውኃ ማጠራቀሚያ ጉድጓድ ውኃ ቀድተው ለዳዊት አመጡለት፤ እሱ ግን ለመጠጣት ፈቃደኛ አልሆነም፤ ከዚህ ይልቅ ውኃውን ለይሖዋ አፈሰሰው።+ 17 ከዚያም “ይሖዋ ሆይ፣ ይህን ማድረግ ፈጽሞ የማላስበው ነገር ነው! ሕይወታቸውን* አደጋ ላይ ጥለው የሄዱትን የእነዚህን ሰዎች ደም ልጠጣ ይገባል?”+ አለ። በመሆኑም ውኃውን ለመጠጣት ፈቃደኛ አልሆነም። ሦስቱ ኃያላን ተዋጊዎቹ ያደረጓቸው ነገሮች እነዚህ ነበሩ።
18 የጽሩያ+ ልጅ የኢዮዓብ ወንድም አቢሳ+ የሌሎች ሦስት ሰዎች መሪ ነበር፤ እሱም ጦሩን ሰብቆ 300 ሰው ገደለ፤ እንደ ሦስቱም ሰዎች ዝነኛ ነበር።+ 19 ምንም እንኳ ከሌሎቹ ሦስት ሰዎች ይበልጥ ታዋቂና የእነሱ አለቃ የነበረ ቢሆንም የመጀመሪያዎቹን ሦስት ሰዎች ያህል ማዕረግ አላገኘም።
20 የዮዳሄ ልጅ በናያህ+ በቃብጽኤል+ ብዙ ጀብዱ የፈጸመ ደፋር ሰው* ነበር። እሱም የሞዓቡን የአርዔልን ሁለት ወንዶች ልጆች ገደለ፤ እንዲሁም በረዶ በሚጥልበት ዕለት ወደ አንድ የውኃ ማጠራቀሚያ ጉድጓድ ወርዶ አንበሳ ገደለ።+ 21 በተጨማሪም እጅግ ግዙፍ የሆነ ግብፃዊ ገደለ። ግብፃዊው በእጁ ጦር ይዞ የነበረ ቢሆንም እሱ ግን በትር ብቻ ይዞ በመሄድ ገጠመው፤ የግብፃዊውንም ጦር ከእጁ ቀምቶ በገዛ ጦሩ ገደለው። 22 የዮዳሄ ልጅ በናያህ ያደረጋቸው ነገሮች እነዚህ ነበሩ፤ እሱም እንደ ሦስቱ ኃያላን ተዋጊዎች ዝነኛ ነበር። 23 ከሠላሳዎቹ ይበልጥ ታዋቂ የነበረ ቢሆንም የሦስቱን ሰዎች ያህል ማዕረግ አላገኘም። ይሁን እንጂ ዳዊት የራሱ የክብር ዘብ አለቃ አድርጎ ሾመው።
24 የኢዮዓብ ወንድም አሳሄል+ ከሠላሳዎቹ አንዱ ነበር፤ ከኃያላኑ ሰዎች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦ የቤተልሔሙ+ የዶዶ ልጅ ኤልሃናን፣ 25 ሃሮዳዊው ሻማህ፣ ሃሮዳዊው ኤሊቃ፣ 26 ጳሌጣዊው ሄሌጽ፣+ የተቆአዊው የኢቄሽ ልጅ ኢራ፣+ 27 አናቶታዊው+ አቢዔዜር፣+ ሁሻዊው መቡናይ፣ 28 አሆሐያዊው ጻልሞን፣ ነጦፋዊው ማህራይ፣+ 29 የነጦፋዊው የባአናህ ልጅ ሄሌብ፣ ከቢንያማውያን የጊብዓው የሪባይ ልጅ ኢታይ፣ 30 ጲራቶናዊው በናያህ፣+ የጋአሽ+ ደረቅ ወንዞች* ሰው የሆነው ሂዳይ፣ 31 አርባዊው አቢዓልቦን፣ ባርሁማዊው አዝማዌት፣ 32 ሻአልቢማዊው ኤሊያህባ፣ የያሼን ልጆች፣ ዮናታን፣ 33 ሃራራዊው ሻማህ፣ የሃራራዊው የሻራር ልጅ አሂዓም፣ 34 የማአካታዊው ልጅ፣ የአሃስባይ ልጅ ኤሊፌሌት፣ የጊሎአዊው የአኪጦፌል+ ልጅ ኤሊያም፣ 35 ቀርሜሎሳዊው ሄጽሮ፣ ዓረባዊው ፓአራይ፣ 36 የጾባህዊው የናታን ልጅ ይግዓል፣ ጋዳዊው ባኒ፣ 37 አሞናዊው ጼሌቅ፣ የጽሩያ ልጅ የኢዮዓብ ጋሻ ጃግሬ በኤሮታዊው ናሃራይ፣ 38 ይትራዊው ኢራ፣ ይትራዊው+ ጋሬብ 39 እንዲሁም ሂታዊው ኦርዮ፤+ በአጠቃላይ 37 ነበሩ።
24 ዳዊትንም “ሂድ፣ እስራኤልንና ይሁዳን+ ቁጠር”+ ብሎ በእነሱ ላይ ባነሳሳው* ጊዜ የይሖዋ ቁጣ እንደገና በእስራኤል ላይ ነደደ።+ 2 ንጉሡም ከእሱ ጋር አብሮት የነበረውን የሠራዊቱን አለቃ ኢዮዓብን+ “የሕዝቡን ብዛት እንዳውቅ እስቲ ከዳን እስከ ቤርሳቤህ+ ባሉት በሁሉም የእስራኤል ነገዶች መካከል ተዘዋውራችሁ ሕዝቡን መዝግቡ” አለው። 3 ኢዮዓብ ግን ንጉሡን “አምላክህ ይሖዋ ሕዝቡን 100 እጥፍ ያብዛው፤ የጌታዬ የንጉሡም ዓይኖች ይህን ይዩ፤ ሆኖም ጌታዬ ንጉሡ ይህን ማድረግ የፈለገው ለምንድን ነው?” አለው።
4 ሆኖም የንጉሡ ቃል ኢዮዓብንና የሠራዊቱን አዛዦች አሸነፋቸው። በመሆኑም ኢዮዓብና የሠራዊቱ አዛዦች የእስራኤልን ሕዝብ ለመመዝገብ+ ከንጉሡ ፊት ወጥተው ሄዱ። 5 እነሱም ዮርዳኖስን ተሻግረው በሸለቆ* ውስጥ ከምትገኘው ከተማ በስተ ቀኝ* ባለችው በአሮዔር+ ሰፈሩ፤ ከዚያም ወደ ጋዳውያን፣ ወደ ያዜር+ ሄዱ። 6 በኋላም ወደ ጊልያድና+ ወደ ታህቲምሆድሺ ምድር ሄዱ፤ ከዚያም ወደ ዳንየዓን ቀጠሉ፤ ዞረውም ወደ ሲዶና+ ሄዱ። 7 ከዚያም ወደ ጢሮስ+ ምሽግ እንዲሁም ወደ ሂዋውያንና+ ወደ ከነአናውያን ከተሞች በሙሉ ሄዱ፤ በመጨረሻም በይሁዳ ባለችው በኔጌብ+ ወደምትገኘው ወደ ቤርሳቤህ+ መጡ። 8 በዚህ መንገድ በመላው ምድር ሲዘዋወሩ ቆይተው ከዘጠኝ ወር ከሃያ ቀን በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። 9 ኢዮዓብም የተመዘገበውን የሕዝቡን ቁጥር ለንጉሡ ሰጠው። በእስራኤል ውስጥ ሰይፍ የታጠቁ 800,000 ተዋጊዎች ነበሩ፤ የይሁዳ ሰዎች ደግሞ 500,000 ነበሩ።+
10 ሆኖም ዳዊት ሕዝቡን ከቆጠረ በኋላ ልቡ* ወቀሰው።+ ከዚያም ዳዊት ይሖዋን “ይህን በማድረጌ ከባድ ኃጢአት ሠርቻለሁ።+ አሁንም ይሖዋ ሆይ፣ እባክህ የአገልጋይህን በደል ይቅር በል፤+ ታላቅ የሞኝነት ድርጊት ፈጽሜአለሁና” አለው።+ 11 ዳዊት ጠዋት ላይ ሲነሳ እንዲህ የሚል የይሖዋ ቃል የዳዊት ባለ ራእይ ወደሆነው ወደ ነቢዩ ጋድ+ መጣ፦ 12 “ሂድና ዳዊትን እንዲህ በለው፦ ‘ይሖዋ “ሦስት ምርጫዎችን ሰጥቼሃለሁ። በአንተ ላይ አመጣብህ ዘንድ አንዱን ምረጥ” ይላል።’”+ 13 ስለዚህ ጋድ ወደ ዳዊት ገብቶ እንዲህ አለው፦ “በምድርህ ላይ ለሰባት ዓመት ረሃብ+ ይሁን ወይስ ጠላቶችህ እያሳደዱህ ለሦስት ወር ከእነሱ ብትሸሽ ይሻልሃል?+ ወይስ ደግሞ በምድርህ ላይ ለሦስት ቀን ቸነፈር ይምጣ?+ እንግዲህ አሁን ለላከኝ ምን መልስ እንደምሰጥ በጥሞና አስብበት።” 14 ስለዚህ ዳዊት ጋድን “ሁኔታው በጣም አስጨንቆኛል። ምሕረቱ ታላቅ ስለሆነ+ እባክህ በይሖዋ እጅ እንውደቅ፤+ ሰው እጅ ላይ ግን አትጣለኝ”+ አለው።
15 ከዚያም ይሖዋ ከጠዋት አንስቶ እስከተወሰነው ጊዜ ድረስ በእስራኤል ላይ ቸነፈር ላከ፤+ በዚህም የተነሳ ከዳን አንስቶ እስከ ቤርሳቤህ+ ድረስ ካለው ሕዝብ መካከል 70,000 ሰዎች ሞቱ።+ 16 መልአኩም ኢየሩሳሌምን ለማጥፋት እጁን ወደ እሷ በዘረጋ ጊዜ ይሖዋ በደረሰው ጥፋት ተጸጸተ፤*+ በመሆኑም በሕዝቡ ላይ ጥፋት እያመጣ የነበረውን መልአክ “ይብቃ! አሁን እጅህን መልስ” አለው። የይሖዋ መልአክ በኢያቡሳዊው+ በአረውና+ አውድማ አጠገብ ነበር።
17 ዳዊትም ሕዝቡን እየገደለ ያለውን መልአክ ሲያይ ይሖዋን “ኃጢአት የሠራሁት እኮ እኔ ነኝ፤ ያጠፋሁትም እኔ ነኝ፤ ታዲያ እነዚህ በጎች+ ምን አደረጉ? እባክህ እጅህ በእኔና በአባቴ ቤት ላይ ትሁን”+ አለው።
18 በመሆኑም ጋድ በዚያው ቀን ወደ ዳዊት መጥቶ “ውጣና በኢያቡሳዊው በአረውና አውድማ ላይ ለይሖዋ መሠዊያ ሥራ” አለው።+ 19 ስለዚህ ዳዊት፣ ጋድ በነገረው መሠረት ይሖዋ እንዳዘዘው ተነስቶ ወጣ። 20 አረውናም ቁልቁል ሲመለከት ንጉሡና አገልጋዮቹ ወደ እሱ ሲመጡ አየ፤ እሱም ወዲያውኑ ወጥቶ በግንባሩ መሬት ላይ በመደፋት ለንጉሡ ሰገደ። 21 ከዚያም አረውና “ጌታዬ ንጉሡ ወደ አገልጋዩ የመጣው ለምንድን ነው?” አለው። ዳዊትም “በሕዝቡ ላይ እየወረደ ያለው መቅሰፍት እንዲቆም+ ለይሖዋ መሠዊያ ለመሥራት ይህን አውድማ ከአንተ ላይ ለመግዛት ነው” አለው። 22 አረውና ግን ዳዊትን እንዲህ አለው፦ “ጌታዬ ንጉሡ አውድማውን ወስዶ መልካም መስሎ የታየውን ነገር ያቅርብበት። ለሚቃጠል መባ የሚሆኑት ከብቶች እነዚሁልህ፣ ማሄጃውና* ከብቶቹ ላይ የሚውሉት መሣሪያዎች ደግሞ ለማገዶ ይሁኑ። 23 ንጉሥ ሆይ፣ አረውና እነዚህን ሁሉ ለንጉሡ ሰጥቷል።” አክሎም አረውና ንጉሡን “አምላክህ ይሖዋ ሞገስ ያሳይህ” አለው።
24 ሆኖም ንጉሡ አረውናን “በፍጹም አይሆንም! ዋጋውን ልከፍልህ ይገባል። ደግሞም ምንም ያልከፈልኩበትን ነገር ለአምላኬ ለይሖዋ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጌ አላቀርብም” አለው። ስለዚህ ዳዊት አውድማውንና ከብቶቹን በ50 የብር ሰቅል* ገዛ።+ 25 ዳዊትም በዚያ ለይሖዋ መሠዊያ+ ሠርቶ የሚቃጠሉ መሥዋዕቶችንና የኅብረት መሥዋዕቶችን አቀረበ። ይሖዋም ስለ ምድሪቱ የቀረበውን ልመና ሰማ፤+ በእስራኤል ላይ ይወርድ የነበረው መቅሰፍትም ቆመ።
ወይም “መትቶ።”
ወይም “ነፍሴ ገና በውስጤ ያለች።”
ወይም “የሐዘን እንጉርጉሮ።”
ወይም “ደስ የሚሉ።”
ቃል በቃል “የገዛባቸው ቀናት ቁጥር።”
ወይም “ይወዳደሩ።”
“ቢትሮንን” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “እነሆ፣ እጄ ከአንተ ጋር ነች።”
ወይም “ነፍስህ በምትሻው።”
የአካል ጉዳተኛ በመሆኑ የተነሳ ሴቶች የሚሠሩትን ሥራ ለመሥራት የተገደደን ወንድ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “መዳብ።”
ቃል በቃል “በዓመፅ ወንዶች ልጆች።”
ወይም “ለዳዊት የእዝን።”
ቃል በቃል “የሳኦል ወንድ ልጅ።”
ቃል በቃል “እጆቹ ዛሉ።”
ወይም “ነፍስህን።”
ወይም “ነፍሴን ከመከራ ሁሉ በተቤዠልኝ።”
ወይም “የሥጋ ዘመዶችህ ነን።”
ቃል በቃል “እስራኤልን የምታስወጣውና የምታስገባው።”
ወይም “የዳዊት ነፍስ የምትጠላቸውን።”
“ስፍራውንም የዳዊት ከተማ ብሎ ጠራው” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ከሚሎ።” “መሙላት” የሚል ትርጉም ያለው የዕብራይስጥ ቃል ነው።
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”
“በመደረማመስ የተዋጣለት” የሚል ትርጉም አለው።
ዳዊትና ሰዎቹ ጣዖታቱን ወስደው እንዳጠፏቸው ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። አንደኛ ዜና 14:12ን ተመልከት።
ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”
“ባካ” የሚለው ስም የዕብራይስጥ ቃል ነው። የተክሉ ዓይነት በትክክል አይታወቅም።
“በኪሩቤል መካከል የተቀመጠው” ማለትም ሊሆን ይችላል።
እዚህ ላይ የገባው የዕብራይስጥ ቃል፣ እርስ በርሱ ሲጋጭ ኃይለኛ ድምፅ የሚያወጣን ክብ ቅርጽ ያለው ከብረት የተሠራ የሙዚቃ መሣሪያ ያመለክታል።
ወይም “ዳዊት አዘነ።”
“በዖዛ ላይ መገንፈል” የሚል ትርጉም አለው።
ቃል በቃል “ታጥቆ።”
ወይም “በቤተ መንግሥቱ።”
ቃል በቃል “ከእስራኤል ወንዶች ልጆች።”
ወይም “ሥርወ መንግሥት።”
“በአዳም” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ሕግ።”
ወይም “ከፈቃድህ ጋር በሚስማማ ሁኔታ።”
ወይም “ሥርወ መንግሥት።”
ቃል በቃል “ልብ።”
ወይም “አዳነው።”
ወይም “አዳነው።”
ቃል በቃል “ካህናት።”
“ከእኔ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ከጦብ ሰዎች።”
ወይም “ከጦብ ሰዎችና።”
ቃል በቃል “እጅ።”
ኤፍራጥስን ያመለክታል።
ይህ ጊዜ የበልግን ወቅት ያመለክታል።
ወይም “አመሻሹ ላይ።”
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
የወር አበባዋን ርኩሰት የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “እግርህን ታጠብ።”
ወይም “የንጉሡ ድርሻ።” አንድ ጋባዥ ለተከበረ እንግዳው የሚልከውን ድርሻ ያመለክታል።
ወይም “በሕያው ነፍስህ።”
ቃል በቃል “በይሖዋ ዓይን መጥፎ።”
ወይም “ለባልንጀራህ።”
ቃል በቃል “በዚህች ፀሐይ ዓይኖች።”
ቃል በቃል “በፀሐይ ፊት።”
ወይም “ኃጢአትህ አልፎ እንዲሄድ ያደርጋል።”
ወይም “ቤተ መንግሥቱም።”
“ሰላም” የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ ቃል የመጣ ነው።
“በያህ የተወደደ” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “የመንግሥቱንም።”
ከተማዋ ውኃ የምታገኝባቸውን የውኃ ምንጮች የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “ስሜ ይጠራባታል።”
ይህ የአሞናውያን ጣዖት ሳይሆን አይቀርም፤ በሌላ ቦታ ላይ ሞሎክ ወይም ሚልኮም ተብሎም ተጠርቷል።
አንድ ታላንት 34.2 ኪሎ ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “የማጽናኛ ምግብ።”
ቃል በቃል “የልብ ቅርጽ ያለው ሁለት ቂጣ።”
ወይም “የማጽናኛ ምግብ።”
ወይም “የማጽናኛ ምግቡን።”
ወይም “ያጌጠ።”
ወይም “ነፍስ።”
የዘሯን የመጨረሻ ተስፋ ያመለክታል።
ወይም “ነፍስ።”
ወይም “በሕያው ነፍስህ።”
ወይም “ከተናገረው ወደ ቀኝም ሆነ ወደ ግራ ዞር ማለት የሚችል አንድም ሰው የለም።”
ይህ የሌሎቹን መለኪያዎች ትክክለኛነት ለማረጋገጥ የሚያስችል በቤተ መንግሥት ውስጥ የሚቀመጥ ሚዛን ወይም ከተለመደው ሰቅል የተለየ “ንጉሣዊ” ሰቅል ሳይሆን አይቀርም።
ወደ 2.3 ኪሎ ግራም ገደማ ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
“በ40ው” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “አምልኮ።” ቃል በቃል “አገልግሎት።”
ወይም “ቤተ መንግሥቱን።”
ወይም “ከጎኑ ሆነው የተሻገሩት።”
ወይም “በንጉሡ ፊት ተሻገሩ።”
ወንዝ ማቋረጥ የሚቻልበት ጥልቀት የሌለው የወንዝ ክፍል።
ወይም “አቀበት።”
ወይም “ሚስጥረኛ።”
የበጋ ፍሬ በዋነኝነት የሚያመለክተው በለስን ሲሆን ቴምርንም ሊጨምር ይችላል።
ወይም “የልጅ ልጅ።”
ወይም “ነፍሴን።”
ወይም “የዳዊት ሚስጥረኛ።”
ወይም “ቤተ መንግሥቱን።”
ወይም “አንድ ሰው የእውነተኛውን አምላክ ቃል እንደጠየቀ ተደርጎ።”
ወይም “እጆቹ በዛሉ።”
ወይም “በነፍሳቸው የተመረሩ።”
ወይም “ጉድጓድ፤ ገደል።”
ወይም “አዝዞ።”
“በረሃማ ሜዳዎች” ማለትም ሊሆን ይችላል። መልካ ወንዝ ማቋረጥ የሚቻልበት ጥልቀት የሌለው የወንዝ ክፍል ነው።
ቃል በቃል “ይዋጣል።”
ቃል በቃል “የከብት እርጎ።”
ቃል በቃል “እጅ።”
ቃል በቃል “በእኛ ላይ ልባቸውን አያኖሩም።”
ቃል በቃል “በሰማይና በምድር መካከል።”
ቃል በቃል “መዳፎቼ ላይ ቢመዘንልኝ።”
ወይም “የልጁን ነፍስ ለማጥፋት ሴራ ጠንስሼ።”
“አነስተኛ ቀስቶች፤ ጦሮች” ማለትም ሊሆን ይችላል። ቃል በቃል “በትሮች።”
ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”
ቃል በቃል “አውራጃውን።”
ቃል በቃል “እጃቸውን ያነሱትን።”
ወይም “የተገኘው መዳን።”
ወይም “ነፍስ።”
ቃል በቃል “ለአገልጋዮችህ ልብ ተናገር።”
ወይም “የሥጋ ዘመዶቼ።”
ቃል በቃል “አዘነበለ።”
“እነሱም” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወንዝ ማቋረጥ የሚቻልበት ጥልቀት የሌለው የወንዝ ክፍል።
“ከኢየሩሳሌም” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ኃይለኛ ነበር።”
“ወደየድንኳንህ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ቤተ መንግሥቱ።”
ቃል በቃል “እነሱም።”
ቃል በቃል “የምትውጠው።”
ቃል በቃል “እጁን አንስቷል።”
ቃል በቃል “ካህን።”
ቃል በቃል “እናሰጣለን።” እጃቸውንና እግራቸውን ሰብረው እንደሚያሰጧቸው ያመለክታል።
“ሜሮብ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
“ባለርስቶች” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “በድናቸው የተሰጣውን።”
ወደ 3.42 ኪሎ ግራም ገደማ ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ኃያል አዳኜና።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “የሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “በነፋስ ክንፎችም።”
ወይም “ሰፊ ወደሆነ ስፍራ።”
“እንደ ሞኝ ትሆናለህ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ቁርጭምጭሚቶቼ።”
ወይም “የጠላቶቼን ማጅራት ትሰጠኛለህ።”
ቃል በቃል “ጸጥ አሰኛለሁ።”
ቃል በቃል “ጆሮ በሰማው ይታዘዙኛል።”
ወይም “ይከስማሉ።”
ወይም “ታላላቅ ድሎችን ያጎናጽፋል።”
ወይም “ተወዳጅ የሆነው።”
ወይም “መዳን አስገኘ።”
ወይም “መዳን አስገኘ።”
ወይም “የድንኳን መንደርም።”
ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”
ወይም “ነፍሳቸውን።”
ቃል በቃል “የጀግና ልጅ።”
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ዳዊት በተነሳሳ።”
ወይም “በደረቁ ወንዝ።”
ወይም “በስተ ደቡብ።”
ወይም “ሕሊናው።”
ወይም “አዘነ።”
ጥርስ መሳይ ጉጦች ያሉት የእህል መውቂያ።
አንድ ሰቅል 11.4 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።