አንደኛ ነገሥት
1 ንጉሥ ዳዊት አረጀ፤+ ዕድሜውም እየገፋ ሄደ፤ ልብስ ቢደራርቡለትም እንኳ ሊሞቀው አልቻለም። 2 በመሆኑም አገልጋዮቹ “ለጌታዬ ለንጉሡ አንዲት ልጃገረድ ትፈለግለት፤ እሷም ንጉሡን እንደ ሞግዚት ሆና ትንከባከበው። ጌታዬ ንጉሡ እንዲሞቀው በእቅፉ ትተኛለች” አሉት። 3 ስለዚህ በመላው የእስራኤል ግዛት በመዘዋወር ቆንጆ ልጃገረድ ፈለጉ፤ ሹነማዊቷን+ አቢሻግንም+ አገኙ፤ ወደ ንጉሡም አመጧት። 4 እሷም እጅግ ውብ ነበረች፤ የንጉሡም ሞግዚት ሆነች፤ ትንከባከበውም ጀመር፤ ሆኖም ንጉሡ ከእሷ ጋር የፆታ ግንኙነት አልፈጸመም።
5 በዚህ ጊዜ የሃጊት ልጅ አዶንያስ+ “ንጉሥ እሆናለሁ!” በማለት ራሱን ከፍ ከፍ ያደርግ ጀመር። ለራሱም ሠረገላ ከነፈረሰኞቹ እንዲሁም ከፊት ከፊቱ የሚሮጡ 50 ሰዎች እንዲዘጋጁለት አደረገ።+ 6 አባቱ ግን አንድም ቀን “ይህን ያደረግከው ለምንድን ነው?” በማለት ተቃውሞት* አያውቅም ነበር። በተጨማሪም አዶንያስ እጅግ መልከ መልካም ነበር፤ እናቱ እሱን የወለደችው ከአቢሴሎም በኋላ ነበር። 7 እሱም ከጽሩያ ልጅ ከኢዮዓብና ከካህኑ ከአብያታር+ ጋር ተመካከረ፤ እነሱም እርዳታና ድጋፍ አደረጉለት።+ 8 ሆኖም ካህኑ ሳዶቅ፣+ የዮዳሄ ልጅ በናያህ፣+ ነቢዩ ናታን፣+ ሺምአይ፣+ ረአይና የዳዊት ኃያላን ተዋጊዎች+ አዶንያስን አልደገፉትም።
9 በኋላም አዶንያስ በኤንሮጌል አቅራቢያ በሚገኘው በጾሃለት ድንጋይ አጠገብ በጎችን፣ ከብቶችንና የሰቡ እንስሳትን መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ፤+ የንጉሡ ልጆች የሆኑትን ወንድሞቹን በሙሉ እንዲሁም የንጉሡ አገልጋዮች የሆኑትን የይሁዳን ሰዎች ሁሉ ጠራ። 10 ይሁን እንጂ ነቢዩ ናታንን፣ በናያህን፣ የዳዊትን ኃያላን ተዋጊዎች ወይም ወንድሙን ሰለሞንን አልጠራም። 11 ከዚያም ናታን+ የሰለሞንን እናት+ ቤርሳቤህን+ እንዲህ አላት፦ “የሃጊት ልጅ አዶንያስ+ ንጉሥ እንደሆነና ጌታችን ዳዊት ደግሞ ስለ ጉዳዩ ምንም የሚያውቀው ነገር እንደሌለ አልሰማሽም? 12 ስለዚህ አሁን ነይ፣ የራስሽንም ሆነ የልጅሽን የሰለሞንን ሕይወት* ማዳን እንድትችይ አንድ ነገር ልምከርሽ።+ 13 ወደ ንጉሥ ዳዊት ገብተሽ እንዲህ በዪው፦ ‘“ልጅሽ ሰለሞን ከእኔ በኋላ ንጉሥ ይሆናል፤ በዙፋኔም ላይ የሚቀመጠው እሱ ነው”+ በማለት ለአገልጋይህ የማልክላት አንተ ንጉሡ ጌታዬ አልነበርክም? ታዲያ አዶንያስ ንጉሥ የሆነው ለምንድን ነው?’ 14 አንቺም እዚያው ገና ከንጉሡ ጋር እየተነጋገርሽ ሳለ እኔ ተከትዬሽ እገባና ያልሽው ትክክል መሆኑን እናገራለሁ።”
15 በመሆኑም ቤርሳቤህ ንጉሡ ወዳለበት ወደ ውስጠኛው ክፍል ገባች። ንጉሡ በጣም አርጅቶ ነበር፤ ሹነማዊቷ አቢሻግም+ ንጉሡን እየተንከባከበች ነበር። 16 ከዚያም ቤርሳቤህ በንጉሡ ፊት ተደፍታ ሰገደች፤ ንጉሡም “ጥያቄሽ ምንድን ነው?” አላት። 17 እሷም እንዲህ ስትል መለሰች፦ “ጌታዬ ሆይ፣ ‘ልጅሽ ሰለሞን ከእኔ በኋላ ንጉሥ ይሆናል፤ በዙፋኔም ላይ የሚቀመጠው እሱ ነው’ በማለት ለአገልጋይህ በአምላክህ በይሖዋ የማልክላት አንተ ነበርክ።+ 18 ይኸው አሁን ግን አዶንያስ ንጉሥ ሆኗል፤ ጌታዬ ንጉሡም ስለዚህ ጉዳይ ምንም የሚያውቀው ነገር የለም።+ 19 እሱም በጣም ብዙ በሬዎችን፣ የሰቡ እንስሳትንና በጎችን መሥዋዕት አድርጓል፤ የንጉሡን ልጆች በሙሉ፣ ካህኑን አብያታርንና የሠራዊቱን አለቃ ኢዮዓብን ጠርቷል፤+ አገልጋይህን ሰለሞንን ግን አልጠራውም።+ 20 አሁንም ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ እስራኤላውያን በሙሉ ከጌታዬ ከንጉሡ በኋላ በዙፋኑ ላይ የሚቀመጠው ማን እንደሆነ እንድታሳውቃቸው ዓይኖቻቸው አንተ ላይ ናቸው። 21 አለዚያ ግን ጌታዬ ንጉሡ ከአባቶቹ ጋር በሚያንቀላፋበት ጊዜ እኔና ልጄ ሰለሞን እንደ ከዳተኞች ተደርገን እንቆጠራለን።”
22 እሷም ገና ከንጉሡ ጋር እየተነጋገረች ሳለ ነቢዩ ናታን ገባ።+ 23 ወዲያውም ለንጉሡ “ነቢዩ ናታን መጥቷል!” ብለው ነገሩት። ናታንም ንጉሡ ፊት ቀርቦ በግንባሩ መሬት ላይ በመደፋት ሰገደ። 24 ከዚያም ናታን እንዲህ አለ፦ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ ‘አዶንያስ ከእኔ በኋላ ንጉሥ ይሆናል፤ በዙፋኔ ላይ የሚቀመጠውም እሱ ነው’ ብለህ ተናግረሃል እንዴ?+ 25 ይኸው ዛሬ በጣም ብዙ በሬዎችን፣ የሰቡ እንስሳትንና በጎችን ለመሠዋት ወርዷል፤+ እንዲሁም የንጉሡን ልጆች በሙሉ፣ የሠራዊቱን አለቆችና ካህኑን አብያታርን ጠርቷል።+ እነሱም በዚያ ከእሱ ጋር እየበሉና እየጠጡ ‘ንጉሥ አዶንያስ ለዘላለም ይኑር!’ እያሉ ነው። 26 ሆኖም እኔን አገልጋይህን ወይም ካህኑን ሳዶቅን አሊያም የዮዳሄን ልጅ በናያህን+ ወይም አገልጋይህን ሰለሞንን አልጠራም። 27 ጌታዬ ንጉሡ ከእሱ በኋላ በጌታዬ በንጉሡ ዙፋን ላይ የሚቀመጠው ማን እንደሆነ ለአገልጋዩ ሳይነግረው ይህ እንዲደረግ ፈቅዷል?”
28 በዚህ ጊዜ ንጉሥ ዳዊት “ቤርሳቤህን ጥሩልኝ” አለ። እሷም ገብታ ንጉሡ ፊት ቆመች። 29 ንጉሡም እንዲህ ሲል ማለ፦ “ከመከራ ሁሉ ባዳነኝ*+ ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ፣ 30 ‘ልጅሽ ሰለሞን ከእኔ በኋላ ንጉሥ ይሆናል፤ በእኔ ምትክ በዙፋኔ ላይ የሚቀመጠውም እሱ ነው!’ በማለት በእስራኤል አምላክ በይሖዋ በማልኩልሽ መሠረት ዛሬም ይህ እንዲፈጸም አደርጋለሁ።” 31 ከዚያም ቤርሳቤህ በግንባሯ መሬት ላይ ተደፍታ ለንጉሡ በመስገድ “ጌታዬ ንጉሥ ዳዊት ለዘላለም ይኑር!” አለች።
32 ንጉሥ ዳዊትም ወዲያውኑ “በሉ አሁን ካህኑን ሳዶቅን፣ ነቢዩን ናታንንና የዮዳሄን+ ልጅ በናያህን+ ጥሩልኝ” አለ። እነሱም ገብተው ንጉሡ ፊት ቀረቡ። 33 ንጉሡም እንዲህ አላቸው፦ “የጌታችሁን አገልጋዮች ውሰዱና ልጄን ሰለሞንን በበቅሎዬ*+ ላይ አስቀምጣችሁ ወደ ግዮን+ ይዛችሁት ውረዱ። 34 በዚያም ካህኑ ሳዶቅና ነቢዩ ናታን በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርገው ይቀቡታል፤+ ከዚያም ቀንደ መለከት እየነፋችሁ ‘ንጉሥ ሰለሞን ለዘላለም ይኑር!’+ በሉ። 35 አጅባችሁትም ተመለሱ፤ እሱም መጥቶ በዙፋኔ ላይ ይቀመጣል፤ በእኔም ምትክ ንጉሥ ይሆናል፤ እኔም በእስራኤልና በይሁዳ ላይ መሪ አድርጌ እሾመዋለሁ።” 36 የዮዳሄ ልጅ በናያህም ወዲያውኑ ንጉሡን እንዲህ አለው፦ “አሜን! የጌታዬ የንጉሡ አምላክ ይሖዋ ይህን ያጽናው። 37 ይሖዋ ከጌታዬ ከንጉሡ ጋር እንደነበረ ሁሉ ከሰለሞንም ጋር ይሁን፤+ ዙፋኑንም ከጌታዬ ከንጉሥ ዳዊት ዙፋን የበለጠ ያድርገው።”+
38 ከዚያም ካህኑ ሳዶቅ፣ ነቢዩ ናታን፣ የዮዳሄ ልጅ በናያህ፣+ ከሪታውያንና ጴሌታውያን+ ወርደው ሰለሞንን በንጉሥ ዳዊት በቅሎ ላይ አስቀመጡት፤+ ወደ ግዮንም+ አመጡት። 39 ካህኑ ሳዶቅም ከድንኳኑ+ ውስጥ የዘይቱን ቀንድ+ ወስዶ ሰለሞንን ቀባው፤+ እነሱም ቀንደ መለከት መንፋት ጀመሩ፤ ሕዝቡም ሁሉ “ንጉሥ ሰለሞን ለዘላለም ይኑር!” እያለ ይጮኽ ጀመር። 40 ከዚያም ሕዝቡ በሙሉ ዋሽንት እየነፋና በደስታ እየፈነደቀ ተከትሎት ወጣ፤ ከጩኸታቸውም የተነሳ ምድሪቱ ተሰነጠቀች።+
41 አዶንያስና የጋበዛቸው ሰዎች ሁሉ በልተው ሲጨርሱ ይህን ድምፅ ሰሙ።+ ኢዮዓብ የቀንደ መለከቱን ድምፅ ሲሰማ “በከተማዋ ውስጥ የሚሰማው ይህ ሁሉ ሁካታ ምንድን ነው?” አለ። 42 እሱም ገና እየተናገረ ሳለ የካህኑ የአብያታር ልጅ ዮናታን+ መጣ። ከዚያም አዶንያስ “መቼም አንተ ጥሩ* ሰው ስለሆንክ ምሥራች ሳትይዝ አትመጣምና ግባ” አለው። 43 ዮናታን ግን ለአዶንያስ እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ምሥራች ይዤስ አልመጣሁም! ጌታችን ንጉሥ ዳዊት ሰለሞንን አንግሦታል። 44 ንጉሡም ካህኑ ሳዶቅ፣ ነቢዩ ናታን፣ የዮዳሄ ልጅ በናያህ፣ ከሪታውያንና ጴሌታውያን አብረውት እንዲሄዱ አደረገ፤ እነሱም በንጉሡ በቅሎ ላይ አስቀመጡት።+ 45 ከዚያም ካህኑ ሳዶቅና ነቢዩ ናታን በግዮን ንጉሥ አድርገው ቀቡት። እነሱም ከዚያ እየተደሰቱ መጡ፤ ከተማዋ በጩኸት እየተናወጠች ነው። እናንተም የሰማችሁት ይህን ድምፅ ነው። 46 ከዚህም በላይ ሰለሞን በነገሥታቱ ዙፋን ላይ ተቀምጧል። 47 የንጉሡ አገልጋዮችም ‘አምላክህ የሰለሞንን ስም ከአንተ ስም በላይ ታላቅ ያድርገው፤ ዙፋኑንም ከአንተ ዙፋን የበለጠ ያድርገው’ በማለት ለጌታችን ለንጉሥ ዳዊት ደስታቸውን ለመግለጽ መጥተዋል። በዚህ ጊዜ ንጉሡ አልጋው ላይ ሰገደ። 48 ከዚያም ንጉሡ ‘ዛሬ በዙፋኔ ላይ የሚቀመጥ ሰው የሰጠኝና ዓይኖቼም ይህን እንዲያዩ ያደረገው የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ይወደስ!’ አለ።”
49 አዶንያስ የጋበዛቸው ሰዎችም ሁሉ ተሸበሩ፤ እያንዳንዳቸውም ተነስተው በየፊናቸው ሄዱ። 50 አዶንያስም ሰለሞንን ስለፈራው ተነስቶ በመሄድ የመሠዊያውን ቀንዶች ያዘ።+ 51 በኋላም ሰለሞን “አዶንያስ ንጉሥ ሰለሞንን ፈርቶታል፤ ‘በመጀመሪያ ንጉሥ ሰለሞን አገልጋዩን በሰይፍ እንደማይገድል ይማልልኝ’ በማለት የመሠዊያውን ቀንዶች ይዟል” ተብሎ ተነገረው። 52 በዚህ ጊዜ ሰለሞን “ጸባዩን ካሳመረ ከራስ ፀጉሩ አንዲቷም እንኳ መሬት ላይ አትወድቅም፤ መጥፎ ነገር ከተገኘበት+ ግን ይሞታል” አለ። 53 በመሆኑም ንጉሥ ሰለሞን አዶንያስን ከመሠዊያው ላይ እንዲያወርዱት ሰዎች ላከ። ከዚያም አዶንያስ መጥቶ ለንጉሥ ሰለሞን ሰገደ፤ ሰለሞንም “ወደ ቤትህ ሂድ” አለው።
2 ዳዊት የሚሞትበት ቀን ሲቃረብ ልጁን ሰለሞንን እንዲህ ሲል አዘዘው፦ 2 “እንግዲህ እኔ የምሞትበት ጊዜ ቀርቧል።* ስለሆነም በርታ፤+ ወንድ ሁን።+ 3 በሙሴ ሕግ ላይ በተጻፈው መሠረት በመንገዶቹ በመሄድ እንዲሁም ደንቦቹን፣ ትእዛዛቱን፣ ፍርዶቹንና ማሳሰቢያዎቹን በመጠበቅ ለአምላክህ ለይሖዋ ያለብህን ግዴታ ፈጽም፤+ ይህን ካደረግክ የምታከናውነው ሁሉ ይሳካልሃል፤ በምትሄድበትም ሁሉ ይቃናልሃል። 4 ይሖዋም እንዲህ በማለት የገባልኝን ቃል ይፈጽማል፦ ‘ልጆችህ፣ በሙሉ ልባቸውና በሙሉ ነፍሳቸው*+ በፊቴ በታማኝነት በመመላለስ መንገዳቸውን ከጠበቁ ከዘር ሐረግህ በእስራኤል ዙፋን ላይ የሚቀመጥ ሰው አይታጣም።’+
5 “የጽሩያ ልጅ ኢዮዓብ በእኔ ላይ ያደረገውን ነገር ይኸውም በሁለቱ የእስራኤል ሠራዊት አለቆች ማለትም በኔር ልጅ በአበኔርና+ በየቴር ልጅ በአሜሳይ+ ላይ ያደረገውን በሚገባ ታውቃለህ። ይህ ሰው እነዚህን ሰዎች በመግደል ጦርነት ሳይኖር በሰላሙ ጊዜ ደም አፍስሷል፤+ እንዲሁም በወገቡ ላይ የታጠቀው ቀበቶና በእግሩ ላይ ያደረገው ጫማ በጦርነት ጊዜ በሚፈሰው ደም እንዲበከል አድርጓል። 6 እንግዲህ እንደ ጥበብህ አድርግ፤ ሽበቱ በሰላም ወደ መቃብር* እንዲወርድ አታድርግ።+
7 “ሆኖም ለቤርዜሊ+ ልጆች ታማኝ ፍቅር አሳያቸው፤ እነሱም ከማዕድህ ከሚበሉ ሰዎች መካከል ይሁኑ፤ ምክንያቱም ከወንድምህ ከአቢሴሎም ፊት በሸሸሁ ጊዜ+ እነሱም ከጎኔ ቆመው ነበር።+
8 “በተጨማሪም ከባሁሪም የመጣው ቢንያማዊው የጌራ ልጅ ሺምአይ አብሮህ አለ። ወደ ማሃናይም በሄድኩበት ዕለት+ ከባድ እርግማን የረገመኝ እሱ ነው፤+ ሆኖም እኔን ለማግኘት ወደ ዮርዳኖስ በወረደ ጊዜ ‘በሰይፍ አልገድልህም’ ብዬ በይሖዋ ማልኩለት።+ 9 አንተ ጥበበኛ ስለሆንክና በእሱ ላይ ምን ማድረግ እንዳለብህ ስለምታውቅ ሳትቀጣ አትተወው፤+ ሽበቱ በደም ወደ መቃብር* እንዲወርድ አድርግ።”+
10 ከዚያም ዳዊት ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊት ከተማም+ ተቀበረ። 11 ዳዊት በእስራኤል ላይ ንጉሥ ሆኖ የገዛው ለ40 ዓመት ነበር። በኬብሮን+ ለ7 ዓመት፣ በኢየሩሳሌም ደግሞ ለ33 ዓመት ነገሠ።+
12 ከዚያም ሰለሞን በአባቱ በዳዊት ዙፋን ላይ ተቀመጠ፤ ቀስ በቀስም ንግሥናው እየጸና ሄደ።+
13 ከጊዜ በኋላም የሃጊት ልጅ አዶንያስ ወደ ሰለሞን እናት ወደ ቤርሳቤህ መጣ። እሷም “የመጣኸው በሰላም ነው?” አለችው፤ እሱም “አዎ፣ በሰላም ነው” አላት። 14 ከዚያም “አንድ የምነግርሽ ጉዳይ አለኝ” አላት። እሷም “እሺ፣ ንገረኝ” አለችው። 15 እሱም እንዲህ አላት፦ “ንግሥናው የእኔ ሊሆን እንደነበረና እስራኤልም ሁሉ ይነግሣል ብለው ይጠብቁ እንደነበር* በሚገባ ታውቂያለሽ፤+ ይሁንና ንግሥናው የእኔ መሆኑ ቀርቶ የወንድሜ ሆነ፤ ምክንያቱም ይሖዋ ንግሥናው የእሱ እንዲሆን ወስኖ ነበር።+ 16 ሆኖም አሁን አንድ የምጠይቅሽ ነገር አለ። መቼም አታሳፍሪኝም።” እሷም “እሺ ንገረኝ” አለችው። 17 እሱም “እባክሽ፣ ንጉሥ ሰለሞን የጠየቅሽውን እንቢ ስለማይልሽ ሹነማዊቷን አቢሻግን+ እንዲድርልኝ ጠይቂው” አላት። 18 በዚህ ጊዜ ቤርሳቤህ “መልካም! ንጉሡን አነጋግርልሃለሁ” አለችው።
19 በመሆኑም ቤርሳቤህ የአዶንያስን ጉዳይ ልትነግረው ወደ ንጉሥ ሰለሞን ገባች። ንጉሡም ወዲያውኑ ሊቀበላት ተነሳ፤ ሰገደላትም። ከዚያም ዙፋኑ ላይ ተቀመጠ፤ የንጉሡም እናት በቀኙ እንድትቀመጥ ዙፋን አስመጣላት። 20 እሷም “አንዲት ትንሽ ነገር ልጠይቅህ አስቤ ነበር። መቼም እንቢ አትለኝም” አለችው። ንጉሡም “እናቴ ሆይ፣ ንገሪኝ፤ የጠየቅሽኝን እንቢ አልልሽም” አላት። 21 እሷም “ሹነማዊቷ አቢሻግ ለወንድምህ ለአዶንያስ ትዳርለት” አለችው። 22 በዚህ ጊዜ ንጉሥ ሰለሞን ለእናቱ እንዲህ ሲል መለሰላት፦ “ለአዶንያስ ሹነማዊቷን አቢሻግን ብቻ ለምን ትጠይቂለታለሽ? ታላቅ ወንድሜ+ ስለሆነ ንግሥናም ጠይቂለት እንጂ፤+ ካህኑ አብያታርና የጽሩያ+ ልጅ ኢዮዓብም+ እየደገፉት ነው።”
23 ከዚያም ንጉሥ ሰለሞን እንዲህ ሲል በይሖዋ ማለ፦ “አዶንያስ ይህን በመጠየቁ ሕይወቱን ሳያጣ ቢቀር* አምላክ ይህን ያድርግብኝ፤ ከዚህ የከፋም ነገር ያምጣብኝ። 24 አሁንም በሚገባ ባጸናኝ፣+ በአባቴ በዳዊት ዙፋን ላይ ባስቀመጠኝና በገባው ቃል መሠረት ቤት በሠራልኝ*+ ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ፣ አዶንያስ በዛሬዋ ዕለት ይገደላል።”+ 25 ንጉሥ ሰለሞንም ወዲያውኑ የዮዳሄን ልጅ በናያህን+ ላከው፤ እሱም ወጥቶ አዶንያስን መታው፤* እሱም ሞተ።
26 ንጉሡም ካህኑን አብያታርን+ እንዲህ አለው፦ “በአናቶት+ ወደሚገኘው እርሻህ ሂድ! አንተ ሞት የሚገባህ ሰው ነህ፤ ሆኖም በአባቴ በዳዊት ፊት የሉዓላዊውን ጌታ የይሖዋን ታቦት ስለተሸከምክና+ በአባቴ ላይ የደረሰውን መከራ ሁሉ ስለተጋራህ ዛሬ አልገድልህም።”+ 27 በመሆኑም ይሖዋ በሴሎ፣+ በኤሊ ቤት+ ላይ እንደሚደርስ የተናገረው ነገር ይፈጸም ዘንድ ሰለሞን አብያታርን የይሖዋ ካህን ሆኖ እንዳያገለግል አባረረው።
28 ኢዮዓብ ቀደም ሲል ከአቢሴሎም+ጋር ወግኖ ያልነበረ ቢሆንም አዶንያስን+ ደግፎ ስለነበር ይህን ወሬ ሲሰማ ወደ ይሖዋ ድንኳን+ በመሸሽ የመሠዊያውን ቀንዶች ያዘ። 29 ከዚያም ንጉሥ ሰለሞን “ኢዮዓብ ወደ ይሖዋ ድንኳን ሸሽቶ እዚያ በመሠዊያው አጠገብ ይገኛል” ተብሎ ተነገረው። በመሆኑም ሰለሞን የዮዳሄን ልጅ በናያህን “ሂድና ግደለው!” ብሎ ላከው። 30 ስለዚህ በናያህ ወደ ይሖዋ ድንኳን ሄዶ ኢዮዓብን “ንጉሡ ‘ና ውጣ!’ ብሎሃል” አለው። እሱ ግን “እዚሁ እሞታታለሁ እንጂ በፍጹም አልወጣም!” አለ። በዚህ ጊዜ በናያህ “ኢዮዓብ እንዲህ እንዲህ ብሏል፤ እንዲህም ሲል መልሶልኛል” በማለት ለንጉሡ ተናገረ። 31 ከዚያም ንጉሡ እንዲህ አለው፦ “በል ልክ እንዳለው አድርግ፤ ግደለውና ቅበረው፤ ኢዮዓብ አላግባብ ካፈሰሰውም ደም እኔንና የአባቴን ቤት አንጻ።+ 32 ኢዮዓብ አባቴ ዳዊት ሳያውቅ ከእሱ ይልቅ ጻድቅና የተሻሉ የነበሩትን ሁለት ሰዎች ማለትም የእስራኤል ሠራዊት አለቃ+ የነበረውን የኔርን ልጅ አበኔርንና+ የይሁዳ ሠራዊት አለቃ+ የነበረውን የየቴርን ልጅ አሜሳይን+ በሰይፍ መትቶ በመግደሉ ይሖዋ ደሙን በራሱ ላይ ይመልስበታል። 33 ደማቸውም ለዘላለም በኢዮዓብ ራስና በዘሮቹ ራስ ላይ ይሆናል፤+ በዳዊት፣ በዘሮቹ፣ በቤቱና በዙፋኑ ላይ ግን የይሖዋ ሰላም ለዘላለም ይሁን።” 34 ከዚያም የዮዳሄ ልጅ በናያህ ወጥቶ ኢዮዓብን መትቶ ገደለው፤ እሱም በምድረ በዳ በሚገኘው በራሱ ቤት ተቀበረ። 35 ከዚያም ንጉሡ በኢዮዓብ ምትክ የዮዳሄን ልጅ በናያህን+ በሠራዊቱ ላይ ሾመው፤ በአብያታር ቦታ ደግሞ ካህኑን ሳዶቅን+ ሾመው።
36 ንጉሡም ሺምአይን+ አስጠርቶ እንዲህ አለው፦ “ኢየሩሳሌም ውስጥ ቤት ሠርተህ በዚያ ኑር፤ ከዚያም ወጥተህ ወደ ሌላ ቦታ አትሂድ። 37 ከዚያ ወጥተህ የቄድሮንን ሸለቆ+ የተሻገርክ ቀን ግን እንደምትሞት እወቅ። ደምህ በራስህ ላይ ይሆናል።” 38 ሺምአይም ንጉሡን “ጥሩ ሐሳብ ነው። አገልጋይህ፣ ጌታዬ ንጉሡ እንዳለው ያደርጋል” አለው። ስለሆነም ሺምአይ በኢየሩሳሌም ለብዙ ጊዜ ተቀመጠ።
39 ሆኖም ከሦስት ዓመት በኋላ ከሺምአይ ባሪያዎች መካከል ሁለቱ የጌት ንጉሥ ወደሆነው ወደ ማአካ ልጅ ወደ አንኩስ+ ኮበለሉ። ሺምአይም “ባሪያዎችህ ያሉት ጌት ነው” ተብሎ ሲነገረው 40 ወዲያውኑ አህያውን ጭኖ ባሪያዎቹን ለመፈለግ በጌት ወዳለው ወደ አንኩስ አቀና። ሺምአይ ባሪያዎቹን ይዞ ከጌት ሲመለስ 41 ለሰለሞን “ሺምአይ ከኢየሩሳሌም ወጥቶ ወደ ጌት ሄዶ ነበር፤ አሁን ግን ተመልሷል” ተብሎ ተነገረው። 42 በዚህ ጊዜ ንጉሡ ሺምአይን አስጠርቶ እንዲህ አለው፦ “‘ከዚህ ወጥተህ ወደ ሌላ ቦታ በሄድክ ቀን እንደምትሞት እወቅ’ ብዬ በይሖዋ አስምዬህና አስጠንቅቄህ አልነበረም? አንተስ ብትሆን ‘ጥሩ ሐሳብ ነው፤ እንዳልከኝ አደርጋለሁ’ ብለኸኝ አልነበረም?+ 43 ታዲያ በይሖዋ ፊት የገባኸውን መሐላና የሰጠሁህን ትእዛዝ ያልጠበቅከው ለምንድን ነው?” 44 ከዚያም ንጉሡ፣ ሺምአይን እንዲህ አለው፦ “በአባቴ በዳዊት ላይ ያደረግከውን ክፉ ነገር ሁሉ ልብህ ያውቀዋል፤+ ይሖዋም ያደረግከውን ክፉ ነገር በራስህ ላይ ይመልስብሃል።+ 45 ንጉሥ ሰለሞን ግን ይባረካል፤+ የዳዊትም ዙፋን በይሖዋ ፊት ለዘላለም ይጸናል።” 46 ከዚያም ንጉሡ የዮዳሄን ልጅ በናያህን አዘዘው፤ እሱም ወጥቶ ሺምአይን መትቶ ገደለው።+
በዚህ መንገድ መንግሥቱ በሰለሞን እጅ ጸና።+
3 ሰለሞን ከግብፁ ንጉሥ ከፈርዖን ጋር በጋብቻ ተዛመደ። የፈርዖንን ሴት ልጅ አገባ፤*+ እሷንም የራሱን ቤት፣ የይሖዋን ቤትና+ በኢየሩሳሌም ዙሪያ ያለውን ቅጥር+ ገንብቶ እስኪጨርስ ድረስ+ ወደ ዳዊት ከተማ+ አመጣት። 2 ሆኖም እስከዚያን ጊዜ ድረስ ለይሖዋ ስም የተሠራ ቤት ስላልነበረ+ ሕዝቡ መሥዋዕት ያቀርብ የነበረው ከፍ ባሉት የማምለኪያ ቦታዎች+ ላይ ነበር። 3 ሰለሞን መሥዋዕቶችንና የሚቃጠሉ መባዎችን ከፍ ባሉት የማምለኪያ ቦታዎች ላይ ከማቅረቡ በስተቀር በአባቱ በዳዊት ደንቦች መሠረት በመሄድ ይሖዋን እንደሚወድ አሳይቷል።+
4 ይበልጥ ታዋቂ* የሆነው ከፍ ያለ የማምለኪያ ቦታ ገባኦን ስለነበር ንጉሡ መሥዋዕት ለማቅረብ ወደዚያ ሄደ።+ ሰለሞን በዚያ መሠዊያ ላይ 1,000 የሚቃጠሉ መሥዋዕቶችን አቀረበ።+ 5 በገባኦንም ይሖዋ ለሰለሞን ሌሊት በሕልም ተገለጠለት፤ አምላክም “እንድሰጥህ የምትፈልገውን ጠይቅ” አለው።+ 6 በዚህ ጊዜ ሰለሞን እንዲህ አለ፦ “አገልጋይህ አባቴ ዳዊት በፊትህ በታማኝነት፣ በጽድቅና በቅን ልቦና ስለሄደ ጥልቅ የሆነ ታማኝ ፍቅር አሳይተኸዋል። በዙፋኑ ላይ የሚቀመጥ ልጅ በመስጠት እስከ ዛሬም ድረስ ለእሱ ይህን ጥልቅ የሆነ ታማኝ ፍቅር አሳይተሃል።+ 7 አሁንም አምላኬ ይሖዋ ሆይ፣ እኔ ገና አንድ ፍሬ ልጅና ተሞክሮ የሌለኝ*+ ብሆንም አገልጋይህን በአባቴ በዳዊት ምትክ አንግሠኸዋል። 8 አገልጋይህ አንተ በመረጥከው፣+ ከብዛቱም የተነሳ ሊቆጠር በማይችለው ሕዝብ መካከል ይገኛል። 9 ስለሆነም አገልጋይህ ሕዝብህን መዳኘት እንዲሁም መልካምና ክፉ የሆነውን ነገር መለየት+ እንዲችል ታዛዥ ልብ ስጠው፤+ አለዚያማ ስፍር ቁጥር የሌለውን* ይህን ሕዝብህን ማን ሊዳኝ ይችላል?”
10 ሰለሞን ይህን መጠየቁ ይሖዋን ደስ አሰኘው።+ 11 ከዚያም አምላክ እንዲህ አለው፦ “ይህን ነገር ስለጠየቅክ እንዲሁም ለራስህ ረጅም ዕድሜ* ወይም ብልጽግና አሊያም የጠላቶችህን ሞት* ሳይሆን የፍርድ ጉዳዮችን መዳኘት እንድትችል ማስተዋልን ስለጠየቅክ+ 12 የጠየቅከውን አደርግልሃለሁ።+ ከአንተ በፊት ማንም ሰው ያልነበረውን+ ከአንተ በኋላም ማንም ሰው የማያገኘውን ጥበበኛና አስተዋይ ልብ እሰጥሃለሁ።+ 13 በተጨማሪም በሕይወት ዘመንህ* ሁሉ ከነገሥታት መካከል አንተን የሚተካከል እንዳይኖር+ አንተ ያልጠየቅከውን+ ብልጽግናና ክብር+ እሰጥሃለሁ። 14 አባትህ ዳዊት እንዳደረገው+ ሥርዓቶቼንና ትእዛዛቴን በመጠበቅ በመንገዶቼ ከሄድክ ረጅም ዕድሜም እሰጥሃለሁ።”*+
15 ሰለሞንም ከእንቅልፉ ሲነቃ ሕልም መሆኑን ተረዳ። ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ በይሖዋ የቃል ኪዳን ታቦት ፊት ቆመ፤ የሚቃጠሉ መሥዋዕቶችንና የኅብረት መባዎችን+ አቀረበ፤ ለአገልጋዮቹም በሙሉ ግብዣ አዘጋጀ።
16 በዚህ ጊዜ ሁለት ዝሙት አዳሪዎች ወደ ንጉሡ መጥተው ፊቱ ቆሙ። 17 የመጀመሪያዋም ሴት እንዲህ አለች፦ “ጌታዬ ሆይ፣ እኔና ይህች ሴት የምንኖረው አንድ ቤት ውስጥ ነው፤ እሷም ቤት ውስጥ እያለች ልጅ ወለድኩ። 18 እኔ ከወለድኩ ከሦስት ቀን በኋላ ይህችም ሴት ልጅ ወለደች። ሁለታችን አብረን ነበርን፤ ከሁለታችን በስተቀር ቤቱ ውስጥ ማንም አብሮን አልነበረም። 19 ሌሊት ላይ ይህች ሴት ልጇ ላይ ስለተኛችበት ልጇ ሞተ። 20 ስለሆነም እኩለ ሌሊት ላይ ተነስታ እኔ አገልጋይህ ተኝቼ እያለሁ ልጄን ከአጠገቤ በመውሰድ በእቅፏ አስተኛችው፤ የሞተውን ልጇን ደግሞ በእኔ እቅፍ ውስጥ አስተኛችው። 21 እኔም በማለዳ ልጄን ለማጥባት ስነሳ ልጁ ሞቷል። ስለሆነም በማለዳ ብርሃን ልጁን ትክ ብዬ ስመለከተው እኔ የወለድኩት ልጅ አለመሆኑን ተረዳሁ።” 22 ሆኖም ሌላኛዋ ሴት “በፍጹም፣ በሕይወት ያለው የእኔ ልጅ ነው፤ የሞተው የአንቺ ልጅ ነው!” አለች። በዚህ ጊዜ የመጀመሪያዋ ሴት “በጭራሽ፣ የሞተው የአንቺ ልጅ ነው፤ በሕይወት ያለው የእኔ ልጅ ነው” አለች። እነሱም እንዲህ እያሉ በንጉሡ ፊት ተጨቃጨቁ።
23 በመጨረሻም ንጉሡ “ይህችኛዋ ‘ይህ በሕይወት ያለው ልጅ የእኔ ነው፤ የሞተው የአንቺ ልጅ ነው!’ ትላለች፤ ያቺኛዋ ደግሞ ‘በፍጹም፣ የሞተው የአንቺ ልጅ ነው፤ በሕይወት ያለው የእኔ ልጅ ነው!’ ትላለች” አለ። 24 ከዚያም ንጉሡ “እንግዲያውስ ሰይፍ አምጡልኝ” አለ። በመሆኑም ለንጉሡ ሰይፍ አመጡለት። 25 ንጉሡም “በሉ በሕይወት ያለውን ልጅ ለሁለት ሰንጥቁትና ግማሹን ለአንደኛዋ ሴት ግማሹን ደግሞ ለሌላኛዋ ስጡ” አለ። 26 በሕይወት ያለው ልጅ እናት ለልጇ ስለራራች ወዲያውኑ ንጉሡን “እባክህ ጌታዬ! በሕይወት ያለውን ልጅ ለእሷ ስጧት! በፍጹም አትግደሉት!” በማለት ተማጸነችው። ሌላኛዋ ሴት ግን “ልጁ የእኔም የአንቺም አይሆንም! ለሁለት ይሰንጥቁት!” ትል ነበር። 27 ንጉሡም መልሶ “በሕይወት ያለውን ልጅ ለመጀመሪያዋ ሴት ስጧት! እናቱ እሷ ስለሆነች በፍጹም አትግደሉት” አለ።
28 እስራኤላውያንም ሁሉ ንጉሡ የሰጠውን ፍርድ ሰሙ፤ ንጉሡ ፍትሐዊ ፍርድ መስጠት ይችል ዘንድ የአምላክን ጥበብ እንደታደለ+ ስለተመለከቱ ለንጉሡ አክብሮታዊ ፍርሃት አደረባቸው።+
4 ንጉሥ ሰለሞን መላውን እስራኤል ይገዛ ነበር።+ 2 ከፍተኛ ባለሥልጣናቱ* እነዚህ ነበሩ፦ የሳዶቅ+ ልጅ አዛርያስ ካህን ነበር፤ 3 የሺሻ ልጆች ኤሌሆሬፍና አኪያህ ጸሐፊዎች ነበሩ፤+ የአሂሉድ ልጅ ኢዮሳፍጥ+ ታሪክ ጸሐፊ ነበር፤ 4 የዮዳሄ ልጅ በናያህ+ የሠራዊቱ አዛዥ ነበር፤ ሳዶቅና አብያታር+ ካህናት ነበሩ፤ 5 የናታን+ ልጅ አዛርያስ የአስተዳዳሪዎቹ ኃላፊ ነበር፤ የናታን ልጅ ዛቡድ ካህንና የንጉሡ ወዳጅ ነበር፤+ 6 አሂሻር የቤቱ አዛዥ ነበር፤ የአብዳ ልጅ አዶኒራም+ የግዳጅ ሥራ እንዲሠሩ በተመለመሉት+ ላይ አዛዥ ነበር።
7 ሰለሞን በመላው እስራኤል ላይ የተሾሙ ለንጉሡና ለቤተሰቡ ቀለብ የሚያቀርቡ 12 አስተዳዳሪዎች ነበሩት። እያንዳንዳቸውም በዓመት ውስጥ ለአንድ ወር ቀለብ የማቅረብ ኃላፊነት ተጥሎባቸው ነበር።+ 8 ስማቸውም የሚከተለው ነው፦ በኤፍሬም ተራራማ አካባቢ የሁር ልጅ፣ 9 በማቃጽ፣ በሻአልቢም፣+ በቤትሼሜሽ እና በኤሎንቤትሃናን የዴቀር ልጅ፣ 10 በአሩቦት የሄሴድ ልጅ (ሶኮህ እና የሄፌር ምድር በሙሉ በሥሩ ነበሩ)፣ 11 በዶር ሸንተረር በሙሉ የአቢናዳብ ልጅ (እሱም የሰለሞንን ልጅ ጣፋትን አግብቶ ነበር)፣ 12 በታአናክ እና በመጊዶ+ እንዲሁም ከኢይዝራኤል በታች ከጸረታን አጠገብ በሚገኘው በቤትሼን+ በሙሉና ከቤትሼን አንስቶ በዮቅመአም+ እስከሚገኘው እስከ አቤልምሆላ ድረስ የአሂሉድ ልጅ ባአና፣ 13 በራሞትጊልያድ+ የጌቤር ልጅ (በጊልያድ+ የሚገኙት የምናሴ ልጅ የያኢር+ የድንኳን ሰፈሮች በእሱ ሥር ነበሩ፤ እንዲሁም በባሳን+ የሚገኘው የአርጎብ ክልል+ ይኸውም በቅጥር የታጠሩና የመዳብ መቀርቀሪያ ያላቸው 60 ትላልቅ ከተሞች በእሱ ሥር ነበሩ)፣ 14 በማሃናይም+ የኢዶ ልጅ አሂናዳብ፣ 15 በንፍታሌም አኪማዓስ (እሱም ሌላኛዋን የሰለሞንን ልጅ፣ ባሴማትን አግብቶ ነበር)፣ 16 በአሴርና በበዓሎት የኩሲ ልጅ ባአና፣ 17 በይሳኮር የፓሩህ ልጅ ኢዮሳፍጥ፣ 18 በቢንያም+ የኤላ ልጅ ሺምአይ+ 19 እንዲሁም የአሞራውያን ንጉሥ የሲሖን+ እና የባሳን ንጉሥ የኦግ+ ምድር በሆነው በጊልያድ+ ምድር የዖሪ ልጅ ጌቤር። በተጨማሪም በምድሪቱ አስተዳዳሪዎች ሁሉ ላይ የተሾመ አንድ አስተዳዳሪ ነበር።
20 ይሁዳና እስራኤል ከብዛታቸው የተነሳ እንደ ባሕር አሸዋ ነበሩ፤+ እነሱም ይበሉና ይጠጡ እንዲሁም ይደሰቱ ነበር።+
21 ሰለሞን ከወንዙ*+ አንስቶ እስከ ፍልስጤማውያን ምድርና እስከ ግብፅ ወሰን ድረስ ባሉት መንግሥታት ሁሉ ላይ ገዛ። እነሱም በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ግብር ያመጡለት እንዲሁም ያገለግሉት ነበር።+
22 ሰለሞን በየቀኑ የሚገባለት ቀለብ ይህ ነበር፦ 30 የቆሮስ መስፈሪያ* የላመ ዱቄት፣ 60 የቆሮስ መስፈሪያ ዱቄት 23 እንዲሁም 10 ቅልብ ከብቶች፣ ከግጦሽ የመጡ 20 ከብቶች፣ 100 በጎችና የተወሰኑ የርኤም* ዝርያዎች፣ የሜዳ ፍየሎችና የሰቡ ወፎች። 24 እሱም ከወንዙ ወዲህ ያሉትን ነገሥታት ሁሉ ጨምሮ ከቲፍሳ አንስቶ እስከ ጋዛ+ ድረስ የሚገኙትን ከወንዙ+ ወዲህ* ያሉትን አካባቢዎች በሙሉ ተቆጣጥሮ ነበር፤ በዙሪያው ባለው አካባቢ ሁሉ ሰላም ሰፍኖለት ነበር።+ 25 በሰለሞን ዘመን ከዳን አንስቶ እስከ ቤርሳቤህ ድረስ በይሁዳና በእስራኤል የሚገኝ እያንዳንዱ ሰው ከገዛ ወይኑና ከበለስ ዛፉ ሥር ያለስጋት ይኖር ነበር።
26 ሰለሞን ሠረገሎቹን ለሚጎትቱት ፈረሶች የሚሆኑ 4,000* ጋጣዎችና 12,000 ፈረሶች* ነበሩት።+
27 እነዚህ አስተዳዳሪዎች ለንጉሥ ሰለሞንና ከንጉሥ ሰለሞን ማዕድ ለሚመገቡት ሁሉ ቀለብ ያቀርቡ ነበር። እያንዳንዳቸውም በተመደበላቸው ወር የሚጠበቅባቸውን ያቀርቡ የነበረ ሲሆን ምንም ነገር እንዳይጓደል ጥንቃቄ ያደርጉ ነበር።+ 28 እንዲሁም እያንዳንዳቸው በተመደበላቸው ድርሻ መሠረት ለፈረሶቹና ለሰንጋ ፈረሶቹ የሚሆነውን ገብስና ገለባ ወደተፈለገው ቦታ ያመጡ ነበር።
29 አምላክም ለሰለሞን እጅግ ታላቅ ጥበብና ማስተዋል እንዲሁም በባሕር ዳርቻ ላይ እንዳለ አሸዋ፣ ሰፊ ልብ* ሰጠው።+ 30 የሰለሞን ጥበብ ከምሥራቅ ሰዎች ሁሉ ጥበብና ከግብፅ ሁሉ ጥበብ የላቀ ነበር።+ 31 እሱም ከማንኛውም ሰው ይልቅ ጥበበኛ ነበር፤ ከዛራዊው ከኤታን+ እንዲሁም የማሆል ልጆች ከሆኑት ከሄማን፣+ ከካልኮል+ እና ከዳርዳ ይልቅ ጥበበኛ ነበር፤ ዝናውም በዙሪያው ባሉት ብሔራት ሁሉ ዘንድ ተሰማ።+ 32 እሱም 3,000 ምሳሌዎችን+ አቀናበረ፤* የመዝሙሮቹም+ ብዛት 1,005 ነበር። 33 በሊባኖስ ከሚገኘው አርዘ ሊባኖስ አንስቶ በቅጥር ላይ እስከሚበቅለው ሂሶጵ+ ድረስ ስለ ዛፎች ተናግሯል፤ እንዲሁም ስለ እንስሳት፣+ ስለ አእዋፍ፣*+ መሬት ለመሬት ስለሚሄዱ ፍጥረታትና*+ ስለ ዓሣዎች ተናግሯል። 34 ስለ እሱ ጥበብ ሲወራ የሰሙ በተለያየ የምድር ክፍል የሚገኙ ነገሥታትን ጨምሮ ከልዩ ልዩ ብሔራት፣ ሰዎች የሰለሞንን ጥበብ ለመስማት ይመጡ ነበር።+
5 የጢሮስ+ ንጉሥ ኪራም ሰለሞን በአባቱ ምትክ ንጉሥ ሆኖ እንደተቀባ ሲሰማ አገልጋዮቹን ወደ እሱ ላከ፤ ምክንያቱም ኪራም ምንጊዜም የዳዊት ወዳጅ ነበር።*+ 2 ሰለሞንም በምላሹ እንዲህ የሚል መልእክት ወደ ኪራም+ ላከ፦ 3 “አባቴ ዳዊት ከተለያየ አቅጣጫ ጦርነት ይከፈትበት ስለነበር ይሖዋ ጠላቶቹን ከእግሩ በታች እስኪያደርግለት ድረስ ለአምላኩ ለይሖዋ ስም የሚሆን ቤት መሥራት እንዳልቻለ በሚገባ ታውቃለህ።+ 4 አሁን ግን አምላኬ ይሖዋ በዙሪያዬ ካሉ ጠላቶቼ ሁሉ እረፍት ሰጥቶኛል።+ የሚቃወመኝም ሆነ እየተፈጸመ ያለ ምንም መጥፎ ነገር የለም።+ 5 በመሆኑም ይሖዋ ለአባቴ ለዳዊት ‘ለስሜ ቤት የሚሠራልኝ በአንተ ምትክ በዙፋንህ ላይ የማስቀምጠው ልጅህ ነው’ ሲል በገባው ቃል መሠረት ለአምላኬ ለይሖዋ ስም ቤት ለመሥራት አስቤአለሁ።+ 6 ስለሆነም አገልጋዮችህ አርዘ ሊባኖስ+ እንዲቆርጡልኝ ትእዛዝ ስጥ። አገልጋዮቼም ከአገልጋዮችህ ጋር ይሠራሉ፤ የአገልጋዮችህንም ደሞዝ አንተ በወሰንከው መሠረት እከፍላለሁ፤ መቼም ከመካከላችን እንደ ሲዶናውያን ዛፍ መቁረጥ የሚችል አንድም ሰው እንደሌለ ታውቃለህ።”+
7 ኪራም የሰለሞንን መልእክት ሲሰማ እጅግ በመደሰቱ “ይህን ታላቅ* ሕዝብ እንዲመራ ለዳዊት ጥበበኛ ልጅ ስለሰጠው ዛሬ ይሖዋ ይወደስ!” አለ።+ 8 ስለዚህ ኪራም እንዲህ የሚል መልእክት ወደ ሰለሞን ላከ፦ “የላክብኝ መልእክት ደርሶኛል። የአርዘ ሊባኖስና የጥድ ሳንቃዎች በማቅረብ ረገድ የፈለግከውን ሁሉ አደርጋለሁ።+ 9 አገልጋዮቼ ሳንቃዎቹን ከሊባኖስ ወደ ባሕሩ ያወርዷቸዋል፤ እኔም በባሕር ላይ ተንሳፈው አንተ ወደምትለኝ ቦታ እንዲደርሱ አንድ ላይ አስሬ እልካቸዋለሁ። እዚያም ሲደርሱ እንዲፈቱ አደርጋለሁ፤ ከዚያ ልትወስዳቸው ትችላለህ። አንተ ደግሞ በምላሹ የጠየቅኩህን ቀለብ ለቤተሰቤ ታቀርባለህ።”+
10 በመሆኑም ኪራም፣ ሰለሞን የፈለገውን ያህል የአርዘ ሊባኖስና የጥድ ሳንቃ አቀረበለት። 11 ሰለሞን ደግሞ ለኪራም ቤተሰብ ቀለብ እንዲሆን 20,000 የቆሮስ መስፈሪያ* ስንዴና 20 የቆሮስ መስፈሪያ ምርጥ የወይራ ዘይት* ለኪራም ሰጠው። ሰለሞን ለኪራም በየዓመቱ ይህን ይሰጠው ነበር።+ 12 ይሖዋም ቃል በገባለት መሠረት ለሰለሞን ጥበብ ሰጠው።+ በኪራምና በሰለሞን መካከል ሰላም ነበር፤ እንዲሁም የስምምነት ውል ተዋዋሉ።*
13 ሰለሞንም ከመላው እስራኤል የግዳጅ ሥራ የሚሠሩ ሰዎችን መለመለ፤ የተመለመሉትም ሰዎች ብዛታቸው 30,000 ነበር።+ 14 እነሱንም በየወሩ አሥር አሥር ሺህ እያደረገ በየተራ ወደ ሊባኖስ ይልካቸው ነበር። እነሱም ለአንድ ወር በሊባኖስ፣ ለሁለት ወር ደግሞ ቤታቸው ይቀመጡ ነበር፤ የግዳጅ ሥራ እንዲሠሩ የተመለመሉት ሰዎች አለቃ አዶኒራም+ ነበር። 15 ሰለሞን በተራሮቹ ላይ 70,000 ተራ የጉልበት ሠራተኞችና* 80,000 ድንጋይ ጠራቢዎች+ ነበሩት፤+ 16 በተጨማሪም ከሰለሞን መኳንንት መካከል አስተዳዳሪዎች+ ሆነው የሚያገለግሉት 3,300 ሰዎች ሠራተኞቹን ይቆጣጠሩ ነበር። 17 የቤቱን መሠረት በተጠረቡ ድንጋዮች ለመጣል+ በንጉሡ ትእዛዝ መሠረት ውድ የሆኑ ትላልቅ ድንጋዮችን+ ፈልፍለው አወጡ።+ 18 ስለዚህ የሰለሞን ግንበኞች፣ የኪራም ግንበኞችና ጌባላውያን+ ድንጋዮቹን ጠረቡ፤ እንዲሁም ቤቱን ለመገንባት የሚያስፈልጉትን ሳንቃዎችና ድንጋዮች አዘጋጁ።
6 እስራኤላውያን* ከግብፅ ምድር በወጡ+ በ480ኛው ዓመት ይኸውም ሰለሞን በእስራኤል ላይ በነገሠ በአራተኛው ዓመት ዚፍ*+ በተባለው በሁለተኛው ወር ሰለሞን የይሖዋን ቤት መሥራት ጀመረ።*+ 2 ንጉሥ ሰለሞን ለይሖዋ የሠራው ቤት ርዝመቱ 60 ክንድ፣* ወርዱ 20 ክንድ፣ ቁመቱ ደግሞ 30 ክንድ ነበር።+ 3 ከቅድስቱ* ፊት ለፊት ያለው በረንዳ+ ርዝመቱ* 20 ክንድ ሲሆን ይህም ከቤቱ ወርድ ጋር እኩል ነው። በረንዳው ከቤቱ አሥር ክንድ ወደ ፊት ወጣ ያለ ነበር።
4 ለቤቱም እየጠበቡ የሚሄዱ ክፈፎች*+ ያሏቸውን መስኮቶች ሠራ። 5 በተጨማሪም በቤቱ ግድግዳ ዙሪያ ተቀጥላ ቤት ሠራ። ቤቱ የተሠራው በቤቱ ግድግዳ ዙሪያ ይኸውም በቤተ መቅደሱና* በውስጠኛው ክፍል+ ግድግዳ ዙሪያ ነበር፤ በዚህ መንገድ በዙሪያው ተቀጥላ ክፍሎችን ሠራ።+ 6 የታችኛው ተቀጥላ ክፍል ወርድ አምስት ክንድ፣ የመካከለኛው ወርድ ስድስት ክንድ፣ የላይኛው ወርድ ደግሞ ሰባት ክንድ ነበር፤ ከቤቱ ግድግዳ ጋር የሚያያዝ ምንም ነገር እንዳይኖር በቤቱ ግድግዳ ዙሪያ ተሸካሚዎችን* ሠርቶ ነበር።+
7 ቤቱ የተገነባው ሁሉ ነገር ባለቀለት ተፈልፍሎ በወጣ ድንጋይ ነበር፤+ በመሆኑም ቤቱ በተገነባበት ጊዜ የመዶሻ ወይም የመጥረቢያ አሊያም የማንኛውም የብረት መሣሪያ ድምፅ ቤቱ ውስጥ አልተሰማም። 8 የታችኛው ተቀጥላ ክፍል መግቢያ የሚገኘው በስተ ደቡብ* በኩል ባለው የቤቱ ጎን ነበር፤+ በተጨማሪም ከታችኛው ወደ መካከለኛው ደርብ እንዲሁም ከመካከለኛው ወደ ላይኛው ደርብ የሚያስወጣ ጠመዝማዛ ደረጃ ነበር። 9 እሱም ቤቱን ገንብቶ አጠናቀቀ፤+ ቤቱንም ከአርዘ ሊባኖስ በተሠሩ ተሸካሚዎችና ርብራቦች ከደነው።+ 10 በቤቱ ዙሪያ እያንዳንዳቸው ቁመታቸው አምስት ክንድ የሆነ ተቀጥላ ክፍሎችን ሠራ፤+ ክፍሎቹም ከቤቱ ጋር በአርዘ ሊባኖስ ሳንቃዎች ተያይዘው ነበር።
11 ይህ በእንዲህ እንዳለ የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ወደ ሰለሞን መጣ፦ 12 “በደንቦቼ ብትሄድ፣ ፍርዶቼን ብትፈጽምና በትእዛዛቴ መሠረት በመሄድ ሁሉንም ብትጠብቃቸው+ እኔም እየገነባህ ያለኸውን ይህን ቤት በተመለከተ ለአባትህ ለዳዊት የገባሁለትን ቃል እፈጽምልሃለሁ፤+ 13 እንዲሁም በእስራኤላውያን መካከል እኖራለሁ፤+ ሕዝቤን እስራኤልንም አልተውም።”+
14 ሰለሞንም ቤቱን ገንብቶ ለማጠናቀቅ የግንባታ ሥራውን ገፋበት። 15 ውስጠኛውን የቤቱን ግድግዳ በአርዘ ሊባኖስ ሳንቃዎች ሠራ። ቤቱንም ከወለሉ አንስቶ እስከ ኮርኒሱ ወራጆች ድረስ በሳንቃ ለበጠ፤ የቤቱንም ወለል በጥድ ጣውላ ለበጠው።+ 16 እንዲሁም ከቤቱ በስተ ኋላ በኩል ከወለሉ አንስቶ እስከ ወራጁ ድረስ በአርዘ ሊባኖስ ሳንቃዎች የተሠራ ባለ 20 ክንድ ክፍል ገነባ፤ በውስጡም፣* የውስጠኛውን ክፍል+ ይኸውም ቅድስተ ቅዱሳኑን+ ሠራ። 17 ከፊቱ ያለው የቤቱ ክፍል ይኸውም ቤተ መቅደሱ*+ 40 ክንድ ነበር። 18 በቤቱ በውስጠኛው በኩል ያለው አርዘ ሊባኖስ የቅሎችና+ የፈኩ አበቦች+ ምስል ተቀርጾበት ነበር። ሙሉ በሙሉ በአርዘ ሊባኖስ የተሠራ ነበር፤ ምንም የሚታይ ድንጋይ አልነበረም።
19 እሱም የይሖዋን የቃል ኪዳን ታቦት+ በዚያ ለማስቀመጥ ቤቱ ውስጥ የውስጠኛውን ክፍል+ አዘጋጀ። 20 ውስጠኛው ክፍል ርዝመቱ 20 ክንድ፣ ወርዱ 20 ክንድ እንዲሁም ቁመቱ 20 ክንድ ነበር፤+ በንጹሕ ወርቅም ለበጠው፤ መሠዊያውንም+ በአርዘ ሊባኖስ ለበጠው። 21 ሰለሞን ቤቱን ከውስጥ በኩል በንጹሕ ወርቅ ለበጠው፤+ በወርቅ በተለበጠው በውስጠኛው ክፍል+ ፊት ለፊትም የወርቅ ሰንሰለት ዘረጋ። 22 ቤቱ ሙሉ በሙሉ እስኪለበጥ ድረስ ቤቱን በሙሉ በወርቅ ለበጠው፤ በውስጠኛው ክፍል አጠገብ ያለውን መሠዊያም+ ሙሉ በሙሉ በወርቅ ለበጠው።
23 በውስጠኛው ክፍል ውስጥ እያንዳንዳቸው አሥር ክንድ ቁመት ያላቸውን+ ሁለት ኪሩቦች+ ከጥድ እንጨት* ሠራ። 24 የኪሩቡ አንድ ክንፍ አምስት ክንድ ሲሆን ሌላኛውም ክንፉ አምስት ክንድ ነበር። ከአንዱ ክንፍ ጫፍ እስከ ሌላው ክንፍ ጫፍ አሥር ክንድ ነበር። 25 ሁለተኛውም ኪሩብ አሥር ክንድ ነበር። ሁለቱ ኪሩቦች ተመሳሳይ መጠንና ቅርጽ ነበራቸው። 26 የአንደኛው ኪሩብ ቁመት አሥር ክንድ ነበር፤ የሌላኛውም ኪሩብ እንደዚሁ ነበር። 27 ከዚያም ኪሩቦቹን+ ውስጠኛው ክፍል* ውስጥ አስቀመጣቸው። የኪሩቦቹም ክንፎች ተዘርግተው ስለነበር የአንደኛው ኪሩብ ክንፍ አንደኛው ግድግዳ ጋ፣ የሌላኛው ኪሩብ ክንፍ ደግሞ ሌላኛው ግድግዳ ጋ ይደርስ ነበር፤ ወደ ቤቱ መሃል የተዘረጉት ክንፎቻቸው ደግሞ ይነካኩ ነበር። 28 ኪሩቦቹንም በወርቅ ለበጣቸው።
29 በቤቱ ግድግዳ ሁሉ ላይ ይኸውም በውስጠኛውና በውጨኛው ክፍሎች ዙሪያ ሁሉ የኪሩቦችን፣+ የዘንባባ ዛፎችንና+ የፈኩ አበቦችን+ ምስል ቀረጸ፤ 30 የቤቱን ወለል ይኸውም የውስጠኛውንም ሆነ የውጨኛውን ክፍሎች ወለል በወርቅ ለበጠው። 31 ለውስጠኛው ክፍል መግቢያ የሚሆኑ በሮችን፣ በጎንና በጎን የሚቆሙ ዓምዶችንና መቃኖችን አንድ አምስተኛ* አድርጎ ከጥድ እንጨት ሠራ። 32 ሁለቱ በሮች ከጥድ እንጨት የተሠሩ ነበሩ፤ በበሮቹም ላይ የኪሩቦችን፣ የዘንባባ ዛፎችንና የፈኩ አበቦችን ምስል ቀረጸባቸው፤ በወርቅም ለበጣቸው፤ ደግሞም ወርቁን በኪሩቦቹና በዘንባባ ዛፎቹ ላይ ጠፈጠፈው። 33 ለቤተ መቅደሱ* መግቢያ የሚሆኑትንና የአንድ አራተኛው* ክፍል የሆኑትን የጥድ እንጨት መቃኖች የሠራው በዚሁ መንገድ ነበር። 34 እሱም ከጥድ እንጨት ሁለት በሮች ሠራ። ሁለት ታጣፊ ሳንቃዎች ያሉት አንዱ በር በመሽከርከሪያዎቹ ላይ፣ ሁለት ታጣፊ ሳንቃዎች ያሉት ሌላኛውም በር በመሽከርከሪያዎቹ ላይ ተገጥሞ ነበር።+ 35 እሱም ኪሩቦችን፣ የዘንባባ ዛፎችንና የፈኩ አበቦችን ምስል ቀረጸ፤ ቅርጾቹንም በወርቅ ለበጣቸው።
36 የውስጠኛውንም ግቢ+ ወደ ላይ በተነባበረ ሦስት ረድፍ ጥርብ ድንጋይና በአንድ ረድፍ የአርዘ ሊባኖስ ሳንቃ ሠራው።+
37 በ4ኛው ዓመት በዚፍ* ወር የይሖዋ ቤት መሠረት ተጣለ፤+ 38 በ11ኛው ዓመት በቡል* ወር (ማለትም በስምንተኛው ወር) የቤቱ እያንዳንዱ ነገር በንድፉ መሠረት ተሠርቶ ተጠናቀቀ።+ በመሆኑም ቤቱን ገንብቶ ለመጨረስ ሰባት ዓመት ፈጀበት።
7 ሰለሞንም የራሱን ቤት*+ ሙሉ በሙሉ ሠርቶ ለማጠናቀቅ 13 ዓመት ፈጀበት።+
2 እሱም የሊባኖስ ደን+ የተባለውን ርዝመቱ 100 ክንድ፣* ወርዱ 50 ክንድ፣ ቁመቱ ደግሞ 30 ክንድ የሆነ ቤት በአራት ረድፍ በተደረደሩ የአርዘ ሊባኖስ ዓምዶች ገነባ፤ በዓምዶቹም ላይ የአርዘ ሊባኖስ ወራጆች+ ነበሩ። 3 ቤቱም በዓምዶቹ ላይ ባረፉት አግዳሚዎች ላይ የተረበረቡ የአርዘ ሊባኖስ ሳንቃዎች ነበሩት፤ ዓምዶቹም* 45 ሲሆኑ በአንዱ ረድፍ ላይ 15 ነበሩ። 4 በሦስት ረድፍ የተሠሩ ባለ ክፈፍ መስኮቶች ነበሩ፤ በሦስቱም ደርቦች ላይ እያንዳንዱ መስኮት ከሌላኛው መስኮት ጋር ትይዩ ነበር። 5 በሦስቱ ደርቦች ላይ ያሉት ትይዩ የሆኑ መስኮቶች ከፊት ለፊት ሲታዩ አራት ማዕዘን እንደሆኑ ሁሉ መግቢያዎቹና መቃኖቹም በሙሉ እንዲሁ ነበሩ።
6 እሱም ርዝመቱ 50 ክንድ፣ ወርዱ ደግሞ 30 ክንድ የሆነ የዓምዶች መተላለፊያ* ሠራ፤ ከፊት ለፊቱም ዓምዶችና ታዛ ያለው በረንዳ ነበር።
7 በተጨማሪም ፍርድ የሚሰጥበትን የዙፋን+ አዳራሽ* ይኸውም የፍርድ+ አዳራሹን ሠራ፤ አዳራሹንም ከወለሉ አንስቶ እስከ ወራጆቹ ድረስ በአርዘ ሊባኖስ ለበጡት።
8 በሌላኛው ግቢ+ ያለው ራሱ የሚኖርበት ቤት* የሚገኘው ከአዳራሹ* ጀርባ ሲሆን አሠራራቸውም ተመሳሳይ ነበር። በተጨማሪም ሰለሞን ላገባት ለፈርዖን ልጅ ከዚህ አዳራሽ ጋር የሚመሳሰል ቤት ሠርቶላት ነበር።+
9 እነዚህ ሁሉ ከውጭ አንስቶ እስከ ትልቁ ግቢ+ ድረስ፣ ከመሠረቱ እስከ ድምድማቱ፣ በውስጥም በውጭም ተለክተው በተጠረቡና በድንጋይ መጋዝ በተቆረጡ ውድ ድንጋዮች የተሠሩ ነበሩ።+ 10 መሠረቱ የተጣለው ውድ በሆኑ ትላልቅ ድንጋዮች ነበር፤ አንዳንዶቹ ድንጋዮች ባለ አሥር ክንድ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ባለ ስምንት ክንድ ነበሩ። 11 በእነዚህም ላይ ተለክተው የተጠረቡ ውድ ድንጋዮችና የአርዘ ሊባኖስ እንጨቶች ነበሩ። 12 ለይሖዋ ቤት ውስጠኛ ግቢና+ ለቤቱ በረንዳ+ እንደተደረገው ሁሉ የትልቁ ግቢ አጥር የተሠራው በሦስት ረድፍ ጥርብ ድንጋይና በአንድ ረድፍ የአርዘ ሊባኖስ ሳንቃ ነበር።
13 ንጉሥ ሰለሞን መልእክተኛ ልኮ ኪራምን+ ከጢሮስ አስመጣው። 14 ኪራም ከንፍታሌም ነገድ የሆነች የአንዲት መበለት ልጅ ነበር፤ አባቱ የጢሮስ ሰው ሲሆን የመዳብ ሥራ ባለሙያ+ ነበር፤ ኪራም ከማንኛውም የመዳብ* ሥራ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ችሎታ፣ ማስተዋልና+ ልምድ ነበረው። በመሆኑም ወደ ንጉሥ ሰለሞን መጥቶ ሥራዎቹን ሁሉ አከናወነለት።
15 እሱም ሁለቱን ዓምዶች+ ከቀለጠ መዳብ ሠራ፤ እያንዳንዱም ዓምድ ቁመቱ 18 ክንድ ነበር፤ ሁለቱ ዓምዶች እያንዳንዳቸው በመለኪያ ገመድ ሲለኩ መጠነ ዙሪያቸው 12 ክንድ ነበር።+ 16 እንዲሁም በዓምዶቹ አናት ላይ የሚሆኑ ሁለት የዓምድ ራሶችን ከመዳብ ሠራ። የአንደኛው የዓምድ ራስ ቁመት አምስት ክንድ የሌላኛው የዓምድ ራስ ቁመትም አምስት ክንድ ነበር። 17 በእያንዳንዱ ዓምድ አናት ላይ ያለው የዓምድ ራስ በሰንሰለት ጉንጉን የተሠሩ መረቦች ነበሩት፤+ በአንደኛው የዓምድ ራስ ላይ ሰባት በሌላኛው የዓምድ ራስ ላይም ሰባት ነበሩ። 18 በዓምዶቹ አናት ላይ ያሉትን የዓምድ ራሶች ለማስጌጥ በአንደኛው መረብ ዙሪያ ሮማኖችን በሁለት ረድፍ ሠራ፤ በሁለቱም የዓምድ ራሶች ላይ እንዲሁ አደረገ። 19 በረንዳው አጠገብ በሚገኙት ዓምዶች አናት ላይ ያሉት የዓምድ ራሶች አራት ክንድ ቁመት ያለው የአበባ ቅርጽ ነበራቸው። 20 የዓምድ ራሶቹ በሁለቱ ዓምዶች ላይ፣ ልክ ከመረብ ሥራው ቀጥሎ ካለው ከሆዱ በላይ ነበሩ፤ በእያንዳንዱ የዓምድ ራስ ዙሪያ 200 ሮማኖች በረድፍ ተደርድረው ነበር።+
21 እሱም የቤተ መቅደሱን* በረንዳ ዓምዶች አቆመ።+ በስተ ቀኝ* ያለውን ዓምድ አቁሞ ያኪን* ብሎ ሰየመው፤ ከዚያም በስተ ግራ* ያለውን ዓምድ አቁሞ ቦዔዝ* ብሎ ሰየመው።+ 22 የዓምዶቹም አናቶች የአበባ ቅርጽ ነበራቸው። በዚህ መንገድ የዓምዶቹ ሥራ ተጠናቀቀ።
23 ከዚያም ባሕሩን* በቀለጠ ብረት ሠራ።+ ባሕሩ ክብ ቅርጽ የነበረው ሲሆን ከአንዱ ጠርዝ እስከ ሌላኛው ጠርዝ 10 ክንድ፣ ከፍታው ደግሞ 5 ክንድ ነበር፤ መጠነ ዙሪያውም በመለኪያ ገመድ ሲለካ 30 ክንድ ሆነ።+ 24 በባሕሩም ዙሪያ ከጠርዙ ዝቅ ብሎ በእያንዳንዱ ክንድ ላይ በቅል ቅርጽ+ የተሠሩ አሥር ጌጦች ነበሩ፤ ቅሎቹም በሁለት ረድፍ ከባሕሩ ጋር አንድ ወጥ ሆነው ተሠርተው ነበር። 25 ባሕሩ 3ቱ ወደ ሰሜን፣ 3ቱ ወደ ምዕራብ፣ 3ቱ ወደ ደቡብ እንዲሁም 3ቱ ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ ፊታቸውን ባደረጉ 12 በሬዎች+ ላይ ተቀምጦ ነበር፤ ባሕሩም ላያቸው ላይ ነበር፤ የሁሉም ሽንጥ ወደ መሃል ገባ ያለ ነበር። 26 የውኃ ማጠራቀሚያው ውፍረት አንድ ጋት* ነበር፤ ጠርዙ የጽዋ ከንፈር ይመስል የነበረ ሲሆን በአበባ ቅርጽ የተሠራ ነበር። የውኃ ማጠራቀሚያውም 2,000 የባዶስ መስፈሪያ* ይይዝ ነበር።
27 ከዚያም አሥር የዕቃ ማጓጓዣ ጋሪዎችን*+ ከመዳብ ሠራ። እያንዳንዱ ጋሪ ርዝመቱ አራት ክንድ፣ ወርዱ አራት ክንድ፣ ቁመቱ ደግሞ ሦስት ክንድ ነበር። 28 የጋሪዎቹ አሠራር እንዲህ ነበር፦ ጋሪዎቹ የጎን መከለያ ነበራቸው፤ የጎን መከለያዎቹም በፍርግርግ መካከል ነበሩ። 29 በፍርግርጎቹ መሃል በነበሩት የጎን መከለያዎች ላይ የአንበሶች፣+ የበሬዎችና የኪሩቦች+ ምስል ነበር፤ በፍርግርጎቹም ላይ እንዲሁ ዓይነት ምስል ነበር። ከአንበሶቹና ከበሬዎቹ በላይና በታች፣ የተንጠለጠሉ የአበባ ጉንጉኖች የሚመስሉ ቅርጾች ነበሩ። 30 እያንዳንዱ የዕቃ ማጓጓዣ ጋሪ አራት የመዳብ መንኮራኩሮችና* የመዳብ ዘንጎች ነበሩት፤ በአራቱ ማዕዘኖች ላይ ያሉት ቋሚዎች ደግሞ ድጋፍ ይሆኗቸው ነበር። ድጋፎቹ ከገንዳው በታች ነበሩ፤ እያንዳንዳቸውም በጎናቸው ወጥ ሆኖ የተሠራ የአበባ ጉንጉን የሚመስል ቅርጽ ነበራቸው። 31 የገንዳው አፍ ያለው በጋሪው አናት ውስጥ ሲሆን አንድ ክንድ ከፍታ ነበረው፤ የጋሪው አፍ ክብ ነበር፤ በአፉ ላይ ያለው ማስቀመጫ አንድ ክንድ ተኩል ከፍታ ነበረው፤ በአፉም ላይ የተቀረጹ ምስሎች ነበሩ። የጎን መከለያዎቹም አራት ማዕዘን እንጂ ክብ አልነበሩም። 32 አራቱ መንኮራኩሮች ከጎን መከለያዎቹ በታች ነበሩ፤ የመንኮራኩሮቹ ድጋፎች ከጋሪው ጋር ተያይዘው ነበር፤ የእያንዳንዱ መንኮራኩር ቁመት አንድ ክንድ ተኩል ነበር። 33 የመንኮራኩሮቹ አሠራር ከሠረገላ መንኮራኩር* አሠራር ጋር ተመሳሳይ ነበር። የመንኮራኩሮቹ ድጋፎች፣ ክፈፎች፣* ራጂዎችና አቃፊዎች ሁሉ ከቀለጠ ብረት የተሠሩ ነበሩ። 34 በእያንዳንዱ ጋሪ አራት ማዕዘኖች ላይ አራት ድጋፎች ነበሩ፤ ድጋፎቹም የጋሪው ክፍል ሆነው* የተሠሩ ነበሩ። 35 በጋሪው አናት ላይ ቁመቱ ግማሽ ክንድ የሆነ ክብ ክፈፍ ነበር፤ እንዲሁም በጋሪው አናት ላይ የሚገኙት ፍርግርጎችና የጎን መከለያዎች የጋሪው ክፍል ሆነው* የተሠሩ ነበሩ። 36 በፍርግርጎቹና በጎን መከለያዎቹም ላይ እንደ ስፋታቸው ኪሩቦችን፣ አንበሶችንና የዘንባባ ዛፍ ምስሎችን ቀረጸባቸው፤ ዙሪያውንም የአበባ ጉንጉን ምስል ሠራበት።+ 37 አሥሩን ጋሪዎች+ የሠራው በዚህ መንገድ ነበር፤ ሁሉም አንድ ዓይነት መጠንና ቅርጽ እንዲኖራቸው ተደርገው በተመሳሳይ መንገድ ቀልጠው የተሠሩ ነበሩ።+
38 እሱም አሥር የመዳብ ገንዳዎችን+ ሠራ፤ እያንዳንዱ ገንዳ 40 የባዶስ መስፈሪያ ይይዝ ነበር። እያንዳንዱ ገንዳ አራት ክንድ ነበር።* በአሥሩም ጋሪዎች ላይ አንድ አንድ ገንዳ ነበር። 39 ከዚያም አምስቱን ጋሪዎች ከቤቱ በስተ ቀኝ በኩል አምስቱን ጋሪዎች ደግሞ ከቤቱ በስተ ግራ በኩል አደረጋቸው፤ ባሕሩንም ከቤቱ በስተ ቀኝ በኩል፣ በስተ ደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ አስቀመጠው።+
40 በተጨማሪም ኪራም+ ገንዳዎቹን፣ አካፋዎቹንና+ ጎድጓዳ ሳህኖቹን+ ሠራ።
ኪራምም በይሖዋ ቤት ለንጉሥ ሰለሞን ያከናውን የነበረውን ሥራ ሁሉ ጨረሰ።+ የሠራቸውም ነገሮች እነዚህ ነበሩ፦ 41 ሁለቱ ዓምዶች፣+ በሁለቱ ዓምዶች አናት ላይ የነበሩት የጎድጓዳ ሳህን ቅርጽ ያላቸው የዓምድ ራሶች፣ በዓምዶቹ አናት ላይ የነበሩትን የጎድጓዳ ሳህን ቅርጽ ያላቸውን ሁለቱን ክብ የዓምድ ራሶች የሚያስጌጡት ሁለት መረቦች፣+ 42 ለሁለቱ መረቦች የተሠሩት 400 ሮማኖች+ ማለትም በሁለቱ ዓምዶች አናት ላይ የነበሩትን የጎድጓዳ ሳህን ቅርጽ ያላቸው የዓምድ ራሶች ለማስጌጥ የተሠሩት በእያንዳንዱ መረብ ላይ በሁለት ረድፍ የተደረደሩት ሮማኖች፣ 43 አሥሩ ጋሪዎችና+ በጋሪዎቹ ላይ የነበሩት አሥር የውኃ ገንዳዎች፣+ 44 ባሕሩና+ ከሥሩ የነበሩት 12 በሬዎች፣ 45 አመድ ማጠራቀሚያዎቹ፣ አካፋዎቹ፣ ጎድጓዳ ሳህኖቹና ኪራም ለይሖዋ ቤት እንዲሆኑ ለንጉሥ ሰለሞን ከተወለወለ መዳብ የሠራቸው ዕቃዎች በሙሉ። 46 ንጉሡ እነዚህ ነገሮች በዮርዳኖስ አውራጃ በሱኮትና በጻረታን መካከል በሚገኝ ስፍራ ከሸክላ በተሠሩ ቅርጽ ማውጫዎች ውስጥ ቀልጠው እንዲሠሩ አደረገ።
47 ሰለሞን ዕቃዎቹ ሁሉ እንዲመዘኑ አላደረገም፤ ምክንያቱም ዕቃዎቹ እጅግ ብዙ ነበሩ። የመዳቡ ክብደት ምን ያህል እንደሆነ አልታወቀም።+ 48 ሰለሞንም ለይሖዋ ቤት መገልገያ የሚሆኑትን የሚከተሉትን ነገሮች ሠራ፦ የወርቅ መሠዊያውን፣+ ገጸ ኅብስት የሚቀመጥበትን የወርቅ ጠረጴዛ፣+ 49 በውስጠኛው ክፍል ፊት በቀኝና በግራ የሚቀመጡትን ከንጹሕ ወርቅ የተሠሩ+ አምስት አምስት መቅረዞች፣+ ከወርቅ የተሠሩትን የፈኩ አበቦች፣+ መብራቶችና መቆንጠጫዎች፣ 50 ከንጹሕ ወርቅ የተሠሩትን ሳህኖች፣ የእሳት ማጥፊያዎች፣+ ጎድጓዳ ሳህኖች፣ ጽዋዎችና+ መኮስተሪያዎች+ እንዲሁም ከወርቅ የተሠሩትን የውስጠኛው ክፍል+ ማለትም የቅድስተ ቅዱሳኑ በሮችና የመቅደሱ በሮች+ የሚሽከረከሩባቸውን መቆሚያዎች።
51 በዚህ ሁኔታ ንጉሥ ሰለሞን ከይሖዋ ቤት ጋር በተያያዘ መሥራት የሚገባውን ሥራ በሙሉ አጠናቀቀ። ከዚያም ሰለሞን አባቱ ዳዊት የቀደሳቸውን ነገሮች ወደዚያ አስገባ፤+ ብሩን፣ ወርቁንና ዕቃዎቹን በይሖዋ ቤት ግምጃ ቤቶች ውስጥ አስቀመጠ።+
8 በዚህ ጊዜ ሰለሞን የእስራኤልን ሽማግሌዎች፣ የነገዶቹን መሪዎች ሁሉና የእስራኤልን የአባቶች ቤት አለቆች+ ሰበሰበ።+ እነሱም የይሖዋን የቃል ኪዳን ታቦት ከዳዊት ከተማ+ ማለትም ከጽዮን+ ለማምጣት በኢየሩሳሌም ወዳለው ወደ ንጉሥ ሰለሞን መጡ። 2 የእስራኤል ሰዎች በሙሉ በሰባተኛው ወር ማለትም በኤታኒም* ወር በሚከበረው በዓል* ላይ ንጉሥ ሰለሞን ፊት ተሰበሰቡ።+ 3 የእስራኤል ሽማግሌዎችም በሙሉ መጡ፤ ካህናቱም ታቦቱን አነሱ።+ 4 የይሖዋን ታቦት፣ የመገናኛ ድንኳኑንና+ በድንኳኑ ውስጥ የነበሩትን ቅዱስ ዕቃዎች በሙሉ አመጡ። እነዚህንም ያመጡት ካህናቱና ሌዋውያኑ ናቸው። 5 ንጉሥ ሰለሞንና ወደ እሱ እንዲመጣ የተጠራው መላው የእስራኤል ማኅበረሰብ ታቦቱ ፊት ነበሩ። ከብዛታቸው የተነሳ ሊቆጠሩ የማይችሉ ብዙ በጎችና ከብቶች መሥዋዕት ሆነው ቀረቡ።+
6 ከዚያም ካህናቱ የይሖዋን የቃል ኪዳን ታቦት አምጥተው ቦታው+ ላይ ማለትም በቤቱ ውስጠኛ ክፍል ይኸውም በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ ከኪሩቦቹ ክንፎች በታች አስቀመጡት።+
7 የኪሩቦቹ ክንፎች ታቦቱ ባለበት ቦታ ላይ ተዘርግተው ስለነበር ኪሩቦቹ ታቦቱንና መሎጊያዎቹን ከላይ ከልለዋቸው ነበር።+ 8 መሎጊያዎቹ+ ረጅም ስለነበሩ የመሎጊያዎቹን ጫፎች ከውስጠኛው ክፍል ፊት ለፊት ባለው በቅድስቱ ውስጥ ሆኖ ማየት ይቻል ነበር፤ ከውጭ ግን አይታዩም ነበር። እስከ ዛሬም ድረስ እዚያው ይገኛሉ። 9 የእስራኤል ሰዎች ከግብፅ ምድር ሲወጡ+ ይሖዋ ከእነሱ ጋር ቃል ኪዳን በገባበት ጊዜ+ ሙሴ በኮሬብ ታቦቱ ውስጥ ካስቀመጣቸው+ ከሁለቱ የድንጋይ ጽላቶች+ በስተቀር በታቦቱ ውስጥ ምንም አልነበረም።
10 ካህናቱ ከቅዱሱ ስፍራ በወጡ ጊዜ ደመናው+ የይሖዋን ቤት ሞላው።+ 11 የይሖዋ ክብር የይሖዋን ቤት ሞልቶት ስለነበር ካህናቱ ከደመናው የተነሳ በዚያ ቆመው ማገልገል አልቻሉም።+ 12 በዚህ ጊዜ ሰለሞን እንዲህ አለ፦ “ይሖዋ በድቅድቅ ጨለማ+ ውስጥ እንደሚኖር ተናግሯል። 13 እኔም እጅግ ከፍ ያለ ቤት፣ ለዘላለም የምትኖርበት ጸንቶ የተመሠረተ ቦታ+ ገንብቼልሃለሁ።”
14 ከዚያም መላው የእስራኤል ጉባኤ ቆሞ ሳለ ንጉሡ ዞሮ የእስራኤልን ጉባኤ ሁሉ መባረክ ጀመረ።+ 15 እንዲህም አለ፦ “ለአባቴ ለዳዊት በገዛ አፉ እንዲህ ብሎ ቃል የገባውና ይህን በራሱ እጅ የፈጸመው የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ይወደስ፦ 16 ‘ሕዝቤን እስራኤልን ከግብፅ ካወጣሁበት ዕለት አንስቶ ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ መካከል ስሜ የሚጠራበት ቤት እንዲሠራበት አንድም ከተማ አልመረጥኩም፤+ ዳዊትን ግን በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ገዢ እንዲሆን መረጥኩ።’ 17 አባቴ ዳዊት ለእስራኤል አምላክ ለይሖዋ ስም ቤት ለመሥራት ከልቡ ተመኝቶ ነበር።+ 18 ሆኖም ይሖዋ አባቴን ዳዊትን እንዲህ አለው፦ ‘ለስሜ ቤት ለመሥራት ከልብህ ተመኝተህ ነበር፤ ይህን በልብህ መመኘትህም መልካም ነው። 19 ይሁንና ቤቱን የምትሠራው አንተ አይደለህም፤ ሆኖም ለስሜ ቤት የሚሠራልኝ የሚወለድልህ የገዛ ልጅህ* ይሆናል።’+ 20 ይሖዋ የገባውን ቃል ፈጽሟል፤ ልክ ይሖዋ ቃል በገባው መሠረት አባቴን ዳዊትን ተክቼ በእስራኤል ዙፋን ላይ ተቀምጫለሁና። በተጨማሪም ለእስራኤል አምላክ ለይሖዋ ስም ቤት ሠርቻለሁ፤+ 21 እንዲሁም አባቶቻችንን ከግብፅ ምድር ባወጣቸው ጊዜ ይሖዋ ከእነሱ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን የያዘው ታቦት+ የሚያርፍበትን ቦታ በዚያ አዘጋጅቻለሁ።”
22 ከዚያም ሰለሞን በይሖዋ መሠዊያ ፊት፣ በመላው የእስራኤል ጉባኤ ፊት ለፊት ቆሞ እጆቹን ወደ ሰማይ ዘረጋ፤+ 23 እንዲህም አለ፦ “የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ሆይ፣ በፊቱ በሙሉ ልባቸው ለሚመላለሱ+ አገልጋዮቹ ቃል ኪዳኑን የሚጠብቅና ታማኝ ፍቅር+ የሚያሳይ እንደ አንተ ያለ አምላክ በላይ በሰማይም ሆነ በታች በምድር የለም።+ 24 ለአገልጋይህ ለአባቴ ለዳዊት የገባኸውን ቃል ጠብቀሃል። በገዛ አፍህ ቃል ገባህ፤ ዛሬ ደግሞ በራስህ እጅ ፈጸምከው።+ 25 አሁንም የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ሆይ ‘አንተ በፊቴ እንደተመላለስከው ሁሉ ልጆችህም በጥንቃቄ በፊቴ ከተመላለሱ ከዘርህ በእስራኤል ዙፋን ላይ የሚቀመጥ ሰው ከፊቴ ፈጽሞ አይታጣም’ በማለት ለአገልጋይህ ለአባቴ ለዳዊት የገባኸውን ቃል ጠብቅ።+ 26 አሁንም የእስራኤል አምላክ ሆይ፣ እባክህ ለአገልጋይህ ለአባቴ ለዳዊት የገባኸው ቃል ይፈጸም።
27 “በእርግጥ አምላክ በምድር ላይ ይኖራል?+ እነሆ ሰማያት፣ አዎ ሰማየ ሰማያት እንኳ ሊይዙህ አይችሉም፤+ ታዲያ እኔ የሠራሁት ይህ ቤትማ ምንኛ ያንስ!+ 28 እንግዲህ አምላኬ ይሖዋ ሆይ፣ የአገልጋይህን ጸሎትና ሞገስ ለማግኘት የሚያቀርበውን ልመና በትኩረት ስማ፤ አገልጋይህ እርዳታ ለማግኘት የሚያሰማውን ጩኸትና በዛሬው ዕለት በፊትህ የሚያቀርበውን ጸሎት አዳምጥ። 29 አገልጋይህ ወደዚህ ስፍራ የሚያቀርበውን ጸሎት ለመስማት ‘ስሜ በዚያ ይሆናል’+ ወዳልከው ወደዚህ ቤት ዓይኖችህ ቀንና ሌሊት ይመልከቱ።+ 30 አገልጋይህ ሞገስ ለማግኘት የሚያቀርበውን ልመናና ሕዝብህ እስራኤል ወደዚህ ስፍራ በመጸለይ የሚያቀርበውን ልመና አዳምጥ፤ በሰማያት ባለው ማደሪያህ ሆነህ ስማ፤+ ሰምተህም ይቅር በል።+
31 “አንድ ሰው ባልንጀራውን በድሎ እንዲምል ቢደረግ፣* በመሐላውም* ተጠያቂ ቢሆን፣ በዳዩም በዚህ መሐላ* ሥር ሆኖ እዚህ ቤት ውስጥ ባለው መሠዊያህ ፊት ቢቀርብ፣+ 32 አንተ በሰማያት ሆነህ ስማ፤ ክፉውን ጥፋተኛ* በማለትና እንደ ሥራው በመመለስ፣ ጻድቁንም ንጹሕ* መሆኑን በማሳወቅና እንደ ጽድቁ ወሮታውን በመክፈል እርምጃ ውሰድ፤ አገልጋዮችህንም ዳኝ።+
33 “ሕዝብህ እስራኤላውያን አንተን ከመበደላቸው የተነሳ በጠላት ድል ቢነሱና+ ወደ አንተ ተመልሰው ስምህን ቢያወድሱ+ እንዲሁም በዚህ ቤት ወደ አንተ ቢጸልዩና ሞገስ ለማግኘት ልመና ቢያቀርቡ+ 34 ከሰማያት ሆነህ ስማ፤ የሕዝብህንም የእስራኤልን ኃጢአት ይቅር በል፤ ለአባቶቻቸው ወደሰጠኸው ምድርም መልሳቸው።+
35 “ሕዝቡ አንተን በመበደሉ የተነሳ+ ሰማያት ተዘግተው ዝናብ ቢጠፋ፣+ እነሱም አንተ ስላዋረድካቸው* ወደዚህ ስፍራ ቢጸልዩና ስምህን ቢያወድሱ እንዲሁም ከኃጢአታቸው ቢመለሱ+ 36 ከሰማያት ሆነህ ስማ፤ የአገልጋዮችህን፣ የሕዝብህን የእስራኤላውያንን ኃጢአት ይቅር በል፤ ስለሚሄዱበት ቀና መንገድ ታስተምራቸዋለህና፤+ ለሕዝብህ ርስት አድርገህ ባወረስከው ምድርህም ላይ ዝናብ አዝንብ።+
37 “በምድሪቱ ላይ ረሃብ+ ወይም ቸነፈር፣ የሚለበልብና የሚያደርቅ ነፋስ ወይም ዋግ+ ቢከሰት፣ የአንበጣ መንጋ ወይም የማይጠግብ አንበጣ* ቢመጣ አሊያም ጠላቶቻቸው በምድሪቱ ላይ ባለ በየትኛውም ከተማ* ውስጥ ሳሉ ቢከቧቸው ወይም ደግሞ ማንኛውም ዓይነት መቅሰፍት አሊያም ማንኛውም ዓይነት በሽታ ቢከሰትና+ 38 ማንኛውም ሰው ወይም ሕዝብህ እስራኤል በሙሉ (እያንዳንዱ የልቡን ጭንቀት ያውቃልና)+ ወደ አንተ ለመጸለይ ወይም ሞገስ እንድታሳየው ልመና+ ለማቅረብ እጁን ወደዚህ ቤት ቢዘረጋ 39 አንተ ከመኖሪያ ቦታህ+ ከሰማያት ሆነህ ስማ፤ ደግሞም ይቅር በል፤+ እርምጃም ውሰድ፤ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው ብድራቱን ክፈለው፤+ ምክንያቱም አንተ ልቡን ታውቃለህ (የሰውን ልብ በሚገባ የምታውቀው አንተ ብቻ ነህ)፤+ 40 ይህም ለአባቶቻችን በሰጠኸው ምድር ላይ በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ አንተን እንዲፈሩ ነው።
41 “በተጨማሪም ከሕዝብህ ከእስራኤል ወገን ያልሆነ የባዕድ አገር ሰው በስምህ* የተነሳ ከሩቅ አገር ቢመጣ፣+ 42 (መቼም ስለ ታላቁ ስምህ፣+ ስለ ኃያሉ እጅህና ስለተዘረጋው ክንድህ መስማታቸው አይቀርም) ወደዚህም ቤት መጥቶ ቢጸልይ 43 ከመኖሪያ ቦታህ ከሰማያት+ ሆነህ ስማ፤ የምድር ሕዝቦች ሁሉ እንደ ሕዝብህ እንደ እስራኤል ስምህን እንዲያውቁና እንዲፈሩህ+ እንዲሁም ስምህ እኔ በሠራሁት በዚህ ቤት እንደሚጠራ እንዲያውቁ ያ የባዕድ አገር ሰው የጠየቀህን ሁሉ ፈጽምለት።
44 “ሕዝብህ ጠላቶቻቸውን ለመውጋት አንተ በምትልካቸው መንገድ ለጦርነት ቢወጡና+ አንተ ወደመረጥከው ከተማ+ እንዲሁም ለስምህ ወደሠራሁት ቤት አቅጣጫ+ ወደ ይሖዋ ቢጸልዩ+ 45 ከሰማያት ሆነህ ጸሎታቸውንና ሞገስ ለማግኘት የሚያቀርቡትን ልመና ስማ፤ ፍረድላቸውም።
46 “በአንተ ላይ ኃጢአት ቢሠሩ (መቼም ኃጢአት የማይሠራ ሰው የለም)፣+ አንተም በእነሱ እጅግ ተቆጥተህ ለጠላት አሳልፈህ ብትሰጣቸው፣ ጠላቶቻቸውም ራቅ ወዳለ ወይም ቅርብ ወደሆነ የጠላት ምድር ምርኮኛ አድርገው ቢወስዷቸው+ 47 እነሱም በምርኮ በተወሰዱበት ምድር ወደ ልቦናቸው ቢመለሱና+ ወደ አንተ ዞር በማለት+ ‘ኃጢአት ሠርተናል፤ አጥፍተናል፤ ክፉ ድርጊትም ፈጽመናል’+ በማለት በተማረኩበት ምድር+ ሆነው ሞገስ ለማግኘት ወደ አንተ ልመና ቢያቀርቡ፣ 48 ማርከው በወሰዷቸው ጠላቶቻቸውም ምድር ሆነው በሙሉ ልባቸውና በሙሉ ነፍሳቸው* ወደ አንተ ቢመለሱ+ እንዲሁም ለአባቶቻቸው በሰጠሃቸው ምድር፣ አንተ በመረጥካት ከተማና ለስምህ በሠራሁት ቤት አቅጣጫ ወደ አንተ ቢጸልዩ+ 49 ጸሎታቸውንና ሞገስ ለማግኘት ያቀረቡትን ልመና ከመኖሪያ ቦታህ ከሰማያት ሆነህ+ ስማ፤ ፍረድላቸውም፤ 50 በአንተ ላይ የፈጸሙትን በደል ሁሉ ይቅር በማለት በአንተ ላይ ኃጢአት የሠራውን ሕዝብህን ይቅር በል። የማረኳቸውም ሰዎች እንዲያዝኑላቸው ታደርጋለህ፤ እነሱም ያዝኑላቸዋል+ 51 (ምክንያቱም እነሱ እንደ ብረት ማቅለጫ+ ከሆነችው ከግብፅ ያወጣሃቸው+ ሕዝቦችህና ርስትህ+ ናቸው)። 52 አገልጋይህም ሆነ ሕዝብህ እስራኤል ወደ አንተ በሚጮኹበት ጊዜ ሁሉ ስማቸው፤ ሞገስ ለማግኘት የሚያቀርቡትንም ልመና+ ዓይኖችህ ይመልከቱ።+ 53 ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ አባቶቻችንን ከግብፅ ባወጣሃቸው ጊዜ በአገልጋይህ በሙሴ በኩል በተናገርከው መሠረት ከምድር ሕዝቦች ሁሉ መካከል ርስትህ አድርገህ ለይተሃቸዋልና።”+
54 ሰለሞንም ይህን ሁሉ ጸሎትና ልመና ወደ ይሖዋ አቅርቦ እንደጨረሰ እጆቹን ወደ ሰማይ ዘርግቶ ከተንበረከከበት ከይሖዋ መሠዊያ ፊት ተነሳ።+ 55 ከዚያም ቆሞ የእስራኤልን ጉባኤ በሙሉ ጮክ ብሎ እንዲህ ሲል ባረከ፦ 56 “በገባው ቃል መሠረት ለሕዝቡ ለእስራኤል የእረፍት ቦታ የሰጠው ይሖዋ ይወደስ።+ በአገልጋዩ በሙሴ አማካኝነት ከሰጠው መልካም ተስፋ ሁሉ መካከል ሳይፈጸም የቀረ አንድም ቃል የለም።+ 57 አምላካችን ይሖዋ ከአባቶቻችን ጋር እንደነበረ ሁሉ ከእኛም ጋር ይሁን።+ አይተወን፤ ደግሞም አይጣለን።+ 58 በመንገዱ ሁሉ እንድንሄድ እንዲሁም አባቶቻችን እንዲጠብቁ ያዘዛቸውን ትእዛዛቱን፣ ሥርዓቱንና ድንጋጌዎቹን እንድንጠብቅ ልባችንን ወደ እሱ ያዘንብል።+ 59 ሞገስ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ያቀረብኩት ይህ ልመና በአምላካችን በይሖዋ ፊት ቀንና ሌሊት ይታወስ፤ ለአገልጋዩና ለሕዝቡ ለእስራኤልም በየዕለቱ የሚያስፈልገውን ፍርድ ይፍረድላቸው፤ 60 ይህም የምድር ሕዝቦች ሁሉ እውነተኛው አምላክ ይሖዋ መሆኑን እንዲያውቁ ነው።+ ከእሱ ሌላ ማንም የለም!+ 61 በመሆኑም እንደ ዛሬው ዕለት ሁሉ በአምላካችን በይሖዋ ሥርዓቶች በመሄድና ትእዛዛቱን በመጠበቅ ልባችሁ በእሱ ዘንድ ሙሉ ይሁን።”*+
62 ከዚያም ንጉሡና ከእሱ ጋር የነበሩት እስራኤላውያን በሙሉ በይሖዋ ፊት ታላቅ መሥዋዕት አቀረቡ።+ 63 ሰለሞን 22,000 ከብቶችና 120,000 በጎች ለይሖዋ የኅብረት መሥዋዕት+ አድርጎ አቀረበ። በዚህ መንገድ ንጉሡና እስራኤላውያን በሙሉ የይሖዋን ቤት መረቁ።+ 64 ንጉሡም በዚያ ቀን በይሖዋ ቤት ፊት የሚገኘውን የግቢውን መሃል መቀደስ አስፈልጎት ነበር፤ ምክንያቱም የሚቃጠሉትን መሥዋዕቶች፣ የእህል መባዎቹንና የኅብረት መሥዋዕቶቹን በዚያ ማቅረብ ነበረበት፤ ይህም የሆነው በይሖዋ ፊት ያለው የመዳብ መሠዊያ+ የሚቃጠሉትን መሥዋዕቶች፣ የእህል መባዎቹንና የኅብረት መሥዋዕቶቹን ስብ+ መያዝ ስላልቻለ ነው። 65 በዚያ ጊዜ ሰለሞን ከመላው እስራኤል ጋር ይኸውም ከሌቦሃማት* አንስቶ እስከ ግብፅ ደረቅ ወንዝ*+ ድረስ ካለው ምድር ከመጣው ታላቅ ጉባኤ ጋር በመሆን በአምላካችን በይሖዋ ፊት ለ7 ቀን፣ ከዚያም ለተጨማሪ 7 ቀን በአጠቃላይ ለ14 ቀን በዓሉን አከበረ።+ 66 በቀጣዩም* ቀን ሕዝቡን አሰናበተ፤ እነሱም ንጉሡን ባረኩ፤ ይሖዋ ለአገልጋዩ ለዳዊትና ለሕዝቡ ለእስራኤል ባሳየው ጥሩነት ሁሉ እየተደሰቱና ከልባቸው እየፈነደቁ+ ወደየቤታቸው ሄዱ።
9 ሰለሞን የይሖዋን ቤትና የንጉሡን ቤት*+ እንዲሁም ለመሥራት የፈለገውን ነገር ሁሉ ገንብቶ እንደጨረሰ+ 2 ይሖዋ በገባኦን እንደተገለጠለት አሁንም ለሁለተኛ ጊዜ ተገለጠለት።+ 3 ይሖዋም እንዲህ አለው፦ “በፊቴ የጸለይከውን ጸሎትና ሞገስ ለማግኘት ያቀረብከውን ልመና ሰምቻለሁ። የገነባኸውን ይህን ቤት ስሜ ለዘለቄታው እንዲጠራበት በማድረግ+ ቀድሼዋለሁ፤ ዓይኔም ሆነ ልቤ ሁልጊዜ በዚያ ይሆናል።+ 4 አንተም አባትህ ዳዊት እንዳደረገው ያዘዝኩህን ሁሉ በመፈጸም+ በንጹሕ ልብና+ በቅንነት+ በፊቴ ብትሄድ+ እንዲሁም ሥርዓቶቼንና ፍርዴን ብትጠብቅ+ 5 ለአባትህ ለዳዊት ‘ከዘር ሐረግህ በእስራኤል ዙፋን ላይ የሚቀመጥ ሰው አይታጣም’ በማለት በገባሁለት ቃል መሠረት የመንግሥትህን ዙፋን በእስራኤል ላይ ለዘላለም አጸናለሁ።+ 6 ሆኖም እናንተም ሆናችሁ ልጆቻችሁ እኔን ከመከተል ዞር ብትሉ እንዲሁም በፊታችሁ ያስቀመጥኳቸውን ትእዛዛቴንና ደንቦቼን ባትጠብቁ፣ ሄዳችሁም ሌሎች አማልክትን ብታገለግሉና ለእነሱ ብትሰግዱ+ 7 እስራኤላውያንን ከሰጠኋቸው ምድር ላይ አጠፋቸዋለሁ፤+ ለስሜ የቀደስኩትንም ቤት ከፊቴ አስወግደዋለሁ፤+ እስራኤላውያንም በሕዝቦች ሁሉ ዘንድ መቀለጃና* መሳለቂያ ይሆናሉ።+ 8 ይህም ቤት የፍርስራሽ ክምር ይሆናል።+ በዚያም የሚያልፉ ሰዎች ሁሉ በመገረም ትኩር ብለው እየተመለከቱ ‘ይሖዋ በዚህች ምድርና በዚህ ቤት ላይ እንዲህ ያለ ነገር ያደረገው ለምንድን ነው?’+ በማለት ያፏጫሉ። 9 ከዚያም እንዲህ ይላሉ፦ ‘ይህ የደረሰባቸው አባቶቻቸውን ከግብፅ ምድር ያወጣውን አምላካቸውን ይሖዋን ትተው ሌሎች አማልክትን ስለተከተሉና ለእነሱ ስለሰገዱ እንዲሁም እነሱን ስላገለገሉ ነው። ይሖዋ ይህን ሁሉ መከራ ያመጣባቸው ለዚህ ነው።’”+
10 ሰለሞን ሁለቱን ቤቶች ይኸውም የይሖዋን ቤትና የንጉሡን ቤት* ገንብቶ በጨረሰበት በ20ኛው ዓመት ማብቂያ ላይ+ 11 የጢሮስ ንጉሥ ኪራም+ ለሰለሞን የሚፈልገውን ያህል የአርዘ ሊባኖስ ሳንቃዎች፣ የጥድ ዛፍ ሳንቃዎችና ወርቅ ሰጠው፤+ ንጉሥ ሰለሞን ደግሞ ለኪራም በገሊላ ምድር የሚገኙ 20 ከተሞችን ሰጠው። 12 ስለሆነም ኪራም ሰለሞን የሰጠውን ከተሞች ለማየት ከጢሮስ ወጥቶ ሄደ፤ ሆኖም በከተሞቹ አልተደሰተም። 13 እሱም “ወንድሜ ሆይ፣ የሰጠኸኝ ምን ዓይነት ከተሞችን ነው?” አለው። ስለዚህ እነዚህ ከተሞች እስከ ዛሬ ድረስ የካቡል ምድር* ተብለው ይጠራሉ። 14 ይህ በእንዲህ እንዳለ ኪራም ለንጉሡ 120 ታላንት* ወርቅ ላከለት።+
15 ንጉሥ ሰለሞን የይሖዋን ቤት፣+ የራሱን ቤት፣* ጉብታውን፣*+ የኢየሩሳሌምን ቅጥር፣ ሃጾርን፣+ መጊዶንና+ ጌዜርን+ እንዲገነቡ ስለመለመላቸው የግዳጅ ሥራ የሚሠሩ ሠራተኞች+ የሚገልጸው ዘገባ ይህ ነው። 16 (የግብፅ ንጉሥ ፈርዖን ወጥቶ ጌዜርን ያዘ፤ በእሳትም አቃጠላት፤ በተጨማሪም በከተማዋ ውስጥ የሚኖሩትን ከነአናውያን+ ገደለ። ከተማዋንም የሰለሞን ሚስት ለሆነችው ለልጁ ጎጆ መውጫ* አድርጎ ሰጣት።)+ 17 ሰለሞንም ጌዜርንና ታችኛውን ቤትሆሮንን+ ሠራ፤ 18 በተጨማሪም ባዓላትን፣+ በምድሩ በሚገኘው ምድረ በዳ ውስጥ ያለችውን ትዕማርን 19 እንዲሁም የሰለሞንን የእህልና የዕቃ ማከማቻ ከተሞች በሙሉ፣ የሠረገላ ከተሞቹን፣+ የፈረሰኞቹን ከተሞች እንዲሁም ሰለሞን በኢየሩሳሌም፣ በሊባኖስና በእሱ ግዛት ውስጥ ባለው ምድር ሁሉ መገንባት የፈለጋቸውን ነገሮች በሙሉ ሠራ። 20 ከእስራኤላውያን ወገን ያልሆኑትን+ ከአሞራውያን፣ ከሂታውያን፣ ከፈሪዛውያን፣ ከሂዋውያንና ከኢያቡሳውያን+ የተረፉትን ሕዝቦች በሙሉ 21 ይኸውም እስራኤላውያን ፈጽመው ሊያጠፏቸው ያልቻሏቸውን በምድሪቱ ላይ የቀሩትን ዘሮቻቸውን ሰለሞን እንደ ባሪያ ሆነው የግዳጅ ሥራ እንዲሠሩ መልምሏቸው ነበር፤ እስከ ዛሬም ድረስ ይሠራሉ።+ 22 ሆኖም ሰለሞን ከእስራኤላውያን መካከል አንዳቸውንም ባሪያ አላደረገም፤+ ምክንያቱም እነሱ ተዋጊዎቹ፣ አገልጋዮቹ፣ መኳንንቱ፣ የጦር መኮንኖቹ እንዲሁም የሠረገለኞቹና የፈረሰኞቹ አለቆች ነበሩ። 23 ሰለሞን የሚያሠራውን ሥራ የሚከታተሉት ይኸውም ሥራውን የሚሠሩትን ሰዎች በቅርብ የሚቆጣጠሩት የበታች ተቆጣጣሪዎቹ አለቆች 550 ነበሩ።+
24 የፈርዖን ሴት ልጅ+ ግን ከዳዊት ከተማ+ ወጥታ ሰለሞን ወዳሠራላት ወደ ራሷ ቤት መጣች፤ ከዚያም ጉብታውን*+ ሠራ።
25 ሰለሞን በዓመት ሦስት ጊዜ+ ለይሖዋ በሠራው መሠዊያ ላይ የሚቃጠሉ መሥዋዕቶችንና የኅብረት መሥዋዕቶችን ያቀርብ ነበር፤+ በተጨማሪም በይሖዋ ፊት በነበረው መሠዊያ ላይ የሚጨስ መሥዋዕት ያቀርብ ነበር፤ ቤቱንም አጠናቀቀ።+
26 እንዲሁም ንጉሥ ሰለሞን በኤዶም ምድር+ በቀይ ባሕር ዳርቻ በኤሎት አጠገብ በምትገኘው በዔጽዮንጋብር+ መርከቦችን ሠራ። 27 ኪራምም ከሰለሞን አገልጋዮች ጋር አብረው እንዲሠሩ አገልጋዮቹን ይኸውም ልምድ ያላቸውን ባሕረኞች ከእነዚህ መርከቦች ጋር ላከ።+ 28 እነሱም ወደ ኦፊር+ በመሄድ 420 ታላንት ወርቅ አምጥተው ለንጉሥ ሰለሞን ሰጡት።
10 የሳባ ንግሥት ስለ ሰለሞን ዝና እንዲሁም ከይሖዋ ስም ጋር ስላለው ግንኙነት ሰማች፤+ በመሆኑም አስቸጋሪ በሆኑ ጥያቄዎች* ልትፈትነው መጣች።+ 2 እሷም እጅግ ታላቅ አጀብ አስከትላ+ እንዲሁም የበለሳን ዘይት፣+ በጣም ብዙ ወርቅና የከበሩ ድንጋዮች በግመል አስጭና ኢየሩሳሌም ደረሰች። ወደ ሰለሞንም ገብታ በልቧ ያለውን ሁሉ ነገረችው። 3 ሰለሞንም ጥያቄዎቿን ሁሉ መለሰላት። ንጉሡ ሊያብራራላት ያልቻለው* ምንም ነገር አልነበረም።
4 የሳባ ንግሥት የሰለሞንን ጥበብ+ ሁሉና የሠራውን ቤት ስትመለከት፣+ 5 በገበታው ላይ የሚቀርበውን ምግብ፣+ የአገልጋዮቹን አቀማመጥ፣ አስተናጋጆቹ በማዕድ ላይ የሚያስተናግዱበትን መንገድና አለባበሳቸውን፣ መጠጥ አሳላፊዎቹን እንዲሁም በይሖዋ ቤት ዘወትር የሚያቀርባቸውን የሚቃጠሉ መሥዋዕቶች ስታይ በመገረም ፈዛ ቀረች።* 6 በመሆኑም ንጉሡን እንዲህ አለችው፦ “ስላከናወንካቸው ነገሮችና* ስለ ጥበብህ በአገሬ ሳለሁ የሰማሁት ነገር እውነት ነው። 7 ይሁንና እኔ ራሴ መጥቼ በገዛ ዓይኔ እስከማይ ድረስ የተነገረኝን ነገር አላመንኩም ነበር። እንደዚያም ሆኖ ግማሹ እንኳ አልተነገረኝም! በጥበብም ሆነ በብልጽግና ከሰማሁት ሁሉ እጅግ የላቅክ ነህ። 8 አብረውህ ያሉ ሰዎች ደስተኞች ናቸው፤ ዘወትር በፊትህ ቆመው ጥበብህን የሚሰሙት አገልጋዮችህም እጅግ ደስተኞች ናቸው!+ 9 አንተን በእስራኤል ዙፋን ላይ በማስቀመጥ በአንተ ደስ የተሰኘው አምላክህ ይሖዋ ይወደስ።+ ይሖዋ ለእስራኤል ካለው ዘላለማዊ ፍቅር የተነሳ ፍትሕንና ጽድቅን እንድታሰፍን ንጉሥ አድርጎ ሾሞሃል።”
10 ከዚያም ለንጉሡ 120 ታላንት* ወርቅ እንዲሁም እጅግ ብዙ የበለሳን ዘይትና+ የከበሩ ድንጋዮች ሰጠችው።+ የሳባ ንግሥት ለንጉሥ ሰለሞን የሰጠችውን የሚያህል መጠን ያለው የበለሳን ዘይት ከዚያ በኋላ መጥቶ አያውቅም።
11 ከኦፊር ወርቅ ጭነው የመጡት የኪራም መርከቦች ከኦፊር+ እጅግ ብዙ የሰንደል ዛፍ ሳንቃዎችንና+ የከበሩ ድንጋዮችንም+ አምጥተው ነበር። 12 ንጉሡም ከሰንደል ዛፍ ሳንቃዎቹ ለይሖዋ ቤትና ለንጉሡ ቤት* ድጋፎችን እንዲሁም ለዘማሪዎቹ የሚሆኑ በገናዎችንና ሌሎች ባለ አውታር መሣሪያዎችን ሠራ።+ ይህን ያህል ብዛት ያለው የሰንደል ዛፍ ሳንቃ እስከ ዛሬ ድረስ መጥቶም ሆነ ታይቶ አያውቅም።
13 ንጉሥ ሰለሞንም ለሳባ ንግሥት በልግስና ተነሳስቶ* ከሰጣት ሌላ የፈለገችውንና የጠየቀችውን ነገር ሁሉ ሰጣት። ከዚያም ተነስታ አገልጋዮቿን በማስከተል ወደ አገሯ ተመለሰች።+
14 ሰለሞን በየዓመቱ 666 ታላንት ወርቅ ይመጣለት ነበር፤+ 15 ይህም ከነጋዴዎች፣ ከሸቃጮች ከሚገኘው ትርፍ፣ ከዓረብ ነገሥታት ሁሉና ከአገረ ገዢዎች የሚሰበሰበውን ሳይጨምር ነው።
16 ንጉሥ ሰለሞን ከቅይጥ ወርቅ 200 ትላልቅ ጋሻዎችን ሠራ፤+ (እያንዳንዱ ጋሻ በ600 ሰቅል* ወርቅ ተለብጦ ነበር)፤+ 17 እንዲሁም ከቅይጥ ወርቅ 300 ትናንሽ ጋሻዎችን* ሠራ፤ (እያንዳንዱ ትንሽ ጋሻ በሦስት ምናን* ወርቅ ተለብጦ ነበር)። ከዚያም ንጉሡ የሊባኖስ ደን+ በተባለው ቤት አስቀመጣቸው።
18 በተጨማሪም ንጉሡ ከዝሆን ጥርስ ትልቅ ዙፋን ሠርቶ+ በተጣራ ወርቅ ለበጠው።+ 19 ወደ ዙፋኑ የሚያስወጡ ስድስት ደረጃዎች ነበሩ፤ ዙፋኑም ከኋላው በኩል ክብ ከለላ ነበረው፤ መቀመጫውም በጎንና በጎኑ የእጅ መደገፊያዎች ያሉት ሲሆን ከእጅ መደገፊያዎቹም አጠገብ ሁለት አንበሶች+ ቆመው ነበር። 20 በስድስቱ ደረጃዎች ዳርና ዳር አንድ አንድ አንበሳ፣ በአጠቃላይ 12 አንበሶች ቆመው ነበር። እንዲህ ያለ ዙፋን የሠራ አንድም ሌላ መንግሥት አልነበረም።
21 የንጉሥ ሰለሞን የመጠጫ ዕቃዎች በሙሉ ከወርቅ የተሠሩ ነበሩ፤ የሊባኖስ ደን በተባለው ቤት+ የነበሩት ዕቃዎችም በሙሉ ከንጹሕ ወርቅ የተሠሩ ነበሩ። ከብር የተሠራ ምንም ነገር አልነበረም፤ በሰለሞን ዘመን ብር እንደ ተራ ነገር ይቆጠር ነበር።+ 22 ንጉሡ ከኪራም መርከቦች ጋር አብረው በባሕር ላይ የሚጓዙ የተርሴስ+ መርከቦች ነበሩት። እነዚህ የተርሴስ መርከቦች በሦስት ዓመት አንድ ጊዜ ወርቅ፣ ብር፣ የዝሆን ጥርስ፣+ ጦጣና ጣዎስ* ጭነው ይመጡ ነበር።
23 በመሆኑም ንጉሥ ሰለሞን በብልጽግናና+ በጥበብ+ ምድር ላይ ካሉ ሌሎች ነገሥታት ሁሉ ይበልጥ ነበር። 24 የምድር ሕዝቦችም ሁሉ አምላክ በሰለሞን ልብ ውስጥ ያኖረውን ጥበብ+ ይሰሙ ዘንድ ከእሱ ጋር ለመገናኘት ይጓጉ ነበር።* 25 ወደ እሱ የሚመጡትም ሰዎች በየዓመቱ የብር ዕቃዎች፣ የወርቅ ዕቃዎች፣ ልብሶች፣ የጦር ትጥቆች፣ የበለሳን ዘይት፣ ፈረሶችና በቅሎዎች ስጦታ አድርገው ያመጡ ነበር።
26 ሰለሞንም ሠረገሎችንና ፈረሶችን* መሰብሰቡን ቀጠለ፤ እሱም 1,400 ሠረገሎችና 12,000 ፈረሶች*+ ነበሩት፤ እነሱንም በሠረገላ ከተሞችና በኢየሩሳሌም በንጉሡ አቅራቢያ አኖራቸው።+
27 ንጉሡ በኢየሩሳሌም ያለውን ብር ከብዛቱ የተነሳ በየቦታው እንደሚገኝ ድንጋይ አደረገው፤ አርዘ ሊባኖሱንም ከብዛቱ የተነሳ በሸፌላ እንደሚገኘው የሾላ ዛፍ አደረገው።+
28 የሰለሞን ፈረሶች ከግብፅ ያስመጣቸው ነበሩ፤ የንጉሡ ነጋዴዎችም የፈረሶቹን መንጋ አንዴ በተተመነው ዋጋ ይገዙ ነበር።*+ 29 ከግብፅ የሚመጣው እያንዳንዱ ሠረገላ 600 የብር ሰቅል ያወጣ ነበር፤ አንድ ፈረስ ደግሞ 150 ሰቅል ያወጣል፤ እነሱ ደግሞ በተራቸው ለሂታውያን+ ነገሥታትና ለሶርያ ነገሥታት ሁሉ ሠረገሎችንና ፈረሶችን ይሸጡ ነበር።
11 ይሁንና ንጉሥ ሰለሞን ከፈርዖን ልጅ+ ሌላ ብዙ የባዕድ አገር ሴቶችን+ ማለትም ሞዓባውያን፣+ አሞናውያን፣+ ኤዶማውያን፣ ሲዶናውያንና+ ሂታውያን+ ሴቶችን አፈቀረ። 2 እነሱም ይሖዋ ለእስራኤላውያን “ከእነሱ ጋር አትቀላቀሉ፤* እነሱም ከእናንተ ጋር አይቀላቀሉ፤ አለዚያ ያለምንም ጥርጥር ልባችሁ አማልክታቸውን ወደ መከተል እንዲያዘነብል ያደርጉታል”+ ብሎ ከነገራቸው ብሔራት ወገን ነበሩ። ሆኖም ሰለሞን ከእነሱ ጋር ተጣበቀ፤ ደግሞም አፈቀራቸው። 3 እሱም ልዕልቶች የሆኑ 700 ሚስቶች እንዲሁም 300 ቁባቶች ነበሩት፤ ሚስቶቹም ቀስ በቀስ ልቡ ወደ ሌላ እንዲያዘነብል አደረጉት።* 4 ሰለሞን በሸመገለ+ ጊዜ ሚስቶቹ ልቡ ሌሎች አማልክትን ወደ መከተል እንዲያዘነብል* አደረጉት፤+ ልቡ እንደ አባቱ እንደ ዳዊት ልብ በአምላኩ በይሖዋ ዘንድ ሙሉ* አልነበረም። 5 ሰለሞን የሲዶናውያንን እንስት አምላክ አስታሮትንና+ አስጸያፊ የሆነውን የአሞናውያንን አምላክ ሚልኮምን+ ተከተለ። 6 ሰለሞንም በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ፤ አባቱ ዳዊት እንዳደረገው ይሖዋን ሙሉ በሙሉ አልተከተለም።+
7 ሰለሞን አስጸያፊ ለሆነው የሞዓብ አምላክ ለከሞሽና አስጸያፊ ለሆነው ለአሞናውያን+ አምላክ ለሞሎክ+ ኢየሩሳሌም ፊት ለፊት በሚገኘው ተራራ ላይ ከፍ ያለ የማምለኪያ ቦታ+ የሠራው በዚህ ጊዜ ነበር። 8 ለአማልክታቸው የሚጨስ መሥዋዕት ለሚያቀርቡትና ለሚሠዉት የባዕድ አገር ሚስቶቹ ሁሉ ልክ እንደዚሁ አደረገ።
9 ሰለሞን ሁለት ጊዜ ከተገለጠለት+ ከእስራኤል አምላክ ከይሖዋ ልቡ ስለሸፈተ+ ይሖዋ በሰለሞን ላይ ተቆጣ፤ 10 ደግሞም ሌሎች አማልክትን እንዳይከተል በማዘዝ ይህንኑ ጉዳይ አስመልክቶ አስጠንቅቆት ነበር።+ እሱ ግን ይሖዋ ያዘዘውን ነገር አልጠበቀም። 11 በዚህ ጊዜ ይሖዋ ሰለሞንን እንዲህ አለው፦ “ይህን ስላደረግክ እንዲሁም ባዘዝኩህ መሠረት ቃል ኪዳኔንና ደንቦቼን ስላልጠበቅክ መንግሥትህን ቀድጄ ከአንተ እወስደዋለሁ፤ ከአገልጋዮችህም መካከል ለአንዱ እሰጠዋለሁ።+ 12 ሆኖም ስለ አባትህ ስለ ዳዊት ስል በአንተ ዘመን ይህን አላደርግም። መንግሥትህን ከልጅህ እጅ ላይ እቀደዋለሁ፤+ 13 ይሁንና መንግሥቱን በሙሉ ቀድጄ አልወስድም።+ ስለ አገልጋዬ ስለ ዳዊትና ስለመረጥኳት+ ስለ ኢየሩሳሌም ስል ለልጅህ አንድ ነገድ እሰጠዋለሁ።”+
14 ከዚያም ይሖዋ ከኤዶም+ ንጉሣዊ ቤተሰብ የሆነውን ኤዶማዊውን ሃዳድን በሰለሞን ላይ ተቃዋሚ አድርጎ አስነሳው።+ 15 ዳዊት ኤዶምን+ ድል ባደረገበት ጊዜ የሠራዊቱ አለቃ የሆነው ኢዮዓብ የተገደሉትን ለመቅበር ወጥቶ የነበረ ሲሆን በኤዶም የሚገኘውን እያንዳንዱን ወንድ ለመግደል ሞክሮ ነበር። 16 (ምክንያቱም ኢዮዓብ በኤዶም የሚገኘውን እያንዳንዱን ወንድ ገድሎ እስኪጨርስ ድረስ ከመላው እስራኤል ጋር በዚያ ለስድስት ወር ተቀምጦ ነበር።) 17 ሆኖም ሃዳድ የአባቱ አገልጋዮች ከሆኑ የተወሰኑ ኤዶማውያን ጋር ሸሸ፤ እነሱም ወደ ግብፅ ሄዱ፤ በወቅቱ ሃዳድ ገና ትንሽ ልጅ ነበር። 18 እነሱም ከምድያም ተነስተው ወደ ፋራን ሄዱ። ከፋራንም+ ሰዎች ይዘው ወደ ግብፅ ይኸውም ወደ ግብፁ ንጉሥ ወደ ፈርዖን መጡ፤ ፈርዖንም ቤትና መሬት ሰጠው፤ ቀለብም እንዲሰፈርለት አደረገ። 19 ሃዳድም በፈርዖን ፊት ሞገስ ስላገኘ ፈርዖን የገዛ ሚስቱን እህት ማለትም የንግሥት ጣፍኔስን እህት ዳረለት። 20 ከጊዜ በኋላ የጣፍኔስ እህት፣ ጌኑባት የተባለ ልጅ ወለደችለት፤ ጣፍኔስም ልጁን በፈርዖን ቤት ውስጥ አሳደገችው፤* ጌኑባት በፈርዖን ቤት ከፈርዖን ልጆች ጋር ኖረ።
21 ሃዳድ በግብፅ ሳለ ዳዊት ከአባቶቹ ጋር እንዳንቀላፋ+ እንዲሁም የሠራዊቱ አለቃ ኢዮዓብ እንደሞተ ሰማ።+ በመሆኑም ሃዳድ ፈርዖንን “ወደ አገሬ እንድሄድ አሰናብተኝ” አለው። 22 ፈርዖን ግን “እዚህ እኔ ጋር እያለህ ምን ጎደለብህና ነው ወደ አገርህ መሄድ የፈለግከው?” አለው። እሱም “ምንም የጎደለብኝ ነገር የለም፤ ብቻ እንድሄድ አሰናብተኝ” አለው።
23 በተጨማሪም አምላክ ከጌታው ከጾባህ ንጉሥ ከሃዳድኤዜር+ የኮበለለውን የኤሊያዳን ልጅ ረዞንን በሰለሞን ላይ ተቃዋሚ አድርጎ አስነሳው።+ 24 እሱም ዳዊት የጾባህን ሰዎች ድል ባደረገበት ጊዜ* ሰዎችን አሰባስቦ የአንድ ወራሪ ቡድን አለቃ ሆነ።+ በመሆኑም ወደ ደማስቆ+ ሄደው በዚያ ሰፈሩ፤ በደማስቆም መግዛት ጀመሩ። 25 ሃዳድ በእስራኤል ላይ ካስከተለው ጉዳት በተጨማሪ ረዞንም በሰለሞን ዘመን ሁሉ የእስራኤል ተቃዋሚ ሆነ፤ በሶርያ ላይ በነገሠበትም ዘመን ሁሉ ለእስራኤል ከፍተኛ ጥላቻ ነበረው።
26 እንዲሁም የሰለሞን አገልጋይ+ የሆነ ኢዮርብዓም+ የተባለ አንድ ኤፍሬማዊ ነበር፤ እሱም ከጸሬዳህ ወገን ሲሆን የናባጥ ልጅ ነበር፤ እናቱም ጽሩዓ የምትባል መበለት ነበረች። እሱም በንጉሡ ላይ ማመፅ* ጀመረ።+ 27 በንጉሡ ላይ ያመፀውም በዚህ የተነሳ ነው፦ ሰለሞን ጉብታውን*+ ሠርቶ እንዲሁም በአባቱ በዳዊት ከተማ+ ቅጥር ላይ የነበረውን ክፍተት ዘግቶ ነበር። 28 ኢዮርብዓም ከፍተኛ ችሎታ ያለው ሰው ነበር። ሰለሞንም ወጣቱ ጠንካራ ሠራተኛ መሆኑን ሲያይ በዮሴፍ ቤት በሚከናወነው የግዳጅ ሥራ ሁሉ ላይ የበላይ ተመልካች አደረገው።+ 29 በዚህ ጊዜ ኢዮርብዓም ከኢየሩሳሌም ወጣ፤ ሴሎናዊው ነቢዩ አኪያህም መንገድ ላይ አገኘው። አኪያህ+ አዲስ ልብስ ለብሶ ነበር፤ በሜዳውም ላይ ሁለቱ ብቻቸውን ነበሩ። 30 አኪያህም ለብሶት የነበረውን አዲስ ልብስ ይዞ 12 ቦታ ቀደደው። 31 ከዚያም ኢዮርብዓምን እንዲህ አለው፦
“አሥሩን ቁራጭ ለራስህ ውሰድ፤ ምክንያቱም የእስራኤል አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እንግዲህ መንግሥቱን ከሰለሞን እጅ እቀደዋለሁ፤ ለአንተም አሥር ነገዶችን እሰጥሃለሁ።+ 32 ሆኖም ስለ አገልጋዬ ስለ ዳዊትና+ ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ መካከል ስለመረጥኳት ከተማ+ ስለ ኢየሩሳሌም ስል አንዱ ነገድ የእሱ እንደሆነ ይቀጥላል።+ 33 ይህን የማደርገው እኔን ትተው+ ለሲዶናውያን እንስት አምላክ ለአስታሮት፣ ለሞዓብ አምላክ ለከሞሽና ለአሞናውያን አምላክ ለሚልኮም ስለሰገዱ ነው፤ አባቱ ዳዊት እንዳደረገው በፊቴ ትክክል የሆነውን ነገር በማድረግ እንዲሁም ደንቦቼንና ድንጋጌዎቼን በመጠበቅ በመንገዴ አልሄዱም። 34 ሆኖም ትእዛዛቴንና ደንቦቼን ስለጠበቀው ስለመረጥኩት አገልጋዬ ስለ ዳዊት+ ስል መንግሥቱን በሙሉ ከእጁ አልወስድም፤ ደግሞም በሕይወት ዘመኑ ሁሉ አለቃ አደርገዋለሁ። 35 ይሁን እንጂ መንግሥቱን ይኸውም አሥሩን ነገድ ከልጁ እጅ ወስጄ ለአንተ እሰጥሃለሁ።+ 36 አገልጋዬ ዳዊት ስሜ እንዲኖርባት ለራሴ በመረጥኳት ከተማ በኢየሩሳሌም ዘወትር በፊቴ መብራት እንዲኖረው+ ለልጁ አንድ ነገድ እሰጠዋለሁ። 37 እኔም እወስድሃለሁ፤ አንተም በተመኘኸው* ሁሉ ላይ ትገዛለህ፤ በእስራኤልም ላይ ንጉሥ ትሆናለህ። 38 አገልጋዬ ዳዊት እንዳደረገው+ ያዘዝኩህን ሁሉ ብትፈጽም እንዲሁም ደንቦቼንና ትእዛዛቴን በመጠበቅ በመንገዶቼ ብትሄድና በፊቴ ትክክል የሆነውን ነገር ብታደርግ እኔም ከአንተ ጋር እሆናለሁ። ለዳዊት እንዳደረግኩለት ሁሉ ለአንተም ጸንቶ የሚኖር ቤት እሠራልሃለሁ፤+ እስራኤልንም እሰጥሃለሁ። 39 በዚህም የተነሳ የዳዊትን ዘር አዋርዳለሁ፤+ ይህን የማደርገው ግን ለሁልጊዜ አይደለም።’”+
40 በመሆኑም ሰለሞን ኢዮርብዓምን ሊገድለው ሞከረ፤ ሆኖም ኢዮርብዓም ተነስቶ ወደ ግብፅ፣+ ወደ ንጉሥ ሺሻቅ+ ሸሸ፤ ሰለሞን እስኪሞትም ድረስ በግብፅ ተቀመጠ።
41 የቀረው የሰለሞን ታሪክ፣ ያደረጋቸው ነገሮች ሁሉና ጥበቡ በሰለሞን የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም?+ 42 ሰለሞን በኢየሩሳሌም ሆኖ በመላው እስራኤል ላይ የገዛበት የጊዜ ርዝመት* 40 ዓመት ነበር። 43 ከዚያም ሰለሞን ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በአባቱ በዳዊት ከተማ ተቀበረ፤ በእሱም ምትክ ልጁ ሮብዓም+ ነገሠ።
12 ሮብዓም እስራኤላውያን በሙሉ ሊያነግሡት+ ወደ ሴኬም+ መጥተው ስለነበር እሱም ወደ ሴኬም ሄደ። 2 የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ይህን እንደሰማ (ምክንያቱም ኢዮርብዓም ከንጉሥ ሰለሞን ሸሽቶ በግብፅ ይኖር ስለነበር በወቅቱ በዚያ ይገኝ ነበር)፣+ 3 ልከው አስጠሩት። ከዚያም ኢዮርብዓምና መላው የእስራኤል ጉባኤ መጥተው ሮብዓምን እንዲህ አሉት፦ 4 “አባትህ ቀንበራችንን አክብዶብን ነበር።+ አንተ ግን አባትህ የሰጠንን አስቸጋሪ ሥራና በላያችን የጫነብንን ከባድ* ቀንበር የምታቀልልን ከሆነ እናገለግልሃለን።”
5 በዚህ ጊዜ “እንግዲያው ሂዱና ከሦስት ቀን በኋላ ተመልሳችሁ ኑ” አላቸው። በመሆኑም ሕዝቡ ሄደ።+ 6 ከዚያም ንጉሥ ሮብዓም አባቱ ሰለሞን በሕይወት በነበረበት ጊዜ ሲያገለግሉት የነበሩትን ሽማግሌዎች “ለዚህ ሕዝብ ምን ምላሽ እንድሰጥ ትመክሩኛላችሁ?” በማለት ምክር ጠየቀ። 7 እነሱም “ዛሬ አንተ የዚህ ሕዝብ አገልጋይ ብትሆንና የጠየቁህን ብትፈጽምላቸው እንዲሁም መልካም ምላሽ ብትሰጣቸው ምንጊዜም አገልጋዮችህ ይሆናሉ” በማለት መለሱለት።
8 ሆኖም ሮብዓም ሽማግሌዎቹ የሰጡትን ምክር ትቶ አብሮ አደጎቹ ከነበሩትና አሁን የእሱ አገልጋዮች ከሆኑት ወጣቶች ጋር ተማከረ።+ 9 እሱም እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፦ “‘አባትህ የጫነብንን ቀንበር አቅልልልን’ ለሚለኝ ለዚህ ሕዝብ ምን ምላሽ እንድንሰጥ ትመክሩኛላችሁ?” 10 አብሮ አደጎቹ የሆኑት ወጣቶችም እንዲህ አሉት፦ “‘አባትህ ቀንበራችንን አክብዶብን ነበር፤ አንተ ግን ቀንበራችንን አቅልልልን’ ለሚልህ ለዚህ ሕዝብ እንዲህ በለው፦ ‘ትንሿ ጣቴ ከአባቴ ወገብ ትወፍራለች። 11 አባቴ ከባድ ቀንበር ጭኖባችሁ ነበር፤ እኔ ግን ቀንበራችሁን የባሰ አከብደዋለሁ። አባቴ በአለንጋ ገርፏችሁ ነበር፤ እኔ ግን በእሾህ አለንጋ እገርፋችኋለሁ።’”
12 ኢዮርብዓምና መላው ሕዝብ ንጉሡ “በሦስተኛው ቀን ተመልሳችሁ ኑ” ባላቸው መሠረት በሦስተኛው ቀን ወደ ሮብዓም መጡ።+ 13 ንጉሡ ግን ሽማግሌዎቹ የሰጡትን ምክር ትቶ ለሕዝቡ መጥፎ ምላሽ ሰጠ። 14 ወጣቶቹም በሰጡት ምክር መሠረት “አባቴ ቀንበራችሁን አክብዶባችሁ ነበር፤ እኔ ግን ቀንበራችሁን የባሰ አከብደዋለሁ። አባቴ በአለንጋ ገርፏችሁ ነበር፤ እኔ ግን በእሾህ አለንጋ እገርፋችኋለሁ” አላቸው። 15 በመሆኑም ንጉሡ ሕዝቡን ሳይሰማ ቀረ፤ ይህም የሆነው ይሖዋ በሴሎናዊው በአኪያህ+ አማካኝነት ለናባጥ ልጅ ለኢዮርብዓም የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ ይሖዋ እነዚህ ነገሮች በዚህ መንገድ እንዲከናወኑ ስላደረገ ነው።+
16 እስራኤላውያን ሁሉ ንጉሡ ሊሰማቸው ፈቃደኛ አለመሆኑን ሲያዩ ንጉሡን እንዲህ አሉት፦ “ከዳዊት ምን ድርሻ አለን? ከእሴይ ልጅ ምንም ርስት የለንም። እስራኤል ሆይ፣ ወደ አማልክትህ ተመለስ። ዳዊት ሆይ፣ እንግዲህ የገዛ ቤትህን ጠብቅ!” ከዚያም እስራኤላውያን ወደየቤታቸው* ተመለሱ።+ 17 ይሁንና ሮብዓም በይሁዳ ከተሞች በሚኖሩት እስራኤላውያን ላይ መግዛቱን ቀጠለ።+
18 ከዚያም ንጉሥ ሮብዓም የግዳጅ ሥራ እንዲሠሩ የተመለመሉት ሰዎች አለቃ የነበረውን አዶራምን+ ላከው፤ ሆኖም እስራኤላውያን በሙሉ በድንጋይ ወግረው ገደሉት። ንጉሥ ሮብዓም ግን እንደ ምንም ብሎ ሠረገላው ላይ በመውጣት ወደ ኢየሩሳሌም ሸሸ።+ 19 እስራኤላውያንም እስከዚህ ቀን ድረስ በዳዊት ቤት ላይ እንዳመፁ+ ናቸው።
20 እስራኤላውያን በሙሉ ኢዮርብዓም መመለሱን እንደሰሙ ወደ ማኅበረሰቡ ካስጠሩት በኋላ በመላው እስራኤል ላይ አነገሡት።+ ከይሁዳ ነገድ በስተቀር ከሕዝቡ መሃል የዳዊትን ቤት የተከተለ ማንም አልነበረም።+
21 ሮብዓም ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ ከእስራኤል ቤት ጋር ተዋግተው ንግሥናውን ለሰለሞን ልጅ ለሮብዓም እንዲያስመልሱ ከመላው የይሁዳ ቤትና ከቢንያም ነገድ የተውጣጡ 180,000 የሠለጠኑ* ተዋጊዎች ወዲያውኑ ሰበሰበ።+ 22 ከዚያም የእውነተኛው አምላክ ቃል የእውነተኛው አምላክ ሰው ወደሆነው ወደ ሸማያህ+ እንዲህ ሲል መጣ፦ 23 “ለይሁዳ ንጉሥ ለሰለሞን ልጅ ለሮብዓም፣ ለይሁዳ ቤት ሁሉ፣ ለቢንያምና ለቀረው ሕዝብ እንዲህ ብለህ ተናገር፦ 24 ‘ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ከወንድሞቻችሁ ከእስራኤላውያን ጋር ለመዋጋት አትውጡ። ይህ እንዲሆን ያደረግኩት እኔ ስለሆንኩ እያንዳንዳችሁ ወደ ቤታችሁ ተመለሱ።”’”+ ስለዚህ የይሖዋን ቃል ሰሙ፤ ይሖዋ እንደነገራቸውም ወደየቤታቸው ተመለሱ።
25 ከዚያም ኢዮርብዓም በኤፍሬም ተራራማ አካባቢ ሴኬምን+ ገንብቶ* በዚያ መኖር ጀመረ። ከዚያ ወጥቶ በመሄድ ጰኑኤልን+ ገነባ።* 26 ኢዮርብዓም በልቡ እንዲህ ሲል አሰበ፦ “እንግዲህ አሁን መንግሥቱ ወደ ዳዊት ቤት ይመለሳል።+ 27 ይህ ሕዝብ በኢየሩሳሌም በሚገኘው የይሖዋ ቤት+ መሥዋዕት ለማቅረብ ወደዚያ መውጣቱን ከቀጠለ የዚህ ሕዝብ ልብ ጌታው ወደሆነው ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ሮብዓም ይመለሳል። እኔንም ይገድለኛል፤ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ሮብዓምም ይመለሳል።” 28 በመሆኑም ንጉሡ ከተማከረ በኋላ ሁለት የወርቅ ጥጃዎችን+ ሠርቶ ሕዝቡን “ወደ ኢየሩሳሌም መውጣት መንገላታት ይሆንባችኋል። እስራኤል ሆይ፣ ከግብፅ ምድር ያወጣህ አምላክህ ይኸውልህ” አለ።+ 29 ከዚያም አንደኛውን በቤቴል+ ሌላኛውን ደግሞ በዳን+ አቆመው። 30 ይህም ለኃጢአት ዳረጋቸው፤+ ሕዝቡም በዳን የሚገኘውን ጥጃ ለማምለክ እስከዚያ ድረስ ይሄድ ነበር።
31 እሱም በኮረብቶቹ ላይ የአምልኮ ቤቶችን ሠራ፤ ከሕዝቡም መካከል ሌዋውያን ያልሆኑ ሰዎችን ካህናት አድርጎ ሾመ።+ 32 በተጨማሪም ኢዮርብዓም በስምንተኛው ወር ከወሩም በ15ኛው ቀን በይሁዳ ይከበር የነበረው ዓይነት በዓል እንዲቋቋም አደረገ።+ ለሠራቸውም ጥጆች በቤቴል+ በሠራው መሠዊያ ላይ መሥዋዕት አቀረበ፤ በቤቴል ለሠራቸው ከፍ ያሉ የማምለኪያ ቦታዎችም ካህናት መደበ። 33 በቤቴል በሠራው መሠዊያም ላይ ራሱ በመረጠው ወር ይኸውም በስምንተኛው ወር በ15ኛው ቀን መባዎችን ማቅረብ ጀመረ፤ ለእስራኤል ሰዎችም በዓል አቋቋመ፤ እንዲሁም መባዎችንና የሚጨሱ መሥዋዕቶችን ለማቅረብ ወደ መሠዊያው ወጣ።
13 ኢዮርብዓም በመሠዊያው+ አጠገብ የሚጨስ መሥዋዕት ለማቅረብ ቆሞ ሳለ አንድ የአምላክ ሰው+ በይሖዋ ቃል በታዘዘው መሠረት ከይሁዳ ወደ ቤቴል መጣ። 2 ከዚያም በይሖዋ ቃል በታዘዘው መሠረት መሠዊያውን በመቃወም እንዲህ ሲል ተጣራ፦ “መሠዊያ ሆይ! መሠዊያ ሆይ! ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እነሆ፣ ኢዮስያስ+ የተባለ ልጅ ለዳዊት ቤት ይወለዳል! እሱም በአንተ ላይ የሚጨስ መሥዋዕት እያቀረቡ ያሉትን ከፍ ያሉ የማምለኪያ ቦታዎች ካህናት በላይህ ይሠዋቸዋል፤ በአንተም ላይ የሰዎችን አጥንት ያቃጥላል።’”+ 3 እሱም በዚያ ቀን እንዲህ በማለት ምልክት* ሰጠ፦ “ይሖዋ የሰጠው ምልክት* ይህ ነው፦ እነሆ፣ መሠዊያው ይሰነጠቃል፤ በላዩም ላይ ያለው አመድ* ይፈስሳል።”
4 ንጉሡ ኢዮርብዓምም የእውነተኛው አምላክ ሰው በቤቴል የሚገኘውን መሠዊያ በመቃወም የተናገረውን ቃል ሲሰማ እጁን ከመሠዊያው ላይ አንስቶ በመዘርጋት “ያዙት!” አላቸው።+ ወዲያውኑም ወደ እሱ የዘረጋው እጁ ደረቀ፤* እጁንም ሊያጥፈው አልቻለም።+ 5 ከዚያም የእውነተኛው አምላክ ሰው በይሖዋ ቃል ታዞ በሰጠው ምልክት* መሠረት መሠዊያው ተሰነጠቀ፤ አመዱም ከመሠዊያው ላይ ፈሰሰ።
6 በዚህ ጊዜ ንጉሡ የእውነተኛውን አምላክ ሰው “እባክህ፣ የአምላክህን የይሖዋን ሞገስ እንዳገኝ ለምንልኝ፤ እጄም ወደ ቦታው እንዲመለስ ጸልይልኝ” አለው።+ በዚህ ጊዜ የእውነተኛው አምላክ ሰው የይሖዋን ሞገስ እንዲያገኝ ለመነለት፤ የንጉሡም እጅ ተመልሶ እንደቀድሞው ሆነ። 7 ከዚያም ንጉሡ የእውነተኛውን አምላክ ሰው “አብረኸኝ ወደ ቤት ሂድና ምግብ ብላ፤ ስጦታም ልስጥህ” አለው። 8 ሆኖም የእውነተኛው አምላክ ሰው ንጉሡን እንዲህ አለው፦ “የቤትህን ግማሽ ብትሰጠኝ እንኳ ከአንተ ጋር አልሄድም፤ በዚህም ቦታ ምግብ አልበላም፤ ውኃም አልጠጣም። 9 ምክንያቱም የይሖዋ ቃል ‘ምግብ እንዳትበላ፤ ውኃም እንዳትጠጣ፤ በሄድክበትም መንገድ እንዳትመለስ’ ሲል አዞኛል።” 10 በመሆኑም በሌላ መንገድ ሄደ፤ ወደ ቤቴል በመጣበትም መንገድ አልተመለሰም።
11 በዚህ ጊዜ በቤቴል የሚኖር አንድ አረጋዊ ነቢይ ነበር፤ ልጆቹም ወደ ቤት መጥተው የእውነተኛው አምላክ ሰው በዚያ ቀን በቤቴል ያደረገውን ነገር ሁሉና ለንጉሡ የተናገረውን ቃል ነገሩት። ይህን ለአባታቸው ከተረኩለት በኋላ 12 አባታቸው “ለመሆኑ የሄደው በየት በኩል ነው?” ሲል ጠየቃቸው። ልጆቹም ከይሁዳ የመጣው የእውነተኛው አምላክ ሰው የሄደበትን መንገድ አሳዩት። 13 እሱም ልጆቹን “በሉ አህያውን ጫኑልኝ” አላቸው። እነሱም አህያውን ጫኑለት፤ እሱም አህያው ላይ ተቀመጠ።
14 ከዚያም የእውነተኛውን አምላክ ሰው ተከተለው፤ በአንድ ትልቅ ዛፍ ሥር ተቀምጦም አገኘው። እሱም “ከይሁዳ የመጣኸው የእውነተኛው አምላክ ሰው አንተ ነህ?” አለው፤+ እሱም “አዎ፣ እኔ ነኝ” ሲል መለሰለት። 15 ከዚያም “አብረን ወደ ቤት እንሂድና ምግብ ብላ” አለው። 16 እሱ ግን እንዲህ አለው፦ “ከአንተ ጋር ተመልሼ ልሄድ ወይም ያቀረብክልኝን ግብዣ ልቀበል አልችልም፤ ደግሞም በዚህ ቦታ ከአንተ ጋር ምግብም ሆነ ውኃ አልቀምስም። 17 ምክንያቱም የይሖዋ ቃል ‘እዚያ ምግብ እንዳትበላ፤ ውኃም እንዳትጠጣ። በመጣህበትም መንገድ እንዳትመለስ’ በማለት አዞኛል።” 18 በዚህ ጊዜ አረጋዊው ሰው “እኔም እኮ እንደ አንተው ነቢይ ነኝ፤ አንድ መልአክ ‘ምግብ እንዲበላና ውኃ እንዲጠጣ መልሰህ ወደ ቤትህ አምጣው’ በማለት የይሖዋን ቃል ነግሮኛል” አለው። (እሱም አታለለው።) 19 በመሆኑም እሱ ቤት ምግብ ለመብላትና ውኃ ለመጠጣት አብሮት ተመለሰ።
20 እነሱም በማዕድ ተቀምጠው ሳሉ የይሖዋ ቃል የእውነተኛውን አምላክ ሰው መልሶ ወዳመጣው ነቢይ መጣ፤ 21 ከዚያም ከይሁዳ የመጣውን የእውነተኛውን አምላክ ሰው ጠርቶ እንዲህ አለው፦ “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘በይሖዋ መመሪያ ላይ ስላመፅክና አምላክህ ይሖዋ የሰጠህን ትእዛዝ ስላልጠበቅክ፣ 22 ከዚህ ይልቅ ምግብ ለመብላትና ውኃ ለመጠጣት ስትል “ምግብ እንዳትበላ፤ ውኃም እንዳትጠጣ” ወደተባልክበት ቦታ ስለተመለስክ ሬሳህ በአባቶችህ የመቃብር ቦታ አይቀበርም።’”+
23 የእውነተኛው አምላክ ሰውም ከበላና ከጠጣ በኋላ አረጋዊው ነቢይ ከመንገድ መልሶ ላመጣው ለዚያ ነቢይ አህያውን ጫነለት። 24 ከዚያም መንገዱን ቀጠለ፤ ሆኖም አንድ አንበሳ መንገድ ላይ አግኝቶ ገደለው።+ ሬሳውም መንገዱ ላይ ተጋድሞ፣ አህያው ደግሞ አጠገቡ ቆሞ ነበር፤ አንበሳውም ሬሳው አጠገብ ቆሞ ነበር። 25 በዚያ የሚያልፉ ሰዎችም ሬሳው መንገድ ላይ ተጋድሞ፣ አንበሳው ደግሞ አጠገቡ ቆሞ አዩ። ከዚያም መጥተው ይህን ነገር አረጋዊው ነቢይ በሚኖርበት ከተማ አወሩ።
26 ከመንገድ መልሶ ያመጣውም ነቢይ ይህን ሲሰማ ወዲያውኑ “ይህ ሰው በይሖዋ መመሪያ ላይ ያመፀው የእውነተኛው አምላክ ሰው ነው፤+ ይሖዋ በነገረው ቃል መሠረት እንዲቦጫጭቀውና እንዲገድለው ይሖዋ ለአንበሳ አሳልፎ ሰጥቶታል” አለ።+ 27 እሱም ልጆቹን “በሉ አህያውን ጫኑልኝ” አላቸው። እነሱም ጫኑለት። 28 ከዚያም ሄደ፤ ሬሳው መንገድ ላይ ተጋድሞ፣ አህያውና አንበሳውም አጠገቡ ቆመው አገኛቸው። አንበሳው ሬሳውን አልበላውም፤ አህያውንም ቢሆን አልቦጫጨቀውም። 29 ነቢዩም የእውነተኛውን አምላክ ሰው ሬሳ አንስቶ አህያው ላይ ከጫነ በኋላ አልቅሶ ሊቀብረው ስላሰበ ወደሚኖርበት ከተማ ይዞት ተመለሰ። 30 ከዚያም ሬሳውን በራሱ የመቃብር ቦታ ቀበረው፤ እነሱም “ወይኔ ወንድሜን!” እያሉ አለቀሱለት። 31 እሱንም ከቀበረው በኋላ ልጆቹን እንዲህ አላቸው፦ “እኔም ስሞት የእውነተኛው አምላክ ሰው በተቀበረበት የመቃብር ቦታ ቅበሩኝ። አጥንቶቼንም ከአጥንቶቹ አጠገብ ቅበሯቸው።+ 32 በይሖዋ ቃል በታዘዘው መሠረት በቤቴል በሚገኘው መሠዊያና በሰማርያ ከተሞች በሚገኙት ኮረብቶች ላይ ባሉት የአምልኮ ቤቶች+ ሁሉ ላይ የተናገረው ቃል ያለጥርጥር ይፈጸማል።”+
33 ይህ ሁሉ ከሆነም በኋላ ቢሆን ኢዮርብዓም ከመጥፎ መንገዱ አልተመለሰም፤ ከዚህ ይልቅ ከፍ ላሉት የማምለኪያ ቦታዎች ከሕዝቡ መካከል ካህናት መሾሙን ቀጠለ።+ እንዲሁም ካህን ለመሆን የሚፈልግን ማንኛውንም ሰው “ከፍ ላሉት የማምለኪያ ቦታዎች ካህን ይሁን” በማለት ይሾመው* ነበር።+ 34 ይህም ኃጢአት የኢዮርብዓም+ ቤት ከምድር ገጽ እንዲጠፋና እንዲደመሰስ ምክንያት ሆነ።+
14 በዚህ ጊዜ የኢዮርብዓም ልጅ አቢያህ ታመመ። 2 በመሆኑም ኢዮርብዓም ሚስቱን እንዲህ አላት፦ “እባክሽ፣ ተነሺና የኢዮርብዓም ሚስት መሆንሽን እንዳያውቁ ራስሽን ለውጠሽ ወደ ሴሎ ሂጂ። ነቢዩ አኪያህ ያለው እዚያ ነው። እኔ በዚህ ሕዝብ ላይ ንጉሥ እንደምሆን የተናገረው እሱ ነው።+ 3 አሥር ዳቦና የተቀቡ ቂጣዎች እንዲሁም አንድ ገንቦ ማር ይዘሽ ወደ እሱ ሂጂ። እሱም በልጁ ላይ የሚደርሰውን ነገር ይነግርሻል።”
4 የኢዮርብዓምም ሚስት እንዳላት አደረገች። ተነስታ ወደ ሴሎ+ በመሄድ ወደ አኪያህ ቤት መጣች። አኪያህ ከማርጀቱ የተነሳ ማየት ተስኖት የነበረ ቢሆንም ዓይኖቹ ፊት ለፊት ትኩር ብለው ይመለከቱ ነበር።
5 ይሖዋ ግን አኪያህን እንዲህ አለው፦ “የኢዮርብዓም ሚስት ልጇ ስለታመመ ስለ እሱ ልትጠይቅህ እየመጣች ነው። እኔም ምን እንደምትላት እነግርሃለሁ።* እሷም እዚህ ስትደርስ ማንነቷ እንዳይታወቅ ራሷን ትለውጣለች።”
6 አኪያህም በሩ ጋ ስትደርስ የእግሯን ኮቴ ሰምቶ እንዲህ አላት፦ “የኢዮርብዓም ሚስት ግቢ። ማንነትሽ እንዳይታወቅ ራስሽን የለወጥሽው ለምንድን ነው? መጥፎ ዜና እንድነግርሽ ታዝዣለሁ። 7 ሂጂና ኢዮርብዓምን እንዲህ በዪው፦ ‘የእስራኤል አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መሪ እንድትሆን ከሕዝብህ መካከል አስነሳሁህ።+ 8 ከዚያም መንግሥቱን ከዳዊት ቤት ላይ ቀድጄ ለአንተ ሰጠሁህ።+ አንተ ግን በፊቴ ትክክል የሆነውን ነገር ብቻ በማድረግ ትእዛዛቴን እንደጠበቀውና በሙሉ ልቡ እንደተከተለኝ እንደ አገልጋዬ እንደ ዳዊት አልሆንክም።+ 9 ከዚህ ይልቅ ከአንተ በፊት ከነበሩት ሁሉ የከፋ ድርጊት ፈጸምክ፤ እኔንም ለማስቆጣት ለራስህ ሌላ አምላክና ከብረት የተሠሩ ምስሎችን* ሠራህ፤+ ጀርባህንም ሰጠኸኝ።+ 10 በዚህም የተነሳ በኢዮርብዓም ቤት ላይ ጥፋት አመጣለሁ፤ በእስራኤል ውስጥ የሚገኘውን ምስኪኑንና ደካማውን ጨምሮ የኢዮርብዓም የሆነውን ወንድ* ሁሉ ጠራርጌ አጠፋለሁ፤ አንድ ሰው ፋንድያን ሙልጭ አድርጎ በመጥረግ እንደሚያስወግድ ሁሉ እኔም የኢዮርብዓምን ቤት ሙልጭ አድርጌ እጠርጋለሁ!+ 11 ከኢዮርብዓም ወገን የሆነውን በከተማ ውስጥ የሚሞተውን ሁሉ ውሾች ይበሉታል፤ በሜዳ ላይ የሚሞተውን ደግሞ የሰማይ አሞሮች ይበሉታል፤ ይሖዋ ይህን ተናግሯልና።”’
12 “እንግዲህ አሁን ተነስተሽ ወደ ቤትሽ ሂጂ። እግርሽ ከተማዋን እንደረገጠ ልጁ ይሞታል። 13 ከኢዮርብዓም ቤተሰብ መካከል በመቃብር ቦታ የሚቀበረው እሱ ብቻ ስለሆነ እስራኤል ሁሉ አልቅሰው ይቀብሩታል፤ ምክንያቱም የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ከኢዮርብዓም ቤት ሁሉ አንድ መልካም ነገር ያገኘበት እሱን ብቻ ነው። 14 ይሖዋም ከዚያን ቀን ጀምሮ እንዲያውም አሁኑኑ፣ የኢዮርብዓምን ቤት+ የሚያስወግድ በእስራኤል ላይ የሚነግሥ ንጉሥ ለራሱ ያስነሳል። 15 ይሖዋ በውኃ ውስጥ እንደሚወዛወዝ ሸምበቆ እስራኤልን ይመታል፤ እንዲሁም እስራኤላውያንን ለአባቶቻቸው ከሰጣቸው ከዚህ መልካም ምድር ላይ ይነቅላቸዋል፤+ ከወንዙም* ማዶ ይበትናቸዋል፤+ ምክንያቱም የማምለኪያ ግንዶችን*+ ለራሳቸው በማቆም ይሖዋን አስቆጥተውታል። 16 እሱም ኢዮርብዓም በሠራው ኃጢአትና እስራኤላውያን እንዲሠሩ ባደረገው ኃጢአት የተነሳ እስራኤልን ይተዋል።”+
17 በዚህ ጊዜ የኢዮርብዓም ሚስት ተነስታ በመሄድ ወደ ቲርጻ መጣች። ቤቱ ደጃፍ ላይ ስትደርስም ልጁ ሞተ። 18 ይሖዋ በአገልጋዩ በነቢዩ አኪያህ አማካኝነት በተናገረውም መሠረት ቀበሩት፤ እስራኤልም ሁሉ አለቀሰለት።
19 ኢዮርብዓም ስላደረገው ውጊያና+ ስለ አገዛዙ የሚናገረው የቀረው ታሪኩ በእስራኤል ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፏል። 20 ኢዮርብዓም የገዛበት የጊዜ ርዝመት* 22 ዓመት ነበር፤ ከዚያም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤+ በእሱም ምትክ ልጁ ናዳብ ነገሠ።+
21 ይህ በእንዲህ እንዳለ የሰለሞን ልጅ ሮብዓም በይሁዳ ላይ ነግሦ ነበር። ሮብዓም በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 41 ዓመት ነበር፤ እሱም ይሖዋ ስሙ እንዲኖርባት+ ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ መካከል በመረጣት ከተማ+ በኢየሩሳሌም ሆኖ ለ17 ዓመት ገዛ። እናቱም ናዕማ የተባለች አሞናዊት+ ነበረች። 22 ይሁዳም በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ፤+ እነሱም በፈጸሙት ኃጢአት የተነሳ ከአባቶቻቸው ይበልጥ አስቆጡት።+ 23 እነሱም ቢሆኑ በእያንዳንዱ ኮረብታ+ ላይና በእያንዳንዱ የለመለመ ዛፍ+ ሥር ከፍ ያሉ የማምለኪያ ቦታዎችን፣ የማምለኪያ ዓምዶችንና የማምለኪያ ግንዶችን*+ ለራሳቸው ሠሩ። 24 ሌላው ቀርቶ በምድሪቱ ላይ የቤተ መቅደስ ቀላጮች* ነበሩ።+ ይሖዋ ከእስራኤላውያን ፊት አባሮ ያስወጣቸው ብሔራት ይፈጽሟቸው የነበሩትን አስጸያፊ ነገሮች በሙሉ አደረጉ።
25 ንጉሥ ሮብዓም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት የግብፁ ንጉሥ ሺሻቅ+ ኢየሩሳሌምን ለመውጋት መጣ።+ 26 እሱም በይሖዋ ቤት የነበሩትን ውድ ንብረቶችና በንጉሡ ቤት* የነበሩትን ውድ ንብረቶች ወሰደ።+ ሰለሞን የሠራቸውን የወርቅ ጋሻዎች ጨምሮ ሁሉንም ነገር ወሰደ።+ 27 በመሆኑም ንጉሥ ሮብዓም በእነሱ ምትክ የመዳብ ጋሻዎችን ሠርቶ የንጉሡን ቤት በር ለሚጠብቁት የዘብ* አለቆች ሰጣቸው። 28 ዘቦቹም ንጉሡ ወደ ይሖዋ ቤት በመጣ ቁጥር ጋሻዎቹን ያነግቡ ነበር፤ ከዚያም ወደ ዘቦቹ ክፍል ይመልሷቸው ነበር።
29 የቀረው የሮብዓም ታሪክና ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉ በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም?+ 30 በሮብዓምና በኢዮርብዓም መካከል የማያቋርጥ ጦርነት ነበር።+ 31 በመጨረሻም ሮብዓም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊት ከተማም+ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ። እናቱ ናዕማ የተባለች አሞናዊት+ ነበረች። በእሱም ምትክ ልጁ አብያም*+ ነገሠ።
15 የናባጥ ልጅ ንጉሥ ኢዮርብዓም+ በነገሠ በ18ኛው ዓመት አብያም በይሁዳ ላይ ነገሠ።+ 2 እሱም በኢየሩሳሌም ለሦስት ዓመት ገዛ። የእናቱ ስም ማአካ+ ሲሆን እሷም የአቢሴሎም የልጅ ልጅ ነበረች። 3 እሱም አባቱ ከእሱ በፊት በሠራው ኃጢአት ሁሉ መመላለሱን ቀጠለ፤ ልቡ እንደቀድሞ አባቱ እንደ ዳዊት ልብ በአምላኩ በይሖዋ ዘንድ ሙሉ* አልነበረም። 4 ሆኖም በዳዊት+ የተነሳ አምላኩ ይሖዋ ከእሱ በኋላ ልጁን በማስነሳትና ኢየሩሳሌም ጸንታ እንድትኖር በማድረግ በኢየሩሳሌም መብራት ሰጠው።+ 5 ምክንያቱም ዳዊት በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር አድርጓል፤ እንዲሁም ከሂታዊው ከኦርዮ ጋር በተያያዘ ከፈጸመው ነገር በስተቀር በሕይወት ዘመኑ ሁሉ እሱ ከሰጠው ከየትኛውም ትእዛዝ ፈቀቅ አላለም።+ 6 በሕይወት ዘመኑ ሁሉ በሮብዓምና በኢዮርብዓም መካከል ጦርነት ነበር።+
7 የቀረው የአብያም ታሪክ፣ ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉ በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም?+ በአብያምና በኢዮርብዓም መካከልም ጦርነት ነበር።+ 8 በመጨረሻም አብያም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊት ከተማም ቀበሩት፤ በእሱም ምትክ+ ልጁ አሳ+ ነገሠ።
9 የእስራኤል ንጉሥ ኢዮርብዓም በነገሠ በ20ኛው ዓመት አሳ በይሁዳ ላይ መግዛት ጀመረ። 10 እሱም በኢየሩሳሌም ለ41 ዓመት ገዛ። የአያቱም ስም ማአካ+ ሲሆን እሷም የአቢሴሎም የልጅ ልጅ ነበረች። 11 አሳ እንደ አባቱ እንደ ዳዊት በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር አደረገ።+ 12 እሱም የቤተ መቅደስ ቀላጮችን* ከምድሪቱ አባረረ፤+ እንዲሁም አባቶቹ የሠሯቸውን አስጸያፊ ጣዖቶች* በሙሉ አስወገደ።+ 13 ሌላው ቀርቶ አያቱ ማአካ+ ለማምለኪያ ግንዱ* አምልኮ ጸያፍ ጣዖት ሠርታ ስለነበር ከእመቤትነቷ* ሻራት። አሳ፣ አያቱ የሠራችውን ጸያፍ ጣዖት ቆርጦ+ በቄድሮን ሸለቆ+ አቃጠለው። 14 ከፍ ያሉት የማምለኪያ ቦታዎች ግን አልተወገዱም ነበር።+ ያም ሆኖ አሳ በሕይወት ዘመኑ* ሁሉ ልቡ በይሖዋ ዘንድ ሙሉ* ነበር። 15 እሱና አባቱ የቀደሷቸውን ነገሮች ይኸውም ብሩን፣ ወርቁንና ልዩ ልዩ ዕቃዎችን ወደ ይሖዋ ቤት አስገባ።+
16 በአሳና የእስራኤል ንጉሥ በሆነው በባኦስ+ መካከል የማያቋርጥ ጦርነት ነበር። 17 በመሆኑም የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ በይሁዳ ላይ ዘመተ፤ እሱም ማንም ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሳ እንዳይገባና እንዳይወጣ* ለማድረግ ራማን+ መገንባት* ጀመረ።+ 18 በዚህ ጊዜ አሳ በይሖዋ ቤት ግምጃ ቤትና በንጉሡ ቤት* ግምጃ ቤት የቀረውን ብርና ወርቅ ሁሉ አውጥቶ ለአገልጋዮቹ ሰጣቸው። ከዚያም ንጉሥ አሳ እነዚህን አገልጋዮቹን በደማስቆ ወደሚገኘው የሶርያ ንጉሥ+ ማለትም የሄዝዮን ልጅ፣ የታብሪሞን ልጅ ወደሆነው ወደ ቤንሃዳድ እንዲህ ሲል ላካቸው፦ 19 “በእኔና በአንተ እንዲሁም በአባቴና በአባትህ መካከል ውል* አለ። እኔ የብርና የወርቅ ስጦታ ልኬልሃለሁ። ስለዚህ ና፣ የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ ከእኔ እንዲርቅ ከእሱ ጋር የገባኸውን ውል* አፍርስ።” 20 ቤንሃዳድ የንጉሥ አሳን ሐሳብ ተቀብሎ የጦር ሠራዊቱን አለቆች በእስራኤል ከተሞች ላይ አዘመተ፤ እነሱም ኢዮንን፣+ ዳንን፣+ አቤልቤትማዓካን እንዲሁም ኪኔሬትን ሁሉና መላውን የንፍታሌም ምድር መቱ። 21 ባኦስም ይህን ሲሰማ ወዲያውኑ ራማን መገንባቱን* አቁሞ በቲርጻ+ መኖሩን ቀጠለ። 22 ከዚያም ንጉሥ አሳ ማንንም ሳያስቀር የይሁዳን ሰዎች ሁሉ ሰበሰበ፤ እነሱም ባኦስ እየገነባባቸው የነበሩትን የራማን ድንጋዮችና ሳንቃዎች አጋዙ፤ ንጉሥ አሳም በድንጋዮቹና በሳንቃዎቹ በቢንያም የምትገኘውን ጌባንና+ ምጽጳን+ ገነባ።*
23 የቀረው የአሳ ታሪክ ሁሉ፣ ኃያልነቱ ሁሉ፣ ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉና የገነባቸው* ከተሞች በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም? ሆኖም አሳ ባረጀ ጊዜ በእግር ሕመም ይሠቃይ ነበር።+ 24 በመጨረሻም አሳ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በአባቱ በዳዊት ከተማም ከእነሱ ጋር ተቀበረ፤ በእሱም ምትክ ልጁ ኢዮሳፍጥ+ ነገሠ።
25 የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት የኢዮርብዓም ልጅ ናዳብ+ የእስራኤል ንጉሥ ሆነ፤ እሱም በእስራኤል ላይ ለሁለት ዓመት ገዛ። 26 በይሖዋም ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር ማድረጉን ገፋበት፤ የአባቱንም መንገድ ተከተለ፤+ እንዲሁም አባቱ እስራኤላውያን እንዲፈጽሙ ባደረገው ኃጢአት ተመላለሰ።+ 27 ከይሳኮር ቤት የሆነው የአኪያህ ልጅ ባኦስ በእሱ ላይ አሴረ፤ ናዳብና እስራኤል ሁሉ የፍልስጤማውያን ከተማ የሆነችውን ጊበቶንን+ ከበው ሳሉ ባኦስ ጊበቶን ላይ ናዳብን ገደለው። 28 በመሆኑም ባኦስ የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት ናዳብን ገድሎ በምትኩ ነገሠ። 29 እሱም እንደነገሠ ወዲያውኑ የኢዮርብዓምን ቤት ሁሉ ፈጀ። ከኢዮርብዓም ቤት እስትንፋስ ያለውን አንድም ሰው አላስቀረም፤ ይሖዋ በአገልጋዩ በሴሎናዊው በአኪያህ በኩል በተናገረው መሠረት ሁሉንም ደመሰሳቸው።+ 30 ይህም የሆነው ኢዮርብዓም በፈጸመው ኃጢአትና እስራኤላውያን እንዲፈጽሙ ባደረገው ኃጢአት የእስራኤልን አምላክ ይሖዋን ክፉኛ ስላስቆጣው ነው። 31 የቀረው የናዳብ ታሪክና ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉ በእስራኤል ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም? 32 በአሳና የእስራኤል ንጉሥ በሆነው በባኦስ መካከል የማያቋርጥ ጦርነት ነበር።+
33 የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት የአኪያህ ልጅ ባኦስ በቲርጻ ሆኖ በመላው እስራኤል ላይ ለ24 ዓመት ገዛ።+ 34 ሆኖም በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር ማድረጉን ገፋበት፤+ የኢዮርብዓምን መንገድ ተከተለ፤ እንዲሁም ኢዮርብዓም እስራኤላውያን እንዲፈጽሙ ባደረገው ኃጢአት ተመላለሰ።+
16 ከዚያም በባኦስ ላይ የተነገረው የይሖዋ ቃል የሃናኒ+ ልጅ ወደሆነው ወደ ኢዩ+ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2 “ከአቧራ ላይ አንስቼ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መሪ አደረግኩህ፤+ አንተ ግን የኢዮርብዓምን መንገድ ተከተልክ፤ ሕዝቤ እስራኤልም ኃጢአት እንዲሠራ አደረግክ፤ እነሱም በኃጢአታቸው አስቆጡኝ።+ 3 ስለሆነም ባኦስንና ቤቱን ሙልጭ አድርጌ እጠርጋለሁ፤ ቤቱንም እንደ ናባጥ ልጅ እንደ ኢዮርብዓም+ ቤት አደርገዋለሁ። 4 ከባኦስ ወገን የሆነውን በከተማ ውስጥ የሚሞተውን ሁሉ ውሾች ይበሉታል፤ ከእሱ ወገን የሆነውን በሜዳ ላይ የሚሞተውን ሁሉ ደግሞ የሰማይ አሞሮች ይበሉታል።”
5 የቀረው የባኦስ ታሪክ፣ ያደረጋቸው ነገሮችና ኃያልነቱ በእስራኤል ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም? 6 በመጨረሻም ባኦስ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በቲርጻም+ ተቀበረ፤ በእሱም ምትክ ልጁ ኤላህ ነገሠ። 7 በተጨማሪም ባኦስ ልክ እንደ ኢዮርብዓም ቤት በእጁ በሠራቸው ነገሮች ይሖዋን በማስቆጣት በፊቱ መጥፎ የሆነውን ነገር ሁሉ ስለፈጸመ እንዲሁም እሱን* ስለገደለ የይሖዋ ቃል የሃናኒ ልጅ በሆነው በነቢዩ ኢዩ አማካኝነት በባኦስና በቤቱ ላይ መጣ።+
8 የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በ26ኛው ዓመት የባኦስ ልጅ ኤላህ በቲርጻ ሆኖ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ ለሁለት ዓመትም ገዛ። 9 የግማሹ የሠረገላ ሠራዊት አለቃ የሆነው አገልጋዩ ዚምሪ በእሱ ላይ አሴረ፤ በዚህ ጊዜ ኤላህ በቲርጻ የሚገኘው የንጉሡ ቤት ኃላፊ በነበረው በአርጻ ቤት ጠጥቶ ሰክሮ ነበር። 10 የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በ27ኛው ዓመት ዚምሪ ገብቶ ኤላህን መትቶ ገደለው፤+ በእሱም ምትክ ነገሠ። 11 እሱም ነግሦ ገና በዙፋኑ ላይ እንደተቀመጠ የባኦስን ቤት ሁሉ መታ። ከዘመዶቹም* ሆነ ከወዳጆቹ መካከል አንድም ወንድ* አላስተረፈም። 12 በዚህ መንገድ ይሖዋ በነቢዩ ኢዩ+ አማካኝነት በባኦስ ላይ በተናገረው ቃል መሠረት ዚምሪ መላውን የባኦስን ቤት አጠፋ። 13 ይህም የሆነው ባኦስ እና ልጁ ኤላህ በፈጸሙት ኃጢአት እንዲሁም ከንቱ በሆኑት ጣዖቶቻቸው አማካኝነት የእስራኤልን አምላክ ይሖዋን በማስቆጣት እስራኤላውያን እንዲፈጽሙ ባደረጉት ኃጢአት የተነሳ ነው።+ 14 የቀረው የኤላህ ታሪክ፣ ያደረጋቸው ነገሮች ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም?
15 የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በ27ኛው ዓመት፣ ሠራዊቱ የፍልስጤማውያን የሆነችውን ጊበቶንን+ ከቦ በነበረበት ወቅት ዚምሪ በቲርጻ ለሰባት ቀን ነገሠ። 16 በኋላም ከተማዋን ከቦ የነበረው ሠራዊት “ዚምሪ ሴራ በመጠንሰስ ንጉሡን ገድሎታል” የሚል ወሬ ሰማ። በመሆኑም መላው እስራኤል የሠራዊቱ አለቃ የሆነውን ኦምሪን+ በዚያን ቀን በሰፈሩ ውስጥ በእስራኤል ላይ አነገሡት። 17 ኦምሪና ከእሱ ጋር የነበሩት እስራኤላውያን በሙሉ ከጊበቶን ወጥተው ቲርጻን ከበቡ። 18 ዚምሪም ከተማዋ መያዟን ሲያይ በንጉሡ ቤት* ወዳለው የማይደፈር ማማ ገብቶ በውስጡ እንዳለ ቤቱን በእሳት አቃጠለው፤ በዚህም የተነሳ ሞተ።+ 19 ይህም የሆነው የኢዮርብዓምን መንገድ በመከተል በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር በመፈጸም በሠራው በገዛ ኃጢአቱና እስራኤላውያን እንዲሠሩ ባደረገው ኃጢአት የተነሳ ነው።+ 20 የቀረው የዚምሪ ታሪክና የጠነሰሰው ሴራ በእስራኤል ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፎ ይገኝ የለም?
21 የእስራኤል ሕዝብ በሁለት አንጃ የተከፈለው በዚህ ጊዜ ነበር። አንደኛው ወገን የጊናትን ልጅ ቲብኒን ለማንገሥ ስለፈለገ የእሱ ተከታይ ሆነ፤ ሌላኛው ወገን ደግሞ ኦምሪን ተከተለ። 22 ሆኖም ኦምሪን የተከተለው ሕዝብ የጊናትን ልጅ ቲብኒን በተከተለው ሕዝብ ላይ አየለ። በመሆኑም ቲብኒ ሞተ፤ ኦምሪም ነገሠ።
23 የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በ31ኛው ዓመት ኦምሪ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ ለ12 ዓመትም ገዛ። በቲርጻም ሆኖ ለስድስት ዓመት ገዛ። 24 እሱም የሰማርያን ተራራ ከሼሜር ላይ በሁለት ታላንት* ብር ገዛ፤ በተራራውም ላይ ከተማ ገነባ። የገነባትንም ከተማ የተራራው ጌታ በሆነው በሼሜር ስም ሰማርያ*+ ብሎ ሰየማት። 25 ኦምሪም በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር ማድረጉን ቀጠለ፤ ከእሱ በፊት ከነበሩት ሁሉ የከፋ ድርጊት ፈጸመ።+ 26 የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም በሄደበት መንገድ ሁሉ ሄደ፤ እንዲሁም ኢዮርብዓም እስራኤላውያን በከንቱ ጣዖቶቻቸው አማካኝነት የእስራኤልን አምላክ ይሖዋን እንዲያስቆጡት በማድረግ በተከተለው የኃጢአት ጎዳና ተመላለሰ።+ 27 የቀረው የኦምሪ ታሪክ፣ ያደረጋቸው ነገሮችና በኃያልነቱ የፈጸማቸው ጀብዱዎች በእስራኤል ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም? 28 በመጨረሻም ኦምሪ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በሰማርያም ተቀበረ፤ በእሱም ምትክ ልጁ አክዓብ+ ነገሠ።
29 የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በ38ኛው ዓመት የኦምሪ ልጅ አክዓብ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ የኦምሪ ልጅ አክዓብ በሰማርያ+ ሆኖ በእስራኤል ላይ ለ22 ዓመት ገዛ። 30 የኦምሪ ልጅ አክዓብ ከእሱ በፊት የነበሩት ሁሉ ከፈጸሙት የከፋ ድርጊት በይሖዋ ፊት ፈጸመ።+ 31 አክዓብ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም+ በተከተለው የኃጢአት ጎዳና መመላለሱ ሳያንሰው የሲዶናውያን+ ንጉሥ የኤትባዓል ልጅ የሆነችውን ኤልዛቤልን+ አገባ፤ እንዲሁም ባአልን ማገልገልና+ ለእሱ መስገድ ጀመረ። 32 እንዲሁም በሰማርያ ለባአል በሠራው ቤት+ ውስጥ* ለባአል መሠዊያ አቆመ። 33 በተጨማሪም አክዓብ የማምለኪያ ግንድ* ሠራ።+ እንዲሁም ከእሱ በፊት ከነበሩት የእስራኤል ነገሥታት ሁሉ ይበልጥ የእስራኤልን አምላክ ይሖዋን የሚያስቆጣ ድርጊት ፈጸመ።
34 በአክዓብ ዘመን የቤቴል ሰው የሆነው ሂኤል ኢያሪኮን መልሶ ገነባ። ይሖዋ በነዌ ልጅ በኢያሱ አማካኝነት በተናገረው ቃል መሠረት የከተማዋን መሠረት ሲጥል የበኩር ልጁ አቤሮን ሞተ፤ በሮቿን ሲያቆም ደግሞ የመጨረሻ ልጁ ሰጉብ ሞተ።+
17 በዚህ ጊዜ ከጊልያድ+ ነዋሪዎች አንዱ የሆነው ቲሽባዊው ኤልያስ*+ አክዓብን “በማገለግለውና* ሕያው በሆነው በእስራኤል አምላክ በይሖዋ እምላለሁ፣ በእኔ ትእዛዝ ካልሆነ በቀር በእነዚህ ዓመታት ጠል ወይም ዝናብ አይኖርም!” አለው።+
2 የይሖዋም ቃል እንዲህ ሲል ወደ እሱ መጣ፦ 3 “ከዚህ ተነስተህ ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ ሂድ፤ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ በሚገኘው በከሪት ሸለቆም* ተደበቅ። 4 ከጅረቱ ትጠጣለህ፤ ቁራዎችም እዚያ ምግብ እንዲያመጡልህ አዛለሁ።”+ 5 እሱም ወዲያውኑ ሄዶ ይሖዋ እንዳዘዘው አደረገ፤ ሄዶም ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ በሚገኘው በከሪት ሸለቆ* ተቀመጠ። 6 ቁራዎቹም ጠዋትና ማታ ምግብና ሥጋ ያመጡለት ነበር፤ እሱም ከጅረቱ ይጠጣ ነበር።+ 7 ሆኖም በምድሪቱ ላይ ዝናብ ስላልዘነበ ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ጅረቱ ደረቀ።+
8 ከዚያም የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ወደ እሱ መጣ፦ 9 “ተነስተህ በሲዶና ወደምትገኘው ወደ ሰራፕታ ሂድ፤ እዚያም ተቀመጥ። እኔም በዚያ አንዲት መበለት እንድትመግብህ አዛለሁ።”+ 10 ኤልያስም ተነስቶ ወደ ሰራፕታ ሄደ። ወደ ከተማዋ መግቢያ በደረሰም ጊዜ አንዲት መበለት ጭራሮ ስትለቅም አገኘ። መበለቲቱንም ጠርቶ “እባክሽ የምጠጣው ትንሽ ውኃ በዕቃ ስጪኝ” አላት።+ 11 ልታመጣለት ስትሄድም ጠራትና “እባክሽ ቁራሽ ዳቦም ይዘሽልኝ ነይ” አላት። 12 በዚህ ጊዜ እንዲህ አለችው፦ “ሕያው በሆነው አምላክህ በይሖዋ እምላለሁ፣ በማድጋው ውስጥ ካለው አንድ እፍኝ ዱቄትና በማሰሮው ውስጥ ካለው ጥቂት ዘይት በስተቀር ምንም ዳቦ የለኝም።+ ለእኔና ለልጄ የሆነች ነገር ለማዘጋጀት ጭራሮ እየለቀምኩ ነው። እኛም እሷን ቀምሰን እንሞታለን።”
13 ከዚያም ኤልያስ እንዲህ አላት፦ “አይዞሽ ስጋት አይግባሽ። ወደ ቤት ገብተሽ እንዳልሽው አድርጊ። ብቻ በመጀመሪያ ከዚያችው ካለችሽ ላይ ትንሽ ቂጣ ጋግረሽ አምጪልኝ። ከዚያ በኋላ ለአንቺና ለልጅሽ የሆነ ነገር ማዘጋጀት ትችያለሽ። 14 ምክንያቱም የእስራኤል አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ይሖዋ በምድሪቱ ላይ ዝናብ እስከሚያዘንብበት ዕለት ድረስ ከማድጋው ዱቄት አይጠፋም፤ ከማሰሮውም ዘይት አያልቅም።’”+ 15 ስለሆነም ሄዳ ኤልያስ እንዳላት አደረገች፤ እሷም ሆነች እሱ እንዲሁም ቤተሰቧ ለብዙ ቀናት ሲመገቡ ቆዩ።+ 16 ይሖዋ በኤልያስ አማካኝነት በተናገረው ቃል መሠረት ከማድጋው ዱቄት አልጠፋም፤ ከማሰሮውም ዘይት አላለቀም።
17 ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ የቤቱ ባለቤት፣ ልጇ ታመመ፤ ሕመሙም እጅግ ስለጠናበት እስትንፋሱ ቀጥ አለ።+ 18 በዚህ ጊዜ ሴትየዋ ኤልያስን “የእውነተኛው አምላክ ሰው ሆይ፣ ምን አደረግኩህ?* የመጣኸው በደሌን ልታስታውሰኝና ልጄን ልትገድል ነው?” አለችው።+ 19 እሱ ግን “ልጅሽን ስጪኝ” አላት። ከዚያም ልጁን ከእቅፏ ወስዶ እሱ ወዳረፈበት በሰገነቱ ላይ ወዳለው ክፍል ይዞት ወጣ፤ ልጁንም በራሱ አልጋ ላይ አስተኛው።+ 20 እሱም “አምላኬ ይሖዋ ሆይ፣+ እኔን ያሳረፈችኝ የዚህች መበለት ልጅ እንዲሞት በማድረግ በእሷም ላይ መከራ ታመጣባታለህ?” በማለት ወደ ይሖዋ ጮኸ። 21 ከዚያም ልጁ ላይ ሦስት ጊዜ ከተዘረጋበት በኋላ “አምላኬ ይሖዋ ሆይ፣ እባክህ የዚህ ልጅ ሕይወት ይመለስለት”* ብሎ ወደ ይሖዋ ጮኸ። 22 ይሖዋም የኤልያስን ልመና ሰማ፤+ የልጁም ሕይወት ተመለሰለት፤* እሱም ሕያው ሆነ።+ 23 ከዚያም ኤልያስ ልጁን ይዞት ሰገነት ላይ ካለው ክፍል ወደ ቤት ከወረደ በኋላ ለእናቱ ሰጣት፤ ኤልያስም “ይኸው፣ ልጅሽ ሕያው ሆኗል” አላት።+ 24 በዚህ ጊዜ ሴትየዋ ኤልያስን “አንተ በእርግጥ የአምላክ ሰው+ እንደሆንክ በአንደበትህም ያለው የይሖዋ ቃል እውነት እንደሆነ አሁን አወቅኩ” አለችው።
18 ከተወሰነ ጊዜ በኋላም በሦስተኛው ዓመት+ የይሖዋ ቃል “ሂድና አክዓብ ፊት ቅረብ፤ እኔም በምድሩ ላይ ዝናብ አዘንባለሁ”+ ሲል ወደ ኤልያስ መጣ። 2 ስለሆነም ኤልያስ አክዓብ ፊት ለመቅረብ ሄደ፤ በዚህ ወቅት ረሃቡ በሰማርያ ክፉኛ ጸንቶ ነበር።+
3 በዚህ ጊዜ አክዓብ በቤቱ ላይ አዛዥ የነበረውን አብድዩን ጠራው። (አብድዩ ይሖዋን በጣም ይፈራ ነበር፤ 4 ኤልዛቤል+ የይሖዋን ነቢያት እያጠፋች በነበረበት ጊዜም አብድዩ 100 ነቢያትን ወስዶ 50ውን በአንድ ዋሻ 50ውን ደግሞ በሌላ ዋሻ ውስጥ ከደበቃቸው በኋላ ምግብና ውኃ ይሰጣቸው ነበር።) 5 ከዚያም አክዓብ አብድዩን እንዲህ አለው፦ “በምድሪቱ ላይ ወደሚገኙት የውኃ ምንጮች ሁሉና ሸለቆዎች* ሁሉ ሂድ። እንስሶቻችን በሙሉ እንዳያልቁ፣ ፈረሶቹንና በቅሎዎቹን በሕይወት ማቆየት የሚያስችል በቂ ሣር እናገኝ ይሆናል።” 6 በመሆኑም አቋርጠውት የሚሄዱትን ምድር ተከፋፈሉ። አክዓብ ለብቻው በአንድ በኩል፣ አብድዩም ለብቻው በሌላ በኩል ሄደ።
7 አብድዩ እየተጓዘ ሳለ ኤልያስን መንገዱ ላይ አገኘው። እሱም ወዲያውኑ ስላወቀው በግንባሩ ተደፋ፤ ከዚያም “ጌታዬ ኤልያስ ሆይ፣ በእርግጥ አንተ ነህ?” አለው።+ 8 ኤልያስም “አዎ፣ እኔ ነኝ። ሄደህ ለጌታህ ‘ኤልያስ እዚህ አለ’ ብለህ ንገረው” አለው። 9 እሱ ግን እንዲህ አለው፦ “እኔ አገልጋይህ እንድሞት ለአክዓብ አሳልፈህ የምትሰጠኝ ምን ኃጢአት ሠርቼ ነው? 10 ሕያው በሆነው አምላክህ በይሖዋ እምላለሁ፣ ጌታዬ አንተን ፍለጋ ሰው ያልላከበት አንድም ብሔር ሆነ መንግሥት የለም። እነሱም ‘እዚህ የለም’ ባሉት ጊዜ ያ መንግሥትም ሆነ ብሔር አንተን አለማግኘቱን በመሐላ እንዲያረጋግጥለት ያደርግ ነበር።+ 11 አንተ ደግሞ አሁን ‘ሄደህ ለጌታህ “ኤልያስ እዚህ አለ” ብለህ ንገረው’ ትለኛለህ። 12 ከአንተ ተለይቼ ስሄድ የይሖዋ መንፈስ ወደማላውቀው ቦታ ይወስድሃል፤+ ለአክዓብ ብነግረውና ሳያገኝህ ቢቀር እንደሚገድለኝ የታወቀ ነው። ነገር ግን እኔ አገልጋይህ ከወጣትነቴ ጀምሮ ይሖዋን ስፈራ ኖሬአለሁ። 13 ኤልዛቤል የይሖዋን ነቢያት በገደለች ጊዜ ከይሖዋ ነቢያት መካከል 100ዎቹን ወስጄ ሃምሳ ሃምሳ በማድረግ ዋሻ ውስጥ እንደደበቅኳቸው እንዲሁም ምግብና ውኃ እሰጣቸው እንደነበር ጌታዬ አልሰማም?+ 14 አሁን ግን አንተ ‘ሄደህ ለጌታህ “ኤልያስ እዚህ አለ” ብለህ ንገረው’ ትለኛለህ። እሱም በእርግጠኝነት ይገድለኛል።” 15 ሆኖም ኤልያስ “በማገለግለው* ሕያው በሆነው በሠራዊት ጌታ በይሖዋ እምላለሁ፣ ዛሬ እሱ ፊት እቀርባለሁ” አለ።
16 ስለዚህ አብድዩ ወደ አክዓብ ሄዶ ነገረው፤ አክዓብም ኤልያስን ለማግኘት ሄደ።
17 አክዓብም ልክ ኤልያስን ሲያየው “በእስራኤል ላይ ከፍተኛ ችግር የምትፈጥረው* አንተ ነህ?” አለው።
18 በዚህ ጊዜ ኤልያስ እንዲህ አለው፦ “የይሖዋን ትእዛዛት በመተውና ባአልን በመከተል በእስራኤል ላይ ችግር የምትፈጥሩት+ አንተና የአባትህ ቤት እንጂ እኔ አይደለሁም። 19 ይልቅስ አሁን እስራኤላውያንን በሙሉ፣ ከኤልዛቤል ማዕድ ከሚበሉት 450 የባአል ነቢያትና 400 የማምለኪያ ግንድ*+ ነቢያት ጋር በቀርሜሎስ+ ተራራ ላይ ሰብስብልኝ።” 20 በመሆኑም አክዓብ ወደ እስራኤል ሰዎች ሁሉ መልእክት ላከ፤ ነቢያቱንም በቀርሜሎስ ተራራ ላይ ሰበሰበ።
21 ከዚያም ኤልያስ ወደ ሕዝቡ ሁሉ ቀርቦ “በሁለት ሐሳብ የምታነክሱት እስከ መቼ ነው?+ እውነተኛው አምላክ፣ ይሖዋ ከሆነ እሱን ተከተሉ፤+ ባአል ከሆነ ደግሞ እሱን ተከተሉ!” አላቸው። ሕዝቡ ግን አንዲት ቃል አልመለሰለትም። 22 ከዚያም ኤልያስ እንዲህ አላቸው፦ “ከይሖዋ ነቢያት መካከል የቀረሁት እኔ ብቻ ነኝ፤+ የባአል ነቢያት ግን 450 ናቸው። 23 እንግዲህ አሁን ሁለት ወይፈኖች ይስጡን፤ እነሱም አንድ ወይፈን መርጠው በየብልቱ እየቆራረጡ በእንጨቱ ላይ ያድርጉት፤ ሆኖም እሳት አያንድዱበት። እኔ ደግሞ ሌላኛውን ወይፈን አዘጋጅቼ በእንጨቱ ላይ አደርገዋለሁ፤ ሆኖም እሳት አላነድበትም። 24 ከዚያም እናንተ የአምላካችሁን ስም ትጠራላችሁ፤+ እኔም የይሖዋን ስም እጠራለሁ። እሳት በመላክ መልስ የሚሰጠው አምላክ እሱ እውነተኛው አምላክ እንደሆነ ያሳያል።”+ በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ “ያልከው ነገር ጥሩ ነው” አሉ።
25 ኤልያስም የባአል ነቢያትን “እናንተ ብዙ ስለሆናችሁ በቅድሚያ አንድ ወይፈን መርጣችሁ አዘጋጁ። ከዚያም የአምላካችሁን ስም ጥሩ፤ ሆኖም እሳት አታንድዱበት” አላቸው። 26 በመሆኑም የተሰጣቸውን ወይፈን ወስደው አዘጋጁ፤ ከጠዋት አንስቶ እስከ እኩለ ቀን ድረስም “ባአል ሆይ፣ መልስልን!” እያሉ የባአልን ስም ጠሩ። ሆኖም ድምፅ የለም፤ የሚመልስም አልነበረም።+ በሠሩትም መሠዊያ ዙሪያ እያነከሱ ዞሩ። 27 እኩለ ቀን ገደማም ኤልያስ እንዲህ በማለት ያፌዝባቸው ጀመር፦ “ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ ጩኹ እንጂ! አምላክ እኮ ነው!+ ምናልባት በሐሳብ ተውጦ ይሆናል፤ ወይም ሊጸዳዳ ሄዶ ይሆናል።* አሊያም ደግሞ ተኝቶ ሊሆን ስለሚችል የሚቀሰቅሰው ያስፈልገው ይሆናል!” 28 እነሱም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ይጮኹ እንደ ልማዳቸውም ደም በደም እስኪሆኑ ድረስ ሰውነታቸውን በጩቤና በጦር ይተለትሉ ነበር። 29 እኩለ ቀን አልፎ የእህል መባ እስከሚቀርብበትም ጊዜ ድረስ እንደ እብድ* ሲያደርጋቸው ቆየ፤ ሆኖም ምንም ድምፅ የለም፤ የሚመልስም የለም፤ ትኩረት የሰጠም አልነበረም።+
30 በኋላም ኤልያስ ሕዝቡን ሁሉ “ወደ እኔ ቅረቡ” አላቸው። ሕዝቡም ሁሉ ወደ እሱ ቀረቡ። ከዚያም ፈርሶ የነበረውን የይሖዋን መሠዊያ ጠገነ።+ 31 በመቀጠልም ኤልያስ “ስምህ እስራኤል ይባላል”+ የሚል የይሖዋ ቃል በመጣለት በያዕቆብ ወንዶች ልጆች ነገዶች ቁጥር ልክ 12 ድንጋዮችን ወሰደ። 32 በድንጋዮቹም በይሖዋ ስም መሠዊያ ሠራ።+ በመሠዊያውም ዙሪያ ሁለት የሲህ መስፈሪያ* ዘር ሊያዘራ የሚችል ስፋት ያለው ቦይ ቆፈረ። 33 ከዚያም እንጨቶቹን ረበረበ፤ ወይፈኑንም በየብልቱ ቆራርጦ በእንጨቶቹ ላይ አደረገ።+ ቀጥሎም “በአራት ጋኖች ውኃ ሞልታችሁ በሚቃጠለው መባና በእንጨቱ ላይ አፍስሱ” አለ። 34 ከዚያም “አሁንም ድገሙ” አለ። እነሱም ደገሙ። “ለሦስተኛ ጊዜ ድገሙ” አላቸው። እነሱም ለሦስተኛ ጊዜ ደገሙ። 35 ውኃውም መሠዊያውን ዙሪያውን አጥለቀለቀው፤ ቦዩንም በውኃ ሞላው።
36 ነቢዩ ኤልያስም የምሽቱ የእህል መባ በሚቀርብበት ጊዜ+ ገደማ ወደ ፊት ቀረብ ብሎ እንዲህ አለ፦ “የአብርሃም፣+ የይስሐቅና+ የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ሆይ፣ አንተ በእስራኤል ውስጥ አምላክ እንደሆንክ፣ እኔም አገልጋይህ እንደሆንኩና እነዚህን ሁሉ ነገሮች ያደረግኩት በአንተ ቃል እንደሆነ ዛሬ ይታወቅ።+ 37 ይሖዋ ሆይ፣ መልስልኝ! እነዚህ ሰዎች አንተ ይሖዋ እውነተኛው አምላክ እንደሆንክና ልባቸውን ወደ አንተ እየመለስክ መሆንህን እንዲያውቁ መልስልኝ።”+
38 በዚህ ጊዜ የይሖዋ እሳት ወርዶ የሚቃጠለውን መባ፣ እንጨቱን፣ ድንጋዮቹንና አፈሩን በላ፤+ በቦዩ ውስጥ የነበረውንም ውኃ ላሰ።+ 39 ሕዝቡ ሁሉ ይህን ሲያዩ ወዲያውኑ በግንባራቸው ተደፉ፤ ከዚያም “እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ነው! እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ነው!” አሉ። 40 በዚህ ጊዜ ኤልያስ “የባአልን ነቢያት ያዟቸው! አንዳቸውም እንዳያመልጡ!” አላቸው። እነሱም ወዲያውኑ ያዟቸው፤ ኤልያስም ወደ ቂሾን ጅረት*+ ይዟቸው በመውረድ በዚያ አረዳቸው።+
41 ኤልያስም አክዓብን “የከባድ ዝናብ ድምፅ እያጉረመረመ ስለሆነ ሂድ ብላ፤ ጠጣም” አለው።+ 42 በመሆኑም አክዓብ ሊበላና ሊጠጣ ሲወጣ ኤልያስ ደግሞ ወደ ቀርሜሎስ አናት ወጣ፤ ፊቱንም በጉልበቶቹ መካከል አድርጎ ወደ መሬት አቀረቀረ።+ 43 ከዚያም አገልጋዩን “እባክህ ውጣና ወደ ባሕሩ አቅጣጫ ተመልከት” አለው። እሱም ወጥቶ ተመለከተና “ኧረ ምንም የለም” አለ። ኤልያስም ሰባት ጊዜ “ተመልሰህ ሂድ” አለው። 44 በሰባተኛውም ጊዜ አገልጋዩ “እነሆ! የሰው እጅ የምታክል ትንሽ ደመና ከባሕሩ እየወጣች ነው” አለ። ኤልያስም “ሄደህ አክዓብን ‘ሠረገላህን አዘጋጅ! ዝናቡ እንዳያግድህ ወደዚያ ውረድ!’ በለው” አለው። 45 በዚህ ጊዜ ሰማዩ በደመና ጠቆረ፤ ነፋስም ነፈሰ፤ ከባድ ዝናብም ይጥል ጀመር፤+ አክዓብም እየጋለበ ወደ ኢይዝራኤል+ ሄደ። 46 ሆኖም የይሖዋ እጅ በኤልያስ ላይ መጣ፤ እሱም ልብሱን ጠቅልሎ መቀነቱ ውስጥ በመሸጎጥ* ከአክዓብ ፊት ፊት እየሮጠ እስከ ኢይዝራኤል ድረስ ሄደ።
19 ከዚያም አክዓብ+ ኤልያስ ያደረገውን ሁሉና ነቢያቱን በሙሉ እንዴት በሰይፍ እንደገደለ+ ለኤልዛቤል+ ነገራት። 2 በዚህ ጊዜ ኤልዛቤል “ነገ በዚህ ሰዓት ከእነሱ እንደ አንዱ ሳላደርግህ* ብቀር አማልክት እንዲህ ያድርጉብኝ፤ ከዚህ የባሰም ያምጡብኝ!” ብሎ ለኤልያስ እንዲነግረው መልእክተኛ ላከችበት። 3 በዚህ ጊዜ ኤልያስ ፈራ፤ በመሆኑም ሕይወቱን* ለማትረፍ ሸሸ።+ በይሁዳ ወደምትገኘው+ ወደ ቤርሳቤህም+ መጣ፤ አገልጋዩንም እዚያ ተወው። 4 ከዚያም በምድረ በዳው የአንድ ቀን መንገድ ከተጓዘ በኋላ ወደ አንድ የክትክታ ዛፍ ሲደርስ ሥሩ ተቀመጠ፤ እንዲሞትም* መለመን ጀመረ። እንዲህም አለ፦ “አሁንስ በቅቶኛል! ይሖዋ ሆይ፣ እኔ ከአባቶቼ አልበልጥምና ሕይወቴን* ውሰዳት።”+
5 ከዚያም በክትክታው ዛፍ ሥር ጋደም አለ፤ እንቅልፍም ወሰደው። ሆኖም ድንገት አንድ መልአክ ነካ አደረገውና+ “ተነስና ብላ” አለው።+ 6 እሱም ቀና ብሎ ሲመለከት ራስጌው አጠገብ በጋሉ ድንጋዮች ላይ የተቀመጠ ዳቦ እንዲሁም በውኃ መያዣ ዕቃ ውስጥ ያለ ውኃ አየ። እሱም ከበላና ከጠጣ በኋላ ተመልሶ ተኛ። 7 በኋላም የይሖዋ መልአክ ለሁለተኛ ጊዜ መጥቶ ነካ አደረገውና “ሩቅ መንገድ ስለምትጓዝ ተነስና ብላ” አለው። 8 ስለሆነም ተነስቶ በላ፤ ጠጣም፤ ከምግቡም ባገኘው ብርታት እስከ እውነተኛው አምላክ ተራራ እስከ ኮሬብ+ ድረስ ለ40 ቀንና ለ40 ሌሊት ተጓዘ።
9 እዚያም ሲደርስ ወደ አንድ ዋሻ+ ገብቶ አደረ፤ በዚህ ጊዜ የይሖዋ ቃል ወደ እሱ መጥቶ “ኤልያስ እዚህ ምን ታደርጋለህ?” አለው። 10 እሱም እንዲህ አለ፦ “እኔ ለሠራዊት ጌታ ለይሖዋ እጅግ ቀንቻለሁ፤+ ምክንያቱም የእስራኤል ሰዎች ቃል ኪዳንህን ትተዋል፤+ መሠዊያዎችህንም አፈራርሰዋል፤ ነቢያትህን በሰይፍ ገድለዋል፤+ እንግዲህ የቀረሁት እኔ ብቻ ነኝ። ይኸው አሁን ደግሞ የእኔንም ሕይወት* ለማጥፋት እየፈለጉ ነው።”+ 11 እሱ ግን “ውጣና ተራራው ላይ ይሖዋ ፊት ቁም” አለው። በዚህ ጊዜ ይሖዋ እያለፈ+ ነበር፤ ታላቅና ኃይለኛ ነፋስም በይሖዋ ፊት ተራሮቹን ሰነጣጠቀ፤+ ዓለቶቹንም ፈረካከሰ፤ ይሖዋ ግን በነፋሱ ውስጥ አልነበረም። ከነፋሱ ቀጥሎ ደግሞ የምድር መናወጥ ተከሰተ፤ ይሖዋ ግን በምድር መናወጡ+ ውስጥ አልነበረም። 12 ከምድር መናወጡ በኋላም እሳት+ መጣ፤ ይሖዋ ግን በእሳቱ ውስጥ አልነበረም። ከእሳቱ በኋላ ደግሞ ዝግ ያለና ለስለስ ያለ ድምፅ ተሰማ።+ 13 ኤልያስ ይህን ድምፅ ሲሰማ ወዲያውኑ በለበሰው የነቢይ ልብስ ፊቱን ሸፈነ፤+ ወጥቶም ዋሻው ደጃፍ ላይ ቆመ። ከዚያም አንድ ድምፅ “ኤልያስ እዚህ ምን ታደርጋለህ?” ሲል ጠየቀው። 14 እሱም እንዲህ አለ፦ “እኔ ለሠራዊት ጌታ ለይሖዋ እጅግ ቀንቻለሁ፤ ምክንያቱም የእስራኤል ሰዎች ቃል ኪዳንህን ትተዋል፤+ መሠዊያዎችህንም አፈራርሰዋል፤ ነቢያትህን በሰይፍ ገድለዋል፤ እንግዲህ የቀረሁት እኔ ብቻ ነኝ። ይኸው አሁን ደግሞ የእኔንም ሕይወት* ለማጥፋት እየፈለጉ ነው።”+
15 ይሖዋም እንዲህ አለው፦ “ወደ ደማስቆ ምድረ በዳ ተመልሰህ ሂድ። እዚያም ስትደርስ ሃዛኤልን+ በሶርያ ላይ ንጉሥ አድርገህ ቀባው። 16 እንዲሁም የኒምሺን የልጅ ልጅ ኢዩን+ በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርገህ ቀባው፤ የአቤልምሆላ ሰው የሆነውን የሻፋጥን ልጅ ኤልሳዕን* ደግሞ በአንተ ምትክ ነቢይ አድርገህ ቀባው።+ 17 ከሃዛኤል ሰይፍ+ ያመለጠውን ኢዩ ይገድለዋል፤+ ከኢዩ ሰይፍ ያመለጠውን ደግሞ ኤልሳዕ ይገድለዋል።+ 18 እኔም ለባአል ያልተንበረከኩና+ እሱን ያልሳሙ+ በእስራኤል ውስጥ የቀሩ 7,000 ሰዎች አሉኝ።”+
19 ኤልያስም ከዚያ ወጥቶ ሄደ፤ የሻፋጥንም ልጅ ኤልሳዕን ከፊቱ 12 ጥማድ በሬዎች እያረሱ፣ እሱም በ12ኛው ጥማድ በሬ እያረሰ አገኘው። ኤልያስም ወደ እሱ በመሄድ የራሱን የነቢይ ልብስ+ አውልቆ ላዩ ላይ ጣል አደረገበት። 20 በዚህ ጊዜ ኤልሳዕ በሬዎቹን እዚያው በመተው ኤልያስን ተከትሎ እየሮጠ “እባክህ፣ አባቴንና እናቴን ስሜ እንድመጣ ፍቀድልኝ። ከዚያ በኋላ እከተልሃለሁ” አለው። እሱም “ሂድ ተመለስ፤ እኔ መቼ ከለከልኩህ?” አለው። 21 በመሆኑም ተመለሰ፤ ከዚያም አንድ ጥማድ በሬ ወስዶ መሥዋዕት አደረገ፤ በእርሻ መሣሪያዎቹም የበሬዎቹን ሥጋ በመቀቀል ለሕዝቡ ሰጠ፤ እነሱም በሉ። ይህን ካደረገ በኋላም ተነስቶ ኤልያስን ተከተለው፤ እሱንም ያገለግለው ጀመር።+
20 በዚህ ጊዜ የሶርያ+ ንጉሥ ቤንሃዳድ+ ጦር ሠራዊቱን በሙሉ አሰባሰበ፤ በተጨማሪም ሌሎች 32 ነገሥታትን ከነፈረሶቻቸውና ከነሠረገሎቻቸው አሰባሰበ፤ ወጥቶም ሰማርያን+ በመክበብ+ ውጊያ ከፈተባት። 2 ከዚያም በከተማዋ ውስጥ ወደሚገኘው ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ አክዓብ+ መልእክተኞች ልኮ እንዲህ አለው፦ “ቤንሃዳድ እንዲህ ይላል፦ 3 ‘ብርህና ወርቅህ እንዲሁም ከሚስቶችህና ከልጆችህ መካከል ምርጥ የሆኑት የእኔ ናቸው።’” 4 በዚህ ጊዜ የእስራኤል ንጉሥ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ አንተ እንዳልከው እኔም ሆንኩ የእኔ የሆነው ሁሉ የአንተ ነን” ሲል መለሰለት።+
5 በኋላም መልእክተኞቹ ተመልሰው በመምጣት እንዲህ አሉት፦ “ቤንሃዳድ እንዲህ ይላል፦ ‘እንዲህ የሚል መልእክት ልኬብህ ነበር፦ “ብርህን፣ ወርቅህን፣ ሚስቶችህንና ልጆችህን ትሰጠኛለህ።” 6 ሆኖም ነገ በዚህ ሰዓት ገደማ አገልጋዮቼን ወደ አንተ እልካለሁ፤ እነሱም የአንተን ቤትና የአገልጋዮችህን ቤት አንድ በአንድ ይበረብራሉ፤ ለአንተ ትልቅ ዋጋ ያለውን ነገር ሁሉ እጃቸው በማስገባት ይወስዳሉ።’”
7 በዚህ ጊዜ የእስራኤል ንጉሥ በምድሪቱ ያሉትን ሽማግሌዎች በሙሉ ጠርቶ “እንግዲህ ይህ ሰው በእኛ ላይ መከራ ለማምጣት ቆርጦ እንደተነሳ ልብ በሉ፤ ሚስቶቼን፣ ልጆቼን፣ ብሬንና ወርቄን እንድሰጠው ላከብኝ፤ እኔም አልከለከልኩትም” አላቸው። 8 ከዚያም ሽማግሌዎቹ ሁሉና ሕዝቡ በሙሉ “እሺ አትበለው፤ በዚህ አትስማማ” አሉት። 9 በመሆኑም የቤንሃዳድን መልእክተኞች “ጌታዬ ንጉሡን እንዲህ በሉት፦ ‘እኔ አገልጋይህ መጀመሪያ ላይ የጠየቅከኝን ነገር ሁሉ እፈጽማለሁ፤ ይህን ግን መፈጸም አልችልም’” አላቸው። መልእክተኞቹም ይህን መልእክት ይዘው ወደ እሱ ሄዱ።
10 ቤንሃዳድም “የሰማርያ አፈር ለሚከተለኝ ሕዝብ ሁሉ አንድ አንድ እፍኝ እንኳ ቢደርሰው አማልክት እንዲህ ያድርጉብኝ፤ ከዚህ የከፋም ያምጡብኝ!” የሚል መልእክት ላከበት። 11 የእስራኤልም ንጉሥ መልሶ “ቤንሃዳድን እንዲህ በሉት፦ ‘ለጦርነት እየታጠቀ ያለ ሰው ጦርነቱን ድል አድርጎ ትጥቁን እንደሚፈታ ሰው መደንፋት የለበትም’” አለ።+ 12 ቤንሃዳድና ነገሥታቱ በድንኳኖቻቸው ውስጥ ሆነው እየጠጡ ሳለ ቤንሃዳድ ይህን ምላሽ ሲሰማ አገልጋዮቹን “ጥቃት ለመሰንዘር ተዘጋጁ!” አላቸው። በመሆኑም በከተማዋ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ተዘጋጁ።
13 ሆኖም አንድ ነቢይ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ አክዓብ+ ቀርቦ “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ይህን እጅግ ብዙ ሕዝብ ትመለከታለህ? እኔ ዛሬ በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ፤ አንተም እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ታውቃለህ’” አለው።+ 14 አክዓብም “በማን አማካኝነት?” ሲል ጠየቀ፤ እሱም መልሶ “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘በአውራጃዎቹ መኳንንት አገልጋዮች አማካኝነት’” አለው። ስለሆነም አክዓብ “ታዲያ ውጊያውን የሚያስጀምረው ማን ነው?” አለ፤ እሱም “አንተ ነህ!” አለው።
15 ከዚያም አክዓብ የአውራጃዎቹን መኳንንት አገልጋዮች ቆጠረ፤ እነሱም 232 ነበሩ፤ በመቀጠልም የእስራኤልን ወንዶች በሙሉ ቆጠረ፤ እነሱም 7,000 ነበሩ። 16 እነሱም እኩለ ቀን ላይ ቤንሃዳድ ረዳቶቹ ከሆኑት 32 ነገሥታት ጋር በድንኳኖቹ ውስጥ ሆኖ ሰክሮ ሳለ ወደዚያ ሄዱ። 17 የአውራጃዎቹ መኳንንት አገልጋዮች ቀድመው በወጡ ጊዜ ቤንሃዳድ ወዲያውኑ መልእክተኞችን ላከ። እነሱም “ከሰማርያ የመጡ ሰዎች አሉ” ብለው ነገሩት። 18 በዚህ ጊዜ ቤንሃዳድ “ሰዎቹ የመጡት ለሰላም ከሆነ በሕይወት እንዳሉ ያዟቸው፤ የመጡት ለጦርነት ከሆነም በሕይወት እንዳሉ ያዟቸው” አለ። 19 ሆኖም እነዚህ ማለትም የአውራጃዎቹ መኳንንት አገልጋዮችና እነሱን ይከተላቸው የነበረው ሠራዊት ከከተማዋ ሲወጡ 20 እያንዳንዳቸው ሊገጥማቸው የመጣውን ሰው ገደሉ። ከዚያም ሶርያውያን ሸሹ፤+ እስራኤላውያንም አሳደዷቸው፤ የሶርያ ንጉሥ ቤንሃዳድ ግን በፈረስ ላይ ሆኖ ከተወሰኑ ፈረሰኞች ጋር አመለጠ። 21 ሆኖም የእስራኤል ንጉሥ ወጥቶ ፈረሶቹንና ሠረገሎቹን መታ፤ በሶርያውያንም ላይ ታላቅ ድል ተቀዳጀ።*
22 በኋላም ነቢዩ+ ወደ እስራኤል ንጉሥ ቀርቦ “የሶርያ ንጉሥ በሚቀጥለው ዓመት መባቻ* ላይ ስለሚመጣብህ+ ሄደህ ራስህን አጠናክር፤ ምን ማድረግ እንደምትችልም አስብ”+ አለው።
23 በዚህ ጊዜ የሶርያን ንጉሥ አገልጋዮቹ እንዲህ አሉት፦ “አምላካቸው የተራሮች አምላክ ነው። በእኛ ላይ ያየሉብንም ለዚህ ነው። ሆኖም ሜዳ ላይ ብንገጥማቸው እናሸንፋቸዋለን። 24 በተጨማሪም እንዲህ አድርግ፦ ነገሥታቱን በሙሉ ከቦታቸው አንስተህ+ በምትካቸው አስተዳዳሪዎች አስቀምጥ። 25 ከዚያም ከተደመሰሰብህ ሠራዊት ጋር የሚመጣጠን ሠራዊት ሰብስብ፤* በፈረሱ ፋንታ ፈረስ፣ በሠረገላውም ፋንታ ሠረገላ ተካ። ከዚያም ሜዳ ላይ እንግጠማቸው፤ ያለምንም ጥርጥር እናሸንፋቸዋለን።” ንጉሡም የሰጡትን ምክር ሰማ፤ እንዳሉትም አደረገ።
26 በዓመቱ መባቻ* ላይም ቤንሃዳድ ሶርያውያንን አሰባስቦ ከእስራኤል ጋር ለመዋጋት ወደ አፌቅ+ ወጣ። 27 የእስራኤል ሰዎችም ከተሰባሰቡና ስንቅ ከተሰጣቸው በኋላ እነሱን ለመግጠም ወጡ። የእስራኤል ሰዎች ፊት ለፊታቸው ሰፍረው ሲታዩ ሁለት ትናንሽ የፍየል መንጋ ይመስሉ ነበር፤ ሶርያውያኑ ግን መላውን ምድር አጥለቅልቀውት ነበር።+ 28 ከዚያም የእውነተኛው አምላክ ሰው ወደ እስራኤል ንጉሥ ቀርቦ “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ሶርያውያን “ይሖዋ የተራሮች አምላክ እንጂ የሜዳ አምላክ አይደለም” ስላሉ ይህን እጅግ ብዙ ሕዝብ በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ፤+ እናንተም እኔ ይሖዋ መሆኔን በእርግጥ ታውቃላችሁ’”+ አለው።
29 እነሱም ለሰባት ቀን ያህል እንደተፋጠጡ ቆዩ። በሰባተኛውም ቀን ውጊያው ተጀመረ። የእስራኤል ሰዎችም በአንድ ቀን 100,000 ሶርያውያን እግረኛ ወታደሮችን ገደሉ። 30 የተረፉትም ወደ ከተማዋ ወደ አፌቅ+ ሸሹ። ሆኖም ከተረፉት ሰዎች መካከል በ27,000ዎቹ ላይ ቅጥሩ ተንዶ ወደቀባቸው። ቤንሃዳድም ሸሽቶ ወደ ከተማዋ ገባ፤ አንድ ክፍል ውስጥ ገብቶም ተሸሸገ።
31 በመሆኑም አገልጋዮቹ እንዲህ አሉት፦ “የእስራኤል ቤት ነገሥታት መሐሪዎች እንደሆኑ* ሰምተናል። እንግዲህ ወገባችንን በማቅ ታጥቀንና ራሳችን ላይ ገመድ አስረን ወደ እስራኤል ንጉሥ እንውጣ። ምናልባት ሕይወትህን* ያተርፍልህ ይሆናል።”+ 32 ስለሆነም ወገባቸውን በማቅ ታጥቀውና ራሳቸው ላይ ገመድ አስረው ወደ እስራኤል ንጉሥ በመምጣት “አገልጋይህ ቤንሃዳድ ‘እባክህ፣ ሕይወቴን* አታጥፋ’ ይላል” አሉት። ንጉሡም “እስካሁን በሕይወት አለ? ወንድሜ እኮ ነው” አለ። 33 ሰዎቹ ይህን እንደ ጥሩ ገድ በመመልከትና ንጉሡ የተናገረውን በማመን “አዎ፣ ቤንሃዳድ እኮ ወንድምህ ነው” አሉ። ንጉሡም “በሉ ሄዳችሁ አምጡት” አለ። ከዚያም ቤንሃዳድ ወደ እሱ መጣ፤ እሱም ወዲያውኑ ሠረገላው ላይ እንዲወጣ አደረገው።
34 ቤንሃዳድም “አባቴ ከአባትህ ላይ የወሰዳቸውን ከተሞች እመልሳለሁ፤ አባቴ በሰማርያ እንዳደረገው ሁሉ አንተም በደማስቆ ለራስህ ገበያ ማቋቋም* ትችላለህ” አለው።
አክዓብም “በዚህ ስምምነት* መሠረት አሰናብትሃለሁ” አለው።
በዚህም መሠረት ከእሱ ጋር ስምምነት አድርጎ አሰናበተው።
35 ከነቢያት ልጆች*+ አንዱ በይሖዋ ቃል ታዞ ጓደኛውን “እባክህ ምታኝ” አለው። ሰውየው ግን ሊመታው ፈቃደኛ አልሆነም። 36 ስለዚህ “የይሖዋን ቃል ስላልሰማህ ከእኔ ተለይተህ እንደሄድክ አንበሳ አግኝቶ ይገድልሃል” አለው። ከእሱ ተለይቶም ሲሄድ አንበሳ አግኝቶ ገደለው።
37 ከዚያም ሌላ ሰው አግኝቶ “እባክህ ምታኝ” አለው። በመሆኑም ሰውየው መትቶ አቆሰለው።
38 ከዚያም ይህ ነቢይ ሄዶ ንጉሡን መንገድ ዳር ቆሞ ጠበቀው፤ ማንነቱም እንዳይታወቅ ዓይኖቹን በመጠምጠሚያ ሸፍኖ ነበር። 39 ንጉሡም በዚያ ሲያልፍ ነቢዩ ጮክ ብሎ ንጉሡን በመጣራት እንዲህ አለ፦ “እኔ አገልጋይህ ወደተፋፋመው ጦርነት ገብቼ ነበር፤ በዚህ ጊዜ አንድ ሰው ከዚያ ወጥቶ የሆነ ሰው ወደ እኔ ይዞ መጣ፤ እንዲህም አለኝ፦ ‘ይህን ሰው ጠብቀው። ይህ ሰው ቢጠፋ በእሱ ሕይወት ፋንታ የአንተ ሕይወት ይተካል፤*+ ወይም ደግሞ አንድ ታላንት* ብር ትከፍላለህ።’ 40 ታዲያ እኔ አገልጋይህ ሥራ በዝቶብኝ ወዲያ ወዲህ ስል ሰውየው ድንገት አምልጦ ሄደ።” የእስራኤልም ንጉሥ “እንግዲህ በራስህ ላይ ፈርደሃል፤ አንተው ራስህ ውሳኔውን አስተላልፈሃል” አለው። 41 ከዚያም ፈጠን ብሎ መጠምጠሚያውን ከዓይኖቹ ላይ አነሳ፤ የእስራኤልም ንጉሥ ይህ ሰው ከነቢያት አንዱ+ መሆኑን አወቀ። 42 ነቢዩም “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እኔ መጥፋት አለበት ያልኩት ሰው ከእጅህ እንዲያመልጥ ስላደረግክ+ በእሱ ሕይወት ፋንታ የአንተ ሕይወት ይተካል፤*+ በእሱም ሕዝብ ፋንታ የአንተ ሕዝብ ይተካል’”+ አለው። 43 በዚህ ጊዜ የእስራኤል ንጉሥ ፊቱ ጠቁሮና አዝኖ ወደ ቤቱ ወደ ሰማርያ+ ሄደ።
21 እነዚህ ነገሮች ከተከናወኑ በኋላ ከኢይዝራኤላዊው ከናቡቴ የወይን እርሻ ጋር በተያያዘ አንድ ሁኔታ ተከሰተ፤ የወይን እርሻው የሚገኘው በኢይዝራኤል+ ውስጥ ከሰማርያው ንጉሥ ከአክዓብ ቤተ መንግሥት አጠገብ ነበር። 2 አክዓብ ናቡቴን እንዲህ አለው፦ “የወይን እርሻህ ከቤቴ አጠገብ ስለሚገኝ የአትክልት ቦታ እንዳደርገው ስጠኝ። እኔም በምትኩ ከዚህ የተሻለ የወይን እርሻ እሰጥሃለሁ። ከፈለግክ ደግሞ የቦታውን ዋጋ እሰጥሃለሁ።” 3 ናቡቴ ግን አክዓብን “የአባቶቼን ርስት ለአንተ መስጠት በይሖዋ ፊት ተገቢ ስላልሆነ ፈጽሞ የማላስበው ነገር ነው” አለው።+ 4 በመሆኑም አክዓብ ኢይዝራኤላዊው ናቡቴ “የአባቶቼን ርስት አልሰጥህም” ስላለው ፊቱ ጠቁሮና አዝኖ ወደ ቤቱ ገባ። ከዚያም ፊቱን ወደ ግድግዳ አዙሮ ተኛ፤ ምግብ ለመብላትም ፈቃደኛ አልሆነም።
5 ሚስቱ ኤልዛቤልም+ ወደ እሱ ገብታ “ምግብ አልበላ እስኪልህ ድረስ እንዲህ ያዘንከው* ለምንድን ነው?” አለችው። 6 እሱም እንዲህ አላት፦ “ኢይዝራኤላዊውን ናቡቴን ‘የወይን እርሻህን በገንዘብ ሽጥልኝ። ከፈለግክ ደግሞ በምትኩ ሌላ የወይን እርሻ ልስጥህ’ ብዬው ነበር። እሱ ግን ‘የወይን እርሻዬን አልሰጥህም’ አለኝ።” 7 ሚስቱ ኤልዛቤልም “በእስራኤል ላይ ንጉሥ ሆነህ የምትገዛው አንተ አይደለህም? በል ተነስና እህል ቅመስ፤ ልብህም ደስ ይበለው። የኢይዝራኤላዊውን የናቡቴን የወይን እርሻ እኔ እሰጥሃለሁ” አለችው።+ 8 ስለሆነም በአክዓብ ስም ደብዳቤዎች ጽፋ በእሱ ማኅተም አተመቻቸው፤+ ደብዳቤዎቹንም ናቡቴ በሚኖርበት ከተማ ወደሚገኙት ሽማግሌዎችና+ ታላላቅ ሰዎች ላከቻቸው። 9 በደብዳቤዎቹም ላይ እንዲህ ስትል ጻፈች፦ “ጾም አውጁ፤ ናቡቴንም በሕዝቡ ፊት በክብር ቦታ ላይ አስቀምጡት። 10 ሁለት የማይረቡ ሰዎችንም አምጥታችሁ ከፊት ለፊቱ አስቀምጡና ‘አምላክንና ንጉሡን ተራግመሃል!’+ በማለት እንዲመሠክሩበት አድርጉ።+ ከዚያም አውጥታችሁ በድንጋይ በመውገር ግደሉት።”+
11 በመሆኑም የከተማዋ ሰዎች ማለትም እሱ በሚኖርበት ከተማ ያሉት ሽማግሌዎችና ታላላቅ ሰዎች ኤልዛቤል በላከችላቸው ደብዳቤዎች ላይ በተጻፈው መሠረት አደረጉ። 12 እነሱም ጾም አወጁ፤ ናቡቴም በሕዝቡ ፊት በክብር ቦታ ላይ እንዲቀመጥ አደረጉ። 13 ከዚያም ሁለት የማይረቡ ሰዎች መጥተው ፊት ለፊቱ ተቀመጡ፤ እነሱም በሕዝቡ ፊት ‘ናቡቴ አምላክንና ንጉሡን ተራግሟል!’ እያሉ በናቡቴ ላይ ይመሠክሩበት ጀመር።+ ከዚያም ወደ ከተማዋ ዳርቻ በመውሰድ በድንጋይ ወግረው ገደሉት።+ 14 እነሱም “ናቡቴ በድንጋይ ተወግሮ ሞቷል” በማለት ወደ ኤልዛቤል መልእክት ላኩባት።+
15 ኤልዛቤልም ናቡቴ በድንጋይ ተወግሮ መሞቱን እንደሰማች አክዓብን “ኢይዝራኤላዊው ናቡቴ በገንዘብ ሊሸጥልህ ያልፈለገውን የወይን እርሻውን ተነስና ውረስ፤+ ምክንያቱም ናቡቴ በሕይወት የለም፤ ሞቷል” አለችው። 16 አክዓብም ናቡቴ መሞቱን እንደሰማ ተነስቶ የኢይዝራኤላዊውን የናቡቴን የወይን እርሻ ለመውረስ ወደዚያ ወረደ።
17 ሆኖም የይሖዋ ቃል ወደ ቲሽባዊው ወደ ኤልያስ+ እንዲህ ሲል መጣ፦ 18 “በሰማርያ+ የሚገኘውን የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን ለማግኘት ተነስተህ ወደዚያ ውረድ። እሱም የናቡቴን የወይን እርሻ ለመውረስ ሄዶ እዚያ ይገኛል። 19 እንዲህም በለው፦ ‘ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ሰው ገድለህ+ ንብረቱን ወሰድክ+ አይደል?”’ ከዚያም እንዲህ በለው፦ ‘ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ውሾች የናቡቴን ደም በላሱበት ቦታ የአንተንም ደም ይልሱታል።”’”+
20 አክዓብም ኤልያስን “ጠላቴ ሆይ፣ አገኘኸኝ?” አለው፤+ እሱም እንዲህ አለው፦ “አዎ፣ አግኝቼሃለሁ። ‘እንግዲህ አንተ በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር ለማድረግ ቆርጠህ ስለተነሳህ*+ 21 ጥፋት አመጣብሃለሁ፤ እየተከታተልኩም ሙልጭ አድርጌ እጠርግሃለሁ፤ እንዲሁም በእስራኤል ውስጥ የሚገኘውን ምስኪኑንና ደካማውን+ ጨምሮ የአክዓብ የሆነውን ወንድ* ሁሉ አጠፋለሁ።+ 22 ቁጣዬን ስላነሳሳህና እስራኤላውያን ኃጢአት እንዲፈጽሙ ስላደረግክ ቤትህን እንደ ናባጥ ልጅ እንደ ኢዮርብዓም+ ቤትና እንደ አኪያህ ልጅ እንደ ባኦስ+ ቤት አደርገዋለሁ።’ 23 ኤልዛቤልን በተመለከተም ይሖዋ እንዲህ ብሏል፦ ‘ውሾች በኢይዝራኤል በሚገኘው ቁራሽ መሬት ላይ ኤልዛቤልን ይበሏታል።+ 24 ከአክዓብ ወገን የሆነውን፣ በከተማ ውስጥ የሚሞተውን ውሾች ይበሉታል፤ በሜዳ ላይ የሚሞተውን ደግሞ የሰማይ አሞሮች ይበሉታል።+ 25 በእርግጥም በሚስቱ በኤልዛቤል ተነድቶ+ በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር ለማድረግ ቆርጦ የተነሳ* እንደ አክዓብ ያለ አንድም ሰው የለም።+ 26 ይሖዋ ከእስራኤላውያን ፊት ያሳደዳቸው አሞራውያን እንዳደረጉት ሁሉ እሱም አስጸያፊ የሆኑ ጣዖቶችን* በመከተል እጅግ አስነዋሪ ነገር አደረገ።’”+
27 አክዓብም ይህን እንደሰማ ልብሱን ቀደደ፤ ማቅም ለበሰ፤ ጾመ፤ እንዲሁም ማቅ ላይ ይተኛና በሐዘን ተኮራምቶ ይሄድ ነበር። 28 ከዚያም የይሖዋ ቃል ወደ ቲሽባዊው ወደ ኤልያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ 29 “አክዓብ ስለ እሱ በተናገርኩት ነገር የተነሳ ራሱን እንዴት እንዳዋረደ ተመለከትክ?+ ራሱን በፊቴ ስላዋረደ ላመጣበት የነበረውን ጥፋት በእሱ ዘመን አላመጣም። ከዚህ ይልቅ በእሱ ቤት ላይ ጥፋት የማመጣው በልጁ ዘመን ነው።”+
22 በሶርያና በእስራኤል መካከል ለሦስት ዓመት ጦርነት አልነበረም። 2 በሦስተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሳፍጥ+ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወረደ።+ 3 የእስራኤልም ንጉሥ አገልጋዮቹን “ራሞትጊልያድ+ የእኛ እንደሆነች ታውቃላችሁ አይደል? ሆኖም እሷን ከሶርያ ንጉሥ እጅ ለማስመለስ እያመነታን ነው” አላቸው። 4 ከዚያም ኢዮሳፍጥን “በራሞትጊልያድ ለመዋጋት ከእኔ ጋር አብረህ ትሄዳለህ?” አለው። በዚህ ጊዜ ኢዮሳፍጥ ለእስራኤል ንጉሥ “እኔ ማለት እኮ አንተ ማለት ነህ። ሕዝቤ ሕዝብህ ነው። የእኔ ፈረሶችም የአንተ ፈረሶች ናቸው” በማለት መለሰለት።+
5 ሆኖም ኢዮሳፍጥ የእስራኤልን ንጉሥ “እባክህ፣ በመጀመሪያ ይሖዋ ምን እንደሚል+ ጠይቅ”+ አለው። 6 በመሆኑም የእስራኤል ንጉሥ 400 ገደማ የሚሆኑ ነቢያትን አንድ ላይ ሰብስቦ “ራሞትጊልያድን ለመውጋት ልዝመት ወይስ ይቅርብኝ?” አላቸው። እነሱም “ዝመት፤ ይሖዋ በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታል” አሉት።
7 ከዚያም ኢዮሳፍጥ “በዚህ ቦታ የይሖዋ ነቢይ የለም? ካለ በእሱም አማካኝነት እንጠይቅ” አለ።+ 8 በዚህ ጊዜ የእስራኤል ንጉሥ ኢዮሳፍጥን “በእሱ አማካኝነት ይሖዋን ልንጠይቅ የምንችልበት አንድ ሰው ይቀራል፤+ ሆኖም ስለ እኔ መጥፎ ነገር ብቻ እንጂ መልካም ነገር ፈጽሞ ስለማይተነብይ በጣም እጠላዋለሁ።+ እሱም የይምላ ልጅ ሚካያህ ነው” አለው። ኢዮሳፍጥ ግን “ንጉሡ እንዲህ ሊል አይገባም” አለ።
9 ስለሆነም የእስራኤል ንጉሥ አንድ የቤተ መንግሥት ባለሥልጣን ጠርቶ “የይምላን ልጅ ሚካያህን በአስቸኳይ ይዘኸው ና” አለው።+ 10 በዚህ ጊዜ የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሳፍጥ የንግሥና ልብሳቸውን ለብሰው በሰማርያ መግቢያ በር ላይ በሚገኘው አውድማ ላይ በየዙፋናቸው ተቀምጠው ነበር፤ ነቢያቱም ሁሉ በፊታቸው ትንቢት ይናገሩ ነበር።+ 11 ከዚያም የኬናአና ልጅ ሴዴቅያስ የብረት ቀንዶች ሠርቶ “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ሶርያውያንን እስክታጠፋቸው ድረስ በእነዚህ ትወጋቸዋለህ’”* አለ። 12 ሌሎቹ ነቢያትም ሁሉ “ወደ ራሞትጊልያድ ውጣ፤ ይሳካልሃል፤ ይሖዋም እሷን በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታል” በማለት ተመሳሳይ ትንቢት ይናገሩ ነበር።
13 ሚካያህን ለመጥራት የሄደው መልእክተኛም “እነሆ፣ ነቢያቱ ሁሉ በአንድ ድምፅ ለንጉሡ የተናገሩት ነገር ጥሩ ነው። እባክህ፣ የአንተም ቃል እንደ እነሱ ይሁን፤ አንተም ጥሩ ነገር ተናገር” አለው።+ 14 ሚካያህ ግን “ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ፣ የምናገረው ይሖዋ የሚለኝን ብቻ ነው” አለ። 15 ከዚያም ወደ ንጉሡ ገባ፤ ንጉሡም “ሚካያህ፣ ራሞትጊልያድን ለመውጋት እንዝመት ወይስ ይቅርብን?” ሲል ጠየቀው። እሱም ወዲያውኑ “ውጡ፤ ይቀናችኋል፤ ይሖዋ በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታል” በማለት መለሰለት። 16 በዚህ ጊዜ ንጉሡ “በይሖዋ ስም ከእውነት በስተቀር ሌላ አንዳች ነገር እንዳትነግረኝ የማስምልህ ስንት ጊዜ ነው?” አለው። 17 በመሆኑም ሚካያህ እንዲህ በማለት ተናገረ፦ “እስራኤላውያን ሁሉ እረኛ እንደሌላቸው በጎች በተራሮች ላይ ተበታትነው አያለሁ።+ ይሖዋም ‘እነዚህ ጌታ የላቸውም። እያንዳንዳቸው በሰላም ወደየቤታቸው ይመለሱ’ ብሏል።”
18 ከዚያም የእስራኤል ንጉሥ ኢዮሳፍጥን “‘ስለ እኔ መጥፎ ነገር ብቻ እንጂ ጥሩ ነገር አይተነብይም’ ብዬህ አልነበረም?” አለው።+
19 በዚህ ጊዜ ሚካያህ እንዲህ አለ፦ “እንግዲህ የይሖዋን ቃል ስማ፦ ይሖዋ በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ+ የሰማያት ሠራዊትም ሁሉ በቀኙና በግራው አጠገቡ ቆመው+ አየሁ። 20 ከዚያም ይሖዋ ‘በራሞትጊልያድ ላይ ዘምቶ እዚያው እንዲሞት አክዓብን ማን ያሞኘዋል?’ አለ። በዚህ ጊዜ አንዱ አንድ ነገር፣ ሌላው ደግሞ ሌላ ነገር ተናገረ። 21 ከዚያም አንድ መንፈስ*+ ወደ ፊት ወጥቶ ይሖዋ ፊት በመቆም ‘እኔ አሞኘዋለሁ’ አለ። ይሖዋም ‘እንዴት አድርገህ?’ አለው። 22 ‘እኔ እወጣና በነቢያቱ ሁሉ አፍ ላይ አሳሳች መንፈስ እሆናለሁ’ አለ።+ እሱም ‘እንግዲያው ታሞኘዋለህ፤ ደግሞም ይሳካልሃል። ውጣና እንዳልከው አድርግ’ አለው። 23 ይሖዋም በእነዚህ ነቢያትህ ሁሉ አፍ ላይ አሳሳች መንፈስ አኑሯል፤+ ሆኖም ይሖዋ ጥፋት እንደሚመጣብህ ተናግሯል።”+
24 የኬናአና ልጅ ሴዴቅያስም ወደ ሚካያህ ቀርቦ በጥፊ መታውና “ለመሆኑ የይሖዋ መንፈስ እኔን በየት በኩል አልፎ ነው አንተን ያናገረህ?” አለው።+ 25 ሚካያህም “በየት በኩል እንዳለፈማ፣ ለመደበቅ ወደ ውስጠኛው ክፍል በምትገባበት ቀን ታውቀዋለህ” አለው። 26 ከዚያም የእስራኤል ንጉሥ እንዲህ አለ፦ “ሚካያህን ወስዳችሁ ለከተማው አለቃ ለአምዖን እና የንጉሡ ልጅ ለሆነው ለዮአስ አስረክቡት። 27 እንዲህም በሏቸው፦ ‘ንጉሡ “በሰላም ተመልሼ እስክመጣ ድረስ ይህን ሰው እስር ቤት አቆዩት፤+ ጥቂት ምግብና ውኃ ብቻ ስጡት” ብሏል።’” 28 ሚካያህ ግን “እውነት አንተ በሰላም ከተመለስክ ይሖዋ በእኔ አልተናገረም ማለት ነው!” አለ።+ ከዚያም “እናንተ ሰዎች፣ ሁላችሁም ልብ በሉ” አለ።
29 በመሆኑም የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሳፍጥ ወደ ራሞትጊልያድ+ ወጡ። 30 የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሳፍጥን “እኔ ማንነቴ እንዳይታወቅ ራሴን ለውጬ ወደ ውጊያው እገባለሁ፤ አንተ ግን ንጉሣዊ ልብስህን ልበስ” አለው። ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ማንነቱ እንዳይታወቅ ራሱን ለውጦ+ ወደ ውጊያው ገባ። 31 በዚህ ጊዜ የሶርያ ንጉሥ 32ቱን የሠረገላ አዛዦች+ “ከእስራኤል ንጉሥ በስተቀር ከትንሹም ሆነ ከትልቁ፣ ከማንም ጋር እንዳትዋጉ” በማለት አዟቸው ነበር። 32 የሠረገሎቹ አዛዦችም ኢዮሳፍጥን ባዩት ጊዜ “ያለጥርጥር ይህ የእስራኤል ንጉሥ ነው” ብለው አሰቡ። በመሆኑም ሊወጉት ወደ እሱ ዞሩ፤ በዚህ ጊዜ ኢዮሳፍጥ እርዳታ ለማግኘት ጮኸ። 33 የሠረገሎቹ አዛዦችም የእስራኤል ንጉሥ አለመሆኑን ሲያዩ ወዲያውኑ እሱን ማሳደዳቸውን ትተው ተመለሱ።
34 ይሁንና አንድ ሰው በነሲብ* ቀስቱን ሲያስወነጭፍ የእስራኤልን ንጉሥ የጥሩሩ መጋጠሚያ ላይ ወጋው። ስለሆነም ንጉሡ ሠረገላ ነጂውን “ክፉኛ ስለቆሰልኩ ሠረገላውን አዙረህ ከጦርነቱ* ይዘኸኝ ውጣ” አለው።+ 35 ያን ቀን ሙሉ የተፋፋመ ውጊያ ተካሄደ፤ ንጉሡንም ሠረገላው ውስጥ እንዳለ ፊቱን ወደ ሶርያውያን አዙረው ደግፈው አቆሙት። ከቁስሉ የሚወጣውም ደም በጦር ሠረገላው ውስጥ ይፈስ ነበር፤ አመሻሹም ላይ ሞተ።+ 36 ፀሐይ ልትጠልቅም ስትል በሰፈሩ መካከል “እያንዳንዱ ሰው ወደ ከተማው፣ እያንዳንዱም ሰው ወደ ምድሩ ይመለስ!” የሚል ጥሪ አስተጋባ።+ 37 በዚህ መንገድ ንጉሡ ሞተ፤ ወደ ሰማርያም ተወሰደ፤ ንጉሡንም በሰማርያ ቀበሩት። 38 እነሱም የጦር ሠረገላውን በሰማርያ ኩሬ ባጠቡት ጊዜ ይሖዋ በተናገረው መሠረት ውሾች ደሙን ላሱት፤ ዝሙት አዳሪዎችም በዚያ ገላቸውን እየታጠቡ ነበር።*+
39 ስለቀረው የአክዓብ ታሪክ፣ ስላደረጋቸው ነገሮች ሁሉ፣ በዝሆን ጥርስ ስለሠራው ቤትና*+ ስለገነባቸው ከተሞች ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፎ ይገኝ የለም? 40 በመጨረሻም አክዓብ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤+ በእሱም ምትክ ልጁ አካዝያስ+ ነገሠ።
41 የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ በነገሠ በአራተኛው ዓመት የአሳ ልጅ ኢዮሳፍጥ+ በይሁዳ ላይ ነገሠ። 42 ኢዮሳፍጥ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 35 ዓመት የነበረ ሲሆን በኢየሩሳሌም 25 ዓመት ገዛ። እናቱ የሺልሂ ልጅ አዙባ ነበረች። 43 እሱም በአባቱ በአሳ+ መንገድ ሁሉ ሄደ። ከዚያ ፈቀቅ አላለም፤ በይሖዋም ፊት ትክክል የሆነውን ነገር አደረገ።+ ይሁን እንጂ ከፍ ያሉት የማምለኪያ ቦታዎች አልተወገዱም ነበር፤ ሕዝቡም ከፍ ባሉት የማምለኪያ ቦታዎች ላይ መሠዋቱንና የሚጨስ መሥዋዕት ማቅረቡን አልተወም ነበር።+ 44 ኢዮሳፍጥ ከእስራኤል ንጉሥ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ነበረው።+ 45 የቀረው የኢዮሳፍጥ ታሪክ፣ በኃያልነቱ የፈጸማቸው ጀብዱዎችና ያደረጋቸው ውጊያዎች በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም? 46 ኢዮሳፍጥ ከአባቱ ከአሳ+ ዘመን የተረፉትን የቤተ መቅደስ ቀላጮች*+ ከምድሪቱ ላይ አስወግዶ ነበር።
47 በዚያ ዘመን በኤዶም+ ንጉሥ አልነበረም፤ እንደ ንጉሥ ሆኖ የሚገዛው አስተዳዳሪው ነበር።+
48 በተጨማሪም ኢዮሳፍጥ ወርቅ ለማምጣት ወደ ኦፊር የሚሄዱ የተርሴስ መርከቦች* ሠርቶ ነበር፤+ ሆኖም መርከቦቹ በዔጽዮንጋብር+ ስለተሰበሩ ወደዚያ አልሄዱም። 49 የአክዓብ ልጅ አካዝያስ ኢዮሳፍጥን “አገልጋዮቼ ከአገልጋዮችህ ጋር በመርከቦቹ ይሂዱ” ያለው በዚህ ጊዜ ነበር፤ ኢዮሳፍጥ ግን በዚህ አልተስማማም።
50 በመጨረሻም ኢዮሳፍጥ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤+ በአባቱ በዳዊት ከተማም ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ፤ በእሱም ምትክ ልጁ ኢዮራም+ ነገሠ።
51 የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሳፍጥ በነገሠ በ17ኛው ዓመት የአክዓብ ልጅ አካዝያስ+ በሰማርያ ሆኖ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ በእስራኤልም ላይ ሁለት ዓመት ገዛ። 52 እሱም በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር ማድረጉን ቀጠለ፤ በአባቱና+ በእናቱ+ መንገድ እንዲሁም እስራኤላውያን ኃጢአት እንዲፈጽሙ ባደረጋቸው በናባጥ ልጅ በኢዮርብዓም መንገድ ሄደ።+ 53 ባአልን ማገልገሉንና+ ለእሱ መስገዱን ቀጠለ፤ አባቱም እንዳደረገው ሁሉ የእስራኤልን አምላክ ይሖዋን አስቆጣ።+
ወይም “ስሜቱን ጎድቶት፤ ገሥጾት።”
ወይም “ነፍስ።”
ወይም “ነፍሴን በዋጃት።”
ወይም “በእንስት በቅሎዬ።”
ወይም “የተከበርክ።”
ቃል በቃል “የምድርን ሁሉ መንገድ ልሄድ ነው።”
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ቃል በቃል “ፊታቸውን ወደ እኔ አቅንተው እንደነበር።”
ወይም “የጠየቀው በገዛ ነፍሱ ፈርዶ ካልሆነ።”
ወይም “ሥርወ መንግሥት ባቋቋመልኝ።”
ወይም “አዶንያስ ላይ ወደቀበት።”
ወይም “ሴት ልጅ ወሰደ።”
ቃል በቃል “ታላቅ።”
ቃል በቃል “መውጫና መግቢያውን የማላውቅ።”
“አስቸጋሪ የሆነውን” ማለትም ሊሆን ይችላል። ቃል በቃል “ከባድ የሆነውን።”
ቃል በቃል “ብዙ ቀናት።”
ወይም “ነፍስ።”
ቃል በቃል “በቀኖችህ።”
ቃል በቃል “ቀናትህን አረዝማለሁ።”
ወይም “መኳንንቱ።”
ኤፍራጥስን ያመለክታል።
አንድ ቆሮስ 220 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ቅርንጫፍ የሚመስሉ ቀንዶች ያሉት አጥቢ እንስሳ፤ ከአጋዘን ጋር ይመሳሰላል።
ከኤፍራጥስ በስተ ምዕራብ ያለውን ያመለክታል።
ይህ አኃዝ በእጅ በተጻፉ አንዳንድ ጥንታዊ ቅጂዎችና በሌላ ቦታ ላይ በሚገኘው ተመሳሳይ ዘገባ ላይ ይገኛል። ሌሎች ጥንታዊ ቅጂዎች ደግሞ 40,000 ይላሉ።
ወይም “ፈረሰኞች።”
ወይም “አስተዋይ ልብ።”
ወይም “ተናገረ።”
ወይም “በራሪ ፍጥረታት።”
በምድር ላይ የሚሳቡ እንስሳትንና ጥቃቅን ነፍሳትን የሚጨምር ሊሆን ይችላል።
ወይም “ዳዊትን ይወደው ነበር።”
ወይም “ብዙ።”
አንድ ቆሮስ 220 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ቃል በቃል “የተጨቀጨቀ ዘይት።”
ወይም “ቃል ኪዳን ተጋቡ።”
ወይም “ተሸካሚዎችና።”
ቃል በቃል “የእስራኤል ወንዶች ልጆች።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ8ን ተመልከት።
አንድ ክንድ 44.5 ሴንቲ ሜትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ቃል በቃል “ከቤተ መቅደሱ።” ቅድስቱን እንደሚያመለክት ከሁኔታው መረዳት ይቻላል።
ወይም “ወርዱ።”
ወይም “ሰያፍ ጠርዝ።”
ቅድስቱን ያመለክታል።
ወይም “ገባ ያሉ ማስቀመጫዎችን።”
ቃል በቃል “በስተ ቀኝ።”
የቤቱን ውስጥ ያመለክታል።
ከቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት የሚገኘውን ቅድስቱን ያመለክታል።
ቃል በቃል “ከዘይት እንጨት።”
ቅድስተ ቅዱሳኑን ያመለክታል።
የበሩን ፍሬም አሠራር ወይም የበሮቹን መጠን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።
ቅድስቱን ያመለክታል።
የበሩን ፍሬም አሠራር ወይም የበሮቹን መጠን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
አንድ ክንድ 44.5 ሴንቲ ሜትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ክፍሎቹም” አሊያም “ወራጆቹም።” ዕብራይስጡ ‘አሥራ አምስት’ መሆናቸውን ከመግለጽ ውጭ ምንነታቸውን አይናገርም።
ወይም “በረንዳ።”
ወይም “በረንዳ።”
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
ቃል በቃል “ከአዳራሹ ቤት።”
ወይም “የነሐስ።” በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ቀጥሎ በሚገኝባቸው ቦታዎች ላይም ይሠራል።
ቅድስቱን ያመለክታል።
ወይም “በስተ ደቡብ።”
“እሱ [ይሖዋን ያመለክታል] አጽንቶ ይመሥርት” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “በስተ ሰሜን።”
“በብርታት” የሚል ትርጉም ሊኖረው ይችላል።
ወይም “የውኃ ማጠራቀሚያውን።”
ወደ 7.4 ሴንቲ ሜትር ገደማ ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
አንድ ባዶስ 22 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “የውኃ ማጓጓዣ ጋሪዎችን።”
ተሽከርካሪ እግር።
ተሽከርካሪ እግር።
ወይም “ቸርኬዎች።”
ወይም “ከጋሪው ጋር ወጥ ሆነው።”
ወይም “ከጋሪው ጋር ወጥ ሆነው።”
ወይም “መሃል ለመሃል ሲለካ አራት ክንድ ነበር።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።
የዳስ በዓልን ያመለክታል።
ቃል በቃል “ከወገብህ የሚወጣው ልጅህ።”
ወይም “ባልንጀራው በእርግማን ሥር ቢያደርገው።” ግለሰቡ የማለው በውሸት ከሆነ ወይም መሐላውን ከጣሰ እርግማኑ እንደ ቅጣት እንደሚደርስበት ያመለክታል።
ቃል በቃል “በእርግማኑም።”
ቃል በቃል “እርግማን።”
ቃል በቃል “ክፉ።”
ቃል በቃል “ጻድቅ።”
ወይም “ስላጎሳቆልካቸው።”
ወይም “ፌንጣ።”
ቃል በቃል “በበሮቹ ምድር።”
ወይም “በዝናህ።”
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ሙሉ በሙሉ ለእሱ ያደረ ይሁን።”
ወይም “ከሃማት መግቢያ።”
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ቃል በቃል “በስምንተኛውም።” ከተጨማሪው ሰባት ቀን በኋላ ያለውን ቀን ያመለክታል።
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
ቃል በቃል “መተረቻና።”
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
“የማይረባ ምድር” ማለትም ሊሆን ይችላል።
አንድ ታላንት 34.2 ኪሎ ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
ወይም “ሚሎን።” “መሙላት” የሚል ትርጉም ያለው የዕብራይስጥ ቃል ነው።
ወይም “የሠርግ ስጦታ።”
ወይም “ሚሎን።” “መሙላት” የሚል ትርጉም ያለው የዕብራይስጥ ቃል ነው።
ወይም “በእንቆቅልሾች።”
ቃል በቃል “ከንጉሡ የተሰወረ።”
ቃል በቃል “በውስጧ መንፈስ አልቀረም።”
ወይም “ስለ ቃሎችህና።”
አንድ ታላንት 34.2 ኪሎ ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
ቃል በቃል “በንጉሥ ሰለሞን እጅ መሠረት።”
አንድ ሰቅል 11.4 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
አብዛኛውን ጊዜ ቀስተኞች የሚይዙት ትንሽ ጋሻ።
በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ አንድ ምናን 570 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ዥጉርጉር ቀለም ያለው ትልቅ የወፍ ዝርያ። እንግሊዝኛ፣ ፒኮክ።
ቃል በቃል “የእሱን ፊት ይሹ ነበር።”
ወይም “ፈረሰኞችን።”
ወይም “ፈረሰኞች።”
“ከግብፅና ከቀዌ ያስመጣቸው ነበሩ፤ የንጉሡ ነጋዴዎች ከቀዌ አንዴ በተተመነው ዋጋ ይገዟቸው ነበር” ማለትም ሊሆን ይችላል። ቀዌ ኪልቅያን ልታመለክት ትችላለች።
ወይም “የጋብቻ ጥምረት አትመሥርቱ።”
ወይም “ሚስቶቹም ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳደሩበት።”
ወይም “ዞር እንዲል።”
ወይም “ሙሉ በሙሉ ለአምላኩ ለይሖዋ ያደረ።”
“ጡት አስጣለችው” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “በገደለበት ጊዜ።”
ቃል በቃል “እጁን ማንሳት።”
ወይም “ሚሎን።” “መሙላት” የሚል ትርጉም ያለው የዕብራይስጥ ቃል ነው።
ወይም “ነፍስህ በተመኘችው።”
ቃል በቃል “የገዛባቸው ቀናት።”
ወይም “ጨቋኝ።”
ቃል በቃል “ወደየድንኳናቸው።”
ቃል በቃል “የተመረጡ።”
ወይም “ምሽግ አድርጎ በመሥራት።”
ወይም “ምሽግ አድርጎ ሠራ።”
ወይም “ተአምራዊ ምልክት።”
ወይም “ተአምራዊ ምልክት።”
ወይም “በስብ የራሰው አመድ።” መሥዋዕት ሆነው በሚቀርቡት እንስሳት ስብ የራሰውን አመድ ያመለክታል።
ወይም “ሽባ ሆነ።”
ወይም “ተአምራዊ ምልክት።”
ቃል በቃል “እጁን ይሞላው።”
ወይም “አንተም እንዲህ እንዲህ ብለህ ንገራት።”
ወይም “ቀልጠው የተሠሩ ሐውልቶችን።”
ቃል በቃል “ግንብ ላይ የሚሸናውን።” ወንዶችን የሚያናንቅ የዕብራይስጥ አገላለጽ ነው።
ኤፍራጥስን ያመለክታል።
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ቃል በቃል “የገዛባቸው ቀናት።”
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ግብረ ሰዶማውያን ሆነው የሴት ዓይነት ሚና ያላቸውን ወንዶች ያመለክታል።
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
ቃል በቃል “የሯጮቹ።”
አቢያህ ተብሎም ይጠራል።
ወይም “ለአምላኩ ለይሖዋ ሙሉ በሙሉ ያደረ።”
ግብረ ሰዶማውያን ሆነው የሴት ዓይነት ሚና ያላቸውን ወንዶች ያመለክታል።
እዚህ ላይ የገባው የዕብራይስጥ ቃል “ፋንድያ” ከሚለው ቃል ጋር ዝምድና ሊኖረው የሚችል ሲሆን ንቀትን ለማመልከት ተሠርቶበታል።
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “እንደ ንጉሡ እናት ተቆጥራ ከተሰጣት ቦታ።”
ቃል በቃል “በቀናቱ።”
ወይም “ሙሉ በሙሉ ለይሖዋ ያደረ።”
ወይም “ከይሁዳ ንጉሥ ከአሳ ግዛት ማንም እንዳይወጣ ወይም ማንም ወደዚያ እንዳይገባ።”
ወይም “ማጠናከር፤ መልሶ መገንባት።”
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
ወይም “ቃል ኪዳን።”
ወይም “ቃል ኪዳን።”
ወይም “ማጠናከሩን፤ መልሶ መገንባቱን።”
ወይም “አጠናከረ፤ መልሶ ገነባ።”
ወይም “ያጠናከራቸው፤ መልሶ የገነባቸው።”
የኢዮርብዓምን ልጅ ናዳብን ያመለክታል።
ወይም “ደም ከሚበቀሉለትም።”
ቃል በቃል “ግንብ ላይ የሚሸና።” ወንዶችን የሚያናንቅ የዕብራይስጥ አገላለጽ ነው።
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
አንድ ታላንት 34.2 ኪሎ ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
“የሼሜር ጎሳ ንብረት” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “ቤተ መቅደስ ውስጥ።”
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
“አምላኬ ይሖዋ ነው” የሚል ትርጉም አለው።
ቃል በቃል “ፊቱ በምቆመውና።”
ወይም “ደረቅ ወንዝም።”
ወይም “ደረቅ ወንዝ።”
ወይም “እኔ ከአንተ ጋር ምን አለኝ?”
ወይም “ነፍስ ትመለስለት።”
ወይም “ነፍስ ተመለሰችለት።”
ወይም “ደረቅ ወንዞች።”
ቃል በቃል “ፊቱ በምቆመው።”
ወይም “እስራኤል እንዲጠላ የምታደርገው።”
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
“መንገድ ሄዶ ይሆናል” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ነቢያት።”
አንድ ሲህ 7.33 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ደረቅ ወንዝ።”
ወይም “እሱም ወገቡን ታጥቆ።”
ወይም “ነፍስህን እንደ እነሱ ነፍስ ሳላደርጋት።”
ወይም “ነፍሱን።”
ወይም “ነፍሱ እንድትሞትም።”
ወይም “ነፍሴን።”
ወይም “ነፍስ።”
ወይም “ነፍስ።”
“አምላክ አዳኝ ነው” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “ሶርያውያንንም ክፉኛ ጨፈጨፋቸው።”
ቀጣዩን የበልግ ወቅት ያመለክታል።
ቃል በቃል “ቁጠር።”
የበልግን ወቅት ያመለክታል።
ወይም “ታማኝ ፍቅር እንደሚያሳዩ።”
ወይም “ነፍስህን።”
ወይም “ነፍሴን።”
ወይም “ጎዳና መሰየም።”
ወይም “ቃል ኪዳን።”
“የነቢያት ልጆች” የሚለው አገላለጽ ነቢያት ትምህርት የሚቀስሙበትን ትምህርት ቤት ወይም የነቢያትን ማኅበር የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም።
ወይም “በእሱ ነፍስ ፋንታ የአንተ ነፍስ ትተካለች።”
አንድ ታላንት 34.2 ኪሎ ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “በእሱ ነፍስ ፋንታ የአንተ ነፍስ ትተካለች።”
ቃል በቃል “መንፈስህ ያዘነው።”
ቃል በቃል “ራስህን ስለሸጥክ።”
ቃል በቃል “ግንብ ላይ የሚሸናውን።” ወንዶችን የሚያናንቅ የዕብራይስጥ አገላለጽ ነው።
ቃል በቃል “ራሱን የሸጠ።”
እዚህ ላይ የገባው የዕብራይስጥ ቃል “ፋንድያ” ከሚለው ቃል ጋር ዝምድና ሊኖረው የሚችል ሲሆን ንቀትን ለማመልከት ተሠርቶበታል።
ወይም “ትገፋቸዋለህ።”
ወይም “አንድ መልአክ።”
ወይም “ሳያስብ።”
ቃል በቃል “ከሰፈሩ።”
“እነሱም የጦር ሠረገላውን ዝሙት አዳሪዎች ገላቸውን በሚታጠቡበት በሰማርያ ኩሬ ባጠቡት ጊዜ ይሖዋ በተናገረው መሠረት ውሾች ደሙን ላሱት” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ቤተ መንግሥትና።”
ግብረ ሰዶማውያን ሆነው የሴት ዓይነት ሚና ያላቸውን ወንዶች ያመለክታል።
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።