የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • nwt ነህምያ 1:1-13:31
  • ነህምያ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ነህምያ
  • አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
ነህምያ

ነህምያ

1 የሃካልያህ ልጅ የነህምያ*+ ቃል ይህ ነው፦ በ20ኛው ዓመት በኪስሌው* ወር በሹሻን*+ ግንብ* ነበርኩ። 2 በዚህ ጊዜ ከወንድሞቼ አንዱ የሆነው ሃናኒ+ በይሁዳ ከነበሩ ሌሎች ሰዎች ጋር መጣ፤ እኔም ከምርኮ ስለተረፉት አይሁዳውያን ቀሪዎችና+ ስለ ኢየሩሳሌም ጠየቅኳቸው። 3 እነሱም እንዲህ አሉኝ፦ “ከምርኮ ተመልሰው በአውራጃው ውስጥ የሚገኙት ቀሪዎች በጣም አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ፤ መሳለቂያም ሆነዋል።+ የኢየሩሳሌም ቅጥሮች ፈራርሰዋል፤+ በሮቿም በእሳት ተቃጥለዋል።”+

4 እኔም ይህን ስሰማ ቁጭ ብዬ ማልቀስ ጀመርኩ፤ ለቀናትም በሰማይ አምላክ ፊት ሳዝን፣ ስጾምና+ ስጸልይ ቆየሁ። 5 ከዚያም እንዲህ አልኩ፦ “የሰማይ አምላክ ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ለሚወዱህ፣ ትእዛዛትህንም ለሚያከብሩ ቃል ኪዳንህን የምትጠብቅና ታማኝ ፍቅር የምታሳይ ታላቅና የምትፈራ አምላክ ነህ፤+ 6 እባክህ ዛሬ ወደ አንተ የማቀርበውን የአገልጋይህን ጸሎት ለመስማት ጆሮህ ወደ እኔ ያዘንብል፤ ዓይኖችህም ይከፈቱ፤ እኛ እስራኤላውያን በአንተ ላይ የፈጸምነውን ኃጢአት እየተናዘዝኩ ስለ አገልጋዮችህ ስለ እስራኤላውያን ቀን ከሌት እየጸለይኩ ነው።+ እኔም ሆንኩ የአባቴ ቤት ኃጢአት ሠርተናል።+ 7 ለአገልጋይህ ለሙሴ የሰጠሃቸውን ትእዛዛት፣ ሥርዓቶችና ድንጋጌዎች ባለማክበር+ በአንተ ላይ መጥፎ ድርጊት እንደፈጸምን ምንም ጥርጥር የለውም።+

8 “እባክህ አገልጋይህን ሙሴን እንዲህ በማለት ያዘዝከውን ቃል* አስታውስ፦ ‘ታማኝነት የጎደለው ድርጊት የምትፈጽሙ ከሆነ በሕዝቦች መካከል እበትናችኋለሁ።+ 9 ወደ እኔ ተመልሳችሁ ትእዛዛቴን ብትጠብቁና ብትፈጽሙ ግን ሕዝቦቻችሁ እስከ ሰማይ ዳርቻ ድረስ ቢበተኑ እንኳ ከዚያ እሰበስባቸዋለሁ፤+ እንዲሁም ስሜ እንዲኖርበት ወደመረጥኩት ስፍራ አመጣቸዋለሁ።’+ 10 እነሱ በታላቅ ኃይልህና በብርቱ እጅህ የዋጀሃቸው አገልጋዮችህና ሕዝቦችህ ናቸው።+ 11 ይሖዋ ሆይ፣ እባክህ የአገልጋይህን ጸሎትና ስምህን በመፍራት ደስ የሚሰኙ አገልጋዮችህን ጸሎት ለመስማት ጆሮህን አዘንብል፤ እባክህ ዛሬ አገልጋይህ እንዲሳካለት አድርግ፤ ይህም ሰው ይራራልኝ።”+

እኔም የንጉሡ መጠጥ አሳላፊ ነበርኩ።+

2 ንጉሥ አርጤክስስ+ በነገሠ በ20ኛው ዓመት+ በኒሳን* ወር በንጉሡ ፊት የወይን ጠጅ ቀርቦ ነበር፤ እኔም እንደተለመደው የወይን ጠጁን አንስቼ ለንጉሡ ሰጠሁት።+ ሆኖም ከዚህ ቀደም እሱ ጋ ስቀርብ በፊቴ ላይ ሐዘን ታይቶ አያውቅም ነበር። 2 በመሆኑም ንጉሡ “ሳትታመም ፊትህ እንዲህ በሐዘን የጠቆረው ለምንድን ነው? ይህ መቼም የልብ ሐዘን እንጂ ሌላ ነገር ሊሆን አይችልም” አለኝ። በዚህ ጊዜ በጣም ፈራሁ።

3 ከዚያም ንጉሡን እንዲህ አልኩት፦ “ንጉሡ ለዘላለም ይኑር! አባቶቼ የተቀበሩባት ከተማ ፈራርሳ፣ በሮቿም በእሳት ተቃጥለው እያለ ለምን ፊቴ በሐዘን አይጠቁር?”+ 4 ንጉሡም መልሶ “ታዲያ ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ?” አለኝ። እኔም ወዲያውኑ ወደ ሰማይ አምላክ ጸለይኩ።+ 5 ከዚያም ንጉሡን እንዲህ አልኩት፦ “ንጉሡን ደስ የሚያሰኘው ከሆነና አገልጋይህ በፊትህ ሞገስ ካገኘ ከተማዋን መልሼ እንድገነባ አባቶቼ ወደተቀበሩባት ከተማ፣ ወደ ይሁዳ እንድሄድ ፍቀድልኝ።”+ 6 ንጉሡም ንግሥቲቱ አጠገቡ ተቀምጣ ሳለ “ጉዞህ ምን ያህል ጊዜ ይፈጃል? መቼ ትመለሳለህ?” አለኝ። ንጉሡም ደስ ብሎት እንድሄድ ፈቀደልኝ፤+ እኔም ጊዜውን ቆርጬ ነገርኩት።+

7 ከዚያም ንጉሡን እንዲህ አልኩት፦ “ንጉሡን ደስ የሚያሰኘው ከሆነ ከወንዙ+ ባሻገር* ያለው ክልል ገዢዎች ይሁዳ እስክደርስ ድረስ በሰላም ምድራቸውን አቋርጬ እንዳልፍ እንዲፈቅዱልኝ ደብዳቤ ይሰጠኝ፤ 8 በተጨማሪም የንጉሡ መናፈሻ ቦታ* ጠባቂ የሆነው አሳፍ ለቤቱ* የግንብ አጥር+ በሮች፣ ለከተማዋ ቅጥሮችና+ ለምሄድበት ቤት የሚያገለግሉ ሳንቃዎች እንዲሰጠኝ ደብዳቤ ይጻፍልኝ።” በዚህ ጊዜ መልካም የሆነው የአምላኬ እጅ በእኔ ላይ ስለነበር+ ንጉሡ እነዚህን ሰጠኝ።+

9 በመጨረሻም ከወንዙ ባሻገር ወዳለው ክልል ገዢዎች ሄጄ የንጉሡን ደብዳቤዎች ሰጠኋቸው። በተጨማሪም ንጉሡ የጦር አለቆችና ፈረሰኞች አብረውኝ እንዲሄዱ አድርጎ ነበር። 10 ሆሮናዊው ሳንባላጥና+ አሞናዊው+ ባለሥልጣን* ጦብያ+ ይህን ነገር ሲሰሙ ለእስራኤላውያን መልካም ነገር የሚያደርግ ሰው በመምጣቱ በጣም ተበሳጩ።

11 በመጨረሻም ኢየሩሳሌም ደረስኩ፤ እዚያም ሦስት ቀን ቆየሁ። 12 ከዚያም በሌሊት ተነሳሁ፤ ከእኔም ጋር ጥቂት ሰዎች ነበሩ፤ አምላኬ ለኢየሩሳሌም እንዳደርግ በልቤ ያኖረውን ነገር ለማንም ሰው አልተናገርኩም፤ ከተቀመጥኩበት እንስሳም በስተቀር ሌላ እንስሳ ከእኔ ጋር አልነበረም። 13 በሌሊትም በሸለቆ በር+ ከወጣሁ በኋላ በትልቁ እባብ ምንጭ ፊት ለፊት በማለፍ ወደ አመድ ቁልል በር+ ሄድኩ፤ የፈራረሱትን የኢየሩሳሌም ቅጥሮችና በእሳት የተቃጠሉትን በሮቿንም አንድ በአንድ መረመርኩ።+ 14 ከዚያም አልፌ ወደ ምንጭ በርና+ ወደ ንጉሡ ኩሬ ሄድኩ፤ በዚያም የተቀመጥኩበትን እንስሳ ማሳለፍ የሚያስችል በቂ ቦታ አልነበረም። 15 ሆኖም ሌሊቱን ሸለቆውን*+ ይዤ ሽቅብ ወጣሁ፤ ቅጥሩንም መመርመሬን ቀጠልኩ፤ ከዚያም ተመልሼ በሸለቆ በር ገባሁ፤ በኋላም ወደመጣሁበት ተመለስኩ።

16 ለአይሁዳውያኑ፣ ለካህናቱ፣ ለተከበሩት ሰዎች፣ ለበታች ገዢዎቹና+ ለቀሩት ሠራተኞች ገና ምንም የነገርኳቸው ነገር ስላልነበር የበታች ገዢዎቹ የት እንደሄድኩና ምን እያደረግኩ እንደነበር አላወቁም። 17 በመጨረሻም እንዲህ አልኳቸው፦ “መቼም ያለንበት ሁኔታ ምን ያህል አሳዛኝ እንደሆነ ሳትመለከቱ አትቀሩም፤ ኢየሩሳሌም ፈራርሳለች፣ በሮቿም በእሳት ተቃጥለዋል። እንግዲህ ተዋርደን እንዳንቀር ኑና የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች መልሰን እንገንባ።” 18 ከዚያም የአምላኬ መልካም እጅ ምን ያህል በእኔ ላይ እንደነበርና+ ንጉሡም ምን እንዳለኝ ነገርኳቸው።+ እነሱም “እንነሳና እንገንባ” አሉ። በመሆኑም መልካሙን ሥራ ለመሥራት ራሳቸውን* አበረቱ።+

19 ሆሮናዊው ሳንባላጥና አሞናዊው+ ባለሥልጣን* ጦብያ+ እንዲሁም የዓረብ+ ተወላጅ የሆነው ጌሼም ይህን ሲሰሙ ያፌዙብንና+ በንቀት ዓይን ይመለከቱን ጀመር፤ እንዲህም አሉን፦ “ምን እያደረጋችሁ ነው? በንጉሡ ላይ ልታምፁ ነው?”+ 20 እኔም እንዲህ ብዬ መለስኩላቸው፦ “ሥራችንን የሚያሳካልን የሰማይ አምላክ ነው፤+ እኛ አገልጋዮቹም ተነስተን እንገነባለን፤ እናንተ ግን በኢየሩሳሌም ምንም ዓይነት ድርሻም ሆነ መብት ወይም መታሰቢያ የላችሁም።”+

3 ሊቀ ካህናቱ ኤልያሺብና+ ካህናት የሆኑት ወንድሞቹ የበግ በርን+ ለመገንባት ተነሱ። እነሱም ቀደሱት፤*+ መዝጊያዎቹንም ገጠሙለት፤ እስከ መአህ ማማና+ እስከ ሃናንኤል ማማ+ ድረስ ቀደሱት። 2 ከእነሱ ቀጥሎ ያለውን ደግሞ የኢያሪኮ+ ሰዎች እየገነቡ ነበር፤ ከእነሱ ቀጥሎ ያለውን የኢምሪ ልጅ ዛኩር እየገነባ ነበር።

3 የሃስናአ ልጆች የዓሣ በርን+ ገነቡ፤ የጣውላ መቃኑንም ሠሩ፤+ ከዚያም መዝጊያዎቹን፣ መወርወሪያዎቹንና መቀርቀሪያዎቹን ገጠሙለት። 4 ከእነሱ ቀጥሎ ያለውን ደግሞ የሃቆጽ ልጅ የሆነው የዑሪያህ ልጅ መሬሞት+ ጠገነ፤ ቀጥሎ ያለውን የመሺዛቤል ልጅ የሆነው የቤራክያህ ልጅ መሹላም+ ጠገነ፤ ከዚያ ቀጥሎ ያለውን የባአና ልጅ ሳዶቅ ጠገነ። 5 ከእነሱ ቀጥሎ ያለውን ደግሞ የተቆአ+ ሰዎች ጠገኑ፤ ሆኖም ከእነሱ መካከል ታዋቂ የሆኑት ሰዎች ራሳቸውን ዝቅ በማድረግ* አለቆቻቸው በሚያሠሩት ሥራ መካፈል አልፈለጉም።

6 የፓሰአህ ልጅ ዮያዳ እና የቤሶድያህ ልጅ መሹላም የአሮጌ ከተማ በርን+ ጠገኑ፤ የጣውላ መቃኑንም ሠሩ፤ ከዚያም መዝጊያዎቹን፣ መወርወሪያዎቹንና መቀርቀሪያዎቹን ገጠሙለት። 7 ከእነሱ ቀጥሎ ያለውን ደግሞ ከወንዙ+ ባሻገር* ባለው ክልል ገዢ ሥልጣን* ሥር የሚገኙት የገባኦንና የምጽጳ+ ሰዎች የሆኑት ገባኦናዊው+ መላጥያህና መሮኖታዊው ያዶን ጠገኑ። 8 ከእነሱ ቀጥሎ ያለውን ከወርቅ አንጥረኞቹ አንዱ የሆነው የሃርሐያህ ልጅ ዑዚኤል ጠገነ፤ ከእሱ ቀጥሎ ያለውን ከቅባት ቀማሚዎች* አንዱ የሆነው ሃናንያህ ጠገነ፤ ኢየሩሳሌምንም እስከ ሰፊ ቅጥር+ ድረስ ድንጋይ አነጠፉባት። 9 ከእነሱ ቀጥሎ ያለውን ደግሞ የኢየሩሳሌም አውራጃ እኩሌታ ገዢ የሆነው የሁር ልጅ ረፋያህ ጠገነ። 10 የሃሩማፍ ልጅ የዳያህ ከእነሱ ቀጥሎ የሚገኘውን ከራሱ ቤት ፊት ለፊት ያለውን ጠገነ፤ ከእሱ ቀጥሎ ያለውን ደግሞ የሃሻበንያህ ልጅ ሃጡሽ ጠገነ።

11 የሃሪም+ ልጅ ማልኪያህና የፓሃትሞአብ+ ልጅ ሃሹብ ሌላኛውን ክፍል* ጠገኑ፤ እንዲሁም የምድጃዎች ማማን+ ጠገኑ። 12 ከእነሱ ቀጥሎ ያለውን ደግሞ የኢየሩሳሌም አውራጃ እኩሌታ ገዢ የሆነው የሃሎሔሽ ልጅ ሻሉም እና ሴቶች ልጆቹ ጠገኑ።

13 ሃኑን እና የዛኖሃ+ ነዋሪዎች የሸለቆ በርን+ ጠገኑ፤ እነሱም ከሠሩት በኋላ መዝጊያዎቹን፣ መወርወሪያዎቹንና መቀርቀሪያዎቹን ገጠሙለት፤ በተጨማሪም እስከ አመድ ቁልል በር+ ድረስ ያለውን 1,000 ክንድ* ቅጥር ጠገኑ። 14 የቤትሃኬሬም+ አውራጃ ገዢ የሆነው የሬካብ ልጅ ማልኪያህ የአመድ ቁልል በርን ጠገነ፤ እሱም ከሠራው በኋላ መዝጊያዎቹን፣ መወርወሪያዎቹንና መቀርቀሪያዎቹን ገጠመለት።

15 የምጽጳ+ አውራጃ ገዢ የሆነው የኮልሆዜ ልጅ ሻሉን የምንጭ በርን+ ጠገነ፤ እሱም ከሠራው በኋላ ጣሪያ አበጀለት፤ ከዚያም መዝጊያዎቹን፣ መወርወሪያዎቹንና መቀርቀሪያዎቹን ገጠመ፤ በተጨማሪም በንጉሡ የአትክልት ስፍራ+ ያለውን የሼላ የውኃ ገንዳ* ግንብ+ ከዳዊት ከተማ+ ተነስቶ ቁልቁል እስከሚወርደው ደረጃ+ ድረስ ጠገነ።

16 ከእሱ ቀጥሎ ደግሞ የቤትጹር+ አውራጃ እኩሌታ ገዢ የሆነው የአዝቡቅ ልጅ ነህምያ ከዳዊት የመቃብር ስፍራ+ ፊት ለፊት አንስቶ እስከ ሰው ሠራሹ ኩሬና+ እስከ ኃያላኑ ቤት ድረስ ገነባ።

17 ከእሱ ቀጥሎ ያለውን በባኒ ልጅ በረሁም ሥር ያሉት ሌዋውያን ጠገኑት፤ ከእሱ ቀጥሎ ደግሞ የቀኢላ+ አውራጃ እኩሌታ ገዢ የሆነው ሃሻብያህ የራሱን አውራጃ ጠገነ። 18 ከእሱ ቀጥሎ ያለውን የቀኢላ አውራጃ እኩሌታ ገዢ በሆነው በሄናዳድ ልጅ በባዋይ ሥር ያሉት ወንድሞቻቸው ጠገኑ።

19 ከእሱ ቀጥሎ ደግሞ የምጽጳ ገዢ የሆነው የኤጼር ልጅ የሹዋ+ በቅጥሩ ቅስት+ አጠገብ ወደሚገኘው የጦር መሣሪያ ግምጃ ቤት ከሚያስወጣው አቀበት ፊት ለፊት ያለውን ሌላኛውን ክፍል ጠገነ።

20 ከእሱ ቀጥሎ ደግሞ የዛባይ+ ልጅ ባሮክ የቅጥሩ ቅስት ከሚገኝበት አንስቶ እስከ ሊቀ ካህናቱ ኤልያሺብ+ ቤት መግቢያ ድረስ ያለውን ሌላኛውን ክፍል በቅንዓት ጠገነ።

21 ከእሱ ቀጥሎ የሃቆጽ ልጅ የሆነው የዑሪያህ ልጅ መሬሞት+ ከኤልያሺብ ቤት መግቢያ አንስቶ እስከ ኤልያሺብ ቤት መጨረሻ ድረስ ያለውን ሌላኛውን ክፍል ጠገነ።

22 ከእሱ ቀጥሎ ያለውን ደግሞ ካህናቱ ይኸውም የዮርዳኖስ አውራጃ*+ ሰዎች ጠገኑት። 23 ከእነሱ ቀጥሎ ቢንያምና ሃሹብ ከቤታቸው ፊት ለፊት ያለውን ጠገኑ። ከእነሱ ቀጥሎ ደግሞ የአናንያ ልጅ የሆነው የማአሴያህ ልጅ አዛርያስ ከራሱ ቤት አጠገብ ያለውን ጠገነ። 24 ከእሱ ቀጥሎ የሄናዳድ ልጅ ቢኑይ ከአዛርያስ ቤት አንስቶ እስከ ቅጥሩ ቅስትና+ እስከ ማዕዘኑ ድረስ ያለውን ሌላኛውን ክፍል ጠገነ።

25 ከእሱ ቀጥሎ የዑዛይ ልጅ ፓላል ከቅስቱ ፊት ለፊት ያለውን ቅጥርና በንጉሡ ቤት*+ አጠገብ በክብር ዘቦቹ ግቢ+ ውስጥ የሚገኘውን የላይኛውን ማማ ጠገነ። ከእሱ ቀጥሎ የፓሮሽ+ ልጅ ፐዳያህ ነበር።

26 እንዲሁም በኦፌል+ የሚኖሩት የቤተ መቅደስ አገልጋዮች*+ በስተ ምሥራቅ እስከ ውኃ በር+ ፊት ለፊት ድረስ ያለውን ቅጥርና ወጣ ያለውን ማማ ጠገኑ።

27 ከእነሱ ቀጥሎ የተቆአ+ ሰዎች ወጣ ካለው ትልቅ ማማ ፊት ለፊት አንስቶ እስከ ኦፌል ቅጥር ድረስ ያለውን ሌላኛውን ክፍል ጠገኑ።

28 ካህናቱ ከፈረስ በር+ በላይ ያለውን ጠገኑ፤ እያንዳንዳቸውም ከቤታቸው ፊት ለፊት ያለውን ጠገኑ።

29 ከእነሱ ቀጥሎ የኢሜር ልጅ ሳዶቅ+ ከራሱ ቤት ፊት ለፊት ያለውን ጠገነ።

ከእሱ ቀጥሎ ደግሞ የምሥራቅ በር+ ጠባቂ የሆነው የሸካንያህ ልጅ ሸማያህ ጠገነ።

30 ከእሱ ቀጥሎ የሸሌምያህ ልጅ ሃናንያህና የጻላፍ ስድስተኛ ልጅ ሃኑን ሌላኛውን ክፍል ጠገኑ።

ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ የቤራክያህ ልጅ መሹላም+ ከራሱ አዳራሽ ፊት ለፊት ያለውን ጠገነ።

31 ከእሱ ቀጥሎ ደግሞ የወርቅ አንጥረኞች ማኅበር አባል የሆነው ማልኪያህ በመቆጣጠሪያ በር አጠገብ እስከሚገኘው እስከ ቤተ መቅደስ አገልጋዮቹና*+ እስከ ነጋዴዎቹ ቤት እንዲሁም በማዕዘኑ ላይ እስካለው ሰገነት ድረስ ያለውን ጠገነ።

32 የወርቅ አንጥረኞቹና ነጋዴዎቹም በሰገነቱ ማዕዘን ላይ በሚገኘው ክፍልና በበግ በር+ መካከል ያለውን ጠገኑ።

4 ሳንባላጥ+ ቅጥሩን መልሰን እየገነባን መሆናችንን ሲሰማ በጣም ተናደደ፤ እጅግም ተበሳጨ፤ በአይሁዳውያንም ላይ ያፌዝ ነበር። 2 በወንድሞቹና በሰማርያ ጦር ሠራዊት ፊትም እንዲህ ይል ጀመር፦ “እነዚህ አቅመ ቢስ አይሁዳውያን ምን እያደረጉ ነው? ለመሆኑ ይህን ሥራ ራሳቸው ሊሠሩት ነው? መሥዋዕትስ ሊያቀርቡ ነው? ደግሞስ በአንድ ቀን ሠርተው ሊጨርሱ ያስባሉ? በእሳት ተቃጥለው የአመድ ቁልል የሆኑትን ድንጋዮች ሕይወት ሊዘሩባቸው ነው?”+

3 በዚህ ጊዜ አጠገቡ ቆሞ የነበረው አሞናዊው+ ጦብያ+ “የሚገነቡት የድንጋይ ቅጥር እኮ ቀበሮ እንኳ ቢወጣበት ይፈርሳል” አለ።

4 አምላካችን ሆይ፣ መሳለቂያ ሆነናልና+ ስማ፤ ስድባቸውን በራሳቸው ላይ መልስባቸው፤+ እንዲበዘበዙና ተማርከው ወደ ሌላ አገር እንዲወሰዱ አድርጋቸው። 5 የግንባታውን ሥራ የሚሠሩትን ሰዎች ስለተሳደቡ በደላቸውን አትሸፍን፤+ ኃጢአታቸውም ከፊትህ እንዲደመሰስ አታድርግ።

6 እኛም ቅጥሩን መገንባታችንን ቀጠልን፤ ዙሪያውን ያለው ቅጥርም ክፍተቱ እየተደፈነ እስከ ቁመቱ እኩሌታ ድረስ ተጠገነ፤ ሕዝቡም ሥራውን ከልቡ መሥራቱን ቀጠለ።

7 ሳንባላጥ፣ ጦብያ፣+ ዓረቦች፣+ አሞናውያንና አሽዶዳውያን+ የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች የመጠገኑ ሥራ እየተፋጠነና ክፍተቶቹም እየተደፈኑ መሆናቸውን ሲሰሙ እጅግ ተናደዱ። 8 እነሱም መጥተው ኢየሩሳሌምን ለመውጋትና በውስጧ ሁከት ለመፍጠር በአንድነት አሴሩ። 9 እኛ ግን ወደ አምላካችን ጸለይን፤ ከእነሱ ጥቃት ሌት ተቀን የሚጠብቁን ጠባቂዎችም አቆምን።

10 የይሁዳ ሰዎች ግን እንዲህ ይሉ ነበር፦ “የሠራተኞቹ* አቅም እየተሟጠጠ ነው፤ ፍርስራሹ ደግሞ በጣም ብዙ ነው፤ ፈጽሞ ቅጥሩን መገንባት አንችልም።”

11 ጠላቶቻችንም “ምንም ሳያውቁ ወይም ሳያዩን መካከላቸው ገብተን እንገድላቸዋለን፤ ሥራውንም እናስቆማለን” ይሉ ነበር።

12 በእነሱ አቅራቢያ የሚኖሩት አይሁዳውያንም በመጡ ቁጥር “በሁሉም አቅጣጫ ይዘምቱብናል” እያሉ ደጋግመው* ይነግሩን ነበር።

13 ስለዚህ ከቅጥሩ ጀርባ በሚገኘው ገላጣ በሆነው ዝቅተኛ ቦታ ላይ ሰዎችን አቆምኩ፤ እነሱም ሰይፋቸውን፣ ጦራቸውንና ቀስታቸውን ይዘው በየቤተሰቦቻቸው እንዲቆሙ አደረግኩ። 14 ሰዎቹ መፍራታቸውን ሳይም ወዲያውኑ ተነስቼ የተከበሩትን ሰዎች፣+ የበታች ገዢዎቹንና የቀረውን ሕዝብ እንዲህ አልኳቸው፦ “አትፍሯቸው።+ ታላቁንና የተፈራውን ይሖዋን አስቡ፤+ ለወንድሞቻችሁ፣ ለወንዶች ልጆቻችሁ፣ ለሴቶች ልጆቻችሁ፣ ለሚስቶቻችሁና ለቤታችሁ ተዋጉ።”

15 ጠላቶቻችንም ሴራቸውን እንዳወቅንባቸውና እውነተኛው አምላክ ዕቅዳቸውን እንዳከሸፈባቸው ሰሙ፤ ከዚያም ሁላችንም ቅጥሩን ወደ መገንባቱ ሥራችን ተመለስን። 16 ከዚያን ቀን ጀምሮ አብረውኝ ካሉት ሰዎች መካከል ግማሾቹ ሥራውን ሲሠሩ+ ግማሾቹ ደግሞ ጦር፣ ጋሻና ቀስት ይዘው እንዲሁም ጥሩር ለብሰው ይቆሙ ነበር። መኳንንቱ+ ከአይሁዳውያኑ ኋላ ቆመው ድጋፍ ሲሰጧቸው 17 እነሱ ደግሞ ቅጥሩን ይገነቡ ነበር። ሸክም የሚሸከሙት ሰዎች እያንዳንዳቸው በአንድ እጃቸው ሥራውን ሲሠሩ በሌላ እጃቸው ደግሞ የጦር መሣሪያ* ይይዙ ነበር። 18 የግንባታውን ሥራ የሚሠራ እያንዳንዱ ሰው ግንባታውን የሚያከናውነው ሰይፉን በወገቡ ታጥቆ ነበር፤ ቀንደ መለከት የሚነፋውም+ ሰው አጠገቤ ይቆም ነበር።

19 ከዚያም የተከበሩትን ሰዎች፣ የበታች ገዢዎቹንና የቀረውን ሕዝብ እንዲህ አልኳቸው፦ “ሥራው እንደምታዩት ብዙና ሰፊ ነው፤ ቅጥሩንም የምንገነባው አንዳችን ከሌላው ተራርቀን ነው። 20 በመሆኑም የቀንደ መለከቱን ድምፅ በምትሰሙበት ጊዜ እኛ ወዳለንበት ቦታ ተሰብሰቡ። አምላካችን ራሱ ይዋጋልናል።”+

21 ስለዚህ ግማሾቻችን ሥራውን ስናከናውን ግማሾቹ ደግሞ ጎህ ከሚቀድበት አንስቶ ከዋክብት እስከሚወጡበት ጊዜ ድረስ ጦር ይዘው ይቆሙ ነበር። 22 በዚህ ጊዜ ሕዝቡን እንዲህ አልኳቸው፦ “እያንዳንዱ ሰው ከአገልጋዩ ጋር ሆኖ ሌሊቱን በኢየሩሳሌም ውስጥ ያሳልፍ፤ እነሱም ሌሊቱን ይጠብቁናል፤ ቀን ላይ ደግሞ ይሠራሉ።” 23 እኔም ሆንኩ ወንድሞቼና አገልጋዮቼ+ እንዲሁም ይከተሉኝ የነበሩት ጠባቂዎች ፈጽሞ ልብሳችንን አናወልቅም ነበር፤ የጦር መሣሪያችንም ከቀኝ እጃችን አይለይም ነበር።

5 ሆኖም ወንዶቹም ሆኑ ሚስቶቻቸው በአይሁዳውያን ወንድሞቻቸው ላይ ታላቅ ጩኸት አሰሙ።+ 2 አንዳንዶቹ “የእኛም ሆነ የወንዶች ልጆቻችንና የሴቶች ልጆቻችን ቁጥር ብዙ ነው። በሕይወት ለመቆየት የምንበላው እህል ማግኘት ይኖርብናል” ይሉ ነበር። 3 ሌሎቹም “የምግብ እጥረት በተከሰተበት ወቅት እህል ለማግኘት ስንል ማሳችንን፣ የወይን እርሻችንንና ቤታችንን መያዣ አድርገን ሰጥተናል” አሉ። 4 የተቀሩት ደግሞ እንዲህ ይሉ ነበር፦ “የንጉሡን ግብር ለመክፈል ስንል ማሳችንንና የወይን እርሻችንን አስይዘን ገንዘብ ተበድረናል።+ 5 እንግዲህ ወንድሞቻችን የአጥንታችን ፍላጭ፣ የሥጋችን ቁራጭ ናቸው፤* ልጆቻችንም እንደ ልጆቻቸው ናቸው፤ ሆኖም ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችንን ለባርነት አሳልፈን ለመስጠት ተገደናል፤ እንዲያውም ከሴቶች ልጆቻችን መካከል አንዳንዶቹ አሁንም በባርነት ላይ ናቸው።+ ያም ሆኖ ማሳችንና የወይን እርሻችን በሌሎች እጅ ስለሆነ ይህን ለማስቆም የሚያስችል አቅም የለንም።”

6 እኔም ጩኸታቸውንና ይህን አቤቱታቸውን ስሰማ በጣም ተናደድኩ። 7 ስለዚህ ነገሩን በልቤ ካጤንኩ በኋላ የተከበሩትን ሰዎችና የበታች ገዢዎቹን “እያንዳንዳችሁ ከገዛ ወንድማችሁ ላይ ወለድ እየተቀበላችሁ* ነው” በማለት ወቀስኳቸው።+

በተጨማሪም በእነሱ የተነሳ ታላቅ ስብሰባ ጠራሁ። 8 እንዲህም አልኳቸው፦ “ለብሔራት ተሸጠው የነበሩትን አይሁዳውያን ወንድሞቻችንን በተቻለን መጠን መልሰን ገዝተናቸው ነበር፤ ታዲያ እናንተ አሁን የገዛ ወንድሞቻችሁን መልሳችሁ ትሸጣላችሁ?+ ደግሞስ እንደገና ለእኛ መሸጥ ይኖርባቸዋል?” በዚህ ጊዜ የሚመልሱት ስለጠፋቸው ዝም አሉ። 9 ከዚያም እንዲህ አልኳቸው፦ “የምትሠሩት ሥራ ጥሩ አይደለም። ጠላቶቻችን የሆኑት ብሔራት መሳለቂያ እንዳያደርጉን አምላካችንን በመፍራት መመላለስ አልነበረባችሁም?+ 10 ከዚህም በላይ እኔም ሆንኩ ወንድሞቼና አገልጋዮቼ ገንዘብና እህል አበድረናቸዋል። እባካችሁ ይህን በወለድ ማበደር የሚባል ነገር እንተው።+ 11 ደግሞም እባካችሁ ማሳዎቻቸውን፣ የወይን እርሻዎቻቸውን፣ የወይራ ዛፎቻቸውንና ቤቶቻቸውን እንዲሁም ከገንዘብ፣ ከእህል፣ ከአዲስ የወይን ጠጅና ከዘይት ወለድ አድርጋችሁ የተቀበላችሁትን ከመቶ አንድ እጅ* ዛሬውኑ መልሱላቸው።”+

12 እነሱም “እነዚህን ነገሮች እንመልስላቸዋለን፤ በምላሹም ምንም ነገር እንዲያደርጉልን አንጠይቅም። ልክ እንዳልከው እናደርጋለን” አሉ። እኔም ካህናቱን ጠርቼ ሰዎቹን ይህን ቃል እንዲጠብቁ አስማልኳቸው። 13 በተጨማሪም የልብሴን እጥፋት* አራግፌ እንዲህ አልኳቸው፦ “ይህን ቃል የማይፈጽመውን ማንኛውንም ሰው እውነተኛው አምላክ ከቤቱና ከንብረቱ እንዲህ አራግፎ ያስወጣው፤ ልክ እንደዚህ ተራግፎም ባዶውን ይቅር።” በዚህ ጊዜ መላው ጉባኤ “አሜን!”* አለ። ይሖዋንም አመሰገኑ፤ ሕዝቡም ቃል እንደገቡት አደረጉ።

14 ከዚህም በላይ ንጉሡ በይሁዳ ምድር ገዢያቸው አድርጎ ከሾመኝ+ ጊዜ አንስቶ ማለትም ንጉሥ አርጤክስስ+ ከነገሠ ከ20ኛው ዓመት+ አንስቶ እስከ 32ኛው ዓመት+ ድረስ ይኸውም ለ12 ዓመት ያህል እኔም ሆንኩ ወንድሞቼ ለገዢው የሚገባውን ቀለብ አልበላንም።+ 15 ከእኔ በፊት የነበሩት የቀድሞዎቹ ገዢዎች ግን በሕዝቡ ላይ ሸክም ጭነውበት የነበረ ከመሆኑም ሌላ ከሕዝቡ ላይ ለምግብና ለወይን ጠጅ በየቀኑ 40 የብር ሰቅል* ይወስዱ ነበር። በተጨማሪም አገልጋዮቻቸው ሕዝቡን ይጨቁኑ ነበር። እኔ ግን አምላክን ስለምፈራ+ እንዲህ አላደረግኩም።+

16 ከዚህም በላይ ይህን ቅጥር በመገንባቱ ሥራ ተሳትፌያለሁ፤ አገልጋዮቼም በሙሉ ሥራውን ለመሥራት እዚያ ተሰባስበው ነበር፤ የራሳችንም መሬት አልነበረንም።+ 17 በተጨማሪም 150 አይሁዳውያንና የበታች ገዢዎች እንዲሁም ከሌሎች ብሔራት ወደ እኛ የመጡ ሰዎች ከማዕዴ ይበሉ ነበር። 18 በየቀኑ አንድ በሬ፣ ስድስት ምርጥ በጎች እንዲሁም ወፎች ይዘጋጁልኝ* ነበር፤ በየአሥር ቀኑ ደግሞ የተለያየ ዓይነት የወይን ጠጅ በብዛት ይቀርብልን ነበር። እንደዚያም ሆኖ ሕዝቡ የራሱ የአገልግሎት ቀንበር ከብዶት ስለነበር ለገዢው የሚገባው ቀለብ እንዲሰጠኝ ጠይቄ አላውቅም። 19 አምላኬ ሆይ፣ ለዚህ ሕዝብ ስላደረግኩት ነገር ሁሉ በመልካም አስበኝ።+

6 ሳንባላጥ፣ ጦብያ፣+ የዓረብ+ ተወላጅ የሆነው ጌሼምና የቀሩት ጠላቶቻችን ቅጥሩን መልሼ እንደገነባሁና+ ክፍተቶቹ ሁሉ እንደተደፈኑ ሲነገራቸው (ምንም እንኳ ገና መዝጊያዎቹን በበሮቹ ላይ ባልገጥማቸውም)፣+ 2 ሳንባላጥና ጌሼም “እስቲ መጥተህ በኦኖ+ ሸለቋማ ሜዳ ከሚገኙት መንደሮች በአንዱ ለመገናኘት ቀጠሮ እንያዝ” የሚል መልእክት ወዲያውኑ ላኩብኝ። ሆኖም እኔን ለመጉዳት አሲረው ነበር። 3 በመሆኑም “ትልቅ ሥራ እየሠራሁ ስለሆነ ወደዚያ መውረድ አልችልም። ሥራውን ትቼ ወደ እናንተ በመውረዴ ምክንያት ለምን ሥራው ይስተጓጎል?” ብለው እንዲነግሯቸው መልእክተኞችን ላክሁባቸው። 4 እነሱም ያንኑ መልእክት አራት ጊዜ ላኩብኝ፤ እኔም በላኩብኝ ቁጥር ይህንኑ መልስ መለስኩላቸው።

5 ከዚያም ሳንባላጥ አገልጋዩን ያልታሸገ ደብዳቤ በእጁ አስይዞ ለአምስተኛ ጊዜ ያንኑ መልእክት ላከብኝ። 6 ደብዳቤውም እንዲህ የሚል ነበር፦ “አንተም ሆንክ አይሁዳውያኑ ለማመፅ እያሴራችሁ+ መሆኑን ብሔራት ሁሉ ሰምተዋል፤ ጌሼምም+ ይህንኑ እየተናገረ ነው። ቅጥሩንም እየገነባህ ያለኸው ለዚሁ ነው፤ እንደተባለው ከሆነ ደግሞ ንጉሣቸው ልትሆን ነው። 7 በተጨማሪም በመላው ኢየሩሳሌም ‘በይሁዳ ንጉሥ አለ!’ ብለው ስለ አንተ እንዲያውጁ ነቢያትን ሾመሃል። እነዚህ ነገሮች ደግሞ ንጉሡ ጆሮ መድረሳቸው አይቀርም። ስለሆነም መጥተህ በጉዳዩ ላይ ብንነጋገር ይሻላል።”

8 እኔ ግን እንዲህ ስል መለስኩለት፦ “ከተናገርከው ነገር መካከል አንዱም አልተፈጸመም፤ ሁሉም ነገር አንተ ራስህ በአእምሮህ* የፈጠርከው ነው።” 9 ምክንያቱም ሁሉም “እጃቸው ስለሚዝል ሥራው እንደሆነ አይጠናቀቅም” በማለት ሊያስፈራሩን ይሞክሩ ነበር።+ በዚህ ጊዜ እጆቼን አበርታልኝ ብዬ ጸለይኩ።+

10 ከዚያም የመሄጣቤል ልጅ ወደሆነው ወደ ደላያህ ልጅ ወደ ሸማያህ ቤት ሄድኩ፤ እሱም ቤቱ ውስጥ ነበር። እንዲህም አለኝ፦ “ሊገድሉህ ስለሚመጡ በእውነተኛው አምላክ ቤት ይኸውም ቤተ መቅደሱ ውስጥ መቼ እንደምንገናኝ እንቀጣጠር፤ የቤተ መቅደሱንም በሮች እንዝጋ። አንተን ለመግደል በሌሊት ይመጣሉ።” 11 እኔ ግን “እንደ እኔ ያለ ሰው መሸሽ ይገባዋል? ደግሞስ እንደ እኔ ያለ ሰው ቤተ መቅደሱ ውስጥ ገብቶ በሕይወት ሊኖር ይችላል?+ በፍጹም አልገባም!” አልኩት። 12 ከዚያም ይህን ሰው አምላክ እንዳላከው ከዚህ ይልቅ ጦብያና ሳንባላጥ+ በእኔ ላይ ይህን ትንቢት እንዲናገር እንደቀጠሩት ተገነዘብኩ። 13 ይህን ሰው የቀጠሩት አስፈራርቶ ኃጢአት እንድሠራ እንዲያደርገኝና በዚህም የተነሳ ስሜን የሚያጠፉበት ምክንያት በማግኘት ሊሳለቁብኝ ፈልገው ነው።

14 አምላኬ ሆይ፣ ጦብያና+ ሳንባላጥ የሚያደርጉትን ይህን ነገር እንዲሁም እኔን ለማስፈራራት ተደጋጋሚ ሙከራ የሚያደርጉትን ነቢዪቱ ኖአድያህንና ሌሎቹን ነቢያት አስብ።

15 ቅጥሩም በኤሉል* ወር በ25ኛው ቀን በ52 ቀናት ውስጥ ተሠርቶ ተጠናቀቀ።

16 ጠላቶቻችን በሙሉ ይህን ሲሰሙና በዙሪያችን ያሉት ብሔራትም ይህን ሲያዩ በኀፍረት ተዋጡ፤*+ ይህ ሥራ የተከናወነው በአምላካችን እርዳታ እንደሆነም ተገነዘቡ። 17 በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ የተከበሩ ሰዎች+ ለጦብያ ብዙ ደብዳቤዎችን ይልኩለት የነበረ ሲሆን እሱም መልስ ይጽፍላቸው ነበር። 18 ጦብያ የኤራ+ ልጅ የሸካንያህ አማች ስለነበርና ልጁ የሆሃናን ደግሞ የቤራክያህን ልጅ የመሹላምን+ ሴት ልጅ ስላገባ በይሁዳ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች በታማኝነት ከጎኑ እንደሚቆሙ ምለውለት ነበር። 19 በተጨማሪም ዘወትር ስለ እሱ መልካም ነገሮችን ይነግሩኝ የነበረ ከመሆኑም ሌላ እኔ የምለውንም ለእሱ ያወሩለት ነበር። ጦብያም እኔን ለማስፈራራት ደብዳቤዎችን ይልክ ነበር።+

7 እኔም ቅጥሩ እንደገና ተገንብቶ እንዳለቀ+ መዝጊያዎቹን+ ገጠምኩ፤ ከዚያም በር ጠባቂዎቹ፣+ ዘማሪዎቹና+ ሌዋውያኑ+ ተሾሙ። 2 በኋላም ወንድሜን ሃናኒን፣+ የምሽጉ+ አለቃ ከሆነው ከሃናንያህ ጋር በኢየሩሳሌም ላይ ሾምኩት፤ ምክንያቱም ሃናንያህ እምነት የሚጣልበትና ከሌሎቹ ሁሉ ይበልጥ እውነተኛውን አምላክ የሚፈራ ሰው ነበር።+ 3 እንዲህም አልኳቸው፦ “የኢየሩሳሌም በሮች ፀሐይ ሞቅ እስከሚል ድረስ መከፈት የለባቸውም፤ ጠባቂዎቹ በጥበቃ ሥራቸው ላይ እያሉ በሮቹን መዝጋትና መቀርቀር ይኖርባቸዋል። እንዲሁም የኢየሩሳሌምን ነዋሪዎች ጠባቂዎች አድርጋችሁ መድቡ፤ የተወሰኑት ሰዎች በተመደቡበት የጥበቃ ቦታ፣ ሌሎቹ ደግሞ ከቤታቸው ፊት ለፊት ይጠብቁ።” 4 ከተማዋ ሰፊና ትልቅ ነበረች፤ በውስጧ የነበሩት ሰዎች ጥቂት ሲሆኑ+ ቤቶቹም እንደገና አልተገነቡም ነበር።

5 ሆኖም አምላኬ የተከበሩትን ሰዎች፣ የበታች ገዢዎቹንና ሕዝቡን በአንድነት እንድሰበስብና በየዘር ሐረጋቸው እንዲመዘገቡ+ እንዳደርግ ይህን ሐሳብ በልቤ ውስጥ አኖረ። ከዚያም መጀመሪያ ላይ የመጡትን ሰዎች የዘር ሐረግ ዝርዝር የያዘ መጽሐፍ አገኘሁ፤ በውስጡም ተጽፎ ያገኘሁት ይህ ነው፦

6 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር+ በግዞት ወስዷቸው+ የነበሩትና ከምርኮ ነፃ ወጥተው፣ በኋላ ላይ ወደ ኢየሩሳሌምና ወደ ይሁዳ ይኸውም ወደየከተሞቻቸው የተመለሱት የአውራጃው ነዋሪዎች እነዚህ ናቸው፤+ 7 ከዘሩባቤል፣+ ከየሆሹዋ፣+ ከነህምያ፣ ከአዛርያስ፣ ከራሚያህ፣ ከናሃማኒ፣ ከመርዶክዮስ፣ ከቢልሻን፣ ከሚስጴሬት፣ ከቢግዋይ፣ ከነሁም እና ከባአናህ ጋር የመጡት እነዚህ ናቸው።

የእስራኤላውያን ወንዶች ቁጥር የሚከተሉትን ይጨምራል፦+ 8 የፓሮሽ ወንዶች ልጆች 2,172፣ 9 የሰፋጥያህ ወንዶች ልጆች 372፣ 10 የኤራ+ ወንዶች ልጆች 652፣ 11 የየሹዋና የኢዮዓብ+ ወንዶች ልጆች የሆኑት የፓሃትሞአብ+ ወንዶች ልጆች 2,818፣ 12 የኤላም+ ወንዶች ልጆች 1,254፣ 13 የዛቱ ወንዶች ልጆች 845፣ 14 የዛካይ ወንዶች ልጆች 760፣ 15 የቢኑይ ወንዶች ልጆች 648፣ 16 የቤባይ ወንዶች ልጆች 628፣ 17 የአዝጋድ ወንዶች ልጆች 2,322፣ 18 የአዶኒቃም ወንዶች ልጆች 667፣ 19 የቢግዋይ ወንዶች ልጆች 2,067፣ 20 የአዲን ወንዶች ልጆች 655፣ 21 የሕዝቅያስ ልጅ የአጤር ወንዶች ልጆች 98፣ 22 የሃሹም ወንዶች ልጆች 328፣ 23 የቤጻይ ወንዶች ልጆች 324፣ 24 የሃሪፍ ወንዶች ልጆች 112፣ 25 የገባኦን+ ወንዶች ልጆች 95፣ 26 የቤተልሔምና የነጦፋ ሰዎች 188፣ 27 የአናቶት+ ሰዎች 128፣ 28 የቤትአዝማዌት ሰዎች 42፣ 29 የቂርያትየአሪም፣+ የከፊራና የበኤሮት+ ሰዎች 743፣ 30 የራማና የጌባ+ ሰዎች 621፣ 31 የሚክማስ+ ሰዎች 122፣ 32 የቤቴልና+ የጋይ+ ሰዎች 123፣ 33 የሌላኛው ነቦ ሰዎች 52፣ 34 የሌላኛው ኤላም ወንዶች ልጆች 1,254፣ 35 የሃሪም ወንዶች ልጆች 320፣ 36 የኢያሪኮ ወንዶች ልጆች 345፣ 37 የሎድ፣ የሃዲድና የኦኖ+ ወንዶች ልጆች 721፣ 38 የሰናአ ወንዶች ልጆች 3,930።

39 ካህናቱ+ የሚከተሉት ናቸው፦ ከየሹዋ ወገን የሆነው የየዳያህ ወንዶች ልጆች 973፣ 40 የኢሜር ወንዶች ልጆች 1,052፣ 41 የጳስኮር+ ወንዶች ልጆች 1,247፣ 42 የሃሪም+ ወንዶች ልጆች 1,017።

43 ሌዋውያኑ+ የሚከተሉት ናቸው፦ የሆዳውያህ ወንዶች ልጆች የሆኑት የየሹዋና የቃድሚኤል+ ወንዶች ልጆች 74። 44 ዘማሪዎቹ+ የአሳፍ+ ወንዶች ልጆች 148። 45 በር ጠባቂዎቹ+ የሻሉም ወንዶች ልጆች፣ የአጤር ወንዶች ልጆች፣ የታልሞን ወንዶች ልጆች፣ የአቁብ+ ወንዶች ልጆች፣ የሃጢጣ ወንዶች ልጆችና የሾባይ ወንዶች ልጆች 138።

46 የቤተ መቅደሱ አገልጋዮች*+ የሚከተሉት ናቸው፦ የጺሃ ወንዶች ልጆች፣ የሃሱፋ ወንዶች ልጆች፣ የታባኦት ወንዶች ልጆች፣ 47 የቀሮስ ወንዶች ልጆች፣ የሲአ ወንዶች ልጆች፣ የፓዶን ወንዶች ልጆች፣ 48 የለባና ወንዶች ልጆች፣ የሃጋባ ወንዶች ልጆች፣ የሳልማይ ወንዶች ልጆች፣ 49 የሃናን ወንዶች ልጆች፣ የጊዴል ወንዶች ልጆች፣ የጋሃር ወንዶች ልጆች፣ 50 የረአያህ ወንዶች ልጆች፣ የረጺን ወንዶች ልጆች፣ የነቆዳ ወንዶች ልጆች፣ 51 የጋዛም ወንዶች ልጆች፣ የዑዛ ወንዶች ልጆች፣ የፓሰአህ ወንዶች ልጆች፣ 52 የቤሳይ ወንዶች ልጆች፣ የመኡኒም ወንዶች ልጆች፣ የነፉሸሲም ወንዶች ልጆች፣ 53  የባቅቡቅ ወንዶች ልጆች፣ የሃቁፋ ወንዶች ልጆች፣ የሃርሑር ወንዶች ልጆች፣ 54 የባጽሊት ወንዶች ልጆች፣ የመሂዳ ወንዶች ልጆች፣ የሃርሻ ወንዶች ልጆች፣ 55 የባርቆስ ወንዶች ልጆች፣ የሲሳራ ወንዶች ልጆች፣ የተማ ወንዶች ልጆች፣ 56 የነጺሃ ወንዶች ልጆችና የሃጢፋ ወንዶች ልጆች።

57  የሰለሞን አገልጋዮች+ ወንዶች ልጆች የሚከተሉት ናቸው፦ የሶጣይ ወንዶች ልጆች፣ የሶፈረት ወንዶች ልጆች፣ የፐሪዳ ወንዶች ልጆች፣ 58 የያአላ ወንዶች ልጆች፣ የዳርቆን ወንዶች ልጆች፣ የጊዴል ወንዶች ልጆች፣ 59 የሰፋጥያህ ወንዶች ልጆች፣ የሃጢል ወንዶች ልጆች፣ የፖክሄሬትሃጸባይም ወንዶች ልጆችና የአምዖን ወንዶች ልጆች። 60 የቤተ መቅደሱ አገልጋዮችና*+ የሰለሞን አገልጋዮች ወንዶች ልጆች በአጠቃላይ 392 ነበሩ።

61 ከቴልመላ፣ ከቴልሃርሻ፣ ከከሩብ፣ ከአዳንና ከኢሜር የወጡት ሆኖም ከየትኛው የአባቶች ቤትና የዘር ሐረግ እንደመጡ በውል መለየትም ሆነ እስራኤላዊ መሆን አለመሆናቸውን በትክክል ማረጋገጥ ያልቻሉት የሚከተሉት ናቸው፦+ 62 የደላያህ ወንዶች ልጆች፣ የጦብያ ወንዶች ልጆችና የነቆዳ ወንዶች ልጆች 642። 63 ከካህናቱም መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦ የሃባያ ወንዶች ልጆች፣ የሃቆጽ+ ወንዶች ልጆች እንዲሁም ከጊልያዳዊው ከቤርዜሊ ሴቶች ልጆች መካከል አንዷን ያገባውና በስማቸው የተጠራው የቤርዜሊ+ ወንዶች ልጆች። 64 እነዚህ የዘር ሐረጋቸውን ለማረጋገጥ በመዝገቡ ላይ የቤተሰባቸውን ስም ለማግኘት ቢጥሩም ሊገኙ አልቻሉም፤ በመሆኑም ከክህነት አገልግሎቱ ታገዱ።*+ 65 ገዢውም*+ በኡሪምና በቱሚም+ አማካኝነት ምክር የሚጠይቅ ካህን እስኪገኝ ድረስ እጅግ ቅዱስ ከሆኑት ነገሮች መብላት እንደማይኖርባቸው ነገራቸው።+

66 መላው ጉባኤ በአጠቃላይ 42,360 ነበር፤+ 67 ይህ 7,337 ወንድና ሴት ባሪያዎቻቸውን አይጨምርም፤+ በተጨማሪም 245 ወንድና ሴት ዘማሪዎች+ ነበሯቸው። 68 ከዚህም ሌላ 736 ፈረሶች፣ 245 በቅሎዎች 69 እንዲሁም 435 ግመሎችና 6,720 አህዮች ነበሯቸው።

70 ከአባቶች ቤት መሪዎች መካከል ለሥራው መዋጮ ያደረጉ ነበሩ።+ ገዢው* 1,000 የወርቅ ድራክማ፣* 50 ጎድጓዳ ሳህኖችና 530 የካህናት ቀሚሶች ለግምጃ ቤቱ ሰጠ።+ 71 ከአባቶች ቤት መሪዎች መካከል አንዳንዶቹ ለሥራው ማስኬጃ የሚሆን 20,000 የወርቅ ድራክማና 2,200 የብር ምናን* ለግምጃ ቤቱ ሰጡ። 72 የቀረው ሕዝብ ደግሞ 20,000 የወርቅ ድራክማ፣ 2,000 የብር ምናን እና 67 የካህናት ቀሚሶች ሰጠ።

73 ካህናቱ፣ ሌዋውያኑ፣ በር ጠባቂዎቹ፣ ዘማሪዎቹ፣+ ከሕዝቡ መካከል አንዳንዶቹ፣ የቤተ መቅደስ አገልጋዮቹና* የቀሩት እስራኤላውያን በሙሉ በየከተሞቻቸው ሰፈሩ።+ በሰባተኛውም ወር+ እስራኤላውያን በየከተሞቻቸው ይኖሩ ነበር።+

8 ሕዝቡም ሁሉ እንደ አንድ ሰው ሆነው ከውኃ በር+ ፊት ለፊት በሚገኘው አደባባይ ተሰበሰቡ፤ ከዚያም የቅዱሳን መጻሕፍት ገልባጭ* የሆነው ዕዝራ+ ይሖዋ ለእስራኤል የሰጠውን ትእዛዝ+ የያዘውን የሙሴን ሕግ+ መጽሐፍ እንዲያመጣላቸው ጠየቁት። 2 በመሆኑም ካህኑ ዕዝራ በሰባተኛው ወር+ የመጀመሪያ ቀን ላይ ወንዶችን፣ ሴቶችንና የሚነገረውን ነገር ሰምተው ማስተዋል የሚችሉትን ሁሉ ወዳቀፈው ጉባኤ ሕጉን አመጣ።+ 3 እሱም ከውኃ በር ፊት ለፊት በሚገኘው አደባባይ በተሰበሰቡት ወንዶች፣ ሴቶችና ሰምተው ማስተዋል በሚችሉ ሁሉ ፊት ድምፁን ከፍ አድርጎ ከማለዳ እስከ እኩለ ቀን ድረስ ሕጉን አነበበ፤+ ሕዝቡም የሕጉ መጽሐፍ ሲነበብ በትኩረት አዳመጡ።+ 4 የቅዱሳን መጻሕፍት ገልባጭ* የሆነው ዕዝራ ለዝግጅቱ ተብሎ በተሠራው የእንጨት መድረክ ላይ ቆሞ ነበር፤ ከጎኑም በስተ ቀኝ በኩል ማቲትያህ፣ ሼማ፣ አናያ፣ ኦርዮ፣ ኬልቅያስ እና ማአሴያህ ቆመው ነበር፤ በስተ ግራው ደግሞ ፐዳያህ፣ ሚሳኤል፣ ማልኪያህ፣+ ሃሹም፣ ሃሽባዳናህ፣ ዘካርያስ እና መሹላም ቆመው ነበር።

5 ዕዝራ ከሕዝቡ ሁሉ ከፍ ብሎ ቆሞ ስለነበር ሁሉም እያዩት በፊታቸው መጽሐፉን ከፈተ። መጽሐፉንም ሲከፍት ሕዝቡ ሁሉ ተነስቶ ቆመ። 6 ከዚያም ዕዝራ ታላቁንና እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን አመሰገነ፤ በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ “አሜን!* አሜን!”+ በማለት መለሰ፤ ሁሉም እጃቸውን ወደ ላይ ዘረጉ፤ መሬት ላይ በግንባራቸው ተደፍተውም ለይሖዋ ሰገዱ። 7 ሌዋውያን የሆኑት የሹዋ፣ ባኒ፣ ሸረበያህ፣+ ያሚን፣ አቁብ፣ ሻበታይ፣ ሆዲያህ፣ ማአሴያህ፣ ቀሊጣ፣ አዛርያስ፣ ዮዛባድ፣+ ሃናን እና ፐላያህ ደግሞ ሕዝቡ እዚያው ቆሞ ሳለ ሕጉን ለሕዝቡ ያብራሩ ነበር።+ 8 እነሱም ከመጽሐፉ ይኸውም ከእውነተኛው አምላክ ሕግ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በማንበብ ሕጉን በግልጽ ያብራሩና ትርጉሙ ምን እንደሆነ ይናገሩ ነበር፤ በዚህ መንገድ የተነበበውን ነገር ማስተዋል እንዲችል ሕዝቡን ይረዱት ነበር።+

9 በወቅቱ ገዢ* የነበረው ነህምያ፣ የቅዱሳን መጻሕፍት ገልባጭ* የሆነው ካህኑ ዕዝራና+ ሕዝቡን ያስተምሩ የነበሩት ሌዋውያን ሕዝቡን ሁሉ “ይህ ቀን ለአምላካችሁ ለይሖዋ ቅዱስ ቀን ነው።+ አትዘኑ ወይም አታልቅሱ” አሉ። ይህን ያሉት ሕዝቡ ሁሉ የሕጉ ቃል ሲነበብ በሚሰማበት ጊዜ ያለቅስ ስለነበር ነው። 10 እሱም እንዲህ አላቸው፦ “ሂዱ፤ ምርጥ የሆኑትን* ነገሮች ብሉ፤ ጣፋጩንም ጠጡ፤ ምንም የተዘጋጀ ነገር ለሌላቸውም ምግብ ላኩላቸው፤+ ይህ ቀን ለጌታችን ቅዱስ ነውና፤ የይሖዋ ደስታ ምሽጋችሁ* ስለሆነ አትዘኑ።” 11 ሌዋውያኑም “ይህ ቀን ቅዱስ ስለሆነ ዝም በሉ! አትዘኑ” በማለት ሕዝቡን ያረጋጉ ነበር። 12 በመሆኑም ሕዝቡ ሁሉ ሊበላ፣ ሊጠጣ፣ ምግቡን ለሌሎች ሊያካፍልና ሊደሰት ሄደ፤+ ምክንያቱም የተነገራቸውን ቃል ተረድተውት ነበር።+

13 በሁለተኛውም ቀን የሕዝቡ ሁሉ የአባቶች ቤት መሪዎች፣ ካህናቱና ሌዋውያኑ የሕጉን ቃል ይበልጥ በጥልቀት ለማስተዋል የቅዱሳን መጻሕፍት ገልባጭ* በሆነው በዕዝራ ዙሪያ ተሰበሰቡ። 14 ከዚያም ይሖዋ በሙሴ አማካኝነት ባዘዘው ሕግ ውስጥ እስራኤላውያን በሰባተኛው ወር በሚከበረው በዓል ወቅት ዳስ*+ ውስጥ መቀመጥ እንዳለባቸው የሚገልጽ ሐሳብ ተጽፎ አገኙ፤ 15 እንዲሁም “ወደ ተራራማው አካባቢ ውጡና በተጻፈው መሠረት ዳሶችን ለመሥራት ከወይራ ዛፍ፣ ከዘይት ዛፍ፣ ከአደስ ዛፍ፣ ከዘንባባና ከሌሎች ዛፎች ቅጠል ያላቸውን ቅርንጫፎች አምጡ” የሚል አዋጅ በከተሞቻቸው በሙሉና በመላው ኢየሩሳሌም ማወጅ እንዳለባቸው+ የሚገልጽ ሐሳብ ተጽፎ አገኙ።

16 ስለዚህ ሕዝቡ ወጥቶ እነዚህን ቅጠሎች በማምጣት እያንዳንዱ ሰው በቤቱ ጣሪያ ላይ እንዲሁም በግቢውና በእውነተኛው አምላክ ቤት ግቢ ውስጥ፣+ በውኃ በር+ አደባባይና በኤፍሬም በር+ አደባባይ ለራሱ ዳሶች ሠራ። 17 በዚህም መንገድ ከምርኮ የተመለሱትን ሰዎች ያቀፈው መላው ጉባኤ ዳሶችን ሠራ፤ በዳሶቹም ውስጥ ተቀመጠ፤ እስራኤላውያን ከነዌ ልጅ ከኢያሱ+ ዘመን ጀምሮ እስከዚያ ቀን ድረስ በዓሉን በዚህ መንገድ አክብረው አያውቁም ነበር፤ ስለሆነም ደስታቸው ታላቅ ሆነ።+ 18 የእውነተኛው አምላክ ሕግ+ መጽሐፍም ከመጀመሪያው ቀን አንስቶ እስከ መጨረሻው ቀን ድረስ በየዕለቱ ይነበብ ነበር። እነሱም በዓሉን ለሰባት ቀን አከበሩ፤ በደንቡ መሠረትም በስምንተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ተደረገ።+

9 በዚህ ወር በ24ኛው ቀን እስራኤላውያን ተሰበሰቡ፤ ማቅ ለብሰውና በላያቸው ላይ አቧራ ነስንሰው ጾሙ።+ 2 ከዚያም የእስራኤል ዘሮች ከባዕዳን ሁሉ ራሳቸውን ለዩ፤+ ቆመውም ኃጢአታቸውንና አባቶቻቸው የፈጸሙትን ስህተት ሁሉ ተናዘዙ።+ 3 ከዚያም ባሉበት ስፍራ ቆሙ፤ በቀኑ አንድ አራተኛም* ከአምላካቸው ከይሖዋ የሕግ መጽሐፍ+ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ያነብቡ፣ በቀኑ አንድ አራተኛ ደግሞ ለአምላካቸው ለይሖዋ ይናዘዙና ይሰግዱ ነበር።

4 የሹዋ፣ ባኒ፣ ቃድሚኤል፣ ሸባንያህ፣ ቡኒ፣ ሸረበያህ፣+ ባኒ እና ኬናኒ ለሌዋውያኑ በተሠራው ከፍ ያለ መድረክ ላይ ቆመው+ ወደ አምላካቸው ወደ ይሖዋ ጮኹ። 5 እንዲሁም ሌዋውያኑ የሹዋ፣ ቃድሚኤል፣ ባኒ፣ ሃሻበንያህ፣ ሸረበያህ፣ ሆዲያህ፣ ሸባንያህ እና ፐታያህ እንዲህ አሉ፦ “ተነሱ፤ አምላካችሁን ይሖዋን ከዘላለም እስከ ዘላለም አመስግኑ።+ ከምስጋናና ከውዳሴ ሁሉ በላይ ከፍ ከፍ ያለውን ክብራማ ስምህን ያመስግኑ።

6 “አንተ ብቻ ይሖዋ ነህ፤+ አንተ ሰማያትን፣ አዎ ሰማየ ሰማያትንና ሠራዊታቸውን ሁሉ፣ ምድርንና በላይዋ ያሉትን ሁሉ፣ ባሕርንና በውስጡ ያሉትን ሁሉ ሠርተሃል። ሁሉንም ሕያው አድርገህ ታኖራቸዋለህ፤ የሰማይ ሠራዊትም ለአንተ ይሰግዳል። 7 አብራምን+ መርጠህ ከከለዳውያን ዑር+ ያወጣኸውና አብርሃም+ ብለህ የጠራኸው እውነተኛው አምላክ ይሖዋ አንተ ነህ። 8 ልቡ በፊትህ ታማኝ ሆኖ ስላገኘኸው+ የከነአናውያንን፣ የሂታውያንን፣ የአሞራውያንን፣ የፈሪዛውያንን፣ የኢያቡሳውያንንና የገርጌሻውያንን ምድር ለእሱ ይኸውም ለዘሩ ለመስጠት ከእሱ ጋር ቃል ኪዳን ተጋባህ፤+ ጻድቅ ስለሆንክም ቃልህን ጠበቅክ።

9 “በመሆኑም አባቶቻችን በግብፅ ሳሉ የደረሰባቸውን ሥቃይ አየህ፤+ በቀይ ባሕር ያሰሙትንም ጩኸት ሰማህ። 10 ከዚያም በፈርዖን፣ በአገልጋዮቹ ሁሉና በምድሩ በሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ ፊት ምልክቶችንና ተአምራትን አሳየህ፤+ ይህን ያደረግከው በእነሱ ላይ የእብሪት ድርጊት+ እንደፈጸሙ ስላወቅክ ነው። ለራስህም እስከ ዛሬ ጸንቶ የኖረ ስም አተረፍክ።+ 11 በባሕሩ መሃል በደረቅ ምድር እንዲሻገሩ ባሕሩን በፊታቸው ከፈልክ፤+ አሳዳጆቻቸውንም የሚናወጥ ባሕር ውስጥ እንደተጣለ ድንጋይ ወደ ጥልቁ ወረወርካቸው።+ 12 ቀን በደመና ዓምድ፣ ሌሊት ደግሞ የሚሄዱበት መንገድ ብርሃን እንዲሆንላቸው ለማድረግ ስትል በእሳት ዓምድ መራሃቸው።+ 13 በሲና ተራራ ላይ ወርደህ+ ከሰማይ አነጋገርካቸው፤+ እንዲሁም የጽድቅ ፍርዶችን፣ የእውነት ሕጎችን፣* መልካም ሥርዓቶችንና ትእዛዛትን ሰጠሃቸው።+ 14 ቅዱስ ሰንበትህን አሳወቅካቸው፤+ እንዲሁም በአገልጋይህ በሙሴ አማካኝነት ትእዛዛትህን፣ ሥርዓቶችህንና ሕግህን ሰጠሃቸው። 15 በተራቡ ጊዜ ከሰማይ ምግብ ሰጠሃቸው፤+ በተጠሙም ጊዜ ከዓለቱ ውኃ አፈለቅክላቸው፤+ ልትሰጣቸው የማልክላቸውን* ምድር ገብተው እንዲወርሱም ነገርካቸው።

16 “ይሁንና እነሱ ማለትም አባቶቻችን የእብሪት ድርጊት ፈጸሙ፤+ ግትሮችም ሆኑ፤*+ ትእዛዛትህንም አልሰሙም። 17 ለመስማትም አሻፈረኝ አሉ፤+ በመካከላቸው የፈጸምካቸውን እጅግ አስደናቂ የሆኑ ነገሮች ረሱ፤ ከዚህ ይልቅ ግትሮች ሆኑ፤* በግብፅ ወደነበሩበት የባርነት ሕይወት ለመመለስም መሪ ሾሙ።+ አንተ ግን ይቅር ለማለት ዝግጁ የሆንክ፣* ሩኅሩኅ፣* መሐሪ፣ ለቁጣ የዘገየህና ታማኝ ፍቅርህ የበዛ* አምላክ ነህ፤+ እነሱንም አልተውካቸውም።+ 18 ሌላው ቀርቶ ለራሳቸው የብረት* ጥጃ ሐውልት ሠርተው ‘ከግብፅ መርቶ ያወጣህ አምላክህ ይህ ነው’+ በማለት ከፍተኛ የንቀት ተግባር በፈጸሙ ጊዜም 19 አንተ ምሕረትህ ታላቅ ስለሆነ በምድረ በዳ አልተውካቸውም።+ ቀን ቀን በመንገዳቸው ይመራቸው የነበረው የደመና ዓምድም ሆነ የሚሄዱበትን መንገድ የሚያበራላቸው ሌሊት ሌሊት ይታይ የነበረው የእሳት ዓምድ ከላያቸው አልተነሳም ነበር።+ 20 ጥልቅ ማስተዋል እንዲያገኙ መልካም መንፈስህን ሰጠሃቸው፤+ መናህንም ከአፋቸው አልከለከልክም፤+ በተጠሙም ጊዜ ውኃ ሰጠሃቸው።+ 21 በምድረ በዳም ለ40 ዓመት መገብካቸው።+ ምንም ያጡት ነገር አልነበረም። ልብሶቻቸው አላለቁም፤+ እግሮቻቸውም አላበጡም።

22 “መንግሥታትንና ሕዝቦችን እየከፋፈልክ ሰጠሃቸው፤+ በመሆኑም የሲሖንን+ ምድር ይኸውም የሃሽቦንን+ ንጉሥ ምድር እንዲሁም የባሳንን ንጉሥ የኦግን+ ምድር ወረሱ። 23 ወንዶች ልጆቻቸውንም በሰማያት ላይ እንዳሉ ከዋክብት አበዛሃቸው።+ ከዚያም ገብተው እንዲወርሷት ለአባቶቻቸው ቃል ወደገባህላቸው ምድር አመጣሃቸው።+ 24 በመሆኑም ወንዶች ልጆቻቸው ገብተው ምድሪቱን ወረሱ፤+ አንተም የምድሪቱ ነዋሪዎች የሆኑትን ከነአናውያን በፊታቸው እንዲንበረከኩ አደረግክ፤+ በነገሥታታቸውና በምድሪቱ ሕዝቦች ላይም ያሻቸውን እንዲያደርጉ በእጃቸው አሳልፈህ ሰጠሃቸው። 25 የተመሸጉ ከተሞችንና+ ለም የሆነውን* መሬት ያዙ፤+ መልካም ነገሮች ሁሉ የሞሉባቸውን ቤቶች፣ የተቆፈሩ የውኃ ማጠራቀሚያ ጉድጓዶችን፣ የወይን እርሻዎችን፣ የወይራ ዛፎችንና+ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን የፍራፍሬ ዛፎች ወረሱ። በመሆኑም እስኪጠግቡ ድረስ በሉ፤ ሰቡም፤ ታላቅ በሆነው ጥሩነትህም ተንደላቀቁ።

26 “ይሁንና ለመታዘዝ እንቢተኞች በመሆን በአንተ ላይ ዓመፁ፤+ ለሕግህም ጀርባቸውን ሰጡ።* ወደ አንተ እንዲመለሱ ሲያስጠነቅቋቸው የነበሩትን ነቢያትህን ገደሉ፤ ከፍተኛ ንቀት የሚንጸባረቅባቸውንም ተግባሮች ፈጸሙ።+ 27 በዚህም የተነሳ መከራ ለሚያሳዩአቸው ጠላቶቻቸው አሳልፈህ ሰጠሃቸው።+ በተጨነቁ ጊዜ ግን ወደ አንተ ጮኹ፤+ አንተም ከሰማያት ሆነህ ሰማሃቸው፤ ከታላቅ ምሕረትህ የተነሳም ከጠላቶቻቸው እጅ የሚታደጓቸውን አዳኞች ሰጠሃቸው።+

28 “ሆኖም ፋታ ሲያገኙ እንደገና በፊትህ መጥፎ ነገር አደረጉ፤+ አንተም በሚጨቁኗቸው* ጠላቶቻቸው እጅ ጣልካቸው።+ ከዚያም ተመልሰው ለእርዳታ ወደ አንተ ጮኹ፤+ አንተም በሰማያት ሆነህ ሰማሃቸው፤ ከታላቅ ምሕረትህም የተነሳ በተደጋጋሚ አዳንካቸው።+ 29 ወደ ሕግህ እንዲመለሱ ለማድረግ ብታስጠነቅቃቸውም እነሱ ግን እብሪተኞች በመሆን ትእዛዛትህን ለመስማት አሻፈረኝ አሉ፤+ ለሚጠብቃቸው ሰው ሁሉ ሕይወት በሚያስገኙት ድንጋጌዎችህ ላይ ኃጢአት ሠሩ።+ ደግሞም በግትርነት ጀርባቸውን ሰጡ፤ አንገታቸውን አደነደኑ፤ ለመስማትም አሻፈረኝ አሉ። 30 አንተ ግን ለብዙ ዓመታት ታገሥካቸው፤+ በነቢያትህም አማካኝነት በመንፈስህ አስጠነቀቅካቸው፤ እነሱ ግን ለመስማት አሻፈረኝ አሉ። በመጨረሻም በምድሪቱ ለሚኖሩት ሕዝቦች አሳልፈህ ሰጠሃቸው።+ 31 ከታላቅ ምሕረትህ የተነሳ ፈጽመህ አላጠፋሃቸውም+ ወይም አልተውካቸውም፤ ምክንያቱም አንተ ሩኅሩኅና* መሐሪ አምላክ ነህ።+

32 “አምላካችን ሆይ፣ አንተ ታላቅ፣ ኃያል፣ የተፈራህ፣ ቃል ኪዳንህን የምትጠብቅና ታማኝ ፍቅር የምታሳይ አምላክ ነህ፤+ ከአሦር ነገሥታት+ ዘመን አንስቶ እስካሁን ድረስ በእኛ፣ በነገሥታታችን፣ በመኳንንታችን፣+ በካህናታችን፣+ በነቢያታችን፣+ በአባቶቻችንና በመላው ሕዝብህ ላይ እየደረሰ ያለውን ይህን ሁሉ መከራ አቅልለህ አትመልከተው። 33 በእኛ ላይ በደረሰው ነገር ሁሉ አንተ ጻድቅ ነህ፤ ምክንያቱም አንተ ማንኛውንም ነገር ያደረግከው በታማኝነት ነው፤ ክፉ ነገር የፈጸምነው እኛ ነን።+ 34 ነገሥታታችን፣ መኳንንታችን፣ ካህናታችንም ሆኑ አባቶቻችን ሕግህን አልጠበቁም፤ ደግሞም እነሱን ለማስጠንቀቅ ብለህ ለሰጠሃቸው ትእዛዛትም ሆነ ማሳሰቢያዎች ትኩረት አልሰጡም።* 35 ሌላው ቀርቶ በራሳቸው መንግሥት ሥር በሚተዳደሩበት፣ አትረፍርፈህ በሰጠሃቸው መልካም ነገሮች በሚደሰቱበት እንዲሁም ባዘጋጀህላቸው ሰፊና ለም* ምድር በሚኖሩበት ጊዜም እንኳ አንተን አላገለገሉም፤+ ከመጥፎ ተግባራቸውም አልተቆጠቡም። 36 በመሆኑም ይኸው ዛሬ እኛ ባሪያዎች ሆነናል፤+ አዎ፣ አባቶቻችን ፍሬዋንና በረከቷን እንዲበሉ በሰጠሃቸው ምድር ላይ ባሪያዎች ሆነናል። 37 በምድሪቱ የተትረፈረፈ ምርት እየተጠቀሙ ያሉት በኃጢአታችን የተነሳ በላያችን እንዲነግሡ ያደረግካቸው ነገሥታት ናቸው።+ እነሱም በሰውነታችንና በቤት እንስሶቻችን ላይ እንዳሻቸው እየገዙ ነው፤ እኛም በከባድ መከራ ውስጥ እንገኛለን።

38 “በዚህም ሁሉ የተነሳ በጽሑፍ የሰፈረ ጽኑ ስምምነት እናደርጋለን፤+ ስምምነቱም በመኳንንታችን፣ በሌዋውያናችንና በካህናታችን ማኅተም የጸደቀ ይሆናል።”+

10 በስምምነቱ ላይ ማኅተማቸውን በማተም ያጸደቁት+ እነዚህ ናቸው፦

የሃካልያህ ልጅ የሆነው ገዢው* ነህምያ፣

ሴዴቅያስ፣ 2 ሰራያህ፣ አዛርያስ፣ ኤርምያስ፣ 3 ጳስኮር፣ አማርያህ፣ ማልኪያህ፣ 4 ሃጡሽ፣ ሸባንያህ፣ ማሉክ፣ 5 ሃሪም፣+ መሬሞት፣ አብድዩ፣ 6 ዳንኤል፣+ ጊነቶን፣ ባሮክ፣ 7 መሹላም፣ አቢያህ፣ ሚያሚን፣ 8 ማአዝያህ፣ ቢልጋይ እና ሸማያህ፤ ካህናቱ እነዚህ ናቸው።

9 ሌዋውያኑ ደግሞ የሚከተሉት ናቸው፦ የአዛንያህ ልጅ የሹዋ፣ ከሄናዳድ ወንዶች ልጆች አንዱ የሆነው ቢኑይ፣ ቃድሚኤል፣+ 10 እንዲሁም ወንድሞቻቸው የሆኑት ሸባንያህ፣ ሆዲያህ፣ ቀሊጣ፣ ፐላያህ፣ ሃናን፣ 11 ሚካ፣ ሬሆብ፣ ሃሻብያህ፣ 12 ዛኩር፣ ሸረበያህ፣+ ሸባንያህ፣ 13 ሆዲያህ፣ ባኒ እና ቤኒኑ።

14 የሕዝቡ መሪዎች የሚከተሉት ናቸው፦ ፓሮሽ፣ ፓሃትሞአብ፣+ ኤላም፣ ዛቱ፣ ባኒ፣ 15 ቡኒ፣ አዝጋድ፣ ቤባይ፣ 16 አዶንያስ፣ ቢግዋይ፣ አዲን፣ 17 አጤር፣ ሕዝቅያስ፣ አዙር፣ 18 ሆዲያህ፣ ሃሹም፣ ቤጻይ፣ 19 ሃሪፍ፣ አናቶት፣ ነባይ፣ 20 ማግፒአሽ፣ መሹላም፣ ሄዚር፣ 21 መሺዛቤል፣ ሳዶቅ፣ ያዱአ፣ 22 ጰላጥያህ፣ ሃናን፣ አናያ፣ 23 ሆሺአ፣ ሃናንያህ፣ ሃሹብ፣ 24 ሃሎሔሽ፣ ፒልሃ፣ ሾቤቅ፣ 25 ረሁም፣ ሃሻብናህ፣ ማአሴያህ፣ 26 አኪያህ፣ ሃናን፣ አናን፣ 27 ማሉክ፣ ሃሪም እና ባአናህ።

28 የቀረው ሕዝብ ማለትም ካህናቱ፣ ሌዋውያኑ፣ በር ጠባቂዎቹ፣ ዘማሪዎቹ፣ የቤተ መቅደስ አገልጋዮቹ* እንዲሁም የእውነተኛውን አምላክ ሕግ ለመጠበቅ በምድሪቱ ካሉት ሕዝቦች ራሳቸውን የለዩ ሁሉ+ ሚስቶቻቸውን፣ ወንዶች ልጆቻቸውንና ሴቶች ልጆቻቸውን ጨምሮ እውቀትና ማስተዋል ያለው* ማንኛውም ሰው 29 ከወንድሞቻቸውና ታዋቂ ከሆኑት ሰዎቻቸው ጋር በመሆን የእውነተኛው አምላክ አገልጋይ በሆነው በሙሴ እጅ በተሰጠው የእውነተኛው አምላክ ሕግ መሠረት ለመሄድ እንዲሁም የጌታችንን የይሖዋን ትእዛዛት፣ ፍርዶችና ሥርዓቶች ሁሉ በጥንቃቄ ለመጠበቅ በእርግማንና በመሐላ ራሳቸውን ግዴታ ውስጥ አስገቡ። 30 ሴቶች ልጆቻችንን በምድሪቱ ለሚኖሩ ሰዎች አንሰጥም፤ ሴቶች ልጆቻቸውንም ለወንዶች ልጆቻችን አንወስድም።+

31 በምድሪቱ የሚኖሩት ሕዝቦች በሰንበት ቀን ሸቀጣ ሸቀጦቻቸውንና የተለያዩ ጥራጥሬዎችን ለመሸጥ ቢያመጡ በሰንበት+ ወይም ቅዱስ በሆነ ቀን+ ከእነሱ ላይ ምንም ነገር አንገዛም። በተጨማሪም በሰባተኛው ዓመት+ ምርት ከማምረት እንቆጠባለን፤ ያልተከፈለን ዕዳም ሁሉ እንሰርዛለን።+

32 በተጨማሪም እያንዳንዳችን በአምላካችን ቤት* ለሚከናወነው አገልግሎት በየዓመቱ አንድ ሦስተኛ ሰቅል* ለመስጠት ራሳችንን ግዴታ ውስጥ እናስገባለን፤+ 33 ይህም በሰንበት ቀናትና+ በአዲስ ጨረቃ ወቅት+ ለሚቀርበው የሚነባበር ዳቦ*+ እንዲሁም በእነዚህ ጊዜያት ዘወትር ለሚቀርበው የእህል መባና+ የሚቃጠል መባ፣ በተጨማሪም በተወሰኑ ጊዜያት ለሚከበሩት በዓላት፣+ ቅዱስ ለሆኑት ነገሮች፣ እስራኤልን ለማስተሰረይ ለሚቀርቡት የኃጢአት መባዎችና+ በአምላካችን ቤት ለሚከናወኑ ሥራዎች ሁሉ ይውላል።

34 ከዚህም ሌላ ካህናቱ፣ ሌዋውያኑና ሕዝቡ በሕጉ ላይ በተጻፈው መሠረት በየዓመቱ በተወሰነው ጊዜ በአምላካችን በይሖዋ መሠዊያ ላይ እንዲቃጠል በየአባቶቻችን ቤት በየተራ ወደ አምላካችን ቤት ሊያመጡ የሚገባውን እንጨት በተመለከተ ዕጣ ጣልን።+ 35 እንዲሁም መሬታችን የሚያፈራውን መጀመሪያ የደረሰውን ፍሬና ማንኛውም ዓይነት የፍራፍሬ ዛፍ የሚያፈራውን መጀመሪያ የደረሰውን ፍሬ ሁሉ በየዓመቱ ወደ ይሖዋ ቤት እናመጣለን፤+ 36 በተጨማሪም በሕጉ ላይ በተጻፈው መሠረት ከወንዶች ልጆቻችንና ከእንስሶቻችን በኩሩን+ እንዲሁም ከከብቶቻችንና ከመንጎቻችን በኩሩን እናመጣለን። ወደ አምላካችን ቤት ይኸውም በአምላካችን ቤት ወደሚያገለግሉት ካህናት እናመጣለን።+ 37 ከዚህም በተጨማሪ የተፈጨውን የእህላችንን በኩር፣+ መዋጮዎቻችንን፣ ማንኛውም ዛፍ የሚያፈራውን ፍሬ፣+ አዲስ የወይን ጠጅና ዘይት+ ወደ አምላካችን ቤት ግምጃ ቤቶች*+ ወደ ካህናቱ እናመጣለን፤ እንዲሁም ከእርሻ ከተሞቻችን ሁሉ አንድ አሥረኛውን* የሚቀበሉት ሌዋውያኑ ስለሆኑ የመሬታችንን አንድ አሥረኛ ለሌዋውያኑ እናመጣለን።+

38 ሌዋውያኑ አንድ አሥረኛውን በሚቀበሉበት ጊዜ ካህኑ የአሮን ልጅ ከሌዋውያኑ ጋር አብሮ መሆን አለበት፤ ሌዋውያኑም የአንድ አሥረኛውን አንድ አሥረኛ ወደ አምላካችን ቤት ይኸውም በግምጃ ቤቱ ውስጥ ወደሚገኙት ክፍሎች* መውሰድ ይኖርባቸዋል።+ 39 ምክንያቱም እስራኤላውያንም ሆኑ የሌዋውያኑ ልጆች የእህሉን፣ የአዲሱን ወይን ጠጅና የዘይቱን+ መዋጮ ማምጣት ያለባቸው ወደ ግምጃ ቤቶቹ* ነው፤+ ደግሞም የመቅደሱ ዕቃዎች የሚቀመጡትም ሆነ የሚያገለግሉት ካህናት፣ በር ጠባቂዎቹና ዘማሪዎቹ የሚገኙት በዚያ ነው። እኛም የአምላካችንን ቤት ቸል አንልም።+

11 በዚህ ጊዜ የሕዝቡ መኳንንት የሚኖሩት በኢየሩሳሌም ነበር፤+ የቀሩት ሰዎች ግን ከአሥር ሰው አንዱ በቅድስቲቱ ከተማ በኢየሩሳሌም እንዲኖርና የቀሩት ዘጠኙ ደግሞ በሌሎች ከተሞች እንዲኖሩ ዕጣ+ ጣሉ። 2 በተጨማሪም ሕዝቡ በኢየሩሳሌም ለመኖር ፈቃደኛ የሆኑትን ሰዎች በሙሉ ባረኳቸው።

3 በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩት የአውራጃው መሪዎች እነዚህ ናቸው። (የቀሩት እስራኤላውያን፣ ካህናቱ፣ ሌዋውያኑ፣ የቤተ መቅደስ አገልጋዮቹና*+ የሰለሞን አገልጋዮች+ ወንዶች ልጆች በሌሎቹ የይሁዳ ከተሞች ማለትም እያንዳንዳቸው በየከተሞቻቸው ባለው በየራሳቸው ርስት ይኖሩ ነበር።+

4 በተጨማሪም ከይሁዳና ከቢንያም ሰዎች መካከል የተወሰኑት በኢየሩሳሌም ይኖሩ ነበር።) ከይሁዳ ሰዎች መካከል ከፋሬስ+ ቤተሰብ የሆነው የመላልኤል ልጅ፣ የሰፋጥያህ ልጅ፣ የአማርያህ ልጅ፣ የዘካርያስ ልጅ፣ የዖዝያ ልጅ አታያህ 5 እንዲሁም ከሴሎማውያን ቤተሰብ የሆነው የዘካርያስ ልጅ፣ የዮያሪብ ልጅ፣ የአዳያህ ልጅ፣ የሃዛያህ ልጅ፣ የኮልሆዜ ልጅ፣ የባሮክ ልጅ ማአሴያህ ነበሩ። 6 በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩት የፋሬስ ወንዶች ልጆች በአጠቃላይ 468 ብቃት ያላቸው ወንዶች ነበሩ።

7 የቢንያም ሰዎች የሚከተሉት ነበሩ፦ የየሻያህ ልጅ፣ የኢቲኤል ልጅ፣ የማአሴያህ ልጅ፣ የቆላያህ ልጅ፣ የፐዳያህ ልጅ፣ የዮኤድ ልጅ፣ የመሹላም ልጅ ሳሉ፣+ 8 ከእሱ ቀጥሎ ደግሞ ጋባይ እና ሳላይ ሲሆኑ በአጠቃላይ 928 ነበሩ፤ 9 የዚክሪ ልጅ ኢዩኤል የእነሱ የበላይ ተመልካች ነበር፤ የሃስኑአ ልጅ ይሁዳ ደግሞ በከተማዋ ላይ ሁለተኛ አዛዥ ነበር።

10 ከካህናቱ መካከል ደግሞ የሚከተሉት ነበሩ፦ የዮያሪብ ልጅ የዳያህ፣ ያኪን፣+ 11 የእውነተኛው አምላክ ቤት* መሪ የሆነው የአኪጡብ+ ልጅ፣ የመራዮት ልጅ፣ የሳዶቅ ልጅ፣ የመሹላም ልጅ፣ የኬልቅያስ ልጅ ሰራያህ፤ 12 እንዲሁም የቤቱን ሥራ የሠሩት ወንድሞቻቸው 822፤ የማልኪያህ ልጅ፣ የጳስኮር+ ልጅ፣ የዘካርያስ ልጅ፣ የአማሲ ልጅ፣ የፐላልያህ ልጅ፣ የየሮሃም ልጅ አዳያህ፣ 13 የአባቶች ቤት መሪዎች የሆኑት ወንድሞቹ 242፤ እንዲሁም የኢሜር ልጅ፣ የመሺሌሞት ልጅ፣ የአህዛይ ልጅ፣ የአዛርዔል ልጅ አማሽሳይ 14 እንዲሁም ኃያላንና ጀግኖች የሆኑት ወንድሞቻቸው 128፤ የእነሱ የበላይ ተመልካች የአንድ ታዋቂ ቤተሰብ አባል የሆነው ዛብድኤል ነበር።

15 ከሌዋውያኑ መካከል ደግሞ የሚከተሉት ነበሩ፦ የቡኒ ልጅ፣ የሃሻብያህ ልጅ፣ የአዝሪቃም ልጅ፣ የሃሹብ ልጅ ሸማያህ፣+ 16 ከእውነተኛው አምላክ ቤት ጋር በተያያዘ በውጭ ያሉትን ጉዳዮች በበላይነት ከሚከታተሉት የሌዋውያን መሪዎች መካከል ሻበታይ+ እና ዮዛባድ፤+ 17 የውዳሴ መዝሙሩንና በጸሎት ጊዜ+ የሚቀርበውን ውዳሴ የሚመራው የአሳፍ+ ልጅ፣ የዛብዲ ልጅ፣ የሚክያስ ልጅ ማታንያህ፣+ ከወንድሞቹ ሁለተኛ የሆነው ባቅቡቅያ እንዲሁም የየዱቱን+ ልጅ፣ የጋላል ልጅ፣ የሻሙአ ልጅ አብዳ። 18 በቅድስቲቱ ከተማ የነበሩት ሌዋውያን በአጠቃላይ 284 ነበሩ።

19 በር ጠባቂዎቹ አቁብ፣ ታልሞን+ እና በየበሮቹ ላይ የሚጠብቁት ወንድሞቻቸው ደግሞ 172 ነበሩ።

20 ከእስራኤላውያን፣ ከካህናቱና ከሌዋውያኑ የቀሩት ደግሞ በሌሎቹ የይሁዳ ከተሞች ሁሉ እያንዳንዳቸው በውርስ ባገኙት ርስት ላይ ይኖሩ ነበር። 21 የቤተ መቅደሱ አገልጋዮች*+ በኦፌል+ ይኖሩ የነበረ ሲሆን ጺሃ እና ጊሽፓ የቤተ መቅደሱ አገልጋዮች* ኃላፊዎች ነበሩ።

22 በኢየሩሳሌም የነበሩት ሌዋውያን የበላይ ተመልካች ከዘማሪዎቹ ከአሳፍ ልጆች መካከል የሚካ ልጅ፣ የማታንያህ+ ልጅ፣ የሃሻብያህ ልጅ፣ የባኒ ልጅ ዑዚ ነበር፤ እሱም በእውነተኛው አምላክ ቤት ሥራ ላይ ኃላፊ ነበር። 23 እነሱን በተመለከተ የወጣ ንጉሣዊ ትእዛዝ ነበር፤+ ለዘማሪዎቹ በየዕለቱ የሚያስፈልገውን ነገር በማቅረብ ረገድም ቋሚ የሆነ ዝግጅት ነበር። 24 የይሁዳ ልጅ ከሆነው ከዛራ ልጆች መካከል የመሺዛቤል ልጅ ፐታያህ ከሕዝቡ ጋር የተያያዘውን ማንኛውንም ጉዳይ በተመለከተ የንጉሡ አማካሪ* ነበር።

25 የሰፈራ መንደሮቹ ከነእርሻ ቦታዎቻቸው የሚከተሉት ናቸው፦ ከይሁዳ ወንዶች ልጆች መካከል የተወሰኑት በቂርያትአርባና+ በሥሯ* ባሉት ከተሞች፣ በዲቦንና በሥሯ ባሉት ከተሞች፣ በየቃብጸኤል+ እና በሥሯ ባሉት የሰፈራ መንደሮች፣ 26 በየሹዋ፣ በሞላዳ፣+ በቤትጳሌጥ፣+ 27 በሃጻርሹአል፣+ በቤርሳቤህና በሥሯ* ባሉት ከተሞች፣ 28 በጺቅላግ፣+ በመኮና እና በሥሯ* ባሉት ከተሞች፣ 29 በኤንሪሞን፣+ በጾራ፣+ በያርሙት፣ 30 በዛኖሃ፣+ በአዱላምና በሥሯ ባሉት የሰፈራ መንደሮች፣ በለኪሶና+ በእርሻ ቦታዎቿ እንዲሁም በአዜቃና+ በሥሯ* ባሉት ከተሞች ይኖሩ ነበር። እነሱም ከቤርሳቤህ እስከ ሂኖም ሸለቆ+ ባለው አካባቢ ሰፈሩ።

31 የቢንያም ሰዎች ደግሞ ከጌባ+ ጀምሮ በሚክማሽ፣ በጋያ፣ በቤቴል+ እና በሥሯ* ባሉት ከተሞች፣ 32 በአናቶት፣+ በኖብ፣+ በአናንያ፣ 33 በሃጾር፣ በራማ፣+ በጊታይም፣ 34 በሃዲድ፣ በጸቦይም፣ በነባላጥ፣ 35 በሎድ እና በኦኖ+ እንዲሁም በእጅ ጥበብ ባለሙያዎች ሸለቆ ተቀመጡ። 36 በይሁዳ ከነበሩት ሌዋውያን መካከል የተወሰኑት ቡድኖች በቢንያም ተመደቡ።

12 ከሰላትያል+ ልጅ ከዘሩባቤልና+ ከየሆሹዋ+ ጋር የወጡት ካህናትና ሌዋውያን የሚከተሉት ነበሩ፦ ሰራያህ፣ ኤርምያስ፣ ዕዝራ፣ 2 አማርያህ፣ ማሉክ፣ ሃጡሽ፣ 3 ሸካንያህ፣ ረሁም፣ መሬሞት፣ 4 ኢዶ፣ ጊነቶአይ፣ አቢያህ፣ 5 ሚያሚን፣ ማአድያህ፣ ቢልጋ፣ 6 ሸማያህ፣ ዮያሪብ፣ የዳያህ፣ 7 ሳሉ፣ አሞቅ፣ ኬልቅያስ እና የዳያህ። እነዚህ በየሆሹዋ ዘመን የካህናቱና የወንድሞቻቸው መሪዎች ነበሩ።

8 ሌዋውያኑ ደግሞ የሹዋ፣ ቢኑይ፣ ቃድሚኤል፣+ ሸረበያህ፣ ይሁዳ እና ከወንድሞቹ ጋር ሆኖ የምስጋና መዝሙሮቹን የሚመራው ማታንያህ+ ነበሩ። 9 ወንድሞቻቸው ባቅቡቅያ እና ዑኒ ከእነሱ ትይዩ ለጥበቃ ቆመው ነበር።* 10 የሹዋ ዮአቂምን ወለደ፤ ዮአቂምም ኤልያሺብን+ ወለደ፤ ኤልያሺብም ዮያዳን+ ወለደ። 11 ዮያዳም ዮናታንን ወለደ፤ ዮናታንም ያዱአን ወለደ።

12 በዮአቂም ዘመን የአባቶች ቤት መሪዎች የሆኑት ካህናት የሚከተሉት ነበሩ፦ ከሰራያህ+ መራያህ፣ ከኤርምያስ ሃናንያህ፣ 13 ከዕዝራ+ መሹላም፣ ከአማርያህ የሆሃናን፣ 14 ከማሉኪ ዮናታን፣ ከሸባንያህ ዮሴፍ፣ 15 ከሃሪም+ አድና፣ ከመራዮት ሄልቃይ፣ 16 ከኢዶ ዘካርያስ፣ ከጊነቶን መሹላም፣ 17 ከአቢያህ+ ዚክሪ፣ ከሚንያሚን . . . ፣* ከሞአድያህ ፒልጣይ፣ 18 ከቢልጋ+ ሻሙአ፣ ከሸማያህ የሆናታን፣ 19 ከዮያሪብ ማቴናይ፣ ከየዳያህ+ ዑዚ፣ 20 ከሳላይ ቃላይ፣ ከአሞቅ ኤቤር፣ 21 ከኬልቅያስ ሃሻብያህ፣ ከየዳያህ ናትናኤል ተወክለው ነበር።

22 በኤልያሺብ፣ በዮያዳ፣ በዮሃናን እና በያዱአ+ ዘመን የነበሩት የሌዋውያኑ የአባቶች ቤት መሪዎች ልክ እንደ ካህናቱ ሁሉ እስከ ፋርሳዊው ዳርዮስ የንግሥና ዘመን ድረስ ተመዘገቡ።

23 የአባቶች ቤት መሪዎች የነበሩት ሌዋውያን የኤልያሺብ ልጅ እስከሆነው እስከ ዮሃናን ዘመን ድረስ በዘመኑ በነበረው የታሪክ መጽሐፍ ላይ ተመዝግበው ነበር። 24 የሌዋውያኑ መሪዎች ሃሻብያህ፣ ሸረበያህና የቃድሚኤል+ ልጅ የሹዋ+ ነበሩ፤ ወንድሞቻቸውም ከእነሱ ትይዩ ቆመው ይኸውም አንዱ የጥበቃ ቡድን ከሌላው የጥበቃ ቡድን ጎን ለጎን ሆኖ የእውነተኛው አምላክ ሰው ዳዊት በሰጠው መመሪያ መሠረት+ ለአምላክ ውዳሴና ምስጋና ያቀርቡ ነበር። 25 ማታንያህ፣+ ባቅቡቅያ፣ አብድዩ፣ መሹላም፣ ታልሞን እና አቁብ+ እንደ በር ጠባቂዎች+ ዘብ በመቆም በበሮቹ አጠገብ ያሉትን ግምጃ ቤቶች ይጠብቁ ነበር። 26 እነዚህም በዮጻዴቅ ልጅ፣ በየሆሹዋ+ ልጅ በዮአቂም ዘመን እንዲሁም በገዢው በነህምያና የቅዱሳን መጻሕፍት ገልባጭ* በሆነው በካህኑ ዕዝራ+ ዘመን አገለገሉ።

27 የኢየሩሳሌም ቅጥሮች በሚመረቁበት ጊዜ የምረቃውን በዓል በምስጋና መዝሙር፣+ በሲምባል፣* በባለ አውታር መሣሪያዎችና በበገና በደስታ እንዲያከብሩ ሌዋውያኑን ከሚኖሩበት ስፍራ ሁሉ ፈልገው ወደ ኢየሩሳሌም አመጧቸው። 28 የዘማሪዎቹ ወንዶች ልጆችም* ከአውራጃው፣* በኢየሩሳሌም ዙሪያ ካሉት ቦታዎች ሁሉና ነጦፋውያን+ ከሰፈሩባቸው መንደሮች ተሰበሰቡ፤ 29 እንዲሁም ከቤትጊልጋል፣+ ከጌባ+ የእርሻ ቦታዎችና ከአዝማዌት+ ተሰበሰቡ፤ ምክንያቱም ዘማሪዎቹ በኢየሩሳሌም ዙሪያ ለራሳቸው የሰፈራ መንደሮችን መሥርተው ነበር። 30 ካህናቱና ሌዋውያኑም ራሳቸውን አነጹ፤+ ሕዝቡን፣ በሮቹንና+ ቅጥሩንም+ አነጹ።

31 ከዚያም የይሁዳን መኳንንት አምጥቼ በቅጥሩ አናት ላይ እንዲቆሙ አደረግኩ። በተጨማሪም ምስጋና የሚያቀርቡ ሁለት ትላልቅ የዘማሪ ቡድኖችን እንዲሁም እነሱን የሚያጅቡ ቡድኖችን መደብኩ፤ አንደኛው ቡድን በስተ ቀኝ በኩል በቅጥሩ አናት ላይ ወደ አመድ ቁልል በር+ ሄደ። 32 ሆሻያህ እና ከይሁዳ መኳንንት ግማሾቹ ከኋላ ተከተሏቸው፤ 33 ከእነሱም ጋር አዛርያስ፣ ዕዝራ፣ መሹላም፣ 34 ይሁዳ፣ ቢንያም፣ ሸማያህ እና ኤርምያስ ነበሩ። 35 መለከት ከሚነፉት+ ካህናት ወንዶች ልጆች መካከል የተወሰኑት አብረዋቸው ነበሩ፤ እነሱም የአሳፍ+ ልጅ፣ የዛኩር ልጅ፣ የሚካያህ ልጅ፣ የማታንያህ ልጅ፣ የሸማያህ ልጅ፣ የዮናታን ልጅ ዘካርያስ 36 እንዲሁም ወንድሞቹ ሸማያህ፣ አዛርዔል፣ ሚላላይ፣ ጊላላይ፣ ማአይ፣ ናትናኤል፣ ይሁዳ እና ሃናኒ ናቸው፤ እነሱም የእውነተኛውን አምላክ ሰው የዳዊትን የሙዚቃ መሣሪያዎች+ ይዘው ነበር፤ የቅዱሳን መጻሕፍት ገልባጭ* የሆነው ዕዝራም+ ከፊታቸው ይሄድ ነበር። 37 ከዚያም፣ ምንጭ በር+ ጋ ሲደርሱ ሽቅብ የሚወጣውን ቅጥር ይዘው ፊት ለፊት ቀጥ ብለው በመሄድ በዳዊት ከተማ+ ደረጃ+ ላይ አልፈው ከዳዊት ቤት በላይ ወዳለው ስፍራና በስተ ምሥራቅ ወዳለው ወደ ውኃ በር+ አቀኑ።

38 ምስጋና የሚያቀርበው ሌላኛው የዘማሪዎች ቡድን ደግሞ በተቃራኒ አቅጣጫ ሄደ፤ እኔም ከግማሹ ሕዝብ ጋር በመሆን ቡድኑን ተከትዬ በቅጥሩ አናት ላይ በመሄድ የመጋገሪያ ምድጃ ማማን+ አልፌ ወደ ሰፊ ቅጥር+ ተጓዝኩ፤ 39 ከዚያም በኤፍሬም በርና+ በአሮጌው ከተማ በር+ አድርጌ ወደ ዓሣ በር፣+ ወደ ሃናንኤል ማማና+ ወደ መአህ ማማ፣ በኋላም ወደ በግ በር+ ሄድኩ፤ እነሱም የጠባቂው በር ጋ ሲደርሱ ቆሙ።

40 በመጨረሻም ምስጋና የሚያቀርቡት ሁለቱም የዘማሪ ቡድኖች በእውነተኛው አምላክ ቤት ፊት ለፊት ቆሙ፤ እኔም እንዲሁ አደረግኩ፤ በተጨማሪም ከእኔ ጋር የነበሩት ግማሾቹ የበታች ገዢዎች፣ 41 ካህናት የሆኑት ኤልያቄም፣ ማአሴያህ፣ ሚንያሚን፣ ሚካያህ፣ ኤሊዮዔናይ፣ ዘካርያስና ሃናንያህ ከነመለከታቸው 42 እንዲሁም ማአሴያህ፣ ሸማያህ፣ አልዓዛር፣ ዑዚ፣ የሆሃናን፣ ማልኪያህ፣ ኤላም እና ኤጼር አብረውኝ ቆሙ። ዘማሪዎቹም በይዝራህያህ መሪነት ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ዘመሩ።

43 እውነተኛው አምላክ እጅግ እንዲደሰቱ ስላደረጋቸው በዚያን ቀን ብዙ መሥዋዕት አቀረቡ፤ ሐሴትም አደረጉ።+ ሴቶችና ልጆችም ጭምር በጣም ተደሰቱ፤+ ስለዚህ የኢየሩሳሌም ደስታ ከሩቅ ይሰማ ነበር።+

44 በዚያን ቀን መዋጮዎች፣+ የእህል በኩራትና+ አሥራት+ በሚቀመጡባቸው ግምጃ ቤቶች+ ላይ ሰዎች ተሾሙ። እነሱም በሕጉ ላይ በታዘዘው መሠረት ለካህናቱና ለሌዋውያኑ የሚሰጠውን ድርሻ ከየከተሞቹ እርሻዎች እየሰበሰቡ ወደዚያ ማስገባት ነበረባቸው፤+ ምክንያቱም በሚያገለግሉት ካህናትና ሌዋውያን+ የተነሳ በይሁዳ ውስጥ ታላቅ ደስታ ነበር። 45 ዘማሪዎቹና በር ጠባቂዎቹ እንዳደረጉት ሁሉ ካህናቱና ሌዋውያኑም አምላካቸው የሚጠብቅባቸውን ግዴታም ሆነ ከመንጻት ጋር በተያያዘ የተጣለባቸውን ኃላፊነት ዳዊትና ልጁ ሰለሞን በሰጡት መመሪያ መሠረት መወጣት ጀመሩ። 46 ጥንት በዳዊትና በአሳፍ ዘመን ዘማሪዎቹን እንዲሁም ለአምላክ የሚቀርቡትን የውዳሴና የምስጋና መዝሙሮች የሚመሩ ሰዎች ነበሩ።+ 47 እንዲሁም በዘሩባቤል+ ዘመንና በነህምያ ዘመን እስራኤላውያን በሙሉ ለዘማሪዎቹና+ ለበር ጠባቂዎቹ+ በየዕለቱ የሚያስፈልጋቸውን ያህል ድርሻ ይሰጧቸው ነበር። በተጨማሪም ለሌዋውያኑ የሚገባውን ድርሻ+ ለይተው ያስቀምጡ የነበረ ሲሆን ሌዋውያኑ ደግሞ ለአሮን ዘሮች የሚገባውን ድርሻ ለይተው ያስቀምጡ ነበር።

13 በዚያን ቀን ሕዝቡ እየሰማ የሙሴ መጽሐፍ ይነበብ ነበር፤+ በዚህ ጊዜ አሞናዊ ወይም ሞዓባዊ+ የሆነ ማንኛውም ሰው ወደ እውነተኛው አምላክ ጉባኤ ፈጽሞ መግባት እንደሌለበት የሚገልጽ ሐሳብ ተጽፎ ተገኘ፤+ 2 ይህም የሆነው ለእስራኤላውያን ምግብና ውኃ በመስጠት ፋንታ እነሱን እንዲረግምላቸው በለዓምን ቀጥረው ስለነበር ነው።+ ይሁንና አምላካችን እርግማኑን ወደ በረከት ለወጠው።+ 3 እነሱም ይህን ሕግ እንደሰሙ የባዕድ አገር ሰዎችን ሁሉ* ከእስራኤላውያን መለየት ጀመሩ።+

4 ይህ ከመሆኑ ቀደም ብሎ የአምላካችን ቤት* ግምጃ ቤቶች*+ ኃላፊ፣ የጦብያ+ ዘመድ የሆነው ካህኑ ኤልያሺብ+ ነበር። 5 እሱም ቀደም ሲል የእህል መባውን፣ ነጩን ዕጣን፣ ዕቃዎቹን እንዲሁም ለሌዋውያኑ፣+ ለዘማሪዎቹና ለበር ጠባቂዎቹ እንዲሰጥ የታዘዘውን የእህሉን፣ የአዲሱን የወይን ጠጅና የዘይቱን+ አንድ አሥረኛ* እንዲሁም ለካህናቱ የሚዋጣውን መዋጮ+ ያስቀምጡበት የነበረውን ቦታ ትልቅ ግምጃ ቤት* አድርጎ አዘጋጀለት።

6 ይህ ሁሉ ሲሆን እኔ በኢየሩሳሌም አልነበርኩም፤ ምክንያቱም የባቢሎን ንጉሥ አርጤክስስ+ በነገሠ በ32ኛው ዓመት+ ወደ ንጉሡ ሄጄ ነበር፤ ከተወሰነ ጊዜ በኋላም ንጉሡን ፈቃድ እንዲሰጠኝ ጠየቅኩ። 7 ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ስመጣ ኤልያሺብ+ በእውነተኛው አምላክ ቤት ግቢ ውስጥ ለጦብያ+ ግምጃ ቤት በማዘጋጀት የፈጸመውን መጥፎ ድርጊት አስተዋልኩ። 8 እኔም በዚህ በጣም አዘንኩ፤ በመሆኑም የጦብያን የቤት ዕቃዎች በሙሉ ከግምጃ ቤቱ* አውጥቼ ወረወርኳቸው። 9 ከዚያም ትእዛዝ ሰጠሁ፤ እነሱም ግምጃ ቤቶቹን አጸዱ፤* እኔም የእውነተኛውን አምላክ ቤት+ ዕቃዎች ከእህሉ መባና ከነጩ ዕጣን+ ጋር እዚያው መልሼ አስቀመጥኩ።

10 በተጨማሪም ሌዋውያኑ የሚገባቸው ድርሻ+ ስለማይሰጣቸው+ ሥራውን ያከናውኑ የነበሩት ሌዋውያንም ሆኑ ዘማሪዎች እያንዳንዳቸው ወደየእርሻቸው መሄዳቸውን ተረዳሁ።+ 11 እኔም የበታች ገዢዎቹን+ “ለመሆኑ የእውነተኛው አምላክ ቤት እንዲህ ቸል የተባለው ለምንድን ነው?” በማለት ገሠጽኳቸው።+ ከዚያም ሁሉንም አንድ ላይ ከሰበሰብኳቸው በኋላ ወደየሥራ ምድባቸው እንዲመለሱ አደረግኩ። 12 የይሁዳ ሰዎችም ሁሉ የእህሉን፣ የአዲሱን የወይን ጠጅና የዘይቱን አንድ አሥረኛ+ ወደ ግምጃ ቤቶቹ አስገቡ።+ 13 ከዚያም ካህኑን ሸሌምያህን፣ የቅዱሳን መጻሕፍት ገልባጭ* የሆነውን ሳዶቅን እንዲሁም ከሌዋውያን መካከል ፐዳያህን በግምጃ ቤቶቹ ላይ ኃላፊዎች አደረግኳቸው፤ የማታንያህ ልጅ፣ የዛኩር ልጅ ሃናን ደግሞ የእነሱ ረዳት ነበር፤ እነዚህ ሰዎች እምነት የሚጣልባቸው ነበሩ። ለወንድሞቻቸው የማከፋፈሉ ኃላፊነት የእነሱ ነበር።

14 አምላኬ ሆይ፣ ስለዚህ ነገር አስበኝ፤+ ለአምላኬ ቤትና በዚያ ለሚከናወነው አገልግሎት* ስል የፈጸምኩትን ታማኝ ፍቅር የተንጸባረቀበት ተግባር አትርሳ።+

15 በእነዚያ ቀናት በይሁዳ በሰንበት ቀን በመጭመቂያ ውስጥ ወይን የሚረግጡና+ እህል አምጥተው በአህያ ላይ የሚጭኑ እንዲሁም የወይን ጠጅ፣ የወይን ዘለላ፣ በለስና የተለያዩ ነገሮችን ጭነው በሰንበት ቀን ወደ ኢየሩሳሌም የሚያመጡ ሰዎችን አየሁ።+ በመሆኑም በዚያን ቀን ሸቀጣ ሸቀጦችን እንዳይሸጡ አስጠነቀቅኳቸው።* 16 በከተማዋ የሚኖሩ የጢሮስ ሰዎችም ዓሣና የተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦችን እያመጡ በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ የይሁዳ ሰዎች በሰንበት ቀን ይሸጡ ነበር።+ 17 ስለሆነም በይሁዳ ያሉትን የተከበሩ ሰዎች እንዲህ በማለት ገሠጽኳቸው፦ “ሰንበትን በማርከስ የምትፈጽሙት ይህ መጥፎ ድርጊት ምንድን ነው? 18 አምላካችን በእኛም ሆነ በዚህች ከተማ ላይ ይህን ሁሉ መከራ ያመጣው አባቶቻችሁ እንዲህ ዓይነት ድርጊት በመፈጸማቸው አይደለም? አሁንም እናንተ ሰንበትን በማርከስ በእስራኤል ላይ የሚነደውን ቁጣ እያባባሳችሁ ነው።”+

19 በመሆኑም በሰንበት ዋዜማ የምሽቱ ጥላ በኢየሩሳሌም በሮች ላይ ማረፍ ሲጀምር በሮቹ እንዲዘጉ ትእዛዝ ሰጠሁ። ሰንበት እስኪያልፍም ድረስ እንዳይከፍቷቸው ነገርኳቸው፤ በሰንበት ቀን ምንም ዓይነት ጭነት እንዳይገባም ከአገልጋዮቼ የተወሰኑትን በበሮቹ ላይ አቆምኩ። 20 ስለዚህ የተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦችን የሚነግዱትና የሚሸጡት ሰዎች ከአንዴም ሁለቴ ከኢየሩሳሌም ውጭ አደሩ። 21 ከዚያም እኔ “ቅጥሩ አጠገብ የምታድሩት ለምንድን ነው? ዳግመኛ እንዲህ የምታደርጉ ከሆነ የኃይል እርምጃ እወስድባችኋለሁ” በማለት አስጠነቀቅኳቸው። ከዚያን ጊዜ ወዲህ በሰንበት መጥተው አያውቁም።

22 ለሌዋውያኑም የሰንበት ቀን ምንጊዜም የተቀደሰ እንዲሆን ዘወትር ራሳቸውን እንዲያነጹና መጥተው በሮቹን እንዲጠብቁ ነገርኳቸው።+ አምላኬ ሆይ፣ ይህንም አስብልኝ፤ ማለቂያ ከሌለው ታማኝ ፍቅርህም የተነሳ እዘንልኝ።+

23 በተጨማሪም በእነዚያ ቀናት አሽዶዳውያን፣+ አሞናውያንና ሞዓባውያን+ ሴቶችን ያገቡ* አይሁዳውያን መኖራቸውን አወቅኩ።+ 24 ከልጆቻቸው መካከል ግማሾቹ የአሽዶድን ቋንቋ ግማሾቹ ደግሞ ከተለያየ አገር የመጡትን ሰዎች ቋንቋ ይናገሩ የነበረ ቢሆንም ማንኛቸውም የአይሁዳውያንን ቋንቋ መናገር አይችሉም ነበር። 25 ስለሆነም ገሠጽኳቸው፤ እርግማንም አወረድኩባቸው፤ አንዳንዶቹንም መታኋቸው፤+ ፀጉራቸውንም ነጨሁ፤ እንዲሁም እንደሚከተለው በማለት በአምላክ አስማልኳቸው፦ “ሴቶች ልጆቻችሁን ለወንዶች ልጆቻቸው መስጠት የለባችሁም፤ ሴቶች ልጆቻቸውንም ለወንዶች ልጆቻችሁም ሆነ ለራሳችሁ መውሰድ የለባችሁም።+ 26 የእስራኤል ንጉሥ ሰለሞን ኃጢአት የሠራው በእነሱ ምክንያት አይደለም? በብዙ ብሔራት መካከል እንደ እሱ ያለ ንጉሥ አልነበረም፤+ ደግሞም በአምላኩ ዘንድ የተወደደ+ ስለነበር አምላክ በመላው እስራኤል ላይ ንጉሥ አደረገው። ይሁንና ባዕዳን ሚስቶች እሱን እንኳ ኃጢአት እንዲሠራ አደረጉት።+ 27 እናንተም ባዕዳን ሴቶችን በማግባት በአምላካችን ላይ ታማኝነት የጎደለው ተግባር ፈጸማችሁ፤ ታዲያ እንዲህ ያለውን ተሰምቶ የማያውቅ እጅግ መጥፎ ድርጊት እንዴት ትፈጽማላችሁ?”+

28 ከሊቀ ካህናቱ ከኤልያሺብ+ ልጅ ከዮያዳ+ ወንዶች ልጆች መካከል አንዱ የሆሮናዊው የሳንባላጥ+ አማች ሆኖ ነበር። በመሆኑም ከአጠገቤ አባረርኩት።

29 አምላኬ ሆይ፣ ክህነቱን+ እንዲሁም ከካህናቱና ከሌዋውያኑ+ ጋር የተገባውን ቃል ኪዳን ስላረከሱ አትርሳቸው።

30 እኔም ርኩስ ከሆነ ከማንኛውም ባዕድ ነገር አነጻኋቸው፤ ለካህናቱና ለሌዋውያኑም ለእያንዳንዳቸው በየምድባቸው መሠረት ሥራ ሰጠኋቸው፤+ 31 እንዲሁም በተወሰነው ጊዜ መቅረብ ያለበትን እንጨትና+ መጀመሪያ የሚደርሰውን ፍሬ በተመለከተ ዝግጅት አደረግኩ።

አምላኬ ሆይ፣ በመልካም አስበኝ።+

“ያህ ያጽናናል” የሚል ትርጉም አለው።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።

ወይም “በሱሳ።”

ወይም “ቤተ መንግሥት፤ ምሽግ።”

ወይም “ለአገልጋይህ ለሙሴ የሰጠኸውን ማስጠንቀቂያ።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።

ወይም “ኤፍራጥስን ተሻግሮ።”

ወይም “የንጉሡ ደን።”

ወይም “ለቤተ መቅደሱ።”

ቃል በቃል “አገልጋይ።”

ወይም “ደረቁን ወንዝ።”

ቃል በቃል “እጃቸውን።”

ቃል በቃል “አገልጋይ።”

ወይም “ወሰኑት።”

ቃል በቃል “አንገታቸውን በማስገባት።”

ወይም “ኤፍራጥስን ተሻግሮ።”

ቃል በቃል “ዙፋን።”

ወይም “ከሽቶ ቀማሚዎች።”

ወይም “የተለካውን ክፍል።”

ወደ 445 ሜትር ገደማ ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ሼላ ማለት ‘ቦይ’ ማለት ነው። ይህ የውኃ ገንዳ ውኃ በቦይ አማካኝነት የሚገባበት ገንዳ ነው።

“በአቅራቢያው ያለው አውራጃ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “በንጉሡ ቤተ መንግሥት።”

ወይም “ናታኒሞች።” ቃል በቃል “የተሰጡ ሰዎች።”

ወይም “ናታኒሞቹና።” ቃል በቃል “የተሰጡት ሰዎችና።”

ወይም “የተሸካሚዎቹ።”

ቃል በቃል “አሥር ጊዜ።”

ወይም “ተወንጫፊ መሣሪያ።”

ቃል በቃል “ሥጋችን እንደ ወንድሞቻችን ሥጋ ነው።”

ወይም “ለገዛ ወንድማችሁ በአራጣ እያበደራችሁ።”

ወይም በየወሩ “አንድ በመቶ።”

ቃል በቃል “እቅፍ።”

ወይም “ይሁን!”

አንድ ሰቅል 11.4 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ወይም “በራሴ ወጪ ይዘጋጁ።”

ቃል በቃል “በልብህ።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።

ቃል በቃል “በገዛ ዓይናቸው ፊት ክፉኛ ወደቁ።”

ወይም “ናታኒሞቹ።” ቃል በቃል “የተሰጡት ሰዎች።”

ወይም “የናታኒሞቹና።” ቃል በቃል “የተሰጡት ሰዎችና።”

ወይም “እንደረከሱ ተቆጥረው ከክህነት አገልግሎቱ ተገለሉ።”

ወይም “ቲርሻታውም።” ለአንድ የአውራጃ ገዢ የሚሰጥ የፋርሳውያን የማዕረግ ስም ነው።

ወይም “ቲርሻታው።” ለአንድ የአውራጃ ገዢ የሚሰጥ የፋርሳውያን የማዕረግ ስም ነው።

አብዛኛውን ጊዜ 8.4 ግራም ከሚመዝነው የፋርሳውያን የወርቅ ዳሪክ ጋር እኩል መጠን አለው። በግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ከተጠቀሰው ድራክማ የተለየ ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ አንድ ምናን 570 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ወይም “ናታኒሞቹና።” ቃል በቃል “የተሰጡት ሰዎችና።”

ወይም “ጸሐፊ።”

ወይም “ጸሐፊ።”

ወይም “ይሁን!”

ወይም “ቲርሻታ።” ለአንድ የአውራጃ ገዢ የሚሰጥ የፋርሳውያን የማዕረግ ስም ነው።

ወይም “ጸሐፊ።”

ቃል በቃል “የሰቡትን።”

ወይም “ብርታታችሁ።”

ወይም “ጸሐፊ።”

ወይም “ጊዜያዊ መጠለያ።”

ወይም “ለሦስት ሰዓትም።”

ወይም “አስተማማኝ ሕጎችን።”

ቃል በቃል “እጅህን ያነሳህላቸውን።”

ቃል በቃል “አንገታቸውንም አደነደኑ።”

ቃል በቃል “አንገታቸውን አደነደኑ።”

ወይም “ይቅር ባይ የሆንክ።”

ወይም “ቸር።”

ወይም “ፍቅራዊ ደግነትህ የበዛ።”

ወይም “ቀልጦ የተሠራ።”

ወይም “የበለጸገውን።”

ቃል በቃል “ሕግህንም ወደኋላቸው አሽቀንጥረው ጣሉ።”

ወይም “በሚያደቋቸው።”

ወይም “ቸርና።”

ወይም “ማስጠንቀቂያዎች ትኩረት አልሰጡም።”

ወይም “የበለጸገ።”

ወይም “ቲርሻታው።” ለአንድ የአውራጃ ገዢ የሚሰጥ የፋርሳውያን የማዕረግ ስም ነው።

ወይም “ናታኒሞቹ።” ቃል በቃል “የተሰጡት ሰዎች።”

“ለማስተዋል የሚያስችል ዕድሜ ላይ የደረሰ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “ቤተ መቅደስ።”

አንድ ሰቅል 11.4 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ገጸ ኅብስቱን ያመለክታል።

ወይም “መመገቢያ አዳራሾች።”

ወይም “አሥራቱን።”

ወይም “መመገቢያ አዳራሾች።”

ወይም “መመገቢያ አዳራሾቹ።”

ወይም “የናታኒሞቹና።” ቃል በቃል “የተሰጡት ሰዎችና።”

ወይም “ቤተ መቅደስ።”

ወይም “ናታኒሞቹ።” ቃል በቃል “የተሰጡት ሰዎች።”

ወይም “የናታኒሞቹ።” ቃል በቃል “የተሰጡት ሰዎች።”

ቃል በቃል “በንጉሡ እጅ።”

ወይም “በዙሪያዋ።”

ወይም “በዙሪያዋ።”

ወይም “በዙሪያዋ።”

ወይም “በዙሪያዋ።”

ወይም “በዙሪያዋ።”

“ባቅቡቅያ እና ዑኒ በአገልግሎቱ ወቅት ከእነሱ ትይዩ ቆመው ነበር” ማለትም ሊሆን ይችላል።

የዕብራይስጡ ጽሑፍ እዚህ ቦታ ላይ ያስቀረው ስም ሳይኖር አይቀርም።

ወይም “ጸሐፊ።”

እዚህ ላይ የገባው የዕብራይስጥ ቃል፣ እርስ በርሱ ሲጋጭ ኃይለኛ ድምፅ የሚያወጣን ክብ ቅርጽ ያለው ከብረት የተሠራ የሙዚቃ መሣሪያ ያመለክታል።

ወይም “የሠለጠኑት ዘማሪዎችም።”

በዮርዳኖስ አካባቢ ያለውን አውራጃ ያመለክታል።

ወይም “ጸሐፊ።”

ወይም “ድብልቅ ዘሮችን ሁሉ።”

ወይም “ቤተ መቅደስ።”

ወይም “መመገቢያ አዳራሾች።”

ወይም “አሥራት።”

ወይም “መመገቢያ አዳራሽ።”

ወይም “ከመመገቢያ አዳራሹ።”

ወይም “መመገቢያ አዳራሾቹን አጸዱ።”

ወይም “ጸሐፊ።”

ወይም “ቤቱን ለመጠበቅና ለመንከባከብ።”

“በመሆኑም ሸቀጣ ሸቀጦችን እንዳይሸጡ በዚያን ቀን አስጠነቀቅኳቸው” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “ወደ ቤታቸው ያስገቡ።”

    የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ ጽሑፎች (2011-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ