የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • nwt ሰቆቃወ ኤርምያስ 1:1-5:22
  • ሰቆቃወ ኤርምያስ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሰቆቃወ ኤርምያስ
  • አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
ሰቆቃወ ኤርምያስ

ሰቆቃወ ኤርምያስ

א [አሌፍ]*

1 በሰዎች ተሞልታ የነበረችው ከተማ አሁን እንዴት ብቻዋን ቀረች!+

ከሌሎች ብሔራት ይበልጥ ብዙ ሕዝብ የነበረባት ከተማ እንዴት እንደ መበለት ሆነች!+

በአውራጃዎች መካከል ልዕልት የነበረችው ከተማ እንዴት ለባርነት ተዳረገች!+

ב [ቤት]

 2 በሌሊት አምርራ ታለቅሳለች፤+ እንባዋም በጉንጮቿ ላይ ይወርዳል።

ከወዳጆቿ ሁሉ መካከል አንድም የሚያጽናናት የለም።+

ባልንጀሮቿ ሁሉ ከድተዋታል፤+ ጠላት ሆነውባታል።

ג [ጊሜል]

 3 ይሁዳ ተጎሳቁላና ለአስከፊ ባርነት ተዳርጋ+ በግዞት ተወስዳለች።+

በብሔራት መካከል ትቀመጣለች፤+ ምንም ማረፊያ ስፍራ አታገኝም።

በተጨነቀች ጊዜ አሳዳጆቿ ሁሉ ያዟት።

ד [ዳሌት]

 4 በዓል ለማክበር የሚመጣ ስለሌለ ወደ ጽዮን የሚወስዱት መንገዶች አዝነዋል።+

በሮቿ ሁሉ ወና ሆነዋል፤+ ካህናቷም ሲቃ ይዟቸዋል።

ደናግሏ* አዝነዋል፤ እሷም አስከፊ ሥቃይ ደርሶባታል።

ה [ሄ]

 5 ባላጋራዎቿ አሁን ጌቶቿ* ሆነዋል፤ ጠላቶቿ ጭንቀት የለባቸውም።+

ከበደሏ ብዛት የተነሳ ይሖዋ ሐዘን አምጥቶባታልና።+

ልጆቿ በጠላት ፊት ተማርከው ተወስደዋል።+

ו [ዋው]

 6 የጽዮን ሴት ልጅ፣ ግርማ ሞገሷ ሁሉ ተገፏል።+

መኳንንቷ መሰማሪያ ቦታ እንዳጡ አጋዘኖች ሆነዋል፤

በሚያሳድዳቸውም ፊት አቅም አጥተው ይጓዛሉ።

ז [ዛየን]

 7 ኢየሩሳሌም በምትጎሳቆልበትና መኖሪያ በምታጣበት ጊዜ፣

በጥንት ዘመን የነበሯትን ውድ ነገሮች ሁሉ ታስታውሳለች።+

ሕዝቧ በጠላት እጅ በወደቀበትና የሚረዳት ባልነበረበት ጊዜ+

ጠላቶቿ አዩአት፤ በደረሰባትም ውድቀት ሳቁ።*+

ח[ኼት]

 8 ኢየሩሳሌም ከባድ ኃጢአት ፈጽማለች።+

አስጸያፊ ነገር የሆነችው ለዚህ ነው።

ያከብሯት የነበሩ ሁሉ አሁን ናቋት፤ እርቃኗን አይተዋልና።+

እሷ ራሷም ትቃትታለች፤+ በኀፍረትም ፊቷን ታዞራለች።

ט [ቴት]

 9 ርኩሰቷ ቀሚሷ ላይ አለ።

ወደፊት የሚገጥማትን ቆም ብላ አላሰበችም።+

ውድቀቷ አስደንጋጭ ነበር፤ የሚያጽናናትም የለም።

ይሖዋ ሆይ፣ ጉስቁልናዬን ተመልከት፤ ጠላት ራሱን ከፍ ከፍ አድርጓልና።+

י [ዮድ]

10 ጠላት በውድ ሀብቶቿ ሁሉ ላይ እጁን አሳርፏል።+

ወደ አንተ ጉባኤ እንዳይገቡ ያዘዝካቸው ብሔራት

ወደ መቅደሷ ሲገቡ አይታለችና።+

כ [ካፍ]

11 ነዋሪዎቿ ሁሉ ሲቃ ይዟቸዋል፤ የሚበላ ነገር ይፈልጋሉ።+

ምግብ ለማግኘትና በሕይወት ለመቆየት* ብቻ ሲሉ ያሏቸውን ውድ ነገሮች ሰጥተዋል።

ይሖዋ ሆይ፣ እይ ደግሞም ተመልከት፤ እንደማትረባ ሴት ሆኛለሁና።*

ל [ላሜድ]

12 በዚህ መንገድ የምታልፉ ሁሉ፣ ይህ ለእናንተ ከምንም የማይቆጠር ነገር ነው?

እዩ፤ ደግሞም ተመልከቱ!

ይሖዋ በሚነድ ቁጣው ቀን እንድሠቃይ ያደረገበትን፣

በእኔ ላይ የደረሰውን ሥቃይ የመሰለ ሥቃይ አለ?+

מ [ሜም]

13 ከከፍታ ቦታ ወደ አጥንቶቼ እሳት ላከ፤+ በእያንዳንዳቸውም ላይ አየለባቸው።

ለእግሬ መረብ ዘረጋ፤ ወደ ኋላ እንድመለስ አስገደደኝ።

የተጣለች ሴት አድርጎኛል።

ቀኑን ሙሉ ታምሜአለሁ።

נ [ኑን]

14 በደሎቼ እንደ ቀንበር ታስረዋል፤ በእጁም ተገምደዋል።

አንገቴ ላይ ተደርገዋል፤ ጉልበቴም ተዳክሟል።

ይሖዋ መቋቋም ለማልችላቸው ሰዎች አሳልፎ ሰጥቶኛል።+

ס [ሳሜኽ]

15 ይሖዋ በውስጤ ያሉትን ኃያላን በሙሉ አስወገደ።+

ወጣቶቼን ለማድቀቅ በእኔ ላይ ጉባኤ ጠርቷል።+

ይሖዋ ድንግሊቱን የይሁዳን ልጅ በወይን መጭመቂያ ውስጥ ረግጧል።+

ע [አይን]

16 በእነዚህ ነገሮች የተነሳ አለቅሳለሁ፤+ ዓይኖቼ እንባ ያፈሳሉ።

ሊያጽናናኝ ወይም መንፈሴን* ሊያድስ የሚችል ሰው ከእኔ ርቋልና።

ወንዶች ልጆቼ ተጥለዋል፤ ጠላት አይሏልና።

פ [ፔ]

17 ጽዮን እጆቿን ዘረጋች፤+ የሚያጽናናትም የለም።

በያዕቆብ ዙሪያ ያሉት ሁሉ ጠላቶቹ እንዲሆኑ ይሖዋ ትእዛዝ አስተላልፏል።+

ኢየሩሳሌም ለእነሱ አስጸያፊ ነገር ሆናለች።+

צ [ጻዴ]

18 ይሖዋ ጻድቅ ነው፤+ ትእዛዙን ተላልፌአለሁና።*+

እናንተ ሰዎች ሁሉ፣ አዳምጡ፤ ሥቃዬንም ተመልከቱ።

ደናግሌና* ወጣት ወንዶቼ በግዞት ተወስደዋል።+

ק [ኮፍ]

19 ወዳጆቼን ጠራኋቸው፤ እነሱ ግን ከዱኝ።+

ካህናቴና ሽማግሌዎቼ በሕይወት ለመቆየት* ብለው

የሚበላ ነገር ሲፈልጉ በከተማዋ ውስጥ አለቁ።+

ר [ረሽ]

20 ይሖዋ ሆይ፣ ተመልከት፤ በከባድ ጭንቀት ተውጫለሁና።

አንጀቴም ተላወሰ።

ልቤ በውስጤ እጅግ ተረብሿል፤ የለየለት ዓመፀኛ ሆኛለሁና።+

በውጭ ሰይፍ ይፈጃል፤+ በቤት ውስጥ ደግሞ ሞት አለ።

ש [ሺን]

21 ሰዎች ሲቃዬን ሰምተዋል፤ የሚያጽናናኝም የለም።

ጠላቶቼ ሁሉ ስለደረሰብኝ ጥፋት ሰምተዋል።

ይህን ጥፋት ስላመጣህ ደስ ተሰኝተዋል።+

አንተ ግን የተናገርከውን ቀን በእነሱ ላይ ታመጣለህ፤+ በዚያን ጊዜ እነሱ እንደ እኔ ይሆናሉ።+

ת [ታው]

22 ክፋታቸው ሁሉ በፊትህ ይቅረብ፤ በሠራኋቸው በደሎች ሁሉ የተነሳ

እኔን እንደቀጣኸኝ፣ እነሱንም ቅጣቸው።+

ለቅሶዬ በዝቷልና፤ ልቤም ታሟል።

א [አሌፍ]

2 ይሖዋ የጽዮንን ሴት ልጅ በቁጣው ደመና እንዴት ሸፈናት!

የእስራኤልን ውበት ከሰማይ ወደ ምድር ጥሏል።+

በቁጣው ቀን የእግሩን ማሳረፊያ አላስታወሰም።+

ב [ቤት]

 2 ይሖዋ የያዕቆብን መኖሪያዎች በሙሉ ያላንዳች ርኅራኄ ውጧል።

የይሁዳን ሴት ልጅ የተመሸጉ ቦታዎች በቁጣው አፈራርሷል።+

መንግሥቱንና መኳንንቷን ወደ መሬት ጥሏል፤ ደግሞም አርክሷል።+

ג [ጊሜል]

 3 የእስራኤልን ብርታት* ሁሉ በታላቅ ቁጣ ቆረጠ።

ጠላት በቀረበ ጊዜ እሱ ቀኝ እጁን መለሰ፤+

በዙሪያው ያለውን ሁሉ እንደሚበላ እሳትም ቁጣው በያዕቆብ ላይ ነደደ።+

ד [ዳሌት]

 4 እንደ ጠላት ደጋኑን ወጠረ፤* ቀኝ እጁም እንደ ባላጋራ ተዘጋጀች፤+

ለዓይን የሚማርኩትን ሁሉ ገደለ።+

በጽዮን ሴት ልጅ ድንኳንም ላይ+ ቁጣውን እንደ እሳት አፈሰሰ።+

ה [ሄ]

 5 ይሖዋ እንደ ጠላት ሆነ፤+

እስራኤልን ዋጠ።

ማማዎቿን ሁሉ ዋጠ፤

የተመሸጉ ስፍራዎቿን ሁሉ አወደመ።

በይሁዳ ሴት ልጅ ዘንድ ለቅሶንና ዋይታን አበዛ።

ו [ዋው]

 6 የራሱን ዳስ በአትክልት ቦታ እንዳለች ጎጆ አፈረሰ።+

በዓሉ እንዲያከትም* አደረገ።+

ይሖዋ በጽዮን፣ በዓልና ሰንበት እንዲረሳ አድርጓል፤

በኃይለኛ ቁጣውም ንጉሡንና ካህኑን አቃሏል።+

ז [ዛየን]

 7 ይሖዋ መሠዊያውን ናቀ፤

መቅደሱን ተወ።+

የማይደፈሩ ማማዎቿን ግንቦች ለጠላት አሳልፎ ሰጠ።+

በበዓል ቀን እንደሚደረገው ሁሉ በይሖዋ ቤት በታላቅ ድምፅ ጮኹ።+

ח [ኼት]

 8 ይሖዋ የጽዮንን ሴት ልጅ ቅጥር ለማፍረስ ቆርጧል።+

የመለኪያ ገመዱን ዘርግቷል።+

ከማጥፋትም እጁን አልመለሰም።

የመከላከያ ግንቡና ቅጥሩ እንዲያዝኑ አደረገ።

በአንድነትም ደከሙ።

ט [ቴት]

 9 በሮቿ ወደ መሬት ሰጠሙ።+

መቀርቀሪያዎቿን አስወገደ፤ ደግሞም ሰባበረ።

ንጉሥዋና መኳንንቷ በብሔራት መካከል ናቸው።+

ሕግ* የለም፤ ነቢያቷም እንኳ ከይሖዋ የተገለጠላቸው ራእይ የለም።+

י [ዮድ]

10 የጽዮን ሴት ልጅ ሽማግሌዎች ዝም ብለው መሬት ላይ ይቀመጣሉ።+

በራሳቸው ላይ አቧራ ይነሰንሳሉ፤ ማቅም ይለብሳሉ።+

የኢየሩሳሌም ደናግል ራሳቸውን ወደ መሬት ደፍተዋል።

כ [ካፍ]

11 ከማልቀሴ ብዛት ዓይኖቼ ፈዘዙ።+

አንጀቴ ተላወሰ።

በሕዝቤ ሴት ልጅ* ላይ ከደረሰው ውድቀት+

እንዲሁም በከተማዋ አደባባዮች ተዝለፍልፈው ከወደቁት ልጆችና ሕፃናት+ የተነሳ ጉበቴ መሬት ላይ ፈሰሰ።

ל [ላሜድ]

12 ልክ እንደቆሰለ ሰው በከተማዋ አደባባዮች ተዝለፍልፈው ሲወድቁና

በእናቶቻቸው ጉያ ሆነው ለመሞት ሲያጣጥሩ፣*

እናቶቻቸውን “እህልና የወይን ጠጅ የት አለ?” ብለው ይጠይቃሉ።+

מ [ሜም]

13 የኢየሩሳሌም ሴት ልጅ ሆይ፣ ምሥክር የሚሆን ምን ነገር ላቀርብልሽ እችላለሁ?

ከምንስ ጋር ላመሳስልሽ እችላለሁ?

ድንግሊቱ የጽዮን ሴት ልጅ ሆይ፣ አጽናናሽ ዘንድ ከማን ጋር ላወዳድርሽ እችላለሁ?

የደረሰብሽ ጥፋት እንደ ባሕር ሰፊ ነውና።+ ማን ሊፈውስሽ ይችላል?+

נ [ኑን]

14 ነቢያትሽ ያዩልሽ ራእይ ሐሰትና ከንቱ ነው፤+

ተማርከሽ እንዳትወሰጂ ለማድረግ በደልሽን አላጋለጡም፤+

ይልቁንም ራእይ ተገለጠልን እያሉ ሐሰትና አሳሳች ቃል ይነግሩሻል።+

ס [ሳሜኽ]

15 በመንገድ የሚያልፉ ሁሉ በማሾፍ እጃቸውን ያጨበጭቡብሻል።+

“‘ፍጹም ውበት የተላበሰችና የምድር ሁሉ ደስታ’+ በማለት ይጠሯት የነበረችው ከተማ ይህች ናት?” እያሉ በመገረም

በኢየሩሳሌም ሴት ልጅ ላይ ያፏጫሉ፤+ ራሳቸውንም ይነቀንቃሉ።

פ [ፔ]

16 ጠላቶችሽ ሁሉ በአንቺ ላይ አፋቸውን ከፍተዋል።

እነሱ ያፏጫሉ፤ ጥርሳቸውንም ያፋጫሉ፤

ደግሞም “ዋጥናት።+ ስንጠብቀው የነበረው ቀን ይህ ነው!+ ጊዜው ደርሶ ለማየት በቃን!”+ ይላሉ።

ע [አይን]

17 ይሖዋ ያሰበውን አድርጓል፤+

የተናገረውን፣ ከጥንትም ጀምሮ ያዘዘውን+ ፈጽሟል።+

ያላንዳች ርኅራኄ አፍርሷል።+

ጠላት በአንቺ ላይ በደረሰው ነገር ደስ እንዲሰኝ፣ የባላጋራዎችሽም ብርታት* ከፍ ከፍ እንዲል አድርጓል።

צ [ጻዴ]

18 የጽዮን ሴት ልጅ ቅጥር ሆይ፣ ልባቸው ወደ ይሖዋ ይጮኻል።

እንባሽ እንደ ጅረት ቀን ከሌት ይፍሰስ።

ለራስሽ ፋታ አትስጪ፤ ዓይንሽ እንባ ማፍሰሱን አያቋርጥ።*

ק [ኮፍ]

19 ተነሺ! ሌሊት፣ ክፍለ ሌሊቶቹ ሲጀምሩ ጩኺ።

በይሖዋ ፊት ልብሽን እንደ ውኃ አፍስሺ።

በረሃብ ምክንያት በየመንገዱ ማዕዘን* ተዝለፍልፈው ለወደቁት+ ልጆችሽ ሕይወት* ስትዪ፣

እጆችሽን ወደ እሱ ዘርጊ።

ר [ረሽ]

20 ይሖዋ ሆይ፣ ክፉኛ የቀጣኸውን እይ፤ ደግሞም ተመልከት።

ሴቶች የሆዳቸውን ፍሬ፣ የገዛ ራሳቸውን ልጆች* ይብሉ?+

ደግሞስ ካህናቱና ነቢያቱ በይሖዋ መቅደስ ውስጥ ይገደሉ?+

ש [ሺን]

21 ወንድ ልጅና ሽማግሌ ሞተው በየመንገዱ ተዘርረዋል።+

ደናግሌና* ወጣት ወንዶቼ በሰይፍ ወድቀዋል።+

በቁጣህ ቀን ገደልክ፤ ያላንዳች ርኅራኄ አረድክ።+

ת [ታው]

22 በበዓል ቀን እንደሚደረገው ሁሉ+ ሽብርን ከየአቅጣጫው ጠራህ።

በይሖዋ የቁጣ ቀን ያመለጠም ሆነ በሕይወት የተረፈ የለም፤+

የወለድኳቸውንና* ያሳደግኳቸውን ልጆች ጠላቴ ፈጃቸው።+

א [አሌፍ]

3 እኔ ከቁጣው በትር የተነሳ መከራ ያየሁ ሰው ነኝ።

 2 ወደ ውጭ አስወጥቶኛል፤ በብርሃን ሳይሆን በጨለማ ውስጥ እንድሄድ አድርጎኛል።+

 3 ቀኑን ሙሉ በተደጋጋሚ እጁን በእኔ ላይ ሰነዘረ።+

ב [ቤት]

 4 ሥጋዬና ቆዳዬ እንዲያልቅ አደረገ፤

አጥንቶቼን ሰባበረ።

 5 ቅጥር ሠራብኝ፤ በመራራ መርዝና+ በመከራ ዙሪያዬን ከበበኝ።

 6 ከሞቱ ብዙ ጊዜ እንደሆናቸው ሰዎች፣ በጨለማ ስፍራዎች እንድቀመጥ አስገደደኝ።

ג [ጊሜል]

 7 ማምለጥ እንዳልችል በቅጥር ዘጋብኝ፤

ከመዳብ በተሠራ ከባድ የእግር ብረት አሰረኝ።+

 8 ደግሞም እርዳታ ለማግኘት አምርሬ ስጮኽ ጸሎቴን አይሰማም።*+

 9 መንገዶቼን በተጠረቡ ድንጋዮች ዘጋ፤

ጎዳናዎቼን አጣመመ።+

ד [ዳሌት]

10 እንደ ድብ፣ እንዳደፈጠ አንበሳም አድብቶ ይጠብቀኛል።+

11 ከመንገድ ገፍትሮ አስወጣኝ፤ ገነጣጠለኝም፤*

ወና አስቀረኝ።+

12 ደጋኑን ወጠረ፤* የፍላጻውም ዒላማ አደረገኝ።

ה [ሄ]

13 ኮሮጆው ውስጥ በያዛቸው ፍላጻዎች* ኩላሊቴን ወጋ።

14 የሕዝብ ሁሉ ማላገጫ ሆንኩ፤ ቀኑን ሙሉ በእኔ ላይ እየዘፈኑ ይሳለቁብኛል።

15 መራራ ነገሮችን እስኪበቃኝ ድረስ አበላኝ፤ ጭቁኝም አጠገበኝ።+

ו [ዋው]

16 ጥርሶቼን በጠጠር ይሰብራል፤

አመድ ላይ ይጥለኛል።+

17 ሰላም ነፈግከኝ፤* ጥሩ ነገር ምን እንደሆነ እንኳ ረሳሁ።

18 ስለዚህ “ግርማ ሞገሴ ተገፏል፤ ከይሖዋ የጠበቅኩት ነገርም ጠፍቷል” እላለሁ።

ז [ዛየን]

19 መጎሳቆሌንና ዱር አዳሪ* መሆኔን እንዲሁም ጭቁኝና መራራ መርዝ መብላቴን አስታውስ።+

20 አንተ በእርግጥ ታስታውሳለህ፤* እኔን ለመርዳትም ታጎነብሳለህ።+

21 ይህ ከልቤ አይጠፋም፤ ከዚህም የተነሳ በትዕግሥት እጠባበቃለሁ።+

ח [ኼት]

22 ከይሖዋ ታማኝ ፍቅር የተነሳ ሙሉ በሙሉ አልጠፋንም፤+

ምሕረቱ ፈጽሞ አያልቅምና።+

23 በየማለዳው አዲስ ነው፤+ ታማኝነትህ እጅግ ብዙ ነው።+

24 እኔ “ይሖዋ ድርሻዬ ነው”+ አልኩ፤* “እሱን በትዕግሥት የምጠባበቀው ለዚህ ነው።”+

ט [ቴት]

25 ይሖዋ በእሱ ተስፋ ለሚያደርግ፣+ እሱንም ዘወትር ለሚሻ ሰው* ጥሩ ነው።+

26 የይሖዋን ማዳን+ ዝም ብሎ* መጠባበቅ ጥሩ ነው።+

27 ሰው በልጅነቱ ቀንበር ቢሸከም ጥሩ ነው።+

י [ዮድ]

28 አምላክ ቀንበሩን በእሱ ላይ ሲጥልበት ዝም ብሎ ለብቻው ይቀመጥ።+

29 ፊቱን አቧራ ውስጥ ይቅበር፤+ ገና ተስፋ ሊኖር ይችላል።+

30 ጉንጩን፣ ለሚመታው ሰው ይስጥ፤ ስድብንም ይጥገብ።

כ [ካፍ]

31 ይሖዋ ለዘላለም አይጥለንምና።+

32 ለሐዘን የዳረገን ቢሆንም እንኳ እንደ ታማኝ ፍቅሩ ብዛት ምሕረት ያሳያል።+

33 የልቡ ፍላጎት የሰው ልጆች እንዲጎሳቆሉ ወይም እንዲያዝኑ ማድረግ አይደለምና።+

ל [ላሜድ]

34 የምድር እስረኞች ሁሉ በእግር ሲረገጡ፣+

35 በልዑል አምላክ ፊት ሰው ፍትሕ ሲነፈግ፣+

36 ሰው ከፍርድ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ሲጭበረበር፣

ይሖዋ እንዲህ ያለውን ነገር በቸልታ አያልፍም።

מ [ሜም]

37 ይሖዋ ካላዘዘ በቀር አንድን ነገር ተናግሮ መፈጸም የሚችል ማን ነው?

38 ከልዑሉ አምላክ አፍ

ክፉ ነገርና መልካም ነገር በአንድነት አይወጣም።

39 ሕያው የሆነ ሰው ኃጢአቱ ባስከተለበት መዘዝ ለምን ያጉረመርማል?+

נ [ኑን]

40 መንገዳችንን እንመርምር፤ ደግሞም እንፈትን፤+ ከዚያም ወደ ይሖዋ እንመለስ።+

41 በሰማያት ወዳለው አምላክ እጃችንን ዘርግተን ከልብ የመነጨ ልመና እናቅርብ፦+

42 “እኛ በድለናል፤ ደግሞም ዓምፀናል፤+ አንተም ይቅር አላልክም።+

ס [ሳሜኽ]

43 ጨርሶ እንዳንቀርብ በቁጣ አገድከን፤+

አሳደድከን፤ ያለርኅራኄም ገደልከን።+

44 ጸሎታችን እንዳያልፍ ወደ አንተ መቅረብ የሚቻልበትን መንገድ በደመና ዘጋህ።+

45 በሕዝቦች መካከል ጥራጊና ቆሻሻ አደረግከን።”

פ [ፔ]

46 ጠላቶቻችን ሁሉ በእኛ ላይ አፋቸውን ከፈቱ።+

47 ፍርሃትና ወጥመድ፣ ባድማነትና ጥፋት ዕጣ ፋንታችን ሆነ።+

48 ከሕዝቤ ሴት ልጅ ጥፋት የተነሳ ዓይኔ የእንባ ጎርፍ አፈሰሰ።+

ע [አይን]

49 ዓይኖቼ ያለማቋረጥና ያለእረፍት ያነባሉ፤+

50 ይሖዋ ከሰማይ ወደ ታች እስኪያይና እስኪመለከት ድረስ ያነባሉ።+

51 በከተማዬ ሴቶች ልጆች* ሁሉ ላይ የደረሰውን በማየቴ አዘንኩ።*+

צ [ጻዴ]

52 ጠላቶቼ ያለምክንያት እንደ ወፍ አደኑኝ።

53 ሕይወቴን በጉድጓድ ውስጥ ጸጥ ሊያደርጓት ሞከሩ፤ በላዬም ላይ የድንጋይ ናዳ ያወርዱብኛል።

54 በራሴ ላይ ውኃ ጎረፈ፤ እኔም “አለቀልኝ!” አልኩ።

ק [ኮፍ]

55 ይሖዋ ሆይ፣ ከጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ ስምህን ጠራሁ።+

56 ድምፄን ስማ፤ እርዳታና እፎይታ ለማግኘት የማሰማውን ጩኸት ላለመስማት ጆሮህን አትድፈን።

57  በጠራሁህ ቀን ወደ እኔ ቀረብክ። “አትፍራ” አልከኝ።

ר [ረሽ]

58 ይሖዋ ሆይ፣ ተሟገትክልኝ፤* ሕይወቴን ዋጀህ።+

59 ይሖዋ ሆይ፣ በእኔ ላይ የደረሰውን በደል አይተሃል፤ እባክህ ፍትሕ እንዳገኝ አድርግ።+

60 በቀላቸውን ሁሉ፣ በእኔም ላይ ያሴሩትን ሁሉ ተመልክተሃል።

ש [ሲን] ወይም [ሺን]

61 ይሖዋ ሆይ፣ ዘለፋቸውን፣ በእኔም ላይ ያሴሩትን ሁሉ ሰምተሃል፤+

62 ከባላንጣዎቼ አፍ የሚወጣውን ቃልና ቀኑን ሙሉ በእኔ ላይ የሚያንሾካሹኩትን ነገር ሰምተሃል።

63 እያቸው፤ ተቀምጠውም ሆነ ቆመው በዘፈናቸው ይሳለቁብኛል!

ת [ታው]

64 ይሖዋ ሆይ፣ እንደ ሥራቸው መልሰህ ትከፍላቸዋለህ።

65 እርግማንህን በእነሱ ላይ በማውረድ ደንዳና ልብ እንዲኖራቸው ታደርጋለህ።

66 ይሖዋ ሆይ፣ በቁጣ ታሳድዳቸዋለህ፤ ከሰማያትህም በታች ታጠፋቸዋለህ።

א [አሌፍ]

4 ያንጸባርቅ የነበረው ጥሩው ወርቅ፣+ ምንኛ ደበዘዘ!

የተቀደሱት ድንጋዮች*+ በየመንገዱ ማዕዘኖች* ላይ እንዴት ተበተኑ!+

ב [ቤት]

 2 በጠራ ወርቅ የተመዘኑት* የጽዮን ውድ ልጆች፣

የሸክላ ሠሪ እጅ እንደሠራው

የሸክላ ዕቃ እንዴት ተቆጠሩ!

ג [ጊሜል]

 3 ቀበሮዎች እንኳ ግልገሎቻቸውን ለማጥባት ጡታቸውን ይሰጣሉ፤

የሕዝቤ ሴት ልጅ ግን በምድረ በዳ እንዳሉ ሰጎኖች ጨካኝ ሆነች።+

ד [ዳሌት]

 4 ከውኃ ጥም የተነሳ፣ የሚጠባው ሕፃን ምላስ ከላንቃው ጋር ይጣበቃል።

ልጆች ምግብ ይለምናሉ፤+ አንዳች ነገር የሚሰጣቸው ግን የለም።+

ה [ሄ]

 5 ምርጥ ምግብ ይበሉ የነበሩ ሰዎች በየጎዳናው ላይ ጠኔ ይዟቸው ይተኛሉ።*+

ውድ ልብስ* ለብሰው ያደጉም+ የአመድ ቁልል ያቅፋሉ።

ו [ዋው]

 6 የሕዝቤ ሴት ልጅ የደረሰባት ቅጣት፣*

የማንም እጅ ሳይረዳት በድንገት የተገለበጠችው ሰዶም፣ በሠራችው ኃጢአት የተነሳ ከደረሰባት ቅጣት ይበልጥ ታላቅ ነው።+

ז [ዛየን]

 7 ናዝራውያኗ+ ከበረዶ ይልቅ የጠሩ፣ ከወተትም ይልቅ የነጡ ነበሩ።

ከዛጎል ይበልጥ የቀሉ ነበሩ፤ እንደተወለወለም ሰንፔር ነበሩ።

ח [ኼት]

 8 መልካቸው ከጥላሸት ይልቅ ጠቁሯል፤

በጎዳና ላይ ማንነታቸውን መለየት የቻለ የለም።

ቆዳቸው ተሸብሽቦ አጥንታቸው ላይ ተጣብቋል፤+ እንደደረቀ እንጨት ሆኗል።

ט [ቴት]

 9 በሰይፍ የሚወድቁት በረሃብ ከሚያልቁት ይሻላሉ፤+

እነዚህ የምድርን ፍሬ በማጣታቸው መንምነው ያልቃሉ።

י [ዮድ]

10 ሩኅሩኅ የሆኑ ሴቶች በገዛ እጃቸው ልጆቻቸውን ቀቅለዋል።+

የሕዝቤ ሴት ልጅ ጥፋት በደረሰባት ጊዜ እንደ እዝን እንጀራ ሆነውላቸዋል።+

כ [ካፍ]

11 ይሖዋ ቁጣውን ገልጿል፤

የሚነድ ቁጣውንም አፍስሷል።+

በጽዮን መሠረቶቿን የሚበላ እሳት አንድዷል።+

ל [ላሜድ]

12 የምድር ነገሥታትና የምድር ነዋሪዎች ሁሉ

ባላጋራም ሆነ ጠላት በኢየሩሳሌም በሮች ይገባል የሚል እምነት አልነበራቸውም።+

מ [ሜም]

13 ይህ የደረሰው ነቢያቷ በሠሩት ኃጢአትና ካህናቷ በፈጸሙት በደል የተነሳ ነው፤+

እነሱ በመካከሏ የነበሩትን ጻድቃን ደም አፍስሰዋል።+

נ [ኑን]

14 ታውረው በየጎዳናው ተቅበዘበዙ።+

በደም ስለተበከሉ+

ማንም ልብሳቸውን ለመንካት አይደፍርም።

ס [ሳሜኽ]

15 “እናንተ ርኩሳን! ሂዱ!” ይሏቸዋል። “ሂዱ! ሂዱ! አትንኩን!” ብለው ይጮኹባቸዋል።

መኖሪያ አጥተው ይቅበዘበዛሉና።

በብሔራት መካከል ያሉ ሰዎች እንዲህ ብለዋል፦ “ከእንግዲህ ከእኛ ጋር እዚህ መኖር አይችሉም።*+

פ [ፔ]

16 ይሖዋ ራሱ በታትኗቸዋል፤+

ዳግመኛም በሞገስ ዓይን አይመለከታቸውም።

ሰዎች ለካህናቱ አክብሮት አይኖራቸውም፤+ ለሽማግሌዎቹም ሞገስ አያሳዩም።”+

ע [አይን]

17 አሁንም እንኳ እርዳታ እናገኛለን ብለን በከንቱ ስንጠባበቅ ዓይኖቻችን ደከሙ።+

ሊያድነን ከማይችል ብሔር እርዳታ ለማግኘት ስንጠባበቅ ቆየን።+

צ [ጻዴ]

18 እግር በእግር ተከታተሉን፤+ በመሆኑም በአደባባዮቻችን መንቀሳቀስ አልቻልንም።

መጨረሻችን ቀርቧል፤ የሕይወት ዘመናችን አብቅቷል፤ ፍጻሜያችን ደርሷልና።

ק [ኮፍ]

19 አሳዳጆቻችን በሰማይ ከሚበርሩ ንስሮች ይልቅ ፈጣኖች ነበሩ።+

በተራሮች ላይ አጥብቀው አሳደዱን፤ በምድረ በዳ አድፍጠው አጠቁን።

ר [ረሽ]

20 በይሖዋ የተቀባው፣+ የሕይወታችን እስትንፋስ፣ ጥልቅ ጉድጓዳቸው ውስጥ ገብቶ ተያዘ፤+

“በእሱ ጥላ ሥር በብሔራት መካከል እንኖራለን” ብለን ነበር።

ש [ሲን]

21 በዑጽ ምድር የምትኖሪ የኤዶም ሴት ልጅ ሆይ፣+ ሐሴት አድርጊ፤ ደስም ይበልሽ።

ይሁንና ጽዋው ለአንቺም ይደርስሻል፤+ ትሰክሪያለሽ፤ እርቃንሽንም ትገልጫለሽ።+

ת [ታው]

22 የጽዮን ሴት ልጅ ሆይ፣ በበደልሽ ምክንያት የደረሰብሽ ቅጣት አብቅቷል።

ከእንግዲህ ወዲህ ወደ ግዞት አይወስድሽም።+

ይሁንና የኤዶም ሴት ልጅ ሆይ፣ ትኩረቱን በሠራሽው በደል ላይ ያደርጋል።

ኃጢአትሽን ይገልጣል።+

5 ይሖዋ ሆይ፣ የደረሰብንን ነገር አስታውስ።

ውርደታችንን እይ፤ ደግሞም ተመልከት።+

 2 ርስታችን ለእንግዶች፣ ቤቶቻችን ለባዕድ አገር ሰዎች ተሰጡ።+

 3 አባት እንደሌላቸው ወላጅ አልባ ልጆች ሆንን፤ እናቶቻችን እንደ መበለቶች ሆኑ።+

 4 የገዛ ራሳችንን ውኃ ለመጠጣት መክፈል ነበረብን፤+ የገዛ እንጨታችንን የምናገኘውም በግዢ ነበር።

 5 አሳዳጆቻችን አንገታችንን ሊይዙ ተቃረቡ፤

ዝለናል፤ እረፍት የሚባል ነገርም አላገኘንም።+

 6 በቂ ምግብ ለማግኘት ወደ ግብፅና ወደ አሦር እጃችንን ዘረጋን።+

 7 ኃጢአት የሠሩት አባቶቻችን አሁን በሕይወት የሉም፤ እኛ ግን የእነሱን በደል ለመሸከም ተገደድን።

 8 አሁን አገልጋዮች ይገዙናል፤ ከእጃቸው የሚያስጥለን ማንም የለም።

 9 በምድረ በዳ ካለው ሰይፍ የተነሳ ምግባችንን የምናመጣው በሕይወታችን* ቆርጠን ነው።+

10 ከከባድ ረሃብ የተነሳ ቆዳችን እንደ ምድጃ ጋለ።+

11 በጽዮን ያሉ ሚስቶችና በይሁዳ ከተሞች ያሉ ደናግል ተዋረዱ።*+

12 መኳንንቱ በእጃቸው ተንጠለጠሉ፤+ ሽማግሌዎችም አልተከበሩም።+

13 ወጣቶች ወፍጮውን ይሸከማሉ፤ ልጆችም ከባድ እንጨት ሲሸከሙ ይደናቀፋሉ።

14 ሽማግሌዎች ከከተማዋ በር ሄደዋል፤+ ወጣቶችም ሙዚቃቸውን መጫወት አቁመዋል።+

15 ደስታ ከልባችን ራቀ፤ ጭፈራችን በሐዘን ተተካ።+

16 ራሳችን ላይ ያለው አክሊል ወድቋል። ኃጢአት ስለሠራን ወዮልን!

17 ከዚህ የተነሳ ልባችን ታመመ፤+

ከእነዚህም ነገሮች የተነሳ ዓይኖቻችን ፈዘዙ፤+

18 ባድማ የሆነችው የጽዮን ተራራ+ አሁን የቀበሮዎች መፈንጫ ሆናለችና።

19 ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ግን ለዘላለም በዙፋንህ ላይ ትቀመጣለህ።

ዙፋንህ ከትውልድ እስከ ትውልድ ነው።+

20 ለዘላለም የረሳኸንና ለረጅም ዘመን የተውከን ለምንድን ነው?+

21 ይሖዋ ሆይ፣ ወደ አንተ መልሰን፤ እኛም በፈቃደኝነት እንመለሳለን።+

ዘመናችንን እንደቀድሞው አድስልን።+

22 አንተ ግን ፈጽሞ ጥለኸናል።

አሁንም በእኛ ላይ እጅግ እንደተቆጣህ ነህ።+

የመጀመሪያዎቹ አራት ምዕራፎች በዕብራይስጥ ፊደላት ቅደም ተከተል የተዘጋጁ ሙሾዎች ናቸው።

ወይም “ወጣት ሴቶቿ።”

ቃል በቃል “ራሶቿ።”

ወይም “ፈነደቁ።”

ወይም “ነፍስን ለመመለስ።”

ኢየሩሳሌምን የሚያመለክት ዘይቤያዊ አነጋገር ነው።

ወይም “ነፍሴን።”

ቃል በቃል “በአፉ ላይ ዓመፅ ፈጽሜአለሁ።”

ወይም “ወጣት ሴቶቼና።”

ወይም “ነፍስን ለመመለስ።”

ቃል በቃል “ቀንድ።”

ቃል በቃል “ረገጠ።”

ወይም “እንዲጠፋ።”

ወይም “መመሪያ፤ ትምህርት።”

በሰውኛ ዘይቤ የተገለጸ ቅኔያዊ አነጋገር፤ አዘኔታን ወይም ርኅራኄን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።

ወይም “ነፍሳቸው ስታጣጥር።”

ቃል በቃል “ቀንድ።”

ቃል በቃል “የዓይንሽ ሴት ልጅ እንባ ማፍሰሷን አታቋርጥ።”

ቃል በቃል “በጎዳና ሁሉ ራስ ላይ።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “የገዛ ራሳቸውን ጤናማ ልጆች።”

ወይም “ወጣት ሴቶቼና።”

ወይም “ጤናማ ሆነው የወለድኳቸውንና።”

ወይም “አገደ፤ ከለከለ።”

“ያልታረሰም መሬት አደረገኝ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ቃል በቃል “ረገጠ።”

ቃል በቃል “ወንዶች ልጆች።”

ወይም “ነፍሴን ሰላም ነፈግካት።”

ወይም “ቤት የለሽ።”

ወይም “ነፍስህ በእርግጥ ታስታውሳለች።”

ወይም “ነፍሴ ‘ይሖዋ ድርሻዬ ነው’ አለች።”

ወይም “ለምትሻ ነፍስ።”

ወይም “በትዕግሥት።”

ወይም “በከተማዬ ዙሪያ ባሉ ከተሞች።”

ወይም “ነፍሴ አዘነች።”

ወይም “ለነፍሴ ተሟገትክላት።”

ወይም “የመቅደሱ ድንጋዮች።”

ቃል በቃል “በጎዳናዎቹ ሁሉ ራስ።”

ወይም “እንደጠራ ወርቅ ውድ የነበሩት።”

ቃል በቃል “ይጠፋሉ።”

ቃል በቃል “ደማቅ ቀይ።” ይኸውም ደማቅ ቀይ የሆነ ውድ ልብስ።

ቃል በቃል “በደል።”

ወይም “የባዕድ አገር ሰዎች ሆነው መኖር አይችሉም።”

ወይም “በነፍሳችን።”

ወይም “ተደፈሩ።”

    የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ ጽሑፎች (2011-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ