ለዮሐንስ የተገለጠለት ራእይ
1 በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሊፈጸሙ የሚገባቸውን ነገሮች ለባሪያዎቹ እንዲያሳይ+ አምላክ ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠውና+ እሱ የገለጠው ራእይ* ይህ ነው። ኢየሱስም መልአኩን ልኮ ለባሪያው ለዮሐንስ+ በምልክቶች ገለጠለት፤ 2 ዮሐንስም አምላክ ስለሰጠው ቃልና ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሰጠው ምሥክርነት ይኸውም ስላያቸው ነገሮች ሁሉ መሥክሯል። 3 የዚህን ትንቢት ቃል ጮክ ብሎ የሚያነብ ደስተኛ ነው፤ እንዲሁም ቃሉን የሚሰሙትና በውስጡ የተጻፉትን ነገሮች የሚጠብቁት ደስተኞች ናቸው፤+ የተወሰነው ጊዜ ቀርቧልና።
4 ከዮሐንስ፣ በእስያ አውራጃ ለሚገኙ ለሰባቱ ጉባኤዎች፦+
“ካለው፣ ከነበረውና ከሚመጣው”+ እንዲሁም በዙፋኑ ፊት ካሉት ከሰባቱ መናፍስት+ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ 5 በተጨማሪም “ታማኝ ምሥክር፣”+ “ከሙታን በኩር”+ እና “የምድር ነገሥታት ገዢ”+ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።
ለወደደንና+ በገዛ ደሙ አማካኝነት ከኃጢአታችን ነፃ ላወጣን፣+ 6 ነገሥታት*+ እንዲሁም ለአምላኩና ለአባቱ ካህናት+ ላደረገን ለእሱ ክብርና ኃይል ለዘላለም ይሁን። አሜን።
7 እነሆ፣ ከደመናት ጋር ይመጣል፤+ ዓይኖች ሁሉ፣ የወጉትም ያዩታል፤ በእሱም የተነሳ የምድር ነገዶች ሁሉ በሐዘን ደረታቸውን ይደቃሉ።+ አዎ፣ ይህ በእርግጥ ይሆናል። አሜን።
8 “እኔ አልፋና ኦሜጋ፣*+ ያለው፣ የነበረውና የሚመጣው፣ ሁሉን ቻይ ነኝ” ይላል ይሖዋ* አምላክ።+
9 የኢየሱስ ተከታይ በመሆኔ+ ከእናንተ ጋር የመከራው፣+ የመንግሥቱና+ የጽናቱ+ ተካፋይ የሆንኩ እኔ ወንድማችሁ ዮሐንስ፣ ስለ አምላክ በመናገሬና ስለ ኢየሱስ በመመሥከሬ ጳጥሞስ በምትባል ደሴት ነበርኩ። 10 በመንፈስ ወደ ጌታ ቀን ተወሰድኩ፤ ከኋላዬም እንደ መለከት ያለ ኃይለኛ ድምፅ ሰማሁ፤ 11 እንዲህም አለኝ፦ “የምታየውን በመጽሐፍ ጥቅልል ላይ ጽፈህ በኤፌሶን፣+ በሰምርኔስ፣+ በጴርጋሞን፣+ በትያጥሮን፣+ በሰርዴስ፣+ በፊላደልፊያና+ በሎዶቅያ+ ለሚገኙት ለሰባቱ ጉባኤዎች ላከው።”
12 እኔም እያናገረኝ ያለው ማን እንደሆነ ለማየት ዞር አልኩ፤ በዚህ ጊዜም ሰባት የወርቅ መቅረዞች ተመለከትኩ፤+ 13 በመቅረዞቹም መካከል የሰው ልጅ የሚመስል አየሁ፤+ እሱም እስከ እግሩ የሚደርስ ልብስ የለበሰና ደረቱ ላይ የወርቅ መታጠቂያ የታጠቀ ነበር። 14 በተጨማሪም ራሱና ፀጉሩ እንደ ነጭ ሱፍ፣ እንደ በረዶም ነጭ ነበር፤ ዓይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ነበሩ፤+ 15 እግሮቹም እቶን ውስጥ እንደጋለ የጠራ መዳብ ነበሩ፤+ ድምፁም እንደ ውኃ ፏፏቴ ነበር። 16 በቀኝ እጁም ሰባት ከዋክብት ይዞ ነበር፤+ ከአፉም በሁለቱም በኩል ስለት ያለው ረጅም ሰይፍ+ ወጣ፤ ፊቱም በሙሉ ድምቀቱ እንደሚያበራ ፀሐይ ነበር።+ 17 ባየሁት ጊዜ እንደሞተ ሰው ሆኜ እግሩ ሥር ወደቅኩ።
እሱም ቀኝ እጁን በላዬ ጭኖ እንዲህ አለኝ፦ “አትፍራ። እኔ የመጀመሪያውና+ የመጨረሻው ነኝ፤+ 18 ሕያው የሆነውም እኔ ነኝ፤+ ሞቼም ነበር፤+ አሁን ግን ለዘላለም እኖራለሁ፤+ የሞትና የመቃብር* ቁልፎችም አሉኝ።+ 19 ስለዚህ ያየሃቸውን ነገሮች፣ አሁን እየተከናወኑ ያሉትንና ከእነዚህ በኋላ የሚፈጸሙትን ነገሮች ጻፍ። 20 በቀኝ እጄ ላይ ያየሃቸው የሰባቱ ከዋክብት እንዲሁም የሰባቱ የወርቅ መቅረዞች ቅዱስ ሚስጥር ይህ ነው፦ ሰባቱ ከዋክብት የሰባቱን ጉባኤዎች መላእክት* ያመለክታሉ፤ ሰባቱ መቅረዞች ደግሞ ሰባቱን ጉባኤዎች ያመለክታሉ።+
2 “በኤፌሶን ላለው ጉባኤ+ መልአክ+ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ ሰባቱን ከዋክብት በቀኝ እጁ የያዘውና በሰባቱ የወርቅ መቅረዞች መካከል የሚመላለሰው+ እንዲህ ይላል፦ 2 ‘ሥራህን፣ ድካምህንና ጽናትህን አውቃለሁ፤ ደግሞም መጥፎ ሰዎችን መታገሥ እንደማትችል እንዲሁም ሐዋርያት ሳይሆኑ ሐዋርያት ነን የሚሉትን+ ፈትነህ ውሸታሞች ሆነው እንዳገኘሃቸው አውቃለሁ። 3 በተጨማሪም በአቋምህ ጸንተሃል፤ ስለ ስሜም ስትል ብዙ ችግሮችን ተቋቁመሃል፤+ ደግሞም አልታከትክም።+ 4 ይሁን እንጂ የምነቅፍብህ ነገር አለኝ፤ ይኸውም መጀመሪያ ላይ የነበረህን ፍቅር ትተሃል።
5 “‘ስለዚህ ከየት እንደወደቅክ አስታውስ፤ ንስሐም ግባ፤+ ቀድሞ ታደርገው የነበረውንም ነገር አድርግ። አለዚያ እመጣብሃለሁ፤ ንስሐ ካልገባህ+ መቅረዝህን+ ከስፍራው አነሳዋለሁ። 6 ያም ሆኖ አንድ የሚያስመሰግንህ ነገር አለ፦ እኔም የምጠላውን የኒቆላውያንን+ ሥራ* ትጠላለህ። 7 መንፈስ ለጉባኤዎቹ የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ፦+ ድል ለሚነሳ+ በአምላክ ገነት ውስጥ ካለው የሕይወት ዛፍ እንዲበላ እፈቅድለታለሁ።’+
8 “በሰምርኔስ ላለው ጉባኤ መልአክም እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ ‘የመጀመሪያውና የመጨረሻው፣’+ ሞቶ የነበረውና ዳግም ሕያው የሆነው+ እንዲህ ይላል፦ 9 ‘መከራህንና ድህነትህን አውቃለሁ፤ ይሁንና ሀብታም ነህ፤+ አይሁዳውያን ሳይሆኑ አይሁዳውያን ነን የሚሉት የሚሳደቡትን ስድብ አውቃለሁ፤ እነሱ የሰይጣን ምኩራብ ናቸው።+ 10 ሊደርስብህ ያለውን መከራ አትፍራ።+ እነሆ፣ ሙሉ በሙሉ እንድትፈተኑና ለአሥር ቀን መከራ እንድትቀበሉ ዲያብሎስ አንዳንዶቻችሁን እስር ቤት ይከታል። እስከ ሞት ድረስ ታማኝነትህን አስመሥክር፤ እኔም የሕይወትን አክሊል እሰጥሃለሁ።+ 11 መንፈስ ለጉባኤዎቹ የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ፦+ ድል የሚነሳ+ በሁለተኛው ሞት+ ከቶ አይጎዳም።’
12 “በጴርጋሞን ላለው ጉባኤ መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ በሁለቱም በኩል ስለት ያለው ረጅም ሰይፍ+ የያዘው እንዲህ ይላል፦ 13 ‘የምትኖረው የሰይጣን ዙፋን ባለበት እንደሆነ አውቃለሁ፤ ያም ሆኖ ስሜን አጥብቀህ ይዘሃል፤+ ሰይጣን በሚኖርበት፣ እናንተ ባላችሁበት ቦታ በተገደለው+ በታማኙ ምሥክሬ+ በአንቲጳስ ዘመን እንኳ በእኔ ላይ ያለህን እምነት አልካድክም።+
14 “‘ይሁን እንጂ የምነቅፍብህ ጥቂት ነገሮች አሉኝ፤ የእስራኤል ልጆች ለጣዖት የተሠዉ ነገሮችን እንዲበሉና የፆታ ብልግና* እንዲፈጽሙ+ በፊታቸው ማሰናከያ እንዲያስቀምጥ ባላቅን+ ያስተማረውን የበለዓምን ትምህርት+ አጥብቀው የሚከተሉ በመካከልህ አሉ። 15 እንደዚሁም የኒቆላዎስን የኑፋቄ ትምህርት+ አጥብቀው የሚከተሉ ሰዎች በመካከልህ አሉ። 16 ስለዚህ ንስሐ ግባ። አለዚያ በፍጥነት ወደ አንተ እመጣለሁ፤ በአፌም ረጅም ሰይፍ እዋጋቸዋለሁ።+
17 “‘መንፈስ ለጉባኤዎቹ የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ፦+ ድል ለሚነሳ+ ከተሰወረው መና ላይ እሰጠዋለሁ፤+ እንዲሁም ነጭ ጠጠር እሰጠዋለሁ፤ በጠጠሩም ላይ ከሚቀበለው ሰው በቀር ማንም የማያውቀው አዲስ ስም ተጽፎበታል።’
18 “በትያጥሮን+ ላለው ጉባኤ መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ እንደ እሳት ነበልባል የሆኑ ዓይኖችና+ እንደጠራ መዳብ ያሉ እግሮች+ ያሉት የአምላክ ልጅ እንዲህ ይላል፦ 19 ‘ሥራህን፣ ፍቅርህን፣ እምነትህን፣ አገልግሎትህንና ጽናትህን አውቃለሁ፤ ደግሞም ከመጀመሪያው ሥራህ ይልቅ የአሁኑ እንደሚበልጥ አውቃለሁ።
20 “‘ይሁን እንጂ የምነቅፍብህ ነገር አለኝ፤ ራሷን ነቢዪት ብላ የምትጠራውን ያቺን ሴት ኤልዛቤልን+ ችላ ብለሃታል፤ እሷም የፆታ ብልግና* እንዲፈጽሙና+ ለጣዖት የተሠዉ ነገሮችን እንዲበሉ ባሪያዎቼን ታስተምራለች እንዲሁም ታሳስታለች። 21 እኔም ንስሐ እንድትገባ ጊዜ ሰጠኋት፤ እሷ ግን ለፈጸመችው የፆታ ብልግና* ንስሐ ለመግባት ፈቃደኛ አይደለችም። 22 እነሆ፣ የአልጋ ቁራኛ ላደርጋት ነው፤ ከእሷ ጋር ምንዝር የሚፈጽሙትም ከሥራዋ ንስሐ ካልገቡ ታላቅ መከራ አመጣባቸዋለሁ። 23 እንዲሁም እኔ የውስጥ ሐሳብንና* ልብን የምመረምር እንደሆንኩ ጉባኤዎቹ ሁሉ እንዲያውቁ ልጆቿን በገዳይ መቅሰፍት እፈጃለሁ፤ ለእያንዳንዳችሁም እንደ ሥራችሁ እሰጣችኋለሁ።+
24 “‘ነገር ግን ይህን ትምህርት ለማትከተሉ ሁሉና “የሰይጣን ጥልቅ ነገሮች”+ የሚባሉትን ለማታውቁ፣ በትያጥሮን ለምትገኙ ለቀራችሁት ይህን እላለሁ፦ በእናንተ ላይ ምንም ዓይነት ተጨማሪ ሸክም አልጭንባችሁም። 25 ብቻ እኔ እስክመጣ ድረስ ያላችሁን አጥብቃችሁ ያዙ።+ 26 ደግሞም ድል ለሚነሳና በሥራዬ እስከ መጨረሻ ለሚጸና በብሔራት ላይ ሥልጣን እሰጠዋለሁ፤+ 27 ይህም ከአባቴ የተቀበልኩት ዓይነት ሥልጣን ነው። ድል የነሳውም ሕዝቦችን እንደ ሸክላ ዕቃ እንዲደቅቁ በብረት በትር ይገዛቸዋል።*+ 28 እኔም አጥቢያ ኮከብ+ እሰጠዋለሁ። 29 መንፈስ ለጉባኤዎቹ የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ።’
3 “በሰርዴስ ላለው ጉባኤ መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ ሰባቱ የአምላክ መናፍስት+ ያሉትና ሰባቱን ከዋክብት+ የያዘው እንዲህ ይላል፦ ‘ሥራህን አውቃለሁ፤ ሕያው ነው የሚል ስም አለህ፤ ነገር ግን ሞተሃል።+ 2 ሥራህን በአምላኬ ፊት በተሟላ ሁኔታ ተጠናቆ ስላላገኘሁት ንቃ፤+ ሊሞቱ የተቃረቡትን የቀሩትን ነገሮችም አጠናክር። 3 ስለዚህ የተቀበልከውንና የሰማኸውን ምንጊዜም አስብ፤ እንዲሁም ዘወትር ጠብቀው፤ ንስሐም ግባ።+ ካልነቃህ ግን እንደ ሌባ እመጣለሁ፤+ በየትኛው ሰዓት ከተፍ እንደምልብህም ፈጽሞ አታውቅም።+
4 “‘ይሁን እንጂ ልብሳቸውን ያላረከሱ+ ጥቂት ሰዎች* ከአንተ ጋር በሰርዴስ አሉ፤ እነሱም የሚገባቸው ስለሆኑ ነጭ ልብስ+ ለብሰው ከእኔ ጋር ይሄዳሉ። 5 ድል የሚነሳም+ልክ እንዲሁ ነጭ ልብስ ይለብሳል፤+ እኔም ስሙን ከሕይወት መጽሐፍ+ በምንም ዓይነት አልደመስስም፤* ከዚህ ይልቅ በአባቴ ፊትና በመላእክቱ ፊት ለስሙ እመሠክራለሁ።+ 6 መንፈስ ለጉባኤዎቹ የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ።’
7 “በፊላደልፊያ ላለው ጉባኤ መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ ቅዱስና+ እውነተኛ የሆነው፣+ የዳዊት ቁልፍ ያለው፣+ ማንም እንዳይዘጋ፣ የሚከፍተው እንዲሁም ማንም እንዳይከፍት፣ የሚዘጋው እሱ እንዲህ ይላል፦ 8 ‘ሥራህን አውቃለሁ፤ እነሆ፣ ማንም ሊዘጋው የማይችል የተከፈተ በር በፊትህ አድርጌአለሁ።+ ደግሞም ጥቂት ኃይል እንዳለህ አውቃለሁ፤ ቃሌንም ጠብቀሃል፤ ስሜንም አልካድክም። 9 እነሆ፣ አይሁዳውያን ሳይሆኑ አይሁዳውያን ነን እያሉ የሚዋሹት፣+ ከሰይጣን ምኩራብ የሆኑት ወደ አንተ መጥተው በእግርህ ፊት እንዲሰግዱ* አደርጋለሁ፤ እንዲሁም እንደወደድኩህ እንዲያውቁ አደርጋለሁ። 10 ስለ ጽናቴ የተነገረውን ቃል ስለጠበቅክ*+ እኔም በምድር ላይ የሚኖሩትን ለመፈተን በመላው ምድር ላይ ከሚመጣው የፈተና ሰዓት እጠብቅሃለሁ።+ 11 ቶሎ እመጣለሁ።+ ማንም አክሊልህን እንዳይወስድብህ ያለህን ምንጊዜም አጥብቀህ ያዝ።+
12 “‘ድል የሚነሳውን በአምላኬ ቤተ መቅደስ ዓምድ አደርገዋለሁ፤ ከዚያ በኋላም በምንም ዓይነት ከዚያ አይወጣም፤ የአምላኬን ስምና+ ከሰማይ ከአምላኬ ዘንድ የምትወርደውን የአምላኬን ከተማ የአዲሲቱን ኢየሩሳሌም+ ስም እንዲሁም የእኔን አዲስ ስም በእሱ ላይ እጽፋለሁ።+ 13 መንፈስ ለጉባኤዎቹ የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ።’
14 “በሎዶቅያ ላለው ጉባኤ+ መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ አሜን የሆነው፣+ ታማኝና እውነተኛ+ ምሥክር+ እንዲሁም ከአምላክ ፍጥረት የመጀመሪያ የሆነው+ እንዲህ ይላል፦ 15 ‘ሥራህን አውቃለሁ፤ ወይ ቀዝቃዛ ወይ ትኩስ አይደለህም። ቀዝቃዛ ወይም ደግሞ ትኩስ ብትሆን ደስ ባለኝ ነበር። 16 ለብ ያልክ እንጂ ትኩስም+ ሆነ ቀዝቃዛ+ ስላልሆንክ ከአፌ አውጥቼ ልተፋህ ነው። 17 ምክንያቱም “ሀብታም ነኝ፤+ ደግሞም ብዙ ሀብት አከማችቻለሁ፤ ምንም ነገር አያስፈልገኝም” ትላለህ፤ ነገር ግን ጎስቋላ፣ ምስኪን፣ ድሃ፣ ዕውርና የተራቆትክ መሆንህን አታውቅም፤ 18 ሀብታም እንድትሆን በእሳት የነጠረ ወርቅ፣ ልብስ እንድትለብስና ለኀፍረት የሚዳርገው እርቃንህ እንዲሸፈን+ ነጭ ልብስ እንዲሁም ማየት እንድትችል+ ዓይንህን የምትኳለው ኩል+ ከእኔ እንድትገዛ እመክርሃለሁ።
19 “‘እኔ፣ የምወዳቸውን ሁሉ እወቅሳለሁ እንዲሁም እገሥጻለሁ።+ ስለዚህ ቀናተኛ ሁን፤ ንስሐም ግባ።+ 20 እነሆ፣ በር ላይ ቆሜ እያንኳኳሁ ነው። ማንም ድምፄን ሰምቶ በሩን ከከፈተልኝ ወደ ቤቱ እገባለሁ፤ ከእሱም ጋር ራት እበላለሁ፤ እሱም ከእኔ ጋር ይበላል። 21 እኔ ድል ነስቼ ከአባቴ ጋር በዙፋኑ ላይ እንደተቀመጥኩ ሁሉ+ ድል የሚነሳውንም+ ከእኔ ጋር በዙፋኔ ላይ እንዲቀመጥ አደርገዋለሁ።+ 22 መንፈስ ለጉባኤዎቹ የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ።’”
4 ከዚህ በኋላ አየሁ፤ እነሆም፣ በሰማይ የተከፈተ በር ነበር፤ በመጀመሪያ ሲያናግረኝ የሰማሁት ድምፅ እንደ መለከት ድምፅ ያለ ነበር፤ እንዲህም አለኝ፦ “ና ወደዚህ ውጣ፤ መፈጸም ያለባቸውን ነገሮች አሳይሃለሁ።” 2 ከዚያም ወዲያውኑ የአምላክ መንፈስ ወረደብኝ፦ እነሆም፣ በሰማይ አንድ ዙፋን ተቀምጦ ነበር፤ በዙፋኑም ላይ የተቀመጠ ነበር።+ 3 በዙፋኑም ላይ የተቀመጠው የኢያስጲድ ድንጋይና+ የሰርድዮን ድንጋይ ዓይነት መልክ ነበረው፤ በዙፋኑም ዙሪያ መረግድ የሚመስል ቀስተ ደመና ነበር።+
4 በዙፋኑ ዙሪያ 24 ዙፋኖች ነበሩ፤ በእነዚህም ዙፋኖች ላይ ነጭ ልብስ የለበሱና በራሳቸው ላይ የወርቅ አክሊል የደፉ 24 ሽማግሌዎች+ ተቀምጠው አየሁ። 5 ከዙፋኑ መብረቅ፣+ ድምፅና ነጎድጓድ ይወጣ ነበር፤+ በዙፋኑም ፊት የሚነድዱ ሰባት የእሳት መብራቶች ነበሩ፤ እነዚህም ሰባቱን የአምላክ መናፍስት ያመለክታሉ።+ 6 በዙፋኑ ፊት የክሪስታል መልክ ያለው እንደ ብርጭቆ ያለ ባሕር+ የሚመስል ነገር ነበር።
በዙፋኑ መካከል* እና በዙፋኑ ዙሪያ ከፊትም ሆነ ከኋላ በዓይኖች የተሞሉ አራት ሕያዋን ፍጥረታት ነበሩ።+ 7 የመጀመሪያው ሕያው ፍጡር አንበሳ ይመስላል፤+ ሁለተኛው ሕያው ፍጡር ወይፈን ይመስላል፤+ ሦስተኛው ሕያው ፍጡር+ የሰው ፊት የሚመስል ፊት ነበረው፤ አራተኛው ሕያው ፍጡር+ ደግሞ የሚበር ንስር ይመስላል።+ 8 እነዚህ አራቱ ሕያዋን ፍጥረታት እያንዳንዳቸው ስድስት ስድስት ክንፎች አሏቸው፤ ክንፎቹ በዙሪያቸውና በውስጥ በኩል በዓይኖች የተሞሉ ናቸው።+ ያለማቋረጥም ቀንና ሌሊት “የነበረው፣ ያለውና የሚመጣው፣+ ሁሉን ቻይ የሆነው ይሖዋ* አምላክ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ ነው”+ ይላሉ።
9 ሕያዋን ፍጥረታቱ በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውንና ለዘላለም የሚኖረውን+ ከፍ ከፍ ባደረጉ ቁጥር እንዲሁም እሱን ባከበሩና ባመሰገኑ ቁጥር 10 ሃያ አራቱ ሽማግሌዎች+ በዙፋኑ ላይ በተቀመጠው ፊት ተደፍተው ለዘላለም ለሚኖረው አምልኮ ያቀርባሉ፤ እንዲሁም አክሊላቸውን በዙፋኑ ፊት ጥለው እንዲህ ይላሉ፦ 11 “ይሖዋ* አምላካችን፣ ሁሉንም ነገሮች ስለፈጠርክ+ እንዲሁም ወደ ሕልውና የመጡትም ሆነ የተፈጠሩት በአንተ ፈቃድ ስለሆነ ግርማ፣+ ክብርና+ ኃይል+ ልትቀበል ይገባሃል።”
5 እኔም በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው+ በሁለቱም በኩል* የተጻፈበትና በሰባት ማኅተሞች በደንብ የታሸገ ጥቅልል በቀኝ እጁ ይዞ ተመለከትኩ። 2 አንድ ብርቱ መልአክም በታላቅ ድምፅ “ማኅተሞቹን ሊያነሳና ጥቅልሉን ሊከፍት የሚገባው ማን ነው?” ብሎ ሲያውጅ አየሁ። 3 ሆኖም በሰማይም ሆነ በምድር እንዲሁም ከምድር በታች ጥቅልሉን ሊከፍትም ሆነ ውስጡን ሊመለከት የሚችል ማንም አልነበረም። 4 ጥቅልሉን ሊከፍትም ሆነ ውስጡን ሊመለከት የሚገባው ማንም ባለመገኘቱ ስቅስቅ ብዬ አለቀስኩ። 5 ሆኖም ከሽማግሌዎቹ አንዱ “አታልቅስ። እነሆ፣ ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ፣+ የዳዊት+ ሥር+ ድል ስላደረገ+ ሰባቱን ማኅተሞችና ጥቅልሉን ሊከፍት ይችላል” አለኝ።
6 በዙፋኑ መካከል፣ በአራቱ ሕያዋን ፍጥረታት መካከልና በሽማግሌዎቹ+ መካከል የታረደ+ የሚመስል በግ+ ቆሞ አየሁ፤ በጉም ሰባት ቀንዶችና ሰባት ዓይኖች አሉት፤ ዓይኖቹም ወደ መላው ምድር የተላኩትን ሰባቱን የአምላክ መናፍስት+ ያመለክታሉ። 7 እሱም ወዲያውኑ ወደ ፊት ቀርቦ በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው+ ቀኝ እጅ ጥቅልሉን ወሰደ። 8 ጥቅልሉን በወሰደ ጊዜ አራቱ ሕያዋን ፍጥረታትና 24ቱ ሽማግሌዎች+ በበጉ ፊት ተደፉ፤ እያንዳንዳቸውም በገናና ዕጣን የተሞሉ የወርቅ ሳህኖች ነበሯቸው። (ዕጣኑ የቅዱሳኑን ጸሎት ያመለክታል።)+ 9 እንዲህም እያሉ አዲስ መዝሙር ዘመሩ፦+ “ጥቅልሉን ልትወስድና ማኅተሞቹን ልትከፍት ይገባሃል፤ ታርደሃልና፤ በደምህም ከየነገዱ፣ ከየቋንቋው፣ ከየሕዝቡና ከየብሔሩ+ ሰዎችን ለአምላክ ዋጅተሃል፤+ 10 እንዲሁም ለአምላካችን መንግሥትና+ ካህናት እንዲሆኑ አድርገሃቸዋል፤+ በምድርም ላይ ነገሥታት ሆነው ይገዛሉ።”+
11 እኔም አየሁ፤ ደግሞም በዙፋኑ፣ በሕያዋን ፍጥረታቱና በሽማግሌዎቹ ዙሪያ የብዙ መላእክትን ድምፅ ሰማሁ፤ ቁጥራቸውም አእላፋት ጊዜ አእላፋትና* ሺዎች ጊዜ ሺዎች ነበር፤+ 12 እነሱም በታላቅ ድምፅ “ታርዶ የነበረው በግ+ ኃይል፣ ብልጽግና፣ ጥበብ፣ ብርታት፣ ክብር፣ ግርማና በረከት ሊቀበል ይገባዋል” አሉ።+
13 እንዲሁም በሰማይ፣ በምድር፣ ከምድር በታችና+ በባሕር ያለ ፍጡር ሁሉ፣ አዎ በውስጣቸው ያሉ ነገሮች ሁሉ “በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠውና+ ለበጉ+ በረከት፣ ክብር፣+ ግርማና ኃይል ለዘላለም ይሁን” ብለው ሲናገሩ ሰማሁ።+ 14 አራቱ ሕያዋን ፍጥረታት “አሜን!” ይሉ ነበር፤ ሽማግሌዎቹም ተደፍተው ሰገዱ።
6 እኔም በጉ+ ከሰባቱ ማኅተሞች አንዱን ሲከፍት አየሁ፤+ ከአራቱ ሕያዋን ፍጥረታትም+ አንዱ እንደ ነጎድጓድ ባለ ድምፅ “ና!” ሲል ሰማሁ። 2 እኔም አየሁ፣ እነሆ ነጭ ፈረስ ነበር፤+ በእሱም ላይ የተቀመጠው ቀስት ነበረው፤ አክሊልም ተሰጠው፤+ እሱም ድል እያደረገ ወጣ፤ ድሉንም ለማጠናቀቅ ወደ ፊት ገሰገሰ።+
3 ሁለተኛውን ማኅተም በከፈተ ጊዜ ሁለተኛው ሕያው ፍጡር+ “ና!” ሲል ሰማሁ። 4 ደማቅ ቀይ ቀለም ያለው ሌላ ፈረስ ወጣ፤ በእሱም ላይ ለተቀመጠው ሰዎች እርስ በርሳቸው ይተራረዱ ዘንድ ሰላምን ከምድር እንዲወስድ ተፈቀደለት፤ እንዲሁም ትልቅ ሰይፍ ተሰጠው።+
5 ሦስተኛውን ማኅተም በከፈተ ጊዜ+ ሦስተኛው ሕያው ፍጡር+ “ና!” ሲል ሰማሁ። እኔም አየሁ፣ እነሆ ጥቁር ፈረስ ነበር፤ በእሱም ላይ የተቀመጠው በእጁ ሚዛን ይዞ ነበር። 6 ከአራቱ ሕያዋን ፍጥረታት መካከል እንደ ድምፅ ያለ ነገር “አንድ እርቦ* ስንዴ በዲናር፣*+ ሦስት እርቦ ገብስም በዲናር፤ ደግሞም የወይራ ዘይቱንና የወይን ጠጁን አትጉዳ” ሲል ሰማሁ።+
7 አራተኛውን ማኅተም በከፈተ ጊዜ አራተኛው ሕያው ፍጡር+ “ና!” ሲል ሰማሁ። 8 እኔም አየሁ፣ እነሆ ግራጫ ፈረስ ነበር፤ በእሱም ላይ የተቀመጠው ስሙ ሞት ነበር። መቃብርም* በቅርብ ይከተለው ነበር። ሞትና መቃብርም በረጅም ሰይፍ፣ በምግብ እጥረት፣+ በገዳይ መቅሰፍትና በምድር አራዊት እንዲገድሉ በምድር አንድ አራተኛ ላይ ሥልጣን ተሰጣቸው።+
9 አምስተኛውን ማኅተም በከፈተ ጊዜ በአምላክ ቃል የተነሳና በሰጡት ምሥክርነት የተነሳ የታረዱትን ሰዎች ነፍሳት*+ ከመሠዊያው በታች+ አየሁ።+ 10 እነሱም “ቅዱስና እውነተኛ የሆንከው ሉዓላዊ ጌታ ሆይ፣+ በምድር በሚኖሩት ላይ የማትፈርደውና ደማችንን የማትበቀለው እስከ መቼ ነው?”+ ብለው በታላቅ ድምፅ ጮኹ። 11 ለእያንዳንዳቸውም ነጭ ልብስ ተሰጣቸው፤+ እንዲሁም ወደፊት እንደ እነሱ የሚገደሉት ባልንጀሮቻቸው የሆኑ ባሪያዎችና የወንድሞቻቸው ቁጥር እስኪሞላ ድረስ ለጥቂት ጊዜ እንዲጠብቁ ተነገራቸው።+
12 ስድስተኛውንም ማኅተም ሲከፍት አየሁ፤ ታላቅ የምድር ነውጥም ተከሰተ፤ ፀሐይም ከፀጉር* እንደተሠራ ማቅ ጠቆረች፤ ጨረቃም ሙሉ በሙሉ ደም መሰለች፤+ 13 ኃይለኛ ነፋስ የበለስን ዛፍ ሲያወዛውዝ ያልበሰሉት ፍሬዎች ከዛፉ ላይ እንደሚረግፉ፣ የሰማይ ከዋክብትም ወደ ምድር ወደቁ። 14 ሰማይም እየተጠቀለለ እንዳለ የመጽሐፍ ጥቅልል ከቦታው ተነሳ፤+ እንዲሁም ተራሮች ሁሉና ደሴቶች ሁሉ ከቦታቸው ተወገዱ።+ 15 ከዚያም የምድር ነገሥታት፣ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ የጦር አዛዦች፣ ሀብታሞች፣ ብርቱዎች፣ ባሪያዎች ሁሉና ነፃ ሰዎች ሁሉ በዋሻዎች ውስጥና ተራራ ላይ ባሉ ዓለቶች መካከል ተደበቁ።+ 16 ተራሮቹንና ዓለቶቹንም እንዲህ እያሉ ተማጸኑ፦ “በላያችን ውደቁና+ በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው+ ፊትና ከበጉ+ ቁጣ ሰውሩን፤ 17 ምክንያቱም ቁጣቸውን የሚገልጹበት ታላቁ ቀን መጥቷል፤+ ማንስ ሊቆም ይችላል?”+
7 ከዚህ በኋላ አራት መላእክት በአራቱ የምድር ማዕዘናት ቆመው አየሁ፤ እነሱም በምድር ወይም በባሕር ወይም በማንኛውም ዛፍ ላይ ምንም ነፋስ እንዳይነፍስ አራቱን የምድር ነፋሳት አጥብቀው ይዘው ነበር። 2 እንዲሁም የሕያው አምላክ ማኅተም ያለው ሌላ መልአክ ከፀሐይ መውጫ* ወደ ላይ ሲወጣ አየሁ፤ እሱም ምድርንና ባሕርን እንዲጎዱ ሥልጣን የተሰጣቸውን አራቱን መላእክት በታላቅ ድምፅ 3 እንዲህ አላቸው፦ “የአምላካችንን ባሪያዎች ግንባራቸው ላይ ማኅተም እስክናደርግባቸው ድረስ+ ምድርን ወይም ባሕርን ወይም ዛፎችን አትጉዱ።”+
4 የታተሙትን ሰዎች ቁጥር ሰማሁ፤ ቁጥራቸው 144,000+ ሲሆን የታተሙትም ከእያንዳንዱ የእስራኤል ልጆች ነገድ ነበር፦+
5 ከይሁዳ ነገድ 12,000 ታተሙ፤
ከሮቤል ነገድ 12,000፣
ከጋድ ነገድ 12,000፣
6 ከአሴር ነገድ 12,000፣
ከንፍታሌም ነገድ 12,000፣
ከምናሴ+ ነገድ 12,000፣
7 ከስምዖን ነገድ 12,000፣
ከሌዊ ነገድ 12,000፣
ከይሳኮር ነገድ 12,000፣
8 ከዛብሎን ነገድ 12,000፣
ከዮሴፍ ነገድ 12,000፣
ከቢንያም ነገድ 12,000 ታተሙ።
9 ከዚህ በኋላ አየሁ፤ እነሆም፣ ከሁሉም ብሔራት፣ ነገዶች፣ ሕዝቦችና ቋንቋዎች የተውጣጡ+ አንድም ሰው ሊቆጥራቸው የማይችል እጅግ ብዙ ሕዝብ ነጭ ልብስ ለብሰው+ በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆመው ነበር፤ የዘንባባ ዝንጣፊዎችንም በእጆቻቸው ይዘው ነበር።+ 10 በታላቅም ድምፅ እየጮኹ “መዳን ያገኘነው በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው+ ከአምላካችን እንዲሁም ከበጉ+ ነው” ይሉ ነበር።
11 መላእክቱ ሁሉ በዙፋኑ፣ በሽማግሌዎቹና+ በአራቱ ሕያዋን ፍጥረታት ዙሪያ ቆመው ነበር፤ እነሱም በዙፋኑ ፊት በግንባራቸው ተደፍተው ለአምላክ ሰገዱ፤ 12 እንዲህም አሉ፦ “አሜን! ውዳሴ፣ ግርማ፣ ጥበብ፣ ምስጋና፣ ክብር፣ ኃይልና ብርታት ለዘላለም ለአምላካችን ይሁን።+ አሜን።”
13 ከሽማግሌዎቹ አንዱ መልሶ “እነዚህ ነጭ ልብስ የለበሱት+ እነማን ናቸው? ከወዴትስ የመጡ ናቸው?” አለኝ። 14 እኔም ወዲያውኑ “ጌታዬ፣ የምታውቀው አንተ ነህ” አልኩት። እሱም እንዲህ አለኝ፦ “እነዚህ ታላቁን መከራ+ አልፈው የመጡ ናቸው፤ ልብሳቸውንም በበጉ ደም አጥበው ነጭ አድርገውታል።+ 15 በአምላክ ዙፋን ፊት ያሉትም ለዚህ ነው፤ በቤተ መቅደሱም ቀንና ሌሊት ቅዱስ አገልግሎት እያቀረቡለት ነው፤ በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውም+ ድንኳኑን በላያቸው ይዘረጋል።+ 16 ከእንግዲህ ወዲህ አይራቡም እንዲሁም አይጠሙም፤ ፀሐይ አይመታቸውም፤ ሐሩሩም አያቃጥላቸውም፤+ 17 ምክንያቱም በዙፋኑ መካከል ያለው በጉ+ እረኛቸው ይሆናል፤+ ወደ ሕይወት ውኃ ምንጭም ይመራቸዋል።+ አምላክም እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል።”*+
8 ሰባተኛውን ማኅተም በከፈተ ጊዜ+ በሰማይ ለግማሽ ሰዓት ያህል ጸጥታ ሰፈነ። 2 እኔም በአምላክ ፊት የሚቆሙትን ሰባቱን መላእክት አየሁ፤+ ሰባት መለከትም ተሰጣቸው።
3 የወርቅ ጥና* የያዘ ሌላ መልአክ መጥቶ በመሠዊያው+ አጠገብ ቆመ፤ እሱም የቅዱሳኑ ሁሉ ጸሎት እየተሰማ በነበረበት ወቅት በዙፋኑ ፊት ባለው በወርቁ መሠዊያ+ ላይ እንዲያቀርበው ከፍተኛ መጠን ያለው ዕጣን+ ተሰጠው። 4 በመልአኩ እጅ ያለው የዕጣኑ ጭስ እንዲሁም የቅዱሳኑ ጸሎት+ በአምላክ ፊት ወደ ላይ ወጣ። 5 ሆኖም መልአኩ ወዲያውኑ ጥናውን ይዞ ከመሠዊያው ላይ እሳት በመውሰድ ጥናውን ሞላውና እሳቱን ወደ ምድር ወረወረው። ከዚያም ነጎድጓድ፣ ድምፅ፣ የመብረቅ ብልጭታና+ የምድር ነውጥ ተከሰተ። 6 ሰባቱን መለከቶች የያዙት ሰባቱ መላእክትም+ ሊነፉ ተዘጋጁ።
7 የመጀመሪያው መለከቱን ነፋ። ከደም ጋር የተቀላቀለ በረዶና እሳት ታየ፤ ወደ ምድርም ተወረወረ፤+ የምድር አንድ ሦስተኛ ተቃጠለ፤ የዛፎችም አንድ ሦስተኛ ተቃጠለ፤ የለመለሙ ተክሎችም ሁሉ ተቃጠሉ።+
8 ሁለተኛው መልአክ መለከቱን ነፋ። በእሳት የተቀጣጠለ ትልቅ ተራራ የሚመስል ነገርም ወደ ባሕር ተወረወረ።+ የባሕሩም አንድ ሦስተኛ ደም ሆነ፤+ 9 በባሕር ውስጥ ካሉ ሕያዋን ፍጥረታትም* አንድ ሦስተኛው ሞተ፤+ ከመርከቦችም አንድ ሦስተኛው ወደመ።
10 ሦስተኛው መልአክ መለከቱን ነፋ። እንደ መብራት ቦግ ያለ አንድ ትልቅ ኮከብም ከሰማይ ወደቀ፤ በወንዞች አንድ ሦስተኛና በውኃ ምንጮች ላይ ወደቀ።+ 11 ኮከቡ ጭቁኝ ይባላል። የውኃውም አንድ ሦስተኛ እንደ ጭቁኝ መራራ ሆነ፤ ውኃውም መራራ+ ከመሆኑ የተነሳ ብዙ ሰዎች በውኃው ጠንቅ ሞቱ።
12 አራተኛው መልአክ መለከቱን ነፋ። የፀሐይ አንድ ሦስተኛ፣+ የጨረቃ አንድ ሦስተኛና የከዋክብት አንድ ሦስተኛ ተመታ፤ ይህም የሆነው የእነዚህ አካላት አንድ ሦስተኛው እንዲጨልም+ እንዲሁም የቀኑ አንድ ሦስተኛና የሌሊቱ አንድ ሦስተኛ ብርሃን እንዳያገኝ ነው።
13 እኔም አየሁ፤ አንድ ንስር በሰማይ መካከል እየበረረ በታላቅ ድምፅ እንዲህ ሲል ሰማሁ፦ “መለከቶቻቸውን ሊነፉ የተዘጋጁት ሦስቱ መላእክት+ በሚያሰሟቸው በቀሩት ኃይለኛ የመለከት ድምፆች የተነሳ በምድር ላይ ለሚኖሩት ወዮላቸው! ወዮላቸው! ወዮላቸው!”+
9 አምስተኛው መልአክ መለከቱን ነፋ።+ እኔም ከሰማይ ወደ ምድር የወደቀ አንድ ኮከብ አየሁ፤ ለእሱም የጥልቁ መግቢያ ቁልፍ+ ተሰጠው። 2 የጥልቁንም መግቢያ ከፈተው፤ በመግቢያውም በኩል ከታላቅ እቶን እንደሚወጣ ጭስ ያለ ጭስ ወጣ፤ ከዚያ በወጣው ጭስም ፀሐይ ጨለመች፤+ አየሩም ጠቆረ። 3 ከጭሱም አንበጦች ወጥተው ወደ ምድር ወረዱ፤+ እነሱም በምድር ላይ ያሉ ጊንጦች ያላቸው ዓይነት ሥልጣን ተሰጣቸው። 4 የአምላክ ማኅተም በግንባራቸው ላይ የሌላቸውን ሰዎች ብቻ እንጂ ማንኛውንም የምድር ተክል ወይም ማንኛውንም ዕፀዋት ወይም ማንኛውንም ዛፍ እንዳይጎዱ ተነገራቸው።+
5 አንበጦቹም ሰዎቹን እንዲገድሏቸው ሳይሆን ለአምስት ወር እንዲያሠቃዩአቸው ተፈቀደላቸው፤ በእነሱም ላይ የሚደርሰው ሥቃይ ጊንጥ+ ሰውን ሲነድፍ እንደሚሰማው ዓይነት ሥቃይ ነው። 6 በእነዚያ ቀኖች ሰዎች ሞትን ይሻሉ፤ ሆኖም ፈጽሞ አያገኙትም፤ ለመሞት ይመኛሉ፤ ሞት ግን ከእነሱ ይሸሻል።
7 የአንበጦቹም ገጽታ ለጦርነት የተዘጋጁ ፈረሶች ይመስል ነበር፤+ በራሳቸውም ላይ የወርቅ አክሊሎች የሚመስሉ ነገሮች ነበሩ፤ ፊታቸው ደግሞ የሰው ፊት ይመስል ነበር፤ 8 ፀጉራቸው የሴት ፀጉር ይመስል ነበር። ጥርሳቸው ግን የአንበሳ ጥርስ ይመስል ነበር፤+ 9 የብረት ጥሩር የሚመስል ጥሩርም ነበራቸው። የክንፎቻቸው ድምፅም ወደ ጦርነት የሚገሰግሱ በፈረስ የሚጎተቱ ሠረገላዎች ድምፅ ይመስል ነበር።+ 10 በተጨማሪም የጊንጥ ዓይነት ተናዳፊ ጅራት አላቸው፤ ደግሞም ሰዎቹን ለአምስት ወር የሚጎዱበት ሥልጣን በጅራታቸው ላይ ነበር።+ 11 በእነሱ ላይ የተሾመ ንጉሥ አላቸው፤ እሱም የጥልቁ መልአክ ነው።+ በዕብራይስጥ ስሙ አባዶን* ሲሆን በግሪክኛ ደግሞ ስሙ አጶልዮን* ነው።
12 አንዱ ወዮታ አልፏል። እነሆ፣ ከዚህ በኋላ ሌሎች ሁለት ወዮታዎች+ ይመጣሉ።
13 ስድስተኛው መልአክ+ መለከቱን ነፋ።+ ደግሞም በአምላክ ፊት ካለው የወርቅ መሠዊያ+ ቀንዶች የወጣ አንድ ድምፅ ሰማሁ፤ 14 ድምፁም መለከት የያዘውን ስድስተኛውን መልአክ “በታላቁ ወንዝ፣ በኤፍራጥስ የታሰሩትን አራቱን መላእክት ፍታቸው” አለው።+ 15 ለዚህ ሰዓት፣ ቀን፣ ወርና ዓመት ተዘጋጅተው የነበሩት አራቱ መላእክትም ከሰዎቹ አንድ ሦስተኛውን እንዲገድሉ ተፈቱ።
16 የፈረሰኞቹ ሠራዊት ብዛት ሁለት እልፍ ጊዜ እልፍ* ነበር፤ ቁጥራቸውንም ሰማሁ። 17 በራእዩ ላይ ያየኋቸው ፈረሶችና በላያቸው የተቀመጡት ይህን ይመስሉ ነበር፦ እንደ እሳት ቀይ፣ እንደ ያክንት ሰማያዊና እንደ ድኝ ቢጫ የሆነ ጥሩር ነበራቸው፤ የፈረሶቹም ራስ እንደ አንበሳ ራስ ነበር፤+ ከአፋቸውም እሳት፣ ጭስና ድኝ ወጣ። 18 ከአፋቸው በወጡት በእነዚህ ሦስት መቅሰፍቶች ይኸውም በእሳቱ፣ በጭሱና በድኙ ከሰዎቹ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ተገደሉ። 19 የፈረሶቹ ሥልጣን ያለው በአፋቸውና በጅራታቸው ላይ ነውና፤ ጅራታቸው እባብ የሚመስል ሲሆን ራስም አለው፤ ጉዳት የሚያደርሱትም በዚህ ነው።
20 ሆኖም በእነዚህ መቅሰፍቶች ያልተገደሉት የቀሩት ሰዎች ከእጃቸው ሥራ ንስሐ አልገቡም፤ ደግሞም አጋንንትን እንዲሁም ማየት፣ መስማትም ሆነ መሄድ የማይችሉትን ከወርቅ፣ ከብር፣ ከመዳብ፣ ከድንጋይና ከእንጨት የተሠሩትን ጣዖቶች ማምለካቸውን አልተዉም።+ 21 እንዲሁም ከፈጸሙት የነፍስ ግድያ፣ ከመናፍስታዊ ድርጊቶቻቸው፣ ከፆታ ብልግናቸውም* ሆነ ከሌብነታቸው ንስሐ አልገቡም።
10 እኔም ደመና የተጎናጸፈ* ሌላ ብርቱ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፤ በራሱም ላይ ቀስተ ደመና ነበር፤ ፊቱም እንደ ፀሐይ፣+ ቅልጥሞቹም* እንደ እሳት ዓምዶች ነበሩ፤ 2 በእጁም የተከፈተች ትንሽ ጥቅልል ይዞ ነበር። እሱም ቀኝ እግሩን በባሕር ላይ፣ ግራ እግሩን ደግሞ በምድር ላይ አሳረፈ፤ 3 እንደሚያገሣ አንበሳም በታላቅ ድምፅ ጮኸ።+ በጮኸም ጊዜ የሰባቱ ነጎድጓዶች ድምፆች+ ተናገሩ።
4 ሰባቱ ነጎድጓዶች በተናገሩም ጊዜ ለመጻፍ ተዘጋጀሁ፤ ሆኖም ከሰማይ+ “ሰባቱ ነጎድጓዶች የተናገሯቸውን ነገሮች በማኅተም አሽጋቸው* እንጂ አትጻፋቸው” የሚል ድምፅ ሰማሁ። 5 በባሕሩና በምድሩ ላይ ቆሞ ያየሁት መልአክ ቀኝ እጁን ወደ ሰማይ አነሳ፤ 6 ሰማይንና በውስጡ ያሉትን ነገሮች፣ ምድርንና በውስጧ ያሉትን ነገሮች እንዲሁም ባሕርንና በውስጡ ያሉትን ነገሮች በፈጠረውና+ ለዘላለም በሚኖረው+ በመማል እንዲህ አለ፦ “ከእንግዲህ ወዲህ መዘግየት አይኖርም። 7 ሆኖም ሰባተኛው መልአክ+ መለከቱን ሊነፋ+ በተዘጋጀባቸው ቀኖች አምላክ የገዛ ራሱ ባሪያዎች ለሆኑት ለነቢያት+ እንደ ምሥራች ያበሰረው ቅዱስ ሚስጥር+ በእርግጥ ይፈጸማል።”
8 ከሰማይ የመጣውም ድምፅ+ እንደገና ሲያናግረኝ ሰማሁ፤ እንዲህም አለኝ፦ “ሂድ፣ በባሕሩና በምድሩ ላይ በቆመው መልአክ እጅ ያለችውን የተከፈተች ጥቅልል ውሰድ።”+ 9 እኔም ወደ መልአኩ ሄጄ ትንሿን ጥቅልል እንዲሰጠኝ ጠየቅኩት። እሱም “ውሰድና ብላት፤+ ሆድህን መራራ ታደርገዋለች፤ አፍህ ላይ ግን እንደ ማር ትጣፍጣለች” አለኝ። 10 ትንሿን ጥቅልል ከመልአኩ እጅ ወስጄ በላኋት፤+ በአፌም ውስጥ እንደ ማር ጣፈጠች፤+ ከበላኋት በኋላ ግን ሆዴ መራራ ሆነ። 11 እነሱም “ሕዝቦችን፣ ብሔራትን፣ ቋንቋዎችንና ብዙ ነገሥታትን በተመለከተ እንደገና ትንቢት መናገር አለብህ” አሉኝ።
11 እኔም ዘንግ* የሚመስል ሸምበቆ+ ተሰጠኝ፤ እንዲህም አለኝ፦ “ተነስና የአምላክን ቤተ መቅደስ ቅዱስ ስፍራ፣* መሠዊያውንና በዚያ የሚያመልኩትን ለካ። 2 ሆኖም ከቤተ መቅደሱ ቅዱስ ስፍራ ውጭ ያለውን ግቢ ሙሉ በሙሉ ተወው፤ አትለካው፤ ምክንያቱም ለአሕዛብ ተሰጥቷል፤ እነሱም የተቀደሰችውን ከተማ+ ለ42 ወራት ይረግጧታል።+ 3 እኔም ሁለቱ ምሥክሮቼ ማቅ ለብሰው ለ1,260 ቀናት ትንቢት እንዲናገሩ አደርጋለሁ።” 4 እነዚህ በሁለቱ የወይራ ዛፎችና+ በሁለቱ መቅረዞች ተመስለዋል፤+ እነሱም በምድር ጌታ ፊት ቆመዋል።+
5 ማንም እነሱን ሊጎዳ ቢፈልግ እሳት ከአፋቸው ወጥቶ ጠላቶቻቸውን ይበላል። ማንም ሊጎዳቸው ቢፈልግ በዚህ ዓይነት ሁኔታ መገደል አለበት። 6 እነዚህ ሰዎች ትንቢት በሚናገሩባቸው ቀናት ምንም ዝናብ እንዳይዘንብ+ ሰማይን የመዝጋት ሥልጣን አላቸው፤+ እንዲሁም ውኃዎችን ወደ ደም የመለወጥና+ የፈለጉትን ጊዜ ያህል፣ በማንኛውም ዓይነት መቅሰፍት ምድርን የመምታት ሥልጣን አላቸው።
7 የምሥክርነት ሥራቸውን ባጠናቀቁ ጊዜ፣ ከጥልቁ የሚወጣው አውሬ ውጊያ ይከፍትባቸዋል፤ ድል ይነሳቸዋል፤ እንዲሁም ይገድላቸዋል።+ 8 አስከሬናቸውም በመንፈሳዊ ሁኔታ ሰዶምና ግብፅ ተብላ በምትጠራውና የእነሱም ጌታ በእንጨት ላይ በተሰቀለባት በታላቂቱ ከተማ አውራ ጎዳና ላይ ይጋደማል። 9 ከተለያዩ ሕዝቦች፣ ነገዶች፣ ቋንቋዎችና ብሔራት የተውጣጡ ሰዎችም ለሦስት ቀን ተኩል አስከሬናቸውን ያያሉ፤+ አስከሬናቸውም እንዲቀበር አይፈቅዱም። 10 እነዚህ ሁለት ነቢያት በምድር ላይ የሚኖሩትን አሠቃይተው ስለነበር በምድር ላይ የሚኖሩት በእነሱ ሞት ይደሰታሉ፤ ሐሴትም ያደርጋሉ እንዲሁም እርስ በርሳቸው ስጦታ ይሰጣጣሉ።
11 ከሦስት ቀን ተኩል በኋላ ከአምላክ የመጣ የሕይወት መንፈስ ገባባቸው፤+ በእግሮቻቸውም ቆሙ፤ ያዩአቸውም ሰዎች በታላቅ ፍርሃት ተዋጡ። 12 ከሰማይም አንድ ታላቅ ድምፅ “ወደዚህ ውጡ” ሲላቸው ሰሙ። እነሱም በደመና ውስጥ ሆነው ወደ ሰማይ ወጡ፤ ጠላቶቻቸውም አዩአቸው።* 13 በዚያም ሰዓት ታላቅ የምድር ነውጥ ተከሰተ፤ የከተማዋ አንድ አሥረኛም ወደቀ፤ በምድር ነውጡም 7,000 ሰዎች ሞቱ፤ የቀሩትም ፍርሃት አደረባቸው፤ ለሰማይ አምላክም ክብር ሰጡ።
14 ሁለተኛው ወዮታ+ አልፏል። እነሆ፣ ሦስተኛው ወዮታ በፍጥነት ይመጣል።
15 ሰባተኛው መልአክ መለከቱን ነፋ።+ በሰማይም ታላላቅ ድምፆች እንዲህ ሲሉ ተሰሙ፦ “የዓለም መንግሥት የጌታችንና+ የእሱ መሲሕ+ መንግሥት ሆነ፤ እሱም ለዘላለም ይነግሣል።”+
16 በአምላክ ፊት በዙፋኖቻቸው ላይ ተቀምጠው የነበሩት 24ቱ ሽማግሌዎችም+ በግንባራቸው ተደፍተው ለአምላክ ሰገዱ፤ 17 እንዲህም አሉ፦ “ያለህና+ የነበርክ፣ ሁሉን ቻይ የሆንከው ይሖዋ* አምላክ ሆይ፣ ታላቅ ኃይልህን ስለያዝክና ንጉሥ ሆነህ መግዛት ስለጀመርክ+ እናመሰግንሃለን። 18 ሆኖም ብሔራት ተቆጡ፤ የአንተም ቁጣ መጣ፤ በሙታን ላይ የምትፈርድበት፣ ለባሪያዎችህ ለነቢያት፣+ ለቅዱሳንና ስምህን ለሚፈሩ ለታናናሾችና ለታላላቆች ወሮታ የምትከፍልበት+ እንዲሁም ምድርን እያጠፉ ያሉትን+ የምታጠፋበት* የተወሰነው ጊዜ መጣ።”
19 በሰማይ ያለው የአምላክ ቤተ መቅደስ ቅዱስ ስፍራ* ተከፍቶ ነበር፤ የቃል ኪዳኑ ታቦትም በቤተ መቅደሱ ቅዱስ ስፍራ ታየ።+ እንዲሁም የመብረቅ ብልጭታ፣ ድምፅ፣ ነጎድጓድ፣ የምድር ነውጥና ታላቅ በረዶ ተከሰተ።
12 ከዚያም በሰማይ ታላቅ ምልክት ታየ፦ አንዲት ሴት+ ፀሐይን ተጎናጽፋ* ነበር፤ ጨረቃም ከእግሯ ሥር ነበረች፤ በራሷም ላይ 12 ከዋክብት ያሉት አክሊል ነበር፤ 2 እሷም ነፍሰ ጡር ነበረች። ልትወልድ ስትል ምጥ ይዟት በጭንቅ ትጮኽ ነበር።
3 ሌላ ምልክት በሰማይ ታየ። እነሆ፣ ሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶች ያሉት፣ በራሶቹም ላይ ሰባት ዘውዶች የደፋ፣ ደማቅ ቀይ ቀለም ያለው ታላቅ ዘንዶ+ ታየ፤ 4 ጅራቱም የሰማይን ከዋክብት+ አንድ ሦስተኛ ጎትቶ ወደ ምድር ወረወረ።+ ዘንዶውም በምትወልድበት ጊዜ ልጇን ለመዋጥ ፈልጎ ልትወልድ በተቃረበችው ሴት+ ፊት ቆሞ ይጠብቅ ነበር።
5 እሷም ብሔራትን ሁሉ በብረት በትር የሚገዛውን*+ ልጅ አዎ፣ ወንድ ልጅ ወለደች።+ ልጇም ወደ አምላክና ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ። 6 ሴቲቱም 1,260 ቀን በዚያ እንዲመግቧት አምላክ ወዳዘጋጀላት ስፍራ ወደ ምድረ በዳ ሸሸች።+
7 በሰማይም ጦርነት ተነሳ፦ ሚካኤልና*+ መላእክቱ ከዘንዶው ጋር ተዋጉ፤ ዘንዶውና መላእክቱም ተዋጓቸው፤ 8 ነገር ግን አልቻሏቸውም፤* ከዚያ በኋላም በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም። 9 ስለሆነም ታላቁ ዘንዶ+ ይኸውም መላውን ዓለም እያሳሳተ ያለው+ ዲያብሎስና+ ሰይጣን+ ተብሎ የሚጠራው የጥንቱ እባብ+ ወደ ታች ተወረወረ፤ ወደ ምድር ተጣለ፤+ መላእክቱም ከእሱ ጋር ተወረወሩ። 10 በሰማይ እንዲህ የሚል ታላቅ ድምፅ ሰማሁ፦
“አሁን የአምላካችን ማዳን፣+ ኃይልና መንግሥት+ እንዲሁም የእሱ መሲሕ ሥልጣን ሆኗል፤ ምክንያቱም ቀንና ሌሊት በአምላካችን ፊት የሚከሳቸው የወንድሞቻችን ከሳሽ ወደ ታች ተወርውሯል!+ 11 እነሱም ከበጉ ደም+ የተነሳና ከምሥክርነታቸው ቃል+ የተነሳ ድል ነሱት፤+ እስከ ሞት ድረስ እንኳ ለነፍሳቸው* አልሳሱም።+ 12 ስለዚህ እናንተ ሰማያትና በውስጣቸው የምትኖሩ ሁሉ ደስ ይበላችሁ! ምድርና ባሕር+ ግን ወዮላችሁ! ምክንያቱም ዲያብሎስ ጥቂት ጊዜ እንደቀረው+ ስላወቀ በታላቅ ቁጣ ተሞልቶ ወደ እናንተ ወርዷል።”
13 ዘንዶውም ወደ ምድር እንደተወረወረ+ ባየ ጊዜ ወንድ ልጅ በወለደችው ሴት ላይ ስደት አደረሰባት።+ 14 ሆኖም ሴቲቱ ከእባቡ+ ፊት ርቃ ለአንድ ዘመን፣ ለዘመናትና ለግማሽ ዘመን*+ ወደምትመገብበት በምድረ በዳ ወደተዘጋጀላት ስፍራ በርራ መሄድ እንድትችል የታላቅ ንስር ሁለት ክንፎች+ ተሰጧት።
15 እባቡም ሴቲቱ በወንዝ ውስጥ እንድትሰምጥ ከአፉ የወጣ እንደ ወንዝ ያለ ውኃ ከኋላዋ ለቀቀባት። 16 ይሁን እንጂ ምድሪቱ ለሴቲቱ ደረሰችላት፤ ምድሪቱም አፏን ከፍታ ዘንዶው ከአፉ የለቀቀውን ወንዝ ዋጠች። 17 ዘንዶውም በሴቲቱ ላይ እጅግ ተቆጥቶ የአምላክን ትእዛዛት የሚጠብቁትንና ስለ ኢየሱስ የመመሥከር ሥራ+ የተሰጣቸውን ከዘሯ+ የቀሩትን ሊዋጋ ሄደ።
13 እሱም* በባሕር አሸዋ ላይ ቆመ።
እኔም አሥር ቀንዶችና ሰባት ራሶች ያሉት አንድ አውሬ+ ከባሕር+ ሲወጣ አየሁ፤ በቀንዶቹም ላይ አሥር ዘውዶች የነበሩት ሲሆን በራሶቹ ላይ አምላክን የሚሰድቡ ስሞች ነበሩት። 2 ያየሁትም አውሬ ነብር ይመስል ነበር፤ እግሮቹ ግን የድብ እግር፣ አፉ ደግሞ የአንበሳ አፍ ይመስል ነበር። ዘንዶውም+ ለአውሬው ኃይልና ዙፋን እንዲሁም ታላቅ ሥልጣን ሰጠው።+
3 እኔም አየሁ፤ ከአውሬው ራሶች አንዱ የሞተ ያህል እስኪሆን ድረስ ቆስሎ ነበር፤ ሆኖም ለሞት የሚዳርገው ቁስሉ ዳነ፤+ ምድርም ሁሉ አውሬውን በአድናቆት ተከተለው። 4 ሰዎችም ዘንዶው ለአውሬው ሥልጣን ስለሰጠው ዘንዶውን አመለኩ፤ እንዲሁም “እንደ አውሬው ያለ ማን ነው? ከእሱስ ጋር ማን ሊዋጋ ይችላል?” በማለት አውሬውን አመለኩ። 5 እሱም የትዕቢት ቃል የሚናገርበትና አምላክን የሚሳደብበት አፍ ተሰጠው፤ ደግሞም ለ42 ወር የፈለገውን እንዲያደርግ ሥልጣን ተሰጠው።+ 6 አምላክን ለመሳደብ+ ይኸውም የአምላክን ስምና የአምላክን መኖሪያ እንዲሁም በሰማይ የሚኖሩትን ለመሳደብ አፉን ከፈተ።+ 7 ቅዱሳኑን እንዲዋጋና ድል እንዲያደርጋቸው ተፈቀደለት፤+ ደግሞም በነገድ፣ በሕዝብ፣ በቋንቋና በብሔር ሁሉ ላይ ሥልጣን ተሰጠው። 8 በምድር ላይ የሚኖሩም ሁሉ ያመልኩታል። ዓለም ከተመሠረተበት* ጊዜ ጀምሮ የአንዳቸውም ስም በታረደው በግ+ የሕይወት መጽሐፍ ጥቅልል+ ላይ አልሰፈረም።
9 ጆሮ ያለው ካለ ይስማ።+ 10 ማንም ሰው መማረክ ካለበት ይማረካል። በሰይፍ የሚገድል ካለ* በሰይፍ መገደል አለበት።+ ቅዱሳን+ ጽናትና+ እምነት ማሳየት+ የሚያስፈልጋቸው እዚህ ላይ ነው።
11 ከዚያም ሌላ አውሬ ከምድር ሲወጣ አየሁ፤ እሱም እንደ በግ ሁለት ቀንዶች ነበሩት፤ ሆኖም እንደ ዘንዶ+ መናገር ጀመረ። 12 በመጀመሪያው አውሬ ፊት የመጀመሪያውን አውሬ+ ሥልጣን ሙሉ በሙሉ ይጠቀማል። ምድርና የምድር ነዋሪዎች፣ ለሞት የሚዳርገው ቁስል የዳነለትን+ የመጀመሪያውን አውሬ እንዲያመልኩ ያደርጋል። 13 በሰው ልጆችም ፊት ታላላቅ ምልክቶችን ይፈጽማል፤ እሳትንም እንኳ ከሰማይ ወደ ምድር ያወርዳል።
14 በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች በሰይፍ ቆስሎ ለነበረው በኋላ ግን ላገገመው+ አውሬ፣ ምስል+ እንዲሠሩ እያዘዘ በአውሬው ፊት እንዲፈጽማቸው በተፈቀዱለት ምልክቶች አማካኝነት በምድር ላይ የሚኖሩትን ያስታል። 15 እንዲሁም ለአውሬው ምስል እስትንፋስ* እንዲሰጠው ተፈቀደለት፤ ይህም የሆነው የአውሬው ምስል መናገር እንዲችልና የአውሬውን ምስል የማያመልኩትን ሁሉ እንዲያስገድል ነው።
16 ሰዎች ሁሉ ማለትም ታናናሾችና ታላላቆች፣ ሀብታሞችና ድሆች እንዲሁም ነፃ ሰዎችና ባሪያዎች በቀኝ እጃቸው ወይም በግንባራቸው ላይ ምልክት እንዲደረግባቸው አስገደደ፤+ 17 ይህም የሆነው ምልክቱ ይኸውም የአውሬው ስም+ ወይም የስሙ ቁጥር+ ካለው ሰው በስተቀር ማንም መግዛት ወይም መሸጥ እንዳይችል ነው። 18 ጥበብ የሚያስፈልገው እዚህ ላይ ነው፦ የማስተዋል ችሎታ ያለው ሰው የአውሬውን ቁጥር ያስላ፤ ቁጥሩ የሰው ቁጥር ነውና፤ ቁጥሩም 666 ነው።+
14 ከዚያም አየሁ፤ እነሆ፣ በጉ+ በጽዮን ተራራ+ ላይ ቆሟል፤ ከእሱም ጋር የእሱ ስምና የአባቱ ስም+ በግንባራቸው ላይ የተጻፈባቸው 144,000+ ነበሩ። 2 ከሰማይ እንደ ብዙ ውኃዎችና እንደ ኃይለኛ የነጎድጓድ ድምፅ ያለ ድምፅ ሲወጣ ሰማሁ፤ የሰማሁትም ድምፅ በገናቸውን እየደረደሩ የሚዘምሩ ዘማሪዎች ዓይነት ድምፅ ነው። 3 እነሱም በዙፋኑ ፊት እንዲሁም በአራቱ ሕያዋን ፍጥረታትና+ በሽማግሌዎቹ+ ፊት አዲስ የሚመስል መዝሙር እየዘመሩ ነበር፤+ ከምድር ከተዋጁት ከ144,000ዎቹ+ በስተቀር ማንም ይህን መዝሙር ጠንቅቆ ሊያውቀው አልቻለም። 4 እነዚህ ራሳቸውን በሴቶች ያላረከሱ ናቸው፤ እንዲያውም ደናግል ናቸው።+ ምንጊዜም በጉ በሄደበት ሁሉ ይከተሉታል።+ እነዚህ ለአምላክና ለበጉ እንደ በኩራት+ ሆነው ከሰዎች መካከል ተዋጅተዋል፤+ 5 በአፋቸውም የማታለያ ቃል አልተገኘም፤ ምንም ዓይነት እንከን የለባቸውም።+
6 ሌላም መልአክ በሰማይ መካከል* ሲበር አየሁ፤ እሱም በምድር ላይ ለሚኖር ብሔር፣ ነገድ፣ ቋንቋና ሕዝብ ሁሉ የሚያበስረው የዘላለም ምሥራች ይዞ ነበር።+ 7 እሱም በታላቅ ድምፅ “አምላክን ፍሩ፤ ክብርም ስጡት፤ ምክንያቱም የሚፈርድበት ሰዓት ደርሷል፤+ በመሆኑም ሰማይን፣ ምድርን፣ ባሕርንና የውኃ ምንጮችን የሠራውን+ አምልኩ” አለ።
8 ሌላ ሁለተኛ መልአክ “ወደቀች! ብሔራት ሁሉ የዝሙቷን* የፍትወት* ወይን ጠጅ እንዲጠጡ ያደረገችው+ ታላቂቱ ባቢሎን+ ወደቀች!”+ እያለ ተከተለው።
9 ሌላ ሦስተኛ መልአክ በታላቅ ድምፅ እንዲህ እያለ ተከተላቸው፦ “ማንም አውሬውንና+ ምስሉን የሚያመልክና በግንባሩ ወይም በእጁ ላይ ምልክት የሚቀበል ከሆነ+ 10 እሱም፣ ሳይበረዝ ወደ ቁጣው ጽዋ የተቀዳውን የአምላክ የቁጣ ወይን ጠጅ ይጠጣል፤+ እንዲሁም በቅዱሳኑ መላእክት ፊትና በበጉ ፊት በእሳትና በድኝ ይሠቃያል።+ 11 የሥቃያቸውም ጭስ ለዘላለም ወደ ላይ ይወጣል፤+ ደግሞም አውሬውንና ምስሉን የሚያመልኩ እንዲሁም የስሙን ምልክት የሚቀበሉ ሁሉ ቀንና ሌሊት ምንም እረፍት አይኖራቸውም።+ 12 የአምላክን ትእዛዛት የሚጠብቁና የኢየሱስን እምነት አጥብቀው የሚከተሉ+ ቅዱሳን፣+ መጽናት የሚያስፈልጋቸው እዚህ ላይ ነው።”
13 ከሰማይም እንዲህ የሚል ድምፅ ሰማሁ፦ “ይህን ጻፍ፦ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ከጌታ ጋር ያላቸውን አንድነት ጠብቀው የሚሞቱ+ ደስተኞች ናቸው። መንፈስም ‘አዎ፣ ያከናወኑት ሥራ ወዲያው ስለሚከተላቸው* ከድካማቸው ይረፉ’ ይላል።”
14 ከዚያም አየሁ፤ እነሆም፣ ነጭ ደመና ነበር፤ በደመናውም ላይ የሰውን ልጅ የሚመስል ተቀምጧል፤+ እሱም በራሱ ላይ የወርቅ አክሊል ደፍቷል፤ በእጁም ስለታም ማጭድ ይዟል።
15 ሌላ መልአክ ከቤተ መቅደሱ ቅዱስ ስፍራ* ወጥቶ በደመናው ላይ ለተቀመጠው “የአጨዳው ሰዓት ስለደረሰ ማጭድህን ስደድና እጨድ፤ ምክንያቱም የምድር መከር ደርሷል” ሲል በታላቅ ድምፅ ጮኸ።+ 16 በደመናውም ላይ የተቀመጠው ማጭዱን ወደ ምድር ሰደደ፤ ምድርም ታጨደች።
17 አሁንም ሌላ መልአክ በሰማይ ካለው ቤተ መቅደስ ቅዱስ ስፍራ ወጣ፤ እሱም ስለታም ማጭድ ይዞ ነበር።
18 እንደገናም ሌላ መልአክ ከመሠዊያው ወጣ፤ እሱም በእሳቱ ላይ ሥልጣን ነበረው። በታላቅ ድምፅ ጮኾም ስለታም ማጭድ የያዘውን መልአክ “የምድሪቱ የወይን ፍሬዎች ስለበሰሉ ስለታም ማጭድህን ስደድና የምድርን የወይን ዘለላዎች ሰብስብ” አለው።+ 19 መልአኩ ማጭዱን ወደ ምድር በመስደድ የምድርን ወይን ሰበሰበ፤ ከዚያም ወደ ታላቁ የአምላክ የቁጣ ወይን መጭመቂያ ወረወረው።+ 20 ወይኑ ከከተማው ውጭ ተረገጠ፤ ከመጭመቂያውም እስከ ፈረሶች ልጓም የሚደርስ ከፍታ ያለውና 296 ኪሎ ሜትር ገደማ* ርቀት ያለው ደም ወጣ።
15 እኔም ሌላ ታላቅና አስደናቂ ምልክት በሰማይ አየሁ፤ ሰባት መቅሰፍቶች የያዙ ሰባት መላእክት+ ነበሩ። የአምላክ ቁጣ የሚደመደመው በእነዚህ ስለሆነ እነዚህ መቅሰፍቶች የመጨረሻዎቹ ናቸው።+
2 እኔም ከእሳት ጋር የተቀላቀለ የብርጭቆ ባሕር+ የሚመስል ነገር አየሁ፤ እንዲሁም አውሬውን፣ ምስሉንና+ የስሙን ቁጥር+ ድል የነሱት+ የአምላክን በገናዎች ይዘው በብርጭቆው ባሕር አጠገብ ቆመው ነበር። 3 የአምላክን ባሪያ የሙሴን መዝሙርና+ የበጉን+ መዝሙር እንዲህ እያሉ ይዘምሩ ነበር፦
“ሁሉን ቻይ የሆንከው ይሖዋ* አምላክ ሆይ፣+ ሥራዎችህ ታላቅና አስደናቂ ናቸው።+ የዘላለም ንጉሥ ሆይ፣+ መንገድህ ጽድቅና እውነት ነው።+ 4 ይሖዋ* ሆይ፣ ለመሆኑ አንተን የማይፈራና ስምህን ከፍ ከፍ የማያደርግ ማን ነው? አንተ ብቻ ታማኝ ነህና!+ የጽድቅ ድንጋጌዎችህ ስለተገለጡ ሕዝቦች ሁሉ መጥተው በፊትህ ይሰግዳሉ።”+
5 ከዚህ በኋላ አየሁ፤ የምሥክሩ ድንኳን+ ቅዱስ ስፍራ* በሰማይ ተከፍቶ ነበር፤+ 6 ሰባቱን መቅሰፍቶች የያዙት ሰባቱ መላእክትም+ ንጹሕና የሚያንጸባርቅ በፍታ ለብሰው እንዲሁም ደረታቸውን በወርቅ መታጠቂያ ታጥቀው ከቅዱሱ ስፍራ ወጡ። 7 ከአራቱ ሕያዋን ፍጥረታት አንዱ ለዘላለም በሚኖረው አምላክ ቁጣ+ የተሞሉ ሰባት የወርቅ ሳህኖችን ለሰባቱ መላእክት ሰጣቸው። 8 ቅዱሱ ስፍራም ከአምላክ ክብርና+ ከኃይሉ የተነሳ በጭስ ተሞላ፤ የሰባቱ መላእክት ሰባት መቅሰፍቶች+ እስኪፈጸሙ ድረስም ወደ ቅዱሱ ስፍራ ማንም መግባት አልቻለም።
16 እኔም ከቅዱሱ ስፍራ*+ የወጣ ታላቅ ድምፅ ሰባቱን መላእክት “ሂዱና የአምላክን ቁጣ የያዙትን ሰባቱን ሳህኖች በምድር ላይ አፍስሱ” ሲል ሰማሁ።+
2 የመጀመሪያው መልአክ ሄዶ በሳህኑ ውስጥ ያለውን በምድር ላይ አፈሰሰው።+ በዚህ ጊዜም የአውሬው ምልክት በነበራቸውና+ ምስሉን ያመልኩ በነበሩት ሰዎች+ ላይ ጉዳት የሚያስከትልና አስከፊ የሆነ ቁስል+ ወጣባቸው።
3 ሁለተኛው መልአክ በሳህኑ ውስጥ ያለውን ወደ ባሕር አፈሰሰው።+ ባሕሩም እንደሞተ ሰው ደም ሆነ፤+ በባሕሩም+ ውስጥ ያለ ሕያው ፍጡር* ሁሉ ሞተ።
4 ሦስተኛው መልአክ በሳህኑ ውስጥ ያለውን ወደ ወንዞችና ወደ ውኃ ምንጮች አፈሰሰው።+ እነሱም ደም ሆኑ።+ 5 እኔም በውኃዎች ላይ ሥልጣን ያለው መልአክ እንዲህ ሲል ሰማሁ፦ “ያለህና የነበርክ+ ታማኝ አምላካችን፣+ እነዚህን የፍርድ ውሳኔዎች ስላስተላለፍክ አንተ ጻድቅ ነህ፤+ 6 ምክንያቱም የቅዱሳንንና የነቢያትን ደም አፍስሰዋል፤+ አንተም ደም እንዲጠጡ ሰጥተሃቸዋል፤+ ደግሞም ይገባቸዋል።”+ 7 መሠዊያውም “አዎ፣ ሁሉን ቻይ የሆንከው ይሖዋ* አምላክ ሆይ፣+ ፍርድህ ሁሉ እውነትና ጽድቅ ነው”+ ሲል ሰማሁ።
8 አራተኛው መልአክ በሳህኑ ውስጥ ያለውን በፀሐይ ላይ አፈሰሰው፤+ ፀሐይም ሰዎችን በእሳት እንድትለበልብ ተፈቀደላት። 9 ሰዎቹም በኃይለኛ ሙቀት ተለበለቡ፤ ሆኖም እነሱ በእነዚህ መቅሰፍቶች ላይ ሥልጣን ያለውን አምላክ ስም ተሳደቡ እንጂ ንስሐ አልገቡም፤ ለእሱም ክብር አልሰጡም።
10 አምስተኛው መልአክ በሳህኑ ውስጥ ያለውን በአውሬው ዙፋን ላይ አፈሰሰው። መንግሥቱም በጨለማ ተዋጠ፤+ እነሱም ከሥቃያቸው የተነሳ ምላሳቸውን ያኝኩ ጀመር፤ 11 ይሁንና ከሥቃያቸውና ከቁስላቸው የተነሳ የሰማይን አምላክ ተሳደቡ፤ ከሥራቸውም ንስሐ አልገቡም።
12 ስድስተኛው መልአክ በሳህኑ ውስጥ ያለውን በታላቁ የኤፍራጥስ ወንዝ ላይ አፈሰሰው፤+ ከፀሐይ መውጫ* ለሚመጡት ነገሥታት መንገድ እንዲዘጋጅላቸውም+ የወንዙ ውኃ ደረቀ።+
13 እኔም እንቁራሪት የሚመስሉ በመንፈስ የተነገሩ ሦስት ርኩሳን ቃላት* ከዘንዶው+ አፍና ከአውሬው አፍ እንዲሁም ከሐሰተኛው ነቢይ አፍ ሲወጡ አየሁ። 14 እንዲያውም እነዚህ በአጋንንት መንፈስ የተነገሩ ቃላት ናቸው፤ ተአምራዊ ምልክቶችም ይፈጽማሉ፤+ እነሱም ሁሉን ቻይ በሆነው አምላክ ታላቅ ቀን+ ወደሚካሄደው ጦርነት ሊሰበስቧቸው+ ወደ ዓለም ነገሥታት ሁሉ ይወጣሉ።
15 “እነሆ፣ እንደ ሌባ እመጣለሁ።+ ራቁቱን እንዳይሄድና ሰዎች ኀፍረቱን እንዳያዩበት+ ነቅቶ የሚኖርና+ መደረቢያውን የሚጠብቅ ሰው ደስተኛ ነው።”
16 እነሱም ነገሥታቱን በዕብራይስጥ አርማጌዶን*+ ወደሚባል ስፍራ ሰበሰቧቸው።
17 ሰባተኛው መልአክ በሳህኑ ውስጥ ያለውን በአየር ላይ አፈሰሰው። በዚህ ጊዜ ከቅዱሱ ስፍራ፣* ከዙፋኑ “ተፈጸመ!” የሚል ታላቅ ድምፅ ወጣ።+ 18 እንዲሁም የመብረቅ ብልጭታ፣ ድምፅና ነጎድጓድ ተከሰተ፤ ሰው በምድር ላይ መኖር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ታይቶ የማያውቅ ታላቅ የምድር ነውጥም ተከሰተ፤+ የምድር ነውጡ መጠነ ሰፊና እጅግ ታላቅ ነበር። 19 ታላቂቱ ከተማ+ ለሦስት ተከፈለች፤ የብሔራት ከተሞችም ፈራረሱ፤ አምላክም የመዓቱን የቁጣ ወይን ጠጅ የያዘውን ጽዋ ይሰጣት ዘንድ+ ታላቂቱ ባቢሎንን+ አስታወሳት። 20 ደሴቶችም ሁሉ ሸሹ፤ ተራሮችም ሊገኙ አልቻሉም።+ 21 ከዚያም ታላቅ የበረዶ ድንጋይ ከሰማይ በሰዎች ላይ ወረደ፤+ እያንዳንዱ የበረዶ ድንጋይ አንድ ታላንት* ይመዝን ነበር፤ መቅሰፍቱ እጅግ ታላቅ ስለነበር ሰዎቹ ከበረዶው መቅሰፍት+ የተነሳ አምላክን ተሳደቡ።
17 ሰባቱን ሳህኖች ይዘው ከነበሩት ሰባት መላእክት+ አንዱ መጥቶ እንዲህ አለኝ፦ “ና፣ በብዙ ውኃዎች ላይ በምትቀመጠው በታላቂቱ አመንዝራ ላይ የተበየነውን ፍርድ አሳይሃለሁ፤+ 2 የምድር ነገሥታት ከእሷ ጋር አመነዘሩ፤*+ የምድር ነዋሪዎች ደግሞ በዝሙቷ* ወይን ጠጅ ሰከሩ።”+
3 እሱም በመንፈስ ኃይል ወደ ምድረ በዳ ወሰደኝ። በዚያም አንዲት ሴት አምላክን የሚሰድቡ ስሞች በሞሉበት እንዲሁም ሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶች ባሉት ደማቅ ቀይ አውሬ ላይ ተቀምጣ አየሁ። 4 ሴቲቱ ሐምራዊና+ ደማቅ ቀይ ልብስ ለብሳ እንዲሁም በወርቅ፣ በከበሩ ድንጋዮችና በዕንቁዎች አጊጣ ነበር፤+ በእጇም አስጸያፊ ነገሮችና የዝሙቷ* ርኩሰት የሞላበት የወርቅ ጽዋ ይዛ ነበር። 5 በግንባሯ ላይ “ታላቂቱ ባቢሎን፣ የአመንዝሮችና+ የምድር አስጸያፊ ነገሮች እናት”+ የሚል ሚስጥራዊ ስም ተጽፎ ነበር። 6 እኔም ሴቲቱ በቅዱሳን ደምና በኢየሱስ ምሥክሮች ደም ሰክራ አየኋት።+
ባየኋትም ጊዜ እጅግ ተደነቅኩ። 7 መልአኩም እንዲህ አለኝ፦ “የተደነቅከው ለምንድን ነው? የሴቲቱን+ እንዲሁም እሷ የተቀመጠችበትን ሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶች ያሉት አውሬ+ ሚስጥር እነግርሃለሁ፦ 8 ያየኸው አውሬ ከዚህ በፊት ነበር፤ አሁን ግን የለም፤ ይሁንና በቅርቡ ከጥልቁ+ ይወጣል፤ ወደ ጥፋትም ይሄዳል። ዓለም ከተመሠረተበት* ጊዜ አንስቶ ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ጥቅልል+ ላይ ያልተጻፈው የምድር ነዋሪዎች አውሬው ከዚህ በፊት እንደነበረ፣ አሁን ግን እንደሌለና ወደፊት እንደሚኖር ሲያዩ በአድናቆት ይዋጣሉ።
9 “ይህ ነገር ጥበብ ያለው አእምሮ* ይጠይቃል፦ ሰባቱ ራሶች+ ሴቲቱ የተቀመጠችባቸውን ሰባት ተራሮች ያመለክታሉ። 10 ደግሞም ሰባት ነገሥታት ናቸው፦ አምስቱ ወድቀዋል፤ አንዱ አለ፤ ሌላው ደግሞ ገና አልመጣም፤ በሚመጣበት ጊዜ ግን ለአጭር ጊዜ ሊቆይ ይገባዋል። 11 ከዚህ በፊት የነበረው፣ አሁን ግን የሌለው አውሬም+ ስምንተኛ ንጉሥ ነው፤ የሚወጣው ግን ከሰባቱ ነው፤ እሱም ወደ ጥፋት ይሄዳል።
12 “ያየሃቸው አሥሩ ቀንዶች ገና መንግሥትን ያልተቀበሉ አሥር ነገሥታትን ያመለክታሉ፤ ይሁንና ከአውሬው ጋር ለአንድ ሰዓት እንዲነግሡ ሥልጣን ይቀበላሉ። 13 እነዚህ አንድ ዓይነት ሐሳብ አላቸው፤ በመሆኑም ኃይላቸውንና ሥልጣናቸውን ለአውሬው ይሰጣሉ። 14 እነዚህ ከበጉ+ ጋር ይዋጋሉ፤ ሆኖም በጉ የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ+ ስለሆነ ድል ይነሳቸዋል።+ ከእሱ ጋር ያሉት የተጠሩት፣ የተመረጡትና የታመኑትም ድል ያደርጋሉ።”+
15 እሱም እንዲህ አለኝ፦ “አመንዝራዋ ተቀምጣባቸው ያየሃቸው ውኃዎች ወገኖችን፣ ብዙ ሕዝብን፣ ብሔራትንና ቋንቋዎችን ያመለክታሉ።+ 16 ያየሃቸው አሥሩ ቀንዶችና+ አውሬውም+ አመንዝራዋን+ ይጠሏታል፤ ከዚያም ይበዘብዟታል፤ ራቁቷንም ያስቀሯታል፤ እንዲሁም ሥጋዋን ይበላሉ፤ ሙሉ በሙሉም በእሳት ያቃጥሏታል።+ 17 አምላክ ቃሉ ፍጻሜውን እስኪያገኝ ድረስ ሐሳቡን ዳር እንዲያደርሱ+ አዎ፣ መንግሥታቸውን ለአውሬው+ በመስጠት አንድ የሆነውን የራሳቸውን ሐሳብ እንዲፈጽሙ ይህን በልባቸው አኑሯልና። 18 ያየሃትም ሴት+ በምድር ነገሥታት ላይ መንግሥት ያላትን ታላቂቱን ከተማ ታመለክታለች።”
18 ከዚህ በኋላ ከፍተኛ ሥልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፤ ከክብሩም የተነሳ ምድር በብርሃን ደመቀች። 2 እሱም በኃይለኛ ድምፅ እንዲህ ሲል ጮኸ፦ “ወደቀች! ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች!+ የአጋንንት መኖሪያ፣ የርኩስ መንፈስ ሁሉ* እንዲሁም የርኩሳንና የተጠሉ ወፎች ሁሉ መሰወሪያ ሆነች!+ 3 ብሔራት ሁሉ የዝሙቷ* የፍትወት* ወይን ጠጅ ሰለባ ሆነዋል፤+ የምድር ነገሥታትም ከእሷ ጋር አመንዝረዋል፤+ የምድር ነጋዴዎችም * ያላንዳች ኀፍረት ባከማቸቻቸው ውድ ነገሮች በልጽገዋል።”
4 ከሰማይም ሌላ ድምፅ እንዲህ ሲል ሰማሁ፦ “ሕዝቤ ሆይ፣ የኃጢአቷ ተባባሪ መሆን የማትፈልጉና የሚደርስባት መቅሰፍት ተካፋይ መሆን የማትፈልጉ ከሆነ ከእሷ ውጡ።+ 5 ኃጢአቷ እስከ ሰማይ ድረስ ተቆልሏልና፤+ አምላክም የፈጸመቻቸውን ኢፍትሐዊ ድርጊቶች* አስቧል።+ 6 በሌሎች ላይ በፈጸመችው በዚያው መንገድ ብድራቷን መልሱላት፤+ አዎ፣ ለሠራቻቸው ነገሮች እጥፍ ክፈሏት፤+ በቀላቀለችበት ጽዋ+ እጥፍ አድርጋችሁ ቀላቅሉባት።+ 7 ለራሷ ክብር የሰጠችውንና ያላንዳች ኀፍረት ውድ ነገሮች በማከማቸት የተቀማጠለችውን ያህል፣ በዚያው ልክ ሥቃይና ሐዘን ስጧት። ሁልጊዜ በልቧ ‘ንግሥት ሆኜ እቀመጣለሁ፤ መበለትም አይደለሁም፤ ሐዘንም ፈጽሞ አይደርስብኝም’ ትላለችና።+ 8 መቅሰፍቶቿ ይኸውም ሞትና ሐዘን እንዲሁም ረሃብ በአንድ ቀን የሚመጡባት ለዚህ ነው፤ ሙሉ በሙሉም በእሳት ትቃጠላለች፤+ ምክንያቱም የፈረደባት ይሖዋ* አምላክ ብርቱ ነው።+
9 “ከእሷ ጋር ያመነዘሩና* ያላንዳች ኀፍረት ከእሷ ጋር በቅንጦት የኖሩ የምድር ነገሥታትም እሷ ስትቃጠል የሚወጣውን ጭስ በሚያዩበት ጊዜ ስለ እሷ ያለቅሳሉ እንዲሁም በሐዘን ደረታቸውን ይደቃሉ። 10 ደግሞም ሥቃይዋን በመፍራት በሩቅ ቆመው ‘አንቺ ታላቂቱ ከተማ፣+ አንቺ ብርቱ የሆንሽው ከተማ ባቢሎን፣ እንዴት ያሳዝናል! እንዴት ያሳዝናል! ፍርድሽ በአንድ ሰዓት ተፈጽሟልና’ ይላሉ።
11 “የምድር ነጋዴዎችም ከዚህ በኋላ ብዛት ያለውን ሸቀጣቸውን የሚገዛቸው ስለማይኖር ስለ እሷ ያለቅሳሉ እንዲሁም ያዝናሉ፤ 12 ብዛት ያለው ሸቀጣቸውም ወርቅን፣ ብርን፣ የከበሩ ድንጋዮችን፣ ዕንቁን፣ ጥሩ በፍታን፣ ሐምራዊ ጨርቅን፣ ሐርንና ደማቅ ቀይ ጨርቅን ያካተተ ነው፤ በተጨማሪም ጥሩ መዓዛ ካለው እንጨት የተሠራ ነገር ሁሉ፣ ከዝሆን ጥርስ፣ ውድ ከሆነ እንጨት፣ ከመዳብ፣ ከብረትና ከእብነ በረድ የተሠራ ማንኛውም ዓይነት ዕቃ ሁሉ ይገኝበታል፤ 13 ደግሞም ቀረፋ፣ የሕንድ ቅመም፣ ዕጣን፣ ጥሩ መዓዛ ያለው ዘይት፣ ነጭ ዕጣን፣ የወይን ጠጅ፣ የወይራ ዘይት፣ የላመ ዱቄት፣ ስንዴ፣ ከብቶች፣ በጎች፣ ፈረሶች፣ ሠረገላዎች፣ ባሪያዎችና ሰዎች* ይገኙበታል። 14 አዎ፣ የተመኘሽው* ጥሩ ፍሬ ከአንቺ ርቋል፤ ምርጥና ማራኪ የሆኑ ነገሮችም ሁሉ ከአንቺ ጠፍተዋል፤ ዳግመኛም አይገኙም።
15 “እነዚህን ነገሮች በመሸጥ በእሷ የበለጸጉ ነጋዴዎች ሥቃይዋን በመፍራት በሩቅ ቆመው እያለቀሱና እያዘኑ 16 እንዲህ ይላሉ፦ ‘ጥሩ በፍታ፣ ሐምራዊና ደማቅ ቀይ ልብስ የለበሰችው እንዲሁም በወርቅ ጌጣጌጥ፣ በከበሩ ድንጋዮችና በዕንቁዎች የተንቆጠቆጠችው+ ታላቂቱ ከተማ፣ እንዴት ያሳዝናል! እንዴት ያሳዝናል! 17 ምክንያቱም ያ ሁሉ ታላቅ ሀብት በአንድ ሰዓት ውስጥ እንዳልነበረ ሆኗል።’
“የመርከብ አዛዦች ሁሉ፣ በባሕር ላይ የሚጓዙ ሁሉ፣ መርከበኞችና መተዳደሪያቸው በባሕር ላይ የተመሠረተ ሁሉ በሩቅ ቆመው 18 እሷ ስትቃጠል የሚወጣውን ጭስ እያዩ ‘እንደ ታላቂቱ ከተማ ያለ ከተማ የት ይገኛል?’ በማለት ጮኹ። 19 በራሳቸው ላይ አቧራ በትነው እያለቀሱና እያዘኑ እንዲህ ሲሉ ጮኹ፦ ‘በባሕር ላይ መርከቦች ያሏቸውን ሁሉ በሀብቷ ያበለጸገችው ታላቂቱ ከተማ በአንድ ሰዓት ውስጥ መጥፋቷ እንዴት ያሳዝናል! እንዴት ያሳዝናል!’+
20 “ሰማይ ሆይ፣ በእሷ ላይ በደረሰው ነገር ደስ ይበልህ፤+ ደግሞም እናንተ ቅዱሳን፣+ ሐዋርያትና ነቢያት ደስ ይበላችሁ፤ ምክንያቱም አምላክ ለእናንተ ሲል ፈርዶባታል!”+
21 አንድ ብርቱ መልአክም ትልቅ የወፍጮ ድንጋይ የሚመስል ድንጋይ አንስቶ ወደ ባሕር በመወርወር እንዲህ አለ፦ “ታላቂቱ ከተማ ባቢሎን እንዲህ በፍጥነት ቁልቁል ትወረወራለች፤ ዳግመኛም አትገኝም።+ 22 በተጨማሪም ራሳቸውን በበገና የሚያጅቡ ዘማሪዎች፣ የሙዚቀኞች፣ የዋሽንት ነፊዎችና የመለከት ነፊዎች ድምፅ ዳግመኛ በአንቺ ውስጥ ፈጽሞ አይሰማም። ደግሞም የማንኛውም ዓይነት የእጅ ጥበብ ባለሙያ ዳግመኛ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይገኝም፤ እንዲሁም የወፍጮ ድምፅ ዳግመኛ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይሰማም። 23 የመብራት ብርሃን ዳግመኛ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይበራም፤ የሙሽራና የሙሽሪት ድምፅም ዳግመኛ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይሰማም፤ ይህም የሚሆነው ነጋዴዎችሽ የምድር ታላላቅ ሰዎች ስለነበሩና በመናፍስታዊ ድርጊቶችሽ+ ብሔራት ሁሉ ስለተሳሳቱ ነው። 24 በእሷም ውስጥ የነቢያት፣ የቅዱሳንና+ በምድር ላይ የታረዱ ሰዎች ሁሉ ደም ተገኝቷል።”+
19 ከዚህ በኋላ በሰማይ እንደ ብዙ ሠራዊት ድምፅ ያለ ታላቅ ድምፅ ሰማሁ። እንዲህም አሉ፦ “ያህን አወድሱ!*+ ማዳን፣ ክብርና ኃይል የአምላካችን ነው፤ 2 ምክንያቱም ፍርዶቹ እውነትና ጽድቅ ናቸው።+ ምድርን በዝሙቷ* ባረከሰችው በታላቂቱ አመንዝራ ላይ የፍርድ እርምጃ ወስዷልና፤ እንዲሁም ስለ ባሪያዎቹ ደም ተበቅሏታል።”*+ 3 ወዲያውኑም ለሁለተኛ ጊዜ “ያህን አወድሱ!*+ ከእሷ የሚወጣው ጭስም ለዘላለም ወደ ላይ ይወጣል” አሉ።+
4 ደግሞም 24ቱ ሽማግሌዎችና+ አራቱ ሕያዋን ፍጥረታት+ ተደፍተው በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው አምላክ ሰገዱ፤ እንዲሁም “አሜን! ያህን አወድሱ!”* አሉ።+
5 በተጨማሪም ከዙፋኑ የወጣ አንድ ድምፅ “እሱን የምትፈሩ ባሪያዎቹ ሁሉ፣+ ታናናሾችና ታላላቆች፣+ አምላካችንን አወድሱ” አለ።
6 እንደ ብዙ ሠራዊት ድምፅ፣ እንደ ብዙ ውኃዎች ድምፅና እንደ ኃይለኛ ነጎድጓድ ድምፅ ያለ ነገር ሰማሁ። እንዲህም አሉ፦ “ያህን አወድሱ፤*+ ምክንያቱም ሁሉን ቻይ የሆነው አምላካችን ይሖዋ*+ ነግሦአል!+ 7 የበጉ ሠርግ ስለደረሰና ሙሽራዋ ራሷን ስላዘጋጀች እንደሰት፤ ሐሴትም እናድርግ፤ ለእሱም ክብር እንስጠው። 8 አዎ፣ የሚያንጸባርቅና ንጹሕ የሆነ ጥሩ በፍታ እንድትለብስ ተሰጥቷታል፤ ይህ ጥሩ በፍታ የቅዱሳንን የጽድቅ ተግባር ያመለክታልና።”+
9 እሱም “ይህን ጻፍ፦ ወደ በጉ ሠርግ+ የራት ግብዣ የተጠሩ ደስተኞች ናቸው” አለኝ። ደግሞም “እነዚህ እውነተኛ የአምላክ ቃሎች ናቸው” አለኝ። 10 እኔም በዚህ ጊዜ ልሰግድለት በእግሩ ፊት ተደፋሁ። እሱ ግን “ተጠንቀቅ! ፈጽሞ እንዳታደርገው!+ እኔ ከአንተም ሆነ ስለ ኢየሱስ የመመሥከር ሥራ ካላቸው ወንድሞችህ ጋር አብሬ የማገለግል ባሪያ ነኝ።+ ለአምላክ ስገድ!+ ትንቢት የሚነገረው ስለ ኢየሱስ ለመመሥከር ነውና” አለኝ።+
11 እኔም ሰማይ ተከፍቶ አየሁ፤ እነሆም፣ ነጭ ፈረስ ነበር።+ በእሱም ላይ የተቀመጠው “ታማኝና+ እውነተኛ”+ ተብሎ ይጠራል፤ እሱም በጽድቅ ይፈርዳል እንዲሁም ይዋጋል።+ 12 ዓይኖቹ የእሳት ነበልባል ናቸው፤+ በራሱም ላይ ብዙ ዘውዶች አሉ። ከራሱ በቀር ማንም የማያውቀው ስም ተጽፎበታል፤ 13 ደም የነካው* መደረቢያም ለብሷል፤ ደግሞም “የአምላክ ቃል”+ በሚል ስም ይጠራል። 14 በተጨማሪም በሰማይ ያሉት ሠራዊቶች በነጭ ፈረሶች ተቀምጠው ይከተሉት ነበር፤ እነሱም ነጭና ንጹሕ የሆነ ጥሩ በፍታ ለብሰው ነበር። 15 እሱም ብሔራትን ይመታበት ዘንድ ከአፉ ረጅም ስለታም ሰይፍ+ ይወጣል፤ እንደ እረኛም በብረት በትር ይገዛቸዋል።*+ በተጨማሪም ሁሉን ቻይ የሆነውን የአምላክን የመዓቱን የቁጣ ወይን ጠጅ መጭመቂያ ይረግጣል።+ 16 በመደረቢያው አዎ፣ በጭኑ ላይ “የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ”+ የሚል ስም ተጽፏል።
17 በተጨማሪም አንድ መልአክ በፀሐይ መካከል ቆሞ አየሁ፤ እሱም በታላቅ ድምፅ ጮኾ በሰማይ መካከል* ለሚበርሩት ወፎች ሁሉ እንዲህ አለ፦ “ወደዚህ ኑ፤ ወደ ታላቁ የአምላክ ራት ተሰብሰቡ፤+ 18 የነገሥታትን ሥጋ፣ የጦር አዛዦችን ሥጋ፣ የብርቱ ሰዎችን ሥጋ፣+ የፈረሶችንና የፈረሰኞችን ሥጋ+ እንዲሁም የሁሉንም ሥጋ ይኸውም የነፃ ሰዎችንና የባሪያዎችን፣ የታናናሾችንና የታላላቆችን ሥጋ ብሉ።”
19 ከዚህ በኋላ አውሬው፣ የምድር ነገሥታትና ሠራዊታቸው በፈረሱ ላይ ከተቀመጠውና ከሠራዊቱ ጋር ለመዋጋት ተሰብስበው አየሁ።+ 20 አውሬውም ተያዘ፤ በፊቱ ተአምራዊ ምልክቶች የፈጸመው ሐሰተኛው ነቢይም+ ከእሱ ጋር ተያዘ፤ ይህ ነቢይ በእነዚህ ምልክቶች አማካኝነት፣ የአውሬውን ምስል የተቀበሉትንና+ ለምስሉ የሰገዱትን+ አስቷል። ሁለቱም በሕይወት እንዳሉ በድኝ ወደሚነደው የእሳት ሐይቅ ተወረወሩ።+ 21 የቀሩት ግን በፈረሱ ላይ ከተቀመጠው አፍ በወጣው ረጅም ሰይፍ ተገደሉ።+ ወፎችም ሁሉ ሥጋቸውን በልተው ጠገቡ።+
20 እኔም የጥልቁን ቁልፍና+ ታላቅ ሰንሰለት በእጁ የያዘ አንድ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ። 2 እሱም ዘንዶውን+ ያዘውና ለ1,000 ዓመት አሰረው፤ ይህም ዘንዶ ዲያብሎስና+ ሰይጣን+ የሆነው የጥንቱ እባብ+ ነው። 3 ደግሞም ይህ 1,000 ዓመት እስኪያበቃ ድረስ ከእንግዲህ ሕዝቦችን እንዳያሳስት ወደ ጥልቁ+ ወረወረውና ዘጋበት፤ በማኅተምም አሸገው። ከዚያ በኋላ ለጥቂት ጊዜ ሊፈታ ይገባዋል።+
4 ዙፋኖችንም አየሁ፤ በዙፋኖቹም ላይ ለተቀመጡት የመፍረድ ሥልጣን ተሰጣቸው። ስለ ኢየሱስ በመመሥከራቸውና ስለ አምላክ በመናገራቸው የተነሳ የተገደሉትን* ሰዎች ነፍሳት* እንዲሁም አውሬውን ወይም ምስሉን ያላመለኩትንና ምልክቱን በግንባራቸውም ሆነ በእጃቸው ላይ ያልተቀበሉትን ሰዎች አየሁ።+ እነሱም ሕያው ሆነው ከክርስቶስ ጋር ለ1,000 ዓመት ነገሡ።+ 5 (የቀሩት ሙታን+ ይህ 1,000 ዓመት እስኪያበቃ ድረስ ሕያው አልሆኑም።) ይህ የመጀመሪያው ትንሣኤ ነው።+ 6 በመጀመሪያው ትንሣኤ ተካፋይ የሆኑ ሁሉ ደስተኞችና ቅዱሳን ናቸው፤+ ሁለተኛው ሞት+ በእነዚህ ላይ ሥልጣን የለውም፤+ ከዚህ ይልቅ የአምላክና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ፤+ ከእሱም ጋር ለ1,000 ዓመት ይነግሣሉ።+
7 ይህ 1,000 ዓመት እንዳበቃም ሰይጣን ከእስራቱ ይፈታል፤ 8 እሱም በአራቱም የምድር ማዕዘናት ያሉትን ብሔራት፣ ጎግንና ማጎግን ለማሳሳትና ለጦርነቱ አንድ ላይ ለመሰብሰብ ይወጣል። የእነዚህም ቁጥር በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ ነው። 9 እነሱም በምድር ሁሉ ተሰራጩ፤ እንዲሁም የቅዱሳኑን ሰፈርና የተወደደችውን ከተማ ከበቡ። ሆኖም እሳት ከሰማይ ወርዶ በላቸው።+ 10 ሲያሳስታቸው የነበረው ዲያብሎስም፣ አውሬውና+ ሐሰተኛው ነቢይ ወዳሉበት ወደ እሳቱና ወደ ድኙ ሐይቅ ተወረወረ፤+ እነሱም ለዘላለም ቀንና ሌሊት ይሠቃያሉ።*
11 እኔም አንድ ትልቅ ነጭ ዙፋንና በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውን አየሁ።+ ምድርና ሰማይ ከፊቱ ሸሹ፤+ ስፍራም አልተገኘላቸውም። 12 ከዚያም ሙታንን፣ ታላላቆችንና ታናናሾችን በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ፤ የመጽሐፍ ጥቅልሎችም ተከፈቱ። ሌላም ጥቅልል ተከፈተ፤ ይህም የሕይወት መጽሐፍ ጥቅልል ነው።+ ሙታን በጥቅልሎቹ ውስጥ በተጻፉት ነገሮች መሠረት እንደየሥራቸው ፍርድ ተሰጣቸው።+ 13 ባሕርም በውስጡ ያሉትን ሙታን ሰጠ፤ ሞትና መቃብርም* በውስጣቸው ያሉትን ሙታን ሰጡ፤ እነሱም እያንዳንዳቸው እንደየሥራቸው ፍርድ ተሰጣቸው።+ 14 ሞትና መቃብርም* ወደ እሳቱ ሐይቅ ተወረወሩ።+ ይህም የእሳት ሐይቅ+ ሁለተኛውን ሞት ያመለክታል።+ 15 በተጨማሪም በሕይወት መጽሐፍ+ ላይ ተጽፎ ያልተገኘ ሁሉ ወደ እሳቱ ሐይቅ ተወረወረ።+
21 እኔም አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር አየሁ፤+ የቀድሞው ሰማይና የቀድሞው ምድር አልፈዋልና፤+ ባሕሩም+ ከእንግዲህ ወዲህ የለም። 2 ደግሞም ቅድስቲቱ ከተማ፣ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ከሰማይ ከአምላክ ዘንድ ስትወርድ አየሁ፤+ እሷም ለባሏ እንዳጌጠች ሙሽራ ተዘጋጅታ ነበር።+ 3 በዚህ ጊዜ ከዙፋኑ አንድ ታላቅ ድምፅ እንዲህ ሲል ሰማሁ፦ “እነሆ፣ የአምላክ ድንኳን ከሰዎች ጋር ነው፤ እሱም ከእነሱ ጋር ይኖራል፤ እነሱም ሕዝቡ ይሆናሉ። አምላክ ራሱም ከእነሱ ጋር ይሆናል።+ 4 እሱም እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፤*+ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤+ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም።+ ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።”
5 በዙፋኑም ላይ የተቀመጠው+ “እነሆ፣ ሁሉንም ነገር አዲስ አደርጋለሁ” አለ።+ ደግሞም “እነዚህ ቃላት አስተማማኝና* እውነት ስለሆኑ ጻፍ” አለኝ። 6 እንዲህም አለኝ፦ “እነዚህ ነገሮች ተፈጽመዋል! እኔ አልፋና ኦሜጋ፣* የመጀመሪያውና የመጨረሻው ነኝ።+ ለተጠማ ሁሉ ከሕይወት ውኃ ምንጭ በነፃ* እሰጣለሁ።+ 7 ድል የሚነሳ ሁሉ እነዚህን ነገሮች ይወርሳል፤ እኔ አምላክ እሆነዋለሁ፤ እሱም ልጄ ይሆናል። 8 ይሁን እንጂ የፈሪዎች፣ የእምነት የለሾች፣+ ርኩስና አስጸያፊ የሆኑ ሰዎች፣ የነፍሰ ገዳዮች፣+ የሴሰኞች፣*+ መናፍስታዊ ድርጊት የሚፈጽሙ፣ የጣዖት አምላኪዎችና የውሸታሞች+ ሁሉ ዕጣ ፋንታቸው በእሳትና በድኝ በሚቃጠል ሐይቅ ውስጥ መጣል ነው።+ ይህ ሁለተኛውን ሞት ያመለክታል።”+
9 በሰባቱ የመጨረሻ መቅሰፍቶች የተሞሉትን ሰባቱን ሳህኖች ይዘው ከነበሩት ሰባት መላእክት+ አንዱ መጥቶ “ና፣ የበጉን ሚስት፣ ሙሽራይቱን+ አሳይሃለሁ” አለኝ። 10 ከዚያም በመንፈስ ኃይል ወደ አንድ ትልቅና ረጅም ተራራ ወሰደኝና ቅድስቲቱ ከተማ ኢየሩሳሌም ከሰማይ ከአምላክ ዘንድ ስትወርድ አሳየኝ፤+ 11 እሷም የአምላክን ክብር ተላብሳ ነበር።+ የብርሃኗም ድምቀት እጅግ እንደከበረ ድንጋይ ይኸውም እንደ ኢያስጲድ ነበር፤ ደግሞም እንደ ክሪስታል ጥርት ብሎ ያንጸባርቅ ነበር።+ 12 ትልቅና ረጅም የግንብ አጥር እንዲሁም 12 በሮች ነበሯት፤ በበሮቹም ላይ 12 መላእክት ነበሩ፤ የ12ቱም የእስራኤል ልጆች ነገዶች ስም በበሮቹ ላይ ተቀርጾ ነበር። 13 በምሥራቅ ሦስት በሮች፣ በሰሜን ሦስት በሮች፣ በደቡብ ሦስት በሮችና በምዕራብ ሦስት በሮች ነበሩ።+ 14 በተጨማሪም የከተማዋ የግንብ አጥር 12 የመሠረት ድንጋዮች ነበሩት፤ በእነሱም ላይ የ12ቱ የበጉ ሐዋርያት 12 ስሞች+ ተጽፈው ነበር።
15 እያነጋገረኝ የነበረው መልአክም ከተማዋን፣ በሮቿንና የግንብ አጥሯን ለመለካት የሚያገለግል የወርቅ ዘንግ ይዞ ነበር።+ 16 ከተማዋ አራት ማዕዘን ቅርጽ ያላት ሲሆን ርዝመቷ ከወርዷ ጋር እኩል ነው። እሱም ከተማዋን በዘንጉ ሲለካት 12,000 ስታዲዮን* ሆና ተገኘች፤ ርዝመቷ፣ ወርዷና ከፍታዋ እኩል ነው። 17 በተጨማሪም የግንብ አጥሯን ለካ፤ አጥሩም በሰው መለኪያ፣ በመልአክም መለኪያ 144 ክንድ* ሆኖ ተገኘ። 18 የከተማዋ የግንብ አጥር የተገነባው ከኢያስጲድ ነበር፤+ ከተማዋም የጠራ መስተዋት የሚመስል ንጹሕ ወርቅ ነበረች። 19 የከተማዋ የግንብ አጥር መሠረቶች በተለያዩ የከበሩ ድንጋዮች* ያጌጡ ነበሩ፦ የመጀመሪያው መሠረት ኢያስጲድ፣ ሁለተኛው ሰንፔር፣ ሦስተኛው ኬልቄዶን፣ አራተኛው መረግድ፣ 20 አምስተኛው ሰርዶንክስ፣ ስድስተኛው ሰርድዮን፣ ሰባተኛው ክርስቲሎቤ፣ ስምንተኛው ቢረሌ፣ ዘጠነኛው ቶጳዝዮን፣ አሥረኛው ክርስጵራስስ፣ አሥራ አንደኛው ያክንትና አሥራ ሁለተኛው አሜቴስጢኖስ ነበር። 21 በተጨማሪም 12ቱ በሮች 12 ዕንቁዎች ነበሩ፤ እያንዳንዱ በር ከአንድ ዕንቁ የተሠራ ነበር። የከተማዋ አውራ ጎዳናም ብርሃን እንደሚያስተላልፍ መስተዋት ንጹሕ ወርቅ ነበር።
22 በከተማዋ ውስጥ ቤተ መቅደስ አላየሁም፤ ሁሉን ቻይ የሆነው ይሖዋ* አምላክና+ በጉ ቤተ መቅደሷ ናቸውና። 23 ከተማዋ የፀሐይም ሆነ የጨረቃ ብርሃን አላስፈለጋትም፤ የአምላክ ክብር ብርሃን ሰጥቷታልና፤+ በጉም መብራቷ ነበር።+ 24 ብሔራትም በእሷ ብርሃን ይጓዛሉ፤+ የምድር ነገሥታትም ክብራቸውን ወደ እሷ ያመጣሉ። 25 በሮቿ በቀን አይዘጉም፤ በዚያም ሌሊት ፈጽሞ አይኖርም።+ 26 የብሔራትን ግርማና ክብርም ወደ እሷ ያመጣሉ።+ 27 ሆኖም የረከሰ ማንኛውም ነገር እንዲሁም አስጸያፊ ነገር የሚያደርግና የሚያታልል ማንኛውም ሰው በምንም ዓይነት ወደ እሷ አይገባም፤+ ወደ እሷ የሚገቡት በበጉ የሕይወት መጽሐፍ ጥቅልል ላይ የተጻፉ ብቻ ናቸው።+
22 መልአኩም ከአምላክና ከበጉ+ ዙፋን ወጥቶ የሚፈሰውን እንደ ክሪስታል የጠራ የሕይወት ውኃ ወንዝ አሳየኝ፤+ 2 ወንዙም በከተማዋ አውራ ጎዳና መካከል ቁልቁል ይፈስ ነበር። በወንዙ ግራና ቀኝ በየወሩ እያፈሩ በዓመት 12 ጊዜ ፍሬ የሚሰጡ የሕይወት ዛፎች ነበሩ። የዛፎቹም ቅጠሎች ሕዝቦችን ለመፈወስ የሚያገለግሉ ነበሩ።+
3 በዚያም ከእንግዲህ እርግማን አይኖርም። ከዚህ ይልቅ የአምላክና የበጉ ዙፋን+ በከተማዋ ውስጥ ይሆናል፤ ባሪያዎቹም ቅዱስ አገልግሎት ያቀርቡለታል፤ 4 ፊቱንም ያያሉ፤+ ስሙም በግንባራቸው ላይ ይሆናል።+ 5 በተጨማሪም ከእንግዲህ ወዲህ ሌሊት አይኖርም፤+ ይሖዋ* አምላክ በእነሱ ላይ ብርሃን ስለሚፈነጥቅ የመብራት ብርሃንም ሆነ የፀሐይ ብርሃን አያስፈልጋቸውም፤+ ደግሞም ለዘላለም ይነግሣሉ።+
6 መልአኩም እንዲህ አለኝ፦ “እነዚህ ቃላት አስተማማኝና* እውነት ናቸው፤+ አዎ፣ ነቢያት በመንፈስ መሪነት እንዲናገሩ የሚያደርገው ይሖዋ* አምላክ፣+ በቅርብ ጊዜ ውስጥ መፈጸም ያለባቸውን ነገሮች ለባሪያዎቹ ለማሳየት መልአኩን ልኳል። 7 እነሆ፣ እኔ ቶሎ እመጣለሁ።+ በዚህ ጥቅልል ውስጥ የሚገኙትን የትንቢት ቃላት የሚጠብቅ ማንኛውም ሰው ደስተኛ ነው።”+
8 እነዚህን ነገሮች ስሰማና ስመለከት የነበርኩት እኔ ዮሐንስ ነኝ። እነዚህን ነገሮች በሰማሁና ባየሁ ጊዜ እያሳየኝ ለነበረው መልአክ ልሰግድ እግሩ ሥር ተደፋሁ። 9 እሱ ግን “ተጠንቀቅ! ፈጽሞ እንዳታደርገው! እኔ ከአንተም ሆነ ነቢያት ከሆኑት ወንድሞችህና በዚህ ጥቅልል ውስጥ የሰፈሩትን ቃላት ከሚጠብቁት ሁሉ ጋር አብሬ የማገለግል ባሪያ ነኝ። ለአምላክ ስገድ” አለኝ።+
10 ደግሞም እንዲህ አለኝ፦ “የተወሰነው ጊዜ ስለቀረበ በዚህ ጥቅልል ውስጥ የሰፈሩትን የትንቢት ቃላት በማኅተም አታሽጋቸው። 11 ጻድቅ ያልሆነ፣ በዓመፅ ጎዳናው ይቀጥል፤ ርኩስ የሆነውም በርኩሰቱ ይቀጥል፤ ጻድቅ የሆነው ግን በጽድቅ ጎዳና መመላለሱን ይቀጥል፤ ቅዱስ የሆነውም በቅድስና ይቀጥል።
12 “‘እነሆ፣ እኔ ቶሎ እመጣለሁ፤ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው የምከፍለው ብድራት ከእኔ ጋር ነው።+ 13 እኔ አልፋና ኦሜጋ፣*+ ፊተኛውና ኋለኛው፣ የመጀመሪያውና የመጨረሻው ነኝ። 14 ከሕይወት ዛፎች ፍሬ የመብላት መብት እንዲያገኙና+ በበሮቿ+ በኩል ወደ ከተማዋ መግባት እንዲፈቀድላቸው ልብሳቸውን የሚያጥቡ+ ደስተኞች ናቸው። 15 ውሾች፣* መናፍስታዊ ድርጊት የሚፈጽሙ፣ ሴሰኞች፣* ነፍሰ ገዳዮች፣ ጣዖት አምላኪዎች እንዲሁም ውሸትን የሚወዱና የሚዋሹ ሁሉ ከከተማዋ ውጭ አሉ።’+
16 “‘እኔ ኢየሱስ ለጉባኤዎቹ ጥቅም ስል ስለ እነዚህ ነገሮች ለእናንተ ለመመሥከር መልአኬን ልኬአለሁ። እኔ የዳዊት ሥርና ዘር+ እንዲሁም ደማቅ አጥቢያ ኮከብ+ ነኝ።’”
17 መንፈሱና ሙሽራይቱም+ “ና!” ይላሉ፤ የሚሰማም ሁሉ “ና!” ይበል፤ የተጠማም ሁሉ ይምጣ፤+ የሚፈልግ ሁሉ የሕይወትን ውኃ በነፃ ይውሰድ።+
18 “በዚህ ጥቅልል ላይ የሰፈሩትን የትንቢት ቃላት ለሚሰማ ሁሉ እመሠክራለሁ፦ ማንም በእነዚህ ነገሮች ላይ አንዲት ነገር ቢጨምር+ አምላክ በዚህ ጥቅልል ውስጥ የተጻፉትን መቅሰፍቶች ይጨምርበታል፤+ 19 ማንም በዚህ የትንቢት መጽሐፍ ጥቅልል ላይ ከሰፈሩት ቃላት አንዲት ነገር ቢያጎድል አምላክ በዚህ ጥቅልል ላይ ከተጠቀሱት የሕይወት ዛፎችና+ ከቅድስቲቱ ከተማ+ ዕጣ ፋንታውን ይወስድበታል።
20 “ስለ እነዚህ ነገሮች የሚመሠክረው ‘አዎ፣ ቶሎ እመጣለሁ’+ ይላል።”
“አሜን! ጌታ ኢየሱስ፣ ና።”
21 የጌታ የኢየሱስ ጸጋ ከቅዱሳኑ ጋር ይሁን።
“ይፋ ማውጣት፤ መግለጥ” የሚል ትርጉም አለው።
ቃል በቃል “መንግሥት።”
የመጀመሪያውና የመጨረሻው ማለት ነው። አልፋ እና ኦሜጋ የመጀመሪያውና የመጨረሻው የግሪክኛ ፊደላት ናቸው።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “የሐዲስ።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “መልእክተኞች።”
ወይም “የኒቆላዎስ ኑፋቄ የሚሠራውን ሥራ።”
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ግሪክኛ፣ ፖርኒያ። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ጥልቅ ስሜትንና።” ቃል በቃል “ኩላሊትንና።”
ቃል በቃል “እንደ እረኛ በብረት በትር ያግዳቸዋል።”
ቃል በቃል “ጥቂት ስሞች።”
ወይም “አልሰርዝም።”
ወይም “እጅ እንዲነሱ።”
“የተውኩትን የጽናት ምሳሌ ስለተከተልክ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “በመካከል ከዙፋኑ ጋር።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ቃል በቃል “በውስጥም በውጭም በኩል።”
ወይም “አሥር ሺዎች ጊዜ አሥር ሺዎችና።”
አንድ እርቦ ስንዴ 0.7 ኪሎ ግራም ገደማ ይመዝናል። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
የሮም የብር ሳንቲም ሲሆን አንድ ሠራተኛ ከሚከፈለው የቀን ደሞዝ ጋር እኩል ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ሐዲስም።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
መሠዊያው ላይ የፈሰሰውን ለሕይወታቸው ወሳኝ የሆነውን ደማቸውን እንደሚያመለክት ግልጽ ነው። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
የፍየል ፀጉር ሳይሆን አይቀርም።
ወይም “ከምሥራቅ።”
ወይም “ይጠርጋል።”
ወይም “ዕጣን ማጨሻ።”
ወይም “ነፍስ ያላቸው ፍጥረታትም።”
“ጥፋት” የሚል ትርጉም አለው።
“አጥፊ” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “20,000 ጊዜ 10,000” ማለትም 200,000,000።
ግሪክኛ፣ ፖርኒያ። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “በደመና የተሸፈነ።”
ቃል በቃል “እግሮቹም።”
ወይም “በሚስጥር ያዛቸው።”
ወይም “መለኪያ ዘንግ።”
ቅድስቱንና ቅድስተ ቅዱሳኑን የያዘውን የቤተ መቅደሱን ማዕከላዊ ክፍል ያመለክታል።
ወይም “ይመለከቷቸው ነበር።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “ምድርን እያበላሹ ባሉት ላይ እርምጃ የምትወስድበት።”
የቤተ መቅደሱን ቅድስተ ቅዱሳን ያመለክታል።
ወይም “ለብሳ።”
ቃል በቃል “እንደ እረኛ በብረት በትር የሚያግደውን።”
“እንደ አምላክ ያለ ማን ነው?” የሚል ትርጉም አለው።
“ሆኖም እሱ [ማለትም ዘንዶው] ድል ተመታ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ለሕይወታቸው።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ሦስት ተኩል ዘመናትን ያመለክታል።
ዘንዶውን ያመለክታል።
ይህ አባባል የአዳምንና የሔዋንን ዘሮች ያመለክታል።
“በሰይፍ የሚገደል ካለ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “መንፈስ።”
ወይም “በአየር ላይ፤ ከላይ።”
ግሪክኛ፣ ፖርኒያ። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “የቁጣ።”
ወይም “አብሯቸው ስለሚሄድ።”
የቤተ መቅደሱን ቅድስተ ቅዱሳን ያመለክታል።
ቃል በቃል “1,600 ስታዲዮን።” አንድ ስታዲዮን 185 ሜትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
የቤተ መቅደሱን ቅድስተ ቅዱሳን ያመለክታል።
የቤተ መቅደሱን ቅድስተ ቅዱሳን ያመለክታል።
ወይም “ነፍስ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “ከምሥራቅ።”
ቃል በቃል “ርኩሳን መናፍስት።”
ግሪክኛ፣ ሐርማጌዶን። “የመጊዶ ተራራ” የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ ቃል የተገኘ ነው።
የቤተ መቅደሱን ቅድስተ ቅዱሳን ያመለክታል።
የግሪኩ ታላንት 20.4 ኪሎ ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
የቃላት መፍቻው ላይ “የፆታ ብልግና” የሚለውን ተመልከት።
ግሪክኛ፣ ፖርኒያ። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ግሪክኛ፣ ፖርኒያ። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ይህ አባባል የአዳምንና የሔዋንን ዘሮች ያመለክታል።
ወይም “የማሰብ ችሎታ።”
“የርኩስ እስትንፋስ ሁሉ፤ ርኩስ የሆነ በመንፈስ የተነገረ ቃል ሁሉ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ግሪክኛ፣ ፖርኒያ። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “የቁጣ።”
ወይም “ተጓዥ ነጋዴዎችም።”
ወይም “ወንጀሎች።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
የቃላት መፍቻው ላይ “የፆታ ብልግና” የሚለውን ተመልከት።
ወይም “የሰዎች ነፍስ።”
ወይም “ነፍስሽ የተመኘችው።”
ወይም “ሃሌሉያህ!” “ያህ” የይሖዋ ስም አጭር መጠሪያ ነው።
ግሪክኛ፣ ፖርኒያ። የቃላት መፍቻው ላይ “የፆታ ብልግና” የሚለውን ተመልከት።
ቃል በቃል “(የባሪያዎቹን ደም) ከእጇ ተበቅሏል።”
ወይም “ሃሌሉያህ!” “ያህ” የይሖዋ ስም አጭር መጠሪያ ነው።
ወይም “ሃሌሉያህ!” “ያህ” የይሖዋ ስም አጭር መጠሪያ ነው።
ወይም “ሃሌሉያህ!” “ያህ” የይሖዋ ስም አጭር መጠሪያ ነው።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
“ደም የተረጨበት” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “እንደ እረኛ በብረት በትር ያግዳቸዋል።”
ወይም “በአየር ላይ፤ ከላይ።”
ቃል በቃል “በመጥረቢያ የተቀሉትን።”
የቃላት መፍቻውንና ራእይ 6:9 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።
ወይም “ቀንና ሌሊት ይታገታሉ፤ ቀንና ሌሊት ይታሰራሉ።”
ወይም “ሐዲስም።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ሐዲስም።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ከዓይናቸው ይጠርጋል።”
ወይም “እምነት የሚጣልባቸውና።”
አልፋ እና ኦሜጋ የመጀመሪያውና የመጨረሻው የግሪክኛ ፊደላት ናቸው።
ወይም “ያለዋጋ።”
የቃላት መፍቻው ላይ “የፆታ ብልግና” የሚለውን ተመልከት።
2,220 ኪሎ ሜትር ገደማ። አንድ ስታዲዮን 185 ሜትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
64 ሜትር ገደማ። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “እምነት የሚጣልባቸውና።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
አልፋ እና ኦሜጋ የመጀመሪያውና የመጨረሻው የግሪክኛ ፊደላት ናቸው።
በአምላክ ዓይን አስጸያፊ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ ሰዎችን ያመለክታል።
የቃላት መፍቻው ላይ “የፆታ ብልግና” የሚለውን ተመልከት።